Search Results for 'ሳህለወርቅ ዘውዴ'

Home Forums Search Search Results for 'ሳህለወርቅ ዘውዴ'

Viewing 11 results - 1 through 11 (of 11 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    “በዚህ ሀገራዊ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን፣ ጠያቂና ተጠያቂ ያላበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስድስተኛው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ውጤትን ያስተላለፉት መልዕክት

    የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት፥

    ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመናት፣ የሀገራችን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነጻ ፈቃዱ የመረጠው መንግሥት እንዲኖረው ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ ቢቆዩም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሲሰናከሉ ነበር። በሂደቱ አያሌ ተማሪዎችና ወጣቶች፣ ገበሬዎችና የቤት እመቤቶች፣ ምሁራንና መለዮ ለባሾች፣ መላው የሀገራችን ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ካለፈ ልምዳችንና ባልተሳኩ ጉዞዎች ጠባሳ ሰበብ፣ የአሁኑም ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱ ተጠብቆ ባይጠናቀቅስ በሚል ስጋት፣ ያለፉትን ወራት እንደ ሀገር በፍርሃት ተወጥረን መክረማችን ሊካድ አይችልም። ኢትጵያውያን ግን ጨዋ ብቻ ሳይሆኑ አርቆ አሳቢ መሆናቸውን ዛሬም አስመስክረዋል። የተሰጋውን ሳይሆን የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ በግብር አሳይተዋል። ዝናብና ፀሐይ ሳይገድባቸው፣ በረጃጅም ሰልፎች ሳይሰለቹ፣ እስከ እኩለ ሌሊት ታግሰው ፍላጎታቸውን በካርዳቸው ገልጸዋል። እንደ እኛ እምነትም በዚህ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ሕዝባችን ነው። ከሕዝባችን በመቀጠል፣ በብዙ ውሱንነቶች ውስጥ አልፈው በዲሞክራሲና በሕዝብ ድምፅ ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት፣ ሀሳብና ፖሊሲያቸውን ለሕዝብ አቅርበው ብርቱ ውድድር ያደረጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ድል አድራጊዎች ናቸው።

    ይህንን ምርጫ ልዩና ታሪካዊ የሚያደርጉት ብዙ ጉዳዮች አሉ። በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተጽዕኖዎች በተላቀቀ የምርጫ ቦርድ ዳኝነት ያደረግነው ምርጫ መሆኑ አንደኛው ነው። የምርጫ ቦርድ ዳኝነት እንዲሳካ ደግሞ ቁጥራቸው የበዙ የግልና የመንግሥት ሚዲያዎች፣ የሲቪል ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎችም ተቋማት በግልጽ የተከታተሉት መሆኑ ሂደቱን ከመቼም ጊዜ በላይ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊነቱ የተጠበቀ ምርጫ ያደርገዋል። ምርጫው ዴሞክራሲን የመትከል ግባችንን አንድ እርምጃ ያስኬደ በመሆኑ፣ ፓርቲያችን ከምንም በላይ ቀዳሚ ድሉ አድርጎ ይቆጥረዋል። በታሪካዊው ምርጫ ተሳታፊ መሆን በራሱ የሚፈጥረው ደስታ እንዳለ ሆኖ፣ ፓርቲያችን በሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ ሀገር ለማስተዳደር መመረጡ አስደስቶናል። በውጤቱም ከአሸናፊነት ይልቅ ኃላፊነት፣ ከድል አድራጊነት ይልቅ ታላቅ የሆነ ሀገራዊ አደራ እንዲያድርብን አድርጎናል።

    መንግሥት የሚመሠረተው በሕዝብ በተመረጡ ፓርቲዎች ቢሆንም ሀገርን መምራትና ማስተዳደር ግን ለተመረጡ ፓርቲዎችና መሪዎች ብቻ የሚተው አይደለም። ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸውም እስከሚቀጥለው ምርጫ በመንግስት አስተዳድርና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ሚናቸው ሰፊ ሊሆን እንደሚገባ ለማስታወስ እወዳለሁ። በቀጣይ ወራት ብልጽግና በሚመሠርተው መንግሥት ውስጥ በአስፈጻሚው አካልም ሆነ በፍርድ ቤቶች፣ በሌሎችም የፌደራልና የክልል ተቋማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ በዘንድሮው ምርጫ በኃላፊነትና በብቃት የተወዳደሩ የሕዝብ አለኝቶችን ከዚህ በፊት ካደረግነው በእጅጉ ከፍ ባለና አዎንታዊ ለውጥ በሚፈጥር መልኩ እንደምናካትታቸው ለመግለጽ እወዳለሁ። በተጨማሪም እስከሚቀጥለው ምርጫ የበለጠ ተጠናክረውና ተቋማዊ አቅማቸው ደርጅቶ ብርቱ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም። በዚህ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን፣ ጠያቂና ተጠያቂ ያላበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው።

    ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፥

    በምርጫ ካርዳችሁ ስትመርጡን በዕቅድና በፖሊሲ የያዝናቸውን የብልጽግና ግቦች እንድናሳካ የድፍረትና የጥንካሬ ስንቅ እንደሚያቀብለን ሁሉ፣ እኛና እናንተን ያስተሳሰረው ቃል ኪዳን ተጠብቆ እንዲቆይ ነገሮች አልጋ በአልጋ እንደማይሆኑን እንገነዘባለን። ቢሆንም ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትከሻችንን አስፍተን፣ ኢትዮጵያን ከሚወዱ አካላት ጋር ሁሉ በትብብር ዐቅማችን አማጥጠን ለመሥራት ቆርጠን እንደተነሣን ሳበስራችሁ ደስ እያለኝ ነው። በቀጣይ ዓመታት ሀገራችን በእውነትም በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ከፍ የምትልበት ዘመን ይሆናል። ይህ እንዲሳካ የሐሳብና የሞራል ስንቅ እንደምታቀብሉን፣ መንገድ ስንስት እንደምትመልሱን፣ ስናጠፋም እንደምታርሙን ተስፋ በማድረግ ነው።

    በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን በቀጣዩ አምስት ዓመት ፈር ጠራጊ እንሆናለን የምንለው፣ በዙሪያችን ባሉና ብልጽግና በሚቀላጠፍባቸው አራት ማዕዘኖች መሐል ቆመን ነው። የመጀመሪያው ማዕዘናችን የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲሆን፥ ሀገራችን እንድትበለጽግ በኢኮኖሚውም ሆነ በማኅበራዊና ፖለቲካ ዘርፎች ዘላቂ መሠረት የሚሆኑ፣ በፍጥነት የሚጠናቀቁ፣ ጥራታቸው የተጠበቁ፣ ከብክነት ነጻ የሆኑ እና የምንፈጥራቸውን ተቋማት መሸከም የሚችሉ ትውልድ ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶችን መገንባታችንን እንቀጥላለን። ጥቂትም ቢሆኑ ባለፉት 3 ዓመታት አመርቂ ሥራዎችን ለመሥራታችን ምስክሮቹ እናንተው ናችሁ።

    ሁለተኛው ማዕዘናችን የተቋማት ግንባታ ሲሆን፣ በጥቂት ግለሰቦችና ነጠላ ተቋማት ላይ ከማተኮር ባለፈ ሀገራችንን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉናል። ዘመን ተሻጋሪ ሥርዓት ለማጽናት የሚስችሉ ገለልተኛና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያገለግሉ ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት ይደረጋል። ይሄ ማሕቀፍ ከፌደራል እስከ ክልል የሚገኙ ተቋማትን የሚያካትት ይሆናል።

    በሦስተኛ ደረጃ እንደ ሀገር የሚያስተሳስሩን የጋራ አመለካከቶችና የጋራ ትርክቶች ላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሠራባቸው ይገባል። እርስ በእርስ የሚቃረኑና የሚጠፋፉ ትርክቶች ምን ያህል ለጠላቶቻችን ተመችቷቸው እኛን ደካማ እንዳደረገን ያሳለፍናቸው ዓመታት ሕያው ምስክሮች ናቸው። ስለዚህ ክፍተቶቻችንን በሚደፍን መልኩ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር አጠንክረው በሚያቆሙን እሴቶች ላይ የተመሰረተ፣ ገዢና ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ትርክት ለመገንባት ጠንክረን እንሠራለን።

    በአራተኛ ደረጃ የሞራል ልዕልናና ግብረገባዊነት ተመጣጣኝ ትኩረት አግኝተው እስካልተሠራባቸው ድረስ በሀገራችን ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በተቃራኒው ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች እየተስፋፉ እንዲመጡ በር ይከፍታል። ይኼንን ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት መንግሥትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ ብቻ የሚጣል ሳይሆን፣ ከግልና ከቤተሰብ ጀምሮ የሚሠራ ሥራ ነው። ሁሉም አካላት ተረባርቦ ሀገርና ትውልዱን እያቆሸሹ ያሉ መጥፎ ተግባሮችን ጠርጎ ሊጥላቸው ይገባል። በቀጣይ ዓመታት በሞራል ንጽህና የተገነቡ ተቋማትንና መሪዎችን አንጥረን የምናወጣበት እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

    ውድ የሀገሬ ዜጎች፥

    ባለፉት ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ጥንቃቄ የቀረጽነው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለተግባራዊነቱ በጋራ ከተጋን ያለ ጥርጥር ቀጣዩቹ ዓመታት ለሀገራችን ብልጽግና እንደ ወሳኝ የመታጠፊያ ኩርባ ይሆናል። ዕምቅ ዐቅሞቻችን ምንድን ናቸው? ምን ዓይነት የመበልጸግ ዕድል እጃችን ላይ አለ? ምን ብናደርግ ኢኮኖሚያችን መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል? የሚሉትን በሚገባ ፈትሸን ያረቀቅነው ዕቅድ ነው።

    በሀገራችን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በፍጥነት የምግብ ፍላጎታችንን በማሟላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከውጭ የምግብ ድጎማ መላቀቅ አለብን። ምግብ ለእኛ ቅንጦት መሆን አይገባም። ጠግቦ መብላት ቅንጦት የሆነበት ሕዝባችንን መርጦ መብላት እንዲጀምር ለማድረግ ቆርጠን መነሳት አለብን። በብዝኃ ዕጽዋትና በብዝኃ እንስሳት የምትታወቅ ሀገራችን የእንስሳት ተዋጽዖና ፍራፍሬዎች ለገበታችን ከቅንጦትነት ወደ አዘቦትነት መለወጥ አለባቸው። ዶሮና ዕንቁላል፣ ወተትና ቅቤ፣ ተርፎን ለገበያ የምናቀርባቸው እንጂ ለዓመት በዓል አይተናቸው የሚሰወሩ የሩቅ እንግዳ መሆናቸው ሊያከትም ይገባል።

    እዚህ ጋር አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ አለ። መንግስትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው እስካልሠሩ ድረስ ሕልማችን ይሳካል ማለት ዘበት ነው። በቀጣይ 5 ዓመታት ተባብረን በተለይ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ ጠንክረን መስራት አለብን። ከዚህ ቀደም ጀምረናቸው ውጤት እያመጡ ያሉ ተግባራት አሉ። የበጋ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች ላይ ለውጥ ለማምጣት ከተጀመሩ አነስተኛ መስኖዎች ባለፈ፣ ዝናብ አጠርነት ለመዋጋት በቴክኖሎጂ አማካኝነት ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ልምምዳችን እያደገ ይገኛል። በቅርቡም ምርትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን ችግሮቻችንን ወደ ዕድል መቀየር ጀምረናል።

    አየር ንብረታችንን የሚያስተካክለውና የብዝኃ ዕጽዋትና የብዝኃ እንስሳት ሀብታችንን በእጅጉ ያሳድጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብራችን እንዲሁ ተጠቃሽ ነው። በቁጥር ግንባር ቀደም ያደረጉን የቀንድ ከብቶቻችን ከመቀንጨር ወጥተው ምርታማ እንዲሆኑ ያደርጋል። ወደየጎረቤት ሀገሩ የሸሹ የዱር አራዊትም ተመልሰው፣ ከታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ጋር የተዋደደ ተፈጥሮአዊ መስህብ በመሆን የቱሪስት ፍስትን እንዲጨምርና ኢኮኖሚያችን መስፈንጠር እንዲችል መደላድል ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

    የሀገራችን ሕዝብ ሆይ፥

    ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረታችንን ሰቅዘው ከያዙት ጉዳዮች መካከል ሌላኛው የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ ጉዳይ ነው። የዴሞክራሲ ጥያቄን አንድ ምዕራፍ ለማሳደግ የምርጫችን መሳካት ወሳኝ እንደነበረው ሁሉ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግራችንን ለመቅረፍና ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀላጠፍ ጉልህ አስተዋጽዖ ከሚያበረክቱ ፕሮጀክቶቻችን መካከል አንዱና ወሳኙ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችን እንደሆነ ይታወቃል።

