-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሳይንስ ሳምንትን ከጥቅምት 25 ቀን እስከ ህዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት ያከብራል።
የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ዓላማዎችና መሪቃል ይከበራል። የኢትዮጵያው የሳይንስ ሳምንት ሲከበር የተባበሩት መግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) በየዓመቱ ኖቬምበር 10 ቀን የሚያከብረውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ባማከለ ሁኔታ ይፈፀማል።
ይህ ሀገራዊ የሳይንስ ሳምንት ሲከበር ዋና ዓላማው ሳይንሳዊ አስተሳሰብንና አሠራርን፣ የሳይንስ ባህል ግንባታ ሥራዎቻችንን ለማሳወቅና እንዲሁም በተለያዩ ሳይንሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በቀጣይም የወጣቱን ትውልድ የሳይንስ ፍላጎት ለማሳደግ እንዲያግዝ ሳይንስ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሳይንስን፣ ሳይንሳዊ እንቅስቃሴዎችን እና የሳይንሳዊ ጥናቶችን ለሕዝብ ለማስተዋወቅም ያለመ ነው።
በሳይንስ ሳምንት ከሚከናወኑ ዝግጅቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
- ከጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል በSTEM (Science, Technology, Engineering, and Mathematics) ዘርፎች ውድድር ይካሄዳል። ተማሪዎቹ በአራቱ የትምህርት ዘርፎች ለውድድር በሚያቀርቡት ፈጠራ ላይ ተመሥርቶ በሚሰጠው ዳኝነት አሸናፊዎች እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ተሸላሚ ይሆናሉ።
- ሐሙስ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶችና ሙያ ማኅበራት ጋር በሒልተን ሆቴል ምክክር ያደርጋል:: በምክክር መድረኩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሳይንስ ሥራዎችና የትኩረት አቅጣጫ፣ የሙያ ማኅበራት ሚና ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና፤ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት ዕይታ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶች የሳይንስ ሥራዎች ትኩረትና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር “ለኢትዮጵያ ግብርና አገር በቀል እይታ” በሚል የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ ይካሄዳል።
- አርብ ጥቅምት 28 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ሳይንስ ለልማትና ብልፅግና በሚል ርዕስ የተለያዩ ባድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሀገራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር ወርክሾፕ ይካሄዳል።
- እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የአረንጓዴ ቀን (Green Day) ይከበራል። በዕለቱ ባለፈው ክረምት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተተከሉ ችግኞችን ቦታቸው ድረስ በመገኘት የመንከባከብ ሥራዎች ይሠራሉ። እፅዋቱ ባሉበት ደረጃ በሚሠሩ የእንክብካቤ ሥራዎች ላይም በተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ሳይንሳዊ ገለፃ ይቀርባል።
- ሰኞ ሕዳር 01 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የባዮዳይቨርሲቲ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute) ጋር በመተባበር “ሰውና ሥነ ምህዳር (Man and Biosphere)” በሚል ርዕስ ትምህርታዊ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል። በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጥሮ ሳይንስና ግብርና ኮሌጆች በርዕሱ ላይ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።
- ማክሰኞ ሕዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biotechnology Institute) ጋር በመተበባር “ባዮቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ በዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርታዊ ገለፃ ይቀርባል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ ሳይንሳዊ ገለፃዎችና ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ስለሆነም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. በሚጀምረው የሳይንስ ሳምንትን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተውት ለህብረተሰቡ የሚመጥኑና ሳይንሳዊ ግንዛቤዎችን የሚፈጥሩ ሥራዎችን በመሥራት የሳይንስ ሳምንት አከባበር አካል እንዲሆኑ እንጋብዛለን።
በተጨማሪም ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የሳይንስ ሳምንት፣ በየዘርፋቸው ሳይንስ ለአገር ልማትና ብልፅግና ያለውን ፋይዳ የሚያሳዩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ በበዓሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንጋብዛለን።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጀ። የአድዋ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት ሰጠ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩት ጥናትና ምርምሮች ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በአገሪቷ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡት የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሚጠበቀው በታች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም እንደ ዋነኛ ምክንያት አስቀምጠውታል። እንዲያውም ለዘርፉ የሚመደበው አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን በመጠቆም።
በተጓዳኝም የምርምር መሠረተ-ልማቶች አለመኖር፣ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ መሆንና መምህራን ለምርምር ትኩረት አለመስጠታቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩት ጥናታ ምርምሮች ቁጥር አነስተኛ መሆነ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ባሏቸው አቅም በአስገዳጅ መልኩ የጥናትና ምርምር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በትምህርት ተቋማቱ ዝቅተኛ ቢሆኑም በሥመ-ጥር ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ምርምሮቻቸውን የሚያወጡ ጉምቱ ምሁራን መኖራቸውንም ዶ/ር ሳሙኤል አልሸሸጉም።
