Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
Tagged: ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ, የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር, የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ, ገብረመስቀል ካሕሳይ, ጎንደር ዩንቨርሲቲ, ጣሰው ወልደሃና
- This topic has 56 replies, 3 voices, and was last updated 1 year, 7 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
April 20, 2020 at 11:56 pm #14230AnonymousInactive
የከፍተኛ ትምህርትን በቴክኖሎጂ በመታገዘ ማስቀጠልን አስመልክቶ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ በቴክኖሎጂ በመታገዘ የከፍተኛ ትምህርትን ለማስቀጠል መወሰኑን መግለፁ ይታወቃል። ይሄንንም ተከትሎ በትግበራው ዙርያ ከስጋትና ከመረጃ ጉድለት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። አፈፃፀሙ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህን ሚኒስቴሩ ይህን ፅሑፍ (ማብራሪያ) አዘጋጅቷል።
የተነሱት ጥያቄዎች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን የተመለከቱ፣ የኢንተርኔት ዋጋ ውድ መሆን ፣ የኔትወርክ ችግር መኖርን፣ የመብራት አለመኖርና መቆራረጥን፣ ሁሉም ተማሪዎች ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ አቅም ሳይኖራቸው ትግበራው የሚያስከትለውን ኢ-ፍትሃዊነት እና ቢተገበር ውጤታማ ላይሆን ይችላል ከሚል ስጋት የሚነሱ ናቸው።
ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት የሰው ልጆችን ህልውና በሚፈታተኑ አስቸጋሪ ወረርሽኞች ውስጥ አልፋለች። ከነዚህም አንዱ በዘመናችን ያጋጠመን ኮቪድ-19 ነው። ቫይረሱ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም መዛመት ከመቻሉ ጋር ተያይዞ የበርካታ አገራትን ዜጎች ከቤት ውጭ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ገድቧል። በሁሉም ዘርፎች ዓለምን ለቀውስ ዳርጓል።
ታዲያ ይህ ቫይረስ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ሲል መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል። ከነዚህም አንዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ወደየቤተሰቦቻቸው መመለስ ነው።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቫይረሱ መቼ በቁጥጥር ስር ውሎ እነዚህ ተማሪዎች ወደቀድሞ እንቅስቃሴያቸው እንደሚመለሱ ስለማይታወቅ ትምህርትን ከማስቀጠል አንፃር የተለያዩ አማራጮችን መመልከት አስፈልጓል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ስንመለከት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ/ UNESCO) በቀውስና አደጋ ጊዜ ስለትምህርት ማስቀጠል “Education Response in Crises and Emergencies” ሲያስረዳ፥ በችግር ጊዜ ትምህርት ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ አገራት የተለያዩ የትምህርት ማስቀጠያ መንገዶችን ተከትለው እንዲሰሩ ያስቀምጣል። በተለይም “Education 2030 Incheon Declaration and Framework for Action“ ላይ በተለያዩ የአደጋ ጊዜዎች በመደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ መንገዶችን በመጠቀም ተለዋጭ የመማር-ማስተማር ዘዴዎችን በመተግበር አካታችና ፍትሃዊ ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ስለሆነም ይህ በትምህርት ላይ የነበሩና በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎቻችንን በተቻለ መጠን በሚቻለው ሁሉም አማራጭ ንባቦችን እንዲያገኙ በማድረግ እያነበቡ እንዲቆዩና ከትምህርታቸውም እንዳይቆራረጡ ማድረግን ግብ አድርጎ እየተሠራ ያለ ተግባር ነው። ስለዚህ እንደሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ባለን አቅም፣ ሀብትና ግብዓት የከፍተኛ ትምህርቱን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማስቀጠሉ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር በመሆኑ ውሳኔው ተላልፏል።
በዚህም የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን በተመለከተ፡
የሁለተኛ ሴሚስተር የሁሉም ትምህርት ዓይነቶች ሞጁሎች (modules)፣ አጋዥ ንባቦች እና ሌሎችም በየትምህርት ዓይነቱ ተሰንደው የሚገኙባቸው ድረ-ገፆችን (ዌብሳይቶችን) የማሟላት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በዚህም፦
