Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 286 through 300 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ራሷን ንግሥተ ነገሥት ብላ በምትጠራው ግለሰብ (እህተ ማርያም) ላይ ምርመራ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ

    ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻውን እህተ ማርያም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋ በቁጥጥር ስር ስትውል አብረው ፖሊስ ጣቢያ ድረስ የመጡ 30 የሚጠጉ ተከታዮቿ ግርግር ሊፈጥሩ ቢሞክሩም ፖሊስ መክሮ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።

    በጥላሁን ካሣ (ኢብኮ) |

    አዲስ አበባ – የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ራሷን “ንግሥተ ነገሥት ዘ–ኢትዮጲያ” ብላ በምትጠራው እና የአራት ልጆች እናት በሆነችው እህተ ማርያም ላይ ምርመራ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ። ፖሊስ ግለሰቧን በቁጥጥር ስር ያዋላት ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. (የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የወታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣሷ ምክንያት) ነበር።

    ከሁለት ዓመት በፊት ባሏ በሞት የተለያት የ43 ዓመቷ እህተ ማርያም በሚል መጠሪያ የምትታወቀው ሴት ስለ ማንነቷ ለፖሊስ ስትገልጽ፥ ትክክለኛ መጠሪያ ስሟ ትዕግሥት ፍትህአወቀ አበበ መሆኑንና መኖሪያዋ አዲስ አበባ ውስጥ ኮልፌ መብራት ኃይል አካባቢ እንደሆነ ተናግራለች።

    ግለሰቧ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ በመኖሪያ ቤቷ በሃይማኖት እና በምገባ ስም እስከ መቶ የሚደርሱ ሰዎችን ሰብስባ በመገኘቷ በቁጥጥር መዋሏ ይታወቃል።

    በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር በድሉ ግርማ፥ ተጠርጣሪዋ እህተ ማርያም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ኮሮናቫይረስ የለም ተሳሳሙ፣ ተቃቀፉ፣ ተጨባበጡ በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመፃረር የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ አጋልጣለች በሚል መጠርጠሯን ገልጸዋል። አክለውም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የተጠረጠረችበት ወንጀል ጉዳይ እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል።

    ተጠርጣሪዋ በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መሀል ላይ የሚገኘውን ኮከብ ቀድዳ አውጥታ በማቃጠሏ መቀጣቷም ተጠቅሷል። ግለሰቧ ከሰማይ ታዝዣለሁ (የማደርገውን ሁሉ የማደርገው ከሰማይ በሚመጣልኝ መልእክት ነው) በማለት ማረሚያ ቤት ድረስ በማቅናት ታራሚዎችን ልታስወጣ ስትሞክር እጅ ከፍንጅ ተይዛ መቀጣቷንም ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።

    ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋ በቁጥጥር ስር ስትውል አብረው ፖሊስ ጣቢያ ድረስ የመጡ 30 የሚጠጉ ተከታዮቿ ግርግር ሊፈጥሩ ቢሞክሩም ፖሊስ መክሮ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም አመልክተዋል። ከእርሷ ጋር በግብረ አበርነት የተጠረጠሩ ሁለት ሴቶች ግን ምርመራ እየተካሔደባቸው መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተር በድሉ ግርማ ተናግረዋል።

    ግለሰቧ ለፖሊስ በሰጠችው የእምነት ክህደት ቃል ርትዕት ተዋሕዶ የተሰኘ ሃይማኖት ለማስተዳደር ከሰማይ እንደተላከች እና ራሷም ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ መሆኗን ተናግራለች።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ንግሥተ ነገሥት እህተ ማርያም

    Anonymous
    Inactive

    የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ይፋ ሆነ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ረቂቅ አዋጅ ሚያዝያ 2 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዋጁን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ይዘት በሚመለከት ሚያዝያ 3 ቀን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

    በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 94 ንዑስ ቁጥር 4 መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል። በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ዝርዝር በሚመለከት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል። ማስፈፀሚያ ደንቡ አጠቃላይ አራት ዋና ዋና ከፍሎች ያሉት ሲሆን ይሄውም ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግደታዎችን የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ክልከላን በሚመለከት ማንኛውም ሃይማኖታዊ ይሁን ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎችም ከአራት (4) ሰው በላይ ስብሰባዎች ክልክል ናቸው። አራት ሰዎችም ቢሆኑ ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ የጠበቀ መሆን እንዳለበት አቃቤ ህአቃቤ ሕጓ አብራርተዋል። ቀብርና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ሊፈቀዱ የሚችሉበት አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል። ታራሚዎች ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚፈቀድ ቢሆንም፥ ጥየቃ ለሚሄዱ ሰዎች የማይፈቀድ መሆኑ ተገልጿል።

    በፖሊስ የተያዙ እስረኞችንም ስንቅ ከማቀበል በስተቀር መገናኘት የተከለከለ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል። በድንበር አካባቢ ከካርጎ፣ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዝግ ተደርገዋል። የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይም አስገድዶ መቀበል/ ማስከፈል መጨመር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል። ሠራተኞችን መቀነስና የሥራ ቅጥር ውል ማቋረጥም መከልከሉን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።

    በዚህ ደንብ መሠረት ተማሪዎችና መምህራን በኦንላይን (online) ካልሆነ በአካል እንዲገናኙ አይፈቀድም። ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የሕፃናትም ይሁን የሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሰላምታ የተከለከለ ነው።

    በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ መሆኑን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ዜና ሳንወጣ፥ እስከዛሬ ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ስዎች ቁጥር ሰባ አንድ (71) መድረሱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቋል። ከእነዚህ ተጠቂዎች መካከል ሦስቱ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ሀምሳ ስድስት (56) ታማሚዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ሁለት የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ አስር (10) ሰዎች ደግሞ ከሕክምና በኋላ ከቫይረሱ ነፃ ሆነው አገግመዋል።

    እስከዛሬ (ሚያዝያ 4 ቀን) ከሰዓት በኋላ ድረስ በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ1.79 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከ109,200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። በአጠቃላይ ቁጥራቸው 406,100 አካባቢ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ከኮቪድ-19 በሽታ ማገገማቸው ታውቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኮቪድ-19

    Anonymous
    Inactive

    የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

    አዲስ አበባ (ሠ.ማ.ጉ.ሚ.) – ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ።

    የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር (ሠ.ማ.ጉ.ሚ.) ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው ላላቸው አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

    በዚህም ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽና በስሩ ላሉት ብሔራዊ ማኅበራት ሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ብር፣ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር ሦስት መቶ ሺህ ብር እንዲሁም ለኢትዮጵያ አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር ስድስት መቶ ሀምሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ አስራ ሰባት ብር ድጋፍ ተደርጓል።

    የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች እና ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አረጋውያን እንደሚገኙ ጠቁመው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን በመወጣት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

    እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለኮሮና ቫይረስ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአቅም ግንባታ ማዕቀፍ ሲያደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እንዲውል መወሰኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፥ ድጋፉ አዲስ አበባንና ክልሎችን ባቀፈ ሁኔታ የምግብ ፍጆታና የንፅህና መጠበቂያ እቃዎች አቅርቦት እንደሚሸፈንበት ተናግረዋል። በቀጣይም ከተለያዩ የልማት ድርጅቶችና የበጎ ፈቃድ ማኅበራት ጋር በመሆን ድጋፉ እንደሚቀጥል ዶ/ር ኤርጎጌ ተናግራዋል።

    በዕለቱ ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን የአካል ጉተኞች የእንቅስቃሴ ችግርን ለመቅረፍ አሜሪካን አገር ከሚገኝ አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ (Agape Mobility Ethiopia) ጋር በመተባበር ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ወጪ 183 ዘመናዊ ዊልቸር (wheelchair) ርክክብ የተደረገ ሲሆን ፥ ድጋፉ በሱማሌ፣ ሀረርና ደቡብ ክልሎች ለሚገኙ የእንቅስቃሴ ችግር ላለባቸው አካል ጉዳተኞች የሚውል ይሆናል ተብሏል። በተጨማሪም በአፍሪኮም የቴክኖሎጂ ኩባንያ (AFRICOM Technologies Plc) እና ድርሻዬን ልወጣ የበጎ ፍቃደኞች የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ ተደርጓል።

    በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እንደሚጠበቅ የተናገሩት ማኅበራቱ ሚኒስቴር፥ መሥሪያ ቤቱ ላደረገው ድጋፍ ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።

    እስከ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ በ አጠቃላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ይገኛሉ። አራቱ ያገገሙ ሲሆን፤ ሁለቱ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ ሀገራቸው ተሸኝተዋል።

    ምንጭ፦ ሠ.ማ.ጉ.ሚ./ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

    Anonymous
    Inactive

    የግብርና ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የሚደርገውን ጥረት ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

    አዲስ አበባ (የግብርና ሚኒስቴር) – የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

    በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የዓለማችን ሀገራት በፍጥነት እየተሰፋፋ ያለው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የዓለም ስጋት ከሆነ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ሀገራትም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ይበጃል ያሉትን መፍትሄ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። በሽታው ወደ ሀገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የመከላከል ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ።

    የግብርና ሚኒስቴርም ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ሀገራዊ ተልዕኮ ድርሻውን ለመወጣት በስሩ ያሉትን ተጠሪ ተቋማት በማስተባበር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል ያስችል ዘንድ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ማዕከል 1 ሚሊየን ብር እና የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራር አባላት የ1 ወር ሙሉ ደመወዝ 363,731 ብር በጠቅላላው 1,363,731 ብር ብሔራዊ የሀብት ማፈላለግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለሆኑት ለአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ አስረክቧል።

    ብሔራዊ የሀብት ማፈላለግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንደተናገሩት፥ በዜጎችና በሀገር ደህንነት ላይ ትልቅ ስጋት የደቀነው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የድጋፍ አሰባሳብ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት የበኩላቸውን ድጋፍ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል። የግብርና ሚኒስቴር በስሩ የሚገኙትን ተጠሪ ተቋማት አመራር አባላት በማስተባበር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ የመጀመሪያው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መሆኑንም አምባሳደሩ ገልፀዋል።

    በመጨረሻም አምባሳደር ምስጋኑ ወረርሽኙ አስከፊ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ርብርብ ላይ የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ላበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ በብሔራዊ የሀብት ማፈላለግ ኮሚቴው ስም ምስጋና አቅርበዋል።

    የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው፥ ወደ ሀገራችን የገባውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲያስችል የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ካበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርመራ ማዕከል የኮሮናቫይረስን ምርመራ ለመሥራት በተወሰነው መሠረት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል።

    ከግብርና ሚኒስቴር ዜና ሳንወጣ፥ ሚኒስቴሩ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታትና ለመከላከል የኬሚካል ርጭት ያካሄደ ሲሆን፤ የኮሮናቫይረስ (ኮቪዲ-19) ስርጭትን ለመግታትና ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በመሆኑም በዋናው መሥሪያ ቤት ግቢ የሚገኙ ቢሮዎችን፣ የደረጃ መወጣጫ ደጋፊ ብረቶች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የአጥር ግቢ በር፣ በአጠቃላይ ከሰው ጋር ንክኪ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚታሰቡ የግቢ ውስጥና ውጭ ቦታዎችን፣ የአጥር ብረቶችን፣ የመብራት ምሰሶዎችን፣ ወዘተ… መጋቢት 22 እና 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሠራተኛው ቢሮ ከመግባቱ በፊት እና በኋላ ተህዋስያንን በሚገል ኬሚካል /disinfectant/ ርጭት በማድረግ የሠራተኞችን ሕይወት ለሚታደግና የቫይረሱን ስርጭት የሚገታ ሥራ ሠርቷል።

    ኮሮናቫይረስን (ኮቪዲ-19) ለመከላከል በግለሰብ ደረጃ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቢሮዎቻቸውን፣ ግቢያቸውንና አካባቢያቸውን ከቫይረሱ ነጻ ለማድረግ የተህዋስያን መከላከያ ኬሚካል መርጨት እንደሚገባቸውና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስተማሪያ ለማድረግ እየረጩ እንደሆነ በርጭቱ የተሳተፉ ሠራተኞች ተናግራዋል። ሌሎችም ሊተገብሩት የሚገባ በጎ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኮሮናቫይረስ ኮቪዲ-19

    Semonegna
    Keymaster

    ቱሉሞዬ እና ኮርቤቲ የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተከናወነ

    አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የፈረንሳዩ ሜሪድየም (Meridiam) ኢንቨስትመንት ኩባንያ የከርሰ ምድር እንፋሎት ኃይል (geothermal energy) ማመንጫ ገንብቶ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

    በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በተካሄደው ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉሞዬ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ሚስተር ማቲው ፒለር (Mathieu Peller) እና የኮርቤቲ ተወካይ ናቸው።

    የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት በኃይል ልማት ዘርፍ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮችን በማስፋት የግል አልሚዎችን ማሳተፍ ተጀምሯል። አሁን የተፈረመው ስምምነትም ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ ወደ ግንባታ እንዲገባ ከግል አልሚዎች ጋር ድርድር ሲያካሂዱ የቆዩትን አባላት አመስግነዋል።

    የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ስብጥሩን በማመጣጠን የሀገሪቱን ኢነርጂ የማምረት አቅም እንደሚያሳድግ በመግለፅ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚን የፈጠረ እንደሆነም ጠቁመዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ከሆነ ሥምምነቱ በሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ የግል አልሚዎችም ትልቅ ዕድል እንደሚከፍትላቸው አብራርተዋል።

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከኩባንያው ጋር የነበረው ድርድር ተጠናቆ ስምምነት ላይ መደረሱ እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው የግል አልሚዎች ተሳትፎ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚያደርገው የሃይል አቅርቦትና ስብጥር የሚግዝ መሆኑን በመግለጽ ሌሎችም የግል አልሚዎች በዚህ ረገድ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

    በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉሞዬ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ሚስተር ማቲው ፒለር (Mathieu Peller) በበኩላቸው በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስመንት ኩባንያ ዋና መቀመጫን አዲስ አበባ ያደረጉት ኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት በመሆኑ ነው ብለዋል። አሁን ከጀመሩት የከርሰ ምድር እንፋሎት በተጨማሪ በትራንስፖርት እና በተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችም መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሰፊ ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

    ቱሉሞዬ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን ግንባታውም በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።

    በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታም 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ግንባታውም እ.ኤ.አ. በ2023 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል። ሁለተኛውን ምዕራፍ ደግሞ 100 ሜጋ ዋት ለማመንጨት እ.ኤ.አ. ከ2023 በኋላ ገንብቶ ለማጠናቀቅ መታሰቡን ለማወቅ ተችሏል።

    የፕሮጀክቱን ግንባታ የሚያከናውነው ቱሉሞዬ ጂኦተርማል ኩባንያ ሲሆን የቁፋሮውን ሥራ ደግሞ ኬንያ ጀነሬሽን የተባለ የኬንያ ሥራ ተቋራጭ የሚያከናውን ሲሆን ሚኪዳ የተባለ ሃገር በቀል ኩባንያም እንደሚሳተፍ ማወቅ ተችሏል።

    ቱሉሞዬ እና ኮርቤቲ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪ እያንዳንዳቸው 800 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም ነው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የተጠቆመው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ቱሉሞዬ እና ኮርቤቲ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የምርጫ 2012 ኦፕሬሽን እቅድ እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ የፈጠረውን ችግር ገምግሞ ያሳለፈው ውሳኔ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ለማስፈፀም የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል።

    በዚህ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲካሄድ ተወስኖ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ እያከናወነ ለሕዝብ እያሳወቀ እንደቆየ ይታወሳል። በዚህም መሠረት በያዝነው መጋቢት እና በሚመጣው ሚያዝያ ወራት 2012 ዓ.ም. መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። መከናወን ካለባቸው ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፤ ስልጠናና ስምሪት፤ የመራጮች ትምህርት፤ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ስርጭት የመሳሰሉት ናቸው።

    እነዚህን ሥራዎች በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ለማከናወን ቦርዱ ተገቢ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ባለፉት ሳምንታት በሃገራችን እና በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ አስገድዷል። ከዚሁ የወረርሽኝ ሥጋት የተነሳ በርካታ ሃገራት ምርጫን ጨምሮ መንግሥታዊ ዕቅዶቻቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል። በሃገራችንም መንግሥት ወረርሺኙን ለመከላከል የሰዎች ግንኙነትን የመቀነስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በመወሰኑ የመንግሥት ሠራተኞች አብዛኛውን ሥራ ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል፡መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ጥብቅ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በክልል መንግሥት መስተዳድሮች ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የውስጥና የአገር አቋራጭ የትራንስፓርት ገደቦች፣ የመሰብሰብ ገደቦችን የመሳሰሉ ጥብቅ ክልከላዎች ይፋ ሆነዋል።

    በመንግሥት ከተላለፉ የክልከላ ውሳኔዎች በተጨማሪ ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለምአቀፍ አጋር ድርጅቶች አብዛኞቹ ሠራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ሲደረጉ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥቂቶቹን ብቻ በማስቀረት ሠራተኞቻቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል። ከላይ የተጠቀሱት ድምር ሁኔታዎች በሚያዚያ ሊጀመር በታቀደው የመራጮች ምዝገባ እና ተያያዥ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል። ከዚህ የሚከተሉት ከችግሩ ማሳያ ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው።

    • በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋዘን የሚገኙ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ሥራ በሁለት ሳምንት ዘግይቷል፤
    • የቀሪ ህትመት ውጤቶች ግዥ በቫይረሱ ምክንያት በተፈጠረ የአቅርቦት ሰንሰለት መደናቀፍ ምክንያት ተጓቷል፤
    • ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ቁጥራቸው 1000 /አንድ ሺ/ በላይ የሚሆን አሰልጣኞችን ክክልሎች ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት አልተቻለም፤
    • ለ150,000 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ) የምርጫ አስፈፃሚዎች በየክልሎቹ መሰጠት ያለበትን ስልጠና መጀመር አልተቻለም፤
    • ቦርዱ የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት ኮቪድ-19 ቫይረስን አስመልክቶ በሚወጡ የማኅበረሰብ ጤና መልእዕቶች ሊዋጡ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

    የቫይረሱ ስጋት በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በአጠቃላይ በተለይም በአፋጣኝ መፈጸም ባለባቸው የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና፤ የመራጮች ትምህርት ተግባራት አፈፃፀም ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ቦርዱ ከሕግ አውጪው አካል፤ በጉዳዩ ላይ ከሚሠሩ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያዎች፣ ከዓለምአቀፍ አጋሮች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጋር ተመካክሯል።

    ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት አብዛኞቹ ፓርቲዎች የችግሩን ግዝፈት እና በምርጫ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ተገንዝበው ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተመካክሮ አማራጭ የአፈጻጸም ዕቅድ ሊኖረው እነደሚገባ መክረዋል። ይሁን እና በዚህ አግባብ የሚወሰደው እርምጃ ችግሩ ከሚጠይቀው በላይ የሆነ መዘናጋት እንዳያመጣ ቦርዱ በወረርሽኙ አፈጻጸማቸው የማይስተጓጎል ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል።

    ቦርዱ ለውሳኔው መሠረት የሚሆነው የዳሰሳ ጥናት በአማካሪ ባለሙያዎቹ ተሠርቶ እንዲቀርብለትም አድርጓል ። የተፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ ከታቀደው የምርጫ ምዝገባና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ባግባቡ ለመዳሰስ ያስችለው ዘንድ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመሥርቶ ቦርዱ ሁለት የቢሆን ሁኔታ ግምቶች (scenarios) ተመልክቷል።

    የመጀመሪያው የቢሆን ሁኔታ ግምት መሠረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአራት ሳምንት ብቻ ማለትም እስከ ሚያዚያ 7 ሊቆይ ይችላል በሚል ግምት ላይ የተመሠረተ ነው። ክልከላው የአራት ሳምንት ብቻ የሚቆይ ከሆነ አሁን ባለው የጊዜ ሰሌዳ ዋና የሆነውን የመራጮች ምዝገባ ቢያንስ በአራት ሳምንት የሚገፋው ሲሆን ምዝገባው ቢከናወን የማኅበረሰቡ ተሳትፎ፣ የምርጫው ተአማኒነት ማግኘትን እና የኦፕሬሽን ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ድጋፍን ሙሉ ለሙሉ ማግኘትን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ያሳያል።

    ቫይረሱ በቁጥጥር ስር ካልዋለም የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ የማኅበረሰብ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ከማኅበረሰብ የጤና ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር ጥቂት እንኳን ክልከላዎች የሚኖሩ ከሆነ ይህንን ዕቅድ ወደ ተግባር መለወጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

    በተጨማሪም በያዝነው ሳምንት መንግሥት ተጨማሪ እርምጃ እየወሰደ መቀጠሉ፣ እንዲሁም ቦርዱ ከጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ባደረገው ውይይት እስከ ሚያዚያ መጨረሻም ሁኔታው የመሻሻል ዕድል እንደሌለ የተገለጸለት በመሆኑ፣ በዚህ የቢሆን ሁኔታ ግምት በታየው መልኩ የመራጮች ምዝገባን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን እንደማይቻል ቦርዱ መረዳት ችሏል።

    የዳሰሳ ጥናቱ ሁለተኛ የቢሆን ሁኔታ ግምት የሚያሳየው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፤ በመሆኑም በመንግሥት የሚደረግ ማንኛውም ከአራት ሳምንት የበለጠ ክልከላ ቢኖር ምርጫውን በተያዘለት ሕገ-መንግሥታዊ የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንዳይቻል ያደርገዋል፤ ስለዚህም ወረርሽኙን መቆጣጠር በሚቻል ጊዜ ቦርዱ ዕቅዶቹ ላይ የተለያዩ ማሻሻያ ሊደርግ ይገባል የሚል ነው።

    በመሆኑም ቦርዱ እነዚህን የቢሆን ሁኔታ ግምቶች መርምሮ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ካደረጋቸው ምክከሮች ያገኘውን ግብአት ታሳቢ በማድረግ የሚከተለውን ወስኗል።

    1. በተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሄድ የማይቻለው መሆኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሠረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ ወስኗል፤
    2. ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን ዕቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቀሴውን የሚያስጀምር ይሆናል፤
    3. ቦርዱ ባደረጋቸው ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናት ላይ በግልጽ የተለዩ፣ በኮቪድ-19 የማይስተጓጎሉ፣ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያሥችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበት ወስኗል።
    4. በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ምክር ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንጻር የሚሰጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ይህ ውሳኔ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት ወስኗል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

    Anonymous
    Inactive

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው “ሰው ነኝ ሌሎችንም እረዳለሁ” የተባለው ኮሚቴ፣ በመንግሥት የተቋቋመው የአማካሪ ምክር ቤት እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ያሉበት ሁኔታ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች “ሰው ነኝ ሌሎችንም እረዳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚሠራ ኮሚቴ አቋቋሙ። ኮሚቴው መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የግንዛቤ ማስጨበጥና ሌሎች የእርዳታ ማሰባሰብ ሥራዎች ላይ እንደሚሠራ ነው ያስታወቀው።

    ተነሳሽነቱን ወስዶ ኮሚቴውን ያዋቀሩት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ “ኮሮናቫይረስ ዘር፣ ቀለምና ሀይማኖት ሳይለይ የሰው ልጅን በስፋት እያጠቃ ይገኛል” ብለዋል።

    ኮሮናቫይረስ የተከሰተባቸው አገሮች በራሳቸው መንገድ ችግሩን ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውሰው፥ ”እኛ ኢትዮጵያውያን የሌሎችን እርዳታ ሳንጠብቅ ስርጭቱን መግታት እንችላለን” ብለዋል አቶ ኦባንግ። “ይህ እውን እንዲሆን ግን ራሳችንን በመጠበቅ አንድ ሆነን መቆም ይገባል” በማለት ጨምረው አስገንዝበዋል።

    ከአካለዊ ንክኪ ርቀን በመንፈስና ተግባር አንድ ሆነን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መግታት ይገባናል ሲሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የኮሚቴው አባላትም ተናግረዋል።

    ሙዚቀኛ ዘለቀ ገሰሰ፥  ወጣቶችን ኮሮና አይዝም የተባለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማሰተካከልን እና ሕብረተሰቡ ሊያውቃቸው የሚገቡ ትክክለኛ መረጃዎች በኪነ-ጥበብ ለሕዝቡ ለማድረሰ እንደሚሠራ አሰታውቋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጤና ሚኒስቴር የሚመራውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ለማጎልበትና ለማፍጠን በጤና ሙያ ማኅበራት የተመሠረተው የአማካሪ ምክር ቤት ሥራ ጀምሯል። ውጤታማ ሥራ ለመሥራትም በስድስት ግብረ ኃይሎች የተዋቀረ ሲሆን እነሱም፦

