Search Results for 'የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ'

Viewing 10 results - 31 through 40 (of 40 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫን በተመለከተ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የሰጠው ወቅታዊ የአቋም መግለጫ
    የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት (Caretaker Government of Technocrats) ይቋቋም!

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት የምትሸጋገረውና መጪው ምርጫ ብሩህ ተስፋ የያዘ የሚሆነው አሳታፊ፣ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ጉባዔ በማድረግ ብቻ ነው። ጉባዔው በአንድ በኩል ሀገራችን ያንዣበበባትን የኮሮና ወረርሽኝን እንዴት ልታልፍ እንደምትችል ምክክር እንዲደረግ የሚያስችል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ቀጣዩ ምርጫ መቼ ይሁን? በምን ቅርጽ ይካሄድ? እስከ ምርጫው ድረስ ሀገራችንን ማንና እንዴት ይምራት? ለሚሉት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ የሚገኝበት መድረክም ነው። ይህን ዓይነቱን ጉባዔ ፍሬያማ ለማድረግ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ዋና ዋና የፖለቲካና የሲቪክ ባለድርሻዎች እንዲሳተፉበት ማድረግ የግድ ይላል።

    ይሁን እንጂ፣ ገዢው ፓርቲ እንደዚህ ዓይነቱ ሀገራዊ ጉባዔ እንዲደረግ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ፥ በሀገራችን ውስጥ ተፅዕኖ ያላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች በማግለል የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጀቶችን ብቻ መርጦ ስብሰባ አድርጓል። በዚህ ሂደት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን ጨምሮ፣ ሌሎች ለገዢው ፓርቲ ብርቱ ተፎካካሪ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳይሳተፉ አድርጎ፣ ቅንነትና ታማኝነት የጎደለው፣ ጠቃሚ ሃሳቦች በተሟላ መልኩ ያልተንሸራሸሩበት፣ ለሃቀኛ ሽግግር ያልቆረጠ ስብሰባ እንዲሆን አድርጎታል።

    በዚህም ሳቢያ በሀገራችን መጻኢ ዕድል ላይ ጥቁር ዳመና እንዲያንዣብብ እየሆነ ነው። ኢትዮጵያን ወደ ሚቀጥለው የተሻለ ደረጃ ከማስፈንጠር አንፃር ማንም ልጅ፣ ማንም የእንጀራ ልጅ ስላልሆነ፣ የማግለል አካሄድ ለሀገራችን ስለማይበጅ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል።

    በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የመንግሥት የሥራ ዘመን 5 ዓመት ብቻ እንደሆነና፣ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ ከወራት በፊት [ብሔራዊ] ምርጫ መደረግ እንዳለበት የደነገገ ቢሆንም፥ በበሽታ፣ በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌላ እክል ምርጫውን ማካሄድ ሳይቻል ቢቀር ምን መደረግ እንዳለበት ምንም መፍትሄ አላስቀመጠም። ይህም አሁን ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫን በተመለከተ ትልቅ ሀገራዊ ተግዳሮት ፈጥሯል።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በሚያዝያ 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ·ም. ባደረገው አስቸኳይ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ፣ የምርጫውን መራዘም አስመልክቶ ገዢው ፓርቲ አግላይ በሆነው ስብሰባ ያቀረባቸውን 4 አማራጮች በጥልቀት ከሕግና ከፖለቲካ አግባብነት አንፃር እያየ መርምሯል።

    ኮሚቴው በገዢው ፓርቲ የቀረቡት አማራጮች ሀገሪቷን ከተጋረጡባት ተግዳሮቶች የማይታደጓት ብቻ ሳይሆኑ፣ በከፊል ሕጋዊ መሠረትም የሌላቸው መሆኑንም ተገንዝቧል። ስለሆነም፣ አማራጭ ሀገራዊ መፍትሄ ለማስቀመጥ ውይይትና ክርክር ከማድረጉ በፊት አራት መስፈርቶች እንደ ቅድመ-ሁኔታ አስቀምጧል። እነዚህም፡-

    1. የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት፣ ሠላምና ደኅንነት የሚያስቀጥል መሆን እንዳለበት፣
    2. መፍትሔው ሀገራዊ ተግዳሮቱን እንደ ክፍተት በመጠቀም የማንንም የስልጣን ጥም እውን ለማድረግና ለማስፈፀም መዋል እንደሌለበት፣
    3. ለዴሞክራሲያዊ ሽግግርና ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት መሆን እንደሌለበት፣
    4. የባልደራስን ጨምሮ ከማንኛቸውንም የፖለቲካ ድርጅት ፍላጎትና አመለካከት የፀዳ መሆን እንዳለበት፣
    5. ለመሰል ሀገራዊ ተግዳሮት ዓለም-አቀፍ ተሞክሮ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት የሚሉት ናቸው።

    እነዚህን መስፈርቶች መመዘኛ አድርጎም፣ በገዢው ፓርቲ በኩል የቀረቡት «አማራጮች»ም ሆኑ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚሹ ኃይሎች የተሰባሰቡበት ያቀረቡት «የሽግግር መንግሥት እንመሥርት» ጥያቄ ለሀገሪቱ እንደማይበጁ ጥርት አድርጎ ማየት ችሏል።

    በአንጻሩ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ ያሉትን መሰል ተሞክሮዎች ግምት ውስጥ ሲገቡ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለኢትዮጵያ የሚበጃት «የባለሙያዎች የባለአደራ መንግሥት» ወይም በእንግሊዘኛ አጠራሩ “Caretaker Government of Technocrats” ነው ብሎ በፅኑ አምኗል።

    ይህ የባለሙያዎች የባለአደራ መንግሥት ከየዘርፉ በሚመለመሉ ምሁራንና ባለሙያዎች የሚቋቋም ሲሆን፣ አዋጪነቱም ተፈትኖ የታየ ብቻ ሳይሆን፣ ገዢው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዋች ሀገራዊ ተግዳሮቱን በመጠቀም ለስልጣን ሽሚያ እንዳይጋበዙና ሀገር እንዳትጎዳ ዋስትና ይሰጣል።

    የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት፡-

    1ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት በሕይወት ዘመናቸው የፖለቲካ ድርጅት አባላት ባልነበሩ ምሁራንና ባለሙያዎች የሚቋቋም ይሆናል፣
    2ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላትና ሹመኞች በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ገደብ የሚጣልባቸው ይሆናል፣
    3ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላትና ሹመኞች ከምርጫ በኃላ በሚቋቋመው መንግሥት የፖለቲካ ሹመት እንዳይሰጣቸው የአንድ የምርጫ ዘመን ገደብ የሚጣልባቸው ይሆናል፣
    4ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላት በፖለቲካ፣ በሲቪክ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታዛቢነት የሚመረጡ ይሆናል፣
    5ኛ. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት አባላት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል ይመረጣሉ፣

    የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት ኃላፊነት፡-

    1. የሀገር ሉዓላዊነትን መጠበቅ፣
    2. የሀገር ጸጥታን ለማስጠበቅ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፣
    3. ለነጻ ምርጫ የሚያስፈልጉ ነጻ የመንግሥት ተቋማትን መገንባት፣
    4. የመንግሥትን የዕለት ተዕለት ሥራ መምራት፣
    5. ከምርጫው በፊት፣ ለሀገራዊ እርቅና መግባባት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሰላም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
    6. ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ቃል ኪዳን (citizen’s covenant) እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
    7. የባለሙያዎቹ የባለአደራ መንግሥት የሥራ ዘመን ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ይሆናል።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ
    ሚያዚያ 26ቀን 2012 ዓ·ም.
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ!

