Semonegna

Forum Replies Created

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 132 total)
  • Author
    Posts
  • Semonegna
    Keymaster

    በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት በጊዜያዊነት መቋረጥን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ መግለጫ

    መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች ለተወሰኑ ሰዓታት መቋረጣቸዉ ይታወቃል።

    እንደሚታወቀው ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ባንኮች በሥርዓቶቻቸዉ ላይ በየጊዜዉ የደህንነት ፍተሻ እንዲሁም የማሻሻያ ሥራዎችን ያከናዉናሉ። በሥርዓቶቹ ላይ በሚከናወን ለዉጦችና ፍተሻዎችም የባንኮች አገልግሎት አልፎ አልፎ ሊቋረጥ ይችላል።

    በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 7 ቀን፤ 2016 ዓ.ም. የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል። ችግሩ ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የባንኩን እና የደንበኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል። በመሆኑም የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲጀምሩና ባንኩ ወደተለመደው እንቅስቃሴው እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል።

    በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ባንኩ በመደበኛነት በሥርዓቶቹ ላይ በሚያደርገዉ ማሻሻያና ፍተሻ ምክንያት የተከሰተ እንጂ የባንኩን፣ የደንበኞቹን እንዲሁም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አለመሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል።በችግሩ ምክንያት የተከሰቱ የደንበኞች መጉላላትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊዉን ምርመራ በማድረግ ወደፊት ለሕብረተሰቡ የሚያሳዉቅ መሆኑን ያረጋግጣል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሟቸዉን ሥርዓቶች ደህንነታቻዉ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉ ስለመሆናቸዉ በየጊዜዉ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደህንነቸዉ የተጠበቀ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ያለምንም ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም መቀጠል ይችላል።

    የገንዘብ (የፋይናንስ) ተቋማትም የሥርዓቶቻቸዉን ደህንነትና ቀልጣፋነት ይበልጥ ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭ ባህርይ በማየት በቀጣይነት መሥራት እንደሚኖርባቸዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።

    በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ ደህንነት የበለጠ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጠል አስፈላጊ እርምጃዎችንና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን መዉሰዱን ይቀጥላል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    “የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተከናወነ

    በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል አዘጋጅነት “የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተካሂዷል።

    በውይይቱ ላይ አጠቃላይ ሙያዊ ትንታኔውን የሙዚቃ ባለሙያና የሙዚቃ ሃያሲ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ያቀረቡ ሲሆን፥ የሙዚቃው አቀናባሪና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ እና ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት (የማ) የሙዚቃ ስብስቡን ሥራ ታሪክና ውጣ ውረድ አብራርተዋል።

    አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ሙዚቃው የዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) ላይ የሚመደብ ምርምራዊ ሥራ መሆኑን አመላካች፣ አስረጅ እና ታሪካዊ ዳራዎችን በመጥቀስ ያብራሩ ከመሆኑም ባሻገር፥ እስካሁን በዓለም ሙዚቃ ዘውግ ከተሠሩ የኢትዮጵያዊያን ሙዚቃዎች ውስጥ የቀለለ ዕድል በሌለበት በጥረትና ትጋት የተፈጠረ የጥበብ ሥራ መሆኑን አብራርተዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ በየዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) አስቴር አወቀ፣ እጅጋየሁ ሽባባው፣ ምንይሹ ክፍሌ፣ ዣን ስዩም ሔኖክን የመሰሉ ከያንያን በውጭ ሀገር ከመኖራቸውና ለወርልድ ሙዚቃ ካላቸው ተጋላጭነት አንጻር በመመዘንም “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ በተለየ ሁኔታ በምርጫና በጥረት የተሠራ ሥራ መሆኑን አቶ ሰርጸ አብራርተዋል።

    የሙዚቃ ስብስቡ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሙዚቀኞች ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር የተጣመሩበት እና በአቀናባሪው ምርጫና ትጋት ወደ እውንነት የተቀየረ መሆኑ ተገልጿል።

    የሙዚቃው አቀናባሪ እና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ ሥራው በቦኬ ማኅበረሰብ ሙዚቃ በመሳብ እና ምርምሮችን በማስፋት ሀገር በቀል የሙዚቃ ቅንጣቶችን ከዓለም አቀፍ የሙዚቃ እሳቤዎች ጋር በመቀየጥ የባሕል ውህደትና ቅንብር ለመፍጠር የተሠራ ሥራ መሆኑን የሙዚቃ ስብስቡን ታሪክ አስረድተዋል።

    ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት ከእንግሊዝኛ የሙዚቃ ድምጻዊነት በሽግግር ወደእንዲህ አይነት የባሕል ቅይጥ እና ዓለማቀፋዊ መልክ ወዳለው ሥራ የተሻገረችበትን መልክ ሆኔታዎች አንስታ ገልጻች። “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ ከሰባት ሀገራት፣ ከሃያ በላይ ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሙዚቃ ስብስብ ሲሆን፥ በሙዚቃ ድርሰት፣ በሁለት የዘፈን ግጥሞች፣ በቅንብር እና በፕሮዲዩሰርነት ኢዩኤል መንግሥቱ፣ ጎላ ጎሕ (የብዕር ስም) ስምንት የሙዚቃ ግጥሞችን በማበርከት፣ አንጋፋው ይልማ ገብረአብ አንድ የሙዚቃ ግጥም ድርሰት በመስጠት የተሳተፉበት ስብስብ ነው።

    በውይይቱ ላይ በርካታ ታዳምያን ተገኝተው ስለሙዚቃ ሥራው የተሰማቸውን ስሜት እና በቀረቡት መነሻ ሃሳቦች ላይ ጥያቄና ማብራሪያ በማቅረብ ጠንካራ ተሳትፎ አድርገዋል።

    በውይይቱም ላይ ከሙዚቃው ድርሰትና ቅንብር በተጨማሪ የተለየ ሆኖ በሀሳብ ላይ ትኩረት አድርጎ ስለመጣው የሙዚቃው ግጥሞች በርካቶች አድናቆታቸውን ሰጥተዋል። በሌላም በኩል ምርምርና የሥነ-ጥበብን ከፍታ ይዘው ለሚመጡ አድካሚና ውድ ሥራዎች አድማጩ ሊሰጠው ስለሚገባው ትኩረት በማንሳት ጠንካራ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

    በዝግጅቱም ላይ ከራያ ማኅበረሰብ የተላኩ ወኪሎች በቦታው ተገኝተው ለድምጻዊቷ፣ ሙዚቃው አቀናባሪና ገጣሚ እንዲሁም በሥራው ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለየማርያም ቸርነትም የራያ ባሕል ልብስ ስጦታ አበርክተዋል።

    የካቲት 2 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በ “ነገረ መጻሕፍት” ዝግጅት የገብረሕይወት ባይከዳኝ “ሕዝብና የመንግሥት አስተዳደር” መጽሐፍ የታተመበትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ጋር በሚደረገው ውይይት ላይ እንድትገኙ ከወዲሁ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋብዟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Semonegna
    Keymaster

    ዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የአየር ትራንስፖርት ክፍያ (የበረራ ክፍያ) አገልግሎት ይፋ አደረጉ

    አዲስ አበባ – ዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅመው ክፍያውን ቆይተው የሚከፍሉበትን አዲስ የክፍያ አማራጭ በጋራ አስተዋወቁ።

    አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን የዳሽን ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ዋና መኮንን፥ ‘ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል’ በሚል የተሰየመው ይህ አገልግሎት በደንበኞች ምርጫ መሠረት በ6 ወር ወይም በ12 ወር የብድር ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል። ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በዳሸን ባንክ የሂሳብ ቁጥር መክፈት እንደሚገባቸው እና በተጨማሪም በባንኩ ቢያንስ ለሦስት ወራት አገልግሎት ያገኙ መሆን እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል።

    አቶ ዮሃንስ አክለውም አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች አቅራቢያቸው ወደሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በሚያመሩበት ወቅት አስፈላጊ ሰነዶችን ማሟላት የሚገባቸው ሲሆን፥ ማስያዣም ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም ገልፀዋል።

    ስምምነቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያዴቻ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፣ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ተኮር አሠራርን እንደመከተሉ የተለያዩ ዘመናዊ እና ለመጠቀም ቀላል የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል። የምናበለጽጋቸው ቴክኖሎጂዎች ለደንበኞቻችን ምቹ መሆናቸው እንደተጠበቁ ሆኖ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት ጋርም የተጣጣሙ እንዲሆኑ እናደርጋለን። ዛሬም አጋራችን ከሆነው የዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር ለደንበኞቻችን ያቀረብነው አዲስ የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ እንዲሆን የሞባይል መተግበሪያችን ከአዲሱ የክፍያ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ እንዲሆን አድርገናል። በዚሁም መሠረት ደንበኞች ስለክፍያ ሳይጨነቁ ጉዟቸውን ማቀድ የሚጀምሩበትን ‘Fly Now Pay Later‘ ተብሎ የተሰየመውን የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ ማድረጋችንን ስንገልጽ በደስታ ነው። ይህ የድኅረ-ጉዞ ክፍያ አማራጭ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ከአየር መንገዳችን እና ከዳሽን ባንክ በኩል ለተሳተፉ አካላት ያለኝን ምስጋና በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እፈልጋለሁ።”

    አዲሱን የበረራ ክፍያ አገልግሎት ለመጠቀም አንድ ደንበኛ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ካሟላ በኋላ በቅርንጫፉ የተፈቀደለትን የብድር መጠን የሚወስድ ሲሆን፥ የተፈቀደለትን ገንዘብ ለመጠቀም የሚያስችል የአንድ ጊዜ መለያ ቁጥር መልዕክትም በተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚደርሰው ይሆናል። በመቀጠልም ደንበኛው የተሰጠውን መለያ ቁጥር በአየር መንገዱ የሞባይል መተግበሪያ ላይ በማስገባት ትኬት መቁረጥና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።

    ደንበኞች የተፈቀደላቸው የብድር መጠን ሲያልቅ ማደስ የሚችሉ ሲሆን፥ በአንዴ የወሰዱትን ብድርም ለተለያዩ በረራዎች ከፍለው መጠቀም ይችላሉ።አገልግሎቱ በተለይም በንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ፣ ጅምላ አስመጪዎች እና ለዕረፍት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ውጭ ለሚሄዱ ደንበኞች አመቺ ነው።

    በሁለቱ ተቋማት ስምምነት በቀረበው በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈቀደው የብድር ገንዘብ መጠን እስከ ስድስት መቶ ሺህ (600,000) ብር የሚደርስ ነው። የሚፈቀደው ብድር ወለድ የሚታሰብበት ሲሆን፥ ይህም ደንበኛው በመረጠውና ብድሩን በወሰደበት የጊዜ ገደብ ከብድሩ ጋር አብሮ የሚከፈል ነው።

    አየር መንገዱ እና ዳሽን ባንክ ወደፊትም የደንበኞችን አገልግሎት ለማዘመን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም በትብብር መሥራታቸውን ይቀጥላሉ።

    ምንጭ፦ ዳሸን ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    ዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የአየር ትራንስፖርት ክፍያ አገልግሎት ይፋ አደረጉ

    Semonegna
    Keymaster

    ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬታቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ

    ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያ (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 16 ቀን፥ 2015 ዓ.ም ባካሄደው የተማሪዎች ምረቃ ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል። በዕለቱ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በሥራ መደራረብ ምክንያት በምረቃ ዕለቱ ተገኝተው ባለመቀበላቸው፥ ኅዳር16 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል።

    በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመጀመሪያዋ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ናት።

    የክብር ዶክተር መዓዛ ብሩን ለክብር ዶክትሬት ሽልማት ያበቋቸው ሥራዎች በዝርዝር:-

    • በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ (ሸገር ኤፍ ኤም 1) መሥራች እና ባለቤት፤
    • የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ማሰራጫ ድርጅት መሥራችና ባለቤት፤
    • በእንግዶች ምርጫዋ፤ በምርምር በተደገፈ የመጠይቅ ዘይቤዋ፣ በትህትናዋ፣ በአነጋገር ለዛዋ በቀጥታ አዘጋጅታ ከምታቀርባቸው መርሃ ግብሮች (የቅዳሜ ጨዋታ እና ሸገር ካፌ) በተጭማሪ በተለያዩ የሸገር ሬዲዮ መርሃ ግብሮች እንዲሁም በሌሎች ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን መርሃ ግብሮች ላይ አሻራ የተወች እና ባጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች አርአያ የሆነች፤

    ምናልባት ከሁሉ በላይ ታዋቂ የሆነችበትና አምሳያ የሌለው የላቀ አስተዋፅኦ ተብሎ ሊወሰድ ከሚችሉት ሥራዎቿ ውስጥ አንዱ፥ በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸውን በርካታ ባለታሪክ ምሁራን፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፤ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይውት ታሪክ፣ ሥራ፣ አስተሳሰብ እና ለሌሎች አርአያ የሚሆነውን የሕይወት ፍልስፍናቸው በራሳቸው አንደበት ተሰናድቶ ለታሪክ እንዲቆይ ማድረጓ ነው። በዚህም ለኢትዮጵያውያን በዓይነቱ ተወዳዳሪ የሌለውና ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የሚሄድ የታሪክ የድምጽ መዘክር አበርክታለች ማለት ይቻላል። የጨዋታ እንግዳ መሰናዶ እንግዶቿ ያካበቱት ልምድ፤ አበርክቶታቸው፤ ያልተጻፉ ሃገራዊ ጉዳዮች እና ሚስጥሮች ከኃላፊ ባለታሪኮቹ ጋር እንዳያልፉ፤ በመቅረጸ-ድምጽ ተሰንቀው በሰፊው እንዲታወቁ እና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ አድርጋለች። በእርግጥም ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ከየተደበቁበት ፈልጋ ቃለ መጠይቅ ካደረገቻቸው ጉምቱ እንግዶች መካከል ጥቂት የማይባሉት አሁን በመሃከላችን አይገኙም፤ ታሪካቸው ግን ህያው ሆኗል።

    ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የተወለደች ሲሆን፥ ዘጠኝ ዓመት ገደማ እስኪሆናት በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው ሂርና ከተማ አደገች። ሂርና ሳለች ጎረቤቶቿ የኦሮሞ፣ የሃረሪና የሶማሌ እንዲሁም የየመን ተወላጆች ስለነበሩ በተለያዩ ባሕላዊ ዕሴቶች እና እርስ በእርስ ትስስር የዳበረ አስተዳደግ ነበራት። ይህም ለሥነ-ጽሁፍ ከነበራት ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ ለዛሬው ማንነቷ መሠረት ሆኗታል።

    • ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ወላጆቿ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የቅድስተ ማርያም የልጃገረዶች ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት አሰገቧት።
    • 1967 ዓ.ም. የሁለትኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች በእድገት በሕብረት ዘመቻ ወደ ውቅሮ፥ ትግራይ ተልካ ለስድስት ወራት አገልግላለች።
    • በ1970 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች።
    • ከሬዲዮ ሥራ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለች በአጋጣሚ ሲሆን፥ በወቅቱ ተወዳጅ ከነበረው የእሁድ ፕሮግራም ጋር ለነበራት ለስምንት ዓመታት ያክል የቆየ ትስስር ምክንያት ሆኖታል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ በቋሚነት የተመደበችበት ሥራዋ በባህል ሚኒስቴር ስር የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢነት ነበር።
    • በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ተሳትፎዋን ሳታቆም በባህል ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ አግልግሎት ክፍል አገልግላለች።
    • ከዚያም በብሔራዊ ባንክ የብሪቱ መጽሄት ዋና አዘጋጅ በመሆን የፋይናንስ ዜናዎችን እና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ እና በአርትኦት አገልግላለች።
    • በ1984 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅላ የፕሬስ እና ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር በመሆን ለአራት ዓመታት ሠርታለች።
    • ከዚያም በግል በአማካሪነት እና በሕዝብ ግንኙነት እና ማስታወቂያ ስትሠራ ከቆየች በኋላ፤ በ1987 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ1 የሬዲዮ ጣቢያን የአየር ሰዓት በመጠቀም የቅዳሜ ከሰዓት የጨዋታ መርሀ ግብርን ከባለቤቷ ከአርቲስት አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዋ አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ጋር የማዘጋጀት ዕድል አግኝታ መርሀ ግብሩን ለስምንት ዓመታት ያክል ስታቀርብ ቆይታለች።
    • በመጨረሻም በ2000 ዓ.ም. አንጋፋና ተወዳጅ የሆነውን ሸገር ኤፍ ኤም1ን እዉን ለማድረግ በቅታለች።

    በአጠቃላይ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የጥንካሬ ተምሳሌትና በዘርፉ ለበርካቶች አርአያ ለመሆኗ ተገቢ ዕውቅና ይሆን ዘንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152 / 2011 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በአርት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት እንዲሰጣቸው ወስኗል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ዳሸን ባንክ እና ማስተርካርድ የመጀመሪያውን ቨርቹዋል ዓለም አቀፍ ቅድመ ክፍያ ካርድ አስተዋወቁ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ዳሸን ባንክ ዓለም አቀፍ ቅድመ ክፍያ ካርድ ከማስተርካድ (Mastercard) ጋር በመተባበር ከተለመደው በስም ከሚታተም የፕላስቲክ ካርድ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ቨርቹዋል ካርድን (virtual card) በማምጣት ነሐሴ 15 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል አስተዋውቀዋል።

    የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ዳሸን ባንክ ይህን በዓይነቱ የተለየ ካርድ ማስተዋወቁ ባንኩ ለደንበኞቹ ቀላል፣ ምቹና አስተማማኝ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል። ካርዱ ደንበኞች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ገንዘባቸውን ያለምንም ስጋት መጠቀም የሚችሉበት አማራጭ መሆኑንም አመልክተዋል።

    የማስተርካርድ የምሥራቅ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ሸህርያር አሊ በበኩላቸው፥ ማስተርካርድ ከዳሸን ባንክ ጋር የፈጠረው ጥምረት በኢትዮጵያ እንደ ዓለም አቀፍ ካርድ ያሉ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ማኅበረሰቡ ይበልጥ የዲጂታል አገልገሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

    “ከዳሸን ባንክ ጋር በመጣመር የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብና ይህን መሰል የክፍያ አማራጭ ለንግዱ ማኅበረሰቡና ሌሎች ደንበኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻላችን ትልቅ ክብር ይሰማናል” ብለዋል።

    በዳሸን ቅድመ ክፍያ ማስተርካርድ ደንበኞች ከኤቲኤም (ATM) እና ፖስ (PoS) በተጨማሪ በኢ-ኮሜርስ ክፍያ መክፈል የሚያስችላቸው ሲሆን፤ ደንበኞች ፕላስቲክ ወይም ቨርቹዋል (virtual) ካርድ በመውሰድ መጠቀም ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ፕላስቲክ ካርዱ ስም የታተመበትና ስም ያልታተመበት የካርድ ዓይነቶችን የያዘ ነው።

    ደንበኞች ዳሸን ማስተርካርድ ላይ የተሞላው የውጪ ምንዛሬ ሲያልቅ እንደገና በመሙላት መጠቀም የሚያስችላቸው ሲሆን ካርዱን ኤቲኤምና ፖስ ማሽን ላይ በማስገባት ወይም ያለ ንክኪ ገንዘብ ማውጣት ወይም ክፍያ መፈፀም ያስችላቸዋል።

    ፕላስቲክ ካርዱ በሚስጢር ቁጥር የተጠበቀ ሲሆን ቨርቹዋል ካርዱ ደግሞ በአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። ደንበኞች ካርዱን ለመጠቀም አቅራቢያቸው በሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ፓስፖርት፣ ቪዛ እና የበረራ ቲኬት በመያዝ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ።

    ዳሸን ባንክ እና ማስተርካርድ ከካርዱ በተጨማሪ የንግድ ተቋማት ክፍያቸውን በበይነ መረብ ከየትኛውም የዓለም ክፍል መቀበል የሚያስችል የማስተርካርድ የክፍያ መቀበያ ማስተርካርድ ጌትዌይ /MasterCard Payment Gateway System/ አስተዋውቀዋል።

    ይህ የማስተርካርድ ጌትዌይ/ MasterCard Payment Gateway System/ ሦስት የካርድ አይነቶችን በመቀበል የተሻለ የአገልግሎት አማራጭ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም ለንግድ ተቋማት ክፍያ ለመቀበል እና ሽያጭ ለማከናወን ለምግባረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ እና የአባልነት ክፍያ ለመሰብሰብ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ዘመናዊ የክፍያ መፈጸሚያ መስመር ነው።

    ምንጭዳሸን ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም መመዘኛዎች ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገቡን አስታወቀ
    የባንኩ ጠቅላላ ሃብት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ደርሷል
    የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች ሹመት ጸደቀ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም መመዘኛዎች ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ፤ እንዲሁም የባንኩ ጠቅላላ ሃብት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር መድረሱን አስታውቋል።

    በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከሚያዝያ 17-19/ 2015 ዓ.ም በተካሄደው የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ ብድር በመስጠትና በመሰብሰብ፣ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና አቅርቦት እንዲሁም በሌሎች ፋይናንስና ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ አፈፃፀሞች ውጤታማ ሥራ መሠራቱ ተጠቁሟል።

    በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ123 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ በጉባዔው የተገለፀ ሲሆን፣ የባንኩ ጠቅላላ ሃብትም 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ያህል ብር መድረሱ ታውቋል።

    የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ባንኩ ወጤታማ እንደነበር የተብራራ ሲሆን፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በዲጂታል ባንክ አማራጮች ብቻ 2 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር ተንቀሳቅሰሷል ብሏል ባንኩ በሥራ አፈፃፀም ግምገማው።

    ባንኩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በሁሉም መመዘኛዎች መልካም አፈፃፀም ነበሩት ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በቀጣይ በተለይ ዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች በሆኑት በተቀማጭ ሃብት አሰባሰብ፣ በዲጂታል ባንክ አገልግሎት፣ በብድር አሰጣጥና አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲሁም የባንኩን የሪፎርም (reform) ሥራዎች በማስቀጠል በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

    የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በበኩላቸው ፋይናንስም ሆነ ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ ዘርፎች የታዩትን አፈፃፀሞች፤ መልካሞቹን በማጠናከር ድክመቶችን ደግሞ በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ሁሉም የባንኩ ማህበረሰብ በአንድ ልብ ሊሠራ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

    በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የሁሉም ዲስትሪክቶች ዳይሬክተሮች እና የልዩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል።

    ከባንክ ዜና ሳንወጣ፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አምስት የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎችን ሹመት ማጽደቁን አስታውቋል። በዚህም መሠረት፥ አቶ ሰይፉ አገንዳ ኬርጋ – ቺፍ የከስተመርና ኦፕሬሽንስ ኦፊሰር (Chief Customer and Operations Officer)፣ አቶ ሰለሞን ጎሽሜ በጅጋ – ቺፍ የኮርፖሬት ሰርቪስስ ኦፊሰር (Chief Corporate Services Officer)፣ አቶ መልካሙ ሰለሞን ይመር – ምክትል ፕሬዚዳንት ሂዩማን ካፒታል (Vice President of Human Capital)፣ አቶ አብርሃም ተስፋዬ አበበ – ምክትል ፕሬዚዳንት የስትራቴጂና ማርኬቲንግ (Vice President of Strategy and Marketing) እና አቶ አሚነ ታደሰ ተስፉ – ምክትል ፕሬዚዳንት የኢንተርናሽናል ባንክ ኦፕሬሽን (Vice President of International Bank’s Operation) ሆነው ተሹመዋል።

    ብሔራዊ ባንክ ሹመቱን ማጽደቁን ባሳወቀበት ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው፥ በባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000፣ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1159/2011 እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር SBB/79/2021 አንጻር የተላኩለትን ሰነዶች እና ሌሎች ማስረጃዎች ላይ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ መሆኑን አረጋግጧል።

    ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በቅርቡ የስትራቴጂክ (መሪ) እቅድ ክለሳ ያደረገ ሲሆን፤ ይኸው የከፍተኛ ኃላፊዎች ሹመትም ከዚሁ ክለሳ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀውን አዲስ የባንኩን አደረጃጀት መሠረት ያደረገ ነው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንብ ኢንተርናሽናል ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ተቋም ለመሆን እየሠራ ነው

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ተቋም ለመሆን እየሠራ መሆኑ ተገለጸ። አስራ ሰባት (17) ችግር ፈቺ ምርምሮች ተሠርተው ወደ ግምገማ እና ትግበራ ገብተዋል።

    ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ ተቋሙ በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ካሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቶች ቀዳሚው ለመሆን እየሠራ ነው።

    በዚህም 17 የሚሆኑ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑንና ከፊሉ ወደ ትግበራ ማስገባታቸውን፥ እንዲሁም የተቀሩትን ምርምሮች ወደ ትግበራ ለማስገባት በግምገማ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

    ምርምሮቹም በጤና፤ በትምህርት፤ በአገልግሎት አሰጣጥና በፋይናንስ ዘርፍ ግልጋሎት እምርታዊ ለውጥ የሚያመጡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ለአብነት ያህልም በጤናው መስክ፥ የተለያዩ የሕክምና ዘርፉን ሊያዘምኑ ወይም ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ውስን የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች የሚገኙባቸው ሴክተሮች ላይ ተጨባጭ ውጤት ያመጣልም ብለዋል።

    የጭንቅላት እጢ፣ የጡት ካንሰር፣ የቆዳ በሽታ ልየታን ማከናወን የሚችሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች መዘጋጀታቸውንም አብራርተዋል። በአዲስ አበባ ስማርት ሲቲ (smart city) ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው የስማርት ሴኩሪቲ (smart security) ግንባታዎች እየተካሄዱ እንዳሉ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፥ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶች በሚካሄዱባት አዲስ አበባም በሺዎች የሚቆጠሩ የአርተፊሻል ኢተለጀንስ ካሜራዎች መገጠማቸውን አንስተዋል። ካሜራዎቹ የፊት ገፅታን እና የመኪና ሰሌዳ ቁጥሮችን የሚለዩ እና የሚመዘግቡ መሆናቸውን አያይዘው ጠቅሰዋል።

    በፋይናንስ ሴክተር የውይይት መለዋወጫ ሮቦት (ቻትቦት/chatbot) በማዘጋጀት ዘርፉን የሚያዘምኑ ሥራዎች እየተከወኑ እንዳሉ በማብራራትም፤ ቻትቦቶቹ በተመረጡ ሀገርኛ ቋንቋዎች ጭምር ግልጋሎት ይሰጣሉ ብለዋል። የደረቅ ጭነት የተቀናጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ ደግሞ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚንስቴር አበርክቶ መተግበሪያዎቹ ግልጋሎት መስጠት መጀመራውን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አትተዋል።

    በትምህርቱ መስክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አሰጣጥ አገልግሎታቸውን ማዘመን የሚያስችል እና የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ማስቀረት የሚያስችል እጅግ ዘመናዊ የሆነ መተግበሪያ ለምቶ ትግበራ ላይ መዋሉንም ጨምረው ጠቅሰዋል። የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶች በቅልጥፍና እንዲሠሩ እና ለመረጃ ቋትነት ግልጋሎት የሚሰጥ ማዕከል ግንባታም በተቋሙ ውስጥ ተከናውኗል ያሉት ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ፥ የመረጃ ቋት መኖሩ ለተማሪዎችም ይሁን ለመምህራን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    Semonegna
    Keymaster

    “መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት አገልግሎት አሰጣጡ ምቹ ባለመሆኑ ለእንግልት ተዳርገናል” ― ተገልጋዮች
    “በጉዳዩ ላይ በቅርቡ መግለጫ እሰጣለሁ” ― የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን ተገልጋዮች ቅሬታ አቀረቡ። የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በበኩሉ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለቀረበለት ተደጋጋሚ ጥያቄ በጉዳዩ ላይ በቅርቡ መግለጫ እሰጣለሁ ከማለት ውጪ መረጃ ሊሰጥ አልቻለም።

    በአዲስ አበባ መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣትም ሆነ ለማደስ ወደተቋሙ የሚሄዱ ተገልጋዮች በተቋሙ ባለው ምቹ ያልሆነ አሠራር ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ይገልጻሉ። ተገልጋዮቹ እንደሚሉት በተቋሙ አገልግሎቱን ለማግኘት ከሌሊት 9፡00 ሰዓት  ጀምሮ ተሰልፎ ወረፋ ከመጠበቅ ጀምሮ ፓስፖርቱ አልቆም ለማግኘት ያለው ሂደት ውስብስብና ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ ነው።

    ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ፓስፖርት አገልግሎትን ለማግኘት በኦንላይን (online) አማካኝነት ምዝገባ የሚካሄድ ቢሆንም፥ ከዚያ በኋላ በተቀጠሩበት ዕለት ሌሊት ወጥቶ ወረፋ መጠበቅ፣ ከዚያም በኋላ ሂደቱን ሲያልፉ ፓስፖርት ለማግኘት ያለው አሠራር ተገልጋይን የሚያማርር ነው።

    የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መዲና ጂብሪል፥ ለልጆቻቸው ፓስፖርት ለማውጣት በስም ዝርዝር ምደባ መሠረ ከካዛንቺስ ፖስታ ቤት እንዲወስዱ የተገለጸላቸው ቢሆንም፥ ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ከፖስታ ቤቱ አልደረሰም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል።

    ወደ ኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ተመልሰው መጠየቅ እንዳለባቸው የተነገራቸው ወይዘሮ መዲና፥ ከዋናው መሥሪያ ቤት ወደፖስታ ቤት በየጊዜው እያመላለሷቸው መቸገራቸውን በምሬት አስረድተዋል።

    ከዚህ ባለፈ በኢምግሬሽን መግቢያ በሮች ላይ ጥበቃዎችና ተራ አስከባሪዎች ወደ ውስጥ እንዳታስገቡ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶናል በሚል ተገልጋዮችን ለመምታት የሚጋበዙ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዚህም የሚመለከተውን አካል ለመጠየቅም ሆነ ለማነጋገር እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

    ችግሩን በተመለከተ ለማን አቤት ይባላል የሚሉት ወይዘሮ መዲና፥ ዜጎችን የሚያጉላሉ አሠራሮችን ማስተካከልና አገልግሎቱን የተሟላ ማድረግ ይገባል ብለዋል። መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት አስፈላጊውን ማስረጃ ከሰጠችና ከተመዘገበች አንድ ወር ከአሥራ አምስት ቀን እንደሆናት የምትገልጸው ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሪት ሰናይት ንጉሴ ነች።

    የአስቸኳይ ፓስፖርት ከመከልከሉ በፊት መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት በመሄድ ማመልከቷን ትገልጻለች። ኦርጅናል የልደት ካርድ፤ መታወቂያና የትምህርት ማስረጃዎችን እንዲሁም አስፈላጊውን መረጃ ሁሉ አሟልቻለሁ። አሻራ የሰጠሁ ቢሆንም ማስረጃውን አጣርተን እንጠራሻለን የሚል ምላሽ ቢሰጠኝም እስካሁን ምላሽ አላገኘሁም ትላለች።

    እኔ ሻይና ቡና በመሸጥ የምተዳደር ነኝ። በሕጋዊ መንገድ ወደ ሌላ አገር ሄጄ ለመሥራት ብዩ ፓስፖርት ለማውጣት ፈልጊያለሁ ስትል ሁኔታዋን አስረድታለች።፡ ከለሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ተራ ለመያዝ ወደኢምግሬሽን የምትሄድ መሆኑን በመግለጽ፤ እንግልቱ ግን ወደ ኢምግሬሽን በተደጋጋሚ የሄደች ቢሆንም ሳንደውል ለምን ትመጫለሽ የሚል ምላሽ እንደተሰጣትና፤ ጉዳዩን ለተቋሙ ቅሬታ ሰሚዎች ያቀረበች ቢሆንም ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እንደተነገራት አስረድታለች።

    የጅማ ከተማ ነዋሪው አቶ አብዲሳ ታደሰ በበኩላቸው፥ በከተማው የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተደጋጋሚ ያቀረበው የፓስፖርት ይሰጠኝ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ወደዋናው መሥርያ ቤት ቢመጡም እዚህም ምላሽ ሊያገኝ እንዳተሰጣቸው ይገልጻሉ።

    አቶ አብዲሳ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ መረጃዎችን ሁሉ ይዘው መቅረባቸውን በመጥቀስ ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱን ሳያገኙ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸዋል። የፓስፖርት ሂደቱን ሲጀምሩ በሦስት ወር እንደሚሰጣቸው የተነገራቸው ቢሆንም በተቀጠሩበት ቀን ፓስፖርቱን መውሰድ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

    የቅርጫፉን ኃላፊ ስለጉዳዩ ማነጋገሩን የሚገልጸው አቶ አብዲሳ፥ ፖስታ ቤት ሂድ በማለት እንደመለሱለት ቢናገርም ፖስታ ቤት ግን ፓስፖርቱን ሊያገኝ እንዳልቻለ አስረድቷል። በዚህ የተነሳ ወደውጭ አገር ለመሄድ ያሰበውን የቪዛ ዕድል ማጣቱን በምሬት ገልጿል።

    ችግሩ ከዋናው መሥሪያ ቤት ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ጠቁሞ፤ በወቅቱ ወደአዲስ አበባ ኢምግሬሽን ለመምጣት የመሸኛ ደብዳቤ እንዲሰጡት በጠየቀበት ወቅት ተጨማሪ 600 ብር በድጋሚ መክፈል እንደሚጠበቅበት የተገለጸለት መሆኑን አስረድቷል።

    የፓስፖርት አገልግሎትለማግኘት እየተጉላሉ የሚገኙ ዜጎች ቀልጣፋ አሠራር እንዲፈጠርና በኢሚግሬሽን አገልግሎትና በፖስታ ቤቶች መካከል ተገቢው መናበብ ሊፈጠር ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

    ጉዳዩን በተመለከተ የኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን በስልክና በደብዳቤ በተደጋጋሚ በመጠየቅ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ኤጀንሲው በጉዳዩ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ በቃል ደረጃ ቢያሳውቅም ይህን ዜና የዘገበው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወደህትመት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳልተሰጠ ማረጋገጥ ተችሏል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    Semonegna
    Keymaster

    የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሠጠው መግለጫ

    የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ያልከፈለው ዋጋ የለም፡፡

    የኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናትም ሲል ከመክፈል የሚሰስተው ዋጋ የለም፡፡ በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ መላው የክልሉ ሕዝብ በሀገር ሕልውና እና በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ ያለው አቋም የጊዜ እና የሁኔታዎች መፈራረቅን ተከትሎ የማይለዋወጥ ጽኑ ሀቅ ስለመሆኑ በታሪክና በዜጎች ህሊና እንዳይፋቅ ሆኖ የተከተበ እውነታ ነው፡፡

    ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልላችን ውስጥ የሚተለሙም ሆነ የሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት ተግባራት ከዚህ ብሔራዊ መዳረሻ አንጻር የሚቃኙ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማንኛውም ዓይነት ተቋማዊ መዋቅሮች የሚደራጁበትም አልፋ እና ኦሜጋዊ አመክንዮ ይኸው ነው፡፡

    ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዋና አጀንዳ ከሆኑት ብሔራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውና በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ዋነኛ እና ብቸኛ ምክንያትም ዓላማው የኢትዮጵያን ሕልውናን የበለጠ የማበርታት የጋራ ግብን ያነገበ፣ በተሟላ ሀገራዊ ጥናት ላይ የተመሠረተ፣ የሕዝቦችን አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተተለመ እንዲሁም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እውን ለማድረግ በሁሉም ክልሎች ታምኖበት የተገባበት ወሳኝ ተግባር ነው።

    የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የአማራ ክልልን ሕዝብ ሠላም እና ጸጥታን ለማስከበር በቅንነትና በቆራጥነት አገልግሏል፡፡

