Home › Forums › Semonegna Stories › የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
- This topic has 54 replies, 3 voices, and was last updated 1 year, 9 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
September 24, 2020 at 3:18 am #16004SemonegnaKeymaster
የተባበረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወደፊት!
ከባልደራስ – መኢአድ ቅንጅት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫኢትዮጵያ ሀገራችን ከገባችበት ምስቅልቅል ፓለቲካዊ ችገሮች ለማውጣት በቅንጅት መሥራት አስፈላጊነቱን የተረዱት የመላው ኢትዮጽያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም በመኢአድ ጽሕፈት ቤት ባደረጉት ስብሰባ ሁለቱ ፓርቲዎች በቅንጅት ለመሥራት ያደረጉትን ስምምነት ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የባልደራስ – መኢአድ ቅንጅት ተመሥርቶ ለሕዝብ ይፋ በተደረገ በቀናት ውስጥ ዓለም-አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ /COVID-19/ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከ4 ሰው በላይ መሰብሰብ በመከልከሉ 20 አባላት ያሉት የቅንጅቱ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ለማድረግ ተቸግሮ ቆይቷል::
የሁለቱ ፓርቲዎቸ ቅንጅት አላማ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የፖለቲካና የልሂቃን ክፍፍል በማጥበብ፥ ብሎም በሚመጣው ምርጫ ላይ ተቀናጅቶ በመወዳደር አብላጫውን የሕዝብ ድምጽ ይዞ መንግሥት በመመሥረት ሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነቷና ሕብረቷ ተጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ ብሎም ከፍተኛ የሆኑ ሀገራዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያችን በሰላምና በልማት ጎዳና ላይ ከፍ ብላ እንድትራመድ ለማድረግ ነው።
የባልደራስ – መኢአድ የጋራው ምክር ቤት መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የቅንጅቱን ፕሬዝደንት፣ ምክትል ፕሬዝደንት እና ሥራ አስፈፃሚውን በሙሉ ድምፅ መርጧል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ለሦስት አስርት ዓመታት በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ አቶ እስክንድር ነጋ አድልዎንና ኢፍትሃዊነትን በብዕራቸው በመታገል የሚታወቁት ናቸው። ነገር ግን ዛሬም እንደገና ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ይህ ውንጀላና እስር በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እንደሆነ የሚያምነው የባልደራስ – መኢአድ ከፍተኛው ምክር ቤት ጥልቅ ውይይት ካካሄደ በኋላ ክቡር አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ሆነውም ቢሆን የባልደራስ – መኢአድ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። እኚህን የሕዝብ ልጅና መሪ መንግሥት በፍጥነት ከእስር እንዲለቅም ምክር ቤቱ በጽኑ አሳስቧል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸውና በተደጋጋሚ ለእስር የተዳርጉትን የነፃነት ታጋዩን አቶ ማሙሸት አማረን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የመረጠ ሲሆን፥ አቶ ማሙሸት አማረ ለሕግ የበላይነት ለዴሞከራሲ ሥርዓት ግንባታ የከፈሉትን ወደር የሌለው መስዋዕትነትና ቁርጠኝነት የቅንጅቱ ምክር ቤት ያደነቀ ሲሆን፥ በቀጣይነት ትግሉን በመምራት ቅንጅቱ በአሸናፊነት እንዲወጣ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ምክር ቤቱ እምነቱን ገልጿል።
ምክር ቤቱ ለሌሎች ፓርቲዎችም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ ከባልደራስ – መኢአድ ጋር አብሮ ለመሥራት የጠየቁትን ፓርቲዎች በቅርቡ አብሮ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚጀምር የገለጸ ሲሆን፥ ሌሎች ከቅንጅቱ ጋር ለመሥራት ፍላጎት ያላቸውን ፓርቲዎች የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ቅንጅቱን እንድትቀላቅሉ ሲል ጥሪውን አቅርቡዋል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከቅንጅቱ ጎን በመሆን ያልተቆጠበ ድጋፉን እንዲሰጥ በታላቅ ትህትና ጥሪውን አቅርቧል።
ምክር ቤቱ በመጨረሻም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን፥ በቅርቡ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በንጹሃን አርሶ አደር ወገኖቻችን ላይ ማንነትን መሠረት ባደረገው ጭፍጨፋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ እና ለመላው ሕዝባችን አምላክ መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን ሲል ተጎጅዎችን ያጽናናል። ምክር ቤቱ ይህንን ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ እያወገዝ፥ መንግሥት ሙሉ ኃላፊንቱን ይወስዳል ሲል አሳስቧል። በወልጋ፣ በሚዛን ቴፒ፣ በሐረር፣ በደራና በሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁ ቡድኖች አማካኝነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ሲሆን፥ በቀጣይም አስከፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የመከላከል እርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክር ቤቱ ያሳስባል።
በሌላ በኩል በጎርፍ መጥለቅለቅ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይም በመተሃራ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እንዲሁም በጣና ዙሪያ ባሉ ጉማራና ርብ ወንዞች መሙላት በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ህይወታቸውንና ንብረታቸው ላጡ ወገኖቻችንም ከልብ ማዘናችንን እየገለጽን፥ መላው ሕዝባችን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በአኩሪ ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍ ባህላችን በመደገፍ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል።
ዓለም-አቀፍ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ /COVID-19/ ወደ ሀገራች መግባቱን ተከትሎ የበሽታውን ወረርሽኝ ለመግታት መላው ሕዝባችን ሳይዘናጋ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ምክር ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።
በመጨረሻም የሀገራችንን ኢትዮጵያ መፃዒ ዕጣ-ፈንታ የተሻለ ለማድረግ በምናደርገው ወሳኝ ትግል ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የምትኖሩ የቅንጅቱ ደጋፊዎች የሚጠበቅባችሁን ትግል እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም
የባልደራስ – መኢአድ ቅንጅትOctober 3, 2020 at 7:34 pm #16189SemonegnaKeymasterኢዜማ በአባላቱ ላይ እየደረሰ ስላለው እስር እና እንግልት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አቤቱታውን አቀረበ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማክሰኞ፥ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በተለያዩ ክልሎች በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ እየተፈፀሙ ስላሉ እስር እና እንግልቶች ውይይት ካደረገ በኋላ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድብዳቤ እንዲፃፍ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ደብዳቤው እንደተፃፈና ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደተላከ የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለዜጎች መድረክ ገለፁ።
ኃላፊው፥ ኢዜማ ምሥረታውን ካደረገበት ጊዜ አንስቶ እዚህም፣ እዚያም ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበርና አብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይም የጸጥታ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። ፓርቲያቸው በእነዚህ ችግሮች ውስጥ በማለፍ አባላቶቹን በማደራጀት መዋቅሮቹን ሲዘረጋ እንደነበር አውስተዋል። “በማደራጀት ሂደት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የጸጥታ ችግር ይገጥመን ነበር” ያሉት አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፥ የተለያዩ ኢ-መደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶች መዋቅሮቻችንን እንዳንዘረጋ የተለያየ ጫና ያሳድሩብን ነበር ብለዋል።
“የተለያዩ ፈተናዎች ነበሩ፤ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ታልፎ ነው እዚህ ደረጃ የተደረሰው። ለዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አባሎቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለዋል›› ያሉት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፥ በአባላቶቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ እስር እና ጫና ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ በመምጣቱ የተነሳ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ጉዳዩን እንዲመረምርና ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ መፃፍ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።
“አባላቶቻችሁ ሲታሰሩ አልያም እንግልት ሲደርስባቸው ብዙም ስትሉ አይደመጥም አሁን ምን ተፈጥሮ ነው ደብዳቤ ለመፃፍ የወሰናችሁት?” በሚል ከዜጎች መድረክ (በኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት የሚዘጋጅ ሳምንታዊ ጋዜጣ) ለተነሳላቸው ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፥ “የተለያዩ ፈተናዎች ሲገጥሙን ችግሩን ወደ አደባባይ በማውጣት ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት የለንም። አሁንም ቢሆን ችግሩን ከመፍታት አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር እንዲፈታ እንፈልጋለን። ከፖለቲካ አተያይ አንጻርም አባሌ ታስሯል እያሉ አባል ለማፍራት አይቻልም። እኛ ሰላማዊ የሆነ ምህዳር ተፈጥሮ ማንኛውም አካል ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ በነፃ አባል እንዲሆን ነው የምንሻው። እዚህ ጋር አባሌ እንዲህ ሆኗል፤ እዚህ ጋር አባሌ ታስሯል እያሉ አባል ማፍራት ያሰቸግራል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው” ያሉት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፥ ፓርቲያቸው በአሁኑ ሰዓት በመላው ኢትዮጵያ 280 ቢሮዎች እንዳሉትና 435 የምርጫ ወረዳ ላይ አደረጃጀቱን መዘርጋቱን ጠቁመዋል። ፓርቲያቸው ይህንን ሊያሳካ የቻለውም ችግሮች ሲከሰቱ ከመካሰስ ይልቅ በችግሮቹ ውስጥ መውጫን በመፈለግ ላይ በማተኮሩ የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ ክልሎች ላይ በሚገኙ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደርሰው እስራትና እንግልት እያየለ በመምጣቱ የተነሳ በደብዳቤ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኙት ለሚመለከተው አካል አቤቱታቸውን ማስገባታቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እየደረሰ ያለው እስር እና እንግልት እየጨመረ መምጣቱን የሚያነሱት የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፥ በቤንች ማጂ ዞን፣ ቴፒና ጋምቤላ ብቻ ከ30 በላይ አባላቶቻቸው ታስረው እንደሚገኙባቸው ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ኢዜማ
October 8, 2020 at 1:32 am #16251AnonymousInactiveሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ የግዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንዲሰርዝ መገደዱ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀበት እና የምርጫ ሰሌዳው በተሰረዘበት ወቅት ወረርሽኙ በሌሎች የዓለማችን ሀገራት የጤና ሥርዓት ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና እና በሰው ሕይወት ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጉዳት በተጨባጭ በማየት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መደረጉ እና በዚህ ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነበር ብለን አምነናል።
ምርጫው አለመካሄዱን ተከትሎ የመንግሥት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አማራጮች መቅረባቸው የሚታወስ ነው። የተለያዩ ፖለቲካ ፖርቲዎችም ከሕገ-መንግሥት ውጪ ያሉ አማራጮችን አቅርበው ነበር። ኢዜማ የመንግሥት ቀጣይነትን በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ጠቅሶ፥ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ከሚሰጣቸው የመፍትሄ አማራጮች ውስጥ ደግሞ የመንግሥትን የሥልጣን ጊዜ እና ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ የሚደነግገውን የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ከአቅም በላይ እና በድንገተኛ ምክንያት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር የመንግሥትን ሥልጣን ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም እንዲያስችል አድርጎ ማሻሻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ማቅረቡ ይታወሳል። ማሻሻያው ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ እና ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት ላይ ግዴታ የማይጥሉ መሆናቸውን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበትም ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክፍተቱን በሕገ-መንግሥት ትርጉም ለመሙላት ወስኖ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት አለመሆኑ በጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም እስኪረጋገጥ ድረስ አራዝሞ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት እና ምክር ቤቶችን የሥራ ጊዜ ያለገደብ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ ኢዜማ የጊዜ እና ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ጉዳዮች ላይ ወሰን ሳይደረግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን መራዘሙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልፆ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በገለጸው መሠረት አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ምርጫው መደረግ በሚችልበት ቅርብ ጊዜ እንዲደረግ ጠይቋል።
በቅርቡ የጤና ሚኒስትር አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳወቀው መሠረት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።
ይህ በእንዲህ እያለ፥ “ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፤ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን እና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ ለማስተዋል ችለናል።
ይህ ቅስቀሳ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ከማወክ እና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን። ይህንን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው የጋራ ሀገራችን ሰላም እና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ ከመምጣት ውጪ በሁከት እና በጉልበት ወደሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገር ሰላምን እና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።
ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዘንድሮ እንዲካሄድ የተወሰነውን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው እና ምርጫው እስከሚካሄድ እና የሕዝብ ድምፅ ያገኘው ተለይቶ እስከሚታወቅ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን በተለይም በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተለያየ ፖሊሲ አቅርበው የሕዝብን ቅቡልነት ለማግኘት በሚወዳደሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ እና ከመተግበር እንዲቆጠብ እናሳስባለን።
እኛንም ጨምሮ በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ ከዚህ ቀደም በተስማማንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና የሌሎችን መብት ያከበረ መሆኑን እያረጋገጥን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ እንጠይቃለን። በሀገራችን የምትንቀሳቀሱ የሲቪክ ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት እንድታደርጉ እና በጋራ ሊሠሯቸው እና ሊስማሙባቸው በሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት መድረክ እንድታዘጋጁ የአደራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፥ በመድረኮቹ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ያለንን ፍላጎት ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመገንዘብ የምርጫውን ሂደት ከአሁን ጀምሮ በንቃት እንዲከታተል እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ምOctober 13, 2020 at 5:14 pm #16337AnonymousInactiveየምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል!
ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫበኢትዮጵያ ሕዝብ የረዥም ጊዜ መራራ ትግል 2010 ዓ.ም ላይ የመጣው ለውጥ ሕዝቡ ከነበረው ተስፋ በተቃራኒ የመክሸፍ አደጋ አጋጥሞታል።
ከእንግዲህ በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ በእርግጠኝነት ደጋግሞ ቃል በመግባት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች ሁሉ በማጠፍ የለየለት አምባገነናዊ መንግሥት መሆን ጀምሯል።
በዚህም ምክንያት የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ክፉኛ የሚፈታተንና የሀገሪቱን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በሀገራችን ተከስቷል። በብዙ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ መክሸፉና ሀገሪቱ ተመልሳ በሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ስር መውደቋ እጅግ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፥ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሀገራችንን ከውድቀት ለማዳን ዛሬም ዕድሉ በእጃችን ነው ብሎ ያምናል።
ይህ ከውድቀት የመዳን እድል እውን ሊሆን የሚችለውም በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት፣ ወይንም ባለፉት 27 ዓመታት ያየነው ዓይነት ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ አይደለም።
በኢዴፓ እምነት ከዚህ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ወጥተን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር ቢያንስ የሚከተሉት አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለን እናምናለን፤
- በሀገራችን የሕግ የበላይነት የመጥፋት ችግር እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ የከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። በኢዴፓ አመራር በአቶ ልደቱ አያሌው እና በሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን እንደታየው ሰዎች በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበትና የፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ የማይከበርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ ሀገር ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀም፤ እና የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት።
- በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ/አብሮነት፣ የኦፌኮ፣ የኦነግና የባልደራስ ከፍተኛ ዓመራሮች፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች /በተለይም በኦሮሚያ ክልል/ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ስለሚገኙ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል። ይህ አሳሳቢ ውጥረት ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው።
- ሀገራችን በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም። ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ድረስ ሀገሪቱ እንዴት ትተዳደር? ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ? ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዴት ይርገብ? ሀገሪቱ ቋሚ መንግሥት እስከሚኖራት ድረስ የኢኮኖሚ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? ያልለየለትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በተመለከተ ምን ልናደርግ ይገባል? በሚሉትና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል አንድ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት /national dialogue / በአስቸኳይ መጀመር አለበት።
- በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት። ጉዳዩ ከሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት።
በአጠቃላይ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩና በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ ተባብሶ በዜጎችና በሀገር ላይ ለሚደርሰው ለማንኛውም የከፋ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን እንገልፃለን። ከማንም በላይ የጉዳዩ እና የሀገሪቱ ባለቤት ሕዝቡ ነውና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ ምላሽ አግኝተው ሀገራችን ከውድቀት እንድትድን ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ሕጋዊ እና ሰላማዊ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባOctober 19, 2020 at 2:36 pm #16408AnonymousInactiveከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሀገራዊ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባዉን ከመስከረም 29 ቀን እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሲያካሂድ በወቅታዊ የኢትዮጵ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላም መደፍረስ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት መክሯል፤ ፓርቲው የሚተገብራቸውን የተለያዩ መመሪያዎች፣ እንዲሁም የ2013-2017 ዓ.ም የፓርቲዉን የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድና የ2013 ዓ.ም የአንድ ዓመት ዕቅድ በስፋት እና በጥልቀት በመመርመር ወደተግባር እንዲገቡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አዉጥቷል።
