Search Results for 'ኦነግ ሽኔ'

Home Forums Search Search Results for 'ኦነግ ሽኔ'

Viewing 5 results - 1 through 5 (of 5 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ለሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ካልታገለ እንደ ብልጽግና መቆም አይችልም!

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ አቋም
    ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.
    ባህር ዳር

    ስናጠፋ የሚገስጸን፣ ስናለማ የሚያግዘን ሕዝብ እንዳለን እናምናለን። በሕዝባችን ስብራት ላይ ተደማሪ ስብራት መሆን ስለማንፈልግ ከሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በመነጨ ቅን ልቦናና ፍላጎት የሕዝባችንን ድምጽ ለማክበርና ለማስከበር ተዘጋጅተናል። የብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ማቅ እና ድሪት አውልቆ የሕዝብን ሀቀኛ ፍላጎትና እውነተኛ መሻት የሆነውን መካከለኛ አማራጭና የወሳኝ ኩነቶች ወሳኝነት ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚበጀውን የፕራግማቲዝም (pragmatism) ድርና ማግ ተጎናጽፎ ነው። በብልጽግና እምነት ቋሚና የማይለወጥ እውነት የለም፤ ሁሉም ነገር ቋሚ ሊሆን አይችልም። በብልጽግና እምነት የማይለወጥ መሠረታዊና ቁሳዊ የሆነ ነገርም አይኖርም። ከብልጽግና ርዕዮተዓለማዊ እምነት አኳያ ቋሚና የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ እሱም ኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።

    መደመርን መንገዳችን፣ ብልጽግናን መዳረሻችን አድርገን ስንነሳ መደመር የሚፈልጉ ዜጎቻችንን ልንቀንሳቸው አንችልም። ዛሬ በማይካድራ፣ በዳንሻ፣ በዓላማጣ፣ በጥሙጋና በዋጃ ባጠቃላይ በራያ ዋጃ ዓላማጣና ኮረም እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ያሰማችሁትን የ‘አማራ ነን’ ድምጽ በአክብሮት የምንቀበለውና በጽናት የታገልንለት ወደፊትም የምንታገልለት የመደመር ኅብረብሔራዊ ፌዴራላዊ ትርጉም ያለው የቆየ ግን በእብሪት የተገፋና መልስ የተነፈገው የዜጎች ጥያቄ ነው።

    ሁሉም የብልጽግና ቤተሰቦችና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኃይሎች እንዲረዱት የምንፈልገው ቁምነገር አለ።

    በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም።

    ክልላዊ ወሰናችንንና ፌዴራላዊ መብታችንን በመጋፋት በግፍ ተጠቃን እንጂ ማንንም አላጠቃንም።

    በጭካኔና ያለርህራሄ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመብን እንጂ በማንም ላይ የግፍ አጸፋ አልመለስንም። በደም ፍላት ስሜት ተገፍትረው ግፍ ለመፈጸም የቃጡና የሚቃጡ በውስጣችን ያሉ ስሁታንንም ያለርህራሄ ታግለናል፤ እየታገልንም እንገኛለን።

    ከልክ በላይ በተወጠረ እብሪት በትምክህተኝነት ስሜትና በተስፋፊነት ልክፍት ተወጥረው ሕዝባችንን፣ መሬታችንን፣ ታሪካችንን፣ መልካም ስማችንን፣ የ30 ዓመት ሁሉአቀፍ ክልላዊ እድገታችንን፣ እድሜያችንንና ሥነ-ልቦናችንን በግፍ ተዘረፍን እንጂ የማንንም ቅንጣት አልዘረፍንም።

    የወሰን፣ የማንነትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቂያችንን በሕግና በሥርዓት አቀረብን እንጂ እንደ ትሕነግ በማን አለብኝነት ‘ዘራፍ’ አላልንም።

    የተገፋን፣ የተበደልንና የተጨፈጨፍን ቢሆንም ለፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ አልፈጠርንም።

    የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የሀገር ሉአላዊነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ቁርጠኛ አጋርነታችንን በክቡር መስዋዕትነት አረጋገጥን እንጂ ሀገራችንና ሕዝባችንን በመካድ አልወጋንም። ሀገርና ሕዝብ ክደው በወገን ላይ የጭካኔ አፈሙዝ ያዞሩትንም የታሪክ ማፈርያዎች እንደሆኑ እንረዳለን።

    በሰላማዊ መንገድ እጅ የሰጡና የተማረኩ የትሕነግ ተዋጊ ኃይሎችን በወንድማማች መንፈስ ቁስላቸውን ጠረግን፣ እንዲያገግሙ በፍቅር ተንከባከብን እንጂ እንደጠላት አልገፋናቸውም። በተለመደው አማራዊ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት እልፍኛችንን ለቀን፣ ከአልጋችን ወርደን የምርኮኛነት ስሜት እንዳይሰማቸው አስተናገድናቸው እንጂ በግፍ አላሸማቀቅናቸውም።

    እብሪተኛው የአፓርታይድ ቡድን በፈጸመብን ሴራ እስከአሁኗ ሰዓት ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በስጋትና በጭንቀት የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ነው። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አሁንም በስደት ላይ ይገኛሉ። በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን የሚፈሰው የአማራ ደም ዛሬም አልቆመም። በሌሎችም አካባቢዎች የስጋት ጅረት አልተገደበም። በማይካድራና በሁመራ በየቦታው የተጣሉ አስከሬኖች ‘በክብር ቅበሩኝ’ ጥሪ ቢያስተጋቡም የንጹሃኑ በድኖች ግን ዛሬም ድረስ ተለቅመው አላለቁም።

    ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ ጥንተ ጠላት የሆነው ትሕነግና ጽንፈኛ ወዳጆቻቸው ከትክክለኛው ወቅታዊ አውድ ፍጹም የሚቃረን ሙግትና ትንታኔ ሲሰጡ ልማዳቸው መሆኑን ብናውቅም ለአንድ አንድ የትግል አጋሮቻችንና ደጋፊዎቻችንን ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን።

    1. ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አረመኔውና የአፓርታይድ ሥርዓት አቀንቃኙ ትሕነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የተጠናና የተደራጀ ሁሉ-አቀፍ ጥቃት ሲፈጽም የወራሪነት፣ የተስፋፊነትና የጨፍጫፊነት አድማሱን በማስፋት በ24 ሰዓት ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ የአማራ ክልል አቅጣጫዎች ጎንደርንና ወልድያን የመቆጣጠር ግብ አስቀምጦ ነው። ይህንን እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ከ3 ዓመት ያላነሰ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ትሕነግ ያስቀመጠውን የወራሪነት ግብ በመቀልበስ ሀገርና ሕዝብን ለመታደግ በወትሮ ዝግጁነት መፈጸሙ የአማራን ሕዝብ ሊያስመሰግነው ሲገባ፥ በጥርጣሬ እንድንታይ የሚያደርግ በፍጹም አይሆንም። የተከፈተብንን የግፍ ጦርነት ተከላክለንም፣ አጥቅተንም ጦርነቱን መቀልበሳችንና በግፍ ተነጥቀን የነበረውን ተፈጥሯዊ መብታችንን በእጃችን ማስገባታችን (repossession right) የተፈጥሮን ሕግ የሚቃረን ሳይሆን በእብሪተኞች የማይታረቅ ተቃርኖ መቃብር ላይ የተረጋገጠ ድል ነው። ስለሆነም እርስት ለማስመለስ ያልታገለን ይልቁንም ላለፉት 30 ዓመታት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየን ሕዝብና መንግሥት እርስት ለማስመለስ እንደተዋጋ አድርጎ ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አመክንዮ የጎደለው ድምጽ ማሰማት ነውር ነው እንላለን። በእርግጥ እርስት ማስመለስ የሚለው ትችት ለባለእርስቶች የተወረወረ የበላ-ልበልሀ ክርክር መሆኑ የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ፍትሀዊነት ያረጋገጠ ሀቅ በመሆኑ ሀሳቡን ደጋግማችሁ ለተጠቀማችሁ ሁሉ ምስጋና እናቀርብላችኋለን።
    2. እንደ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ሕዝብ ሀቅ ይታወቃል። የአማራ ሕዝብ ሀቅ ዛሬም በአደባባይ በሕዝባዊ ሰልፍ በይፋ እንደሚታየው የማንነት፣ የወሰን፣ በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት ፍትሀዊ ጥያቄ ነበር። ከ500ሺ ሕዝብ በላይ የተፈናቀለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተገደለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተሰወረባቸው እነዚህ አካባቢዎች ዛሬም የተረጋገጠ የጅምላ መቃብር የተገኘባቸውና የአፓርታይድ ሥርዓት በተጨባጭ የተፈጸመባቸው የትሕነግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ጭካኔ ማረጋገጫ የግፉአን መቀበርያ አጽመ እርስቶች ናቸው።

    በግፍ የተጨፈጨፉ የንጹሀን ወገኖቻችን አስከሬኖች ተለቅመው በክብር ባላረፉበት በዚህ ወቅት የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት የወንበዴውን ቡድን ወንጀል ለመደበቅና ለማድበስበስ እየተፈጸመ የሚገኝ ሌላኛው የትሕነግ ሸፍጥ ማምለጫ መንገድ ሲሆን፥ የአካባቢውን ነባራዊ ሀቅ በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት የሚራመዱ የተሳሳቱ ሀሳቦች የሞራል ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው።

    ስለሆነም የሕግ የበላይነት ለማስከበር፣ የሀገር ሉአላዊነት ለማጽናት በተደረገ ሁሉ አቀፍ የትግል ጀብዱ በታሪክ አጋጣሚ ወደባለእርስቱ የገቡ አካባቢዎች (repossessed lands) ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በሥርዓቱና በአግባቡ በቀጣይ ማየት ይቻላል የሚል እምነት አለን። ግን ደግሞ የትሕነግን የአፓርታይድነት የወንጀል ፈለግ (criminal scene) መፈተሽና መመርመር፣ ለትግራይና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማጋለጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለን። ስለሆነም:-

      • ላለፉት 50 ዓመታት የዜጎች ማጎርያና ማሰቃያ የሆኑ ከመሬት በታች የተሰሩ ዋሻዎች (underground torching caves) ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው።
      • ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጅምላ መቃብሮች ታስሰው ላለፉት 50 ዓመታት እንደ ሕዝብ የተፈጸመብንን ግፍና ጭካኔ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን።
    1. በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ግፈኛና ግፍን ነቅሎ በአዲስና በተረኛ ግፈኛና ግፈኝነትን ማጽናት አይደለም። ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ችግር ከግፈኞች አልነበረም። እንደሀገር ግፈኞችን መቅበር የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በየታሪክ ምዕራፉ ግፈኞችን መቅበር የምትችል ሀገር ግፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ግን አልቻለችም። ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ ግፈኝነትን በጽናት በሚታገልበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ የየበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ እየጠየቅን፥ በእኛ በኩል እብሪተኝነትም ሆነ ግፈኝነት የሕዝባችንን ክብር ዝቅ ስለሚያደርገው በጽናትና በታማኝነት የምንታገለው መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።
    2. በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሕግ የበላይነት የምናስከብር መሆኑን እያረጋገጥን፤ በቤንሻንጉል ክልል በሕዝባችን ላይ ተደጋጋሚ ግፍ የሚፈፅሙ የእብሪተኞች ቅሪት ዓላማና ፍላጎት በድል እንደሚቋጭ ሳንጠራጠር የተጀመረውን ሕግ የማስበር ሥራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ጎን ለጎንም የተፈናቃይ ወገኖቻችንን መሠረታዊና ወቅታዊ ፍላጎት እንዲሟላ ከማድረግ ባሻገር የሕዝባችንን እንቅፋት በሕግ አግባብ ተጠራርጎ መጥፋቱ ከተረጋገጠ በኋላ ዜጎቻችንን ተመልሰው በቀያቸው ላይ እንዲሰፍሩ የሚደረግ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን።

    በመጨረሻም በትሕነግ መራሹ እብሪተኛ አፓርታይድ እርምጃ ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመባችሁ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የማይካድራና የሁመራ ሰማዕታት ሁልጊዜም በሕዝባችን ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ክብር አላችሁ።

    የሕግ የበላይነት ለማስከበር በተፈጸመው እልህ አስጨራሽ ግብ ግብ ክቡር መስዋዕትነት የፈጸማችሁ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የአባቶቻችን ልጆች ስለሆናችሁ ኮርተንባችኋል፤ ለዘላለምም እንኮራባችኋለን።

    የኦነግ ሽኔንና የጉሙዝ አማጺ ቡድንን ለመደምሰስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ስምሪት ወስዳችሁ ታሪካዊ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የምትገኙ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች፣ የኦሮምያና የቤንሻንጉል ክልል ሀቀኛ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጀግንነታችሁን ስንዘክር በአማራ ሕዝብ አክብሮትና ትህትና ነው።

    ድል ከኢትዮጵያና ከአማራ ሕዝብ አብራክ ለተገኙ ታሪካዊ ጀግኖቻችን!!!
    ውርደት በእብሪትና በትዕቢት ተወጥረው ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለሚወጉ ጠላቶቻችን!!!
    ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ!!!
    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    በህወሓትና በውጭ ኃይሎች የተቃጣውን የእብሪት ጦርነት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም
    ነአምን ዘለቀ

    በሀገራችን አንድነትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነት ላይ በህወሓትና በውጭ ኃይሎች የተቃጣውን የእብሪት ጦርነት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ከባድ የህልውና አደጋ፣ ከባድ ፈተና ውስጥ እየገባች ነው። በእብሪት፣ በበታችነት፣ በዘረኝነት በሽታ የተለከፈው፣ በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ሁለንተናዊ የበላይነት ያጣው የመሰሪው የህወሓት መሪዎች ትግራይ ወስጥ በሚገኘው የሰሜን እዝ የመከላከያ ካምፕ ላይ የኃይል እርምጃ በውሰድ ሀገሪቱን ወደ ጦርነት ለመውሰድ የመጀመሪያ እርምጃቸውን እንደወሰዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተላለፈው መልዕክት ያሳያል።

    1ኛ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በጋራ ከመቆም ሌላ አማራጭ የለም። በልዩ ልዩ የህገሪቱ ችግሮች ከመንግሥት ጋር የሚገኙ ልዩነቶች ሁሉ ወደ ጎን ማድረግ አማራጭ የለውም።

    2ኛ) በሀገራችን አንድነትና በሕዝብ አብሮነት ላይ የተቃጣውን የህወሓት እብሪት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።

    3ኛ) የህወሓቶች ዒላማ የፌደራሉ መንግሥት ብቻ አይደለም፤ ይህ ጥቃት የተቃጣው በኢትዮጵያ ህልውና፣ በሕዝባችን ሰላም፣ ደህነትና አብሮነት ላይ ነው።

    4ኛ) የህወሓቶች ጥቃት በመከላከያ ሠራዊትበብልጽግና ፓርቲና እና በመንግሥት ላይ ብቻ አይደለም፤ የህወሓቶች እብሪትና ጠብ አጫሪነት እነሱ ያልገዟት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ፣ ብሎም እነሱ የሚያስታጥቁትና የሚደግፉዋቸው ኃይሎች በቤኒሻንጉል፣ በወለጋ እንደተደረጉት እጅግ ዘግናኝና አረመኔያዊ ግድያዎች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲደደገሙ በማድረግ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ይህን በጋራ ህልውናችውን ላይ የተቃጣ ከባድ አደጋ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ሆነን መመከት አለብን።

    5ኛ) ሕወሓት፣ ኦነግ ሸኔ፣ ግብጽ፣ እና በዲያስፓራም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቅጥረኖቻቸው ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከቻሉ ማዕከላዊ መንግሥቱን ዳግም ለመቆጣጠር፥ ካልቻሉም ደግሞ ህወሓት አባይ ትግራይን ይመሠርታል፤ ግብጽም የአባይን ግድብ ህልውና እና አገልግሎት ለማምከን ትችላለች፤ ኦነግ ሸኔም የኦሮሚያ ሪፑብሊክ ይመሠርታል። አነዚህን ዋና ዒላማቸው አድርገው በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚያ ስለሚከተለው ምድራዊ ሲኦል ህወሓትና የኦነግ ሽኔ የሞራልና የስብዕና ድኩማኖች ፈጽሞ ሊረዱ የሚችሉት አይደለም።

    ኢትዮጵያውያን ሁሉ፥ በዲያስፓራ የምንገኝ ሀገር ወዳዶች ሁሉ፥ በሀገር ውስጥም ወጣቱ፥ ጀግናው የቀድሞ ሠራዊት አባላት ሁሉ ከዳር አስከ ዳር በጋራ ሆነን፣ በጋራ ቆመን ከማዕከላዊ መንግሥትና ከመከላከያ ሠራዊቱ ጀርባ በመሰለፍ፣ አሰፈላጊውን ድጋፍና መስዋዕትነት መክፈል አለብን። የሀገራችንን ህልውና፣ የሕዝብን ሰላምና ደህነት፥ የጥፋት፣ የዘረኝነት፣ የእብሪት ክምችት ከሆነው ከህወሓትና ግብረ-አበሮቹ ለመታደግ በጋራ መቆም፣ በጋራ መሰለፍ የወቅቱ [ዋና ተግባራችን መሆን አለበት።]

    ይህን የማያደርግ የታሪክ ተወቃሽ ብቻ ሳይሆን የራሱንም፣ የቤተሰቡንም ዕጣ ፈንታ ለህወሓቶች ዳግማዊ የክረፋው ዘረኝነት፣ ጭካኔና ባርነት መዳረግ ይሆናል፤ ከዚያም ሲያልፍ ሀገር-አልባ መሆንም ይከተላል።

    ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ሆነ ከብልጽግና ጋር ያለ ማናቸውም ልዩነት ወደ ጎን አድርገን የመጣብንን የህልወና አደጋ በጋራ መመከት የወቅቱ አብይ ተግባር ነው!!

    ነአምን ዘለቀ (ከአሜሪካ)

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በህወሓት የተቃጣው የእብሪት ጦርነት

    Anonymous
    Inactive

    በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል መራሹ የኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው!!!
    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)

    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት ድርጊት የተሰማውን መሪር ሀዘን ይገልፃል።

    ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር የማፅዳት ወንጀል እየተፈፀመ ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ማስቆም የሚችል የመንግሥት ኃይል አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን እያባባሰው መጥቶ ዛሬ ላይ የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል።

    በዚህም ምክንያት በእነዚህ በርካታ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል። መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራት እና ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን ርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ቀንደኛ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።

    በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የሚንቀሳቀሰው ታጣቂው የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ በየቦታው ካሉ አማራጠል ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በቅንጅት አማራዉን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግሥቱ ነው።

    በኦህዴድ መራሹ የብልጽግና መንግሥት የስልጣን መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አፍቃሬ ኦነግ የኦህዴድ ባለስልጣናት በአካባቢው የነበረውን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በማስወጣትና ድርጊቱ ሲፈፀም እየሠሙና እያወቁ እንዳላዩ ማለፋቸው የዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳታፊ እንደሆኑ ይቆጠራል። በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ታውጆበት እያለ የማዕከላዊ መንግሥቱ ዝምታና እንዳላየ ማለፉ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው።

    የአማራው ሕዝብ በመንግሥት ድጋፍ እየተፈፀመበት ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እና ተዘጋጅቶ እንዲመክት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥሪውን እያቀረበ በአሸባሪው የኦነግ ሽኔ ሽፍታ ቡድን ህይወታቸን ላጡ ወገኖቻችን ቤተሰቦች መፅናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን።

    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
    ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም

    በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ባለው የዘር ማጥፋት መንግሥት ተጠያቂ ነው

    Semonegna
    Keymaster

    በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግፍ እውነታ በመረጃ የማሳየትና ማስረዳት ግዴታ ሁላችንም አለብን
    (ነአምን ዘለቀ)

    ሰላም ወገኖቼ ኢትዮጵያውያን፦

    ሀገራችን ኢትዮጵያን ከምንም ችግር ለመታደግ የሚያስችል ከፍተኛ ብቃቱም የሀገር ፍቅሩም ያላችሁ አያሌ የኢትዮጵያ ልጆች በውጪው ዓለም ትኖራላችሁ። የኢትዮጵያ ችግር እንደሚያሳስባችሁና በጎዋ ደግሞ እንደሚያስደስታችሁም ግልጽ ነው። ነገር ግን አብዛኞቻችሁ በተለያየ ምክንያት የዳር ተመልካች መሆንን መምረጣችሁ ሀገራችንንና ወገኖቻችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ እያየን ነው። ሄዶ ሄዶ ያልተጠበቀና ከእስካሁኑም በከፋ ሁኔታ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለማይወጡት አደጋ ለማጋለጥ እየተመቻቸን እንደሆነ ስጋቴን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ።

    በኦሮሞ ጽንፍ ኃይሎች መሪነት የኢትዮጵያ ጥላቻ ያላቸው ባዕዳን እንዲሁም የህወሓት ዲያስፓራ ሚዲያዎችና ካድሬዎች በጋራ በመሆን የአሜሪካ፣ የካናዳንና የአውሮፓን የሕግ አውጪዎችና አስፈጻሚዎች በማወናበድ ጸረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ለማራመድ በስፋት ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ ። ይህም በሰፊው እየወሰዷቸው ካሉ በርካታ አፍራሽ እርምጃዎች እንዱ ብቻ ነው። እነኚህ ኃይሎች ያለማጋነን ላለፉት 27 ዓመታት የጸረ-ወያኔ ሁለንተናዊ የትግል ቆይታዬ ያላየሁትን ከፍተኛ የዓላማ አንድነት (unity of purpose)፣ ቅንጅትና መናበብ በመፍጠር ከዳር እሰከ ዳር እየሰሩ ለመሆናቸው ብዙ መረጃዎች ይገኛሉ።

    ከዚህ መልዕክት ጋር ያያያዝኩት የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት ለአሜሪካ ስቴት ሴክሬታሪ/የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ (Mike Pompeo) የጻፉት ደብዳቤ የዚህ ሴራ አንዱ ውጤት ነው። በተቀናጀ መልክ የሀገራችንን እውነታና ሂደት በማዛባት፣ የሃሰት ትርክቶችን በመደራረት የውጭ ኃይሎችንና መንግሥታትን ለማወናበድ ያለተቀናቃኝ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ይህን ማድረግ የቻሉት ደግሞ በእነሱ ጥንካሬ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት፣ ለፍትህ፣ ለሕዝብ እኩልነት፣ ለሕግ የበላይነት ቀናዊ የሆነው ኢትዮጵያዊ ጎራ (silent majority) የተበታተነ መሆኑና የሚያምንበትን የሀገርና ሕዝብ አንድነት እውን ለማድረግ የድርሻውን ለመወጣት ቁርጠኛ አለመሆኑ ነው።

    “ነፍጠኛን ምታ፣ አቃጥል፣ ግደል፤ ቁረጥ” የሚሉ ያልተቋረጡ የጥላቻ ዘመቻዎች በሶሻል ሚዲያና በኦኤምኤን (OMN) ሚዲያ እንደሚክያሄድ ታውቃላችሁ ብዬ አምናለሁ። የዚህ ዘመቻ ውጤትም ብዙ መቶ ወገኖቻችን በኦሮሞ ጽንፈኞች አርመኔያዊ በሆነ መንገድ መጨፍጨፍ ነው። ይህም ግፍ በቅድመ ጄኖሳይድ (pre-genocide) ደረጃ የሚመደብ የዘርና የሃይማኖት ተኮር ፍጅት ነው ማለት ከእውነቱ የራቀ አይደለም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ይህን ሀቅ በመካድ አፈናቃይና ገዳዮቹ በተገላቢጦሽ ከሳሽ በመሆን “መንግሥት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚያደርገው አፈና” ያለ በማስመስል የተቀናጀ የሀሰት ትርክት በማሥራጨት ላይ ይገኛሉ። ዓላማቸውም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አመንስቲ (Amnesty) እና ሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን፣ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና፣ የካናዳ የሕግና የፓሊሲ አውጪዎችን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲሯሯጡ ይታያሉ።

    በአሜሪካና በአንዳንድ ሀገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ይህን የሀሰት ትርክት ለመለወጥ ጥረት ያደረጋሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ ኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አደጋውን መመከት በሚቻልበት ልክ የአቅምና ፓለቲካ ቁርጠኝነት ይዘው ሲንቀሳቀሱ አይታዩም። ከዚህ ከተያያዙት የተመልካችነትና ተከላካይነት ውሱን እንቅስቃሴ አልፈው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና፣ የየሀገሩን የፓሊሲና የሕግ አውጪዎችን እውነታውን ለማስጨበጥ በቂና አጥጋቢ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

    ይህ በጽንፈኞች የተቀነባበረ ርብርብና ዘመቻ በጊዜ ካልተገታ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የያዘውን መንግሥት እየቦረቦረ እንዳያዳክመው ስጋት አለ። ከህወሓት እስከ ኦነግ ሽኔ በተለያዩ አፍራሽ ኃይሎች ተወጥሮ የሚገኘው በዶ/ር ዓብይ አህመድ የሚመራው መንግሥት ከተዳከመ ሀገሪቷን ለትርምስ፣ ለሁከትና ሌላም የከፋ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። ስለዚህም እንደሕዝብና ሀገር ከፊታችን የተደቀነውን አደጋ በቀላሉ ማየት የለብንም።

    አደጋው በጣም የሚያስፈራው ደግሞ ቅራኔው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ብቻ መሆኑ ቀርቶ የ27 ዓመቱ የጥላቻ ቅስቀሳ ስር ሰዶ ሕዝብ አቃቅሯል። በየጊዜው የምናየው ግድያ፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም የዚህ የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት ነው። “ብሔር ለብሔር” ቅራኔዎችና ግጭቶችን እነማን ለምን ዓላማ ሲያራግቡ፣ ሲደግፉና ሲቆሰቁሱ እንደነበሩና ዛሬም ድረስ ያማያርፉበት፣ የሚተጉበት መሆኑን ሁላችንም የምናውቅም ይመስለኛል።

    እነዚህን የውስጣዊና የውጭ ከባድ አደጋዎች ድምር ለመግታትም በተደራጀ መልክ በካናዳ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የተናበቡ ሥራዎች መሥራት ግድ ይላል። ለየሀገራቱ የሕግ አውጪ (lawmakers) እና የሥራ አስፈጻሚ/የፓሊሲ ወሳኞች (policymakers) በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግፍ እውነታ በመረጃ የማሳየትና ማስረዳት ግዴታ ሁላችንም አለብን። ስለዚህም ሁላችንም በየሀገሩና በየከተማው መሰባሰብ፣ መነጋገር፣ መተባበር፣ መቀናጀትና ጠንካራ የአድቮኬሲ ቡድን (advocacy group) ማቋቋም ይኖርብናል። ከዛሬ ሁለት ወር በፊት ገደማ በሀገርና በሕዝብ ላይ የመጣው አደጋ አሳስቧቸው የተሰባሰቡ በርካታ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፡ የፓለቲካ፣ የአድቮኬሲ፣ የድርጅታዊ ልምድና ተሞከሮ ያላቸው ኢትዮጵያውን የሚገኙበት ዓለም ኣቀፍ ኔትዎርክ እገዛ ያደርግላችኋል። ይህን መሰል እንቅስቃሴ የምታደርጉ ለማድረግ የተዘጋጃችሁ ሁሉ፣ አሰፈላጊውን የሰነድ፣ የምክር፣ የአቅጣጫ ድጋፍ ልናደርግላችሁ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ስለሆን በውስጥ መስመር (messenger inbox) ልታገኙን ትችላላችሁ።

    ነአምን ዘለቀ
    bit.ly/NeaminZeleke

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ-ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግፍ እውነታ በመረጃ የማሳየትና ማስረዳት ግዴታ ሁላችንም አለብን

    Anonymous
    Inactive

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!

    (ያሬድ ኃይለማርያም*)

    በ1994 እ.ኤ.አ. ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በዋናነት የመሩት ሁለት ሬድዮ ጣቢያዎች ነበሩ። አንዱ በመንግሥት ስር የነበረው ሬድዮ ሩዋንዳ (Radio Rwanda) የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው እና ዋናው የእልቂቱ አነሳሽና ቀስቃሽ የነበረው Radio Télévision des Milles Collines (RTLM) ተብሎ የሚጠራው ጣቢያ ነበር። ይህ ጣቢያ በወቅቱ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ስለነበር በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን እና የቀኝ አክራርሪ የሆኑትን የሁቱ ኢንተርሃሞይ ሚሊሻዎችን (Interahamwe militia) በቀላሉ ወደ ጥላቻ በመንዳት በመምራት እና እልቂት እንዲፈጽሙም በማነሳሳት ትልቅ ሥራ ሠርቷል። ይህ ጣቢያ ከእልቂቱም በፊት ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል ጥላቻን ሲሰብክ ቆይቷል።

    ዛሬ ደግሞ ተራው የእኛ በሚመስል ሁኔታ እጅግ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ለዓመታት ጥላቻን ለኦሮሞ ወጣቶች እና ለኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ሲሰብክ የነበረው OMN የተባለው ሚዲያ የወንድማችንን ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ባስተላለፋቸው ተከታታይ የአመጽ እና የእልቂት ጥሪዎች እና ቅስቀሳዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል። ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ልክ የሩዋንዳው RTLM እንዳደረገው ሁሉ ጥሪው ክልሉ ውስጥ ላሉ ሥራ-አጥ ወጣቶች እና በሽኔ ስም ለሚጠሩት ሚሊሺያዎች ነበር። በዚህም እጅግ ለመስማትና ለማየት የሚሰቀጥጡ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲፈጸሙ ተደርጓል። ሰዎች እቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከነቤተሰቦቻቸው በእሳት ጋይተዋል፤ ህጻናት፣ ሴቶች እና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በስለት እና በቆንጨራ ተቆራርጠው ተገድለዋል፤ እናት ከህጻን ልጇ ጋር በአንድ ገመድ ታንቃ ተገድላለች፤ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል፤ ብዙዎች ከቤታቸው ሸሽተው በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ተደብቀዋል።

    አንዳንድ እማኞች በመገናኛ ብዙኃን ምስክርነታቸውን እንደሰጡት እና እኛም ማረጋገጥ እንደቻልነው ለጥቃት የተሰማሩት ኃይሎች በቂ ዝግጅት ያደረጉ፣ የተለያዩ የጥቃት መሣሪያዎችን የያዙ እና የጥቃት ዒላማ የሆኑ ሰዎችን ስም እና አድራሻም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ ተችሏል። ነገሩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በክልሉ ውስጥ ያሉ የክልሉ ታጣቂ ኃይሎች ይህ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ድርጊቱን ለማቆም አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው። በአሜሪካ ድምጽ (ቬኦኤ) እና አንዳንድ ሚዲያዎች እንደተዘገበውም በተወሰኑ ቦታዎች የመንግሥቱ ታጣቂዎች ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ጥቃት ሲፈጸም እያዩ ዝምታን መርጠው መቆየታቸው ነው። በሩዋንዳም የዘር ማጥፋት ጥቃት ሲፈጸም የሆነው ይሄው ነበር። እነዚህ ኃይሎች በምንም መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል የበቀሉ እንክርዳዶች ናቸው። በመሆኑም እንዲህ ያሉ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ ቡድኖችን እና ነገሩን በቸልታ ሲያዩ በነበሩ የክልሉ ኃላፊዎች ላይ በቂ ምርመራ ሊካሔድ እና በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።

    OMN አዲስ አበባ ያለው ጽሕፈት ቤቱ ቢዘጋም ተመሳሳይ የእልቂት ጥሪዎችን ከሀገር ውጭ ባሉ ባልደረቦቹ በኩል ሲያስተላልፍ ቆይቷል። ዛሬ ደግሞ ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ አየር ላይ ያዋላቸውን እና በዩቲዩብ (YouTube) የተላለፉ ዝግጅቶቹን ከአየር ላይ እያወረደ እና መረጃዎችን ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፦

    (ኛ) የእነዚህ የእልቂት ጥሪዎች ቅጂዎቻቸው ጣቢያው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት እጅ ስለሚገኙ እና የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲውም የእነዚህ ቅስቀሳዎች ቅጂ እንዳለው ባለሥልጣኑ ስለተናገሩ ጣቢያው መረጃ ለማጥፋት እያደረገ ያለው ጥረት ይሳካል ብዬ አላምንም። ነገር ግን እነዚህ መረጃዎች በመንግሥት በኩል በቂ ጥበቃ ተደርጎላቸው በክልሉ ውስጥ ለተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ያላቸው አስተዋጽኦ በአግባቡ ሊመረመር ይገባል፤

    (ኛ) በOMN የተላለፉ የዘር ተኮር ቅስቀሳ ቪዲዮዎች እና ዘገባዎች በእጃችው ላይ የሚገኝ እና ጉዳዩ የሚያሳስባችው ግለሰቦች፤ እንዲሁም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና አንዳን አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፍ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ያላችሁ ሰዎች በዚህ የኢሜል አድራሻ end.empunity.eth@gmail.com እንድታቀብሉን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

    ዘር ተኮር ጥቃት ይቁም!

    አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም

Viewing 5 results - 1 through 5 (of 5 total)