-
Search Results
-
እነዚህን የተከለከሉ የምግብ ምርት ዓይነቶች ዝርዝራቸውን በማውጣት ምርቶቹን ሕብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸውና ተቆጣጣሪ አካላት ምርቶቹን በአፋጣኝ ከገበያ ላይ ባለስልጣኑ ጥሪውን አቅርቧል።
አዲስ አበባ (ኤፍ.ቢ.ሲ.) – የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን 57 የምግብ ምርት ዓይነቶችን ሕብረተሰቡ እንዳይጠቀም አሳሰበ።
ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በላከው መግለጫ በምግቦቹ ጥራትና ደኅንነት ላይ ባደረገው የገበያ ጥናት የምግብ ምርቶቹ መሰረታዊ የገላጭ የፅሁፍ ክፍተት ያለባቸው፣ የሚመረቱበት ቦታ የማይታወቅ፣ የንጥረ ነገር ይዘት የሌላቸው፣ አምራች ድርጅቶቹ የማይታወቁ፣ የምርት መለያ ቁጥር፣ የተመረቱበት ጊዜ እና የምርቱ ማብቂያ ጊዜ ገላጭ ፅሁፍ የሌላቸው ናቸው ብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ምርቶቹን ሕብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸውና ተቆጣጣሪ አካላት ምርቶቹን በአፋጣኝ ከገበያ ላይ እንዲሰበስቡም ጥሪውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ሕብተረሰቡ እንዳይጠቀማቸው የተከለከሉ የምግብ ምርት ዓይነቶች ዝርዝር፤
- የከረሚላ ምርቶች፦
• ጆሊ ሎሊፖፕ፣
• አናናስ ከረሚላ፣
• ኮላስ ከረሚላ፣
• ኦሊ ፖፕ፣
• ቤስት ከረሚላ፣
• የስ ከረሚላ (ኮፊ ከረሚላ)፣
• ማሚ ሎሊ ፖፕ፣
• ሳራ ከረሚላ፣
• ጃር ሎሊ ፖፕ፣
• ጸሃይ ሎሊ ፖፕ፣
• ዩኒክ ሎሊ ፖፕ፣
• እንጆሪ ከረሚላ፣
• ብርቱካን ከረሚላ፣
• ይናቱ ሎሊ ፖፕ እና
• ሃላዋ ከረሚላ፤ - የማር ምርቶች፦
• አፍያ የተፈጥሮ ማር፣
• ሪትም ማር እና
• በላይ ማር፤ - የገበታ ጨው፦
• ዊዲ የገበታ ጨው፣
• ሱላ የገበታ ጨው፣
• ናይ የገበታ ጨው፣
• ሃያት የገበታ ጨው፣
• አቤት የገበታ ጨው፣
• በእምነት የገበታ ጨው፣
• እናት የገበታ ጨው፣
• አባይ የገበታ ጨው፣
• አባት የገበታ ጨው፣
• ሴፍ የገበታ ጨው እና
• ጣዕም የገበታ ጨው፤ - የለውዝ ቅቤ፦
• ደስታ የለውዝ ቅቤ፣
• አስነብ የለውዝ ቅቤ፣
• ኑኑ የለውዝ ቅቤ፣
• አቢሲኒያ የለውዝ ቅቤ፣
• ብስራት የለውዝ ቅቤ፣
• ፈሌ የለውዝ ቅቤ፣
• ሳባ የለውዝ ቅቤ፣
• አዳ የለውዝ ቅቤእና
• አደይ የለውዝ ቅቤ፤ - የኑግ ዘይት፦
• አደይ አበባ የኑግ ዘይትእና
• ቀመር የኑግ ዘይት፤ - አልሚ የህጻናት ምግቦች፦
• ምሳሌ የህጻናት ምግብ፣
• ኤልሞ የልጆች ምግብ፣
• ሂሩት የህጻናት አጃ፣
• ዘይነብ የህጻናት አጥሚት፣
• ተወዳጅ ገንቢ የህጻናት አጥሚት፣
• ተወዳጅ የህጻናት ሽሮ እና
• ፋሚሊ ሃይል ሰጭና ገንቢ የህጻናት ሽሮ፣ - ሌሎች የተከለከሉ የምግብ ምርት ዓይነቶች፦
• ቪንቶ፤ ዴኮ፣ እስፔሻል፣ ዳና፣ ቃና፣ ላራ፣ ዛጎል አቼቶ፣ ናይስ አቼቶ፣ አምቴሳ አቼቶ፣ ማይ አቼቶ፣ መስ አቼቶ እና ቫይኪንግ አቼቶ ምርቶች
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩትን የምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ሕብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው ታግደዋል። ባለስልጣኑ ከሦስት ሳምንታት በፊትም 46 የብቃት ማረጋገጫ የሌላቸው የታሸጉ የምግብ ምርቶች ላይ እርምጃ መውሰዱንና፤ ሕብረተሰቡም እንዳይጠቀማቸው መከልከሉን መዘገባችን ይታወሳል። ዘገባውንና የተከለከሉትን የምግብ ዓይነቶች ዝርዝር ለማግኘት እዚህ ጋር ይጫኑ።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ./ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
