Search Results for 'ጎንደር ዩኒቨርሲቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ጎንደር ዩኒቨርሲቲ'

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 35 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የፈረንሳይኛ ቋንቋ አስተምሮ በዲፕሎማ ፕሮግራም ተቀብሎ ለማሰልጠን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቋል።
    —–

    ጎንደር (ኢዜአ) – ጎንደር ዩንቨርሲቲ የፈረንሳይኛ ቋንቋ የስልጠና ማእከል ለመክፈት ከፈረንሳይ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መድረሱን አስታወቀ።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማሪዎችን በዲፕሎማ ፕሮግራም ተቀብሎ ለማሰልጠን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቋል።

    የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የስልጠና ማዕከሉ መከፈት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ቱሪስቶችን በቋንቋቸው ለማስጎብኘትም ሆነ በሆቴሎችና በመዝናኛ ስፍራዎች ቀልጣፋ የቱሪስት መስተንግዶ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብሏል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንዳስታወቁት፥ የትምህርት ስልጠናው የሚሰጠው ከኢምባሲው ጋር በመተባበር ነው። ስልጠናውን በተቀናጅ አግባብ ለመስራት ማዕከል ይቋቋማል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ማዕከሉን ለመክፈት የሚያስችለው ስምምነት ከኤምባሲው ጋር ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፈራረማል።

    በሚደረገው ስምምነቱም የፈረንሳይኛ ቋንቋ አስተማሪዎችን ከመመደብ ጀምሮ የማስተማሪያ ግብአቶችን በራሱ ወጪ ለዩኒቨርሲቲው እንደሚያሟላ ገልፀዋል። የማዕከሉ መከፈት ዋና ዓላማ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሰለጠኑ አስጎብኚዎችና የሆቴል አስተናጋጆችን እጥረት ለመቅረፍ እንዲያስችል የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከቱሪዝም ትምህርት ክፍሉ ጋር በመቀናጀት ከዚህ ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ቋንቋውን በሰርተፊኬትና በዲፕሎማ ደረጃ ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው ያሉት ፕሬዘዳንቱ፥ በአፍሪካም ከ20 በላይ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

    የጎንደር ከተማ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መዳረሻ በመሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፈረንሳይ ቱሪሰቶች ለጉብኝት እንደሚመጡ ተናግረዋል።

    የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት የህብረተሰብና ቱሪዝም ሃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው እንዳሉት ከሆነ በአካባቢው ካሉት 80 አስጎብኚዎች መካከል የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከ2 አይበልጡም።

    በርካታ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ፓርኩን ለመጎብኘት እንደሚመጡ የተናገሩት ኃላፊው፥ ዩኒቨርሲቲው ለመክፈት ያሰበው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ማሰልጠኛ የፓርኩን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አስጎብኚ እጥረት እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ በተጨማሪ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግእዝ ቋንቋ ለመታደግ በዚህ ዓመት የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ቤት ለመክፈት መዘጋጀቱ በቅርቡ መገለጹ የሚታወስ ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሥር ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጎንደር ዩንቨርሲቲ በርካታ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ መጻህፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቋል።

    ጎንደር ዩንቨርሲቲ የግእዝ ቋንቋ በመጀመሪያ ዲግሪ መስጠት ሊጀምር ነው

    ጎንደር (ኢዜአ) – ጎንደር ዩንቨርሲቲ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግእዝ ቋንቋ ለመታደግ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ የቋንቋ ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

    የጎንደር ዩንቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የግእዝ ቋንቋ ባለቤት ብትሆንም ለቋንቋው ማደግና መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። “በዚህም ሳቢያ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ከመሆኑም በላይ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የብራና መጻፍትን ለጥናትና ምርምር ስራ ለማዋል አልተቻለም “ብለዋል።

    ዘመናት የተሻገሩና በቋንቋው የተጻፉ ለዘመናዊ ሕክምና ሙያ የሚያግዙ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ መጻሕፍት በኃይማኖት ተቋማትና ገዳማት ተወስነው መኖራቸውን አመልክተዋል።

    ዩንቨርሲቲው እነዚህን ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ መጻህፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

    በትምህርት ዘመኑ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ያመለከቱት ዶክተር ካሳሁን፥ ትምህርቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውም በኤክስቴንሽንና በክረምት መርሃ ግብሮች መሆኑን አስረድተዋል። ትምህርቱ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ሲሄድ መደበኛ ተማሪዎችን ጭምር በቀጣይ በግእዝ ቋንቋ አሰልጥኖ ለማስመረቅ መታቀዱን አመልክተዋል።

    በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሥር ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጎንደር ዩንቨርሲቲ፥ በአጠቃላይ 87 የመጀመሪያ ዲግሪ፤ 158 ሁለተኛ ዲግሪና 29 የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዳሉት ተገልጿል። በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን የሚከታታሉ ከ45ሺ በላይ ተማሪዎች በዩንቨርሲቲው ይገኛሉ።

    ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ተመሳሳይ ዜናዎች

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊው የበጎ ሰው ሽልማት ከግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዕጩዎችን ሲጠቁሙ እንደነበር ይታወሳል።

