-
Search Results
-
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሥር ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጎንደር ዩንቨርሲቲ በርካታ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ መጻህፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ጎንደር ዩንቨርሲቲ የግእዝ ቋንቋ በመጀመሪያ ዲግሪ መስጠት ሊጀምር ነው
ጎንደር (ኢዜአ) – ጎንደር ዩንቨርሲቲ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግእዝ ቋንቋ ለመታደግ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ የቋንቋ ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።
የጎንደር ዩንቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የግእዝ ቋንቋ ባለቤት ብትሆንም ለቋንቋው ማደግና መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። “በዚህም ሳቢያ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ከመሆኑም በላይ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የብራና መጻፍትን ለጥናትና ምርምር ስራ ለማዋል አልተቻለም “ብለዋል።
ዘመናት የተሻገሩና በቋንቋው የተጻፉ ለዘመናዊ ሕክምና ሙያ የሚያግዙ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ መጻሕፍት በኃይማኖት ተቋማትና ገዳማት ተወስነው መኖራቸውን አመልክተዋል።
ዩንቨርሲቲው እነዚህን ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ መጻህፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በትምህርት ዘመኑ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ያመለከቱት ዶክተር ካሳሁን፥ ትምህርቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውም በኤክስቴንሽንና በክረምት መርሃ ግብሮች መሆኑን አስረድተዋል። ትምህርቱ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ሲሄድ መደበኛ ተማሪዎችን ጭምር በቀጣይ በግእዝ ቋንቋ አሰልጥኖ ለማስመረቅ መታቀዱን አመልክተዋል።
- የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሥር ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጎንደር ዩንቨርሲቲ፥ በአጠቃላይ 87 የመጀመሪያ ዲግሪ፤ 158 ሁለተኛ ዲግሪና 29 የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዳሉት ተገልጿል። በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን የሚከታታሉ ከ45ሺ በላይ ተማሪዎች በዩንቨርሲቲው ይገኛሉ።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች- አሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሰላማዊ ለማድረግ ተዘጋጅቷል
- ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለነበሩ አርሶ አደሮች ያደረገው ድጋፍ
- ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ክስ መሠረተ
- አድማስ ዩኒቨርስቲ አይ ኤስ ኦ የምስክር ወረቀት (ISO Certificate) ለማግኘት የሚያስችል ሥራ እየሠራ መሆኑን ገለጸ
- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር የ2012 ዓ.ም. መማር ማስተማርና የተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት አደረገ
ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ካምፓስ (Jimma University Addis Ababa Campus) ተማሪዎች የሰጠው መግለጫ
ጉዳዩ፡- ተገቢነት በሌላቸው ጽሁፎችና መግለጫዎች እንዳትደናገሩ ስለማሳሰብ
ጅማ (ጅማ ዩኒቨርሲቲ) – ዩኒቨርሲቲያችን መንግሥት የከፍተኛ ትምህርትን ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በማሳካት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ያለው መሆኑ ከሁላችሁም የተሰወረ አይደለም። የመንግሥትን የትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊነት ከማረጋገጥ አኳያ ዩኒቨርሲቲያችን በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጠውን ትምህርት አድማስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ መምጣቱ የቁርጠኝነቱ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። ይኸውም ዋና መቀመጫው ጅማ ከተማ ሆኖ በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎችና ከአገር ውጪም በሐርጌሳ ጭምር ካምፓሶችንና የትምህርት ማዕከሎችን ከፍቶ ትምህርቱን በማስፋፋት ላይ የሚገኘውም በዚሁ አግባብ ነው።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲያችን የሚያደርገውን ሕጋዊ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና ለማስቆም የሚሞክሩ አካላት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተገንዝበናል። ይኸውም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና ጥቂት የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በኤጀንሲው የፌስቡክ ገጽ እና በግል የፌስቡክ ገጽ በለቀቋቸው መረጃዎች እንዲሁም የፕሬስ ኮንፈረንስ ጠርተው በመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዩኒቨርሲቲያችንን ስም ሲያጠፉና ሲያቆሽሹ መቆየታቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲያችንን ስም ከማጥፋት አልፈው በቁጥር 01/መ-4/2688/11 መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በተፃፈ ደብዳቤ በአዲስ አበባው ካምፓሳችን (Jimma University Addis Ababa Campus) በመማር ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች ጥሪ በማድረግ ወደ ሌላ ተቋም እንደሚያዛውሯቸው በኤጀንሲው የፌስቡክ ገጽ መረጃ ለቀዋል።
