-
Search Results
-
በጉራጌ ዞን የመስቀል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ተጀመረ
(የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ)
በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው። የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ፥ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የዘንድሮውን የዋዜማ ዝግጅት በዞኑ ቸሃ ወረዳ የጠናቃ ቀበሌ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ከመስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት መከበር ተጀምሯል።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ታዳሚዎችን እንኳን አደረሳችሁ በማለት “የመስቀል በዓል የኛነታችን መገለጫ ነው፤ የመስቀል በዓል ትውፊታዊም መንፈሳዊም ነው። በመስቀል በዓል የእርስ በእርስ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላም እንዲሆን የመልካም ምኞት ማብሰሪያ አበባ የሚሰጣጡበት ጊዜ ነው። እንዲሁም በሥራም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ተራርቆ የቆየ ሰው የሚገናኝበት፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጠያየቅበት፣ የሚረዳዳበት እንዲሁም አዲስ ጎጆ የሚቀለስበት ጊዜ መሆኑ ማኅበረሰባችን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። አያይዘውም በበዓሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን በደንብ አልምተን እንደ አንድ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ በማድረግ ለሀገራዊ ብልጽግናችን መሠረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።
የመስቀል በዓል ከሀይማኖታዊ ክዋኔ ባሻገር ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር ቢሆንም መስቀል በጉራጌ በተለየ የአከባበር ሁኔታ ይከበራል ብለዋል – አቶ መሐመድ።
እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ እንደ መስቀል ያሉ ቱባ ባህሎቻችን ታሪካቸው ሳይሸራረፍ ለትውልድ በማስተላለፍ ዘረኝነት፣ ጥላቻና ቂም በቀል በማስወገድ የሀገራችን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
መርሀ-ግብሩን በጋራ ያዘጋጁት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የጉራጌ ዞን አስተዳደር እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመተባበር ሲሆን፥ የዚህ ክብረ በዓል አከዋወን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /UNESCO/ ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ባህላዊ እሴቶች (“intangible heritages of Ethiopia”) ተርታ መመዝገቡን በማስመልከት ሲሆን፥ በአከባበሩ ሥርዓት ውስጥ ያሉት ትውፊቶች በትውልድ ቅብብሎሹ ውስጥ ተጠብቀው ያለ ምንም ተፅዕኖ ክዋኔዎቹ እየቀጠሉ እንዲሄዱ የማስተማር ዓላማ ያለው እንደሆነ ተነግሯል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ እስከዳር ግሩም በበኩላቸው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም በተገቢው ማልማትና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ እንዳላደገ ገልጸዋል።
አንድነታችን አጠናክረን ሀብቶቻችን ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ አለብን። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ያደርገዋል። በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
የቸሀ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፈለቀ የመስቀል በዓል በጉራጌ ሁሉም በድምቀት ከማክበር ባለፈ የጉራጌ እሴት የሚገለፅበት በመሆኑ የረጅም ጊዜ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግበት በማስታወስ፤ በዓሉንም በድምቀት ለማክበር ሁሉም የቤተሰብ አባል የድርሻውን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚከበር ገልጸዋል።
ለበዓሉ ማብሰሪያ የጉራጌ ዞን የባህል ቡድንም ያሰናዳቸውን ሙዚቃዊ ክዋኔዎች እንደነ “ጊቻዌ፣ ጊቻዌ”፣ “አዳብና” የመሳሰሉት ተውኔታዊ ክዋኔዎች በሴቶችና ወንዶች የታየበት፣ የሥራ ባህልን፣ ሠርቶ ማደግን የሚያወድሱ፣ የሚያስተምሩ ማሳያዎች፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በአንድነት በአብሮነት ባህላዊ እሴቶች የሚጎለብቱበት ተውኔታዊ ትዕይንቶች የተንፀባረቁበት ነበር።
