-
Search Results
-
ቡሬ ከተማ ውስጥ በአቶ በላይነህ ክንዴ የተቋቋመው የፊቤላ ኢንዳስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስር እየተገነባው ያለው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር በሀገራችን የሚስተዋለዉን የምግብ ዘይት እጥረት በ60 በመቶ ይቀንሳል።
አዲስ አበባ – በሀገራችን በህብረተሰቡ የመሰረታዊ እቃዎች የዕለት ፍጆታ ላይ የአቅርቦት እጥረት ይስተዋላል። የምግብ ዘይት አቅርቦት እጥረት በመኖሩ መንግስት ለህብረተሰቡ በየወሩ በኮታ ልክ ያከፋፍላል። ይሁንና ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅሬታ ያነሳሉ። በአማራ ክልል በወር ከ23 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት አቅርቦት ያስፈልገዋል። ክልሉ እያሰራጨ ያለው ግን 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት እንደሆነ ከአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በቡሬ ከተማ በላይነህ ክንዴ በተሰኙ ባለሀብት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚል ስያሜ የምግብ ዘይትና ሌሎች ምርቶች ማምረቻ ፋብሪካ እየተገነባ ይገኛል። ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦለት ግንባታው የተጀመረው ፋብሪካ የምግብ ዘይት፣ ፕላስቲክ፣ ሳሙና እና የተቀነባበረ ሰሊጥ ያመርታል።
የፊቤላ ኢንደስትሪያል ኃ/የተ/የግል ማህበር አስተዳደር እና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ ጎጃም ዓለሙ እንደተናገሩት በ2006 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ወደ ግንባታ ገብቷል። የህንጻ እና መሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ተጠናቋል። ነገር ግን የዘይት ፋብሪካው የማሽን ተከላ ዘግይቷል። ለዚህም በዋነኝነት እንደምክንያት የሚጠቀሰው ሀገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እንደሆነ ከዚህ በፊት Mutesi የተሰኘ በአፍሪካ የንግድና ቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ሚዲያ ዘግቦ ነብር። አሁን ላይ ግን ማሽኑን ለመትከል ዝግጅቱ ተጠናቋል አቶ ጎጃም እንደገለጹት። በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ምርት ይገባል ነዉ ያሉት። የፊቤላ ኢንደስትሪ የምግብ ዘይት ማምረት ሥራ ሲጀምር ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ በቀን የማምረት አቅም ይኖረዋል። በዚህም የአማራ ክልል የዘይት አቅርቦት እጥረትን ከመፍታት አልፎ ከክልሉ ውጭ ላሉ አካባቢዎች ማድረስ ይችላል።
“የዘይት ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር በሀገራችን ያለውን የፋብሪካ ቁጥር ያሳድጋል። በሀገር ደረጃ የሚስተዋለዉን የምግብ ዘይት እጥረት ችግር እስከ 60 በመቶ ይቀንሳል። በየዓመቱ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባት እህሎችን በግብዓትነት ስለሚጠቀም ለአርሶ አደሩ የገበያ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ያደርጋል” በማለት አቶ ጎጃም ተናግረዋል። ወደ ውጭ ምርቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛልም ብለዋል።
የመብራት እና የውሀ አቅርቦት ችግር የምርት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር እና ጊዜ የማይሰጥ እንቅፋት፥ ምናልባትም ፋብሪካው ሊያጋጥሙት ከሚችሉት ተግዳሮቶች ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዉ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
◌ Ethiopian millionaire Belayneh Kinde and others awarded for investing in pulses, oilseeds & spices
የቡሬ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ፣ ኢንደስትሪ እና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይገርማል ሙሉሰዉ በበኩላቸዉ ፊቤላ ኢንደስትሪያል ኃ/የተ/የግል ማኅበር በሀገር ደረጃ የሚስተዋለዉን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግር ይቀንሳል ብለዋል። ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከማስገኘቱ በላይ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በስፋት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የህንጻ እና የመሠረተ ልማት ግንባታዉ ከ95 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ጠቅሰዉ የመብራት እና ውሀ አቅርቦት ችግር ካልገጠመው በተያዘው በጀት ዓመት ፋብሪካው ሥራ ይጀምራል። ይሁን እንጂ የመብራት እና የውሀ ችግሩ ስር የሰደደ እና ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ትኩረት እንደሚያሻዉ አቶ ይገርማል ነግረውናል።
ፋብሪካው እስከ 1500 ለሚሆኑ ሰዎች በቋሚነት እና በጊዚያዊነት የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትን ዋቢ በማድረግ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ዘግቧል።
አቶ በላይነህ ክንዴ ማን ናቸው?