ነገር ግን ዩኒቨርሲቲያችን የአዲስ አበባውን ካምፓስ (Jimma University Addis Ababa Campus) የከፈተውም ሆነ ላለፉት ሰባት ዓመታት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ሲሰጥ የቆየው ዩኒቨርሲቲውን እንደገና ለማቋቋም በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 አንቀጽ 2(1) እና አንቀጽ 3 መሠረት ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሆኖ ስለተቋቋመ እና ዋና ግቢው ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎች እና የምርምርና የማሕበረሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን የማቋቋም መብት በሕግ ስተሰጠው ነው። የድጋፍ አገልግሎት ከሚሰጥ የግል ተቋም ጋር ሕጋዊ ስምምነት ተፈራርሞ ለትምህርቱ የሚያስፈልጉ የአገልግሎት ግብአቶችን በማግኘት ላይ ያለው ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 93(1) ስር ማንኛውም የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊ መብት እንዳለው በተደነገገው መሠረት ነው። ይህም ሆኖ በሕግ ድንጋጌዉ ላይ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ትርጓሜ እንዲሰጥ ተጠይቆ ዉጤቱን እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት ሁከት ለመፍጠር የሚደረገዉ እንቅስቃሴ አግባብነት የጎደለዉ ነዉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ሥልጣንና ተግባር ኤጀንሲው በተቋቋመበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 261/2004 አንቀጽ 6 እና በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 89 ስር የተዘረዘረ ሲሆን በሁለቱም ሕጎች ኤጀንሲው ተማሪዎችን ከአንድ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነጥቆ ለሌላ ተቋም ለመስጠትም ሆነ አንድን ካምፓስ ለመዝጋት የሚያስችል ሥልጣንና ኃላፊነት አልተሰጠውም። ስለሆነም ኤጀንሲውንና የሥራ ኃላፊዎቹ በዩኒቨርሲቲያችን ዙሪያ የሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች በሙሉ ተገቢነት የሌላቸዉ እና በሌላቸው ስልጣን የተፈፀሙ በመሆናቸው በሕግ የሚያስጠይቁ ናቸው።
ውድ ተማሪዎቻችን! ዩኒቨርሲቲያችን በአዲስ አበባ ካምፓስ ከፍቶ ለተማሪዎች ትምህርት ሲሰጥ የቆየው በሕጋዊ መንገድ መሆኑን እያረጋገጥን ይህንኑ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን በመጋፋት ኤጀንሲውና የሥራ ኃላፊዎቹ በማድረግ ላይ ያሉት አግባብ የሌለዉ እንቅስቃሴ ሕዝብና መንግሥት እንዳይረጋጋ የሚያደርግ በመሆኑ በፅኑ የምናወግዘው ነው። ዩኒቨርሲቲያችን እስከ አሁን ድረስ በኤጀንሲው በበላይ የሥራ ኃላፊዎች ሲፈፀሙ የነበሩትን አግባብነት የሌላቸዉን ተግባራት በትዕግስትና በሰከነ መንፈስ ሲከታተልና መፍትሄ ሲያፈላልግ የቆየ ሲሆን፤ የአሁኑ ተግባር ግን የዩኒቨርሲቲውን ህልውና የሚፈታተንና የኤጀንሲውን የስልጣን እና ኃላፊነት ገደብ የጣሰ በመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲያችን ጉዳዩን ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት መፍታትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለመፈፀም ቁርጠኛ አቋም የያዘ መሆኑን እየገለፅን፤ በኤጀንሲው ጥሪ ሳትረበሹና ሳትሳሳቱ ዩኒቨርሲቲዉ ከተማሪ እና ከወላጅ ተወካዮች ጋር ባደረገዉ ዉይይት መሠረት ጉዳዩን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አዉቃችሁ በትዕግስት እንድትጠብቁን እናሳስባለን።
ምንጭ፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Topic: የ10ኛ ክፍል ውጤት ለተማሪዎች ይፋ ተደረገ
የ10ኛ ክፍል ውጤት ፈተናውን ለተፈተኑ ለተማሪዎች ይፋ ተደረገ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) የ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ10ኛ ክፍል ውጤት መስከረም 02 ቀን 2012 ዓ.ም. ከ10 ሰዓት ጀምሮ ይፋ እንደሚሆን ባስታወቀው መሠረት ተማሪዎች በኤጀንሲው ድህረ ገጽ http://www.app.neaea.gov.et ወይም በአጭር የጽሁፍ መልእክት 8181 ላይ ID- በማለት አድሚሽን ቁጥራቸውን በማስገባት መመልከት እንደሚችሉ አሳውቋል።
- መጀመሪያ የኢጀንሲውን ድረ ገጽ http://www.app.neaea.gov.et ይክፈቱ፤
- ቀጥሎ Student Result የሚለውን ይጫኑ፤
- ቀጥሎ Click here for Grade 10 result የሚለውን ይጫኑ።
**. የተማሪዉ/ዋ/ን መለያ ኮድ ወይም አድሚሽን ቁጥር ማስገባት
**. ከተዘረዘሩት የትምህርት አይነቶች ውስጥ የማይቀሩና በሌላ የትምህርት ዓይነት መተካት የሌለባቸው፦ ሒሳብ (Maths), እንግሊዝኛ (English) እና እና የሲቪክስ ትምህርት (Civics) ውጤቶችን በመመዝገብ እና ተጨማሪ 4 (አራት) የተሻሉ የትምህርት ዓይነት ውጤቶችን መዝገቦ በአጠቃላይ 7 የትምህርት ዓይነቶች ሲሆኑ በዚሀም መሠረት የ7ቱን የትምህርት ዓይነቶች አጠቃላይ ድምር ማግኘት አና ለ7 በማካፈል ውጤቱን ማወቅ ይቻላል ማለት ነው።ሌሎች ዜናዎች፦
- የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላይ ውሳኔ ተሰጠ
- NEAEA: የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ይፋ ሆነ
- አሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሰላማዊ ለማድረግ ተዘጋጅቷል
- ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
- አድማስ ዩኒቨርስቲ አይ ኤስ ኦ የምስክር ወረቀት (ISO Certificate) ለማግኘት የሚያስችል ሥራ እየሠራ መሆኑን ገለጸ
- የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንደሚቀርና የሁለተኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ይሆናል
- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር የ2012 ዓ.ም. መማር ማስተማርና የተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት አደረገ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር የ 2012 ዓ.ም. መማር ማስተማርና የተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት አደረገ። ዶ/ር ፋሲል ንጉሴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን ከ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚገቡ አዲስ ተማሪዎች በ4 ዓመት ቆይታ ጊዜአቸው ተማሪዎቹን መሠረታዊ ዕውቀት ሊያስጨብጧቸው የሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች እንደሚሰጡና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የዝግጅት ምዕራፍ እንደተወጠነ ገልጸዋል።
