Search Results for 'ዳምጠው ዳርዛ'

Home Forums Search Search Results for 'ዳምጠው ዳርዛ'

Viewing 10 results - 1 through 10 (of 10 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ወደነበረበት ለመመለስ ለሚሠራው ፕሮጀክት የአመራሮች የጋራ መድረክ ተመሠረተ

    አርባ ምንጭ (አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ) – ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ 25 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ወደነበረበት ለመመለስ በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲሆን ከጋሞና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ከደራሼ፣ ቡርጂና አማሮ ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ አስተዳዳሪዎችን እና የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኃላፊዎችን ያካተተ የአመራሮች የጋራ መድረክ ጥር 10 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ ተመሥርቷል። በዕለቱ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴም የአመራር መድረኩ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።

    የዕለቱን መርሃ-ግብር በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ በሁለት ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች ባሉ 10 ወረዳዎች የሐይቁን ህልውና ለመታደግ በቅርቡ ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን አሳታፊና ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል። ለ5 ዓመታት በሥራ ላይ የሚቆየው ፕሮጀክቱ ሕብረተሰቡን ማዕከል አድርጎ የሚሠራ ሲሆን፥ ሕብረተሰቡን በማስተባበርና በማንቀሳቀስ ሂደት ውስጥ የአካባቢው አመራሮች የሚኖራቸው ሚና የጎላ በመሆኑ፥ ይህንን የአመራሮች መድረክ መፍጠር አስፈልጓል ብለዋል። የአካባቢው አመራሮችም ፕሮጀክቱ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ወደነበሩበት ከመመለስ ባሻገር ከሥራ ዕድል ፈጠራና የማኅበረሰቡን የአኗኗር ሁኔታ ከመቀየር አንፃር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።

    እንደ አቶ ኃይለማርያም ለፕሮጀክቱ እውን መሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተደረጉ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎች ሚናቸው የጎላ ሲሆን፥ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በፕሮጀክቱ አፈፃፃም ወቅት የተጣለበትን በዕውቀትና ሳይንስ ላይ የተመሠረተ የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች በአግባቡ እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

    በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው በተፋሰሱ ላይ የሚጀመረው ፕሮጀክት የሐይቁን ህልውና ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል። በጫሞ ተፋሰስ ላይ የሚሠራው ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሀገር ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ለውጤታማነቱ የአካባቢው አመራሮች ማኅበረሰቡን በተለይ ወጣቶችን በስፋት በማሳተፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። እንደ ግብርና ሚኒስቴርም ጽ/ቤታቸው በፕሮጀክቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

    የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ሲገልጹ፥ ከዚህ ቀደም በወዜ ሻራ ተፋሰስ፣ አሁን ላይ ደግሞ በቤራ ተራራ ላይ እየሠራ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጠቃሽ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ሙሉ በሙሉ በሸፈነ መልኩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የታቀደ መሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ የአካባቢው አመራሮችም ይህን በብዙ ጥረት የተገኘ ዕድል በአግባቡ መጠቀም አለባቸው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ለፕሮጀክቱ እውን መሆን እንዳደረጉት ጥረት ሁሉ ለአፈፃፀሙም የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል።

    የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን ችግር ከማውራት ወጥተን ወደመፍትሄው እንድንገባ በር የከፈተ መሆኑን ጠቅሰው በዕለቱ የተመሠረተው የአመራሮች መድረክም አመራሩ ሥራውን በባለቤትነት ወስዶት እንዲሠራ ያስችላል ብለዋል። የችግሩን አንገብጋቢነት በመገንዘብ አመራሩ ማኅበረሰቡን የማንቃትና የማስተባበር እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የሚውሉ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በመወሰን ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበው እንደመድረኩ ሰብሳቢነታቸውም የበኩላቸውን ሚና በቁርጠኝነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

    በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ”AMU-IUC” ፕሮግራም ማኔጀርና የውሃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ብዙ ጊዜ መሰል ፕሮጀክቶች በፖለቲካ አመራሩ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፈጠር ባለመቻሉ ስኬታማ ሳይሆኑ እንደሚቀሩ አውስተዋል። አሁን ላይ የተመሠረተው የአመራሮች የጋራ መድረክ ማኅበረሰቡን ከማስተባበር አንፃርና ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የተለያዩ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን መውሰድ የሚችሉ አመራሮችን በሥራው ሂደት ላይ በኃላፊነት ስሜት ማሳተፍ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። እንደዘርፉ ተመራማሪ በግላቸውም ሆነ በሚመሩት ፕሮግራም አማካኝነትና በፕሮጀክቱ ለዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ለፕሮጀክቱ ስኬት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ሥራው የጫሞ ሐይቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    የአመራሮች መድረኩ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሂደት ውስጥ ፈጣን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን የሚወስድ የአስተዳደር መዋቅር ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑ በዕለቱ በቀረበው መመሪያ ላይ ተመላክቷል። በመመሪያው እንደተመላከተው መድረኩ በፕሮጀክቱ የተያዙ የሥራ ዕቅድና ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ የመሥራትና ቁጥጥር የማድረግ፣ የፕሮጀክቱ አፈፃፀምን በየጊዜው የመገምገም፣ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችንና ማነቆዎችን ለይቶ በፍጥነት የመፍታት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በፕሮጀክቱ ላይ በስፋት መሳተፉንና ተጠቃሚ መሆኑን የማረጋገጥና ሌሎች ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል።

