Home › Forums › Semonegna Stories › ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን) › በፊትም፣ አሁንም እስትንፋሷ በመሪዋ ላይ ብቻ የሆነባት ሀገር
በፊትም፣ አሁንም እስትንፋሷ በመሪዋ ላይ ብቻ የሆነባት ሀገር
(ጋዜጠኛ መላኩ ብርሀኑ)
እንደአለመታደል ሆኖ የዚህች ሀገር ሰላምና ደህንነት ተጠቃሎ በመሪዎቿ በሰላም ውሎ በሰላም የማደር መዳፍ ውስጥ የገባው ዛሬ አይደለም።
እንኳን በሰላም ጊዜ ሀገርን መምራት ቀርቶ በጦርነት የማሸነፍና ወጥሮ የመዋጋት ነገር እንኳን የንጉሡን በህይወት መኖር የሚታከክ ነገር ነበር – እዚህ ሀገር። እልፍ ሆኖ ተሰልፎ ድል በእጁ መግባቱን እንኳን እያወቀ ንጉሡ ከተመታ ጦሩ በቀላሉ ይፈታል። ሕዝቡ ንጉሡ ከሌሉ ሀገር የለም እየተባለ ሲሰበክ ነው የኖረው።
እናቶች ንጉሥ ከሌለ የሚመጣውን መአትና እልቂት በመፍራት ለንጉሡ ረጅም ዕድሜ ከመመኘት በላይ “ከንጉሡ በፊት እኔን አስቀድመኝ” ብለው ይጸልዩም ነበር። ምኒልክ ሲሞቱ የሞታቸው ዜና ለሕዝብ ሳይነገር ስንት ዓመት ፈጀ? መልሱ ይኸው ነው። አጼ ኃይለሥላሴ አንድ ነገር ቢሆኑ ሀገር ያበቃላታል ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ደርግ በቮልስዋገን ከቤተ መንግሥት ይዟቸው ሲወጣ ሲያዩ ነው ወደሩሃቸው የተመለሱት።
መንግሥቱ ኃይለማርያም በተራው በኢህአፓ የመግደል ሙከራ ሲደረግበት “ሞተ” ተብሎ አብዮቱ የእልቂት እንዳይሆን (ላይቀርለት ነገር) አደባባይ ወጥቶ ነው እግሩን እጥፍ ዘርጋ እያደረገ ነው “አለሁ” ያለው። መለስ ዜናዊ ሞተ ሲባልም በርካቶች በዚሁ “ሀገር ያበቃላታል” ፍርሃት ውስጥ ነበሩ። እነበረከት አደባባይ ወጥተው “ታጋይ ያልፋል ሀገር ይቀጥላል” ዓይነት ነገር ተናግረው ስጋት ቀንሰዋል።
የዛሬው መሪ አብይ አህመድ ጉዳይ ግን ከነገሥታቱ በኋላ ካሉት መሪዎች ሁሉ በብዙ ይለያል። ጊዜው ጥቂት ቢሆንም ቅሉ ሃሳቡንና አመራሩን ተቋማዊ ማድረግና ግለሰባዊ ተጽዕኖውን በጥቂቱም ቢሆን ለመቀነስ አልቻለም። ስለዚህ አብይ ተወደደም ተጠላ አሁን ባለው አስተዳደር ውስጥ ብቸኛና መተኪያ የሌለው መሪ ነው።
አብይ አህመድ እና ጓዶቹ ሲሠሩለት እና ሲያስተዳድራቸው የኖረውን ኢህአዴግ የተባለ ተቋም ከውጭ በነበረ ተቃውሞ ታግዘው ከውስጥ በመፈርከስ ቀንብሩን ከላያቸው ገርስሰው የጣሉ የግለሰቦች ስብስብ እንጂ የተደራጀ ተቋም አልነበሩም። የለውጡ መሪዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች በመሃል እየተንጠባጠቡ አብይ ብቻ ሲቀር፣ ቀርቶም ብዙዎች ያደነቁትን ለውጥ እያመጣ ሲቀጥል ብቻውን ገንኖ ወጣ።
አብይ ከመጣበት ማኅበራዊ መሠረቱ አካባቢ የገጠመው ተግዳሮት አሁን ድረስ በብርቱ ቢገርመኝም በሰሜን አካባቢ ካሉ ሰዎች ዘንድ የተጠላ ሰው መሆኑ ግን አይደንቀኝም። በካልቾ ብሎ ከወንበራቸው ላይ ያባረራቸው ሰዎችና “ገዢነት ካለኛ ለማን!?” ያሉ ጀሌዎቻቸው ሊወዱት አይጠበቅም። ይህም ከዚያ ሰፈር በአብይ ጥላቻ ሳቢያ ሀገር እንድትበተን የሚሠሩና የሚመኙ ድኩማን እንዲፈለፈሉ ምክንያት ሆኗል። መተከል ላይ እየሆነ ባለው “መሪና አቀነባባሪ” ብለው እሱ ላይ ጥርስ የነከሱበት፣ “ወለጋ ላይ ቢገኝ እኔን አያርገኝ” ያሉ የበረከቱበት፣ በመጋቢት መጥቶ በሰኔ ሞቱ የተደገሰለት ሰው ነው አብይ።
ሰውየው የሀገሪቱን ፖለቲካ ብቻውን እየዘወረ፣ በዚህም በዚያም ሁሉን ነገር ብቻውን እየሠራ፣ አውቆም ይሁን ሳይታወቀው ያለምንም ቀሪ ብቻውን የቆመ፣ የማይካፈል ቁጥር ሆኖ ወጣ። ዛሬ በሰሜን ለተፈጠረውም፣ በደቡብ ላለውም፣ በመሃል ለሆነውም፣ በምዕራብ ለተከሰተውም ችግር ሁሉ ተጠያቂው አብይ ነው የሚል አቋም ባላቸው በርካታ አካላት ሲሰደብ ውሎ የሚያድረው ሰውዬ ወዲህ ጦር እያዘዘ፣ ወዲህ ሀገርና ከተማ እየለወጠ ብቻውን ሲሠራ አጠገቡ የሚተካው ቀርቶ የሚመስለው እንኳን አለማየታችን ፈሪ አድርጎናል።
[ሰሞኑን] አብይ [ሞተ/ታመመ] ምናምን ሲባል ድንጋጤው የበረታው ከርሱ ሞትም በላይ ነገ ሊሆን የሚችለውን እያሰበ ሁሉም ሰላምና ደህንነቱ ስላስጨነቀው ነው፤ ይህ አለመታደል ነው።
በግሌ ኢትዮጵያን በከረጢት ውስጥ እንዳለ የተፈጨ ዱቄት፣ አብይን ደግሞ ከረጢቱን የዝቅዝቆሽ አዝሎ ጫፉን በእጁ ጨምድዶ እንደያዘው ተሸካሚ ዓይነት ነው የምመስላቸው። የከረጢቱ ጫፍ ከተለቀቀ ዱቄቱ ከአፈር ይደባለቃል። ይሄ ነው የሚያስፈራኝ።
አብይን በብዙ የማደንቀው መሪ ቢሆንም በዚህ “the one and only” አካሄዱ ግን ቅሬታ አለኝ። ስለዚህ የእርሱን ደህንነት አጥብቄ የምመኘው በግል ለርሱ ባለኝ ጥሩ ስሜት እና ከፍ ያለ አድናቆት ብቻ ሳይሆን በዋናነት ለዚህች ሀገር ሰላምና መረጋጋት፣ ሲቀጥል ለሕዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት፣ ጠበብ ሲል ለቤተሰቤ ደህንንት፣ በጣም ሲጠብ ለራሴ ደህና ወጥቶ ደህና መግባት ብዬ ነው።
ሰሜኑ አቅሙ ከነሞራሉ ቢደቅቅም ቂሙ ግን ከምንጊዜውም በላይ ጠንኖ ሀገር ብትፈርስ ደስ እንደሚለው በአደባባይ በሚናገርበት፣ ምዕራቡ በፈሪ ዱላ ጫካ ለጫካ እየተሯሯጠ የተሸከመውን መሣሪያ አፍ እያስከፈተ ንጹኃንን በሚረፈርፍበት፣ ከውጭ ግብጽና ሱዳን ቤንዚን በጀሪካን ይዘው እሳታችን ላይ ለመድፋት አጋጣሚ በሚቋምጡበት፣ ብቻ በየትኛውም መስመር ለዚህች ሀገር መልካም የሚመኝ በታጣበት በዚህ ጊዜ አብይ አንድ ነገር ቢሆን ስርዓት ሲናድና ነገር እንዳልነበር ሲሆን ሰዓት የሚፈጅበት አይመስለኝም። ሌሊት እንኳን ቢሆን በርህን ለመስበር እስኪነጋና ከእንቅልፍህ እስክትነቃ እንኳን የሚጠብቅህ የለም!
በበኩሌ በመሪ ደህንንት ላይ የተንጠለጠለች ሀገር ይዘን ዛሬ ድረስ መኖራችንን ስታዘብ ያለመታደል እለዋለሁ።
ሰውየውን መደገፍና መቃወም ሌላ ነገር ሆኖ የማንክደው ሃቅ ግን አሁንም ሰላማችን በዚህ ሰው ደህና መሆንና አለመሆን የተወሰነ ሆኖ መዝለቁ ነው። ስለዚህ የተወራበት እንኳን ሀሰት ሆነ! አሹ! ብያለሁ። እንደሰው ሳስብ ደግሞ አብይን ሞት ቀርቶ ጭረት እንዲነካው አልመኝም። [እርሱም ቢሆን] እንደማናችንም የሰላም እንቅልፍ ተኝቶ ማደር አይጠላም። ሀገር ብሎ መሰለኝ የጋለ ምጣድ ላይ የተቀመጠው።
በግሌ ግን መንግሥት ይሁን አስተዳደር ተቋማዊ ሆነው “ሰዎች ያልፋሉ፣ ሀገር ግን ትቀጥላለች” የምንልበትን ዘመን እናፍቃለሁ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።