“ለሰላም መደፍረስ መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮችን እየለየን ከሚመለከታቸው ጋር በማቀናጀት መፍትሔ እንዲያገኙ እንጥራለን፤ የመማር ማስተማር ሂደቱ መስመሩን ጠብቆ እንዲሄድ የቁጥጥር ሥርዓቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ ብሔርን፣ ሀይማኖትንና ፖለቲካን መሠረት ያላደረጉ የዶርም ድልድሎችን እናደርጋለን” በማለት ዶ/ር ፋሲል በ 2012 ዓ.ም. ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ የምንከተላቸው አቅጣጫዎች በሚል ርዕስ ባቀረቡት ገለጻ (presentation) ላይ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናም የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን የጠቆሙትን ሲያጠናክሩ “ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በብሔር እየተደራጁ የሚመጡ ማናቸውም ዓይነት የተማሪዎች አደረጃጀት፣ የተማሪዎች ክበባት… ወዘተ አናስተናግድም” በማለት አሳስበዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ተፈጥረው በነበሩ ብሔር-ተኮር የተማሪዎች ግጭትን አስመልክተው ዶ/ር ፋሲል የሚከተለውን ብለዋል፥ “ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ በብሔርና በሃይማኖት መሰባሰብ፣ መከፋፈል፣ መጣላት፣ መደባደብ የንብረት የአካልና የሕይወት መጥፋት ጉዳት የማድረስ እኩይ ተግባራት እንዳይኖሩ ተቋማችን ጠንክሮ ይሠራል” በማለት አስረድተዋል።
በዋነኝነት ለ 2012 ዓ.ም. አዲስ ገቢና ነባር የቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ተማሪዎች የሚደረግላቸውን የአቀባበልና የመተዋወቂያ ገለጻ (orientation) አሰጣጥን አስመልክተው ፕሮፌሰር ጣሰው ሲያብራሩ፥ “ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ መዋል የሚጀምር በተማሪዎች፣ በወላጆቻቸውና በዩኒቨርሲቲያችን መካከል የሚፈረም ውል ይኖረናል፤ ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲያችን እንደገቡ በቅድመ ምረቃ ትምህርት አስተባባሪዎች እና ነባርና ልምድ ባላቸው መምህራን ስለ ዩኒቨርሲቲያችን አጠቃላይ መረጃ ይሰጣቸዋል፤ የመጀመሪያ ዓመት ለሆኑት ተማሪዎች ስለሚወስዷቸው የትምህርት ዓይነቶችና ፋይዳቸው፣ ስለተማሪዎች ሥነ-ምግባር መመሪያና ስለተቋማችን ሥነ-ሥርዓት፣ ሕግና ዲሲፕሊን ጉዳዮች ማብራሪያ እንዲያገኙ ይደረጋል” በሚል ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የምጣኔ ሃብት መምህርና በአሁን ጊዜ የተቋሙ የቦርድ አባል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተቋሙ በሚሻሻልበት ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን ሲሰጡ ተቋሙን በከፍተኛ ደረጃ ለማዘመንና ከሌሎች ታዋቂና ስመ-ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ እንዲመደብ ለማስቻል የመምህራን፣ የአስተዳደር፣ የማህበረሰቡና የመንግሥት ርብርብ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንደሃገር እንድንቀጥል ባሉት ገለጻቸው ሲናገሩ፥ “የሃገሪቱ የትምህርት አወቃቀር የሚሻሻልበትን አቅጣጫ እንቀይስ፤ ፈጣሪና አምራች ዜጋ እንድናገኝ ተማሪዎቻችንን በጥልቀት የሚያስቡና የሚያስተውሉ እናድርጋቸው፤ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ጠቃሚ ሃሳቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበትና ልቆ የተገኘው ሃሳብ ተደማጭነትን አግኝቶ የሚተገበርበት ቁልፍ ቦታ እናድርገው” በሚል ገለጻቸውን ሰጥተዋል።
ምንጭ፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች፣ በውጭ ወራሪ ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሰዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው።
እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱትን ዘመናት የማይሽሩት ታሪካዊ ውለታዎችን ለሀገር ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የጥፋት ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚፈጽሙት ከፍተኛ የሆነ አስተዳደራዊ በደልና የተቀናጀ ጥቃት እያደረሰብን ያለውን መከራና ችግር ቤተ ክርስቲያናችን ባላት ሀገራዊ ኃላፊነት ችግሩን በትዕግስት አሳለፈችው እንጂ እየተፈጸመባት ካለው ግፍና በደል አንጻር ይከሰት የነበረው ችግርና ሀገራዊ ቀውስ በቀለሉ የሚታለፍ ባልሆነም ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እየደረሰብን ያለውን በደልና መከራ ከዛሬ ነገ ይሻላል በማለት ታግሰን ብንችለውም እያደር እየባሰና የችግሩም አድማስ እየሰፋ ሊሄድ ችሏል። ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም ቅሉበተለይ በአሁኑ ወቅት መልኩን እየቀያየረ እና ለዘመናት የቆየ አንድነቷን በማፈራረስ ከቤተ ክርስቲያኒቱም አልፎ ሀገራዊ ቀውስና አለመረጋጋት የሚያስከትል የጥፋት አጀንዳን ባነገቡ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የጀመሩት እንቅስቃሴ ወደከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ እና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በስፋት ከተወያየ የሚከተለውንየአቋም መግለጫ አውጥቷል፡-
- አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ እና ለጥፋት ለተደራጁ ቡድኖች ፖለቲካዊ ሽፋን በመስጠት በልዩ ልዩ ክልሎች የተፈጸሙት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የአገልጋይ ካህናት እና ምእመናን መገደል፣ ዘመን የማይተካቸው የሀገር መገለጫ የሆኑትን ጥንታውያን እና ታሪካውያን ቅርሶችን በማቃጠል ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿን ታሪክ እና ቅርስ አልባ በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን በደሎች እና ግፎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል።
- ቤተ ክርስቲያኒቱ ባህል፣ ቀለም፣ ቋንቋ እና ብሔር ሳትለይ በአንድነት እና በአቃፊነት ለሀገር ውለታ ያበረከተች መሆኗ ተዘንግቶ በእምነት ሽፋን የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች የሆኑ ምእመናን ካደጉበትና ሀብት እና ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ፣ በእምነታቸው ብቻ ተገደው በመደፈር እና ልዩ ልዩ የሥነ ልቦና ጥቃት እንዲደርስባቸው በማድረግ እንዲሁም በድብደባ እና በዛቻ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረገ ያለውን ሕገ ወጥ አድራጎትን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል።
