Search Results for 'የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 15 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    “የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተከናወነ

    በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል አዘጋጅነት “የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተካሂዷል።

    በውይይቱ ላይ አጠቃላይ ሙያዊ ትንታኔውን የሙዚቃ ባለሙያና የሙዚቃ ሃያሲ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ያቀረቡ ሲሆን፥ የሙዚቃው አቀናባሪና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ እና ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት (የማ) የሙዚቃ ስብስቡን ሥራ ታሪክና ውጣ ውረድ አብራርተዋል።

    አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ሙዚቃው የዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) ላይ የሚመደብ ምርምራዊ ሥራ መሆኑን አመላካች፣ አስረጅ እና ታሪካዊ ዳራዎችን በመጥቀስ ያብራሩ ከመሆኑም ባሻገር፥ እስካሁን በዓለም ሙዚቃ ዘውግ ከተሠሩ የኢትዮጵያዊያን ሙዚቃዎች ውስጥ የቀለለ ዕድል በሌለበት በጥረትና ትጋት የተፈጠረ የጥበብ ሥራ መሆኑን አብራርተዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ በየዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) አስቴር አወቀ፣ እጅጋየሁ ሽባባው፣ ምንይሹ ክፍሌ፣ ዣን ስዩም ሔኖክን የመሰሉ ከያንያን በውጭ ሀገር ከመኖራቸውና ለወርልድ ሙዚቃ ካላቸው ተጋላጭነት አንጻር በመመዘንም “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ በተለየ ሁኔታ በምርጫና በጥረት የተሠራ ሥራ መሆኑን አቶ ሰርጸ አብራርተዋል።

    የሙዚቃ ስብስቡ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሙዚቀኞች ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር የተጣመሩበት እና በአቀናባሪው ምርጫና ትጋት ወደ እውንነት የተቀየረ መሆኑ ተገልጿል።

    የሙዚቃው አቀናባሪ እና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ ሥራው በቦኬ ማኅበረሰብ ሙዚቃ በመሳብ እና ምርምሮችን በማስፋት ሀገር በቀል የሙዚቃ ቅንጣቶችን ከዓለም አቀፍ የሙዚቃ እሳቤዎች ጋር በመቀየጥ የባሕል ውህደትና ቅንብር ለመፍጠር የተሠራ ሥራ መሆኑን የሙዚቃ ስብስቡን ታሪክ አስረድተዋል።

    ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት ከእንግሊዝኛ የሙዚቃ ድምጻዊነት በሽግግር ወደእንዲህ አይነት የባሕል ቅይጥ እና ዓለማቀፋዊ መልክ ወዳለው ሥራ የተሻገረችበትን መልክ ሆኔታዎች አንስታ ገልጻች። “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ ከሰባት ሀገራት፣ ከሃያ በላይ ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሙዚቃ ስብስብ ሲሆን፥ በሙዚቃ ድርሰት፣ በሁለት የዘፈን ግጥሞች፣ በቅንብር እና በፕሮዲዩሰርነት ኢዩኤል መንግሥቱ፣ ጎላ ጎሕ (የብዕር ስም) ስምንት የሙዚቃ ግጥሞችን በማበርከት፣ አንጋፋው ይልማ ገብረአብ አንድ የሙዚቃ ግጥም ድርሰት በመስጠት የተሳተፉበት ስብስብ ነው።

    በውይይቱ ላይ በርካታ ታዳምያን ተገኝተው ስለሙዚቃ ሥራው የተሰማቸውን ስሜት እና በቀረቡት መነሻ ሃሳቦች ላይ ጥያቄና ማብራሪያ በማቅረብ ጠንካራ ተሳትፎ አድርገዋል።

    በውይይቱም ላይ ከሙዚቃው ድርሰትና ቅንብር በተጨማሪ የተለየ ሆኖ በሀሳብ ላይ ትኩረት አድርጎ ስለመጣው የሙዚቃው ግጥሞች በርካቶች አድናቆታቸውን ሰጥተዋል። በሌላም በኩል ምርምርና የሥነ-ጥበብን ከፍታ ይዘው ለሚመጡ አድካሚና ውድ ሥራዎች አድማጩ ሊሰጠው ስለሚገባው ትኩረት በማንሳት ጠንካራ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

    በዝግጅቱም ላይ ከራያ ማኅበረሰብ የተላኩ ወኪሎች በቦታው ተገኝተው ለድምጻዊቷ፣ ሙዚቃው አቀናባሪና ገጣሚ እንዲሁም በሥራው ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለየማርያም ቸርነትም የራያ ባሕል ልብስ ስጦታ አበርክተዋል።

    የካቲት 2 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በ “ነገረ መጻሕፍት” ዝግጅት የገብረሕይወት ባይከዳኝ “ሕዝብና የመንግሥት አስተዳደር” መጽሐፍ የታተመበትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ጋር በሚደረገው ውይይት ላይ እንድትገኙ ከወዲሁ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋብዟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Semonegna
    Keymaster

    ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ሕንፃ ምህንድስና፣ በሕክምና እና በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

    ዲላ (ዲላ ዩኒቨርሲቲ) – ዲላ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂና ምህንድስና ኮሌጅ ስር በሥነ-ሕንፃ ምህንድስና (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል፣ በሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሕክምና (ሜዲሲን) ትምህርት ክፍል እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች መጋቢት 02 ቀን፥ 2015 ዓ.ም አስመርቋል።

    በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ፤ ለተመራቂ ተማሪዎች፣ ለተመራቂ ወላጆች እንዲሁም ለተማሪዎቹ ለምረቃ መብቃት በተለያየ መልኩ ለተጉ ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ዶ/ር ማቴዎስ አክለውም፥ “የዘንድሮ ተመራቂዎች ከትምህርት እና ፈተና ባለፈ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች ተቋቁማችሁ ለዚህ የበቃችሁ በመሆናችሁ በራሳችሁ ልትኮሩ ይገባል” ብለዋል።

    ተመራቂዎች ምንም እንኳ ከተቋሙ ተመርቀው ቢወጡም በዩኒቨርሲቲው አሉምናይ (alumni) በኩል ቤተሰባዊ ግንኙነቱ እንደሚቀጥል የገለፁት ዶ/ር ማቴዎስ፥ በቀጣይ ተመራቂዎች በሚሰማሩበት መስክ ሁሉ አምባሳደር ሁነው የዩኒቨርሲቲውን መልካም ስም እንዲያስቀጥሉ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ከተመራቂዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ችግር በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በዘገበው ዜና ገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራርና አሉምናይ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ይልማ በበኩላቸው፥ በበዕለቱ በድኅረ-ምረቃ መርሃ-ግብር 68 ወንድ እና ዘጠኝ (9) ሴት፤ በድምሩ 77፣ በመደበኛው መርሃ-ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ 64 ወንድ እና 24 ሴት በድምሩ 88፣ በተከታታይ የትምህርት መርሃ-ግብር 117 ወንድ እና 30 ሴት፤ በድምሩ 147፣ በአጠቃላይ 249 ወንድ እና 63 ሴት፤ በድምሩ 312 ተመራቂዎች ለምርቃት መብቃታቸውን አብስረዋል።

    በዕለቱ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነው ዶ/ር ብርሃን አዳነ አጠቃላይ ውጤት 3.86 ነጥብ በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

    የማዕረግ ተመራቂው ዶ/ር ብርሃን አዳነ፥ “ከምንም በላይ ፈጣሪዬ ለዚህ ክብር እንድበቃ ስላደረገኝ ክብር ይግባው” ሲል በስኬቱ መደሰቱንና በትምህርቱ ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክሮ በመስራቱ በከፍተኛ ውጤት መመረቁን ጠቅሷል።

    ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የድንቅ ኪነ-ሕንፃ ጥበብ ባለቤት መሆኗን የምትናገረው የሥነ-ሕንፃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ተማሪ ሴና ኤቢሳ፥ ይሁንና ዘመናዊ ሕንፃዎች የኢትዮጵያን ባህልና ቀለም በማንጸባረቅ ረገድ ውስንነት እንዳለባቸው ተናግራለች። በቀጣይ በሥራ ሕይወቷ በግል ሆነ በቡድን ሀገር በቀል የሥነ-ሕንፃ ጥበብን ከዘመናዊው ጋር በማዋሃድ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ የድርሻዬን እወጣለሁ ብላለች ።

    የምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ የሕክምና ተመራቂዎች ሙያዊ ቃለ-ምሃላ በመፈፀም የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ የክብር እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አባላት እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልም ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረብ ዝግጅቱን አድምቆታል።

    ምንጭ፦ የዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ድረ ገጽ

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የልጆች የሳይንስ ማዕከል አስመረቀ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የልጆች የሳይንስ ማዕከል አስመርቋል። አካዳሚዉ ከጀርመን የባህል ተቋም በኢትዮጵያ (Goethe-Institut Ethiopia) እና ጀርመን ሀገር ከሚገኘው ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከል (Phänomenta e.V. Science Center) ጋር በመተባበር ማቋቋሙም ተገልጿል።

    በማዕከሉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

    የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ይህንኑ በማጠናከር የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑትን ሕፃናት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉና ለሀገራቸዉ ሁሉ አቀፍ ልማትና ብልጽግና ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የልጆች የሳይንስ ማዕከል ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ማቋቋሙ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

    የሳይንስ አካዳሚዉ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም ባደርጉት ንግግር፥ አካዳሚው የሳይንስ ዕውቀትንና ባሕልን ለማሳደግ እንዲሁም ሕፃናት በተመቻቹ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች እየተዝናኑ ስለሳይንስና ቴክኖሎጂ ፅንሰ-ሐሳብና አሠራር ዕውቀት እንዲያገኙና ለዘርፉ ያላቸው ዝንባሌ እንዲያድግ ታቅዶ መቋቋሙን አብራርተዋል።

    አካዳሚዉ በዋናነት የሳይንስ ዕውቀትንና ባሕልን የማሳደግና የማስፋፋት፤ እንዲሁም ለመንግሥትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ምክር የመስጠት ዓበይት ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸዉን ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።

    የማዕከሉ ግንባታ ከተጀመረ በ3 ዓመት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ለግንባታው የጀርመን ባህል ማዕከል 1.5 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መንግሥት የሳይንስ ዘርፍን ለማጠናከር ከሰጠው 40 ሚሊዮን ብር 7.3 ሚሊዮን እና የጀርመኑ ፌኖሜንታ የሳይንስ ማዕከል 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።

    ፕሮፌሰር ፅጌ አያይዘዉ አገራችን ወቅቱ በሚፈልገው የእድገት አቅጣጫና ፍጥነት እንድትጓዝ ለማድረግ የሳይንስ እውቀት ማበልፀጊያ ተቋማት ግንባታ የሳይንስ ማህበረሰብ ምስረታና የአገር በቀል እውቀት አጣምሮ መስራት እንዳለበት ገልጸዉ ለዚህ አላማ ስኬት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የጀርመን የባህል ተቋም እና ጀርመን ሀገር የሚገኘው ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከል ላደረጉት ቴክኒካዊና ፋይናንስ ድጋፍ በራሳቸውና በአካዳሚው ሥም ምስጋና አቅርበዋል።

    የጀርመን የባህል ተቋም እና ጀርመን ሀገር የሚገኘው ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከልን ወክለዉ በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉ ተወካዮቻቸዉ በተለያየ የእድሜ ደረጃና የትምህርት እርከን ላይ የሚገኙ የማኀረሰቡን አካላት ግንዛቤ ለማሳደግና የሳይንስ እውቀትን ለማስረፅ ማዕከሉ ጉልህ ሚና እንደሚኖረዉ ገልጸዋል።

    የሳይንስ አካዳሚው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ባስተላለፉት መልእክት የበርካታ አገር በቀል እውቀቶች፣ የጥንታዊ ታሪክ ቅርሶችና የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤቶች በመሆናችን እነዚህን በሳይንሳዊ መንገዶች በማዘመን ለህብረተሰባችን ህይወት መሻሻል የጀመርናቸዉን ዉጥን ተግባራት ከግብ ለማድረስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ብርቱ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    የልጆች የሳይንስ ማዕከል

    Semonegna
    Keymaster

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 70 አዳዲስ የድኅረ-ምረቃ ትምህርት ክፍሎችን ሊከፍት ነው

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በሁለተኛ እና ሦስተኛ ድግሪ 70 አዳዲስ ትምህርት ዓይነቶችን ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ይህም ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት ዓይነቶች 101 እንደሚያደርሰው ተጠቁሟል።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታምሩ አኖሌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንዳሉት በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው አዲስ ከሚከፈቱት 19 የሦስተኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ውስጥ የገዳ እና የአስተዳደር ጥናት አንዱ ነው።

    ቀሪዎቹ የተለያዩ የሁለተኛ ዲግሪ መርሀግብሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በሦስተኛ ዲግሪ ይሰጥ የነበረውን አንድ መርሀግብር ወደ 20 ከፍ ሲያደርገው የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከ30 ወደ 81 የትምህርት ክፍሎች እንደሚያሳድገው ዶ/ር ታምሩ አመላክተዋል። የትምህርት ክፍሎችን ፍላጎት ከመለየት አንስቶ የየሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ቀረጻና ትችት እንዲሁም የሰው ኃይልና ግብዓት የማሟላት ሥራዎች በጥንቃቄ መከናወናቸውንም በማከል አስረድተዋል።

    የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም ዶ/ር ታምሩ ገልጸዋል። የመምህራን እጥረት እንዳይከሰት ረዳት ፕሮፈሰርና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው 73 የውጭና 43 የሀገር ውስጥ መምህራን ቅጥር መፈጸሙንም አስታውቀዋል።

    ለመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ የሆኑ በተለይ ለኢንጅነሪግና ለተፈጥሮ ሳይንስ ቤተ-ሙከራና ቤተ-መጽሐፍት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ መደራጀቱን ገልጸዋል። ይህም ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለማድረስ እገዛ ከማድረግ ባለፈ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው ለተለያዩ የተግባር ትምህርቶች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎችን በመውሰድ የሚያወጣውን ውጭ እንደሚያስቀር አስረድተዋል።

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) አቋቁሞ ከኢትዮጵያ ምርጥ አምስት እንዲሁም ከአፍሪካ ምርጥ 10 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አንዱ ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ ናቸው።

    በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የገዳ ሥርዓት እንዲካተት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደሚ ሚናውን ከመወጣት ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ከኮመን ኮርስ (common course) እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የገዳ ሥርዓት ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

    “ዩኒቨርሲቲው በስሩ ባሉት ስምንት ኮሌጆችና በአንድ ኢንስትቲዩት ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል” ብለዋል ዶ/ር ጫላ።

    ምንም እንኳን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ለጊዜው ቢቆምም በቀጣይ ዓመታት የተማሪዎችን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ከፕሬዝዳንቱ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዲላ/አርባ ምንጭ (ኢዜአ/አ.ም.ዩ) – ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,043 ተማሪዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 283 በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በምስክር ወረቀት የተመረቁ መሆኑን አስረድተዋል።

    ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲከታተሉ እንደቆዩ አመልክተው፥ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ዶ/ር ጫላ ገልጸዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኡዴሳ ክዮላ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በቀጣይ በሚሰማሩበተ የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና ታታሪነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ከተመራቂዎቹ መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን የተከታተለው ቅዱስ ይገረሙ በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሰለጠነበት በ“ሶፍትዌር ዲዛይን” ዘርፍ በመሰማራት እራሱንና ሀገሩን ለመጥቀም እንደሚሠራ ተናግሯል።

    በሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ዋቆ ጥላሁን በበኩሉ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ገልጿል።

    የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

    ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመርቋል።

    ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በስድስት የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው። በመሆኑም የዕለቱ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል።

    በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አ.ም.ዩ)

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 7520 ተማሪዎች በበይነ-መረብ አስመረቀ

    (ባሕር ዳር) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምርቃ መርሀ-ግብር በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛውና በተከታታይ መርሀ-ግብር 2254 ተማሪዎች፣ በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ-ግብር 40 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲ መርሀ-ግብር 41 ተማሪዎች፣ በምስክር ወረቀት መርሀ-ግብር 642 ተማሪዎች በድምሩ 7520 ተማሪዎችን በበይነ-መረብ በመታገዝ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። ከተመራቂ ተማሪዎቸ መካከል 2345 ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል አምስቱ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ፣ እንዲሁም የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

    በሥነ-ሥርዓቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክዕት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ዓለምን ባስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ ተግዳሮት ሳይደናቀፉ የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ለተመረቁ ተማሪዎች አድናቆታቸውን ገልፀው ወደ ቀደምት ትልቅነታችን እና ጥበብ ለመመለስ እና አሁን የጀመርናቸውን የአባይ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት የጋራ መድኃኒት ስለሚያስፈልገን ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም በጋራ መሥራት እንደሚገባን አሳስበዋል።

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን (ኮቪድ-19) ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዩኒቨርስቲዎች ሕይወትን ለመታደግ የእውቀት እና የሕዝብ ተቋምነታቸውን ማስመስከራቸውን ጠቅሰው ለዚህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በማምረት እና በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን በማበርከት ሕበረተሰቡን ከወረርሽኙ እየታደገ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ገልፀዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከትምህርት እንዳይለዩ በዩኒቨርሲቲው የICT ባለሙያዎች የበለፀገ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት (learning management system) ለአማራ ክልለዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ማበርከቱን አውስተዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንዳሉት መማር ትርጉም የሚኖረው የሕበረሰተቡን ኑሮ ማሻሻልና ለችግሮቹ መፍቻ የሚሆን አዳዲስ አሠራሮችንና ሀሳቦችን መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቁመው የሀገራችን ችግር የሚፈታው የችግሮችን ስፋትና ጥልቀት በሚረዱ ምሁራን በመሆኑ የምንግዜም ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    አክለውም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የልሕቀት ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ትጋት አድንቀው፤ በእምቦጭ ዙሪያ ብዙ ሥራ መሥራት የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። ከአባይ ፏፏቴ ጀምሮ እስከ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ድረስ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግ የሚቻልበትን ምርምር በመሥራት መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማሳየትም ከዩኒቨርሲቲው እንደሚጠበቅ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል።

    የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን ጥቂት ተማሪዎች አዳራሽ ውስጥ በአካል በመገኘት፥ አብዛኛዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው በአማራ ቴሌቪዥን ከጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቀጥታ ስርጭት፣ በፌስቡክ (Facebook) እና ዩቲዩብ (YouTube) የተላለፈውን ታድመዋል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

     

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው አሰልጥኖ ነሐሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምረቃ ካበቃቸው 2 ሺህ ተማሪዎች  በዶክትሬት ዲግሪ እና በሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

    በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጥቂት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በቨርቹዋል (virtual) አማካይነት ምርቃታቸውን ማካሄዳቸው ታውቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ለማ ጉዲሳ፥ ተማሪዎች በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውን በተማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። “የሲቪል ሰርቪሱን ሀገልግሎት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድርግ በተማሩት የትምህርት መስክ የበለጠ መሥራት ይኖርባቸዋል” ሲሉም አመልክተዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው እንደ ኦንላይን (online) ያሉ የተለያዩ አማራጭ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ምሩቃን ተማሪዎች ማሟላት ያለባቸውን እንዲያሟሉ ማድረጉንም ገልጸዋል።

    ምሩቃኑ በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማሩ ሀገራዊ ለውጡንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ሀገልግሎት በመስጠት ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም ነው ያስገነዘቡት። ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣትና ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

    ከዛሬው ተመራቂዎች መካከል ብቸኛ የዶክትሬት ተመራቂ የሆኑት ዶ/ር ሰይፉ ተሾመ በበኩላቸው፥ በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በተሻለ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። “ሁላችንም በመተባበር ለሀገራችን ብልጽግና በአንድነትና በመተባበር መሥራት አለብን” ብለዋል።

    ሌላዋ ተመራቂ መሠረት መልኬ በበኩሏ፥ በምትሰማራበት የሥራ መስክ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ እድገት የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግራለች። በሀገሪቱ በሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩሏን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጻለች።

    የዛሬ ምሩቃንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በቅድመ ምረቃ እና ድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል።

    ዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴም ለ300 አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች በኮሮና ቫይረስ የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቀነስ የምግብ እና የዘይት ድጋፍ አድርጓል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል
    መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ900 ተማሪዎች የትምህርት መከታተያ ሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ድጋፍ አደረገ

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በመጪው የትምህርት ዘመን በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

    የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፀጋዬ ደዮ በተቋሙ በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ላይ እንዳሉት፥ በ2013 የትምህርት ዘመን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዘኛ ቋንቋና ሥነ-ልሳን በተጨማሪ በሶሻል አንትሮፖሎጂ (social anthropology) ዘርፍ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል።

    እንዲሁም በጤና ሣይንስ ኮሌጅ የትምህርት ዘርፍ በሥነ ተዋልዶ፣ ሥነ ምግብ፣ ማኅበረሰብ ጤና፣ እናቶችና ሕፃናት ጤና የትምህርት ዘርፎች እንደሚከፈቱም አስታውቀዋል።

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በሚጀምራቸው ዘጠኝ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በእያንዳንዱ የትምህርት ዘርፍ እስከ 15 የሚደርሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርና ይህም ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ ለውጥ መሆኑን ዶ/ር ፀጋዬ ገልጸዋል።

    የትምህርቱ ዓላማ ዩኒቨርሲቲው አቅምና ዕውቀትን ከማጐልበትና ከማሻገር በተጓዳኝ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ ለማመቻቸት ነው ብለዋል። በተለይ በትምህርት ጥራት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንዲወገዱ የትምህርት መርሃ ግብሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አመልክተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የውጭ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶ/ር የሺመቤት ቦጋለ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ለሚጀምረው የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በቂ የሰው ኃይልና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። መረሃ ግብሩ በትምህርት ተግባቦት ቴክኖሎጂ በቤተ ሙከራዎችና በኢንተርኔት በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተ መጽሕፍትን አደራጅተናል ብለዋል።

