-
Search Results
-
Topic: አሸናፊን የራሱ የሚያደርግ ብልህ ሕዝብ
[በዚህ ጽሑፍ ላይ አማራ ብዬ የጠቀስኩት ማኅበረሰብ በአሰፋ ጨቦ ትንታኔ መሠረት ሲሆን፥ ዘርን ሳይሆን የአባቶቻችንን ድል እና ኃያልነት የተቀበለውን፣ የማሸነፍ መንፈሱ የማይደረመስ ተራራ የሆነውን፣ በየሄደበት ሁሉ የአባቶቹን ድል አድራጊነት እያሰበ የበታችነትን እንቢ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚመለከት ነው።]
አሸናፊን የራሱ የሚያደርግ ብልህ ሕዝብ
(ሙሉዓለም ጌታቸው)
የዛሬ አንድ ወይም ሁለት ዓመት ፌስቡክ ላይ በአንድ የኦሮሞ አክቲቪስት ተጽፎ ብዙ ሰው የተለዋወጠው ጽሑፍ ነበር። ጽሑፉ ኦሮሞ ጀግኖቹን አሳልፎ የሚሰጥ ባህል አለው ብሎ ይከራከራል። አማራ* ደግሞ የሌላን ጀግና ሳይቀር የራሱ የማድረግ፣ የማጠጋጋት ባህል አለው ይላል። ይሄ ጽሑፍ ባሰብኩት ጊዜ ሁሉ ይገርመኛል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ አንቱታን ያተረፉ ጀግኖች አብዛኛው ከኦሮሞ ናቸው፤ ነገር ግን የሚያከብራቸው እና የሚወዳቸው አማራው ወይም ሌላው ብሔር ነው። በተቃራኒው በሕይወት በነበሩበት ዘመን ሳይቀር ከሃዲ፣ የአማራ ተላላኪ እያለ ሲሰድባቸው የነበሩትን ልክ ሲሸነፉ ወይም ሲመቱ የራሱ አድርጎ የመቀበል እና ሞታቸውን የእሱ የማድረግ ባህል ቢያንስ በእኔ ዕድሜ በማውቀው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ የሰረጸ ባህል ይመስላል።
ኃይሌ ፊዳ ጎበና እየተባለ መከራውን እንዳየ እንደተሰደበ ደረግ ጭዳ አደረገው። አሁን ደግሞ ለብዙ የኦሮሞ የዘመኑ ጎበዞች ጃዋርን ጨምሮ ኃይሌ ፊዳ የኦሮሞ ጀግና እየተደረገ ሲቀርብ እና ለትግል ማነሳሻ ሲውል መመልከት የተለመደ ሆኗል። “The Ethiopian Revolution and Its Implication” በሚል ርዕስ በአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤ. (CIA) እ.ኤ.አ. በማርች 1977 (March 1977) ተዘጋጅቶ በጥብቅ ምስጢርነት ለአሜሪካው የሥራ አስፈጻሚው አካል የቀረበው ሰነድ መንግስቱ ኃይለማርያም ኦሮሞ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ፥ በንጉሡ ወዳጆች ከስልጣን የሚፈነቀል ከሆነ “በኦሮሞነቴ” ወይም “ኦሮሞ” ስለሆንኩ ከስልጣን አባረሩኝ ብሎ ዘሩን ሊጠቀምበት እንደሚችል ትንቴውን ያቀርባል። “እንደዚህ ዓይነት አደጋ ካልገጠመው ግን ኦሮሞነቱን የማሳየት (ለስልጣን ሲል ማለቱ ነው) ዝንባሌ አይታይበትም” ይላል የስለላው ሰነድ። ተመልከቱ የሚሸነፍ ከሆነ በኦሮሞ የዘር ጉርጓድ ውስጥ ሊደበቅ ይችላል እያለን ነው (ሽንፈቱን እንጂ ድሉን ለኦሮሞ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም ማለቱ ነው)። ይሄ በዘመኑ ሳይቀር በራሳቸው የዓለም ትግል ሲሸነፉ ኦሮሞነታቸውን (ዘራቸውን) ለውድቀታቸው ሰበብ የማቅረብ ዝንባሌ እንዳለ ከማሳየቱ ባሻግር፥ ሲሸነፉ የራሱ የሚያደርጋቸው ማኅበረሰብ እንዳለ ይነግረናል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከአባታቸው መኮንን ጉዲሳ የተወለዱ ኦሮሞ ናቸው። በዓለም የተደነቁ፣ ዘመናዊ ኢትዮጵያን በዘመናዊ ተቋም የመሠረቱ፣ እጅግ አስደናቂ መሪ ናቸው። ኢትዮጵያ በእሳቸው ጊዜ የነበራትን ዝና ለመመለስ ቢያንስ 100 ዓመት በትንሹ ሊያስፍልጋት ይችላል፤ እሱም ጠንክረን ከሠራን። በርግጥ ፍጹም ሥልጣን የሚወዱ በመሆናቸው ፍጻሜያቸውን ክፉ አደረጉት። ንጉሡን የሚወዳቸው እና የራሱ ያደረጋቸው ግን ማነው? አማራው! በእሳቸው ዘመን ክፉኛ የተጨፈጨፉ ሁለት አመጾች አሉ። አንዱ የቀዳማይ ወያኔ ትግል በትግራይ ሲሆን ሌላኛው የጎጃም አመጽ ነው። የጎጃምን አመጽ ድባቅ የመቱበት ዘግናኝ ክስተት የታሪክ ጸሐፊዎች እንኳ ቃላት ያጡለት ነው። ግን ዛሬ ለሃውልታቸው መሠራት፣ ለስማቸው ክብር የሚቆመው ይሄው አማራው ነው። ምክንያቱም ጀግናን የራሱ የማድረግ ሥነ-ልቦና አለው። ሰቅለው ለገደሉት ለበላይ ዘለቀ እየዘፈነ ፥ ለእሳቸው ክብርና ዝና ዜማ ሲያወርድ ምንም አይጣላበትም። ድንቅ ሥነ-ልቦና። ኦሮሞው ደግሞ የመኮንን ጉዲሳን ሃውልት ሐረር ላይ አፍርሶ፣ ሰው ሀገር ላይ ሎንደን (London) ደግሞ የሳቸውን ያፈርሳል። ምክንያቱም ተሸናፊን እንጂ አሸናፊን የመቀበል ሥነ-ልቦና አላወረሱትም። የተቆረጠ የጡት ሃውልት ለልጆቹ ዘወትር እያሳየ፥ በባዶ እግሩ የሚሄድ ከእሱ በምንም የማይሻለው አማራ አደረገው ይላቸዋል። ልጅ በውስጡ ፍርሃት ይሰርጽበታል። የተሸናፊው ዘር አባል መሆኑ በራሱ የሚፈጥርበት የሥነ-ልቦና ቀውስ ቀላል አይደለም። ከዛ ሕይወቱን በጥላቻ መነጽር መመልከት ይጀምራል። ጥላቻ ደግሞ የሽንፈት ዋስታና ነው።
በቅርቡ ቤት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በእናቱ አማራ ነው እያለች አንድ ዘመዳችን በደስታ ትፈነድቃለች። ጠቅላዩ ብዙም አልቆየም፤ በOBN ላይ ቀርበው በእናታቸውም በአባታቸውም ኦሮሞ እንደሆኑ ገለጹ። ይሄውልሽ ተሳስተሻል ስላት፥ እሱ ነው የተሳሳተው አለችኝ። ቀጥላም የሰላም ኖቤል ሽልማት ሲቀበል አስተዋዋቂዋ በእናቱ አማራ እንዲሁም በአባቱ ኦሮሞ እያለች የተናገረችውን አሳየችኝ። ይሄ እኮ እሱ የተናገረው ሳይሆን እነሱ በስማ በለው ጽፈው ያቀረቡት ነው። ደግሞ ካስተዋልሽው በእናቱ አማራ ስትል እኮ ሳቀ። ይሄም የሚጠቁምሽ ነገር አለ ስላት፥ “ችግር የለውም እኔ ነው ብያለው፤ ነው!” አለችኝ። ይሄ አሸናፊን፣ ጀግናን የራስ የሚያደርግ፣ የሚቀበል ሥነ-ልቦና እንዲሁ በከንቱ የመጣ አይደለም፤ ሲገነባ የቆየ እንጂ። በእውቀቱ ስዩም ኢትዮጵያውያን ‘እኛ በዚህ ነገር አንደኛ ነን’ የማለት ሥነ-ልቦና አለን ይላል። “ለምሳሌ እኔ የቤቱ ሦስተኛ ልጅ ብሆንም ለሰው ስናገር ግን” ይላል፥ “ከቤታችን ሦስተኛ በመሆን አንደኛ ነኝ ብዬ ነው” በማለት የባህላችንን ራስን ከፍ የማድረግ ድንቅ ሥነ-ልቦና ይገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ነገ ቢገደል ወይም አንድ ነገር ቢያደርጉት ኦሮሞ ስለሆነ ተገደለ ብለው አሁን የምታይዋቸው እሱን የሚቃወሙ የኦሮሞ ጎበዞች የራሳቸው ጀግና ያደርጉታል። እሱም ይሄን ሥነ-ልቦና ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሥልጣኑ ባልጸናበት ወቅት “ከቡራዩ ጠቅላያችን ተነካ ብለው ወጣቶች ሲመጡ፥ ኦሮሞ መምራት አይችልም እያሉ” ምናምን እያለ ሆዳቸውን እያባባው ነበር። በበታችነት ሥነ-ልቦና ትልቅ ሀገር መገንባት እንደማይቻል ጠንቅቆ የሚያውቀው አብይ ይሄን “rhetoric” ብዙ አልገፋበትም። ደካማ አድርጎ ራሱን ዘወትር የሚስል ማንም፥ በዙሪያው ባሉ ሊከበር እንደማይችል ያውቃል’ና፤ በተለይ በፖለቲካ። አብይ ጠንክሮ ሲወጣ፣ ኮስታራ መሪ ሲሆን፣ ቀጥ ለጥ አድርጎ ሲገዛ ሲሰድቡት የነበሩ የአማራ አክቲቪስቶች ሳይቀሩ መልሰው በፍቅሩ እያበዱለት ነው። አማራው የተቀረጸበት እና ያደገበት ሥነ-ልቦና ከጀግንነት እና ከቆራጥነት ጋር እጅግ የተሳሰረ ነው። ባለፉት 30 ዓመታት በኦሮምኛ የተዘፈኑ እና የአማርኛ (በተለይ የባህል) ዘፈኖችን ቁጭ ብላችሁ አነጻጽሩ። አሁን የምናገረው እንደ ጉድ ይታያችኋል።
ሀጫሉ ሁንዴሳ ከሌላው ዘፈኝ በተለየ ይሄ በጣም የገባው አዋቂ ዘፋኝ ነበር። ኦሮሞ ተገፋ፤ ጡት አስቆረጠ፤ ተኮረኮመ የሚሉ ዘፈኖች እምብዛም የሉትም። የአድዋ ድል ሲመጣ እነ ግርማ ጉተማ ይሄ ድል እኛን አይመለከተንም፤ እነ ጸጋዬ አራርሳ እኛ ለሌላ ቅኝ ግዛት የተዳረግንበት ነው ብለው በድል ቀን ሲያለቃቅሱ ሀጫሉ ግን ፈረሱ ላይ ጉብ ብሎ ባለፉት 28 ዓመታት ባልተለመደ መልኩ ይሄ ድል ከማንም በላይ የኛ ነው እያለ መስቀል አደባባይ ወጣ። የአድዋ ተራራ ሄደን ትግራይ የኛ ናት ያልነው ኦሮሞዎች ነን አለን። ታሪክ ብዙ ነገሩ ተረት ነው። ዋናው ቁም ነገር የሰው ልጅ እጅግ ኢ-ምክንያታዊ ስለሆነ ተረትም