-
Search Results
-
ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ አቶ አየነው በላይን በመተካት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።
ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ቴክሳስ (The University of North Texas) ተከታትለዋል። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ አት ኦስተን (The University of Texas at Austin) እና በሌሎችም በተመራማሪነት ማገልገላቸውም ታውቋል። የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአሜሪካና ካናዳ ማቅረባቸውም በግለ ታሪካቸው ተብራርቷል።
ዶክተር መሐሪ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሙያ ማኅበራት አባል መሆናቸውም ነው የተገለጸው። የአሜሪካ የስታትስቲክስ ማኅበር (American Statistical Association)፣ የአሜሪካ የትምህርት ጥናት ማኅበር (American Educational Studies Association)፣ የተቋማዊ ጥናት ማኅበር፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥናት ማኅበር፣ የደቡብ ምዕራብ የትምህርት ጥናት ማኅበርና የቴክሳስ የትምህር ጥናት ማኅበር አባል እንደሆኑም ነው የተገለጸው።
ከ13 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና የተለያዩ ትምህርቶችን በማስተማር እንደቆዩም ተገልጿል፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ማገልገላቸውም ነው የተነገረው።
ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስን ልምዳቸውንና የአመራር ብቃታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሄድ በጀመረው መደበኛ ጉባኤው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟቸዋል።■
ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የበላይ ባለ ኮኮብ 5 ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ፕላን በዘርፉ ባለሙያዎች ተገመገመ። የፕሮጀክቱ ዲዛይንና አማካሪ የሆኑት አቶ ነቢዩ ሰለሞን እንዳብራሩት፥ ሆቴሉ በ3,690 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ፣ 3 ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ 120 የመኝታ ክፍሎች፣ 2 ሬስቶራንቶች፣ ባር፣ ጂም እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች እንደሚኖሩት፣ ዲዛይኑ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ህንጻ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ መኮንን በበኩላቸው በቀረበው ዲዛይን መሠረት ገንቢ አስያየት በመስጠት ሆቴሉ ከታሰበው በላይ ተሻሽሎና ዳብሮ እንዲሠራ ባለሙያዎች የድርሻቸውን አንዲወጡ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቡና ስኒ በዲዛይኑ ላይ መካተቱ ከደብረብርሃን ጋር ምን ያገናኘዋል? የሠራተኞች ማረፊያ ክፈል፣ ሕፃናት መዝናኛ፣የመዋኛ ገንዳ መካተት አለበት የሚሉና እና ሌሎችም በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በመድረኩ ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከህንጻ ሹም፣ ከህንጻ ዲዛይን አማካሪዎች፣ ከባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የበላይ ባለ 5 ኮኮብ ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት የመሠረት ድንጋው ሲጣል መገለጹ የሚታወስ ነው።
ምንጮች፦ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ጠብቀው ከመሥራትና ማህበረሰቡን ከማስተማር ይልቅ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ የሚሠሯቸውን የዘገባ ስህተቶች እና አባባሽ ይዘቶች እንዲያስተካክሉ በቃልና በደብዳቤ እያሳወቅኩ ነው ይላል።
ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚፅፉት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ “የክልል መገናኛ ብዙሃን ወገንተኝነት እና ለገዥው ቡድን አጎብዳጅነት” እንደሚታይባቸው አንስተው፤ ብዙ ፖለቲካዊ ዘገባዎችን እና ትርክቶችን በተዛባ መልኩ የሚያቀርቡ እንደሆኑ ነው የገለጹት።
ዘውግ-ተኮር የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው ያለመዘገብ፣ ሀቅን እንዳለ ያለማቅረብና ሚዛናዊ አለመሆን እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፥ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ግጭት በሚስተዋልበት ወቅት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዳይዘግቡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስህተት የሚፈጽሙት ባለማወቅ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ ዓይነት ስህተት እንዲወጡ መጀመሪያ በማስተማር የተለየ ሁኔታ ሲያጋጥም በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ የሕዝብ ማስተማሪያ አልያም የጦር መሣሪያ የመሆን ዕድል ስላላቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሀሳባቸውን በመስጠት፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣልም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ሃይማኖት ጌታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ “ፅንፍ ይዞ እየተጓዘ” መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ለግጭት አባባሽ እየሆነ ነው ይላሉ።