- ለባለውለታዋ እናት ቤተ ክርስቲያን በማይመጥን እና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕጋዊ ይዞታዋን እና የአምልኮት ቦታዎቿን በመንጠቅ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን እንደ ሽፋን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በደል እና ግፍ የሚፈጽሙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎችን ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ አድራጎታቸው እንዲታቀቡ በጥብቅ ያሳስባል።
- እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ በሀገራዊ የሀላፊነት ስሜት ታግሶ እና ችሎ ሞቱ፣ እሥራቱ፣ ዛቻው፣ ስደቱ እና እንግልቱ ሳይበግረው ሀገር በአንድነት እና በፍቅር እንዲሁም በመተሳሰብ እንድትቀጥል ታሪክ የማይረሳው መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን አገልጋይ ካህናት እና መላውን ምእመናንን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአጠቃላይ መላው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ላሳያችሁት ትዕግስት የተመላበት ሀገራዊ ሀላፊነት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያመሰገነ እንደአሁን ቀደሙ ሁሉ ትዕግስት የተመለበትን ሀገራዊ ኃላፊነታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን እና ወደፊትም ሊደርስ የታቀደውን ግፍ እና ጥፋት በአንድነት እና በኅብረት ከእኛ ከመንፈስ ቅዱስ አባቶቻችሁ ጋር በመሰለፍ በጽናት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንድትጠብቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በቤተ ክርስቲያናች እምነት እና ቀኖና መሠረት በእምነታቸው ምክንያት በሰይፍ የታረዱ፣ በጥይት የተገደሉት፣ በእሳት የተቃጠሉ፣ ሕይወታቸውን ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው የሰጡ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በሰማእትነት ክብር እና ማዕረግ ዘወትር እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በሰማእትነት ሕይወታቸውንየሰጡ አገልጋዮች እና ምእመናን ቤተሰቦች ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይናጋ በተቻለ አቅም ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ ሁላችንም ከጎናቸው በመሆን የድርሻችንን እንወጣ ዘንድ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽኑ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- እናት ቤተ ክርስቲያችን በእንግዳ ተቀባይነቷ እና በአቃፊነቷ ዛሬ ለቁጥር አዳጋች የሆኑት ቤተ እምነቶች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ሰላማዊ፣ የማምለክ መብታቸው እንዲረጋገጥ የበኩሏን ድርሻ የተወጣች መሆኗን ሁሉም ቤተ እምነቶች በየአደባባዩ የሚመሰክሩት እውነታ እንደመሆኑ መጠን በእናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ ሁሉም ቤተ እምነቶች በአንድነት እና በተባበረ ድምጽ በጽናት እንዲያወግዙ እና ለእምነት ተከታዮቻቸውም የቤተ ክርስያናችን ጥፋት እና በደል እንዲወገድ የበኩለቸውን ሚና እንዲወጡ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን እንዲያስተላልፉልን በቅድስተ ቤተ ክርስቲያናችን ስም የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለልን።
- የፍትሕ አካላት ለምሥረታችሁ እና ለእድገታችሁ ውለታ የከፈለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የቀደመ ውለታዋን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ ተጥሶ እና ፍትሕ ተጓድሎ በቤተ ክርስቲያነቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል በጽናት ከማውገዝ በተጨማሪ አጥፊዎችን ለፍትሕ በማቅረብ እና ተመጣጣኝ እና ለሌሎችም አስተማሪ የሆነ ውሳኔ በመስጠት እና በማሰጠት የራስዋየሆነ ተቋማዊ ሕልውና እና መዋቅር ያላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት እና ልእልና መከበር የበኩላችሁን ድርሻ ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ጥሪ ያስተላልፋል።
- በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የተከበረውን እና የተረጋገጠውን የእምነት ተቋማት ነፃነት እና ሉዓላዊ ክብር በሚጋፋ ሁኔታ እየተፈጸሙ ያሉት የመብት ጥሰቶች እና የጥፋት በደሎችን የማረም እና ከመፈጸማቸውም በፊት የመከላከል ኃላፊነት ያለባችሁ በየደረጃው የምትገኙ የመንግሥት አካላት በሕገ መንግሥቱ የተጣለባችሁን ሕግን የማስከበር አደራና ኃላፊነት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መብት የማስጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስያኒቱን ልዕልና እና ክብር እንድታስጠብቁ በቅድስት ቤተ ክርስያናችን ስም ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎባችኋል በማለት በጽኑ ያሳስባል፤
- አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ ሰላም እና ፍቅርን በመስበክ እና በተግባር በመፈጸም ለሀገር እና ለመላው ዓለም አርኣያ የሆነችውን እናት ቤተ ክርስቲያን ያለ ስሟ ስም፣ ያለግብረዋ ግብር በመስጠት በተለይም የተከበረውን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ባለውለታ የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳገለልችው እና አቅዳ እንደበደለቸው ለማስመሰል እና ለማስቆጠር አቅደው ቤተ ክርስያኒቱን እና ሀገርን ለመከፋፈል ድብቅ አጀንዳ ይዘው በተነሡ ግለሰቦች እና ቡድኖች አለአግባብ እየተሠራጨ ያለው አፍራሽ እና ከፋፋይ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም እና ድምጽ ካለመሆኑ በተጨማሪ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ እንደሚያስረዳን ሕገ ወጦቹ ግለሰቦቹ እና ቡድኖች የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የሚያገለግለው