ተነገረው ታሪክ ‘አንተ እኮ ልዩ ነህ፤ አሸናፊ ነህ’ ከተባለ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአልያንስ ኃይሎች (the Allies) ጀርመንን ወደ አመድነት ከቀየሯት በኋላ አንድ የጀርመን ፖለቲከኛ ለጀርመኖች ያለው ነገር ነበር። “አገራችንን ከፈሏት። ሕንጻዎቻችንን አፈራረሱት። ስልጣኔያችንን አመድ አደረጉት። ጀርመናዊ አዕምሮአችንን ግን ከኛ መውሰድ አልቻሉም” ነበር ያለው። ጀርመን ዛሬ ካፈረሰቻት እንግሊዝ በተሻለ የኢኮኖሚ ቁመና ላይ ትገኛለች። በአውሮፓ ሕብረት በኩል ትልቅ ኢምፓየር ሆና ብቅ ብላለች። እዚህ ላይለመድረስ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ አልፈጀባትም። አይሁዶችንም በተመሳሳይ መመልከት ነው። ከናዚ (Nazi) በኋላ የመጡት የጀርመን መሪዎች ብዙዎቻችን እንደምንገምተው በናዚ በተፈጸመ በደል ክፉኛ የሚጸጸቱ አልነበሩም። ይልቁስ ያን ሁሉ ተዓምር ጀርመን መሥራቷ ኩራት የወጠራቸው፣ ድጋሚ ኃያል ሀገር እንደሚሆኑ ለአፍታም ያልተጠራጠሩ ሕዝቦች ነበሩ። Paul Berman የተባለ አሜሪካዊ ጸሐፊ “Power and the Idealist” ብሎ በጻፈው ድንቅ መጽሐፍ መጸጸት የጀመረ ትውልድ የመጣው ጀርመን በድጋሚ በኢኮኖሚ ከአበበች በኋላ በመጣው ትውልድ ነው ይላል። ዛሬ ለገጠማቸው ከስደተኛ ጋር ለተያያዘ መጠነ ሰፊ ችግር የጸጸት ሥነ-ልቦና ያለውን አስተዋጽኦ ያብራራል። ጄኔቫ (Geneva) እያለው አለቃዬ አይርሻዊ (Irish) ነበር። እንግሊዞች እንደ እኛ የበደሉት የለም ይለኛል። ለብዙ ዘመን እንግሊዝ እንዲህ አደረገን እያልን የተበዳይነት ፖለቲካ (victim politics) ስንሠራ ኖርን። ከእንግሊዝ ተላቀን እንኳ አዕምሮአችን ከእነሱ ነጻ አልወጣም ነበር። የገነቡትን ሃውልት ማፍረስ ሥራችን አደረግን። ወይ መልሰን የራሳችንን ሃውልት አላቆምን። መንገዶቹንም ሃውልቱን በማፍረስ ከትላንት የተሻለ ውብ አላደረግናቸውም፤ አስቀየሙ እንጂ። በኋላ ግን ባነንን አለ። ያኔ ነው ማደግ እና መለወጥ የጀመርነው። ከታሪካችን ጋር ታረቅን። የእንግሊዝን ድል የእኛ ድል አድርገን መቀበል እና መተረክ ጀመርን አለኝ። ከዚያ በብዙ ነገር ለመመንደግ ጊዜ አልፈጀብንም አለኝ።
ኢትዮጵያኖች ራሳቸውን ከድል አድራጊ እና ከትልቅ ነገር ማጠጋጋት ነበር ታሪካቸው። ይሄ ተራ ጉራ የሚመስለው ሞኝ ይኖራል። በቅርብ ያገኘሁት አንድ ሸምገል ያለ ጥቁር አሜሪካዊ ዳኛ ጋር ስናወራ ለብዙ ጊዜ በራሴ እጠራጠር ነበር አለኝ። ውስጤ ውስጥ “ትችላለህ፣ አትችልም” የሚል ከባድ ትግል ነበር። ብዙ ምሳሌ እና እኔን የሚመስሉ አርአያ የሉኝም። ቀለሜ ያለመቻል ምሳሌ ሆኖ አሜሪካ ውስጥ ቆሟል። ይሄ የውስጥ ትግል ለእኔ አሰልቺ ነበር አለኝ። ኢትዮጵያኖች “ፑሽኪንን” ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ያበረከተው ነገር ኖሮ አይደለም። ነገ ለሚወለዱት፣ ከዛም ለሚሰደዱት ልጆቻቸው ‘የትም ሄደክ በሄድክበት ሀገር ካሉ ዜጎች በላይ አንተ የመብለጥ አቅም አለህ፤ አንተ ልዩ ነህ’ የሚል ታሪክ እየነገሩት ነው። ይሄ ትርክት ነው ነገ ልዩ የሚያደርገው። አስጨናቂውን የሕይወት ትግል አሸናፊ የሚያደርገው። የውብሸት ወርቃለማሁ ልጅ ዶ/ር ዳግማዊ ውብሸት በአሜሪካ ውስጥ ካሉ ስምንት ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው Cornell University የእንግሊዘኛ ሥነ-ጽሑፍ አስተማሪ ነው። በአንድ ቃለ-መጠይቁ ላይ ወደ አሜሪካ ሲመጣ እንግሊዘኛ ካለመቻሉ በላይ አንብብ ሲባል ተማሪዎቹ በሳቅ ይወድቁ እንደነበረ ይገልጻል። “እነሱ ሲስቁ ጣልያንን ማሸነፋችን ትዝ እያለኝ፥ ‘ምናለ በሉኝ በራሳችሁ ቋንቋ እናንተን ካልበለጥኩ’ እያልኩ ለውስጤ እነገረው ነበር” ይላል። እንዳለውም በCornell University ታሪክ በእድሜ ትንሹ የእንግሊዘኛ ሥነ-ጽሑፍ ፕሮፌሰር ሆነ። ይሄ ተራ ዩኒቨርሲቲ አይደለም። አይደለም አስተማሪ ለመሆን ተማሪ ለመሆን እራሱ አስደናቂ አዕምሮ ሊኖርህ ይገባል። በነገራችን ላይ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በቅርብ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀች የመጀመሪያዋ ጥቁር፥ ኢትዮጵያዊት ናት። ዶ/ር ረድኤት አበበ ትባላለች። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ የምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን (Joe Biden) የሽግግር ካቢኔ መሪ ከታዋቂው ዬል ዩኒቨርሲቲ (Yale University) እና ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ (Harvard University) የተመረቀው ዮሐንስ አብርሃም የተባለ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ታውቃላችሁ። ይሄ ማለት ጆ ባይደን ካሸነፈ በዋይት ሀውስ (White House) ውስጥ ካሉት ትልልቅ ስልጣኖች ቁልፉ ቦታን የሚይይዘው ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ አብርሃም ይሆናል ማለት ነው። ደግሞም አምናለው በእኛ የእድሜ ዘመን ውስጥ ከኦባማ ቀጥሎ የአሜሪካ ጥቁር ፕሬዝዳንት የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይችላል። ብዙ ድንቅ ኢትዮጵያውያን በሪፖብሊካንም ሆነ በዲሞክራቶች የፓርቲ መስመር የስልጣን መሰላሉን እየወጡ እየተመለከትን ነው።
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስ እና – የኦሮሞ ባህል ይሄን ነገር ካልመረመረ የብዙ አቅመ ድኩማን መደበቂያ እና የሽንፈት ታሪክ ወራሽ ልጆች መፈልፈያ ይሆናል። እስቲ ተመልከቱ – ብርሃነመስቀል አበበ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአብይ ደጋፊ እና ደንበኛ የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ ነበር። በአቅም ማነስ ከስልጣን ሲባረር ግን ኦሮሞነቱ ትዝ አለው። የወጣለት የኦሮሞ የመብት አቅንቃኝ ሆነ። ኦሮሞዎቹም ዓይንህን ለአፈር ብለው መስኪድ እንደገባ ውሻ እንዳላባረሩት፥ በአቅም ማነስ ተባሮ ሲመጣ ጀግና አድርገው ተቀበሉት። በተመሳሳይ አማራን እንይ፤ ልክ እንደ ብርሃነመስቀል አበበ ሲባረሩ አማራ ጉያ ውስጥ ለመደበቅ የፈለጉ ሰዎች በቅርብ ታሪካችን ነበሩ። ለምሳሌ ታምራት ላይኔ አንዱ ነው። አማራው ግን ከታምራት ላይኔ ይልቅ መለስ ዜናዊን ይወዳል። በተመሳሳይ ልደቱ አያሌውም ከፖለቲካው መድረክ ሲገለል፥ አማራ ስለሆንኩ ነው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የጠላኝ አለ። ዶ/ር ብርሃኑ እኮ የተደነቀ አዋቂ ሰው ነው። ምን ዓይነት ጅል ቢሆን ነው የድጋፍ ማዕከሉ የሆነውን የአማራን ሕዝብ የሚጠላው? የአማራ ሕዝብ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን እንደሚያፈቅር ለማወቅ በአማራ ክልል እሱ የተገኘባቸውን ሠልፎች እና ስብሰባዎች ማየት ነው። ከልደቱ ይልቅ የአማራው ሕዝብ የብርሃኑ አመለካከት ይስበዋል። ሽንፈት፣ውድቀትን በዘር ቅርፊት ማሳበብ አማራው አምርሮ የሚጸየፈው ነገር ነው። ተሸንፈህ ከመጣ አማራነትህ ይነጠቃል።
አጼ ቴዎድሮስ በመጀመሪያ በአማራው ሕዝብ እጅግ የተጠላ መሪ እንደነበረ ታሪክን ማገላበጥ ብቻ በቂ ነው። እነ ዮፍታሔ እና ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ግን ቴዎድሮስን በጀግንነት ካባ አዲስ ሰው አድርገው አቀረበቱ። የቋራ ሰው እየተባለ፣ የኮሶ ሻጭ ሲባል ሲሰደብ የከረመው ቴዎድሮስ ህልሙ እና ጀግንነቱ ለሕዝቡ ተብራርቶ በአዋቂዎች ሲቀርብለት አማራ የሆነው በፍቅር አበደለት። ጀግና እና ዘመን ተሻጋሪ አዋቂን የሱ እንኳ ባይሆን እንደምንም የራሱ የማድረግ ባህል አለውና።
በምድር ላይ እንደእሱ ዓይነት ጠቢብ የለም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ የሰበከለትን ሰሎሞን የተባለ ሌጀንድ የኢትዮጵያ ጠበብት ሲመለከቱት ጊዜ አላጠፉም። ኢትዮጵያዊ አጋቡት። በዓለም ታሪክ የዓለምን ፖለቲካ በመቀየር ፈጽሞ አቻ የሌለው የPlato “The Republic” መጽሐፍ ድንቅ ሕዝብ እና ታላቅ ሀገር በፈላስፋ ይመራል በሚል አስደናቂውን መጽሐፍ ይዘጋል። አባቶቻችን ይሄን ለመረዳት ከባድ የሆነን መጽሐፍ ያነበቡ ስለነበሩ ፥ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚነግሰውን ሁሉ ከፈላስፋው ሰሎሞን ወልደ ዳዊት ጋር ሲያዛምዱት ቆዩ። ኢትዮጵያኖች ልጆቻችሁን አዎ ልዩ ናችሁ እያላችሁ አሳድጓቸው። አንብበው፣ ተመራምረው አዋቂ ሲሆኑ ሁሉን በራሳቸው ይደርሱበታል። እስከዛ ግን ይሄን ሥነ-ልቦና ፈጽማችሁ አትንጠቋቸው። እነሱን እዚህ አሜሪካ እንደሚወለደው ከአንጎላ በመርከብ ከመጣው ጥቁር አሜሪካዊ ጋር የተገዢነት ሥነ-ልቦና አታላብሷቸው። ጥቁሩን ሁሉ ነጻ የሚያወጣው ኢትዮጵያዊው እሱ መሆኑን ከልጅነቱ ጀምራችሁ ስበኩት።
በመጨረሻም በአንድ አፈ-ታሪክ ምሳሌ ጹሑፌን ልዝጋ። ጅብ አህያን ለብዙ ጊዜ ሲፈራት ይኖር ነበር። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የአህያ ጆሮ ቀንድ እየመሰለው ነው። አህያ ጅብን መወዳጀት ስለምትፈልግ ለብዙ ጊዜ እንዲቀርባት ትሻ ነበር። አንድ ቀን ግን ለምን እንደሚሸሻት ጨክና ጠየቀችው። እሱም ቀንዶቿን እጅግ እንደሚፈራው ለዛም እንደሚሸሻት ነገራት። በመገረም “ይሄ እኮ ቀንድ አይደለም፤ ጆሮዬ ነው፤ ስጋ እንጂ አይዋጋም አለችው።” ከዚያ ቀን ጀምሮ አባራሪ እና ተባራሪ ቦታ ተለዋወጡ። ኢትዮጵያኖች ታሪኮቻችን፣ ድሎቻችን፣ ሃውልቶቻችን፣ ሃይማኖታችን ጅብ ከሆኑ ጠላቶቻችን መጠበቂያ ጋሻዎቻችን፣ ምሽጎቻችን ናቸው። ይሄን አጥተን ከመኖር ሁላችን ማለቅን መምረጥ ይሻለናል። ጆን ስቱዋርት ሚል (John Stuart Mill) እንዳለው “የተደሰተ አሳማ ከመሆን የተከፋ ሰው መሆን ይሸላል፣ ጅል ሆኖ ከመደሰት ሶቅራጦስን ሆኖ ዕድሜ ልክን ማዘን ይሻላል።” ለልጆቻችን የባርነትን፣ የተሸናፊነትን ሥነ-ልቦናን ከምናወርስ ሁላችን ቀድመን ማለቅ ይሻለናል። አባቴ ጀግና ነው እያለ ካላባት ያደገ ልጅ በፈሪ አባት ካደገ ልጅ በላይ በራስ መተማመኑ ኃያል ነው።
* በዚህ ጽሑፍ ላይ አማራ ብዬ የጠቀስኩት ማኅበረሰብ በአሰፋ ጨቦ ትንታኔ መሠረት ሲሆን፥ ዘርን ሳይሆን የአባቶቻችንን ድል እና ኃያልነት የተቀበለውን፣ የማሸነፍ መንፈሱ የማይደረመስ ተራራ የሆነውን፣ በየሄደበት ሁሉ የአባቶቹን ድል አድራጊነት እያሰበ የበታችነትን እንቢ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚመለከት ነው።
አዲስ አበባ ― ዳቦ፣ የመኖሪያ ቤት፣ መብራት እና ውሃ፣ የመሬት ቅርምት፣ ተረኝነተ፣ ሙስና፣ ግፍ፣ ወዘተ…
(ያሬድ ኃይለማርያም)
አዲስ አበባ ብዙ ስር የሰደዱ እና ውስብስብ ችግሮችን በጉያዋ የያዘች ጉደኛ ከተማ ነች። ልክ እንደ ከተማዋም አዲስ አበቤዎችም እንዲሁ ከዳቦ አንስቶ እጅግ ብዙ እና ውስብስብ የመብት እና የጥቅም ጥያቄዎች እንዳረገዙ ከዚህ ሁሉ ጭንቅ የሚገላግላቸው አስተዳደር ሲናፍቁ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይህ ችግር በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ምን ያህል ሊከፋ እንደሚችል መገመት ይቻላል።
የኋላውን ትተን ባለፉት ሁለት ዓመታት [የአዲስ አበበባ ከተማ መስተዳድር] እና የፌደራል መንግሥቱ ከተማዋን ለማዘመን በሚል አዳዲስ ዕቅዶችን ይዘው እና አንዳንዱንም ጀምረው የከተሜውን ቀልብ ለመግዛት ጥረዋል። እነዚህ የተጀመሩ አንዳንድ የልማት ዕቅዶች በእርግጥም ከተማዋን ለማዘመን ይረዱ ይሆናል። ነገር ግን የከተማዋን ሕዝብ የቆዩ እና ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱ ስለመሆናቸው በቂ ጥናት መደረጉን የሚያሳዩ ነገሮች አይታዩም።