ጉራጌ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የክልሉ መንግሥት በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው የብሔሩ ተወላጆች ጠየቁ።
ኧዣ ወረዳ ፥ጉራጌ ዞን (ሰሞነኛ) – የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው ከጉራጌ ማኅበረሰብ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጉራጌ ዞን ኧዣ ወረዳ በደሳለኝ ሎጅ ውይይት አካሄዱ። የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጉራጌ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ በሰላማዊና በሰለጠነ መልኩ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ።
በጠንካራ የሥራ ባህሉና ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተግባብቶ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የቆየ ልማድ ያለው የጉራጌ ብሔር ባለፋት 27 ዓመታት በማኅበራዊ፣ በፓለቲካዊና በኢኮኖሚው ከፍተኛ በደልና ጭቆና ሲደርስበት እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ አሁን በመጣው የሀገሪቱ ለውጥ ፍትሃዊ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ተጠቃሚነቱ ሊረጋገጥለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አክለውም ብዙ ጊዜ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲነሳ ጉራጌ ክልል አያስፈልገውም የሚል አስተያየት የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፥ ክልል የማያስፈልግ ከሆነ አሁን ያለው የዞን አስተዳደር ለምን ያስፈልጋል፣ ጉራጌ በክልል ቢደራጅ ስጋቱ ምንድን ነው የሚል ጥያቄዎች ተነስተው በመድረክ አወያዮቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንደገለጹት፥ ዞኑ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ስትሆን መንግሥት እንኳ ባይኖር ሕዝቡ ራስ በራሱ መምራት የሚችልበት ቱባ ባህል፣ እሴትና እምነት እንዲሁም ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ያለው ነው ብለዋል።
የዞኑ ሰላም ለማስጠበቅ የሀይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች እየሠሩት ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ መሀመድ፥ በቀጣይም የሕዝቦች አንድነት ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ጉራጌ በክልል የመደራጀት ጥያቄ የሚጠይቀው ለቅንጦት ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ስለሆነ መንግሥት አፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ አቶ መሀመድ ጠይቀዋል።
በክብር እግድነት የዞኑ ማኅበረሰብ ለማወያየት የመጡት የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደተናገሩት፥ የጉራጌ ብሔር ለሥራ እንጂ ለግጭትና ለንትርክ ጊዜ የሌለው ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰብ ጋር ተከባብሮና ተዋዶ በፍቅር የሚኖር ነው ብለዋል። ጉራጌ በክልል እንዲደራጅ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አሁን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልስ መስጠት እንደማይችሉና በቀጣይ በመመካከር ለህብረተሰቡ ምላሽ እንደሚሰጠው አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ እንደተናገሩት፥ በመስቃን ቤተ ጉራጌና በማረቆ መካከል የተፈጠረው ግጭት ለመፍታት ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በአጭር ጊዜ መፍትሄ ያገኛል ብለዋል።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝቡ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲመልሱ እንደተናገሩት፥ ጉራጌ በክልል የመደራጀት መብት እንዳለው ጠቁመው ጥያቄው የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ በማያደናቅፍ መልኩ መሆን አለበት በማለት አቋማቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የደቡብ ክልል የካቢኔ አባላት፣ ከአዲስ አበባ የመጡ አመራሮችና ተወላጆች፣ ባለሀብቶች፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ነበሩ ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ነው።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አቶ ርስቱ ይርዳው በሹመት ንግግራቸው “ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ በሚሹበት ሰዓት ቢሆንም፤ የሕዝቦችን ኃላፊነት በመቀበሌ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