እና የሚባርከው መንፈሳዊ አባት እንደሌለው ቢገልጹም እንኳንስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ነፃነት ከተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ የተገኙት እና ነፍሳቸውን ሳይሳሱ በሰማዕትነት ዋጋ የከፈሉትን የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ታሪክ የማይረሳውን ውለታ የዘነጋ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት በመዓርገ ጵጵስና ሹማ በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት ለሐዋርያ አገልግሎት አሠማርታ መላውን የክልሉን ሕዝበ ክርስቲያን በማገልገል ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ ለክልሉ ሰላም እና አንድነት ዋጋ በመክፈል ላይ የሚገኙትን ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙትን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና በእነሱ የሚመሩ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ያሉ በርካታ ጽ/ቤቶች ከዐሥራ አምስት የሚበልጡ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶች እና መዋቅሮችን ፈጽሞ የካደ አድርጎት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ እያወገዘ በዚህ አድርጎት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከዚህ አድርጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል።
- የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የኦሮሞ ሕዝብ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ እንደ ትናንቱ ሁሉ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ በተቻላት አቅም መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ለማድረግ የጸሎት፣ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እና ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጎም እና በማዘጋጀት፣ ከአምስት በላይ የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ አንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅን በጀት መድባ በማቋቋም መላውን የኦሮሞ ብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ስታገለገል የቆየችውን እና ያላቸውን ወደ ፊትም ዘመኑን በዋጀ መልኩ አጠናክራ የምታገለግለውን እናት ቤተ ክርስያናችሁ መሆኗን አውቃችሁ አንድነታችሁን እና ፍቅረ ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመከፋፈል የተነሡትን የጥፋት ኃይሎች በጽናት በመቃወምና አንድነት እና ፍቅራችሁን አጠናክራችሁ ቤተ ክርስያናችሁን እና ሃይማኖታችሁን ከጥፋት ኃይሎች ትጠብቁ እና ትንከባከቡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል።
- አዲስ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚል መዋቅር በራሳቸው ሥልጣን መሥርተው በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ በሰጣቸው እድል ቀርበው የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም ወቅት ጥያቄውን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን ቀደም በኮሚቴ ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቶበት እያለ ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠው በማስመሰል ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ አዲስ መዋቅር ፈጥረው መግለጫ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን አምነው ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 የተቀጠሩ ቢሆንም በዕለቱ የኮሚቴው ዋና ተጠሪ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ያልተገኙ ሲሆን 2 የኮሚቴው አባላት ብቻ ከተሰጣቸው ሰዓት አሳልፈው ከመምጣታቸውን በላይ 2ቱ ግለሰቦች በጽሑፍ ባቀረቡት ምላሽ በሕገወጥ አቋማቸው የፀኑ መሆናቸውን የገለጹ በመሆኑ የግለሰቦቹ እንቅስቃሴም ሆነ የኦሮሞ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተብሎ የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን አውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተ ክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ትጠብቁ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- ከዚህ በላይ በተገለጸው መሠረት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልናም ሆነ ከሕገ የመነጨ ሥልጣን ሳይኖራቸውና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሕግ የመነጨ መብት በመጋፋት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሎጎ /አርማ/፣ ማህተምና መጠሪያ ስያሜ መጠቀማቸው ሕገወጥ አድራጎት በመሆኑ የሚመለከታችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሎጎ /አርማ/ እና ማህተም እንዲሁም መጠሪያ ስያሜ መጠቀም የማይችሉ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምት በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ታስከብሩ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት እያሳሰበ፤ የጽ/ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያም በሕገወጦች ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ አዟል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በዝርዝር በተገለጹት የአቋም መግለጫዎችና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የተነሱ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሳት ቅዱስ ሲኖዶስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት በቢሯቸው ተወያይተዋል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በተደረገው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያለውን አቋምና ያከናወናቸውን ተግባራት አውስተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የተከናወኑ በጎ ተግባራትን በመዘርዘር ምስጋና አቅርበዋል።
በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በውይይቱ የተነሡ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሳት ጳጳሳቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የእርሳቸውም ሆነ የመንግሥታቸው ፍላጎት የተጠናከረች፣ ለሀገር ግንባታ የሚቻላትን ሁሉ የምታደርግና አንድነቷ የተጠበቀ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ማየት መሆኑን ገልጠዋል። የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድ መሆን ጥቅሙ ለእምነት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል።
የቀረቡት ችግሮች በለውጥ ውስጥ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያነሱ ሲሆን ዓይነታቸው ቢለያይም የተለያዩ የእምነት ተቋማት በለውጡ ሂደት ፈተና አጋጥመዋቸዋል፣ በመሆኑም ዕንቅፋት የሚፈጥሩትን አካላት መታገል ያለብን በጋራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የቀረቡትን ችግሮች በዝርዝር በማጥናትና በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመነጋገር በጋራ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል። በሀገር ላይ የሚደርሱ ጥፋቶች በሁሉም ላይ የሚደርሱ በመሆናቸው መንግሥትና የእምነት ተቋማት በጋራ በመሥራት መፍታት እንዳለባቸው ገልጠዋል።
በመጨረሻም የተፈጠሩትን ችግሮች የጋራ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ክብር በጠበቀ መልኩ በጋራ ለመፍታት ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ምንጭ፦ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስት ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ሌሎች ዜናዎች፦- ሀገሬን ምን ነካት? (አባይነህ ካሴ (ዲ/ን)) ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- አገራችን ዘመን ተሸጋሪ የሆኑ ቅርሶቿን ጠብቃ ለትውልድ ለማቆየት የአርክቴክቱና የአንጂነሩ ሚና ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
- ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከእልቂት ለማዳን ቆም ብለን በሰከነ ሁኔታ ማሰብና መራመድ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን ከእንግሊዝ ሀገር አቻው ጋር ውይይት ተደረገ
ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል በሚል በመሠረተው የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ) – የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) እንዲሁም አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ላይ ላደረሱትና ለሚደርሰው ጉዳት የ174.6 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ እስከሚያልቅ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ክስ እንዳቀረበባቸውና ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት እንደቀርቡ ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ጥምረት ለተሻለ ጤና) /ABH Partners/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት ኤጀንሲው የድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማጠልሸቱ ይቅርታ እንዲጠይቅና ችግሩን እንዲያርም ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
በዚህም ድርጅቱ ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ-ብሔር ስድስተኛ ምድብ ችሎት የመዝገብ ቁጥር 241863 ክስ ለመመሥረት ተገዷል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴን ጨምሮ አምስት የሥራ ኃላፊዎችም ተከሰዋል።
ኤጀንሲው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) ጋር በጥምረት የሚሠሩትን ሥራ እንደማያውቀው ቢያስተባብልም፤ ሁለቱ ተቋማት ውል ተፈራርመው ሥራውን ሲጀምሩ በወቅቱ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በቦታው ተገኝተው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው እንደነበር ዶ/ር ማርቆስ አስታውሰው፤ “ይህም መንግሥት አያውቀውም የሚለውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አመላካች ነው። ከወራት በፊት ትምህርት የሚሰጥበትን ቦታ ተገኝተው የጎበኙ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች ግን ‘ሥራው የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማዳበር ያገዘ ነው’ ሲሉ አሞካሽተውታል። ለጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመስጠት የመምህራን ፍልሰት እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱንና ለትምህርት ጥራት እንዲተጋ የሚያግዙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ሚኒስቴሩ ምስክርነቱን በደብዳቤ ሰጥቷል” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ፥ የዚህ መሰል የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነት ለትምህርት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ሚናው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፥ ለዚህ ሊበረታታ ለሚገባው ድርጅት አገራዊ ፋይዳውን በማየት የግንባታ መሬት በመስጠት ትብብር እንዲደረግላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የትብብር ደብዳቤ እንደፃፈላቸውም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ለዩኒቨርሲቲውና ለድርጅቱ ምስክርነት በመስጠት ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሲያደርግ፥ ኤጀንሲው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከሰጠው ሥልጣን ውጪ “ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቅና የለውም፤ ሕጋዊም አይደለም” በማለት እግድ ማስተላለፉ “ባለፉት ሰባት ዓመታት የት ነበረ?” የሚል ጥያቄንም የሚጭር እንደሆነ ዶ/ር ማርቆስ አብራርተዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራውን ሊሰራ፤ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊሰጥ በገቡት ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ባለው ካምፓስ ምንም ዓይነት የመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግለት ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ለመማር-ማስተማሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ በውሉ መሠረት ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ ማስተማርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችል ኤጀንሲው ቢገልጽም፣ በዩኒቨርሲቲው እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ግን ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል።
በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሟላት ድጋፍ ሊሰጣቸው ከሚችል ከማንኛውም ተቋም ጋር መሥራት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በዚህም በአዋጁ ያልተከለከለን ሥልጣን ኤጀንሲው በደብዳቤ መሻሩ ተገቢነት እንደሌለው ዶ/ር ማርቆስ ገልፀዋል። በመሆኑም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች በሁኔታው መደናገጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ (ቁጥር 650/2001) አንቀጽ 93፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች እንዲሰጥ ስለማድረግ ይደነግጋል። በዚህም ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስቀምጧል።
በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (ቁጥር 240/2003) በአንቀጽ ሦስት መሠረት የዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን፣ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ተቀምጧል።
ባለፉት 15 ቀናት ኤጀንሲው “የትብብር ሥልጠና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ” በሚል ሚኒስቴሩ በደብዳቤ ማሳወቁን መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መልኩ ሲሠሩ የነበሩ የጅማ፣ የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታገዱ አሳውቋል።
ሆኖም ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሥራቸውን በመቀጠላቸው “አደብ ሊገዙ ይገባል” ብሎም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በተቋማቱ በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች ዝርዝር እንዲላክለት የጠየቀ ሲሆን፤ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልገው አሳውቆ ነበር።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላይ ውሳኔ ላይ ከመደረሳቸው በፊት በፈተናው ያጋጠመውን ችግር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲመረምር መቆየቱን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ውሳኔ አሳለፈ።
ሚኒስቴሩ በተፈተኞች ወጤት መሰረት እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ባደረገው ጥናት ማረጋገጡንም አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) እና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ በፈተናው ያጋጠመውን ችግር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲመረምር መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት በተፈጥሮ ሳይንስ (natural science) እና ማኅበራዊ ሳይንስ (social science.) መስኮች ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ፈተናቸው የተሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ታሳቢ የተደረጉ ሲሆን ሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ ፈተናዎች ውጤቶች ግን ተሰርዘዋል።
ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ እንዲያገለግሉ የተወሰነው ሂሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ፊዚክስ፣ አፕቲትዩድ እና ጂኦግራፊ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።
ሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ ፈተናዎች ከግምት ውስጥ ያልገቡት እጅግ የጋሸበ ውጤት የተመዘገበባቸው በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- NEAEA: የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ይፋ ሆነ
- አሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሰላማዊ ለማድረግ ተዘጋጅቷል
- ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
- አድማስ ዩኒቨርስቲ አይ ኤስ ኦ የምስክር ወረቀት (ISO Certificate) ለማግኘት የሚያስችል ሥራ እየሠራ መሆኑን ገለጸ
- የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንደሚቀርና የሁለተኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ይሆናል
Topic: 7ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት ተካሔደ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ዘንድሮ ለሰባተኛ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን የሸለመው የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) ተካሂዷል።