አብዛኛዎቹ የመስተዳድሩ እንቅስቃሴዎች ገጽታ እና ምርጫ ተኮር ስለሆኑ የከተማዋን ገበና በእነዚህ ትላልቅ እና ከፍተኛ ገንዘብ በሚወስዱ ፕሮጀክቶች ለመሸፈን ጥድፊያም ላይ ያሉ ይመስላል። በሌላው ጎን ከንቲባው በአደባባይ የታሙባቸው እና ጠያቂ ቢኖር በሕግ በሚያስጠይቁ ተግባራት በማኅበረ ድኅረ ገጾች (social media) እና በሚዲያ ሲብጠለጠሉ ቆይተዋል። ከዚህ በሚከተሉት ጉዳዮች መስተዳድሩ አንድም ጊዜ አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጥ አልተስተዋለም፤
- በሕገ-ወጥ መንገድ ዘር-ተኮር የነዋሪነት መታወቂያ ማደል፣
- በአንድ ሰው መኖሪያ ቤት ባለቤቱ ሳያውቅ ለበርካታ ሰዎች ዘር-ተኮር የመታወቂያ እና የቁጠባ ብድር መስጠት፣
- በከተማዋ ፕላን መሠረት በየአካባቢው ለልጆች መጫወቻ እና ለልማት የተተው ክፍት ስፍራዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ እና ዘር-ተኮር በሆነ መንገድ በግለሰቦች እጅ እንዲገቡ ማድረግ፣
- ሕገ-ወጥ መኖሪያዎች በሚል የሚደረጉ ዘር-ተኮር የቤት ማፍረስ እርምጃዎች፣
- የከተማዋ ነዋሪ ከዕለት ጉርሱ ቆጥቦ የሠራቸውን የመኖሪያ ቤቶች [የኮንዶሚኒየም ቤቶች] አሁንም ዘር-ተኮር በሆነ መንገድ ለሌሎች አሳልፎ መስጠት፣
- በከተማዋ መስተዳድር ውስጥ ዘር-ተኮር የሆነ የሠራተኞች ድልድልና ሽግሽግ ማድረግ እና በሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች በአደባባይ መስተዳድሩ እየተወነጀለ ነው።
እነዚህ ክሶች እውነት ተደርገው ከሆነ ሁለት ዋና የጥፋት ዓይነቶችን የያዙ ናቸው። አንደኛው ድርጊቶቹ ለማንም ጥቅም ተብሎ ይፈጸሙ የሀገሪቱን እና የከተማዋን ሕግ የጣሱ ናቸው። ሁለተኛው ጥፋት እያንዳንዱ ድርጊት ዘር-ተኮር መሆኑ ነው። ሌሎቸን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተፈጸሙ ነው ባይባልም እንኳ አንድን ዘር ባልተገባ መልኩ፣ ስልጣንን ከለላ በማድረግ እና ሕግን በተላለፈ መልኩ ለመጥቀም የተፈጸሙ ናቸው መባሉ ነው።
በእነዚህ ክሶች ላይ መስተዳድሩ በድፍኑ አልፈጸምኩም ከማለት ባለፈ ወቀሳዎቹን በዝርዝር እና በማስረጃ ሲያስተባብል አይታይም። የእነዚህን ጉዳዮች ክብደት ከግምት በማስገባት የፌዴራል መንግሥቱ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት እና ገለልተኛ አጣሪ አካል መድቦ ለእነዚህ የሕዝብ ብሶቶች በአፋጣኝ ምላሽ ቢሰጥ ጥሩ ነው። ይህን ቸል ማለት ድርጊቶቹ የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ የተቸሩ ያስመስላቸዋል። እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ወደ ጎን ለመግፋትም ሆነ በዳቦና በዘይት እደላ ለመሸፈን ከተሞከረ ግን ሌላ የፖለቲካ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም። አዲስ አበቤዎችም ያቄሙበትን ፖርቲ እንዴት መቅጣት እንደሚችሉ የሚያውቁበት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ምርጫ 97ን ማስታወሱ በቂ ነው።
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።
የወላይታ ዞን ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 7ተኛ ዓመት 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በጠራው ስብሰባ ላይ ያወጣው የአቋም መግለጫ