- የተወለዱት በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ሰቀላ ወረዳ (ቡሬ አጠገብ) ነው፤
- የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ስላልመጣላቸው ሁርሳ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ገብተው ወታደራዊ ስልጠና ተከታትለዋል፤
- ነገር ግን በውትድርና ሕይወት ብዙም አልገፉም፤ የደርግ መንግስት ወድቆ የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ሲይዝ የውትድርና ሥራን ትተው እጅግ አናሳ በሆነ ገቢ የቀን ሥራ ላይ ተሰማሩ፤
- በቀን ሥራ ገፍትው ጥቂት ገንዘብ እንዳጠራቀሙ የማር እና የቅቤ ንግድ ጀመሩ፤
- በማር እና ቅቤ ንግድ ለአስር ዓመታት ሠርተው ንግዳቸውን በማሳደግ “በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ” የሚል ድርጅት መሠረቱ፤
- ይህንን የአስመጪና ላኪነት ሥራ ከጊዜ ወደጊዜ በካፒታል፣ በሥራ ዘርፍ እና ሠራተኞችን በመቅጠር፣… በአጠቃላይ በሁሉም አቅጣጫዎች በማሳደግ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት ሚሊየነሮች ተርታ ሊሰለፉ ችለዋል (ይህንንም በዓለም ታዋቂው የቢዝነስ መጽሔት ፎርቤስ/Forbes በ2009 ዓ.ም ዘገባው አንስቷቸው ነበር)፤
- በአሁኑ ወቅት የአቶ በላይነህ ክንዴ አጠቃላይ ሀብት ከሶስት ቢሊየን ብር (ከ111 ሚሊየን ዶላር) በላይ ሲሆን የተሰማሩበት የንግድና ምርት ዘርፍም አስመጪና ላኪነት፣ ትራንስፖት፣ የግንባታ ምርቶች፣ እርሻ እና ፋይናንስ ሲሆኑ ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ግዙፍ አክሲዮን ማኅበራት፥ ለምሳሌ ያህል ጎልደን ባስ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ አዳማ ራስ ሆቴል፣ ፀሐይ ኢንዱስትሪያል ፣ ኳሊቲ ብረታ ብረት ማምረቻ አክሲዮን ማኅበራት ውስጥ ሁነኛ ድርሻ አላቸው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና Mutesi
አዲስ አበባ – የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስነ-ሥርዓት በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የተከፈተ ሲሆን፥ ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው በምክር ቤቶቹ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን የታሰቡ ተግባራትን አንስተዋል።
በንግግራቸው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ሀገሪቱ በሁለተኛው እድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP II) አሳካዋለሁ ያለቻቸውን ዕቅዶች በሀገሪቱ በተከሰተ ግጭት እና አለመረጋጋት ምክንያት ማሳካት አልተቻለም ብለዋል።
ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች በሀገሪቱ ሲከሰቱ ከጅምራቸው እንዲቆሙ የማድረግ ውስንነት እንደነበርም ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አንስተዋል። ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ ከቶታል። በቀጣይ ህልውናዋን ለማረጋገጥ የሚያስችል ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ ተጀምሯል ። በዚህ የለውጥ ሂደት የሕዝቡን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች የህግ የበላይነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ አቋም ተይዟል ብለዋል።
ከቅርብ ወራት ጀምሮ በፖለቲካው ዘርፍ የታዩ ለውጦች ለወደፊት የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በስደት ላይ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር የተደረገው ሰላማዊ ድርድር ትልቅ ለውጥ የታየበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነበር። እንደ ዶክተር ሙላቱ ገለፃ ለዚህ ፖለቲካዊ መሻሻል ምክር ቤቱ ያፀደቀው የምህረት አዋጅ ትልቁን ሚና ተጫውቷልም ነው ያሉት። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በተደረገው ጅምር እንቅስቃሴ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ምሁራን፣ጦማሪ እና አክቲቪስቶች በነፃነት የመሥራት እድል ተፈጥሮላቸዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በተቃርኖ ውስጥ የነበሩት ሁለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክረስቲያን ሲኖዶሶች ችግር ተፈትቶ ወደ አንድ እንዲመጡ መደረጉም የለውጡ አካል ነበር። ለረጅም ዓመታት አለመግባባት ውስጥ የነበሩት አትዮጵያ እና ኤርትራ መግባባታቸው በቀጠናው የነበረውን የድህነት እና ኋላቀርነት መገለጫ ማጥፋት ችሏል።
———————————————-
———————————————-
በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ኢትዮጵያ መታደግ ችላለች። ከሌሎች አጎራባች እና የውጭ ሀገራት ጋርም ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት እንዲኖራት መደረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመለከትነው የፖለቲካ ለውጥ ውጤት ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው የዜጎችን ነፃነት እና መሰረታዊ መብቶች ከማስጠበቅ አንፃር የተሠራው ሥራ ውስን እንደነበር ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅ የሕዝቡ የዴሞክራሲ እና የፖለቲካ ጥያቄዎች የጎለበተበት በመሆኑ መንግስት የፖለቲካ ማሻሻያ የሚያደርግበት ነው ። የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል መንግስት በበጀት ዓመቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል።
አሁን በሀገሪቱ የተጋረጠው የሰላም መደፍረስ ሕዝቡን አደጋ ውስጥ አስገብቶታል። የህግ የበላይነትም ተጥሷል። ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል። የመገናኛ ተቋማት በማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል።
ተከስቶ የነበረው ሁከት እና አለመረጋጋት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አድርሷል።በስፋት እየታየ ያለውን የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ለመቀነስ እና የኢኮኖሚ ምህዳሩን ለማስፋት በዚህ የበጀት ዓመት በተጨባጭ እንደሚሠራም ተናግረዋል። መንግስት የተረጋጋ እና ቀጣይነት ያለው ማክሮ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ፅኑ አቋም እንዳለው አንስተዋል። ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው ድርድር በዚህ ዓመት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ከመክፈቻ ንግግሩ ለመረዳት እንደተቻለው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግስት (ኢጋድ) በማጠናከር እና ወደ ተግባር ገብቶ ቀጠናዊ አገልግሎቱን እንዲያሰፋ ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ትወጣለች።
ሀገራችን በርካታ አለማቀፍ የስብሰባ መድረክ አገልግሎት እየተካሄደባት በመሆኑ የቪዛ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል። የሚሰጠው የቪዛ አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።
የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እንዲሁም የመስኖ እርሻን በማጠናከር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ይሠራል።
የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ አዲሱን ፍኖተ-ካርታ መሰረት ያደረገ የሥርዓት ትምህርት ማሻሻያ የደረጋል። የሴቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በያዝነው በጀት ዓመት የጤና ተቋማት ግንባታ እና ቁሳቁስ አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራል። አሁን የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በሥርዓት አልበኞች ምክንያት እየታዩ ያሉ መፈናቀሎችን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው አንስተዋል።ምንጭ፦ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
አዲስ አበባ (ኢዜአ)፦ መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ልማት ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥሪ ከግምት ያስገባ አዲስ አቅጣጫ እየቀየሰ መሆኑን የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማኅበር አስታወቀ።
አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ሥራ ለማገዝ፣ እንደዚሁም በውጭ የሚኖረው ዜጋ በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል ማህበሩ አደረጃጀቱን መልሶ በማዋቀር ላይ ነው ተብሏል።
በሽርክና ወይንም በሌላ መንገድ በመደራጀት በአገሪቱ የልማት እድገት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ዝግጁ መሆናቸውን ኢትዮጵያዊያን የዲያስፖራ አባላት ገልፀዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መዋዕለ ንዋያቸውን በማቀናጀት አገር ውስጥ መሥራት የሚሹ ከሆነ መንግሥት የተለየ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ ባስተለላፉት መልዕክት፤ በውጭ የመኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቱ ልማት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም በስቶክ ማርኬት ወይንም በአክሲዮን ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ አባላት በተናጠልም ሆነ በመደራጀት ወደ አገራቸው ተመልሰው በልማት እንዲሰመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
ያላቸውን እውቀትና ገንዘብ በማደራጀት መቅረብ ለሚችሉ የዲያስፖራ አባላት መንግሥት የተለየ ድጋፍ እንደሚያቀርብ ነው ዶ/ር አብይ ያረጋገጡት።
