-
Search Results
-
ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል እየተጠናቀቀ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። በቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ 3 ሺህ የከተማ አውቶቡሶችን ለማሰማራት የግዥ ሂደት ላይ መሆኑንም የትራንስፖርት ቢሮው አክሎ አስታውቋል።
በቢሮው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሀንዲስ ኢ/ር ናትናኤል ጫላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደጠቆሙት፥ መንግሥት በመደበው ከፍተኛ በጀት መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል ግንባታው ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመከናወን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ87 በመቶ በላይ መድረሱንም ኢ/ር ናትናኤል አመልክተዋል።
በዘመናዊ መልኩ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያሉት መሆኑንም ኢ/ር ናትናኤል ጨምረው ጠቅሰዋል። ከነዚሁ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መካከል ዘመናዊ የትኬት መቁረጫ፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ፣ የተገልጋይ ማረፊያ፣ ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ አሳንሰር፣ የመረጃ ማዕከልእና የተገልጋይ መጸዳጃ ቤቶች ይገኙበታል።
በመሀል ገበያ 4 ሺህ ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ የሚገነባው የአውቶቡስ ተርሚናል ባለ ሁለት ወለል ከፍታ ያለው መሆኑን ኢ/ር ናትናኤል አስረድተዋል። በአፍሪካ ትልቁ ክፍት የገበያ ማዕከል በሆነው መርካቶ በአንድ ቀን ብቻ ከ50,000 እስከ 80,000 ገበያተኛ ሕዝብ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግበት የሚገመት ሲሆን የአውቶቡስ ተርሚናሉ በዚህ የገበያ ማዕከል አቅራቢያ መገንባቱ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባብሪያ ጽሕፈት ቤት በከተማዋ ውስጥ አራት (ማለትም፥ መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ሰሚት እና መገናኛ አካባቢዎች) ዘመናዊ የአውቶቡስ ተርሚናሎችን ለመገንባት ከ2008 ዓም ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።
ከሚገነቡት ተርሚናሎች ውስጥ አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም በመገናኛ አካባቢ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አንድ ዘመናዊ የብዙኃን ትራንስፖርት ተርሚናል ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢ/ር ናትናኤል ጠቁመዋል። ይህ የአውቶቡስ ተርሚናል ተገንብቶ ሲጠናቀቅዘመናዊ ተርሚናሉ የአንበሳ አውቶቡስ፣ ሸገር ባስንና ታክሲዎችን ጨምሮ የተለያዩ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በማጣመር በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢ/ር ናትናኤል እንዳሉት የመገናኛው የአውቶቡስ ተርሚናል በአንድ ሄክታር ቦታ ላይ የሚገነና እና ባለስምንት ወለል ሲሆን አራቱ ወለሎች የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥበት ነው። በተጨማሪም የፈጣን አውቶቡስ፣ የታክሲ እና የቀላል ባቡር አገልግሎቶች በጣምራ የሚሰጥበት መሆኑንም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ለእግረኞች አገልግሎት የሚውል አንድ ዘመናዊ ድልድይና 200 መኪኖችን በአንድ ቦታ ለማስቆም በሚያስችል የመኪና ማቆሚያ ቦታ (ፓርኪንግ) እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የብዙኃን ትራንስፖርትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጅነር ናትናኤል፥ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት ግንባታን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን በከተማዋ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን 1 ሺህ የከተማ አውቶቡሶች ቁጥር ለማሳደግ በቀጣዩ ዓመት 3 ሺህ አውቶቡሶችን ግዥ ለመፈጸም እተሠራ መሆኑንም ኢ/ር ናትናኤል ጨምረው ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል በሚል በመሠረተው የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ) – የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) እንዲሁም አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ላይ ላደረሱትና ለሚደርሰው ጉዳት የ174.6 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ እስከሚያልቅ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ክስ እንዳቀረበባቸውና ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት እንደቀርቡ ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ጥምረት ለተሻለ ጤና) /ABH Partners/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት ኤጀንሲው የድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማጠልሸቱ ይቅርታ እንዲጠይቅና ችግሩን እንዲያርም ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
በዚህም ድርጅቱ ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ-ብሔር ስድስተኛ ምድብ ችሎት የመዝገብ ቁጥር 241863 ክስ ለመመሥረት ተገዷል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴን ጨምሮ አምስት የሥራ ኃላፊዎችም ተከሰዋል።