ለጥናትና ምርምር የሚበጀተውን በጀት በተመለከተም ከአገሪቷ እድገትና ከመምህራኑ አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ እያደገ የሚመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ጆርናሎች ጥራታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጥናት እየተደረገበት መሆኑንም አስረድተዋል። መመሪያውንም በቅርቡ ወደ ሕግ በመቀየር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ጆርናሎች የሚመሩበት ወጥ ሥርዓት በመዘርጋት የእውቅና ደረጃም እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ መውሰድ (ረቂቅ አዋጁን ማውጣትም ሆነ ለጆርናሎች መመሪያ መዘጋጀት) የሚካሄዱትን ምርምሮች ጥራታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፥ በቀጣይም ጥናትና ምርምር ላይ የግሉ ዘርፍ የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ቁጥር 33 ሺህ ደርሷል፤ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺህ 500 የሚሆኑት ናቸው ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው – የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው።
ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ፥ ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት መስጠቱን በትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የአድዋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የዩኒቨርስቲውን ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘብራአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ እንዲውል መሬቱ ተሰጥቷል። በዚህም 131 የአካባቢው አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ላይ ተነስተዋል። ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮችም ካሳ ክፍያ ለመፈፀም 15 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ በበኩላቸው ግንባታውን ለማስጀመር ከፌዴራልና ከትግራይ ክልል መንግሥታት 450 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። ከዚህም የትግራይ ክልል መንግሥት 250 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል መግባቱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ አስተዳደርም በቅርቡ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – STEMpower የተሰኘ መቀመጫውን USA (ሳሌም፥ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ) ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲዎች እየረዳ የሚገኝ ሲሆን በአገራችን 13 ማዕከላትን ከፍቶ በትብብር እየሠራና እየረዳ ይገኛል።
ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 10 ማዕከላትን (ሰባት ማዕከላትን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶስቱን በተለያዩ ከተሞች እ.አ.አ. በ2019) ለመክፈት ከኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት የካቲት 14 ቀን 2011ዓ.ም. ተፈራርመዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) STEMpower ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን ለማበልጸግ እያደረገ ያለውን ትብብር በማመስገን፥ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕድሉን በመጠቀም በአግባቡ ማዕከላቱን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
◌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ዲጂታል ሰሌዳዎችን መጠቀም ጀመረ።
የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ለሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ) ማዕከሉን በመጠቀም በአካባቢዎቻቸው ያሉትን የማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የSTEMpower አስተባባሪ ዳይሬክተርና ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ቅድስት ገብረአምላክ፥ “STEMpower ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከድርጅቱ አመሠራረት ጀምሮ ዓላማውን፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና የወደፊት ዕቅድ አጭር ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል። ለወደፊትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በስፋት እንደሚሠሩ ፣ በ2040 የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ ገልጸዋል።
አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ድርጅቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማዕከሎቹ በከፍተኛ ትምህርት እና በሳይንስ ትምህርቶች አከባቢ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ ረገድ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና እና ኪነ-ሕንፃ ዘርፍ ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
- ሁለተኛው SolveIT ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር (የኢዲስ አበባ ከተማን) በይፋ ተጀመረ ― የአሜሪካ ኢምባሲ
- በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የቀጠና/ወረዳ ጤና መረጃ ስርዓት አካዳሚ (DHIS2) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ
- የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በአንድነት ለመሥራት ቃል ገቡ
- የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት እና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አውስቷል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር ያለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል 40ኛ የጥበብ ውሎ መድረኩን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አካሒዷል።
በዝግጅቱ ላይ የዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ተደርጓል። ሥራዎቹን እና ሕይወቱን አስመልክቶ የሙዚቃ ባለሙያ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ የተሾመው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የውይይት መነሻ ጥናት አቅርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተካሂዶ ነበር።
“ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ <ባለዋሽንቱ እረኛ>(The Shepherd Flutist) በተሰኘ ታላቂ ሥራ የኢትዮጵያን መልክ በረቂቅ ሙዚቃ ያሳዩ ናቸው” በማለት አቶ ሠርፀ የገለጿቸው የሙዚቃውን ረቂቅነት በመጥቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አውስቷል።