ሀዋሳ (ሰሞነኛ) – የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዘጠነኛ መደበኛ ጉበኤው የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሾምና ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ የርዕሰ መስተዳድር ለውጥ እንዲደረግ በወሰነው መሠረት አቶ ርስቱ ይርዳው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲመሩ ሾሟቸዋል።
በተጨማሪም ደኢህዴን ለ2012 በጀት ዓመት 40 ቢልዮን 56 ሚሊዮን 938 ሺህ 826 ብር አጽድቋል። በጀቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።
የበጀቱ ምንጭ ከፌዴራል መንግሥት ድጎማ፣ ከውጭ እርዳታና ከክልሉ ገቢ እንደሚሰበሰብ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ ገልጸዋል።
አቶ ርስቱ ይርዳው በሹመት ንግግራቸው ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብና ሠላምን ማስፈን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል። በመልዕክታቸው “ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ በሚሹበት ሰዓት ቢሆንም፤ የሕዝቦችን ኃላፊነት በመቀበሌ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
ከደኢህዴን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጣሉባቸውን እምነት፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን በማገልገል ለመወጣት ቅን ፍላጎት እንዳላቸው አቶ ርስቱ ይርዳው ገልፀዋል።
በክልሉ የተነሱ የክልልነትና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለክልሉና ለደህኢዴን ከባድ ፈተና ስለመሆናቸው ያነሱት አቶ ርስቱ፥ የተፈጠሩትም ሁከቶች ከባድ ጉዳት ያደረሱና የአብሮነት ሕልውናን የተፈታተኑ ነበሩ ብለዋል።
በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ሰላም የማስፈንና ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ መሆናቸውንም አቶ ርስቱ ገልፀዋል።
አቶ ርስቱ በሹመት ንግግራቸው “የብሔር ፅንፈኝነትን፣ የሀይማኖት አክራሪነትን እና ሕገ ወጥነት ለመከላከል ጠንካራ ሥራ ይሠራል” ብለዋል።
የአመራር ማስተካካያዎችም በጥብቅ ትኩረት እንደሚከናወንም ነው አቶ ርስቱ በንግግራቸው ያስገነዘቡት።የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ርስቱ፥ ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት በመግለፅ፣ የእንደጋገፍ ጥሪ ለባለ ሀብቶቹ አቅርበዋል።
አቶ ርስቱ ይርዳው ከ1985 እስከ 2001 ዓ.ም. በክልሉ ጉራጌ ዞን ከወረዳ አመራርነት እስከ ዞን አስተዳዳሪነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የደኢህዴን ሥራ አስፈፃሚ እና በፌደራል ደረጃ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተካሄደው የሰላም ንቅናቄ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ እና በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል።
ወልቂጤ (ሰሞነኛ)– “ጥበብ ለሰላም” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን ከሚገኙ 17 ወረዳዎችና ከ4 ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአገራችን ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ አመራሮች፣ የሲቪል ሰርቪስ (civil service) ሠራተኞች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ትልቅ ስብሰባ/ውይይት በድምቀት ተካሂዷል።