-
- የተዘጋጁ የኮርስ ማቴሪያሎችና አጋዥ የትምህርት መጽሃፍቶች ተደራሽ የሚሆኑበት የዲጂታል ላይብረሪ ዝግጁ ተደርጓል። (http://ndl.ethernet.edu.et/) አስፈላጊ በሆኑ የትምህርት ይዘቶች እየበለፀገ ይገኛል።
- እንዲሁም በርካታ ይዘቶችን የያዘዉ የ TechIn ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ዝግጁ ሆኗል (http://library.techin.et/)
- የኦንላይን ትምህርት መስጠት የሚያስችል የLearning Management System/MOOCS ዝግጁ ተደርጓል። (https://courses.ethernet.edu.et/)
እንዲሁም ተማሪዎች ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በስልክም ይሁን በላፕቶፕ እንዲሁም በታብሌት ወደእነዚህ ዌብሳይቶች ገብተው በሚያነቡበት ጊዜ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ከኢትዮ ቴሎኮም ጋር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
እንደተገለፀው ወረርሽኙ መቼ እንደሚገታ አይታወቅም። ነገር ግን ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑ ተረጋግጦ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እስከሚመለሱ ድረስ በተለያዩ ድረ-ገፆች (ዌብሳይቶች) ለንባብ የቀረቡላቸውን ግብዓቶች (ማቴሪያሎች) እያነበቡ ይቆዩና ሲመለሱ እንደየተቋማቱ ተጨባጭ ሁኔታ ቀሪ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት ፕሮግራም ይቀይሳሉ።
የምረቃ እና ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎችን በሚመለከት
አብዛኞቹ የማስተር (MSc, MA, MPH…) እና የፒኤችዲ (PhD) ተማሪዎች በምርምር ላይ እንደመሆናቸው ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ትምህርቱን በኦንላይን ለማስቀጠል እንዲያመቻቹ ሆኗል። በዚህም ለመማር-ማስተማሩ የሚያግዙ ግብዓቶች (ማቴሪያሎች) በኦንላይን፣ በኢ-ሜይል እና ሌሎች ዘዴዎች ለተማሪዎች እንዲቀርቡ እየተሠራ ይገኛል። ምርምሮቻቸውን ያላጠናቀቁና ዳታ ለማሰባሰብ የግድ መውጣት ከሚያስፈልጋቸው ውጭ ያሉት በሙሉ የመመራቂያ ጽሁፋቸዉን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እንዲያቀርቡ ይመቻቻል።
የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸዉ ጋር የሚገናኙበት የኦንላይን የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማድረግ፣ ማንኛዉንም ሰነዶችን ማጋራት ሌሎችንም የቨርቹዋል (virtual) ግንኙነቶች ማድረግ የሚያስችል የ Office 365 Teams ቴክኖሊጂ ዝግጁ ተደርጓል። በተጨማሪም በሃገር ዉስጥ የተሠሩ የ Thesis and Dissertations ሰነዶች ለማጣቀሻ እንዲሆኑ በ<https://nadre.ethernet.edu.et/> ዝግጁ ሆነዋል።
በተጨማሪም አብዛኞቹ የ Educational Private አገልግሎቶች ከኢተርኔት ዳታ ማዕከል የሚሰጡ ስለሆነ፣ ለዳታ ማዕከሉ ለጊዜዉ ያልተቆጠበ የኢንተርኔት ባንድዊድዝ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲያቀርብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመነጋገር ላይ ይገኛል።
ይህ አቅጣጫ እንዳለ ሆኖ ዩኒቨርስቲዎች እንደየትምህርት ክፍላቸውና የትምህርት ዓይነቶቹ እንደሚያስፈልጓቸው ተጨማሪ ሁኔታዎች እያዩ ሌሎች የመገናኛ ፕላትፎርሞችንም የሚያቻቹ ይሆናል።በመጨረሻም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሁን በዓለማችን ያጋጠመውን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሁሉም ዘርፍ ያለውን የሀገራችንን እና የዜጎቿን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እና በተቻለ መጠን ሁሉ ትምህርትን ተደረሽ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትክክለኛ የTelegram Channel <https://t.me/MinistryoSHE>ነው። ይቀላቀሉ! በሌላ አማራጭ ትክክለኛ መረጃ ያግኙ።
May 8, 2020 at 12:52 am #14425AnonymousInactiveየጤና ሳይንስ ምሩቃን በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ከሀገር ውጭ ሲወጡ ደግሞ በተማሩበት የሙያ መስክ ጥራት ያለውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ የሚያበቃ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና የስልጠና ፕሮግራም ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የጤና ሳይንስ ትምህርቶችን ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር Jhpiego ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር የጤና የሰው ኃይል ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም (Health Workforce Improvement Program /HWIP/) ላይ የቪዲዮ ውይይት (webinar) አድርጓል።
በውይይቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጤና ሳይንስ የሚመረቁ ምሁራን በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ከሀገር ውጭ ሲወጡ ደግሞ በተማሩበት የሙያ መስክ ጥራት ያለውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ የሚያበቃ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና የስልጠና ፕሮግራም ደረጃ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው እንዲህ ዓይነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እገዛም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በጤና ዘርፍ በየዓመቱ መሰልጠን ያለባቸውን ቁጥር አጥንቶ መመጠን፣ ኢ-ለርኒንግን (e-learning) ማጠናከር፣ የትምህርት መርሃግብሮች ዕውቅና አሰጣጥ (programs accreditation) ላይ መሥራት፣ የመርሃግብር ደረጃ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎች ይጠበቃል ብለዋል።
የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው ሆስፒታል እና የጤና ማዕከላት ሲኖራቸው የሌላቸው ደግሞ ተማሪዎቻቸውን በአከባቢያቸው ከሚገኙ የጤና ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ያሰለጥናሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ስለሆነም በጤና ዘርፍ ያሉ አመራሮችን፣ መምህራንን እና የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባትና ግብዓት ማሟላት ለጥራት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ የ5 ዓመት መሆኑን እና በጤና ዘርፍ የሚወጡ ተማሪዎች ጥራት እንዲኖራቸው መሥራትና፣ ለጤና ዘርፍ ትምህርት ጥራት የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ግብዓቶችንና ቴክኒካዊ ምክረሃሳቦችን በማቅረብ ተግባራዊ እንዲረግ መሥራት ዋና ዓላማቸው መሆኑን የገለፁት የJhpiego ዳይሬክተር ዶ/ር ተግባር ይግዛው የጤና ሳይንስ ትምህርትን ጥራትን ለመደገፍ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የ39.5 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክቱን ተግባዊ ለማድረግም በጤና ትምህርት ዘርፍ በሚደረጉ ድጋፎች ላይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በተለይ ለጾታ እኩልነት ቦታ እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።
ዶ/ር ተግባር ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ውስጥ የሚከሰቱትን ወሳኝ የሰው ኃይል ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ መንገዶችን ለማመቻቸት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ስምምነት የሚሠራ መሆኑን ገልጸው፥ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራትም የኢትዮጵያን የጤና ባለሙያዎች ጥራት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ብቃት ለማሻሻል እና የጤና የሰው ኃይል አስተዳዳሪዎች ችሎታን ለመገንባት በተቋም እና ግለሰቦች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ብለዋል።
በውይይቱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ቢሠራበት የሚሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል። በዚህም በሚኒስቴሩ በኩል ከድርጅቱ ጋር በጋራ የሚሠራባቸው መስኮች ተለይተው እና የትግበራ ዕቅድ አውጥተው ወደሥራ እንደሚገቡ ተጠቁሟል።
በውይይቱ ዩኒቨርሲቲዎችን ዓለምአቀፋዊ ማድረግ ላይ የሚሠራውን ሥራ ለማገዝ ዕውቅና መስጠት (accreditation) መጀመር እንዳለበትና በተለይ የሕክምና ትምህርት ላይ ቀድሞ መጀመር ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑም ተመላክቷል።
June 18, 2020 at 12:36 am #14838SemonegnaKeymasterዲላ ዩኒቨርሲቲ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የሥነ ሕዝብ እና የጤና ምርምር ማዕከል ተመረቀ
