-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል ኩዊንስ ሱፐርማርኬት እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የቀራኒዮ ፕላዛ ቅርንጫፍ ሱፐርማርኬቱን አስፈላጊዎቹን ሕጋዊ መስፈርቶች አሟልቶ በማደራጀት ማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁሉን በአንድ ባቀፈውና ማራኪ በሆነው በኮልፌ ቀራኒዮ ፕላዛ ቅጥር ጊቢው አስመረቀ።
በዚሁ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር፤ በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ደንቦችን መሠረት ባደረገ ዲዛይን የተሠራው፤ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት አካሄዱም ለደምበኞች ቀላልና ምቹ የግብይት ሁኔታ ለማስፈን ትኩረት የሠጠ ነው ብለዋል።
ሱፐርማርኬቱ በሚገኝበት በቀራንዮ ፕላዛ፣ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የነዳጅ ጣቢያ/ማደያና የተሽከርካሪ እጥበትና መለስተኛ ጥገና አገልግሎት መስጫ እና በትንሹ ከ150 በላይ መኪኖች ማቆሚያ፣ የእርሻ ምርቶች መሸጫ፣ ካፌና ሱቅ፣ ባንክ፣ እና ሁለገብ አዳራሽ መኖሩን የገለጹት ዶ/ር አረጋ፥ እነዚህ በአንድ አካባቢ መደራጀታቸው ደንበኞቹን በአንድ የንግድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ፣ሱፐርማርኬቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀ-መንበርና ባለሀብት ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በቅድሚያ ምስጋና ያቀረቡት ዶ/ር አረጋ፥ በዛሬው ቀን በመካከላችን ለተገኙት ወንድማቸው ለሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ ለረዱን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የሚመለከታቸው ሠራተኞች፣ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ መብራት ኃይል፣ የቴሌፎንና የውሃ ተቋማት፣ የአዲስ አበባ የመንገድ ሥራዎች ተቋም፣ የአካባቢው የፖሊስ እና የፀጥታ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ላደረጉልን መተባበር ከፍተኛ ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል።
ዶ/ር አረጋ በዚሁ ንግግራቸው፥ የኩዊንስ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ለቅድመ መደበኛ አገልግሎት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ ለሥራ ማስኬጃ እና ለሽያጭ የሚያገለግሉ ዕቃዎች (መደርደሪያዎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣…) ግዢ፣ የሲስተም ዝርጋታ ወጪን ጨምሮ፣ ለሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ጠቅላላ ወጪ 59.3 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስረድተው፤ ሕንፃው በ37.7 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱንና የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ንብረት በመሆኑ፣ ኩዊንስ በኪራይ እንደሚገለገልበት አስታውቀዋል።
የሪቴል ግሩፕ ፕሪንሰፓል ኦፕሬሽን ኦፊሰር ወ/ሮ ታህሳሥ ወንድምነህ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ሰኔ 25 ቀን 2002 ዓ.ም. 46 ቋሚ እና 5 ኮንትራት፣ በድምሩ 51 ሠራተኞች በመያዝ የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው፥ ኩባንያው የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶችን (የዶሮ፣ የወተት እና የሥጋ ተዋጽዖዎችን)፣ የእርሻ ምርቶችን (ሰብሎች፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና አበባዎች)፣ የባሕር ምግቦች (ዓሣ)፣ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች (ሣሙና….) የታሸጉ ምርቶች፣ መጠጦች እና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችን (የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን እና የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎች) በችርቻሮ እና በጅምላ በመሸጥ እና በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ወ/ሮ ታህሳሥ በዚሁ ንግግራቸው፤ ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ የካፒታል መጠኑ ወደ ብር 23,786,000፣ የሠራተኞቹ ብዛት ወደ 142 (132 ቋሚ እና 10 ኮንትራት) ማደጉን አመልክተው፤ ዓመታዊ ሽያጩም ሥራ ሲጀምር ከነበረው ከብር 12,192,000 ወደ ብር 157,000,000 ማደጉን አሰታውቀዋል።
አያይዘውም ኩባንያው ቅርንጫፎቹን ወደ ሰባት በማሳደግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ እና ተጨማሪም አንድ የዳቦ ማምረቻና መሸጫ በመቻሬ ቅርንጫፍ በማቋቋም ለሠራተኞችና ለኀብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አስረድተው፤ ሱፐርማርኬቱ ለ50 ተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ዓመታዊ ሽያጩም ብር 75,000,000 እንደሚሆን፤ የኩባንያውን ዓመታዊ የሽያጭ መጠንንም በግማሽ በማሳደግ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አሰታውቀዋል።
ወ/ሮ ታህሳሥ ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና ባለሀብት ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ፣እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ የፕሮጀክት ሀሳብ በማቅረብ፣ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ በፕሮጀክቱ ሂደትም ያልተቋረጠ የዕለት ተዕለት ክትትል በማድረግ፣ የቅርብ አመራር በመስጠት እና አቅጣጫ በማስያዝ ፕሮጀክቱ በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላበቁት ለዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና ፕሬዚዳንት፤ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለፕሮጅክቱ መሳካት አሰተዋጽኦ ያበረከቱ ድርጅቶችና ግለሰቦች፤ የተዘጋጀላቸውን ሠርቲፊኬት ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ እጅ ተቀብለዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ፤ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ደንበኞች በተገኙበት ተካሂዷል።
ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢትዮጵያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አድማስ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የጥራት ደረጃዎች ኤጀንሲ የተዘጋጁት ስታንዳርዶች በተገቢው መልክ በመፈፀም በ2012 ዓ.ም. በተቋም ደረጃ አይ ኤስ ኦ የምስክር ወረቀት (ISO Certificate) ለማግኘት የሚያስችለውን ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብሩ አስማረ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት አሰጣጥ ጥራት ደረጃውን በማሳደግ ለዚሁ ተገቢ የሆነ እውቅና ለማግኘት የሚያስችለው ብቃት ላይ ይገኛል።
በቴክኒክና ሙያ ኮሌጀች የትምህርት ሥልጠና ጥራት ለማስጠበቅና በየሙያ ደረጃው የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ አድርጓል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የማስልጠኛ መሳሪያዎች (Training Teaching and Learning Materials /TTLM) ዝግጅት በሁሉም የብቃት አሃዶች ማዘጋጀቱንና የትብብር ሥልጠናን አፈፃፃምን የሚያሻሻሉ የተለያዩ ተገባራት እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ብሩ አስማረ አያይዘውም የምዘና ሥርዓቱን ለማጠናከርና በዩኒቨርሲቲው የሚተገበረውን የተከታታይ ማጠቃለያና ተቋማዊ ምዘና ዝግጅትና አፈፃፃም ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን መደረጉንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የደረጃ ኤጀንሲ (Ethiopia Standard Agency) የተዘጋጁ የጥራት ምዘናዎችን (stadards) ማለትም የስርዓተ ትምህርት (Curriculum Requirement ES. 6259-1: 2018)፣ የመሣሪያዎች ማሽነሪዎች (Tools, Machines and Equipment Requirement ES 6259-8: 2018)፣ የምዘናና የማሰልጠኛ መሣሪያዎች (Assessment & Instructional Materials ES 6299-9: 2011 ) እና የመሳሰሉትን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አቶ ብሩ ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም በዩኒቨርሲቲው የሚስጠውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በምርምር ለማገዝ እንዲቻል የተለያዩ ጥናቶች በማካሄድ ያሉ ችግሮችን የመለየት ሥራ በየጊዜው እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጥቅምት ወር 1990 ዓ.ም. “አድማስ የቢዝነስ ማሰልጠኛ ማዕከል” በሚል ሥራውን የጀመረው ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም፥ በፍጥነት ራሱን በማሳደግ በሚያዝያ ወር 1991 ዓ.ም. የኮሌጅነት ደረጃ አግኝቶ ስሙን “አድማስ ኮሌጅ” ብሎ በመሰየም ሥራውን አስፋፋ። ቀጥሎም በመጋቢት ወር 1999 ዓ.ም. “አድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ” በሚል ስም የትምህርትና የስልጠና ተግባሩን አሳደገ። የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2009 የሚጠይቃቸውን አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች በሙሉ በማሟላት በሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም. የሙሉ ዩኒቨርሲቲ ደረጃን አግኝቶ “አድማስ ዩኒቨርሲቲ” ተባለ።
አድማስ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮን ተመራቂዎችን ጨምሮ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከ70 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና እርከኖች አስመርቋል።
በአሁኑ ወቅትም በውጭ/ጎረቤት ሀገራት ሶማሌላንድና ፑንትላንድ በሚገኙት ካምፓሶቹ ያሉትን ጨምሮ በጠቅላላው ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው።
ክበቡ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እና ባህል እንዲሁም ተዛማጅ እሴቶችን በማስተዋወቅ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የነበረውን ፍቅር፣ ሰላምና አብሮ የመኖር እሴት ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ጠንክሮ እንደሚሠራ እምነታቸው መሆኑን የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።
ድሬ ዳዋ (ሰሞነኛ) – “ቋንቋችንን፣ ባህላችንን፣ እሴቶቻችንንና ታርካችንን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የአሁኑ ትውልድ ግዴታ ነው።” በሚል መሪ ቃል የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እና ባህል ማበልፀጊያ ክበብ በድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተቋቁሟል። በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እና ባህል ክበብ ምሥረታ ቀደም ብለው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ማሞ፣ የኦሮሞ ቋንቋ እና ባህል ክበብ ፕሬዝዳንት ተማሪ ገሊማ፣ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ጥበቡ ሙሉጌታ እንዲሁም የ2011 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተማሪ ቢቅላ ጋሮምሳ የክበቡን መመሥረት በማብሰር መርሃ ግብሩን ይፋ አድርገዋል።
ክበቡ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እና ባህልን በማስተዋወቅ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የነበረውን ፍቅርና ሰላም እንዲሁም አብሮ የመኖር እሴት ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ጠንክሮ እንደሚሠራ እምነታቸው መሆኑን የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ማሞ ተናግረዋል። ዶ/ር ያሬድ አያይዘውም ክበቡ ለሌላ ዓላማና እኩይ ተግባር እንደማይውል ሙሉ እምነታቸው መሆኑን በመግለጽ፤ ግንባር ቀደም ክበብ በመሆኑ ሌሎች ብሔሮችም ተመሳሳይ ጥያቄ ይዘው ቢመጡ ክበቡ እነሱን የማገዝ ሃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል። በመጨረሻም ዶ/ር ያሬድ ተማሪዎቻችን ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ በመምጣታቸው የራሳቸውን ቋንቋና ባህል ለማስተዋወቅ ክበብ ለመመሥረት ቢፈልጉ ዩኒቨርሲቲው እኩል ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
በምስረታው ላይ ታዋቂ ሰዎች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፎበታል። የኦሮሞን ባህል ከማስተዋወቅ አንጻርም የኦሮሞ ባህላዊ ምግቦች ቅምሻ ሥነ-ስርዓትና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አለባበስ ትዕይንትም ተካሂዷል። በእለቱ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ፣ ባህልና ታርክ ላይ የተመሠረተ ጥናታዊ ጽሁፍ በዶ/ር ተሾሜ ኤጌሬ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ገዳ እንስቲትዩት ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር፡ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋና ታርክ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል።
የዩኒቨርሲቲው የአፋን ኦሮሞ ቋንቋና ባህል ክበብ ፕሬዝዳንት እና መሥራች ተማሪ ገልማ ብዱ እንደተናገረው ክበቡ ኃይማኖት ተኮር ነገሮችን ከማንፀባረቅና ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት የፀዳመሆኑን በመግለጽ የኦሮሞን ቋንቋ እና ባህል ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በማዋሀድ ልምድ ልውውጥ በማድረግ በልዩነታችን ውስጥ ውበት አንድነታችን የሚጠናከርበትና የሚካሄድበት ክበብ ነው ብሏል። በክበቡም የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ተወላጆች አባል ሆነው መሳተፍና አኩሪ የኢትዮጵያዊነት መልካም ባህላቸውን ማበልጸግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ስር ክበባትን ማደራጀት በሚፈቅደው መመሪያ መሰረት የኦሮምኛ ቋንቋና ባህልን ለማበልፀግ እንደ አንድ ክበብ የኦሮምኛን ቋንቋና ባህል ክበብ ሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመሥርቷል። የክበቡም ምሥረታ በአፍራን ቀሎ ባንድ ጣዕመ ዜማ፣ መነባነብ በገጣሚ እና ደራሲ ሲሳይ ዘለገሃሬ እና በዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች ቀርቧል። በዩኒቨርሲቲያችን እስታዲየም ከአዲስ አበባ በተጋበዙ ታዋቂ የኦሮምኛ ዘፋኞች፣ የቀድሞ የአፍራን ቀሎ መሥራቾችና ዘፋኞች ተገኝቷል። እንዲሁም የማነቃቂያ ንግግሮች፣ የዕውቅና እና የስጦታ ሥነ-ስርዓቶችም ተካሂዷል።
ምንጭ፦ ድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
አዲስ አበባ – የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮቸ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ተጠቃሚነት ለማሳጣት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረን ጨዋታ በዝግ ወይም አዳማ ከተማ ላይ ተጫወቱ በማለት ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጎል ብሏል።
ይህን ጨዋታ ከዚህ በፊት የተቋረጡ የሌሎች ክለቦች ጨዋታወችን ባስተናገደበት ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አላስተናገደም ሲል በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታውን አቅርቧል።
እንዲሁም በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የተሰጠው ፎርፌ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ መሆኑንም ነው በመግለጫው ያመላከተው።
አዲስ ከመጡት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመተባበር፣ በመቻቻል እና በመተጋገዝ ለመሥራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷልም ነው ያለው።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ. / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ኢትዮጵያ ቡና የአዲስ አበባ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ
- ከመጣንበት መንገድ በላይ የሚቀረን ይከብዳል!! (ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች)
- የኢትዮጵያ ቡና ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር አዳማ ላይ አልጫወትም አለ፤ በዒድ አል ፈጥር ምክንያት ጨዋታው በድጋሚ ተራዝሟል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በአዳዲስ የቢዝነስና የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች አፍላቂነታቸውና በፈር-ቀዳጅ ኢንቬስተርነታቸው (entrepreneur) በሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስትና ባለሃብት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሕይወት ታሪክና ሥራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው < የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > የተሰኘው የሕይወት ታሪክ (biography) መጽሐፍ ከሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል።
አጠቃላይ ዝግጅቱ ከስድስት ዓመታት በላይ ፈጅቶ የተጠናቀቀው ይህ መጽሐፍ፥ ከወላጆቻቸው የበስተጀርባ ታሪክ አንስቶ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን የልጅነት ሕይወትና አስተዳደግ፣ የወጣትነት ዘመንና የትምህርት ቆይታ እንዲሁም ወደ አሜሪካ አቅንተው ከዘበኝነትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እስከ ግዙፉ የዓለማችን የፋይናንስ ማዕከል ዎልስትሪት (Wall Street) የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ስመጥር ባለሙያነት የዘለቁበትን የረጅም ዓመታት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን፥ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ከ20 ዓመታት በላይ የተጓዙበትን በስኬትና በውድቀት የታጀበ፣ ፈተናና ውዝግብ ያልተለየው ረጅም የሕይወት ጎዳናም በዝርዝር ይዳስሳል።
◌ ኤርሚያስን የትኛው “ወንጀል” ሊያሳስረው ይችላል?
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የወጠኗቸውን አዳዲስና ሰፋፊ የፋይናንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕቅዶቻቸውን ከዳር ለማድረስ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ ያጋጠሟቸውን እሾህ አሜካላዎች፣ የተጋፈጧቸውን ፈተናና እንቅፋቶች በዝርዝር የተረኩበት መጽሐፉ፣ ከባለታሪኩ የግልና የሥራ ሕይወት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማይታወቁ በርካታ አዳዲስና አነጋጋሪ መረጃዎችን ያካተተ ነው።
በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውና 12 ዋና ዋና ምዕራፎች ያሉት < የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፣ “ማረፊያ አንቀጾች” እና “ድህረ-ታሪክ” የሚሉ ተጨማሪ ንዑሳን ክፍሎችን ጨምሮ አጠቃላይ የገጽ ብዛቱ 394 ነው።
< የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ መጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች፣ በአዲስ አበባ በሁሉም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎችና በሸዋ ሱፐርማርኬቶች፣ በስልክ ትዕዛዝ የቤት ለቤት እደላና በአማዞን ድረ-ገጽ አማካይነት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሚሸጥ ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋውም 300 ብር እንደሆነ ተነግሯል።
◌ ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ – (ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የታሸገ ውሃ “ሃይላንድ” ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም “ዘመን ባንክ” እና “አክሰስ ሪል ስቴት”ን ጨምሮ ባቋቋሟቸው የተለያዩ ኩባንያዎች የሚታወቁት አወዛጋቢው ኢኮኖሚስት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፥ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በአሁኑ ወቅትም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ጸሃፊው ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው ከዚህ ቀደም “መልስ አዳኝ” እና “ባቡሩ ሲመጣ” የተሰኙ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፥ ለ54 ተከታታይ ሳምንታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተላለፈውንና “ስውር መንገደኞች” የተሰኘውን ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማብቃቱም ይታወሳል።
ለተጨማሪ መረጃ፦
Email: yemayseberew@gmail.com, amelgaermiyas283@gmail.com
Facebook: Ermyas Tekil Amelga
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሰሞነኛ የተማሪዎች ምርቃት — በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች (የግል/ የመንግስት) የተማሪዎች ምርቃት።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ። በተመሳሳይ የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎችን አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው በአምስት ኮሌጆች ውስጥ ያስተማራቸውን ተማሪዎች 1 ሺህ 112 በመጀመሪያ ዲግሪ እና 201 በሁለተኛ ዲግሪ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ብርሃኑ የተማሪዎች ምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነት ማገልገል አለባቸው።
”ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እና በኢንጅነሪንግ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚያስተምር በመሆኑ ተማሪዎችም በዚሁ መስክ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን መሥራት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን እንደሚያካሂድና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ተመራቂዎች በበኩላቸው ባገኙት ዕውቀት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሪፖርተር እንደተናገሩት፥ ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመጥቀም ይሠራሉ። ወደ መንግስትም ሆነ ግል ተቋማት በመሄድ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ያገኙትን ትምህርት በተግባር ማስደገፋቸውን ገልጸው በኮንስትራክሽ ዘርፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ የተመረቁ ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት ለማህበረሰቡ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 578 ዕጩ መምህራንን በተመሳሳይ ዕለት በዲፕሎማ አስመርቋል።
ከዕውቀት ባለፈ በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሠሩ የኮሌጅ ተመራቂ እጩ መምህራን ተናግረዋል።
ከተመራቂ መምህራን መካከል በሒሳብ ትምህርት ክፍል የተመረቀችው መምህርት ስንቂት ማሙየ እንዳለችው፥ በቀጣይ ዕውቀቷን ለተማሪዎች ከማካፈል በተጨማሪ ሀገራቸውን የሚወዱና በሥነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በኃላፊነት እንደምተሠራ ተናግራለች።
“ሀገራችን ከመምህራን ብዙ ትጠብቃለች፤ እኛ መምህራንም ትውልድን በዕውቀት አንፀን በመቅረፅ ለሀገራቸው እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ አለብን” ብላለች።
በማኅበራዊ ሳይንስ ዕጩ መምህርና በኮሌጁ 3 ነጥብ 8 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው መንግስቱ ማሬ በበኩሉ ቀጣዩ ትውልድ በዕውቀት የዳበረና ማኅበረሰቡን አገልጋይ እንዲሆን በተመደበበት የሥራ ቦታ ተማሪዎቹን እንደሚያበቃ ተናግሯል።
“መመረቅ የመጨረሻ ሳይሆን ለአስተማረችኝ ሀገሬና ወገኔ አገልግሎት መስጠት የምጀመርበት ነው” ያለው ተመራቂው ሲሆን፥ በቀጣይም ዕውቀቱን በማዳበር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን አስረድቷል።
“የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ዕውቀትንና ማኅበራዊ ግብረ-ገብነትን ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ በቀጣይ የሥራ ዘመኔ የምከተለው መርህ ነው” ያለችው ደግሞ በሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ዘርፍ የተመረቀችው መምህርት መሰረት የኔሁን ናት።
የኮሌጁ ዲን አቶ ስንታየሁ ነጋሽ በበኩላቸው ኮሌጁ ከተቋቋመ 38 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው በእነዚህ ዓመታት ከ44 ሺህ በላይ መምህራንን ማስመረቁን ተናግረዋል። በዕለቱ ከተመረቁ 1ሺህ 578 እጩ መምህራን መካከልም 798ቹ ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ ዲኑ ገለጻ፥ ተመራቂዎቹ በትምህርት ቆይታቸው በቂ ዕውቀት ይዘው መውጣት የሚያስችላቸውን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት አግኝተዋል። ምሩቃን በቀጣይ ሙያውን አክብረው በመሥራትና ራሳቸውን ወቅቱ በሚፈልገው ልክ አቅማቸውን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ዓላማው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉን በኢፌዴሪ ጠቅላይ የሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። አቶ ንጉሱ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ላይ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) በሰጡት መግለጫ በክልሉ መንግስት ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል።
በተደራጀ ሁኔታ በመንግስት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረው የተደራጀ እንቅስቃሴ ከሽፏል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ።
የአማራ ክልል ወደ መረጋጋት እየመጣ ባለበትና እና ሕዝቡ ቀደም ሲል ያነሳ የነበረውን የህግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ባለበት ወቅት የተሰነዘረው ጥቃት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ላይ የተሞከረ ነው ብለዋል።
ሙከራው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት ይህን መሰሉን ተግባር የመግታት ሥራ እንደሚሠራና ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጸረ-ህገ መንግስትና መፈንቅለ መንግስቶች እንዲሁም በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፥ ክልሉን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ቴለቭዥን ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉትን አጭር ቃል ምልልስ እዚህ ጋር በመጫን ያዳምጡ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ!
- ከዴሞክራሲና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች
- አቶ አዲሱ አረጋን ነጻ ያወጣችው የእስክንድር ፌስታል
- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተቀሰቀሰ ረብሻ የአንድ ተማሪ ህይወት አለፈ
- ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል