Search Results for 'በድሉ ዋቅጅራ'

Home Forums Search Search Results for 'በድሉ ዋቅጅራ'

Viewing 8 results - 1 through 8 (of 8 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የሰሞኑ “ቃል በተግባር” የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘጋቢ /ገላጭ/ ፊልም በሁለት ኢትዮጵያውያን አተያይ
    [ቃል በተግባር ― በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እና በአቶ ያሬድ ኃይለማርያም አተያይ]

    • ቃል በተግባር ― ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት
      [በድሉ ዋቅጅራ (/)]

    ኢትዮጵያን እንደሀገር ያገለገልኳት፣ ያፈቀርኳት በ1970ዎቹ መጨረሻ (1976-79) ባለው ጊዜ ነበር፤ በመጀመሪያው ዙር የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘመኔ። ከትምህርት ቤት በግዴታ ታፍሼ የገባሁበት የብሔራዊ ውትድርና ከሀገሬ ጋር ልብ ለልብ አስተዋወቀኝ፤ አፈቀርኳት።

    ግዳጄን ፈጽሜ፣ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ፣ በ1983 አ.ም. ወደ ሥራ ስሰማራ ኢትዮጵያን አጣኋት። በብሔር ፖለቲካ ሴራ የተካኑ፣ ስሟን መጥራ የሚዘገንናቸው መሪዎች እጅ ወድቃለች። ለጎሳና ቋንቋ ድንበር ከልላ፣ ባንዲራ [ሰንደቅ ዓላማ] ሰቅላ እሷ ፈዝዛለች።… ለብሔረሰቦችና ለቋንቋዎች እኩልነትና ለሰብዓዊ መብት መከበር ዝም ብዬ አላውቅም፤ እሟገታለሁ። ባንዲራቸው ሲከልላት፣ የምትተነፍሰው አየር ሲያጥራት፣ ኢትዮጵያን ሲረሷት ግን አዝናለሁ፤ ያመኛል።

    ከረዥም ጊዜ በኋላ በትላንትናው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት። ዘመንን መስላ፣ ተስፋ አዝላ አነበብኳት። በሦስት ዓመት፣ ያለጥላቻና ግጭት ዜና ነግቶ በማይመሽበት ሀገር፣ ‘የእኔ ሀሳብ ካልሆነ ሀገሬ ትበተን’ በሚል ጽንፍ ረገጥ ፖለቲካዊ መርገምት ውስጥ፣ እንኳን በልዕልና መሥራት፥ በትክክል ማሰብስ ይቻላል ወይ? ያውም ይህ ሁሉ ኃላፊነት ለተጫነበት መሪ?!

    የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው!

    አዎ፣ ሀገራችን የብሔር ፖለቲካው ካጣባት ደዌ አልተፈወሰችም። አዎ አሜሪካ ማእቀብ ጥላብናለች። አዎ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ መሬታችንን ይዛለች። አዎ የትግራይ ወገኞቻችን በከፍተኛ ሰብዓዊ ችግር ላይ ናቸው። አዎ የኤርትራ ወታደሮች ከሀገራችን ጨርሶ አልወጡም። አዎ ሸኔና የጁንታው ርዝራዦች በሚሰነዝሩት ጥቃት አሁንም ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነው። አዎ የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል።… ሀገራችን ውስጥ በርካታ ችግሮች፣ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

    እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ እነዚህ አስደናቂ ፕሮጀክቶች መሠራታቸው አግባብ አይደለም በማለት ሰዎች ለጥላቻቸው የሰበብ ድር ያዳውራሉ። እኔን የሚገርመኝ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ መሠራት መቻላቸው ነው።

    መሠራት የነበረበት ያልተሠራ አለ። ካልተሠራው የበለጠ የተሠራው የወደፊት መንገዳችንን ያሳያል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሀገሪቱ ባጀት ሳይነካ፣ የተሸለመውን የግል ገንዘብ ሳይሰስት፣ ወዳጆቹን ለምኖ በሦስት ዓመት፣ ጥላቻና ዘለፋን ቁብ ሳይል ይህንን ሠራ። ባለቤቱ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁ ከሀያ በላይ ትምህርት ቤቶችን በገጠር ቀበሌዎች ገነባች። ለመሆኑ እነዚህን ሰዎች የማናደንቀው ከእነማን ጋር እያወዳደርናቸው ነው? እንኳን በሦስት ዓመት፣ በሦስት አስርታት ውስጥ የዚህን ግማሽ የሠራ መሪ ኖሮን ያውቃል?

    እንደመሪ እነሱ ይህን ሠሩ፤ ያልመለሷቸው ችግሮችም አሉ። እኛስ! እንደ ዜጋ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምን ሠራን? እኛ እንደዜጋ ያለነው የት ነው? የሠሩት በጎ ተግባር ወይስ ያልመለሷቸው ችግሮች አካል ነን? በዋናነት የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው። ሀገራችን በውስጥና ውጭ ችግር ተተብትባለች፤ ፈተና ላይ እንደሆነችም እናውቃለን። ዋናው፣ እያንዳንዳችን ማወቅ ያለብን ጉዳይ ግን ሀገራችንን የተበተባት ችግር፣ የተጋረጠባት ፈተና አካል አለመሆናችንን ነው። እና እንጠይቅ! እንደዜጋ የቆምነው የት ነው?!