- ሁሉንም ተግባራት ማከናወን የሚቻለዉ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘኖች ሰላም ሲኖርና የሕግ የበይላነት ሲከበር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነዉ፤ ነገር ግን በመላ ኢትዮጵያ ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲዘርፍና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመንፈግ እንደፈለገ ሲያስር ሲገድልና ሲያኮላሽ የነበረዉ ዘረኛዉ ህወሓት ከጠቅላይ አምባገነንቱ ተባሮ መቀሌ ከመሸገበት እና በዶ/ር ዐቢይ አህመድየሚመራዉ “የለዉጡ ቡድን” መንግሥታዊ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሁነቶች ተከስተዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ነፍስ ባላወቁ እምቡጥ ሕፃናት ሳይቀር በጽንፈኛ ብሔርተኞችና እነሱ በሚደግፏቸዉ ታጣቂ ቡድኖች፤ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ (በተለይ በመተከል በተደጋጋሚ) እንዲሁም በደቡብ ክልሎች እስካሁን ድረስ እየተፈጸሙ ነዉ። ዜጎች በገዛ ሀገራቸዉ እንደሁለተኛ ዜጋ እየታዩ ሀብት ንብረታቸዉ እየተዘረፈና እየወደመ፣ ከመኖሪያ ቀያቸዉ እየተፈናቀሉ ነዉ። ኢሕአፓ ከዚህ በፊት ባወጣቸዉ ተደጋጋሚ አቋሞቹ እንደገለጸዉ፥ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያሳየዉ ቸልተኝነትና መዘግየት እነዚህ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር እንደከፈተ ያምናል። ስለዚህ ሉዓላዊነታችንንና የሕግ የበላይነትን የማስከበር፣ ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸዉን የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የሚመራዉ መንግሥት ስለሆነ፥ አሁን የጀመረዉን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአጥፊዎችም ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ መሽገው የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትጥቅ የማስፈታት እና ወደሕግ የማቅረብ፤ በወንጀል ድርጊት ያልተሳተፉትን አጣርቶ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸዉ እንዲመለሱ የማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፤ ፓርቲያችን ኢህአፓም ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በጽናት ይታገላል።
- በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚፈጸሙት ዘግናኝ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ መንስዔው በዋነናት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል። ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል በተደጋጋሚ ቃል ገብቶ እንደነበረ ይታወቃል። ነገር ግን ያ ሁሉ ቃል-ኪዳንና ያ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደጎን ተትቶ፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ወቅት ይታያል ተብሎ የነበረው ሕገ-መንግሥት ምንም ዓይነት ማሻሻያም ሆነ ማስተካከያ ሳይደረግበት ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋነኛው መንስዔ እንደሆነ አለ። ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ ለሚፈጸሙት ግፎች ሁሉ የመጀመሪያው ተጠያቂ ይህ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትና ይዘቱ ስለሆነ አስቸኳይ ማሻሻያ እንዲደረግበት መንግሥትን ይጠይቃል።
- በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በተደጋጋሚ ይደረጋል እያለ ቃል ሲገባ የነበረው የብሔራዊ ዕርቅና የሀገራዊ መግባባት አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አጀንዳ እንደሆነ ኢሕአፓ ጽኑ እምነት አለው። በኢትዮጵያ የሚገኙት ሕጋዊና ሰላማዊ የሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት፣ ሀገራዊ መግባባትን ትኩረቱ ያደረገ የፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት የጋራ መድረክ አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ፥ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ለዚህ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ የውይይትና የድርድር መድረኩ በአፋጣኝ እንዲካሄድ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በያዝነው የ2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይካሄዳል የተባለውና የሚጠበቀው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሕጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲተገበር ኢሕአፓ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለው። በመሆኑም፥ ምርጫ የአንድ ቀን ተግባር ሳይሆን የብዙ ወራትን የመደራጀትና የማደራጀት ተግባራት ከእያንዳንዱ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበር የሚጠይቅ ክንውን መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ከ5ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ሰላምንና ጸጥታን ማስከበር ተስኖት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እየተከሰተ ይገኛል። በዚህ ያለመረጋጋትና የሰላም እጦት ውስጥ ሆኖ ምርጫን የሚያክል ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም አጅግ አዳጋች ነው። በመሆኑም መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበትንና የሚዳኙበትን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምህዳር አስፍቶ የዜጎችን በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ኃላፊነቱን በተግባር እንዲወጣ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በየጊዜዉ እያሻቀበ ያለዉ የዋጋ ግሽበትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ የጨመረዉ ሥራ አጥነት የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ በሰቆቃ የተሞላ አድረጓል፤ ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነዉ 2012 ዓ.ም በተከሰቱ ሰው-ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ለከፋ የርሀብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። በመሆኑም ኢሕአፓ መንግሥት በረዥም ጊዜ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያስፋፋ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱን ከ2 ዲጂት በታች የሚወርድበትን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲተገበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉም ተገቢዉን ድጋፍ በወቅቱ እንዲያቀርብ በአጽንኦት ይጠይቃል።
- ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ ሲመለሱ ታፍነዉ ተወስደዉ እስካሁን ድረስ ደብዛቸዉ የጠፋዉ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ የኢሕአፓ የእግር እሳት ነዉ፤ ስለዚህ መንግሥት ልዩ ተኩረት ሰጥቶ ተማሪዎቹ እዉነት በህይወት ካሉ የማስመለስ ሥራ እንዲሠራ፥ አለያም እዉነቱን ለቤተሰቦቻቸዉ፣ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ እንዲያሳውቅ ኢሕአፓ የዘወትር ጥያቄዉን ዛሬም ያቀርባል።
- ኢሕአፓ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፣ በሕዝቧ ዉህድ ማንንነት የማይጠራጠሩ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለሚያምኑና በሕጋዊ መንግድ ለተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ኑ! ሀገራችን ከገባችበት ጽንፈኛ የጎሳ እና የጥላቻ ፖለቲካ ቅርቃር በጋራ እንታደጋት፤ ሀገራዊ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና የፖቲካ ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰለማና እድገት የሰፈነባት ሀገር እናድርጋት፤ የሚል የአክብሮት ጥሪዉን ያስተላልፋል።
- በሀገር ቤትና በዉጪ ሀገር ለምትገኙ ቀደምት የኢሕአፓ አባላትና መሥራቾች ዘላለማዊ ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህላዌ ጋር በየጊዜዉ እየታደሰ የሚዘልቅ ዘመን ተሸጋሪ ሀሳብ ያነገበዉ ኢሕአፓ ከዉጪ ሀገር ወደ ሀርቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሀገሩ ምድር ላይ ትግሉን በጽናትና ቁርጠኝነት እያካሄደ መሆኑን ተገንዝባችሁ ፓርቲያችን ኢሕአፓን በተለያየ መንገድ በመደገፍና በማጠናከር የትግላችሁን ፍሬ ማፍራት እውን ታደርጉ ዘንድ ጥሪዉን ያስተላልፋል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባOctober 24, 2020 at 1:53 am #16458AnonymousInactiveበእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ ሂደትን አጀንዳ በማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል። ፓርቲው እስክንድር ነጋ (ሊቀ መንበር)፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ በምንም ዓይነት የሚያስከስስ ወንጀል ጉዳይ እንዳልተሳተፉ እና ንጹሃን መሆናቸውን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወቃል፤ ይልቁንም የፍትህ ሥርዓቱን መጠቀሚያ በማድረግ በቀጣዩ [ሀገራዊ] ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኗቸውን እነ እስክንድር ነጋ እና ፓርቲያቸውን ለማጥቃት ታስቦ እንደሆነ ገልጸናል። ይህንን አቋማችንን የበለጠ የሚያጠናክርልን ሁለት ነገሮች ደግሞ በጥቅምት 12 ቀን የችሎት ውሎ ታዝበናል፦
1ኛ. ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት ያሰማውን የምስክሮች ቃል በመተው እንደገና 21 (ሀያ አንድ) ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጽ ከመጋራጃ ጀርባ እንዲሰሙ እና በዝግ ችሎት እንዲደመጡ ጥያቄ ማቅረቡ ላይ እየተደረገ ያለው የፍትህ አሰጣጡን የሚያዛባ እና የሚያጓትት ሂደት፤
2ኛ. የሚሰጡ ቀጠሮዎች (በተለይም አዳዲስ ዳኞች እንደተሾሙ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማም ከተናገሩ በኋላ) ረጅም መሆናቸው ሂደቱን በማጓተት እነ እስክንድር ነጋ ሳይፈረድባቸው በእስር እንዲቀጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ከክሱ ነጻ ቢባሉ እንኳን እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ሆኖ አግኝተነዋል።
እነዚህ እና መሰል ጉዳዩች በክስ ሂደቱ ላይ የአስፈጻሚው አካል ረጅም እጆች እንዳሉበት የሚያስረዱ ሆነው አግኝተናቸዋል። ከዚህም በመነሳት ፓርቲያችን መሪዎቻችን ትክክለኛ ፍትህ፣ ሳይዘገይ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳይኖረን አድርጎናል። ስለሆነው ፓርቲያችን የኦህዴድ/ብልጽግና ፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት በማሰብ በሀሰት በተቀነባበረ ክስ የተያዙ አመራሮቻችንን ለማስፈታት ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው ትግል በተለየ እና በበለጠ ሁኔታ ውጤታማ የሚያደርጉ የትግል መንገዶችን ነድፎ በሥራ ላይ ያውላል። መላው የፓርቲያችን አባላት እና ፍትህ ወዳጅ ሕዝባችን በቀጣይ ይፋ ለምናደርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች እንደከዚህ ቀደሙ እራሱን እንዲያዘጋጅ እና ለነጻነት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፉ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
አዲስ አበባ
ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ምምንጭ፦ ባልደራስ
——
ሌሎች ተመሳሳይ ዜናዎች፦- የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
- ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
- የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል! – ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ
- ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል! ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
October 26, 2020 at 12:12 am #16485AnonymousInactiveየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎችን ለማድረግ ጥሪ አደረገ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ አስታውቋል። አብን ስለሰላማዊ ሰልፎቹ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ያልተቋረጠ በደል እየደረሰበት መሆኑን ያመላከተበት ትንታኔ የሚከተለውን ይመስላል።
ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥታዊና ሥርዓታዊ ጭቆና እና የዘር ጥቃት ያንዣበበትን የአማራን ሕዝብ ከህልውና ስጋት ለመታደግና በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በወንድማማችነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቆመ ድርጅት ነው።
አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን፣ በትግላችን የተንበረከኩ አማራ-ጠል ኃይሎች ዳግም እንዳያንሰራሩና የሀገር እና የሕዝብ ህልውና በድጋሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። የአማራ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዎንታዊ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና የግንባታ ሚና እንዲኖረው ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።
ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት “ለውጥ” እያደር መስመሩን በመሳቱ አዲሱ አገዛዝ የአምባገነንነትና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስፈፃሚነት አዝማሚያ ማሳየቱ ገሃድ ወጥቷል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል።
አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ወትውቷል። እንደ ሕዝብም መቻቻልና ሀገር ወዳድነት ትርጉም እስኪያጡ ድረስ ታግሰናል። ነገር ግን ብልፅግና-መራሹ መንግሥት የሕዝባችንን ሆደ-ሰፊነትና አስተዋይነት እንደ ዓይነተኛ ድክመት በመቁጠር፥ ንቅናቄያችን ለሀገር ህልውና ሲባል የሰጠውን ይሁንታ በሰፊው በማጓደል ዛሬም አማራው መንግሥት-አልባ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጦልናል።
አብን በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ቀንደኛው ተጠያቂ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን ያምናል። መንግሥት ‹‹የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል›› የሚባለውን የዘር ማጥፋትን በመከላከል፣ በማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የረባ ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም የዘር ጥቃቶችን “ግጭት” እያለ ለማድበስበስ፣ መረጃዎችን ለማፈንና ሰለባዎችን ጭምር ለመወንጀል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። መንግሥት በአማራ ላይ የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ልዩ ጠባሳ የሆነውን የጉራ ፈርዳ ጥቃት መሪ አቀናባሪ የነበረውን ግለሰብ ለዳግም ሹመት የመምረጡን አንድምታ እንረዳለን፤ አሁን የሚፈፀመውን ካለፈው የሚያስተሳስር ረጅም ክር አለው።
በሁለተኛ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት በተፈፀመባቸው ክልሎች ያሉ መንግሥታት በተለያየ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው፥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በመሣሪያና በገንዘብ ጥቃቶችን መደገፋቸውና ማቀናበራቸው በገሃድ ይታወቃል። ከጥቃቱም በኋላ የየክልሎቹ የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በሕዝባችን ላይ በየፊናቸው በማንአለብኝነት የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጊቱ አለመጸጸታቸውንና ችግሩን ለማረም ፈቃደኝነት እንደሌላቸውም ያረጋግጣል።
ሦስተኛው ተጠያቂ “የአማራ ብልፅግና” የሚባለው ነው። ለአማራ ሕዝብ ብልፅግናውን ቀርቶ ህልውናውንም ሊያስጠብቅለት አልቻለም። ቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ አቋም መሻሻል አላሳየም። ንቅናቄያችን አማራው እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ለማስቻል ለሁለት ዓመታት ያክል “የአማራ – ብልፅግናን” ለማግባባት ያደረገው ሰፊ እና ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የአማራ ሕዝብንም፣ አብንንም በተደጋጋሚ ያሳዘነ ሲሆን፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያመልጥም።
አብን በማዕከልም ሆነ በክልል ያሉ መንግሥታት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ውጤቱ በአማራው ሕዝብ ተገድቦ እንደማይቀር በውል እንዲጤን ይሻል። መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን የማያስጠብቅለትን ሕዝብ ማናቸውንም የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ሊጥልበት አይቻለውም። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ማኅበራዊ ውልም ክፉኛ ይናጋል።
አብን በአማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዞሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ይገነዘባል። ንቅናቄያችን እስካሁን የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ አመፅ እንዲያመራ የሚደረገውን አሉታዊ ጥረት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም ከእንግዲህ ወዲያ የሕዝባችን ህልውና በምንም መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ ለማረጋገጥ ይወዳል።
አብን የአማራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና አስተዋይ በመሆኑ ተፈጥሯዊ መብቱንና ነፃነቱን በልቅሶና በልመና ሳይሆን በተደራጀ ትግል እንደሚያስከብር ይተማመናል። ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመምራት ከግብ ለማድረስ ድርጅታችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል።
አብን መንግሥት ችግሩን በአስቸኳይ ከማስቆም በተጨማሪ ጥቃቱን እንዲያምንና በስሙ እንዲጠራ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በፍጥነት እንዲሰይም፣ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎችም ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ ይጠይቃል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ምንጭ የሆነው አማራ-ጠል ሕገ-መንግሥት የሚሻሻልበትን አግባብ በአስቸኳይ እንዲያመቻች ይጠይቃል።
አብን መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር አለመቻሉንና በተደጋጋሚ የአማራ ተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ችላ ማለቱን በማጤን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት መጀመር ጥሪም ያሳስበዋል። ብዙ ሽህ የአማራ ተማሪዎች በፅንፈኞች ጥቃት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ሲደበደቡና ሲታገቱ በአሳፋሪ ሁኔታ አልታደጋቸውም። አሁንም ለተማሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ በጥብቅ እንጠይቃለን።
የአብን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው መሠረት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመቀልበስ፤ የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ጥረቶችና ስልቶች ለሕዝባችን ለማሳወቅ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፤ እሁድ ጥቅምት 22 በአዲስ አበባ ታላላቅ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ይደረጋሉ።
በእነዚህ ሰልፎች ላይ መላው የአማራ ሕዝብ ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበው እንዲሳተፍ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች በወገናችሁ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንድትቃወሙ ጥሪ እናደርጋለን።
አብን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑና ሊከተሉ የሚችሉ አላስፈላጊ ረብሻዎችንና ጥቃቶችን ለማስቀረት ሕዝቡ የራሱን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ ያሳስባል።
ሰልፉን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በማዕከል ተዘጋጅተው በፓርቲያችን ይፋዊ ገፅ የሚለጠፉትና ለየአካባቢው የሚላኩት ናቸው።
ጉዳዩ የሕዝብ ህልውና ጥያቄና የራሱ ሰልፍ በመሆኑ የሀገር መከላከያና አጠቃላይ የደህንነት ኃይሉ የሕዝቡ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን የፀጥታ ሥራ እንዲያከናውን ጥሪ እናደርጋለን።
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አማሮች እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ድምፃችሁን እንድታሰሙ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
ሰልፉ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ እያሳሰበ፥ ሕዝባችን በየአካባቢውና በየቤተሰቡ በገጠመን ፅኑ ወቅታዊ ችግር ላይ ውይይት እንዲያካሂድ፤ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ አብን ዓለምአቀፍ የመላው አማራ ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻች መግለጽ ይወዳል።
በአዲስ አበባም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የማናለብኝነትና የተረኝነት አካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጉዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድሙ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል በመቃወም አብሮ እንዲሰለፍ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
አብን ከእንግዲህ ጉዳዩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ማናቸውንም የሰላማዊ ትግልና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ስልቶችን በየደረጃው የሚተገብር በመሆኑ ሕዝባችን ከወዲሁ እንዲያውቀውና ወትሮ ዝግጁ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም
ሸዋ፥ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ!October 31, 2020 at 11:28 pm #16572AnonymousInactiveከዓመቱ የትምህርት ፕሮግራም መጀመር ጋር ለተማሪዎች ደህንነትም አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ አለበት
ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግለጫበኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የመማር-ማስተማሩ ሂደት ከተስተጓጎለ ከስድስት ወራት በላይ ሆኖታል። መንግሥት የተቋረጠውን የትምህርት ፕሮግራም መልሶ ለማስጀመርና የወረርሽኙን ጥቃት ለመቆጣጠር በሚያስችል ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ከሕዝብ ዜና ማሰራጫዎች እየሰማን እንገኛለን። በእርግጥም የትምህርት ፕሮግራሙን መልሶ ማስጀመር የግድ እንደሆነ ብንረዳም፤ ከዚሁ ጋርም ስለወጣት ተማሪዎቹ ደህንነትም መታሰብ እንዳለበት ለማስገንዘብ ይህንን መግለጫ አወጥተናል።
ከኮሮና ወረርሽኝ ስጋት በተጓዳኝ የሀገራችን የፖለቲካ ቀውስ እና በየቦታው እየተነሱ የሕዝቦቻችንን ደህንነት የሚያውኩ ግልገል አምባገነኖች የሚፈጽሙት እኩይ ተግባራት ተጨማሪ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ግምት አለን። ጠባብ ዓላማ ያነገቡ የተለያዩ ኃይሎች በሚፈጥሩት ግጭቶች፣ መንግሥት የሚመድባቸው ባለሥልጣናት የማስፈጸም አቅም ውስንነት እና አንዳንዶች ደግሞ ከሕዝባዊ ወገናዊነት ማነስ የተነሳ ለትምህርት ፕሮግራሙ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ግደታ በትክክል ሳይወጡ ሲቀሩ፥ ለጋ ወጣት ተማሪዎች አደጋ ላይ ይወድቃሉ፤ ደርሶም ታይቷል። በዚህን ጊዜ ቁጥራቸውን መግለፅ አስፈላጊ ባይሆንም፥ በ2012 ዓ.ም የአንደኛ ሴሚስተር ጊዜ ውስጥ ከደረሰባቸው የሕይወትና ንብረት መጎዳት የተነሳ የኦሮሚያ ክልል ወጣት ተማሪዎች ወደ ሌሎች ክልሎች የትምህርት ተቋማት ሄደው ለመማር የሚያሳዩት ፍላጎት እያነሰ በመሄድ ላይ እንደሚገኝና በክልላቸው ለመማር እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነ ተረድተናል።
-
- የትምህርት መጀመር ሁኔታን አስመልክቶ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት
- የትምህርት መጀመር ሁኔታን አስመልክቶ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት
በተጠቀሰው ጊዜ በየትም ክልል ይሁን በተማሪዎቹ ላይ ወንጀል የፈጸሙ ኃይሎች ላይ ስለተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ የተሰማ ነገር ባይኖርም፤ አሁንም በማንኛውም ክልል የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለማንኛውም ወጣት ተማሪ ምክር እየተለገሳቸው ራሳቸውን ብሎም ሀገርን ማስተዳደር የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠሪያ ቦታና ተቋማቱ ደግሞ ከቤት ውጭ ቤት ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው እንገነዘባለን። ይህ ይሆን ዘንድ ማረጋገጫ መስጠት የሚችለው ማንም ሳይሆን መንግሥት ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ እንደከዚህ ቀደሙ የወጣት ተማሪዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ሁኔታ ከተፈጠረ በሀገራችን ሌላ ተጨማሪና ሊያባራ የማይችል ቀውስ እንዳይፈጥር እንሰጋለን።
ስለሆነም፥ የተቋረጠውን የትምህርት ፕሮግራም መልሶ ለማስጀመር ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ብቻ ሳይሆን ለመማር ማስተማሩ ሥራ አመቺ የሆነና በአንፃራዊነትም ከግጭት ነፃ የሆነ ከባቢ ለመፍጠር አስፈላጊው እንዲደረግ ለመንግሥትና ለሁሉም የፌዴራሉ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከአደራ ጭምር እናሳስባለን።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ፊንፊኔ፤ ጥቅምት 2013 ዓ.ም.November 2, 2020 at 2:06 pm #16588AnonymousInactiveበአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በትላንትናው ዕለት ማታ [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል።
በሀገሪቱ ውስጥ ለበርካታ አስርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል፤ እየተፈፀመም ይገኛል። ጥቃቶቹ ሊደርስ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ያሳወቅን ቢሆንም ተጨባጭ መፍትኼ ሊገኝ አልቻለም።
የጥቃቱ ምንጭ ውስብስብ እንደሆነ እንረዳለን፤ የአረመኔዎች ቅንጅት ሕዝባችን በደም ጎርፍ እንዲታጠብ አድርጓል። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል።
መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራትና ብሔራዊ የደህንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን እርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደኅንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።
በተለይም የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ በየቦታው ካሉ አማራ-ጠል ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በቅንጅት አማራዉን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግሥቱ ነው።
በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ለማውገዝ የተጠራውን ሰልፍ አማራ ማዘን እንኳን አይችልም በሚል እርቃን በወጣ አምባገነንነት የከለከለ መንግሥት ሕዝባችን ላይ የሚደርስን ቀጣይነት ያለው ጥቃት ለማስቆም ፍላጎት ማጣቱ ጥቃቱን እንደሚፈልገው አብይ ማሳያ ነው።
ሕዝባችን የዘር ማጥፋት ታውጆበትና መንግሥትም የጥቃቱ ተባባሪ ሆኖ ከገዳዮቹ ጋር በአንድ ሀገር ለመቀጠል የሚቸገር በመሆኑ ሁሉም የሀገሪቱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርግ አብን ጥሪ ያስተላልፋል።
ሕዝባችንም በየቦታው የሚፈፀምበትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እንዲመክት አብን ጥሪውን ያቀርባል።
ውድ አማራዉያን፥ አሁን ሐዘናችንንና ቁጭታችንን በቅጡ ለመግለፅ እንኳ አቅም ማጣታችን ግልፅ ነው። ከሂደቶች የምንገነዘበው ተጨማሪ ጥቃቶች ሊከፈቱ እንደሚችሉ ነው። ፈጣን ምክክር በማድረግ የኅልውና አደጋዉን በዘላቂ ሁኔታ ለመቀልበስ በቂ ዝግጅት ማድረግ አለብን።
ይህ ጉዳይ በመደበኛ እንቅስቃሴ ሊመከት አልቻለም። የአማራ ሕዝብ የሀገራዊ ፖለቲካው ሽኩቻ ሁሉ ብቸኛና ቋሚ ማስያዥያ ሆኖ ቀጥሏል። አሁን የሕግ የበላይነት ቦታ አጥቷል። መንግሥት ሕግ የማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት አለመፈለጉና አለመቻሉ ተረጋግጧል። ቀሪው ነገር የአማራ ሕዝብ ተደራጅቶ ራሱን ይከላከል የሚለው ነው።
አብን ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። አብን የተደራጁ የትግል ስልቶችን ነድፎ ለሕዝባችን ይፋ እንደሚያደርግም ለመጠቆም ይወዳል።
በድጋሚ ነፍስ ይማር።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
November 2, 2020 at 2:36 pm #16595AnonymousInactiveንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም
ብልጽግና ፓርቲባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በሀገራችን እዉነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር ለማደረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸዉ ይታወሳል።
በዚህም በሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ተስፋና መነቃቃት መታየት የጀመረ ሲሆን ሀገራችን በሰላማዊ፣በሰለጠነና በሰከነ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሚመራ ነጻ፣ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር እንደምትችን የተስፋ ብርሃን የታየበት የፖለቲካ ሪፎርም ሲካሄድ መቆየቱ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት የማይዋጥላቸዉና ግድያን፣ ማፈናቀልን፣ ንብረት ማዉደምንና ንጹሃን ዜጎችን ማሸማቀቅን እንደ ዋነኛ የስልጣን ምንጭ አድርገዉ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን መረጋጋትና የዜጎቿን ሰላም የማይፈልጉ ሃይሎች ቅንጅት በመፍጠር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸዉን ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸዉ ብቻ ኢላማ በማድረግ ጥቃት በማደረስ ላይ ይገኛሉ።
በዚህ እኩይና ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ የጥፋት ተግባራቸዉ ባለፉት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ንብረት እንዲወድምና ዜጎች የሰላም ስሜት እንዳይሰማቸዉ ሲደረግ ቆይቷል።
በተለይም ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ የበርካታ ንጹሃንን ህይወት የቀጠፈ ጨካኝ የሽብር ተግባር ተፈጽሟል።
የንጹንን ደም በማፍሰስ ስልጣን መያዝን ካልሆነም አገርን መበታተንን ዋነኛ ዓላማቸዉ አድርገዉ ከሚነቀሳቀሱ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነዉ ኦነግ ሸኔ የተባለዉ አሸባሪ ቡድን በሀይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ከሚፈልጉ ካልተሳካላቸዉም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን ከሚሰሩ ተቀናጅተዉና በትጥቅ ተደግፈዉ በትናንትናዉ ዕለት ማታ [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለዉ ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት የዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካታ የአካል ጉዳትም ደርሷል።
ይህ የሽብር ጥቃት ፍጹም ሰላማዊ በሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተቃጣ መሆኑ አጥፊ ቡድኑ የሚከተለዉ መንገድ ምን ያህል ያልሰለጠነ፣ ኋላ ቀርና ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን ለአለም ሕዝብ ያጋለጠበት ነዉ።
በዚህ አረመኔዊ ተግባር ህይወታቸዉን ላጡ ዜጎቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለተጎጂዎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን መጽናናትን እንመኛለን።
መንግሥት እነዚህን ነብሰ ገዳዮች ከያሉበት አድኖ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እያረጋገጥን የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላዉ የሀገራችን ሕዝቦች የንጹሃን ዜጎችን ህይወት ያጠፉና አካል ያጎደሉ ሽብርተኛ ቡድኖችን አድነን እርምጃ በመዉሰድ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገዉ እርምጃ ዉስጥ ከጎናችን በመሆን አስፈላጊዉን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት
ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ምNovember 2, 2020 at 11:11 pm #16609AnonymousInactiveምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ እናወግዛለን
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ከትላንት በስትያ ህዳር 1 ቀን 2020 [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማን ሲሆን፥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ይህንን የግድያ ተግባር በጽኑ እያወገዘ፤ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም ይገልጻል።
መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ከአሁን ቀደም እንደለመደው ይህንን ግድያ የፈጸሙት ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔ ናቸው በሚል ገልጿል። ኦነግ-ሸኔ በሚል የሚታወቅም ይሁን በዚህ ስም እራሱን የሚጠራ ድርጅት ግን አላገኘንም። ለኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይሁን ለዓለም ማኅበረሰብ በዚህ ስም የሚከሰሰው ድርጅት ማንነት ግልጽ አይደለም።
ይህ የግድያ ድርጊት እና ሌሎች መሰል ድርጊቶች ሁሉም ነጻና ተዓማኒነት ባለው ገለልተኛ አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጣርተው ለተጎጂዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ ግልጽ እንዲሆኑ እንጠይቃለን። ከዚህ ባሻገር ሁሉም አካላት ሕዝቦችን የሚያጋጩና በብሔሮች መካከል መጠራጠርን የሚፈጥሩ ማናቸውንም ዓይነት መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ያለው ቀውስና የደህንነት ችግር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ካልተበጀለት፥ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ኦነግ በመግለጫው ሲያሳስብ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን እያየን ያለነውን አደጋ ለማስቀረት እና ኦሮሚያና ዜጎችን ከባሰ ቀውስ ለመታደግ ያለው ብቸኛው መፍትሄ የኦሮሚያ ሽግግር መንግሥት ማቋቋም በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን በድጋሚ እናድሳለን።
በድጋሚ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በምዕራብ ኦሮሚያ በዜጎች ላይ የተፈጸመውንና ካሁን ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ የተፈጸሙ ግድያዎችን ሁሉ በጥቅብ እንደሚያወግዝ እያሳሰበ፥ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች እንዲሁም ሰላም ወዳዶች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።
ድል ለሰፊው ሕዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
ህዳር 3 ቀን 2020 ዓ.ም- በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ― አብን
- ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም ― ብልጽግና ፓርቲ
- የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ
- የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል! – ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ
- ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል! ― ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
November 2, 2020 at 11:42 pm #16613AnonymousInactiveበአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል መራሹ የኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው!!!
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት ድርጊት የተሰማውን መሪር ሀዘን ይገልፃል።
ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር የማፅዳት ወንጀል እየተፈፀመ ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ማስቆም የሚችል የመንግሥት ኃይል አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን እያባባሰው መጥቶ ዛሬ ላይ የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል።
በዚህም ምክንያት በእነዚህ በርካታ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል። መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራት እና ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን ርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ቀንደኛ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።
በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የሚንቀሳቀሰው ታጣቂው የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ በየቦታው ካሉ አማራጠል ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በቅንጅት አማራዉን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግሥቱ ነው።
በኦህዴድ መራሹ የብልጽግና መንግሥት የስልጣን መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አፍቃሬ ኦነግ የኦህዴድ ባለስልጣናት በአካባቢው የነበረውን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በማስወጣትና ድርጊቱ ሲፈፀም እየሠሙና እያወቁ እንዳላዩ ማለፋቸው የዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳታፊ እንደሆኑ ይቆጠራል። በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ታውጆበት እያለ የማዕከላዊ መንግሥቱ ዝምታና እንዳላየ ማለፉ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው።
የአማራው ሕዝብ በመንግሥት ድጋፍ እየተፈፀመበት ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እና ተዘጋጅቶ እንዲመክት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥሪውን እያቀረበ በአሸባሪው የኦነግ ሽኔ ሽፍታ ቡድን ህይወታቸን ላጡ ወገኖቻችን ቤተሰቦች መፅናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ምNovember 6, 2020 at 2:05 am #16654AnonymousInactiveየሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ሙሉ ትኩረታችንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ላይ እናድርግ!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫበሀገራችን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መንግሥታዊ ድጋፍ አግኝቶ በተግባር ላይ የቆየው ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ በዜጎች እና ማኅበረሰቦች መካከል የጥላቻ እና ያለመተማመን ስሜት እንዲሰፍን ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው አገዛዝ በስልጣን ላይ ለመቆየት የጥላቻ እና አለመተማመን መስፈኑን እንደአንድ መሣሪያ ሲጠቀመው ቆይቷል። ይህን ለረጅም ጊዜ በመንግሥት መዋቅር ጭምር እየተደገፈ የተሠራው ማንነትንን መሠረት ያደረገ መከፋፈል፣ የጥላቻ እና የእርስ በርስ አለመተማመን አሁንም ድረስ በየአካባቢው ተንሰራፍቶ፤ ዜጎች በሀገራቸው በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው ደህንነታቸው ተጠብቆ የመኖር፣ የመሥራት እና ሀብት የማፍራት ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና ያለውን ሰብዓዊ መብታቸውን እየገፈፈ ነው።
ይህ መከፋፈል፣ የእርስ በርስ ጥላቻ እና አለመተማመን ከሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ውጪ የፖለቲካ አመለካከታቸውን በኃይል ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት እንደአጋጣሚ ወስደው እየተጠቀሙበት እንደሆነ ግልፅ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት መዋቅርም ሙሉ በሙሉ ከዚህ ችግር ያልጸዳ ብቻ ሳይሆን አደጋ በደረሰባቸው ቦታዎች የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከአጥፊዎች ጋር በትብብር እየሠሩ ከአደጋ መጠበቅ የሚገባቸውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛል።
የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እንዲሁም አንድነትን የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸው የደህንነት መዋቅሮች የደህንነት ስጋት ያለባቸው ቦታዎችን በአግባቡ ተንትኖ ደረጃቸውን መለየት እና በዚያም ልክ ተዘጋጅቶ የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት እና የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ ላይ በተደጋጋሚ ክፍተት እንዳለባቸው አይተናል። የንፁሃንን ሕይወት የቀጠፉ እና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶች መደጋገማቸው ከተፈፀሙ በኋላ የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎችም አጥጋቢ እንዳልሆኑ በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህን ጉድለቶችን ሙሉ ለሙሉ ማረም እና አስተማማኝ የሆነ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የረጅም ጊዜ ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም፥ ክፍተቱ እያስከተለ ያለው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ጥፋት የማስተካከያ እርምጃዎች ከማንኛውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ትኩረት ቅድሚያ ተሰጥቶዋቸው እንዲሠሩ የሚያስገድድ ነው።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ አባል የነበሩ ሰዎች በሀገር እና ዜጎች ላይ ላደረሱት ጥፋት ሁሉ ይቅርታ ጠይቀው፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊያንም ተቀብሎት፤ ሀገር አቀፍ ለውጥ ሂደት ጅማሮ ውስጥ መግባታችን ይታወቃል። የነበረውን ስልጣን የበላይነት ያጣው ህወሓት በተለያየ ጊዜ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከአጠቃላይ የለውጡ መንፈስ ውጪ ከመሆን አልፈው፤ የሀገር ሰላም እና አንድነትን በተደጋጋሚ አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የፌደራሉን መንግሥትና የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በቀጥታ በመቃወም ራሱ አስመራጭ፣ ተመራጭ፣ ታዛቢ እና ቆጣሪ የነበረበት ሕገ-ወጥ የክልል ምርጫ አድርጓል። በዚህም የተነሳ የፈደራል መንግሥት ከክልሉ ጋር ያለዉን ቀጥተኛ ግንኙነት ማቋረጡን እናስታውሳለን። “ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም!” የሚል አደገኛ ቅስቀሳ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ ፍፁም ሥርዓት አለበኝነት እንዲነግሥ በባለስልጣናቱ እና በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል። በሀገሪቱ በተለያየ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን ቢያንስ በእርግጠኝነት የምናውቀውን የሚዲያ እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የብዙ ንጹሀን ሕይወት እንዲቀጠፍ ተባባሪ ሆኗል።
በሀገራችን የመከላከያ ሠራዊት ላይም በተደጋጋሚ ሥራዉን የማደናቀፍ እና የሚገባዉን ክብር የመንፈግ ድርጊቶች ፈጽሟል። የሠራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ መንገድ በመዝጋት እና በማዘጋት እንዲሁም በመከላከያ ሕግ እና ደንብ መሠረት የሚፈጸሙ የከፍተኛ የጦር ኃይል አመራር ሹመቶችን ባለመቀበል አስተጓጎሏል። ህወሓት የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የትግራይን ሕዝብ እንደከለላ በመውሰድ እና ያከማቸውን ገንዘብ እና የኃይል አቅም በመጠቀም በማንአለብኝነት የፈፀማቸው ድርጊቶች እያደር የብዙ ዜጎችን ሕይወት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ አደጋ ውስጥ እየከተቱ መጥተው መንግሥት ያለውን ኃይልን ተጠቅሞ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተገደደበት ደረጃ ላይ መድረሱን እንገነዘባለን።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እራሱን ለመከላከል እና ለሀገር አንድነትና ሰላም ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ ስጋት ሲደቅን የነበረው ህወሓት ላይ መውሰድ የጀመረው እርምጃ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም ኃይልን ተጠቅመው የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት ላይ አደጋ በመጣል የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በሙሉ ሥርዓት የሚያሲዝ እና ከአሁን በኋላ የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት ከሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ውጪ ለመንቀሳቀስ ያሉ አማራጮችን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚዘጋ መሆን ይኖርበታል።
በሁሉም አካባቢዎች ችግር ሲያጋጥም አሰስፈላጊውን መስዕዋትነት እየከፈለ የሚጠብቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን በዚህ ወቅት ከውጭ ጠላቶች ሀገርን የመከላከል እና ከሀገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች ሀገርን የመታደግ ድርብርብ ከባድ ኃላፊነቶችን እንደተሸከመ እንረዳለን። ምንም እንኳን ተደራራቢ እና አስቸጋሪ ኃላፊነት ቢሆንም የተቋቋመበት ኃላፊነት እና የተሰጠው ሕገ-መንግሥታዊ ግዳጅ በመሆኑ እንደሚወጣው እናምናለን። በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን አንድነት እና ሰላምን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች የኢዜማ አባላት እና አመራር ሙሉ በሙሉ ከጎኑ እንደሚቆም ለማረጋገጥ እንወዳለን።
በመሆኑም፦
- መከላከያ ሠራዊቱ እና ሌሎች የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የሁሉንም ዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበረ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶች እና በዕድሜ የገፉ አረጋውያን ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ ልናሳስብ እንወዳለን። የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላምን እና አንድነትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ በተቻለው አቅም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ በሁሉም አካባቢዎች መደበኛ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚቀጥልበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል።
- የትግራይ ሕዝብ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሀገር ሰላም እና አንድነትን የማረጋገጥ እርምጃ መሆኑ በማወቅ ለረጅም ጊዜ የስጋት ድባብ በመፍጠር እንደሽፋን እየተጠቀመ ሲበዘብዘው እና በስሙ ሲነግድ የነበረው ህወሓትን በፍፁም ሳይተባበር ከአብራኩ ከወጣው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለሀገር ሰላም እና አንድነት ከአባት እና እናቶቹ የወረሰውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያረጋግጥ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
- የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል አባላት ህወሓት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማድረግ በኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ መዳከም እንዲፈጠር በሚያደረገው ሀገርን የማፍረስ ዘመቻ ላይ እንዳይሳተፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆምም ሕዝቡን ከስጋት እና ከአደጋ እንዲጠብቅ እንጠይቃለን።
- መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚወሰደው እርምጃ የዜጎችን ደህንነት እና የሀገር ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ መሆኑን በመረዳት አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ለሰላም እና ደህንነት እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ከማድረግ እንዲቆጠብ፣ በሁሉም አካባቢ ስጋት የገባቸውን ሰላማዊ ዜጎች ከለላ እና ማበረታቻ በመስጠት እንዲሁም አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ለሰላም እና ደህንነት መከበር ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ትብብር እንዲያደርግ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
- አሁን እንደ ሀገር የተደቀነብን አደጋ ማንንም ከማንም የማይመርጥ የህልውና አደጋ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን አደጋ የሚመጥን መፍትሄ በማፈላለግ ረገድ የተማረው ማኅበረሰብ ሚና ትልቅ እንደሆነ እሙን ነው። የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ከዳር ቆሞ አስተያየት ሰጪና ተቺ ከመሆን ወጥቶ ወደመሀል በመግባት ሊመጡ የሚችሉ የፖለቲካ መፍትሄዎችን በመጠቆም፤ እንዲሁም በቀጥታ ድጋፉን የሀገር አንድነትን እና ሰላምን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጎን በማሰለፍ ያለበትን ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት እንዲወጣ በዚህም በታሪክ ከሚመጣበት ወቀሳ እንዲድን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
- አሁን እየተተገበረ ላለው ሀገራዊ ግዳጅ ጥሪ ተደርጎላችሁ የምትሳተፉ ኃይሎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ስር ብቻ ተልኮውን እንድትፈፅሙ እና በተሰጣችሁ ሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ እንድታተኩሩ እናሳስባን። ኢዜማ ለሀገራዊው ጥሪ በፍጥነት ለሕይወታችሁ ሳትሳሱ ምላሽ ለሰጣችሁ ሁሉ ምስጋናውን እያቀረበ በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት በይፋ ከመንግሥት ከተሰጠ ተልዕኮ ወጪ የሆነ ለሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ እንቅፋት የሚሆን ተግባር እንዳትፈፅሙ ስንል እናሳስባለን። በተለይም ኢ-መደበኛ በሆነ አደረጃጀት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የገባንበትን ችግር የበለጠ የሚያወሳስብ እጅግ አደገኛ ተግባር እንደሆነ ልናሳስብ እንወዳለን። ስለዚህም አሁን የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማስከበር የተገባው በሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ አተኩረን በመንቀሳቀስ በፍጥነት የሕዝብን ጭንቀት በመቋጨት ሌሎች የዴሞክራሲ እና የይገባኛል ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገዶች ወደፊት የሚፈቱበት መንገድን እንድናመቻች በአፅንዖት እናሳስባለን።
- ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅእኖ ያላገገመው የኢኮኖሚ እንቀውሰቃሴ የአንበጣ መንጋ ጥቃት ተጨምሮበት ኅብረተሰባችን ምን ያህል ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ ለመገመት የሚከበድ አይደለም። በዚህ አስቻጋሪ ሁኔታ የተቀሰቀሰው ግጭት ሊፈጥር የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በመክተት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የእርዳታ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ዜጎች ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ ለማሳሰብ እንወዳለን።
- በተደጋጋሚ እንደገለፅነው የዜጎችን ደህንነትና ያለስጋት የመኖር መብት የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት የመንግሥት ነው። መንግሥት በተደጋጋሚ ይህን ኃላፊነቱን መወጣት ሳይችል በመቅረቱ ዜጎች ውድ የሆነውን ሕይወታቸውን ሲያጡ ቆይተዋል። በሀገር ውስጥ የሚፈፀሙ በተለይም ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በማንም ይፈፀሙ በማን የማስቆም እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ መንግሥት ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆን አይችልም። ጠመንጃ ደግነው ጥይት ተኩሰው ሰው ከሚገድሉት ነብሰበላዎች እኩል እነዚህን ኃይሎች በተለያየ መንገድ የሚያበረታቱ ከጎናችሁ ነን የሚሉ በተለይም በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ንፁሃን ላይ ለሚደርስ ጥቃት ድጋፍ ሲሰጡ የሚታዩ ኃይሎች ላይ መንግሥት አስተማሪ የእርምት እርምጃ በመውሰድ እንዲያስቆም እናሳስባለን። ምንም እንኳን ሰላምን የማረጋገጥ ኃላፊነት በዋናነት የመንግሥት ቢሆንም መንግሥት ብቻውን የሚፈፅመው አይደለም። ማኅበረሰቡን ያላስተባበረ እና ያላካተተ የሕግ ማስከበር እርምጃ ውጤታማ እንደማይሆን በተደጋጋሚ ታይቷል። ስለሆነም መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን መላውን ማኅበረተሰብ ባሳተፈ መልኩ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ በየቀበሌው የፀጥታና አካባቢ ጥበቃ ሥርዓት እንዲዘረጋ ለማሳሰብ እንወዳለን። በተለይም መንግሥት በተደጋጋሚ በመግለጫ ጭምር የችግሩ አካል እንደሆኑ የሚገልፃቸው የመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችን ወደ ተጠያቂነት በማምጣት ራሱን እንዲያጠራ አፅንኦት ሰጥተን እናሳስባለን። ለዚህም ኅብረተሰቡን የመፍትሄው አካል ማድረግ ወሳኝ ነው። መንግሥት በቅርብ ጥቃት የተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደመደበኛ ሕይወታቸው የሚመለሱበት ሁኔታን በአፋጣኝ እንዲያመቻች እንዲሁም ሌላ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን። ተመሳሳይ ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች ሊፈጸሙ የሚችሉባቸው ቦታዎችን አስቀድሞ በመለየት በልዩ ትኩረት ጥበቃ እንዲደረግም እናሳስባለን። በተለይም የክልል አስተዳደሮች በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ የመጀመሪያ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
- ኢዜማ በክልል የተደራጀው ልዩ ኃይል በምንም መስፈርት ሕጋዊ ነው ብሎ እንደማያምን እና ለዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል። ይህ አደረጃጀት በሀገር አንድነት ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ተጨባጭ አደጋ ማሳያ በትግራይ ክልል ሰሞኑን የተከሰተው ክስተት አንዱ እና ዋነኛው ነው። በዘውግ ላይ የተመሠረተው የሀገራችን ፖለቲካ አንዱን የዘውግ ማንነት ከሌላው ለመከላከል ወይም ሌላውን ለማጥቃት በሚዋቀረው የልዩ ኃይል እየተደገፈ የሀገራችንን ሕዝብ ወደበለጠ ስቃይ እና የጭንቅ እየከተታት ይገኛል። ሕዝቡም እርስ በእርሱ በጠላትነት እንዲተያይ የሚያደርግ እኩይ አደረጃጀትም መሆኑን በተደጋጋሚ በተግባር ለማየት ችለናል። ስልዚህም በየክልሉ በስፋት የተደራጀውን ልዩ ኃይል ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ ወይንም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚቀላቀልበትን አሠራር እንዲዘረጋ እንጠይቃለን።
- በሁሉም አካባቢ የምትገኙ የኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች በተለመደው ሥነ-ምግባር በየአካባቢያቹ ሰላም እና ደህንነትን ለማስከበር በንቃት ማኅበረሰቡን በማስተባበር እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንድትሠሩ እናሳስባለን።
በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚጠበቀው የሁሉም ዜጎች እኩል መብት የሚከበርበት እና ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲመሠረት እንደሆነ በፅኑ እናምናለን። የሀገራችን አንድነት እና ሰላም ተጠብቆ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር አንድነት እና ሰላም ተባብረው ለመሥራት ፈቃደኛ እና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ ተቀራርበው እንዲሠሩ የሚያስችል ከምር የሚወሰድ የውይይት መድረክ መዘጋጀት አለበት። ይህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎች ግን ሁሉም የሕግ የበላይነትን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሙትን የቃልኪዳን ሰነድ የሚያከብሩ መሆን አለባቸው። የደህንነት እና የፍትህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት መቻላቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ውጤታማ እንዲሆን የማይተካ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም መንግሥት ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ ስልጣኑን አረጋግጦ እውነተኛ እና ለውጥ ማምጣት የሚችል ውይይት እንዲጀመር መንገድ የመጥረግ ሥራውን በአፋጣኝ አጠናቆ ሁላችንም ትኩረታችንን ወደዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንድናዞር አበክረን ጥሪ እናደርጋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ምNovember 6, 2020 at 5:10 am #16658AnonymousInactiveከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!
በቅርቡ በወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ፣ ባለፈው ሳምንት በጉራፈርዳ በአማራ ዜጎቻችን ላይ የተካሄደው ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በጽኑ እንደሚያወግዝ ይገልጻል። እንዲሁም ይህንን ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ኃይሎች ለሕግ እንዲቀርቡ ፓርቲያችን አበክሮ ይጠይቃል።
ይህ የዘር ፍጅት እየተባባሰ በመምጣቱ እና ማቆሚያው ባለመታወቁ መንስ ዔውም የአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ዳተኝነት መሆኑን የተገነዘበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዚህ የዘር ፍጅት አስፈጻሚው የመንግሥት አካልን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት በፓርላማው የተነሳበትን ተጠያቂነት መሠረት በማድረግ እና ህወሓት በሰሜኑ እዝ ላይ በከፈተው ጥቃት በህወሓት ላይ ጦርነት አውጇል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጠየቁት መሠረት እና ከጦርነቱ ጎን ለጎን ህወሓት በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ እና አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል።
ልክ በህወሓት ላይ እንደሚካሄደው ጦርነት የዘር ፍጅት እየፈጸመ በሚገኘው በኦነግ ሸኔ እና በኦሮሞ ጽንፈኞች እና ተመሳሳይ ተግባር በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በሚፈጽሙት ሁሉ ላይ መደረግ ያለበት የዘገየ እርምጃ እንደሆነ የባልደራስ እምነት ነው። ይህም በሽብርተኝነት የመፈረጁ እርምጃ በዘር ፍጅት ላይ በማስፈጸም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉትን ማጠቃለል ይኖርበታል።
ሀገራችንን ለዚህ ሁሉ የዘር ፍጅትና ትርምስ ውስጥ የከተታት ህወሓት እና ኦነግ ያዘጋጁት ሕገ-መንግሥት ለሀገር አንድነት እና ስጋት ምንጭ ስለሆነ ሊታገድ ይገባል። ከጦርነቱ በኋላ መንግሥት ሕገ-መንግሥቱ የሚታገድበትን እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚስማሙበት አዲስ ሕገ-መንግሥት እንዲዘጋጅ ሁኔታዎችን ሊያመቻች እንደሚገባ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል።
በመጨረሻም፥ አሁን በሀገራችን በህወሓት ላይ የሚደረገው ጦርነት ተገቢ እንደሆነ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል። ዳሩ ግን ወንድም በሆነው በትግራይ ሕዝብ ላይ እልቂት እንዳይፈጸም ፓርቲያችን ማሳሰብ ይወዳል። በጦርነቱ ላይ ለሚሳተፉት የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፓርቲያችን ልዩ ክብር አለው። ጦርነቱንም የሚመሩ ባለስልጣናት ከእልህ እና ከቂም በቀል በራቀ ሕግን በማስከበር ብቻ እንዲመሩ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በሂደቱ መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊታችን እና ለአማራ ልዩ ኃይል አክብሮት እና እድናቆቱን ዳግም እየገለጸ፥ ሌሎችን ሀገራዊ ጉዳዮችን ከጦርነት ጎን ለጎን የሚፈቱበትን አማራጭ ላይ ሁሉም ስለኢትዮጵያ ያገባኛል የሚል ኃይል እንዲሳተፍ ያሳስባል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ምDecember 7, 2020 at 2:54 am #16915AnonymousInactiveየአማራ ብልጽግና ፓርቲ ለሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ካልታገለ እንደ ብልጽግና መቆም አይችልም!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ አቋም
ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.