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ

    ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
    ለድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣
    ለመላው ኢትዮጵያውያን!

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሀገራችንን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አውዶችን በጥልቀት በመገምገም፤ የአማራ ሕዝብን ወቅታዊ አቋምና ዘላቂ ጥቅሞችን፤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ፍላጎቶችን እና የቀረቡ አማራጮችን በፅሞና በመመርመር፤ በዚህም መሠረት፦

    • ለሰላማዊና ጠንካራ ሀገራትና መንግሥታት እንኳን የሚያዳግቱ ግዙፍና አሳሳቢ ብሔራዊ ተግዳሮቶች የተደቀኑብን መሆኑን በማመን፤
    • የዴሞክራሲያዊ ውድድር፣ የልሂቃን ውይይትና ድርድር ባህል ባልዳበረበት በጥልቅ በተከፋፈለ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደምንገኝ በመገንዘብ፤
    • የኢትዮጵያ ቀጣይ ሁኔታ በምርጫ ወይም በይስሙላ ማሻሻያዎች ብቻ እንደማይወሰን፣ የአሸናፊዎችና የጉልበተኞች ጫናም ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ በማመን፤
    • ከምንም ከማንም በላይ የአማራን ሕዝብ ሰላም፣ ደኅንነትና ዘላቂ ጥቅሞች መከበርና የሀገራችንን ህልውና ቀጣይነት በማስቀደም፤

    አብን እነዚህንና ሌሎችንም ተጓዳኝ ታሳቢዎችን በማድረግ ሀገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ በአስተማማኝ ልትወጣ የምትችልባቸውን መንገዶች በተመለከተ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል።

    1ኛ. የሽግግር ጊዜ (transitional period) አስፈላጊነት
    ንቅናቄያችን አብን ሌሎች በሀገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቋማት ላቀረቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ክብር ያለው ቢሆንም አሁን ለገባንበት ፖለቲካዊ ቀውስ አዲስ የሽግግር መንግሥት (transitional government) መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት የለውም።

    ከዚህ ይልቅ የተወሰነ የሽግግር ጊዜ መፍጠር የተሻለ አማራጭ መሆኑን እንገነዘባለን። ምክንያቱም የሕዝባችንና የሀገራችን ዕጣፈንታ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቆም ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ነባራዊ ውጥረቶችና ክፍተቶች እንዲረግቡና የጥሞናና ውይይት መንፈስ እንዲሰፍን ያስችላል። የሽግግር ጊዜ ያላሰለሰ ሕዝባዊ ውይይት፣ ልሂቃዊ ምክክርና ድርድር እንዲደረግና ሊያሠራ የሚችል ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ዕድል ይሰጣል።

    2ኛ. የመንግሥት-መር (state-led) ሽግግር አስፈላጊነት
    አብን ከገባንበት ብሔራዊ አጣብቂኝ ለመውጣት የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት፣ የሕግን የበላይነት በማስከበር ረገድ ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ አካል መኖር እንዳለበት ያምናል። አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍጠር በሀገራችን ወቅታዊ የፖለቲካና የኃይል አሰላለፍ አውድ ሊሳካ እንደማይችል ይገነዘባል።

    ስለዚህም ምንም እንኳን ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የታየው መንግሥት መሩ የለውጥ ሂደት የከሸፈና የማያሰራ እንደነበር ብንረዳም፣ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቆየትና የሽግግር ሂደቱን መምራት ለሕዝባችንና ሀገራችን ሰላምና ደህንነት ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት የተሻለው ነው ብለን እናምናለን።

    3ኛ. የመዋቅራዊና ሁሉን አካታች ሽግግር ሂደት አስፈላጊነት
    አብን የአማራ ሕዝብና የሌሎች ወንድም ህዝቦች መሠረታዊ ጥያቄዎች ሥርዓታዊና መዋቅራዊ በመሆናቸው በዋነኝነት የሚፈቱት በልሂቃን መካከል በሚደረግ ውይይትና ድርድር ከሚመነጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ መሆኑን ያምናል።

    ብሔራዊ ፖለቲካችን ከጥሬ የስልጣን ትግል ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሻገር ከታሰበ ከአጭር ፖለቲካዊ ትርፍ ይልቅ ዘላቂ የሀገርና የሕዝብ ጥቅምን ያማከለና አዲስ ቅርፅና አቅጣጫ ያለው ሰፊና የማያቋርጥ የድርድርና እርቅ ሂደት ያስፈልጋል። በተለይም የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት ማሻሻል፣ አጠቃላይ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦችን ማድረግ ያሻል። ከሁሉም በላይ በአሳሳቢ ሁኔታ እየወደቀ የመጣውን ምጣኔ ሀብታችንን እንዲያንሰራራ ማድረግ የግድ ነው። ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን ያካተተና ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆነ የብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን እንዲቋቋም ድርጅታችን አብን ይጠይቃል።

    4ኛ. መሠረታዊ የሕዝባችንን ጥያቄዎች በተመለከተ

      • ሀ. የኮቪድ-19 ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ በመሠረታዊ የሕዝቦች ጥያቄዎች ላይ ቅርፅ ያለውና ተቋማዊ የሆነ ብሔራዊ ውይይት (national dialogue) እንዲጀመር ለማድረግ ዋስትና እንዲሰጥ ንቅናቄያችን አበክሮ ይጠይቃል።
      • ለ. የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ፣ ንቅናቄያችን የ1999 ዓ.ም. ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሳይንሳዊ ያልሆነና ሸፍጥ የተሞላብት የሕዝባችንን ቁጥር በእጅጉ የቀነሰ በዚህም ፖለቲካዊ ውክልናውን እና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነቱን ያሳጣ በመሆኑ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ፤ ለተከሰቱት ጉዳቶች ፍትኃዊ ማካካሻ (restorative justice) እንዲደረግና ቀጣዩም ቆጠራ ሳይንሳዊና ገለልተኛ በሆነ ተቋም እንዲካሄድ ይጠይቃል።
      • ሐ. የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ፤ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ሕዝባችንን የማይወክልና በሂደትም ቅቡልነትን ያላተረፈ፣ በአማራ ጠል ትርክት ላይ የተመሠረተ፣ ለሀገር አንድነትና ህልውና የማይበጅ፣ እንደዚህ ያለ ፈታኝ ወቅት ሲያጋጥም እንኳን በአግባቡ ሊያሻግር የማይችል በመሆኑ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የሕገ-መንግሥት ለውጥ ወይም ማሻሻያ እንዲደረግ ይጠይቃል።
      • መ. የሀገራችንንና ሕዝባችንን የሰላምና ደኅንነት ዋስትና በተመለከተ፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሕግና ሥርዓት በማስከበር ረገድ ያሳየው ድክመት ተገቢ አለመሆኑንና በፍፁም መቀጠል እንደሌለበት በማመን፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ከመንግሥት ግንባር ቀደም ኃላፊነቶች መካከል መሆኑን በመገንዘብ፤ ሀገራችን ባለችበት የስጋት ሁኔታ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተለየ ዝግጁነት እንዲደረግ አበክሮ ይጠይቃል።