    /ር በድሉ ዋቅጅራ ደራሲና ገጣሚ ሲሆኑ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሂዩማኒቲስ፤ የቋንቋዎች ጥናት የጆርናሊዝምና የኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ውስጥ ደግሞ መምህር ናቸው። ከዚህ ቀደም ለህትመት ከበቁላቸው ሥራዎች ውስጥ የማይፃፍ ገድል፣ የራስ ምስል፣ ያልተከፈለ ስለት፣ የወይራ ስር ጸሎት፣ የማይጻፍ ገድል፣ የተስፋ ክትባት፣ እና ፍካት ናፋቂዎች የጠቀሳሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ ቲያትር ቀርቦ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘውደብተራውየተሰኘው የሁለት ገጸባሕርያት ቲያትር (two-handler theater) ደራሲ ናቸው።

    • ቃል በተግባር ― እያደነቅን ስጋታችንንም እንገልጻለን፤ አቧራው መሬት ላይ ያለ ግፍ፤ ሃሜቱም ሃቅ ነው
      [አቶ ያሬድ ኃይለማርያም]

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ የሠሯቸውን እና እየሠሯቸው ያሉ ድንቅ ነገሮችን አደንቃለሁ። ለዚህ ሥራቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ከሠሯቸው ሥራዎቹ አንዱ የሆነውን የእንጦጦ ፖርክን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞኛል። የሚያስደምም ድንቅ ሥራ ነው።

    ከትላንት መግለጫቸውም ሁለት ነገር መረዳት ይቻላል። አንደኛው ሀገር ለማልማት ብዙ እቅድ እና ህልም እንዳላቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግ አንባገነን እሰከመሆን የሚሄዱ መሆናቸውን ነው። አገሪቱ አሁን ያለችበትን ውጥንቅጥ እና አሳሳቢ ችግር፣ የተቃዋሚዎቻቸውን ቅሬታ እና በመንግሥታቸው ላይ የሚሰነዘሩ ቅሬታዎችን ‘አቧራ’ በሚል ገልጸውታል። “ሀሜት አቧራ እንጂ አሻራ መሆን አይችልም። አቧራውን ንቀን አሻራ ማኖራችንን እንቀጥላለን” የምትለዋ ንግግራቸው አለቃቸው የነበሩትን መለስን [የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን] አስታወሱኝ። ባጭሩ የመለስን የመታበይ ንግግር ነው የደገሙት። መለስ ‘ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሎቹም ጉዟቸውን ይቀጥላሉ’ ነበር ያሉት?

    ታቃዋሚዎቻቸውን ውሻ አድርገው እና ተቋውሟቸውንም እንደ ውሻ ጩኸት ቆጥረው እሳቸው ከጉዟቸው ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል እንደማያስቆማቸው ሊያውም በፓርላማ ፎክረው ነበር። የመሠረት ድንጋይ ጥለው ያስጀመሩትን የሕዳሴ ግድብ መጨረሻ ለማየትና ሪባን ለመቁረጥ ግን አልታደሉም። ግመሎቹስ ዛሬ ወዴት አሉ? አብይም ያች በሽታ እየታየችበት ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ያፈጠጠ እና አሳሳቢ ችግር እንደ አቧራ መቁጠር መጥፎ መታበይ ነው። አቧራው እንዲሰክን የሚቀርቡ ምክርና ወቀሳዎችንም እንደ ሀሜት መቁጠር ሌላው አሳሳቢ የክሽፈት ምልክት ነው።

    ሕዝብ እየተራበ ነው፤ የኑሮ ውድነት ሌላ የቀውስ ምንጭ ነው፤ ያልተረጋጋ ፖለቲካም የልማት ጸር ነው፤ ጦርነትም አውዳሚ ነው፤ የመብት ጥሰቶች መበራከት የአፈና ሥርዓት መሳለጫ ነው። እነዚህ ችግሮች አቧራ አይደሉም። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚቀርብብዎት ወቀሳና ነቀፌታዎች ሀሜት አይደለም። ልማቱን ግፉበት፤ መታበይዎን አቁመው ለዲሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና ለፍትህ ቀናዕይ በመሆን እንደ ልማቱ አፋጣኝ መልስ ይስጡ። ካልሆነ ግን መካር እንደሌለው ንጉሥ… ይሆናሉ።

    አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ቃል በተግባር

    Anonymous
    Inactive

    የገዳዮች ወንድማማችነት

    የገዳዮች ወንድማማችነት
    አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ

    ሰዎች በተለያየ ርዕሰ ነገር ወይም ዓላማ ይወዳጃሉ። የወዳጅነቱ ዓይነት የትየለሌ በመሆኑ ቆጥሬ አልዘልቀውም። በጥቅሉ ግን ማኅበራዊ ፋይዳው መልካም የሆነ ሕብረት ሲሆን ያ ጓድ የለውጥ ሠራዊት/ሐዋርያት “pioneers of change” የሚል ታሪካዊ ቅጽል ያገኛል። እንደሰንደቅ የሚውለበለብ ድል ባያቀዳጅም ዘወትራዊ ሕይወትን በድል የሚያሻግር መደበኛ ወንድማማችነትም ክብር ይገባዋል። ዓላማው በጉልህ የማይታየው የፈንጠዝያ ውድጅትንም ቢሆን የሚለካው አግኝቶ “ቢሰፍሩት” ዋጋው ከፍ ሳይል አይቀርም። ዝንጋኤ እስካላስከተለ ድረስ አብሮነት ደግ ነው።

    እኔን ግርም የሚለኝ የነፍሰ-ገዳዮች “ወንድማማችነት” (Fraternity of Assassins) ነው። ይህ ውድጅት በተለያየ ምክንያት ይመሠረታል። አንዳንዱ እጅግ እውቀታዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ፍልስፍናዊ መሠረት ያለው ይመስላል። ይሁንና የዚህን ሕብረት መሠረት ቢያናጉት ከሆድ ወይም ከግላዊ ጥቅም የዘለለ ጉዳይ አታገኙበትም። ይህ ቡድን ለስሙ መጠርያ ተጨናቂ፣ ለቀለሙ ማማር ተብረቅራቂ፣ የሆዱን ጩኸት “በሕዝብ አለኝታነት” ደባቂ ነው። ይህን መልከ ቀናነት ለመቀዳጀት የታቀደ “እውነት”የሚመስል ቅደም ተከተላዊና ፈር ያለው ስልት ያዘወትራል። ይህ ውድጅት በነገረ ፆታ፣ በነገረ ወሲብ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በፖለቲካ አቋም፣ በሙያ… በመሳሰለው ታላላቅ ሰብዓዊ ጉዳይ ሁሉ ልታይ፣ ልታይ ይላል፤ ሀገር ያውካል። ይህ ዓይነቱ ውድጅት ይሉኝታ ሲያልፍም አይነካው። እንደደጎች ሁሉ የዚህን ቡድን ደቀ-መዛሙርት በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።

