-
AuthorSearch Results
-
July 21, 2020 at 12:20 am #15134
In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveሂሩት ክፍሌ ማን ናቸው?
አዲስ አበባ (ኢዜማ) – ሂሩት ክፍሌ በ1967 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ነው የተወለዱት። ትውልዳችው ጎንደር ቢሆንም እድገታቸው ግን በአዲስ አበባ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ እቴጌ መነን የአሁኑ የካቲት 12 ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
ሂሩት የፖለቲካ ተሳትፎ አሀዱ ብለው የጀመሩት በአስራት ወልደየስ (ፕሮፌሰር) አማካኝነት በተመሠረተው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአህድ) መሥራች አባል በመሆን ነበር። ይህ የፖለቲካ ተሳፏቸው መአህድ ወደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከተለወጠ በኋላ የቀጠለ ሲሆን መኢአድ ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ጋር ከተጣመረ በኋላ በቅንጅት ውስጥም በአባልነት ተሳትፎ አድርገዋል። በ1998 ዓ.ም. የቅንጅቱ አመራሮች ወደ ወህኒ ሲጋዙ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ወደ ወህኒ ከወረዱት አባላት መካከል አንዷ የነበሩ ሲሆን ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ›› የሚል ክስ ቀርቦባቸው 18 ዓመት ተፈርዶባቸው ነበር። ሁለት ዓመት ለተጠጋ ጊዜ ከሌሎች የቅንጅት አመራር እና አባላት ጋር ከታሰሩ በኋላ ‹‹በምኅረት›› በሚል በ2000 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ዋዜማ ከእስር ተለቀው ነበር። ከቅንጅቱ እስር ከተለቀቁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ2003 ዓ.ም. በድጋሚ በእነ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ ‹‹በሽብር›› ተከሰው 19 ዓመታት ተፈርዶባቸው ነበር። በዚህ ክስ 6 ዓመታት ከታሰሩ በኋላም በ2009 ዓ.ም. ከእስር ‹‹በምኅረት›› ሊለቀቁ ችለው ነበር።
ሂሩት ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሲመሠረት መሥራች አባል ከመሆናቸውም በተጨማሪ የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ሂሩት ክፍሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ለውጥ እንዲመጣና አምባገነኑ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ከፌደራል መንግሥትነት ሥልጣኑ እንዲወገድ ከፍተኛ ዋጋ ከከፈሉ ዜጎች መካከል በግምባር ቀደምነት የሚነሱ ኢትዮጵያዊት ናቸው። እጅግ በጣም ጥቂት እንስቶች በሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍም የፅናት ምሳሌ የሆኑ ዜጋ ናቸው። በሥልጣን ላይ የነበረው የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝም ለሁለት ጊዜያት ያህል አስሯቸው በድምሩ ለ9 ዓመታት በፖለቲካ እስረኝነት አሳልፈዋል። ለውጥ መጣ በሚባልበት ጊዜም የበኩሌን አስተዋፅኦ ልወጣ በማለት ኢዜማን በመመሥረት ፓርቲውን በከፍተኛ ኃላፊነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
መረጃ ― የመሥራች አባል ሂሩት ክፍሌ መታሰር እና አሁን ያሉበት ሁኔታ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሥራ አስፈጻሚ አባል እና የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሂሩት ክፍሌ ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ተወስደው መታሰራቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ቀን ፖሊስ የፍርድቤት ማዘዣ በመያዝ መኖሪያ ቤታቸውን የፈተሸ ሲሆን ሦስት የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎች፣ ልጃቸው የሚገለገልበት ከሚሠራበት ድርጅት የተሰጠው ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና የቤተሰብ ዝግጅት የተቀዳበት የቪዲዮ ካሴት ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስዷል።
ሐምሌ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት የኢዜማ ጠበቃ ሂሩትን አግኝተው የተያዙበትን ሁኔታ እና የተጠረጠሩበት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል። ሐሙስ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ከጠበቃቸው ጋር የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ «ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት እንዲነሳ አስተባብረዋል» ብዬ ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሏል። ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀን ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ 10 ቀን ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ በቤተሰብ የመጎብኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር ሂሩት ያቀረቡትን አቤቱታ ተንተርሶ በቤተሰብ እንዲጎበኙ እንዲሁም አልባሳት እና ምግብ እንዲገባላቸው ለፖሊስ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ፖሊስ ትዕዛዙን እስከ አርብ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት ድረስ ሳያከብር የቆየ ቢሆንም ከአርብ ከሰዓት በኋላ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመቀበል ለሂሩት አልባሳት እና ምግብ እንዲገባላቸው ፈቅዷል።
ኢዜማ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ያሉት የሥራ አስፈጻሚ አባል ሂሩት ክፍሌ እና ሌሎችም ዜጎች በሕገ መንግሥት እውቅና የተሰጠው የሰብዓዊ እና የተያዙ ዜጎች መብቶቻቸው ምንም ሳይሸራረፍ እንዲከበርላቸው እና የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳሰቡ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ኢዜማ
July 15, 2020 at 3:06 pm #15093AnonymousInactiveየሕግ የበላይነትን ማስከበር እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሀገር ህልውና መሠረት ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ምግለጫበቅርቡ በልጃችን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ይህን ተከትሎ በሀገራችን በደረሰው የንፁሃን ዜጎች ሞትና የንብረት ውድመት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድጋሚ መፅናናትን እንመኛለን።
በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት ሁላችንም ሀዘን እና የልብ ስብራት ውስጥ እንዳለን፥ ግድያውን ተከትሎ የደረሰው የበርካታ ዜጎቻችን ሞትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ሀዘናችንን እጅግ መራር አድርጎታል። የአርቲስቱ ግድያ እና እሱን ተከትሎ በብዙ ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት እጅግ አሳሳቢ፣ አሳፋሪ እንዲሁም በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተወገዘ እና በሀገራችን በምንም ዓይነት ሊደገም የማይገባው ድርጊት ነው።
ኢትዮጵያውያን ከአምባገነናዊ አገዛዝ ነፃ ለመውጣትና የሚመጥነንን ሕዝባዊ አስተዳደር ለመትከል ረጅም ጊዜያትን በትግል አሳልፈናል፣ ብዙ ዋጋም ተከፍሏል። ዋጋ የተከፈለባቸው ሙከራዎች የከሸፉ ቢሆኑም በዚህ ሁሉ የታሪክ ውጣ ውረድ ግን የሀገር ህልውና በዚህ መልኩ ተፈትኖ አያውቅም።
ሀገራችን ከነችግሮቿ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያላት፣ የምናወሳቸው እና የምንዘክራቸው ዛሬ ላለው ትውልድ መኩሪያ እና መመኪያ የሆኑ የማንነታችን መገለጫዎች የሞሉባት ሀገር ናት። በአንድ ወቅት አርቲስ ሃጫሉ እንደተናገረው ኢትዮጵያችን በብዙ የማንነት ቀለማት ኅብር የተዋበች ሀገር ናት። ኢትዮጵያዊነታችን በልዩነት ውስጥ የተጋመደ አንድነት መሆኑ ሃቅ ሆኖ እያለ የዘውግ ማንነት እና የቋንቋ ልዩነቶችን እየመዘዙ በሀገር አንድነት ላይ አደጋ መጣል ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንደሚከተን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ግልፅ ሆኗል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት አስርተ ዓመታት በተለይም በሕወሃት/ኢህአዴግ ከፋፋይ አገዛዝ ስር ያሳለፈችው የፖለቲካ ትርክት ምን ያህል አደገኛ እንደነበር በግልፅ አይተናል። የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ምንም እንኳን ያረጀና በሕዝብ ትግል የተሸነፈ ቢሆንም፤ የተከላቸው መርዘኛ ቅራኔዎች በአጭር ጊዜ የሚነቀሉ አልሆኑም። እያየን ያለነው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ እና በረጅም ጊዜ ድካም የተገነቡ ሀብቶች ውድመት የዚሁ አገዛዝ ቅሪቶች እንጂ የኢትዮጵያዊያን እሴቶች አለመሆናቸውን እንገነዘባለን።
በሰሞነኛው ብጥብጥ የደረሰው የበርካታ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እጅግ አስከፊና የትውልዱ ማፈሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ በዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መቀመቅ እየወሰደን እንደሆነ ሕዝብና መንግሥት ከበቂ በላይ ትምህርት አግኝተዋል ብለን እናምናለን። በኢዜማ እምነት እውነተኛ ፌዴራሊዝም ሁሉም ራሱን በራሱ የማስተዳደር እና በመረጠው የመተዳደር መብት እንደሆነ እያስረገጥን ፖለቲካችን ከዘውግ እና ከሃይማኖት ካልተላቀቀ በስተቀር መጨረሻችን እጅግ አደገኛ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ነበር። በዘውግ እና በሃይማኖት ልዩነት ላይ የተንጠለጠለ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መጠፋፋት እየወሰደን መሆኑን በመገንዝብ በማስተዋል እና በመረጋጋት እንድንጓዝ፤ በአንድ ሀገር ለውጥን ማዋለድ ብዙ ትግልና መስዋትነትን የሚጠይቅ እንደዚሁም ከፍተኛ ትዕግስትና ማስተዋል የሚሻ መሆኑን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ብንቆይም ይህ አቋማችን ባንዳንድ ወገኖች እንደመለሳለስ ሲቆጠር ቆይቷል።
ሰሞኑን በተከሰተው ቅስም-ሰባሪ ጥፋት በሀገራችን ፖለቲካ የሚከተሉትን አበይት ነጥቦች በተለየ እንድንታዘብ አስገድዶናል። እነዚህም፦
- በድንገት የሚፈጠር ነውጥ ሀገራችንን ከማትወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል፣
- በዘውግ እና በሃይማኖት ላይ የሚሰበክ የፖለቲካ ትርክት፤ ከዚህ ትርክት ተነስቶ የሚቆሠቆሰው ፍጹም ስሜታዊ ጥላቻ እና ጥላቻው የሚቀሰቅሰው የደቦ እንቅስቃሴ፤ የሰውን ልጅ ከሰብዓዊነት ማማ አውርዶ ወደ አውሬነት ሊቀይረው እንደሚችል ተገንዝበናል። በሌላ መልኩ ደግሞ በዚህ ዓይነት ፍጹም ስሜታዊ ሁኔታም ውስጥ ብሔራቸውን እና ሃይማኖታቸውን ተሻግረው፤ ለሰብዓዊነት እና ለጋራ ህልውናችን ዘብ ቆመው፤ በሁከቱ ምክንያት ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን በመሸሸግ እና በማስጠለል የንፁሀንን ነፍስ የታደጉ የምንኮራባቸው ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን፣ ይህንን የመሰለው ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያዊያን እሴት ቢፈተንም በዚህ ዘመንም መቀጠሉን፣
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር እንደገለፁት፥ ችግር ፈጣሪዎች በመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ጭምር መሆናቸውን፤
- ችግሩ በተከሰተበት ጊዜ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች ሕይወት በአደባባይ ሲቀጠፍ፣ የሀገር ሃብት ሲወድም አይተው እንዳላዩ የማለፍ ሁኔታ እንደነበር፤ የዚያኑ ያክል ደግሞ የሕግና የሞራል ኃላፊነታችውን በመወጣት እየሞቱና እየቆሰሉ ማኅበረሰቡን ከጥቃት የተከላከሉ ብዙ የጸጥታ ኃይሎችን ያየንበት መሆኑ፣
- በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ በወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ውድቀት ማግስት የፀጥታ ኃይሎች ባልተደራጁበት እና ከፍተኛ የመንግሥት አስተዳደር ክፍተት በነበረበት ወቅት ነዋሪው ለሰላምና መረጋጋት አኩሪ አሰተዋፅኦ እንዳበረከተ ሁሉ፥ ዛሬም ሕዝባችን በመኖሪያ ቀዬው ራሱን በማደራጀት ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ንብረቱን እና አካባቢውን ለመጠበቅ ያሳየው ቁርጠኝነት እጅግ የሚመሰገን ተግባር ሆኖ ጎልቶ መታየቱ፤
ከሰኔ 22 በኋላ በጉልህ የታዘብናቸው ክስተቶች ነበሩ።
በቅርቡ የተከሰተው እና የሀገርን አንድነት የተፈታተነው አውዳሚ ክስተት ለጊዜውም ቢሆን መክሸፉ ችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ አግኝቷል ማለት አይደለም። የሀገራችንን አንድነት የሚፈታተኑ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እንደ ተፎካካሪ ድርጅቶችም ሆነ እንደ ዜጎች ያለብን ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማወቅና በተግባር ለማሳየት መዘጋጀት ይጠበቅብናል። የሀገርን አንድነት እና ሰላም ባጭር ጊዜ፤ ለዘላቂው ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ምሥረታ፤ ከምሩ የቆመ መንግሥት እስካለን ድረስ (በተለያዩ የፖለቲካ እና የፖሊሲ አመለካከት የምናምን የፖለቲካ ድርጅቶችና ዜጎች ብንሆንም እንኳን) ይህን ማዕከላዊ መንግሥት ለማዳከም፤ በዚህም የተለያዩ የጦር አበጋዞች የሚርመሰመሱበት የእርስበርስ ግጭት ውስጥ ሊዳርጉን የሚፈልጉ ኃይሎች የሚያደርጉትን ዘመቻ በማስቆም በኩል ሙሉ ትብብር ማድረግ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል። በእነኝህ አንኳር ጉዳዮች ላይ የምንስማማ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት እና አባላት ለሀገራችን መኖር እና ለሕዝቧ ሰላም ባንድነት በተግባር መቆም እንደሚኖርብን መገንዘብ ያለብን ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ኢዜማ በሀገር አንድነትና በማኅበረሰባችን ሰላም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር መኖር የለበትም ብሎ ያምናል። እነኝህን ሁለት መሠረታዊ እሴቶች በዋናነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ደግሞ ሀገራዊ መንግሥቱ ነው። ያለ ሀገር ፖለቲካም ሆነ ዴሞክራሲ ትርጉም የላቸውም። ለዘላቂው የሀገር አንድነት እና ሰላም ከዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መኖር፤ ከፍትህ መኖር፤ ከዜጎች እኩልነት መረጋገጥ ወዘተ… ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን እናምናለን። ስለሆነም ሁሉም የሀገራችን ዜጎች ይህን ፈታኝ ጊዜ በትግስት፣ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንዲሻገሩት እና የሀገራችንን አንድነት እና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም ያለብንን ኃላፊነትና ድርሻ የመወጣት ግዴታ እንዳለብን በማሰብ ኢዜማ በሚከተሉት ወሳኝ ነጠቦች ላይ በድርጅታችን መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፤
- የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጥረት በመሆኑ በተለይም ፈታኝ ጊዜያትን ያሳለፈው፣ ከፍጥረታት ልቆ የቆየው እና ተፈጥሮን ገርቶ ትውልድን ማስቀጠል የቻለው በተለያዩ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አቅም ፈጥሮ በመተጋገዝ ነው። በአደረጃጀቱ አያሌ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ተቋቁሞ አሳልፏል፤ ከእነዚህም አደረጃጀቶች መካከል «መንግሥት» ትልቁ የሰው ልጅ አደረጃጀት ሲሆን በውስጡ በርካታ አደረጃጀቶችን እንደያዘ ግልፅ ነው።
የእነዚህ አደረጃጀቶች ዋና መሠረት ደግሞ የቆየው ማኅበራዊ አደረጃጀት ነው። በሀገራችንም በርካታ የቆዩ የአደረጃጀት ዓይነቶች አሉ። ይህንን ማጠናከር የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በእጅጉ ይረዳል የሚል እምነት አለን። ማኅበራዊ ፍትህ በነገሰባቸው በርካታ ሀገራት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነፃ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አሉ። እኛም ሀገር ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ሕዝቡ በየመኖሪያ ቀዬው ተደራጅቶ ሰላሙን ሲያስከብር ተመልክተናል። በተለይም በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ ከተሞች የታየው አደረጃጀት ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ሁሉንም የሀገራችንን ማኅበረሰቦች አቅፋ የምትኖር፤ በዓለማችን በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የዲፕሎማቲክ ከተሞች አንዷ እንደመሆንዋ በውስጧ ያቀፈቻቸው ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባትና ልዩልዩ አስተሳሰቦችና እምነቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት። ይህን መሰሉ ማኅበራዊ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን። ይሁን እንጂ ሰሞነኛው ክስተት እንደሀገር ለከፍተኛ ውርደት የዳረገን የታሪካችን ማፈሪያ ሆኖ አልፏል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሕዝብ ዘመኑን በሚመጥን እና በሠለጠነ መንገድ በዘውግ ማንነት፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳያደርግ በመደራጅት ቤተሰቡን እና አካባቢውን ከጥፋት ከመከላከሉም ባሻገር ከተማዋን እጅግ ከከፋ ውድመት ታድጓታል። ለዚህም አክብሮት እና ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።