ባህር ዳርስናጠፋ የሚገስጸን፣ ስናለማ የሚያግዘን ሕዝብ እንዳለን እናምናለን። በሕዝባችን ስብራት ላይ ተደማሪ ስብራት መሆን ስለማንፈልግ ከሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በመነጨ ቅን ልቦናና ፍላጎት የሕዝባችንን ድምጽ ለማክበርና ለማስከበር ተዘጋጅተናል። የብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ማቅ እና ድሪት አውልቆ የሕዝብን ሀቀኛ ፍላጎትና እውነተኛ መሻት የሆነውን መካከለኛ አማራጭና የወሳኝ ኩነቶች ወሳኝነት ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚበጀውን የፕራግማቲዝም (pragmatism) ድርና ማግ ተጎናጽፎ ነው። በብልጽግና እምነት ቋሚና የማይለወጥ እውነት የለም፤ ሁሉም ነገር ቋሚ ሊሆን አይችልም። በብልጽግና እምነት የማይለወጥ መሠረታዊና ቁሳዊ የሆነ ነገርም አይኖርም። ከብልጽግና ርዕዮተዓለማዊ እምነት አኳያ ቋሚና የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ እሱም ኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
መደመርን መንገዳችን፣ ብልጽግናን መዳረሻችን አድርገን ስንነሳ መደመር የሚፈልጉ ዜጎቻችንን ልንቀንሳቸው አንችልም። ዛሬ በማይካድራ፣ በዳንሻ፣ በዓላማጣ፣ በጥሙጋና በዋጃ ባጠቃላይ በራያ ዋጃ ዓላማጣና ኮረም እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ያሰማችሁትን የ‘አማራ ነን’ ድምጽ በአክብሮት የምንቀበለውና በጽናት የታገልንለት ወደፊትም የምንታገልለት የመደመር ኅብረብሔራዊ ፌዴራላዊ ትርጉም ያለው የቆየ ግን በእብሪት የተገፋና መልስ የተነፈገው የዜጎች ጥያቄ ነው።
ሁሉም የብልጽግና ቤተሰቦችና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኃይሎች እንዲረዱት የምንፈልገው ቁምነገር አለ።
በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም።
ክልላዊ ወሰናችንንና ፌዴራላዊ መብታችንን በመጋፋት በግፍ ተጠቃን እንጂ ማንንም አላጠቃንም።
በጭካኔና ያለርህራሄ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመብን እንጂ በማንም ላይ የግፍ አጸፋ አልመለስንም። በደም ፍላት ስሜት ተገፍትረው ግፍ ለመፈጸም የቃጡና የሚቃጡ በውስጣችን ያሉ ስሁታንንም ያለርህራሄ ታግለናል፤ እየታገልንም እንገኛለን።
ከልክ በላይ በተወጠረ እብሪት በትምክህተኝነት ስሜትና በተስፋፊነት ልክፍት ተወጥረው ሕዝባችንን፣ መሬታችንን፣ ታሪካችንን፣ መልካም ስማችንን፣ የ30 ዓመት ሁሉአቀፍ ክልላዊ እድገታችንን፣ እድሜያችንንና ሥነ-ልቦናችንን በግፍ ተዘረፍን እንጂ የማንንም ቅንጣት አልዘረፍንም።
የወሰን፣ የማንነትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቂያችንን በሕግና በሥርዓት አቀረብን እንጂ እንደ ትሕነግ በማን አለብኝነት ‘ዘራፍ’ አላልንም።
የተገፋን፣ የተበደልንና የተጨፈጨፍን ቢሆንም ለፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ አልፈጠርንም።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የሀገር ሉአላዊነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ቁርጠኛ አጋርነታችንን በክቡር መስዋዕትነት አረጋገጥን እንጂ ሀገራችንና ሕዝባችንን በመካድ አልወጋንም። ሀገርና ሕዝብ ክደው በወገን ላይ የጭካኔ አፈሙዝ ያዞሩትንም የታሪክ ማፈርያዎች እንደሆኑ እንረዳለን።
በሰላማዊ መንገድ እጅ የሰጡና የተማረኩ የትሕነግ ተዋጊ ኃይሎችን በወንድማማች መንፈስ ቁስላቸውን ጠረግን፣ እንዲያገግሙ በፍቅር ተንከባከብን እንጂ እንደጠላት አልገፋናቸውም። በተለመደው አማራዊ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት እልፍኛችንን ለቀን፣ ከአልጋችን ወርደን የምርኮኛነት ስሜት እንዳይሰማቸው አስተናገድናቸው እንጂ በግፍ አላሸማቀቅናቸውም።
እብሪተኛው የአፓርታይድ ቡድን በፈጸመብን ሴራ እስከአሁኗ ሰዓት ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በስጋትና በጭንቀት የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ነው። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አሁንም በስደት ላይ ይገኛሉ። በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን የሚፈሰው የአማራ ደም ዛሬም አልቆመም። በሌሎችም አካባቢዎች የስጋት ጅረት አልተገደበም። በማይካድራና በሁመራ በየቦታው የተጣሉ አስከሬኖች ‘በክብር ቅበሩኝ’ ጥሪ ቢያስተጋቡም የንጹሃኑ በድኖች ግን ዛሬም ድረስ ተለቅመው አላለቁም።
ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ ጥንተ ጠላት የሆነው ትሕነግና ጽንፈኛ ወዳጆቻቸው ከትክክለኛው ወቅታዊ አውድ ፍጹም የሚቃረን ሙግትና ትንታኔ ሲሰጡ ልማዳቸው መሆኑን ብናውቅም ለአንድ አንድ የትግል አጋሮቻችንና ደጋፊዎቻችንን ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን።
- ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አረመኔውና የአፓርታይድ ሥርዓት አቀንቃኙ ትሕነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የተጠናና የተደራጀ ሁሉ-አቀፍ ጥቃት ሲፈጽም የወራሪነት፣ የተስፋፊነትና የጨፍጫፊነት አድማሱን በማስፋት በ24 ሰዓት ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ የአማራ ክልል አቅጣጫዎች ጎንደርንና ወልድያን የመቆጣጠር ግብ አስቀምጦ ነው። ይህንን እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ከ3 ዓመት ያላነሰ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ትሕነግ ያስቀመጠውን የወራሪነት ግብ በመቀልበስ ሀገርና ሕዝብን ለመታደግ በወትሮ ዝግጁነት መፈጸሙ የአማራን ሕዝብ ሊያስመሰግነው ሲገባ፥ በጥርጣሬ እንድንታይ የሚያደርግ በፍጹም አይሆንም። የተከፈተብንን የግፍ ጦርነት ተከላክለንም፣ አጥቅተንም ጦርነቱን መቀልበሳችንና በግፍ ተነጥቀን የነበረውን ተፈጥሯዊ መብታችንን በእጃችን ማስገባታችን (repossession right) የተፈጥሮን ሕግ የሚቃረን ሳይሆን በእብሪተኞች የማይታረቅ ተቃርኖ መቃብር ላይ የተረጋገጠ ድል ነው። ስለሆነም እርስት ለማስመለስ ያልታገለን ይልቁንም ላለፉት 30 ዓመታት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየን ሕዝብና መንግሥት እርስት ለማስመለስ እንደተዋጋ አድርጎ ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አመክንዮ የጎደለው ድምጽ ማሰማት ነውር ነው እንላለን። በእርግጥ እርስት ማስመለስ የሚለው ትችት ለባለእርስቶች የተወረወረ የበላ-ልበልሀ ክርክር መሆኑ የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ፍትሀዊነት ያረጋገጠ ሀቅ በመሆኑ ሀሳቡን ደጋግማችሁ ለተጠቀማችሁ ሁሉ ምስጋና እናቀርብላችኋለን።
- እንደ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ሕዝብ ሀቅ ይታወቃል። የአማራ ሕዝብ ሀቅ ዛሬም በአደባባይ በሕዝባዊ ሰልፍ በይፋ እንደሚታየው የማንነት፣ የወሰን፣ በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት ፍትሀዊ ጥያቄ ነበር። ከ500ሺ ሕዝብ በላይ የተፈናቀለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተገደለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተሰወረባቸው እነዚህ አካባቢዎች ዛሬም የተረጋገጠ የጅምላ መቃብር የተገኘባቸውና የአፓርታይድ ሥርዓት በተጨባጭ የተፈጸመባቸው የትሕነግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ጭካኔ ማረጋገጫ የግፉአን መቀበርያ አጽመ እርስቶች ናቸው።
በግፍ የተጨፈጨፉ የንጹሀን ወገኖቻችን አስከሬኖች ተለቅመው በክብር ባላረፉበት በዚህ ወቅት የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት የወንበዴውን ቡድን ወንጀል ለመደበቅና ለማድበስበስ እየተፈጸመ የሚገኝ ሌላኛው የትሕነግ ሸፍጥ ማምለጫ መንገድ ሲሆን፥ የአካባቢውን ነባራዊ ሀቅ በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት የሚራመዱ የተሳሳቱ ሀሳቦች የሞራል ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው።
ስለሆነም የሕግ የበላይነት ለማስከበር፣ የሀገር ሉአላዊነት ለማጽናት በተደረገ ሁሉ አቀፍ የትግል ጀብዱ በታሪክ አጋጣሚ ወደባለእርስቱ የገቡ አካባቢዎች (repossessed lands) ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በሥርዓቱና በአግባቡ በቀጣይ ማየት ይቻላል የሚል እምነት አለን። ግን ደግሞ የትሕነግን የአፓርታይድነት የወንጀል ፈለግ (criminal scene) መፈተሽና መመርመር፣ ለትግራይና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማጋለጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለን። ስለሆነም:-
-
- ላለፉት 50 ዓመታት የዜጎች ማጎርያና ማሰቃያ የሆኑ ከመሬት በታች የተሰሩ ዋሻዎች (underground torching caves) ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው።
- ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጅምላ መቃብሮች ታስሰው ላለፉት 50 ዓመታት እንደ ሕዝብ የተፈጸመብንን ግፍና ጭካኔ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን።
- በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ግፈኛና ግፍን ነቅሎ በአዲስና በተረኛ ግፈኛና ግፈኝነትን ማጽናት አይደለም። ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ችግር ከግፈኞች አልነበረም። እንደሀገር ግፈኞችን መቅበር የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በየታሪክ ምዕራፉ ግፈኞችን መቅበር የምትችል ሀገር ግፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ግን አልቻለችም። ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ ግፈኝነትን በጽናት በሚታገልበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ የየበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ እየጠየቅን፥ በእኛ በኩል እብሪተኝነትም ሆነ ግፈኝነት የሕዝባችንን ክብር ዝቅ ስለሚያደርገው በጽናትና በታማኝነት የምንታገለው መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።
- በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሕግ የበላይነት የምናስከብር መሆኑን እያረጋገጥን፤ በቤንሻንጉል ክልል በሕዝባችን ላይ ተደጋጋሚ ግፍ የሚፈፅሙ የእብሪተኞች ቅሪት ዓላማና ፍላጎት በድል እንደሚቋጭ ሳንጠራጠር የተጀመረውን ሕግ የማስበር ሥራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ጎን ለጎንም የተፈናቃይ ወገኖቻችንን መሠረታዊና ወቅታዊ ፍላጎት እንዲሟላ ከማድረግ ባሻገር የሕዝባችንን እንቅፋት በሕግ አግባብ ተጠራርጎ መጥፋቱ ከተረጋገጠ በኋላ ዜጎቻችንን ተመልሰው በቀያቸው ላይ እንዲሰፍሩ የሚደረግ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን።
በመጨረሻም በትሕነግ መራሹ እብሪተኛ አፓርታይድ እርምጃ ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመባችሁ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የማይካድራና የሁመራ ሰማዕታት ሁልጊዜም በሕዝባችን ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ክብር አላችሁ።
የሕግ የበላይነት ለማስከበር በተፈጸመው እልህ አስጨራሽ ግብ ግብ ክቡር መስዋዕትነት የፈጸማችሁ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የአባቶቻችን ልጆች ስለሆናችሁ ኮርተንባችኋል፤ ለዘላለምም እንኮራባችኋለን።
የኦነግ ሽኔንና የጉሙዝ አማጺ ቡድንን ለመደምሰስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ስምሪት ወስዳችሁ ታሪካዊ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የምትገኙ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች፣ የኦሮምያና የቤንሻንጉል ክልል ሀቀኛ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጀግንነታችሁን ስንዘክር በአማራ ሕዝብ አክብሮትና ትህትና ነው።
ድል ከኢትዮጵያና ከአማራ ሕዝብ አብራክ ለተገኙ ታሪካዊ ጀግኖቻችን!!!
ውርደት በእብሪትና በትዕቢት ተወጥረው ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለሚወጉ ጠላቶቻችን!!!
ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ!!!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.