    1. የጋራ የሆነችውን ሀገራችንን ጠፍጥፈው ዛሬ የሠሯት ይመስል፥ እኔ ብቻ አውቅልሻለሁ ይሏታል። መሽቶ እስኪነጋ “አያምኗትም”፤ ከቆሙበት ስፍራ በቀር ተጨማሪ ወይም የትየለሌ ግላዊም ቡድናዊም አንጻር፣ ምልከታ፣ አቋም፣ ወዘተ… እንዳለ አይረዱም። ቢረዱም ሌላው ሁሉ የማይረባና የተዋረደ ነው። በጉልህ የሚታያቸው “ከሀገር የሚሰፋው ሆዳቸው” ነው። ሀገር አፍ አውጥተሽ ተናገሪ ቢሏት ስለነዚህ ሰዎች ቃላት የሚያጥሯት ይመስለኛል።

    በሌላ ወገን እነዚህ ሰዎች በሰይፉ መታፈርያ ፍሬው አንዲት የግጥም አንጓ እንዲህ ይታዩኛል:-

    ይህ ዓለም ይህ ዓለም” ይላሉ፥
    ይህን ዓለም ሞልተው እንደኖሩ ሁሉ።

    ሀገሩ የማናየው፣ የማናውቀው፣ የማንሰፍረው፣ የማንለካው፣ የማንገምተው ጭምር ብዙ ጉዳይ አለው፤ ዓለም ሰፊ ነው። ይህን ሲያውቅ ሰው ትህትና ትዘልቀው ይመስለኛል።

    1. ጩኸት መቀማት ዓይነተኛ ጠባያቸው/ፍሬያቸው ነው። በዚህ ጠባያቸው “ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው አልቃሽ” በመሆን ከፊት ተሰላፊ ናቸው።
    2. ስለመቃወም መቃወም የሚያስገኘውን ትርፍ ያሰላሉ። ጀብድ እንጂ ጀግንነት አያውቃችውም።
    3. ተቆርቋሪ ከሚመስለው የፊት ገፃቸው ባሻገር ድብቁ ህልማቸው ሆድ መሙላት ወይም ጥቅም ማሳደድ በመሆኑ ያቀዱት ሲከሽፍ ካሸናፊው ጎን ለመሰለፍ እፍረት አታውቃቸውም። የጠበቁት ጥቅም ካልተገኘ ጠላት ለመሆን እንዲሁ አይሰንፉም፤ ይቸኩላሉ።
    4. በእነሱ ዘንድ ወዳጅ ማለት ከጠባብ ሆዳቸው የመንጨ ደካማ ህልማቸውን የሚያገለግል እና ለሙት ህልማቸው ሕይወት መዝራት “ለምን? “ ሳይል የሚሰለፍ agent/object ነው።

    እነዚህ ሰዎች ውድጅት የሚያስፈልጋቸው የሰው ልጅ ለብቻው የማይገፋቸው በርካታ ሕይዎታዊ ጉዳዮች ስላሉት ነው። ወዳጅነት ለብቻ የማይገፋውን ለመግፋት የሚመሠርቱት ስላታዊ ኮንትራት ወይም ‘strategic alliances’ ነው። እንደተራራ የከበዳቸውን ሸክም ካራገፉ በኋላ ግን “ሆዳቸው አምላካቸው” ሆኖ ያርፈዋል።

    በተለምዶ “ባንዳነት” ለፍርፋሪ ተገዝቶ ከውጭ ጠላት ጋር በግልፅ በመወገን ሀገርን መጉዳት/መክዳት ብቻ የሚመስለው ብዙ የዋህ አለ። ነገር ግን ባንዳነት መጠነ ዙሪያው እጅግ ሰፊ ነው። የሀገርን ህልም ለግል ሆድ መሸቀጫ ማድረግ መጠኑም ልኩም ካቅም በላይ ነው።

    የገዳይ ወንድማማቾቹን መስፋፋት በማኅበራዊ ድረ-ገፆች፣ በቴሌቪዥን መስኮቶች፣ በሬዲዮና በመሰለው ሁሉ አዋጅ ነጋሪ ሆነው ማየት አዲስ አልሆን አለ፤ ተለመደ። የምናዋጣት ማንኛዋም “ቅንጣት” ነገ ለሚፈጠረው ሀገራዊ ግዙፍ ምስል አስተዋፅኦ ስላለው እየተስተዋለ ለማለት የተፃፈ። ምክሩ መካሪውን እንዲጨምር ይሁን አሜን!

    አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ

    አቶ አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፥ ቲያትርና ጥበባት ኮሌጅ ውስጥ በሚገኘው አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና መምህር ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የገዳዮች ወንድማማችነት

    Anonymous
    Inactive

    ዛሬ በይቅርታ ላይ ስናፌዝ ዋልን!
    በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

    የሀገሬ ሰዎች ለይቅርታ (ይቅርታ ለመጠየቅም፣ ይቅርታ ለማድረግም) ንፉግ ናቸው። “ሳላውቅ ያስቀየምኳቸሁ፣…” ብሎ ይቅርታ መጠየቅ። መጀመሪያ እስቲ አውቀን የበደልናቸውን ይቅርታ እንጠይቅ። አውቄ የበደልኩት የለም ለማለት ነው? በየአንዳንዳችን ልብ የበደል ቁልል አለ፤ ያንን ለመናድ መድፈር ነው ይቅርታ። የበደልከውን ሰው፥ “ይህን ስላደረግኩህ ይቅር በለኝ” ብለህ መጋፈጥ። በደለኛነትን ሸሽጎ በይቅርታ መንጻት አይቻልም።