ይህን ዓይነቱ መሰባሰብ ለወቅታዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆን ለዘላቂውም ጭምር ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ የማኅበረሰቡ የቆዩ አደረጃጀቶች እንዲበረታቱ መሥራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር አሁን እየታዩ ያሉ አደረጃጀቶችን በየአካባቢው በሕዝብ በሚመረጡ አካላት ማጠናከር፣ እውቅና መስጠት እና የፀጥታ ጉዳይን በሚመለከት አደራጃጀቶቹን ከማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ እና የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር የማጣመሩን ተግባር መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። አደረጃጀቶቹ የጋራ ደኅንነትን ከመጠበቅ በተጨማሪ የከተማዋ ምልክት የሆነውን ሁሉም ዓይነት ማንነቶች ተከብረውባት፣ ዜጎች ተጋግዘው እና ተባብረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን በቀጣይነት ለማረጋገጥም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አደራ እንላለን።
እነዚህ አደረጃጀቶች በሌሎች ኃይሎች እንዳይጠለፉ እና ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ደኅንነታቸውን ከመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እንዲያስጠብቁ ከማስቻል ያፈነገጠ ዓላማ ማስፈፀሚያ መሣሪያ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባም ልናሳስብ እንወዳለን።
- የደኅንነት እና የፀጥታ ተቋማት ዋና ተግባር የሀገርን ደኅንነት እና የሕዝብን ሰላም ማስጠበቅ ነው። ሰሞኑን ሀገራችን በገባችበት ችግር ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩ የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎች ችግሩ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ የዘገዩት በሆደ-ሰፊነት የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት መንግሥት በያዘው አቋም ምክንያት መሆኑን ሲገልፁ ሰምተናል። ይህ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን የዘነጋ አካሄድ እና አገላለፅ በቶሎ ሊታረም ይገባል። የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ለከፋ አደጋ ዳርጎ ሆደ-ሰፊነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መነገር የለበትም። ይህንን የማድረግ መብትም ሆነ የሕግ ድጋፍም የላቸውም። የፀጥታ ተቋማት በየደረጃው ተቀናጅተው በመሥራት እና ሀገርን እና ዜጎችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጥቃት መታደግ ነው ዋና ተልዕኳቸው። በተለይም በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ሕዝብን በማስተባበር አደጋ ከመድረሱ ቀድሞ የማክሸፍ ሥራ በመሥራት፤ አንዴ ከተፈጠረ ደግሞ በፍጹም ቁርጠኝነት ሀገርን እና ሰላማዊ ሕዝብን ከጥቃት መከላከል የፀጥታ አካላት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር እንደሆነ በአንክሮ እንገልፃለን።
- ለዘመናት የታገልንለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሀገርን እና ሕዝብን ለአደጋ እስከሚያጋልጥ ልቅነት ድረስ መሆን እንደሌለበት ደጋግመን ስንገልጽ ቆይተናል። አሁን እንደምናየው የግል የብዙሃን መገናኛዎች የተወሰኑት በፓርቲ ልሳንነት፣ የተወሰኑት ደግሞ በጥቅም አሳዳጅነት ሀገርን እና ዜጎችን አደጋ ላይ ሲጥሉ ሥልጣን የተሰጠው አካል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ አለበትም። ከዚህ አንፃር የግል ብዙሃን መገናኛዎች የሀገሪቱን ሕግና የሙያውን ሥነ-ምግባር ጠብቅው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን። በሌላ በኩል የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ በተለይም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቃለመጠይቆችን ብቻ በማስተናገድ መሪ አዘጋገብ እና ፍረጃ ውስጥ መግባታቸው የዜጎችን በፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ እንደነፃ የመታየት መብት የሚጋፋ እና የፍትህ ተቋማቱን አካሄድ የሚያዛባ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲያርሙት እናሳስባለን። የመገናኛ ብዙሃን እንዲመሠረት የምንፈልገውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርህ የተከተሉ፣ የሕዝብ መረጃ ማሳወቂያ፣ ማስተማሪያ እና ማረጋጊያ መሆን እንሚገባቸውም በአፅንዖት እንገልፃለን። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የብዙሃን መገናኛ ተቋማትን በቅርበት እየተከታተለ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድም አበክረን እናሳስባለን።
- የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ለዘላቂ ሀገራዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን እናምናለን። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመሠረተውም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማለትም በእውነተኛ ውይይትና ድርድር ብቻ ነው።
ይህንን ለማድረግም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘመናዊ፣ የሠለጠነ ፖለቲካ እና የጨዋታ ሜዳውን ሕግ ያከበረ አካሄድ መከተል ይገባናል። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደምም ሆነ ሰሞኑን የተከሰተው የመገዳደልና የመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ የሚወስደን ሳይሆን ከዚህ ቀደም ዋጋ ወደከፍልንባቸው የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ መልሶ የሚዘፍቀን አካሄድ ነው። በዚህ ረገድ የሁሉም ድርሻ አስፈላጊ ቢሆንም በሀገር አንድነት፣ በሰላማዊ እና በሠለጠነ የፖለቲካ ትግል እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግርን ከሚያምኑ ወገኖች ጋር ለሚደረግ ውይይት ገዢው ፓርቲ ወሳኝ ድርሻ አለው። በአንድ በኩል የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቁን አጠናክሮ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችል እና ለሁሉም ተሰፋ የሚሰጥ የባለድርሻዎች ውይይት ሳይውል ሳያድር እንዲጀመር እንጠይቃለን።
- የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት በአጠቃላይ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ በተለይ ደግሞ እንደኛ ሀገር ፖለቲካችንን ሰቅዞ ከያዘው የዘውግ ፖለቲካ ወደ ጤናማ የሀሳብ ፖለቲካ በማሸጋገር እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖራቸው ሚና እጅግ የጎላ እና ሚዛንን ማስጠበቅ የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል። ባለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሙያ ማኅበራት በገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ስር የወደቁ እና ተዳክመው የቆዩ መሆናቸውን እንረዳለን።
ረጅም ጊዜ ከቆየ አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር ውስጥ ለረጅም ጊዜ የተጠራቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሁሉ በቶሎ እንዲፈቱ መጓጓት እና ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን የሚያቀርቡበት እና እንዲመለስላቸው ጫና ለማሳደር ኃይልን የቀላቀለ መንገድ መከተላቸው ትልቅ ተግዳሮት ይፈጥራል። የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት ራሳቸውን ከነበረባቸው ጭቆና ነፃ አውጥተው እና ተጠናክረው የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እና ተደራሽ የሆኑ ብዙሃን መገናኛዎችን በመጠቀም ስለ ሰላማዊ ተቃውሞን የማሰሚያና ጫና የማሳደሪያ መንገዶች በሰፊው በማስተማር ከሕዝብና ከእውነት ጎን ቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር መረጋጋት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን።
- በሀገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ ፖለቲካዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ከተነሱ ረብሻዎች ጋር በተያያዘ በርካታ የንፁሃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ሲቀጠፍ እና የግል ባለሃብቶችም ንብረት በሚያሳዝን ሁኔታ ሲወድም እየተመለከትን ነው። እነዚህ ረብሻዎች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም የሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ እንዳያደርሱ መቆጣጠር እና የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ዋነኛ የመንግሥት ሥራ በመሆኑ፣ መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን በሚገባ ሳይወጣ ቀርቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ ወጥቶ ይቅርታ መጠየቅ እና ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ጥፋት በፍፁም እንደማይደገም ቃል ሊገባ እና ሊያረጋግጥ ይገባዋል።
መንግሥት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ጉዳይ ባስቸኳይ አጣርቶ ፍትህ እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባል። እንደዚሁም የሀገራችን ኢኮኖሚ ዳዴ በሚልበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ባለሀብቶች አንጡራ ሃብታቸውን አፍስሰው የገነቧቸው መሠረተ ልማቶች እንደዘበት ወድመው፣ ተቃጥለው እና ሠራተኞች ተበትነው ማየቱ እጅግ ያሳዝናል። በቀጣይም ሃብታቸውን አፍስስው ሊያለሙ የሚችሉ ባለሃበቶችም ዋስትና ስለማይኖራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ከማፍሰስ ይታቀባሉ። ከዚህ አንፃር በሰሞኑ ክስተት ቤት ንብረታቸውና ትልልቅ የንግድ ተቋሞቻቸው ለወደመባቸው ዜጎች መንግሥት ተገቢውን ካሳ ከፍሎ እንዲያቋቁማቸው አበክረን እንጠይቃለን።
በመጨረሻም አሁን ያለንበት ሁኔታ ለሀገራችን እጅግ ፈታኝ መሆኑ ግልፅ ነው። ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ከዕለት ዕለት እየተስፋፋ መጥቷል። ከአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም በተለይም ከህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብፅ የፈጠረችው እሰጥአገባ ያመጣው ጫና ከሀገራችን አልፎ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መነጋገሪያ ሆኗል። ኢትዮጵያውያንም በእነዚህ አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምንግዜውም በላይ በጋራ መቆም የሚገባን ትክክለኛው ሰዓት ላይ እንገኛለን።
በመሆኑም የውስጥ ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ ፖለቲካ አሰታርቀን እንደሀገር የተደቀኑብንን ተደራራቢ ፈተናችዎች በፅናት ማለፍ ካልቻልን ለትውልድ የምትሆን ሀገር ማሻገር ይቅርና እኛ ራሳችን ከማንወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ገብተን እንደምንዳክር መረዳት ይኖርብናል። ስለሆነም የሕግ የበላይነትን በማክበር፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት በመተባበር እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አሁን ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን ሀገራችንን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ እንድናሻግር ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ሐምሌ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.June 3, 2020 at 1:57 am #14685AnonymousInactiveየህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሰጠውን መግለጫ በተመለከተ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ሕዝባዊነት እና ዲሞክራሲያዊነት ከማያውቀው የህወሓት ገዢ መደብ፣ የተጎሰመው የሁከትና ብጥብጥ አቋቁሙኝ ነጋሪት መግለጫ ሰምና ወርቅ።
የህወሓት ጥገኛ ገዢ መደብ የሰሞኑ መግለጫ ሰሙ በሕዝባዊነት፣ ሕጋዊነት፣ ሰላማዊነት፣ የዲሞክራሲያዊነትና የሀገራዊ አንድነት የተለበጠ አዛኝ ቅቤ አንጋችነት ባዶ ጩኸት ነው፤ ወርቁ ደግሞ በሴረኝነት፣ በቡድነኝነት፣ በሀገር ጠልነት እና በኢ-ዲሞክራሲያዊነት ሁሉን ፍጥረት በሚያስማማ ሕዝባዊ ቅቡልነት እጦት የተንሳፈፈን ኃይል በማንኛውም ኢ-ሰላማዊ መንገድ በመጠቀም የመተንፈሻ ድጋፍ በመስጠት ለመመለስ ያለመ የስሌት ችግር የሚስተዋልበት ኢ-ሞራላዊ የሁከት አታሞ ነው።
የህወሓት የጥገኛ ገዢ መደብና ከተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች የተሰባሰቡ የኩርፍያ አድመኞች በቀድሞ የኢህአዴግ አወቃቀር በተለያዩ ግዜያት በተደረጉ ግምገማዎች የሥርዓትና የሀገር አደጋዎችን በመለየት ለማስወገድ በተዘጋጁ መድረኮች ሲናዘዙ ቆይተዋል።
እንደ ኮሮና ቫይረስ ባሉ በማያከራክሩ ህልው ዓለማዊ፣ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎች ውስጥም ሆነን ጭምር ግላዊ ፍላጎቶቻቸው ሕዝብ ላይ ለመጫን እየሄዱበት ያለው አቅጣጫና ርቀት አሁንም አነጋጋሪና ዳግም የስህተት ታሪክ ሀወልትና ማፈርያ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
ይህ ለእኔ ስለኔ እና የእኔ ብቻ የሆነ የገዢ መደብ በሕዝባዊነት በዲሞክራሲያዊነትና በቀናኢ የኢትዮጵያዊ አንድነትም የማያምን መሆኑን አንዳንድ አባላቱ በድፍረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በቀረቡበት ሚድያዎች ሁሉ ለሕዝብና ሕዝባዊነት ያላቸውን ቅጥ ያጣ ንቀት በገዛ አፋቸው ያለህፍረት መስክረዋል።
አስተዋይና አርቆ አሳቢ የሆንከው መላው የሀገራችን ሕዝብ ሆይ፤ በዲሞክራሲ ስም እየማለ እና እየተገዘተ፣ ዲሞክራሲ ማዕከላዊነት በሚል ማሞኛ ፈሊጥ ለዓመታት እራስን በራስ ለማስተዳደርና ለሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበብና መበልፀግ እንቅፋት ሆኖ፣ በምስለኔዎች የሞግዚትነት አሠራር የሀገራችን የፖለቲካ እድገት አቀጭጮ፣ በመጠላለፍ ሴራና በመከፋፈል ላይ የመሠረተውን ይህን የገዢ መደብ የጥፋት ሃሳብ በጥብቅ በማውገዝ ሰላምና አንድነትህን በንቃት በመጠበቅ እንድትታገለው ታሪካዊ ጥሪ ይድረስህ።
በተለይም መላው የትግራይ ሕዝብ፥ አርሶ አደሩ፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች፣ ምሁራን፣ ነጋዴዎች፣ ነባር ታጋዮችና ለፍትህና ለነፃነት አካላችሁን ያጎደላቹ ሀቀኛ የሕዝብ ልጆች፣ ወጣቶች፥
- በሀገረ ኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ምሥረታ የትግራይ ሕዝብ ያለውን ጉልህ ታሪክና ጅግንነት ከካዱና ካሳነሱ፤
- ላለፉት 29 ዓመታት የትግራይ ሕዝብ የታገለለትን አላማ ረስተው ለግልና ቡድናዊ ጥቅማቸው ካደሩ፤
- ሕዝባዊ የልማት ተጠቃሚነትን በቡድናዊ ጥቅም ለውጠው በገዛ መሬትህና ሀገርህ ለዘመናዊ ባርነት የሽጥሁን፤
- በኢትዮጵያዊ አንድነትህ የማትደራደረውንና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ጋር በሰላምና በመተሳሰብ ለዘመናት መኖርህ እንቅልፍ ነስቷቸው ሌት ተቀን የሚያሴሩብህን፤
- “በምድር ላይ ያለ የፖለቲካ ኃይል እኔ ነኝ” በሚል ያነሰ አስተሳሰብ፣ በሺዎች ዓመታት የሚቆጠረውን ጅግንነትህን እና ታሪክህን ወደ አርባዎች አውርደው “ከኛ በላይ ለአሳር” የሚመስለውን ትምክህታዊና ሸውራራ የታሪክ ትርክታቸውን ‘በንቀት ለመጋት ከሚሞክሩ የዘመኑ አዋቂ ነን ባይ አላዋቂዎች፤
- ለዓመታት በስልጣን ዘመናቸው በከተማ ሲንደላቀቁ፣ በመላው የትግራይ ገጠሮችና ከተሞች የንፁህ ውሃ እጦት እሮሮህ ለመስማትና ለመመለስ ጀሮ ዳባ ልበስ ካሉ፤
- ከምንም በላይ የጥይት ባሩድ ለሰለቸህ፣ የጦርነት ኪሳራውን በተግባር በማወቅህ አጥብቀህ ሰላም ናፋቂና ፈላጊ መሆንህ የጎረበጣቸው፤
እነዚህ የገዢ መደብ አለቆች ጠንቀኝነታቸውንና ተዘርዝሮ የማያልቀውን ጥፋታቸውን በጊዜው በመገንዘብ፥ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆነህ በድጋሚ እንቢተኝነትህን እንድታሳይና በሰላማዊ መንገድ ታግለህ ታሪክህን በድምቀት እንድታድስ ልዩ ጥሪ እናቀርብልሀለን።
ለሕጋዊ፣ ሰላማዊ እና አስተዋይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች፥ በፖለቲካዊ አመለካክታችሁና አቋማቹ የቱንም ያህል ብትቃረኑ፣ ሕዝባዊነት፣ ሕጋዊነት እና ሰላማዊነትን ተላብሳችሁ የሚጠብቅባችሁን ታሪካዊ ድርሻ እንድታዋጡ አደራችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን።
እንግዲህ “ከክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ አይጠበቅምና” መልዕክትና መልዕክተኛው የተቃረኑበትን ሰሞነኛ መግለጫው፣ ብሩህና አስተዋይ ለሆነው ሕዝባችን ሰምና ወርቁን እንደሚገነዘበው የሚያምነው የብልፅግና ፓርቲ፣ በየትኛውም ደረጃ ሕዝባዊ ተሳትፎን በመተማመን ከፊቱ የተጋረጠበትን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልን ቀዳሚ ትኩረቱ በማድረግ፣ ሕዝቡ ራሱንና ወገኑን እንዲጠብቅ በአፅንኦት ይገለፅፃል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
