Forum Replies Created
-
AuthorPosts
-
SemonegnaKeymaster
ከክረምቱ ወቅት መግባት ጋር ተያይዞ መንገዶች ላይ የሚደረጉ ማንኛውም ቁፋሮዎች እንደማይከናወኑ
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) አስታወቀአዲስ አበባ (አአመባ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) የክረምት መግባት ጋር በተያያዘ በመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚካሄዱ የቁፋሮ ሥራዎችን ከግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማስቆሙን ገልፆ፥ ለተግባራዊነቱም የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
የክረምት ወራት መግባትን ተከትሎ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትና ግለሰቦች ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚቀርቡለትን የመንገድ መሠረተ ልማት ቁፋሮ ፈቃድ ማቆሙ ይታወቃል።
ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የቁፋሮ ፈቃድ ይሰጥባቸው ከነበሩት ውስጥ የመጠጥ ውሃ ዝርጋታ፣ የዝናብ ውሃ ከቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ መስመር (drainage system) ጋር ይገናኝልኝ ጥያቄ፣ የፍሳሽ መስመር ለማገናኘት፣ የመግቢያ መውጫ ይከፈትልንና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማት የሚቀርቡ የመንገድ መቁረጥ ፈቃድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በክረምት የሚደረጉ ቁፋሮዎች በነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እክል እንዳይፈጥሩ፣ ከአደጋ ለመጠበቅና የትራፊክ ፍሰት እንዳይስተጓጎል የቁፋሮና የአስፋልት መቁረጥ ፍቃድ መስጠት እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማቆሙን አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በቁጥር 443 የሚሆኑ ከተለያዩ አካላት የቀረቡለትን የመንገድ መቁረጥ ጥያቄ ፍቃድ ሰጥቷል። በተጨማሪም የመንገድ ሃብት ላይ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል የሚያስችል አሠራርን በመዘርጋት እንቅስቃሴ እያደረግ ይገኛል።
በመንገድ ሀብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቅረፍና መንገዶችን ለመንከባከብ ባለስልጣኑ ከመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር እና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማትና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናቦ በመሥራት ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡ መንገዶችን ከሚደርስባቸው የተለያዩ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም የመንገድ መሠረተ ልማቶች በሚፈለገው መጠን ከጉዳት ተጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማስቻሉም ባለፈ የመንገዶችን የጥገና ወጪ በመቀነስ የጎላ አስተዋፅኦ አድርጓል።
በመጨረሻም ሕብረተሰቡ የተገነቡ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከመንገድ መብት ጥሰቶችና ከሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት በመከላከልና በመጠበቅ ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከ375.2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የግንባታ ግብዓቶችን አምርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉንአስታውቋል።
ባለስልጣኑ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በ134.9 ሚሊዮን የካባ፣ በ73.7 ሚሊዮን ብር ሲሚንቶ፣ በ166.6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአስፋልት ምርቶችን አምርቶ ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ያሰራጨ ሲሆን፥ አጠቃላይም የዕቅዱን 89 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል።
በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በራስ አቅም ተመርተው ሥራ ላይ ከሚውሉ የተለያዩ ምርቶች መካከል፥ ገረገንቲ፣ ቤዝ ኮርስ (base course)፣ ሰብቤዝ (subbase)፣ ጠጠር፣ ነጭ ድንጋይ፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቱቦዎች፣ ሲሚንቶ ኮንክሪት፣ ከርብስቶን (curbstone)፣ የማንሆል ክዳን (manhole cover)፣ ፍርግርግ፣ ቦላርድ (bollard)፣ ታይልስ (tiles)፣ ባይንደር ሚክስ (binder mix)፣ ሰርፊስ ሚክስ (surface mix) የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ባለስልጣኑ የግንባታ ግብዓቶችን በራሱ አቅም ማምረት መቻሉ በራሱ አቅም እየገነባቸው ለሚገኙ የግንባታና የጥገና ሥራዎች የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቀጣይም የግብዓት ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠርም አሁን ላይ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ማሽነሪዎችን በመግዛት በትጋት እየሠራ ይገኛል።
ምንጭ፦ አአመባ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 2, 2020 at 1:41 am in reply to: ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ #15252SemonegnaKeymasterየኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ስርጭት እጅግ ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል። የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀቡ ይስተዋላል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰብሳቢነት ሥራውን የሚከውነው እና ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን የሚያስተባብረው የሚኒስቴሮች ኮሚቴ፥ ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በወቅታዊው ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። የጤና ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አካሄድ በተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፥ እስከ አሁን [ሃምሌ 25 ቀን] ድረስ በኢትዮጵያ 17,500 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል፣ 84 በመቶው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን፣ ከመመርመራቸው በፊት በቫይረሱ የመያዝ ምልክቶች አልታዩባቸውም። ይህም ምልክት ሳይታይባቸው ቫይረሱን የሚያስተላልፉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ያመላክታል።
የትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ትምህርት ሁኔታዎችን መረጃ አጠቃልሎ አቅርቧል። በዚህም መሠረት፥ ትምህርት ቤቶች [በ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን] ተመልሰው ከመከፈታቸው በፊት ሊተኮርባቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አመላክተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የቫይረሱ የስርጭት መጠን መቀነስ ዋነኛው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምርመራ መጠንን ከፍ ማድረግ የወረርሽኙን አካሄድ ለመረዳት ወሳኝ ተግባር መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል። ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ እንዲካሄድም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ADDIS ABABA (Semonegna) – The Office of Prime Minister – Ethiopia issued a press statement on 1st August 2020 stating that the country will carry out nationwide mass testing of COVID-19 for one month amid the surge of COVID-19 cases in the country, especially in recent weeks. The press statement reads as follows.