    ከክልል አቀፍ ውለታው ባሻገር በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ተጋርጦ የነበረን ከፍተኛ አደጋ ለመቀልበስ ሲል ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን በኢትዮጵያዊነት የላቀ ሥነ-ልቦናዊ ከፍታ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት ከፍሎ ኢትዮጵያና አትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣን አደጋ በታማኝነት አምክኗል፡፡ ይህ አኩሪ ገድልና ውለታ ሁልጊዜም በታሪክና በትውልድ ልቦና ውስጥ እየተዘከረና ጽንቶ የሚኖር ታላቅ ተግባር ነው፡፡

    ይህን መሰሉን ብሔራዊ ውለታ የበለጠ ለማጎልበትና ለማስፋት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አማራ ክልል ጨምሮ በሁሉም ክልላዊ መንግሥታት ውስጥ የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን ያሰባሰበ በጥናት ላይ የተመሠረተ መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ካለው የፀጥታ አመራር፣ የመንግሥት አመራር፣ የልዩ ኃይል አመራርና አባላት፣ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት የተደረገበትና እየተደረገበት ያለ በሂደት ላይ የሚገኝ የጋራ ሀገራዊ ተግባር ነው።

    ይህ የልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀቶችን መልሶ የማደረጃት ወይም የሪፎርም ሥራ በሁሉም የፌደራልና ክልላዊ መንግሥታት መሪዎች የጋራ ስምምነትና እንደ አንድ ሀገር አንድ ጠንካራ የፌደራልና የክልል የፀጥታ መዋቅር እንዲኖረን ታስቦ የተለያዩ አማራጮች ለልዩ ኃይል አባላቶቻችን ያቀረበ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በኩር ያደረገ ሀገር አቀፍ ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡ ተግባሩም ለሁሉም ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራልና የክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራልና የክልል የማረሚያ ቤቶችን ፖሊስ አባል እንዲሆኑ አማራጮች ያቀረበ ብሔራዊ ተግባር ነው።

    በቅርቡ በመንግሥት የተጀመረው የልዩ ኃይል ፖሊሶች የሪፎርም ተግባር እውነታዉ ከላይ በተቀመጡት አማራጮች ለሁሉም ክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደየፍላጎታቸው በቀረቡት አማራጮች እንዲካተቱ ታሳቢ ያደረገ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላትን የማጠናከር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኝ ብሔራዊ ተግባር ነው።

    ይሁን እንጂ እውነታዉ ይሄ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አካላት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚል ከእውነት የራቀ ፍፁም በተሳሳተ መንገድ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የአማራን ሕዝብ ውስጣዊ ሰላምና አንድነት የሚያደፈርስ፣ የልዩ ኃይሉን አንድነት የሚረብሽ፣ ባልተገባ መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ። ድርጊቱም ሕዝባችንና የልዩ ኃይል አባሎቻችንን በተጨባጭ እየረበሸ ይገኛል።

    ስለሆነም መላው የልዩ ኃይል አባላትና መላው የክልሉ ሕዝብ እንዲገነዘቡት የምንፈልገው መንግሥት ይህንን የመልሶ ማደራጀት ሥራ የሚከውነው የልዩ ኃይላችንን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀትና ብቁ የማድረግ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ የማዘጋጀት ተግባር እንጅ በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት ምንም ዓይነት የሚበተንም ኃይል የሌለ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።

    ስለሆነም መላው የአማራ ሕዝብ በአንዳንድ አፍራሽ የሚዲያ ቡድኖች በሚነዛው አሉቧልታ ሳይታለልና ሳይደናገር እንደ አንድ ሕዝብ ያለውን ታሪኩን እና ሥነ ልቦናውን በሚመጥነው የኢትዮጵያዊነት ላዕላዊ ማእቀፍ ጥላ ስር በመሰባሰብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጽናት ሂደትን እንዲደግፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

    የተከበራችሁ የክልላችን ሕዝቦች፥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም ዓይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል።

    የተከበራችሁ የክልላችን የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት እንዲሁም መላው ሕዝባችን፥ ለራሳቸው ጥቅምና ፖለቲካዊ ዓላማ ሲሉ ክልላችንን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ከሚሠሩ አካላት ራሳችሁን በመጠበቅ የክልላችን የፀጥታ ኃይል ብቁ ዘቦች ሁናችሁ ሰላምና ፀጥታን በማስጠበቅ ሥራችሁ እንድትተጉ እያሳሰብን የተጀመረውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ መላው ሕዝባችንንና ልዩ ኃይላችንን በማወያየት እና በመተማመን የሚፈፀም በመሆኑ በየካምፓችሁ ወይም በየተመደባችሁበት የሥራ ቦታ ተረጋግታችሁ በትግስት እንድትጠብቁ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።

    የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
    መጋቢት 29/2015 ዓም
    ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያ

    ምንጭ፦ የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት

    Amhara Regional State የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

    Semonegna
    Keymaster

    ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ሕንፃ ምህንድስና፣ በሕክምና እና በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

    ዲላ (ዲላ ዩኒቨርሲቲ) – ዲላ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂና ምህንድስና ኮሌጅ ስር በሥነ-ሕንፃ ምህንድስና (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል፣ በሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሕክምና (ሜዲሲን) ትምህርት ክፍል እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች መጋቢት 02 ቀን፥ 2015 ዓ.ም አስመርቋል።

    በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ፤ ለተመራቂ ተማሪዎች፣ ለተመራቂ ወላጆች እንዲሁም ለተማሪዎቹ ለምረቃ መብቃት በተለያየ መልኩ ለተጉ ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ዶ/ር ማቴዎስ አክለውም፥ “የዘንድሮ ተመራቂዎች ከትምህርት እና ፈተና ባለፈ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች ተቋቁማችሁ ለዚህ የበቃችሁ በመሆናችሁ በራሳችሁ ልትኮሩ ይገባል” ብለዋል።

    ተመራቂዎች ምንም እንኳ ከተቋሙ ተመርቀው ቢወጡም በዩኒቨርሲቲው አሉምናይ (alumni) በኩል ቤተሰባዊ ግንኙነቱ እንደሚቀጥል የገለፁት ዶ/ር ማቴዎስ፥ በቀጣይ ተመራቂዎች በሚሰማሩበት መስክ ሁሉ አምባሳደር ሁነው የዩኒቨርሲቲውን መልካም ስም እንዲያስቀጥሉ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ከተመራቂዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ችግር በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በዘገበው ዜና ገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራርና አሉምናይ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ይልማ በበኩላቸው፥ በበዕለቱ በድኅረ-ምረቃ መርሃ-ግብር 68 ወንድ እና ዘጠኝ (9) ሴት፤ በድምሩ 77፣ በመደበኛው መርሃ-ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ 64 ወንድ እና 24 ሴት በድምሩ 88፣ በተከታታይ የትምህርት መርሃ-ግብር 117 ወንድ እና 30 ሴት፤ በድምሩ 147፣ በአጠቃላይ 249 ወንድ እና 63 ሴት፤ በድምሩ 312 ተመራቂዎች ለምርቃት መብቃታቸውን አብስረዋል።

    በዕለቱ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነው ዶ/ር ብርሃን አዳነ አጠቃላይ ውጤት 3.86 ነጥብ በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

    የማዕረግ ተመራቂው ዶ/ር ብርሃን አዳነ፥ “ከምንም በላይ ፈጣሪዬ ለዚህ ክብር እንድበቃ ስላደረገኝ ክብር ይግባው” ሲል በስኬቱ መደሰቱንና በትምህርቱ ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክሮ በመስራቱ በከፍተኛ ውጤት መመረቁን ጠቅሷል።

    ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የድንቅ ኪነ-ሕንፃ ጥበብ ባለቤት መሆኗን የምትናገረው የሥነ-ሕንፃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ተማሪ ሴና ኤቢሳ፥ ይሁንና ዘመናዊ ሕንፃዎች የኢትዮጵያን ባህልና ቀለም በማንጸባረቅ ረገድ ውስንነት እንዳለባቸው ተናግራለች። በቀጣይ በሥራ ሕይወቷ በግል ሆነ በቡድን ሀገር በቀል የሥነ-ሕንፃ ጥበብን ከዘመናዊው ጋር በማዋሃድ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ የድርሻዬን እወጣለሁ ብላለች ።

    የምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ የሕክምና ተመራቂዎች ሙያዊ ቃለ-ምሃላ በመፈፀም የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ የክብር እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አባላት እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልም ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረብ ዝግጅቱን አድምቆታል።

    ምንጭ፦ የዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ድረ ገጽ

    Semonegna
    Keymaster

    ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጆርናል ለማስጀመር በምሁራን አስገመገመ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በማስተማርና በምርምር ሥራዎቻቸው ዕውቅናን ያተረፉ ፕ/ር አማረ አስግዶም እና ፕ/ር ያለው እንዳወቅ እንዲሁም በኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ምርምርና ስርጭት (research and dissemination expert) ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ተስፋማርያም ሽመክት፣ ብሎም የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በተገኙበት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ‘ኮተቤ የትምህርት ጆርናል’ (Kotebe Journal of Education, KJE) የተሰኘውን ጆርናል ለማስጀማር ዝግጅቱን አጠናቆ ለዚሁ ዓላማ የተሰነዱ ፖሊሲንና መመሪያን የካቲት 16 ቀን፥ 2015 ዓ.ም አስገምግሟል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በአዋጅ ከተቋቋመ እነሆ አንድ ዓመት ከጥቂት ወራት በሆነ ጊዜ ውስጥ በርካታ የማቋቋም ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ። ከእነዚህም አንዱ ዩኒቨርሲቲው የሚታወቅበት የራሱ መለያ ጆርናል እንዲኖረው ማስቻል ነው። ጆርናል ምሁራን ጥናትና ምርምሮቻቸውን ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ለሶስተኛ ወገን ተጠቃሚ የሚያደርሱበት ድልድይ ነው። ለዩኒቨርሲቲ ይህ ድልድይ አንዱ የሀገራዊነት እና ከዚያም ባሻገር መለኪያ ነውና በጥንቃቄ የምንይዘው ነው ብለዋል። በመሆኑም ይህንኑን እውን ለማድረግ ስንሠራ ቆይተን የሚተገበርበትን አሠራር (ፖሊሲ እና የአሠራር መመሪያ) ቀርፀን ለዛሬ ማስጸደቂያ ቀን (validation) አድርሰናልና፤ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ በሙሉ ትልቅ አክብሮት አለኝ ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    በመልዕክታቸው አያይዘውም ፕሬዝዳንቱ ‘ኮተቤ የትምህርት ጆርናል’ (KJE) በዓይነቱ ለየት ያለ፣ ሀገራችንን፣ ተቋማችንን እና ትውልዱን የሚያሻግር እንዲሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲታተም ለዚሁ ሥራ አመራርነት ለተሠየመው ቲም አደራ ብለዋል።

    የ‘ኮተቤ የትምህርት ጆርናል’ አስመልክቶ የተዘጋጀ ፖሊሲን ያቀረቡት የጆርናሉ ዋና አርታኢ የሆኑት ዶ/ር ሩቂያ ሀሰን፥ የጆርናሉ ዋና ዓላማ ላቅ ባለ ሁኔታ ለተመራማሪዎች ሀገራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ የትምህርት እና የምርምር ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙበትን ተጨማሪ ዕድል መፍጠር መሆኑን ገልፀዋል። የጆርናሉ ተባባሪ አርታኢ ሆነው የተመደቡ ዶ/ር ይታያል አዲስም በበገለጻቸው የሚቀርቡ ጽሑፎች ከዚህ በፊት በማንኛውም ጆርናል ላይ ያልቀረቡና ሳይንሳዊ ሥነ-ዘዴዎችን (guidelines) ያሟሉ ስለመሆናቸው በጥብቅ ዲሲፕሊን ተገምግመውና የተቀመጠላቸውን መስፈርቶችን አሟልተው ሲገኙ ብቻ ለህትመት እንደሚበቁ ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲው የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT) መሠረተ ልማት ቡድን መሪ አቶ ማቲያስ አድማሱ በበኩላቸው፥ ለህትመት የሚቀርቡ ጽሑፎች በኦንላይን ሲስተም ሆነው ጆርናሉ ለህትመት እስኪበቃ ድረስ ያለው ሂደት ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን ይሠራል ብለዋል።

    ምንጭ፦ የዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

    Semonegna
    Keymaster

    ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱን ገለጸ

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና ገለጹ።

    መንግሥት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከመዋቅር ጀምሮ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

    ለአብነትም 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ብሔራዊ ፈተና በ12ኛ ክፍል እንዲሰጥ ከማድረግ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች በ3 ዓመት ይመረቁ የነበረውን ወደ 4 ዓመት እንዲያድግ መደረጉን አስታውሰዋል።

    ባለፉት ዓመታት በተለይ በትምህርት ፍኃዊነትና ተደራሽነት ላይ በርካታ ሥራ የተሠራ ቢሆንም በትምህርት አግባብነትና ጥራት ላይ የተሳካ ወይንም አጥጋቢ ሥራ ባለመሠራቱ ውጤት ሊመዘገብ አልተቻለም ብለዋል። ለዚህም በቅርቡ የወጣው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ችግር ምን ላይ እንዳለ በግልጽ አሳይቷል ብለዋል።

    በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ለመምህራን ምዘና ተሰጥቶ በርካቶቹ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን አውስተው፤ ይህ ለትምህርት ጥራት ችግሩ ዓይነተኛ አስተዋፆኦ እንዳለው ነው ያስረዱት። ለተማሪዎቹ ዝቅተኛ ውጤት መመዝገብ መምህራንን ጨምሮ አጠቃላይ የትምህርት ማኅበረሰቡ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ችግሩን በጋራ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

    መንግሥት የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አለመኖር ለትምህርት ጥራት መጓደል አንዱ ምክንያት መሆኑን በመረዳት ችግሩን ለማቃለል ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሙን ገልፀዋል። ጨምረውም፥ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ለማከም ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

    ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን ትምህርት ዋነኛ ምሰሶ በማድረግ የትምህርት አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ አማካሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎችን ማፍራት ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የሚያስችል የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱን ነው የተናገሩት። ፍኖተ-ካርታው በቀጣይ ለትምህርት ሚኒስቴር እንደሚቀርብም ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና የገለጹት።

