Search Results for 'ምርጫ'

Home Forums Search Search Results for 'ምርጫ'

Viewing 15 results - 91 through 105 (of 116 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    በኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ አድናቂዎች ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፈ የመጣው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። ቁራኛዬ ፊልም ሦስት ሽልማቶችን ሲያገኝ፥ ድምጻዊ ቸሊና እና ዘመን ተከታታይ ድራማ ሁለት፣ ሁለት ሽልማቶችን አግኝተዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ እጅግ መቀዛቀዝ፣ የሙዚቃ አልበምም ህትመት መፍዘዝ፣ ፊልም ሠሪዎችም ሥራዎቻችውን ተመልካቾች ፊታቸውን ባዞሩባቸው ወቅት እንደ አንድ የኪነጥበብ አባልና የሚዲያ ባለሙያ አቅማቸው በፈቀደ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት፣ እንዲሁም አድማጭ እና ተመልካቹን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማነቃቃት በማሰብ ነበር ጋዜጠኛ ብርሀኑ ድጋፌ እና ባልደረቦቹ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ላይ “ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት” ሥነ ሥርዓትን የየጀመሩት።

    በእርግጥ ኪነ-ጥበብና ኢትዮጵያ ሀገራችን በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው መንገድ እጅግ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቁርኝት ቢኖራቸውም ቅሉ የኪነ ጥበብ ሙያዉን እንደተከበረ ሙያ ባለሙያዉንም የተከበረ ሙያ እንዳለው ቆጥሮ ወቅት ጠብቆ በተገደበ የጊዜ ኡደት ለሙያውና ለባለሙያው ተገቢውን ዕውቅና፣ ብሎም ክብር የሚሰጥ ቋሚ ተቋም ባለመኖሩ ያለመኖሩን በማስገንዘብ የሥነ ስርዓቱ ሀሳብ ጠንሳሾች “ለምን እኛ የቻልነውን አናደርግም?” በሚል ነበር የኪነ ጥበብ ሰዎችን በዓመት አንድ ጊዜ እያሰባሰቡ ለማወያየት፣ በዓመቱ በሙያውና በሙያቸው ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉትን “በጎ ሥራ ሠርታችኋል! ይበል!” ለማለት ለዛ የኤድማጮች ምርጫ ሽልማትን በ2003 ዓ.ም የጀመሩት።

    በ2003 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ ሽልማት ‘የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ’፣ ‘ምርጥ ተዋናይት’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ፊልም’ እና ‘የዓመቱ ምርጥ አልበም’ በሚሉ አምስት ዘርፎች (ዘውጎች) ኢትዮጵያውያን የኪነ ጠበብ ሰዎች ተመርጠው የተሸለሙ ሲሆን ሽልማቱም ያገኙትም ከያኒት ዘሪቱ ከበደ “አርቴፍሻል” በሚለው ነጠላ ሙዚቃዋ፣ ተዋናይት ሰሃር አብዱልከሪም “ያንቺው ሌባ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣ ጋሽ አበበ ባልቻ “ሄሮሺማ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣ “ሄሮሺማ” ፊቸር ፊልም በምርጥ በፊልምነት፣ እንዲሁም ከያኒ ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) በመጀመሪያው አልበሙ በአምስቱ የተዘረዘሩት ዘርፎች አሸናፊዎች ሆነው የሥነ ሥርዓቱ የበኩር ተሸላሚዎች ሆኑ።

    በዚህ መልኩ የተጀመረው ለዛ የአድማጮች ምርጫ በየዓመቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ሃምሌ ድረስ የሚወጡ የኪነ ጥበብ ሰዎችንና ሥራዎችን በአድማጮች ምርጫ አወዳድሮ ዕውቅና እየሰጠ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሳታፊዎችን እያበዛ፣ በባለሙያዉም፣ በመራጭነት በሚሳተፈውም ይሁን በየበይ ተመልካችነት በሚከታተለው ኢትዮጵያዊ ዘንድም ተወዳጅነት እያተረፈ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። በዘጠነኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች ሽልማት ያገኙት የሚከተሉት ናቸው።

    • ምርጥ ነጠላ ዜማ፦ “ቢልባ” (ጃንቦ ጆቴ) [ኦሮምኛ ሙዚቃ]፣
    • ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፦ ቸሊና የሺወንድም (“ቸሊና” በተባለው የሙዚቃ አልበሟ)፣
    • ምርጥ የሙዚቃ አልበም፦ “ቸሊና” (ቸሊና የሺወንድም)፣
    • ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ፦ ከእሁድ እስከ እሁድ (ጎሳዬ ተስፋዬ)፣
    • ምርጥ ሙዚቃ/ዘፈን፦ “ሰርካለሜ” በድምጻዊ ዚጊ ዛጋ (በኃይሉ ታፈሰ)፣
    • ምርጥ ተዋናይት፦ የምስራች ግርማ ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣
    • ምርጥ ተዋናይ፦ ዘሪሁን ሙላት ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣
    • ምርጥ ፊልም፦ ቁራኛዬ
    • ምርጥ ተዋናይት በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ሀና ዮሐንስ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
    • ምርጥ ተዋናይ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ አበበ ባልቻ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
    • ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ደርሶ መልስ በፋና ቴሌቪዥን፣ እና
    • “የ2010 ዓ.ም የኪነ ጥበባ በለውለታ” የክብር ተሸላሚ፦ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ደማቅ አሻራቸውን ያስቀመጡትን የቀድሞዎቹን አይቤክስ ባንድ እና ሮሃ ባንድ ከመሠረቱት አባላት አንዱ የሆኑት ጂዮቫኒ ሪኮ (Giovanni Rico)

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ቁራኛዬ


    Anonymous
    Inactive

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲ ስለሚገቡ አዲስ ተማሪዎች እና የሚደረግላቸውን አቀባበል በተመለከተ የሰጠው መግለጫ
    —–

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በ2011 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ 142,840 ተማሪዎች በመደበኛ መርሀ ግብር (regular program) በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል። ምደባቸውም የተማሪዎቹን የትምህርት መስክና የተቋም ምርጫ፣ የተማሪዎቹን ውጤት እና የዩኒቨርሲቲዎችን የቅበላ አቅም ባገናዘበ መልኩ የተካሄደ ነው።

    በዚሁም መሠረት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ተቀብለዋል። ቀሪዎቹም እየተቀበሉ ይገኛሉ። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አብዛኞቹ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በተመደቡበት በመገኘት ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል። ነባር ተማሪዎችም ትምህርታቸውን መከታተል ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

    ከዚህ ጋር ተያይዞም የ2012 ዓ.ም. የመማር-ማስተማር ሰላማዊ እንዲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ከነዚህም መካከል አንዱ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚረዳ ወላጆችን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የኃላፊነት መውሰጃ የስምምነት ውል እንዲገቡ መደረጉ አንዱ ነው። በዚህም ላይ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል አዲስ ተማሪዎች ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ከመግባታው ቀድም ብሎ እንዲሁም ከገቡ በኃላ፣ ነባር ተማሪዎችም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠናዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደርጓል። በተጨማሪም በያዝነው ዓመትም አዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ተደርጓል።

    የመማር-ማስተማር ሥራው የግብዓትም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙትም ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን አቋም እና ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረጉትን ቅድመ-ዝግጅት ለመገምገም ያገዙ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተሳተፉባቸው የመስክ ጉብኝቶች ተካሂደዋል። በቪዲዮ ኮንፈረነስም ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችና የደረሱበትን የዝግጅት ደረጃ የመገምገም እና የማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በውጤቱም ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሰላማዊ ለማድረግ ሊሠሩ የሚገባቸው አስፈላጊ ቅድመ-ዝግጅቶችን ማካሄዳቸው ተረጋግጧል።

    ከተማሪዎች ቅበላ ጋር ተያይዞም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች) ሲታይ እንደነበረው ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበት አከባቢ ማኅበረሰብ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የአከባቢው የጸጥታ ኃላፊዎች ጋር በመተባበር ፍፁም ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ቤተሰባዊ አቀባበሎችን ሲያደርጉ ታይቷል፤ እያደረጉም ይገኛሉ። ይህ በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ከተካሄዱ ተከታታይ ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች በኋላ የተገኘ ውጤት ነው።
    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምደባውን ተግባራዊ ሲያደርግ የተማሪዎችን ምርጫ፣ ውጤት እና የየተቋማቱን የቅበላ አቅም ከማገናዘብ ጎን ለጎን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚያስችሉ አካሄዶችንም ተከትሏል። ይሄው ታውቆ የክልል መንግስታት፣ የዩኒቨርሲቲ ቦርዶችና አመራሮች እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት በጠቅላላ የተቀመጠውን የቅበላና ድልደላ መርህ ተገንዝበው ለአፈፃፀሙ ሁሉም የድርሻቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ እንተማመናለን።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም የኖቤል ሽልማት ለመቀበል የበቁት ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ባበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑ ሽልማቱን የሚሰጠው ኮሚቴ ገልጿል

    በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ዓለምን ያስገረመና ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠለት የቅርብ ወዳጅ ዘመድ ጥየቃ ዓይነት ቃና የነበረው ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሁለት ዓይነት ሀሳቦች ቢስተናገዱም ሚዛን የሚደፋው ጉብኝቱ ሰላምን ለማምጣት መሠረት የተደረገ መሆኑ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያለውን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ‘ሽልማቱ ይገባቸዋል’ የሚሉ ድምጾች አሸናፊነታቸውን ቀድመው እንዳወጁላቸው ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ በጎረቤት አገሮች መካከል ሰላምንና አብሮነት ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል።

    ኖርዌይ ላይ አሸናፊው ይፋ ሲደረግ በኮሚቴው እንደተገለጸው፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እውቅናና ማበረታቻ ያስፈልገዋል።

    በእንግሊዝ ኪል ዩኒቨርሲቲ (Keele University) የህግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አወሎ አሎ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ገጭት እንዲያበቃ በማድረጋቸው ሽልማቱ ይገባቸዋል” ማለት ግጭቱ በሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስከተለና የማይተካውን ብዙ ህይወት እንደቀጠፈም ተናግረዋል።”

    ከኤርትራ ጋር የወረደው ሰላም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ሙገሳ ያስገኘላቸው ሲሆን ለሁለቱ አገሮች ወንድማማች ህዝቦች ደግሞ ትርጉሙ ከዚህ የላቀ ነበር። በተለይ ተለያይተው የነበሩ ቤተሶች ሲገናኙ ያፈሰሱት የደስታ እምባ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳላት በተጨባጭ የመሰከረ ነው።

    • ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገር ውስጥ የጀመሯቸው የለውጥ ማሻሻያዎች የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን በመልቀቅ ተጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው አስከመቀበል የዘለቀ ነው።
    • ኢትዮጵያና ኤርትራ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ መሠረት ጥሏል።
    • በሱዳን የተነሳውን የለውጥ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ የተጀመረው ተቃውሞ በሰላም እንዲጠናቀቅና ተቃዋሚዎች ከወታደራዊ ቡድኑ ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳናውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። በተለይ በሰኔ 2011 ዓ.ም ወደ ሱዳን በማቅናት ሁለቱን አገሮችለማስማማት የጀመሩትን ጥረት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬት እንዲደግፉት በማድረግ ለውጤት እንዲበቃ አድርገዋል።
    • ከዚህ ባለፈ ኤርትራና ጂቡቲ ጀርባ የተሰጣጡበትን አለመግባባቶች በሰላም እንዲቋጩና ለጋራ እድገት በጋራ እንዲነሱ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
    • በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር በአፍሪካ ቀንድአገሮች መካከል የኢኮኖሚ ህብረት እንዲኖር ያደረጉት ጥረት ለሰላምና ወንድማማችነት ያላቸውን ክፍት ልብ ያሳየ ነው።
    • ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን የማይደፈረውን ደፈረው ተንቀሳቅሰዋል።
    • በዚህም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ተፈርጀው ለእስር የተዳረጉትን አቶ ዳንኤል በቀለን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አድርገው የሾሟቸው ሲሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር አድርገዋቸዋል።
    • በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ ውይይት ማድረጋቸው ሌላው ስኬታቸው ነው። በውጭ አገር ተቀምጠው የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር ሲጥሩ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋርም ሰላም በማውረድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ሜዳውን ከፍተውላቸዋል።
    • የደህንነቱንና የፍትህ ዘርፉንም ተአማኒ ለማድረግ በሩን ክፍት በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጡ እያገዙ ነው።
    • በአገሪቱ ወደ ኋላ የቀረውን የሴቶች ተሳትፎ ከነበረበት አዘቅት በማውጣት ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸውም አድርገዋል።
    • በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። በዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አብሮነቱንና ዕውቅናውን ሰጥቷቸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ።

    በአጠቃላይ 301 ዕጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሽልማት


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በዓለም ምርጡ ተብሎ በይፋ የተሰየመውን እና በህዳር ወር የሚካሄደውን 45,000 ህዝብ የሚሳተፍበት የ2012 ዓ.ም. ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪ.ሜ. ውድድር የሚያዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዚህ ጎን ለጎን የሚያካሂደውን “ሌሎችን ለመርዳት ሮጣለሁ” የእርዳታ ማሰባሰቢያ ሥራ እንዲሁም የዘንድሮውን ሩጫ መሪ ቃል “ሴቶች ልጆች በእኩል ሚዛን መታየት፤ መደመጥ እና ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል” በመለየት መሰናዶውን በተቀላጠፈ መልኩ በማካሄድ ላይ ሲሆን ውድድሩ ከዛሬ 45 ቀን በኋላ እሁድ ህዳር 07 እንደሚካሄድ ተገልጿል።

    በጎ አድራጎ ሥራ ከተጀመረበት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ከ13.5 ሚሊዮን ብር በላይ ሰላሳ (30) ለሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተሰባሰበበት “ሌሎችን ለመርዳት ሮጣለሁ” መርሀ ግብር 9 ሚሊዮን ብሩ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተሰባሰበ ሲሆን ዘንድሮ 1.9 ሚሊዮን ብርለማግኘት ታቅዶበታል። ይሄም ገንዘብ በዋግህምራ ዞን ትምህርት ቤት ለማስገንባት የሚውል ሲሆን የፕሮጀክቱ መነሻ ጀግናው አትሌት ሀይሌ ገብረሥላሴ በቅርቡ በአካባቢው አንድ ትምህርት ቤት ማሠራቱን ተከትሎ የመጣ ነው።

    ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ በውድድር ዝግጅት ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ አንጋፋ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ጋር ተፎካክሮ ያገኘው ትልቅ ዕውቅና እና ሽልማት ለሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ የሚኖረው ጉልህ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። ስኬቱ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ይበልጥ ለማስተዋወቅ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን እንደ አንድ መስህብ መጠቀም የሚያስችል ሲሆን በተለይም ከቱሪዝም ኢትዮጵያከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ሌሎች የውድድሩ አጋሮች ጋር አብሮ በመሥራት የአገሪቷን ቱሪዝም ለማሳደግ ካለው አላማ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።