    ምንጭ፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

    የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ወደነበረበት የመመለስ ፕሮጀክት

    Semonegna
    Keymaster

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቅድመና ድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ለ35ኛ ጊዜ አስመረቀ

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት፣ እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ በመደበኛ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,561 ተማሪዎችን ሰኔ 25 ቀን፥ 2014 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 662ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የኢትዮጵያን እድገትና ክብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብና ምሩቃን ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሀገር ሰላምን ለማደፍረስ የሚሰራጩ እኩይ ተልዕኮዎችን ሳያስተናግዱ በስኬት አጠናቀው ለምረቃ በመብቃታቸው አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይህን መልካም ሥነ ምግባር በማስቀጠል በሚሄዱበት የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ለሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ቅድሚያ ሰጥተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አደራ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ6 ካምፓሶች በ75 የመጀመሪያ፣ በ114 የ2ኛ እና በ26 የ3ኛ ዲግሪ በአጠቃላይ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ ሲሆን የዛሬዎቹን ተመራቂዎች ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው ከ72 ሺህ በላይ ምሩቃንን ማፍራቱን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

    የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባልና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ፈጠነ ተሾመ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ እንዲሁም የማይከስር ሀብት መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት በሚሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ለዘላቂ እድገትና ሽግግር እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል፡፡

    የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን /አልሙናይ/ ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ ተመራቂዎች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ውጤታማ ለማድረግ ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተናግረው በቀጣይ ራሳቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ያስተማራቸውን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ሀገር ለማገልገል በታማኝነትና በትጋት እንዲሠሩ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን አባል በመሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብና ለዓለም መልካም አስተዋጽኦዎችን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራልና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እጩ ምሩቃንን ለምረቃ በማቅረብ አስመርቀዋል፡፡

    ምንጭ፦ የዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    5ኛው “ሀገረሰባዊ ዕውቀት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት” ሀገራዊ ዓውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

    አርባ ምንጭ (አምዩ) –  የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አምዩ) የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 5ኛው “ሀገረሰባዊ ዕውቀት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት” ሀገራዊ ዓውደ ጥናት ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል።

    በዓውደ ጥናቱ “የአሪ ብሔረሰብ ባህላዊ የተፈጥሮ ሀብት ዕውቀት፣ እሳቤዎችና ክዋኔዎች፣” “ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ፣” “ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በጋሞ ሕዝብ፡- የኦቾሎ ደሬ ተሞክሮ” እና “ሀገር በቀል ዕውቀት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፡- የጋሞ እና ኮንሶ ጥብቅ ደኖች” የሚሉ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ክዋኔና እሳቤዎች ለአካባቢ ጥበቃና ለግጭት አፈታት ያላቸውን ሚና የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ጥናታዊ ጽሑፎቹ በዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩትና በሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህራንና ተመራማሪዎች የተሠሩ ናቸው።

    በጽሑፎቹ እንደተመለከተው ሀገር በቀል ዕውቀት፣ እሳቤዎችና ክዋኔዎች የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም ግጭቶችን በመከላከልና በመፍታት ረገድ ለበርካታ ዘመናት አዎንታዊ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ዘመናዊነትና ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ለውጦች፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በፌዴራልና በአካባቢ አስተዳደር በቂ ትኩረት አለማግኘትና ሌሎችም ምክንያቶች ለሀገር በቀል እሴቶቹ አደጋ የጋረጡ ሆነዋል። ተመራማሪዎቹ በጥቆማቸው ከመንግሥት አካላት ተገቢው ትኩረትና ዕውቅና እንዲሰጠው፣ ማኅበረሰብ መር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲጠናከር እንዲሁም የምርምር፣ የካርታና ዶኪዩሜንቴሽን ሥራዎች እንዲሠሩ ሃሣብ አቅርበዋል።

    የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕክምና፣ በግብርና፣ በግጭት አፈታት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በሌሎችም በርካታ መስኮች የእምቅ ባህልና ዕውቀት ባለቤት መሆኗ ለማኅበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ለመስጠት የሚያስችል ነው። በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እንዲሁም ምርምሮች እንዲካሄዱ ድጋፍ በማድረግ ሀገር በቀል ዕውቀትና ክዋኔዎች ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ በትኩረት ይሠራል።

    ዓውደ ጥናቱ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የክልሉና የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች እንዲሁም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት ያቀዷቸውን ሥራዎች የሚያጠናክር መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አርባ ምንጭ እና አካባቢው በርካታ ባህላዊ እሴቶችን ያቀፈ በመሆኑ ለዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ሀገር በቀል ዕውቀት ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር ተጣምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገርና ለሀገር ልማት እንዲውል ለሀገር በቀል ዕውቀት ያለንን የተሳሳተ ግንዛቤ ማረም ብሎም በምርምር ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አህመድ ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን ከማካሄድ ባሻገር የሥነ-ጥበብ ዘርፍን ለማሳደግ አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ሀገራዊ የትርጉምና የተርጓሚነት ሙያ ጉባዔ ማዘጋጀቱን አስታውሰው መሰል መድረኮች ልምድና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም፣ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ሙያዊ አቅምን ለመገንባት ፋይዳ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

    የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በዓውደ ጥናቱ ተሳትፈዋል።

    ምንጭ፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

    ሀገረሰባዊ ዕውቀት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ዓውደ ጥናት

    Semonegna
    Keymaster

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዲላ/አርባ ምንጭ (ኢዜአ/አ.ም.ዩ) – ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,043 ተማሪዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 283 በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በምስክር ወረቀት የተመረቁ መሆኑን አስረድተዋል።

    ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲከታተሉ እንደቆዩ አመልክተው፥ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ዶ/ር ጫላ ገልጸዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኡዴሳ ክዮላ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በቀጣይ በሚሰማሩበተ የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና ታታሪነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ከተመራቂዎቹ መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን የተከታተለው ቅዱስ ይገረሙ በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሰለጠነበት በ“ሶፍትዌር ዲዛይን” ዘርፍ በመሰማራት እራሱንና ሀገሩን ለመጥቀም እንደሚሠራ ተናግሯል።

    በሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ዋቆ ጥላሁን በበኩሉ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ገልጿል።

    የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

    ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመርቋል።

    ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በስድስት የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው። በመሆኑም የዕለቱ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል።

    በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አ.ም.ዩ)

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    Anonymous
    Inactive
    • ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የጸጥታ ችግር የተሳተፉ ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ
    • ወሎ ዩኒቨርሲቲ በ335 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ ወሰደ
    • የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያዩ ሀይሎች ሴራ እንዳይጠመዘዝ አስቀድመው በመሥራታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አስታወቁ

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ታህሳስ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በ2012 ዓ.ም. በተደጋጋሚ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተለያየ ተሳትፎ በነበራቸው ተማሪዎች ላይ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።

    1. ሁለት (2) ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው እንዲሰናበቱ፣
    2. ሰባት (7) ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሦስት (3) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ፣
    3. ስምንት (8) ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሁለት (2) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ፣
    4. አንድ (1) ተባሮ የነበረ (በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ያልነበረ) ነገር ግን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ ተሳታፊ የነበረ ዩኒቨርሲቲው ክስ መስርቶ ግለሰቡን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፤

    በመጨረሻም በወቅቱ ለሴኔቱ ውሳኔ ለቀረበ ተጨማሪ ስልሳ ዘጠኝ (69) ተማሪዎች ዲሲፕሊን ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ጥፋታቸው በሂደት ተጣርቶ ወደ ፊት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እንዲሁም በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተለያየ መልኩ ተሳታፊ የነበሩ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ላይ እንደየጥፋታቸው እርምጃ እንደሚወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል።

    በተያያዘ ዜና የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያዩ ሀይሎች ሴራ እንዳይጠመዘዝ አስቀድመው በመሥራታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አስታወቁ።

    ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሃይማኖትና የብሄር ተኮር ግጭቶች ማዕከል ሆነው እና የጸጥታ ችግር ተጋርጦባቸው ጥቂት የማይባሉ ዩኒቨርሲቲዎችም በተደጋጋሚ ትምህርት ለማቆም ተገደዋል፤ በተማሪዎች ላይም ጉዳት አጋጥሟል። የግጭት መንስኤዎች የተለያዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ከአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ጋር የተያያዙ ናቸው።

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን አውከዋል ያላቸውን 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቋል።

    ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ባለፉት ሁለት ወራት ችግር ፈጣሪዎችን ለመለየት በተከናወነው ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይቀጥል ፍላጎት ባላቸው 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መወሰዱን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ለ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ተመራጭ እና ተምሳሌት ሆኖ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በብሔር እና በሀይማኖት ሽፋን በተፈጠረ አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ሥራው ባለፉት ወራት ውስጥ ለሦስት ጊዜ መቋረጡን አውስተዋል።

    በዚህም የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉንና በተወሰኑት ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፣ ይህም ከአንድ የእውቀት ምንጭ ተቋም የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

    የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚታዩት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለግድያ የሚያደርሱ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ሰላም ወዳድ መሆናቸውን የሚገልጸው ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ለማወክ የሞከሩ ጥቂት ተማሪዎች እንዳልተሳካላቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

    ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ የሚገኘው ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲም ሁነኛ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው የመማር ማስተማሩ ሂደት በሰላማዊ ሁኔታ ከቀጠለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተጠቃሹ ነው። ዩኒቨርሲቲው ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት የአንደኛ መንፈቅ ዓመት ትምህርትን ወደማገባደድ መቃረቡን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡጁሉ ኦካክ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

    የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛም የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ በተለይም ተማሪዎች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ካልተቻለም ለማሻሻል ጥረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

    ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተናገድ ከጀመሩ በኋላ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአጭሩ ለመፍታትም ከተማሪዎች ጋር የሰከነ እና የሰለጠነ ውይይት ማድረጋቸውን የአርባምንጭ እና ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ገልፀዋል። ለዚህም ተማሪዎች እያንዳንዱ ጥያቄ በሂደት እንደሚፈታ ማመናቸውና አርቆ ተመልካችነታቸው ሰላማዊ ሁኔታው እንዲቀጥል ትልቁን ድርሻ እንደተወጣም ተጠቁሟል።

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙባቸው አካባቢዎች የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች እና ወጣቶች በሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ መደረጉንም ዩኒቨርሲቲዎቹ የገለጹት።

    የዩኒቨርሲቲዎቹ ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ ተማሪዎቹን እንደ ራሱ ልጆች ተመልክቶ እንዲጠብቃቸው የተሰራው ሥራም ውጤታማ እንደነበር ነው ፕሬዚዳንቶቹ የገለጹት።

    ተማሪዎችም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የታዩ አሰቃቂ ተግባራት እንዳይደገሙ በጋራ መሥራት አለባቸው፤ ከስሜታዊ ድርጊትም ሊታቀቡ ይገባልም ነው ያሉት። የብዙሃኑን ሰላም ለመጠበቅ ጥቂት በጥባጮችን አደብ ማስገዛት ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው።

    ምንጮች፦ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ / የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    በዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ችግር

    Anonymous
    Inactive

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሠላማዊ ለማድረግ የሠላም ጥምር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እንደሚሠራ ገለፀ

    አርባ ምንጭ (ሰሞነኛ)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሠላማዊ ለማድረግ የሠላም ጥምር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እንደሚሠራ ገለፀ። ዩኒቨርሲቲው በ2012 የትምህርት ዘመን ሠላማዊ መማር ማስተማር ለማረጋገጥ በተዘጋጀ የሠላም ጥምር ግብረ ኃይል መሪ ዕቅድ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጋር ጳጉሜ 2/2011 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል።

    ጥምር ግብረ ኃይሉ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማዕከል እንዲሁም በየካምፓሱ የሚቋቋም ሲሆን ዓላማውም የትምህርት ዘመኑ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማና ሠላመዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማድረግ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል። ጥምር ግብረ ኃይሉ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ባሻገር የተማሪዎች ኅብረት ተወካዮችን፣ የሠላም ፎረም አመራሮችን፣ የዞንና የከተማ የሥራ ኃላፊዎችንና ፀጥታ አካላትን ያካተተ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል።

    ጥምር ግብረ ኃይሉ በዋናነት ከታች እስከ ላይ ባለው የዩኒቨርሲቲው መዋቅር መማር ማስተማሩን ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዮችን በየጊዜው እየተከታተለና እየገመገመ መፍትሔና ማስተካከያ የሚሰጥ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው ገልፀዋል። ጥምር ግብረ ኃይሉ በውስጥና በውጪ ጭምር የሚዋቀር መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ መዋቅሩ ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ይሠራል ብለዋል።

    በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች ቅበላ ይረዳ ዘንድ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እቀድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ሲሆን በቅርቡም አፈፃፀሙን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ልዑክ ወደየካምፓሱ በመሄድ ምልከታ እንደሚያደርግና ሥራው ያለበትን ደረጃ በመገምገም አቅጣጫ እንደሚሰጥ ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል።

    ሠላማዊ የመማር ማስተማሩ ሥራ ካለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ስኬታማ መሆን ስለማይችል መስከረም መጀመሪያ አካባቢ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀይማኖት አባቶችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ32ኛ ጊዜ 6,857 ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል
    —–