Over the past couple of weeks there has been a noticeable increase in the number of positive COVID-19 cases. The ministerial committee overseeing prevention activities and chaired by Prime Minister Abiy Ahmed, met this afternoon to discuss the current status, where the Ministers of Health and Education presented on the international and domestic trends of the pandemic.
According to Ministry of Health reports, there are currently 17,500 positive COVID-19 cases confirmed [in the country] as of date with 70% located in Addis Ababa. While 84% of positive cases are above the age of 50 years, 92% of positive cases showed no symptoms prior to testing, which indicates the presence of many silent spreaders.
The Minister for Education, combining data for primary, secondary and tertiary education, highlighted that a number of issues need to be factored before considering opening schools [for the coming academic year], with declining rate of cases being the key number one factor to enable an opening decision.
Prime Minister Abiy Ahmed emphasized the critical importance of increased testing to understand the trends better for effective decision making, and gave direction for the launch of a one-month nationwide mass testing.
SemonegnaKeymasterደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ፤ ለመጪው የትምህርት ዘመን የቅድመ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።
ደብረ ብርሀን (ኢዜአ/ሰሞነኛ) – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በ2ኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 61 ተማሪዎች ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ አንዳርጌ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በትምህርት ዘርፉ ላይ በርካታ እንቅፋቶች አጋጥመዋል። የመማር ማስተማሩ እንዲቋረጥ በመደረጉም ተማሪዎችን አቅም በፈቀደ መንገድ በቴክኖሎጂ ለማገዝ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይም የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቴክኖሎጂ እንዲከታተሉ በማድረግ ለምረቃ ቀናቸው ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ያስመረቃቸው ተማሪዎችም በቀን፣ በማታ እና በሳምንታዊ የትምህርት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ተከታትለው ማጠናቀቅ የቻሉ መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹ በጤና፣ በግብርና እና ተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ቀመር እና የቢዝነስ የትምህርት መስክን ጨምሮ በ21 የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከልም 52ቱ ሴቶች መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ አስታውቀዋል።
አሁን ላይ ሀገሪቱ የተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች ውስጥ መሆኗን አመልክተው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ ከገጠማት ችግር ፈጥና እንድትወጣ በቆይታቸው ወቅት ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዶ/ር ደረጀ አሳስበዋል።
በአካውንቲንግና ፋይናስ የትምህርት ዘርፍ 3.91 በማምጣት የተመረቁት አቶ ገብረሀና ደበበ በበሰጡት አስተያየት በተመረቁበት ዘርፍ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በእናቶች እና ሕፃናት ጤና የተመረቁት ወ/ሮ ዘነቡ አጎናፍር በበኩላቸው፥ ሕብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።
ሐምሌ 21 ቀን በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት በኮሮና ቨይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተወካይ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት ብቻ ተገኝተው የምረቃ መረሐ ግብሩን ተከታትለዋል።
ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ ዩኒቨርሲቲው ለ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል።
የ2013 ዓ.ም. የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀርቦ ነበር። በፕሬዝዳንቱ የቀረበው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በ5 ዋና ዋና ዘርፎች ተከፍለዋል። በአስተዳደር፣ በፕ/ጽ/ቤት፣ በአካዳሚክ፣ በጥናትና ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት እና በቢዝነስና ልማት ዘርፍ የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን በጥልቀት የመረመረ እቅድ እንደነበረ ለማየት ተችሏል።
ዶ/ር ንጉስ ታደሰ እንዳቀረቡት፥ በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ዝርዝር እና የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳን አስቀምጠዋል። የቀጣይ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮች ተለይተው ጥናት ተካሂዷል ብለዋል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ያለው የግንባታ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱና እያለቁ መሆናቸውንም ዶ/ር ንጉስ ገልጸዋል።
በዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ላይ መከናወን አለባቸው ከተባሉት ዋና ዋና ተግባራት መካከል፥ ለሀኪም ግዛው መታሰቢያ ሆስፒታልና ለአዲሱ ማስተማሪያ ካምፓስ የውስጥ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲ (applied university) ደረጃን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል (center of excellence) የሚያዘጋጅ ቡድን ማዋቀርና ወደ ሥራ ማስገባት፤ የምኒልክ የቴክኖሎጂ ካምፓስን የዲዛይን፣ የካሳ ክፍያና ሌሎች ሥራዎች መሥራት፣ የአካዳሚክ አመራሩን መገምገምና ጊዜያቸው ያጠናቀቁ አመራሮች በአዲስ መተካት፣ የተጀመሩትን የጥናትና ምርምር ሥራ ማስቀጠል፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተዘጋጀውን የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ በቁሳቁስና በሰው ኃይል ማሟላት እና በ2013 ዓ.ም ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት ማድረግና የተስተጓጎለውን ትምህርት በአጭር ጊዜ ለማካካስ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
በመቀጠልም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በዕቅዱ ላይ ቢካተቱ ያሏቸውን ሀሳቦችና ትኩረት የሚያሻቸውን ነጥቦች ላይ ሀሳብና አስተያየት ሰጥተዋል።
የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው፥ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዙ ምርምሮች እየተካሄዱ እንደሆነና የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርን ለ3ኛ ጊዜ ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቀድሞ ይከናወኑ የነበሩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።
የአስተዳርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ አጅቤ እንዳሉት፥ በዝግጅት ምዕራፍ እቅድ በየሥራ ዘርፉ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ተግባራትን እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ተወያይቶ ለተግባራዊነቱ እንዲሰራ ሁሉም አመራር የሚጠበቅበትን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ምንጮች፦ ኢዜአ/ ዩኒቨርሲቲው
SemonegnaKeymasterከ19.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 12 መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል ውል ስምምነት ፊርማ ተካሄደ
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንአዲስ አበባ (ኢመባ) – የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢመባ) ከ19.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 12 መንገዶችን በአስፋልት ደረጃ ለመገንባት የሚያስችል ውል ስምምነት ፊርማ ከተለያዩ ሀገር በቀል እና የውጭ ተቋራጮች ጋር አካሄደ።
አሥራ ሁለቱ የሚፈረሙት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በደምሩ 825.23 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያላቸው ሲሆን፥ ለግንባታቸው የሚወጣው ወጪ የሚሸፈነው የአስሩን መንገዶች በኢትዮጵያ መንግሥት፣ የሁለቱን መንገዶች ደግሞ ከዓለም ባንክ (World Bank) በተገኘ ብድር ነው። የውል ስምምነት ከፈጸሙት የሥራ ተቋራጮች መካከል ስድስቱ አገር በቀል የሥራ ተቋራጮች ሲሆኑ፥ የተቀሩት አራቱ አለም አቀፍ የውጭ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሰጠው መግለጫ፥ መንገዶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንደመንገዶቹ ሁኔታ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር ጀምሮ እስከ አራት ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
- የአስራ ሁለቱን የመንገድ ፕሮጀክቶች ዝርዝር እና እያንዳንዱን የመንገድ ፕሮጀክት ለመገንባት ያሸነፈውን ተቋራጭ ዝርዝር ለማየት እዚህ ጋር ይጫኑ።
የግንባታ ፕሮጀክቶቹ የመንገድ ግራና ቀኝ ትከሻን ጨምሮ በገጠር በአማካይ ከስምንት እስከ አስር ሜትር ስፋት ሲኖራቸው፥ በከተማ ውስጥ የሚገነቡት ምንገዶች ተጨማሪ ስፋት እንዲኖራቸው ተደርገው የሚገነቡ ይሆናል። በተጨማሪም ግንባታው የአነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች እና ድልድዮችንም አካቷል።
የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ሕብረተሰብ በቀላሉ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ከዚህም ባለፈ አንድን ክልል ከሌላ ክልል፣ እንዲሁም በየክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ዞኖችንና ወረዳዎችን እርስ በእርስ የሚያስተሳስሩ ይሆናሉ። ከተፈረሙት መንገዶች መካከልም ወደ ጎረቤት አገር የሚያዘልቁ መንገዶችም በመኖራቸው አገራዊ ፋይዳቸው ላቅ ያለ እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መግለጫ ያስረዳል።
መንገዶቹ የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ጊዜና ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሱ ከመሆኑም በተጨማሪ የምርትና የሸቀጥ ልውውጥ ያለምንም እንግልት በቀላሉ እንዲከናወን ከማድረግ አኳያ የተፈረሙት መንገዶች ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል።
እነዚህ መንገዶች በአገሪቱ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም መንግሥት ከያዘው የድህነት ቅነሳ ስልት (poverty reduction strategy) አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይታመናል። ስለሆነም የመንገድ ኘሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቁ በአካባቢው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጉዳዮች ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያሳስባል።
ምንጭ፦ ኢመባ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።
ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterዲላ ዩኒቨርሲቲ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የሥነ ሕዝብ እና የጤና ምርምር ማዕከል ተመረቀ
ዲላ (ኢዜአ) – ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በወናጎ ወረዳ ያስገነባው የሥነ ሕዝብ እና የጤና ምርምር ማዕከል ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ማዕከሉ፥ ከNorwegian Programme for Capacity Development in Higher Education and Research for Development (NORHED) ጋር በመተባበር በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የተገነባ ሲሆን፥ በዋናነት በአከባቢው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ መጠጋጋት (overpopulation) የሚያስከትለውን ችግር በምርምርና ጥናት ለመቅረፍ ይሠራል። እንዲሁም በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ እና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ምርምር በማካሄድና በማስተማር ሕብረተሰቡን ለማገዝ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ ለወጣቶች የውይይት ዕድል የሚፈጥርና ዕውቀት የሚገበዩበት ይሆናል ነው ያሉት። በቀጣይ የሰው ኃይልና ግብዓቶችን በማሟላት፣ የምርምር ሥራ ለሚሰማሩ ምሁራን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን አስተዳደሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው፥ በወናጎ ወረዳ በአንድ ኪሎ ሜትር ካሬ ውስጥ ከ1,200 በላይ (>1,200/km2) ሕዝብ የሚኖርበትና ከፍተኛ ጥግግት (overpopulation) እንዳለ ገልጸዋል። በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠርም ሆነ በጥግግቱ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን በምርምር ለመለየት የማዕከሉ መገንባት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ማዕከሉ የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን ወደ ፊት ዩኒቨርሲቲው ለሚሰራው የምርምር ሥራ ሕብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የሥነ ሕዝብ እና የጤና ምርምር ማዕከሉ በጤናና በሥነ ተዋልዶ የምርምር መረጃዎች ምንጭ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን በአካባቢ ለሚገኘው ሕብረተሰብና ለጤና ተቋማት ለማድረስ የሚረዳ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሣይንስ ኮሌጅ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሰላማዊት አየለ ናቸው።
በሥነ ተዋልዶ መስክ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ የምርምር ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ ጠቀሜታው ከዩኒቨርሲቲውና ከማኅበረሰቡ አልፎ ለሀገር የጎላ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