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማንን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በዘጠኝ ዘርፎች 291 ሰዎች ከሕዝብ ዘንድ ተጠቁመው የነበረ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 27ቱ ተመርጠው ለመጨረሻ ዕጩነት (በዘጠኝ ዘርፎች፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ ሦስት ሦስት ዕጩዎች) ቀርበው ኢትዮጵያውያን አሸናፊዎችን እንዲመርጡ ተደርጎ ነበር።
ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በእያንዳንዱ ዘርፍ ከቀረቡት ዕጩዎች ውስጥ የመጨረሻ ተሸላሚዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት አሸናፊዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
በመምህርነት ዘርፍ
- ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል
በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)
- ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በ አትክልት ምርምር ፕሮፌሰር፣ የጎለሌ ዕፅዋት ማዕከል የበላይ ኃላፊ፣ በሀገረ እንግሊዝ የተከበረው KEW International ሜዳል ተሸላሚ)
በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ
- አቶ በዛብህ አብተው (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የስፖርት ፎቶግራፍ አንሺ)
በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)
- አቶ አብድላዚዝ አህመድ
በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ
- አቶ ነጋ ቦንገር (የነጋ ቦንገር ሆቴል፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ የንግድ ተቋማት ምሥራች እና ባለቤት)
በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት
- አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ
በቅርስና ባህል ዘርፍ
- አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)
በሚዲያና ጋዜጠኝነት
በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች
- አቶ ኦባንግ ሜቶ (ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) መሥራች እና ሊቀ-መንበር)
የሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ የክብር ተሸላሚዎች
- የጋሞ ሽማግሌዎች (በቡራዩ የተከሰተውን ግድያ በመቃወም በአርባ ምንጫ የተቃውሞ ሠልፍ ላይ፣ በቁጣ ንብረት ለማውደም የቃጡ ወጣቶች እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ አንደ አካባቢው ባሕል ሣር ይዘው በአካላቸው ቆመው ንብረቱን ከጥፋት የተከላከሉት የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ነበሩ።)
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎችን እንኳን ደስ አላቸሁ ብለዋል። ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቷ፥ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎች ለነገው ትውልድ ተረካቢዎች አርዓያ የሚሆን ሥራ በመሥራታቸው ሊደነቁ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በ2005 ዓ.ም. በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተቋቋመው የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵይውያን በጎ ሥራን የሠሩ እና ለሌሎች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ማበረታታት እና ዕውቅና መስጠት ነው።
በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዓይነተኛ ሚናን መጫወት ችሏል።
አዲስ አበባ (ኢመደኤ) – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ባሳለፍነዉ 2011 በጀት ዓመት በተለያዩ ቁልፍ የሀገሪቱ ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች ላይ ሊፈጸሙ የነበሩ 791 የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን (cyber-attacks) ማክሸፍ መቻሉን ገለጸ።
በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን (Ethiopian Cyber Emergency Readiness & Response Team – ETHIO CERT) ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ገብረጻዲቅ እንደገለጹት፥ በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ ኢመደኤ ዓይነተኛ ሚናን መጫወት መቻሉን ገልጸዋል። ኃላፊዉ ጨምረዉ እንደገለጹት በ2011 በጀት ዓመት በአገሪቱ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል በመቻሉ ሊደርስ ከነበረው የደኅንነት እና የገንዘብ ኪሳራ በድምሩ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማዳን መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ በገንዘብ የማይተመን ሰላምን እና ፍትህ ማስጠበቅ ተችሏል ብለዋል። በቀጣይ 2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት አገራዊ የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ሽፋን በማሳደግ እና ዓለም አቀፍ ትስስርንና ቅንጅትን በማጠናከር የአገሪቱን ቁልፍ የሳይበር መሠረት ልማቶችን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራም ኃላፊዉ ገልጸዋል።
በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን በኢትዮጵያ የሳይበር ሥነ-ምህዳር የሚገኙ የሳይበር መኃረተ ልማቶችን ከጥቃት ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የሳይበር ደህንነት ክፍተት ትንተና (vulnerabilities) በማከናወን የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ የመከላከል፣ የሳይበር ጥቃቶች ከመፈጠራቸው በፊት የማስቀረት፣ የተፈጠሩት ሳይበር ጥቃቶች ከጥቃቱ በፊት ይሠሩበት ወደነበረው ይዞታቸው የመመለስ እና በተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጠቁ የደኅንነት ክፍተታቸውን እንዲደፈን የማድረግ፤ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የሳይበር ጥቃት መከላከያ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትስስር ሥራዎችን የሚሠራ ክፍል ነዉ።
ምንጭ፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