Search Results for 'ሳሙኤል ክፍሌ'

Home Forums Search Search Results for 'ሳሙኤል ክፍሌ'

Viewing 8 results - 1 through 8 (of 8 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን መቀበል ከመጀመራቸው በፊት የተቋማቱ ዝግጁነት እንደሚረጋገጥ ተገለጸ

    አዲስ አበባ (የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመክፈት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል።

    በውይይቱ መጀመሪያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከል የትምህርትና ስልጠና ተቋማት መልሶ የመክፈት ሂደትና ዝግጅት በሚል ርዕስ ምክረ-ሃሳብ አቅርበዋል።

    በ2012 ዓ.ም የተቋረጠዉን ትምህርት በልዩ ዕቅድ ለማጠናቀቅ በሚሠሩ ሥራዎችና ትምህርት ሲጀመር ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲሁም ቀደም ተብለው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ምን መምሰል እንዳለባቸው በምክረ-ሃሳባቸው ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

    በጉባኤው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ‘መቼ እንክፈት?’ ለሚለው ትክክለኛ መልስ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በዓለም የጤና ድርጅት መለኪያ መስፈርት መሠረት ደረጃውን ጠብቆ በተዘጋጀ ዝርዝር በጥልቀት የዝግጅት መጠኑ ተፈትሾ ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል። በዚያ መሠረት የተቋማት ዝግጅት ይፈተሻል፤ በዳሰሳውም መሠረት መቀበል እንደሚችሉ ፍቃድ ይሰጣል ሲሉ አብራርተዋል።

    ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለፁት፥ ቅድሚያ ለተመራቂዎች [ቅድሚያ] በመስጠት፣ ተማሪዎችን በመከፋፈል በትንሽ ቁጥር ይጀመራል። ይህም ከሚታዩ ነገሮች እየተማርን የተማሪ ቁጥር ለመጨመር ዕድል ይሰጠናል ብለዋል። ዝርዝር አፈጻጸሙ በምን እንደሚመራ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ፕሮቶኮል ይዘጋጃልም ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንደመሆናቸው የክልል መንግሥታት ሥራ ይጠበቅባቸዋል። አማራጭ የለይቶ ማቆያ (quarantine) ቦታዎችን ማዘጋጀትም ግድ ስለሚላቸው እዚያ ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሠራል ብለዋል። ተማሪዎችን በማጓጓዝ ሂደት ችግር እንዳያጋጥም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንሠራበታለን ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የሚያስችል እቅድ ካሁኑ አዘጋጅተው ከአስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን ጋር በመወያየት የጋራ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል። የበፊቱን አሠራር ይዘን መቀጠል አንችልም፤ ዝግጅታችንን፣ ተጋላጭነታችንን አውቀን ተማሪ እንቀበላለን። አንድ ብሎክ ወይም አንድ ካምፓስ ኮቪድ-19 ቢያጋጥም ምን እናደርጋለን ከሚለው ጀምሮ በዝርዝር መሥራት እና እያንዳንዱ እቅድ ያለተማሪዎች እገዛ ተፈፃሚ ስለማይሆን ወደእነሱ ለማስረፅ መሥራት የግድ ይለናል ብለዋል።

    ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት፥ ጊዜው የተማሪዎች ሕብረት ኃላፊነት የሚፈተንበት ነው። የተማሪዎች ሕብረት አባላት የመፍትሄ ሃሳብ ሆናችሁ ለተፈፃሚነቱ ከዩኒቨርሲቲያችሁ ጋር በትብብር እንድትሠሩ ከእናንተ ይጠበቃል። ሰላማችሁን ማስጠበቅና ለደህንነታችሁ ዘብ መቆም ለትምህርታችሁ ቀጣይነት ዋስትና ነው ሲሉ አብራርተዋል። ዩኒቨርሲቲዎች መከፈታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ተመልሰው እንዳይዘጉም ጭምር የተማሪዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል።

    የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን አስመልክቶም የትኞቹ በዩኒቨርሲቲዎች ይቅረቡ የትኞቹ በተማሪዎች ይሟሉ የሚለውን ከተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለይቶ መወሰን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