    የሕዳሴ ግድብ አጀንዳ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከግድብም፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነትም በላይ ነው። ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ ዳግም የመነሣታችን ተምሳሌት ነው። በራስ ዐቅም የመቆም፣ በራስ ፍላጎት የመመራት፣ የሉዓላዊነታችን ምልክት፤ የሀገራዊ አንድነታችን ገመድ ነው። በሕዳሴ ጉዳይ ብዙ አይተናል፣ ብዙ ተፈትነንበታል። በራሳችን ዐቅም መቆማችን የሚያስደነግጣቸው፣ በፍላጎታችን መመራት መጀመራችን የሚቆጫቸው ብዙ ጋሬጣዎችን ሲጥሉብን ነበር። “ሚስማር አናቱን ሲመቱት ይበልጥ ይጠብቃል” እንዲሉ ሆኖ፤ በዓባይ ጉዳይ በገፉን ቁጥር እየቆምን፣ በተጫኑን ቁጥር እየበረታን፣ ባዋከቡን ቁጥር ይበልጥ እየጸናን አሁን የደረስንበት ቦታ ላይ ቆመናል። በቅርቡ ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት አድርገን፣ በምርጫው ስኬት የተደሰትነውን ያህል፣ በሕዳሴያችንም ሐሴት እንደምናደርግ አልጠራጠርም።

    በሕዳሴ ግድብ ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነታችን እንዲጠበቅልን እንጂ መቼም ቢሆን ሌሎች ሀገራትን የመጉዳት ፍላጎት ኖሮን አያውቅም። አሁንም ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግመን ማረጋገጥ የምንፈልገው ሐቅ፣ የዓባይ ወንዝ እንደሚያስተሳስራቸው ወንድም ሕዝቦች በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የመፍጠር ፍላጎት የለንም። ዛሬም ሆነ ወደፊት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለመመካከር በራችን ክፍት ነው። እኛንም ሆነ እናንተን ነጥሎ ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ በሚያደርጉ አካሄዶች ላይ እንድንሳተፍ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን አይፈቅም።

    ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚቀዳ ነው። በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁዎች ነን። የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላሙ እንዲጠበቅ፣ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር፣ በትብብርና በመግባባት እንድናድግ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች፤ ጥሪም ታቀርባለች።

    የተከበራችሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፥

    የሀገራችን መጻኢ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ በተገቢው መወጣት ከሚገቡን የቤት ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንን በሠለጠነ መንገድ መምራት ነው። ከላይ በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ይኼ ኃላፊነት በመንግሥትና በተመረጠው ፓርቲ ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም፤ አንድ አካል ልሥራው ብሎ ቢነሣ እንኳን በአግባቡ የሚወጣው ጉዳይ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አይተናል። እንኳንስ የሠለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባትን የሚያህል ነገር ይቅርና፣ አንድ ዙር ምርጫን ዴሞክራሲያዊ አድርጎ ለማጠነቀቅ ብዙ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው ካለፍናቸው ምርጫዎች በሚገባ ተረድተናል። የዘንድሮውንም ምርጫ ካለ እናንተ ድጋፍና ትብብር ፍትሐዊና ዴሞራሲያዊ በሆነ መንገድ ማከናወን ባልተቻለ ነበር።

    በቀጣይም ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደታችን መሬት እንዲረግጥ የተለመደ ትብብራችሁና በየምዕራፉ ያላሰለሰ ድጋፋችሁ እንደሚያሻን ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። በሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የሚኖራችሁ ድርሻ ወሳኝ እንደሆነ እናምናለን።

    የፖለቲካ ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው፣ ለሀገርና ለሕዝባችን በሚጠቅሙ ማናቸውም የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ ከእናንተ ጋር በመግባባት ለመሥራት ዝግጁዎች ነን።

    ምርጫውን ስኬታማ ያደረጋችሁ ውድ የተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች፣

    ይህ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የምርጫ ቦርድ አመራሮችና ሠራተኞች፣ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ሁሉ ከደም መሥዋዕትነት በመለስ ያለ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላችኋል። ከግራ ከቀኝ የሚመጡትን ጫናዎች ተቋቁማችሁ በውጣ ውረዶች ሳትበገሩ ለሀገራችን የማይደበዝዝ የዴሞክራሲ አሻራ አትማችኋል፤ በዚህም ታሪክ ስማችሁን አድምቆ ይጽፈዋል።

    የጸጥታ አካላት፤ ምርጫው ሰላማዊ እንደሆን ጉልህ ሚና ተጫውታችኋል፤ እናንተ ዕንቅልፍ አጥታችሁ ሥጋቶቻችን ሁሉ እንደ ጉም እንዲተንኑ ስላደረጋችሁ ክብር ይገባችኋል። በተመሳሳይ፣ ፈጣንና ሚዛናዊ መረጃን ወደ ሕዝቡ በማድረስ በኩል የግልና የመንግስት ሚዲያዎች፤ እንዲሁም አጭር የጽሑፍ መልዕልት ስርጭት በኩል የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኞች፣ ላበረከታችሁት አስተዋጽዖ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች።

    ውድ የፓርቲያችን አመራሮችና አባላት፥

    በዚህ ምርጫ ሕዝቡ ያስተላለፈውን መልእክት በሚገባ መረዳት የወደፊቱን መንገዳችንን ቀና እንደሚያደርገው እናምናለን። ሕዝቡ በአብላጫ ድምጽ እኛን የመረጠው ፓርቲያችን እንከኖች ስለሌሉበት አይደለም፤ ከነስሕቶቻችንን ዕድል ሰጠን እንጂ ድል አላደረግንም። ሕዝብ የመረጠን በአንድ በኩል ያጠፋናቸውን እንድናርም፣ በሌላ በኩል መልካም ጅማሮዎቻችንን እንድናስቀጥል፣ ከሀገር ግንባታ አንጻር በወሳኝ ደረጃ ላይ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን በቀጣይ ጊዜያት ፈጽመን እንድናሰረክብ ነው። ሕዝባችን ጉድለቶቻችንን በሚገባ ያውቃል። ከስርቆት ዓመል ያልተላቀቁ፣ ለሰው ነፍስ ግድ የሌላቸው፣ ሕግን የማያከብሩ፣ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አመራሮች በመካከላችን መኖራቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። ድምፁን ሲሰጠን ታረሙ፣ ውስጣችሁን አጥሩ እያለን ጭምር ነው። እኛም በተግባር ሆነን ማሳየት አለብን። ይኼን ማድረግ ካልቻልን ከአምስት ዓመት በኋላ በካርዱ እንደሚቀጣን እናውቃለን።