    በሌላ በኩል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውድድር ስያሜ ስፖንሰሩ ቶታል ጋር ያለውን ኮንትራት ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት አድሷል። ከዚህ በተጨማሪ የ2012 ዓ.ም. ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የምዝገባ ሰኔ ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን የተቀሩት ጥቂት ለበጎ አድራጎት የሚውሉ ቦታዎች ለማቀላጠፍ ከአሞሌ የዲጂታል መገበያያ ቴክኖሎጂ ጋር በአጋርነት መሥራት ጀምሯል። ማንኛውም ለበጎ አድራጎት የሚውለውን የሩጫ ቲሸርት የሚፈልግ ግለሰብ አሞሌን በመጠቀም መግዛት የሚችል ሲሆን አሞሌን ለማይጠቀሙ ግለሰቦች ደግሞ በማንኛውም የዳሽን ባንክ በመሄድ 600ብር በመክፈል መመዝገብ የሚችሉበትን መንገድ አመቻችቷል። የመወዳደሪያው ቲሸርት ለሁሉም ተሳታፊዎች ከጥቅምት 28-30 ቀን ከውድድሩ 1 ሳምንት ቀድሞ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በታላቁ ሩጫ የስፖርት ኤክስፖ ላይ ይሰጣል።

    ዘንድሮ ታላቁ ሩጫ አዳዲስ አጋሮችን ይዞ መቷል። “ከሥራዎች ሁሉ ውድ ÷ ክፍያ የማይፈፀምላቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች እና ክብካቤዎች ናቸው!”) የሚል መልዕክት ይዞ የመጣው አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ (ActionAid Ethiopia)፤ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራው ኤች ፒ (HP) እና ዘመናዊው ሃየት ሬጀንሲ ሆቴል (Hyatt Regency Addis Ababa) ናቸው።

    ከ2012 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ በሩጫው ዋዜማ በድምቀት የሚካሄደውና በአጠቃላይ 3,500 ልጆች የሚሳታፉበት የሕፃናት ውድድር ከአዋቂዎቹ ሩጫ ጋር በተመሳሳይ “ሴቶች ልጆች በእኩል ሊታዩ፤ ሊደመጡ እና ቦታ ሊሠጣቸው ይገባል” በሚል መሪ ቃል ይደረጋል። የልጆች ሩጫ ከሚያስተላለፈው መልዕክት በተጨማሪ ሕፃናት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ገና በለጋ እድሜያቸው እንዲለምዱ እድል ሲሰጥ በተጨማሪም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ተሳትፎ የሚያሰፋበት መንገድ ነው።

    የ14ኛው የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ (Plan International Ethiopia) የሕፃናት ሩጫ ምዝገባ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ቦሌ መንገድ ዓለም ህንጻ በሚገኘው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ ይጀመራል ።

    የ19ኛው ዙር የ2012 ዓ.ም. ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከፊታችን እሁድ 6 ሳምንታት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን በቀጣይ ያሉት 6 ሳምንታት የተለያዩ 6 አንኳር ህሳቦች ላይ እንዲያጠነጥኑ የታቀደ ሲሆን እነሱም፡

    1. ዱበ ዱብ፡ ተሳታፊዎች ለሩጫው ዝግጅታቸውን የሚጀምሩበት ሳምንት ሲሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ6 ሳምንት የልምምድ ምክር ከሻለቃ ሀይሌ ገብረሥላሴ እንዲያገኙ ያመቻቻል።
    2. ጥንቃቄ፡ ይህ ተሳታፊዎች ጤናቸውን የሚያረጋግጡበት (ቼክ የሚያደርጉበት) ሳምንት ሲሆን አዘጋጆች ደግሞ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እንዲሁም ከጠብታ አምቡላንስ እና ከውድድሩ ሜዲካል ዳይሬክተር የተጠናከረ ዝግጅት የሚደረግበት ነው።
    3. ምንጭ፡ አርንጓዴ ምንጭ በመባል የሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የአትሌቲክስ ቡድን ሲሆን የዚህ ምንጭ የሆኑት ታዳጊ እና አዳዲሰ አትሌቶች በቃታቸውን የሚያሳዩበት የምርጫ ውድድር የምናደርግበት ሲሆን፣ ጥቅምት 9 ቀን 300 የሚሆኑ ታዳጊ አትሌቶች በውድድሩ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ወድድሩ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሜ የሚካሄድ ይሆናል።
    4. በጎ ፈቃደኛ፡ ለውድድራችን በየአመቱ መሳካት ትልቅ ድጋፍ ለሚያደርጉልን በጎ ፈቃደኞቻችን እውቅና የምንሰጥበት ሳምንት ነው።
    5. ጽዱ፡ የሩጫችን መንገድ ንጹህ ሆኖ እንዲዘጋጅ የሙከራ የጽዳት ፕሮግራም የምናደርግበትና በዋናነት ከቂቆስ ክ/ከተማ ጽዳት ቢሮ ጋር የሚሰራ ሲሆን ውድድሩ የሚንካቸውን ሌሎች ክ/ከተማዎችን ጨምሮ የሚካሄድ ሲሆን ከውድድሩም በኋላ ከተማችን ጽድ እንድትሆን ከአጋሮቻችን አርኪ ውሃ እንዲሁም ዳይናሚክ የጽዳት ድርጅት ጋር አብረን እንሰራለን።
    6. ስፖርት ኤክስፖ፡ ለተሳታፊዎቻችን የሩጫ ቲ-ሸርት የሚሰጥበት ሳምንት ሲሆን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከጥቅምት 27-30 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ የስፖርት ትጥቅ የሚያገኙበት እንዲሁም የተለያዩ ስፖርቶችን የሚሞክሩበት እና የሚዝናኑበት ነው።

    ለበለጠ መረጃ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የማርኬቲንግ እና ኮሚኒኬሽን ሃላፊ መርከብ መንግስቱን በስ.ቁ. 0911-671002/0116-635757 ኢሜይል፡ merkeb@ethiopianrun.org ማግኘት ይችላሉ።

    ምንጭ፦ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ


    Anonymous
    Inactive

    ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በ2012 የትምህርት ዘመን የሚካሄደው የተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ምደባ ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን መቀየር እንሚችሉ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የዘንድሮ ምደባ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ እና በመምህርነት የሚካሔድ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ተማሪዎች ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት መስክ መቀየር እንሚችሉ ገለፀው ተቋሙ ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ መቀየር የሚቻለው ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የተዘጋጀውን ማለፊያ ነጥብ ለሚያሟሉ ተማሪዎች ብቻ መሆኑን አስታውቋል።

    የትምህርት መስክ ምርጫ በተመለከተም ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች፣ ተፈጥሮ ሳይንስና መምህርነት፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ማኅበራዊ ሳይንስና እና መምህርነት ብቻ እንደሚሆንም ነው የገለፀው።

    ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን መቀየር እንሚችሉም ተገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲ ምርጫን ማስተካከልም ሆነ የትምህርት መስክ መቀየር (ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ) የሚቻለው ተማሪዎች ትምህርታቸዉን በተከታታሉበት ትምህርት ቤት ወይም ፈተና በወሰዱበት የፈተና ጣቢያ ነው ተብሏል።

    የዩኒቨርሲቲ ምርጫ ማስተካከያና የፊልድ መቀየሪያ ቀናት እስከ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ብቻ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር በድረ ገፁ አስነብቧል።

    ምንጭ፡- ኢቢሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    ኢትዮጵያ ቡና ክለብ ካሳዬ አራጌን በይፋ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

    አዲስ አበባ (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ነሃሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ሾሟል።

    የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ እና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በዕለቱ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደ ዝግጅት በይፋ የፊርማ ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል። በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይም የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት መቶ አቀላ ፈቃደ ማሞ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ስንታየሁ በቀለ እና የደጋፊ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ክፍሌ አማረ ተገኝተዋል።

    በስምምነቱ መሠረትም አሳልጣኝ ካሳዬ አራጌ ክለቡን ለ4 ዓመታት በአሰልጣኝነት የሚመራ ሲሆን፥ በውሉ መሠረት የመጀመሪያው ዓመት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሠራ ተገልጿል። በቀሪዎቹ 3 ዓመታት ግን ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዞ መጨረስ እንዳለበት ቅድመ ሁኔታ በውሉ ላይ ተቀምጧል።

    በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይም የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደ ቡና መምጣት የቀድሞ የክለቡን አጨዋወት እንደሚመልስ ተስፋ እንደጣለ ተነግሯል። አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ባሳለፈው የተጫዋችነት ጊዜ ይለብስ የነበረው 15 ቁጥር ማልያም በወቅቱ በነበረው መልክ ታትሞ ተበርክቶለታል።

    የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የሥራ አመራር ቦርድ አዲስ የአሰልጣኝ ቅጥርን የሚያከናውን የእግር ኳስ ኦፕሬሽንና ቴክኒክ አስተዳደር ኮሚቴ አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወሳል።

    የክለቡን የጨዋታ ዘይቤ ይረዳል በሚል የቀድሞውን የክለቡን ኮከብ ካሳዬ አራጌን በአሰልጣኝነት እንዲመረጥ በወሰነው መሰረትም ምርጫው ተካሂዷል።
    ካሳዬ አራጌ በዕለቱም በይፋ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ በመሆን የፈረመ ሲሆን፥ በቀጣይ የውድድር ዘመንም ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የሚመራ ይሆናል።

    አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከ1979 እስከ 1994 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡናን በመሃል ሜዳ ተጫዋችነት ያገለገለ ሲሆን፥ ከተጫዋችነት ዘመኑ በኋላም ለ1 ዓመት ከ6 ወር ገደማ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝነት መርቷል። ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ጋር በነበረው የ1 ዓመት ከግማሽ ቆይታው የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከክለቡ ጋር ማንሳት እንደቻለ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

    Semonegna
    Keymaster

    ‘በሕገ-ረቂቁ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች አልተካተቱም፤ ሃሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ያልተካተቱበትን ሰነድ ለመቀበል እንቸገራለን’ በማለት የተወሰኑ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረኩን ረግጠው መውጣታቸውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ-ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

    ‘በሕገ-ረቂቁ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች አልተካተቱም፤ ሃሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ያልተካተቱበትን ሰነድ ለመቀበል እንቸገራለን’ በማለት የተወሰኑ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረኩን ረግጠው መውጣታቸውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።

    እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች ሳይካተቱ ሕገ-ረቂቁ እንዳይጸድቅ ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮቹ ቋሚ ኮሚቴውን አሳስበዋል።

    የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ በበኩላቸው መሠረታዊ ማሻሻያዎች የተደረገባቸው አሥራ ሦስት ነጥቦች በሕገ-ረቂቁ መካተታቸውን ገልጸው፣ የብዙሃኑን የተፎካካሪ ፓርቲ ሃሳብና አስተያየት አካተናል ብለዋል።

    ማሻሻያዎቻችን አልተካተቱም ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚችሉም ወይዘሮ የሺእመቤት አሳውቀዋል።

    በውይይቱ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደመወዝና ጥቅማ-ጥቅማቸውም እንደማይከር በሚዘረዝረው ረቂቅ-ሕግ አንቀጽ 33 ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።

    በደመወዙ ኑሮውን መደጎም ያልቻለን የመንግሥት ሠራተኛ ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ደመወዙና ጥቅማ-ጥቅሙ አይከበርም ማለት ወደ ምርጫ አትግቡ ከማለት ለይተን አናየውም ብለዋል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮቹ።

    የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ኃላፊነት ያገኙትን ስልጣን፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ሃብትና ንብረት ለምርጫው አገልግሎት እንዳያውሉት ለማስቻል እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል።

    ረቂቅ ሕጉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ጀምሮ እስከ የመሥራች ቁጥር አባላት ድረስ አዳዲስ አሠራሮችን እንዳካተተም ተገልጿል።

    አንድ ሃገር-አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ቢያንስ አስር ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመሥረት ደግሞ ቢያንስ አራት ሺህ አባላት እንደሚያስፈልጉ በረቂቅ ሕጉ ተጠቅሷል።

    ሃገር አቀፍም ሆነ የክልል ፓርቲ ለመመሥረት ሃገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ የተጠቀሰውን የመሥራች ቁጥር አባላት ለማሟላት እንደሚቸገሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።

    መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት ሃገር የተጠቀሰውን የመሥራች ቁጥር አባል ማሟላት አስቸጋሪ እንደማይሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ አብራርተዋል።

    በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. 107 የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር አሁን ላይ 137 እንደደረሰ ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    [caption id="attachment_11503" align="aligncenter" width="600"]የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች[/caption]


    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በግንቦት ወር በይፋ ተመሥርቶ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን ከገለፀ በኋላ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ፥ የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ከሕኮ) ተከትሎ ራሱን አክስሞ ኢዜማን የተቀላቀለ ሁለተኛ ፓርቲ ሆኗል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከተመሠረተ 11 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መክሰሙን አስታወቀ።

    ኢራፓ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መክሰሙንና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህን (ኢዜማ) መቀላቀሉን የኢራፓ ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ አስታውቀዋል። ፓርቲው በጠቅላላ ጉባዔው ላይ 8 ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫውም ይፋ አድርጓል።

    ኢራፓ በአቋም መግለጫው፥ ኢትዮጵያ ያለችበትን ችግር ለመፍታትና ከምንጩ ለማድረቅ መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መላው የሀገሪቱ ሕዝቦች በመቻቻል፣ በትዕግስትና በአብሮነት መሥራት እንዳለባቸው ገልጿል። “ጣት መቀሳሰሩን ወደ ጎን በመተው የምክክርና የድርድር መድረኮች ተዘጋጅተው ተቀራርቦ መነጋገር ይገባል” ሲል ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል።

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    በጠቅላላ ጉባኤው መገባደጃ ላይ ኢዜማን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ ኢዜማ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ይፈጥሯቸው ከነበሩ ህብረቶች በተለየ መልኩ ራሳቸውን ያከሰሙ ድርጅቶች በምርጫ ወረዳ የተዘረጉ መዋቅሮችን በመቀላቀል እንደአዲስ ፓርቲ የተመሠረተ ፓርቲ መሆኑን አስታውሰው፤ “ትንሽ ፓርቲ ውስጥ ትልቅ ከመሆን ትልቅ ፓርቲ ውስጥ ትንሽ ሰው መሆን ይሻላል” ሲሉ በመሠረታዊ መርኾች የተስማሙ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው ሰፊ ድንኳን ያለው ጠንካራ ድርጅት የማቆምን አስፈላጊነትን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ በተደራጁ የኢዜማ ምርጫ ወረዳ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረጉት የኢዜማ መሪ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰከነ ውይይት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ባሕል አዳብረን ኢዜማን ታሪክ የሚሠራ ድርጅት እናደርገዋለን ብለዋል።

    የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአማራ ሕዝብ ህልውና እና ለሀገር እንድነት አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገለፀ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ግንቦት 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ተመሥርቶ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን ከገለፀ በኋላ ኢራፓ፣ የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ከሕኮ) ተከትሎ ራሱን አክስሞ ኢዜማን የተቀላቀለ ሁለተኛ ፓርቲ ሆኗል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)