    በውይይቱ ማጠቃለያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ውይይቱ ተቋማት የት ላይ እንደሆኑ ለይተን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ለመያዝ ታስቦ የተካሄደ ነው ብለዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎች በአሁኑ ጊዜ ቁርጠኝነት የሚፈልግ የለውጥ ሥራ እየሠራን እንደሆነ መገንዘብ እና በዚያው መጠን መፍጠን ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት የመመለስ ሂደት ባለድርሻ አካላትን በተገቢው መንገድ የማቀናጀት ኃላፊነት ተወስዶ መሠራት ያለበት ጉዳይ ነውም ብለዋል።

    ተማሪዎችን ከመመለስና የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ከማዘጋጀት አንፃር የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥታት እያንዳንዱ የራሱን ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል። እንደከፍተኛ ትምህርት ዓለም-አቀፋዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ምርምር ላይ የተገኘውን እውቀት ተጠቅመን ለሀገር የሚውል አድርገን መጠቀምም ይገባናል ብለዋል።

    ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ሥራውን በማስፈፀም ሂደት ኃላፊዎች የግንኙነት (communication) ክፍተት እንዳይኖር በመነጋገር ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመው አመራር የሁሉ ነገር ቁልፍ እንደመሆኑ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

    ነገ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፤ ከዚያም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተቋማቱን ለመክፈት ያበቃሉ ተብለው የተቀመጡ ዝርዝሮችን በመያዝ በዩቨርሲቲዎች በመገኘት ብቁ መሆን አለመሆናቸው ታይቶ አስፈላጊውን መስፈርት ካሟሉ ብቻ እንዲከፍቱ ይደረጋል ብለዋል – ዶ/ር ሳሙኤል።

    ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ወደኋላ የቀራችሁ ዩኒቨርሲቲዎች ካላችሁ ፈጥናችሁ ዝግጅታችሁን አጠናቅቁ ብለው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ጉዳዩንም እንደፕሮጀክት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለባቸው አስበዋል።

    ከተሳታፊዎች የተለያዩ ስጋት ናቸው ተብለው የተነሱ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ለመፍታት እንደሚሠራ ተገልጿል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን መቀበል

    Semonegna
    Keymaster

    በሁለቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የልህቀት ማዕከላት የሚሹትን ትኩረት ለይቶ ለመደገፍ ያለመ ጉብኝት ተካሄደ

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ዳይሬክተር ጄኔራሎች፣ ከፍተኛ አማካሪዎች እና ሌሎች ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና በአዳማ ሳይንስና ቴክሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል።

    በጉብኝቱ በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በአካል በመገኘት ዩኒቨርሲቲዎቹ የልህቀት ማዕከላት ሆነው ከተፈጠሩ ጊዜ አንስቶ ‘የመንግሥትን ተልዕኮ ተሸክመው የት ደርሰዋል? ምን ውጤት አስመዝግበዋል? ያጋጠማቸው ማነቆ ካለስ ምንድን ነው?’ የሚሉትን ጉዳዮች ለመለየትና መፍትሄ ለማስቀመጥ እንደተካሄደ ተገልጿል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ የጉብኝቱ ዓላማ በሀገራችን 16 የተለያዩ የልህቀት ማዕከላትን የያዙት አዲስ አበባ እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋቋሙለት ዓላማ አንፃር የሚገባቸውን ያህል እየሠሩ ነው ወይ የሚለውን ለማየት፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመለየትና በዚያው መጠን ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

    ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች ሐምሌ 2006 ዓ.ም መንግሥት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም እንዲሆኑ አድርጎና ተጠሪነታቸውን በወቅቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አድርጎ ሲያዋቅራቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስርጸት ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው በልዩ ሁኔታ የተመሠረቱ ሲሆን፤ ከመማር-ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር ልህቀት ማዕከልነት (centers of excellence) በኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ትስስር (industry-university linkages) እና በኢንኩቤሽን ማዕከልነት (incubation centers) እንዲያገለግሉ ታስበው ነው ብለዋል።