    በአሁኑ ምርጫ መምረጥ ያልቻላሁ ወገኖቻችን በሙሉ፥

    በልዩ ልዩ የጸጥታና የደኅንነት ምክንያቶች፣ እንዲሁም በሎጅስቲክና በተለያዩ ውሱንነቶች ምርጫው በተያዘለት ክፍለ ጊዜ መሠረት ከተቀረው ሕዝብ ጋር አብራቸሁ ድምፅ ባለመስጠታችሁ ታላቅ የሆነ ቅሬታ ፈጥሮብናል። ይኼ የሆነው ባልተጠበቁ ምክንያቶች እንደሆነ ግንዛቤ ትወስዳላችሁ የሚል ግምት አለን። ሁኔታዎች ተስተካክለው የምርጫ ቦርድ በወሰነው ቀን ምርጫው እንደሚደረግ እምነቴ ነው።

    ትግራይን በተመለከተ የትግራይ ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ ከተደራራቢ ችግር የሚወጣበትን፣ ተያያዥ ሀገራዊ ችግሮች የሚፈቱበትን እና ሰላምና ደኅንነት የሚረጋገጥበትን የመፍትሔ አቅጣጫ እንከተላለን።

    በመጨረሻም፣ ከለውጡ ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ሀገር አንድነትና ስለ ሕዝባችን ተጠቃሚነት ቀና ቀናውን በማሰብ በመንገዳችን ሁሉ ድጋፍ ሲያደርጉልን የነበሩ አካላትን ከልብ ሳላመሰግን አላልፍም። ኢትዮጵያ በታሪክ ለውጥ ላይ ናት። በዚህ የለውጥ ሂደት ተሳፍረን የተሻለች ሀገር እንገነባለን። በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያችን አሸናፊ ስለሆነች በድጋሚ ለመግለጽ እወዳለሁ። ቀጣይ ዘመናችንን ብሩህ ያድርግልን፤ ሁላችንም እንኳን ደስ አለን።

    ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
    ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
    ሐምሌ፣ 2013 ዓ.ም

    • በስድስተኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን ማሸነፉን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 3 ቀን  2013 ዓ.ም. አስታውቋል። ዝርዝሩን ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ
    • የስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ውጤት መታወቅን ተከትሎ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ “ኢትዮጵያ ሀገራችን ተከብራ የምትኖረው ስንቻቻል፣ ስንደማመጥና የሌላውን ሃሳብ ስንቀበል ብቻ ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
    • ይህ ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ትልቁን ሚና የተጫወተውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የሚመሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ “ሀገራዊ ምርጫው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት በይፋ የታየበት ነው” ብለዋል።

    ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ

    Semonegna
    Keymaster

    ሸገር ፓርክ በትልቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባን ከተማ የቀይራል ተብሎ የሚጠበቀው ሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም በተገኙበት ተካሂዷል።

    ሸገር ፓርክ የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊነት በሚያሳይ መልኩ የተገነባ ሲሆን፥ በውስጡ የተፈጥሮ እጽዋትንም ያካተተ ነው። ፓርኩ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ በማሳየት የወደፊት ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ የወዳጅነት ፓርክ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    ግንባታው ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ሸገር ፓርክ በቻይና ግዙፉ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ “China Communications Construction Company (CCCC)” የተገነባ ነው።

    በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርኩ ግንባታ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቻይና የተለያዩ ኩባንያዎች ትልቁን የወዳጅነት ሽልማት አበርክተዋል። በግንባታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንም እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

    ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ ነጥቦች፡-

    • አዲስ አበባ ይህን ፓርክ ማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል፤
    • ይህ እና ሌሎች ፓርኮች የከተማይቱንና የሀገራችንን ገፅታ ያስውቡታል፤
    • ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤
    • ፓርኩ ተባብሮ መሥራት የሚያስገኘውን ውጤት ማሳያ ነው፤
    • ሸገር ፓርክ ከመሃል ሀገር ሳንወጣ ሩቅ ቦታ የተጓዝን የሚያስመስለን ፓርክ ነው፤
    • ከተለምዶው የተለየ ነገር ማየት አድማሳችንን ያሰፋዋል፤
    • [በግሌ] ይህ ፓርክ በዚህ ፍጥነት ለምረቃ ይበቃል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤
    • በፓርኩ በሚገኘው የአበባ ማፍያ ስፍራ ከዓይናችን ጠፍተው የቆዩ አበቦችን ሳይቀር ማስተዋል ችያለሁ፤
    • ውበትን መሻት ካለንበት ሀኔታ ጋር አይፃረርም፤
    • አገራችንን የማስዋብ ጥረታችንን ከሌሎች የልማት ጥረቶቻችን ጋር ጎን ለጎን ካስኬድነው በአጭር ጊዜ የአገራችንን ገፅታ መቀየር እንችላለን፤
    • በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሸገር ፓርክ

    Anonymous
    Inactive

    8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ስምንት ግለሰቦችንና ተቋማትን የዓመቱ በጎ በማለት ሸልሟቸዋል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በልዩ ሁኔታና መስፈርት ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም በኢንተርኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል የተከናወነው 8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ስምንት የተለያዩ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችንና ማኅበራትን በጎ ተሸላሚዎች በማለት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

    የዘንድሮውን የስምንተኛውን ዙር የበጎ ሰው ሽልማት እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ በተለመዱት በአስሩ ዘርፎች እና በተለየ ድምቀት እንዳይካሄድ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) የሽልማቱ አዘጋጆችን እንደገታቸው ጋዜጠኛና የሥራ አመራ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ ሕሊና አዘዘ በመግቢያ ንግግሯ ላይ ገልጻለች።

    የዚህን ዓመት ሽልማት ለማከናወን ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ከ200 በላይ የዕጩዎች ጥቆማ ከሕዝብ መቀበላቸውን እና የሽልማት ድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ የዕጩዎቹን ታሪካቸውንና አብርክቷቸውን በማጥናት ላይ እያለ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት የተሟላ ዝግጅት ሊያደርጉ አለመቻላቸውን ጋዜጠኛ ሕሊና ጠቅሳለች።

    የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ) ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፣ እንዲሁም የበጎ ሰው ሽልማት የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የአግዮስ መጻሕፍት ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኘተዋል።

