Home › Forums › Semonegna Stories › ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን) › የብልፅግናው ታዬ ደንደዓ… ስለማያወቀው ታሪክ የሚጽፈው ነገርስ ምን ይሉታል?
የብልፅግናው ታዬ ደንደዓ … ስለማያወቀው ታሪክ የሚጽፈው ነገርስ ምን ይሉታል?
(ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)
ለታላቋ ኢትዮጵያ ተብሎ ዝም ቢባል አሁንስ በዛ። ታዬ ደንደዓ፣ የብልፅግናው ባለስልጣን፣ ስለማያውቀው ታሪክ እየጻፈ የአብይ አህመድን መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው። አብይ አህመድ ህወሓት የቀደዳትን ኢትዮጵያን እንቅልፉን አጥቶ ለመስፋት ይሞከራል፤ ታዬ ደንደዓ እና መሰሎቹ ደግሞ በጎን ይተረትራሉ።
አብይ አህመድን ለማመስገን የኢትዮጵያን ታሪክ ማጠልሸት አይስፈልግም። አብይ በተደጋጋሚ እንዳለው ነው፤ ኢትዮጵያ ከሱ በፊት በነበሩ መሪዎች እየተገነባች እዚህ የደረሰች አገር ናት።
ታዬ ደንደዓ ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ የተሳሳተ ታሪክ ጻፈ። በዚህ ስህተቱ ሳያፍር ቀጥሎ ደግሞ የዛግዌንና የዶ/ር አብይን መንግሥት አወዳድሮ ሌላ የማይሆን ታሪክ ጫረ። “ሞኝ ባያፍር፣ የሞኝ ዘመድ ያፍር” ነው ነገሩ።
ታዬ ከዛገዌ መጨረሻ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበረውን የነገሥታቱን ዘመን ምንም ሥራ እንዳልሠራ አድርጎ ረገመው። በአጭሩ የደርግን ፕሮፓጋንዳ ደገመው። ዓላማው እነሱ የአማራ መንግሥት የሚሉት የሰሎሞናዊው መንግሥት ምንም እንዳልሠራ በማሳየት አማራን መወረፍ ነው።
አላዋቂነት የወለደው ድፍረትና ስልጣን የወለደው ትዕቢት ታዬን እያቅበዘበዘው ነው።
ከዛገዌ በኋላ ሸዋ ላይ የተመሠረተው ታላቅ ስልጣኔ በማን እንደፈረሰ ታዬ የሚያውቅ አይመስልም። አክሱም፣ ዛግዌና የሰሎሞናዊው ስርወ-መንግሥት ስልጣኔዎች የማይነጣጠሉ፣ ተያያዥነትና ተደጋጋፊነት ያላቸው የኢትዮጵያ ታሪኮች መሆናቸውን ለማወቅ የልብ ብርሃን ያስፈልጋል።
ደግሞ የታሪክ ሒሳብ ማወራረድ ውስጥ ከተገባ በማን እንደሚከፋ ታዬና ቢጤዎቹ ያወቁትም ያሰቡበትም አይመስልም። ደርግ እንዳስወራውና ታዬ እንደደገመው ሳይሆን፥ የኢትዮጵያ ነገሥታት ለእደ ጥበብ ሰዎች አክብሮት ነበራቸው። በሄዱበት ሁሉ ይዘዋቸው ከሚዞሩ ሰዎች መካከል የእደ ጥበብ ባለሙያዎች ይገኙበት ነበር። የኢትዮጵያ ነገሥትታና የሙስሊም ነጋዴዎች ቁርኝት በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኝ ነው። ይህ ሲባል እንከን አልነበረም ማለት አይደለም፤ እንኳንስ ትናንት ዛሬም ብዙ እንከኖች አሉ።
የመካከለኛው ዘመን ነገሥታት የሠሩትን ሥራ ለማወቅ እኮ የዛሬዋን አዲስ አበባ ቆፈር ቆፈር ማድረግ ነው። አንቶን ዲ አባዲ የተባለው ፈረንሳዊው አሳሽ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቆመበት ቦታ ላይ የነበረውን በመካከለኛው ዘመን የተሠራውን የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ዓይቶ አግራሞቱን እንዲህ ሲል ገልጾ እንደነበር Abba Emile Foucher እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“Who could have been the architect of such a building? … People who constructed such a building with well-cut stone, linked with mere clay, must have been of another type of civilizations.”