ለግንባታ የፈጀው አጠቃላይ ካፒታል 4.9 ሚሊዮን ብር በላይ እንደደሆነ የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ኢ/ር በፍቃዱ መኩሪያ ተናግረዋል። ከምረቃው ሥነ ሥርዓት ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲውና የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ አመራሮች የሁለተኛውን አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በማስታከክ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አካሔደዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 18, 2020 at 12:00 am in reply to: ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ #14832SemonegnaKeymasterወሎ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ድጋፍ የተቋቋመው የባቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ተመረቀ
(ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – ከአፋር ክልልና ከጅቡቲ የሚመጡ መንገደኞችን ለይቶ በማቆየት የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል በባቲ ወረዳ የተቋቋመው የለይቶ ማቆያ ማዕከል (quarantine center) ተመርቋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ድጋፍ የተቋቋመው የባቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ከሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ማዕከሉን የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሚያ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ የባቲ ወረዳና ከተማ አመራሮች፣ በጎ ፍቃደኞችና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ተመርቋል።
የቅኝት አምባ፣ የወሎየነት ተምሳሌትና የንግድ የመተላለፊያ አውድ ባቲ በታሪክ አጋጣሚ ከጅቡቲ አፋርን አቋርጠው በሚመጡ መንገደኞች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መተላለፊያ ኮሪደር ልትሆን ትችላለች የሚል ስጋት ተጭኖባታል። ከጅቡቲና አፋር ክልል እያቋረጡ የሚመጡ መንገደኞች ምርመራና ክትትል ሳይደርግላቸው ከመሀል ሀገር እንዳይገቡ ለማድረግ የለይቶ ማቆያ ማዕከል በባቲ ወረዳ ማቋቋም ተገቢ መሆኑን በጥናት ለይተናል ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ባቲ ወረዳን ማዳን ወሎን፣ ሰሜን ሸዋን በአጠቃላይ ከቫይረስ ስርጭት ሀገርን መታደግ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ የኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞንና የባቲ ወረዳ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸውን የለይቶ ማቆያ ቁሳቁስ በቀናት ውስጥ ሁሉን ነገር አዘጋጅተው ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጋቸው የአመራሩ፣ የኮሚቴውና የማኅበረሰቡ የቅንጅት ውጤት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴና ኮምቦልቻ ካቋቋመው የለይቶ ማቆያ ማዕከል እኩል ግብአቶችንና ቁሳቁሶችን በማሟላት ሦስተኛው ማዕከል እንዲሆን የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ እንሞክራለን ያለት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አማረ ምትኩ (ዶ/ር) ባቲ ወረዳ ከጅቡቲና አፋር የሚመጡ የከባድ መኪና ሹፌሮችና መንገደኞች መተላለፊያ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ የወሎ ሕዝብ አምባሳደርነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው ያሉት የኦሮሚያ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀሰን ዩኒቨርሲቲው የዞናችንን አቅም መሠረት ያደረጉ የልማት ሥራዎችን ከመሥራትና ከማስተዋወቅ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለከሚሴና ባቲ ወረዳዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከሎች ያደረገው ድጋፍ በታሪክ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘከር ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የባቲ ወረዳ ለይቶ ማቆያ ማዕከልን ለማቋቋም ከ5 መቶ ሺ ብር በላይ የሚያወጡ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊት ዘግቦ ነበር።
ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterሕብረት ባንክ አዲሱን መለያ እና አርማውን ይፋ አደረገ
ሕብረት ባንክ የተገነባበትን የሕብረትና የአካታችነት መርሁን የሚያጐላለትን አዲስ መለያ እና አርማ ይፋ አደረገ። ባንኩ አዲሱን መለያ ቀርጾ ያጠናቀቀው ዓለም-አቀፍ ደረጃ ያለውን የባንኩን የጨረታ መስፈርቶች በሟሟላት ከተመረጠው ስቱዲዩኔት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከተሰኘ ሀገር በቀል አማካሪ ድርጅት ጋር በመሆን ነው። እንደ ምንጊዜውም ባንኩ እንዲህ ዓለም-አቀፋዊ ብቃት ካላቸው ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር በመሥራት ይህንን የመሰሉ ትልልቅ ፕሮጀክት ሊያሳካ ችሏል። በተመሳሳይ ሕብረት ባንክ በቅርቡ የኮርባንኪንግ እና የኦንላይን ፕላትፎርም በራሱ የየመረጃ ቴክኖሎጂ (information technology) ቡድን ማዘመኑ የሚታወስ ነው።
አዲሱ የባንኩ መለያ ሕብረት ባንክ ከደንበኞቹ፣ ከአጋሮቹና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትስስር እንዲያንፀባርቅ ሆኖ የተቀረፀ ሲሆን፤ በሕብረት እና በጋራ እድገት ላይ የተመሠረተ መስተጋብር ወይም “eco-system” ለመፍጠር ባንኩ የወሰደውን ቁርጠኝነትም ጭምር የሚያረጋግጥ ነው። ባንኩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ “በእርግጥም የስኬታችን ምንጭ ደንበኞቻችን እና አጋሮቻችን ናቸው። ‘በሕብረት እንደግ’ የሚለው የባንካችን መሪ ቃልም ለዚህ እውነት እማኝ ነውና በጐላ እና በደመቀ መልኩ መገለጥ እና መታየት ይገባዋል” ብሏል።
መግለጫው ሲቀጥል እንደሚከተለው ይነበባል፦
ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አዲሱ የባንካችን መለያ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከቴክኖሎጂ ጋር ያለንን ቁርኝት ከግንዛቤ ውስጥ የከተተና፣ ከዚህ በስተጀርባ ውስብስብ የሚመስሉ አያሌ ጉዳዮች በመላ የሚቃለሉበትን መንገድ የሚጠቁም ብሎም ወደፊት ለመገስገስ የምንገባውን ቃልኪዳን የሚያረጋግጥ ነው።
ሕብረት ባንክ ያካበተውን የቴክኖሎጂ ብቃት፣ የደንበኞቹንና የአጋሮቹን አብሮነት እንዲሁም በፋይናንሱ ዘርፍ ያዳበረውን ልምድ በመሰነቁ የተሻለ ነገን በሕብረት ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ ጉልበት እንዳለው እሙን ነው።
አዲሱ የሕብረት ባንክ መለያ የተለያዩ ሕብረ ቀለማትን ያካተተ ሲሆን ይህም የሕብረትን ምንነት የሚያንጸባርቅ ነው። ቀለማቱ ዘመናዊነትን፣ ሙያዊ ጨዋነትንና፣ መስህብን በማመላከት ዕይታን የሚስቡና በቀላሉ ተለይተው የሚታወቁ ናቸው ።
የአዲሱ የባንካችን መለያ እና አርማ ፍሬ ሀሳብ ‹‹ሕብረት›› ከሚለው ስማችን የተወሰደ ሲሆን መልዕክቱም ትብብርን፣ ሕብርን፣ አብሮነትን፣ አጋርነትን፣ ቅንጅትንና መተጋገዝን የሚገልጽነው።