    በልህቀት ማዕከላቱ ተማሪዎች ተምረው ሲወጡ ኢንዱስትሪውን በቀጥታ መቀላቀል የሚችሉበት አቅም እንዲያፈሩ ታልሞ መሠራት እንዳለበት ጠቁመው፥ ይህ እውን እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራዎች ጋር አገናዝበን በቋሚነት በዕቅድ እንድናግዛቸው እንሠራለን ብለዋል ፕ/ር አፈወርቅ። የልህቀት ማዕከላት በሀብት መደገፍ እንዳለባቸው ገልጸው፥ ነገር ግን ከመንግሥት ቋት ብቻ ሊሆን ስለማይቻል ሀብቶች ማፈላለግ ላይ በጋራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው፥ የተደራጀ ተቋማዊ አሠራር በመፍጠርና ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ተቋማቱን ወደ ትክክለኛ የልህቀት ማዕከልነት መለወጥ ይቻላል ብለዋል። በአከባቢያቸው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የሀገራችን የቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ ሳይንስና ምርምር ተቀባይ ብቻ ሆኖ መቀጠል የለበትም ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል፥ መሪ እንዲሆኑ ሀብት አፈላልጎ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ፈጥሮ መሥራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ በሁሉም የልዕቀት ማዕከላት የሰው ኃይል ችግር መፍታት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለሀገር ብልጽግና ካላቸውም ፈይዳ አንጻር በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንዲሚደረግላቸውም ገልፀዋል።

    ቡድኑ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ጉብኝት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳ በዩኒቨርሲቲው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የገለፁ ሲሆን፤ ዓለምአቀፍ እውቅና ለማግኘት የሚያግዙ የአሠራር ሂደቶችን ተከትለው ለመሥራት እየጣሩ መሆኑን ገልፀው፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢያግዘን ያሏቸውን ተግዳሮቶች አቅርበው ውይይቶች ተካሂደው የመፍትሄ ኃሳቦችም ተጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ያሉ የልህቀት ማዕከላት፣ ቤተ-ሙከራዎች እና የግንባታ ሥራዎችም ተጎብኝተዋል።

    በተመሳሳይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ሲካሄድ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ ዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከተሰየመበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተሰሩ ሥራዎችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን፥ እንዲሁም የተፈጠሩ ትስስሮችን (partnerships) እና አጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ያለውን የሰው ሀብትና ተማሪዎች መረጃ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል። በዩኒቨርሲቲው ልዩ ነው ያሉትን የደብል ሜጀር እና ፋስት ትራክ የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታንም ጨምረው አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፥ በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው 161 የሦስተኛ ዲግሪ (doctoral) ተማሪዎች አሉ።

    በሁለቱ ጉብኝቶች ከተነሱት ዋና ዋና ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች ውስጥ የግዥ ሥርዓት ችግሮች፣ የተሽከርካሪዎች እጥረት፣ ብቁ መምህራን ከገበያ ላይ በቀላሉ ያለማግኘት፣ በፋይናንስ ምክንያት የግንባታ ሥራዎች መዘግየት ይገኙበታል።

    በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ ማጠቃለያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፥ የልህቀት ማዕከላት ሲባል አንድ ተቋም በአገሪቱ መሪ የሆነ የቴክኖሎጂ ማዕከል መሆን ማለት ነው። ይሄንን ደግሞ ከኢንዱስትሪ ጋር ትስስር በመፍጠር፣ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና (TVET) ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ኢንዱስትሪውን የሚመጥን፣ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ያሟላ ሰልጣኝ ለገበያ የሚያቀርብ፣ ተግባራዊ ምርምሮች የሚካሄዱበት መሆን ሲቻል ነው ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ እንፈልጋለን ብለው ያቀረቧቸውን በመውሰድ እንሠራበታለን ሲሉም ዶ/ር ሙሉ አክለዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ ዘመናዊ የሳይንሳዊ አስተሳሰቦች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተገናኝተው ለሀገር ብልጽግና የሚውሉባቸው እንደመሆናቸው አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

    በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የልህቀት ማዕከላት በቡድኑ የተጎበኙ ሲሆን፤ በጉብኝቱም ዩኒቨርሲቲዎቹ የተለያዩ የሀገር ሀብት የሆኑና ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች ተቋማት የሌሉና በተለይ ለምርምር ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እንደ ኤሌክትሮማይክሮስኮፕ ያሉ መሣሪያዎች መኖራቸው ተመልክቷል። ይሄንንም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በጋራ ለመጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ማመቻቸት ያስፈልጋል ተብሏል። በቀጣይም ተቋማቱ የተፈጠሩበትን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ እና ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲቻላቸው የሚያግዙ የታቀዱ ድጋፍና ክትትሎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ይካሄዳሉ ተብሏል።

    አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የልህቀት ማዕከላት፦

    1. Sustainable Energy
    2. Mineral Exploration, Extraction and Processing
    3. Nano Technology
    4. Bioprocessing and Biotechnology
    5. Construction Quality and Technology
    6. High Performance Computing and Big Data Analysis
    7. Artificial Intelligence and Robotics
    8. Nuclear Reactor and Technology

    አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የልህቀት ማዕከላት፦

    1. Space Technology Institute
    2. Institute Of Pharmaceutical Science
    3. Institute Of Water Resource and Irrigation Engineering
    4. Electrical System and Electronics
    5. Advanced Manufacturing Engineering
    6. Advanced Material Engineering
    7. Urban Housing and Development
    8. Transportation and Vehicle

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 34 የሕክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ለሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1233 ተማሪዎቸ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመርቋል።

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በዋና ግቢው እና በዱራሜ ካምፓስ 6 ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በተከታታይ ትምህርት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።

    በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፥ ኢትዮጵያ ለእርሷ እና ለዜጎቿ ክብር እና ፍቅር ያለው ባለሙያ ያስፈልጋታል ብለዋል። አክለውም ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት በተገቢው ሁኔታ ለማኅበረሰብ ለውጥ እንዲያውሉት አሳስበዋል።

    ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን በማጠናከር የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስረግጡም ዶ/ር ሳሙኤል ጠይቀዋል።

    የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያየ መልኩ ከሚንፀባረቀው የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ኋላ ቀርነት በመራቅ ለኅብረተሰብ ዕድገት እና ብልፅግና እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።

    በሌላ በኩል ደግሞ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም ያሰለጠናቸውን 33 የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ።

    ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም (hybrid innovative curriculum) በሕክምና ዶክትሬት ያሰለጠናቸውን 33 ተማሪዎች በተመሳሳይ ቀን አስመርቋል።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ለተማሪዎቹ የሥራ መመሪያ የሰጡት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ ተመራቂዎቹ ቃለመሀላ በገቡለት የሕክምና ሥነ-ምግባር በመታገዝ ቅን አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል። ከዚህም ባለፈ በተግባር በተደገፈው ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም የቀሰሙትን የሕክምና ትምህርት የሀገሪቱን ብሎም የዓለምን ሕዝብ ስጋት ላይ ከጣሉ ዘመን-ወለድ የጤና ችግሮች ኅብረተሰቡን ለመታደግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በውጤት በታገዘው የቅይጥ ፈጠራ-አከል ሥርዓት (ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም) ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸው በመሆናቸው ማኅበረሰቡን ከጤና እክሎች ከመታደግ ባለፈ በምርምር ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር ብልፅግና የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ 26 የማስተርስ ዲግሪ (ሁለተኛ ዲግሪ) ተማሪዎችንም አስመርቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ጎንደር (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. 251 የህክምና ዶክተሮችን አስመርቋል። በዚሁ ዕለት ዩኒቨርሲቲው ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዘርፍ እያደረገ ያለው ምርምር አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን አስታውቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በህክምናው ዘርፍ ከአጋር አካላት ጋር በተባበር በአባላዘር፤ በወባ በሽታ፤ በሳንባ ምች እና ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች (communicable and noncommunicable diseases) ዙሪያ ምርምሮችን በማካሄድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አስመዝግቧል። የምርምር ውጤቶቹም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሠራባቸው የቆዩ የህክምና መመሪያዎችን እስከ ማስቀየር የደረሱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን መብቃታቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

    “የምርምር ውጤቶቹ የህክምና ጊዜን በማሳጠር በመርፌ ይሰጡ የነበሩ ህክምናዎችን በአፍ በሚሰወዱ መድኃኒቶች በመተካትና የህሙማንን ስቃይ፤ እንግልትና የህክምና ወጪንም ለመቀነስ አስችለዋል” ብለዋል ዶ/ር አስራት።