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ ምረቃና በድኅረ ምረቃ ያሰለጠናቸውን 6,857 ተማሪዎች ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. አባያ ካምፓስ በሚገኘው አዳራሽ እና ሰኔ 30 ቀን2011 ዓ.ም. በሣውላ ካምፓስ በድምቀት አስመርቋል። ከተመራቂዎች መካከል 4,434 ወንዶች ሲሆኑ 2,423 ሴቶች ናቸው።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ተመራቂዎች የሥራ ዓለምን ሲቀላቀሉ ከዩኒቨርሲቲው በገበዩት እውቀት፣ ክህሎትና መልካም ሥነ-ምግባር መንግሥትና ህዝብ የአገሪቱን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እያደረገ ባለው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንዲሁም ራሳቸውን፣ ወገናቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች በተለያየ መልኩ ወደ ሥራው ዓለም ሲቀላቀሉ በአገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

    በአሁኑ ጊዜ በአገራችን መልካም ተስፋ እየታየ ቢሆንም ተስፋውን የሚያደበዝዙ ችግሮች ይስተዋላሉ ያሉት ዶ/ር ይናገር፥ ችግሮች እንዳይከሰቱና ከተከሰቱም በሰከነ ሁኔታ እንዲፈቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚሠራጩ ሀሰተኛ ወሬዎች ቦታ ሳይሰጡ ለአገራችን አንድነትና አብሮነት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

    የዕለቱ እንግዳና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል ዶ/ር አብርሃም አላኖ በበኩላቸው የአንድ አገር ልማት ያለ ትምህርት መስፋፋት እውን ሊሆን እንደማይችል መንግሥት ተረድቶ ለከፍተኛ ትምህርት ፍትሃዊ መስፋፋትና ተደራሽነት በትኩረት ሲሠራ የቆየ በመሆኑ በዘርፉ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል። መንግሥትና የዘርፉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር አብርሃም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በአገሪቱ ከሚገኙ የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በሁሉም መስኮች ቀዳሚ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

    አገራችን ኢትዮጵያ በዕድገት ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን ያወሱት የክብር እንግዳው ከለውጡ ጋር ተያይዞ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ ከፍተኛ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች የተጋረጡ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የዕለቱ ተመራቂዎች ምክንያታዊ በመሆንና ከግለኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ለማኅበረሳባችን ለውጥ ብሎም አገሪቱ ከገጠማት ፈተና እንድትወጣና የተጀመረው ለውጥ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

    ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 4 ነጥብ በማምጣት የሜዳልያና ዋንጫ ተሸላሚ የሆነው የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተመራቂ እስማኤል ፈድሉ በሰጠው አስተያየት ጠንክሮ መሥራቱና ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ ለስኬት እንዳበቃው ገልጿል። ማንኛውም ሰው በተሰማራበት መስክ ዓላማ በመሰነቅ በቁርጠኝነት ከሠራ ውጤታማ መሆን ይችላል ያለው ተሸላሚው አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ ጅምር በመሆኑ የትምህርት ደረጃውን በማሻሻል አገሩን በታማኝነትና በቅንንት እንደሚያገለግል ተናግሯል።

    በአጠቃላይ ውጤት 3.98 በማምጣትና 43 A+ በማስመዝገብ በ2ኛነት የተሸለመው የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል ተመራቂ ቃለአብ ወንድሙ ታሪኩ በዓላማ መንቀሳቀስና ተግቶ መሥራት ለስኬት ያበቃል ብሏል። ሰሚራ ዲልቦ አወል ከኮኦፕሬቲቭ አካውንቲንግ እና ኦዲቲንግ ትምህርት ክፍል 3.94 ከሴቶች ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት እንዲሁም ተመራቂ ዘሀራ ያሲን አማን ከኮምፒውተር ሣይንስ ትምህርት ክፍል 3.92 በማምጣትና 16A+ በማስመዝገብ ልዩ የወርቅ ሀብል ተሸላሚዎች ሆነዋል።

    በዕለቱ ከየትምህርት ክፍላቸው 1ኛ ለወጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሽልማት፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ምሩቃን የወርቅ ሜዳልያ፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ሴት ምሩቃን ልዩ ሽልማት፣ በአጠቃላይ ሴት ምሩቃን መካከል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበች ምሩቅ የአንገት ሐብል ሽልማት እንዲሁም ከአጠቃለይ ምሩቃን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበው ምሩቅ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ‹‹የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር›› በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሠራተኞችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