    አብን በሕዝባችን ትግል የተሸነፉ ቋሚ የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ጠላቶችና ግብረ አበሮቻቸው ሀገራችንን ለማተራመስና እንደገና የጭቆና መንበራቸውን ለመመለስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጥብቆ እንደሚታገለው በአፅንኦት ያረጋግጣል።

    ንቅናቄያችን ከላይ የገለፃቸውን አቋሞች በተመለከተ ከመንግሥትና ከተለያዩ የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ንግግሮችንና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን እያሳወቀ የተከበረው የአማራ ሕዝብ፣ የድርጅታችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በአሁኑ ወቅት የተደቀነብንን ብሔራዊ አደጋ በማጤን ላቀረብናቸው አማራጭ ኃሳቦች ስኬት ከጎናችን እንድትሰለፉ በአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    አንድ አማራ ለሁሉም አማራ! ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ ኮሚቴ
    አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
    ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም.

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    Anonymous
    Inactive

    ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ
    ስልጣንን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ በአስቸኳይ ይቁም!

    ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ግን የስልጣን ዘመኑን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚያስችለውን ጥረት ለሕዝብ ይፋ ባልሆነ መንገድ እያደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች እየደረሱን ነው። ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ከተሰጠው ስልጣንና መብት ውጭ በሦስት አማራጮች ስልጣኑን ለማራዘም እየሞከረ እንደሚገኝ ታውቋል።
    እነዚህ አማራጮችም፤-

    1. በዓመቱ መጨረሻ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ እንዲበተን ማድረግና በ6ወር ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፤
    2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደገና በማራዘም የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከር፤
    3. የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት በማሻሻል የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም የሚሉ ናቸው።

    ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ በየትኛው መንገድ የመንግሥትን ስልጣን ለማራዘም እንደሚቻልም ገዥው ፓርቲ ከራሱ መዋቅሮችና በዙሪያው ከሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ጋር እየመከረ እንደሆነ ታውቋል።

    አብሮነት ከዚህ ቀደም ደጋግሞ ለመግለፅ እንደሞከረው ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግሥት ዕድሜ ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ድንጋጌ በሀገራችን ሕገ-መንግሥት ውስጥ የለም። በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 72/3 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ ስለመሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም የመንግሥትን ዕድሜ እንዴት ማራዘም እንደሚቻል ሕገ-መንግሥቱ ምንም ዓይነት ድንጋጌ አላስቀመጠም። ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትን የሕገ-መንግሥቱን አርቃቂዎች እና ለሕገ-መንግሥቱ ክፍተት መታየት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስን “ከመርገም” ውጭ በሕጋዊ መንገድ የስልጣን ዘመኑን ለአንድም ቀን የሚያራዝምበት ምንም ዓይነት መብትና ስልጣን በሕገ-መንግሥቱ አልተሰጠውም።

    በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስልጣን የተሰጣቸውም በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን አምስት ዓመት የመንግሥት የስልጣን ዘመን ለመጨረስ ነው እንጂ ከአምስት ዓመት በላይ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም አይደለም። እንዲያውም በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60/1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ በሕግ የተሰጠን የሥራ ዘመን ለማጠናቀቅ ከመቻል ጋር እንጂ የሥራ ዘመንን ከማራዘምና የመንግሥት የሥራ ዘመን ካለቀ በኋላ ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም።

    በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 93/1፣ ሀ እና ለ ላይ በግልፅ እንደተደነገገውም የመንግሥትን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ተብሎ ሊታወጅ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም። አሻሚና አከራካሪ ባልሆነ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ዓይነት ጉዳዮች ሊታወጅ እንደሚችል ሕገ-መንግሥቱ በዝርዝርና በግልፅ ስላስቀመጠ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማዎጅ ስልጣኑን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችለው ሕጋዊ መብትና ስልጣን የለውም።

    እንደ ሦስተኛ አማራጭ እየታየ ያለው ሕገ-መንግሥቱን አሻሽሎ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከርም ሕጋዊነትን የተከተለ አሠራር አይደለም። አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግሥት የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት የሚያሻሽል ከሆነ፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደ አንዳንድ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች በዓለም ፊት መሳቂያ እና መሳለቂያ የሚያደርግ የአምባገነኖች ድርጊት እንጂ ሕጋዊ አሠራር ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ሕገ-መንግሥትን ለማሻሻል የመሞከር እርምጃም ከሕግ መኖርና አስፈላጊነት መሠረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሂደትም ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል የሕዝብ ቅቡልነት ሊያገኝ አይችልም። እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ሀገራዊ ጉዳይ አሳታፊና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመወሰን መሞከርም ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሁለንተናዊ የህልውና ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ አለመረዳት ነው። ይህም እንደተለመደው የገዥውን ፓርቲ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ስልጣን የማስቀደም ኃላፊነት የጎደለው ፍልጎት የሚያሳይ ነው።

    ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች በሠሩት ስህተት እና በኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የመንግሥት የሥራ ዘመንን አስመልክቶ ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ (constitutional crisis) መፈጠሩን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በአንድ አገር ሲፈጠር ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በመደበኛ የሕግ አሠራር ሳይሆን ከመደበኛ የሕግ አሠራር ውጭ (extra-constitutional) በሆነ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መፍትሄ ለመስጠትም በተለየ ሁኔታ በሕግ መብት የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መንግሥታዊ ተቋም ስለሌለ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው? በሚለው ጥያቄ ተነጋግሮ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የምክከር ሂደት (national dialogue) መጥራት ያስፈልጋል። ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በሀገራችን በሕጋዊም ይሁን በይስሙላ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ስለማይኖር የወደፊቱን የአገሪቱን ዕጣ-ፈንታ በመወሰን ረገድ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ከማንኛችንም በአገሪቱ ከምንገኝ ፓርቲዎች የተለየ መብትና ስልጣን ስለሌለው በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ብቻውን መወሰን አይችልም። ገዥው ፓርቲ ይህንን ማድረግ ከሞከረ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ እና ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።

    ስለሆነም፦

    1ኛ. በአሁኑ ወቅት ዋናውና ቀዳሚው ትኩረታችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር መሆን ስላለበት ቢያንስ እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2012 ዓ.ም. ድረስ ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በተመለከተ ምንም ዓይነት አጀንዳ ይዞ እንዳይነጋገርም ሆነ የተናጠል ውሳኔ እንዳያስተላልፍ፤

    2ኛ. የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በዘንድሮው ዓመት በተናጠል ምርጫ ለማካሄድ ማሰቡ ሕገ-መንግሥታዊ ውሳኔ አይደለም። በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ብቸኛ መብት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑን በመገንዘብ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ህወሓት ከዚህ ዓይነቱ ሕገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤

    3ኛ. ብልፅግና ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በሚመለከት በድብቅ የሚፈፅማቸውን ተግባራት ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በንቃት እንዲከታተሉ፣ ገዥው ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በተመለከተ ሕገ-ወጥ እርምጃ መውሰዱን የሚቀጥልበት ከሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመቺ የመገናኛ መንገድ ፈጥረው በአስቸኳይ መመካከር እንዲችሉና በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን አቋም እንዲይዙ፣ ከዚህ በኋላም በሀገራችን ጉዳይ አንዳችን ጋባዥ ሌላችን ተጋባዥ የምንሆንበት ምክንያት እንደሌለ ተገንዝበን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የምናደርገው ማንኛውም ግንኙነትና ድርድር በእኩልነት መንፈስ ብቻ እንዲሆን የሚያስችል አቋም እንድንይዝ፤

    4ኛ. የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 29 ዓመታት በአፈናና በይስሙላ ምርጫ በስልጣን ላይ የኖረው ገዥው ፓርቲ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ በሕገ-ወጥ መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገውን ጥረት አጥብቆ እንዲቃወም፣ መቃወምም ብቻ ሳይሆን የገዥውን ፓርቲ ሕገ-ወጥ እርምጃ በጠንካራ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማስቆም እንዲዘጋጅ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል።

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
    ሚያዚያ 21 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት

    Anonymous
    Inactive

    የምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ ሀገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል! ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። ወረርሽኙ በሰዎች ጤና እና ደኅንነት ላይ ካደረሰው እና እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ የዓለምን እና የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እና ሥርዓትን ከባድ አደጋ ውስጥ ከቷል። ወረርሽኙ በሀገራችን ኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። በሌሎች ሀገር ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አሁንም አለ። የጎረቤት ሀገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት የጀመረበትና በተለይ ከጅቡቲ ጋር ካለን የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው።

    ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከአሁኑ እየታየ ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ጫናም በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ይህም በቶሎ ወደቀድሞ ሁኔታው የሚመለስ አይሆንም። የበረሀ አንበጣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ እንደዚሁም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና እስከ ሰኔ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዋስትና የማጣት ስጋት/አደጋ እንዳንዣበበባቸው በቅርቡ ተገልጿል። በአጠቃላይ ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው መጠነ ሰፊ መቀዛቀዝና የአገራዊ ጥቅል አመታዊ ምርትና እድገት ማሽቆልቆል ሀገራችን ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው።

    በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል።

    ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባን ካለነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ከሌሎች ሀገሮች የተደቀነብን አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ የነበረውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ሀገርን ማን ያስተዳድራል የሚል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ነው የሚሉትን ሀሳብ እያቀረቡ ይገኛሉ።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በተለይም ከሕገ-መንግሥት ጠበቆች (constitutional lawyers) ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። ባለሙያዎቹ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ-መንግሥታዊ አግባብ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለውን የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ የባለሙያዎች ጉባዔ (high level panel of experts) በማቋቋም ለአንድ ወር ያህል ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት ቆይቷል። ኢዜማ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ልንከተለው የሚገባው የመፍትሔ ሀሳብ የሚከተሉትን ታሳቢዎች ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤

    1. አገራችን ከምትገኝበት የሕግም የፖለቲካ አጣብቂኝ በአጭር ጊዜ ለመውጣት የሚረዳ መሆን እንዳለበት፣
    2. ተቋማዊ አሠራሮችን ከማጎልበት አንፃር የተሻለ ዕድል የሚፈጥር መሆን እንዳለበት፣
    3. አጠቃላይ ችግሩ በአጭር ጊዜ ፈቶ አገራችን ወደተረጋጋ የምርጫ ሂደት ለመግባት የሚያስችል መሆን እንዳለበት፣
    4. ከወጪም ከጊዜም አንፃር አገሪቱን ብዙ ዋጋ የማያስከፍል የተሻለው አማራጭ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በፍጥነት የተቀያየሩት የአገራችንንና የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካዊና የደኅንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት።

    ኢዜማ ከላይ የገለፅናቸውን ሀገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት እንደሚያስፈልገን ያምናል። ለዚህም እንደፓርቲ ልንከተለው የሚገባን የመፍትሄ ሀሳብ ይህንን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው በፅኑ ይረዳል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፓርቲያችንን የሕግ ባለሙያዎች ጨምሮ በሌሎች አካላትም የቀረቡትን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

    1. ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሄ በሚል በተለያዩ አካላት የቀረበ የመፍትሄ ሀሳብ

    በዋናነት በዚህ ረገድ የቀረበው ሀሳብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚያበቃ በመሆኑ እና ሕገ-መንግሥቱም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ክፍተት ስለማይሰጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሠረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ነው። ይህ መፍትሄ ሀሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው። ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ያሉብንን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር አይደለም። ይህም የገባንበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ ያደርገዋል።

    1. በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች

    2.1. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ማድረግ፦ ይሄ አማራጭ በ6 ወር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እና ሕግ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ የሀገር እና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ከግምት የማያስገባ፣ የፌደራል መንግሥትን እንጂ ሥልጣናቸው አብሮ የሚጠናቀቀውን የክልል ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ያላገናዘበ አማራጭ በመሆኑ የምንፈልገውን ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር አማራጭ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.2. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀመጠ አንቀጽ አይደለም። አስቸኳይ ግዜ ማዋጅም በቀጥታ የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘምን አያስከትልም። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር የሚደረግ ምርጫን ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም።

    2.3. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ከፌደሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ፦ በዚህ አማራጭ መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ሥራ የሚሠራው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሙሉ ነፃነት እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተመራለትን ጉዳይ በመመርመር የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ያ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ክብደት አንጻር ጉዳዩን መዳረሻ ውጤቱ አስቀድሞ በእርግጠኝነት ለማይታወቅ እና ምናልባትም መልሶ እዚህ ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል አንደኛውን እንድንከተል ሊያደርግ ለሚችል ሂደት መስጠት ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.4. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፦ ይህ አማራጭ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።

    ምንም እንኳን ኢዜማ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም፥ አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። አሁን ለገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በኢዜማ እምነት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ሀገራዊ መረጋጋት፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እንዲሁም በከፍተኛ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው ሀገራዊ ጉዳይ በዚህ ወቅት ሊከወን አይገባም ብለን እናምናለን። ሆኖም አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልፅ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ-መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

    በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቁ እንዲሁም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ 2/3ኛ ክልሎች (6 ክልሎች) በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁት በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ 3 ስር ከሚገኙት እና አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን የሕገ-መንግሥት አንቀጾች ማሻሻል እንደሚቻል ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58/3 ከላይ በተገለጸው መሠረት ማሻሻል የተሻለ መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን።

    ይህ መፍትሄ ተግባራዊ ከተደረገ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት ተከትሎ የሚፈፀም በመሆኑ ሕገ ምንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። በዚህ አማራጭ ላይ በተለያዩ አካላት የሚነሳው ጥያቄ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት በአንቀጽ 104 ድንጋጌ መሠረት ህዝብን ለማወያየት አያስችልም የሚል ሲሆን ይህንን ክፍተት ግን ሕዝቡን በወኪሎቹ አማካኝነትና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በማወያየት መሸፈን ይቻላል።

    ከዚህ ቀደም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የጋራ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን በሚመለክት የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀጽ 103/5 በሕገ-መንግሥቱ የተጠቀሰውን የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሳይከተሉ ለየብቻ በተለያየ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ አሁን መደረግ ያለበት ማሻሻያ ግን የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105/2 ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች በሙሉ አሟልቶ ሊሆን እንደሚገባው እናምናለን።

    ይህ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌድሬሽን ምክር ቤትንም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት።

    የፓርቲያችን እምነት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ቢሆንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተራ ቁጥር 2.3 ላይ የጠቀስነውን አማራጭ በመውሰድ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጥ 54/1፤ 58/3 እና 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደመራው ታውቋል። ምንም እንኳን ኢዜማ ይህንን አማራጭ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ-መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ አለበት። ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት።

    በአጠቃላይ እንደሀገር የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ለማሳሰብ ይወዳል። በተጨማሪም በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መዳበራቸው መፍጠር የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድንለማመድ በር የሚከፍት እና ሁሉንም ኃይሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የምናደርግበት መድረክ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያካሄደውን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀመንበርነት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን በአቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን በመተካት፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አመራሮችን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቀቀ።

    ደብረ ብርሃን (አብን) – የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኘበት በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።

    ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አብን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለሥ በሚያስችለውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ይገኝ ዘንድ ላለፉት ጊዜያት የመጣበትን መንገድ መርምሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ ማሻሽያ መዘጋጀቱን ገለፀው በዚህ ላይ ጠቅላላ ጉባዔው በደንብ ተወያይቶ አቋም እንዲይዝበት ጠይቀዋል።

    ጉባዔው በመጀመረያ ቀን ውሎው የአብን መዋቅራዊ ማሻሽያ (reform) አስፈላጊነትና አላማ፣ የንቅናቄው ጥቅል የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የፋይናንስ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት፣ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሪፖርት፣ የተሻሻለው የንቅናቄው መተዳደሪያ ደንብና ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኃላ አፅድቋል።

    ጠቅላላ ጉባዔው 5 ተለዋጭ አባላት ያሉት 45 የንቅናቄውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥም መርጦ ያፀደቀ ሲሆን የተመረጡት አባላትም የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጠዋል። በተጨማሪም በሊቀመንበሩ የቀረቡለትን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚዎችን አፅድቋል። በዚህም መሠረት 9ኙ የአብን ሥራ አስፈፃሚ አመራሮች፦

    1. አቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን – ሊቀመንበር፣
    2. አቶ የሱፍ ኢብራሂም – ምክትል ሊቀመንበር፣
    3. አቶ አዲስ ኃረገወይን – የፖሊሲ ስትራቴጂ ኃላፊ፣
    4. አቶ ጣሂር ሞሐመድ – የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
    5. ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም – የውጭ ጉዳይ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት
    6. አቶ ጋሻው መርሻ – የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣
    7. አቶ መልካሙ ፀጋዬ – የፅሕፈት ቤት ኃላፊ፣
    8. አቶ ጥበበ ሰይፈ – የሕግ እና ሥነ-ምግባር ኃላፊ፣ እና
    9. አቶ ክርስቲያን ታደለ – የፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው።

    ምንጭ፦ አብን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ተመሳሳይ ዜናዎች

    በለጠ ሞላ ጌታሁን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ

    Anonymous
    Inactive

    በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የኢትዮጵያውያን የፍትህ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን የአያሌ ዜጎችን ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የወሰደ ረጅም ጉዞ ነው። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የሁሉንም ተሳትፎ ያማከለና አገዛዙ ከሚቋቋመው በላይ የሆነ ንቅናቄ የታየበት ትግል ተደርጓል። ውጤቱም የዛሬዋን ሁኔታ ወልዷል።

    ከበርካታ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ እንዳየነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማዋለድ ከባድ ምጥ ያለበት የጭንቅ ጊዜ ማሳለፍ የግድ መሆኑን ነው። በኢትዮጵያችንም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው። በእንደዚህ ዓይነት አስጨናቂ ወቅት ይህን ሂደት እንደአንድ ከባድ ታሪካዊ ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ የመኖራቸውን ያህል ግርግር ፈጥረውና የራሳቸውን ፍላጎት በኃይል ለመጫን የሚፍጨረጨሩ ቡድኖችና ግለሰቦች መኖራቸውን በየእለቱ በየቦታው የምናየው አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።

    ፓርቲያችን ከተመሠረተ ጀምሮ ለሀገር ሠላምና ለሕዘብ መረጋጋት የራሱን ያልተቆጠበ አሥተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። በእኛ ዕምነት የተያዘው የሽግግር ሂደት ለአንድ ወገን የማይተውና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነ እናምናለን። ያም ሆኖ በዚህ ፈታኝ ወቅት የመንግሥት ሚና ትልቅና ከፍተኛ እንደሚሆን እንገነዘባለን።

    ፓርቲያችን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሠቱ ፈታኝ ሁኔታዎችንና የመንግሥትን ምላሽ በመገምገም በሚከተሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ይገልፃል።

    1. የየትኛውም በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ተግባር የሀገራችን ሕጎ እና ሀገራችን ያፀደቀቻቸውንና የተቀበለቻቸውን ድንጋጌዎች ባከበረ መልኩ ብቻ እንዲሆን ማድረግ የሚገባን ዛሬ ነው። ዜጎች በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ካልተረጋገጠላቸው እና ከሕግ በታች መሆናቸውን ካልተረዱ ማንም እየተነሳ የፈለገውን አድርጎ “አልጠየቅም” የሚል ማንአለብኝነት ከሠፈነ መቼም ማቆሚያ ወደማይኖረው የሁከት ዓለም ጅው ብሎ እንዳይገባ ያሠጋል።
    2. የሁሉም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በነፃነት እና በሠለጠነ መንገድ መግለፅ፣ በሥልጣን ላይ ያለውንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን መተቸት፣ ማጋለጥ አልፎም በምርጫ ከሥልጣን ማውረድ የተለመደና ተገቢም ሊሆን ይችላል። ሀገርን የሚያዋርድ ተግባር መፈፀም ግን ለማንም ያልተፈቀደ የሀገር ከህደት ወንጀል መሆኑ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል። በሕዝብ፣ በሃይማኖቶች፣ በብሔረሰቦች፣ በሰንደቅ ዓለማና በመሳሰሉት የአገር መገለጫዎች ላይ የሚፈፀም ማንኛውም የነውር ተግባር አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚያስከትል መሆን አለበት።
    3. ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚሠጠው ትኩረት ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየና ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚጠብቃቸው መሆን እደሚገባው እናምናለን። በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርስቲ ግቢዎች የተከሠቱ ችግሮች የሕዝባችንን ልብ ሰብረው ያለፉ ክስተቶች ናቸው። ከሁሉም በላይ በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የተደረገው እገታ ውሉ የጠፋና የመንግሥትን የተማሪዎችን ህይወት የመጠበቅ ኃላፊነት አለመወጣት ያጋለጠ ነው። ከዚህ ቀደም መንግሥት ስለለተማሪዎቹ እገታ ወቅቱን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለተማሪዎቹ ቤተሰቦች እና ለሕዝብ እንዲሰጥ ኢዜማ መጠየቁ ይታወሳል። ሆኖም መንግሥት ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ከፍተኛ ክፍተት ታይቶበታል። ከዚህ አንጻር መንግሥት ተማሪዎቹን ከእገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ እና የሕዝብን ልብ እንዲያሳርፍ አበክረን እንጠይቃለን።
    4. በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸም ግፍ ለየትኛውም አካባቢ ለሚገኝ ሰላም ጠንቅ ነው” እንዲሉ፥ ለተማሪዎቻችን የመቆም ጉዳይ የአንድ ወገን ወይም የአንድ ክልል ጉዳይ ሊሆን አይገባውም። የሁላችንንም ተናብቦ መሥራት ግድ ይላል። ከዚህ አንጻር የታገቱ ልጆቻችንን በሰላም ለማስለቀቅ ሕግ እና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች በሕዝባችን የሚደረጉ ሀቀኛ ጥረቶችን እንደግፋለን።
    5. ሀገርን እና ሕዝብን የማወክ አንድ አካል የሆነው የሞጣ መስጂዶችን የማቃጠል ድርጊት በአጥፊዎቹ ላይ አስተማሪ ርምጃ ተወስዶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ መስጂዶቹን አድሶና ምዕመናኑን ክሶ ወደቀድሞው ሰላማዊ አገልግሎት ለመመለስ የሚደረጉትን የአብሮነት እንቅስቃሴዎችን እንደግፋለን።
    6. በቅርቡ የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በተወሰኑት አካባቢዎች በተለይም በአቦምሳ የከተራ በዓል ሳይከበር የቀረበትን ሁኔታ ታዝበናል። የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዳይከበር እንቅፋት የሆኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ እንጠይቃለን።
    7. ኢዜማ የምርጫ ወረዳዎችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንደዚሁም ሕዝባዊ ውይይቶች በሚያካሄድበት ጊዜ ጥቂት ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ግርግር ሕዝብን የሚወክል እንዳልሆነ ብንረዳም በአጠቃላይ የፖለቲካ ድባቡ ላይ የሚፈጠረው የስሜት መሻከር ያሳስበናል። በተለይም ወደምርጫ ለመግባት ዝግጅት እያደረግን ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት ሕዝቡ ሕገመንግሥታዊ የሆነውን የመሰብሰብ መብቱን መጠቀም የማይችልበት ሁኔታ ይታያል። ባሳለፍነው ሳምንት በተከሠቱ በተለይ የጎንደር እና የሸዋሮቢት ድርጊቶችን ተከታትሎ አጥፊዎችን እንዲቀጣ አቤቱታችንን ለመንግሥት አቅርበናል። ኢዜማ ላይ የሚከሠቱ ችግሮች ሁለት ገጽ አላቸው አንደኛው ከመንግስት መዋቅር የሚመጣ ሲሆን ሁለተኛው ከዚያ ውጭ የሆኑ ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ነው። “ባለጌና ጨዋ በተጣሉ ጊዜ ለጊዜውም ቢሆን ባለጌ ያሸነፈ ይመስላል” የሚል የቆየ የሀገራችን ብሂል አለ። ይህም ጨዋው በሕግ ስለሚያምንና የሕግ አስከባሪ ባለጌውን ይቀጣል፤ ብሎ በማመን ነው። በእኛ መዋቅርም የሚታየው ይሄው ሕግን የማክበር ጉዳይ ነው፤ ይህም ቢሆን ልክ አለው፤ ከገደብ ያለፈ ነውር ሲፈፀም አመራሩም፣ አባሉም፣ ደጋፊውም ራሱን፣ ፓርቲውንና ሀገሩን የመጠበቅ ተፈጥሯዊ መብት አለው። ኢዜማ ሀገርንና ሕዝብን ለድርድር አያቀርብም። ይህንንም ደግመን ደጋግመን ተናግረናል! መንግሥት በራሱ ውስጥም ሆነ ከራሱ ውጭ ያሉትን ሥርዓት አልበኞች በሕግ ሊቀጣ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ራሱን ወደመከላከልና ሰላሙን ወደ ማስጠበቅ ሊገፋ ይችላል። ይህም በየትኛውም መመዘኛ ስህተት ሊሆን አይችልም።

    በመጨረሻም የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን መጠበቅ ለሁላችንም የሚጠቅም ሀገር እና ሕዝብን የሚታደግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አውቀን እንድንጓዝበት መልዕክታችንን እያስተላለፍን ሥርዓት አልበኝነትን በጋራ በቃ የምንልበት ጊዜው ዛሬ መሆኑን በአፅንኦት እንገልፃለን።

    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    Semonegna
    Keymaster

    ሀገር የማዳን ጥሪ
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነት

    ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሥርዓት አልበኞች በተወሰደ የጥፋት እርምጃ የማይተካ የዜጎቻችንን ሕይወት አጥተናል፣ የብዙዎች አካል ጎድሏል፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩት ንብረት ወድሟል እዲሁም በተዘጉ መንገዶች ምክንያት ዜጎች ተንገላተዋል፤ የሀገሪቷ የኢኮኖሚ እቅስቃሴም ተስተጓጉሏል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዜጎች ሕይወት ላይ በደረሰው ጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል። ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል። የተፈጸመውን ሕገ ወጥ እና አሳፋሪ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል!

    የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረጉ የሥርዓት አልበኞች ሙከራዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ መጥቷል። የመንግሥት እነዚህን ሙከራዎች አስቀድሞ የመተንበይ፣ ሲከሰቱም አፋጣኝ እና ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅሙ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እየታየበት አይደለም። በዚህም ምክንያት የዜጎች ሕይወት በተደጋጋሚ አደጋ ላይ ወድቋል፤ አሁንም እየወደቀ ይገኛል። በቁጥር ቀላል የማይባሉ ዜጎች በሀገራቸው ደኅንነታቸው ተጠብቆ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት እና የመኖር መብታቸውን መጠቀም የማይችሉበት ብቻ ሳይሆን በማያቋርጥ ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የተገደዱበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከዚህም አልፎ በዕምነት ተቋማት እና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለመተማመን ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ የማይታረም ከሆነ የሽግግር ሂደቱ ተጨናግፎ ወደማንወጣው ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል።

    መንግሥት የችግሩን ጥልቀት እና ሕግ የማስከበር ድክመቱን በሚገባ ፈትሾ በአስቸኳይ ክፍተቶቹን እንዲያስተካክል እና የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ እና ጥፋተኞችን ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቀን እናሳስባለን።

    መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ የጋራ ሀገራችንን ከጥፋት አፋፍ ለማዳን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የሚገባን ወቅት ላይ መሆናችንን ተገንዝበን ልዩነቶቻችንን አቻችለን በአንድነት እንድንቆም እና ሀገራችን ከተደቀነባት ከባድ አደጋ እንድንታደግ ከአደራ ጭምር ጥሪ እናስተላልፋለን።

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    ምንጭ፦ ኢዜማ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ሀገር የማዳን ጥሪ

    Semonegna
    Keymaster

    ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
    ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።

    —–

    አዲስ አበባ (ማኅበረ ቅዱሳን) – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ዓርማ አድርጋ ስትጠቀምበት የኖረችውን እና አሁንም የምትጠቀምበትን ባንዲራ ለበዓል ይዛችሁ ወጥታችኋል፤ በቤተ ክርስቲያን ጣሪያ እና ጉልላት ላይ ቀብታችኋል በማለት ምእመናንን የሚያዋክቡ፣ ወጣት ክርስቲያኖችን የሚያስሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ።

    በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያንን ተቀማጭ ገንዘብ ከንግድ ባንክ አውጥታችሁ እኛ በምንፈልገው ባንክ አስቀምጡ በማለት የሚያስገድዱ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀው 38ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጠናቀቀበት ዕለት ነው።

    ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው፣ የሐሰት ታሪክ ፈጥረው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚነዙ አቀጣጣዮችን (‘አክቲቪስት’/ ‘activist’ ነን ባዮች) እና ፖለቲከኞችን እኩይ ድርጊት መቃወም እንደሚገባ ጉባኤው በመግለጫ አሳውቋል።

    ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።

    የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም ጉባኤው አሳስቦ አገራዊ ለውጡ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው እኩይ ተግባር ቤተ ክርስቲያንን እያሳዘናት እና እያሳሰባት መሆኑንም አስገንዝቧል።

    በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን ጥፋት በሰላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ እንደሚኖርበትም አሳስቧል።

    የጥምቀት እና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ነጥቀው፣ አንዳንድ ጊዜም ቆርሰው ለሌሎች የሚሰጡ አካላትን እኩይ ድርጊት አጥብቆ የተቃወመው መግለጫው በአገር ውስጥም በውጭም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እኩይ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥበብ እና በትዕግሥት ማሳለፉ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጧል።

    ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል

    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
    የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትህ እና ነፃነት ጥያቄ በግድየለሽነት በሚንቀሳቀሱ ሰዎችና ተግባራቸው እንዳይጠለፍ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል!

    የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ይገባናል በሚል ሁሉንም አገዛዞች ሲታገል የቆየ ሕዝብ መሆኑ ሃቅ ነው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንኳን ፍትሃዊ እና የሁሉንም ዜጎች ነፃነት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል በትግል የተገኙ አራት ዕድሎች መክነውብናል። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች እና የዜጎች አልገዛም ባይነት እና እምቢተኝነት ትንቅንቅ የሚቋጨው ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭ ሆኖ የሚመርጠው እና የሚቆጣጠረው መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው።

    የሩቁን ትተን በ2007 ዓ.ም. እንኳን ብናይ፣ በሙሉ ድምጽ ተመርጫለሁ ብሎ ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረዉ ገዢ ቡድን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ስብርብሩ የወጣው በዜጎች የጋለ የዴሞክራሲ ጥያቄ እና የተባበረ ትግል ነው።

    ይህ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተባበረ ክንድ የተሰበረ አምባገነናዊ አሠራርና አስተሳሰብ መልክ እና ቅርፁን በመቀያየር የተገኘውን የለውጥ ጭላንጭል ድርግም አድርጎ በማጥፋት ጥለነዉ ወደመጣነዉ ጨለማና ወደራሱ የአገዛዝ አቅጣጫ ሊጠልፈው እንደተዘጋጀ ከበቂ በላይ ምልክቶችን አይተናል።የኢትዮጵያን ሕዝብ ትዕግስት፣ አስተዋይነት እና አርቆ አሳቢነት የመረዳት ችሎታ ያነሳቸው ጥቂት ፅንፈኞች ሀገራችን የምትጠብቀውን ተስፋ ሊነጥቋትና እነሱም አጥፍተው ሊጠፉ የተዘጋጁ ይመስላል። በእንደዚህ ዓይነት አቅላቸውን በሳቱ የአገዛዝ ቡድኖች እጅ መውደቅ ለአገራችን የመጀመሪያ ባይሆንም ይህ አሁን የገጠመን አጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መቆምን እና መታገልን የሚያሻ መሆኑን ማሳሰብ እንወዳለን። በተደጋጋሚ እንዳልነው አሁን ያገኘነውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ሀገራዊ መረጋጋት በእጅጉ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ በተፃራሪ የአንድ ወገን አሸናፊነት ተረክ መፍጠር ያገኘነውን ዕድል አደጋ ላይ የሚጥል እና ለማንም የማይጠቅም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንሸጋገርበትን መደላድል ለመፍጠር ሰላም እና መረጋት ለማስፈንና ተቋማትን ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ቢሆንም በገዢው ፓርቲ ውስጥም ይሁን ከዚያ ውጪ ለውጡ የጋራ ትግል ውጤት መሆኑን የዘነጉ ቡድኖች የሚሠሩትን ነውረኛ አካሄድ በማየት በሚከተሉት 7 ነጥቦች ላይ ያለውን አቋም ይገልጻል።

    1. የአማራ እና የቅማንት ሕዝብ ብዙ መከራዎችን በጋራ ያሳለፈ ድንበር የሌለው አንድ ሕዝብ ዛሬ በአስተዳደር ወሰን እና በማንነት ጉዳዮች የሚነሱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን የሚያስተናግደው በክፋት በተዋቀረው ፌደራላዊ አሠራር መሆኑን ተገንዝበን ለዘላቂ ሰላም እና ለሕዝብ አብሮ መኖር በትዕግስት እንድንሠራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ግጭቶች ባሉበት አካባቢ የሚኖረውም ሕዝብ፤ በመሀከሉ ያለውን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እና ሰላሙን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ እኩይ ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን በሕዝባችን አንድነት ስም እንማጸናለን።
    2. ኢሕአዴግ በጌታ እና ሎሌ አደረጃጀት የተዋቀረ ከዚህም ሲያልፍ መንግሥትነት የሚያስገኘውን የሥልጣን ጥቅም በመቀራመት ጎን ለጎን ሲጓተቱ የነበሩ ቡድኖች ስብስብ መሆኑን ለምናውቅ ሁሉ የዛሬው እሽኮለሌ አያስደንቀንም። ሆኖም ግን ሕዝባችንን በእነሱ ጦስ ወደእልቂት ለመክተት የሚያደርጉትን የትንኮሳ አካሄድ እንዲያቆሙ በኢሕአዴግ ውስጥ የተሰባሰቡ የብሔር ድርጅቶችን በጥብቅ እናሳስባለን።
    3. የተቋማትን መኖር እና መጠንከር አስፈላጊ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክንውኖች ከፖለቲካ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ቢሆንም ከሰሞኑ በተለይም የኦዴፓ አደረጃጀት የሰላም፣ የይቅርታ እና የምስጋና ታላቅ በዓል የሆነውን ኢሬቻን መጥለፉ ሳያንስ የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የሚጎትት እና የሚበርዝ በመሆኑ እንዲህ ዓይነትቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም አንጠይቃለን። የሀገር አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሂደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።

    በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ አዲስ አበባ ለተከበረው ኢሬቻ በዓል ከየቦታው የመጡ የበዓሉ ታዳሚ ኢትዮጵያዊያንን በመንከባከብ ላሳየው አብሮነት እና ወገናዊ ፍቅር እንዲሁም በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላሳየው ትዕግስት ያለንን አክብሮት እና ምስጋና እየገለጽን ወደፊትም ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲታገል የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡

    1. የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን አፈና እስካሁን በሆደሰፊነት ማለፉ ሊያስመሰግነው ቢገባም ይህን ያልተረዱ ወገኖች ትዕግስቱን እንደፍርሀት፤ ጨዋነቱን እንደ የዋህነት እየወሰዱ ማኅበረሰቡን መተንኮስ እየተለመደ መጥቷል። ይህ የሀገራችንን ሁሉንም ሕዝብ አቅፎ የያዘ፤ ከዚያም በላይ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከል የሆነና ለፌደራል መንግሥቱም ከፍተኛ የሆነ የግብር ገቢ የሚያስገኝ ከተማን በጥንቃቄና በአክብሮት፤ የሚገባውን መብት አክብሮ መያዝ ይገባል። የከተማው ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም እውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን አይቀበልም። ይህንን መብቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅም ራሱን ከቀበሌ ጀምሮ በሁሉም ያስተዳደር እርከን በጠንካራ ሁኔታ አደራጅቶ የራሱን መብት ለማስከበርና የራሱን መሪዎች ለመምረጥ መዘጋጀት ይጠበቅበታል። ኢዜማ ይህንን ራስን የማስተዳደር እንቅስቃሴውን እውን ለማድረግ ከከተማው ሕዝብ ጋር አብሮ ይሠራል፤ የከተማውን ሕዝብም ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ በዜግነቱና በከተማ ነዋሪነቱ ያደራጃል። ከዚህም በተጨማሪ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንደግፋለን፤ በሥነ ሥርዓት እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በጠበቀና ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጎለብት ሁኔታ እንዲካሄድም ጥሪ እናስተላልፋለን።
    2. በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ያስተዋወቀው አዲስ የደንብ ልብስ ለከተማ የፖሊስ አገልግሎት የሚመች ባለመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውል አጥብቀን እናሳስባለን። የከተማዋ ፖሊስ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እንዲሁም በኮሚኒቲ ፖሊስ ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት እያለው እና የፌደራል ፖሊስ ኃይል በቋሚነት በሚገኝበት ከተማ ውስጥ ተጨማሪ ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ማቋቋም ተቀባይነት የለውም። ይልቁንም የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የከተማዋን ኅብረተሰብ ደኅንነት ማስጠበቅ እና አባላቱ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። በክልሎች የተደራጀው ልዩ ኃይል እና አዲስ አበባ አስተዳደር አቋቋምኩት ያለው ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ለሚደረገው ትግል ትልቅ ተግዳሮቶች ናቸው። ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው እነዚህ አደረጃጀቶች ፈርሰው ወደመደበኛ ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት እንዲካተቱ በድጋሚ ጥሪ እናስተላልፋለን።
    3. በአማራ ክልል የተከሰቱ የወንድማማች ሕዝብ ግጭቶች ተከትሎ ሁኔታው እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሰፍን ከመስበክ ይልቅ ሥራዬ ብለው ወሬ እየፈበረኩ ግጭቶችን በሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣን በአስቸኳይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እናሳስባለን።
    4. ላለፉት 27 አመታት ሲሰራበት የቆየው ሀገርን እና ሕዝብን ሆን ብሎ የሚከፋፍልና የሚበትን የዘረኝነት አሠራር ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም የሚቻለው ፖለቲካችንን በማዘመንና በመግራት፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ተደራጅቶ በመታገል በመሆኑ፤ ሌሎች ያደርጉልናል ብሎ ከመጠበቅ ዜጎች በተለይም ለዘብተኛ አመለካከት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ እንድናልፍ ባላችሁ አቅም ሁሉ በሀገራችሁ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ እንድትሆኑ የዘወትር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    በአጠቃላይ ሰላምን፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያይ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲገነባ ሕዝባችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ የኢዜማ አደረጃጀቶች በመግባት የጀመረውን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ ከዳር እንዲያደርስ ጥሪያችንን እያቀረብን ሌሎች የማኅበረሰብ መሪዎች ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ መረጋጋት ዘብ መቆም የሚገባቸው ጊዜ ዛሬ መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሀገር አንድነትን ማስቀጠል እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። አሁን ያለንበት የሽግግር ወቅት የሀገር አንድነትን እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን እንዲያረጋግጥ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንደምናደርግ እና አስፈላጊውን መስዕዋትነት ለመክፈልም ወደኋላ እንደማንል በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናችን እንደሚቆም አንጠራጠርም።

    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
    መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)


    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በግንቦት ወር በይፋ ተመሥርቶ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን ከገለፀ በኋላ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ፥ የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ከሕኮ) ተከትሎ ራሱን አክስሞ ኢዜማን የተቀላቀለ ሁለተኛ ፓርቲ ሆኗል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከተመሠረተ 11 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መክሰሙን አስታወቀ።

    ኢራፓ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መክሰሙንና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህን (ኢዜማ) መቀላቀሉን የኢራፓ ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ አስታውቀዋል። ፓርቲው በጠቅላላ ጉባዔው ላይ 8 ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫውም ይፋ አድርጓል።

    ኢራፓ በአቋም መግለጫው፥ ኢትዮጵያ ያለችበትን ችግር ለመፍታትና ከምንጩ ለማድረቅ መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መላው የሀገሪቱ ሕዝቦች በመቻቻል፣ በትዕግስትና በአብሮነት መሥራት እንዳለባቸው ገልጿል። “ጣት መቀሳሰሩን ወደ ጎን በመተው የምክክርና የድርድር መድረኮች ተዘጋጅተው ተቀራርቦ መነጋገር ይገባል” ሲል ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል።

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    በጠቅላላ ጉባኤው መገባደጃ ላይ ኢዜማን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ ኢዜማ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ይፈጥሯቸው ከነበሩ ህብረቶች በተለየ መልኩ ራሳቸውን ያከሰሙ ድርጅቶች በምርጫ ወረዳ የተዘረጉ መዋቅሮችን በመቀላቀል እንደአዲስ ፓርቲ የተመሠረተ ፓርቲ መሆኑን አስታውሰው፤ “ትንሽ ፓርቲ ውስጥ ትልቅ ከመሆን ትልቅ ፓርቲ ውስጥ ትንሽ ሰው መሆን ይሻላል” ሲሉ በመሠረታዊ መርኾች የተስማሙ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው ሰፊ ድንኳን ያለው ጠንካራ ድርጅት የማቆምን አስፈላጊነትን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ በተደራጁ የኢዜማ ምርጫ ወረዳ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረጉት የኢዜማ መሪ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰከነ ውይይት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ባሕል አዳብረን ኢዜማን ታሪክ የሚሠራ ድርጅት እናደርገዋለን ብለዋል።

    የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአማራ ሕዝብ ህልውና እና ለሀገር እንድነት አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገለፀ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ግንቦት 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ተመሥርቶ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን ከገለፀ በኋላ ኢራፓ፣ የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ከሕኮ) ተከትሎ ራሱን አክስሞ ኢዜማን የተቀላቀለ ሁለተኛ ፓርቲ ሆኗል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)


Viewing 10 results - 31 through 40 (of 40 total)