በዚህም ዞን አቀፍ የሰላም ንቅናቄ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች (በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ደራሲ እንዳላጌታ ከበደ፣ ደራሲ ህይወት ተፈራ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራልና የሙዚቃ ሀያሲው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት እና ደራሲ ተስፋዬ ጎይቴ ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል። የሁሉም የመቋጫ ሀሳብ የአገራችን ህዝቦች አጥር ሳይገድባቸው በብሔር፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በሀይማኖትና በመሳሰሉ ከፋፋይ ጉዳዮችን ትተው በአንድነትና በሰብዓዊነት ስሜት ተዋደውና ተቻችለው እንደቀድሞው አብረው ሊኖሩ እንደሚገባ ነው።
በዚህ ታላቅ የሰላም ንቅናቄ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማልና የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ ሰላም ለሁሉም ጉዳዮች መሠረት መሆኑ እና ሰላም በሌለበት ምንም ሊኖር እንዳማይችል ገልፀው የዞኑ ህዝብ በሙሉ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“ጥበብ ለሰላም” በሚል በተካሄድው በዚህ መርሀግብር ታዋቂ የአገራችን ደራሲያን፣ የጉራጌ ዞን የባህል ኪነት ቡድን፣ ከወልቂጤና ከቡታጅራ ከተማ አስተዳደሮች የኪነ ጥበብ ክበባት የተውጣጡ አማተር ኪያንያን ድንቅ የሙዚቃ፣ ድራማና የሥነ ግጥም ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። እንዲሁም በሱዑዱ አብደላ የተሳሉ ድንቅ የሥነ ስዕል ሥራዎቹን አቅርቧል። የ11ኛ ክፍል ተማሪ ይዘዲን የፈጠራ ሥራዎች በመድረኩ ከቀረቡ ሥራዎች ይገኝበታል።
በመጨረሻም ለፕሮግራሙ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ያዘጋጃቸው ባህላዊ ስጦታዎች፣ የማበረታቻ ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር ― ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
- መርፌ ጨርቅ እንጂ አለት አይበሳም ― ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የምክር ደብዳቤ
- አጣየ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ እና አካባው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች እያደረሱት ያለው ኢ-ሰብአዊ በደል
- ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በሙዚቃ ሥራ ምርምርና ጥናት ውስጥ ቀዳሚ ኢትዮጵያዊ ናቸው ― አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት
- ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ መንግስት ስለጀመረው ለውጥ እና የሚታዩትን ጉድለቶች አብሮ በመሆን ስለመሙላት (በወልቂጤ ከተማ)
በቤተ ጉራጌ ዘንድ በወጌሻ ሕክምና ሙያቸው ስማቸው እጅግ ከፍ ብሎ የሚጠራው አቶ ፈንቅር ሳረነ ሲሆኑ፥ ይህም ሙያ ከእርሳቸው አልፎና ከልጅ ልጆቻቸው ተዋርሶ፣ አሁን የልጅ ልጆቻቸው በቤተ ጉራጌ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እያገለገሉ ይገኛሉ። አቶ መኮንን አመርጋ ደግሞ የአቶ ፈንቅር ሳረነ አራተኛ የልጅ ልጅ ናቸው።
ኑሬ ረጋሳ (የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)
ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – ከባህላዊ የሕክምና ዘዴዎች ውስጥ የወጌሻ ሕክምና አንዱ ነው። የሰዉ ልጆች በተለያዩ ምክንያቶች በአካላቸዉ ላይ የተለያዩ አደጋዎች ይገጥማቸዋል። በአንድ ወቅት በወጌሻ ፈንቅር ሳረነ በሰውነታቸው ላይ እባጭ ወጥቶባቸው ሁለተኛ ወገን ባለማግኘታቸው በቻሉት አቅም ራሳቸውን አክመው እባጩን በማዳናቸው ምክንያት አድርገው የጀመሩት የባህላዊ ወጌሻ ሙያ ከልጅ ልጅ እየተላለፈ አሁንም ድረስ የፈንቅር ሳረነ የልጅ ልጆቻቸው ከቤተ ጉራጌ ክልል አልፈው በሌሎችም ቦታዎች ህብረተሰቡን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አቶ ፈንቅር ሳረነ የተወለዱት በ1814 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ኧዣ ወረዳ የወግወረ በቢባል አካባቢ ነበር። የአካባቢው ማህበረሰብ አንደግባ የሚል የክብር ስም ሰጥቷቸዋል። በባህላዊ ሕክምና ህዝቡን የማገልገል እሳቤ ይዘው ወደ ወጌሻነት ሙያ የገቡት ፈንቅር ሳረነ ለዘመናት ህዝቡን አገልግለዋል። የወጌሻነ ሕክምና አገልግሎታቸው እና ከተለያዩ እፅዋት በባህላዊ መንገድ በመቀመም የሚያዘጋጇቸው መድኃኒቶች እስከ በጊዜው እስከ ቤተ መንግስት ድረስ አድርሷቸዋል። ፈንቅር ሳረነ የ8 ወንድ ልጆችና የአንድ ሴት ልጅ ወላጅ አባት ሲሆኑ ለአብነት ያህል ካቤ ፈንቅር ሳረነ፣ ጫሚሳ ፈንቅር፣ ድድራ ፈንቅር፣ ገብረማሪያም ፈንቅር፣ እንዱሁም ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ወጌሻ መኮንን አመርጋ የአራተኛ የልጅ ልጅ (ማለትም ፈንቅር፣ መኮንን አመርጋ ጫሚሳ ፈንቅር) ሲሆኑ፥ እሳቸውም በሚሰጡት የወጌሻነት ሕክምና አገልግሎት አንቱታን አትርፈዋል።