    ይቅርታ በጅምላ አይሆንም። መሪዎች የገደሉትን፣ ያሰሩትን፣ ያፈረሱበትን፣ የወረሱትን፣… ወዘተ በስም እየጠሩ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው – እውን ይቅርታ ከፈለጉ። ጎንደር ላይ ወጣት ሲረሽን የነበረ፣ ተነስቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ የሚጠይቅበት ምክንያት የለም፤ የገደለውን ያስገደለውን በስም እየጠራ፣ የሟች ቤተሰቦች ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ስትላቀቅ የተደረገው ይኸውም ነው። በሀገር ላይ የተሠራ በደል ካለ (ለምሳሌ ኢትዮጵያን የባህር በር እንደማሳጣት ዓይነት) ሕዝብ ይቅርታ ይጠየቃል። አንድ ተማሪ የበደለ መምህር ክፍል ገብቶ “ያስቀየምኳችሁ ይቅርታ” ሲል፥ ‘ፐ! ይቅርታ ጠየቀ’ ይባልለታል። በፍጹም፤ ይቅርታ አልጠየቀም!! ስሙን ጠርቶ፣ የበደለውን ገልጾ ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት።

    ይቅርታ መጠየቅ ነው ወይንስ ማግኘት ቁም ነገሩ? እንዴ ይቅርታችንን ተበዳይ መቀበል አለመቀበሉን ማወቅ የለብንም? ካለብን ከበደልነው ጋር መጋፈጥ የግድ ነው። የጎረቤቴ ልጅ በተገደለ፣ በታሰረ እናት አባቱ እንጂ እኔን ማን ይቅርታ አድራጊ አደረገኝ?

    ደግሞ አንዳንዱ ይገርማል፤ እራሱን ከኢየሱስ መስቀል ላይ ሰቅሎ መሀሪ ይቅር ባይ መሆን ያምረዋል፤ ይቅርታ እኮ ዝቅ ማለት ነው። “ሳላውቅ በድያችኋለሁ፥ ይቅርታ አድርጉልኝ፤ እናንተ ግን አውቃችሁ በድላችሁኛል፥ ይሁንና ይቅር ብያችኋለሁ” ሲባል እኔ ንጹህ፣ እናንተ ኃጢአኞች ማለት እኮ ነው። እስቲ የሚከተለውን ይቅርታ እንመልከት።

    “… እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ። እኔንም ለበደሉኝ፣ ያለበደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታን አድርጊያለሁ።

    አሁን እዚህ ውስጥ ምን የይቅርታ መንፈስ አለ? ይቅርታ ጠያቂው፣ አውቆ የበደለው አንድም ነገር የለም። እሱ ላይ የተደረገውን በደል ግን ሆን ተብሎ፣ ታቅዶ እንደተደረገ በዝርዝር ተቀምጧል። ምናለ የእነሱንም፥ ‹‹ሳታውቁ ለበደላችሁኝ›› ብሎ ቢያልፈው? ወይ የእሱንም (እሱ የበደለውንም፣ ያጠፋውንም) ቢዘረዝረው?

    እና እባካችን ያልደረስንበትን እንተወው፤ ቢያንስ ጽንሰ-ሀሳቡ ለልጆቻችን ይቀመጥ፤ እነሱ ይደርሱበት ይሆናል፤ የልጅ ልጆቻቸውም ቢሆኑ።

    በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)*

    * በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ደራሲና ገጣሚ ሲሆኑ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሂዩማኒቲስ፤ የቋንቋዎች ጥናት የጆርናሊዝምና የኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ውስጥ ደግሞ መምህር ናቸው። ከዚህ ቀደም ለህትመት ከበቁላቸው ሥራዎች ውስጥ የማይፃፍ ገድል፣ የራስ ምስል፣ ያልተከፈለ ስለት፣ የወይራ ስር ጸሎት፣ የማይጻፍ ገድል፣ የተስፋ ክትባት፣ እና ፍካት ናፋቂዎች የጠቀሳሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ ቲያትር ቀርቦ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው “ደብተራው” የተሰኘው የሁለት ገጸባሕርያት ቲያትር (two-handler theater) ደራሲ ናቸው። በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ሊያገኟቸው ይችላሉ።

    ** ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በድሉ ዋቅጅራ

    Anonymous
    Inactive

    የምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ ሀገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል! ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። ወረርሽኙ በሰዎች ጤና እና ደኅንነት ላይ ካደረሰው እና እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ የዓለምን እና የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እና ሥርዓትን ከባድ አደጋ ውስጥ ከቷል። ወረርሽኙ በሀገራችን ኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። በሌሎች ሀገር ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አሁንም አለ። የጎረቤት ሀገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት የጀመረበትና በተለይ ከጅቡቲ ጋር ካለን የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው።

    ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከአሁኑ እየታየ ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ጫናም በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ይህም በቶሎ ወደቀድሞ ሁኔታው የሚመለስ አይሆንም። የበረሀ አንበጣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ እንደዚሁም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና እስከ ሰኔ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዋስትና የማጣት ስጋት/አደጋ እንዳንዣበበባቸው በቅርቡ ተገልጿል። በአጠቃላይ ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው መጠነ ሰፊ መቀዛቀዝና የአገራዊ ጥቅል አመታዊ ምርትና እድገት ማሽቆልቆል ሀገራችን ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው።

    በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል።

    ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባን ካለነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ከሌሎች ሀገሮች የተደቀነብን አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ የነበረውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ሀገርን ማን ያስተዳድራል የሚል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ነው የሚሉትን ሀሳብ እያቀረቡ ይገኛሉ።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በተለይም ከሕገ-መንግሥት ጠበቆች (constitutional lawyers) ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። ባለሙያዎቹ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ-መንግሥታዊ አግባብ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለውን የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ የባለሙያዎች ጉባዔ (high level panel of experts) በማቋቋም ለአንድ ወር ያህል ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት ቆይቷል። ኢዜማ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ልንከተለው የሚገባው የመፍትሔ ሀሳብ የሚከተሉትን ታሳቢዎች ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤

    1. አገራችን ከምትገኝበት የሕግም የፖለቲካ አጣብቂኝ በአጭር ጊዜ ለመውጣት የሚረዳ መሆን እንዳለበት፣
    2. ተቋማዊ አሠራሮችን ከማጎልበት አንፃር የተሻለ ዕድል የሚፈጥር መሆን እንዳለበት፣
    3. አጠቃላይ ችግሩ በአጭር ጊዜ ፈቶ አገራችን ወደተረጋጋ የምርጫ ሂደት ለመግባት የሚያስችል መሆን እንዳለበት፣
    4. ከወጪም ከጊዜም አንፃር አገሪቱን ብዙ ዋጋ የማያስከፍል የተሻለው አማራጭ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በፍጥነት የተቀያየሩት የአገራችንንና የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካዊና የደኅንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት።

    ኢዜማ ከላይ የገለፅናቸውን ሀገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት እንደሚያስፈልገን ያምናል። ለዚህም እንደፓርቲ ልንከተለው የሚገባን የመፍትሄ ሀሳብ ይህንን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው በፅኑ ይረዳል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፓርቲያችንን የሕግ ባለሙያዎች ጨምሮ በሌሎች አካላትም የቀረቡትን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

    1. ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሄ በሚል በተለያዩ አካላት የቀረበ የመፍትሄ ሀሳብ

    በዋናነት በዚህ ረገድ የቀረበው ሀሳብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚያበቃ በመሆኑ እና ሕገ-መንግሥቱም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ክፍተት ስለማይሰጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሠረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ነው። ይህ መፍትሄ ሀሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው። ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ያሉብንን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር አይደለም። ይህም የገባንበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ ያደርገዋል።

    1. በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች

    2.1. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ማድረግ፦ ይሄ አማራጭ በ6 ወር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እና ሕግ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ የሀገር እና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ከግምት የማያስገባ፣ የፌደራል መንግሥትን እንጂ ሥልጣናቸው አብሮ የሚጠናቀቀውን የክልል ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ያላገናዘበ አማራጭ በመሆኑ የምንፈልገውን ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር አማራጭ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.2. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀመጠ አንቀጽ አይደለም። አስቸኳይ ግዜ ማዋጅም በቀጥታ የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘምን አያስከትልም። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር የሚደረግ ምርጫን ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም።

    2.3. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ከፌደሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ፦ በዚህ አማራጭ መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ሥራ የሚሠራው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሙሉ ነፃነት እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተመራለትን ጉዳይ በመመርመር የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ያ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ክብደት አንጻር ጉዳዩን መዳረሻ ውጤቱ አስቀድሞ በእርግጠኝነት ለማይታወቅ እና ምናልባትም መልሶ እዚህ ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል አንደኛውን እንድንከተል ሊያደርግ ለሚችል ሂደት መስጠት ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.4. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፦ ይህ አማራጭ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።

    ምንም እንኳን ኢዜማ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም፥ አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። አሁን ለገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በኢዜማ እምነት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ሀገራዊ መረጋጋት፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እንዲሁም በከፍተኛ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው ሀገራዊ ጉዳይ በዚህ ወቅት ሊከወን አይገባም ብለን እናምናለን። ሆኖም አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልፅ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ-መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

    በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቁ እንዲሁም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ 2/3ኛ ክልሎች (6 ክልሎች) በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁት በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ 3 ስር ከሚገኙት እና አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን የሕገ-መንግሥት አንቀጾች ማሻሻል እንደሚቻል ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58/3 ከላይ በተገለጸው መሠረት ማሻሻል የተሻለ መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን።

    ይህ መፍትሄ ተግባራዊ ከተደረገ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት ተከትሎ የሚፈፀም በመሆኑ ሕገ ምንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። በዚህ አማራጭ ላይ በተለያዩ አካላት የሚነሳው ጥያቄ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት በአንቀጽ 104 ድንጋጌ መሠረት ህዝብን ለማወያየት አያስችልም የሚል ሲሆን ይህንን ክፍተት ግን ሕዝቡን በወኪሎቹ አማካኝነትና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በማወያየት መሸፈን ይቻላል።

    ከዚህ ቀደም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የጋራ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን በሚመለክት የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀጽ 103/5 በሕገ-መንግሥቱ የተጠቀሰውን የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሳይከተሉ ለየብቻ በተለያየ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ አሁን መደረግ ያለበት ማሻሻያ ግን የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105/2 ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች በሙሉ አሟልቶ ሊሆን እንደሚገባው እናምናለን።

    ይህ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌድሬሽን ምክር ቤትንም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት።

    የፓርቲያችን እምነት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ቢሆንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተራ ቁጥር 2.3 ላይ የጠቀስነውን አማራጭ በመውሰድ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጥ 54/1፤ 58/3 እና 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደመራው ታውቋል። ምንም እንኳን ኢዜማ ይህንን አማራጭ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ-መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ አለበት። ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት።

    በአጠቃላይ እንደሀገር የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ለማሳሰብ ይወዳል። በተጨማሪም በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መዳበራቸው መፍጠር የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድንለማመድ በር የሚከፍት እና ሁሉንም ኃይሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የምናደርግበት መድረክ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    Anonymous
    Inactive

    ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ተሰብስቦ የነበረው የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባለ አምስት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

    ከህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

    የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በክልላችንና በሀገራችን እንዲሁም በንዑስ ቀጣናው የተከሰቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስፋት በመመርመር የውሳኔ ሃሳቦችን አሳልፏል። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በክልላችን እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የክልላችንና የሕዝባችን ድኅንነት የመታደግ ሥራዎችን እንዲሁም የኮረናን ወረርሽኝ ለመመከት የተሠሩ ሥራዎች በሚመለከት በዝርዝር የተወያየበት ሲሆን፣ እስካሁን የታዩ ጥንካሬዎችን ጠብቆ ለማቆየትና የታዩ ጉድለቶችን ለማረም የተሠሩ ሥራዎችን በመመርመር ውሳኔዎችን አሳልፏል። በክልላችን ያሉ ወይም የሚኖሩ ፈተናዎች ለመመከት አሁንም ወሳኙ ውስጣዊ ጥንካሬያችን መሆኑን በድጋሚ በማረጋገጥ በዚህ ረገድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል።

    የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሦስት ቀን ስብሰባው በስፋት ከመከረባቸው ጉዳዮች ዋነኛው በሀገር ደረጃ በብልፅግና ፓርቲ እየተካሄደ መጥቶ አሁን በመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ ዘመቻ የሚመለከተው አጀንዳ የጎላ ትኩረት የተሰጠው ነበር። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዝርዝር ተወያይቶ እንዳስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት ያላሳየበትን ሀገራዊ ምርጫ የCOVID-19 ወረርሽኝ መከሰትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በግልፅ እንደታየው የፓርቲዎችን ሃሳብ ለመቀበል በሚል በተጠራ የይስሙላ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለቀለት ያሉትን ሃሳብ ማጠናቀቂያ ክፍል ምን ሊመስል እንደሚችል በግልፅ አመላክተዋል።

    የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህ ያለበቂ ዝግጅትም ሆነ ያለግልፅ አጀንዳ የተጠራውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕግ ውጭ በሥልጣን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት መድረክ ተከትሎ በፓርላማው የተጀመረውና ሕግን ያላግባብ በመተርጎም የብልፅግና ፓርቲን ሕገ-ወጥ የስልጣን ዕድሜ የማራዘም እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ አስምሮበታል። አሁንም ሥልጣን ላይ ባለው ኣካል የተጀመረውና ሕገ-መንግሥትን መተርጎም በሚል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ ግልፅ ሆኗል።

    በዚህም መሠረት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉተን ውሳኔዎች አሳልፏል።

    1. የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግሥቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የተጀመረው ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም። ሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልፅ መስፈርት መሠረት አሻሚ ሁኖ ለተገኙ አንቀፆች እንጂ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ውጭ ለማራዘም ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፍያ በአስቸኳይ ቆሞ አሁንም የኮረና ወረርሽኝን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ሆነ ሀገራዊ ምርጫን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውሰጥ በመሆን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ተደርጎ ሀገርን ከለየለት የጥፋት አደጋ ለመታደግ እንዲቻል መድረክ እንዲመቻች ይጠይቃል።
    2. የእንደዚህ ዓይነቱ መድረክ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የብልፅግና ፓርቲ ነፃና ግልፅ ምርጫ የመምራት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ብቃት የሌለው በመሆኑ ይህንን ለማስፈፀም የሚችል የተለየ አደረጃጀት የመፍጠር አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስከበር አስፈላጊነት በቂ ትኩረት በሰጠ መልኩ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲጀመር ጥሪውን ያቀርባል።
    3. ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወትሮውኑም ገዢውን ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሶ ራሱን በወራሽነት ያስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ከመስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ጠባብም ቢሆን ዕድል የማይኖር በመሆኑ የሀገሪቱ ችግር ለመፍታት ወደሚከብድ ችግር የምትገባበት ዕድል መፈጠሩ የማይቀር ይሆናል። ህወሓት እንደዚሁ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጥረው የሚችለውን ትርምስ ለማስወገድ በሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶች ውስጥ ድርሻውን በቀናነት ለመጫወት ዝግጁ ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ በተከለው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደዋዛ እንዲጣልበት አይፈቅድም። ለዚህም ሲባል ከትግራይ ሕዝብና ለትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ ዕውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ ይህንኑ የሕዝባችንን መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ወስኗል። ይህ እንቅስቃሴ የፀረ ኮረና ወረርሽኝ ዘመቻችንን እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸውን ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎችን ባሟላ መልኩ የሚፈፀም ይሆናል።
    4. የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ህልውናቸው ያረጋገጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በጠራራ ፀሀይ ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር በማስቆም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳቸውን እንዲያርቁ በዚህ አጋጣሚ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ጥሪውን ያቀርባል።
    5. በመጨረሻም ህወሓት ሆነ የትግራይ ሕዝብ የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን ያረጋገጠውን ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማዳን በሚደረገው ርብርብ መሰል አጀንዳ ከሚያራምዱ ብሔር ብሔረሰቦችም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን አሁንም በድጋሚ ማረጋገጥ እንፈልጋለን።

    የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ጽ/ቤት
    ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.

    ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

    የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉተን ውሳኔዎች

    Anonymous
    Inactive

    “የጃዋርና የልደቱ ትልቁ ችግር ሕዝብን በኪሳቸው እንደያዙት ሳንቲም ሲፈልጉ ሊያስቀምጡት፣ ሲፈልጉ ደግሞ አውጥተው ሊጠቀሙበት፣ ደፍነው ለጅምላ ግዢ፣ ዘርዝረው ለችርቻሮ ሊያውሉት የሚችሉት አድርገው መቁጠራቸው ነው።”

    ሕዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም (በድሉ ዋቅጅራ)

    የጃዋርን እና የልደቱን ውይይት አየሁት፤ ሰማሁት። ላየው የቀሰቀሰኝ ዋና ነጥብ አንድ ላይ ያመጣቸውን ጉዳይ የማወቅ ጉጉት ነበር። አገኘሁት። ያቀረቡበት መንገድ ነው ልዩነቱ፤ የጃዋር በፖለቲከኛ (ብስለትና መሰሪነት)፣ የልደቱ በወታደር (ጉልበትና ማስፈራራት) ከመቅረቡ በስተቀር፤ ‹መስከረም 30 የመንግሥት ሕጋዊ ተቀባይነት ስለሚያበቃ፣ መንግሥት እኛ የምንለውን የማይቀበል ከሆነ ሕዝቡ ከእኛ ጋር ቆሞ መንግሥት እንዲቃወም፣ እንዲታገል› ነው።