    በዚህ በተጠቀሰው የጊዘ ገደብ ውስጥም በ አጠቃላይ 291 ሰዎች ተጠቁመው 27 ዕጩዎች ለዳኞች ውሳኔ ቀርበዋል ለመጨረሻው የዳኞች ውሳኔ መቅረባቸውን የበጎ ሰው ሽልማት አስተባባሪዎች በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

    እንደወትሮው ሁሉ በሽልማቱ ዕጩዎች የተጠቆሙባቸውና ሽልማት የሚያሰጡት አስር የተለያዩ ዘርፎች ናቸው። በእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ የቀረቡት ዕጩዎች የሚከተሉት ናቸው።

    በመምህርነት ዘርፍ

    1. ፕሮፌሰር ሽታዬ ዓለሙ ባልቻ (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ)
    2. ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል
    3. ዶ/ር መስከረም ለቺሳ ደበሌ (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ሥነ-ባህሪ ኮሌጅ)

    በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)

    1. ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ
    2. ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ
    3. ዶ/ር ታደለች አቶምሳ

    በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ

    1. አቶ ሚካኤል ፀጋዬ
    2. አቶ በዛብህ አብተው
    3. አቶ ዳኜ አበራ

    በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)

    1. ዶ/ር ጀምበር ተረፈ
    2. አቶ አብድላዚዝ አህመድ
    3. አቶ ላሌ ለቡኮ

    በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ

    1. አቶ ዳንኤል መብራቱ
    2. አቶ ክቡር ገና
    3. አቶ ነጋ ቦንገር

    በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት

    1. አቶ በትሩ አድማሴ (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩ)
    2. ዶ/ር አሚር አማን (የአሁኑ የጤና ሚኒስትር)
    3. አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ

    በቅርስና ባህል ዘርፍ

    1. አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)
    2. አርሶ አደር አቶ አድማሴ መላኩ (በምስራቅ ጎጃም ዞን በጮቄ ተራራ አካባቢ የሚገኘውን ‹‹አባ ጃሜህ›› ደን ለ52 ዓመታት በግል ተነሳሽነት ሲጠብቁና ሲንከባከቡ የነበሩ)
    3. ሳሙኤል መኮነን (ከጎንደር)

    በሚዲያና ጋዜጠኝነት

    1. አቶ በልሁ ተረፈ
    2. አቶ አማረ አረጋዊ
    3. ወ/ሮ አንድነት አማረ

    በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች

    1. አቶ ኦባንግ ሜቶ
    2. አርቲስት ታማኝ በየነ
    3. ፕሮፌሰር ፀጋዬ ታደሰ

    በተጠቀሱት የሽልማት ዘርፎች ከእያንዳንዳቸው አንደኛ ሆነው የሚመረጡት ዕጩዎች በተመረጡበት ዘርፍ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ተብለው ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ይሸለማሉ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የበጎ ሰው ሽልማት


    Anonymous
    Inactive

    ፌዴሬሽኑ ዛሬም የሸገር ክለቦችን በአደባባይ እየናቀ ነው
    (ከቡና ሠማይ ሥር)
    —–

    ኳስ ክብ መሆኗን የፌዴሬሽን ወንበር ላይ ከተቀመጡ በኋላ ያወቁት የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኝ አመራሮች በዘር ተቧድነው በደካማ ውሳኔቸው የእግር ኳሱን የቁልቁሊት ጉዙ እያፈጠኑት ይገኛሉ።

    ይህ አዲስ አበባ ጠል የሆነው እግር ኳስ ፌዴሬሽን አምና የኤሌትሪክ እግር ኳስ ክለብን በግፍ ከሊጉ ያሰናበተው ፌዴሬሽን ዘንድሮ ደግሞ የግፍ አርጩሜውን መከላከያ እግር ኳስ ክለብ ላይ አሳርፏል።

    የስሑል ሽረ እና የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ (ወልዋሎ ዓ. ዩ.) ጨዋታ ከነመከላከያ እና ከደቡብ ፖሊስ ጋራ የመትረፍ እና የመውረድ አደጋ ውስጥ ያለው። ስሑል ሽረ ቀደም ብሎ እንዲጫወት እንዲሁም እስከ 71ኛው ደቂቃ ድረስ በወልዋሎ ዓ. ዩ. አንድ ለዜሮ ሲመራ የነበረው ስሑል ሽረ ደጋፊው ሜዳ ውስጥ ገብቶ ለአርባ አምስት ደቂቃ ያህል ጨዋታውን ካቋረጠ በኋላ ዋና አሰልጣኙ ዮሃንሰ ሳህሌ ጨዋታውን እንዳይመራ በማድረግ ውጤቱን በግፍ ነጥቋል። በየጨዋታው ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ በመመደብ ጨዋታውን በአምስት ካሜራ እና በሦስት ኮሜሽነር ሲቆጣጠር የነበረው ፌዴሬሽን ጉዳዩን ባላየ በማለፍ መከላከያን ከሊጉ እንዲወረድ አድርጓል።

    በሸገር ክለቦች ላይ ግፍ መሥራት የማይሰለቸው ፌዴሬሽን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የዋንጫ ፉክክር ውስጥ እያለ ቀሪ ጨዋታዬን ሳልጫወት ወደ ጎንደር በማቅናት ከፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ጋር አልጫወትም በማለት ተገቢ ጥያቄ እያቀረበ ቢገኝም ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ‘ምን ታመጣላቹ!?’ በሚል በእብሪት በተሞላበት እና ባላዋቂነት ውሳኔ ፎርፌ በመስጠት ዛሬም ለሸገር ክለብ ያለውን ንቀት አሳይቷል።

    አሁን ከዚህ በብሄር ከተደራጀው ሊግ እና በዘር ከተቧደነው ፌዴሬሽን ጋር አብሮ መቀጠል የማያዋጣበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረስን ይመስለኛል ስለዚህ የከተማውን ሊግ ሳይውል ሳያድር ይፋ ማድረግ ምርጫ የሌለው መፍትሄ ነው።

    የአዲስ አበባ ክለቦች መግለጫ ከማውጣት እና የአንድ ሰሞን አጀንዳ ከመሆን በዘለለ አትኩሮት በመስጠት የተሻለ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

    እግር ኳስ ሳይገባው እግር ኳስ ላይ ከተቀመጠ አመራር ጋራ መለያያት ይመጨረሻው አማራጭ ነው።
    (ከቡና ሠማይ ሥር)

    Semonegna
    Keymaster

    ሰሞነኛ የተማሪዎች ምርቃት — በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች (የግል/ የመንግስት) የተማሪዎች ምርቃት።

    የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ። በተመሳሳይ የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎችን አስመረቀ።

    ዩኒቨርሲቲው በአምስት ኮሌጆች ውስጥ ያስተማራቸውን ተማሪዎች 1 ሺህ 112 በመጀመሪያ ዲግሪ እና 201 በሁለተኛ ዲግሪ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ብርሃኑ የተማሪዎች ምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነት ማገልገል አለባቸው።

    ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እና በኢንጅነሪንግ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚያስተምር በመሆኑ ተማሪዎችም በዚሁ መስክ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን መሥራት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

    የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን እንደሚያካሂድና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነም ጠቁመዋል።

    ተመራቂዎች በበኩላቸው ባገኙት ዕውቀት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሪፖርተር እንደተናገሩት፥ ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመጥቀም ይሠራሉ። ወደ መንግስትም ሆነ ግል ተቋማት በመሄድ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ያገኙትን ትምህርት በተግባር ማስደገፋቸውን ገልጸው በኮንስትራክሽ ዘርፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

    በተመሳሳይ በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ የተመረቁ ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት ለማህበረሰቡ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

    በተያያዘ ዜና የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 578 ዕጩ መምህራንን በተመሳሳይ ዕለት በዲፕሎማ አስመርቋል።

    ከዕውቀት ባለፈ በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሠሩ የኮሌጅ ተመራቂ እጩ መምህራን ተናግረዋል።

    ከተመራቂ መምህራን መካከል በሒሳብ ትምህርት ክፍል የተመረቀችው መምህርት ስንቂት ማሙየ እንዳለችው፥ በቀጣይ ዕውቀቷን ለተማሪዎች ከማካፈል በተጨማሪ ሀገራቸውን የሚወዱና በሥነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በኃላፊነት እንደምተሠራ ተናግራለች።

    “ሀገራችን ከመምህራን ብዙ ትጠብቃለች፤ እኛ መምህራንም ትውልድን በዕውቀት አንፀን በመቅረፅ ለሀገራቸው እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ አለብን” ብላለች።

    በማኅበራዊ ሳይንስ ዕጩ መምህርና በኮሌጁ 3 ነጥብ 8 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው መንግስቱ ማሬ በበኩሉ ቀጣዩ ትውልድ በዕውቀት የዳበረና ማኅበረሰቡን አገልጋይ እንዲሆን በተመደበበት የሥራ ቦታ ተማሪዎቹን እንደሚያበቃ ተናግሯል።

    “መመረቅ የመጨረሻ ሳይሆን ለአስተማረችኝ ሀገሬና ወገኔ አገልግሎት መስጠት የምጀመርበት ነው” ያለው ተመራቂው ሲሆን፥ በቀጣይም ዕውቀቱን በማዳበር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን አስረድቷል።

    “የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ዕውቀትንና ማኅበራዊ ግብረ-ገብነትን ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ በቀጣይ የሥራ ዘመኔ የምከተለው መርህ ነው” ያለችው ደግሞ በሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ዘርፍ የተመረቀችው መምህርት መሰረት የኔሁን ናት።

    የኮሌጁ ዲን አቶ ስንታየሁ ነጋሽ በበኩላቸው ኮሌጁ ከተቋቋመ 38 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው በእነዚህ ዓመታት ከ44 ሺህ በላይ መምህራንን ማስመረቁን ተናግረዋል። በዕለቱ ከተመረቁ 1ሺህ 578 እጩ መምህራን መካከልም 798ቹ ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

    እንደ ዲኑ ገለጻ፥ ተመራቂዎቹ በትምህርት ቆይታቸው በቂ ዕውቀት ይዘው መውጣት የሚያስችላቸውን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት አግኝተዋል። ምሩቃን በቀጣይ ሙያውን አክብረው በመሥራትና ራሳቸውን ወቅቱ በሚፈልገው ልክ አቅማቸውን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የተማሪዎች ምርቃት


    Semonegna
    Keymaster

    ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከዓርብ ጀምሮ እስካሁን በውል ባልታወቀ ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።

    ደብረ ማርቆስ (ቢቢሲ አማርኛ)– በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱን ተማሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ። ሟች ሰዓረ አብርሃ እንደሚባልና የሦስተኛ ዓመት የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል (economics department) ተማሪ እንደነበረ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

    በዩኒቨርስቲው ከዓርብ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።

    የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደሳለው ጌትነትም በተቋሙ ከባለፈው አርብ (ግንቦት 16 ቀን) 12 ሰዓት ጀምሮ ግጭቶች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

    በዚህም አርብ ግንቦት 16 ላይ 3 ልጆች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረው ልጆቹ አሁን ሆስፒታል ይገኛሉ ብለዋል። የተጎዱት ተማሪዎች በባህር ዳር እና አዲስ አበባ ሪፈራል ተጽፎላቸው ወደዚያው መወሰዳቸውንም ጨምረው ያስረዳሉ። በግጭቱ ሁለት ተማሪዎች በድንጋይና በስለት ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን እማኞቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

    በተፈጸመበት ጥቃት ምክንያት አንደኛው ተማሪ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉንና ሌላኛው ተማሪ ደግሞ ለሕክምና እርዳታ ወደ ባህር ዳር መወሰዱን ከተማሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

    የረብሻውን ምክንያት እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አርብ ዕለት ተሳትፎ የነበራቸውን የተወሰኑ ልጆች ፖሊስ ተከታትሎ ከግቢ ውጭ ይዟቸው ፖሊስ ጣቢያ ስለሚገኙ ጉዳያቸው እየተጣራ ነው በማለት የግጭቱ መንስዔ ከዚያ በኋላ ተጣርቶ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል።

    በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ የተጠለሉ ተማሪዎች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን ትላንት የሟችን አስክሬን ለመሸኘት የተሰበሰቡ ተማሪዎችም “ትምህርቱ ይቅርብን ወደ መጣንበት መልሱን” በማለት ለዩኒቨርሲቱው ፕሬዚዳንት ጥያቄ ማቅረባቸውን ነግረውናል።

    የዚህን ዜና ተጨማሪ መረጃ ቢቢሲ አማርኛ ላይ ማንበብ ይቀጥሉ

    ከዚያው ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) ዘግቧል። በቀጣይም ከ967 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

    ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለአብመድ በጻፈው ደብዳቤ እንዳመላከተው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች 967ሺህ 786 ብር ከወር ደመወዛቸው አዋጥተው ድጋፍ አድርገዋል።

    የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በሚደረገው አገራዊ እና ክልላዊ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ተማሪዎችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

    ከዚህ በፊት ሠራተኞች እና ዩኒቨርሲቲው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋሙ አንድ ሚሊዮን ብር በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።

    ምንጮች፦ ቢቢሲ አማርኛ እና አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    እ.ኤ.አ በ2011 የተመሠረተው ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ዶክተሮችን ሲያስመርቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ስድስት ኮሌጆች፣ አንድ ትምህርት ቤት እና አንድ ተቋም (ኢንስቲትዩት) አለው። 

    ዓዲግራት (ሰሞነኛ)– ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለመጀመርያ ግዜ ሰባት ሴቶች 25 ወንዶች በድምሩ 32 የሕክምና ዶክተሮችን (medical doctors) እንዲሁም በድኅረ መሠረታዊ መርሃግብር (post basic program) 30 ተማሪዎችን አስተምሮ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል። በዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩ የትግራይ ክልል ም/ር/መስተዳደር ክቡር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች እጥረት እንዳለና ችግሮቻችን በማቃለል አንዳንዱን በመፍታት ልዩነት የሚያመጣ ድርሻ እንደሚኖራችሁ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ ብለው መልእክታቸው አስተላልፍዋል።

    በዕለቱ የምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ስሃረላ ኣብዲላሂ በበኩላቸው የጤና ባለሙያ ማለት የግል ምቾትን እንደ መስዋዕትነት በመክፈል እንብካቤ ለሚያስፈልጋቸው እንክብካቤ መስጠት መሆኑን በማወቅ በየተኛውም የሃገሪቱ ክፍል ሄዳችሁ ያስተማራችሁን ህብረተሰብ ለማገልገል ዝግጁ እንድትሆኑ በማለት ለዕለቱ ተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል። ዩኒቨርሲቲው የነበሩበትን ፈተናዎች ኣልፈው ለመመረቅ መብቃታችው በጣም የሚያኮራ ታሪክ መሆኑ የዩኒቨርሲቲው ግዝያዊ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገ/መስቀል ገልፀዋል።

    ኬር ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውን የምርምርና የስልጠና ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ

    ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ዶክተሮችን ሲያስመርቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተው እ.ኤ.አ በ2011 ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ስድስት ኮሌጆች፣ አንድ ትምህርት ቤት እና አንድ ተቋም (ኢንስቲትዩት) አለው። ከሁለት ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲው ባወጣው የአሃዝ ዘገባ በአጠቃላይ ከ16,000 በላይ ተማሪዎች በመደበኛው፣ እንዲሁም ከ6,000 በላይ ተማሪዎች በተከታታይ (continuing education) መርሀ ግብር እያስተማረ ይገኛል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የጠቅላይ ሚኒስትር የመሠረተ ልማት እና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ርዕስ መስተዳደር ሆነው ተሹመዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መልቀቂያ ጥያቄ አቀረቡ። ርዕሰ መስተዳድሩ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው ጥያቄውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ምክር ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሏል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)በበኩሉም የርዕሰ መስተዳድሩን ጥያቄ መቀበሉን የ አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግበዋል።

    አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ለሦስተኛ ዙር በርዕሰ መስተዳድርነት ተመርጠው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል። በአጠቃላይም ከታህሳስ ወር 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን አገልግለዋል።

    አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “ታላቁን የአማራ ሕዝብ ለመምራት ዕድል የሰጠኝን ፓርቲዬን አመሠግናለሁ፤ በስልጣን ዘመኔ በሰጠኋቸው ውሳኔዎች ያስከፋኋችሁ ካላችሁ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ወኔና ጉልበት ሆኖኝ የኖረውን የአማራ ሕዝብ አመሠግናለሁ፤ ለአዲሱ ርዕሰ መስተዳድርም መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ” ብለዋል በመሰናበቻ ንግግራቸው።

    የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ ምክር ቤቱ የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ዶ/ር አምባቸው መኮንንን ርዕስ መስተዳደር አደርጎ ሾሟል። ዶ/ር አምባቸው ከአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን የመሠረተ ልማት እና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ነበር።

    እድገታቸው ጋይንት፣ ጎንደር ውስጥ የሆነው ዶ/ር አምባቸው መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በተለያዩ የመንግስት ቦታዎች ለ28 ዓመታት ሠርተዋል።

    ዶ/ር አምባቸው ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ቀጥሎም ደቡብ ኮርያ ከሚገኘው ከኮርያ የልማት ኢንስቲትዩት (Korea Development Institute) በፐብሊክ ፖሊሲ የማስተርስ ዲግሪ፣ ከዚያም እንግሊዝ ሀገር ካንተርበሪ ከተማ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬንት (University of Kent) ሌላ ማስተርስ ዲግሪ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ዶ/ር አምባቸው መኮንን


    Semonegna
    Keymaster

    ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው?

    ባሕር ዳር – በጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ አራት ማስወገጃ መንገዶች በአማራጭነት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ምክረ-ሐሳብ ይቀርባል። ከእነዚህ ማስወገጃ መንገዶች እስካሁን ሁለቱ (የሕዝብ ጉልበት እና ማሽነሪዎች) ጣና ሐይቅ ዙሪያ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው።

    ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው? ስንል የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣንን ጠየቅን።

    በዚህ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሁለት ማሽኖች ብቻ እንደሆኑ የነገሩን በአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ሥርዓተ ምኅዳር ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘው ሁለቱ ማሽኖች ካናዳና እሥራኤል ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በአማጋ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ድጋፍ የተገዙ ናቸው ብለዋል።

    “በባሕር ዳር እና ጎንደር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) እየተዘጋጁ ያሉ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች መኖራቸውን አውቃለሁ” ያሉት አቶ መዝገቡ፥ እስካሁን ድረስ ግን ከተቋማቸው ጋር ርክክብ ፈፅመው ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ገልጸዋል።

    አብመድ የተሰሩት ማሽኖች ለምን ርክክብ ተፈፅሞ አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም ሲል ሁለቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አነጋግሯል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ከሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር የሠራው የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት ቢመረቅም ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ጊዜ ድረስ አገልግሎት አይሰጥም።

    “ማሽኑ አገልግሎት ለመስጠት ምንም ዓይነት ችግር የለበትም፤ በቅርቡም ለሦስት ወራት ያክል የሙከራ ትግበራ ከተደረገ በኋላ ከሚመለከተው አካል ጋር ርክክብ ይደረጋል” ያሉት የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ የዘገየው ማሽኑን ለማንቀሳቀስ የሚሠራ ራሱን የቻለ የሰው ኃይል አደረጃጀት ባለመኖሩ ቅጥርና ምልመላ ለመፈፀም ጊዜ በመውሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ከሙላት ኢንዳስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር ለባለሙያዎቹ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ያስታወቁት ዶ/ር ሰይፉ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገቡም ገልፀውልናል። ማሽኑን በዘላቂነት ለማስተዳደርና ሥራውን ለማስተባበር ራሱን የቻለ ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።

    በጎርጎራ ወደብ አካባቢ የሚገኘው ሌላው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአረም ማስወገጃ ማሽንም ከአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ጋር ርክክብ ያልተፈፀመበት ማሽን ነው። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ኢንጅነር ሰለሞን መስፍን “ለአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ርክክብ እንዲፈፀሙ ደብዳቤ ልከናል” ብለዋል። የተዘጋጀው ማሽን አገልግሎት ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ማሽኑን የሚያንቀሳቅስ የሰው ኃይል (ኦፕሬተር) ማዘጋጀት የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ድርሻ እንደሆነም አስታውቀዋል።

    የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በበኩሉ ማሽኖቹን ለመረከብና የሰው ኃይል ለመቅጠር በተግር ሲሠሩ ማየት እፈልጋለሁ ብሏል።

    በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጅነሪንግ የተዘጋጀው ማሽን ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህ ሳምንት ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የተገዛ ሌላ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጣና ሐይቅ ላይ ደርሶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

    ምንጭ፦ አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – STEMpower የተሰኘ መቀመጫውን USA (ሳሌም፥ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ) ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲዎች እየረዳ የሚገኝ ሲሆን በአገራችን 13 ማዕከላትን ከፍቶ በትብብር እየሠራና እየረዳ ይገኛል።

    ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 10 ማዕከላትን (ሰባት ማዕከላትን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶስቱን በተለያዩ ከተሞች እ.አ.አ. በ2019) ለመክፈት ከኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት የካቲት 14 ቀን 2011ዓ.ም. ተፈራርመዋል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) STEMpower ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን ለማበልጸግ እያደረገ ያለውን ትብብር በማመስገን፥ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕድሉን በመጠቀም በአግባቡ ማዕከላቱን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ዲጂታል ሰሌዳዎችን መጠቀም ጀመረ።

    የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ለሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲአዲግራት ዩኒቨርሲቲአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ) ማዕከሉን በመጠቀም በአካባቢዎቻቸው ያሉትን የማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    የSTEMpower አስተባባሪ ዳይሬክተርና ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ቅድስት ገብረአምላክ፥ “STEMpower ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከድርጅቱ አመሠራረት ጀምሮ ዓላማውን፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና የወደፊት ዕቅድ አጭር ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል። ለወደፊትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በስፋት እንደሚሠሩ ፣ በ2040 የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ ገልጸዋል።

    አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ድርጅቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማዕከሎቹ በከፍተኛ ትምህርት እና በሳይንስ ትምህርቶች አከባቢ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ ረገድ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    STEMpower


    Anonymous
    Inactive

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በኪነ ህንፃ ሲያስመርቅ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፥ ዘንድሮ የተመረቁት 18 ወንዶችና 16 ሴቶች በአጠቃላይ 34 የኪነ ህንፃ ሙያተኞች መሆናቸውን በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

    ጎንደር (ሰሞነኛ)–የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለአምስት ዓመት ተኩል በኪነ ህንፃ ትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ቅዳሜ፥ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በባችለር ዲግሪ (BSc in Architecture) አስመረቀ።

    በምረቃ ሥነ ስርአቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፥ ዩኒቨርሲቲው በኪነ ህንፃ የትምህርት ዘርፍ ዘንድሮ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን ገልፀዋል።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ የትምህርት መስኮች ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ እንደሚገኝ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፥ ቅዳሜ ዕለት የተመረቁት 18 ወንዶችና 16 ሴቶች በአጠቃላይ 34 የኪነ ህንፃ ሙያተኞችም በሀገራችን የሚታየውን የህንፃ ጥበብ ችግር ለማስተካከልም ሆነ በሙያው የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመቅረፍ እንዲተጉ አሳስበዋል።

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ማሰገንቢያ የሚውል አስር ሚሊዮን ብር ለገሰ

    የጎንደር ከተማ ም/ከንቲባ ዶ/ር ሙሉቀን አዳነ በምርቃቱ ሥነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የተመራቂዎቹ የምርቃት ዕለት የልጅነት ዘመን አብቅቶ ለሀገር ብቁ የሆነ የኪነ ህንፃ ባለሙያ የሚሆኑበት ዕለት እንደሆነ አስገንዝበዋል። ከዚህ በኋላም ተመራቂዎቹ ሀገሪቱ ለረዥም ዓመታት የምትጠራበትና የምትታወስበትን የኪነ ህንፃ ጥበብ እንደሚያበረክቱ እምነታቸውን ገልፀዋል።

    ተመራቂዎቹም በሙያቸው ሀገራቸውን ለማገልገል የገቡትን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

    ከዩኒቨርሲቲው ዜና ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኔጅመንትና የህዝብ አስተዳደር ት/ቤት “በወቅታዊ የፖለቲካ ለውጥ ዘላቂነት ላይ የምሁራን ሚና” (‘The Role of Academicians in Sustaining the Current Political Reforms’) በሚል ርዕስ ዙሪያ ከካቲት 6 እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ኮንፈረንስ አካሂዷል።

    በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የጎንደር ከተማ ም/ከንቲባ ዶ/ር ሙሉቀን አዳነ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ፖለቲከኛ ፕ/ር መረራ ጉዲና፣ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የጎንደር ከተማ የልማትና የሰላም ሸንጎ አባላት የዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንቶች፣ ዲኖች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

    Semonegna
    Keymaster

    ጎንደር (ሰሞነኛ)– በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እየተተገበረ ለሚገኘው የጤና መረጃ አብዮት ትልቅ የሰው ኃይል የሚፈጥር የቀጠና/ወረዳ ጤና መረጃ ሥርዓት (District Health Information System 2 – DHIS2) አካዳሚ እና የኤለክትሮኒክስ ጤና ፈጠራ ቤተሙከራ (e-health innovation lab) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ተመረቀ።

    በምረቃ ፕሮግራሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየሁ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሄልዝ ኢንፎርማቲክስ (Health Informatics) ትምህርት ክፍል የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች፣ የአቅም ግንባታ እና የሜንተርሽፕ ድጋፍ ፕሮጀክትን (Capacity Building and Mentorship Project – CBMP) ከሚተገብሩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተሳታፊ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

    VIDEO: Ethio-American Doctors Group (EADG): Building a regional healthcare system & medical tourism

    የምረቃ መርሀግብሩን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የተመረቀው አካዳሚ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች እየተተገበረ የሚገኘውን የአቅም ግንባታ እና የሜንተርሽፕ ድጋፍ ፕሮጀክት (CBMP) ለመደገፍ ታስቦ የተከፈተ መሆኑን ገልፀው፤ በተለይ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ የጤና ተቋማት የሰው ኃይል በማሰልጠን ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ሀገሪቱ የያዘችውን የጤና መረጃ ሥርዓት በማዘመን የልህቀት ማዕከል ለመሆን ዩኒቨርሲቲው እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ለተሳታፊዎች ለፕሮጀክቱ ቡድን አባላት እዲሁም ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምስጋና አቅርበዋል ዶ/ር ደሳለኝ በንግግራቸው መብቂያ።

    በሀገራችን የሚታየው የጤና መረጃ አያያዝ ሥርዓት ከማሰባሰብ እስከ መረጃ መተንተን የሚታዩ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ እንደ DHIS2 ዓይነት ሥርዓቶችን መጠቀም ግድ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አበባው፥ ዩኒቨርሲቲው በትክክለኛው ሰዓት አካዳሚውን በመክፈቱ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። ዶ/ር አበባው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው የተጀመረው ሥራ እንደሀገርም እንደ ዩኒቨርሲቲም የሚያኮራ ነው ብለዋል።

    በአሁኑ ሰዓት 90 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት በDHIS2 ሥርዓት ሪፖርቶችን ማቅረብ መጀመራቸው ከጤና ጥበቃ ሚንስተር የመጡ ኃላፊዎች ተናግረዋል። መሆኑም ተመርቆ የተከፈተው አካዳሚ የጤና ኬላዎችን በመከታተል እና በመገምገም ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ወረዳዎችን በመረጃ አያያዝ ሥርዓት ሞዱል የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ኃላፊዎች ተናግረዋል።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ እየሠራ የሚገኘው ሥራ ለሌሎች ተቋማትም አርአያ መሆኑን የገለፁት ተሳታፊዎች፥ የ DHIS2 አካዳሚ በዩኒቨርሲቲው መከፈቱ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች እና አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ የሚያኮር ሥራ መሆኑ ገልፀዋል።

    በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተያዘው የጤና መረጃ አብዮት ዙሪያ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፥ ዶ/ር ቢንያም ጫቅሉ በአቅም ግንባታ እና የሜንተርሽፕ ድጋፍ ፕሮጀክት (CBMP) እስካሁን የተሠሩ ተግባራትን እና የወደፊት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል። በቀረበው ሀሳብ ላይ ውይይት ተደርጎ መርሀ ግብሩ ተጠናቋል።

    District Health Information System 2 (DHIS2) ምን እንደሆነ በዝርዝር ለማንበብ እዚህ ይጫኑ (እንግሊዝኛ)

    ምንጭ፦ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    DHIS2


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በቅርቡ ዋና ካምፓሱን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፍቼ ከተማ በምድረግ ከተመሠረተው ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዮ እና የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገናናው ጎንፌ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ እውቀትን ለማሸጋገር፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በጋራ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

    የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዮ በስምምነት ፊርማው ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር አብሮ ሊያሠራው የሚችል ስምምነቶችን በመፈራረም የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን መቻሉን ገልጸዋል። ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዱረም ስንዴ ላይ በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥና ድርቅን መቋቋም የሚችል ውጤት መገኝቱን፤ ከጎንደር ዩኒቨረሲቲ ጋር በመተባበር በደን ልማት ላይ እየተሠራ መሆኑን እና ከዲላ ዩኒቨረሲቲ ጋርም በመተባበር ለምርምርና ለቱሪስት መስህብ የሚውል የቦታኒክ ጋርደን ግንባታ ሥራ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

    VIDEO: Ethiopia: After mandatory preparations, Selale University accepts incoming students

    የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገናናው ጎንፌ በበኩላቸው ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በቅርብ ጊዜ ሥራ የጀመረ፣ እየሰፋ የሚሂድና ለግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው። የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ካለው መልካአ ምድራዊ አቀማመጡ ጋር በተያያዘም በእንስሳት ዝርያ አጠባበቅ በተለይም የተለያዩ ዝርያዎችን በማዳቀል ለአዲስ አበባ ከተማ 50 በመቶ የሆነውን የወተት ምርት የሚያቀርበው የሰላሌ አርሶ አደርን ተጠቃሚ ለማድረግ ከኢንስቲትዩቱ ጋር አብረው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

    ዶ/ር ገናናው አክለውም ስምምነቱ የወረቀት ላይ ስምምነት ብቻ እንዳይሆን ለማድረግና የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ሥራዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የአካባቢውን ማሕበረሰብ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ለማከናወን ዩኒቨርሲቲው መዘጋጀቱን ገለጸዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦  

    የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሚያዘጋጀው ሽልማት ዓላማ በኢትዮጵያ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ሥራ ማበረታታት መሆኑ በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ጊዜ የአገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆነ። ዩኒቨርሲቲው ያገኘውን ሽልማት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ደሳለኝ መንገሻ (ዶ/ር) ከፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ ተቀብለዋል።

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ስድስተኛ ዙር የጥራት ሽልማት ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተካሂዷል። በሽልማትና ዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ 40 ድርጅቶችና ተቋማት የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በውድድሩ ላይ

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ሐረር ቢራ አክሲዮን ማኅበር እና አማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት የአንደኛ ደረጃ ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የጥራት ደረጃውን ጠብቆ አሸናፊ በመሆኑ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

    The Ethiopian Quality Award Organization

    ከ336 በላይ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ጥሪ የተደረገ ቢሆንም የተመዘገቡት 52 ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ 21 በአምራች፣ አምስት በአገልግሎት፣ አራት በከፍተኛ ትምህርት፣ አምስት በጤና እና አምስት በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ፤ በድምሩ 40 ተቋማት እስከመጨረሻው በውድድሩ የዘለቁ ናቸው።

    የሽልማቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ሥራ ማበረታታት መሆኑ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ የሆኑት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጥራት ጉዳይ የሥነ-ልቦናና የፈረጠመ የኢኮኖሚ የበላይነት እንዲሁም የበለፀገ ማኅበረሰብ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል። የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከደረሱበት የጥራት ደረጃ ለመድረስ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በ2000 ዓ.ም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተቋቋመ ነው። ድርጅቱ ሲመሠረት ዓላማውን መንግስት በጥራት ረገድ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍና የጥራት ጽንሰ ሀሰብን በማኅበረሰቡ፣ በአምራቾች፣ በአገልግሎት ሰጪዎችና በግንባታ (ኮንስትራክሽን) ዘርፍ በተሰማሩ ድርጅቶችና ተቋማት ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ ነው። እስካሁን 49 ድርጅቶችና ተቋማት የድርጅቱን የልዕቀት ማዕረግ የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት


    Semonegna
    Keymaster

    ወራቤ (ሰሞነኛ)–በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስት፣ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የሚገኘው የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ክብርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት በተገኙበት ኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቋል።

    የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ ክብርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ካስተላለፉት መልዕክት ስለ ክልላዊነትና ዓለም አቀፋዊነት (localization and internationalization) የተናገሩት የሚገኝበት ሲሆን በንጽጽር መልክ ባስቀመጡት በዚህ ንግግራቸው ዓለማቀፋዊነት አጉልተው በማሳየት የሚከተለውን ብለዋል።

    ብዝሃነትና ዓለም አቀፋዊነት የዩኒቨርሲቲ መሰረታዊና ልዩ መለያ ባህሪዎች ናቸዉ። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ማኅበረሰቦች የብዝሃነት ባህሪን የሚገልጹ ሲሆን፤ ይህም በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በአመራሩ እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አከባቢያዊ እና ህብረብሄራዊ አመጣጥ ይገለጻል።

    ስለሆነም ዩኒቨርሲቲዎች የፌደራል ተቋማት እንደመሆናቸዉ መጠን ተማሪዎች በየአካባቢያቸው ባለው ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንዲማሩ፣ መምህራንም በአካባቢያቸው ባለው ዩኒቨርሲቲ ብቻ ተቀጥረው እንዲያስተምሩ፣ አመራሩም በተወለዱበት አከባቢ የሚገኘውን ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንድያስተዳድሩ የሚለው አስተሳሰብ ከዩኒቨርሲቲ ብዝሃነትና ዓለም አቀፋዊነት የማስተናገድ ባህሪ የወጣ ስለሚሆን የዩኒቨርሲቲዎቻችንን ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ነዉ።

    ዓለም አቀፍ ቶሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ዩኒቨርሲቲዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩበት አንዱና ዋነኛው መስፈርት፣ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍል ለሚመጡ ተማሪዎችና ሠራተኞች አቃፊ በመሆናቸውና ዓለም አቀፋዊነትን በማስተናገዳቸው ነው። ዩኒቨርሲቲዎች አለማቀፋዊነት ባህሪ እንጂ አካባቢያዊ ዉስንነት እንደማይመጥናቸዉ ያሳያል።

    ስለዚህ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና አሠራር በተቃራኒ አቅጣጫ መሄድ የለብንም! የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ከብሄራዊ አስተሳሰቦች አልፎ ዓለም አቀፋዊነት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎቻችንን በአካባቢያዊነትና በባህል በመከፋፈል፣ ባህላዊና ክልላዊ ማድረግ ወይም መከፋፈል አያስፈልግም።

    በሌላ የከፍተኛ ትምህርት እንቅስቃሴ ዜና፥ የጎንደር የኒቨርሲቲ ለሴት መምህራንና ሠራተኞች በወሊድ ወቅት በመደበኛነት የሚፈቀድላቸውን የወሊድ ፈቃድ አጠናቀው ወደ ሥራ በሚመለሱበት ጊዜ ህፃናትን በሥራ ቦታ የማቆያና የመንከባከቢያ ማዕከል ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።

    በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ክብርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ባስተላለፉት መልዕክት “የህፃናት ማቆያ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መጀመሩ ትልቅ ሥራ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲ ያሉ ሴቶችን ተሳትፎና ስኬታማነት ከማረጋገጥ አኳያ በጣም ትልቅ ሚና መኖሩን ገልፀው፥ ሴት መምህራን በሥራ ገበታቸው ላይ ቤት ትተው የመጡትን ህፃን በማሰብ በተከፈለ ልብ እንዳይሰማሩና ከወንድ አቻቸው ጋር ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ይህ የህፃት ማቆያ ችግራቸውን እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል።

    የዚህ ዓይነቱ የህፃናት ማቆያ ማዕከል በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢስፋፋ ሴቶች መምህራን በጥናትና ምርምር ሥራቸው ላይ አትኩረው እንዲሠሩ እገዛ እንደሚያደርግላቸውም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ጨምረው ገልፀዋል።

    ከዚህ በፊት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የወራቤ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 35 total)