ኤጀንሲው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) ጋር በጥምረት የሚሠሩትን ሥራ እንደማያውቀው ቢያስተባብልም፤ ሁለቱ ተቋማት ውል ተፈራርመው ሥራውን ሲጀምሩ በወቅቱ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በቦታው ተገኝተው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው እንደነበር ዶ/ር ማርቆስ አስታውሰው፤ “ይህም መንግሥት አያውቀውም የሚለውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አመላካች ነው። ከወራት በፊት ትምህርት የሚሰጥበትን ቦታ ተገኝተው የጎበኙ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች ግን ‘ሥራው የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማዳበር ያገዘ ነው’ ሲሉ አሞካሽተውታል። ለጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመስጠት የመምህራን ፍልሰት እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱንና ለትምህርት ጥራት እንዲተጋ የሚያግዙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ሚኒስቴሩ ምስክርነቱን በደብዳቤ ሰጥቷል” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ፥ የዚህ መሰል የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነት ለትምህርት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ሚናው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፥ ለዚህ ሊበረታታ ለሚገባው ድርጅት አገራዊ ፋይዳውን በማየት የግንባታ መሬት በመስጠት ትብብር እንዲደረግላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የትብብር ደብዳቤ እንደፃፈላቸውም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ለዩኒቨርሲቲውና ለድርጅቱ ምስክርነት በመስጠት ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሲያደርግ፥ ኤጀንሲው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከሰጠው ሥልጣን ውጪ “ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቅና የለውም፤ ሕጋዊም አይደለም” በማለት እግድ ማስተላለፉ “ባለፉት ሰባት ዓመታት የት ነበረ?” የሚል ጥያቄንም የሚጭር እንደሆነ ዶ/ር ማርቆስ አብራርተዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራውን ሊሰራ፤ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊሰጥ በገቡት ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ባለው ካምፓስ ምንም ዓይነት የመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግለት ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ለመማር-ማስተማሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ በውሉ መሠረት ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ ማስተማርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችል ኤጀንሲው ቢገልጽም፣ በዩኒቨርሲቲው እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ግን ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል።
በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሟላት ድጋፍ ሊሰጣቸው ከሚችል ከማንኛውም ተቋም ጋር መሥራት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በዚህም በአዋጁ ያልተከለከለን ሥልጣን ኤጀንሲው በደብዳቤ መሻሩ ተገቢነት እንደሌለው ዶ/ር ማርቆስ ገልፀዋል። በመሆኑም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች በሁኔታው መደናገጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ (ቁጥር 650/2001) አንቀጽ 93፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች እንዲሰጥ ስለማድረግ ይደነግጋል። በዚህም ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስቀምጧል።
በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (ቁጥር 240/2003) በአንቀጽ ሦስት መሠረት የዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን፣ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ተቀምጧል።
ባለፉት 15 ቀናት ኤጀንሲው “የትብብር ሥልጠና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ” በሚል ሚኒስቴሩ በደብዳቤ ማሳወቁን መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መልኩ ሲሠሩ የነበሩ የጅማ፣ የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታገዱ አሳውቋል።
ሆኖም ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሥራቸውን በመቀጠላቸው “አደብ ሊገዙ ይገባል” ብሎም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በተቋማቱ በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች ዝርዝር እንዲላክለት የጠየቀ ሲሆን፤ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልገው አሳውቆ ነበር።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Topic: ደሃን በማጥፋት ድህነትን መዋጋት አይቻልም!
ሴተኛ አዳሪዎች እና የእኔ ቢጤዎች (ለምኖ አዳሪዎች) ላይ መስተዳድሩ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ሰብዓዊነት የጎደለው እና መንግሥት ድህነትን ለማጥፋት በቅድሚያ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ሠርቶ ሳይጨርስ በድሃ ላይ ለመዝመት ማሰቡ የአስተዳደሩን ብልሹ አተያይ ከወዲሁ የሚያሳይ ነው።
ደሃን በማጥፋት ድህነትን መዋጋት አይቻልም!
(ያሬድ ኃይለማርያም)የአዲስ አበባ መስተዳደር የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ በሚል የፈረጃቸውን የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን ከከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለማወገድ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ሽር ጉድ እያለ መሆኑን እና ሕግ ያረቀቀ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል። ህብር ሬዲዮ እንደገለጸው በመስተዳድሩ የከንቲባው ጽ/ቤት የፕሬስ ጉዳይ ሹም ከፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የአገሪቱን እና የከተማዋን መልካም ገጽታን የሚያበላሹት ከ50 ሺህ በላይ የእኔ ቢጤዎች እና 10 ሺህ የሚገመቱ ሴተኛ አዳሪዎች ከከተማው ጎዳናዎች የሚወገዱበት እርምጃ ሊተገበር ተቃርቧል” በማለት መግለጻቸውን ዘግቧል።
ከ90 በመቶ በላይ ድሃ ሕዝብ የያዘች እና በዓለምም የድሃ ድሃ በሚል ማዕረግ የምትታወቅ አገር ድህነትን ለመቅረፍ ገና ረብ ያለው እርምጃ ሳትወስድ ድሃን ለማጥፋት መጣደፏ አጃይብ የሚያሰኝ ነው። ለነገሩ ለአንዳንድ ችግሮቻችን መስተዳድሩም ሆነ በአገር ደረጃ የሚወሰዱቱ እርምጃዎች እጅግ አስገራሚ እና በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር ምን ያህል ያህል ይተዋወቃሉ የሚለውን እንድንጠየቅ የሚያደርጉ ነገሮች ደጋግመን እያየን ነው። ለምሳሌ ያህል ሌብነት በእግረኛ፣ በሞተረኛ፣ በመኪና እና በሌሎች የተደራጁ ቡድኖች በአደባባይ በሚፈጸምባት መዲና፤ አዲስ አበባ ሌብነት ለመከላከል ተብሎ በሞተር አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደው የጅምላ እቀባ፣ ፈተና እንዳይሰረቅ በሚል የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናዎች ሲቃረቡ የኢንተርኔት አገልግሎት ለቀናቶች ማቋረጥ እና እነኚህን የመሳሰሉ አንዱን ችግር በሌላ ችግር የመቅረፍ አካሄድ ግራ ከማጋባት ባለፈ የአስተዳዳሪዎቹንም ብቃት እና ለሕዝብ ችግር ያላቸውንም ቀረቤታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። የተደራጀው ሌብነት በመኪና ቢሆን የሚካሄደው ምን ሊደረግ ይሆን?
ወደ ተነሳሁነት ዋና ጉዳል ልመለስና በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት ሥራ በተሰማሩ የአገሪቱ ዜጎች ላይ መስተዳድሩ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ሰብዓዊነት የጎደለው እና መንግሥት ድህነትን ለማጥፋት በቅድሚያ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ሠርቶ ሳይጨርስ በድሃ ላይ ለመዝመት ማሰቡ ደግሞ የአስተዳደሩን ብልሹ አተያይ ከወዲሁ የሚያሳይ ነው። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ የድሃ ደሃ አገር አይደለም በሰለጠኑት እና በሃብት በተትረፈረፉት አገሮች እንኳን የመንገድ ላይ ለማኝ እና ሴተኛ አዳሪ አይታሰርም፣ አይሳደድም ወይም ከከተማ እንዲወገድ አይደረገም። አንዳንዱ አገር ሴተኛ አዳሪነት እንደ ማንኛውም የንግድ ሥራ ጭምር ተቆጥሮ የግብር ከፋይ ኮድ ተሰጥቷቸው እና ፍቃድ ተሰጥቷቸው በአደባባይ እንደልባቸው እና ሙሉ ጥበቃ ተደርጎላቸው ይሰራሉ። እኛ ጋ ይህ ይሁን እያልኩ አለመሆኑ ይታወቅልኝ። ነገር ግን እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ከጎዳና ላይ ለማጽዳት ሕግ ከማርቀቅ እና ከመፎከር በፊት ዜጎችን ለልመና እና ለሴት አዳሪነት የሚዳርጉትን ዋና ዋና ምክንያቶችን በቅጡ ማጥናት እና ምንጩን ለማንጠፍ ማቀድ ይቀድም ነበር።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም ሆኑ አብረዋቸው ሃሳቡን የሚገፉ የመስተዳድሩ አካላት የሚያስተዳድሯትን ከተማ እና የሚመሩትን አገር ባህሪ በቁጡና በደንብ ያጠኑት እና ያወቁት አልመሰለኝም። የአዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሴተኛ አዳሪዎች ለመስተዳድሩ ተሿሚዎች እና በቅንጦት ለሚኖረው የከተማዋ ነዋሪ የዓይን ቁስል እንደሆኑባቸው ግልጽ ነው። የአዲስ አበባን አውራ ጎዳናዎች ከእነዚህ ድህነት ገፎት አደባባይ ላይ ካሰጣቸው ዜጎች በማጽዳት ግን የኢትዮጵያን ድህነት ወይም የከተማዋን እውነተኛ ገጽታ መሸፈን አይቻልም። ከንቲባው ከጥቂት ወራቶች በፊት የአዲስ አበባን የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ተለያዩ የማኖሪያ ተቋማት ለማስገባት ዘመቻ ጀምሬያለው በማለት በየጎዳናው ላይ ሕጻናት ሲሰበስቡ የተነሱትን ፎቶ በየማኅበራዊ ድረ-ገጹ ለቀው እና ዜናውም በአገሩ ተናኝቶ አይቻለው። ያን ጅምራቸውን የት አድርሰውት ይሆን? በወቅቱ የተሰማኝ ነገር ነገርየው እጅግ ተገቢ እርምጃ ቢሆንም ከገጽታ ግንባታ የዘለለ መሆኑ ስጋት ፈጥሮብኝ ነበር። ዛሬም የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመንገድ ላይ ተዳዳሪዎች እንደተሞሉ ናቸው። ያንን ፕሮጀት ፍሬውን ሳያሳዩን ድሆቹን ከመንገድ ለማጥፋት ሕግ ማርቀቅ መጀመራቸው የበለጠ ለገጽታ ግንባታ የሰጡትን ክብደት እንጂ ሰብዓዊነታቸውን አያሳይም።
ወያኔም ይችን ድሃን ከጎዳና ላይ የማራቅ ስልት በከፋ ሁኔታ ደጋግማ ሞክራዋለች። አዲስ አበባ ከሚመጡ ዓለም አቀፍ እንግዶች አይን ድሃን ለማራቅ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን አፍሰው በሌሊት ከአዲስ አበባ አርቀው በመጣል እና ወደ ከተማዋ እንዳይመለሱ በማድረግ የጅብ እራት ያደረጓቸው ዜጎች ነበሩ። ይህ አስነዋሪ እርምጃ በወቅቱ በኢሰመጉ ተጣርቶ መግለጫ ወጥቶበታል። ዛሬ መስተዳድሩ ይህን አይነት አስነዋሪ ድርጊት ይፈጽማል ብዮ ባላስብም የእነዚህን መጠጊያ የሌላቸው ድሆች እንቅስቃሴ በሕግ ለመገደብ የጀመረው እንቅስቃሴ ግን አልሸሹም ዞር አሉ ነው የሚሆነው።
የዛሬ ሃያ ዓመት ግድም በአዲስ አበባ ከተማ በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት በተሰማሩ ዜጎች ላይ ያተኮረ እና አንድ ዓመት ተኩል ግድም በወሰደ ጥናት ላይ የመሳተፍ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን መንግሥት የከተማው ነዋሪ ጭምር የማያውቀው ብዙ ጉድ እንዳለ የታዘብኩበት እና እንደ ዜጋ እራሴም የተሸማቀቅኩበት ብዙ ገበናችንን አይቻለሁ። አዲስ አበባ ቢያጠኗት የማታልቅ የጉድ ከተማ ነች። በውስጧ ብዙ አይነት ሕይወትን የያዘች እና ብበዙ ድሃ ዜጎች ገበና ሸፋኝ ከተማ ነች። ችግሩ ገበናዋን አስተዳዳሪዎቿም ሆኑ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ አያውቀውም። የሚያስተዳድሯትን ከተማ የማያውቁ አስተዳዳሪዎች ታክተው ትተዋት እሲኪሄዱ የነሱንም ገበና ተሸክማ የምትቆይ ጉደኛ ከተማ ነች።
በሴተኛ አዳሪዎች ላይ ያደረግነው ጥናት እና የሰማናቸው የህይወት ታሪኮች ቢጻፉ መጻህፍት ይወጣቸዋል። ከ14 ዓመት ህጻን ሴተኛ ዳሪ አንስቶ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ታናናሽ ወንድም እና እህቶቿን ለማስተማር እና ለማስተዳደር በአንድ ምሽት ከ24 ወንዶች ጋር በየተራ ግንኙነት አድርጋ በስተመጨረሻ እራሷን ስታ የወደቀችውን የጎጃም በረንዳ ወጣት ሴት ታሪክ ከራሳቸው ከባለታሪኮቹ አንደበት ሰምቻለሁ።