የትግራይ ብልፅግና ፓርቲJune 1, 2020 at 1:31 am #14664AnonymousInactiveየህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከግንቦት 15 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው በፍጥነት እየተለዋወጠ ያለው የዓለም፣ የአካባቢያችንና የሀገራችን ሁኔታ ጨምሮ የክልላችን ሰላምና ደኅንነት፣ የኮረና ቫይረስ በሽታ ስጋትና የመከላከል ሥራ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት፣ የድርጅትና የመንግሥት ሥራ አፈፃፀም እንዲሁም በአስተዳደር በኩል እየመጡ ያሉት ለውጦች አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አካሂዷል።
ኮሮና ቫይረስን ወይም ኮቪድ-19ን ተከተሎ እየመጣ ያለውን አዲስ ዓለማዊ ሁኔታ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር አስፈላጊነትንና ትክክለኛነትን የሚያረጋግጥ ነው። ቀድመውንም ቢሆን የመንግሥት ስልጣን ሽግግርን ለብቻ ተቆጣጥረህ ጠባብ ጥቅምህን ለማርካት፣ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለአፍታ እንኳን ግድ የሌለው ጥገኛ የብልፅግና ቡድን በተፈጠረው አዲስ ዓለማዊ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ራሱን አስተካክሎ በሕዝባዊ ትግልና በሕዝብ ልጆች መስዋእትነት በግንቦት 20 የተመዘገቡ አስደናቂ የዴሞክራሲና የልማት ድሎች አጠናክሮ ከማስቀጠል ይልቅ የጥፋት መንገድ አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
በጊዜያዊ ጥቅም ወይም በጥላቻ የዚህ ሥርዓት መጠቀሚያ በመሆን ሙያቸውንና ስብዕናቸውን አሳልፈው የሰጡ አካላት ከፊት በማሰለፍ በግላጭ ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ስልጣን ላይ እንደሚቆይ ይፋ ያደረገው የብልፅግና ቡድን ለማስመስል እንኳን ውሳኔ ይሰጣሉ የተባሉትን ተቋሞች የሚሉትን እስከምንሰማ ድረስ እንኳን ሊታገስ አልቻለም። በእንደነዚህ ዓይነት ወደ ጥፋት የሚምዘገዘገው የብልፅግና ቡድን የሚያስተዳድረው መንግሥት ባላት ሀገር ሆነን መሠረታዊ ዓላማችንንና ልማታችንን ለማሳካትም ሆነ የገጠመንን የኮሮና ቫይረስ ፈተና ለመመከት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሁሉም ሊገምተው የሚችል ነው።
የ‘ብልፅግና’ ቡድን ሉዓላዊነትና መሠረታዊ የሚባሉ የሀገር ጥቅሞች ለሽያጭ በማቅረብ፣ ሕገ መንግሥትንና ሥርዓትን እንዲሁም ሁሉም ዓይነት ከፊቱ ላይ የቆሙትን ሕጎችንንና ተገቢ የመንግሥት አሠራሮችን በመጣስ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከመወሰን አልፎ ሥርዓትንና ሕግን አክብረው በሄዱት አካላት ላይ ይፋዊ ጦርነት ወደ ማወጅ ተሸጋግሮ ይገኛል። የዚህ ቡድን ፉከራዎችና ሴራዎች በአካሄዳችን ላይ ይሁን በሕዝባዊ ትግላችን ተጨማሪ ቁጭትና ወኔ ከመፍጠር አልፈው ሌላ ፋይዳ ያላቸው እንዳልሆኑ ግልፅ ቢሆንም ለጠባብ ፍላጎት ሲባል የሀገርና የመላ ሕዝቦች ጥቅም ወደ ገደል ገፍትሮ ለመጣል ‘ብልፅግና’ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ ሆኗል።
ይሁን እንጂ ወትሮም ቢሆን ህልውናውንና ጥቅሙን በጠንካራ ክንዱና በትክክለኛ አስተሳሰቡ የተመሠረተ መሆኑን፤ ታሪኩንና ትግሉን በተጨባጭ አሳምሮ የሚያውቅ ሕዝባችን፤ የጥገኞች ቀጣይ በርካታ ጥቃቶችን ተቋቁሞና የመመከት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠናል። ድርጅታችን ህወሓት ሕዝባችን እያካሄደ ላለውን ፍንክች የማይል ቀጣይነት ያለው ትግል ከፍተኛ ክብርና አድናቆቱን ይገልፃል። ወደፊትም ሁኔታዎች በጥብቅ እየገመገምን የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች በንቃት እንደሚከታተልና እንደሚፈፅም የትናንትም የዛሬም ታሪካችን ምስክር ነው። እያካሄድን ያለነው የተፋፋመ ትግል በሁሉም የሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ አውዶች ተስፋ የሚያሰንቁና ለቀጣይ ድሎችም አመቺ ቦታ የሚፈጥሩ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም ሕዝባችንን ያላረካንባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ አሳምረን የምንረዳው እውነታ ነው።
ከሕዝባችንና ከመሪ ድርጅታችን ፊት ለፊት መግጠም ከብረት ጋር መጋጨት የሆነባቸው ጥገኛ ቡድንና ተከታዮቹ በዋነኛነት በተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ የታገዘ ግልፅ ውሸት በመመሥረትና ባንዳዎችን በማዝመት ውስጣዊ ሰላማቻንን በማደፍረስና ልማታችንን በማደናቀፍ ወደ ድቅድቅ ጭለማ ሊያስገቡን እየሠሩ መሆናቸውን ሁሉም በተለይ ደግሞ ሕዝባችን የሚገነዘበው ጉዳይ ነው።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ሆነን በአንድ እጃችን ሁለገብ የመመከት ሥራዎቻችን እያጎለበትን በሌላም በኩል ፈጣን የልማትና የመልካም አስተዳደር ማስፈን፣ ሕዝባችንንና መላ መዋቅራችንን እንዲሁም የሰላምና የልማት ወዳጅ የሆነ ኃይል ሁሉ ሊረባረብላቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው በማረጋገጥ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው ያሳለፋቸው ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን በማጽደቅና መሠረት በማድረግ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አሳልፏል።
- የኮሮና ቫይረስ መከላከል ሥራ ከዚህ በፊት ሲደረግ እንደቆየው አዲስ ለውጦች፣ ተጨባጭ የክልላችን ሁኔታ እንዲሁም ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ ሕዝባችንን ለማዳን እየተከላከልን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በሚቀንስ መልኩ እየተገመገመ በጥብቅ እንዲመራ ተወስኗል።
- የ‘ብልፅግና’ ቡድን ከድሃ ጉሮሮ እና ልማት ቀምቶ ያልተቆጠበ ሃብት በማፍሰስ ሀገር ከጫፍ እስከ ጫፍ ለማበጣበጥ፣ በዶክሜንተሪ ፊልሞች የታገዘ ዘር የማጥፋት ጥሪ እንዲካሄድና ሁሉም መብቶች እንዲረጋገጡ እያደረገ ያለው ጭፍን ፀረ-ሕዝብና ስልጣንን በገንዘብ የመግዛት ተግባር እንዲቆም ብቻም ሳይሆን ከጥፋት መንገድ ወጥቶ በሕገ-መንግሥት መሠረት የሚመለከተው ወገን ሁሉ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እና ወደ ምክንያታዊ ውይይት እንዲገባ እንዲሁም ጨርሶ ሳይረፍድ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ከማፍረስ እንዲቆጠብ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሳስባል።
- ሙሉ ዝግጅትና የሕብረተሰቡን ጤና የመጠበቅ ሥራ በመሥራት በሕገ መንግሥት በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት ሁሉንም እኩል ማየት የሚችል ኃይል የሚመራው ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ዳግም ያሳስባል።
- ምርጫ በሀገር-አቀፍ ይሁን በክልል ደረጃ በሺዎች መስዋዕትነትና ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ያገኘ መብት እንጂ ገደብ የለሽ የስልጣን ጥማት ያለው ግልገል አምባገነን የሚሰጠው ወይም የሚከለክለው ችሮታ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ከድሮም ቢሆን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠ፣ በማንኛውንም ሁኔታ በራሱ ላይ ይሁን በሌሎች ሕዝቦች ላይ ባርነት እንዲነግስ የማይፈቅድ ሕዝብ ነው።
የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው መብት በማንኛውንም ጊዜ እና ሁኔታ ወደ ድርድር እንደማይቀርብና የዚህን መብት ተግባራዊነት ወደ ኋላ መመለስ የሚችል ማንኛውም ምድራዊ ፖለቲካዊ ኃይል እንደሌለ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስምሮበታል። ስለዚህም የፌደራል ስልጣን በአምባገነናዊ አኳኋን ተቆጣጥሮ ያለው ኃይል በተለመደው አካሄዱ የሕዝቦችን መብት እየደፈጠጠ መቀጠሉን አጠናክሮ እየገፋበት በመሆኑ ሕዝባችን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው እና የማንም ፈቃድ የማይጠይቅበት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም በክልላችን ምርጫ እንድደረግ እና ይህንን ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች በሕግ አገባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ወስኗል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በትግራይ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን በ‘ብልጽግና’ ጥገኛ ባህርይ ምክንያት የተጀመረው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የማፍረስና ሀገር የመበተን ሂደት ወደ መጨረሻ ምዕራፍ እየደረሰ መሆኑን ይገነዘባል። አሁንም ቢሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና እና ሕዝቦች የሀገራችንን ሕገ-መንግሥት ያጎናፀፋቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳያጡ ትግላቸው ማጠናከር እንደሚገባቸው ህወሓት ያምናል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን ተገንዝቦ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
- የ‘ብልፅግና’ ቡድን ምርጫ ላለማካሄድና የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም እየወሰዳቸው ካሉ ሕገ-ወጥ እርምጃዎችና ሴራዎች በተጨማሪ የድርጅታችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትግራይ ክልል ሕግና ሥርዓት እንደሚቀጥልና ‘ብልፅግና’ ምርጫ ለማስቀረት እየሠራ በመሆኑ በትግራይ ደረጃ በሕግ መሠረት ምርጫ ለማካሄድ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት የብልጽግና መሪ አሁንም መሠረታዊ የሕዝቦች ራስን በራስ የመወሰን መብት ክብር እንደሌለው በሚያሳይ መልኩ የጦርነት አዋጅ ይፋ አድርጓል። የትግራይ ሕዝብ በፉከራና የጦርነት ነጋሪት መጉሰም እንደማይደነግጥና መብቱን አሳልፎ እንደማይሰጥ የሚታወቅ ሃቅ ነው። ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ እንዲሁም የ‘ብልፅግና’ ቡድን እና መሪው የሚመጣ ማንኛውንም ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂዎች ራሳቸው መሆናቸው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ መገንዘብ ይገባቸዋል።
- በልማት ሥራዎች፣ የዴሞክራሲ ባህል እና አስተዳደር የተጀመሩ ለውጦች በጊዜ የለንም መንፈስ በበለጠ ፍጥነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በየደረጃው ያለው አመራር በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እንዲሠራው ተወስኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለ መላው ሕዝባችንና ሁሉም የመንግሥትና የድርጅት መዋቅሮች ለርካሽ ዓላማቸው ሲሉ ከልማትና የዴሞራሲ ግንባታ ሃዲድ አውጥተው ወደ ብጥብጥና ጥፋት ሊያስገቡን የሚረባረቡ ብልጽግና ኃይሎች፣ አይዞህ ባዮችና እና ተላላኪዎቹ ለመመከት የተጀመረውን ትግል እንዲጠናከር ተወስኗል።
- የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የሕዝባችን ደኅንነትና ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳዮች ላይ አብሮው ሊሠሩ ዝግጅ ከሆኑ የሀገራችንና የክልላችን የፖለቲካ ኃይሎች የተጀመረውን ዝምድና በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገርና ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ ወደሚችልበት የሕዝባችን ደኅንነትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሥራዎች እንዲገባ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስኗል። የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትንና መንግሥትን አስፈላጊነትና ቀጣይነት በአግባቡ ተረድታችሁ፣ ይህን ለማረጋገጥ የድርሻችሁ ሀገራዊ ግዴታ እንደምትወጡ እና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሰያችሁን አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያምናል።
የትግል ጥሪ፤
የተከበርክ የትግራይ ሕዝብ፥ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች ለመናድ ሕገወጡ የ’ብልፅግና’ ቡድን እየተከተለው ያለው የተቻኮለ አካሄድ እና የጦርነት አባዜ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በማካሄድ ለመመከት የትግራይ ሕዝብ በተለይ ደግሞ የትግራይ ወጣቶች የትግል ዝግጁነታቸውና አደረጃጀታቸውንእንዲያጠናክሩ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።
ኮሮና ቫይረስ በህልውናችን ላይ እና በጀመርነው የመመከት እንቅስቃሰያችን ለያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ በመረዳት፣ የባለሞያዎች ምክርና የመንግሥት መመሪያዎች በጥብቅ በመተግበር፣ ሕዝባችን ተገቢ ትኩረት በመስጠት እንዲመክተው ከከፍተኛ አደራ ጭምር ጥሪውን ያቀርባል። ህልውናችን፣ ሰላማችንና ልማታችን ለማረጋገጥ ደግሞ መላ ሕዝባችን የሚያጋጥሙትን ችግሮች ተሸክሞ፣ ምርቱና ምርታማነቱ ይበልጥ እንዲጠናክር በድጋሜ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የድርጅታችን ህወሓት አባላት፣ በየደረጃው ያላችሁ አመራሮች፥ አሁን ያለንበት መድረክ የሚጠይቀውን ፅናትና መስዋዕትነት በውል ተገንዝባችሁ፣ ሕዝባችን ለማዳን በሚደረገው ሁለንተናዊ ትግል ግንባር ቀደም ድርሻችሁ እንዲትወጡና አርአያነታችሁ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበራችሁ የክልላችን የሕዝብ ማኅበራትና ሲቪክ ተቋሞች፥ ዛሬም እንደትላንቱ ለሰላማችሁ፣ ለልማታችሁና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከእናንተ በላይ ሊቆረቆር የሚችል ኃይል እንደሌለ ተገንዝባችሁ በመመከት እንቅስቃሴ በጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ምርጫውን በድል እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት እንድቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፥ የአፈና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ጭቆናና የተለያዩ በደሎች እንዲሁም ሁለንተናዊ ችግሮች የጀመራችሁት ትግል አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለመሠረታዊ መብቶች፣ ፍትህና እኩልነት በምታደርጉት ትግል ህወሓት ዛሬም እንደትላንቱ ከጎናችሁ እንደሚቆም ያረጋግጣል።
የተከበራችሁ የሀገራችን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፥ ሕገ-መንግሥቱን ለመናድ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ሊያስከትለው የሚችል ሀገር የማፍረስና እልቂት በውል ተገንዝባችሁ፣ ይህ ተግባር እንዲቆም ታሪካዊ ኃላፊነታችሁ እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በሕገ-መንግሥት መሠረት የተዋቀራችሁ የሀገራችን የክልሎችና ተቋማት፥ ሕዝብ የሚያስቀድምና ሕገ-መንግሥቱን የሚያከብር መንገድ እንድትከተሉ እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በመናድ ላይ ከመሳተፍ እንድትቆጠቡ ጥሪያችን እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ በትግራይ ሕግ አክብራችሁ የምትንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አስተዋፅኦ ያላችሁ ኃይሎች፥ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በጥሞናና በዕውቀት በመመርመር የብልፅግና ቡድን የያዘው የጥፋት መንገድ እንዲቆም ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ፣ ከሕግና ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳችሁን እንድታድኑ ጥሪ እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የትግላችን አጋር፣ የጎረቤት ሀገሮች ሕዝቦች በተለይ የኤርትራ ሕዝብ፥ አሁንም እንደ ትላንቱ የጋራ ችግሮቻችን ለመፍታት ትግላችንና ትብብራችን እንድናስቀጥልና ይበልጥ እንድናጎለብት ጥሪ እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የዓለማቀፍ ተቋሞች በተለይ ደግሞ ኢጋድ (IGD)፥ አፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታችሁ አካላት፥ በኢትዮጵያ በለውጥ ስም እየተካሄደ ያለው ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የመናድና ሀገሪቱን የማፍረስ እንቅስቃሴ በጠራ መረጃ እና ዕውቀት እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ አወንታዊ ሚናችሁ እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖች ሰማዕታት!
ድልና ድምቀት ለ29ኛው የግንቦት 20 ድል በዓል!
አሁንም መስመራችን አጥብቀን እንመክት!
ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላይ ኮሚቴ
ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም.
መቐለMay 24, 2020 at 11:28 pm #14589AnonymousInactive“የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን በቃህ ሊለው ይገባል” አቶ ደረጀ በቀለ – የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን (ህዝበ ወያኔ ሃርነት ትግራይ) በቃህ ሊለው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር አስታወቁ። 45 ዓመታት የዘለቀው የህወሓት ትግል የጉዞ ምዕራፉ ወደመጠቃለሉ መቃረቡንም አመልክተዋል።