    መንግሥት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመምህራን ሙያ በማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀው፥ የመምህራን ዕውቀትንና አቅምን ማጎልበት ደግሞ ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ሥራ መሆኑን አመላክተዋል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ

    Semonegna
    Keymaster

    ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በቢሾፍቱ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው

    አዲስ አበባ – ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በ108 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቢሾፍቱ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የካቲት 17፥ ቀን 2015 ዓ.ም ስምምነት ተፈራረመ።

    በስምምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፥ ኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብት-ተኮር (ኢኮኖሚያዊ) ማሻሻያዎችን እያደረገች እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ማሻሻያዎቹ አዳዲስ እና ያሉትንም ኢንቨስትመንቶች አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል።

    እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፥ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለማጠናከር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በልዩ ሁኔታ የሚደግፉ ፖሊሲዎች እና ማሻሻያዎች ጸድቀው ወደ ሥራ በመግባት አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገበ ነው። ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (foreign direct investment) መሳብ ተችሏል ብለዋል ።

    የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር ሊቀመንበር ዶክተር ብዙአየሁ ታደለ በበኩላቸው እንደገለጹት፥ የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ ስፋቱ ወደ 100 ሄክታር የሚያድግ ሲሆን ለ15 ሺህ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለቴክኖሎጂ ሽግግር ዕድል የሚፈጥር ነው።

    የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በ108 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚለማ ሲሆን ንድፉ የኢንዱስትሪያል ፓርክ አጠቃቀም ሥርዓትን የተከተለ፣ መሠረተ ልማት የተሟላለት፣ 40 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት የሚኖረው እና ታዳሽ ኃይል (renewable energy) ላይ በትኩረት የሚሠራ እንዲሁም ኤክስፖርትን የሚያሳድግ ነው ሲሉ አብራርተዋል። በተጨማሪም የአካባቢውን አርሶ አደሮች በምርት አቅርቦት የሚያስተሳስር እና ለሀገር ውስጥ ግብዓት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው ሲሉ አክለዋል።

    እንደ ዶክተር ብዙአየሁ ገለጻ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ሲገባ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማቅረብ ባሻገር ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ይሆናል።

    የኢንዱስትሪ ፓርኩ ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ላይ መገኘቱ እና ከኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ጣቢያ በቅርብ ርቀት እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከአዲስ አበባ – አዳማ ፈጣን መንገድ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባ መሆኑ እና ከሞጆ ደረቅ ወደብ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑ ፓርኩን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

    ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በውስጡ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን የያዘ የሀገር በቀል ኩባንያ ሲሆን፤ ከዚህም መካከል የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፣ ሲሚንቶ ምርት፣ አላቂ እቃዎች፣ የሪል ስቴት ልማት፣ ማዕድን ልማት እና ሎጀስቲክ የንግድ ዘርፍ የያዘ እና ከስድስት ሺህ በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ነው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    Semonegna
    Keymaster

    ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች በሚፈለገው ደረጃ ድጋፍ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። እስካሁን ከ204 ሺህ በላይ ኩንታል እህል ለተጎጂ ዜጎች መሠራጨቱም ተጠቁሟል።

    የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በቦረና ዞን በድርቅ አደጋ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ውስጥ በ13 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ወደ 604 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ድጋፍ ቀርቦላቸዋል። ካለፉት ሁለት ወራት በ15 ቀናት ውስጥም ለእነዚሁ ወገኖች 204 ሺህ 765 ኩንታል ምግብ ወደ አካባቢው ተልኮ ተሠራጭቷል። ከጉዳቱ አንጻርና የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በመንግሥትና በአጋር አካላት ቀጣይ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

    እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ ኮሚሽኑ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አጥቢ እናቶችና አቅመ ደካሞች የሚሆን 10 ኩንታል አልሚ ምግብ ወደ አካባቢው ተልኳል። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ሕብረተሰብ፣ ባለሀብቱ፣ ድጋፍ ሰጪዎችና መንግሥትም በዚሁ መልኩ ለወገኖች ሊደርስ የሚችለውን ድጋፍ እያቀረቡ ይገኛሉ።

    የኦሮሚያ ክልል 800ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የዕለት ድጋፍ መጠየቁን ገልጸው፥ በዚሁ ቁጥር ልክ ድጋፉ እንዲሰጥ ከአጋር አካላት ጋር አብሮ የሚሠራ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

    ድርቅን በሚመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ክስተቱ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ክስተቱ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል።

    በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜም በሦስት አካላት ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ እነዚህም መንግሥት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህም በየአካባቢው ጉዳት ባጋጠመባቸው ስፍራዎች የየድርሻቸውን በመያዝ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ከክልል ጋር በመሆን ለሥርጭት እንዲበቃ ያደርጋሉ ነው ያሉት።

    እንዲህ ዓይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የማስተባበር ሥራን በመሥራት ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ከክልሎች ጋር አብሮ የሚሠራባቸው ስልቶች እንዳሉ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል። ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥም በክልል ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ማቋቋም አንዱ እንደሆነና በዞን ደረጃ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ጉዳት ሲደርስባቸው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት እንደሚቋቋም ጠቅሰዋል።

    ይህም በክልል የሚመራና ኮሚሽኑ የሚደግፈው የጤና፣ የግብርና፣ የውሃ፣ የትምህርትና ሌሎች ጉዳዮች እንደመኖራቸው ሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን አስተባብሮ ማስኬድ የሚያስችል ድጋፍ በቅንጅት እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ሁኔታዎች ምክንያት በአጋር አካላት የሚደርሰው ድጋፍ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የተበታተነውን ሁኔታ መሰበሰብ የሚያስችል ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ያሉ አካላት የሚሳተፉበት ተግባራትም እንዳሉ ጠቁመዋል።

    አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያምን ጨምሮ በየቢሯቸው በመገኘት አጋር አካላትን፣ ኤምባሲዎችን፣ የመንግሥታቱ ኅብረት ተወካዮችን እያነጋገሩ እንዳለ ገልጸዋል። በዚህ መልክ ድጋፉ እንዲጠናከር ይደረጋል ሲሉም አስታውቀዋል።

    ዳይሬክተሩ እንዳሉት፥ በሀገሪቷ ድርቅና ሌሎች ተዛማች ችግሮች አሉ። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ከሀገር ውስጥ አቅም ባሻገር የአጋር አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው። ለዚህም አጋር አካላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅትም ድጋፉ እየመጣ ነው፤ ለዚህም በሚፈለገው ደረጃ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

    ከመንግሥት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊ ተቋማት ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የተለያዩ እርዳታዎችን እያሰባሰቡ ይገኛሉ። እርስዎም በዚህ ድጋፍ ለመሳተፍ የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጫኑ።

    1. ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (GARE) በጎፈንድሚ (GoFundMe) በኩል፦ GARE4Borena
    2. በሀገር ውስጥ ደግሞ የጉዞ አድዋ ማኅበር አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ (Yared Shumete) እና መምህር ታዬ ቦጋለ አረጋ “ዓድዋ 127 ለቦረና” በሚል እንቅስቃሴ በመጀመር የተለያዩ ድጋፎችን (ገንዘብ፣ የምግብ ምርቶችን፣ ወዘተ) እያሰባሰቡ ነው። ያግኟቸው፦ http://www.facebook.com/shumeteyared እና http://www.facebook.com/tayebogale.arega

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 132 total)