    በጎው ነገራቸው ―
    “መንግሥት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሁኔታው ላይ መወያየትና መስማማት አለበት” የሚለው ነው። በእርግጥ መንግሥት ይህን ማድረግ አለበት፤ ይህ ሕዝብ በኮሮና ድቀቱ ላይ፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጠር ነውጥን የሚሸከም ትከሻ አይደለም፤ የሚሰማ ጆሮ የለውም።

    የጃዋርና የልደቱ ትልቁ ችግር ሕዝብን በኪሳቸው እንደያዙት ሳንቲም ሲፈልጉ ሊያስቀምጡት፣ ሲፈልጉ ደግሞ አውጥተው ሊጠቀሙበት፣ ደፍነው ለጅምላ ግዢ፣ ዘርዝረው ለችርቻሮ ሊያውሉት የሚችሉት አድርገው መቁጠራቸው ነው። ሕዝቡን እውን ቢያውቁት የትላንቱን ውይይታቸውን ይዘውለት ለመቅረብ ባልደፈሩ ነበር። በተለይ አዚህ ላይ የልደቱ ድፍረት ለከት አልነበረውም። ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት ስብሰባ እንኳን ለመምራት፣ መብት እንደሌለው ሲናገር፣ ስለራሱ ሀገር የሚያወራ ፈጽሞ አይመስልም፤ በወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ስለተራዘመበት መንግሥት ሳይሆን፣ ሀገር ለቅቄ እወጣለሁ ያለበትን ቀን ስላላከበረ ቅኝ ገዢ የሚያወራ ነው የሚመስለው። የሚገርመው ከወራት በፊት ልደቱ “ተቃዋሚ ፖርቲዎችን 10 ሺህ ፊርማ እንዲያሰባስቡ መጠየቅ፣ ፓርቲዎችን ማዳከምና እንዳይመሠረቱ ማድረግ ነው…” ባለበት አፉ ዛሬ 100 ሚሊየን ሕዝብ ከጎኑ እንደሆነ በሙሉ ልብ ሲናገር መስማት ጤንነቱን ያጠራጥራል፤ .. ሕዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም።

    ውይይታቸውን ልብ ላለ የልደቱና የጃዋር ልዩነት (ምንም እንኳን ጃዋር የፓርቲያቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ግልጽ ባያወጣውም) ለችግሩ የሚያቀርቡት የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ነው። በግሌ የጃዋር ፓርቲ የሽግግር መንግሥትን እንደመፍትሄ የሚያቀርብ አይመስለኝም። ዶ/ር መረራ እና ጃዋር እራሱ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች በመሆናቸው እውቀታቸውን ተጠቅመው የተሻለ ሀሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ።

    የልደቱ “የሽግግር መንግሥት” ሀሳብ ግን እንዳለው ቀድሞም በቀዳማዊ ኢህአዴግ መውደቅ ፍትጊያ (2009/10 ዓ.ም.) የነበረ፣ ዛሬም ከኮረና ጋር ያለ ነው። ልደቱ ከፍተኛ የስልጣን ፍላጎት ያለው ይመስለኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የ97ቱ ምርጫ ሕዝባዊ ቅቡልነቱን እንዳወረደውና የሚፈልገውን የስልጣን እርካብ እንደማያስረግጠው ያውቃል። በመሆኑም ፓርቲዎች በመዋጮ የሚያቋቁሙት የሽግግር መንግሥት ነው ብቸኛ የማርያም መንገዱ። ይኸው ነው።

    በርካታ ሀገሮች በኮሮና የተነሳ ምርጫ አራዝመዋል፤ የትኛው ሀገር ነው የሽግግር መንግሥት የመሠረተው? የሽግግር መንግሥት የተወሰነ ጊዜ ተሰፍሮለት የሚመሠረት ነው። አሁን ያጋጠመው ችግር ወረርሽኝ ነው፤ 6 ወር ወይም ዓመት ሊወስድ ይችላል፤ አናውቅም።

    ለሁለቱም ―
    ፖለቲከኛ መሆን ካሻችሁ ሕዝቡን እወቁት፤ አክብሩት። አክብሮታችሁ ቀርባችሁ ከማወቃችሁ ይሁን። ሕዝብን የማያከብር ፖለቲከኛ ሕዝብን ሊመራ አይችልም። ሕዝብን አክብሩ። ሕዝብ ጉልበት ስትፈልጉ የምትገዙበት የሚስጢር ኪሳችሁ ሳንቲም፤ ስልጣን ሲርባችሁ እየነቀላችሁ የምትጥዱት የጓሮአችሁ ጎመን አድርጋችሁ አትኩጠሩት።

    በድሉ ዋቅጅራ

    የጃዋርና የልደቱ

    Semonegna
    Keymaster

    ‹‹የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር›› በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሠራተኞችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

    አርባ ምንጭ (AMU) – በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል።

    የዝግጅቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በንባብ ባህል ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር እውቀት እንዲስፋፋ እና ልምድ እንዲዳብር ለማድረግ እንዲሁም ማኅበረሰቡ የመጽሐፍትን ጥቅም ተረድቶ ከሌሎች ወጪዎች በመቀነስ የመግዛት ልምድ እንዲቀስም ለማስቻል መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሰገድ ካሣሁን ገልፀዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ ገጣሚ፣ ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የንባብ ጅማሮ፣ ጥቅምና የመምህራን ሚናን አስመልክቶ ባቀረቡት አንኳር ሀሳብ ንባብ ሊለካ የሚችለው በአንባቢው ላይ በሚያመጣው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ንባብ የተለያየ ነገር ግን የተዋሀደ ይዘት ያለው እንደመሆኑ ማኅበራዊ ተግባቦት እንዲጨምር፣ ተአማኒ እውቀት እንዲዳብር ብሎም ባልኖርንበት ዘመንና ቦታ በምናብ እንድንኖር የሚያደርግ ጥልቅ ምስጢር አለው ብለዋል።

