-
Search Results
-
‘አገር የሆነች ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ የመንግሥት ግዴታ መሆኑን’ በማሳሰብ ማኅበረ ቅዱሳን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጻፈ። የደብዳቤው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።
ለክቡር ዶክተር ዐቢይ አህመድ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- በተለያዩ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ስለመጠየቅክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ፡- አስቀድመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሀገር ግንባታ የነበራትን ታላቅ ሚና ተገንዝበው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም ያረጉትን አስተዋጽኦ ሳናመሰግን አናልፍም።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ይህን ደብዳቤ ለእርስዎ ለመጻፍ ያነሳሳን ዐቢይ ጉዳይ በሀገራችን በየጊዜው ድንገት በሚፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦች ሁሉ ምክንያት ተፈልጎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ካህናቶቿና ተከታዮቿ ምእመናን የአደጋ ሰለባ እንዲሆኑ እየተደረገ መምጣቱ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ በመንግሥት ሊሰጠው የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል።
በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ የእምነት ተቋማት ለሀገር ግንባታና ዕድገትም ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው። እንደዚሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የማይተካ ሚና እንደ ነበራት ግልጽ ነው። በሥነ ጥበብ፣ በኪነ ሕንፃ፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሕግ ቀረጻና ሀገራዊ ክብርና እሴትን በማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተች መንፈሳዊ ተቋም ናት። በረከታቸው ይደርብንና በሕይወት የተለዩን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በተለያዩ ጽሑፎቻቸውና አባባሎቻቸው እንዳስቀመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ ከነፊደሉ፣ ነጻነት ከነክብሩ፣ ዘመን ከነቀመሩ፣ ሀገር ከነድንበሩ፣ አንድነት ከነጥብዓቱ ያስረከበች የኢትዮጵያ ባለውለታ ናት። ቀደም ሲል በክቡርነትዎም አንደበት እንደተነገረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሀገር ባለውለታ ከማለት ይልቅ ራሷን ሀገር አድርጎ መግለጽ የውለታዋን ታላቅነት በተሻለ ሁኔታ ያሳያል። ይህን የምታደርገው ደግሞ የሀገሪቱን ከፍተኛ ቁጥር የያዘ ሕዝብ የምትመራ እንደመሆኗ እንደ ሀገር ስለምታስብና ለሀገር ልማትና እድገት ትኩረት ሰጥታ ስለምትሠራ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-
ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችው አስተዋጽኦና ውለታ ይህ ሆኖ ሳለ ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ እየተፈጸመባት ያለው ግፍ ከበጎነቷ በተቃራኒ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በይዘቱ እየባሰና እየጨመረ በዐይነቱም ለመናገር እስከሚሰቀጥጥ ድረስ ዘግናኝ እየሆነ መጥቷል። ይህ ግፍ የተጀመረው ዛሬ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያጋጠሙ ያሉ ተደጋጋሚና ቀን ቆጥረው የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተበረታቱባት ይገኛሉ። በተለይም ጽንፍ የረገጠው የዘውግ ፖለቲካ ርእዮተ ዓለምና ኢትዮጵያን በጠላትነት የፈረጁ “የውጭ አካላትን” ሽፋን ያደረገ እንቅስቃሴ ግብ ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋትና ለሀገር አንድነትና ነጻነት ያላትን ሚና መቀነስ እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ከሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዘው የመጡ የብዙ አካላት ፍላጎቶችም እንዲህ ዐይነት ቀውሶች እንዲፈጠሩ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም እንረዳለን። በሀገር ውስጥም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚለው ሃሳብ ላይ ዋልታ ረገጥ የሆነ አመለካከት በሚያራምዱ አካላት መካከል ያለው ውጥረትም ቀላል እንዳልሆነ እንገምታለን።
ይህም ሁሉ ሆኖ መንግሥት ችግሩን ለመፍታትና ምላሽ ለመስጠት ያሳየውን በጎና ቅን ሙከራዎችን ግን ሳንጠቅስ አናልፍም። ነገር ግን አሁንም ቤተ ክርስቲያን የጥፋት መልእክተኞች የጥቃት ዒላማ ሆና ትገኛለች። በዚህ ረገድ የሕግ የበላይነት ኖሮ ፍትሕ ማግኘት አለመቻል ከመንግሥትም በቂ ከለላ ሳታገኝ መቅረቷ በኦርቶዶክሳውያን አእምሮ ብሶትና እሮሮ ያስነሳ በመንግሥትም ላይ ትልቅ ጥርጣሬን የሚያጭር እየሆነ መጥቷል። ለዚህም በምሳሌነት ቀደም ያለውን እንኳ ትተን የቅርቡን ብናይ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በተነሳው ውዝግብና ከአክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ጥበቃ መነሣት ውዝግብ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰው ረብሻ በቤተ ክርስቲያን፤ በአገልጋዮችና በምእመናን የተፈጸመውን ጥቃትና የደረሰውን ዕልቂት ማስታወስ ይበቃል። በአጠቃላይ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋና አካባቢው ከተፈጸመው ጥቃት እስከ አሁን ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራን አስተናግዳለች። እርስዎ ከመጡ ጀምሮ በተረጋገጠ መረጃ መሠረት በትንሹ 25 አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለዋል። ጅግጅጋ፣ ጅማ፣ ሲዳማ፣ ከሚሴ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ባሌና አርሲ በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ካህናትና ምእመናን በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይ ተቀጥቅጠው፣ በእሳት ተቃጥለውና በገጀራ ተቆራርጠው ሕይወታቸውን አጥተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሕፃናትንና አሮጊቶችን ጨምሮ ብዙ ሴቶች ተደፍረዋል። የብዙ ክርስቲያኖች ቤቶች ተቃጥለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸውና ከሀብት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተለያዩ የሥነ ልቡና ጫናዎች ውስጥ ወድቀው በፍርሃትና በሥጋት የሚኖሩት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