በተለይ አንዳንድ “የፅንፍ ፖለቲካ” የሚያራምዱ ግለሰቦች የራሳቸውን መገናኛ ብዙሃን በመክፈት የሚፈልጉትን “ፅንፈኛና የጥላቻ አጀንዳ” እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል። በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በኩል ደግሞ “ሕዝብ ሲሞት እና ጉዳት ሲደርስበት ተከታትሎ ከመዘገብና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ መንግሥትን እየጠበቁ የመዘገብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል” ነው ያሉት።
መገናኛ ብዙሃኑ አስቀድመው የስጋት ትንተናዎችን በሚዛናዊነት በማቅረብ ግጭትን የመከላከል ሚና እየተወጡ አይደለም ያሉት አቶ ሃይማኖት፥ ብሮድካስት ባለስልጣንም ለመገናኛ ብዙሃኑ የተሰጣቸው ነጻነት እንዳይታፈን ጥንቃቄ በማድረግ፤ በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ባሉት ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደወሰን አንዱዓለም “የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ በተረበሸ ቁጥር መገናኛ ብዙሃኑም አብረው መታመማቸው ከፍተኛ ችግር አስከትሏል” ነው ያሉት።
አብዛኛው መገናኛ ብዙሃን ሕዝብን ከሕዝብ፣ ክልልን ከክልል፣ መንግሥትን ከሕዝብ የሚያራርቁ ዘገባዎችን እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች የሕይወት መልኮችን ትተው ፖለቲካ ላይ ብቻ የመጠመድ ችግር ይታይባቸዋል ነው ያሉት።
ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃኑን ሥራዎች መዝኖ እርምጃ ለመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፖለቲካዊ መስፈርት በመቀየር ሙያዊ መመዘኛ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፥ በመስፈርቱ መሠረት ድክመትና ጥንካሬ ተለይቶ እንዲያስተካክሉት ለተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ደብዳቤ መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።
“ሀገሪቱ ለውጥ ላይ ናት በሚል መገናኛ ብዙሃኑ የነውጥ አራጋቢ ሆነው እንዲቆዩ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ የፖለቲካ ሁኔታ በተረበሸ ቁጥር ሚዲያው አብሮ መረበሽ እንደለሌበትና በቅርቡ በሚወጣው የመገናኛ ብዘሃን አዋጅ ግልፅ ድንበር እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ አመራሮች በቦርድም ሆነ በሚዲያ መሪነት እንዳይሰየሙ በረቂቅ አዋጁ መቀመጡን አንስተው፥ መገናኛ ብዙሃኑ ከባለሥልጣኑ ጋር እንደ ‘አይጥ እና ድመት’ ከሚተያዩ እርስ በራሳቸው የሚተራረሙበት፣ የሚነጋገሩበትና የሚደጋገፉበት የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል መቋቋሙንም ነው የገለጹት።
“በልቅነት እየሠሩ ያሉትን ለማረም ሲባል በነጻነት ላይ ያሉት መጎዳት የለባቸውም” ያሉት አቶ ወንደወሰን፥ ችግሩን ለማረምና ሁለቱን ለመለየት ከውይይትና ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በቀጣይ በሕግ የተጠና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል በሚል በመሠረተው የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ) – የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) እንዲሁም አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ላይ ላደረሱትና ለሚደርሰው ጉዳት የ174.6 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ እስከሚያልቅ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ክስ እንዳቀረበባቸውና ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት እንደቀርቡ ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ጥምረት ለተሻለ ጤና) /ABH Partners/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት ኤጀንሲው የድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማጠልሸቱ ይቅርታ እንዲጠይቅና ችግሩን እንዲያርም ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
በዚህም ድርጅቱ ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ-ብሔር ስድስተኛ ምድብ ችሎት የመዝገብ ቁጥር 241863 ክስ ለመመሥረት ተገዷል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴን ጨምሮ አምስት የሥራ ኃላፊዎችም ተከሰዋል።
ኤጀንሲው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) ጋር በጥምረት የሚሠሩትን ሥራ እንደማያውቀው ቢያስተባብልም፤ ሁለቱ ተቋማት ውል ተፈራርመው ሥራውን ሲጀምሩ በወቅቱ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በቦታው ተገኝተው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው እንደነበር ዶ/ር ማርቆስ አስታውሰው፤ “ይህም መንግሥት አያውቀውም የሚለውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አመላካች ነው። ከወራት በፊት ትምህርት የሚሰጥበትን ቦታ ተገኝተው የጎበኙ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች ግን ‘ሥራው የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማዳበር ያገዘ ነው’ ሲሉ አሞካሽተውታል። ለጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመስጠት የመምህራን ፍልሰት እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱንና ለትምህርት ጥራት እንዲተጋ የሚያግዙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ሚኒስቴሩ ምስክርነቱን በደብዳቤ ሰጥቷል” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ፥ የዚህ መሰል የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነት ለትምህርት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ሚናው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፥ ለዚህ ሊበረታታ ለሚገባው ድርጅት አገራዊ ፋይዳውን በማየት የግንባታ መሬት በመስጠት ትብብር እንዲደረግላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የትብብር ደብዳቤ እንደፃፈላቸውም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ለዩኒቨርሲቲውና ለድርጅቱ ምስክርነት በመስጠት ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሲያደርግ፥ ኤጀንሲው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከሰጠው ሥልጣን ውጪ “ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቅና የለውም፤ ሕጋዊም አይደለም” በማለት እግድ ማስተላለፉ “ባለፉት ሰባት ዓመታት የት ነበረ?” የሚል ጥያቄንም የሚጭር እንደሆነ ዶ/ር ማርቆስ አብራርተዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራውን ሊሰራ፤ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊሰጥ በገቡት ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ባለው ካምፓስ ምንም ዓይነት የመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግለት ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ለመማር-ማስተማሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ በውሉ መሠረት ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ ማስተማርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችል ኤጀንሲው ቢገልጽም፣ በዩኒቨርሲቲው እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ግን ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል።
በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሟላት ድጋፍ ሊሰጣቸው ከሚችል ከማንኛውም ተቋም ጋር መሥራት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በዚህም በአዋጁ ያልተከለከለን ሥልጣን ኤጀንሲው በደብዳቤ መሻሩ ተገቢነት እንደሌለው ዶ/ር ማርቆስ ገልፀዋል። በመሆኑም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች በሁኔታው መደናገጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ (ቁጥር 650/2001) አንቀጽ 93፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች እንዲሰጥ ስለማድረግ ይደነግጋል። በዚህም ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስቀምጧል።
በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (ቁጥር 240/2003) በአንቀጽ ሦስት መሠረት የዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን፣ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ተቀምጧል።
ባለፉት 15 ቀናት ኤጀንሲው “የትብብር ሥልጠና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ” በሚል ሚኒስቴሩ በደብዳቤ ማሳወቁን መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መልኩ ሲሠሩ የነበሩ የጅማ፣ የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታገዱ አሳውቋል።
ሆኖም ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሥራቸውን በመቀጠላቸው “አደብ ሊገዙ ይገባል” ብሎም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በተቋማቱ በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች ዝርዝር እንዲላክለት የጠየቀ ሲሆን፤ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልገው አሳውቆ ነበር።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊው የበጎ ሰው ሽልማት ከግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዕጩዎችን ሲጠቁሙ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ በተጠቀሰው የጊዘ ገደብ ውስጥም በ አጠቃላይ 291 ሰዎች ተጠቁመው 27 ዕጩዎች ለዳኞች ውሳኔ ቀርበዋል ለመጨረሻው የዳኞች ውሳኔ መቅረባቸውን የበጎ ሰው ሽልማት አስተባባሪዎች በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
እንደወትሮው ሁሉ በሽልማቱ ዕጩዎች የተጠቆሙባቸውና ሽልማት የሚያሰጡት አስር የተለያዩ ዘርፎች ናቸው። በእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ የቀረቡት ዕጩዎች የሚከተሉት ናቸው።
በመምህርነት ዘርፍ
- ፕሮፌሰር ሽታዬ ዓለሙ ባልቻ (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ)
- ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል
- ዶ/ር መስከረም ለቺሳ ደበሌ (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ሥነ-ባህሪ ኮሌጅ)
በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)
- ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ
- ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ
- ዶ/ር ታደለች አቶምሳ
በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ
- አቶ ሚካኤል ፀጋዬ
- አቶ በዛብህ አብተው
- አቶ ዳኜ አበራ
በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)
- ዶ/ር ጀምበር ተረፈ
- አቶ አብድላዚዝ አህመድ
- አቶ ላሌ ለቡኮ
በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ
- አቶ ዳንኤል መብራቱ
- አቶ ክቡር ገና
- አቶ ነጋ ቦንገር
በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት
- አቶ በትሩ አድማሴ (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩ)
- ዶ/ር አሚር አማን (የአሁኑ የጤና ሚኒስትር)
- አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ
በቅርስና ባህል ዘርፍ
- አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)
- አርሶ አደር አቶ አድማሴ መላኩ (በምስራቅ ጎጃም ዞን በጮቄ ተራራ አካባቢ የሚገኘውን ‹‹አባ ጃሜህ›› ደን ለ52 ዓመታት በግል ተነሳሽነት ሲጠብቁና ሲንከባከቡ የነበሩ)
- ሳሙኤል መኮነን (ከጎንደር)
በሚዲያና ጋዜጠኝነት
- አቶ በልሁ ተረፈ
- አቶ አማረ አረጋዊ
- ወ/ሮ አንድነት አማረ
በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች
- አቶ ኦባንግ ሜቶ
- አርቲስት ታማኝ በየነ
- ፕሮፌሰር ፀጋዬ ታደሰ
በተጠቀሱት የሽልማት ዘርፎች ከእያንዳንዳቸው አንደኛ ሆነው የሚመረጡት ዕጩዎች በተመረጡበት ዘርፍ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ተብለው ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ይሸለማሉ።
ባህር ዳር (አብመድ)፦ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ሹመታቸው የጸደቀላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለምክር ቤት አባላትና ለሕዝቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንትነት ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ንግግር ያደረጉት አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት ምክንያት ሳይሆኑ በሕግ እንዲመለሱ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገቱም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ለኢንቨስትመንት ዕድገትም አትኩሮት እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስከትለውም “የሕግ የበላይነትን ማስፈንም ለነገ የምንለው ጉዳይ አይሆንም” ብለዋል ለአማራ ክልል ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት።
ለመሆኑ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ማን ናቸው?
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ወረዳ ወይራ ቀበሌ ነው የተወለዱት። ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እስከ ፌዴራል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል።
በትምህርት ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቀያቸው በጎተራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ የመለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በብቸና በሚገኘው የበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከማይክሮሊንክ ኮሌጅ በሶፍትዌር ዘርፍ እና የሁለተኛ ዲግሪቸያውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ (University of Greenwich) በለውጥ አመራርና አስተዳደር ተከታትለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ በ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በፌደራል መንግስት ደረጃ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።
በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሠርተዋል።
ፌደራል መንግስት ደረጃ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Information Network Security Agency) ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም አገልግለዋል።
አቶ ተመስገን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም እስከ ሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሥራች ከመሆን ባለፈ በዚሁ መሥሪያ ቤት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነትም አገልግለዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲ፣ ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” በሚል ቃል የተዘጋጀው 5ኛው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባዔ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲሐቂ ካምፓስ ሲካሄድ ቆይቶ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ሰኔ 2 ቀን 2011ዓ.ም. ተጠናቋል።
በጉባዔው መክፈቻው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ክብርት ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ያስተላለፉት መልዕክት “አገራችን ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ብዝሃ-ባህል ያለን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር መሆናችን እንደአፍሪካ አህጉር መልካም አጋጣሚዎች ቢኖረንም ያሉንን ባህላዊ እሴቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን አስተዋውቀን በሚገባ አልተጠቀምንባቸውም። የራሳችን የሆነ ፊደልና የግዕዝ ቋንቋ ያለን ሲሆን፣ እነዚህ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው በጥናትና ምርምር እየተደገፈ በመሰነድ ለትውልድ ማስተላለፍ የሁላችን ኃላፊነት ሆኖ ይገኛል ካሉ በኋላ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላለፉት አራት ዓመታት ተመሳሳይ የጥናትና ምርምር መድረኮች የተካሄዱበት አግባብና ውጤታማነት ሲገመግም ጉባዔዎች በተባባሪ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በጋራ የሚካሄዱ መሆናቸው እንደ ጥሩ ጅምር የሚወሰድ ነው ብለዋል።
አክለው ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ጉባዔያቱ በቋንቋው ጥናት ዙሪያ ያሉ ጠቃሚ ልምዶች፣ በቋንቋው ጥናት አስፈላጊነት በቂ ግንዛቤ ያገኘንባቸው ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። የዘንድሮው የመቀሌ ጉባዔ ለየት የሚያደርገው ከግዕዝ ወጣ ብሎ በሥነ-ፈውስ ላይ ትኩረት ማድረጉ ጭምር መሆኑ ነው። የግእዝ ቋንቋ በሥነ-ፈውስ ደረጃ ምን ይላል የሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥባቸው፣ አቅጣጫና መፍትሄ የሚቀርብባቸው ጥናታዊ ጽሑፎች በጉባዔው የሁለት ቀን ውሎ ይቀርባሉ ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል።ሥነ-ፈውስ ኅሊናዊ፣ ሥነ-ፈውስ ሥጋዊ፣ ሥነ-ፈውስ መድኃኒታዊ፣ ሥነ-ፈውስ መንፈሳዊ፣ እያልን ብዙ ነጥቦችን ማንሣት እንችላለን። ሰው በጎ አስተሳሰብ እንዲኖረው፣ ለአገር፣ ለወገን፣ እንዲኖር ጤናማና ያልተዛባ አእምሮ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ሁሉን ጎጂ አድርጎ የሚመለከት አእምሮዊ ህልውናዊ እንደሚያስፈልገው አምናለሁ። በዚህ ጉባዔ የስነ-ፈውስ ደረጃ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ መልስ የሚሰጡ አማራጮችን በስፋት መዳሰስና በጉባዔው ማጠቃለያም የተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎና ውይይት ለቋንቋው ልማት ለምናካሂደው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ምክረ-ሀሳቦች እንደሚመጡ ያለኝ ተስፋ ላቅ ያለ ነው በማለት መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ጉባዔው በይፋ አስጀምረዋል።
5ኛው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባዔ በተያዘለት መርሃ-ግብሮች መሠረት በግእዝ ላይ የተደረጉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ገለፃና ውይይት ተደርጎባቸዋል። እነዚህም ግዕዝና ሥነ-ፈውስ በመጋቤ ምስጢር ፍሬስብሃት ዱባሌ (ከኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን)፣ ግዕዝና ለፈውስ የሚደረስ ጸሎት በዶ/ር አባ ዳንኤል አሰፋ (ከፍራንቺስኮ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ)፣ ግዕዝና የባህል መድሃኒት በመጋቤ ምስጢር ስማቸው ንጋቱ (ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ)፣ ዘይትረከቡ በውስጠ ልሳነ ግዕዝ ሕቡኣነ ስመ እግዚአብሔር ዘይህቡ ፈውሰ ድኅነት በአቶ ሃፍተ ንጉስ (ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ)፣ ግዕዝ (The General Features of the Geez Magical Texts) በአቶ ጉኡሽ ሰለሞን (ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ)፣ ጸበልና ማየ ጸሎት በግዕዝ ባህል ወፊዚክስ በዶ/ር ሀጎስ አብርሃ (ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ) ይገኙበታል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ.) ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከሰኔ 1-2 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” በሚል መሪ ቃል በመቐለ ከተማ ለሚካሄደው 5ኛውን የግዕዝ ጉባኤ ቀንን አስመልክቶ መረጃውን አስቀድሞ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንቦት 26 ቀን 20011 ዓ.ም. ተሰጥቷል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን በጥምረት የሰጡት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው፣ የብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐጎስ አብርሃ ናቸው።