    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የሲዳማ ዞን መስተዳደር ምክር ቤት ውሳኔን መሰረት በማድረግ በህዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ለመወሰን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

    በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እንደ አዲስ የማደራጀት፣ የምርጫ ቦርድ ስልጣንና ተግባር የሚወስነውን ሕግ የማርቀቅ እና በተወካዮች ምክር ቤት የማጸደቅ፣ የምርጫ ህጎችን የማሻሻል፣ ተቋማዊ ለውጦችን የማከናወን እንቅስቃቄ ሲደረግ ቆይቷል። ከነዚህ ተቋማዊ ለውጦች መካከል የቦርዱን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት አድርጎ የተከናወነው የምርጫ ቦርድ አባላት መረጣ ዋነኛው ነው።

    በዚህም መሰረት ከዚህ የቦርድ አባለት መረጣ ሰፊ ምክክርና ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጐበት ከተለየ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 06 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ተጨማሪ አራት የቦርድ አባላት ሹመት ተከናውኖ ቦርዱ አባላት ተሟልተውለት ሥራውን ጀምሯል።

    ቦርዱ ተሟልቶ ሥራ በጀመረበት ባለፈው አንድ ወር በእንጥልጥል የሚገኙ እና አስቸኳይ ናቸው ያላቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በቦርዱ አለመሟላት ምክንያት በእንጥልጥል ከቆዮት ጉዳዮች አንዱ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ለቦርዱ የቀረበው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት ነው።

    ቦርዱ ሥራ ከጀመረ አንስቶ የሲዳማ ዞን ክልልነትን የሚመለከቱ በተለያዩ ጊዚያት የቀረቡትን ጥያቄዎች ከመመልከቱም በላይ ከክልሉና የዞን መስተዳድር አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርጓል።

    እንደሚታወቀው የሲዳማ ዞን የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ የማደራጀት ጥያቄ ከክልሉ ምክር ቤት ለቦርዱ የደረሰው ህዳር 12/2011 ዓ.ም. ሲሆን በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 47/3/ለ/ ለክልሉ የተሰጠው “ጥያቄው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት” የሚለው የማደራጀት ጊዜ ገደብ ለቦርዱም ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

    በመሆኑ በሕግ መንግስቱ የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በቀሩት 5 ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን የመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

    ሕዝበ ውሳኔ የሚከናወነው የሕዝብን ፍላጐትና ውሳኔ ህጋዊ እና ነፃ በሆነ አግባብ መሰጠቱን ለማረጋገጥ ነው። በመሆኑም ቦርዱ ተገቢና በቂ ዝግጅት አድርጐ ሕዝበ ውሳኔውን ማካሄድ ይችል ዘንድ የሚያደርጋቸው ዝግጅቶች፦

    • የሕዝበ ውሳኔ አካሄድ የሚመራበት የሥነ-ስርዓት መመሪያ ማዘጋጀት
    • የሕዝበ ውሳኔ አጠቃላይ ጊዜ ሰሌዳና በጀት ማዘጋጀት
    • በሕዝበ ውሳኔ ዝግጅትና ድምፅ መስጠት ሂደት ስለሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ግብረ ኃይል ማደራጀትና ዕቅድ ማፅደቅ
    • ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚዎች መመልመል፣ ማሰልጠንና ማሰማራት
    • ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ ማዘጋጀት፣ የድርጊት መርሃ ግብር ማውጣት
    • በሕዝበ ውሳኔ አፈፃፄም ሂደቱ ላይ የጋራ ምክክር መርሃ ግብሮችን አውጥቶ መተግበር
    • የሰነድና ቁሳቁስ ዝግጅትና ህትመት ሥራዎች ማከናወን
    • ድምፅ መስጫ ወረቀቶችና ፖስተሮች ማዘጋጀት፣ ማሳተም፣ ማሰራጨት
    • ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ማሰጠት
    • ቆጠራና ውጤት ማሳወቅ

    ሲሆኑ በሌላ በኩል ሂደቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

    በዚህም መሰረት፦

    1. የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ከክልሉ መንግስትና ከዞኑ መስተዳደር ጋር በመመካከር በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሀዋሳ ከተማ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልል መሆን የሚያረጋግጥ ቢሆን በከተማዋ ላይ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብትና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበትን አሠራር አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዲያሳውቁ፤
    2. በአዋጅ 532/1999 አንቀጽ 107 በተጠቀሰው የትብብር ድንጋጌ መሰረት የሕዝበ ውሳኔው ጸጥታና ደኅነትን (electoral security) ማስጠበቅን አስመልክቶ የፌደራል ፓሊስ፣ የክልሉ ፓሊስና የዞኑ ፓሊስ በትብብር የሚሠሩበትን ዝርዝር እቅድ እንዲያወጡና ከቦርድ ጋር ተባብረው እንዲሠሩ፤
    3. የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሄር ብሔረሰብ አባላት ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ግልጽ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፍ እንዲያዘጋጅና ለቦርዱ እንዲያሳውቅ ምርጫ ቦርድ የወሰነ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ምላሽ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሁፍ እንዲያሳውቁ ወስኗል፤
    4. በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግስቱና በምርጫ አዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነት ዓለም አቀፍ የምርጫ መሰረታዊ መርሆዎች ጋር በማጣመር ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ለመግለጽ ይወዳል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ሐምሌ 10/2011 ዓ.ም.

    የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ


    Anonymous
    Inactive

    ፌዴሬሽኑ ዛሬም የሸገር ክለቦችን በአደባባይ እየናቀ ነው
    (ከቡና ሠማይ ሥር)
    —–

    ኳስ ክብ መሆኗን የፌዴሬሽን ወንበር ላይ ከተቀመጡ በኋላ ያወቁት የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኝ አመራሮች በዘር ተቧድነው በደካማ ውሳኔቸው የእግር ኳሱን የቁልቁሊት ጉዙ እያፈጠኑት ይገኛሉ።

    ይህ አዲስ አበባ ጠል የሆነው እግር ኳስ ፌዴሬሽን አምና የኤሌትሪክ እግር ኳስ ክለብን በግፍ ከሊጉ ያሰናበተው ፌዴሬሽን ዘንድሮ ደግሞ የግፍ አርጩሜውን መከላከያ እግር ኳስ ክለብ ላይ አሳርፏል።

    የስሑል ሽረ እና የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ (ወልዋሎ ዓ. ዩ.) ጨዋታ ከነመከላከያ እና ከደቡብ ፖሊስ ጋራ የመትረፍ እና የመውረድ አደጋ ውስጥ ያለው። ስሑል ሽረ ቀደም ብሎ እንዲጫወት እንዲሁም እስከ 71ኛው ደቂቃ ድረስ በወልዋሎ ዓ. ዩ. አንድ ለዜሮ ሲመራ የነበረው ስሑል ሽረ ደጋፊው ሜዳ ውስጥ ገብቶ ለአርባ አምስት ደቂቃ ያህል ጨዋታውን ካቋረጠ በኋላ ዋና አሰልጣኙ ዮሃንሰ ሳህሌ ጨዋታውን እንዳይመራ በማድረግ ውጤቱን በግፍ ነጥቋል። በየጨዋታው ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ በመመደብ ጨዋታውን በአምስት ካሜራ እና በሦስት ኮሜሽነር ሲቆጣጠር የነበረው ፌዴሬሽን ጉዳዩን ባላየ በማለፍ መከላከያን ከሊጉ እንዲወረድ አድርጓል።