ቀደም ሲልም የቤተክርስቲያን መቃጠልና ጥቃት ይቁም ብለው የተሰባሰቡና ለክቡርነትዎ ቀርበው ሃሳባቸውን ገልጸው እርስዎም በሰጡት ምላሽ ከክልሎች ጋር በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። ብዙ ክልሎችም አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ግን ጉዳዩ ላይ ትኩረት አልሰጠም፤ ፍላጎትም አላሳየም። አሁን እንደሚታዩት አብዛኞቹ ችግሮች የተፈጸሙትና በመፈጸምም ላይ የሚገኙት በዚሁ ክልል ውስጥ ነው። ይህን የምንጠቅሰው ስለማያውቁት ሳይሆን እንዲህ ዐይነቶች ጥቃቶች እየተፈጸሙ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ ሳይወሰድ ሲቀርና የዜጎች የደኅንነት ዋስትና አለመረጋገጥ ምን ማለት እንደሆነ ምንስ ያህል ከባድ እንደሆነ በኋላ የሚያስከትለውም አደጋ ከባድ እንደሆነ ለማሳሰብ ጭምር ነው።
በያዝነው ወርኃ ኅዳር ደግሞ የጥቃት ዒላማ ተረኛ የሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ናቸው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙ ፍላጎቶች የሚስተናገዱባቸው፣ የሀሳብ ፍጭቶች የሚካሔዱባቸውና፣ ማኅበራዊ መስተጋብሮች የሚፈጸሙባቸው የልሕቀት ማእከላት ናቸው። በአግባቡ ከተያዙ ሀገርን ከድህነት የሚያወጡና ለሀገር ፈውስ የሚሆኑ ሊቃውንት የሚወጡባቸው፣ በአግባቡ ካልተያዙና ለጥፋ መልእክተኞች መሣሪያ ከሆኑ ግን ሀገርን የሚያጠፉ ትምህርትን በአግባቡ ያልተጠቀሙበት የጥፋት ዐርበኞች የሆኑ ትውልዶች የሚፈሩባቸው እንደሚሆኑ የታመነ ነው። ይህን እውነት ከግንዛቤ አስገብተን ስንመለከተው ለሀገር የሚበጅ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ለሕዝብ የሚቆረቆር የተማረ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተረጋጋ የመማር ማስተማር ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር ከቻሉ ብቻ ነው። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ አጥልቶ የሚታየው የጥቃት ድባብ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ልጆቻቸውን የላኩ ወላጆችንም ሆነ ተማሪዎችን በተረጋጋ መንፈስ እንዲኖሩ የሚፈቅድ አይደለም። በአንዳንድ ቦታ አልፎ አልፎ እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎችና ሁከቶች ወላጆችን ለከፍተኛ ሥጋትና ጭንቀት እየዳረጋቸው ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተፈጸመ ያለው ጥቃትም ሃይማኖትን ማእከል ያደረገ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። ስለሆነም መንግሥት በአጥፊዎች ላይ ርምጃ አለመውሰድን እንደ “ትዕግሥት” በመቁጠር ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በዝምታ መመልከቱ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ነውና የዜጎችን የመኖር መብትና የደኅንነት ዋስትና ማረጋገጥን መንግሥት በአግባቡ እንዲተገብረው እንጠይቃለን። ሰሞኑን እንደተመለከትነው ጥቃቶችና ግጭቶችን በእንጭጩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይወጡ መቆጣጠር እየተቻለ ከትኩረት ማነስ ምክንያት ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ በምሥራቅና ምዕራብ ሐራርጌ ምእመናንና አብያተ ክርስቲያናት በሁለት ቀናት ብቻ የደረሰውን ጥፋት ዘርዝረን የማንጨርሰው ሆኖብናል።
በመሆኑም በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች በሚዲያ እንደተገለጸው ከመንግሥት አቅም በላይ ካልሆኑ በአጭር ጊዜ ችግሮቹ እልባት እንዲያገኙ መደረግ አለበት፣ ካልተቻለ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተወሰነ ጊዜ ተዘግተው የማረጋጋት ሥራዎችን ሠርቶ እንደገና ማስጀመር እንደ አማራጭ መፍትሔ መታየት ይገባዋል ብለን እናምናለን። ከዚህም በተጨማሪ ጥቃቶችን እየፈጸሙና እያስፈጸሙ ባሉ አጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ በግልጽና ሁሉንም ዜጋ በሚያሳምን መልኩ መውሰድ ለዜጎች ደኅንነት ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን። ችግሩ አልፎ አልፎ ከኦርቶዶክሳውያን ውጭ የሚገኙትንም የሚያካትት ቢሆንም አሁን ግልፅ ሆኖ ግን የሚታየው ኦርቶዶክሳውያኑ ላይ እጅግ ያነጣጠረ የሰፋና የከፋም ነው። አስቸኳይ መፍትሔ ካልተገኘለትም ‘’ኦርቶዶክሳውያኑ በሁሉም አካባቢ የጥቃት ዒላማ ተደርገን እየተቆጠርን ያለነው እኛን ነን’’ በማለት የራሳቸውን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከፍተኛ መተላለቅንም ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ የመንግሥት ሚዲያዎች አደጋዎችን በትክክል እንደመዘገብ እውነትን ማስተባበልና የተሳሳተ መረጃ ማስተላለፋቸው ደግሞ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ሆነ ተብሎ የሚወሰድ ርምጃና በአብዛኛውም ምእመንም ዘንድ መንግሥታዊ ሽፋን ያለው ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል። በአጠቃላይ የችግሮቹ ሂደት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ከመፈጠራቸው በፊት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እየጠየቅን በጉዳዩ ዙሪያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሆኑ ሃይማታዊ ተቋማት ሊሳተፉባቸው በሚገባቸው ኃላፊነቶች ሁሉ የድርሻችን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