    የ8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

    1. አቶ ካሊድ ናስር

    የመጀመሪያ ልዩ ተሸላሚ ባለፉት አምስት ወራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገዛ መኖሪያ ግቢያቸውን ሳይቀር በመስጠት፣ መጠለያ የሌላቸውን (የጎዳና ተዳዳሪዎችን) በመደገፍ የበጎ አድራጎት ሥራ የሠሩት አቶ ካሊድ ናስር ናቸው።

    1. አቶ ኪሮስ አስፋው

    አቶ ኪሮስ አስፋው ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያለማቋረጥ መቶ ጊዜ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ የገዙ እና በደም መፍሰስ የሚሞቱ እናቶችን ለመታደግ ለ21 ጊዜ ደም የለገሱ ግለሰብ ናቸው።

    1. አቶ ብንያም ከበደ

    የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን መሥራች ጋዜጠኛ ብንያም ከበደ የ8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት 3ኛ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። ጋዜጠኛ ብንያም ከበደ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ልጆች በየቤታቸው ሲሆኑ የሚመለከቱት የሚመጥናቸውና በተለያየ ቋንቋ መሰናዶዎች የሚቀርብበት የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቭዥንን ከመክፈት ጀምሮ ያደረጉት አስተዋጽዖም የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ አድርጓቸዋል።

    1. ጋዜጠኛ መሀመድ አል-አሩሲ (محمد العروسي / Mohammed Al-Arousi)

    በአረብኛ ቋንቋ የኢትዮጵያን ሀሳብና እውነት (በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ) በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲያስረዳና ሲከራከር የቆየው አቶ መሐመድ አል-አሩሲ (محمد العروسي / Mohammed Al-Arousi) የዘንድሮ የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች በሳዑዲ አረቢያ የተወለደው መሐመድ አል አሩሲ፥ የሕዳሴ ግድብን በሚመለከት ስለኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሙግት በማድረግ ይታወቃል።

    1. ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ

    በሕዳሴ ግድብ ላይ እንዲሁም በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ባላት የልማት ተጠቃሚነት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉትና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ስለሕዳሴ ግድብ ተግተው በመሞገት የሚታወቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ የዘንድሮው የበጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል።

    1. ኢትዮ ቴሌኮም

    ኢትዮ-ቴሌኮም በዓመቱ ውስጥ በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል መልዕክት በማስተላለፍ፣ ማዕድ በማጋራት፣ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሠራቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎቹ የ2012 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል። ድርጅቱን በመወከል የተገኙት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ሽልማቱን ተረክበዋል።

    1. የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተ ጀምሮ ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከፊት የተሰለፉ የጤና ባለሞያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የ2012 ዓ.ም የዓመቱ የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመድረኩ የጤና ባለሞያዎችንና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በመወከልም ሽልማቱን ተቀብለዋል።

    1. የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሠራተኞች በሙሉ

    የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጸጥታውን የሚቆጣጠሩ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፓሊስ አባላት፣ እንዲሁም የሕዳሴው ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በጉባ በሥራ ላይ የሚገኙ የግድቡ ሠራተኞች የ2012 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። በጉባ የሚገኙ ሠራተኞችን ወክለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ ሽልማቱን ተረክበዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።

    ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

    ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።

    የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።

    ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።

    የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ዘንድሮ ለሰባተኛ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን የሸለመው የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) ተካሂዷል።

    በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማንን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

    ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በዘጠኝ ዘርፎች 291 ሰዎች ከሕዝብ ዘንድ ተጠቁመው የነበረ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 27ቱ ተመርጠው ለመጨረሻ ዕጩነት (በዘጠኝ ዘርፎች፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ ሦስት ሦስት ዕጩዎች) ቀርበው ኢትዮጵያውያን አሸናፊዎችን እንዲመርጡ ተደርጎ ነበር

    ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በእያንዳንዱ ዘርፍ ከቀረቡት ዕጩዎች ውስጥ የመጨረሻ ተሸላሚዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት አሸናፊዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

    በመምህርነት ዘርፍ

    • ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል

    በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)

    • ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በ አትክልት ምርምር ፕሮፌሰር፣ የጎለሌ ዕፅዋት ማዕከል የበላይ ኃላፊ፣ በሀገረ እንግሊዝ የተከበረው KEW International ሜዳል ተሸላሚ)

    በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ

    • አቶ በዛብህ አብተው (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የስፖርት ፎቶግራፍ አንሺ)

    በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)

    • አቶ አብድላዚዝ አህመድ

    በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ

    • አቶ ነጋ ቦንገር (የነጋ ቦንገር ሆቴል፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ የንግድ ተቋማት ምሥራች እና ባለቤት)

    በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት

    • አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ

    በቅርስና ባህል ዘርፍ

    • አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)

    በሚዲያና ጋዜጠኝነት

    • አቶ አማረ አረጋዊ (ሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር በስሩ የሚታተመው ሪፖርተር ኢትዮጵያ (የአማርኛ እና የእንግሊዝኛ) ጋዜጣ መሥራች)

    በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች

    • አቶ ኦባንግ ሜቶ (ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) መሥራች እና ሊቀ-መንበር)

    የሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ የክብር ተሸላሚዎች

    • የጋሞ ሽማግሌዎች (በቡራዩ የተከሰተውን ግድያ በመቃወም በአርባ ምንጫ የተቃውሞ ሠልፍ ላይ፣ በቁጣ ንብረት ለማውደም የቃጡ ወጣቶች እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ አንደ አካባቢው ባሕል ሣር ይዘው በአካላቸው ቆመው ንብረቱን ከጥፋት የተከላከሉት የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ነበሩ።)

    በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎችን እንኳን ደስ አላቸሁ ብለዋል። ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቷ፥ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎች ለነገው ትውልድ ተረካቢዎች አርዓያ የሚሆን ሥራ በመሥራታቸው ሊደነቁ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    በ2005 ዓ.ም. በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተቋቋመው የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵይውያን በጎ ሥራን የሠሩ እና ለሌሎች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ማበረታታት እና ዕውቅና መስጠት ነው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    The 7th edition of Bego Sew Award የበጎ ሰው ሽልማት


    Semonegna
    Keymaster

    በአደጋው የሁሉም ህይወት (157 ሰዎች) ያለፈ ሲሆን፥ ከተሳፋሪዎቹ መካከል 32ቱ ኬኒያዊያን ሲሆኑ፤ 17ቱ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በዛሬው ዕለት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፋሪዎች በሙሉ ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

    ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ (ኬንያ) ሲጓዝ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ላይ የተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ET302 የሆነው ቦይንግ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የ33 አገራት 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ ነበር።

    ከተሳፋሪዎቹ መካከል 32ቱ ኬኒያዊያን ሲሆኑ፤ 17ቱ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቋል።

    አውሮፕላኑ አደጋው የደረሰበት ዛሬ ማለዳ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተነሳ በስድስት ደቂቃ ልዩነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የአደጋው መንስዔ እስካሁን አልታወቀም።

    በአደጋው የሁሉም ህይወት (157 ሰዎች) ያለፈ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአደጋው የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝቷል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 በረራ ዛሬ ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ይበር በነበረው አውሮፕላን በደረሰው የመከስከስ አደጋ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሁሉ የጠ/ሚር ጽ/ቤት በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ኀዘኑን ይገልጻል።የኢትዮጵያ ተቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሰፈረው።

    በተመሳሳይ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ለአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።

    የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ እያለ አደጋ አጋጥሞት የመከስከሱን ዜና በከፍተኛ ድንጋጤና መሪር ሀዘን እንደሰሙ ገልጸዋል።

    ፈጣሪ አምላክ በቸርነቱ ለቤተሰቦቻቸው በሙሉ፣ ከብዙ በጥቂቱ ናይሮቢ ለማውቃቸው ለካፒቴን ያሬድ ወላጆች፣ ዶ/ር ጌታቸውና ዶ/ር ራያን፣ ለሆስተስ ሣራ ባለቤትና ሕጻን ልጆቿ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ላየኋት የጂቡቲዋ ራሻ ቤተስብ… መጽናናትን ይስጥልን። ዛሬ በ157 ሟች ቤተሰቦች ላይ የወደቀው መሪር ሐዘን እኔና ቤተሰቤ ኮሞሮስ በደረሰው አደጋ ያየነው በመሆኑ የሚያሳልፉትን ከባድ ፈተና ከማንም በላይ እረዳዋለሁ። 149 መንገደኞችና 8 የበረራ ሠራተኞችን ይዞ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲግዋዝ የነበረው [ET 302] በረራ ላይ በደረሰው የመከስከስ አደጋ በውስጡ የነበሩት ኢትዮጵያውያንና የ33 አገሮች ዜጎች ሕይወት ማለፍ ልቤን ሰንጥቆታል፤ እጅግ በጣም ነው ያዘንኩት።ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት።

    “ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ትልቅ የሀዘን ቀን ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቷ “በዜጎቻችንና ሌሎች የአየር መንገዱ ደንበኛ መንገደኞች ላይ በደረሰው አደጋ ልቤ ተሰብሯል” ብለዋል። በአደጋው ተጎጂ ለሆኑ ቤተሰቦች ፣ ወዳጅ ዘመዶችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።

    በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን አደጋ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መፅናናትን ተመኝቷል።

    የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርም (ኢህአዴግ) እንዲሁ በአደጋው የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ የሟች ወገኖች ነፍስ በአፀደ ገነት እንዲያርፍ ፣ ለወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መፅናናትን ተመኝቷል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በደረሰው አደጋ የሰው ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል። አውሮፕላኑ ምንም ዓይነት ቴክኒካዊ ችግር እንዳልነበረበትም አመልክቷል።

    የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በሰጡት መግለጫ፤ በአውሮፕላኑ መከስከስ የመንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት በማለፉ ከፍተኛ ሃዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ህይወታቸው ያለፉት ቤተሰቦችና ወገኖች ማስተናገጃ በአዲስ አበባ እና በናይሮቢ ቢሮ መከፈቱን ተናግረዋል።

    በአጠቃላይ 1ሺ 200 ሰዓታትን የበረራ ሰዓት ያስመዘገበው አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ለበረራ የተነሳው 2 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ሲሆን፤ 2 ሰዓት ከ40 ላይ ችግር እንዳጋጠመውና ከራዳር እይታ ውጪ እንደሆነም ገልጸዋል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ከተረከበው አራት ወር የሆነው ቦይንግ 737 ወደ ኬንያ የሚያደርገወን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ከጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪካ ተመልሶ ለሦስት ሰዓት ያህል አርፏል።

    ይሄው በዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ሙሉጌታ ወደ ኬንያ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን፤ ቀደም ብሎ በተካሄደ የቴክኒክ ፍተሻ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበረበት አመልክተዋል። ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር መሃመድ ኑር የሚባል ሲሆን፤ ከ200 ሰዓታት በላይ መብረሩም ተገልጿል።

    የአደጋው መንሰኤ አለማቀፍ የአቬሽን ሕግን በተከተለ መልኩ ዓለምአቀፍ ምርመራ ተካሂዶ ዝርዝር መረጃው ወደፊት እንደሚገለጽ አመልክተዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ


     

    Semonegna
    Keymaster

    “በርቱ! ባየሁት ነገር ተደስቻለሁ… የሥራ ፍላጎት ተነሳሽነት ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን” – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ 

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኘተው የሥራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

    በቆይታቸውም የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በጋራ ያስገነቡትን የልብ ህክምና ማዕከል፣ በሀገሪቱ ብቸኛና የመጀመሪያ የሆነውን የተመረዙ ሰዎች የሚታከሙበት የቶክሲኮሎጂ ህክምና ማዕከል እንዲሁም የእናቶችና ህጻናት የህክምና ከፍልን ዋና ዳይሬክተሩ ጎብኝተዋል።

    በሆስፒታሉ ፈጣን እድገት ተደስቻለሁ ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የልብ ህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩና በሀገሪቱ ካለው የህክምና እጥረት አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው ብዙም ትኩረት ያልተሰጠበት የመመረዝ ህክምና በሆስፒታሉ መሰጠቱም ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

    ቪዲዮ፦ የኢትዮጵያዊያን-አሜሪካዊያን ዶክተሮች ቡድን እያስገነባ ያለው ግዙፉ ዓለምአቀፋዊ ሆስፒታል በአዲስ አበባ

    ሆስፒታሉ የሰሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ህክምና ብቻ ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ቴዎድሮስ በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ መሠረታዊ የሆስፒታል አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩና የተወሰኑ የህክምና አገልግሎቶች ላይም የበለጠ ስፔሻላይዝድ ለማድረግ መሥራቱ በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