ቪድዮ፦ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ሀገር ውስጥ ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት እና የሚያጋጥማቸው የቢሮክራሲ ችግር
ኢትዮጵያዊያኑ ዲያስፖራዎች በበኩላቸው መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እያደረገ ያለውን ጥሪ በአዎንታዊ መልኩ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።
በዚህም በተለይም በሽርክና ወይንም በሌላ መንገድ በመደራጀት በአገሪቱ የልማት እድገት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተደራጀ አግባብ ከጓደኞቻቸው ጋር ተነጋግረው ትልቅ ካምፓኒ ይዘው ለመምጣት ሃሳብ እንዳላቸው የተናገሩት በውጭ የሚኖሩት ወይዘሮ አማኒ መሃመድ ናቸው።
“የሥራ ሁኔታ እየተመቻቸ ነው፤ ሁሉም ሰው እውቀቱንና ገንዘቡን ኢንቨስት በማድረግ የአገሪቱን እድገት ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልካም ነው። እኔም እንደ አንድ ውጭ አገር እንደሚኖር ዜጋ ወደ ሃገሬ መጥቼ ለመሥራት ትልቅ እቅድ ይዤ እንደምመጣ ተስፋ አደርጋለሁ” ያሉት ደግሞ አቶ አማን አህመድ ናቸው።
የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማኅበር ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው ማኅበራቸው ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን የዲያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ እየሠራ ነው።
በተለይ ደግሞ በኢንደዱትሪ ፓርኮች ላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሊኖራቸው የሚችለውን ተሳትፎ ለማጎልበት ፓርኮቹን የሚጎበኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ዲያስፖራው ስለ ፓርኮቹ በቂ መረጃ እንዲኖረው ትልቅ እድል እንደሚከፍት ገልጸው ማኅበሩ መረጃ ከመስጠቱ ሥራ ጎን ለጎን ሌሎች የውጭ ዜጎችም በዘርፉ እንዲሰማሩ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል ባደረጉላቸው ግብዣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ በጥቅምት ወር ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ጀርመን የሚያቀኑ ሲሆን፥ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያዊንን አግኝተው ያነጋግራሉ ተብሏል።
አዲስ አበባ (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ በጥቅምት ወር ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ጀርማን የሚያቀኑ ሲሆን፥ በዚሁ ጉብኝታቸውም ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል (Angela Merkel) እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን እንደሚገናኙም ነው የተገለጸው።
የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል በፈረንጆቹ ነሃሴ ወር በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ በመደገፍ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጎን መሆናቸውን በስልክ በገለጹበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀርመን ይፋዊ ጉብኝት እንዲያደረጉ መጋበዛቸውም ታውቋል።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ በጥቅምት ወር መጨረሻ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ጀርመን የሚያቀኑ ሲሆን፥ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያዊንን አግኝተው ያነጋግራሉ ተብሏል።
በፈረንሳይ ፓሪስ፣ ጀርመን ፍራንክፈርት ከተሞችም በሚዘገጁ መድረኮችም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር እንደሚገናኙ የተገለጸው።
ሀገራዊ ዜና፦ አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ደመቀ መኮንን በድጋሚ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ
በፈረንጆቹ ጥቅምት 31 ቀን 2011 (ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓም) ዓም በጀርመን ሁለተኘዋ ከተማ ፍራንክፈርት ላይ መድርክ እንደሚዘጋጅ እና ጠቅላይ ሚኒትሩ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያዊንን አግኝተው እንደሚያነጋግሩም ታውቋል።
ለዚሁ ፕሮግራምና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አቀባበልን እስመልክቶ ከ80 ማህበራት የተውጣጡ አበላት ያሉት ኮሚቴ አየሰራ መሆኑንም ነው የተገለጸው።
በጀርመን የኢትዮጵያ ቆንሰላ ጄኔራል ምህረት አብ ሙሉጌታ እንደገለጹት አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ለውጥ በመደገፍ 25 ሺህ ያህል ኢትዮጵያን ፍርንክፈረት ኮመርዝባክ አረና ስታዲየም (Commerzbank-Arena) በሚዘጃጀው ፕሮግራም ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት