Search Results for 'የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን'

Home Forums Search Search Results for 'የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን'

Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ባካሄደው የአንድ ሳምንት የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ።

    ኮሚሽኑ የፀጥታ ሥራውን በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ የጋራ በማድረግ በተግባር ምዕራፉ የመጀመሪያ ሳምንት ባካሄደው ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሂደት ባከናወናቸው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባራት

    1. በተደራጀ መንገድ ታቅደው የሚፈፀሙ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች፣
    2. የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም አፈና እና ግድያ፣
    3. የተሽከርካሪ ስርቆት፣
    4. ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን መቀነስ መቻሉን ገልጿል።

    ኮሚሽኑ እንደገለፀው በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 359 ተጠረጣሪዎች ተከታትሎ በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥ

    ትግራይ ላይ በተፈፀመው የጁንታው ጥቃት የተሳተፉና በተለያየ መንገድ አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በተለያየ የወንጀል ተገባር ሲሳተፉ በተገኘ የሕዝብ ጥቆማ 135 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰባት የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በማጣራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

    ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ በዘረፋና በግድያ ከተወሰዱ 10 ራይድ ተሽከርካሪዎች ስምንቱ እንደተያዙና የሁለቱ አካላቸው እንደተፈታ ፖሊስ ደርሶበት በቁጥጥር ስር አውሎ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አመልክቷል።

    ኮሚሽኑ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እና የንግድ ስር-ዓቱን ለማዛባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በዚህ ኦፕሬሽን በቀጥጥር ስር አውሎ ከእነሱም ብዛት ያላቸው ሸቀጦችና ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

    በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባካሄደው በዚህ የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ንብረቶች መካከል በዝርፊያ የተወሰደ አንድ ሲኖ-ትራክ ከባድ መኪናንና ከግለሰቦች የተነጠቁና ከድርጅቶች የተዘረፉ ባርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመያዝ ለባለ ንብረቶቹ ተመላሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ሐሰተኛ መታወቂያ በመቀያየርና በመጠቀም በተለያዩ የተሽከርካሪ መሸጫ ድርጅቶች እየተቀጠሩ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች በማሰረቅ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች መያዛቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

    በመጨረሻም ኮሚሽኑ ይህ ከጅምሩ ውጤት ያስመዘገበ የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፆ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው የከተማው ህዝብ ለሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መረጃዎችን ባለመቀበልና ሀሰተኛ መረጃዎችንም ባለመጋራት እንዲሁም ለፖሊስ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት እንደተለመደው መረጃ በመስጠት እንዲተባበር እየጠየቀ ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት የከተማው ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ኮሚሽኑ ሌሎች የፀጥታ ሀይሎችንም በመወከል የላቀ ምስጋና ያቀርባል።

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
    መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    እውነታውን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም! ― የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወረራን እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢ-ፍትሃዊ ዕደላን በተመለከተ የሚደርሱትን ጥቆማዎች በመቀበል ጉዳዩን የሚመረምር ከብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተወጣጣ ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። የጥናቱን ውጤት ለሕዝብ እና ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ለማድረግ ዛሬ አርብ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ተዘጋጅቶ ነበር።

    ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲዘጋጅ ከዚህ ቀደም ጋዜጣዊ መግለጫ ስንሰጥ እንደምናደርገው ሁሉ ጋዜጣዊ መግለጫው ለሚደረግበት ራስ ሆቴል እንዲሁም በደብዳቤ ቁጥር ኢዜማ/695/12 ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር አስቀድመን አሳውቀናል።

    ፓርቲያችን ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ ለመከታተል እና ለሕዝብ ለማድረስ የተጠሩ ጋዜጠኞች ከተባሉት ሰዓት ቀድመው በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ሲሆን፥ ብዙዎቹም የቀረጻ መሣሪዎቻቸውን አሰናድተው  የመግለጫውን መሰጠት በመጠባበቅ ላይ እያሉ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባል መሆናቸውን የገለፁ የፖሊስ አባላት መግለጫው መሰጠት እንደማይቻል በማሳወቅ፥ ጋዜጠኞቹ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል። ፖሊሶቹ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለማስቆም የሰጡት ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲካሄድ ትዕዛዝ አልተሰጠንም የሚል ነበር።