በሙዚቃ ላይ ከሠሯቸው ከበርካታ የምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ “Roots of Black Music” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙ የዓለማችን የሙዚቃ አጥኚዎች የተዘነጉ (የተዘለሉ) የአፍሪካ/የምሥራቁ ዓለምን የሙዚቃ ስልትና ፍልስፍናን አጉልተው ለተቀረው ዓለም ያሳዩበት እንደሆነም አቅራቢው አብራርተዋል።
በውይይቱም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ችግር ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፥ “ዋናው ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተቋም ፈርሷል፤ እሱን መልሶ መገንባት የቤት ሥራችን ነው” ብለዋል አቶ ሠርፀ። አክለውም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ትምህርት ሥርዓት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ሥርዓተ-ትምህርት ነፃ መውጣት ያለመቻሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ጠቅሰዋል።
ውይቱን የመሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እንዳለጌታ ከበደ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ማደግ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የጥበብ ሰዎችን ፈለግ እና ሥራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በሁሉም አካላት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ፋንታዬ ነከሬ ያባሉ ነበር። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል። የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በመሆን ሙዚቃን ከማስተማሩ ባሻገር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።
በድጋሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተመልሰው፣ ኮነቲከት ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዌስልያን ዩኒቨርሲቲ (Wesleyan University) በ1961 ዓ.ም የማስትሬት፣ እንዲሁም በ1963 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ምዕራባዊ ባልሆኑ ሙዚቃዎች ምርምር (ethnomusicology) አግኝተዋል።
ከሙዚቃው መምህርነትና ተመራማሪነት ባሻገር ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ደራሲም ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ኮንፌሽን (Confession)፣ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሩትስ ኦፍ ብላክ ሙዚክ (Roots of Black Music) የሚሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ በሙዚቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሁፎችን፥ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ-አሜሪካውያን ባህልና አኗኗር ላይ ለሚያተኩረው “The Chronicler” ለተሰኘው መጽሔት ጽፈዋል።
በአሜሪካ ፕሮፌሰር አሸናፊ ኑሯቸው ፍሎሪዳ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Florida State University) የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት የሠራ ሲሆን፣ ተቀማጭነቱን እዚያው አሜሪካ ያደረገውናታዋቂውን የኢትዮጵያ ምርምር ካውንስልን (Ethiopian Research Council) በዳይረክተርነት መርቷል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወ/ሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ሁለተኛ ባለቤታቸው (አሜሪካዊ) አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የ60ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባትም የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።
PHOTO: Ethiopian Academy of Sciencesአዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 34ኛውን እና የዓመቱ የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት ምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አካሄደ።
ገለፃውን ያቀረቡት ዶ/ር ዓለማየሁ ሥዩም (በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም (IFPRI) ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ) ሲሆኑ፣ አቅራቢው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና በምግብ እራስን መቻል መካከል ያለው ብያኔ የተዛነፈ በመሆኑ በምሁራን እና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ወጥ የሆነ አረዳድ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል። ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአገር፣ በክፍለ-ዓለምና በዓለም ደረጃ፤ ሁሉም ሰዎች፣ ዘወትር፣ በመጠኑ በቂ የሆነ፣ በጤና ላይ አደጋን የማያስከትል እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ፍላጎትም ሆነ የአይነት ምርጫ ቁሳዊናኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ሲኖራቸው እንደሆነና ምንም ዓይነት ወቅታዊ መዋዠቅን፣ ያልተጠበቁ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ ክስተቶችን (አደጋዎችን) መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ ሲፈጠር እንደሆነ አቅራቢው ይገልፃሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ መካከለኛ መጠን ያላቸው ከተሞች በዓመት በአማካይ ከ5-6 በመቶ ዕድገት እያሳዩ መሆኑ እና መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ-ተኮር ኢኮኖሚ ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል። ነገር ግን ዛሬም የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ የህፃናት መቀንጨር በአማካይ 38 በመቶ መድረሱ፣ የምግብ እህል እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ መጨመሩ እና ከፍተኛ የምግብ እህል/ሸቀጥ ከውጪ እንዲገባ መደረጉ “የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም እልባት ያላገኘ አገራዊ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ።
ለእንደዚህ ዓይነት የምግብ ዋስትና ስጋት ያጋልጣሉ ያሏቸውንም ምክንያቶች ዶ/ር ዓለማየሁ ዘርዝረዋል። “በገጠር የተወሳሰበ የመሬት ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሁኔታ (የይዞታ ባለቤትነትና አጠቃቀም ሥርዓት)፣ የእርሻ መሬት ይዞታ ማነስና መበጣጠስ፣ የመሬት ምርታማነት መቀነስ/የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የሥራ ዕድል መጥበብ እና ወጥነት የጎደለው የፖሊሲ አፈፃፀም” ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ። ችግሩም ህፃናትን ለበሽታና ለሞት እንዲሁም ለአካልና አእምሮ ህመም ከመዳረጉ እና የመማርና የማምረት አቅምን ከማኮሰስ አልፎ ድህነት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል።
በሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረኩ ከችግሩም ለመላቀቅና የተሟላ ማህበራዊ ዋስትና ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል። በውይይቱም ከፍተኛ የግብርና ማስፋፊያ ተግባራት በማከናወን አርሶ አደሮች የተሻለ መረጃ እንዲያገኙና የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን እንዲያላምዱ ማትጋት፤ ዘመናዊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ማድረግ፤ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማካሄድ አማካይ በህይወት የመኖሪያ እድሜን ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ተጋላጭነትን እያጠኑ ስልት የሚቀይሱ ጠቃሚ ተቋማትን መፍጠር (የፖሊሲ ተቋማት፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች፣ የገበያ፣ የአምራቾች ማህበራት፣ የማህበራዊ ዋስትና ስልት፣ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዘዴዎች) ቅድሚያ የሚፈልጉ አገራዊ ተግባራት መሆናቸው ተነስቷል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም ከ20-25 ዓመት የሚደርስ የግብርናው ዘርፍን ሊያዘምን የሚችል አሠራር በተለይ ደረቅ-አብቃይ አካባቢዎችን፣ ለድርቅ-ተጋላጭቦታዎችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያሻሽል የተቀናጀ መርሐ-ግብር መንደፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል። እንደ ህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት መለዋወጥ ያሉ አባባሽ ሁኔታዎችንም መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ዝግጁነት መገንባት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማስጠበቅ ይረዳልም ብለዋል።
በጥቅሉ የገለፃው አቅራቢና ተሳታፊዎች፣ ተቋማት መገንባትና በስፋትና በተፈለገው የህብረተሰብ ፍላጎት ልክ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር መፈጠር አለበት በማለት የዕለቱን ውይይት አጠናቀዋል።
ውይይቱን ፕሮፌሰር በላይ ካሳ (የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ከፍተኛ አመራር) የመሩት ሲሆን፣ ከ110 በላይ የሚሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የአካዳሚው አባላትና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በዶክትሬት ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ከፍተው ተማሪዎችን ይቀበላሉ።
ደብረ ብርሃን/ባህር ዳር – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ (2011 ዓ.ም) የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor degree) አራት በሁለተኛ ዲግሪ (master degree) አስራ ሁለት መርሃ ግብሮችን እንደሚከፍት አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት አሸናፊ ለኮሙኒኬሽን ጉዳዮች እንደገለጹት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አስራ ስድስት አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ይከፍታል።
ዶክተር ጌትነት አሸናፊ እንዳሉት የትምህርት ክፍሎቹ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀ ግብሮች የመጀመሪያ ድግሪ ከ49 ወደ 53 እንዲሁም 34 የነበረውን የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ወደ 46 ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
ከተመሠረተ 11 ዓመት የሞላው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ መስኮች እያስተማረ ይገኛል።
በተመሳሳይ ዜና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ፣ በበሁለተኛ እና በዶክትሬት (doctorate) ዲግሪ በሚከፍታቸው 18 አዳዲስ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልም አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ተቋሙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት አገራዊ እድገቱን በእውቀት ለማገዝ እየሠራ ነው።
በተያዘው የትምህርት ዘመንም ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 12 የሁለተኛ ዲግሪና አራት የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ 250 ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ዶክተር እሰይ እንዳሉት ህግ፣ መሬት አስተዳደር፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ትምህርት፣ ፖለቲካል ሳይንስና የመሳሰሉት የትምህርት መስኮች አዲስ የሚከፈቱባቸው ናቸው። “የተሳካ የመማር ማስተማር ተግባር ለማካሄድም ቀደም ብሎ የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉንና የመምህራን ቅጥርም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል” ብለዋል።
የኒቨርሲቲው በአፋን ኦሮሞ ትምህርትም በዚህ ዓመት አጋማሽ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ ሥራ ማካሄዱንና የመምህራን ቅጥር እየፈጸመ መሆኑን ዶክተር እሰይ አስታውቀዋል።
ተቋሙ በህክምናው ዘርፍ የተሻለ እውቅት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ “የተሻለ የማስተማርም ሆነ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አዲስ የማስተማሪያ ሆስፒታል ገንብቶ የ170 መምህራንን በመቅጠር ላይ ነው” ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በመደባኛው የትምህርት መርሀግብር ብቻ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።
በተለይም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዩኒቨርሲቲ እየወረደ የመጣውን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተሻለ አቅም ያላቸውን መምህራን በመመደብ፣ ቤተ ሙከራዎችንና ቤተ መጻህፍትን በማደረጀት ጥራትን ለማምጣት እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል። ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊትም አጠቃላይ የጥራት መለኪያ ፈተና እንዲወስዱም እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛውና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓመታዊ የተማሪ የቅበላ አቅሙ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ደርሷል።
ምንጭ፦ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ (ፎቶ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ)
Search Results for 'የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ'
Viewing 15 results - 1 through 15 (of 15 total)
Viewing 15 results - 1 through 15 (of 15 total)