    በየዓመቱም በጤናው ዘርፍ ብቻ ከ150 በላይ የምርምር ውጤቶች በታወቁ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ጭምር ለህትመት የበቁበት ሁኔታን መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ36ኛ ጊዜ በህክምናው ዘርፍ ካስመረቃቸው 251 ዶክተሮች መካከልም 64ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው፥ ምሩቃኑ በህክምናውና በምርምሩ ዘርፍ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል። የዕለቱ ተመራቂዎች ለሙያቸውና ለገቡት ቃል-ኪዳን ታማኝ በመሆን ከግል ጥቅም ይልቅ ሕዝብን በማገልገል ፍጹም አዛኝና ሩህሩህ በመሆን ለህክምናው ሥነ-ምግባር ተገዥነታቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡም መክረዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው “የህክምና ሳይንስ ትምህርት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት የሚታደግ የተከበረ ሙያ ነው” ብለዋል። “ተማራቂዎች ለዚህ የደስታ ቀን ትደርሱ ዘንድ እውቀት ላቀበሏችሁ መምህራን፤ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ለወላጆቻችሁ ብሎም ከእናንተ ብዙ ለምትጠብቀው ውድ ሀገራችሁ ድርብ ኃላፊነት አለባችሁ” ሲሉ አሳስበዋል።

    “ትምህርት የሁሉም መሠረት በመሆኑ ሀገርንና ወገንን ወደ እድገት ለማሻገር በተማርኩት ሙያ ለማገልገል ዝግኙ ነኝ” ያለችው ከዕለቱ ተመራቂዎች መካካል በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነችው ዕ ዶክተር ነጻነት ሃይሉ ነች። የሀገሪቱን ስር የሰደዱ የጤና ችግሮች ለመፍታት በጤናው ዘርፍ ምርምሮችን በማካሄድ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማድረግ የረጅም ጊዜ ህልሟ መሆኑንም ተናግራለች።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በዩኒቨርሲቲው በምርምርና በህክምናው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሀኪሞችና ተመራማሪዎች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት በጤናው ዘርፍ 26 የመጀመሪያ፤ 37 የሁለተኛና 6 የሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም 10 የስፔሻሊቲ የትምህርት ፕሮግራሞች ሲኖሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በጠቅላላው (በአምስቱ ካምፓሶቹ) 87 የመጀመሪያ፤ 137 የሁለተኛና 29 የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች አሉት። በጠቅላላው ከ45,000 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ሲሆን፣ 8,300 ሠራተኞች አሉት።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ
    —–

    ፍቼ (ሰሞነኛ) – ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ ሀምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት አስመርቋል። በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

    በምርቃት መርሀግብሩ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕት ‛ከጀግናው ጀነራል ታደሰ ብሩ መገኛና ከየዋኋ እናት አበበች ጎበና አገር የምትመረቁ ተማሪዎች በጀግንነት ሀገርን ማሻገር፣ በየዋህነት ሁሉን ማቀፍ መርሀችሁ ሊሆን ይገባል’ ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት በበኩላቸው ‛መማር ለራስ ብቻ መኖርና መለወጥ ሳይሆን ለሀገራችን ህዝብ ችግር መፍትሄ መፈለግ ነው’ በማለት የዕለቱ ተመራቂዎች የሀገራቸውን ችግር የሚፈቱ ብርቱ ዜጎች እንዲሆኑ አበክረው ተናግረዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ግርማ አመንቴ ሲሆኑ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ‛በዓለም ላይ ያለምንም ድንበር ከሀገራችሁ ጀምሮ በየትኛዉም ቦታ የመሥራትና ማንኛዉንም ዕድሎች በመለየትና በመጠቀም በምክንያታዊነት፤ ከስሜታዊነት የወጡ ዉሳኔዎችን በመዉሰድ ለዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ የምታደርጉ ዜጎች ለመሆን ራሳችሁን ማዘጋጀት ይጠበቅባችኋል’ ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ለሦስት ዓመታት በሁለት ኮሌጆች፥ ማለትም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።

    በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጀ። የአድዋ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት ሰጠ።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩት ጥናትና ምርምሮች ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በአገሪቷ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡት የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሚጠበቀው በታች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም እንደ ዋነኛ ምክንያት አስቀምጠውታል። እንዲያውም ለዘርፉ የሚመደበው አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን በመጠቆም።

    በተጓዳኝም የምርምር መሠረተ-ልማቶች አለመኖር፣ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ መሆንና መምህራን ለምርምር ትኩረት አለመስጠታቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩት ጥናታ ምርምሮች ቁጥር አነስተኛ መሆነ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ባሏቸው አቅም በአስገዳጅ መልኩ የጥናትና ምርምር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸዋል።

    ምንም እንኳን በትምህርት ተቋማቱ ዝቅተኛ ቢሆኑም በሥመ-ጥር ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ምርምሮቻቸውን የሚያወጡ ጉምቱ ምሁራን መኖራቸውንም ዶ/ር ሳሙኤል አልሸሸጉም።

    ለጥናትና ምርምር የሚበጀተውን በጀት በተመለከተም ከአገሪቷ እድገትና ከመምህራኑ አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ እያደገ የሚመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ጆርናሎች ጥራታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጥናት እየተደረገበት መሆኑንም አስረድተዋል። መመሪያውንም በቅርቡ ወደ ሕግ በመቀየር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ጆርናሎች የሚመሩበት ወጥ ሥርዓት በመዘርጋት የእውቅና ደረጃም እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

    እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ መውሰድ (ረቂቅ አዋጁን ማውጣትም ሆነ ለጆርናሎች መመሪያ መዘጋጀት) የሚካሄዱትን ምርምሮች ጥራታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፥ በቀጣይም ጥናትና ምርምር ላይ የግሉ ዘርፍ የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

    በአሁኑ ወቅት የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ቁጥር 33 ሺህ ደርሷል፤ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺህ 500 የሚሆኑት ናቸው ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው – የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው።

    ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ፥ ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት መስጠቱን በትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የአድዋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የዩኒቨርስቲውን ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

    የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘብራአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ እንዲውል መሬቱ ተሰጥቷል። በዚህም 131 የአካባቢው አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ላይ ተነስተዋል። ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮችም ካሳ ክፍያ ለመፈፀም 15 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ በበኩላቸው ግንባታውን ለማስጀመር ከፌዴራልና ከትግራይ ክልል መንግሥታት 450 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። ከዚህም የትግራይ ክልል መንግሥት 250 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል መግባቱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ አስተዳደርም በቅርቡ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – STEMpower የተሰኘ መቀመጫውን USA (ሳሌም፥ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ) ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲዎች እየረዳ የሚገኝ ሲሆን በአገራችን 13 ማዕከላትን ከፍቶ በትብብር እየሠራና እየረዳ ይገኛል።

    ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 10 ማዕከላትን (ሰባት ማዕከላትን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶስቱን በተለያዩ ከተሞች እ.አ.አ. በ2019) ለመክፈት ከኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት የካቲት 14 ቀን 2011ዓ.ም. ተፈራርመዋል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) STEMpower ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን ለማበልጸግ እያደረገ ያለውን ትብብር በማመስገን፥ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕድሉን በመጠቀም በአግባቡ ማዕከላቱን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ዲጂታል ሰሌዳዎችን መጠቀም ጀመረ።

    የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ለሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲአዲግራት ዩኒቨርሲቲአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ) ማዕከሉን በመጠቀም በአካባቢዎቻቸው ያሉትን የማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    የSTEMpower አስተባባሪ ዳይሬክተርና ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ቅድስት ገብረአምላክ፥ “STEMpower ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከድርጅቱ አመሠራረት ጀምሮ ዓላማውን፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና የወደፊት ዕቅድ አጭር ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል። ለወደፊትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በስፋት እንደሚሠሩ ፣ በ2040 የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ ገልጸዋል።

    አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ድርጅቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማዕከሎቹ በከፍተኛ ትምህርት እና በሳይንስ ትምህርቶች አከባቢ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ ረገድ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    STEMpower