    1. ማኅበረሰቡን ስለ በሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች በሳይንሳዊ ዘዴ ማስተማርና ማንቃት፣
    2. ጤና ተቋማት የባለሙያውንና የታካሚውን ደኅንነት በጠበቀ መንገድ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ማዘጋጀት፣
    3. የሕክምና መሣሪያዎች መድኃኒቶችና ግባቶች አቅርቦት እንዲሻሻል ማድረግ፣
    4. የወረርሽኝ ስርጭት ቅኝትና በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር የተገናኙ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት፣
    5. የወረርሽኙንመጠነስርጭት፣ማንንእንዲሚያጠቃ፣የትበብዛትእንደሚከሰት፣በጊዜሂደትያለውንለውጥናለወረርሽኙአጋላጭሁኔታዎችንማጥናትናበመረጃማጠናቀር፣እና
    6. ከወረርሽኙጋርተያይዘውየሚመጡየአዕምሮጤናእናየሥነ-ልቦናእናማኅበራዊጫናዎችንመፍታትናቸው።

    ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሰጠው ወቅታዊ መግለጫ፥ ማንኛውም ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ መንገደኛ በሆቴል ውስጥ ለ14 ቀናት ተለይቶ እንዲቆይ በተወሰነው መሠረት እስካሁን ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት (636) መንገደኞች ወደ ሀገራችን የገቡ ሲሆን፥ በተመረጡ አስር ሆቴሎች ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።

    መንገደኞቹ ባሉባቸው ሁሉም ሆቴሎች የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።

    በሌላ በኩል ከላይ የተገለፀው ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስምንት መቶ ሰባ ሶስት (873) ሰዎች በቤታቸው ሆነው በስልክ ለ14 ቀን በጤና ባለሙያዎች የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። ከዘሁ ጋር በተያያዘ ለ14 ቀናት ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው ሁለት ሺ ዘጠና (2,090) ሰዎች ክትትላቸው እንዲረቋጥ ተደርጓል።

    ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ የኮሮናቫይረስ በሽታ ምልክት ያሳዩ ሰባ ዘጠኝ (79) ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል።

    በሀገራችን እስካሁን አሥራ ስድስት (16) ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው በላቦራቶሪ ምርመራ መረጋገጡ ኢንስቲትዩቱ እና የጤና ሚኒስቴር በመግለጫዎቻቸው ማሳወቃቸውን ተዘግቧል። ከእነዚህ አሥራ ስድስት (16) ታማሚዎች መካከል ሁለቱ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን አሥራ አራት (14) ታማሚዎች በለይቶ ሕክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ። የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸውና የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ከሚገኙ ታማሚዎች ውስጥ አንድ (1) ታማሚ በድጋሚ በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ መሆናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት ተጨማሪ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚቆዩ ይሆናል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት/ የጤና ሚኒስቴር/ አኢጋን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኮሮናቫይረስ

    Semonegna
    Keymaster

    መንግሥት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ አዳዲስ እርምጃዎችን ይፋ አደረገ

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን ለመከላከል ከተቋቋመው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ጋር ያለውን የክንውን ሁኔታ እና ተጨማሪ መመሪያዎች እንዲሁም <ኮቪድ-19>ን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ በኢንተርኔት አማካኝነት (virtually) ውይይት አድርገዋል።

    እስከ ዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ አጠቃላይ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 በመጨመሩ፣ ቫይረሱ በፍጥነት እየተዛመተ እንዳይሄድ ለመግታት ሲባል በቂ የመከላከል ሥራዎች መሠራታቸውን ለማረጋገጥ፣ የፌደራል መንግሥት በስፋት የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተዋል።

    ከውይይቱ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሚከተሉትን ተጨማሪ ቁልፍ እርምጃዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን ጥሪም አቅርበዋል።

    በዚህም መሠረት፦

    1. ከዛሬ (መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከሰዓት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚደርሱ እና ለለይቶ መከታተያ በተዘጋጁት ሆቴሎች ለመቆየት አቅም የሌላቸው መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች ለ15 ቀናት ተለይተው እንዲቆዩ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይሆናል።
    2. ከዛሬ አንስቶ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን ጨምሮ፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የሚቆዩ ይሆናል።
    3. በገበያ ስፍራዎች እና በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ በጥብቅ ተፈጻሚ ሊደረጉ ያስፈልጋል። የፌደራል መንግሥት አስከፊ ብሔራዊ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ሀይማኖታዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ሕገመንግሥታዊ መብት አለው። ሆኖም፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት፣ ዜጎች የማኅበራዊ ርቀት መመሪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
    4. ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍን የሚጠይቅ ከሆነ ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
    5. የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው መገልገያዎችን የያዙ ከ134 በላይ ተቋማት ለለይቶ መከታተያ፣ ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና እንዲሆኑ ተለይተዋል። ስለዚህ፣ መንግሥት ሁሉም ዜጎች እንደ አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ አንሶላዎች፣ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና ሌሎች ከሕክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው እና የሌላቸው መገልገያዎችን ለማሰባሰብ በመሥራት ላይ የሚገኘውን የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ ያቀርባል።
    6. የማክሮ-ኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴው ኢኮኖሚው ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመቀየስ በልዩ ልዩ ዘርፍ ከተሠማሩት አበይት የኢንደስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትን ሲያካሂድ ቆይቷል። ይህንኑ ተከትሎም፣ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚከተሉት እርምጃዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡-
      • የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎች እና ግብአቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ይደረጋል።
      • የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ የመቀጠል እና ባንኮች በ<ኮቪድ-19> ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች ይሰጣል።
      • የውጪ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው እና የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎችን እና ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ ይደረጋል።
      • በፋይናንስ አገልግሎት የተነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘት እና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ ክፍያ እና ገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ ያደርጋል።
      • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ተደርጓል። ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሂደቱን በተለየ መልኩ እንዲያፋጥን ይደረጋል።
      • የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የሸቀጦች እጥረት እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር በንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

    ምንጭ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

    ኮቪድ-19

    Semonegna
    Keymaster

    በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

    በሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠር፣ በከተማና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ!