የረርን፣ በራራን፣ ፈጠጋርን፣ ጋሞን፣ ጉራጌን በአጠቃላይ የሸዋን የጥንት ታሪክ ያጠና ሰው፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ለማጥናት እየዘመቱ፣ በጎን ደግሞ ታላቅ ስልጣኔ ገንብተው እንደነበር ይረዳል። ያው እነዚህ ስልጣኔዎች እንዴት እና በእነማን እንደፈረሱ ዝርዝር ውስጥ አልገባም። ታሪካችን ስለሆነ ከመቀበልና ወደፊት ከመጓዝ ውጭ በታሪክ ‘እኘኘ…’ ስንል አንገኝም። እንደ ታዬ ደንደዓ ዓይነት አምቦጫራቂዎች ከበዙ ግን እውነቱን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።
ታዬ የዛግዌ መንግሥትን ከአብይ አህመድ መንግሥት ጋር ሲያነጻጻር በተዘዋዋሪ መንገድ የአብይን መንግሥት የኦሮሞ መንግሥት አድርገን እንድንቀበለው እየነገረን ነው። አብይን የሚደግፈው አብዛኛው ሰው የአብይን መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት እንጅ የኦሮሞ መንግሥት አድርጎ አያየውም። ከተሳሳትኩ እታረማለሁ። እንዲህ ከሆነማ አንዳንዶች “ተረኝነት አለ!” የሚሉት ትክክል ነው ማለት ነው።
አብይ አህመድ የራሱን መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ የኦሮሞ መንግሥት ብሎ ሲጠራው ወይም ተራው የኦሮሞ ነው በሚል አስተሳሰብ ስልጣን እንደያዘ ሲናገር ሰምቼ አላውቅም። አብይን የደገፉት ሰዎች ሁሉ አብይን በኢትዮጵያዊነት እንጂ በኦሮሞነት የሚስሉትም አይመስለኝም። አብይ ከኦሮሞ ነገድ ቢወጣም፥ ስልጣን የያዘው በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ የስልጣን ተራው የኦሮሞ ስለሆነ አይደለም። ስልጣን በብሔር ተራ ተከፋፍሎ ከሆነማ ኦሮሞ በየትኛው የዕጣ ድልድል ነው ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከአማራ ወይም ከጉራጌ ቀድሞ ስልጣን የያዘው? እስኪ ዕጣው መቼ እንደወጣና እንዴት እንደወጣ ንገሩን?
የእነ ታዬ ደንደዓ አመለካከት በጣም አደገኛ የሚሆነው በምርጫ ቢሸነፉ፣ እንደ ህወሓቶች ሁሉ፣ “ኦሮሞ መሪ ካልሆነ ወይም በእጅ አዙር ካልገዛ ስልጣን አንለቅም” የሚሉ መሆናቸው ነው። ስልጣንን በብሔር መንጽር ማየት ኢትዮጵያዊነትን ማዳከም ብቻ ሳይሆን፣ የብሔር አምባገነንነትም ይፈጥራል። ዋ!
የታዬ አስተሳሰብ ያላቸው ብዙ የኦሮሞ ብሔርተኞች መንግሥት ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል። ዶ/ር አብይ አህመድ ከእነዚህ በብሔር ከሚያስቡ ሰዎች በላይ ከፍ ብሎ የሚበር ስልጡን ሰው እንደሆነ በግሌ አስባለሁ። ስለኢትዮጵያ ታሪክ ያለው አመለካከትም ከብዙዎቹ የተለየና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ነው። አብይ እንደነ ታዬ ደንደዓ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አያላግጥም። በአላዋቂነት ድፍረትም ሆነ በስልጣን ግብዝነት የማያውቀውን ታሪክ ሲዘባርቅ ሰምቼው አላውቅም። አብይ ንባብ ከአላዋቂነት ድፍረት ነጻ ያወጣው ሰው ነው።
የኦሮሞ ብልፅግና ውስጥ እንደ አብይ አህመድ ንባብ ነጻ ያወጣቸው አርቀው የሚያዩ ስንት ሰዎች አሉ? ስለአንድ አብይ ብለን የኦሮሞ ብልፅግናን ሁሉ ይቅር እንበለው ወይስ ስለኦሮሞ ብልፅግና ብለን አንድ አብይ አህመድን እንርገመው የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ከባድ እየሆነ ነው።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።