ማኅበረ ቅዱሳን (EOTCMK)ሀገር የማዳን ጥሪ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነትባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሥርዓት አልበኞች በተወሰደ የጥፋት እርምጃ የማይተካ የዜጎቻችንን ሕይወት አጥተናል፣ የብዙዎች አካል ጎድሏል፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩት ንብረት ወድሟል እዲሁም በተዘጉ መንገዶች ምክንያት ዜጎች ተንገላተዋል፤ የሀገሪቷ የኢኮኖሚ እቅስቃሴም ተስተጓጉሏል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዜጎች ሕይወት ላይ በደረሰው ጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል። ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል። የተፈጸመውን ሕገ ወጥ እና አሳፋሪ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል!
የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረጉ የሥርዓት አልበኞች ሙከራዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ መጥቷል። የመንግሥት እነዚህን ሙከራዎች አስቀድሞ የመተንበይ፣ ሲከሰቱም አፋጣኝ እና ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅሙ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እየታየበት አይደለም። በዚህም ምክንያት የዜጎች ሕይወት በተደጋጋሚ አደጋ ላይ ወድቋል፤ አሁንም እየወደቀ ይገኛል። በቁጥር ቀላል የማይባሉ ዜጎች በሀገራቸው ደኅንነታቸው ተጠብቆ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት እና የመኖር መብታቸውን መጠቀም የማይችሉበት ብቻ ሳይሆን በማያቋርጥ ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የተገደዱበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከዚህም አልፎ በዕምነት ተቋማት እና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለመተማመን ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ የማይታረም ከሆነ የሽግግር ሂደቱ ተጨናግፎ ወደማንወጣው ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል።
መንግሥት የችግሩን ጥልቀት እና ሕግ የማስከበር ድክመቱን በሚገባ ፈትሾ በአስቸኳይ ክፍተቶቹን እንዲያስተካክል እና የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ እና ጥፋተኞችን ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቀን እናሳስባለን።
መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ የጋራ ሀገራችንን ከጥፋት አፋፍ ለማዳን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የሚገባን ወቅት ላይ መሆናችንን ተገንዝበን ልዩነቶቻችንን አቻችለን በአንድነት እንድንቆም እና ሀገራችን ከተደቀነባት ከባድ አደጋ እንድንታደግ ከአደራ ጭምር ጥሪ እናስተላልፋለን።
የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
ምንጭ፦ ኢዜማ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ (ህወሃት እየፈጠረ ያለው ተግዳሮት)
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
- “ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል” በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
- ጥፋተኞች ለሕግ ይቀርባሉ፤ ሰላምን ለማስፈን እንተጋለን ― አዲስ የተሾሙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው
- ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።
—–አዲስ አበባ (ማኅበረ ቅዱሳን) – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ዓርማ አድርጋ ስትጠቀምበት የኖረችውን እና አሁንም የምትጠቀምበትን ባንዲራ ለበዓል ይዛችሁ ወጥታችኋል፤ በቤተ ክርስቲያን ጣሪያ እና ጉልላት ላይ ቀብታችኋል በማለት ምእመናንን የሚያዋክቡ፣ ወጣት ክርስቲያኖችን የሚያስሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ።
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያንን ተቀማጭ ገንዘብ ከንግድ ባንክ አውጥታችሁ እኛ በምንፈልገው ባንክ አስቀምጡ በማለት የሚያስገድዱ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀው 38ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጠናቀቀበት ዕለት ነው።
ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው፣ የሐሰት ታሪክ ፈጥረው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚነዙ አቀጣጣዮችን (‘አክቲቪስት’/ ‘activist’ ነን ባዮች) እና ፖለቲከኞችን እኩይ ድርጊት መቃወም እንደሚገባ ጉባኤው በመግለጫ አሳውቋል።
ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።
የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም ጉባኤው አሳስቦ አገራዊ ለውጡ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው እኩይ ተግባር ቤተ ክርስቲያንን እያሳዘናት እና እያሳሰባት መሆኑንም አስገንዝቧል።
በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን ጥፋት በሰላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ እንደሚኖርበትም አሳስቧል።
የጥምቀት እና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ነጥቀው፣ አንዳንድ ጊዜም ቆርሰው ለሌሎች የሚሰጡ አካላትን እኩይ ድርጊት አጥብቆ የተቃወመው መግለጫው በአገር ውስጥም በውጭም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እኩይ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥበብ እና በትዕግሥት ማሳለፉ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጧል።
ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች፣ በውጭ ወራሪ ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሰዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው።
እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱትን ዘመናት የማይሽሩት ታሪካዊ ውለታዎችን ለሀገር ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የጥፋት ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚፈጽሙት ከፍተኛ የሆነ አስተዳደራዊ በደልና የተቀናጀ ጥቃት እያደረሰብን ያለውን መከራና ችግር ቤተ ክርስቲያናችን ባላት ሀገራዊ ኃላፊነት ችግሩን በትዕግስት አሳለፈችው እንጂ እየተፈጸመባት ካለው ግፍና በደል አንጻር ይከሰት የነበረው ችግርና ሀገራዊ ቀውስ በቀለሉ የሚታለፍ ባልሆነም ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እየደረሰብን ያለውን በደልና መከራ ከዛሬ ነገ ይሻላል በማለት ታግሰን ብንችለውም እያደር እየባሰና የችግሩም አድማስ እየሰፋ ሊሄድ ችሏል። ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም ቅሉበተለይ በአሁኑ ወቅት መልኩን እየቀያየረ እና ለዘመናት የቆየ አንድነቷን በማፈራረስ ከቤተ ክርስቲያኒቱም አልፎ ሀገራዊ ቀውስና አለመረጋጋት የሚያስከትል የጥፋት አጀንዳን ባነገቡ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የጀመሩት እንቅስቃሴ ወደከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ እና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በስፋት ከተወያየ የሚከተለውንየአቋም መግለጫ አውጥቷል፡-
- አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ እና ለጥፋት ለተደራጁ ቡድኖች ፖለቲካዊ ሽፋን በመስጠት በልዩ ልዩ ክልሎች የተፈጸሙት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የአገልጋይ ካህናት እና ምእመናን መገደል፣ ዘመን የማይተካቸው የሀገር መገለጫ የሆኑትን ጥንታውያን እና ታሪካውያን ቅርሶችን በማቃጠል ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿን ታሪክ እና ቅርስ አልባ በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን በደሎች እና ግፎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል።
- ቤተ ክርስቲያኒቱ ባህል፣ ቀለም፣ ቋንቋ እና ብሔር ሳትለይ በአንድነት እና በአቃፊነት ለሀገር ውለታ ያበረከተች መሆኗ ተዘንግቶ በእምነት ሽፋን የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች የሆኑ ምእመናን ካደጉበትና ሀብት እና ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ፣ በእምነታቸው ብቻ ተገደው በመደፈር እና ልዩ ልዩ የሥነ ልቦና ጥቃት እንዲደርስባቸው በማድረግ እንዲሁም በድብደባ እና በዛቻ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረገ ያለውን ሕገ ወጥ አድራጎትን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል።
- ለባለውለታዋ እናት ቤተ ክርስቲያን በማይመጥን እና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕጋዊ ይዞታዋን እና የአምልኮት ቦታዎቿን በመንጠቅ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን እንደ ሽፋን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በደል እና ግፍ የሚፈጽሙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎችን ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ አድራጎታቸው እንዲታቀቡ በጥብቅ ያሳስባል።
- እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ በሀገራዊ የሀላፊነት ስሜት ታግሶ እና ችሎ ሞቱ፣ እሥራቱ፣ ዛቻው፣ ስደቱ እና እንግልቱ ሳይበግረው ሀገር በአንድነት እና በፍቅር እንዲሁም በመተሳሰብ እንድትቀጥል ታሪክ የማይረሳው መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን አገልጋይ ካህናት እና መላውን ምእመናንን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአጠቃላይ መላው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ላሳያችሁት ትዕግስት የተመላበት ሀገራዊ ሀላፊነት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያመሰገነ እንደአሁን ቀደሙ ሁሉ ትዕግስት የተመለበትን ሀገራዊ ኃላፊነታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን እና ወደፊትም ሊደርስ የታቀደውን ግፍ እና ጥፋት በአንድነት እና በኅብረት ከእኛ ከመንፈስ ቅዱስ አባቶቻችሁ ጋር በመሰለፍ በጽናት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንድትጠብቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በቤተ ክርስቲያናች እምነት እና ቀኖና መሠረት በእምነታቸው ምክንያት በሰይፍ የታረዱ፣ በጥይት የተገደሉት፣ በእሳት የተቃጠሉ፣ ሕይወታቸውን ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው የሰጡ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በሰማእትነት ክብር እና ማዕረግ ዘወትር እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በሰማእትነት ሕይወታቸውንየሰጡ አገልጋዮች እና ምእመናን ቤተሰቦች ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይናጋ በተቻለ አቅም ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ ሁላችንም ከጎናቸው በመሆን የድርሻችንን እንወጣ ዘንድ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽኑ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- እናት ቤተ ክርስቲያችን በእንግዳ ተቀባይነቷ እና በአቃፊነቷ ዛሬ ለቁጥር አዳጋች የሆኑት ቤተ እምነቶች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ሰላማዊ፣ የማምለክ መብታቸው እንዲረጋገጥ የበኩሏን ድርሻ የተወጣች መሆኗን ሁሉም ቤተ እምነቶች በየአደባባዩ የሚመሰክሩት እውነታ እንደመሆኑ መጠን በእናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ ሁሉም ቤተ እምነቶች በአንድነት እና በተባበረ ድምጽ በጽናት እንዲያወግዙ እና ለእምነት ተከታዮቻቸውም የቤተ ክርስያናችን ጥፋት እና በደል እንዲወገድ የበኩለቸውን ሚና እንዲወጡ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን እንዲያስተላልፉልን በቅድስተ ቤተ ክርስቲያናችን ስም የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለልን።
- የፍትሕ አካላት ለምሥረታችሁ እና ለእድገታችሁ ውለታ የከፈለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የቀደመ ውለታዋን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ ተጥሶ እና ፍትሕ ተጓድሎ በቤተ ክርስቲያነቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል በጽናት ከማውገዝ በተጨማሪ አጥፊዎችን ለፍትሕ በማቅረብ እና ተመጣጣኝ እና ለሌሎችም አስተማሪ የሆነ ውሳኔ በመስጠት እና በማሰጠት የራስዋየሆነ ተቋማዊ ሕልውና እና መዋቅር ያላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት እና ልእልና መከበር የበኩላችሁን ድርሻ ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ጥሪ ያስተላልፋል።
- በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የተከበረውን እና የተረጋገጠውን የእምነት ተቋማት ነፃነት እና ሉዓላዊ ክብር በሚጋፋ ሁኔታ እየተፈጸሙ ያሉት የመብት ጥሰቶች እና የጥፋት በደሎችን የማረም እና ከመፈጸማቸውም በፊት የመከላከል ኃላፊነት ያለባችሁ በየደረጃው የምትገኙ የመንግሥት አካላት በሕገ መንግሥቱ የተጣለባችሁን ሕግን የማስከበር አደራና ኃላፊነት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መብት የማስጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስያኒቱን ልዕልና እና ክብር እንድታስጠብቁ በቅድስት ቤተ ክርስያናችን ስም ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎባችኋል በማለት በጽኑ ያሳስባል፤
- አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ ሰላም እና ፍቅርን በመስበክ እና በተግባር በመፈጸም ለሀገር እና ለመላው ዓለም አርኣያ የሆነችውን እናት ቤተ ክርስቲያን ያለ ስሟ ስም፣ ያለግብረዋ ግብር በመስጠት በተለይም የተከበረውን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ባለውለታ የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳገለልችው እና አቅዳ እንደበደለቸው ለማስመሰል እና ለማስቆጠር አቅደው ቤተ ክርስያኒቱን እና ሀገርን ለመከፋፈል ድብቅ አጀንዳ ይዘው በተነሡ ግለሰቦች እና ቡድኖች አለአግባብ እየተሠራጨ ያለው አፍራሽ እና ከፋፋይ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም እና ድምጽ ካለመሆኑ በተጨማሪ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ እንደሚያስረዳን ሕገ ወጦቹ ግለሰቦቹ እና ቡድኖች የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የሚያገለግለው እና የሚባርከው መንፈሳዊ አባት እንደሌለው ቢገልጹም እንኳንስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ነፃነት ከተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ የተገኙት እና ነፍሳቸውን ሳይሳሱ በሰማዕትነት ዋጋ የከፈሉትን የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ታሪክ የማይረሳውን ውለታ የዘነጋ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት በመዓርገ ጵጵስና ሹማ በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት ለሐዋርያ አገልግሎት አሠማርታ መላውን የክልሉን ሕዝበ ክርስቲያን በማገልገል ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ ለክልሉ ሰላም እና አንድነት ዋጋ በመክፈል ላይ የሚገኙትን ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙትን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና በእነሱ የሚመሩ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ያሉ በርካታ ጽ/ቤቶች ከዐሥራ አምስት የሚበልጡ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶች እና መዋቅሮችን ፈጽሞ የካደ አድርጎት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ እያወገዘ በዚህ አድርጎት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከዚህ አድርጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል።
- የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የኦሮሞ ሕዝብ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ እንደ ትናንቱ ሁሉ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ በተቻላት አቅም መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ለማድረግ የጸሎት፣ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እና ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጎም እና በማዘጋጀት፣ ከአምስት በላይ የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ አንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅን በጀት መድባ በማቋቋም መላውን የኦሮሞ ብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ስታገለገል የቆየችውን እና ያላቸውን ወደ ፊትም ዘመኑን በዋጀ መልኩ አጠናክራ የምታገለግለውን እናት ቤተ ክርስያናችሁ መሆኗን አውቃችሁ አንድነታችሁን እና ፍቅረ ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመከፋፈል የተነሡትን የጥፋት ኃይሎች በጽናት በመቃወምና አንድነት እና ፍቅራችሁን አጠናክራችሁ ቤተ ክርስያናችሁን እና ሃይማኖታችሁን ከጥፋት ኃይሎች ትጠብቁ እና ትንከባከቡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል።
- አዲስ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚል መዋቅር በራሳቸው ሥልጣን መሥርተው በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ በሰጣቸው እድል ቀርበው የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም ወቅት ጥያቄውን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን ቀደም በኮሚቴ ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቶበት እያለ ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠው በማስመሰል ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ አዲስ መዋቅር ፈጥረው መግለጫ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን አምነው ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 የተቀጠሩ ቢሆንም በዕለቱ የኮሚቴው ዋና ተጠሪ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ያልተገኙ ሲሆን 2 የኮሚቴው አባላት ብቻ ከተሰጣቸው ሰዓት አሳልፈው ከመምጣታቸውን በላይ 2ቱ ግለሰቦች በጽሑፍ ባቀረቡት ምላሽ በሕገወጥ አቋማቸው የፀኑ መሆናቸውን የገለጹ በመሆኑ የግለሰቦቹ እንቅስቃሴም ሆነ የኦሮሞ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተብሎ የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን አውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተ ክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ትጠብቁ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- ከዚህ በላይ በተገለጸው መሠረት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልናም ሆነ ከሕገ የመነጨ ሥልጣን ሳይኖራቸውና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሕግ የመነጨ መብት በመጋፋት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሎጎ /አርማ/፣ ማህተምና መጠሪያ ስያሜ መጠቀማቸው ሕገወጥ አድራጎት በመሆኑ የሚመለከታችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሎጎ /አርማ/ እና ማህተም እንዲሁም መጠሪያ ስያሜ መጠቀም የማይችሉ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምት በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ታስከብሩ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት እያሳሰበ፤ የጽ/ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያም በሕገወጦች ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ አዟል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በዝርዝር በተገለጹት የአቋም መግለጫዎችና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የተነሱ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሳት ቅዱስ ሲኖዶስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት በቢሯቸው ተወያይተዋል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በተደረገው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያለውን አቋምና ያከናወናቸውን ተግባራት አውስተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የተከናወኑ በጎ ተግባራትን በመዘርዘር ምስጋና አቅርበዋል።
በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በውይይቱ የተነሡ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሳት ጳጳሳቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የእርሳቸውም ሆነ የመንግሥታቸው ፍላጎት የተጠናከረች፣ ለሀገር ግንባታ የሚቻላትን ሁሉ የምታደርግና አንድነቷ የተጠበቀ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ማየት መሆኑን ገልጠዋል። የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድ መሆን ጥቅሙ ለእምነት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል።
የቀረቡት ችግሮች በለውጥ ውስጥ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያነሱ ሲሆን ዓይነታቸው ቢለያይም የተለያዩ የእምነት ተቋማት በለውጡ ሂደት ፈተና አጋጥመዋቸዋል፣ በመሆኑም ዕንቅፋት የሚፈጥሩትን አካላት መታገል ያለብን በጋራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የቀረቡትን ችግሮች በዝርዝር በማጥናትና በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመነጋገር በጋራ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል። በሀገር ላይ የሚደርሱ ጥፋቶች በሁሉም ላይ የሚደርሱ በመሆናቸው መንግሥትና የእምነት ተቋማት በጋራ በመሥራት መፍታት እንዳለባቸው ገልጠዋል።
በመጨረሻም የተፈጠሩትን ችግሮች የጋራ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ክብር በጠበቀ መልኩ በጋራ ለመፍታት ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ምንጭ፦ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስት ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ሌሎች ዜናዎች፦- ሀገሬን ምን ነካት? (አባይነህ ካሴ (ዲ/ን)) ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- አገራችን ዘመን ተሸጋሪ የሆኑ ቅርሶቿን ጠብቃ ለትውልድ ለማቆየት የአርክቴክቱና የአንጂነሩ ሚና ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
- ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከእልቂት ለማዳን ቆም ብለን በሰከነ ሁኔታ ማሰብና መራመድ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን ከእንግሊዝ ሀገር አቻው ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይና ከጣልያን የባህል ማዕከላትና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።
በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ረዳት ዳይሬክተር መ/ር ተመስገን ዮሐንስ ሙሉ ፕሮግራሙን የመሩት ሲሆን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ካፈራቸው ምሁራን አንዱ ናቸው።
በመርሐ ግብሩ መሠረት የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሲሆኑ በመግቢያ ንግግራቸው ላይ ኮሌጁ በመማር ማስተማሩ ሂደት ዛሬ ላይ ለመድረስ የነበሩትን ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለዩኒቨርሲቲ ደረጃ መድረሱ እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ዩኒቨርሲቲው አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዲደርስ ሌት ተቀን የሠሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን፣ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት፣ የቦርድ የሥራ አመራር አባላትና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
ከብፁዕነታቸው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኃይሉ ሀብቱ ናቸው።ተባባሪ ፕሮፌሰ ርኃይሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚገኙ አምስት ኮሌጆችና ት/ቤቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልፀው፥ ትምህርት ቤቱ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በማስተርስ ኦፍ አርትስ (M.A.) ዲግሪ ደረጃ የድኅረ ምረቃ ትምህርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። ፕሮግራሙን ለማጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜ ሁለት ዓመት መሆኑንና የአንደኛው ዓመት መርሐ ግብር ለተማሪዎች፦ (1) በኢትዮጵያ ታሪክ፣ (2) በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ (3) በብሔረሰቦች ወግና ሥርዓት ሰፊጥናትና ጥልቅ ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን በሁለተኛው መርሃ ግብርም፦ (1) በትውፊታዊ ሥነ መድኃኒት/ ሥነ ፈውስ፣ (2) በትውፊታዊ ሥርዓተ ሕግ፣ (3) በኢትዮጵያ ጥናት አውራ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያተኩሩ እንደሆኑ አብራርተዋል። የማስተማሪያ መደበኛ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም አገርኛ ቋንቋዎች ግዕዝን ጨምሮ እንደ አማራጭ ማስተማሪያ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ነፃነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ለአብነት ያህል በ17ኛው እና 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ እንደነ ወለተ ጴጥሮስ፣ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ማካኤልን የመሳሰሉ አባቶችና እናቶች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ሰማዕት ሆነዋል ብለዋል።
ከዚህ በመቀጠል የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ንግግር አድርገዋል። ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊያ ልሆኑ የትምህርት ተቅዋማትና ድርጅቶች የመጡትን እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ከልብ አመስግነዋል። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በመቀጠልም በፕሮግራሙ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙ እንግዶች ለዩኒቨርሲቲው ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦችና አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን ከቅድስት በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን የመጡ መምህር በዓሉን የሚገልጽ ቅኔ አቅርበዋል።
በመጨረሻም በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በብራና መጻሕፍት ዝግጅት ክፍል የሚዘጋጁትን የተለያዩ የብራና መጻሕፍት፣ ቀለምና የብራና መሣሪያዎችን በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ እንግዶች ጐብኝተዋል።
የቀድሞ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በ1935 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ካህናትንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ዘመናዊውንና የአብነት ትምህርታቸውን አስተባብረው እንዲይዙ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ኮሌጁ በዚህ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፥ በመቀጠልም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማዕረግ በማስተማር ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ዕጩዎችን ሲያበቃ ቆይቷል። የኮሌጅን ደረጃ በ1960 ዓ.ም. ካገኘ በኋላ ከሦስት ዓመት በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ ፋኩልቲ አካል ሆኖ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ዘልቋል። የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ፋኩልቲው ሲዘጋ በወቅቱ በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩት በሚፈልጉት የትምህርት መስክ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ መደረጉ ይታወሳል። መንፈሳዊ ኮሌጁ ተወርሶ አራት ኪሎ ከጎኑ የሚገኘው የሳይንስ ፋኩልቲ ለራሱ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲጠቀምበት ተደረገ። በ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሌጁ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመልሶ በነበረው ዕውቅናና ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሒደት ሲያከናውን ቆይቷል። ኮሌጁ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ከፍተኛ የሆኑ የልማት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