ባለሥልጣናት በሚሊዮን ገንዘብ በሚቆጠር ወድ መኪኖች፣ በተንጣለሉ ቪላዎች፣ በውድ ሆቴሎች በሚንፈላሰሱባት እና ባስነጠሳቸው ቁጥር ከአገር ውጭ ውጥተው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ህክምና እንዲያገኙ በምታደርግ አገር ውስጥ የኑሮ ዋስትና አጥተው ጎዳና ላይ የሚለምኑ እና ሰውነታቸውን የሚሸቅጡ ዜጎች (ሴተኛ አዳሪዎች) ቁጥር ቢበረክት ምን ይገርማል። እያንዳንዱ ዜጋ በአገሪቱ ሃብት እኩል የመጠቀም መብት እና ድርሻ እንዳለው ባልተቀበለች አገር ውስጥ የሺዎችን ድርሻ ለአንድ ድንቁርና ለተጫነው እና ሰብዓዊነት ከውስጡ ተንጠፍጥፎ ላወጣ ባለስልጣን ምቾት እና ድሎት የምታውል አገር በጎዳና ተዳዳሪ ዘጎች ብትወረር ምን ይደንቃል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከድህነት እና ከድሃ ጋር በተያያዘ የሚናገሩት ሁለት ቁምነገር ይህን እየጻፍኩ ወደ አዕምሮ ስለመጣ ላካፍላችሁ። አንዱ “ድሃ ባይኖር ኖሮ ሃብታም ተብድሎ አያድርም ነበር” የምትለዋ ነች። አዎ ማኅበራዊ ፍትህ በተጓደለበት፣ ሙስና ያለቅጥ በተንሰራፋበት፣ ግለኝነት በነገሰበት እና ለድሃ አሳቢ መንግሥት በሌለበት ስፍራ ሁሉ የሚሊዎኖች ድህነት የጥቂቶች የብልጽግና ምንጭ ይሆናል። ዘርፎ የበለጸገውን ባለሃብት እንተወው እና ለአንድ ባለሥልጣን ምቾት ተብለው የሚበጀት ገንዘብ ለስንት ድሃን የመኖር ዋስትና እና መሠረታዊ ነገሮች ሟሟያ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ለእናንተው እተዋለሁ።
ሁለተኛው የፕሮፌሰር ምክረ ሃሳብ ድህነትን የመርሳት በሽታችንን የሚያሳይ ነው። ምን ይላሉ “እንደ ድህነት ቶሎ የሚረሳ ነገር የለም፤ እኔም ድህነቴን እንዳልረሳ ድሆች ያሉበት አካባቢ መኖርን እመርጣለሁ። ድህነቴን ካልረሳው ድሃንም አረሳም፤ ያለኝን በወር በወር ከድሃ ጋር እካፈላለሁ።” እያሉ ድህነታችንን ቶሎ እንዳንረሳ እና በድሃ ላይ እንዳንጨክን እና እንዳንከፋ ደጋግመው ያስተምሩን ነበር። ድሃ ሰው ድህነቱን ቢረሳ ኩነኔው ለራሱ ነው። በሌሎች ድሆች ላይ የሚያደርሰውም ጉዳት ያን ያህል ላይሆን ይችላል። ድሃ ሕዝብ የሚያስተዳድር ድሃ መንግሥት ድህነቱን ቶሎ ሲረሳ እና ከተማዋን የሀብታሞች ደሴት ለማድረግ እንቅልፍ ሲያጣ ግን አደጋው ብዙ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው ሕዝቧ ትልቁን ቁጥር በሚይዝበት አገር ድሃን ከመንገድ ለማራቅ መዳከር ውድቀትን መለመን ነው። በሞቀ ጎጇቸው ውስጥ እየሆሩ በድህነት አቅሙ የጣላትን ደሳሳ ጎቾ በላዩ ላይ አፍርሰው ሲያበቁ መንገድ ላይም ለምኖ እንዳያድር ሕግ የሚያወጡ እና ስልት የሚነድፉ ሹመኞች ጸባቸው ከድሃ እንጂ ከድህነት ሊሆን አይችልም። ባለፉት 27 የታከለ ኡማ ፓርቲ ኢህአዴግ መኖሪያ ቤታቸውን እያፈረሰ ለጎዳና ላይ ሕይወት የዳረጋቸውን ዜጎች የፈረሰው ቤት ይቁጠራቸው።
የአዲስ አበባ መስተዳድርም ሆነ የአገሪቱ መንግሥት እንዲህ አይነት የዜጎችን መሠረታዊ መብት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና በተለይም ድሃውን የአገሪቱን ሕዝብ የመኖር ዋስትና የሚያሳጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከመሞከር በፊት ለዜጎች ድህነት እና ለጎዳና ሕይወት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለማንጠፍ ቢሰራ መልካም ነው። ይህ ደግሞ እንዲህ በጥድፊያ በአንድ ዓመት አይደለም በአምስት እና አስር ዓመትም ውስጥ የሚሳካ ነገር ስላልሆነ ቅድሚያ ድህነትን ለማጥፋት ይሰራ። ድሃነት መአረግ ስላልሆነ ማንም መርጦ የገባበት ህይወት አይደለም እና ድህነት ሲጠፋ ድሃም እቤቷ ትሰበሰባለች። ድሃ ላይ ያነጣጠሩ የጽዳት ዘመቻዎች ግን ‘ወጡ ሳይወጠወጥ…’ ነው የሚሆነው።
በቸር እንሰንብት!