ይኽንን ምከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ባንክ ስማችን በዓለም-አቀፍ ደረጃ “ሕብረት ባንክ” በሚለው ስያሜ ብቻ የሚወከል ስለሆነ እንደከዚህ ቀደሙ “ዩናይትድ ባንክ” የሚለውን የእንግሊዝኛ ትርጓሜ እንደአማራጭ ስያሜ በቀጣይ የማንጠቀም መሆኑን እናሳውቃለን። የአዲሱ መለያ ቃል-ኪዳንም (brand promise) “በሕብረት የተሻለ ነገን እንገነባለን” የሚል ነው። ይህም ቃልኪዳን ውስጣችንን የሚያነቃቃና ከጅምሩ የተመሰረትንለትንና አሁንም የምንጠቀምበትን መሪ ቃል (tag line) “በሕብረት እንደግ” የሚለውን በሕብረት የማደግ ዓላማ የሚያጸና ነው።
ምንጭ፦ ሕብረት ባንክ
June 4, 2020 at 12:26 am in reply to: ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ #14696SemonegnaKeymasterየኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከ220 በላይ የሕክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ዝግጁ ተደርገዋል ― የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት) – በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ ከ220 በላይ የሕክምናና የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 የተቋማት ዝግጁነት ክፍል አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ መሠለ እንደገለጹት፥ የኮሮና ቫይረስ በቻይና ዉሃን ከተማ (Wuhan) ከተከሰተ ጀምሮ በሀገራችንም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህም ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች የሕክምና መስጫ ማዕከል (treatment centers)፣ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው እስኪታወቅ ተለይተው የሚቆዩበት (isolation centers) እንዲሁም ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ግለሰብ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ መግባት እንዳለበት በተላለፈው ውሳኔ መሠረት የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን (quarantine centers) መለየትና ዝግጁ ማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው።
በዚህም መሠረት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባና በክልሎች ሙሉ በሙሉ ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ጨምሮ ከ10,000 በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ40 በላይ ማዕከሎች (treatment centers) ዝግጁ የሆኑ ሲሆን ከ15,000 በላይ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ100 የሚበልጡ የለይቶ ማቆያዎች (isolation centers) እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ የለይቶ ማቆያዎች (quarantine center) ተዘጋጅተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ብሔራዊ የድንገተኛ ማዕከል የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር የውሀ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (WASH) ክፍል አስተባባሪ ወ/ሮ ኢክረም ሬድዋን እንደተናገሩት፥ ለኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ያሉ የውሀ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (WASH) እንዲሁም ኢንፌክሽንን ከመከላከልንና መቆጣጠር አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ለመሙላት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህም ከውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሀ ልማት ኮሚሽን እና ከአጋር ድርጅቶች በተደረጉ ድጋፎች ሲሆን የውሀ መቆራረጥና እጥረት ያለባቸውን ተቋማት ክፍተት መሙላት፤ የውሀ አቅርቦት መቆራረጥን ለመቀነስ የውሀ ታንከሮችና ፓምፖችን መግጠም፣ ውሀን በትራክ ማቅረብ እንዲሁም የእጅ መታጠቢያ እጥረት ባለባቸው የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ከእጅ ንክኪ የጸዱ በእግር መከፈት የሚችሉ ተንቀሳቃሽ የእጅ መታጠቢያዎች እንዲተከሉ ተደርጓል።
በተጨማሪም ለሁሉም ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ለሚገኙ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ባለሙያዎች ተመድበዋል። ለነዚህ ባለሙያዎችም የኮቪድ-19 የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ባለሙያዎቹም በአጠቃላይ የሚከናወኑ ተግባራት ኢንፌክሽንን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር በአግባቡ እየተካሄዱ መሆናቸውን በየዕለቱ ይከታላሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚሰሩ ሥራዎች ባሻገር ህብረተሰቡ የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለበሽታው ያለመስፋፋት ወሳኝ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችን እና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 በመደወል ወይም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢሜል አድራሻ ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
SemonegnaKeymasterቱሉሞዬ እና ኮርቤቲ የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተከናወነ
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የፈረንሳዩ ሜሪድየም (Meridiam) ኢንቨስትመንት ኩባንያ የከርሰ ምድር እንፋሎት ኃይል (geothermal energy) ማመንጫ ገንብቶ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በተካሄደው ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉሞዬ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ሚስተር ማቲው ፒለር (Mathieu Peller) እና የኮርቤቲ ተወካይ ናቸው።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት በኃይል ልማት ዘርፍ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮችን በማስፋት የግል አልሚዎችን ማሳተፍ ተጀምሯል። አሁን የተፈረመው ስምምነትም ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ ወደ ግንባታ እንዲገባ ከግል አልሚዎች ጋር ድርድር ሲያካሂዱ የቆዩትን አባላት አመስግነዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ስብጥሩን በማመጣጠን የሀገሪቱን ኢነርጂ የማምረት አቅም እንደሚያሳድግ በመግለፅ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚን የፈጠረ እንደሆነም ጠቁመዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ከሆነ ሥምምነቱ በሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ የግል አልሚዎችም ትልቅ ዕድል እንደሚከፍትላቸው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከኩባንያው ጋር የነበረው ድርድር ተጠናቆ ስምምነት ላይ መደረሱ እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው የግል አልሚዎች ተሳትፎ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚያደርገው የሃይል አቅርቦትና ስብጥር የሚግዝ መሆኑን በመግለጽ ሌሎችም የግል አልሚዎች በዚህ ረገድ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉሞዬ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ሚስተር ማቲው ፒለር (Mathieu Peller) በበኩላቸው በአፍሪካ የሜሪድየም ኢንቨስመንት ኩባንያ ዋና መቀመጫን አዲስ አበባ ያደረጉት ኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት በመሆኑ ነው ብለዋል። አሁን ከጀመሩት የከርሰ ምድር እንፋሎት በተጨማሪ በትራንስፖርት እና በተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችም መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሰፊ ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ቱሉሞዬ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን ግንባታውም በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታም 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ግንባታውም እ.ኤ.አ. በ2023 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል። ሁለተኛውን ምዕራፍ ደግሞ 100 ሜጋ ዋት ለማመንጨት እ.ኤ.አ. ከ2023 በኋላ ገንብቶ ለማጠናቀቅ መታሰቡን ለማወቅ ተችሏል።