የወላይታ ሕዝብ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ሕገ-መንግሥት መሠረት አድርጎ ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበረ ይታወቃል። ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ወላይታ ብሔር ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት እንደሚገባው ሕገ-መንግሥቱ በግልጽ ቢደነግግም የክልሉ ምክር ቤት የወላይታን ክልል የመመሥረት ጥያቄን ለምክር ቤት እንደ አጀንዳ ላለማቅረብ በማሰብ መደበኛ ስብሰባዎችን በተደጋጋሚ ሆን ብሎ እየዘለለ ቆይቷል።
ከዚህም ባሻገር የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ የምክር ቤት ጉባዔ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ባካሄዳቸዉ አስቸኳይ ጉባዔዎች የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ለጉባዔው እንዳይቀርብ የተደረገ ሲሆን የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በምክር ቤቱ አጀንዳ ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ታፍነዉ ዕድል እንዳይሰጣቸዉ ተደርገዋል።
ይህንን ኢፍትሐዊ አሠራር መነሻ በማድረግ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አስቸኳይ ጉባኤ የጠራ ሲሆን፥ በዚህ አስቸኳይ ጉባዔ በዋናነት የዞኑ መስተደድር የሕዝቡን ክልል የመመሥረት ጥያቄን የመራበት ሂደት በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን፥ እስካሁን ያለው ሂደት አመርቂ መሆኑንም ገምግሟል።
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ በስፋትና በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የሚከተለዉን ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥቷል፤
- የወላይታ ሕዝብ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47 (3) መሠረት የጠየቀዉ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን የሚመሠረተዉ ክልል ስያሜው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የሥራ ቋንቋ ወላይትኛ (Wolaittatto Doona)፣ የክልሉ ርዕሰ-ከተማ ‹‹ወላይታ ሶዶ›› ይሆናል። ስለሆነም መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ ለሆነ ሕዝብ ጥያቄ ሕገ–መንግሥትን በተከተለ መንገድ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የወላይታ ብሔር ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል።በተጨማሪም ይሄ ጥያቄ በጊዜ ባለመመለሱ የተነሳ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰ፣ የዞኑ መንግሥት ሙሉ ጊዜውን በልማት ሥራ እንዳያውል እንቅፋት እየሆነ የሚገኝ በመሆኑ ሂደቱም ወደ ፀጥታ ችግር ሳይሸጋገር የፈደራል መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ እንዲሰጥ ምክርቤቱ ጠይቋል።
- የወላይታ ብሔርን ወክለዉ በክልል ምክር ቤት ሲሳተፉ የነበሩ የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በቀን ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደዉ 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ላለመሳተፍ ራሳቸዉን ከምክር ቤት አባልነት ማግለላቸዉ ለሁሉም ኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነዉ። ይህንን ያደረጉበት ምክንያት የክልሉ ምክር ቤት ለወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ ነዉ። ይህ የወላይታ ብሔር ተወካዮች ውሣኔ ለወላይታ ብሔር ያላቸዉን ክብር የሚያሳይ ስለሆነ ምክር ቤቱ በአድናቆት ተመልክቷል። ነገር ግን እነዚህን ተወካዮች የክልሉ አስተዳደርና የክልሉ ምክር ቤት ጠርተዉ ማወያየት ሲገባዉ እስካሁን ድረስ ዝም ማለቱ መላዉን የወላይታ ሕዝብ አለማክበሩን ያሳያል። የሕዝብ ውክልና የያዘ አካል ለክልሉ ምክር ቤት ያለዉን ቅሬታ ለማሳየት መልቀቂያ ቢያስገባ የዚህን ሕዝብ ተወካዮች ጠርቶ አለማወያየትና ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን እንገነዘባለን። የወላይታ ሕዝብ በሀገሪቱ ለመጣዉ ለዉጥ ትልቅ ዋጋ የከፈለ ታሪክ ያለዉ ሕዝብ ነዉ። ስለዚህም የፌዴራል መንግሥት እነዚህን የወላይታ ሕዝብ ተወካዮችን ጠርቶ እንዲያነጋግር የዞኑ ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል።
- የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚወስናቸው ወላይታን የሚመለከት ማንኛውም ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆናቸው አስቀድሞ በወላይታ ዞን ምክር ቤት ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት ወስኗል። በተጨማሪም በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የሚወስኑ የወላይታ ሕዝብ ጥቅም የሚጎዱ ማነኛውም ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክር ቤቱ ወስኗል።
- የደቡብ ክልል ፀጥታ መዋቅር የሚመሩ አካላት ላይ እምነት ስሌለንና ገለልተኛ ባለመሆናቸው እንዲሁም የክልሉ ፀጥታ ሥራ በኮማንድ ፓስት (Command Post) የሚመራ በመሆኑ የወላይታ ዞን ፀጥታ ሥራ በሕዝቡ እና በዞኑ ፀጥታ መዋቅር ጋር በትብብር መፈፀም እንዳለበት እና ድጋፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ከፈደራል ፀጥታ መዋቅር በትብብር መሠራት እንዳለበትም ተወስኗል።
- ወደፊት የሚመሠረተው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ፓለቲካዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን እንዲያዘጋጅ ሰክራቴሪያት ፅ/ቤት እንዲቋቋም ተወስኗል። በተጨማሪም የዞኑ መንግሥት እንደየአስፈላጊነቱ ለወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ የሚያግዙ ተቋማትንና ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሂደቱን በበላይነት እንዲመራም ተወስኗል።
- ቀጣይ ሕዝባዊ ጥያቄ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ ተወስኗል።
- የወላይታና አጎራባች ሕዝቦች ትስስር ለዘመናት የቆየና በቀጣይ አብሮ የሚኖርና የሕዝቦች ትስስር ከመዋቅር በላይ በመሆኑ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የዞኑ ምክር ቤት ወስኗል።
ለመላዉ የወላይታ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት ሕገ–መንግሥታዊ መብት በሚመለከተው ፌዴራል መንግሥት አካል ለጥያቄዉ ተገቢ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ እንደተለመደው ሁሉ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የወላይታ ዞን ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል።
“የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትና ዓለማቀፍ ሕግ ያጎናጸፈዉ የወላይታ ሕዝብ ክልል የመመሥረት መብት ጥያቄ በሰላማዊ ሕዝብ ትግል እውን ይሆናል!”
ሰላም ለሀገራችን
የወላይታ ዞን ምክር ቤት
ወላይታ ሶዶ፣ ኢትዮጵያ
ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም.