Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች › ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ፈፅመው በተገኙ 77 ተማሪዎች ተማሪዎች ላይ ዛሬ እርምጃ ወሰደ
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ፈፅመው በተገኙ 77 ተማሪዎች ተማሪዎች ላይ ዛሬ እርምጃ ወሰደ
ሐረማያ (ሰሞነኛ) – ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑት የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ችግሮች እንደጋጠማቸው ይታወቃል። በተለይ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለምንም ምክንያት ውድ የሆነው የሰው ሕይወት በሚያሳዝን ሁኔታ ጠፍቷል።
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ይህ እንዳይሆን ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ቅንጅት በማድረግ ሲሠራ በመቆየቱ የሰው ሕይወት ባያልፍም የጥፋት አላማን አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ግን ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲታወክ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ህልውናን ጭምር አደጋ ውስጥ በመክተት የጥፋት ተልዕኮአቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። እነዚህ ለጥፋት የተሰማሩ ተማሪዎች ከጥፋታቸው እንዲመለሱና እንዲታረሙ ተደጋጋሚ ምክርና ጊዜ የተሰጣቸው ቢሆንም ከጥፋታቸው ሊታረሙ አልቻሉም።
በመሆኑም የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማስቀጠል እንዲቻል በተለያዩ ጊዜያት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲስተጓጎል ምክንያት በሆኑ 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን ለእርምጃው መወሰድ ምክንያቶች በዋናነት የሚከተሉትን ያካትታል፦
- በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዳይኖር በተደራጀ ሁኔታ ሰላማዊ ተማሪ ላይ ጥቃት በማድረስ፣ ሕገ-ወጥ ሰልፍ በማደራጀት እና መማር ማስተማር እንዳይካሄድ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር፣
- በቡድን ተደራጅተው በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥቃት ማድረስ ፣ የማሸማቀቅ እና የማስፈራራት ተግባርን በመፈፀም፣
- በሕገ-ወጥ ሰልፍ በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ውድመት ማድረስ፥ ለምሳሌ፡- ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ተቋም 3 (ሦስት) ተሸከርካሪዎችን አውድመዋል፤ የባንክ ኤቲኤም (ATM) ማሽን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርገዋል፤ ዩኒቨርሲቲው ላይም ከፍተኛ ውድመት እንዲከሰት እሳት አቀጣጥለዋል።
- የብሔር ግጭት የሚቀሠቅሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ንግግሮችን በማጉላት በተማሪዎች መሀከል የስጋት ድባብ እንዲነግስ ማድረግ እና ብሔርን መሠረት አድርጎ ተማሪን በመከፋፈል ትምህርት አቋርጠው እንዲበተኑ ማድረግ ይጠቀሳል።
በዚሁ መሠረት ሰላማዊ ተማሪዎችን ሕይወት ለመጠበቅና ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስቀጠል ሲባል እርምጃ ከተወሰደባቸው አጥፊ ተማሪዎች መካከል 2 (ሁለቱ) ሙሉ ለሙሉ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን 75 ተማሪዎች ደግሞ ለ2 (ሁለት) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ ተወስኗል።
በተጨማሪም ሁለት መምህራን ተማሪዎችን በማስኮብለል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በመገኘታቸው በደመወዝ ቅጣትና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ዩኒቨርሲቲው ድብቅ ዓላማን አንግበው በተለያዩ ማደነጋገሪያ ሽፋኖች የሚንቀሣቀሱ እና ተቋሙ የጥፋት ዓላማዎች ማራመጃ ሜዳ እንዲሆን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚሠሩ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ በቀጣይ የማጣራት ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ እንደጥፋታቸው ደረጃ እና ጥልቀት ሕጋዊ እና ተቋሟዊ እርምጃ ለመውሰድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ እያሳወቅን፥ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው እና የሀገራቸው እና የዩኒቨርሲቲያቸው ሰላም የሚያሳስባቸው የአስተዳደር፣ ፀጥታ እና ማኅበረሰብ አካላት እንደተለመደው ከዩኒቨርሲቲው ጐን እንዲቆሙ በአክብሮት እንጠይቃለን። በተጨማሪም የተማሪ ቤተሰቦች ልጆቻችሁን በመምከር እንድታግዙን ዩኒቨርሲቲው ጠይቋል።
ምንጭ፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