የፕሮጀክቱን ግንባታ የሚያከናውነው ቱሉሞዬ ጂኦተርማል ኩባንያ ሲሆን የቁፋሮውን ሥራ ደግሞ ኬንያ ጀነሬሽን የተባለ የኬንያ ሥራ ተቋራጭ የሚያከናውን ሲሆን ሚኪዳ የተባለ ሃገር በቀል ኩባንያም እንደሚሳተፍ ማወቅ ተችሏል።
ቱሉሞዬ እና ኮርቤቲ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪ እያንዳንዳቸው 800 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም ነው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የተጠቆመው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
March 27, 2020 at 5:17 pm in reply to: ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ #13990SemonegnaKeymasterመንግሥት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ አዳዲስ እርምጃዎችን ይፋ አደረገ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን ለመከላከል ከተቋቋመው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ጋር ያለውን የክንውን ሁኔታ እና ተጨማሪ መመሪያዎች እንዲሁም <ኮቪድ-19>ን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ በኢንተርኔት አማካኝነት (virtually) ውይይት አድርገዋል።
እስከ ዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ አጠቃላይ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 በመጨመሩ፣ ቫይረሱ በፍጥነት እየተዛመተ እንዳይሄድ ለመግታት ሲባል በቂ የመከላከል ሥራዎች መሠራታቸውን ለማረጋገጥ፣ የፌደራል መንግሥት በስፋት የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተዋል።
ከውይይቱ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሚከተሉትን ተጨማሪ ቁልፍ እርምጃዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን ጥሪም አቅርበዋል።
በዚህም መሠረት፦
- ከዛሬ (መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከሰዓት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚደርሱ እና ለለይቶ መከታተያ በተዘጋጁት ሆቴሎች ለመቆየት አቅም የሌላቸው መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች ለ15 ቀናት ተለይተው እንዲቆዩ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይሆናል።
- ከዛሬ አንስቶ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን ጨምሮ፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የሚቆዩ ይሆናል።
- በገበያ ስፍራዎች እና በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ በጥብቅ ተፈጻሚ ሊደረጉ ያስፈልጋል። የፌደራል መንግሥት አስከፊ ብሔራዊ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ሀይማኖታዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ሕገመንግሥታዊ መብት አለው። ሆኖም፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት፣ ዜጎች የማኅበራዊ ርቀት መመሪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
- ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍን የሚጠይቅ ከሆነ ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
- የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው መገልገያዎችን የያዙ ከ134 በላይ ተቋማት ለለይቶ መከታተያ፣ ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና እንዲሆኑ ተለይተዋል። ስለዚህ፣ መንግሥት ሁሉም ዜጎች እንደ አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ አንሶላዎች፣ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና ሌሎች ከሕክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው እና የሌላቸው መገልገያዎችን ለማሰባሰብ በመሥራት ላይ የሚገኘውን የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ ያቀርባል።
- የማክሮ-ኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴው ኢኮኖሚው ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመቀየስ በልዩ ልዩ ዘርፍ ከተሠማሩት አበይት የኢንደስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትን ሲያካሂድ ቆይቷል። ይህንኑ ተከትሎም፣ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚከተሉት እርምጃዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡-
-
- የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎች እና ግብአቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ይደረጋል።
- የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ የመቀጠል እና ባንኮች በ<ኮቪድ-19> ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች ይሰጣል።
- የውጪ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው እና የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎችን እና ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ ይደረጋል።
- በፋይናንስ አገልግሎት የተነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘት እና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ ክፍያ እና ገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ ያደርጋል።
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ተደርጓል። ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሂደቱን በተለየ መልኩ እንዲያፋጥን ይደረጋል።
- የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የሸቀጦች እጥረት እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር በንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ምንጭ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
SemonegnaKeymasterዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 34 የሕክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ለሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1233 ተማሪዎቸ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመርቋል።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በዋና ግቢው እና በዱራሜ ካምፓስ 6 ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በተከታታይ ትምህርት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።
በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፥ ኢትዮጵያ ለእርሷ እና ለዜጎቿ ክብር እና ፍቅር ያለው ባለሙያ ያስፈልጋታል ብለዋል። አክለውም ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት በተገቢው ሁኔታ ለማኅበረሰብ ለውጥ እንዲያውሉት አሳስበዋል።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን በማጠናከር የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስረግጡም ዶ/ር ሳሙኤል ጠይቀዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያየ መልኩ ከሚንፀባረቀው የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ኋላ ቀርነት በመራቅ ለኅብረተሰብ ዕድገት እና ብልፅግና እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም ያሰለጠናቸውን 33 የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም (hybrid innovative curriculum) በሕክምና ዶክትሬት ያሰለጠናቸውን 33 ተማሪዎች በተመሳሳይ ቀን አስመርቋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ለተማሪዎቹ የሥራ መመሪያ የሰጡት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ ተመራቂዎቹ ቃለመሀላ በገቡለት የሕክምና ሥነ-ምግባር በመታገዝ ቅን አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል። ከዚህም ባለፈ በተግባር በተደገፈው ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም የቀሰሙትን የሕክምና ትምህርት የሀገሪቱን ብሎም የዓለምን ሕዝብ ስጋት ላይ ከጣሉ ዘመን-ወለድ የጤና ችግሮች ኅብረተሰቡን ለመታደግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በውጤት በታገዘው የቅይጥ ፈጠራ-አከል ሥርዓት (ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም) ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸው በመሆናቸው ማኅበረሰቡን ከጤና እክሎች ከመታደግ ባለፈ በምርምር ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር ብልፅግና የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ 26 የማስተርስ ዲግሪ (ሁለተኛ ዲግሪ) ተማሪዎችንም አስመርቋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterበ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየተሠራ ነው
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም. የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየሠራ መሆኑን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲው ከ135 በላይ ለመድኃኒት የሚሆኑ እጽዋት ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።
ወልቂጤ (ኢዜአ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአገር በቀል እውቀት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ጥሩውሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት፥ እስካሁን የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት ቤት፣ በመሥሪያ ቤት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አልተካተተም። በቋንቋው ውስጥ የተለያየ የአነጋገር ዘዬ መኖር በትምህርት እንዳይሰጥ ካደረጉት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጉራጊኛ ቋንቋን እየረሳ በመምጣቱ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር የፊደል ገበታ መቀረጹን ገልጸዋል። የተወሰኑ ፎነቲኮች በአማርኛ ፓወር ግዕዝ ላይ ባለመኖራቸው ዩኒቨርሲቲው “የተንቢ” የተሰኘ የኮምፒተር መተየቢያ አበልጽጓል።
በጉራጊኛ ቋንቋ 13 የአነጋገር ዘዬ የሚገኝ ሲሆን በየትኛው መጀመር እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።
”የኮምፒተር መተየቢያና የፊደል ገበታን በማሰልጠን እንዲሁም ሌሎች ግብአቶች እንዲሟሉ በመጠቆም የጉራጊኛ ቋንቋ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ ለማስቻል እየተሠራ ነው” ብለዋል አቶ ካሳሁን።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከ135 ዓይነት በላይ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎች ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ለዚህም የተፈጥሮ መድኃኒት ማምረት የሚያስችል የስልት ሰነድ (strategic document) እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ መድኃኒቱን ማምረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። በዚህም ንጥረ ነገሮችን የመሥራትና የአሠራር ዘዴ ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ምርምር እየተደረገባቸው ያሉ እጽዋት ለደም ብዛት፣ ጋንግሪን፣ አስም፣ አጥንት ካንሰርና ለሌሎች በሽታዎች ፈውስ ያስገኛሉ የተባሉ ናቸው።
ቀደም ሲል ከእጽዋት የባህላዊ መድኃኒቶች ልኬት እንደማይታወቅ ያነሱት አቶ ካሳሁን፥ የፋርማሲና የኬሚስትሪ ባለሙያዎች ከአካባቢው የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በምርምሩ እንዲሳተፉ ተደርጓል።
በሌላ በኩል የማኅበረሰቡ ለበርካታ ዓመታት ይተዳደርበት የነበረው ባህላዊ የሕግና አስተዳደር ዘዴ እየቀነሰ በመምጣቱ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው ምርምር እያደረገ ነው።
ቋንቋና ሥነ-ጹህፍ፣ አገር በቀል መድኃኒት፣ አስተዳደርና ሕግ፣ ባህልና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኒቨርሲቲው ትኩረት ተሰጥቷቸው ምርምርና ጥናት እየተካሄደባቸው ነው።
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ክልል የሚገኝ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን የተመሠረተው በ2004 ዓ.ም. ነው።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterየኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያወጣው ወቅታዊ የአቋም መግለጫ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ለመወሰንና ለማስወሰን አንዳንድ ሀገራት የተዛባ ውሳኔ እንዲሰጥ ጫና ለመፍጠር እየጣሩ ይገኛሉ። በአንድ ወቅት ተመሳሳይ የተዛባ ውሳኔ በ League of Nations ሲተላለፍ እ.ኤ.አ. በ1949 የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የሚከተለውን ብለው ነበር፡-
“ሀገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ለነፃነቷና ለመብቷ ከኮሎኒያልስት ጣሊያን ጋር በየጊዜው ስትዋጋ ያሸነፈችውም ብቻዋን ነው። የተጠቃችውም ብቻዋን ስለሆነ ሀገሬ መቼውንም በሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም። ዛሬም ሆነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያለባት እሷ ራሷ ብቻ ናት!”
እንዳሉት ሁሉ፥ አሁንም ያለን ትውልዶች የተዛባውን ሚዛን ማስተካከል ያለብን እኛው ነን። እናም የአድዋውን ድል በተባበረው የአያቶቻችን ክንድ እዳሸነፍነው ሁሉ የሕዳሴውንም ግድብ በተባበረው አንድነታችን፣ ክንዳችን እና ሀብታችን ሠርተን የምንጨርሰው መሆናችንን እያረጋገጥን እኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች አቋማችንን በጋራ ስንገልፅ መነሻ ያደረግነው፡-
- የግድቡ መገንባት በአገሪቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ልዩነት እንደሌለው፣
- ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን እና ሀብቷን ለመቀራመት አውጥተውት የነበረና አሁን የሚያፍሩበት እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ኢትዮጵያ ባልተወከለችበት በተደረገ ስምምነት የሕግ ተገዥ የምትሆንበት ሕጋዊም ሆነ አመክኗዊ ነገር የሌለ መሆኑን፣
- የሀገራችን ምሁራን በሠሯቸው ጥናቶች ግድቡ የሚገነባው ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ባልሆነ ቦታ ከመሆኑም በተጨማሪ ውሀው ግብፅ ወይም ሱዳን ላይ ቢከማች ኖሮ በትነት የሚባክነውን ውኃ ስለሚያስቀር ተመራጭ የሚያደርገው መሆኑን ነው።
ከዚህ በላይ በቀረበው መነሻነትም እኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ባለ ስድስት ነጠብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
- የጀመርነውን እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምናደርግ እናረጋግጣለን።
- የሕዳሴው ግድብ የአንድነታችን ተምሣሌት በመሆኑ በዘር፣ በኃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይኖር የመንግሥትን አቋም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደግፍ እንጠይቃለን።
- እኛ ጠግበን በብርሃን እየኖርን እናንተ በረሃብና በጨለማ ኑሩ የሚል ራስ ወዳድ አስተሳሰብን በፅኑ እናወግዛለን።
- እኛ የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውን የየድርሻቸውን እንዲወጡና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንደያሳድሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
- የአረብ ሊግ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ሰሞኑን የወሰደውን ኢ-ፍትሐዊ ውሣኔ እየተቃወምን የአፍሪካ ህብረት እንዲህ ዓይነት ጣልቃ ገብነትን እንዲቃወምና መርህን እና ሕግን መሠረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን።
- የአሜሪካ መንግሥት በታዛቢነት ገብቶ ሀብት እና የዲፕሎማሲያዊ ኃይሉን በመጠቀም ወደ አደራዳሪነት ራሱን ከማሸጋገር በላይ የወሣኝነት ሚና ያለው የሚመስል መግለጫ ማውጣቱን አጥብቀን እንቃወማለን።
የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ
የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች
የካቲት 28 /2012 ዓ/ም
ካፒታል ሆቴል
አዲስ አበባየሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterአቢሲንያ ባንክ በታላቁ የንግድ ሰው በሞላ ማሩ ስም ቅርንጫፍ ከፈተ፤ የባንኩ አሚን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝቷል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ቅርንጫፎቹን በሀገር ባለውለታዎች ስም እየሰየመ የሚከፍተው አቢሲንያ ባንክ አሁን ደግሞ (በየካቲት ወር 2012 ዓም) በሀገራችን ስመ-ጥር የንግድ ሰው በሆኑት ሞላ ማሩ ስም አዲስ አበባ ውስጥ ከአብነት ወደ ተክለኃይማኖት በሚወስደው መንገድ ሞላ ማሩ አካባቢ <አቢሲንያ ባንክ ሞላ ማሩ ቅርንጫፍ> ከፍቶ ሙሉ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ቀኛዝማች ሞላ ማሩ ከአባታቸው ከአቶ ማሩ ዶሬ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዳዊቴ ሁሉቃ፥ በክስታኔ ጉራጌ፣ ዋጮ ፉሌ ቀበሌ፣ በመጋቢት ወር 1918 ዓ.ም. ተወለዱ። ከሊስትሮነት፣ ከጎዳና ንግድ፣ ከአልባሳት ሽያጭ የሥራ ዘርፍ ጀምሮ እስከ ቡና ንግድ፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ዘይትና አረቂ ፋብሪካ ማቋቋም ድረስ የዘለቀ የንግድ ሥራ ታሪክ ባለቤት ናቸው። በተጨማሪም ቀኛዝማች ሞላ ማሩ በሆቴል ሥራ፣ በብሎኬት ፋብሪካ ሥራ፣ በእርሻ ሥራ፣ በድንጋይ መፍለጫ ካባ ሥራ እና ሌሎች በርካታ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው። በአጠቃላይ ቀኛዝማች ሞላ ማሩ በበርካታ የሥራ ዘርፎች ላይ በመሠማራት፤ የሥራ ፈጠራን (entrepreneurship) ወርድና ቁመት በዕውን ያሳዩ የሀገር ባለውለታ ናቸው።
በንግድና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያከናወኗቸው ተግባራት ከራሳቸው ባለፈ ለሀገርና ሕዝብ ጠቃሚ መሆናቸውን ያመነበት የቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለሥላሴ መንግሥት፣ በ1964 ዓ.ም. የቀኛዝማችነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።
ባለትዳርና የ6 ልጆች አባት የነበሩት ቀኛዝማች ሞላ ማሩ በ1972 ዓ.ም፣ በ54 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም አርአያነታቸው በርካቶችን እያነሣሣ ለትውልድ ይቀጥላል።
‘ቅርንጫፎቹን በሀገር ባለውለታዎች ስም እየሰየም ለትውልድ የሚዘክረው አቢሲንያ ባንክ በእኚህ የሀገር ባለውለታ ስም ቅርንጫፉን በመሰየሙ ከፍተኛ ደስታና ክብር ይሰማዋል’ – ይላል ባንኩ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ።
ከአቢሲንያ ባንክ ዘገባ ሳንወጣ፥ ባንኩ አሚን (Ameen) በተሰኘው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝቷል። ሽልማቱ መቀመጫውን ዱባይ ባደረገው አልሁዳ ኢስላሚክ ባንኪንግና ኢኮኖሚክስ (AlHuda Centre of Islamic Banking and Economics) በመባል የሚታወቀው ማዕከል ባዘጋጀው 2ተኛው “የአፍሪካ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ታክፉል ሽልማት 2020” (African Interest-Free Banking and Takaful Awards 2020) ፎረም ላይ ተበርክቷል። ሽልማቱ አቢሲንያ ባንክን “በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና ፋይናንስ” የላቀ የገበያ አበርክቶ ተሸላሚ ሲያደርገው፥ የባንኩን አሚን ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አብዱልቃድር ሬድዋንን “በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አንጸባራቂ ሰብዕና እየገነባ የመጣ” በሚል የ2020 ተሸላሚ አድርጓል።
-
AuthorPosts