    በስፍራው የተገኙት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮች ሙሉ ትብብር ያደረጉ ሲሆን፥ ስለመግለጫው ለሰላም ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ለፖሊስ አባላቱ አስረድተዋል። ወደ ሰላም ሚኒስቴር በመደውልም የተፈጠረውን ለሚንስትር መሥሪያ ቤቱ ያሳወቁ ሲሆን፥ የፖሊስ አባላቱን ከሰላም ሚኒስቴር ጋርም በስልክ የማገናኘት ሥራ ተሠርቷል። ነገር ግን የፖሊስ አባላቱ መልሰው “የሰላም ሚኒስቴር ሊፈቅድ የሚችለው ስብሰባዎችን እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን አይደለም። የመግለጫ ጉዳይ የሚመለከተው ፖሊስን ነው።” በሚል መግለጫውን በመከልከል ጸንተዋል። ይህንንም ተከትሎ የኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ እየተፈፀመ ያለውን የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢ-ፍትሃዊ ዕደላን አስመልክቶ የሠራውን ጥናት ውጤት ለሕዝብ ለማሳወቅ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ተስተጓጉሏል።

    ትላንት የአዲስ አበባ መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ እየታጠረ ሲወረር እና ሲዘረፍ ማቆም ያልቻሉ የሕግ አስከባሪዎች፥ በሕጋዊ መንገድ የተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ አጥር ሆነዋል። የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን እና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደዛሬው ዓይነት እክል ትላንትናም አላስቆመንም፤ ዛሬም አያስቆመንም! የተፈጸመ ስህተት ካለ አዳምጦ ለማረም ከመዘጋጀት ይልቅ የዜጎችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት በማፈን እና እውነቱን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ለመራቅ መሞከር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንቅፋት እንደሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ዛሬ በተከሰተው መግለጫውን የማስተጓጎል ተግባር እውነታውን ማድበስበስ እና ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም።

    ከዚህ ቀደም የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ በጥናታችን የደረስንበትን ውጤት አያይዘን የእነሱን ምልከታ በጥናት ውጤታችን ውስጥ ለማካተት ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀን የነበረ ቢሆንም፥ ሁሉም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆናቸው በተጨማሪ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ የላክንላቸውን ደብዳቤም ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

    ኢዜማ በጥናቱ የደረሰበትን ሕገ-ወጥነት እና ኢፍትሃዊነት ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት 8 ሰዓት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል። ሀሳባችንን የመግለጽ ሕገ-መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር ወደኋላ እንደማንል እና ያገኘነውን ውጤት ሕዝብ ጋር እንደምናደርስ እንዲያውቁት በድጋሚ ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ልከናል።

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    Anonymous
    Inactive

    በኦሮሚያ ክልል “ከአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው” በተባሉ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ― የአሜሪካ ድምፅ

    በኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው በተባሉ ዜጎች ላይ በተነጣጠረ ጥቃት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።

    በሌላ በኩል ጥቃቱ የተፈፀመው “ከአንድ ብሔር የመጡ ናቸው” የሚሉ ሰዎች ላይ በማነጣጠር ቢሆንም፥ ሕብረተሰቡ የተጋባና የተዋለደ በመሆኑ ተጎጂ ከሆኑት ውስጥ ከተለያየ ብሔር የተወጣጡ ሰዎች መሆናቸውን ነዋሪዎችም፣ የዞኑ አስተዳዳሪም ተናግረዋል።

    ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ ገላን ኮንደሚኒየም አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች የተገደለውን ዝነኛውን የኦሮሚኛ ቋንቋ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እጅግ አሰቃቂ በሆኑ ሁኔታዎች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ማጉደል፣ ዘረፋና በከፍተኛ ሁኔታ ንብረት ማቃጠል መከሰቱንም ተጎጂዎችና የዓይን እማኝ መሆናቸውን የተናገሩ ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።

    አንዳንዶቹ ግድያዎች በደቦ የተፈፀሙ ሲሆኑ፥ አንዳንዶቹ ግን በሰለጠኑ እና ተኩሰው በማይስቱ ታጣቂዎች የተፈፀሙ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የአሜሪካ ድምፅ ቤተሰቦቻቸው ፊት ለፊታቸው እደተገደሉባቸው የሚናገሩ፣ ንብረታቸው እንደተቃጠለባቸውና ያለ መጠለያ መቅረታቸውን የሚገልፁ በተለያዩ ከተማ የሚገኙ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎችን ያነጋገረ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት (ሰኔ 29 ቀን) በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ዴራ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ከጥቃት ከተረፉት መካከል የተወሰኑትን አስደምጧል።

    በሌላ በኩል የአርሲ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ጀማል አልዩ በአርሲ ዞን ውስጥ እርሳቸው ከሚያስተዳድሯቸው 25 ወረዳዎችና ሦስት ከተሞች መካከል በስድስቱ ውስጥ በተፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች የ34 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገፀዋል። ድርጊቱ በአካባቢው ከነበረው ፖሊስ አቅም በላይ እንደነበርና የፀጥታ አባል ጭምር መገደሉን አረጋግጠዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተለያዩ ከተሞች ጥቃቶቹ መፈፀማቸውን አምነዋል።

    ድርጊቱ የተፈፀመው በሁለት ብሔሮች መካከል የተካረረ ፀብና ግጭት በመቀስቀስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማቸው ባደረጉ አካላት ነው ሲሉም ከግጭቱ ጀርባ ሌሎች ቡድኖች እንዳሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። መንግሥት ይህንን በአስቸኳይ በመረዳት የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላቱን ከክልል የፀጥታ ጥበቃ አባላት ጋር በማዋቀር የመከላከል ሥራ በመሥራቱ እንጂ ከዚህም የባሰ ጥቃት ይደርስ ነበር ሲል መንግሥት መግለጫ ሰጥቷል።

    የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ገላን እስካሁን የ145 ሰላማዊ ዜጎች እና የ11 የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት በድምሩ የ156 ዜጎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ደግሞ በአዲስ አበባ የሁለት የፀጥታ ኃይሎችና የስምንት ሲቪሎች በድምሩ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አረግጋጠዋል። በአጠቃላይ ከመንግሥት የተገኘው መረጃ 166 ሰዎች በቦምብ፣ በጥይት፣ በድንጋይና በመሳሰሉት ሕይወታቸው ማለፉ ይጠቁማል።

    (ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

    ምንጭ፦ የአሜሪካ ድምፅ

    ከአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው በተባሉ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት

    Anonymous
    Inactive

    የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል መሪ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያስተላለፉት መልዕክት

    አዲአ አበባ (EBC) – የታዋቂዉና ተዋዳጁ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ አስመልክቶ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስትዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሀዘናቸውን ገለፁ።

    በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ጀግናችን፣ የቅርብ አካላችን የትግልና የለዉጥ ምልክት የሆነዉ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት መመታቱን ሰምቻለሁ ሲሉ አሳዛኙ ዜና እንዴት እንደደረሳቸው አስረድተዋል። ሕይወቱንም ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም ሕይወቱ ሊተርፍ አለመቻሉንም ነው ያስታወቁት።

    በአርቲስቱ ህልፈተ ሕይወት እንደ ግለሰብና እንደ አብሮ አደግ አብሮም እንደኖረ ሰዉ እንደ ታጋይና የትግል አጋር እንደ የችግር ጊዜ ጀግና ትልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ።

    ሃጫሉ ሁንዴሳ አርቲስት ብቻ ሳይሆን ታጋይም ነዉ ያሉት ርዕሰ መስትዳደሩ፥ ለእኔ ደግሞ ወንድሜም መካሪዬም ነዉ።  ይህንን ጀግና ነዉ ያጣነዉ ብለዋል አቶ ሽመልስ።

    የዚህ ጀግና ግድያም እንደቀላል እና ለቀላል ነገር የተፈጸመ ወንጀል አይደለም። ታስቦበት እና ታቅዶበት የተፈጸመ ድርጊት ነዉ። ይሄ ምንም ጥርጥር የለዉም ሲሉም ነው አቶ ሽመለስ የገለጹት። በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ የተወሰኑት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለጹት ርዕሰ መስትዳደሩ፥ ምርመራም እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

    የጸጥታ አካላት በሁሉም አቅጣጫ ተሰማርቷል። የዚህ ግድያ ዓላማም ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት፣ ሀገር ለማፍረስ፣ ሲዝቱ የነበሩ ኃይሎች ድርጊት ነው ብለዋል።

    ከለዉጡ ወዲህ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። አብዛኛዎቹን በማክሸፍ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔር ብሔረሰቦች አንድ ላይ ቆመዋል። አሁን ያለዉን ለዉጥ ለማደናቀፍ ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት፥ ይህንን ለማክሸፍ የኦሮሚያ ፖሊስና የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎችም ትልቅ ሥራ ሠርተዋል ብለዋል። ዛሬ ደግሞ ይህንን የግድያ ወንጀል በመፈጸም ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት ሀገር ለማፍረስ፣ አቅደዉ እንደተነሱ ጥርጥር የለዉም ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች እርስ በርስ በመደማመጥ፣ አንድላይ በመቆም ጀግናችን የከፈለለትን መስዋዕትነት፣ ይህ ለዉጥ እንዲሳካ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁሉም ሰዉ በእርጋታ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ እንድንሻገር ጥሪ አቅርበዋል።

    መንግሥታዊ መዋቅሩም ይህንን አደጋ ለመታደግ በአንድነት ሊቆም ይገባል ብለዋል አቶ ሽመልስ አብዲሳ። ለቤተሰቦቹ ፣ ለኦሮሞ ሕዝብና ለመላዉ የሀገራችን ሕዝቦች መጽናናትን እንደሚመኙ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።

    ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተወዳጁና ጀግናው አርቲስት ሃጫሉ ሞት የተሰማቸውን ከባድ ሀዘን ገልፀዋል።

    ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፥ “ሃጫሉ ቢሞትም መሞት የማይችል ሥራ ሠርቷል። ማንም ይሁን ማን ሃጫሉን የገደለው ሰው ከሕግ ማምለጥ አይችልም። የእኩይ እና አስነዋሪ ሥራውን ዋጋ በሕግ ያገኛል። የአርቲስት ሃጫሉን ነብስ ፈጣሪ በገነት ያኑር! ለቤተሰቡና ለመላው ሕዝባችን ፈጣሪ ትዕግስቱን፣ ብርታትና መጽናናትን ይስጠን!” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባስተላለፉት የሐዘን መልእክት ደግሞ፥ “ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች፥ ውድ ሕይወት አጥተናል። የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሕይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሀዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ ። የዚህን ክፉ ድርጊት ሙሉ የፖሊስ ምርመራ ሪፖርት እየተጠባበቅን እንገኛለን። የድርጊቱን መጠን በመረዳት በሀገራችን ውስጥ ስለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ትኩረት ሰጥተን የምንከታተልበት ወቅት ላይ ነን። ሀዘናችንን ራሳችንን በመጠበቅ እና ተጨማሪ ወንጀልን በመከላከል እንግለፅ” ብለዋል።

    ሃጫሉ ሁንዴሳ

    Anonymous
    Inactive

    በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሞታ በተገኘችው ተማሪ (ሃይማኖት በዳዳ) የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

    አዲስ አበባ (ኢፕድ) – ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የተገደለችው የወጣት ሃይማኖት በዳዳ ተጠርጣሪ ገዳይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ያዋለው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ደግነት ወርቁ የተባለ ወጣት ሲሆን፥ ወጣት ደግነት ወርቁን ፖሊስ የ27 ዓመቷን ሃይማኖት በዳዳ ሕይወት በማጥፋት ጠርጥሮት በቁጥጥር ስር አውሎታል።

    ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ባካሄደው ክትትል ነው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር የዋለው። ቀን ከሌሊት በተካሄደው በዚህ ክትትል የተያዘው ወጣቱ ደግነት ወርቁ ከሟች ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ እንዳልነበራቸው በቁጥጥር ስር በኋላ ለሰዓታት በተደረገ ምርመራ የወንጀሉን ዝርዝር ለፖሊስ አስርድቷል።

    ግለሰቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርና የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ስለሆንኩ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች ይርዱኝ በማለት ወደ ግቢው በተለያዩ ጊዜያት ይመላለስ እንደነበር ዘርዝሯል። ከዚያም በግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደልማዱ ለዚሁ ጉዳይ እንደመጣ ገንዘብ እንደተቸገረና ቢላዋ ይዞ በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎች በአንዱ ላፕቶፕ ወይም ሞባይል ካገኘ ሰርቆ ሽጦ ለመጠቀም ሲዟዟር የሟች ክፍል ክፍት በመሆኑ መግባቱን አስረድቷል። ሟች ሃይማኖት በዳዳ ሞባይሏን እንድትሰጠው ጠይቋት እምቢ ስትለው መታገላቸውንና ከዚያም በያዘው ስለት ወግቷት ንብረቱን ይዞ መውጣቱን ተናግሯል።

    ፖሊስ ከሟች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው 12 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ተጨማሪ ምርመራ ማድረጉን የግድያ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ገልጿል። ለፖሊስ ምርመራ ትልቅ አቅም የሆነው የሟች ወላጅ አባት ከሳምንት በፊት ለልጃቸው የሰጧት የ5 ሺ ብር ቼክ ነው።

    ገዳዩ በወቅቱ የሟችን ላፕቶፕና ሞባይል ፓስፖርት መታወቂያና ይህንን ቼክ ወስዶ ስለነበር ቼኩን የካ አካባቢ በአንድ ባጃጅ ተሳፍሮ አሽከርካሪውን መታወቂያ ስላልያዝኩ በአንተ መታወቂያ ይህንን ብር አውጣልኝ ብሎት የባጃጁ ሹፌርም (አቶ እንዳለማው ታረቀኝ) መልኩን አስተውሎ ስለነበር ምርመራው ከዚህ እንደጀመረ ፖሊስ ገልጿል፡

    ኮሚሽኑ በወቅቱ የሆስፒታሉ የደኅንነት (security) ካሜራ ከአገልግሎት ውጪ መሆኑን (‘update’ እንዳልተደረገ) እና የጥበቃ ሠራተኞችም ቢላዋ ተይዞ እስከሚገባ ፍተሻቸው አጋላጭ መሆኑንም ጠቁሟል ሲል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዘግቧል።

    ሃይማኖት በዳዳ ማነች?

    ወጣት ሃይማኖት በዳዳ ተወልዳ ያደገችው መተሃራ ከተማ ሲሆን፥ ወላጆች በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖራሉ። በ2009 ዓ.ም. ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በ’ክሊኒካል ፋርማሲ’ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማዕረግ ያገኘች ሲሆን፥ በዚያው በተማረችበት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ስታገለግል ነበር። ከዚያም በ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሁለተኛ ዲግሪዋን በመከታተል ላይ እንደነበረች አባቷ አቶ በዳዳ ፈይሳ ተናግረዋል።

    የሃይማኖት አባት አቶ በዳዳ ፈይሳ ልጃቸው 2009 ዓ.ም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በ’ክሊኒካል ፋርማሲስት’ በማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርስቲው በመምህርነት ስታገለግል መቆየቷን ያስታውሳሉ። ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንደነበረች ይናገራሉ።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) እና ቢቢሲ አማርኛ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ሃይማኖት በዳዳ

    Anonymous
    Inactive

    የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እህተ ማርያም በሌሎች ወንጀሎችም በመጠርጠሯ ምርመራውን እያጠናከረ መሆኑን ገለጸ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ራሷን ንግሥተ ነገሥት (እህተ ማርያም) እያለች በምትጠራው ትዕግሥት ፍትህአወቅ ላይ የአስቸኳይ አዋጁን ከመጣስ በተጨማሪ በሌሎች ወንጀሎችም በመጠርጠሯ ምርመራውን እያጠናከረ መሆኑን ገለጸ።

    በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀል ዲቪዥን ምርመራ ኃላፊ ኢንስፔክተር በድሉ ግርማ ትዕግሥት ፍትህአወቅ (እህተ ማርያም) ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነቴንና ቀኖናዬን አቃላለች መገልገያ አልባሳቴን ያለ አግባብ ጥቅም ላይ አውላለች በሚል ያቀረበችው ክስም በምርመራው እየታየ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ግለሰቧ ሃይማኖትም ሆነ ማኅበር ለመመሥረት ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) የሰላም ሚኒስቴር ተገቢውን ፈቃድ ሳታገኝ ርትዕት ተዋሕዶ የሚል ሃይማኖት መሥርታ ተከታዮቿን አላግባብ እየሰበሰበች የነበረበት ሂደትም እየተመረመረ ነው ተብሏል።

    ተጠርጣሪዋ የትዳር አጋሯ በትራፊክ አደጋ እንደሞተ ብትገልጽም የሟች ቤተሰቦች ይህ ስለመሆኑ ምንም ማስረጃ ባለመኖሩ ተጨማሪ ምርመራ ይደረግልን ማለታቸውም ምርመራው የሚያተኩርበት ሌላ ጭብጥ መሆኑንም ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።

    በተጠርጣሪዋ ቤት የተገኘው አስከሬንም ለምርመራ ወደ ሆስፒታል መላኩንም ኢንስፔክተር በድሉ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ሌሎች ዜናዎች፦

    እህተ ማርያም

    Anonymous
    Inactive

    የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ራሷን ንግሥተ ነገሥት ብላ በምትጠራው ግለሰብ (እህተ ማርያም) ላይ ምርመራ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ

    ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻውን እህተ ማርያም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋ በቁጥጥር ስር ስትውል አብረው ፖሊስ ጣቢያ ድረስ የመጡ 30 የሚጠጉ ተከታዮቿ ግርግር ሊፈጥሩ ቢሞክሩም ፖሊስ መክሮ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።

    በጥላሁን ካሣ (ኢብኮ) |

    አዲስ አበባ – የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ራሷን “ንግሥተ ነገሥት ዘ–ኢትዮጲያ” ብላ በምትጠራው እና የአራት ልጆች እናት በሆነችው እህተ ማርያም ላይ ምርመራ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ። ፖሊስ ግለሰቧን በቁጥጥር ስር ያዋላት ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. (የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የወታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣሷ ምክንያት) ነበር።

    ከሁለት ዓመት በፊት ባሏ በሞት የተለያት የ43 ዓመቷ እህተ ማርያም በሚል መጠሪያ የምትታወቀው ሴት ስለ ማንነቷ ለፖሊስ ስትገልጽ፥ ትክክለኛ መጠሪያ ስሟ ትዕግሥት ፍትህአወቀ አበበ መሆኑንና መኖሪያዋ አዲስ አበባ ውስጥ ኮልፌ መብራት ኃይል አካባቢ እንደሆነ ተናግራለች።

    ግለሰቧ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ በመኖሪያ ቤቷ በሃይማኖት እና በምገባ ስም እስከ መቶ የሚደርሱ ሰዎችን ሰብስባ በመገኘቷ በቁጥጥር መዋሏ ይታወቃል።

    በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር በድሉ ግርማ፥ ተጠርጣሪዋ እህተ ማርያም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ኮሮናቫይረስ የለም ተሳሳሙ፣ ተቃቀፉ፣ ተጨባበጡ በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመፃረር የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ አጋልጣለች በሚል መጠርጠሯን ገልጸዋል። አክለውም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የተጠረጠረችበት ወንጀል ጉዳይ እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል።

    ተጠርጣሪዋ በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መሀል ላይ የሚገኘውን ኮከብ ቀድዳ አውጥታ በማቃጠሏ መቀጣቷም ተጠቅሷል። ግለሰቧ ከሰማይ ታዝዣለሁ (የማደርገውን ሁሉ የማደርገው ከሰማይ በሚመጣልኝ መልእክት ነው) በማለት ማረሚያ ቤት ድረስ በማቅናት ታራሚዎችን ልታስወጣ ስትሞክር እጅ ከፍንጅ ተይዛ መቀጣቷንም ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።

    ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋ በቁጥጥር ስር ስትውል አብረው ፖሊስ ጣቢያ ድረስ የመጡ 30 የሚጠጉ ተከታዮቿ ግርግር ሊፈጥሩ ቢሞክሩም ፖሊስ መክሮ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም አመልክተዋል። ከእርሷ ጋር በግብረ አበርነት የተጠረጠሩ ሁለት ሴቶች ግን ምርመራ እየተካሔደባቸው መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተር በድሉ ግርማ ተናግረዋል።

    ግለሰቧ ለፖሊስ በሰጠችው የእምነት ክህደት ቃል ርትዕት ተዋሕዶ የተሰኘ ሃይማኖት ለማስተዳደር ከሰማይ እንደተላከች እና ራሷም ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ መሆኗን ተናግራለች።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ንግሥተ ነገሥት እህተ ማርያም

Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)