ወጌሻ መኮንን አመርጋ እንደሚሉት በባህላዊ ሕክምና ሙያ፣ ልምድና ዕውቀት የቀሰሙት የልጅ ልጅ በሆኑት በወጌሻ ወልዴ ጫሚሳ እንደሆነና ወጌሻ ወልዴ ጫሚሳ ከቤተ ጉራጌ ክልል አልፈው እስከ ስልጢ ድረስ እየዞሩ ያገለግሉ እንደነበረም ተናግረዋል። ድርድራ ፈንቅር ከጅማ እስከ ከፋ ድረስ የባህላዊ ሕክምና ሲሰጥ እንደነበረ እንዲሁም የካቤ ፈንቅር ልጆች (ለምሳሌ ዜናዬ ካቤ፣ መዝገበ ካቤ) አዲስ አበባ ላይ አገልግሎት እንደሰጡ፤ በወሊሶና አካባቢው ደግሞ ተክሌ ሙራረ በአግባቡ የወጌሻነት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ይሰጡ እንደነበረም አስረድተዋል። የልጅ ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ ዙሪያሽ ደግሞ አጠቃላይ ቤተ ጉራጌ በአካለለ መልኩ ቸሃ ላይ መቀመጫ አድርገው ይሠሩ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
◌ የEBS ቴለቭዥን አርአያ ሰብ መርሀግብር በፈንቅር ሳረነ የሕይወት ታሪክ ላይ የሠራውን ጥንቅር እዚህ ጋር ይመልከቱ
የወጌሻነት ሙያ ከአጎታቸው የተማሩት መኮንን አመርጋ ወልቂጤ ከተማ ላይ በመምጣት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ወልቂጤና አካባቢዋ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገልገል ተጠቃሽ የሆነው ወጌሻ መኮንን አመርጋ ለበርካታ ዓመታት ቤታቸው ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ የህብረተሰብ ማለትም በስፖርታዊ ውድድሮች ተሰብሮና እግሩ ወልቆ ለሚመጣ፣ የተሸከርካሪ አደጋ ለደረሰበት፣ ውልቃትና መሰል አደጋ ለደረሰበት ሰው አገልግሎት በመስጠት ይታወቃሉ።
ወጌሻ መኮንን አመርጋ የወልቂጤ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ብሔራዊ ሊግ እያለ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ያህል በወጌሻነት በማገልገል ለስፖርተኞች ጥሩ ወንድማዊ ፍቅርን በመለገስ በጫወታ ወቅት የሚደርስባቸው ጉዳት በማከም ስፖርተኞች ውጤታማ እንዲሆኑና አሁን ለደረሱበት ከፍተኛ ሊግ በሙያቸው የበኩላቸውን ሚና ተወጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለበርካታ ዓመታት የወረዳውና የዞን ውድድሮችን እንዲሁም በየዓመቱ በሚደረጉ የትምህርት ቤቶች ውድድሮች ላይ ሳይሰለቹ በቅንነት በማገልገል ስማቸው ከምስጋና ጋር ይነሳል።
ለሙያው እና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ባላቸው ክብር የተነሳ በጣም ጉዳት ደርሶበት ውይም ደርሶባት መኖሪያ ቤቱ መምጣት የማይችሉት ጉዳተኞች እስከ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ ሙያዊ እገዛ በማድረግ ይታወቃሉ – ወጌሻ መኮንን። አንድ ባለ ጉዳይ አገልግሎቱን ለማግኘት ከመጣ ገንዘብ እንኳን ባይኖረውም መጎዳትና አካለ ስንኩል መሆን የለበትም በማለት አገልግሎቱን በነጻ በመስጠት በጎነታቸው የሚታወቁት መኮንን ዓመርጋ፥ የወጌሻነት ሙያ ወደ ልጆቻቸው ለማስረጽ ሙያውን ሙሉ ለሙሉ እንዲያውቁት ለማድረግ የዕውቀትና የሙያ ሽግግር የማድረግ ዓላማ ይዘውም ይሠራሉ።
በዚህም የበኩር ልጃቸው የአባቱን የወጌሻነት የጥበብ ትምህርት የእረፍት ጊዜውን በመጠቀም አባቱን በማገዝና ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት በመቅሰም ወይም ትምህርት በመውሰድ፣ ወጌሻ መኮንን ራቅ ወዳለ ቦታ ከሄዱ አገልግሎት ፈልገው ለሚመጡ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነና ሙያውን ሙሉ ለሙሉ አውቆ በእረፍት ጊዜው እየሠራበት እንደሆነም ወጌሻ መኮንን ገልጸዋል።
መንግስት የባህላዊ ሕክምናው ዘርፍ ለማዘመን ነጻ የትምህርትና ስልጠና እድል በማመቻቸት የሕክምናውን ሳይንስ እንዲያውቁት በማድረግ ረገድ ውስንነት መኖሩን አስታውቀው፥ የጤናውን ትምህርት ባይወስዱም ህብረተሰቡን እያገለገሉበት ያለውን የወጌሻ ሙያ ዕውቀታቸውን የበለጠ ለማዳበር ቴክኖሎጂ በመጠቀም እና ሀኪም ጓደኞቻቸውን በማማከር ትምህርት እየተማሩ እንደሆነና በሥራ ላይ የሚገጥማቸውን ውስንነት እየቀረፉ እንደሆነም አስረድተዋል። በሳምንት በርካታ ሕመምተኞች በቀላልና ከባድ አደጋ ቤት ድረስ መጥተው አገልግሎት እንደሚያገኙ የተናገሩት መኮንን ዓመርጋ በከተማው ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት የሚሰጡት በመኖሪያ ቤታቸው ሲሆን መንግስት በከተማው ሴንተር ቦታዎች ላይ ቋሚ መሥሪያ ቦታ ቢያመቻችላቸው የበለጠ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል።
የወጌሻ ሙያ ከጀመሩ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠሩት መኮንን በሥራ ላይ ብዙ ገጠመኞች እንደገጠማችው አስታውሰው ለአብነት ያህል በአንድ ወቅት በእግር ኳስ ሜዳ ላይ አንድ አጥቂ ጎል ለማግባት ሲል እርስ በእርስ ተጋጭተዉ ላንቃው ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ምላሱን ማንቀሳቀስ አቅቶት ሊሞት ሲል አንደምንም ርብርብ አድርገን አፉን በመክፈት በባንድራ እንጨት አፉን በመክፈት ወደ ሕክምና ማእከል በመውሰድ እንዳዳኑትም ተናግረዋል።
አቶ ኢሳያስ ናስር ቀደም ሲል የወልቂጤ ከነማ ሥራ አስኪያጅ የነበሩ ሲሆ ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ ከሕክምናው ሙያው በተጨማሪ ክለቡን ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ መስዋትነት የከፈሉ ምርጥ ባለሙያ ናቸው ብለው ይመስክሩላቸዋል። አክለውም፥ ስፖርተኞች የከፋ አደጋ እንኳን ቢደርስባቸው ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን በመጠቀም የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ ጉዳት የደረሰባቸው ሲታደጉ ነው የሚታዩት። ከስፖርተኞች ጋር ጥሩ ፍቅር በማሳየት ከብሔራዊ ሊግ ጀምሮ ክለቡ አሁን ለደረሰበት ሁኔታ የአንበሳውን ሥራ ሰርተዋል፤ አሁንም ድረስ በበጎ ፍቃደኝነት በሙያው አገልግሎት በመስጠት ናቸው በማለት የወጌሻ መኮንን አመርጋ ታታሪነት ይመሰክራሉ። አቶ ኢሳያስ በመቀጠልም የሙያና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ መንግስት እነዚህ የወጌሻ ባለሙያተኞች በተገቢው ምቹ የሥራ ቦታ ቢያመቻችላቸው የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።
አንዳንድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ ቅንና ለሙያው ክብር ሰጥተው የሚሠሩ ባለሙያ እንደሆኑ፣ ሰውን ለማዳን እንጂ ገንዘብ ማትረፍን ዓላማ አድርገው የማይሠሩና አቅም ለሌላቸው በነጻ ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ ከህመማቸው እንዲድኑ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ባለሙያ መሆናቸውን ይመሰክሩላቸዋል። የዚህ ጹሁፍ አዘጋጅም ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ በሙያው ያላቸውን የካበት ልምድ እና ህብተረሰቡን ለማገልገል ያላቸውን ከፍተኛ ፈላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሙያው ያላቸውን መልካም ፍቃድ የበለጠ አጠናክሮ እንዲሰራበትና በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲታደግ እያልኩኝ ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ መንግስት በዘርፉ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ የመስሪያ ቦታ እንዲያመቻችለት እና ተተኪ ባለሙያተኞች መፍጠር ይኖርበታል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ። የጃፓን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት ያስችላል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ (Daisuke Matsunaga) የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።
በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።
እነዚህ አራት የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።
በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ መለገሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የእርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስ እና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል።
የጃፓን መንግስት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል።
በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፤ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል።
በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በስሩ ያቀፋቸው ቤተ-መጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው። በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል።
እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ኢዜአ እና ሪፖርተር ጋዜጣ
በሐረር የሚኖሩ የጉራጌ ህብረተሰብ አባላት በመስቃን እና ማረቆ በተፈጠረው ግጭት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ስልሳ ኩንታል ሩዝ እና አስር ኩንታል የፉርኖ ዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸዉና ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ1 መቶ 41 ሺህ ብር በላይ ነው።
ሀረር (ሰሞነኛ) – በሐረር የሚኖሩ የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች በመስቃን እና በማረቆ ብሔረሰብ አባላት መካከል በተፈጠረዉ ግጭት ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከአንድ መቶ ሺህ (100,000) ብር በላይ ድጋፍ ማበርከታቸው ተገለጸ።
በግጭቱ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዉ በአንድ ማዕከል እየተረዱ እንደሆነም ተዘግቧል።
በሐረር ከተማ የጉራጌ ማህበረሰብ የድጋፍ አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዱላ ሟኖጂ በርክክቡ ወቅት በሰጡት አስተያየት ለዘመናት ተዛምደውና ተከባብረው በሚኖሩ በመስቃንና ማረቆ ህብረተሰብ መካከል በተፈጠረዉ ግጭት ለጠፋው የሰዉ ሕይወትና ለወደመው ንብረት እጅግ ማዘናቸዉም ገልፀው፥ ተፈናቅለዉ የሚገኙ ወገኖችም መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚችለው መንገድ (በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ ወዘተ) ተገቢዉን ድጋፍ ሊያደርግላቸዉ ይገባል ብለዋል።
አሁን የተፈጠረው የለዉጥ ሂደት ባልጣማቸውና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተከባበረው እንዲኖሩ የማይፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች ቡድኖች በጠነሰሱት ተንኮል ምንም የማያዉቁ ጨቅላ ሕፃናት፣ እናቶች፣ እንዲሁም አቅመ ደካሞች መሰቃየታቸውና ቀዬአቸውን ጥለው መፈናቀላቸው በጣም ልብ የሚነካ ነዉ ብለዋል።
መንግስት እንደሀገር የጀመረውን አብሮ የመኖር (‘የመደመር’) አሰተማሪ እርምጃ አጠናክሮ በማስቀጠል ሕይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድምና ዜጎች ከቀዬአቸው አንዲፈናቀሉ ያደረጉ አካላትና ድርጊቱን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፈጸሙ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በአስቸኳይ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብለዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከወራት በፊት የጀመረችውን የጀመረችውን የለወጥ ጎዞን ለማደናቀፍ ሕዝቡ የሚያነሣቸ የወሠንና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄዎችን በተሳሳተ ወይም አጥፊ በሆነ መንገድ በማሳየት ሕዝቡን ወደ እልቂትና የማያባራ ግጭት እንደገባ የሚየደርጉ አካላትን ከየተኛውም ወገን ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር አጋልጦ መስጠት አንዳለበት አሳስበዋል።
በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የቤተ ጉራጌዎች እምቅ አቅም ከዞኑ አልፈው ከጂግጂጋ፣ በቡራዪና በተለያዩ አካባቢ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማድረጋቸው አሰታዉሰዉ አሁንም በዞኑ በተለያዩ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ እንዲሁም ከመኖርያ መንደራቸው ወገኖችን ለማቋቋም የሚደረገው ደጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ ዱላ ሟኖጂ አሳስበዋል።
በሐረር የሚኖሩ ቤተ ጉራጌዎች በመስቃንና ማረቆ በተፈጠረው ግጭት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ስልሳ ኩንታል ሩዝ እና አስር ኩንታል የፉርኖ ዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸዉና ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ1 መቶ 41 ሺህ ብር በላይ እንደሆነም አስረድተዋል።
በመጨረሻም ለወገን ደራሽ ወገን ነዉና በቀጣይ እነዚህ ወገኖች በቋሚነት እስኪቋቋሙ ድረስ ደጋፋቸዉን አጠናከረዉ እንደሚቀጥሉ የኮሚቴዉ ሰብሳቢ አቶ ዱላ ተናግረዋል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን ግንኙነት ጽህፈት ቤት | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Search Results for 'ጉራጌ ዞን'
Viewing 12 results - 1 through 12 (of 12 total)
Viewing 12 results - 1 through 12 (of 12 total)