ሊቀመንበሩ አቶ ደረጀ በቀለ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፥ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የሚያደርገውን አካሄድ ተገንዝቧል፤ በቃህ ሊለው ይገባል። የትግራይ ወጣቶች፣ የትግራይ ምሁራን፣ በትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተው፣ ላለፉት 45 ዓመታት ያደረጋቸውን በማሰብ፤ የህወሓትን አመራሮች በቃችሁ ሊሏቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የትግራይ ወጣት የህወሓትን ወቅታዊ አካሄድ እንደማይቀበለው መገንዘባቸውን የጠቆሙት አቶ ደረጀ፥ ሕዝቡ ከድህነት መውጣትን የሚፈልግ መሆኑን አመልክተዋል። ህወሓት የዘረፈውን ወደአውሮፓና መሰል አገሮች ከማሸሽ የዘለለ ለሕዝቡ የሰራለት ነገር እንደሌለም መታዘባቸውን ተናግረዋል። በተለይ በትግራይ ያለው የገጠር ሕዝብ ስለህወሓት መሰሪነትና ተንኮል በደንብ ይገነዘባል ያሉት ሊቀመንበሩ፥ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የሚያደርገውንም አካሄድ ሕዝቡ መገንዘቡን አመልክተዋል። የትግራይ ተወላጆችና የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን በቃህ ሊሉት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የህወሓት አመራሮች በመቐለ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ጭምር ከህንጻ እስከተሽከርካሪ የሚገለጽ ሀብት አከማችተዋል። በአንጻሩ በክልሉ የዕለት ጉርሱን፣ ጫማና ልብስ ማሟላት እንኳን ያቃተው ሕዝብ (በተለይ በገጠሩ) ተፈጥሯል። የህወሓት አመራሮች ለዚህ ሕዝብ ታግለንለታል ካሉ ሕዝቡ ነጻ መውጣት ነበረበት፤ ቢያንስ ትንሽ መሻሻልም ሊያሳይ ይገባ ነበር። ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ፣ ልሂቃንና ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቆም አለባቸው ሲሉ መክረዋል።
በየክልሉ ተበትነው ያሉና በውጭ አገራት የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም ለህወሓት የሚያደርጉትን ድጋፍ ቆም ብለው እንዲያስቡ ጥሪ አቅርበዋል። በሚያደርጉት ድጋፍ በአገራቸው ለውጥ ስለመኖሩ መመልከት እንዳለባቸው፣ ህወሓት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲገዛና ሀብቱን እንደፈለገው ሲያሽከረክር ለትግራይ ሕዝብ ምን አደረገ? ብለው ሊያስተውሉ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።
ችግር ሲመጣባቸው መቐለ ተሰበሰቡ እንጂ አካባቢውን እንኳን አይተው የማያውቁ ብዙዎች ናቸው ያሉት ሊቀመንበሩ፥ ክልሉን ባስጎበኟቸው ጊዜ አምባሳደር ስዩም መስፍን በተገኙበት የጉብኝት መርሐ ግብር የአምባሳደር ስዩም የትውልድ አካባቢ መመልከታቸውን አስታውሰው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች አምባሳደር ስዩምን ከዛን ዕለት በስተቀር እንደማንኛውም ሰው በቴሌቪዥን ከመመልከት ውጪ በአካል አይተዋቸው እንደማያውቁ እንደነገሯቸውም ነው የገለጹት።
በክልሉ፣ በሌሎች ክልሎችና በውጭ አገራት የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ሕወሓት ለሕዝቡ ምን አደረገለት ወይም ምን አደረገበት ብለው ሊመረምሩ እና እነዚህን ግለኛ አመራሮች በቃ ሊሏቸው እንደሚገባ በመጠቆም፥ የትግራይ ሕዝብ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ የሚፈልገውን ፓርቲ ደግፎ የነጻነት አየር መተንፈስ እንዲችል ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የትግራይ ሕዝብ ትክክለኛ አካሄድ የሚሄድ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በመጠቆምም፤ የትግራይን ሕዝብ እገነጥላለሁ ብሎ የሚፎክረው ህወሓትም የግል ስሜትና ፍላጎቱን እንጂ የሕዝቡ ፍላጎትና ድጋፍ እንዳልሆነም ተናግረዋል። ሕዝቡ ለህወሓት ባዶ ፉከራ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነቱ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያዊነቱን እንደሚያከብር መገንዘባቸውንም አቶ ደረጀ ተናግረዋል። ህወሓት ለራሱ ጥቅምና ስልጣን ማስቀጠያ በሚያመች መልኩ እንጂ ለክልሉ ሕዝብም ሆነ ለክልሉ የተሻለ እድገት ሲል ያከናወነው ነገር አይታይም ብለዋል። በትግራይ ክልል እየሆነ ያለው የማግለል ተግባር ግን የህወሓት ሥራ ውጤት እንጂ የሕዝቡ ፍላጎትም ተግባር እንዳልሆነም አስታውቀዋል።
የትግራይ ሕዝብ በድህነት ውስጥ የሚገኝ፣ በአፈና ውስጥ ያለ፤ ከስጋት ያልተላቀቀ መሆኑን ገልጧል። እንደሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ የፈለገውን የመደገፍ የሚፈልግ፣ ከተወሰኑ የህወሓት ቡድኖች አፈና መውጣትን የሚናፍቅ መሆኑንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ለህወሓት ባዶ ፉከራ ሳይሆን ለዚህ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የትግራይ ሕዝብ ጆሮ ሰጥቶ የሕዝቡን እውነት ማድመጥ እንደሚኖርበት ደረጀ በቀለ አመልክተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 20, 2020 at 2:44 am #14559AnonymousInactiveበወቅታዊ ጉዳይ ላይ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ የሰጠው መግለጫ
ከሁሉ አስቀድመን በመቐለ ከተማ በጠራራ ፀሀይ ክልሉን እየገዛ ባለው ፓርቲ በታጠቁ ሀይሎች በጥይት ተደብድቦ በተገደለው ትግራዋይ ወጣት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን፤ ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ እንዲሁም ለሰላም ወዳድ የትግራይ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን።
በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተዉ ገዳይና አሰከፊ የሆነዉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሕዝብ ጋር በመሆን የመከላከል እና ሕዝብን የማዳን ሥራ እተሠራ ይገኛል።
በዚሁ ሁኔታ መንግሥትና ፓርቲያችን ዘርፈ-ብዙ የሆኑ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወንና በመተግበር ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ጉልህ ዘርፈ ብዙ አወንታዊ ዉጤቶች ባሻገር የተለያዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች አብይ ፈተና ሆነዋል። በተለይም በግጭት አትራፊዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚፈጥሩትና በሚቀሰቅሱት ግጭቶችና ሁከቶች ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ሲቀጥፍ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ድርጊት ለሕዝቦች ሆነ ለሀገራዊ አንድነት የማይበጅ እንዲሁም አሳዛኝ ድርጊት ነዉ።
ሕዝባችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ያጋጠመውን ድርብ ፈተናና ችግር በማለፍ ወደሚፈልገውና ወደሚገባው የሰላም፣ የብልጽግና የመረጋጋት፣ የዲሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግሥት ሆነ በፓርቲ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግሥት አመራሮችና ሠራተኞች ሕዝባዊነታቸው፣ የአመራር እሴቶቻቸውና ጥበባቸው የሚፈተንበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንደምንገኝም ማስተዋልና መበርታት ይገባል።
ሆኖም መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመለየትና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም የስጋት ደረጃና መጠኖችን በመመርመርና በመፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ፀረ ለውጥና ጸረ-ኢትዮጵያዊያን ኃይሎች ሆን ብለዉና አቅደዉ በተሳሳተ መንገድ ሕዝቡን በማደናገርና ወደ ጥፋት ጎዳና ለመምራት እየሠሩ ይገኛሉ።
በተጨማሪም ይህንን አስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚ ለግላዊ ጥቅማቸዉና ፍላጎታቸው ለማሟላት ሕዝብንም ሆነ ሀገርን የሚጎዱ አስነዋሪና አጸያፊ ተግባሮችን በመፈፀም ላይ እንደሚገኙ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል።
የትግራይ ሕዝብ የቅርብ ሆነ የሩቅ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ ጭቆናንም ሆነ አፈናን የሚፀየፍ ለኢትዮጵያ አንድነት መስዋዕት የከፈለ ሕዝብ ነው። በትግሉና በመስዋዕትነቱም ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች ጉልህ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩሉን ድርሻ የተወጣና በመወጣትም ላይ ያለ ሕዝብ ነዉ። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በከፈለው መስዋዕትነት የሰላምና ዲሞክራሲ ብልጭታ የማየት ፍላጎቱ በቀረበው ቁጥር የሚሸሽበት ምናባዊ ዓለም ብቻ እየሆነበት መጥቷል። ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ሕይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ዉስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነዉ።
በሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ በሆነዉ የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሪር የሀዘንና ውጥረት ድባብ ዉስጥ ይገኛል። ይህ ክቡር የሰው ሕይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ፀጥታን በሕግ አግባብ ለማስጠበቅ ኃላፊነት በተሰጠው የፀጥታ አካል የተፈፀመ መሆኑ እጅጉን በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል። ይህም ድርጊት ብዙ መስዋዕት ለከፈለ የማይገባዉ ነዉ። በመሆኑም የወጣቱ ግብረመልስም በክልሉ ሰላምና ዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ የኔ ጉዳይ ነዉ የሚል ከፍተኛ የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ፍላጐቶችና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዝግጁነት መኖሩን በግልፅ አሳይቷል።
እንደሚታወቀዉ በአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደርና የማሰፈፀም አግባቦች ውስጥ የሰው ልጅን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና በሕግ የማስከበር ተግባር ላይም የፀጥታ አካላት የላቀ ሰብአዊነት፣ ታጋሽነትና፣ ፍፁም ሕዝባዊነትን የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል። የዲሞክራሲና የተሻለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልምድ ጉዳይ ከአስተምህሮት ስርፀትና ግልፅ ተጠያቂነትን ከማስፈን አሠራር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ ሲሆን፤ ዜጎች በመንግሥታቸው የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቢሆንም እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ክልል በወቅቱ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ክስተቶች አፈናና ግልፅ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዳለ ማስተዋል ተችሏል። በተለይም እራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ሕይወታቸዉን እስከመቅጠፍ የደረሰ የኃይል እርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር ነው። ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው እርምት እርምጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ይህ እኩይ ተግባር በተለይ በክልሉ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ፣ ይህን መሰል የአፈና ተግባር የክልሉ ወጣት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ አጥብቆ እንዲታገለው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በአጠቃላይ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረግ በክልሉና በሀገር ደረጃ የተደቀኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ድጋፉ እንደማይለያችሁ ለመግለፅ እንወዳለን።
“ወደ ሕዝብ የተኮሰ ውድቀቱን አፋጠነ” እንደሚባለው፣ የገዢዎች የውድቀት ምልክት የሚጀምረዉ ወደ ሕዝብ መተኮስ የጀመሩ ዕለት ነው። ስለሆንም በትግራይ ክልል በተለይ ደግሞ በመቐለ ከተማ ባጋጠመው ክስተት፣ በክልሉ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የክልሉ ገዢ ፓርቲና መንግሥት አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲመረምር አስገዳጅ ማንቂያ ደወል ነው። የትግራይ ብልፅግና ፓርቲም ጉዳዩን በአፅንኦት እንደሚከታተለውና ለሚመለከታችሁ ሁሉ በጥብቅ ያሳስባል።
በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም የትግራይ ወጣት እና ለውጥ ፈላጊ ኃይል ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጋር በመሆን የለውጥ ሂደቱን እንዲያፋጥኑ ከፓርቲያችን ጋር እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ፓርቲያችን የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሚገባዉን ጥቅም እንዲረጋገጥ እና ሃገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር ይሠራል። በጥቂት ገዥ የህወሓት ቡድን በተለይ በዝምድና እና ጥቅም ትስስር እንዲሁም በሥልጣን ጥማት ምክንያት ትግራይን ከሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ለመነጠል የሚደረግ ሥራም ሆነ ሴራ በጥብቅ የምንታገለዉና የምናወግዘዉ መሆኑን በጥብቅ እናሳዉቃለን።
በመጨረሻም ለሟች የዘለዓለም እረፍት፣ ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ከልብ እንመኛለን።
የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ
ግንቦት 11ቀን 2012 ዓ.ም.May 17, 2020 at 7:58 pm #14542AnonymousInactiveከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) ከግንቦት ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገራችን የተከሰተው “የለውጥ ሂደት” መሠረታዊ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል አግባብ ያልተካሄደና የከሸፈ መሆኑን በመገንዘብ ሀገሪቱን ወደ አንድ አዲስና ጤናማ የሽግግር ሂደት የሚያስገባ አማራጭ ሃሳብ በረቂቅ ደረጃ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ውይይት ማቅረቡ ይታወቃል።
ከኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት ጋር በተያያዘ በረቂቅ ሰነዱ ላይ በአሰብነው መጠን ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሄድ ባንችልም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ቀላል የማይባል የሕብረተሰብ ክፍል በረቂቅ ሰነዱ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ማድረግ ተችሏል። በአብሮነት አባል ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ መዋቅሮች በረቂቁ ላይ በስፋት እንዲወያዩበት የተደረገ ሲሆን፥ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ከተገኙ ግብአቶች በተጨማሪ ከ700 በላይ የሆኑ አስተያየቶች በኢሜል (email) አማካኝነት መሰብሰብ ተችሏል። የተለያዩ ምሁራንና የፖለቲካ መሪዎችም ሰነዱ እንዲደርሳቸውና ሃሳብ እንዲሰጡበት ማድረግ ተችሏል።
እነዚህን ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ አስተያየቶች ባገናዘበ ሁኔታ የአብሮነት አባል የሆኑት ሦስቱ ፓርቲዎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ካካሄዱበት በኋላ ገንቢ የሆኑ ማሻሻያዎችን በረቂቅ ሰነዱ ላይ በማድረግ ይህንን የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ሰነድ የጋራ ሰነዳቸው እንዲሆን ተቀብለውታል። በይዘት ደረጃ ማሻሻያ የተደረገባቸው ጉዳዮችም ሁለት ናቸው።
አንደኛ- ሀገር አቀፍ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ጉዳይ አወዛጋቢ የፖለቲካ አጀንዳ እየሆነ በመምጣቱ የሽግግር መንግሥቱ አንዱ ኃላፊነት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ማካሄድ እንዲሆን፤ ሁለተኛ- የሽግግር መንግሥቱ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ረቂቅ የማቅረብ ብቻ ሳይሆን በሕዝበ-ውሳኔ ሕገ-መንግሥት የማሻሻል ኃላፊነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። እነዚህንና ሌሎች መለስተኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሰነዱ ከዛሬ ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሦስቱ አባል ድርጅቶችና የአብሮነት ኦፊሴላዊ ሰነድ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፥ የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡ ጥያቄውን እስከሚቀበሉት ድረስ ሰነዱ አንድ ቁልፍ የፖለቲካ የመታገያ አጀንዳችን ሆኖ እንዲቀጥል ተወስኗል።
አብሮነት በወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የረጅም ጊዜ ግምገማ አካሂዶ የደረሰበት አቋም “ሀገራችን ኢትዮጵያ ከእንግዲህ መዋቅራዊ ችግሮቿን በአስተማማኝ ሁኔታ ሊፈታ በሚችል ውጤታማ የሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ እስካልቻለች ድረስ እንደተለመደው በየአምስት ዓመቱ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ ወደ መዋቅራዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ልትሸጋገር አትችልም” የሚል ነው።
በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘውና ከሁለት ዓመት በፊት ስልጣን ለመያዝ የበቃው ብልፅግና ፓርቲ በሀገሪቱ ውጤታማ ሽግግር ለማካሄድና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ቃሉን ጠብቆ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ መዋቅራዊ ዲሞክራሲ ማሸጋገር አልቻለም። ፓርቲው ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል እውቀትና ልምድ ብቻ ሳይሆን ቅንነትና ፍላጎት የሌለው ኃይል በመሆኑ ምክንያት ሀገሪቱን ወደ በጎ አቅጣጫ ከመምራት ይልቅ የራሱን የፖለቲካ ስልጣን በማጠናከር ወደ ለየለት አምባገነናዊ ኃይልነት መቀየርን የመረጠ ይመስላል።
ይህ ኃይል እራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ወደ ከፍተኛና ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከማስገባቱ በፊት፥ በሀገሪቱ የምንገኝ የፖለቲካ ኃይሎችና የሀገሪቱ ዋና ባለቤት የሆነው ሕዝብ ተባብረን በሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገባ ካላስገደድነው በስተቀር በአጭር ጊዜ ውስጥ በታሪካችን አይተነው ወደማናውቅ አምባገነናዊ ኃይል እራሱን ሊቀይርና ሀገሪቱንም ከባድ እና ውስብስብ ወደ ሆነ አደጋ ሊያስገባት ይችላል።
አብሮነት ሀገራችንን ከእንዲህ ዓይነት አስፈሪ ጥፋት መታደግ የሚቻለው በቂ የሥነ-ልቦናና የመዋቅር ዝግጅት ያልተደረገበት ሀገራዊ ምርጫ በማካሄድ ሳይሆን፥ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ሁሉን አቀፍ የሆነ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ነው ብሎ በፅኑ ያምናል።
መዋቅራዊ የሆኑ የፖለቲካ ችግሮቻችንን በአግባቡ ለመፍታት በሚያስችል የሽግግር ሂደት ውስጥ እስካላለፍን ድረስ ግን ላለፉት 29 ዓመታት በስልጣን ላይ በቆየው ገዢ ፓርቲ፣ በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት እየተመራንና ከአለፉት አምስት ምርጫዎች ያልተለየ ስድስተኛ ዙር ምርጫ በማካሄድ የሀገራችንን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት አንችልም። እንዲያውም ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች የተለየና የተሻለ ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ሀገራችን ህልውናዋን ወደሚፈታተን የእርስ በእርስ ጦርነት ወይም መንግሥት-የለሽ ሁኔታ ልትገባ ትችላለች የሚል ከፍተኛ ስጋት አለን። ይህንን የሽግግር መንግሥት ሰነድ ብዙ ተጨንቀንና ተጠበን እንድናዘጋጅ ያስገደደንም ይኸው ስለ ሀገራችን ህልውና መቀጠል የሚሰማን ስጋት ነው።ይህ ለሀገራችን ህልውና መቀጠል መድኅን የሚሆን የሽግግር መንግሥት መቼና እንዴት ሊቋቋም ይችላል? በማንና ለምን ሊቋቋም ይገባዋል? ሂደቱና የመጨረሻ ግቡስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር ለመመለስ በሚያስችል መጠን ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
ስለሆነም፦
ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ሀገራችን ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዳ በዘላቂነት ወደ መዋቅራዊ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር በምን ዓይነት የሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ ይገባታል?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የየራሳቸውን ዝርዝር አማራጭ ለውይይት እንዲያቀርቡ፤
የኮሮና ቫይረስን ስርጭት በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማያስተጓጉል ሁኔታ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ዙሪያ ውይይትና ድርድር አካሂደው የጋራ መፍትሄ የሚያመነጩበት ሀገራዊ የምክክር ሂደት /national dialogue/ በፍጥነት እንዲያመቻች፤
የኢትየጵያ ሕዝብም በአንድ ውጤታማ የሽግግር ሂደት ማለፍ ለሀገሪቱ ችግሮች በዘላቂነት መፈታት አስፈላጊና የማይተካ ሚና ያለው ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን በመገንዘብ ሀገራዊ የምክክር ሂደት እንዲጠራ የራሱን ግፊትና ትግል እንዲያደርግ
አብሮነት በአፅንኦት ይጠይቃል።
ከዚህ ውጭ ገዢው ፓርቲ ላለፉት 29 ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም “የሀገሪቱንዕጣ-ፈንታ መወሰን የሚገባኝ እኔ ብቻ ነኝ” በሚል መታበይ ወይም “እኔ አሻግራችኋለው” በሚል ያልተገባ ፍልስፍና በስልጣን ላይ የሚቀጥል ከሆነ ግን ሀገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አደገኛ የብጥብጥ አዙሪት ልትገባ የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ሀገራችን ከዚህ ዓይነቱ አሳሳቢ ስጋት ወጥታ ወደ ዘላቂ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በየበኩሉ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል።
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባMay 10, 2020 at 2:04 am #14452AnonymousInactive“ሕግ አክባሪው የትግራይ ሕዝብ፣ የህወሓትን ውሳኔ አይቀበለውም” ― አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – ህወሓት የዘንድሮውን ምርጫ በክልል ደረጃ አካሂዳለሁ ብሎ ያወጣው መግለጫ ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ በመሆኑ ሕግ አክባሪው የትግራይ ሕዝብ በምንም መልኩ የማይቀበለው መሆኑን የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል አስታወቁ።
የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፥ ምርጫ የማካሄድ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆኖ ሳለ ህወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስ ከመሆኑም ባለፈ ሕግ አክባሪው የትግራይን ሕዝብ የማይመጥ ነው። ሕዝቡ ይህንን ሕገ መንግሥቱን የሚንድ ተግባር አይቀበልም።
«የህወሓት መግለጫው ከሕገ መንግሥት ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን የምርጫ ቦርድ ኃላፊነትን የዘነጋና አልፎ ተርፎም እውቅና መስጠት ያልፈለገ መግለጫ ነው» ያሉት አቶ ነብዩ፥ ይህም ሕገ መንግሥትና አገርን መናድ በመሆኑ በወንጀል ሕጉ የሚያስጠይቅ መሆኑንን አስገንዝበዋል።
የትግራይን ሕዝብ አስተዳድራለሁ የሚለው ህወሓት እያደረገ ያለው ተግባር ይህንን ጨዋ ሕዝብ ደረጃ የማይመጥንና የሥልጣንን ጥማትን ለማርካትና ወንበርን ለመጠበቅ ብቻ የሚሄድበት መንገድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ ሥርዓት አለ ለማለት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፥ በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ በሚል ዝግ የሆኑ የካድሬዎች ስብሰባ እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህም ደግሞ በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጥስ መሆኑን አመልክተዋል። “ይህም የሚያሳየው ራሳቸው ላወጁት አዋጅ እንኳን ተገዢ አለመሆናቸውን ነው” ብለዋል።
በሌላ በኩል እንደ አገር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ እያለ፤ በቫይረሱ የተየዙ ሰዎችን ውጤት እንደ አገር መረጃ እየተላለፈ ባለበት ሁኔታ የክልሉ ጤና ቢሮ በተናጠል መረጃ ማውጣቱ የህወሓትን አመራሮች ምን ያህል ለሕዝብም ሆነ ለአገር ደኅንነት የማያስቡ መሆናቸውን እንደሚያመላክት አስረድተዋል። “የትግራይ ሕዝብ እንዲህ ዓይነት የመንግሥት አገልግሎት አይመጥነውም፤ አይገባውምም” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች መንገዶች የህወሓትን ተግባር እየኮነነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መንግሥትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ጊዜው ከማራዘም ባለፈ የሕዝብና የአገር ግዛት አንድነትን እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት አስታውሰው፤ ሕገ መንግሥቱን ለመናድና በአቋራጭ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ብሎም አገር የሚበጠብጡ አካላትን ሕግን መሠረት በማድረግ እርምት የሚወሰድባቸው መሆኑን አስታውቀዋል። “የአገርና የሕዝብን ደኅንነትን በማስቀደም ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ ይወስዳል” ብለዋል።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 7, 2020 at 10:45 pm #14418AnonymousInactiveቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫን በተመለከተ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የሰጠው ወቅታዊ የአቋም መግለጫ
የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት (Caretaker Government of Technocrats) ይቋቋም!ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት የምትሸጋገረውና መጪው ምርጫ ብሩህ ተስፋ የያዘ የሚሆነው አሳታፊ፣ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ጉባዔ በማድረግ ብቻ ነው። ጉባዔው በአንድ በኩል ሀገራችን ያንዣበበባትን የኮሮና ወረርሽኝን እንዴት ልታልፍ እንደምትችል ምክክር እንዲደረግ የሚያስችል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ቀጣዩ ምርጫ መቼ ይሁን? በምን ቅርጽ ይካሄድ? እስከ ምርጫው ድረስ ሀገራችንን ማንና እንዴት ይምራት? ለሚሉት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ የሚገኝበት መድረክም ነው። ይህን ዓይነቱን ጉባዔ ፍሬያማ ለማድረግ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ዋና ዋና የፖለቲካና የሲቪክ ባለድርሻዎች እንዲሳተፉበት ማድረግ የግድ ይላል።
ይሁን እንጂ፣ ገዢው ፓርቲ እንደዚህ ዓይነቱ ሀገራዊ ጉባዔ እንዲደረግ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ፥ በሀገራችን ውስጥ ተፅዕኖ ያላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች በማግለል የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጀቶችን ብቻ መርጦ ስብሰባ አድርጓል። በዚህ ሂደት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን ጨምሮ፣ ሌሎች ለገዢው ፓርቲ ብርቱ ተፎካካሪ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳይሳተፉ አድርጎ፣ ቅንነትና ታማኝነት የጎደለው፣ ጠቃሚ ሃሳቦች በተሟላ መልኩ ያልተንሸራሸሩበት፣ ለሃቀኛ ሽግግር ያልቆረጠ ስብሰባ እንዲሆን አድርጎታል።
በዚህም ሳቢያ በሀገራችን መጻኢ ዕድል ላይ ጥቁር ዳመና እንዲያንዣብብ እየሆነ ነው። ኢትዮጵያን ወደ ሚቀጥለው የተሻለ ደረጃ ከማስፈንጠር አንፃር ማንም ልጅ፣ ማንም የእንጀራ ልጅ ስላልሆነ፣ የማግለል አካሄድ ለሀገራችን ስለማይበጅ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል።
በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የመንግሥት የሥራ ዘመን 5 ዓመት ብቻ እንደሆነና፣ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ ከወራት በፊት [ብሔራዊ] ምርጫ መደረግ እንዳለበት የደነገገ ቢሆንም፥ በበሽታ፣ በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌላ እክል ምርጫውን ማካሄድ ሳይቻል ቢቀር ምን መደረግ እንዳለበት ምንም መፍትሄ አላስቀመጠም። ይህም አሁን ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫን በተመለከተ ትልቅ ሀገራዊ ተግዳሮት ፈጥሯል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በሚያዝያ 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ·ም. ባደረገው አስቸኳይ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ፣ የምርጫውን መራዘም አስመልክቶ ገዢው ፓርቲ አግላይ በሆነው ስብሰባ ያቀረባቸውን 4 አማራጮች በጥልቀት ከሕግና ከፖለቲካ አግባብነት አንፃር እያየ መርምሯል።
ኮሚቴው በገዢው ፓርቲ የቀረቡት አማራጮች ሀገሪቷን ከተጋረጡባት ተግዳሮቶች የማይታደጓት ብቻ ሳይሆኑ፣ በከፊል ሕጋዊ መሠረትም የሌላቸው መሆኑንም ተገንዝቧል። ስለሆነም፣ አማራጭ ሀገራዊ መፍትሄ ለማስቀመጥ ውይይትና ክርክር ከማድረጉ በፊት አራት መስፈርቶች እንደ ቅድመ-ሁኔታ አስቀምጧል። እነዚህም፡-
- የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት፣ ሠላምና ደኅንነት የሚያስቀጥል መሆን እንዳለበት፣
- መፍትሔው ሀገራዊ ተግዳሮቱን እንደ ክፍተት በመጠቀም የማንንም የስልጣን ጥም እውን ለማድረግና ለማስፈፀም መዋል እንደሌለበት፣
- ለዴሞክራሲያዊ ሽግግርና ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት መሆን እንደሌለበት፣
- የባልደራስን ጨምሮ ከማንኛቸውንም የፖለቲካ ድርጅት ፍላጎትና አመለካከት የፀዳ መሆን እንዳለበት፣
- ለመሰል ሀገራዊ ተግዳሮት ዓለም-አቀፍ ተሞክሮ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት የሚሉት ናቸው።
እነዚህን መስፈርቶች መመዘኛ አድርጎም፣ በገዢው ፓርቲ በኩል የቀረቡት «አማራጮች»ም ሆኑ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚሹ ኃይሎች የተሰባሰቡበት ያቀረቡት «የሽግግር መንግሥት እንመሥርት» ጥያቄ ለሀገሪቱ እንደማይበጁ ጥርት አድርጎ ማየት ችሏል።
በአንጻሩ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ ያሉትን መሰል ተሞክሮዎች ግምት ውስጥ ሲገቡ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለኢትዮጵያ የሚበጃት «የባለሙያዎች የባለአደራ መንግሥት» ወይም በእንግሊዘኛ አጠራሩ “Caretaker Government of Technocrats” ነው ብሎ በፅኑ አምኗል።
ይህ የባለሙያዎች የባለአደራ መንግሥት ከየዘርፉ በሚመለመሉ ምሁራንና ባለሙያዎች የሚቋቋም ሲሆን፣ አዋጪነቱም ተፈትኖ የታየ ብቻ ሳይሆን፣ ገዢው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዋች ሀገራዊ ተግዳሮቱን በመጠቀም ለስልጣን ሽሚያ እንዳይጋበዙና ሀገር እንዳትጎዳ ዋስትና ይሰጣል።
የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት፡-
1ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት በሕይወት ዘመናቸው የፖለቲካ ድርጅት አባላት ባልነበሩ ምሁራንና ባለሙያዎች የሚቋቋም ይሆናል፣
2ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላትና ሹመኞች በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ገደብ የሚጣልባቸው ይሆናል፣
3ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላትና ሹመኞች ከምርጫ በኃላ በሚቋቋመው መንግሥት የፖለቲካ ሹመት እንዳይሰጣቸው የአንድ የምርጫ ዘመን ገደብ የሚጣልባቸው ይሆናል፣
4ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላት በፖለቲካ፣ በሲቪክ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታዛቢነት የሚመረጡ ይሆናል፣
5ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል ይመረጣሉ፣የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት ኃላፊነት፡-
- የሀገር ሉዓላዊነትን መጠበቅ፣
- የሀገር ጸጥታን ለማስጠበቅ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፣
- ለነጻ ምርጫ የሚያስፈልጉ ነጻ የመንግሥት ተቋማትን መገንባት፣
- የመንግሥትን የዕለት ተዕለት ሥራ መምራት፣
- ከምርጫው በፊት፣ ለሀገራዊ እርቅና መግባባት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሰላም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
- ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ቃል ኪዳን (citizen’s covenant) እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
- የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት የሥራ ዘመን ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ይሆናል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ
ሚያዚያ 26ቀን 2012 ዓ·ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ!May 7, 2020 at 3:21 pm #14411AnonymousInactiveየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ
ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣
ለመላው ኢትዮጵያውያን!የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሀገራችንን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አውዶችን በጥልቀት በመገምገም፤ የአማራ ሕዝብን ወቅታዊ አቋምና ዘላቂ ጥቅሞችን፤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ፍላጎቶችን እና የቀረቡ አማራጮችን በፅሞና በመመርመር፤ በዚህም መሠረት፦
- ለሰላማዊና ጠንካራ ሀገራትና መንግሥታት እንኳን የሚያዳግቱ ግዙፍና አሳሳቢ ብሔራዊ ተግዳሮቶች የተደቀኑብን መሆኑን በማመን፤
- የዴሞክራሲያዊ ውድድር፣ የልሂቃን ውይይትና ድርድር ባህል ባልዳበረበት በጥልቅ በተከፋፈለ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደምንገኝ በመገንዘብ፤
- የኢትዮጵያ ቀጣይ ሁኔታ በምርጫ ወይም በይስሙላ ማሻሻያዎች ብቻ እንደማይወሰን፣ የአሸናፊዎችና የጉልበተኞች ጫናም ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ በማመን፤
- ከምንም ከማንም በላይ የአማራን ሕዝብ ሰላም፣ ደኅንነትና ዘላቂ ጥቅሞች መከበርና የሀገራችንን ህልውና ቀጣይነት በማስቀደም፤