    ወቅታዊ የሰው ልጅ ሥጋት በመሆን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሥጋት ስለተከሰተ መንግሥታት ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከሞት ለመጠበቅ አዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ።

    ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ እምነትና ቀኖናን ጠብቆ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ኃላፊነት አለባት።

    ስለዚህ ቋሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፡-

    1. በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ እጅ በመንሳት ወይም በእማሄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
    2. ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምዕመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
    3. ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አሰፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ እጆቻንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
    4. ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማኅሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
    5. የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
    6. በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልዕኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር
    7. ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለከተ፡-
      • በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
      • በዕለቱ ለሚቆርቡ ምዕመናን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣
      • ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
      • የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
      • ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈፃፀም ጉዳዮችን ግብረ ኃይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፤
    1. ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና በውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈፀም፣
    2. ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምኅረትና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣
    3. በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሐዘን፣ በእድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈፃፀምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሠራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈፀም፤
    4. ምዕመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣
    5. ለነዳያን እና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣
    6. ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል።

    በአጠቃላይ በበሽታው እስካሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምህረቱን እንዲሰጥልን እንጸልያለን፤

    በመላው ዓለም ዜጎቻቸውን በበሽታው ለተነጠቁ ሁሉ መጽናናቱን እንዲሰጥልን ያረፉትንም እንዲምርልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፤

    በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን የራሳችሁና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠበቅ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲሆኑ በጥብቅ እናስታውቃለን።

    ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ዓለማችንን ከጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን። አሜን።

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

    አባ ማትያስ ቀዳማዊ
    ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
    (መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም.)
    አዲስ አበባ

    በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በከሚሴ ከተማ ቅርንጫፍ (ካምፓስ) ለመክፈት ቦታ ተረከበ

    ከሚሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተደራሽነቱን በማስፋፋት የግቢ (የካምፓስ) ብዛቱን ሦስት ለማድረስ ከከሚሴ ከተማ አስተዳደር 100 ሄክታር መሬት ተርክቧል። በዚህም የቦታ ርክክብ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የከሚሴ ከተማ አስተዳደር በስጦታ ያበረከተውን ቦታ ከጎበኙ በኋላ ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል። በዚህም ውይይት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በከሚሴ በቀጣይ የሚከፈተው ኮሌጅ የከሚሴንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥቅም፣ ፍላጎትና ሃብት መሰረት ያደረገ እንዲሆን በጥናት ላይ ተሞርኩዞ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱም የከሚሴ ከተማ አስተዳደር ላደረገው የቦታ ስጦታ ላቅ ያለ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ፥ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በየዘርፋቸው ቦታውን ተረክቦ የከሚሴንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥያቄዎች ለመመለስ በሎም የተሰማቸውን አስተያየት እንዲሰጡ አድርገዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በርካታ በሆኑ የቅድመና ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሆነ የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ብረሃን አስማሜ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የትምህርት ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ኮሌጆችን፥ ትምህርት ክፍሎችንና መርሀ-ግብሮችን (ፕሮግራሞችን) ለመክፈት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

    በምሥራቅ አማራ ጨፋ ሸለቆ ያለው ከፍተኛ የሃብት ክምችት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ተርፎ ለገበያ እንዲውል የምርምር ማዕከል በቦታው በመክፈት ሕዝባችንን ከድህነት የሚያወጡ የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ዕድሉን ለመጠቀም እንደሚሠሩ የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ኃይሉ ናቸው። የቦታው ሕጋዊ ሰነዶች በሙሉ በዩኒቨርሲቲው ስም ሆነው እንደተጠናቀቁ ተገቢውን የግንባታና ተቋሙን የማደራጀት ተግባራት እንደሚጀምሩ የገለጹት የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ፥ ዩኒቨርሲቲው ተደራሽነቱን በማስፋት የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የአቅሙን ሁሉ ይሠራል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    በከሚሴና አካባቢ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ ከክህሎት ስልጠና ጀምሮ በአዋጭ የሥራ መስኮች ወጣቱ እንዲሰማራ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የቢዝነስ ልማትና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዝዳንቷ ዶ/ር አጸደ ተፈራ ሲገልጹ፥ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ በበኩላቸው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ፍላጎት በማየት በኮምፒዩተር ሳይንስ መርሀ-ግብሮችን መክፈት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮች በጉብኝቱ ያዩትን፣ የተሰማቸውንና በቀጣይ በቦታው ቢሠራ ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል። ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት ከከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ፣ የመዝናኛ፣ የቤተ መጻሕፍትና ተዛማጅ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን የሚሰጥበት ማዕከል ተቀብሎ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወቅ ነው።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሚሴ ካምፓስ

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራር አባላት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በማስገንባት ላይ የሚገኘውን ግዙፍ የምግብ ዘይት ፋብሪካን ጎበኙ

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራር አባላት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በማስገንባት ላይ የሚገኘውን ግዙፍ የምግብ ዘይት ፋብሪካን ጎበኙ። ፋብሪካው በተያዘው በጀት ዓመት ተመርቆ ምርት እንደሚጀምር በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፋይናንስ በማድረግ እየተሳተፈበት የሚገኘውና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቡሬ ከተማ በኢትዮጵያዊው ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ የተገነባው የዘይት ፋብሪካ በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርት ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ መሸፈን የሚያስችልና ለዘይት ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተገልጿል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩና ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ብድር የሚያቀርብ ሲሆን፥ በቡሬ ከተማ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ወጥቶበት በመገንባት ላይ ለሚገኘው የምግብ ዘይት ፋብሪካም ባንኩ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረቡን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የጉብኝት ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ሙሉነህ አቦዬ ይገልፃሉ።

    በቡሬ ከተማ በ30 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው ተገባዶ የማሽን ተከላ ሥራው እየተጠናቀቀ የሚገኘው ይህ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ምርት እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን፥ ከ2500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

    በአቶ በላይነህ ክንዴ በመገንባት ላይ ያለው ፋብሪካው፥ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሸፍን በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል። በሀገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ወደ ዘርፉ መግባታቸውን የገለጹት አቶ በላይነህ ክንዴ፥ ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

    በመገንባት ላይ ያለው ትልቅ የምግብ ዘይት ፋብሪካ አካባቢው ከሱዳን ጠረፍ እስከጃዊ አኩሪ አተር፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ስንዴና በቆሎ በከፍተኛ ደረጃ ትርፍ አምራች በመሆኑ ምርቶቹን በግብአትነት በመጠቀም የምግብ ዘይት በከፍተኛ ደረጃ በማምረት የአገሪቱን ከ50 እስከ 60 በመቶ ፍላጎት እንደሚሸፍንም ነው አቶ በላይነህ የጠቆሙት።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በቡሬ ከተማ በመገንባት ላይ ለሚገኙት ሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ፋይናንስ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙና በአምራች ኢንዱስትሪው ለተሰማሩ የግል ኢንቨስተሮች ፋይናንስ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ይህን ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሙሉነህ አቦዬ አስታውቀዋል።

    በቡሬ ከተማ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለው ፊቤላ ኢንዳስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የዘይት ፋብሪካ በ2006 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የጀሪካን፣ የማሸጊያ፣ የሳሙና፣ የማርጋሪንና የካርቶንን ጨምሮ ሰባት የተለያዩ ፋብሪካዎችን በውስጡ ይዟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ፊቤላ ኢንዱስትሪያል

    Anonymous
    Inactive

    ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአርክቴክቸር ዘርፍ ለአምስት ዓመት ተኩል ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

    ኮምቦልቻ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – በወሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘው ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (Kombolcha Institute of Technology) የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ለአምስት ዓመት ተኩል ሲያስተምራቸው ከነበሩት ተማሪዎች ውስጥ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓም በዋለው ሴኔት ውጤታቸውን መርምሮ ሃያ ስድስት ተማሪዎችን በደማቅ ዝግጅት አስመርቋል።

    በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት፥ ኢትዮጵያ በኪነ ህንፃ ዘርፍ የቆየ ጥበብ ባለቤት መሆኗን አስታውሰው፤ ተማሪዎች በቆዩባቸው ዓመታት ከአካዳሚያዊ እውቀት ባለፈ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና ችረዋል።

    ዶ/ር መላኩ በመልዕክታቸው፥ በ2012 ዓ.ም. ከተመረቁት ሃያ ስድስት ተማሪዎች መካከል በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ሁለት ተማሪዎች በትምህርት ክፍሉ እና በማኔጅመንት ውሳኔ በተቋሙ ውስጥ በመምህርነት እንዲቀጠሩ መወሰኑን አብስረዋል።
    የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ሲሸጋገሩ ያገኙትን እውቀት እና ልምድ በተግባር በማዋል ዘርፉ ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበው፤ ምሩቃኑ በአገሪቱ ነባራዊ ሁናቴ ላይ በጎ አሻራ በማስቀመጥ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት መቻል እንዳለባቸው ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል።

    ዶ/ር አባተ ኢትዮጵያ ከጣራ ወደ መሠረት እነዲሁም ከአንድ ፍልፍል ደንጋይ ህንፃ በማዋቀር የቀደመ የጥበብ ተምሳሌት መሆኗን አውስተው ተመራቂ ተማሪዎች ራሳቸወን በማብቃት በአለም ገበያ ጭምር ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

    የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍም በምረቃ ፕረግራሙ ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ለምሩቃኑ ንግግር አድርገዋል።

    በ2012 ዓ.ም. ትምህርት ዘመን ከአጠቃላይ ተመራቂዎች 3.67 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ኤደን ሽመልስ እና 3.54 ያመጣው ዳዊት ማለደ ወደ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መቀላቀላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በቆይታቸው ባገኙት እውቀትና ልምድ ተቋሙን እና አገራቸው ለማገልገል ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ፥ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስናና በሒሳብ የትምህርት መስኮች የተሻለ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች እንድኖሩ የSTEM ማዕከል በማቋቋም እየሠራ ይገኛል። ይህንን የSTEM ማዕከል በቴክኖሎጅ ለማደራጀት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር “የኮምፒዩተርና የኤሊክትሮኒክስ” ቤተ-ሙከራ ከፍቷል። ይህ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የSTEMpower ማበልጸጊያ “የኮምፒተርና የኤሌክትሮኒክስ ቤተ ሙከራ” በአሜሪካን STEMpower.org ከተሰኘ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ የተመሠረተ ነው። ማዕከሉ በዘመናዊና ደረጃቸውን በጠበቁ የቤተ-ሙከራ ማቴሪያሎች የተደራጀ እንዲሆን ድርጅቱ ሁሉንም መሣሪያዎች በቀጥታ ከውጭ እንድገቡ አድርጓል። ይህም የSTEM ማዕከል የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና ድጋፍ አድራጊው የSTEMpower.org ድርጅት ተወካይ ባሉበት “ማዕከሉ” በይፋ ተከፍቷል።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት

    Semonegna
    Keymaster

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 34 የሕክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ለሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1233 ተማሪዎቸ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመርቋል።

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በዋና ግቢው እና በዱራሜ ካምፓስ 6 ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በተከታታይ ትምህርት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።

    በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፥ ኢትዮጵያ ለእርሷ እና ለዜጎቿ ክብር እና ፍቅር ያለው ባለሙያ ያስፈልጋታል ብለዋል። አክለውም ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት በተገቢው ሁኔታ ለማኅበረሰብ ለውጥ እንዲያውሉት አሳስበዋል።

    ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን በማጠናከር የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስረግጡም ዶ/ር ሳሙኤል ጠይቀዋል።

    የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያየ መልኩ ከሚንፀባረቀው የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ኋላ ቀርነት በመራቅ ለኅብረተሰብ ዕድገት እና ብልፅግና እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።

    በሌላ በኩል ደግሞ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም ያሰለጠናቸውን 33 የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ።

    ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም (hybrid innovative curriculum) በሕክምና ዶክትሬት ያሰለጠናቸውን 33 ተማሪዎች በተመሳሳይ ቀን አስመርቋል።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ለተማሪዎቹ የሥራ መመሪያ የሰጡት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ ተመራቂዎቹ ቃለመሀላ በገቡለት የሕክምና ሥነ-ምግባር በመታገዝ ቅን አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል። ከዚህም ባለፈ በተግባር በተደገፈው ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም የቀሰሙትን የሕክምና ትምህርት የሀገሪቱን ብሎም የዓለምን ሕዝብ ስጋት ላይ ከጣሉ ዘመን-ወለድ የጤና ችግሮች ኅብረተሰቡን ለመታደግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በውጤት በታገዘው የቅይጥ ፈጠራ-አከል ሥርዓት (ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም) ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸው በመሆናቸው ማኅበረሰቡን ከጤና እክሎች ከመታደግ ባለፈ በምርምር ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር ብልፅግና የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ 26 የማስተርስ ዲግሪ (ሁለተኛ ዲግሪ) ተማሪዎችንም አስመርቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየተሠራ ነው

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም. የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየሠራ መሆኑን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲው ከ135 በላይ ለመድኃኒት የሚሆኑ እጽዋት ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

    ወልቂጤ (ኢዜአ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአገር በቀል እውቀት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ጥሩውሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት፥ እስካሁን የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት ቤት፣ በመሥሪያ ቤት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አልተካተተም። በቋንቋው ውስጥ የተለያየ የአነጋገር ዘዬ መኖር በትምህርት እንዳይሰጥ ካደረጉት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

    በዚህም አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጉራጊኛ ቋንቋን እየረሳ በመምጣቱ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር የፊደል ገበታ መቀረጹን ገልጸዋል። የተወሰኑ ፎነቲኮች በአማርኛ ፓወር ግዕዝ ላይ ባለመኖራቸው ዩኒቨርሲቲው “የተንቢ” የተሰኘ የኮምፒተር መተየቢያ አበልጽጓል።

    በጉራጊኛ ቋንቋ 13 የአነጋገር ዘዬ የሚገኝ ሲሆን በየትኛው መጀመር እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።

    ”የኮምፒተር መተየቢያና የፊደል ገበታን በማሰልጠን እንዲሁም ሌሎች ግብአቶች እንዲሟሉ በመጠቆም  የጉራጊኛ ቋንቋ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ ለማስቻል እየተሠራ ነው” ብለዋል አቶ ካሳሁን።

    በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከ135 ዓይነት በላይ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎች ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ለዚህም የተፈጥሮ መድኃኒት ማምረት የሚያስችል የስልት ሰነድ (strategic document) እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ መድኃኒቱን ማምረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። በዚህም ንጥረ ነገሮችን የመሥራትና የአሠራር ዘዴ ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

    ምርምር እየተደረገባቸው ያሉ እጽዋት ለደም ብዛት፣ ጋንግሪን፣ አስም፣ አጥንት ካንሰርና ለሌሎች በሽታዎች ፈውስ ያስገኛሉ የተባሉ ናቸው።

    ቀደም ሲል ከእጽዋት የባህላዊ መድኃኒቶች ልኬት እንደማይታወቅ ያነሱት አቶ ካሳሁን፥ የፋርማሲና የኬሚስትሪ ባለሙያዎች ከአካባቢው የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በምርምሩ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

    በሌላ በኩል የማኅበረሰቡ ለበርካታ ዓመታት ይተዳደርበት የነበረው ባህላዊ የሕግና አስተዳደር ዘዴ እየቀነሰ በመምጣቱ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው ምርምር እያደረገ ነው።

    ቋንቋና ሥነ-ጹህፍ፣ አገር በቀል መድኃኒት፣ አስተዳደርና ሕግ፣ ባህልና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኒቨርሲቲው ትኩረት ተሰጥቷቸው ምርምርና ጥናት እየተካሄደባቸው ነው።

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ክልል የሚገኝ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን የተመሠረተው በ2004 ዓ.ም. ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጉራጊኛ ቋንቋ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያወጣው ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ለመወሰንና ለማስወሰን አንዳንድ ሀገራት የተዛባ ውሳኔ እንዲሰጥ ጫና ለመፍጠር እየጣሩ ይገኛሉ። በአንድ ወቅት ተመሳሳይ የተዛባ ውሳኔ በ League of Nations ሲተላለፍ እ.ኤ.አ. በ1949 የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የሚከተለውን ብለው ነበር፡-

    ሀገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ለነፃነቷና ለመብቷ ከኮሎኒያልስት ጣሊያን ጋር በየጊዜው ስትዋጋ ያሸነፈችውም ብቻዋን ነው። የተጠቃችውም ብቻዋን ስለሆነ ሀገሬ መቼውንም በሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም። ዛሬም ሆነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያለባት እሷ ራሷ ብቻ ናት!

    እንዳሉት ሁሉ፥ አሁንም ያለን ትውልዶች የተዛባውን ሚዛን ማስተካከል ያለብን እኛው ነን። እናም የአድዋውን ድል በተባበረው የአያቶቻችን ክንድ እዳሸነፍነው ሁሉ የሕዳሴውንም ግድብ በተባበረው አንድነታችን፣ ክንዳችን እና ሀብታችን ሠርተን የምንጨርሰው መሆናችንን እያረጋገጥን እኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች አቋማችንን በጋራ ስንገልፅ መነሻ ያደረግነው፡-

    • የግድቡ መገንባት በአገሪቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ልዩነት እንደሌለው፣
    • ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን እና ሀብቷን ለመቀራመት አውጥተውት የነበረና አሁን የሚያፍሩበት እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ኢትዮጵያ ባልተወከለችበት በተደረገ ስምምነት የሕግ ተገዥ የምትሆንበት ሕጋዊም ሆነ አመክኗዊ ነገር የሌለ መሆኑን፣
    • የሀገራችን ምሁራን በሠሯቸው ጥናቶች ግድቡ የሚገነባው ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ባልሆነ ቦታ ከመሆኑም በተጨማሪ ውሀው ግብፅ ወይም ሱዳን ላይ ቢከማች ኖሮ በትነት የሚባክነውን ውኃ ስለሚያስቀር ተመራጭ የሚያደርገው መሆኑን ነው።

    ከዚህ በላይ በቀረበው መነሻነትም እኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ባለ ስድስት ነጠብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

    1. የጀመርነውን እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምናደርግ እናረጋግጣለን።
    2. የሕዳሴው ግድብ የአንድነታችን ተምሣሌት በመሆኑ በዘር፣ በኃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይኖር የመንግሥትን አቋም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደግፍ እንጠይቃለን።
    3. እኛ ጠግበን በብርሃን እየኖርን እናንተ በረሃብና በጨለማ ኑሩ የሚል ራስ ወዳድ አስተሳሰብን በፅኑ እናወግዛለን።
    4. እኛ የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውን የየድርሻቸውን እንዲወጡና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንደያሳድሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    5. የአረብ ሊግ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ሰሞኑን የወሰደውን ኢ-ፍትሐዊ ውሣኔ እየተቃወምን የአፍሪካ ህብረት እንዲህ ዓይነት ጣልቃ ገብነትን እንዲቃወምና መርህን እና ሕግን መሠረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን።
    6. የአሜሪካ መንግሥት በታዛቢነት ገብቶ ሀብት እና የዲፕሎማሲያዊ ኃይሉን በመጠቀም ወደ አደራዳሪነት ራሱን ከማሸጋገር በላይ የወሣኝነት ሚና ያለው የሚመስል መግለጫ ማውጣቱን አጥብቀን እንቃወማለን።

    የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ

    የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች
    የካቲት 28 /2012 ዓ/ም
    ካፒታል ሆቴል
    አዲስ አበባ

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች

Viewing 15 results - 286 through 300 (of 730 total)