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን የግንባታ አፈፃፀም በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተደረገ የክዋኔ ኦዲት መሠረት በማድረግ ይፋዊ ስብሳባ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. አካሂዷል። በስብሰባው ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ11 ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት በተጠና ዕቅድ ላይ ያልተመራ እንደነበረ ገልጿል።

    በኦዲት ሪፖርቱ ግንባታዎቹ በምዕራፍ ተከፋፍለው መቼ እንደሚሠሩ፣ እያንዳንዱ ሥራ ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅና በአጠቃላይ በመሪ ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ ባለመደረጉ በግንባታው ሊሟሉ የሚገቡ የግብዓት፣ የቤተ ሙከራና የመፅሐፍት ግዥ ማሟላት እና የካሣ ክፍያ በተገቢው ሁኔታ መፈፀም አለመቻሉ ተገልጿል።

    በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ11 ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደስታ በሰጡት ምላሽ ግንባታዎቹ የ5 ዓመት መሪ ዕቅድ ቢያዘጋጁም በዕቅዱ መሠረት ለማከናወን የበጀት እጥረት በመኖሩ በዕቅዱ መሠረት መፈፀም እንዳልተቻለ፤ የግብዓትና የቤተ ሙከራ እቃዎችን የመንግሰት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በወቅቱ ባለማቅረቡ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ገልፀው፥ እንደመፍትሔ ተማሪዎች ወደ አጎራባች ዩኒቨርሲቲዎች ሄደው የቤተ ሙከራ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ እንደሚገኝ እና የካሣ ክፍያን በተመለከተ ክልሎች የተከፋዮችን ዝርዝር በተሟላ ሁኔታ አደራጅተው የማይልኩና ለተከፋዮቹም በቀጥታ በአካውንታቸው እንዳይገባ የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ ክፍያው እነሱ በፈለጉት አግባብ መፈፀሙን ተናግረዋል።

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ማሰገንቢያ የሚውል አስር ሚሊዮን ብር ለገሰ

    ለዲዛይን መጣጣምና ቁጥጥር ለሚሠሩ አማካሪዎች ክፍያ በበጀት ብር 28,600,000.00 የተያዘ ሲሆን ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር ውል ሲፈራረሙ ብር 117,668,636.09 በመሆኑ ብር 89,068,636.09 (311%) በብልጫ መዋዋሉ የኦዲት ግኝቱ አመልክቷል።

    አማካሪዎች ክፍያን በተመለከተ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ምላሽ 28 ሚሊዮን ብር በ2008 ዓ.ም. /ለአንድ ዓመት/ ብቻ ለሚከናወን ግንባታ የተገመተ እንደሆነ እና ብር 117 ሚሊዮን ግንባታው በሚቆይባቸው አጠቃላይ ዓመታት የተቀመጠ ወጪ መሆኑን ተናግረዋል።

    ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚሠራቸው የግንባታ ሥራዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት የሚጠበቅበት ቢሆንም ቅንጅት ባለመፈጠሩ ምክንያት የውሃ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት ችግር ማጋጠሙን፣ የካሣ ክፍያ ተፈፅሞላቸው ከይዞታቸው ያልተነሱ መገኘታቸውን እና በደምቢ ዶሎ፣ በወራቤ፣ በራያ፣ በመቅደላ፣ በአምቦና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ለካሣ ክፍያ በበጀት ለግንባታ ተነሽዎች 100 ሚሊዮን ተይዞ የነበረ ቢሆንም ተከፍሎ የተገኘው 215,071,377.16 መሆኑንና ይህም ክፍያ የብር 115,071,377.16 ብልጫ ያለው መሆኑ ተገልጿል።

    ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ከመፍጠር አንጻርም ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር በተለያየ ሁኔታ እንደተደረገላቸው፤ የሚመለከታቸውን አካላትን ማወያየታቸውንና አስፈላጊ ክፍያዎችንም ለአገልግሎት አቅራቢ ተቋማት መፈፀማቸውን ገልፀው ነገር ግን በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስካሁን በተሟላ ሁኔታ ሊያገኙ አለመቻላቸውን የተቋሙ ኃለፊዎች ተናግረዋል።

    በኦሮሚያ ክልል አቦካዶ አምራች ገበሬዎች የተሻሻሉ ዘሮችን በመጠቀም ምርታቸውን ማሳደግ ችለዋል

    በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የ3,210,218.24 ብር የካሣ ክፍያ ሰነድ ማስረጃ ሳይኖረው መከፈሉን፤ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ሳይት 17 አባወራዎች የግንባታ ካሣ ቢከፈላቸውም አለመነሳታቸው፤ በራያ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፕሮጀክት ለሚገኙ 35 ካሣ ተከፋዮች ክልሉ በመጀመሪያ አጥንቶ ካፀደቀው ብር 7,347,757.30 ውስጥ ብር 4,049,779.00 በመቀነስ ብር 3,279,978.30 ብቻ የከፈለና ለሌሎች በጥናቱ ውስጥ ለሌሉ 6 ተነሺዎች ብር 399,706.32 ካሣ መከፈሉ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል።

    የካሣ ክፍያ በበጀት ከፀደቀው ሊቀነስ የቻለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዕቅድ ያስቀመጠውን የካሣ ተመን እንዲቀንሱ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት መፈፀሙን፤ ካሣ ተከፍሏቸው ከተነሱ በኋላ እንደገና ተመልሰው የሚሠፍሩ ነዋሪዎችን በተመለከተም ተነሺዎች ካሣው አንሶናል፣ ተተኪ ቦታ አልተሰጠንም የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችን በማንሳት ተመልሰው የሚሠፍሩ መሆኑን አቶ ሰለሞን ደስታ አስረድተዋል።

    የዩኒቨርስቲዎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ለባለይዞታዎች ካሣ ተከፋዮች የግል አካውንታቸው ማስገባት እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ ቢገልፅም መመሪያው ተጥሶ ለ468 ባለይዞታዎች ለራያ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች በጥቅል በደደቢት ብድርና ቁጠባ ሂሣብ ቁጥር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ፤ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች ለፍቼ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት መምሪያ፣ ለቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች ከፋ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ግዥ፣ ክፍያና ንብረት አስተዳደር እና ለእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት አጠቃላይ ብር 79,925,769.02 እንዲገባ መደረጉ እና እስከ ህዳር 29/2009 ዓ.ም ድረስ ገንዘቡ ያልተወራረደ መሆኑ ግኝቱ አመልክቷል።

    The Yellow Movement AAU: Speaking up for women and girls – empowering women (Ethiopia)

    ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በሰጡት ምላሽ ካሣ ለባለይዞታዎቹ እንዲከፈል መመሪያ ተዘጋጅቶ በመመሪያው መሠረት ለተነሺዎች ካሣ እንዲከፈል ቢታቀድም ክልሎች በአንድ ጊዜ ገንዘቡ ለተነሺዎች ቢሰጣቸው በዘላቂ አኗኗራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል በሚልና በሌሎች ምክንያቶች በተነሺዎች በአካውንታቸው ገቢ አለመደረጉን ገልፀዋል።

    የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር አቅዶና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ የመሥራት ውስንነት መኖሩን፤ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አለመደረጉን ገልፀው የግለሰቦች የካሣ ክፍያ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በወጣው መመሪያ መሠረት በየግል አካውንታቸው ገቢ ሊደረግ እና የግንባታ ፕሮጀክቶች ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በተገቢ መጠን ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ11 ዩኒቨርሲቲዎችን ለመገንባት ሲያስብ በዕቅዱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በተገቢ ሁኔታ ያለየ መሆኑን፤ ከፌዴራልና ከክልል አካላት ጋር ከፍተኛ የቅንጅት ችግር መኖሩን፤ ከግብዓት ጋር በተያያዘ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ግቢ ሜዳ ላይ ሣር እየበቀለባቸው ያሉ ግብዓቶች እስካሁንም በመኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የካሣ ክፍያዎች በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ሊፈፀም እና ክፍያዎቹ ለባለመብቶቹ መድረሱን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ በኦዲት ግኝቱ የታዩ ችግሮችን በዕቅድ መፍታትና ማረም እንደሚገባ ጠቅሰው ችግሮቹ በሌሎች ተመሳሳይ ግባታዎች እንዳይደገሙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

    ምንጭ፦ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የ11 ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት


Viewing 8 results - 1 through 8 (of 8 total)