አዲስ አበባ – የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮቸ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ተጠቃሚነት ለማሳጣት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረን ጨዋታ በዝግ ወይም አዳማ ከተማ ላይ ተጫወቱ በማለት ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጎል ብሏል።
ይህን ጨዋታ ከዚህ በፊት የተቋረጡ የሌሎች ክለቦች ጨዋታወችን ባስተናገደበት ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አላስተናገደም ሲል በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታውን አቅርቧል።
እንዲሁም በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የተሰጠው ፎርፌ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ መሆኑንም ነው በመግለጫው ያመላከተው።
አዲስ ከመጡት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመተባበር፣ በመቻቻል እና በመተጋገዝ ለመሥራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷልም ነው ያለው።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ. / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ኢትዮጵያ ቡና የአዲስ አበባ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ
- ከመጣንበት መንገድ በላይ የሚቀረን ይከብዳል!! (ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች)
- የኢትዮጵያ ቡና ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር አዳማ ላይ አልጫወትም አለ፤ በዒድ አል ፈጥር ምክንያት ጨዋታው በድጋሚ ተራዝሟል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በአዳዲስ የቢዝነስና የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች አፍላቂነታቸውና በፈር-ቀዳጅ ኢንቬስተርነታቸው (entrepreneur) በሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስትና ባለሃብት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሕይወት ታሪክና ሥራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው < የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > የተሰኘው የሕይወት ታሪክ (biography) መጽሐፍ ከሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል።
አጠቃላይ ዝግጅቱ ከስድስት ዓመታት በላይ ፈጅቶ የተጠናቀቀው ይህ መጽሐፍ፥ ከወላጆቻቸው የበስተጀርባ ታሪክ አንስቶ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን የልጅነት ሕይወትና አስተዳደግ፣ የወጣትነት ዘመንና የትምህርት ቆይታ እንዲሁም ወደ አሜሪካ አቅንተው ከዘበኝነትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እስከ ግዙፉ የዓለማችን የፋይናንስ ማዕከል ዎልስትሪት (Wall Street) የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ስመጥር ባለሙያነት የዘለቁበትን የረጅም ዓመታት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን፥ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ከ20 ዓመታት በላይ የተጓዙበትን በስኬትና በውድቀት የታጀበ፣ ፈተናና ውዝግብ ያልተለየው ረጅም የሕይወት ጎዳናም በዝርዝር ይዳስሳል።
◌ ኤርሚያስን የትኛው “ወንጀል” ሊያሳስረው ይችላል?
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የወጠኗቸውን አዳዲስና ሰፋፊ የፋይናንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕቅዶቻቸውን ከዳር ለማድረስ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ ያጋጠሟቸውን እሾህ አሜካላዎች፣ የተጋፈጧቸውን ፈተናና እንቅፋቶች በዝርዝር የተረኩበት መጽሐፉ፣ ከባለታሪኩ የግልና የሥራ ሕይወት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማይታወቁ በርካታ አዳዲስና አነጋጋሪ መረጃዎችን ያካተተ ነው።
በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውና 12 ዋና ዋና ምዕራፎች ያሉት < የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፣ “ማረፊያ አንቀጾች” እና “ድህረ-ታሪክ” የሚሉ ተጨማሪ ንዑሳን ክፍሎችን ጨምሮ አጠቃላይ የገጽ ብዛቱ 394 ነው።
< የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ መጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች፣ በአዲስ አበባ በሁሉም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎችና በሸዋ ሱፐርማርኬቶች፣ በስልክ ትዕዛዝ የቤት ለቤት እደላና በአማዞን ድረ-ገጽ አማካይነት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሚሸጥ ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋውም 300 ብር እንደሆነ ተነግሯል።
◌ ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ – (ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የታሸገ ውሃ “ሃይላንድ” ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም “ዘመን ባንክ” እና “አክሰስ ሪል ስቴት”ን ጨምሮ ባቋቋሟቸው የተለያዩ ኩባንያዎች የሚታወቁት አወዛጋቢው ኢኮኖሚስት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፥ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በአሁኑ ወቅትም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ጸሃፊው ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው ከዚህ ቀደም “መልስ አዳኝ” እና “ባቡሩ ሲመጣ” የተሰኙ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፥ ለ54 ተከታታይ ሳምንታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተላለፈውንና “ስውር መንገደኞች” የተሰኘውን ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማብቃቱም ይታወሳል።
ለተጨማሪ መረጃ፦
Email: yemayseberew@gmail.com, amelgaermiyas283@gmail.com
Facebook: Ermyas Tekil Amelga
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሰሞነኛ የተማሪዎች ምርቃት — በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች (የግል/ የመንግስት) የተማሪዎች ምርቃት።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ። በተመሳሳይ የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎችን አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው በአምስት ኮሌጆች ውስጥ ያስተማራቸውን ተማሪዎች 1 ሺህ 112 በመጀመሪያ ዲግሪ እና 201 በሁለተኛ ዲግሪ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ብርሃኑ የተማሪዎች ምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነት ማገልገል አለባቸው።
”ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እና በኢንጅነሪንግ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚያስተምር በመሆኑ ተማሪዎችም በዚሁ መስክ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን መሥራት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን እንደሚያካሂድና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ተመራቂዎች በበኩላቸው ባገኙት ዕውቀት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሪፖርተር እንደተናገሩት፥ ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመጥቀም ይሠራሉ። ወደ መንግስትም ሆነ ግል ተቋማት በመሄድ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ያገኙትን ትምህርት በተግባር ማስደገፋቸውን ገልጸው በኮንስትራክሽ ዘርፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ የተመረቁ ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት ለማህበረሰቡ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 578 ዕጩ መምህራንን በተመሳሳይ ዕለት በዲፕሎማ አስመርቋል።
ከዕውቀት ባለፈ በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሠሩ የኮሌጅ ተመራቂ እጩ መምህራን ተናግረዋል።
ከተመራቂ መምህራን መካከል በሒሳብ ትምህርት ክፍል የተመረቀችው መምህርት ስንቂት ማሙየ እንዳለችው፥ በቀጣይ ዕውቀቷን ለተማሪዎች ከማካፈል በተጨማሪ ሀገራቸውን የሚወዱና በሥነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በኃላፊነት እንደምተሠራ ተናግራለች።
“ሀገራችን ከመምህራን ብዙ ትጠብቃለች፤ እኛ መምህራንም ትውልድን በዕውቀት አንፀን በመቅረፅ ለሀገራቸው እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ አለብን” ብላለች።
በማኅበራዊ ሳይንስ ዕጩ መምህርና በኮሌጁ 3 ነጥብ 8 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው መንግስቱ ማሬ በበኩሉ ቀጣዩ ትውልድ በዕውቀት የዳበረና ማኅበረሰቡን አገልጋይ እንዲሆን በተመደበበት የሥራ ቦታ ተማሪዎቹን እንደሚያበቃ ተናግሯል።
“መመረቅ የመጨረሻ ሳይሆን ለአስተማረችኝ ሀገሬና ወገኔ አገልግሎት መስጠት የምጀመርበት ነው” ያለው ተመራቂው ሲሆን፥ በቀጣይም ዕውቀቱን በማዳበር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን አስረድቷል።
“የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ዕውቀትንና ማኅበራዊ ግብረ-ገብነትን ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ በቀጣይ የሥራ ዘመኔ የምከተለው መርህ ነው” ያለችው ደግሞ በሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ዘርፍ የተመረቀችው መምህርት መሰረት የኔሁን ናት።
የኮሌጁ ዲን አቶ ስንታየሁ ነጋሽ በበኩላቸው ኮሌጁ ከተቋቋመ 38 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው በእነዚህ ዓመታት ከ44 ሺህ በላይ መምህራንን ማስመረቁን ተናግረዋል። በዕለቱ ከተመረቁ 1ሺህ 578 እጩ መምህራን መካከልም 798ቹ ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ ዲኑ ገለጻ፥ ተመራቂዎቹ በትምህርት ቆይታቸው በቂ ዕውቀት ይዘው መውጣት የሚያስችላቸውን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት አግኝተዋል። ምሩቃን በቀጣይ ሙያውን አክብረው በመሥራትና ራሳቸውን ወቅቱ በሚፈልገው ልክ አቅማቸውን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ዓላማው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉን በኢፌዴሪ ጠቅላይ የሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። አቶ ንጉሱ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ላይ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) በሰጡት መግለጫ በክልሉ መንግስት ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል።
በተደራጀ ሁኔታ በመንግስት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረው የተደራጀ እንቅስቃሴ ከሽፏል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ።
የአማራ ክልል ወደ መረጋጋት እየመጣ ባለበትና እና ሕዝቡ ቀደም ሲል ያነሳ የነበረውን የህግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ባለበት ወቅት የተሰነዘረው ጥቃት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ላይ የተሞከረ ነው ብለዋል።
ሙከራው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት ይህን መሰሉን ተግባር የመግታት ሥራ እንደሚሠራና ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጸረ-ህገ መንግስትና መፈንቅለ መንግስቶች እንዲሁም በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፥ ክልሉን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ቴለቭዥን ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉትን አጭር ቃል ምልልስ እዚህ ጋር በመጫን ያዳምጡ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ!
- ከዴሞክራሲና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች
- አቶ አዲሱ አረጋን ነጻ ያወጣችው የእስክንድር ፌስታል
- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተቀሰቀሰ ረብሻ የአንድ ተማሪ ህይወት አለፈ
- ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል
Topic: አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ!
አቶ አዲሱ አረጋ የዛሬ ሁለት ዓመት፥ ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ እንዳይቀጥል “አይደገምም” በማለት ታሳሪዎችን በማስተማር¡¡ የተጀመረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ኒዮሊበራሎች በአገራችን “የቀለም አብዮት” ለማስነሳት እንደሆነ፣ የተፈጠውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ነግረውን ነበር።
አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ!
(ይድነቃቸው ከበደ)የህወሃት መራሹ የኢህአዴግ የአገዛዙ ሥርዓት በሕዝባዊ እንቢተኝነት የዛሬ ሦስት እና ሁለት ዓመት በሚናጥበት ወቅት፤ መስከረም ወር 2009 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሕዝባዊ ትግሉን ለመቀልበስ፣ በአገዛዙ በኩል የመጨረሻ እና ትልቁ የተባለ አፋኝ አዋጅ ታውጆ ነበር።
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ፤ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ዜጎች በተለያዩ ቦታዎች በኃይል በማስገደድ እስራት ተፈጽሟል። በአዋሽ አርባ፣ አዋሽ ሰባት፣ ብርሸለቆ፣ ጦላይ፣ ሰንከሌና ሌሎች ካምፖች ውስጥ ለ‹ተሃድሶ ስልጠና› በሚል ለመግለፅ የሚከብዱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በእነዚህ ካምፖች ውስጥ ተፈጽሟል። በተለይ ከአዲስ አበባ ተይዘን ወደ አዋሽ 7 ከገባን ታሳሪዎች በፊት አንድ ወር ቀድመው እዚሁ ካምፕ የገቡ ከኦሮሚያ ክልል የተያዙ ወጣቶች የደረሰባቸው በደል ለመግለጽ እጅግ በጣም የሚከብድ ሰቅጣጭ ነው።
በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በሺዎች በማሰር ይፈጸም የነበረው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት፣ በአገር ወዳደ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ ሆነ። ይህ ደግሞ በወቅቱ በአገዛዙ ሥርዓት ላይ ጫና በመፍጥር የተጀመረው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ሌላ ተጨማሪ ጉልበት ሆነ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖር አለመኖሩን እናጣራለን ያሉ “በመንግስት” ፍቃድ ታጉረን የምንገኝበት ካምፕ እንዲመጡ ተደርጓል። እንዲያናግራቸው ከተመረጡ ታሳሪዎች ጋር እኛን ወክለው ያዩትን እና የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት ተናግሯል። በወቅቱ የመንግስት ሚዲያዎች ዜና ሲያቀርብ መሠረታዊውን የመብት ጥሰት ወደ ጎን በመተው፣ በጥሩ ሆኔታ ላይ እንደምንገኝ እና ስልጠና እየተከታተልን እንደሆነ ይገልጹ ነበር።
በዚያን ጊዜ አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ በአዋሽ አርባ፣ አዋሽ ሰባት፣ ብርሸለቆ፣ ጦላይ፣ ሰንከሌና ሌሎች ካምፖች ውስጥ በመዘዋወር፤ ‘መንግስት’ ወጣቶችን አላሰረም ‹ተሃድሶ ስልጠና› እየሰጠ ነው¡¡ ለማስባል በሚደረገው ጥረት፣ መንግስታዊ ድራማ አስመስሎ ለመከወን የአንበሳውን ድርሻ በታታሪነት ከፈጸሙት መካከል አቶ አዲሱ አረጋ አንዱ ናቸው።
በተለይ እኔ በነበርኩበት ካምፕ አዋሻ 7፤ “አይደገምም” ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው ዕድገት አንፃር አሁን የገጠማት “ሁከትና ብጥብጥ” አይገባትም፤ የሚል እንድምታ ያለው፣ “እኛ ታሳሪዎች” ሁከትና ብጥብጥ ማቆምና ማስቆም እንዳለብን የሚያትት። ሌላኛው ደግሞ “የቀለም አብዮት” ኒዮሊበራሎች፣ ግብጽ እና ኤርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ እና አለመረጋጋት ለመፍጠር ስለሚፈልጉ “እኛ ታሳሪዎች” ከዚህ “የቀለም አብዮት” እራሳችንን እንድንጠብቅ የሚያሳስብ “የስልጠና” አርዕስት ላይ አቶ አዲሱ አረጋ ስልጠና በመስጠት በእኛ ታሳሪዎች ላይ “እጅግ በጣም” ጎብዘውብን ነበር¡¡
አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ ማለትም የዛሬ ሁለት ዓመት፥ ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ እንዳይቀጥል “አይደገምም” በማለት ታሳሪዎችን በማስተማር¡¡ የተጀመረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ኒዮሊበራሎች በአገራችን “የቀለም አብዮት” ለማስነሳት እንጂ፣ መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዳሴ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጠላቷ ድህነት እንደሆነ እና በወቅቱ የተፈጠው የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ። አቶ አዲሱ ለመናገር እንጂ ለማዳመጥ ወይም ለመጠየቅ ቅንጣት ፍላጎታ ሳይኖራቸው እሳቸው እና “መንግስታቸው” ብቻ የሚፈልጉትን ነግረውን ያ’ኔ ሄደዋል።
እኚህ ሰው አሁን ላይ “የለውጥ ኅይል” ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ናቸው።
‹‹የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር›› በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሠራተኞችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
አርባ ምንጭ (AMU) – በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል።
የዝግጅቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በንባብ ባህል ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር እውቀት እንዲስፋፋ እና ልምድ እንዲዳብር ለማድረግ እንዲሁም ማኅበረሰቡ የመጽሐፍትን ጥቅም ተረድቶ ከሌሎች ወጪዎች በመቀነስ የመግዛት ልምድ እንዲቀስም ለማስቻል መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሰገድ ካሣሁን ገልፀዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ ገጣሚ፣ ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የንባብ ጅማሮ፣ ጥቅምና የመምህራን ሚናን አስመልክቶ ባቀረቡት አንኳር ሀሳብ ንባብ ሊለካ የሚችለው በአንባቢው ላይ በሚያመጣው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ንባብ የተለያየ ነገር ግን የተዋሀደ ይዘት ያለው እንደመሆኑ ማኅበራዊ ተግባቦት እንዲጨምር፣ ተአማኒ እውቀት እንዲዳብር ብሎም ባልኖርንበት ዘመንና ቦታ በምናብ እንድንኖር የሚያደርግ ጥልቅ ምስጢር አለው ብለዋል።
ጥሩ አንባቢ የአፃፃፍ ስልትና የቃላት አመራረጥን ከመረዳት ባለፈ በሚያነበው ጉዳይ ራሱን የሚመለከትና የሚፈትሽ እንዲሁም የሌሎችንም ስሜት መረዳት የሚችል እንደሆነ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ተናግረዋል። ለዚህም መምህራን ከመጽሐፍት ምርጫ አንስቶ መልካም ልምዶችን ለትውልዱ በማካፈል በመረጃ የዳበረና ያወቀ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ለአንድ ማኅህበረሰብ እድገት የተማረ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገሪቱ ከመሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።
ማንበብና መጻፍ ከግለሰብ ባለፈ ለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ናቸው ያሉት ፕሬዝደንቱ፥ የንባብ ባህል እንዲዳብር አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት፣ አቅምና ጊዜ በተገቢው በመጠቀም፣ ተፈላጊውን የአዕምሮና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት እንዲሁም ምክንያታዊ ትውልድ በመፍጠር ከግለሰብና ከማኅበረሰብ ባለፈ ለአገር ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚቻል ገልፀዋል። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ ባህል መዳበር አጽንዖት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ምንም እንኳ ጥንታዊ የሆኑና የተለያየ ዘውግ ያላቸው የስነ-ጽሑፍ ውጤቶች እንዲሁም ወቅታዊ አዕምሯዊ ውጤት የሆኑ የህትመት ውጤቶች ቢኖሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው የንባብ ባህል መቀዛቀዝ በመረጃ የበለጸገና ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ እንደ አገር ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ ተናግረዋል። በአገሪቱ ለንባብ የሚውለው ጊዜ በዓለም አንባቢ ዜጋ ካላቸው አገራት አንጻር በሣምንት ለንባብ ከሚያውሉት አማካይ ጊዜ በእጅጉ መራቁን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያስረዱም ዶ/ር የቻለ ገልፀዋል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ መጽሐፍትን ገዝቶ ከማንበብ ይልቅ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ምርኮኛ መሆን፣ የወረቀትና የህትመት ዋጋ መጨመርና ሌሎችም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ የንባብ ባህል መዳበር ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ባህሉ እንዲያንሰራራና መሻሻሎች እንዲመጡ ጠንከር ያለ ጥረትን ይጠይቃል።
በንባብና ሚዲያ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚያጠነጥን የውይይት መነሻ ጽሑፍ የዶክትሬት (PhD) ተማሪ በሆኑት አቶ ተመስገን ካሣዬ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በዚህም ዘመኑ የቴክኖሎጂና የመረጃ ከመሆኑ ባሻገር የሚዲያ ተግባቦት ባህሎችን ከሌላው ጋር የመቀየጥ አቅም ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል።
ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ንባብ የአንድ ወቅት ሂደት ስላልሆነ በየደረጃው ያለው ሁሉም ማኅበረሰብ ከዋና ሥራው ጎን ለጎን መጽሐፍት ማንበብን ልምድ በማድረግ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችል አቅም ማጎልበት እንደሚገባው ገልጸዋል። በተለይም በአገራችን ያሉ ደራሲያን መጽሐፍት ስነ-ጽሑፋዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ፣ ታሪክን ሳያዛቡ እንዲሁም በሥነ-ምግባር ረገድ የተሻለ አቀራረብ እንዲይዙ በማድረግ ንቁ ማኀበረሰብ በመፍጠር ለአገራዊ ለውጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመጽሐፍት አውደ ርዕይና ሲምፖዚየሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከአዲስ አበባ የመጡ የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎችና የመጽሐፍት ሽያጭ መደብሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- የከረሚላ ምርቶች፦