    በሸገር ክለቦች ላይ ግፍ መሥራት የማይሰለቸው ፌዴሬሽን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የዋንጫ ፉክክር ውስጥ እያለ ቀሪ ጨዋታዬን ሳልጫወት ወደ ጎንደር በማቅናት ከፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ጋር አልጫወትም በማለት ተገቢ ጥያቄ እያቀረበ ቢገኝም ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ‘ምን ታመጣላቹ!?’ በሚል በእብሪት በተሞላበት እና ባላዋቂነት ውሳኔ ፎርፌ በመስጠት ዛሬም ለሸገር ክለብ ያለውን ንቀት አሳይቷል።

    አሁን ከዚህ በብሄር ከተደራጀው ሊግ እና በዘር ከተቧደነው ፌዴሬሽን ጋር አብሮ መቀጠል የማያዋጣበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረስን ይመስለኛል ስለዚህ የከተማውን ሊግ ሳይውል ሳያድር ይፋ ማድረግ ምርጫ የሌለው መፍትሄ ነው።

    የአዲስ አበባ ክለቦች መግለጫ ከማውጣት እና የአንድ ሰሞን አጀንዳ ከመሆን በዘለለ አትኩሮት በመስጠት የተሻለ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

    እግር ኳስ ሳይገባው እግር ኳስ ላይ ከተቀመጠ አመራር ጋራ መለያያት ይመጨረሻው አማራጭ ነው።
    (ከቡና ሠማይ ሥር)

    Semonegna
    Keymaster

    ‹‹የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር›› በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሠራተኞችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

    አርባ ምንጭ (AMU) – በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል።

    የዝግጅቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በንባብ ባህል ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር እውቀት እንዲስፋፋ እና ልምድ እንዲዳብር ለማድረግ እንዲሁም ማኅበረሰቡ የመጽሐፍትን ጥቅም ተረድቶ ከሌሎች ወጪዎች በመቀነስ የመግዛት ልምድ እንዲቀስም ለማስቻል መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሰገድ ካሣሁን ገልፀዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ ገጣሚ፣ ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የንባብ ጅማሮ፣ ጥቅምና የመምህራን ሚናን አስመልክቶ ባቀረቡት አንኳር ሀሳብ ንባብ ሊለካ የሚችለው በአንባቢው ላይ በሚያመጣው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ንባብ የተለያየ ነገር ግን የተዋሀደ ይዘት ያለው እንደመሆኑ ማኅበራዊ ተግባቦት እንዲጨምር፣ ተአማኒ እውቀት እንዲዳብር ብሎም ባልኖርንበት ዘመንና ቦታ በምናብ እንድንኖር የሚያደርግ ጥልቅ ምስጢር አለው ብለዋል።

    ጥሩ አንባቢ የአፃፃፍ ስልትና የቃላት አመራረጥን ከመረዳት ባለፈ በሚያነበው ጉዳይ ራሱን የሚመለከትና የሚፈትሽ እንዲሁም የሌሎችንም ስሜት መረዳት የሚችል እንደሆነ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ተናግረዋል። ለዚህም መምህራን ከመጽሐፍት ምርጫ አንስቶ መልካም ልምዶችን ለትውልዱ በማካፈል በመረጃ የዳበረና ያወቀ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ለአንድ ማኅህበረሰብ እድገት የተማረ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገሪቱ ከመሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።

    ማንበብና መጻፍ ከግለሰብ ባለፈ ለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ናቸው ያሉት ፕሬዝደንቱ፥ የንባብ ባህል እንዲዳብር አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት፣ አቅምና ጊዜ በተገቢው በመጠቀም፣ ተፈላጊውን የአዕምሮና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት እንዲሁም ምክንያታዊ ትውልድ በመፍጠር ከግለሰብና ከማኅበረሰብ ባለፈ ለአገር ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚቻል ገልፀዋል። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ ባህል መዳበር አጽንዖት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ምንም እንኳ ጥንታዊ የሆኑና የተለያየ ዘውግ ያላቸው የስነ-ጽሑፍ ውጤቶች እንዲሁም ወቅታዊ አዕምሯዊ ውጤት የሆኑ የህትመት ውጤቶች ቢኖሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው የንባብ ባህል መቀዛቀዝ በመረጃ የበለጸገና ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ እንደ አገር ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ ተናግረዋል። በአገሪቱ ለንባብ የሚውለው ጊዜ በዓለም አንባቢ ዜጋ ካላቸው አገራት አንጻር በሣምንት ለንባብ ከሚያውሉት አማካይ ጊዜ በእጅጉ መራቁን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያስረዱም ዶ/ር የቻለ ገልፀዋል።

    በማኅበረሰቡ ዘንድ መጽሐፍትን ገዝቶ ከማንበብ ይልቅ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ምርኮኛ መሆን፣ የወረቀትና የህትመት ዋጋ መጨመርና ሌሎችም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ የንባብ ባህል መዳበር ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ባህሉ እንዲያንሰራራና መሻሻሎች እንዲመጡ ጠንከር ያለ ጥረትን ይጠይቃል።

    በንባብና ሚዲያ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚያጠነጥን የውይይት መነሻ ጽሑፍ የዶክትሬት (PhD) ተማሪ በሆኑት አቶ ተመስገን ካሣዬ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በዚህም ዘመኑ የቴክኖሎጂና የመረጃ ከመሆኑ ባሻገር የሚዲያ ተግባቦት ባህሎችን ከሌላው ጋር የመቀየጥ አቅም ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል።

    ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ንባብ የአንድ ወቅት ሂደት ስላልሆነ በየደረጃው ያለው ሁሉም ማኅበረሰብ ከዋና ሥራው ጎን ለጎን መጽሐፍት ማንበብን ልምድ በማድረግ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችል አቅም ማጎልበት እንደሚገባው ገልጸዋል። በተለይም በአገራችን ያሉ ደራሲያን መጽሐፍት ስነ-ጽሑፋዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ፣ ታሪክን ሳያዛቡ እንዲሁም በሥነ-ምግባር ረገድ የተሻለ አቀራረብ እንዲይዙ በማድረግ ንቁ ማኀበረሰብ በመፍጠር ለአገራዊ ለውጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

    በመጽሐፍት አውደ ርዕይና ሲምፖዚየሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከአዲስ አበባ የመጡ የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎችና የመጽሐፍት ሽያጭ መደብሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የንባብ ባህል


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች አሜሪካ ውስጥ በካሊፎርንያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር አዲስ በተቋቋመው ፓርቲ አጠቃላይ ሁኔታና የሀገራችን ኢትዮጵያን (የፖለቲካ) ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተ ተወያዩ።

    የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ሦስት ከተሞች ከሚያደርጉት ውይይቶች የመጀመሪያው በሆነው የሎስ አንጀለስ ውይይት፣ የፓርቲው አመሠራረት፣ ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፓርቲው እና በአጠቃላይ ሀገሪቷ ውስጥ እንዲገነባ የሚፈለገው የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዴት ማገዝ እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል። በቪዛ መዘግየት ምክንያት ለስብሰባው መድረስ ያልቻሉት የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ የመክፈቻ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ኢዜማ ባደረገው በዚህ ውይይት፥ የሀገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም የውይይቱ አካል ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ “ሁለንተናዊ መሻሻል” ተብሎ የሚፈረጅ (reform) እንጂ አብዮት (revolution) አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ለውጡ ያልገባቸው (የሚያስጨንቃቸው) የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈጥሩት እንቅፋት፣ በየክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እና ብዛት ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር የለውጡ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ እና በየደረጃው መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

    በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢዜማ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት አደረጃጀት (ቻፕተሮች) በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች የሚዋቀሩ ሲሆን በሀገራችን ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የሚፈልጉ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በነዚህ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ተላልፏል።

    ከፓርቲው ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢዜማ ግብረ-ኃይል በአምስት አቅጣጫ ተንቀሳቅሷል። ከአዲስ አበባ በመነሳት በአምስት አቅጣጫ መዳረሻውን ያደረገ ግብረ-ኃይል ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ጀምሯል።

    መነሻውን ከመስቀል አደባባይ ያደረገው ግብረ-ኃይል የኢዜማ ምክትል የፓርቲ መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት መሸኛ ተደርጎለታል።

    ግንቦት 24 ቀንጉዞውን የጀመረው ግብረ ኃይል፣ በኢዜማ ለተደራጁ ለ216 የምርጫ ወረዳዎች ጊዚያዊ የእውቅና ደብዳቤ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ደረሰኝ፣ የአባላት ፎርም እና የድርጅት ጉዳይ መመሪያዎቹን ተደራሽ ለማድረግ በአምስት አቅጣጫዎች ጉዞ ጀምሯል። በየመጀመሪያው ዙር ጉዞ ተደራሽ የሚደረግባቸው፡-
    1. ከአዲስ አበባ – ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ወልዲያ መዳረሻውን ሰቆጣ
    2. ከአዲስ አበባ – ፍቼ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር አድርጎ መዳረሻውን ጎንደር
    3. ከአዲስ አበባ – ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ ጌድኦ፣ አለታ፣ መዳረሻውን አዶላ (ክብረ መንግስት)
    4. ከአዲስ አበባ – አምቦ፣ ነቀምት፣ ጊምቢ፣ ጅማ፣ መዳረሻውን ቤንች ማጂ
    5. ከአዲስ አበባ – አዳማ፣ አሰላ፣ ወላይታ፣ ሀዲያ፣ ዳውሮ፣ ወልቂጤ፣ መዳረሻውን ጉራጌ በማድረግ ሲሆን በቀጣይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ ቦታዎችንና ከተማዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ጉዞ እንደሚኖር ታውቋል።

    የሀገር መረጋጋትን ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ የሚሠራው ኢዜማ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ይህንኑ ዓላማ ተፈፃሚ ለማድረግ እንዲሠሩ በሁሉም አቅጣጫ የሚጓዙት የግብረ ኃይሉ አባላት አፅዕንዎት ሰጥተው የሚያስገነዝቡ ይሆናል። በየአካባቢው የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የየአካባቢው ሕዝብ ለግብረ -ኃይሉ አባላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ ተላልፏል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ


    Semonegna
    Keymaster

    ባለፉት ስድስት የሽልማት መርሀግብሮች አገራችን የምትኮራባቸውን የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ላከናወኑ ሰዎች እውቅና የተሰጠው ከሕዝብ በቀረበ ጥቆማ መሠረት ሲሆን፥ የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም ለአገራቸው እድገት አርአያነት ያለው አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች ዕውቅና የሚያገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–ሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም የዕጩዎች ጥቆማ ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደጀመረ እና እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንደሚከናወን የሽልማት አስተባባሪ ኮሚቴው አስታወቀ።

    ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለአገርና ለሕዝብ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባርን ያከናወኑ ሰዎችን ዕውቅና የሚሰጠው የበጎ ሰው ሽልማት ሰባተኛው መርሃ ግብር ነሀሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ይካሄዳል።

    ሽልማቱም በመምህርነት፣ በሳይንስ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በበጎ አድራጎት ሥራ፣ በቢዝነስ ሥራ ፈጠራ፣ በመንግስት የሥራ ተቋማት ኃላፊነት፣ በቅርስና ባህል፣ በማኅበራዊ ጥናት፣ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፎች እና ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎችን የሚያካትት እንደሆነ ኮሚቴው ገልጿል።

    ለእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ ሦስት ዳኞች ተመርጠው ምርጫው የሚከናወን ሲሆን ዳኞቹም የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና በታማኝነት ምርጫውን ያከናውናሉ ተብለው የታመነባው እንደሆኑ በመግለጫው ወቅት ተጠቅሷል።

    ኮሚቴው እንደገለፀው፥ ባለፉት ስድስት የሽልማት መርሀግብሮች አገራችን የምትኮራባቸውን የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ላከናወኑ ሰዎች እውቅና የተሰጠው ከሕዝብ በቀረበ ጥቆማ መሠረት መሆኑን ገልፆ፥ መርሀግብሩን ለዚህ ያበቃው በሂደቱ የሕዝብ ተሳትፎ በመኖሩ ስለሆነ ይህም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

    የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማ ለአገራችን መልካም የሠሩ፣ አገራዊ ተልዕኳውን በብቃት የተወጡ፣ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጪ ተግባራትን ያከናወኑ፣ የአገሪቱን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል እንዲጠበቅና የሀገራቸው ስልጣኔ ከፍ እንዲል የሠሩ ኢትዮጵያዊያንን በማበረታታት ዕውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሥራዎችን ለሀገራቸው ማበርከት እንዲችሉ ማስቻል ነው።

    ይህንን የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማ ከግምት ውስጥ በማስገባት ህብተረሰቡ ጥቆማውን ከግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በስልክ፣ በቫይበር (Viber)፣ በቴሌግራም (Telegram)፣ በኋትሳፕ (WhatsApp)፣ በኢሜይል (e-mail)፣ በፖስታና በአካል በመቅረብ መጠቆም እንደሚቻል ኮሚቴው ያሳወቀ ሲሆን፥ ለዚህም አገልግሎት በስልክ ቁጥር 0940140813begosewprize@gmail.com እና ፖስታ ሳጥን ቁጥር 150035 አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ መጠቀም ይቻላል ተብሏል።

    የዘንድሮው የሽልማት ፕሮግራም ለአገራቸው እድገት አርአያነት ያለው አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች ዕውቅና የሚያገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የበጎ ሰው ሽልማት


    Anonymous
    Inactive

    ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል። የብርሃኑ ነጋን ፅናትና የአቋም ሰውነቱን መካድ ነውር ነው! እሱን በፍርሃትና በአቋም የለሽነት ማማት ብልግና ነው። እሱን በዘርና በጎሳ ጉሊት መመደብ ውለታ ቢስነት ነው!

    የነጋ ቦንገር ልጅ!
    («ዘውድዓለም ታደሠ»)

    የልደቱ አያሌው ድብን ያልኩ አድናቂ ስለሆንኩና ብርሃኑ በልደቱ ጉዳይ የወሰደው አቋም አግባብነት ያለው (fair) ነው ብዬ ስለማላምን ትንሽ አዝኜበታለሁ። ሆኖም ግን እውነት እውነት ነችና ስለብሬ [ብርሃኑ ነጋ] የማልክዳቸው ሃቆች አሉ! (ስለእሱ የሰማኋቸውን “ሴራዎችን” (conspiracies) እዚህ ጋር አላነሳቸውም።)

    ብርሃኑ ነጋ እንደብዙዎቹ ፖለቲከኞቻችን ‘ፖለቲካ ክፍት የሥራ ቦታ ነው’ ብሎ ወደተመታው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልተቀላቀለም። በደርግ ዘመን ብዙዎች በወላጆቻቸው ሽካ ከብሔራዊ ውትድርና አምልጠው ማታ ማታ ገዳም ሰፈር ከቆነጃጅት ጋር ቡጊ ቡጊ ሲጨፍሩ ብሬ በዚያ እድሜው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሆኖ በአገሩ ጉዳይ ከሞት ጋር ሌባና ፖሊስ ይጫወት ነበር። (የሚወዳት እህቱንም አጥቷል።)

    በኢህአዴግም ግዜ ከመለስ፣ ከታምራትና ከበረከት ጋር ባለው ልዩ ወዳጅነት (special friendship) ተሞዳሙዶ ቢያሻው ስልጣን፣ ቢያሻው መሬት ሸምቶ፣ ቢያሻው ሚኒስትር፣ ቢያሻው ቀጭን ኢንቨስተር ሆኖ ዘንጦ መኖር ሲችል ላመነበት ነገር ጎምበስ ቀና ሳይል የተቃዋሚውን ጎራ ተቀላቅሏል።

    ምንም እንኳ በየትኛውም ዓለም ቢሄድ እጁን ስመው የሚቀበሉት ምርጥ ምሁር ቢሆንም ከምቾቱ ይልቅ ወደወህኒ ወርዶ ሞት ተፈርዶበታል። እስር ቤት ውስጥ የረሃብ አድማ አድርጓል። በስተርጅና ዘመኑም እንዳቅሚቲ የትጥቅ ትግል ለማድረግ ተሟሙቷል። በተደጋጋሚ በርሃ ወርዷል። የፖለቲካ አኪያሄዱን ወደድነውም ጠላነውም በሚችለው አቅም ለአገሩ ህዝብ ድምፅ ሆኗል! ይሄ የማይካድ ሃቅ ነው!

    ከግማሽ ምእተ-ዓመት በላይ የሃብት ማማ ላይ ከተቀመጠ ቤተሰብ ተወልዶ፣ ዩኒቨርሲቲ ደሞዙን ለምስኪን ተማሪዎች እየሰጠ አስተምሮ፣ እድሜውን ሙሉ ባለሰባት ኮከብ (seven-star) ሆቴል እንደፓፍ ዳዲ አምስት ቺኮች አቅፎ መዝናናት እየቻለ ያሻው አገር ሄዶ በዕውቀቱ ተከብሮ መሥራት እየቻለ፣ በአፍሪካ ገናና የሆነ የጦር ኃይል አለኝ የሚልን ኃይል በጦርነት አሸንፋለሁ ብሎ በወኔ የተነሳ፣ ቤተሰቡን ጥሎ በእስር የማቀቀ፣ አገሩ ላይከፍተኛ ዕውቅና እንዳለው ግለሰብ (VIP standard) መኖር ሲችል በአሸባሪነት ተፈርጆ ብላክ ሊስት (black list) ውስጥ የገባ አንድ ሰው ባፈላልግ ያገኘሁት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ብቻ ነው!

    አሁን ደግሞ ብሬ በተጋዳላይ ታርጋ የሚንቀሳቀስ ፓርቲውን አክስሞ አዲስ ፓርቲ በማቋቋም ከመጀመሪያው “ሀ” ብሎ (from the scratch) ሊነሳ ነው። ይህን ሁሉ የሚያደርገው ለምንድን ነው? ለሀብት እንዳንል እንኳን እሱ ዘር ማንዘሩም ሃብታም ነው። ለስልጣን እንዳንል ገና ድሮ በቀላሉ ማግኘት ይችል ነበር! እና ለምንድነው ህይወቱን እንዲህ በከባድ ወጥ ውረዶች የተሞላ (tragedy) ያረገው?… መልሱ ቀላል ነው። ብሬ (ብርሃኑ ነጋ) የአቋም ሰው ነው! ብሬ ላመነበት ነገር ከገገመ ገገመ ነው! አዲዮስ!

    እኔ ከላይ እንደነገርኳችሁ ‘ለብሬ እሰዋለታለሁ፣ ብርሃኑ ነጋ ያማልዳል፣…’ ምናምን የምል አድናቂው አይደለሁም። ነገር ግን አክባሪው ነኝ። ፅናትና የአቋም ሰውነቱን መካድ ነውር ነው! እሱን በፍርሃትና በአቋም የለሽነት ማማት ብልግና ነው። እሱን በዘርና በጎሳ ጉሊት መመደብ ውለታ ቢስነት ነው!

    […] የባቄላ ፍሬ የምታህል ዛኒጋባ ቤት ሳትኖርህ ቫንዳም፣ ቫንዳም መጫወት፣ የምታጣው ነገር ሳይኖር ኃላፊነት (risk) መውሰድና ከባዱን የሕይወት መንገድ መምረጥ’ኮ ያለና የነበረ ነው። ነገር ግን ሁሉ ሞልቶልህ ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል! ይኸው ነው!

    ረጅም ዕድሜ ለነጋ ቦንገር ልጅ!

    [ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዱአለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ መሪና ምክትል መሪ በመሆን ተመረጡ። ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ 912 ድምፅ በማግኘት የፓርቲው መሪ በመሆን ተመርጠዋል። በተመሳሳይ አቶ አንዱአለም አራጌ የፓርቲው ምክትል መሪ በመሆን ተመርጠዋል። እንደዚሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ 722 ድምፅ በማግኘት ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፥ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን ተመርጠዋል። — ሰሞነኛ ኢትዮጵያ]

    ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ


     

    Semonegna
    Keymaster

    የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል። ዶ/ር ጀማል ዩኒቨርሲቲው ውስጥ እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች አገልግለዋል።

    ጅማ (ሰሞነኛ) – ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዝዳንትነት ቦታ ብቃቱና ፍላጎት ያላቸዉ አመልካቾች እንዲወዳደሩ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባወጣዉ ግልጽ ማስታወቂያ መሠረት አመልካቾች መረጃቸዉን በማስገባት በተለያዩ ደረጃዎች ዉድድር ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል::

    በምርጫ ሂደቱም ከ250 በላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የዩቨርሲቲዉ ሴኔት እና የሥራ አመራር ቦርድ መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የቃለ-መጠይቅ ፓናል በማካሄድ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩና ማጣሪያዎችን አልፈው የደረሱ 9 ዕጩዎችን በመገምገም 5 ዕጩዎችን ለዩኒቨሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ አስተላልፏል።

    የዉድድሩ ሂደት የተመራዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣዉ መስፈርት ሲሆን፤ ሂደቱን ለመምራት አምስት ሰዎችን የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየደረጃዉ ግምገማ ሲያካሄድ ቆይቷል። ኮሚቴዉ ከቦርድ አባላት፣ ከሴኔት አባላት፣ ከተማሪ፣ ከመምህራን እና ከአስተዳደር ሠራተኞች ተወካይ የተዉጣጣ ሲሆን የዉድድር ማስታወቂያ ከማዉጣት ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ጉባዔ የሂደቱን ዉጤት እስከ ማሳወቅ ድረስ በትጋት ሲሠራ ቆይቷል።

    በዚሁ መሠረት የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ሚያዚያ 02 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔደው ልዩ ጉባዔ 3 ዕጩዎችን (ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ ፕሮፌሰር አርጋዉ አምበሉ እና ዶ/ር ናቃቸዉ ባሹን) በዕጩነት ለሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቅርቧል:: የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ዶ/ር ጀማል አባፊጣን ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል።

    ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የዩኒቨርሲቲዉ ነባር መምህር እና ተመራማሪ ሲሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች በዩኒቨርሲቲውና ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በሃላፊነት ያገለገሉና በአሁኑም ወቅት የማኅበረሰብ አገልግሎት ቢሮ ዳይሬክተር ሆነዉ እያገለገሉ ይገኛሉ። ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታቲስቲክስ (BSc in Statistics)፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ (MA in Economics)፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በደቡብ ኮርያ ቻንችኦን ከተማ ከሚገኘው ካንግዎን ናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Kangwon National University; Chuncheon, South Korea) በግብርና ግብዓቶች ምጣኔ ሀብት (Agricultural Resources Economics) አግኝተዋል።

    ስለ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ይህን ማስፈንጠርያ በመጫን ሙሉ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።

    ምንጭ፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ጀማል አባፊጣ


Viewing 15 results - 91 through 105 (of 116 total)