አብን እነዚህንና ሌሎችንም ተጓዳኝ ታሳቢዎችን በማድረግ ሀገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ በአስተማማኝ ልትወጣ የምትችልባቸውን መንገዶች በተመለከተ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል።
1ኛ. የሽግግር ጊዜ (transitional period) አስፈላጊነት
ንቅናቄያችን አብን ሌሎች በሀገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቋማት ላቀረቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ክብር ያለው ቢሆንም አሁን ለገባንበት ፖለቲካዊ ቀውስ አዲስ የሽግግር መንግሥት (transitional government) መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት የለውም።ከዚህ ይልቅ የተወሰነ የሽግግር ጊዜ መፍጠር የተሻለ አማራጭ መሆኑን እንገነዘባለን። ምክንያቱም የሕዝባችንና የሀገራችን ዕጣፈንታ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቆም ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ነባራዊ ውጥረቶችና ክፍተቶች እንዲረግቡና የጥሞናና ውይይት መንፈስ እንዲሰፍን ያስችላል። የሽግግር ጊዜ ያላሰለሰ ሕዝባዊ ውይይት፣ ልሂቃዊ ምክክርና ድርድር እንዲደረግና ሊያሠራ የሚችል ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ዕድል ይሰጣል።
2ኛ. የመንግሥት-መር (state-led) ሽግግር አስፈላጊነት
አብን ከገባንበት ብሔራዊ አጣብቂኝ ለመውጣት የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት፣ የሕግን የበላይነት በማስከበር ረገድ ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ አካል መኖር እንዳለበት ያምናል። አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍጠር በሀገራችን ወቅታዊ የፖለቲካና የኃይል አሰላለፍ አውድ ሊሳካ እንደማይችል ይገነዘባል።ስለዚህም ምንም እንኳን ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የታየው መንግሥት መሩ የለውጥ ሂደት የከሸፈና የማያሰራ እንደነበር ብንረዳም፣ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቆየትና የሽግግር ሂደቱን መምራት ለሕዝባችንና ሀገራችን ሰላምና ደህንነት ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት የተሻለው ነው ብለን እናምናለን።
3ኛ. የመዋቅራዊና ሁሉን አካታች ሽግግር ሂደት አስፈላጊነት
አብን የአማራ ሕዝብና የሌሎች ወንድም ህዝቦች መሠረታዊ ጥያቄዎች ሥርዓታዊና መዋቅራዊ በመሆናቸው በዋነኝነት የሚፈቱት በልሂቃን መካከል በሚደረግ ውይይትና ድርድር ከሚመነጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ መሆኑን ያምናል።ብሔራዊ ፖለቲካችን ከጥሬ የስልጣን ትግል ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሻገር ከታሰበ ከአጭር ፖለቲካዊ ትርፍ ይልቅ ዘላቂ የሀገርና የሕዝብ ጥቅምን ያማከለና አዲስ ቅርፅና አቅጣጫ ያለው ሰፊና የማያቋርጥ የድርድርና እርቅ ሂደት ያስፈልጋል። በተለይም የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት ማሻሻል፣ አጠቃላይ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦችን ማድረግ ያሻል። ከሁሉም በላይ በአሳሳቢ ሁኔታ እየወደቀ የመጣውን ምጣኔ ሀብታችንን እንዲያንሰራራ ማድረግ የግድ ነው። ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን ያካተተና ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆነ የብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን እንዲቋቋም ድርጅታችን አብን ይጠይቃል።
4ኛ. መሠረታዊ የሕዝባችንን ጥያቄዎች በተመለከተ
-
- ሀ. የኮቪድ-19 ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ በመሠረታዊ የሕዝቦች ጥያቄዎች ላይ ቅርፅ ያለውና ተቋማዊ የሆነ ብሔራዊ ውይይት (national dialogue) እንዲጀመር ለማድረግ ዋስትና እንዲሰጥ ንቅናቄያችን አበክሮ ይጠይቃል።
- ለ. የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ፣ ንቅናቄያችን የ1999 ዓ.ም. ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሳይንሳዊ ያልሆነና ሸፍጥ የተሞላብት የሕዝባችንን ቁጥር በእጅጉ የቀነሰ በዚህም ፖለቲካዊ ውክልናውን እና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነቱን ያሳጣ በመሆኑ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ፤ ለተከሰቱት ጉዳቶች ፍትኃዊ ማካካሻ (restorative justice) እንዲደረግና ቀጣዩም ቆጠራ ሳይንሳዊና ገለልተኛ በሆነ ተቋም እንዲካሄድ ይጠይቃል።
- ሐ. የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ፤ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ሕዝባችንን የማይወክልና በሂደትም ቅቡልነትን ያላተረፈ፣ በአማራ ጠል ትርክት ላይ የተመሠረተ፣ ለሀገር አንድነትና ህልውና የማይበጅ፣ እንደዚህ ያለ ፈታኝ ወቅት ሲያጋጥም እንኳን በአግባቡ ሊያሻግር የማይችል በመሆኑ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የሕገ-መንግሥት ለውጥ ወይም ማሻሻያ እንዲደረግ ይጠይቃል።
- መ. የሀገራችንንና ሕዝባችንን የሰላምና ደኅንነት ዋስትና በተመለከተ፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሕግና ሥርዓት በማስከበር ረገድ ያሳየው ድክመት ተገቢ አለመሆኑንና በፍፁም መቀጠል እንደሌለበት በማመን፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ከመንግሥት ግንባር ቀደም ኃላፊነቶች መካከል መሆኑን በመገንዘብ፤ ሀገራችን ባለችበት የስጋት ሁኔታ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተለየ ዝግጁነት እንዲደረግ አበክሮ ይጠይቃል።
አብን በሕዝባችን ትግል የተሸነፉ ቋሚ የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ጠላቶችና ግብረ አበሮቻቸው ሀገራችንን ለማተራመስና እንደገና የጭቆና መንበራቸውን ለመመለስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጥብቆ እንደሚታገለው በአፅንኦት ያረጋግጣል።
ንቅናቄያችን ከላይ የገለፃቸውን አቋሞች በተመለከተ ከመንግሥትና ከተለያዩ የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ንግግሮችንና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን እያሳወቀ የተከበረው የአማራ ሕዝብ፣ የድርጅታችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በአሁኑ ወቅት የተደቀነብንን ብሔራዊ አደጋ በማጤን ላቀረብናቸው አማራጭ ኃሳቦች ስኬት ከጎናችን እንድትሰለፉ በአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ! ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ ኮሚቴ
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም.—
May 7, 2020 at 1:52 am #14398AnonymousInactiveከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ
ስልጣንን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ በአስቸኳይ ይቁም!ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ግን የስልጣን ዘመኑን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚያስችለውን ጥረት ለሕዝብ ይፋ ባልሆነ መንገድ እያደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች እየደረሱን ነው። ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ከተሰጠው ስልጣንና መብት ውጭ በሦስት አማራጮች ስልጣኑን ለማራዘም እየሞከረ እንደሚገኝ ታውቋል።
እነዚህ አማራጮችም፤-- በዓመቱ መጨረሻ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ እንዲበተን ማድረግና በ6ወር ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፤
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደገና በማራዘም የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከር፤
- የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት በማሻሻል የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም የሚሉ ናቸው።
ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ በየትኛው መንገድ የመንግሥትን ስልጣን ለማራዘም እንደሚቻልም ገዥው ፓርቲ ከራሱ መዋቅሮችና በዙሪያው ከሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ጋር እየመከረ እንደሆነ ታውቋል።
አብሮነት ከዚህ ቀደም ደጋግሞ ለመግለፅ እንደሞከረው ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግሥት ዕድሜ ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ድንጋጌ በሀገራችን ሕገ-መንግሥት ውስጥ የለም። በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 72/3 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ ስለመሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም የመንግሥትን ዕድሜ እንዴት ማራዘም እንደሚቻል ሕገ-መንግሥቱ ምንም ዓይነት ድንጋጌ አላስቀመጠም። ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትን የሕገ-መንግሥቱን አርቃቂዎች እና ለሕገ-መንግሥቱ ክፍተት መታየት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስን “ከመርገም” ውጭ በሕጋዊ መንገድ የስልጣን ዘመኑን ለአንድም ቀን የሚያራዝምበት ምንም ዓይነት መብትና ስልጣን በሕገ-መንግሥቱ አልተሰጠውም።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስልጣን የተሰጣቸውም በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን አምስት ዓመት የመንግሥት የስልጣን ዘመን ለመጨረስ ነው እንጂ ከአምስት ዓመት በላይ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም አይደለም። እንዲያውም በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60/1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ በሕግ የተሰጠን የሥራ ዘመን ለማጠናቀቅ ከመቻል ጋር እንጂ የሥራ ዘመንን ከማራዘምና የመንግሥት የሥራ ዘመን ካለቀ በኋላ ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 93/1፣ ሀ እና ለ ላይ በግልፅ እንደተደነገገውም የመንግሥትን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ተብሎ ሊታወጅ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም። አሻሚና አከራካሪ ባልሆነ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ዓይነት ጉዳዮች ሊታወጅ እንደሚችል ሕገ-መንግሥቱ በዝርዝርና በግልፅ ስላስቀመጠ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማዎጅ ስልጣኑን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችለው ሕጋዊ መብትና ስልጣን የለውም።
እንደ ሦስተኛ አማራጭ እየታየ ያለው ሕገ-መንግሥቱን አሻሽሎ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከርም ሕጋዊነትን የተከተለ አሠራር አይደለም። አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግሥት የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት የሚያሻሽል ከሆነ፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደ አንዳንድ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች በዓለም ፊት መሳቂያ እና መሳለቂያ የሚያደርግ የአምባገነኖች ድርጊት እንጂ ሕጋዊ አሠራር ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ሕገ-መንግሥትን ለማሻሻል የመሞከር እርምጃም ከሕግ መኖርና አስፈላጊነት መሠረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሂደትም ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል የሕዝብ ቅቡልነት ሊያገኝ አይችልም። እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ሀገራዊ ጉዳይ አሳታፊና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመወሰን መሞከርም ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሁለንተናዊ የህልውና ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ አለመረዳት ነው። ይህም እንደተለመደው የገዥውን ፓርቲ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ስልጣን የማስቀደም ኃላፊነት የጎደለው ፍልጎት የሚያሳይ ነው።
ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች በሠሩት ስህተት እና በኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የመንግሥት የሥራ ዘመንን አስመልክቶ ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ (constitutional crisis) መፈጠሩን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በአንድ አገር ሲፈጠር ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በመደበኛ የሕግ አሠራር ሳይሆን ከመደበኛ የሕግ አሠራር ውጭ (extra-constitutional) በሆነ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መፍትሄ ለመስጠትም በተለየ ሁኔታ በሕግ መብት የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መንግሥታዊ ተቋም ስለሌለ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው? በሚለው ጥያቄ ተነጋግሮ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የምክከር ሂደት (national dialogue) መጥራት ያስፈልጋል። ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በሀገራችን በሕጋዊም ይሁን በይስሙላ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ስለማይኖር የወደፊቱን የአገሪቱን ዕጣ-ፈንታ በመወሰን ረገድ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ከማንኛችንም በአገሪቱ ከምንገኝ ፓርቲዎች የተለየ መብትና ስልጣን ስለሌለው በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ብቻውን መወሰን አይችልም። ገዥው ፓርቲ ይህንን ማድረግ ከሞከረ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ እና ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።
ስለሆነም፦
1ኛ. በአሁኑ ወቅት ዋናውና ቀዳሚው ትኩረታችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር መሆን ስላለበት ቢያንስ እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2012 ዓ.ም. ድረስ ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በተመለከተ ምንም ዓይነት አጀንዳ ይዞ እንዳይነጋገርም ሆነ የተናጠል ውሳኔ እንዳያስተላልፍ፤
2ኛ. የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በዘንድሮው ዓመት በተናጠል ምርጫ ለማካሄድ ማሰቡ ሕገ-መንግሥታዊ ውሳኔ አይደለም። በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ብቸኛ መብት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑን በመገንዘብ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ህወሓት ከዚህ ዓይነቱ ሕገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤
3ኛ. ብልፅግና ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በሚመለከት በድብቅ የሚፈፅማቸውን ተግባራት ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በንቃት እንዲከታተሉ፣ ገዥው ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በተመለከተ ሕገ-ወጥ እርምጃ መውሰዱን የሚቀጥልበት ከሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመቺ የመገናኛ መንገድ ፈጥረው በአስቸኳይ መመካከር እንዲችሉና በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን አቋም እንዲይዙ፣ ከዚህ በኋላም በሀገራችን ጉዳይ አንዳችን ጋባዥ ሌላችን ተጋባዥ የምንሆንበት ምክንያት እንደሌለ ተገንዝበን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የምናደርገው ማንኛውም ግንኙነትና ድርድር በእኩልነት መንፈስ ብቻ እንዲሆን የሚያስችል አቋም እንድንይዝ፤
4ኛ. የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 29 ዓመታት በአፈናና በይስሙላ ምርጫ በስልጣን ላይ የኖረው ገዥው ፓርቲ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ በሕገ-ወጥ መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገውን ጥረት አጥብቆ እንዲቃወም፣ መቃወምም ብቻ ሳይሆን የገዥውን ፓርቲ ሕገ-ወጥ እርምጃ በጠንካራ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማስቆም እንዲዘጋጅ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል።
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ሚያዚያ 21 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባMay 6, 2020 at 6:20 pm #14394AnonymousInactiveየምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ ሀገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል! ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። ወረርሽኙ በሰዎች ጤና እና ደኅንነት ላይ ካደረሰው እና እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ የዓለምን እና የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እና ሥርዓትን ከባድ አደጋ ውስጥ ከቷል። ወረርሽኙ በሀገራችን ኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። በሌሎች ሀገር ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አሁንም አለ። የጎረቤት ሀገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት የጀመረበትና በተለይ ከጅቡቲ ጋር ካለን የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከአሁኑ እየታየ ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ጫናም በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ይህም በቶሎ ወደቀድሞ ሁኔታው የሚመለስ አይሆንም። የበረሀ አንበጣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ እንደዚሁም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና እስከ ሰኔ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዋስትና የማጣት ስጋት/አደጋ እንዳንዣበበባቸው በቅርቡ ተገልጿል። በአጠቃላይ ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው መጠነ ሰፊ መቀዛቀዝና የአገራዊ ጥቅል አመታዊ ምርትና እድገት ማሽቆልቆል ሀገራችን ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው።
በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል።
ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባን ካለነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ከሌሎች ሀገሮች የተደቀነብን አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ የነበረውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ሀገርን ማን ያስተዳድራል የሚል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ነው የሚሉትን ሀሳብ እያቀረቡ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በተለይም ከሕገ-መንግሥት ጠበቆች (constitutional lawyers) ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። ባለሙያዎቹ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ-መንግሥታዊ አግባብ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለውን የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ የባለሙያዎች ጉባዔ (high level panel of experts) በማቋቋም ለአንድ ወር ያህል ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት ቆይቷል። ኢዜማ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ልንከተለው የሚገባው የመፍትሔ ሀሳብ የሚከተሉትን ታሳቢዎች ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤
- አገራችን ከምትገኝበት የሕግም የፖለቲካ አጣብቂኝ በአጭር ጊዜ ለመውጣት የሚረዳ መሆን እንዳለበት፣
- ተቋማዊ አሠራሮችን ከማጎልበት አንፃር የተሻለ ዕድል የሚፈጥር መሆን እንዳለበት፣
- አጠቃላይ ችግሩ በአጭር ጊዜ ፈቶ አገራችን ወደተረጋጋ የምርጫ ሂደት ለመግባት የሚያስችል መሆን እንዳለበት፣
- ከወጪም ከጊዜም አንፃር አገሪቱን ብዙ ዋጋ የማያስከፍል የተሻለው አማራጭ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በፍጥነት የተቀያየሩት የአገራችንንና የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካዊና የደኅንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት።
ኢዜማ ከላይ የገለፅናቸውን ሀገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት እንደሚያስፈልገን ያምናል። ለዚህም እንደፓርቲ ልንከተለው የሚገባን የመፍትሄ ሀሳብ ይህንን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው በፅኑ ይረዳል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፓርቲያችንን የሕግ ባለሙያዎች ጨምሮ በሌሎች አካላትም የቀረቡትን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።
- ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሄ በሚል በተለያዩ አካላት የቀረበ የመፍትሄ ሀሳብ
በዋናነት በዚህ ረገድ የቀረበው ሀሳብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚያበቃ በመሆኑ እና ሕገ-መንግሥቱም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ክፍተት ስለማይሰጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሠረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ነው። ይህ መፍትሄ ሀሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው። ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ያሉብንን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር አይደለም። ይህም የገባንበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ ያደርገዋል።
- በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች
2.1. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ማድረግ፦ ይሄ አማራጭ በ6 ወር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እና ሕግ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ የሀገር እና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ከግምት የማያስገባ፣ የፌደራል መንግሥትን እንጂ ሥልጣናቸው አብሮ የሚጠናቀቀውን የክልል ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ያላገናዘበ አማራጭ በመሆኑ የምንፈልገውን ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር አማራጭ ሆኖ አላገኘነውም።
2.2. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀመጠ አንቀጽ አይደለም። አስቸኳይ ግዜ ማዋጅም በቀጥታ የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘምን አያስከትልም። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር የሚደረግ ምርጫን ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም።
2.3. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ከፌደሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ፦ በዚህ አማራጭ መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ሥራ የሚሠራው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሙሉ ነፃነት እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተመራለትን ጉዳይ በመመርመር የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ያ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ክብደት አንጻር ጉዳዩን መዳረሻ ውጤቱ አስቀድሞ በእርግጠኝነት ለማይታወቅ እና ምናልባትም መልሶ እዚህ ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል አንደኛውን እንድንከተል ሊያደርግ ለሚችል ሂደት መስጠት ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።
2.4. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፦ ይህ አማራጭ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።
ምንም እንኳን ኢዜማ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም፥ አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። አሁን ለገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በኢዜማ እምነት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ሀገራዊ መረጋጋት፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እንዲሁም በከፍተኛ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው ሀገራዊ ጉዳይ በዚህ ወቅት ሊከወን አይገባም ብለን እናምናለን። ሆኖም አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልፅ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ-መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቁ እንዲሁም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ 2/3ኛ ክልሎች (6 ክልሎች) በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁት በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ 3 ስር ከሚገኙት እና አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን የሕገ-መንግሥት አንቀጾች ማሻሻል እንደሚቻል ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58/3 ከላይ በተገለጸው መሠረት ማሻሻል የተሻለ መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን።
ይህ መፍትሄ ተግባራዊ ከተደረገ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት ተከትሎ የሚፈፀም በመሆኑ ሕገ ምንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። በዚህ አማራጭ ላይ በተለያዩ አካላት የሚነሳው ጥያቄ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት በአንቀጽ 104 ድንጋጌ መሠረት ህዝብን ለማወያየት አያስችልም የሚል ሲሆን ይህንን ክፍተት ግን ሕዝቡን በወኪሎቹ አማካኝነትና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በማወያየት መሸፈን ይቻላል።
ከዚህ ቀደም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የጋራ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን በሚመለክት የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀጽ 103/5 በሕገ-መንግሥቱ የተጠቀሰውን የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሳይከተሉ ለየብቻ በተለያየ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ አሁን መደረግ ያለበት ማሻሻያ ግን የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105/2 ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች በሙሉ አሟልቶ ሊሆን እንደሚገባው እናምናለን።
ይህ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌድሬሽን ምክር ቤትንም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት።
የፓርቲያችን እምነት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ቢሆንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተራ ቁጥር 2.3 ላይ የጠቀስነውን አማራጭ በመውሰድ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጥ 54/1፤ 58/3 እና 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደመራው ታውቋል። ምንም እንኳን ኢዜማ ይህንን አማራጭ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ-መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ አለበት። ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት።
በአጠቃላይ እንደሀገር የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ለማሳሰብ ይወዳል። በተጨማሪም በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መዳበራቸው መፍጠር የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድንለማመድ በር የሚከፍት እና ሁሉንም ኃይሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የምናደርግበት መድረክ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያMay 5, 2020 at 12:19 am #14365AnonymousInactiveከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ተሰብስቦ የነበረው የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባለ አምስት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ከህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በክልላችንና በሀገራችን እንዲሁም በንዑስ ቀጣናው የተከሰቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስፋት በመመርመር የውሳኔ ሃሳቦችን አሳልፏል። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በክልላችን እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የክልላችንና የሕዝባችን ድኅንነት የመታደግ ሥራዎችን እንዲሁም የኮረናን ወረርሽኝ ለመመከት የተሠሩ ሥራዎች በሚመለከት በዝርዝር የተወያየበት ሲሆን፣ እስካሁን የታዩ ጥንካሬዎችን ጠብቆ ለማቆየትና የታዩ ጉድለቶችን ለማረም የተሠሩ ሥራዎችን በመመርመር ውሳኔዎችን አሳልፏል። በክልላችን ያሉ ወይም የሚኖሩ ፈተናዎች ለመመከት አሁንም ወሳኙ ውስጣዊ ጥንካሬያችን መሆኑን በድጋሚ በማረጋገጥ በዚህ ረገድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሦስት ቀን ስብሰባው በስፋት ከመከረባቸው ጉዳዮች ዋነኛው በሀገር ደረጃ በብልፅግና ፓርቲ እየተካሄደ መጥቶ አሁን በመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ ዘመቻ የሚመለከተው አጀንዳ የጎላ ትኩረት የተሰጠው ነበር። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዝርዝር ተወያይቶ እንዳስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት ያላሳየበትን ሀገራዊ ምርጫ የCOVID-19 ወረርሽኝ መከሰትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በግልፅ እንደታየው የፓርቲዎችን ሃሳብ ለመቀበል በሚል በተጠራ የይስሙላ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለቀለት ያሉትን ሃሳብ ማጠናቀቂያ ክፍል ምን ሊመስል እንደሚችል በግልፅ አመላክተዋል።
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህ ያለበቂ ዝግጅትም ሆነ ያለግልፅ አጀንዳ የተጠራውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕግ ውጭ በሥልጣን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት መድረክ ተከትሎ በፓርላማው የተጀመረውና ሕግን ያላግባብ በመተርጎም የብልፅግና ፓርቲን ሕገ-ወጥ የስልጣን ዕድሜ የማራዘም እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ አስምሮበታል። አሁንም ሥልጣን ላይ ባለው ኣካል የተጀመረውና ሕገ-መንግሥትን መተርጎም በሚል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ ግልፅ ሆኗል።
በዚህም መሠረት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉተን ውሳኔዎች አሳልፏል።
- የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግሥቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የተጀመረው ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም። ሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልፅ መስፈርት መሠረት አሻሚ ሁኖ ለተገኙ አንቀፆች እንጂ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ውጭ ለማራዘም ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፍያ በአስቸኳይ ቆሞ አሁንም የኮረና ወረርሽኝን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ሆነ ሀገራዊ ምርጫን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውሰጥ በመሆን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ተደርጎ ሀገርን ከለየለት የጥፋት አደጋ ለመታደግ እንዲቻል መድረክ እንዲመቻች ይጠይቃል።
- የእንደዚህ ዓይነቱ መድረክ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የብልፅግና ፓርቲ ነፃና ግልፅ ምርጫ የመምራት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ብቃት የሌለው በመሆኑ ይህንን ለማስፈፀም የሚችል የተለየ አደረጃጀት የመፍጠር አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስከበር አስፈላጊነት በቂ ትኩረት በሰጠ መልኩ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲጀመር ጥሪውን ያቀርባል።
- ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወትሮውኑም ገዢውን ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሶ ራሱን በወራሽነት ያስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ከመስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ጠባብም ቢሆን ዕድል የማይኖር በመሆኑ የሀገሪቱ ችግር ለመፍታት ወደሚከብድ ችግር የምትገባበት ዕድል መፈጠሩ የማይቀር ይሆናል። ህወሓት እንደዚሁ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጥረው የሚችለውን ትርምስ ለማስወገድ በሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶች ውስጥ ድርሻውን በቀናነት ለመጫወት ዝግጁ ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ በተከለው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደዋዛ እንዲጣልበት አይፈቅድም። ለዚህም ሲባል ከትግራይ ሕዝብና ለትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ ዕውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ ይህንኑ የሕዝባችንን መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ወስኗል። ይህ እንቅስቃሴ የፀረ ኮረና ወረርሽኝ ዘመቻችንን እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸውን ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎችን ባሟላ መልኩ የሚፈፀም ይሆናል።
- የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ህልውናቸው ያረጋገጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በጠራራ ፀሀይ ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር በማስቆም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳቸውን እንዲያርቁ በዚህ አጋጣሚ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ጥሪውን ያቀርባል።
- በመጨረሻም ህወሓት ሆነ የትግራይ ሕዝብ የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን ያረጋገጠውን ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማዳን በሚደረገው ርብርብ መሰል አጀንዳ ከሚያራምዱ ብሔር ብሔረሰቦችም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን አሁንም በድጋሚ ማረጋገጥ እንፈልጋለን።
የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ጽ/ቤት
ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.February 24, 2020 at 12:53 am #13693Topic: አቶ በለጠ ሞላ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ
in forum Semonegna StoriesAnonymousInactiveየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያካሄደውን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀመንበርነት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን በአቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን በመተካት፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አመራሮችን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቀቀ።
ደብረ ብርሃን (አብን) – የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኘበት በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አብን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለሥ በሚያስችለውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ይገኝ ዘንድ ላለፉት ጊዜያት የመጣበትን መንገድ መርምሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ ማሻሽያ መዘጋጀቱን ገለፀው በዚህ ላይ ጠቅላላ ጉባዔው በደንብ ተወያይቶ አቋም እንዲይዝበት ጠይቀዋል።
ጉባዔው በመጀመረያ ቀን ውሎው የአብን መዋቅራዊ ማሻሽያ (reform) አስፈላጊነትና አላማ፣ የንቅናቄው ጥቅል የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የፋይናንስ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት፣ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሪፖርት፣ የተሻሻለው የንቅናቄው መተዳደሪያ ደንብና ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኃላ አፅድቋል።
ጠቅላላ ጉባዔው 5 ተለዋጭ አባላት ያሉት 45 የንቅናቄውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥም መርጦ ያፀደቀ ሲሆን የተመረጡት አባላትም የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጠዋል። በተጨማሪም በሊቀመንበሩ የቀረቡለትን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚዎችን አፅድቋል። በዚህም መሠረት 9ኙ የአብን ሥራ አስፈፃሚ አመራሮች፦
- አቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን – ሊቀመንበር፣
- አቶ የሱፍ ኢብራሂም – ምክትል ሊቀመንበር፣
- አቶ አዲስ ኃረገወይን – የፖሊሲ ስትራቴጂ ኃላፊ፣
- አቶ ጣሂር ሞሐመድ – የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
- ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም – የውጭ ጉዳይ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት
- አቶ ጋሻው መርሻ – የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣
- አቶ መልካሙ ፀጋዬ – የፅሕፈት ቤት ኃላፊ፣
- አቶ ጥበበ ሰይፈ – የሕግ እና ሥነ-ምግባር ኃላፊ፣ እና
- አቶ ክርስቲያን ታደለ – የፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው።
ምንጭ፦ አብን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦
- የህወሓት አመራሮችና አባላት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ህወሓት የሰጠው መግለጫ
- ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ
- ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ መፍርሱን እና ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ንብረት እንዲከፋፈል ምርጫ ቦርድ አጸደቀ
- በኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ― ኦነግ
- በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው! የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
February 4, 2020 at 1:32 pm #13511SemonegnaKeymasterየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ሕጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጠ። ይህንንም ተከትሎ አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ እና ራሱን ያገለለው ህወሓት ንብረት እንዲከፋፈሉ ቦርዱ ወስኗል።
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ) – የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ያሳወቀ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ቦርዱ) ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ አቅርበዋል።
የግንባርን (የጥምረት ፓርቲን) መፍረስ የመወሰን ስልጣን የቦርዱ በመሆኑ፥ ግንባሩም ሆነ ህወሓት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም ቦርዱ ሁለቱ ሊቃነመናብርት ያቀረቧቸውን የጽሁፍ ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ “ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይሆናል?” በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
በመሆኑም ቦርዱ የግንባሩ አባል ሦስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመሥረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሠራረት ከሚያሳየው መዝገብ ተረድቷል። በመሆኑም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። የግንባሩ መፍረስ ተከትሎ ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተረድቷል።
በመሆኑም የኢህአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሦስቱ ፓርቲዎች (ማለትምየአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/) “ብልጽግና ፓርቲ” የሚባል አዲስ ፓርቲ መመሥረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ በሕጉ መሠረት በብልጽግና እና በህወሃት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል። በመሆኑም ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።
- ብልጽግና እና ህወሃት የኢህአዴግ ንብረት እና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
- በኢህአዴግ ስም (የተመዘገበ) ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
- ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት ሦስት ሩብ ያህሉ (¾ ተኛው) ለብልጽግና ፓርቲ (የሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ሩብ ያህሉ (¼ተኛ) ደግሞ ለህወሃት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሠረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ፣
- ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በሕጉ መሠረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል። (ውሳኔው በጽሁፍ የሚደርሳቸው ይሆናል)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ -
AuthorSearch Results
Search Results for 'ህወሓት'
-
Search Results
-
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያካሄደውን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀመንበርነት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን በአቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን በመተካት፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አመራሮችን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቀቀ።
ደብረ ብርሃን (አብን) – የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኘበት በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አብን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለሥ በሚያስችለውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ይገኝ ዘንድ ላለፉት ጊዜያት የመጣበትን መንገድ መርምሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ ማሻሽያ መዘጋጀቱን ገለፀው በዚህ ላይ ጠቅላላ ጉባዔው በደንብ ተወያይቶ አቋም እንዲይዝበት ጠይቀዋል።
ጉባዔው በመጀመረያ ቀን ውሎው የአብን መዋቅራዊ ማሻሽያ (reform) አስፈላጊነትና አላማ፣ የንቅናቄው ጥቅል የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የፋይናንስ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት፣ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሪፖርት፣ የተሻሻለው የንቅናቄው መተዳደሪያ ደንብና ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኃላ አፅድቋል።
ጠቅላላ ጉባዔው 5 ተለዋጭ አባላት ያሉት 45 የንቅናቄውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥም መርጦ ያፀደቀ ሲሆን የተመረጡት አባላትም የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጠዋል። በተጨማሪም በሊቀመንበሩ የቀረቡለትን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚዎችን አፅድቋል። በዚህም መሠረት 9ኙ የአብን ሥራ አስፈፃሚ አመራሮች፦
- አቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን – ሊቀመንበር፣
- አቶ የሱፍ ኢብራሂም – ምክትል ሊቀመንበር፣
- አቶ አዲስ ኃረገወይን – የፖሊሲ ስትራቴጂ ኃላፊ፣
- አቶ ጣሂር ሞሐመድ – የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
- ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም – የውጭ ጉዳይ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት
- አቶ ጋሻው መርሻ – የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣
- አቶ መልካሙ ፀጋዬ – የፅሕፈት ቤት ኃላፊ፣
- አቶ ጥበበ ሰይፈ – የሕግ እና ሥነ-ምግባር ኃላፊ፣ እና
- አቶ ክርስቲያን ታደለ – የፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው።
ምንጭ፦ አብን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦
- የህወሓት አመራሮችና አባላት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ህወሓት የሰጠው መግለጫ
- ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ
- ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ መፍርሱን እና ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ንብረት እንዲከፋፈል ምርጫ ቦርድ አጸደቀ
- በኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ― ኦነግ
- በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው! የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ሕጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጠ። ይህንንም ተከትሎ አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ እና ራሱን ያገለለው ህወሓት ንብረት እንዲከፋፈሉ ቦርዱ ወስኗል።
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ) – የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ያሳወቀ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ቦርዱ) ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ አቅርበዋል።
የግንባርን (የጥምረት ፓርቲን) መፍረስ የመወሰን ስልጣን የቦርዱ በመሆኑ፥ ግንባሩም ሆነ ህወሓት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም ቦርዱ ሁለቱ ሊቃነመናብርት ያቀረቧቸውን የጽሁፍ ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ “ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይሆናል?” በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
በመሆኑም ቦርዱ የግንባሩ አባል ሦስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመሥረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሠራረት ከሚያሳየው መዝገብ ተረድቷል። በመሆኑም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። የግንባሩ መፍረስ ተከትሎ ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተረድቷል።
በመሆኑም የኢህአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሦስቱ ፓርቲዎች (ማለትምየአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/) “ብልጽግና ፓርቲ” የሚባል አዲስ ፓርቲ መመሥረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ በሕጉ መሠረት በብልጽግና እና በህወሃት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል። በመሆኑም ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።
- ብልጽግና እና ህወሃት የኢህአዴግ ንብረት እና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
- በኢህአዴግ ስም (የተመዘገበ) ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
- ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት ሦስት ሩብ ያህሉ (¾ ተኛው) ለብልጽግና ፓርቲ (የሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ሩብ ያህሉ (¼ተኛ) ደግሞ ለህወሃት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሠረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ፣
- ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በሕጉ መሠረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል። (ውሳኔው በጽሁፍ የሚደርሳቸው ይሆናል)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