መንፈሳዊ ኮሌጁ እስከ አሁን ድረስ ከ3,500 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን ከዚሁ በበለጠ መልኩ እንዲጠናከርና የቤተክርስቲያኒቱ የጥናትና የምርምር ተቅዋም እንዲሆን መሉ ዝግጁቱን አጠናቅቆ በመጨረሱ በአሁኑ ሰዓት በቲዮሎጂ (ስነ መለኮት) የትምህርት ዘርፍ በዶክትሬት፣ በማስተርስ ዲግሪ፤ በመደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በማታው ተከታታይ እና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ዲፕሎማ፤ በግእዝቋንቋ (extension) ዲግሪና ዲፕሎማ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።
ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ ወደ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል። በዚሁም መሠረት ከኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚጀምረው የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት በቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊና ሥነ ሰብእ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ተናግረዋል።
ደሴ (ኢዜአ) – የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከያዝነው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የግዕዝ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመጀመር በቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ዙሪያ ከምሁራንና ባለድርሻ አካላት ጋር መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።
በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊና ሥነ ሰብእ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ዶክተር እንድሪስ አብይ እንዳስረዱት ግዕዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የላቀ ሥፍራ አለው።
ትምህርቱን ለማስጀመር አራት መምህራን የተቀጠሩ ሲሆን፣ እስከ 18 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ አገር በቀል ህክምናና መድኃኒት፣ የሥነ ከዋክብት ቀመርና የቀን አቆጣጠር፣ የባህልና የህግ ሥርዓቶች ተካተውበታል።
ትምህርቱ በቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል ዶክተር እንድሪስ ተናግረዋል።
በቋንቋው በፍልስፍና፣ በህክምና፣ በሥነ ከዋክብትና በመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች በርካታ ጽሁፎች ቢጻፉም፤ ህዝቡንም ሆነ አገሪቱን መጠቀም የሚገባቸውን ያህል አልተጠቀሙበትም። ዕውቀቱም ለሌሎች ሳይተላለፍ ለረጅም ዓመታት መቆየቱን ተጠሪው ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ትምህርት ክፍል አስተባባሪና መምህር አቶ ዘላለም ጌትነት በበኩላቸው የመጥፋት አደጋ ላይ የሚገኘውንና የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ቋንቋ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መስጠቱ ታሪክን ከማቆየትና እውቀትን ከማጋራት አንጻር ጠቀሜታው ጉልህ ነው ብለዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ በተለይ ቋንቋው ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ያለውን ቁርኝት በሚያሳይ መልኩ ቢቀረጽ የተሻለ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህርና የሥነ ጥበባት ኮሌጅ የድህረ ምረቃ ተባባሪ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ ”ዩኒቨርሲቲው የአገር ሃብት የሆነውን የግዕዝ ቋንቋ ለማስተማር መወሰኑ የሚያስመሰግነውና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ኃላፊነት እንዲወስዱ መነቃቃትን የሚፈጥርላቸው ነው” ብለዋል።
ግዕዝ ኢትዮጵያን የምናውቅበት የዕውቀት ምንጭ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህንን መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ፋይዳ ያለውን የዕውቀት ዘርፍ በማስተዋወቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የወሎ ዩንቨርሲቲም ተማሪዎችን ካስመረቀ በኋላ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከር እንዳለበትም አቶ አሰፋ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መአምራን ብርሃነሕይወት እውነቱ ቋንቋው በዩኒቨርሲቲው መሰጠቱ በርካታ አገራዊ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ መንፈሳዊና ዓለማዊ ሥራዎች፣ ምርምርን የሚጋብዙ ሥራዎች ለማወቅና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በአዲስ መንፈስ ለማስቀጠል ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
የአብነት ተማሪዎች እንቅስቃሴ መዳከም ቋንቋውን እንዳዳከመው አውስተው፣ የወሎ ዩንቨርሲቲ የጀመረው ጥረት እንዲሳካ ቤተክርስቲያኗ ድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።ከዚህ ጋር በተያያዘ በ1999 ዓ.ም. የተመሠረተው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የቅበላ አቅም ዘንድሮ ከ20 ሺህ በላይ ደርሷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
Search Results for 'የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን'
Viewing 12 results - 1 through 12 (of 12 total)
Viewing 12 results - 1 through 12 (of 12 total)