Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 31 through 45 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    በ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል — የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፥ በተለያዩ አካባቢዎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መሥመር ውጪ ያሉ (ኦፍግሪድ/off-grid) የተሠሩ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን ቤቶችን ተጠቃሚ አድርገዋል።

    ከኦፍ ግሪድ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎቹ በተጨማሪ የቤት ለቤት የፀሐይ ኃይል ቁሶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህ ሥራ በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

    የ2014 ዓ.ም በተለይ በኢነርጂው ዘርፍ ትልቅ የማምረት አቅም የተፈጠረበት ዓመት መሆኑን የጠቁመው ሚኒስቴሩ፥ ሆኖም እምርታ እየታየበት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያዳርሳቸው የማይችላቸው የተንጠባጠቡ መንደሮችን የፀሐይ ኃይል እንደ አማራጭ እንደሚወሰድም ገልፀዋል።

    እስካሁን በተጠኑ ጥናቶችና ባለው ነባራዊ እውነታ በሀገሪቱ ያሉ የኢነርጂ ምንጮች የመጀመሪያው ውሃ፣ ቀጥሎ ደግሞ የፀሐይ ኃይል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ከውሃ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማሳደግ ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን ሶላር ኢነርጂን (solar energy) በመጠቀም የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከፍ ለማድረግ እየሠራች የምትገኘው ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

    በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሕብረተሰቡ በመንግሥት በኩልና በግሉ ከሚያገኛቸው የፀሐይ ኃይል አገልግሎቶች በተጨማሪ በተበታተነ መልኩ ያሉ መንደሮችን ለማገልገል የተገነቡ የውሃ ተቋማት ከሚጠቀሙት ጄነሬተር ኃይል በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ ኢነርጂዎች እንዲጠቀሙ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

    ሕብረተሰቡ በግሉ የፀሐይ ኃይልን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀይሩ መሣሪያዎችን መጠቀም መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ፥ መንግሥት ይህንን ለመደገፍ በአግባቡ የማይሠሩና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የሶላር ኢነርጂ መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በትኩረት መሥራቱንም ተናግረዋል።

    ከዚህ ጎን ለጎን የተበታተኑ መንደሮችን ከዋናው የኤሌክትሪክ መሥመር ውጭ በሆነ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በ2015 ዓ.ም አነስተኛ የሆኑ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ዲዛይን ማድረግ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

    በተለይ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ብዙ ወንዞች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ ወንዞቹን ለኃይል ማመንጫነት በመጠቀም ዜጎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

    ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ፥ ሀገሪቱ ካላት ወንዞች አብዛኞቹ ያሉበት ተፋሰስ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ምቹ መሆናቸው መረጋገጡንና በትናንሽ ወንዞች እንኳ ብዙ የኃይል እጥረቶች መፍታት እንደሚቻልም አብራርተዋል።

    በተመሳሳይ መልኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በባዮጋዝ (biogas) አጠቃቀም ረገድም ሕብረተሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ እንዲጠቀም ለማስቻል ጥረት መደረጉን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በዚህም ብዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በዘርፉ በመቀላቀል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፤ ጥረቱ በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

    Semonegna
    Keymaster

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በባህር ዳር ከተማ፣ በጣና ሐይቅ እና ሐዋሳ ሐይቅ ሦስት ሆቴሎችን ሊከፍት ነው
    /MIDROC Investment Group to open three international brand hotels in Bahir Dar, Lake Tana, and Lake Hawassa/

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ “ፕሮቴያ ማርዮት”ን በባህር ዳር ከተማ፣ በጣና ሀይቅ እና በሀዋሳ ሀይቅ ደግሞ “ፎር ፖይንትስ ባይ ሸራተን”ን ለመክፈት የሚያስችሉ ሦስት የፍራንቻይዝ ስምምነቶችን ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር ተፈራረመ።

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር በባህር ዳር የሚገኘውን ጣና ሆቴል እና ሀዋሳ የሚገኘውን ፕሮግረስ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ሁለቱንም በ“ፎር ፖይንት ባይ ሸራተን” ብራንድ እንዲሁም የብሉ ናይል (አቫንቲ) ሪዞርትን በ“ፕሮቴያ ማርዮት” ብራንድ ለመክፈት ነው ስምምነቱን ያደረገው።

    በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኩል ስምምነቱን የተፈራረሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አህመድ እና የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሰለሞን ዘውዱ ናቸው፡፡ ሚስተር ከሪም ቼሎት፣ ሚስተር ጁጋል ኩሻላኒ እና ሚስተር ኤድዋርድ ኤድዋርት ሳንቼዝ ደግሞ በማርዮት ኢንተርናሽናል በኩል ስምምነቱን ፈርመዋል።

    የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድም ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር ስምምነት በማድረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ፥ “ከዚህ ዝነኛ ብራንድ ጋር የረጅም ጊዜ አጋርነታችንን እያሰፋን በመምጣችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።

    ማርዮትን ወክለው የተናገሩት ሚስተር ከሪም ቼሎት በበኩላቸው ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ያላቸውን አጋርነት በማሳደጋቸው እና በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ በማስፋታቸው ደስታ እንደተሰማቸው አስረድተዋል።

    ሁለቱ ወገኖች ባለፈው በፈረንጆቹ ህዳር 2021 በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ የሚገኘውን የዌስቲን ሆቴል ለማስተዳደር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ

    MIDROC Investment Group to open three international brand hotels in Bahir Dar, Lake Tana, and Lake Hawassa

    MIDROC Investment Group signs three franchise agreements with Marriott International to open Protea by Marriott in Bahir Dar, Four Points by Sheraton at Lake Tana as well as another Four Points by Sheraton at Lake Hawassa, Ethiopia.

    MIDROC Investment Group has signed an agreement with Marriott International to open the Tana Hotel located in Bahir Dar and Progress International Hotel located in Hawassa, both with Four Points by Sheraton, and Blue Nile (Avanti) Resort, located in Bahir Dar to Protea by the Marriott brand.

    Mr. Jamal Ahmed, CEO, and Mr. Solomon Zewdu, D/CEO of the Hospitality Cluster, signed the agreement on the Midroc Investment Group side. On the other hand, Mr. Karim Cheltout, Mr. Jugal Khushalani, and Mr. Edward Edwart Sánchez signed the agreement on Marriott International’s side.

    Mr. Jamal Ahmed, CEO of the Investment Group, said that we are excited to work with Marriott International as we continue to expand our long-standing partnership with this famous brand.

    Mr. Karim Chelout of The Marriot said with this significant project, we are thrilled to grow our partnership with MIDROC Investment Group and expand our presence in Ethiopia.

    It is recalled that the two parties signed to manage the Westin Addis Hotel located next to the African Union Headquarters in Addis Ababa in last November 2021.

    Source: MIDROC Investment Group

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን አስረከበ

    ባሕር ዳር – የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ነሐሴ 21 ቀን፥ 2014 ዓ.ም የተማሪዎችን ምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በማኅበረሰብ አገልግሎት ጉልህ አስተዋፅዖ ላበረከቱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ) የሰሜን ወሎ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለሆኑት ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማት ለተወካያቸው መስጠቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን ብፁዕ አባታችን በአሁኑ ሰዓት የሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን ጨርሰው በመመለሳቸው መስከረም14 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ሕንፃ ተገኝተው የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

    የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የዕለቱ የክብር እንግዳ በሆኑት በብፁዕ አቡነ አብርሃም ፀሎትና ቡራኬ ተጀምሯል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት በጭንቅ እና በመከራ ወቅት ሀይማኖትና ዘር ሳይለዩ የከበረ ሥራን ሠርተው የከበሩትን ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በማክበራችን እኛም ብዙ አትርፈናል ሲሉ ተናግረዋል። በወቅቱ አቅም ያላቸው በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው በሚሸሹበት ወቅት በጦርነት፣ በችግር እና መከራ ውስጥ ወደ ሚገኘው ሕዝባቸው ጋር በመሄድ የመከራው ቀንበር እንዳይሰማቸው ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመጣውን ክፉ ቀን እንዲያልፍ በማድረጋቸው ታሪክ የማይረሳው ሥራን ሠርተዋል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

    የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ እንዲሁም ዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀይማኖት፣ ዘር እና ቀለም ሳይለይ በሥራቸው ብቻ መዝኖ ለብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የክብር ዶክትሬት በመስጠቱ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ስም ምስጋና አቅርበዋል። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በዚያ ሽብር እና ጭንቅ በነገሰበት ወቅት ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ አማኝ እና ኢ-አማኝ ሳይሉ ሁሉንም የሰው ዘር በእኩል ዓይን በማየት የመከራውን ቀን ከሕዝባቸው ጋር ያሳለፉትን ድንቅ አባት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዕውቅና ሽልማት በመስጠቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መደሰቷን ተናግረዋል።

    አቡነ ኤርምያስ በበኩላቸው የተሰጠኝ የክብር ዶክትሬት ለእኔ ሳይሆን በሁለቱም ወገን በጦርነቱ ወቅት ቆስለው በየጫካው የወደቁ ወገኖችን ቁስል በማጠብ እና ከልጆቻቸው ጉሮሮ ቀንሰው ለቁስለኞች በማብላት ትልቅ ፍቅር ላሳዩን እናቶች እና በጸሎት ሲጠብቁኝ ለነበሩት ለብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ከጎኔ ሆነው በምክር ለረዱኝ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሀዋርያዊ ተልዕኮ ዘወትር ለሚፋጠኑት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ድልድይ ሆነው ላገናኙኝ የመስጊድ ኮሚቴ አባላት፣ ሰብዓዊ ግዴታቸውን ለተወጡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ወሎ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚዳንቶች መምህራን እና ሠራተኞች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    አቡነ ኤርምያስ

    Semonegna
    Keymaster

    የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል በሰላምና በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው – አስተዳደሩ

    ደሴ (ኢዜአ) – የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልን በሰላምና በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

    ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪዝም መስህቦች መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙበት ባህላዊና ሀይማኖታዊ የንግሥ በዓላት ዋነኞቹ ናቸው።

    የመስቀል/ ደመራ በዓል፣ የጥምቀት በዓል፣ እሬቻና ፍቼ ጨምበላላን የመሳሰሉት በዓላት ደግሞ አገሪቷ ለዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ የቱርስቶችን ዓይን መማረክ የቻሉ ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ናቸው።

    በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በየዓመቱ መስከረም 21 የሚከበረው ግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልም ሰላሙን በማረጋገጥ ሀይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በማክበር እስከ ዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሰፊ ሥራዎች መሠራት ይገባቸዋል።።

    የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን እንደገለጹት፥ በዓሉን በሰላምና በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ናቸው።

    በኮሮና ቫይረስ እና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚፈለገው መልኩ አለመከበሩን ጠቁመው ዘንድሮ በርካታ ምዕምናን በተገኙበት በልዩ ሁኔታ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።

    በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግርና በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ኮሚቴ እስከ ታች ድረስ በማዋቀር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው የመሠረተ ልማት ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

    የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮነን በበኩላቸው በዓሉን በድምቀት በማክበር አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ጭምር በማድረግ ለገቢ ምንጭነት እንዲውል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

    ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንና የመስቀል በዓልን በግሸን ለማክበርም ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት ቦታ ሁሉም ሰው ተገኝቶ የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆን ጥሪ አስተልፈዋል።

    “ሁሉንም በዓላት ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ያሉት ኃላፊው በተለይም የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና የቴሌ መሠረተ ልማቶችን የማስተካከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

    በዓሉን ለማክበርም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ምዕመንና ጎብኚዎች በቦታው በመገኘት ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የትራንስፖርት ችግር እንዳይከሰትም ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

    የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፈራው በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላምና በደስታ እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

    በዓሉ ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ መስከረም 22 በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ጠቁመው አካባቢው ፍጹም ሰላማዊ በመሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሁሉ የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።፡

    ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት ቦታ በመሆኑ በየዓመቱ መስከረም 21 በድምቀት ይከበራል፡፡

    ምንጭ፦ ኢዜአ

    የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን

    Semonegna
    Keymaster

    አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመደበኛና በርቀት ትምህርት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

    አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በድኅረ ምረቃ 210 እንዲሁም በቅድመ-ምረቃ 1,850 ተማሪዎችን መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም. አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝደንት አቶ ዘሪሁን መስፍን፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብት በመጠቀም ወቅቱ የሚጠይቀውን ችግር የሚፈታላት የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋታልና ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት በመጠቀም የሀገራቸውን ችግር እንዲፈቱ አሳስበዋል።

    “ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ በሥራ ዕድሜ የሚገኝ የሠው ኃይል፣ አኩሪ ታሪክና ባህል ያላት ውብ ሀገር ናት፤ እነዚህን ገፀ በረከቶች ወደ ውጤት በመቀየር የሀገራችን ሕዝቦች ካሉባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች መታደግ ወቅቱ የሚጠይቀው የተማሩ ዜጎች የዕለት ተዕለት ተግባር እንደሚሆን ይጠበቃል፤ በመሆኑም በቀጣይ እናንተ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጃችን በዛሬው ዕለት ትምህርታችሁን በሚገባ ተከታትላችሁ ያጠናቀቃችሁ የዕለቱ ተመራቂዎቻችን ያገኛችሁትን ዕውቀትና ክህሎት በምትሠማሩበት የሥራ መስክ በአግባቡና ኃላፊነት በተሞላበት ጭምር ለሀገራችሁና ለሕዝቦቿ እንደምታበረክቱ የፀና እምነት አለኝ” ብለዋል።

    ቀጣይ ዘመናችሁ የፍቅር፣ የመከባበርና የአንድነት ጉዞ እንዲሆን በመመኘት በሄዳች ሁበት ሁሉ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጃችንን በአግባቡ በመወከል አምባሳደሮቻችን እንድትሆኑ ሲሉም አደራ አስተላልፈዋል።

    የአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የቦርድ አባል ዶክተር ብርሃኔ አስፋው በበኩላቸው ለተመራቂ ተማሪዎች በባስተላለፉት መልዕክት፥ የትምህርት ፍላጎታችሁን ለማሳካትና የሚፈለገው ርቀት ላይ ለመድረስ አሁንም አልረፈደም ሲሉ የትምህርት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

    በየጊዜው ራስን በማሳደግ ሁልጊዜ በማንበብ ለቀጣይ ከፍተኛ ትምህርት ተግታችሁ ተገኙ ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎች አሳስበዋል።

    ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዜና ሳንወጣ፥ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ናቸው።

    ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአቅም ግንባታ፣ በጋራ ፕሮጀክት ቀረጻና ትግበራ፣ በሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን፣ ጉባኤዎችን ማዘጋጀትና የምርምር ሥራዎችን በጋራ መሥራት የሚያስላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

    ከተመሠረተ 80ኛ ዓመቱን የያዘው ኢዜአ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ” ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስገንብቶ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ስቲዲዮ ሥራ ለማስጀመር እየሠራ መሆኑን አቶ ሰይፈ ገልጸዋል። የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ ሥራ ለማስገባት የድርጊት ማስፈጸሚያ እቅድ መፈረሙን አመልክተዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደ ፊት ለማራመድ የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት መሆኑንና ኢዜአ ይሄን ሥራ በሙያው ማገዝና መደገፍ አለበት ብለዋል።

    ተቋማቱ በተለይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ጭምር በውድድር ተቀብሎ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ እየሠራ ያለውን ሥራ ለማስተዋወቅ በጋራ ይሠራሉ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው።

    ኢዜአ በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ግብ አስቀምጦ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአቅም ግንባታ፣ በጋራ ፕሮጀክት ቀረጻና ትግበራ፣ በሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን፣ ኮንፈረንሶች ለማዘጋጀትና የምርምር ሥራዎችን በጋራ መሥራት የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።

    የመግባቢያ ሰነዱን ወደ ተግባር ለመቀየር ኢዜአ ከዩንቨርስቲው የኢንፎርሜሽን፣ ኮምዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ቡድን ጋር ፕሮጀክት በመቅረጽ በጋራ መሥራት መጀመሩን ጠቁመዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

    አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይዟቸው የመጡ አዳዲስ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

    የትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ፣ በ2015 ዓ.ም ትምህርት አጀማመር እና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥቷል።

    በያዝነው 2015 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አጣምሮ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ዛፉ አብርሃ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል።

    መስከርም 6 ቀን 2015 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ዛፉ፥ ከዚህ በፊት የነበረው ሥርዓተ ትምህርት የነበሩበት ክፍተቶች በጥናት የተለየ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።

    በመሆኑም አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሀገር በቀል እውቀትን፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን፣ እንዲሁም ተግባር ተኮር ትምህርትን ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አቀናጅቶ ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ በመሆኑ በእውቀትና ከህሎት የታነጸ ትውልድ ከመገንባት አንጻር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

    በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የአደረጃጀት ለውጥ የተደረገ ሲሆን፥ በዚህም 6፣2፣2፣2 የነበረው አደረጃጀት ቅድመ መደበኛ 2 ዓመት፣ አንደኛ ደረጃ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል (6 ዓመት)፣ መካከለኛ ደረጃ 7 እና 8ኛ ክፍል (2 ዓመት)፣ እንዲሁም 2ኛ ደረጃ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል (4 ዓመት) /2፣6፣2፣4/ እንዲሆን ተደርጓል።

    በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ከፍል አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ደግሞ የሙከራ ትግበራ በተመረጡ 80 ትምህርት ቤቶች የሚካሄድ መሆኑን ወ/ሮ ዛፉ ገልፀዋል።

    በሌላ በኩል የትምህርት ፕሮግራሞች ጥራትና ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሃንስ ወጋሶ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መስከረም 9 /2015 ዓም ተከፍተው የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

    በልዩ ልዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ሰኞ መስከረም 9 ቀን፥ 2015 ዓ.ም ትምህርት የማይጀምሩ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀምሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

    የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አመለወርቅ ህዝቅኤል በበኩላቸው ሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ሕብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

    አምስት ዓመታትን በፈጀውና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ክለሳ የያዛቸው አዳዲስ ነገሮች

    • አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ባሉ የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚተገበር ቢሆንም፤ ኢንተርናሽናልና የማህበረሰብ አቀፍ ትምህርትቤቶችን አያካትትም፤
    • በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብ፣ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት ተደርጎባቸው እንዲሰጡ ይሆናሉ፤
    • ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ላሉ የክፍል ደረጃዎች ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ይሰጣል፤
    • ከሰባተኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት ደግሞ ሁሉም ተማሪ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ይማራል፤
    • ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉት ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይወስዳሉ፤
    • ሦስተኛ ክፍል ላይ ተጨማሪ ቋንቋዎችን መስጠት ይጀመራል፤ በክልሎቹ ውስጥ በስፋት የሚነገረውን ተጨማሪ ቋንቋ በመምረጥ ተማሪዎቹ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲወስዱት ይደረጋል፤
    • በቀድመው የትምህርት ሥርዓት 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ሀገራዊ የመልቀቂያ ፈተና ይቀርና በምትኩ አጠቃላይ ፈተናው በክልል ደረጃ ስድስተኛ ክፍል እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ይሰጣል፤
    • ከዚህ ቀደም ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የዩኒሸርስቲ ቆይታ ደግሞ ዝቅተኛዉ አራት ዓመት ይደረጋል፤
    • ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ከሚሠጡ ትምህርቶች ውስጥ እንደ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሺዮሎጂ እና ሥነ-ምግባር የመሳሰሉት ይካተታሉ፤
    • ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የግብረገብ ትምህርት ይሰጣል፤ በተጨማሪም የማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ (social and natural sciences) ውህድ የሆነ ትምህርት ይሰጣል፤
    • ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል በተናጠል ይሰጡ የነበሩት ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና ባይሎጂ አጠቃላይ ትምህርት ወይም ጀነራል ሳይንስ (general science) ተብለው እንዲሁም ጆግራፊና ታሪክም ተቀናጅተው የሚሰጡ ይሆናል፤
    • የሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የእርሻ ትምህርት፣ አካውንቲንግ፣ ቢዝነስ እና ጀነራል የሆነውን የሥራና ክህሎት ትምህርት በሙያ ትምህርት ተካቶላቸው የሚሰጣቸው ይሆናል፤
    • 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ላይ ደግሞ ጤና፣ ግብርና፣ የእርሻ ትምህርት፣ ማኒፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ቢዝነስ፣ አካውንቲንግ የመሳሰሉት የሙያ ትምህርትነቶችን እንዲማሩ ይደረጋል፤
    • የዘጠነኛ እና የ10ኛ ክፍልን እንዲሁም ከአንድ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ የተመረጡ አምስት የትምህርት ዓይነቶችን መጽሐፍት ዝግጅት ትምህርት ሚኒስቴር ያከናውነዋል፤
    • ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት መጽሐፍት ክልሎች በራሳቸው ባህልና አካባቢያዊ ሁኔታ ቃኝተው ያዘጋጁታል።

    ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር/ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት

    Semonegna
    Keymaster

    የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ (tax incentive) ተግባራዊ ተደረገ

    አዲስ አበባ (የገንዘብ ሚኒስቴር) – የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን እና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር መስከረም 6 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. አስታውቋል።

    በዚህም የታክስ ማሻሻያ (tax incentive) ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከተጨማሪ እሴት ታክስ / ቫት/ (value added tax /VAT/)፣ ከኤክሳይዝ ታክስ (excise tax) እና ከሰር ታክስ (surtax) ነፃ እንደሚደረጉም ታውቋል።

    የታክስ ማሻሻያው ዓላማ በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደኅንነት ጋር የሚስማማ (environmentally friendly) ለማድረግ፣ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝኃ ህይወት (climate and biodiversity) ላይ ተጽዕኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን፥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻልም ነው።

    በታክስ ማሻሻያው መሠረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

    በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም 5 በመቶ (5%) የጉምሩክ ቀረጥ (custom duty) ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

    ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ (15%) የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ የመለክታል።

    ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሽከርካሪና የተሽከርካሪ ባለቤቶችን ቁጥር ለመጨመር መንግሥት ተሽከርካሪ በማምርት ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን ከመሳብና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ታክስ ላይ ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

    መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ ተሽከርካሪዎች ካሏቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፥ የእ.ኤ.አ 2019 ዓ.ም መረጃ እንደሚያሳየው፥ በአማካይ ሁለት መኪኖች ለአንድ ሺህ ሰዎች (2 cars to 1000 people) ነው።  በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተሽከርካሪዎቾ ቁጥር 600,000 አካባቢ ሲሆን፥፥ ከእነዚህ ውስጥ 84 በመቶ (84%) የሚሆኑት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ናቸው። አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎችም ከውጭ ሀገር ሲገቡ ያገለገሉ (secondhand) ሲሆኑ፥ አብዛኛዎቹም የሚመጡት ከገልፍ (Gulf) ሃገራት ከፍተኛ ቀረጥ (ታክስ) ተከፍሎባቸው ነው ሲል ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።

    የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ

    Semonegna
    Keymaster

    ጥቁር ገበያ ላይ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ ደርሷል

    አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቁር ገበያ ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

    ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ እንቅስቃሴ ነው ያለው ብሄራዊ ባንክ ዝውውሩ የሚከናወንባቸውን የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ባላገሩ ቴሌቭዥን ዘግቧል።

    ከብር አንፃር የዶላር ዋጋ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ መደበኛ ባልሆነው የሃዋላ ምንዛሬ (ጥቁር ገበያ) ባለፉት ጥቂት ቀናት ዶላር ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱን የባላገሩ ዘጋቢ ባደረገው ቅኝት ተረድቷል።

    ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አንድ ዶላር ጥቁር ገበያ ላይ ከ85 እስከ 87 ብር ድረስ በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ ዋጋ እስከ 92 ብር ድረስ ከፍ እንደሚል ባላገሩ ቴሌቪዥን ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ ከሚገኙት የጥቁር ገበያ መንዛሪዎች መረዳት ችሏል፡፡

    በመደበኛው የምንዛሬ ገበያ አንድ ዶላር በ53 ብር አከባቢ እየተመነዘረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ ያሳያል። በአሁኑ ጊዜ በጥቁር ገበያ እና መደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከ26 ብር በላይ ሆኗል።

    የዶላር ዋጋ መጨመሩ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ዋጋ ንረት ላይ የራሱን የሆነ ጫና የሚያሳድር መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ ያነሳሉ፡፡ የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያ ላይ በዚህ ያህል መናር የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ንግድ አለመመጣጠን መሠረታዊ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር አጥላው ገልጸዋል፡፡

    ሀገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሏ ነጋዴው ማኅበረሰብ በቂ ዶላር በባንክ ቤቶች በኩል ማግኘት አለመቻሉን ዶ/ር አጥላው አንስተዋል፡፡ በዚህም ምርት ከውጭ የሚያስገቡ ነጋዴዎች የጥቁር ገበያውን እንደ ዋና የውጭ ምንዛሬ ምንጭነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን እንዳሳደገው አብራርተዋል፡፡

    የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር በዋናነት የባንኮችን የዶላር ክምችት ማሳደግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ያነሱ ሲሆን፤ ለዚህም ምርትን በማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

    በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ከሰሞኑ ሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በተለይም ጥቁር ገበያ ላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

    ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን ጦርነት ተከትሎ የዓለም ምርት ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት መጨመሩንና ይህን ተከትሎ በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ እድገት ማሳየቱን ምክትል ገዥው አብራርተዋል፡፡

    በዓለም ገበያ ላይ የዩሮ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ በተቃራኒው የአሜሪካ ዶላር ፍላጎቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

    ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ ባንኩ የዚህ እንቅስቃሴ ማካሄጃ የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤ በቅርቡም በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ሲሳተፉ በተገኙ የሒሳብ ቁጥሮች ላይ እርምጀ እንደሚወሰድ ጨምረው አንስተዋል፡፡

    በመደበኛ የዶላር ምንዛሬ ገበያውም ላይም ቢሆን ባለፉት ስድስት ወራት በአንድ ዶላር የምንዛሬ ዋጋ ላይ የ2 ብር ከ60 ሳንቲም ጭማሪ እንደተደረገበት ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

    ምንጭ፦ ባላገሩ ቴሌቭዥን

    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት በጋራ ለመመከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን ከሕዝባቸው ጎን በቆራጥነት በመቆም የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ይህ የህልውና ጦርነት በውጭ ሀገር የምንገኘውን ኢትዮጵያውያን እንቅልፍ የነሳና ሀገራችን እንደ ሀገር እንዳትቀጥል በወያኔ ጁንታ ቡድን፣ በአልሸባብ፣ እና በሸኔ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በቅንጅት የከፈቱብን ጦርነት ብሔራዊ ክብራችንና የሚነካ የሀገራችንን ሰላም የሚያውክ በመሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል።

    ስለዚህ መንግሥት በሆደ ሰፊነት ቀደም ሲል የወሰዳቸውን ቁርጠኛ የሰላም ፍላጎቶቹን በማድነቅ የሰላም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ሙሉ ድጋፍ ስንሰጥ መቆየታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀቱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከሰላም ይልቅ ጦርነትንና እልቂትን መርጠው የከፈቱብንን የአጥፍቶ መጥፋት ጦርነትን በጥብቅ አውግዘን መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የአሸባሪውን ጁንታ ቡድን እንዲሁም አልሸባብና ሸኔን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሕልውናና ለሕዝባችን ሰላምና ጥቅም ስንል ከመንግሥትና እንዲሁም ከመከለከያ ሠራዊታች ጎን በመቆም የዜግነት ድርሻችንን ለመወጣት የትግባር ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።

    በእርግጥ ዲያስፖራው ዛሬም ነገም ለሀገሩ ለወገኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ቢሆንም በሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው ሀገር የማዳን ዘመቻ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ እምነት ሳንከፋፈል ከስሜታዊነትና ከኩሪፊያ በመውጣት ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ነገር ለማምጣት፣ የተሻለችውን ኢትዮጵያ ለማየት ትግሉን የሚጠይቀውን ማንኛውንም ድጋፉ እንድናደርግ ምክር ቤታችን በድጋሚ በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ጥሪ ያቀርባል።

    መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን፣ ውስጣዊ ችግሮቻችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት ግጭቶችና የጦርነትን ውድመት እንዳይቀጥል በቁርጠኝነት ተነሳስቶ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መሠረት ለመጣል ፖለቲካዊ ችግሮችን በአግባቡ ፈትሾ ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድርድር ማድረግ፤ በሀገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ቡድኖች ወደ ዘላቂ ሰላም የጠረንጴዛ ድርድር እንዲቀመጡ ወስዶት የነበረውን የሰላም ጥረት አሁንም ወደፊትም እንዲቀጥል ምክር ቤታችን መደገፉን ይቀጥላል።

    ነገር ግን ከጦርነት በተሻለ ሰላምን መምረጥ ትርፋማነቱ ቢያዋጣም አሸባሪውና ጎጠኛው የጁንታው ቡድን የአማራና አፋርን ሕዝብ በመውረር የትግራይን ሕዝብ አግተው በሰላማዊ ሕዝብና በመሠረተዊ የልማት ተቋማት ላይ ያደረሱትን መጠነ ሰፊ ውድመት መልሰን ለማቋቋም እርብርብ በምናደርግበት ወቅት የሀገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ለሦስተኛ ዙር የተከፈተብን ታሪክ ይቅር የማይለው ጦርነት በእጅጉ አስቆጥቶናል። ስለዚህ፦

    1ኛ የአማራና የአፋር ክልልን በመውረር ሲዋጉና አመራር ሲሰጡ የነበሩትን እንዲሁም እድሚያቸው ለውትድርና ሞያ ያልደረሱ የትግራይ ህፃናትን በመመልመል ለጦርነት ያሰልፉትን የወያኔ ጁንታ አመራሮች ተለይተው በጦር ወንጀለኝነትና በሀገር ክህደት ክስ ተመሥርቶባቸው በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥትን እንጠይቃለን።

    2ኛ ሀገራችን በገጠማት የሰላም ማጣት ችግርና ተገዳ ከገባችበት የህልውና ጦርነት በተጨማሪ የሕዝብ ሞትና የሥነ ልቦና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የሐሀት ቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በሚያደርጉ ቅጥረኛ ሚዲያዎች፣ አለአግባብ ለመበልፀግ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈፅሙ ነጋዴዎች፣ በተለይ የመንግሥት ሙሰኞችና ሌቦች ላይ ያለምንምንም ይቅርታ ጠንካራ እርምጃ መንግሥት እንዲወስድ እናሳስባለን።

    3ኛ መንግሥት የሚቻለው ሁሉ ጥረት በማድረግ ለሀገር ጠቀሜታ ሲል ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ አካሄዶችና አዳዲስ ስልቶችን (strategies) መንደፍ አለበት። በተለይ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ የሚያውኩትን የሚዲያ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለድፕሎማቶቹን ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጥና ለተግባራዊነቱም ልዩ ክትትል እንዲያደርግ በጥብቅ እናሳስባለን።

    በመጨረሻም ምክር ቤቱ ወደፊት ከሚያደርጋቸው የድጅታል ዲፕሎማሲ ትግል በተጨማሪ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ በሚደረገው የህልውና ጦርነት የዘማቹ ሠራዊት ደጀን በመሆን ጠንካራ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እናረጋግጣለን።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት (ኢዳተም)

    Semonegna
    Keymaster

    ሳንቴ የሕክምና ኮሌጅ ለ5ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የጤና ባለሙያዎች አስመረቀ

    አዲስ አበባ (የጤና ሚኒስቴር) – ሳንቴ የሕክምና ኮሌጅ በአጠቃላይ ሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ፣ በጥርስ ሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ፣ በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በBSc እና MPH ዲግሪ፣ በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ፣ ኒውትሪሽን በMPH ዲግሪ እና በሥነ-ተዋልዶ ጤና በMPH ዲግሪ ያሰለጠናቸውን የጤና ባለሙያዎች አስመረቀ።

    በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተግንኝተዉ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ እንዳሉት፥ ተመራቂዎች በኮሌጁ ቆይታችሁ ፈታኙን የሕክምናና የጤና ሳይንስ ትምህርት እንዲሁም ሌሎች ተግዳሮቶችን አልፉችሁ ነውና የእናንተን የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ ያረጋገጣችሁበት ስለሆነ ላደረጋችሁት ጥረት፣ ውጤታማነት ምስጋናና አድናቆት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

    ዶ/ር አየለ አያይዘውም የተመራቂ ቤተሰቦችንና የኮሌጁ መምህራን እንዲሁም አመራር/አስተዳደር አባላት ተማሪዎች በስኬት መንገድ እንዲጓዙና ውጤታማ እንዲሆኑ ለከፈላችሁት ዋጋ የሚያስመሰግናቸውና የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ገልፀው፤ በዛሬው ጊዜ ልጆችን በኃላፊነት አንፆ ለፍሬ ማብቃትና ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ የወላጅ፣ መምህራን እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጥረት እንደሚያስፈልግ አንስተው፣ ለትውልድ ቅብብሎሹ ላደረጉት መስዋዕትነት ሀገርም እንደምታመሰግናቸው ተናግረው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዘርፉ የሚስተዋለውን የጤና ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከከፍተንኛ ትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የጤናና የሕክምና ትምህርት የሚሰጡ በርካታ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።

    የኮሌጁ ተጠባባቂ ዲን ዶ/ር አህመዲን ኑርሁሴን በበኩላቸው፥ የኮሌጁ ዓላማ ከኮሌጁ ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎች ሰውን ወዳድ እና አክባሪ፣ አዋቂ፣ በተለያዩ ክህሎቶች የታነፁ፣ ብቁ ለህሙማንና ለማኅበረሰቡ ተቆርቋሪና በጎ አመለካከት ያላቸው ጠቅላላ ሀኪሞች፣ የጥርስ ሀኪሞች፣ ጤና መኮንኖች፣ የሜዲካል ላብራቶሪ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ (ፐብሊክ ሔልዝ)፣ ሥነ ምግብ (ኒውትሪሽን) እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሆነ ገልፀው፥ ተመራቂዎች ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ ትውልድ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመው ለ5ኛው ዙር ተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሌጁ የቦርድ አባል በተጨማሪ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተመራቂዎች የተማራችሁት የትምህርት ዓይነት ስለ ሰው ነው፤ ሰው ደግሞ ክቡር የሆነ ህይወትን የተላበሰ ልዩ የሆነ የእርሱ ፍጡር እንደሆነ አንስተው፤ ተመራቂዎች በተማራችሁበት ትምህርት ማኅበረሰቡን ለመርዳትና ሀገራችንን በሕክምናው ዘርፍ የላቀ ደረጃ ለማድረስ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድትወጡ በማለት ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው መልካም የምርቃ ጊዜ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

    ምንጭ፦ የጤና ሚኒስቴር

    Semonegna
    Keymaster

    ከ350 በሚበልጡ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን
    የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በ2014 በጀት ዓመት የሥነ-ሥርዓት ጥሰት በፈጸሙ ከ350 በላይ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ ከአረጋገጣቸው 10 ሺህ የትምህርት ማስረጃዎች 505 ቱ ሀሰተኛ ናቸው ብሏል።

    የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር ዶ/ር አንዷለም አድማሴ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በ2014 በጀት ዓመት ከየትኛውም በጀት ዓመት የበለጠ የትምህርት ጥራትን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን የማጽዳት ሥራ ተከናውኗል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ገምግሞ አቅጣጫ ካስቀመጠ ጊዜ ጀምሮ ከ350 በላይ በሚሆኑ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ወስዷል።

    መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየወሰዳቸው ካሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ውስጥ ሕገ-ወጥ የትምህርት ተቋማትን መቆጣጠር አንዱ ተግባር ነው ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ አሁን ላይ የትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ትርፍን ብቻ አላማ ያደረጉ ሕገ ወጥ የግል የትምህርት ተቋማት መስፋፋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

    ተቋምና ፕሮግራም መዝጋት አማራጭ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጣቸው በትውልድ ህይወት የሚነግዱ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

    እንደ ዶ/ር አንዷለም ገለጻ፥ በርካታ ዜጎች እውቅና በሌለው የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገንዘባቸውን ከፍለው ከተማሩ በኋላ ባለስልጣኑ ማረጋገጫ ሲሠራላቸው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሆንባቸው ለተመሰቃቀለ ህይወት እየተዳረጉ ነው። በተቋማት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ በ355 የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ከፕሮግራም መዝጋት እስከ ተቋሙን ሙሉ በሙሉ እስከ መዝጋት የደረሰ የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል። ለዚህም መገናኛ ብዙኃን የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

    የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ሥራ በበጀት ዓመቱ በትኩረት ከተሠራባቸው መካከል መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር አንዷለም፤ በዘርፉ የጤና ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን ለሚቀጥሯቸው ሠራተኞች ቅጥር ከመፈጸማቸው በፊት የትምህርት ማስረጃቸው በባለስልጣኑ እንዲረጋገጥ የሚያደርጉበት አግባብ ለሕገ-ወጥ የትምህርት ማስረጃ ቁጥጥር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። ዕድገትና ቅጥር ሲያከናውኑም በሙሉ ሳያስፈትሹ እንደማያከናውኑ ተናግረዋል።

    ዋና ዳይሬክተሩ የትምህርት ማስረጃ ሲረጋገጥ በቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች ተገደው የሚመጡ አካላትን የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥና ከውጭ ሀገር የተገኘ የትምህርት ማስረጃን አቻ ግምት በመስጠት በሁለት መልኩ የሚረጋገጥ ነው ብለዋል። የማረጋገጥ ሥራ የሚጀምረው ከሀገር አቀፍ ፈተናዎች እንደሆነና በወቅቱ ከነበረው የመቁረጫ ነጥብ በመጀመር እያንዳንዱ የትምህርት ማስረጃ ተፈትሾ እስከ ዲፕሎማና ዲግሪ እንደሚረጋገጥም ጠቁመዋል።

    በ2014 በጀት ዓመት የጤና ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽንን ሳያካትት ተገደው ከመጡ ከ10 ሺ በላይ የትምህርት ማስረጃዎችን ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ ከተረጋገጡት የትምህርት ማስረጃዎች 505 የሚሆኑት ትክክለኛ ያልሆኑ የትምህርት ማስረጃዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።

    ፈቃድ ሳያገኙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዱ ያሉ ትውልድን እያቀጨጩ የሚገኙ ሕገ-ወጥ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደት ሕብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርግም ዶ/ር አንዷለም ጥሪ አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    በሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያገኛሉ

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት አስታወቀ።

    የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዲጅታል መታወቂያ የሕግ አግባብነት፣ ዓላማና አዋጅ ጋር በተያያዘ ውይይት አድርጓል።

    የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ግንኙነት መሪ ሚና አወል፤ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ አንድን ሰው ማንነት በእርግጠኝነት መለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። መታወቂያው ዕድሜ፣ ፆታ፣ የአስር ጣቶች አሻራ፣ የመኖሪያ አድራሻና ሌሎች ገላጭ መረጃዎችን የሚይዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

    በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮችና በገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዴት መመዝገብ ይችላሉ የሚለውን ለማወቅ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች 125 ሺህ ዜጎች በሙከራ ደረጃ ተመዝግበው ውጤታማነቱ ተረጋግጧል ብለዋል። በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚኖሩ 12 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ለዚህም በንግድ ባንክ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና መሰል አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ በቀላሉ መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል።

    የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል፥ ዲጅታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ ነው። ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ በኪስ የሚያዝ ወረቀት ሳይሆን የራሱ መለያ /ፋይዳ/ የሚባል ቁጥር ብቻ ይዞ በማንኛውም ቦታ በቁጥሩ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዘመናዊ አሠራር መሆኑንም አስረድተዋል። ከቤቱ ሆኖ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማግኘትና በአገልግሎት ሰጭውና ተቀባዩ ዘንድ መተማመን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

    በዚህም እስከ 2018 ዓ.ም ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዕቅድ መያዙን አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል። የፎቶ ኮፒና ሌሎች የህትመት ሥራዎች ሁሉ የንግዱ ማኅበረሰብ በየሱቆቹ ማስመዝገብ የሚችልበትን አሠራር እንዘረጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

    የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ለጤናው ዘርፍ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ባለመኖሩ ምክንያት ዲጅታል የጤና መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያው ሥራ መጀመር በመላ ሀገሪቱ ያሉ ከ40 ሚሊየን በላይ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መታወቂያቸውን በቀላሉ አድሰው የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል። የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ትብብር እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል። ዘገባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ነው።

    የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ

    Semonegna
    Keymaster

    አዋሽ ባንክ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
    አዋሽ ባንክ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የብር 5 ሚሊየን ድጋፍ አደረገ
    አቶ ሰለሞን ሶካ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

    አዋሽ ባንክ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ሐምሌ 26 ቀን፥ 2014 ዓ.ም በጋራ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እና የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ፈርመውታል።

    በስምምነቱ መሠረት ኢመደአ የሀገሪቱን የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ ለሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ ሥራዎች የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ በአዋሽ ባንክ የሚደረግ ሲሆን፤ በሌላም በኩል የባንኩን የኢንፎርሜሽንና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍና እገዛ በኢመደአ በኩል እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

    የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ኢመደአ የፋይናንስ ሴክተሩን ጨምሮ ቁልፍ የሀገራችንን ተቋማት የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚሠራቸው ሥራዎች ከፍተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ ለኢመደአ መደረጉን ጠቅሰዋል። በቀጣይም የሁለቱ ተቋማት የትብብርና የቅንጅት ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

    የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው፥ ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚቻለው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ሲቻል መሆኑን በማስታወስ፥ ኢመደአ የሀገራችንን የሳይበር ደኅንነት የማስጠበቅ ዋና ተልዕኮውን ለማሳካት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ይሠራል ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ከአዋሽ ባንክ ጋር የተደረገው የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማም የአስተዳደሩ የትብብርና የቅንጅት ሥራ አንዱ አካል እንደሆነ መግለጻቸን አዋሽ ባንክ በሰጠው መግለጫ ላይ አስፍሯል።

    ከአዋሽ ባንክ ሳንወጣ፥ ባንኩ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
    የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ጸጋዬ ማሞ እንደገለጹት፥ የክልሉ መንግሥት ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የአጋሮችን ድጋፍ በመጠየቅ ሃብት የማሰባሰብ ሥራ መሠራቱን የገለፁ ሲሆን፤ አዋሽ ባንክ ላደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግሥት ስም በማመስገን በክልሉ ባንኩ ለሚሠራቸው ሥራዎች የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

    የአዋሽ ባንክ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ዋና ዳይሬክተር አቶ ይርጋ ይገዙ በበኩላቸው፥ የአዋሽ ባንክ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ክልላዊና ሀገራዊ ጥሪዎችን በመቀበል ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ለመነሻ የሚሆን የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

    በሌላ ዜና ደግሞ፥ አቶ ሰለሞን ሶካ ከሐምሌ 27 ቀን፥ 2014 ዓ.ም ጀምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር በመሆን በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) መሾማቸውን ተቋሙ ዘግቧል።

    አቶ ሰለሞን ሶካ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን ከመሠረቱት ቀደምት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ከቴክኒካል ባለሙያነት ጀምሮ እስከ ምክትል ዳይሬክተርነት ለ10 ዓመታት ያክል ተቋሙን አገልግለዋል። በ2008 ዓ.ም ተቋሙን ከለቀቁ በኋላም “ቴክ ማሂንድራ” (Tech Mahindra) በተባለ የህንድ የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎት እና አማካሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለስድስት ዓመታት ሠርተዋል።

    አቶ ሰለሞን ሶካ “ቴክ ማሂንድራ” ውስጥ ከ6 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ኢመደአ በመመለስ ከኅዳር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው ከሐምሌ 27 ቀን፥ 2014 ዓ.ም ጀምሮ  የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾመዋል ።

    አቶ ሰለሞን ሶካ ከማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ (Microlink Information Technology College) በሶፍትዌር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ የማስተርስ ዲግሪያቸው ደግሞ ከቻይና ኤሌክትሮኒክ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (University of Electronic Science and Technology of China – UESTC) በኮምፒውተር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አግኝተዋል።

    የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ የደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንን ወክለው ተወዳድረው በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን የምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።

    Semonegna
    Keymaster

    “በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው!!”
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሀገራችን ላይ እውን እንዲሆኑ ከሚታገልላቸው የፖለቲካ መሠረቶች አንዱ እና ዋነኛው የዜጎች እውነተኛ የስልጣን ባለቤትነትንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው!!

    ፌደራሊዝም “የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ሕዝብ ነው” የሚለውን ትልቅ የዴሞክራሲ መርህ ሰፋ ያለ ትርጉም በመስጠት፥ “ሕዝብ በሚኖርበት አከባቢ ራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት” የሚለውን መርህ ተግባራዊ የሚያደርግ የአስተዳደር መዋቅር ነው።

    ፓርቲያችን ኢዜማ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ ከአንድ ቦታ ሁሉን ማስተዳደር የማይመች መልከአ ምድር፣ በተለያየ ደረጃ ያለ ኢኮኖሚ በየአካባቢው ባለበት፣ ብዝኀ ማንነት ማለትም ብዙ ዘውግ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት አንፃር ያልተማከለ ሥርዓት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። ካልተማከሉ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ደግሞ የመጀመርያው ምርጫ ፌደራሊዝም ነው።

    እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ፌደራሊዝም ተመራጭ የሚሆነው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው። አንደኛው ሕዝብ በአካባቢው ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል ሙሉ መብትና ስልጣን የሚሰጥ የመንግሥት ሥርዓት ስለሆነ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ፌደራሊዝም ከአሐዳዊ መንግሥት በተሻለ ብዝኀነትን ማስተናገድ መቻሉ ነው።

    ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት የተከተለችው የፌደራሊዝም ሥርዓት፤ ፌደራል ሥርዓቱን የፈጠረው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ በነበሩ ሂደቶች ብዙኃኑን ያላሣተፈ መሆኑ ዴሞክራሲያዊነቱን አሳጥቶታል። ከዚያ በተጨማሪ የፌደራሊዝም ዋና ጥቅም ለሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመስጠትና በዘውግና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው የሚነሱ ግጭቶችን ማስወገድ ሆኖ እያለ፤ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ግን ራሱ የተመሠረተው በዘርና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ስለሆነ ማስወገድ የሚገባውን ችግር ጭራሹኑ አባብሶታል። በተለይ የፌደራል ሥርዓቱ ማንነትንና የመሬት ባለቤትነት በሕገ መንግሥት ደረጃ እንዲያያዝ በማደረጉ ከዚህ ቀደም በመካከላቸው የሚለያያቸው ወሰን ባልነበረ ኩታ ገጠም በሆኑ ወረዳዎች በሚኖሩ የዘውግ ማኅበረሰቦች መካከል ደም ያፋሰሱ በርካታ ግጭቶች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል። አሁንም መሆኑን ቀጥሏል።

    በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው ብሎ ያምናል።

    ይህንን አደጋ ለማስወገድ የፌደራል ሥርዓቱ እንዴት መመሥረት አለበት? ክልሎች እንዴት መዋቀር አለባቸው? በክልሎችና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? የሚሉና ከፌደራል መንግሥትና ከክልል መንግሥታት ማን የበለጠ ስልጣን ይኑረው? ለሚሉት ጥያቄዎች እና ሌሎች ሀገሪቱን አደጋ ላይ ጥለዋታል የሚባሉ የሕገ መንግሥቱ ክፍሎችን አንድ በአንድ ነቅሶ በማውጣት ከፊታችን ሀገራችን ታደርገዋለች ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ማቅረብ የግዴታ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

    ኢዜማ ለዚህ ምክክር ጠንካራ አማራጭ ሀሣቦችን ይዞ ለመቅረብ ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ብቻ ትኩረትን ሰጥቶ የሚሠራ ኮሚቴ በማዋቀር እየሠራ ሲሆን ዝግጅቱንም አጠናቆ የመድረኩን መጀመር እየተጠባበቀ ይገኛል።

    ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የ “ክልል ወይንም ዞን እንሁን” የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት እየተደመጡ ነው። ይህንንም ተከትሎ ሁለት ሕዝበ-ውሳኔዎች ተደርገው ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ ከነበሩት ዘጠኝ ክልሎች ሁለት ተጨምረው የክልሎች ቁጥር ወደ 11 ከፍ ብሏል።

    አንዳንዶቹ የክልልነት ጥያቄዎች የሚቀርቡት ሕዝብ በወከላቸው እንደራሴዎች ሳይሆን ስልጣን ላይ ባሉ አካላት የግል የፖለቲካ እና ሌሎች ጥቅሞችን የማግበስበስ ፍላጎት መነሻነት መሆኑን ፓርቲያችን በተደጋጋሚ ገልጾ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ጥሪ አስተላልፏል። አሁንም በዚህ ተግባር የተጠመዱ ስልጣን ላይ ያሉ አካላት ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

    ማኅበረሰቡም ለእነዚህ ጥቅመኛ ግለሰቦች የግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣርያ ከመሆን ይልቅ ከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ጀምሮ ያጋጠሙትን አስተዳደራዊ በደሎች ለመፍታት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ በሚታመነው የአካባቢ፣ የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ በንቃት በመሣተፍ በአግባቡ ሊያስተዳድሩት የሚችሉ ግለሰቦችን እንዲመርጥ ጥሪ እያስተላለፍን፤ የሀገራዊ ምክክሩንም ሂደት በተመሣሣይ እንዲሁ በአንክሮ እንዲከታተል እንጠይቃለን።

    ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የፌደራል ሥርዓቱ ያሉበት እንከኖች ሳያንስ ያለ ሕዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ እንዲሁም አማራጭ ሐሣቦችን ሣይመለከት “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስትን በክላስተር ለማዋቀር” ብቸኛው አማራጭ አድርጎ ይዞ መምጣቱ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን እና ሀገራዊ ምክክሩ ላይ አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል ተብለው ከሚታመንባቸው አንዱ የሆነውን የፌደራል አወቃቀር ከወዲሁ በመነካካት ሀገራዊ ምክክሩ ላይ እምነት እንድናጣ ከማድረግ ሊቆጠብ ይገባል።

    ኢዜማ ፌደራሊዝም ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝቡ ራሱን ለማስተዳደር መፈለጉ በራሱ ችግር አለመሆኑን ይገነዘባል፡፡

    የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው ማኅበረሰቦች ምንም እንኳ አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47(2) መሠረት ጥያቄዎችን የማንሳት ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢኖራቸውም፤ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ከዘውግ ይልቅ ዜግነትን መሠረት ያደረገ እና ሁሉንም ማህበረሰብ ባቀፈ መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ኢዜማ ማስገንዘብ ይወዳል፡፡ ይህም ለጋራ የወደፊት ዘላቂ ሰላም እና ልማታችን  ቁልፍ መሆኑን ያምናል፡፡

    ኢዜማ በአራቱም አቅጣጫ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚጠቅመው በጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የህዝብን ከታች እስከ ላይ ባሉ መዋቅሮች ራስን በቀጥታ የማስተዳደር መብት የሚያጎናጽፈው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም መሆኑን ያምናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ከፍተኛ በጀት ፈሰስ ተደርጎበት በአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተጠናው የአስተዳደር ክልሎች እንዴት ይዋቀሩ የሚለው የጥናት ውጤት ለሀገራዊ ምክክሩ እንደ ግብአት ሆኖ እንዲቀርብ እንጠይቃለን።

    የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው አካላት ቀጣይ ሀገራችን ታካሂደዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ተነስተው መፍትሄ ያገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ ጉዳዮች ላይ ከወዲሁ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ማድረግ ምክክሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን ተረድተው ከጊዚያዊ አካባቢያዊ ጥቅም ይልቅ የትልቋን ኢትዮጵያ ምስል በማየት ለነገ የጋራ ጥቅማችን አስቦ አጀንዳውን በማሳደር፤ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በሰከነ እና የሀገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ በተረዳ መልኩ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ሀሳቦችን ከመመዘን እስከ ሕዝባዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

    ሀምሌ 28 ቀን፥ 2014 ዓ.ም
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    ኢዜማ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 890.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ
    በሲቢኢ ኑር አገልግሎት ተጨማሪ 17.5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ተሰበሰበ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 (2021/22) በጀት ዓመት 154.9 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘቡን 890.1 ቢሊዮን ብር ማድረሱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስታውቀዋል።

    የ2014 (2021/22) በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን ከሐምሌ 21 እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲሱ የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ያካሄደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአጠቃላይ ከዕቅድ በላይ ወይም ተቀራራቢ አፈጻጸም ያስመዘገበበት ዓመት መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት ካቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

    ባንኩ በበጀት ዓመቱ 27.5 ቢሊየን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፤ ይህም ከዕቅዱ 16.3 በመቶ፣ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ43.9 በመቶ ብልጫ እንደሚያሳይ አቶ አቤ ገልጸዋል።

    ባንኩ 179.2 ቢሊዮን ብር ብድር ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መስጠቱን ያስረዱት አቶ አቤ፥ 120.6 ቢሊዮን ብርም ከተሰጡ ብድሮች መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።

    የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተ፥ ከተለያዩ ዘርፎች 2.6 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ በመንግስት ትኩረት ለተሰጣቸው ለተለያዩ የገቢ እቃዎች እና ለሌሎችም 7.7 ቢሊዮን ዶላር ባንኩ መክፈሉንም ነው አቶ አቤ የገለጹት።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሀብት 1.2 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም አቶ አቤ ካቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

    የባንኩን አገልግሎት ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ 124 አዳዲስ ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሲሆን፤ የባንኩ አጠቃላይ የቅርንጫፍ ብዛትም 1824 ደርሷል።

    የደንበኞችን በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት በማሳደግ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ ባንኩ በሚያደርገው ጥረት በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ የሒሳብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ 35 በመቶ የሚሆነው በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች መከናወኑን አቶ አቤ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

    በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ 2.9 ሚሊዮን አዳዲስ ሒሳቦች መከፈታቸውነ የገለጹት አቶ አቤ፥ የባንኩ አጠቃላይ የገንዘብ አስቀማጮች ብዛት 35.9 ሚሊዮን መድረሱንም ጨምረው ገልጸዋል።

    ባንኩ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ ፈተናዎች ወስጥ አልፎ አበረታች ወጤት ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሪክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ባንኩ እያካሄደ ባለው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተናግረዋል።

    ከባንኩ ጋር በተያያዘ ዜና፥ በሲቢኢ ኑር አገልግሎት (የሸሪዓ መርህን የተከተለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት) ተጨማሪ 17.5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን ባንኩ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር (CBE Noor) በተባለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 69.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን በሪፖርታቸው የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ፣የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም ከ5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አሳውቀዋል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር በሚል ስያሜ የሸሪአ መርህን ተከትሎ በሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 69.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን በሪፖርታቸው የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፥ የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም ከ5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አሳውቀዋል።

    የተገኘው ውጤት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት ባንኩ እያደረገ ያለው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ አቤ፥ ባንኩ በሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት 9.3 ቢሊዮን ብር የፋይናንሲንግ አገልግሎት መስጠቱንም ነው አክለው የገለፁት።

    ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ

Viewing 15 results - 31 through 45 (of 730 total)