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በዛሬው ዕለት (የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም.) በአዲስ አበባ 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም ቤቶች) ዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ተካሄደ።
ዕጣ ከወጣባቸው ቤቶች ውስጥም 32 ሺህ 653 ቤቶች የ20/80 ቤቶች ሲሆኑ፥ ቀሪዎቹ 18 ሺህ 576 ደግሞ የ40/60 ቤቶች ናቸው። በዚህም መሠረት የ20/80 ፕሮግራም ኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 248 ስቲዲዮ፣ 18 ሺህ 823 ባለ አንድ መኝታ፣ 7 ሺህ 127 ባለ ሁለት መኝታ እና 5 ሺህ 455 ቤቶች ደግሞ ባለ ሦስት መኝታ ክፍሎች ናቸው። በእነዚህ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውስጥ የሚካተቱት በ1997 ዓ.ም ተመዝግበው በ2005 ዓ.ም በነባር መደብ የተመዘገቡና በ2005 ዓ.ም የአዲስ ባለ ሦስት መኝታ ክፍል ተመዝጋቢዎች ናቸው።
በዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደተናገሩት፥ በግንባታ ሂደት ሁሉም ተጠቃሚ እንደሚሆን ቢታሰብም በጥንቃቄ ጉድለት ለጉዳትና ማኅበራዊ ቀውስ የተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ኢንጅነር ታከለ ልማት በጋራ ተጠቃሚነት ካልተመኅረተ ተጎጅና ተጠቃሚን የሚፈጥርም ነው ብለዋል። በተለይ ለቤቶች ግንባታ ሲባል ከእርሻ ቦታቸው የለቀቁ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች የሁላችንም ህመም ነው ብለዋል። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔና የቤቶች አሰተዳደር ቦርድ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች ያለ ዕጣ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።
ተሰርዞ የነበረው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ (የዕድለኞች ስም ዝርዝር)
ኢንጂነር ታከለ በቀጣይም የቤት ልማትን ከአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ጋር ለማስኬድ ትኩረት በማድረግ ይሠራል ነው ያሉት። በቤት ልማቱ የመንግስትን ተሳትፎ በመቀነስ የግሉንና የባለሀብቱን ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። ከንቲባው በዘርፉ የመንግስትና የባላሀብቶችን ግንኙነትን ለማጠናከር በትኩረት ለመንቀሳቀስ ኮሚቴ መዋቀሩን ነው ያስታወቁት።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር አባይ በበኩላቸው፥ መንግስት በቤት ልማት ዘርፍ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን የተናገሩ ሲሆን፥ በዚህ ወጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል። በቤት ልማት ዘርፉ የፍላጎቱን ያህል ባይሠራም የተሻለ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
አቶ ዣንጥራር በኢትዮጵያ ያለው የቤት ልማት ዘርፍ ህዝቡን የቤት ባለቤት ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል። ባለፉት 13 ዓመታት በአዲስ አበበና በመላ ሀገሪቱ ከ385 ሺህ በላይ ቤቶች እንደተገነቡና በግንባታ ላይ እንደሚገኙ የገለፁ ሲሆን፥ በዚህም 1 ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።
በተለያዩ ወገኖች በተደረገ ጥናት መሠረት ካለው የቤት ፍላጎት አንፃር ከ2007 እስከ 2017 ዓመተ ምኅረት ባለው ጊዜ ውስጥ 471 ሺህ ቤቶችን በየዓመቱ እየገነቡ ማቅረብ ይገባ ነበር። ሆኖም መንግስት በፋይናንስ እና በግንባታ ፕሮጀክት የማስፈፀም አቅም ባለበት ክፍተት ምክንያት ይህን ማድረግ እንዳልተቻለ በመጠቆም በቀጣይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ፍላጎቱን ለማሟላት እንደሚሠራ ነው አቶ ዣንጥራር በንግግራቸው ላይ ያነሱት።
ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች ስም ዝርዝር
◌ 13ኛ ዙር የ20/80 ፕሮግራም ባለ ስቱዲዮ ቤት የዕድለኞች ስም ዝርዝር
◌ 13ኛ ዙር የ20/80 ፕሮግራም ባለ አንድ መኝታ ክፍል የዕድለኞች ስም ዝርዝር
◌ 13ኛ ዙር የ20/80 ፕሮግራም ባለ ሁለት መኝታ ክፍል የዕድለኞች ስም ዝርዝር
◌ 13ኛ ዙር የ20/80 ፕሮግራም ባለ ሦስት መኝታ ቤት የዕድለኞች ስም ዝርዝር
◌ የ40/60 መርሃ ግብር ባለ አንድ መኝታ ቤት የዕድለኞች ስም ዝርዝር
◌ የ40/60 መርሃ ግብር ባለ ሁለት መኝታ የዕድለኞች ስም ዝርዝር
◌ የ40/60 መርሃ ግብር የባለ ሦስት መኝታ ቤት የዕድለኞች ስም ዝርዝርምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ የተከፈተው ቆንስላ ጽ/ቤት ቆንሱል ጄኔራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ ቆንስላ የጽ/ቤቱ መከፈት በሚኒሶታ ግዛት ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ አባላት ምቹ ሁኔታና መነቃቃትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ዋሽንግተን፥ ዲሲ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግስት በሀገረ አሜሪካ በሎስ አንጀለስ ከተማ (ካሊፎርንያ ግዛት) ከሚገኘው ቆንጽላ ጽ/ቤት ቀጥሎ ሁለተኛውን ቆንጽላ ጽ/ቤት በሴይንት ፓል ከተማ (ሚኖሶታ ግዛት) ከፍቷል።
ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ የተከፈተው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ በአሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት በገቡት ቃል መሠረት ነው።
በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ብርቱካን አያኖ፣ የሴይንት ፓል ከተማ ከንቲባ ሚስተር ሜልቪን ካርተር፣ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ተገኝተዋል።
ክቡር አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት የቆንስላ ጽ/ቤቱ መከፈት ለአካባቢው ብሎም በመላው አሜሪካ የሚኖረውን ዳያስፖራ ለማገልግል የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል። ዳያስፖራው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚና ፖለቲካ ለውጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ፣ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከምንጊዜውንም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ የተከፈተው ቆንስላ ጽ/ቤት ቆንሱል ጄኔራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ በበኩላቸው የጽ/ቤቱ መከፈት በሚኒሶታ ግዛት ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ የዳያስፖራ አባላት ምቹ ሁኔታና መነቃቃትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የሴይንት ፖል ከተማ ከንቲባ ሚስተር ማልቪን ካርተር በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራትና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. (ማርች 2 ቀን 2019) በከተማ ደረጃ “የኢትዮጵያ ቀን” ተብሎ እንዲከበር መወሰኑንም ጠቁመዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ዋሽንግተን፥ ዲሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ድረስ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል
- የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ የተወሰኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ
- “መንግስት ዜግነታችንን የካደ ግፍ ፈጽሞብናል” ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ውስጥ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች
- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋሙን ተከትሎ ወደ ተግባር ለመግባት የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን አጠናቀቀ
- ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ – አዲስ አበባን እንደስሟ አድርጎ ለትውልድ ለማሸጋገር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አድርጎ ለትውልድ ለማሸጋገር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደዘገብው፥ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባን የወንዞችና ወንዝ ዳርቻዎች ማልማት አዲስ ፕሮጀክትን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት “በተራሮች ከፍታ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ ሆና ለትውልድ የምትሸጋገር ውብ ከተማ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መሪነት በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነትና በከተማዋ ነዋሪዎችና በወጣቶች ትብብር ለትውልድ የሚሸጋገር ድንቅ ከተማ መገንባታችንን እንቀጥላለንም ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ። ፕሮጀክቱ ለትውልድ የሚተላለፍ የትውልድ አሻራ ያለበትና ሁላችንም የጋራ እሴቶቻችንን የምናስተላልፍበት በመሆኑ ልንደሰት ይገባል በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል።
ፕሮጀክቱ ከተማዋ እንደስሟ እንድትኖር ወንዞችና የወንዞች ዳርቻዎች ሁሉ የቆሻሻ መናኸሪያ ሳይሆኑ የሰው ልጅ በተለይም ደግሞ ወጣቶች ቁጭ ብለው በመነጋገር ሀሳብ የሚቀያየሩበትና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ ፒያሳን አካሎ እስከ ብሔራዊ ቤተመንግስት የሚዘልቅ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እስከ ብሔራዊ ቤተመንግስት ገራዥ የሚያልፍ ሆኖ እንደማሳያ የሚጀመር ነው ብለዋል።
በከተማዋ የተያዘው የልማት የወደፊት ስሌት (strategy) ሕዝቦቿ ከልማቱ ጋር የሚያድጉና የሚበለፅጉ እንዲሆኑ የሚያስችል እንጂ አንዱን የህንፃ ባለቤት በማድረግ ሌላውን ለማፈናቀል የሚሠራ አለመሆኑንም ተናግርዋል ኢንጂነር ታከለ ኡማ።
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ከተማዋ ብዙ ታላላቅ ቅርሶች ያሏት፣ አብያተ መንግስት፣ ቤተ እምነቶችና እንደመርካቶ ያሉ የታላላቅ ገበያዎች መገኛ ናት ብለዋል። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ምርጥ ሕዝቦች በፍቅር በአንድነት በደም ተሳስረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗንም አስረድተዋል ኃላፊው።
ራሳችን ተንፍሰንና ተዝናንተን ቁጭ ብለን የምንወያይበት እነጂ የተጣበበ የአስተሳሰብ መንገድ እንዳይኖረን ሰፋ ያለ የስፍራ አጠቃቀምን የሚያሳዩ የቱሪስት መዳረሻዎች የሉንም ያሉት ኃላፊው፤ ፕሮጀክቱ ለልጆቻችን ልናተርፍላቸው የሚገባ የመዝናኛ፣ የመነጋገሪያና የመናፈሻ ቦታ እንዳለውም ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር ልጆቻችን ሌሎች ሰዎችን ጋብዘው የሚጠቀሙበት የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ሊሰጥ ነው
- ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛዎቹ የታሸጉ ውሃዎች የጥራት ችግር ይታይባቸዋል
- “ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ” በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በይፋ ተጀመረ
- በአዲስ አበባ “ለሁሉ” የክፍያ ማዕከላት ተገልጋዮች መጉላላት እየገጠማቸው ነው
- አንበሳ የከተማ አውቶቡስ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ተገልጋዮች ለችግር ተዳርገዋል
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለም ከዚህ በኋላ በልማት ሰበብ የሚፈናቀልና የአርሻ መሬቱ የሚነጠቅ አርሶ አደር እንደማይኖር አረጋግጠውላቸዋል። በእስካሁኑ ሂደት የተጎዱ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እና ሕይወታቸውን ለመቀየር አስተዳደሩ ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ አርሶ አደሮችን አወያዩ። ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባላት እንዲሁም የክፍለ ከተማ አመራሮች አርሶ አደሮችን ያወያዩ ሲሆን በውይይታቸው መጀመርያም ኢንጂነር ታከለ ኡማ “የአርሶ አደሮችን ሕይወት መቀየር ታሪካዊ ኃላፊነት የጣለብን ግዴታ ነው፣ ይህንን ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነት እንወጣዋለን” ብለዋል።
አርሶ አደሮችም አላግባብ ከቀያቸው ስለመፈናቀላቸው፣ ከካሳ ክፍያና በማቋቋሚያ ድጎማ፣ በመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ በካርታ አሰጣጥና የአርሶ አደር ልጆች ካሳ ክፍያ ዙሪያ እንዲሁም በክፍለ ከተሞች ስላለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጥያቄ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለም ከዚህ በኋላ በልማት ሰበብ የሚፈናቀልና የአርሻ መሬቱ የሚነጠቅ አርሶ አደር እንደማይኖር አረጋግጠውላቸዋል። በእስካሁኑ ሂደት የተጎዱ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እና ሕይወታቸውን ለመቀየር አስተዳደሩ ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል።
ምንጭ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት
——
ሌሎች ዜናዎች:- በአዲስ አበባ የትምህርት ጥራት ደረጃን ያላሟሉ 52 ትምህርት ቤቶች ተዘጉ
- የደንበኞቹን ፍላጎት ያልቻለው የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ (ኢትፍሩት)
- ራይድ የተባለዉ የታክሲ አገልግሎት ድርጅት የስም ማጥፋት ዘመቻ እና ጥቃት ደርሶብኛል በማለት ወቀሰ
- የዱባይ አቡዳቢው ኤግል ሒልስ በአዲስ አበባ ለገሀር የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ሥራውን ጀመረ
- በአገሪቱ ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኤች አይ ቪ/ኤድስ፥ አዲስ አበባ ውስጥ በአፍላ ወጣቶች ላይ ግን ችግሩ ይከፋል