ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) በትብብር ለመሥራት ስምምነት አደረገ

Home Forums Semonegna Stories የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) በትብብር ለመሥራት ስምምነት አደረገ

#13341
Semonegna
Keymaster

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) በትብብር ለመሥራት ስምምነት አደረገ

ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካን ሀገር ካምብሪጅ ከተማ ከሚገኘው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) ከተሰኘው ዕውቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።

ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡትን ውል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችላቸውን የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ማከናወንም ጀምረዋል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ሐብቴ ዱላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር የሚኖረው የትብብር ሥራ በዋናነት በኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የሚሰጡትን የትምህርት ፕሮግራሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የቤተ-ሙከራ ትምህርት ለማስደገፍ የሚያስችልና በመምህራንና በተማሪዎች የሚሠሩትን የምርምር ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

እንዲሁም የትብብር ሥራው የኮሌጁን የመማር-ማስተማር ሥራ ለማዘመንና ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን ለማስጠበቅ የሚያግዘው ከመሆኑም ባሻገር በምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶ/ር ሐብቴ አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኮርአብዛ ሸዋረጋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፥ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባው ውል መሠረት በያዝነው የ2012 የትምህርት ዘመን ከሁለተኛው መንፈቀ-ዓመት /ሴሚስተር/ ጀምሮ ዓመታዊ ክፍያው ከ160 ሺህ በላይ የሆነውን የኦንላይን ትምህርት በነጻ በመስጠት የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅን ተጠቃሚ ማድረግ ይጀምራል። ለዚህም ዕቅድ ተግባራዊነት ኢንሰቲትዩቱ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በዚህም መሠረት ድጋፍ ሰጪው ቡድን የኦንላይን ትምህርቱን ለመስጠት ወሳኝ የሆኑት የቤተ-ሙከራ ዕቃዎችን ይዞ በመምጣት ለዩኒቨርሲቲው በእርዳታ አበርክቷል። የተበረከቱት ዕቃዎች እስካሁን ድረስ በንድፈ-ሐሳብ /theory/ ብቻ ሲሰጡ የነበሩትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ /artificial intelligence/፣ ሮቦቲክስ /robotics/ እና ተዛማጅ የትምህርት ዓይነቶች የማስተማር ዘዴ በተግባር የታገዘ አንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አቶ ኮርአብዛ ገልጸዋል።

ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከታቸውን የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል ከኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅና ከኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለተውጣጡ 10 መምህራን ከጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ያዘጋጀውን በኮምፒዩተር ፕሮግራም ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

በመጨረሻም ዶ/ር ሐብቴ አክለውም፥ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመሥራት እንዲችሉ በማገናኘቱ ሥራ በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ እንደነበረ በመግለፅ ይህንን የዜግነት ግዴታቸውን ለተወጡት የዲያስፖራ አባላት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።

ምንጭ፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