    አርባ ምንጭ (AMU) – በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል።

    የዝግጅቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በንባብ ባህል ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር እውቀት እንዲስፋፋ እና ልምድ እንዲዳብር ለማድረግ እንዲሁም ማኅበረሰቡ የመጽሐፍትን ጥቅም ተረድቶ ከሌሎች ወጪዎች በመቀነስ የመግዛት ልምድ እንዲቀስም ለማስቻል መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሰገድ ካሣሁን ገልፀዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ ገጣሚ፣ ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የንባብ ጅማሮ፣ ጥቅምና የመምህራን ሚናን አስመልክቶ ባቀረቡት አንኳር ሀሳብ ንባብ ሊለካ የሚችለው በአንባቢው ላይ በሚያመጣው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ንባብ የተለያየ ነገር ግን የተዋሀደ ይዘት ያለው እንደመሆኑ ማኅበራዊ ተግባቦት እንዲጨምር፣ ተአማኒ እውቀት እንዲዳብር ብሎም ባልኖርንበት ዘመንና ቦታ በምናብ እንድንኖር የሚያደርግ ጥልቅ ምስጢር አለው ብለዋል።

    ጥሩ አንባቢ የአፃፃፍ ስልትና የቃላት አመራረጥን ከመረዳት ባለፈ በሚያነበው ጉዳይ ራሱን የሚመለከትና የሚፈትሽ እንዲሁም የሌሎችንም ስሜት መረዳት የሚችል እንደሆነ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ተናግረዋል። ለዚህም መምህራን ከመጽሐፍት ምርጫ አንስቶ መልካም ልምዶችን ለትውልዱ በማካፈል በመረጃ የዳበረና ያወቀ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ለአንድ ማኅህበረሰብ እድገት የተማረ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገሪቱ ከመሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።

    ማንበብና መጻፍ ከግለሰብ ባለፈ ለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ናቸው ያሉት ፕሬዝደንቱ፥ የንባብ ባህል እንዲዳብር አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት፣ አቅምና ጊዜ በተገቢው በመጠቀም፣ ተፈላጊውን የአዕምሮና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት እንዲሁም ምክንያታዊ ትውልድ በመፍጠር ከግለሰብና ከማኅበረሰብ ባለፈ ለአገር ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚቻል ገልፀዋል። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ ባህል መዳበር አጽንዖት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ምንም እንኳ ጥንታዊ የሆኑና የተለያየ ዘውግ ያላቸው የስነ-ጽሑፍ ውጤቶች እንዲሁም ወቅታዊ አዕምሯዊ ውጤት የሆኑ የህትመት ውጤቶች ቢኖሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው የንባብ ባህል መቀዛቀዝ በመረጃ የበለጸገና ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ እንደ አገር ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ ተናግረዋል። በአገሪቱ ለንባብ የሚውለው ጊዜ በዓለም አንባቢ ዜጋ ካላቸው አገራት አንጻር በሣምንት ለንባብ ከሚያውሉት አማካይ ጊዜ በእጅጉ መራቁን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያስረዱም ዶ/ር የቻለ ገልፀዋል።

    በማኅበረሰቡ ዘንድ መጽሐፍትን ገዝቶ ከማንበብ ይልቅ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ምርኮኛ መሆን፣ የወረቀትና የህትመት ዋጋ መጨመርና ሌሎችም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ የንባብ ባህል መዳበር ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ባህሉ እንዲያንሰራራና መሻሻሎች እንዲመጡ ጠንከር ያለ ጥረትን ይጠይቃል።

    በንባብና ሚዲያ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚያጠነጥን የውይይት መነሻ ጽሑፍ የዶክትሬት (PhD) ተማሪ በሆኑት አቶ ተመስገን ካሣዬ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በዚህም ዘመኑ የቴክኖሎጂና የመረጃ ከመሆኑ ባሻገር የሚዲያ ተግባቦት ባህሎችን ከሌላው ጋር የመቀየጥ አቅም ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል።

    ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ንባብ የአንድ ወቅት ሂደት ስላልሆነ በየደረጃው ያለው ሁሉም ማኅበረሰብ ከዋና ሥራው ጎን ለጎን መጽሐፍት ማንበብን ልምድ በማድረግ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችል አቅም ማጎልበት እንደሚገባው ገልጸዋል። በተለይም በአገራችን ያሉ ደራሲያን መጽሐፍት ስነ-ጽሑፋዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ፣ ታሪክን ሳያዛቡ እንዲሁም በሥነ-ምግባር ረገድ የተሻለ አቀራረብ እንዲይዙ በማድረግ ንቁ ማኀበረሰብ በመፍጠር ለአገራዊ ለውጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

    በመጽሐፍት አውደ ርዕይና ሲምፖዚየሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከአዲስ አበባ የመጡ የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎችና የመጽሐፍት ሽያጭ መደብሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የንባብ ባህል


    Semonegna
    Keymaster

    አርባ ምንጭ (አ.ም.ዩ.)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ5ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 76 የህክምና ዶክተሮች ኅዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በደማቅ ሥነ ስርዓት አስመርቋል።

    የዩኒርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የትምህርት መርሀ ግብሮችን (ፕሮግራሞች)እና የሚካሄዱ ምርምሮች የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የትምህርት ጥራት፣ አግባብነትና ተደራሽነት ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል። ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

    ዩኒቨርሲቲው የጤና ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ፥ የዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 127 መምህራን እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን 69ኙ 2ኛ ዲግሪ፣ 11ዱ 3ኛ ዲግሪ እና 41ዱ የስፔሻሊቲ መ/ራን ደረጃቸውን ሊያሻሽል ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

    እንደ ፕሬዝደንቱ ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲው ከአርባ ምንጭ ሆስፒታልና አጎራባች የጤና ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር፣ በማኅበረሰቡ ጤና መሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ምርምሮችን በማከናወንና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው።

    Selale University (Fiche, Ethiopia) accepts students for the first time

    ፕሬዝደንቱ በህክምና ትምህርት የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በተመለከተ በ2009 ዓ.ም. ከነበሩት 58 የህክምና ዶክትሬት ምሩቃን መካከል የሴት ምሩቃን ቁጥር 1 (አንድ) ብቻ የነበረ ሲሆን በ2011 ዓ.ም. ከተመረቁት 76 የህክምና ዶክተሮች የሴት ምሩቃን ቁጥር 18 መድረሱ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በተጨማሪም ምሩቃን በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ከሥራው ዓለም ጋር አዋህደው የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ለአገራችን ህዳሴ ታላቅ ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በድሩ ሂሪጎ በበኩላቸው እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ፣ የወባ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም መሰል የጤና መሻሻል ሊያመጡ የሚችሉ አገር አቀፍ ምርምሮችን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን እየተገነባ ያለው የዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ጥራት ያለው የጤና ትምህርትና የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ያስችላል።

    ዓለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር በአገራችን ትምህርትና ሥልጠና አቅርቦት፣ ተገቢነትና ጥራት ላይ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ያለነው በታዳጊና ኢኮኖሚዋ ባልዳበረ አገር እንደመሆኑ መጠን ምሩቃን ችግሮችን በሰከነ መንፈስ በመጋፈጥ በድል መወጣት፣ ቀና አስቢነትንና ትህትናን መላበስ እንዲሁም በአሸናፊነት እና በ”እችላለሁ!” ስሜት ተነሳሽነት የወገናችውን ህይወት የሚቀይር ሃሳብና አሠራር ሊቀይሱ ይገባል በማለት አሳስበን ንግግራቸውን በመቀጠል፦

    ‹‹ዛሬ ተንብዩ፤ ለነጋችሁ ያለእረፍት ሥሩ፤ የምትይዙት ጓደኛ፣ የምታዩት ፊልም ሁሉ ከህልማችሁ እና መድረሻችሁ ጋር የተገናኘና ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያግዛችሁ መሆኑን አረጋግጡ›› ያሉት ሚኒስትሯ ዘረኝነት፣ ሌብነት እና ራስ ወዳድነት ከአገራችን ወግና ባህል የወጡ በመሆኑ ልትታገሏቸው ይገባል ብለዋል ።

    የኢትዮጵያ የህክምና ማኅበር ተወካይ እንዲሁም የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ ዶ/ር መስከረም አለቃ በበኩላቸው የተመረቃችሁበት ሙያ ትልቁን የሰው ልጅ የማዳን ተግባር በመሆኑ በሥራው ዓለም የሚጠብቋችሁን ተግዳሮቶች በትጋት በመወጣት ለወገናችሁን ጤና መሻሻል ልትሠሩ ይገባል በማለት ለአገሪቱ ጤና መሻሻል በጋራ ለመሥራት ለምሩቃኑ በማኅበሩ ሥም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኑ እንዳስደሰተው የገለፀውና 3.54 አማካኝ ወጤት በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ የሆነው ምሩቅ መሠረት ሙሉ በቀጣይ የማህፀንና ፅንስ ሐኪም መሆን እንደሚፈልግና የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠብቀው ተናግሯል።

    አማካኝ ወጤት 3.46 የማዕረግ ውጤት በማምጣት ሴቶች በህክምና ትምህርት ዘርፍ የተሻለ ተሳትፎ መኖሩን ጥሩ ማሳያ የሆነችው ምሩቅ ትዕግስት ገረሱ የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ሊቀንሱ የሚችሉ በቂ ምርምሮችን በማከናወን ባለት ዕውቀትና ክህሎት ማኅበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነች ገልፃለች።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

    Semonegna
    Keymaster

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል፤ የትምህርት ዘመኑን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፤ በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ማዕከላትን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ነው።

    አርባ ምንጭ (ኢዜአ/AMU)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።

    የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጥናል። ከነዚህም ከ6ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አዲስ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

    ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የክህሎት ትምህርት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ጥቅምት 11 እና 13 ቀናት የነባር ተማሪዎች ቅበላ የሚያከናውን ሲሆን፣ ጥቅምት 15 ና 16 ቀናት 2011 ዓ.ም ደግሞ አዲስ ገቢዎችን እንደሚቀበል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

    ተማሪዎቹ ከአቀባበል ጀምሮ በመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዱት ዶክተር ዳምጠው፣ ከግቢ ውጭ ችግር እንዳያጋጥማቸው የከተማው ነዋሪዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

    ◌ ተመሳሳይ ዜና፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ጥራትና ለኅብረተሰቡ ንጹህ ውሃ ለማቅረብ እየሠራ ነው

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፖለቲካ፣ ኃይማኖትና ከትምሀርት ጋር ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች የጸዳ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    የአርባ ምንጭ ከተማ የሰላም ፎረም አባል አቶ ገረሱ በየነ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ተግባሩን ለማከናወን እንዲያስችለው የሰላም ፎረም እንዲያቋቁም አሳስበዋል።

    ሌላኛው የሀይማኖት አባት መጋቢ ካሳዬ በየነ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ እየተስፋፉ የመጡትን የሺሻ፣ የጫትና የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

    የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከውሃና ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር የሚያጋጥሙትን ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚታዩ ሕገ ወጥ የሺሻ፣ የመጠጥና ጭፈራ ቤቶችን በመቆጣጠርና በመከታተል እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

    በውይይቱ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላም ኮሚቴ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ገልጸዋል። ዳይሬክቶሬቱ ማዕከላቱን በቅርበት እንዲከታተል ኃላፊነት የተሠጠው ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት የቢሮ መጠሪያውን ወደ ‹‹ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት›› እንደሚቀይርም አስታውቋል።

    የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህለ እንደገለፁት በፌዴራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 48(6) መሠረት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ከወሊድ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ በሚሠሩበት ተቋም ውስጥ ህጻን ልጆቻቸውን በቅርበት እየተንከባከቡና እየተከታተሉ መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማገዝ የህፃናት ማቆያ ማቋቋም አስፈላጊ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 36(1) መሠረት ህጻናት ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢውን እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

    የህፃናት ማቆያዎቹ መቋቋም ዓላማዎች ከሆኑት ውስጥ እናቶቻቸው በሥራ ምክንያት በአቅራቢያቸው ባለመኖራቸው ምክንያት በህፃናት ጤንነትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ እናት ሠራተኞች በህጻን ልጆቻቸው ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጥሩትን ክፍተቶች መሙላት፣ በሴት ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን መቀነስ እና ውጤታማነታቸውን ማሳደግ ጥቂቶቹ ናቸው።

    የህፃናት ማዋያዎቹ ከመደበኛው የሥራ መግቢያ ሰዓት  እስከ ሥራ መውጫ ሰዓት ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የመኝታ፣ የማረፊያ፣ የመጫወቻ፣ የምግብ ማብሰያ፣ የመመገቢያ አቅርቦትና አገልግሎት እንዲሁም የእንክብካቤ፣ የቅርብ ክትትል እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎቶችን አካቷል።

    እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አገልግሎቱን ለማግኘት ወላጆች የማንነት መግለጫ መታወቂያ ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን የህፃናቱን ምግብ በተመለከተ ከማቆያ ማዕከሉ ጋር በሚደረግ ስምምነት ወላጆች አዘጋጅተው ማቅረብ አልያም ተመጣጣኝ ክፍያ ፈጽመው የማዕከሉን አቅርቦት መጠቀም ይችላሉ። የማዕከሉን የውስጥ ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ተንከባካቢ ሞግዚት የመቅጠሩ ተግባር የዩኒቨርሲቲው ይሆናል።

    ወ/ሪት ሠናይት እንደገለጹት በህፃናት ደህንነት ላይ የወጡትን ህግጋት መሠረት በማድረግ በህፃናት ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ኬሚካሎች፣ ብናኞች፣ ድምፅ ያላቸው የማምረቻ ቦታዎችና መሠል ጎጂ ነገሮች የራቀ የህፃናት ማቆያ ለመገንባት ዩኒቨርሲቲው የቦታ መረጣ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የህፃናት ማቆያ ማዕከላቱ ህንፃዎች የመኝታ፣ የመጫወቻና የንፅህና መጠበቂያ ክፍሎችን የሚያካትቱ ይሆናል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 10 results - 1 through 10 (of 10 total)