እንደኃላፊዎቹ መግለጫ፥ በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በርካታ በመሆናቸው ልንማርበት፣ ልንጠቀምበትና ልትውልድ በማሸጋገር ወደ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ማምራት ይቻላል። በመሪ ቃሉ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” ስንል እንደየባህሉ ሥነ-ልቦናን፣ ፀሎትን፣ ሥነ-ቃልን ለማወቅና መዳንን የሚያበረታታታ ሀገር በቀል ዕውቀት መሆኑንማወቅ ስላለብን፣ ብሎም ስለግዕዝ ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም በሀገራችን በርካታ ጥንታዊ የጽሑፍ ሀብቶቻችን የምናገኝበት በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ በመሆኑ፣ ጥንታዊ የስልጣኔ መገለጫ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በሀገራችን በግዕዝ ቋንቋ በተሠሩ ሥራዎች ላይ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 750,000 በብራና ላይ የተፃፉ መጽሕፍት መኖሩ ታውቋል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው
- ጉዞ ዓድዋ ― ታላቁ የዓድዋ ድልን የሚገባው የታሪክ ማማ ላይ ለመስቀል የሚጥር ኢትዮጵያዊ ማኅበር
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን ከእንግሊዝ ሀገር አቻው ጋር ውይይት ተደረገ
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከዓርብ ጀምሮ እስካሁን በውል ባልታወቀ ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
ደብረ ማርቆስ (ቢቢሲ አማርኛ)– በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱን ተማሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ። ሟች ሰዓረ አብርሃ እንደሚባልና የሦስተኛ ዓመት የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል (economics department) ተማሪ እንደነበረ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።
በዩኒቨርስቲው ከዓርብ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደሳለው ጌትነትም በተቋሙ ከባለፈው አርብ (ግንቦት 16 ቀን) 12 ሰዓት ጀምሮ ግጭቶች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም አርብ ግንቦት 16 ላይ 3 ልጆች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረው ልጆቹ አሁን ሆስፒታል ይገኛሉ ብለዋል። የተጎዱት ተማሪዎች በባህር ዳር እና አዲስ አበባ ሪፈራል ተጽፎላቸው ወደዚያው መወሰዳቸውንም ጨምረው ያስረዳሉ። በግጭቱ ሁለት ተማሪዎች በድንጋይና በስለት ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን እማኞቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በተፈጸመበት ጥቃት ምክንያት አንደኛው ተማሪ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉንና ሌላኛው ተማሪ ደግሞ ለሕክምና እርዳታ ወደ ባህር ዳር መወሰዱን ከተማሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።
የረብሻውን ምክንያት እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አርብ ዕለት ተሳትፎ የነበራቸውን የተወሰኑ ልጆች ፖሊስ ተከታትሎ ከግቢ ውጭ ይዟቸው ፖሊስ ጣቢያ ስለሚገኙ ጉዳያቸው እየተጣራ ነው በማለት የግጭቱ መንስዔ ከዚያ በኋላ ተጣርቶ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ የተጠለሉ ተማሪዎች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን ትላንት የሟችን አስክሬን ለመሸኘት የተሰበሰቡ ተማሪዎችም “ትምህርቱ ይቅርብን ወደ መጣንበት መልሱን” በማለት ለዩኒቨርሲቱው ፕሬዚዳንት ጥያቄ ማቅረባቸውን ነግረውናል።
የዚህን ዜና ተጨማሪ መረጃ ቢቢሲ አማርኛ ላይ ማንበብ ይቀጥሉ።
ከዚያው ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) ዘግቧል። በቀጣይም ከ967 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለአብመድ በጻፈው ደብዳቤ እንዳመላከተው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች 967ሺህ 786 ብር ከወር ደመወዛቸው አዋጥተው ድጋፍ አድርገዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በሚደረገው አገራዊ እና ክልላዊ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ተማሪዎችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ከዚህ በፊት ሠራተኞች እና ዩኒቨርሲቲው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋሙ አንድ ሚሊዮን ብር በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።
ምንጮች፦ ቢቢሲ አማርኛ እና አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