    ጥሩ አንባቢ የአፃፃፍ ስልትና የቃላት አመራረጥን ከመረዳት ባለፈ በሚያነበው ጉዳይ ራሱን የሚመለከትና የሚፈትሽ እንዲሁም የሌሎችንም ስሜት መረዳት የሚችል እንደሆነ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ተናግረዋል። ለዚህም መምህራን ከመጽሐፍት ምርጫ አንስቶ መልካም ልምዶችን ለትውልዱ በማካፈል በመረጃ የዳበረና ያወቀ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ለአንድ ማኅህበረሰብ እድገት የተማረ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገሪቱ ከመሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።

    ማንበብና መጻፍ ከግለሰብ ባለፈ ለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ናቸው ያሉት ፕሬዝደንቱ፥ የንባብ ባህል እንዲዳብር አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት፣ አቅምና ጊዜ በተገቢው በመጠቀም፣ ተፈላጊውን የአዕምሮና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት እንዲሁም ምክንያታዊ ትውልድ በመፍጠር ከግለሰብና ከማኅበረሰብ ባለፈ ለአገር ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚቻል ገልፀዋል። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ ባህል መዳበር አጽንዖት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ምንም እንኳ ጥንታዊ የሆኑና የተለያየ ዘውግ ያላቸው የስነ-ጽሑፍ ውጤቶች እንዲሁም ወቅታዊ አዕምሯዊ ውጤት የሆኑ የህትመት ውጤቶች ቢኖሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው የንባብ ባህል መቀዛቀዝ በመረጃ የበለጸገና ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ እንደ አገር ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ ተናግረዋል። በአገሪቱ ለንባብ የሚውለው ጊዜ በዓለም አንባቢ ዜጋ ካላቸው አገራት አንጻር በሣምንት ለንባብ ከሚያውሉት አማካይ ጊዜ በእጅጉ መራቁን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያስረዱም ዶ/ር የቻለ ገልፀዋል።

    በማኅበረሰቡ ዘንድ መጽሐፍትን ገዝቶ ከማንበብ ይልቅ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ምርኮኛ መሆን፣ የወረቀትና የህትመት ዋጋ መጨመርና ሌሎችም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ የንባብ ባህል መዳበር ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ባህሉ እንዲያንሰራራና መሻሻሎች እንዲመጡ ጠንከር ያለ ጥረትን ይጠይቃል።

    በንባብና ሚዲያ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚያጠነጥን የውይይት መነሻ ጽሑፍ የዶክትሬት (PhD) ተማሪ በሆኑት አቶ ተመስገን ካሣዬ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በዚህም ዘመኑ የቴክኖሎጂና የመረጃ ከመሆኑ ባሻገር የሚዲያ ተግባቦት ባህሎችን ከሌላው ጋር የመቀየጥ አቅም ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል።

    ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ንባብ የአንድ ወቅት ሂደት ስላልሆነ በየደረጃው ያለው ሁሉም ማኅበረሰብ ከዋና ሥራው ጎን ለጎን መጽሐፍት ማንበብን ልምድ በማድረግ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችል አቅም ማጎልበት እንደሚገባው ገልጸዋል። በተለይም በአገራችን ያሉ ደራሲያን መጽሐፍት ስነ-ጽሑፋዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ፣ ታሪክን ሳያዛቡ እንዲሁም በሥነ-ምግባር ረገድ የተሻለ አቀራረብ እንዲይዙ በማድረግ ንቁ ማኀበረሰብ በመፍጠር ለአገራዊ ለውጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

    በመጽሐፍት አውደ ርዕይና ሲምፖዚየሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከአዲስ አበባ የመጡ የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎችና የመጽሐፍት ሽያጭ መደብሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የንባብ ባህል


    Semonegna
    Keymaster

    በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተካሄደው የሰላም ንቅናቄ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ እና በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል።

    ወልቂጤ (ሰሞነኛ)– “ጥበብ ለሰላም” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን ከሚገኙ 17 ወረዳዎችና ከ4 ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአገራችን ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ አመራሮች፣ የሲቪል ሰርቪስ (civil service) ሠራተኞች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ትልቅ ስብሰባ/ውይይት በድምቀት ተካሂዷል።

    በዚህም ዞን አቀፍ የሰላም ንቅናቄ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች (በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ደራሲ እንዳላጌታ ከበደ፣ ደራሲ ህይወት ተፈራ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራልና የሙዚቃ ሀያሲው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት እና ደራሲ ተስፋዬ ጎይቴ ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል። የሁሉም የመቋጫ ሀሳብ የአገራችን ህዝቦች አጥር ሳይገድባቸው በብሔር፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በሀይማኖትና በመሳሰሉ ከፋፋይ ጉዳዮችን ትተው በአንድነትና በሰብዓዊነት ስሜት ተዋደውና ተቻችለው እንደቀድሞው አብረው ሊኖሩ እንደሚገባ ነው።

    በዚህ ታላቅ የሰላም ንቅናቄ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማልና የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ ሰላም ለሁሉም ጉዳዮች መሠረት መሆኑ እና ሰላም በሌለበት ምንም ሊኖር እንዳማይችል ገልፀው የዞኑ ህዝብ በሙሉ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    “ጥበብ ለሰላም” በሚል በተካሄድው በዚህ መርሀግብር ታዋቂ የአገራችን ደራሲያን፣ የጉራጌ ዞን የባህል ኪነት ቡድን፣ ከወልቂጤና ከቡታጅራ ከተማ አስተዳደሮች የኪነ ጥበብ ክበባት የተውጣጡ አማተር ኪያንያን ድንቅ የሙዚቃ፣ ድራማና የሥነ ግጥም ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። እንዲሁም በሱዑዱ አብደላ የተሳሉ ድንቅ የሥነ ስዕል ሥራዎቹን አቅርቧል። የ11ኛ ክፍል ተማሪ ይዘዲን የፈጠራ ሥራዎች በመድረኩ ከቀረቡ ሥራዎች ይገኝበታል።

    በመጨረሻም ለፕሮግራሙ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ያዘጋጃቸው ባህላዊ ስጦታዎች፣ የማበረታቻ ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።

    ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ጥበብ ለሰላም መድረክ በጉራጌ ዞን


Viewing 8 results - 1 through 8 (of 8 total)