    ከዚህ ሌላም የሆስፒታሉ ሰራተኞች የሥራ ተነሳሽነትም በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። ለሆስፒታሉ ፈጣን ዕድገትም ሁሉም የሆስፒታሉ ሠራተኞች ዋና ተዋናይ መሆናቸውን እንዳዩ ገልጸው በዚህም የሥራ ፍላጎት መኖር ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን ብለዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዚሁ ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ከመጎብኘታቸው በተጨማሪም ከየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር) እንዲሁም ከኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝትው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

    ከሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀን ጀምሮ ዋና መቀመጫው ጄነቭ፣ ስዊዘርላንድ የሆነውን የዓለም ጤና ድርጅትን (WHO) በዋና ዳይረክተርነት የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከዚህ ስልጣናቸው በፊት ከ ከኅዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከጥቅምት 2 ቀን 1998ዓ.ም. እስከ ኅዳር 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ደግሞ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

    ምንጭ፦ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

     

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሚያዘጋጀው ሽልማት ዓላማ በኢትዮጵያ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ሥራ ማበረታታት መሆኑ በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ጊዜ የአገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆነ። ዩኒቨርሲቲው ያገኘውን ሽልማት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ደሳለኝ መንገሻ (ዶ/ር) ከፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ ተቀብለዋል።

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ስድስተኛ ዙር የጥራት ሽልማት ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተካሂዷል። በሽልማትና ዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ 40 ድርጅቶችና ተቋማት የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በውድድሩ ላይ

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ሐረር ቢራ አክሲዮን ማኅበር እና አማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት የአንደኛ ደረጃ ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የጥራት ደረጃውን ጠብቆ አሸናፊ በመሆኑ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

    The Ethiopian Quality Award Organization

    ከ336 በላይ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ጥሪ የተደረገ ቢሆንም የተመዘገቡት 52 ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ 21 በአምራች፣ አምስት በአገልግሎት፣ አራት በከፍተኛ ትምህርት፣ አምስት በጤና እና አምስት በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ፤ በድምሩ 40 ተቋማት እስከመጨረሻው በውድድሩ የዘለቁ ናቸው።

    የሽልማቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ሥራ ማበረታታት መሆኑ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ የሆኑት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጥራት ጉዳይ የሥነ-ልቦናና የፈረጠመ የኢኮኖሚ የበላይነት እንዲሁም የበለፀገ ማኅበረሰብ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል። የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከደረሱበት የጥራት ደረጃ ለመድረስ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በ2000 ዓ.ም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተቋቋመ ነው። ድርጅቱ ሲመሠረት ዓላማውን መንግስት በጥራት ረገድ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍና የጥራት ጽንሰ ሀሰብን በማኅበረሰቡ፣ በአምራቾች፣ በአገልግሎት ሰጪዎችና በግንባታ (ኮንስትራክሽን) ዘርፍ በተሰማሩ ድርጅቶችና ተቋማት ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ ነው። እስካሁን 49 ድርጅቶችና ተቋማት የድርጅቱን የልዕቀት ማዕረግ የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት


    Semonegna
    Keymaster

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ከኢትዮጵያም አልፈው በአፍሪካ አህጉር ለረዥም ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉ ግለሰብ ሲሆኑ፥ ለዚህም አገልግሎታቸው እ.ኤ.አ በኅዳር ወር 2015 የአፍሪካ ህብረት የክብር ሽልማት ሸልሟቸዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ለ52 ዓመታት በተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ኢትዮጵያን በመወከል በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ላባረከቱት አገልግሎት ከኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዕውቅና ተሰጣቸው።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የአገልግሎት የክብር እውቅናው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሰጣቸው ጥር 07 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው።

    ይህ ሽልማት አምባሳደሯ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ የዓለም ሀገራት፣ በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ተወካይና ዲፕሎማት በመሆን ላበረከቱት ስኬታማ አገልግሎት እንደተበረከተላቸው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ዘግቧል።

    አምባሳደር ቆንጂት በግብፅ ፣ በእስራኤል፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሀገራቸውን በዲፕሎማትነት በመወከል ውጤታማ ስራ ማስመዝገባቸው ተገልጿል።

    አምባሳደሯ ከምንም በላይ ሀገራቸውን በማስቀደም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽዖም ለሌሎቸ ዲፕሎማቶች አርዓያ የሚሆን ነው ተብሏል።

    ለአምባሳደሯ የተሰጣቸውን የክብር እውቅና ተገቢ እንደሆነ በመደገፍ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዲህ ብለው ጽፈዋል

    እህቴ፣ ባልንጀራዬ ክብርት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ረዥሙን የአገልግሎት ዘመን የያዙ ዲፕሎማት በዛሬው ዕለት ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚገባቸውን ሽልማትና እውቅና በማግኘታቸው እንኳን ደስ አላቸው! ደስ አለን! አገርን በጨዋነት፣ በታማኝነት፣ በታታሪነት የማገልገል ዋጋ ነው። ለሁሉም በተለይ በዛሬ ጊዜ ትልቅ ትምህርት ልንወስድበት ይገባል።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ለተደረገላቸው እውቅና ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ በቅርቡ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሀገሪቱ ትልልቅ ቦታዎች ላይ ሴቶች ሹመት እንዲያገኙ መደረጉንም አድንቀዋል።

    በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል የሚሠሩ ዲፕሎምቶችና አምባሳደሮችም ለሀገራቸው ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የተወለዱት በሐረር ከተማ እ.ኤ.አ. በ1940 ሲሆን፥ በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ከሚገኘው ለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እ.ኤ.አ በ1954 ዓለም አቀፍ ግንኙነት (International Relations) በዲግሪ ተመርቀዋል። እ.ኤ.አ በ1963 ኒው ዮርክ ከተማ፣ አሜሪካ ከሚገኘው የኮለምብያ ዩኒቨርሲቲ የካርኒጌ ፌሎውሺፕ (Carnegie Fellowship) አግኝተዋል። ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥረው መሥራት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1962፥ ይህም የአፍሪካ አንድነ ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) ከመቋቋሙ ከአንድ ዓመት በፊት ነው።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ከኢትዮጵያም አልፈው በአፍሪካ አህጉር ለረዥም ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉ ግለሰብ ሲሆኑ፥ ለዚህም አገልግሎታቸው እ.ኤ.አ በኅዳር ወር 2015 የአፍሪካ ህብረት የክብር እውቅና ሰጥቷቸዋል

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአምባሳደር ቆንጂት በተጨማሪም በተለያዩ ሀገራት በአምባሳደርነት ሲሠሩ ቆይተው በጡረታ ለተሰናበቱ ቀደምት ዲፕሎማቶች የዕውቅና ምስክር ወረቀት ሰጥቷል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄዱት ልዩ ስብሰባቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን 4ኛው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር (ፕሬዝዳንት) አድርጎ በሙሉ ድምፅ መርጧል።

    ፕሬዝዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሃላ ፈፅመው ኃላፈነታቸውን በትጋትና በታኝነት አገርና ህዝብን ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

    አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ላለፉት አመስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ላይ የነበሩትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ይሆናል። ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ከተመራጯ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።

    አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ማን ናቸው?

    ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው። አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝትው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵይ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

    ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ለመሾም ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ እንስት ናቸው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትም ሴኔጋል ሲሆን የአምባሳደርነት ስልጣናቸውም ሴኔጋልን ጨምሮ ማሊን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ጊዚ ቢሳውን፣ ጋምብያን እና ጊኒን (እ.ኤ.አ 1989–1993) ያጠቃልል ነበር። ቀጥሎም እ.ኤ.አ 1983–2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በኢጋድ (IGAD) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረሰ በፈረንሳይ (ሞሮኮን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።

    ከሀያ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እ.ኤ.አ በ2009 የተበባሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) በመቀላቀል የድርጅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተቀናጀ ሰላም ግንባታ መሪ (Head BINUCA) በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ይህ አገልግሎታቸውም ወደ ሚቀጥለው ኃላፊነት አሸጋግሯቸው እ.ኤ.አ በ2011 ዓም የዚያን ጊዜ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ ባን ኪ-ሙን (Ban Ki-moon) አዲስ ለተቋቃመው በናይሮቢ የተመድ ጽህፈት ቤት (UNON) የመጀመሪያዋ ጠቅላይ-መሪ አድርገው ሾማቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2010 የአሁኑ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬስ (António Guterres) አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በተመድ ጠቅላይ-መሪ ስር (Under-Secretary-General) የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተጠሪ (UN’s Special Representative to the AU) እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የተመድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ (Head of UNOAU) አድርገው ሾሟቸው እስካሁን ድረስ በዚሁ ሹመታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።

    አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሳህለወርቅ ዘውዴ


    Semonegna
    Keymaster

    የኢፌዴሪ መንግስት የፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመን የመልቀቂያ ጥያቄ ከተቀበለ ከሀያ ዓመታት በላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር በአምባሳደርነትና የኢትዮጵያ ተጠሪነት ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዝዳንት ሆነው እንደሚሾሙ የተለያዩ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

    አዲስ አባባ – ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ሀሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚውለው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 2ኛ አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ የሥራ መልቀቂያ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። የአስቸኳይ ስብሰባው ዋና አጀንዳ የፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመን የሥራ መልቀቂያ መቀበልና አዲስ ፕሬዚዳንት መምረጥ እንደሚሆን ተገልጿል።

    ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም ሲሆን ሶስተኛው ፕሬዚዳንትም (ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ቀጥሎ) ናቸው።

    ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ አርጆ ከተማ በ1949 ዓ.ም ነው የተወለዱት፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቻይና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍልስፍና፣ ሁለተኛውን በህግና ዲፕሎማሲ ከአሜሪካ፣ 3ኛ ዲግሪያቸውን ከቻይና ቤጂንግ ዩኒቨርስቲ በህግ አግኝተዋል።

    ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በጃፓንና በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ ከ1993-1994 ዓ.ም የግብርና ሚኒስትር፣ ከጥቅምት 1994-1998 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነውም አገልግለዋል። በፕሬዝዳንትነት እስከተመረጡበት ጊዜም በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነበሩ።

    ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በተለያዩ መስኮች ያከናወኑና በመምህርነትም ያገለገሉ ሲሆን ከአገር ውስጥ አማርኛና ኦሮምኛ ከውጭ ደግሞ እንግሊዝኛ፣ ቻይንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን መናገርና መጻፍ ይችላሉ።

    በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት የአንድ ፕሬዝዳንት አገልግሎት ጊዜ ስድስት ዓመት ሲሆን፥ አንድ ግለሰብ ከሁለት ጊዜ በላይ በርዕሰ ብሔርነት ሊመረጥ እንደማይችል ይደነግጋል። ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የመጀመሪያ ቨፕሬዝዳትነት አምስተኛ ዓመታቸው ነው።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን ከሀያ ዓመታት በላይ በሚኒስቴርነትና በአምባሳደርነት ያጋለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዝዳንት) ይሆናሉ ብለው ቅድመ ግምታቸውን እየሰጡ ነው። በዚህም አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ እንስት ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ማለት ነው።

    ለመሆኑ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ማን ናቸው?

    ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው። አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝትው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵይ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

    ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ለመሾም ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ እንስት ናቸው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትም ሴኔጋል ሲሆን የአምባሳደርነት ስልጣናቸውም ሴኔጋልን ጨምሮ ማሊን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ጊዚ ቢሳውን፣ ጋምብያን እና ጊኒን (እ.ኤ.አ 1989–1993) ያጠቃልል ነበር። ቀጥሎም እ.ኤ.አ 1983–2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በኢጋድ (IGAD) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረሰ በፈረንሳይ (ሞሮኮን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።

    ከሀያ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እ.ኤ.አ በ2009 የተበባሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) በመቀላቀል የድርጅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተቀናጀ ሰላም ግንባታ መሪ (Head BINUCA) በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ይህ አገልግሎታቸውም ወደ ሚቀጥለው ኃላፊነት አሸጋግሯቸው እ.ኤ.አ በ2011 ዓም የዚያን ጊዜ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ ባን ኪ-ሙን (Ban Ki-moon) አዲስ ለተቋቃመው በናይሮቢ የተመድ ጽህፈት ቤት (UNON) የመጀመሪያዋ ጠቅላይ-መሪ አድርገው ሾማቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2010 የአሁኑ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬስ (António Guterres) አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በተመድ ጠቅላይ-መሪ ስር (Under-Secretary-General) የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተጠሪ (UN’s Special Representative to the AU) እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የተመድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ (Head of UNOAU) አድርገው ሾሟቸው እስካሁን ድረስ በዚሁ ሹመታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።

    አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሳህለወርቅ ዘውዴ


Viewing 11 results - 1 through 11 (of 11 total)