    የሚጀምረው መረሃ ግብር የተቋሙ መምህራንና ተማሪዎች አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የኦሮምኛ ቋንቋ ዲፓርትመንት ኃላፊ ወ/ት ሁርሜ ደገፋ ናቸው።

    በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለአንድ ቀን በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው ከ100 በላይ መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች ተካፍለዋል።

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም. ከተቋቋመ ጀምሮ በ33 የትምህርት ዘርፎች ከ4 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱም ተመልክቷል።

    ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን በሬዲዮ በመከታተል ላይ ለሚገኙ 900 ተማሪዎች የሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ድጋፍ አደረገ። ድጋፉ ከ700ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ 500 ሬዲዮኖችና 400 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች ናቸው።

    የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት እንደገለጹት፥ ድጋፉ በመቀበያ ችግር ምክንያት የሬድዮ ትምህርት ፕሮግራም መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ድጋፉ የተደረገላቸው መቀሌን ጨምሮ በአምስት የክልሉ ወረዳዎች የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች እንደሆኑ አመልክተው፥ በየቤታቸው ትምህርታቸውን በሬዲዮ ለመከታተል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

    የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይቋረጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል – ፕ/ር ክንደያ። ተማሪዎች በሬድዮ የሚተላለፍ ትምህርት በመከታተል ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ፕ/ር ክንደያ አስረድተዋል።

    የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፥ የተደረገው ድጋፍ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። ከዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አይነስውሩ አለም ተስፋዬ በሰጠው አስተያየት የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት መርሃ ግብሩ በተጨማሪ ወቅታዊ የዓለማችን ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችለን ነው ብሏል። በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ድጋፍ ማድረግ ሰብአዊና ዜግነታዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሳይንስ ሳምንትን ከጥቅምት 25 ቀን እስከ ህዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት ያከብራል።

    የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ዓላማዎችና መሪቃል ይከበራል። የኢትዮጵያው የሳይንስ ሳምንት ሲከበር የተባበሩት መግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) በየዓመቱ ኖቬምበር 10 ቀን የሚያከብረውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ባማከለ ሁኔታ ይፈፀማል።

    ይህ ሀገራዊ የሳይንስ ሳምንት ሲከበር ዋና ዓላማው ሳይንሳዊ አስተሳሰብንና አሠራርን፣ የሳይንስ ባህል ግንባታ ሥራዎቻችንን ለማሳወቅና እንዲሁም በተለያዩ ሳይንሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በቀጣይም የወጣቱን ትውልድ የሳይንስ ፍላጎት ለማሳደግ እንዲያግዝ ሳይንስ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሳይንስን፣ ሳይንሳዊ እንቅስቃሴዎችን እና የሳይንሳዊ ጥናቶችን ለሕዝብ ለማስተዋወቅም ያለመ ነው።

    በሳይንስ ሳምንት ከሚከናወኑ ዝግጅቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

    1. ከጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል በSTEM (Science, Technology, Engineering, and Mathematics) ዘርፎች ውድድር ይካሄዳል። ተማሪዎቹ በአራቱ የትምህርት ዘርፎች ለውድድር በሚያቀርቡት ፈጠራ ላይ ተመሥርቶ በሚሰጠው ዳኝነት አሸናፊዎች እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ተሸላሚ ይሆናሉ።
    2. ሐሙስ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶችና ሙያ ማኅበራት ጋር በሒልተን ሆቴል ምክክር ያደርጋል:: በምክክር መድረኩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሳይንስ ሥራዎችና የትኩረት አቅጣጫ፣ የሙያ ማኅበራት ሚና ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና፤ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት ዕይታ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶች የሳይንስ ሥራዎች ትኩረትና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር “ለኢትዮጵያ ግብርና አገር በቀል እይታ” በሚል የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ ይካሄዳል።
    3. አርብ ጥቅምት 28 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ሳይንስ ለልማትና ብልፅግና በሚል ርዕስ የተለያዩ ባድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሀገራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር ወርክሾፕ ይካሄዳል።
    4. እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የአረንጓዴ ቀን (Green Day) ይከበራል። በዕለቱ ባለፈው ክረምት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተተከሉ ችግኞችን ቦታቸው ድረስ በመገኘት የመንከባከብ ሥራዎች ይሠራሉ። እፅዋቱ ባሉበት ደረጃ በሚሠሩ የእንክብካቤ ሥራዎች ላይም በተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ሳይንሳዊ ገለፃ ይቀርባል።
    5. ሰኞ ሕዳር 01 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የባዮዳይቨርሲቲ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute) ጋር በመተባበር “ሰውና ሥነ ምህዳር (Man and Biosphere)” በሚል ርዕስ ትምህርታዊ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል። በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጥሮ ሳይንስና ግብርና ኮሌጆች በርዕሱ ላይ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።
    6. ማክሰኞ ሕዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biotechnology Institute) ጋር በመተበባር “ባዮቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ በዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርታዊ ገለፃ ይቀርባል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ ሳይንሳዊ ገለፃዎችና ውይይቶች ይካሄዳሉ።

    ስለሆነም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. በሚጀምረው የሳይንስ ሳምንትን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተውት ለህብረተሰቡ የሚመጥኑና ሳይንሳዊ ግንዛቤዎችን የሚፈጥሩ ሥራዎችን በመሥራት የሳይንስ ሳምንት አከባበር አካል እንዲሆኑ እንጋብዛለን።

    በተጨማሪም ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የሳይንስ ሳምንት፣ በየዘርፋቸው ሳይንስ ለአገር ልማትና ብልፅግና ያለውን ፋይዳ የሚያሳዩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ በበዓሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንጋብዛለን።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሳይንስ ሳምንት በኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጀ። የአድዋ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት ሰጠ።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩት ጥናትና ምርምሮች ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በአገሪቷ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡት የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሚጠበቀው በታች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም እንደ ዋነኛ ምክንያት አስቀምጠውታል። እንዲያውም ለዘርፉ የሚመደበው አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን በመጠቆም።

    በተጓዳኝም የምርምር መሠረተ-ልማቶች አለመኖር፣ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ መሆንና መምህራን ለምርምር ትኩረት አለመስጠታቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩት ጥናታ ምርምሮች ቁጥር አነስተኛ መሆነ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ባሏቸው አቅም በአስገዳጅ መልኩ የጥናትና ምርምር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸዋል።

    ምንም እንኳን በትምህርት ተቋማቱ ዝቅተኛ ቢሆኑም በሥመ-ጥር ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ምርምሮቻቸውን የሚያወጡ ጉምቱ ምሁራን መኖራቸውንም ዶ/ር ሳሙኤል አልሸሸጉም።

    ለጥናትና ምርምር የሚበጀተውን በጀት በተመለከተም ከአገሪቷ እድገትና ከመምህራኑ አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ እያደገ የሚመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ጆርናሎች ጥራታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጥናት እየተደረገበት መሆኑንም አስረድተዋል። መመሪያውንም በቅርቡ ወደ ሕግ በመቀየር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ጆርናሎች የሚመሩበት ወጥ ሥርዓት በመዘርጋት የእውቅና ደረጃም እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

    እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ መውሰድ (ረቂቅ አዋጁን ማውጣትም ሆነ ለጆርናሎች መመሪያ መዘጋጀት) የሚካሄዱትን ምርምሮች ጥራታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፥ በቀጣይም ጥናትና ምርምር ላይ የግሉ ዘርፍ የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

    በአሁኑ ወቅት የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ቁጥር 33 ሺህ ደርሷል፤ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺህ 500 የሚሆኑት ናቸው ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው – የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው።

    ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ፥ ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት መስጠቱን በትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የአድዋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የዩኒቨርስቲውን ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

    የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘብራአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ እንዲውል መሬቱ ተሰጥቷል። በዚህም 131 የአካባቢው አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ላይ ተነስተዋል። ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮችም ካሳ ክፍያ ለመፈፀም 15 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ በበኩላቸው ግንባታውን ለማስጀመር ከፌዴራልና ከትግራይ ክልል መንግሥታት 450 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። ከዚህም የትግራይ ክልል መንግሥት 250 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል መግባቱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ አስተዳደርም በቅርቡ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ


    Anonymous
    Inactive

    ተማሪዎች እና መምህራን 123ኛውን የአድዋን ድል እየዘከሩ ነው
    —–

    ‹‹3ቱ የካቲቶች›› የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እስከ የካቲት 30 ይቆያል

    የ‹መለከት አፀደ ሕጻናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት› ተማሪዎች በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር በሚገኘው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በመገኘት 123ኛውን የአድዋን ድል እየዘከሩ ነው፡፡

    የአድዋን ድል በማስመልከትም ያዘጋጁትን ቴአትር አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ክፍል አዘጋጆች በቦታው ተገኝተው የተማሪዎቹን ጉብኝትና ቴአትር ቀረጻ አድርገዋል፡፡

    ሕጻናቱ ባቀረቡት ቴአትር ላይ አገር ስለመውደድ፣ ስለፍቅር እና የፆታ እኩልነትን አስመልክተው አስተማሪ ጭብጦችን አንስተዋል፡፡

    ‹‹3ቱ የካቲቶች›› የተሰኘው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እስከ የካቲት 30 ስለሚቆይ ሁላችሁም እንድትጎበኙት ተጋብዛችኋል፡፡

    —————————-
    አድራሻች፡- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ከፒያሳ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ፣ ሆስፒታሉ አካባቢ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉለሌ ቅርንጫፍን አልፎ በሚገኘው ቅያስ 500 ሜትር ገባ ብሎ፡፡

    ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – STEMpower የተሰኘ መቀመጫውን USA (ሳሌም፥ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ) ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲዎች እየረዳ የሚገኝ ሲሆን በአገራችን 13 ማዕከላትን ከፍቶ በትብብር እየሠራና እየረዳ ይገኛል።

    ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 10 ማዕከላትን (ሰባት ማዕከላትን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶስቱን በተለያዩ ከተሞች እ.አ.አ. በ2019) ለመክፈት ከኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት የካቲት 14 ቀን 2011ዓ.ም. ተፈራርመዋል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) STEMpower ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን ለማበልጸግ እያደረገ ያለውን ትብብር በማመስገን፥ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕድሉን በመጠቀም በአግባቡ ማዕከላቱን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ዲጂታል ሰሌዳዎችን መጠቀም ጀመረ።

    የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ለሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲአዲግራት ዩኒቨርሲቲአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ) ማዕከሉን በመጠቀም በአካባቢዎቻቸው ያሉትን የማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    የSTEMpower አስተባባሪ ዳይሬክተርና ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ቅድስት ገብረአምላክ፥ “STEMpower ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከድርጅቱ አመሠራረት ጀምሮ ዓላማውን፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና የወደፊት ዕቅድ አጭር ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል። ለወደፊትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በስፋት እንደሚሠሩ ፣ በ2040 የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ ገልጸዋል።

    አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ድርጅቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማዕከሎቹ በከፍተኛ ትምህርት እና በሳይንስ ትምህርቶች አከባቢ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ ረገድ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    STEMpower


    Semonegna
    Keymaster

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አውስቷል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር ያለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል 40ኛ የጥበብ ውሎ መድረኩን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አካሒዷል።

    በዝግጅቱ ላይ የዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ተደርጓል። ሥራዎቹን እና ሕይወቱን አስመልክቶ የሙዚቃ ባለሙያ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ የተሾመው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የውይይት መነሻ ጥናት አቅርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተካሂዶ ነበር።

    “ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ <ባለዋሽንቱ እረኛ>(The Shepherd Flutist)  በተሰኘ ታላቂ ሥራ የኢትዮጵያን መልክ በረቂቅ ሙዚቃ ያሳዩ ናቸው” በማለት አቶ ሠርፀ የገለጿቸው የሙዚቃውን ረቂቅነት በመጥቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አውስቷል።

    በሙዚቃ ላይ ከሠሯቸው ከበርካታ የምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ “Roots of Black Music” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙ የዓለማችን የሙዚቃ አጥኚዎች የተዘነጉ (የተዘለሉ) የአፍሪካ/የምሥራቁ ዓለምን የሙዚቃ ስልትና ፍልስፍናን አጉልተው ለተቀረው ዓለም ያሳዩበት እንደሆነም አቅራቢው አብራርተዋል።

    በውይይቱም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ችግር ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፥ “ዋናው ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተቋም ፈርሷል፤ እሱን መልሶ መገንባት የቤት ሥራችን ነው” ብለዋል አቶ ሠርፀ። አክለውም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ትምህርት ሥርዓት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ሥርዓተ-ትምህርት ነፃ መውጣት ያለመቻሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ጠቅሰዋል።

    ውይቱን የመሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እንዳለጌታ ከበደ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ማደግ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የጥበብ ሰዎችን ፈለግ እና ሥራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በሁሉም አካላት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ፋንታዬ ነከሬ ያባሉ ነበር። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል። የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በመሆን ሙዚቃን ከማስተማሩ ባሻገር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።

    በድጋሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተመልሰው፣ ኮነቲከት ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዌስልያን ዩኒቨርሲቲ (Wesleyan University) በ1961 ዓ.ም የማስትሬት፣ እንዲሁም በ1963 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ምዕራባዊ ባልሆኑ ሙዚቃዎች ምርምር (ethnomusicology) አግኝተዋል።

    ከሙዚቃው መምህርነትና ተመራማሪነት ባሻገር ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ደራሲም ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ኮንፌሽን (Confession)፣ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሩትስ ኦፍ ብላክ ሙዚክ (Roots of Black Music) የሚሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ በሙዚቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሁፎችን፥ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ-አሜሪካውያን ባህልና አኗኗር ላይ ለሚያተኩረው “The Chronicler” ለተሰኘው መጽሔት ጽፈዋል።

    በአሜሪካ ፕሮፌሰር አሸናፊ ኑሯቸው ፍሎሪዳ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Florida State University) የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት የሠራ ሲሆን፣ ተቀማጭነቱን እዚያው አሜሪካ ያደረገውናታዋቂውን የኢትዮጵያ ምርምር ካውንስልን (Ethiopian Research Council) በዳይረክተርነት መርቷል።

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወ/ሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ሁለተኛ ባለቤታቸው (አሜሪካዊ) አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የ60ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባትም የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
    PHOTO: Ethiopian Academy of Sciences

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 34ኛውን እና የዓመቱ የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት ምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አካሄደ።

    ገለፃውን ያቀረቡት ዶ/ር ዓለማየሁ ሥዩም (በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም (IFPRI) ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ) ሲሆኑ፣ አቅራቢው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና በምግብ እራስን መቻል መካከል ያለው ብያኔ የተዛነፈ በመሆኑ በምሁራን እና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ወጥ የሆነ አረዳድ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል። ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአገር፣ በክፍለ-ዓለምና በዓለም ደረጃ፤ ሁሉም ሰዎች፣ ዘወትር፣ በመጠኑ በቂ የሆነ፣ በጤና ላይ አደጋን የማያስከትል እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ፍላጎትም ሆነ የአይነት ምርጫ ቁሳዊናኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ሲኖራቸው እንደሆነና ምንም ዓይነት ወቅታዊ መዋዠቅን፣ ያልተጠበቁ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ ክስተቶችን (አደጋዎችን) መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ ሲፈጠር እንደሆነ አቅራቢው ይገልፃሉ።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ መካከለኛ መጠን ያላቸው ከተሞች በዓመት በአማካይ ከ5-6 በመቶ ዕድገት እያሳዩ መሆኑ እና መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ-ተኮር ኢኮኖሚ ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል። ነገር ግን ዛሬም የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ የህፃናት መቀንጨር በአማካይ 38 በመቶ መድረሱ፣ የምግብ እህል እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ መጨመሩ እና ከፍተኛ የምግብ እህል/ሸቀጥ ከውጪ እንዲገባ መደረጉ “የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም እልባት ያላገኘ አገራዊ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ።

    ለእንደዚህ ዓይነት የምግብ ዋስትና ስጋት ያጋልጣሉ ያሏቸውንም ምክንያቶች ዶ/ር ዓለማየሁ ዘርዝረዋል። “በገጠር የተወሳሰበ የመሬት ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሁኔታ (የይዞታ ባለቤትነትና አጠቃቀም ሥርዓት)፣ የእርሻ መሬት ይዞታ ማነስና መበጣጠስ፣ የመሬት ምርታማነት መቀነስ/የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የሥራ ዕድል መጥበብ እና ወጥነት የጎደለው የፖሊሲ አፈፃፀም” ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ። ችግሩም ህፃናትን ለበሽታና ለሞት እንዲሁም ለአካልና አእምሮ ህመም ከመዳረጉ እና የመማርና የማምረት አቅምን ከማኮሰስ አልፎ ድህነት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል።

    በሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረኩ ከችግሩም ለመላቀቅና የተሟላ ማህበራዊ ዋስትና ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል። በውይይቱም ከፍተኛ የግብርና ማስፋፊያ ተግባራት በማከናወን አርሶ አደሮች የተሻለ መረጃ እንዲያገኙና የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን እንዲያላምዱ ማትጋት፤ ዘመናዊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ማድረግ፤ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማካሄድ አማካይ በህይወት የመኖሪያ እድሜን ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ተጋላጭነትን እያጠኑ ስልት የሚቀይሱ ጠቃሚ ተቋማትን መፍጠር (የፖሊሲ ተቋማት፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች፣ የገበያ፣ የአምራቾች ማህበራት፣ የማህበራዊ ዋስትና ስልት፣ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዘዴዎች) ቅድሚያ የሚፈልጉ አገራዊ ተግባራት መሆናቸው ተነስቷል።

    ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም ከ20-25 ዓመት የሚደርስ የግብርናው ዘርፍን ሊያዘምን የሚችል አሠራር በተለይ ደረቅ-አብቃይ አካባቢዎችን፣ ለድርቅ-ተጋላጭቦታዎችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያሻሽል የተቀናጀ መርሐ-ግብር መንደፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል። እንደ ህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት መለዋወጥ ያሉ አባባሽ ሁኔታዎችንም መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ዝግጁነት መገንባት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማስጠበቅ ይረዳልም ብለዋል።

    በጥቅሉ የገለፃው አቅራቢና ተሳታፊዎች፣ ተቋማት መገንባትና በስፋትና በተፈለገው የህብረተሰብ ፍላጎት ልክ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር መፈጠር አለበት በማለት የዕለቱን ውይይት አጠናቀዋል።

    ውይይቱን ፕሮፌሰር በላይ ካሳ (የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ከፍተኛ አመራር) የመሩት ሲሆን፣ ከ110 በላይ የሚሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የአካዳሚው አባላትና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Semonegna
    Keymaster

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በዶክትሬት ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ከፍተው ተማሪዎችን ይቀበላሉ።

    ደብረ ብርሃን/ባህር ዳር – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ (2011 ዓ.ም) የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor degree) አራት በሁለተኛ ዲግሪ (master degree) አስራ ሁለት መርሃ ግብሮችን እንደሚከፍት አስታወቀ።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት አሸናፊ ለኮሙኒኬሽን ጉዳዮች እንደገለጹት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አስራ ስድስት አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ይከፍታል።

    ዶክተር ጌትነት አሸናፊ እንዳሉት የትምህርት ክፍሎቹ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀ ግብሮች የመጀመሪያ ድግሪ ከ49 ወደ 53 እንዲሁም 34 የነበረውን የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ወደ 46 ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

    ከተመሠረተ 11 ዓመት የሞላው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ መስኮች እያስተማረ ይገኛል።

    በተመሳሳይ ዜና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ፣ በበሁለተኛ እና በዶክትሬት (doctorate) ዲግሪ በሚከፍታቸው 18 አዳዲስ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልም አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ተቋሙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት አገራዊ እድገቱን በእውቀት ለማገዝ እየሠራ ነው።

    በተያዘው የትምህርት ዘመንም ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 12 የሁለተኛ ዲግሪና አራት የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ 250 ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

    ዶክተር እሰይ እንዳሉት ህግ፣ መሬት አስተዳደር፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ትምህርት፣ ፖለቲካል ሳይንስና የመሳሰሉት የትምህርት መስኮች አዲስ የሚከፈቱባቸው ናቸው። “የተሳካ የመማር ማስተማር ተግባር ለማካሄድም ቀደም ብሎ የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉንና የመምህራን ቅጥርም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል” ብለዋል።

    የኒቨርሲቲው በአፋን ኦሮሞ ትምህርትም በዚህ ዓመት አጋማሽ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ ሥራ ማካሄዱንና የመምህራን ቅጥር እየፈጸመ መሆኑን ዶክተር እሰይ አስታውቀዋል።

    ተቋሙ በህክምናው ዘርፍ የተሻለ እውቅት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ “የተሻለ የማስተማርም ሆነ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አዲስ የማስተማሪያ ሆስፒታል ገንብቶ የ170 መምህራንን በመቅጠር ላይ ነው” ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በመደባኛው የትምህርት መርሀግብር ብቻ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።

    በተለይም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዩኒቨርሲቲ እየወረደ የመጣውን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተሻለ አቅም ያላቸውን መምህራን በመመደብ፣ ቤተ ሙከራዎችንና ቤተ መጻህፍትን በማደረጀት ጥራትን ለማምጣት እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል። ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊትም አጠቃላይ የጥራት መለኪያ ፈተና እንዲወስዱም እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

    ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛውና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓመታዊ የተማሪ የቅበላ አቅሙ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ደርሷል።

    ምንጭ፦ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ (ፎቶ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ)

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 15 total)