ዲላ (ኢዜአ) – ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በወናጎ ወረዳ ያስገነባው የሥነ ሕዝብ እና የጤና ምርምር ማዕከል ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ማዕከሉ፥ ከNorwegian Programme for Capacity Development in Higher Education and Research for Development (NORHED) ጋር በመተባበር በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የተገነባ ሲሆን፥ በዋናነት በአከባቢው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ መጠጋጋት (overpopulation) የሚያስከትለውን ችግር በምርምርና ጥናት ለመቅረፍ ይሠራል። እንዲሁም በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ እና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ምርምር በማካሄድና በማስተማር ሕብረተሰቡን ለማገዝ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ ለወጣቶች የውይይት ዕድል የሚፈጥርና ዕውቀት የሚገበዩበት ይሆናል ነው ያሉት። በቀጣይ የሰው ኃይልና ግብዓቶችን በማሟላት፣ የምርምር ሥራ ለሚሰማሩ ምሁራን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን አስተዳደሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው፥ በወናጎ ወረዳ በአንድ ኪሎ ሜትር ካሬ ውስጥ ከ1,200 በላይ (>1,200/km2) ሕዝብ የሚኖርበትና ከፍተኛ ጥግግት (overpopulation) እንዳለ ገልጸዋል። በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠርም ሆነ በጥግግቱ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን በምርምር ለመለየት የማዕከሉ መገንባት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ማዕከሉ የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን ወደ ፊት ዩኒቨርሲቲው ለሚሰራው የምርምር ሥራ ሕብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የሥነ ሕዝብ እና የጤና ምርምር ማዕከሉ በጤናና በሥነ ተዋልዶ የምርምር መረጃዎች ምንጭ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን በአካባቢ ለሚገኘው ሕብረተሰብና ለጤና ተቋማት ለማድረስ የሚረዳ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሣይንስ ኮሌጅ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሰላማዊት አየለ ናቸው።
በሥነ ተዋልዶ መስክ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ የምርምር ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ ጠቀሜታው ከዩኒቨርሲቲውና ከማኅበረሰቡ አልፎ ለሀገር የጎላ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
ለግንባታ የፈጀው አጠቃላይ ካፒታል 4.9 ሚሊዮን ብር በላይ እንደደሆነ የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ኢ/ር በፍቃዱ መኩሪያ ተናግረዋል። ከምረቃው ሥነ ሥርዓት ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲውና የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ አመራሮች የሁለተኛውን አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በማስታከክ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አካሔደዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 16, 2020 at 12:05 pm #15097AnonymousInactiveየከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ተሰጥቷቸው የዓመቱን ትምህርት ያጠናቅቃሉ ― የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።
የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አጋማሽ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) በመከሰቱና በፍጥነት በመዛመቱ ምክንያት የዓለም ሀገራት የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተቋርጦ መንግሥታት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ቅድሚያ ሰጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
እንደሚታወቀው ቫይረሱ ወደሀገራችን መግባቱ በምርመራ ከተረጋገጠበት ጀምሮ የሀገራችን መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ እየሠራ ይገኛል። በዚሁ መሠረት የቫይረሱን መስፋፋት ለመቀነስ ሲባል የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የገጽ-ለገጽ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ይታወሳል። ሆኖም ባሉበት ሆነው ከትምህርትና ንባብ እንዳይርቁ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።
የትምህርትና ስልጠና ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ከትምህርትና ስልጠና ተቋማት መከፈት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እያነሱ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተዘጋጅቷል።
አሁን ባለው ሁኔታ ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረው የኦንላይን ትምህርት የሚቀጥል ሆኖ፥ ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ ሌሎች መንገዶችንም በቀጣይ የሚታዩ ይሆናል። ለዚህም ሁሉም ዜጎች የቫይረሱን መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ መሥራት ያስፈልጋል። ስለዚህ ተማሪዎችና መምህራን ባሉበት ሆነው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ሌሎችንም እንዲያስተምሩ ይጠበቃል። ያም ሲሆን የስርጭት መጠኑ ሲቀንስ ቀጣይ የትምህርትና ስልጠና አካሄዶችን ይፋ የምናደርግ ይሆናል።
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የለይቶ ማቆያና ምርመራ ማዕከላት በመሆን በማገልገል ላይ ሲሆኑ፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ እንዲሁም መጠነ ሰፊ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት እያገዙም ይገኛሉ። ስለሆነም ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም የትምህርትና ስልጠና ተቋማቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ የሚቆዩ ይሆናል።
በዚሁ መሠረት ወደፊት በሀገራችን የሚኖረውን የቫይረሱን ስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ ከሚመለከተው አካል በሚሰጠን መረጃ መሠረት ነባር ተማሪዎችን ከተለመደው አካሄድ በተለየ ሁኔታ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ሥራ ተጀምሯል።
ነባር ተማሪዎችን በተመለከተ፡-
ሙሉ በሙሉ ኮርስ ያጠናቀቁ ተመራቂ ተማሪዎች (ለምሳሌ፡- የሕግ፣ የእንስሳት ሕክምና /veterinary medicine/፣ የሕክምና ተማሪዎች ወዘተ)፥ የመጀመሪያ ሴሚስቴር ያላጠናቀቁ ተማሪዎች፣ ሁለተኛ ሴሚስቴር ምንም ያልጀመሩ ተማሪዎች በባች/በደረጃ ተለይተዉ፣ የሴሚስቴሩን ኮርስ እስከ 25% እና 75% ያጠናቀቁ ተማሪዎች የቀሩ ምዕራፎች ተለይተዉ ማካካሻ ትምህርት በማመቻቸት እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ይሆናል።ተግባራዊ ለማድረግም በሁለት ዙር ተከፍለው ወደ ተቋማቱ እንዲገቡ በማድረግ የገጽ-ለገጽ ትምህርት ወስደዉ እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ሆኖ በአጭር ጊዜ ለማካካስ እንዲቻል የኦንላይን ትምህርቱም የሚቀጥል ትምህርት የሚሰጥበት አካዴሚክ ካሌንደር (academic calendar)፣ ቀናትና ሰዓታት ማሻሻያ የሚደረግባቸው ይሆናል። ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲዎች ሲመለሱም በቤተ-መፃሕፍት፣ በመማሪያ፣ መመገቢያ እና ማደሪያ ክፍሎች የሚኖራቸው ቁጥርም የተመጠነ ይሆናል።
በዚሁ መሠረት፡-- ተመራቂ ተማሪዎች እና ተመራቂ ያልሆኑ 4ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ያሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 3፣ 4 እና 5 ሰልጣኞች በመጀመሪያዉ መርሃ-ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
- የ1ኛ ዓመት፣ 2ኛ ዓመት እና ተመራቂ ያልሆኑ የ3ኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 1 እና 2 ሰልጣኞች በሁለተኛዉ መርሃ ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
- የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አዲስ ገቢ ተማሪዎች እና የነባር ተማሪዎች ቀጣይ ዓመት ትምህርቶች የማካካሻ ፕሮግራሞች ከተካሄዱ በኃላ በቀጣይ የሚገለፅ ይሆናል።
በዚሁ አጋጣሚ ተማሪዎች ወደትምህርት የሚመለሱበት ዕለት ተወስኖ እስከሚገለፅ ድረስ ከቫይረሱ ራሳቸውን በመከላከል ባሉበት ሆነው ንባባቸውን እንዲቀጥሉና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዲሁም በአከባቢያቸው ያሉ ወገኖችን እንዲያስተምሩ መልዕክት እናስተላልፋለን።
ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.
ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር)
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርJuly 21, 2020 at 1:38 am #15139AnonymousInactiveሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ900 ተማሪዎች የትምህርት መከታተያ ሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ድጋፍ አደረገሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በመጪው የትምህርት ዘመን በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፀጋዬ ደዮ በተቋሙ በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ላይ እንዳሉት፥ በ2013 የትምህርት ዘመን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዘኛ ቋንቋና ሥነ-ልሳን በተጨማሪ በሶሻል አንትሮፖሎጂ (social anthropology) ዘርፍ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል።
እንዲሁም በጤና ሣይንስ ኮሌጅ የትምህርት ዘርፍ በሥነ ተዋልዶ፣ ሥነ ምግብ፣ ማኅበረሰብ ጤና፣ እናቶችና ሕፃናት ጤና የትምህርት ዘርፎች እንደሚከፈቱም አስታውቀዋል።
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በሚጀምራቸው ዘጠኝ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በእያንዳንዱ የትምህርት ዘርፍ እስከ 15 የሚደርሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርና ይህም ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ ለውጥ መሆኑን ዶ/ር ፀጋዬ ገልጸዋል።
የትምህርቱ ዓላማ ዩኒቨርሲቲው አቅምና ዕውቀትን ከማጐልበትና ከማሻገር በተጓዳኝ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ ለማመቻቸት ነው ብለዋል። በተለይ በትምህርት ጥራት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንዲወገዱ የትምህርት መርሃ ግብሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የውጭ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶ/ር የሺመቤት ቦጋለ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ለሚጀምረው የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በቂ የሰው ኃይልና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። መረሃ ግብሩ በትምህርት ተግባቦት ቴክኖሎጂ በቤተ ሙከራዎችና በኢንተርኔት በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተ መጽሕፍትን አደራጅተናል ብለዋል።
የሚጀምረው መረሃ ግብር የተቋሙ መምህራንና ተማሪዎች አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የኦሮምኛ ቋንቋ ዲፓርትመንት ኃላፊ ወ/ት ሁርሜ ደገፋ ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለአንድ ቀን በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው ከ100 በላይ መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች ተካፍለዋል።
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም. ከተቋቋመ ጀምሮ በ33 የትምህርት ዘርፎች ከ4 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱም ተመልክቷል።
ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን በሬዲዮ በመከታተል ላይ ለሚገኙ 900 ተማሪዎች የሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ድጋፍ አደረገ። ድጋፉ ከ700ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ 500 ሬዲዮኖችና 400 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች ናቸው።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት እንደገለጹት፥ ድጋፉ በመቀበያ ችግር ምክንያት የሬድዮ ትምህርት ፕሮግራም መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ድጋፉ የተደረገላቸው መቀሌን ጨምሮ በአምስት የክልሉ ወረዳዎች የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች እንደሆኑ አመልክተው፥ በየቤታቸው ትምህርታቸውን በሬዲዮ ለመከታተል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይቋረጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል – ፕ/ር ክንደያ። ተማሪዎች በሬድዮ የሚተላለፍ ትምህርት በመከታተል ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ፕ/ር ክንደያ አስረድተዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፥ የተደረገው ድጋፍ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። ከዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አይነስውሩ አለም ተስፋዬ በሰጠው አስተያየት የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት መርሃ ግብሩ በተጨማሪ ወቅታዊ የዓለማችን ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችለን ነው ብሏል። በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ድጋፍ ማድረግ ሰብአዊና ዜግነታዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።
August 16, 2020 at 2:25 am #15429AnonymousInactiveየቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክት ግንባታ ደረጃ 84 በመቶ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ – በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተገነባ ያለውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት /Innovation and Technology Talent Development Institute/ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፌደራልና የክልል ቢሮ አመራሮች ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጎብኝተውታል። ከጉብኝቱ በተጨማሪም አመራሮቹ የአረንጓዴ አሻራቸውን በማዕከሉ ቅጥር ግቢም አኑረዋል።
እንደ የኢኖቬሽን ልማትና ምርምር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ክቡር አቶ ሲሳይ ቶላ ፕሮጀክቱ ባለፉ ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ምክንያቶች መዘግየት አጋጥሞት ነበር። በአሁኑ ወቅት በተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ በተጠናከረ አመራርና ድጋፍ በማጠናቀቅ በ2013 ዓ.ም. ሁለተኛ ሩብ ዓመት መጀመሪያ ወራት ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ለአካባቢው ማኀበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር በሀገራችን የሚገኙ ባለተሰጥኦዎችን አሰባስቦ ተሰጥኦዋቸውን በማጎልበት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩበት ስለሆነ፥ መላ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉትና እንዲሳተፉበት ጥሪ አቅርበዋል። ያለፉ ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ለውጥ ሂደቶች የተነሳ ያጋጠሙ መዘግየቶችን በቀሪ ወራት አካክሶ ሥራ ለማስጀመር የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅም ተመድቦለታል።
ክቡር አቶ ሲሳይ አክለውም ለዓመታት ያጋጠመ የመዘግየት ችግር ተካክሶ በሦስት ወራት ውስጥ አመርቂ የግንባታ ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል። በቀጣይም በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉና መሟላት የሚገባቸው ግብዓቶችን ከግንባታው ጎን ለጎን እየተሟሉ ይገኛል። ለስልጠናና ትምህርት እንዲሁም ተሰጥኦ ማፍለቅና ትግበራ የሚውሉ የቁሳቁስ እገዛና ድጋፍ ከልዩ ልዩ አካላት መገኘት ጀምሯል ያሉት ክቡር አቶ ሲሳይ፥ በቀጣይ የግሉ ዘርፍ፣ ሀገር-አቀፍና ዓለም-አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ልዩ ልዩ ተቋማት እና የመንግሥት አካላትን ትብብር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን ብለዋል።
የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ሥራ ሲጀምር በየደረጃው ካሉ አመራሮች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እንደሚጠበቅ አውስተው፥ ተቋሙ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካና ዘላቂነት እንዲኖረው የአሠራር መመሪያዎችን፣ የትብብር ማዕቀፎችን፣ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትን፣ የተውህቦና የክህሎት መለያ መስፈርቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ቀድሞ የማዘጋጀት ሥራ ከወዲሁ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ለዚህ ሀገራዊ ማዕከል መገንቢያ ቦታ በመስጠት፣ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ክስተቶች ወቅት የተጀመሩ ግንባታዎችና ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላደረጉ የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል። ባለተሰጥኦዎችም ወደፊት ወደተቋሙ መጥተው በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን እገዛና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ሁሉ ትብብራቸው እንዳይቋረጥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ተቋሙን ሥራ ማስጀመር የሚያስችሉትን የግንባታ ሥራዎችን ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንዲቻል በተሰጠ አመራር እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የግንባታ ሥራ ተቋራጩ ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር መስፍን ባልቻ ናቸው። እንደ ኢ/ር መስፍን የቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ ወርክሾፖች፣ የመማሪያ ክፍል እና የማደሪያ ሕንጻዎችን በልዩ ትኩረት ተገንብተው ከ78% እስከ 90% የአፈጻጸም ደረጃዎች ማድረስ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ያለበት አማካይ የአፈጻጸም ደረጃ ከ84% በላይ ነው። ቀሪ የሲቪል ሥራዎችን በማጠናቀቅ የቁሳቁስ ገጠማና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ ለማጠናቀቅ እየተሠራ በመሆኑ በቀጣይ ሦስትና አራት ወራት ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል ብለዋል።
የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ግንባታ ከሦስት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በተሰጠ አምስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በተያዘ የመንግሥት በጀት የተጀመረ ነው። ከመላው ኢትዮጵያ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል እስከ 1000 ባለተሰጥኦዎችን መልምሎና ተቀብሎ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለግን ተሰጥኦዋቸውን በማልማት፣ በማጎልበትና ወደ ተጨባጭ አምራችነት በመቀየር ለሀገራዊ ብልጽግና መሠረት መጣል የሚችል ተቋም መሆኑን መግለጻችን ይታወቃል።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
August 19, 2020 at 3:01 am #15470AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው አሰልጥኖ ነሐሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምረቃ ካበቃቸው 2 ሺህ ተማሪዎች በዶክትሬት ዲግሪ እና በሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጥቂት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በቨርቹዋል (virtual) አማካይነት ምርቃታቸውን ማካሄዳቸው ታውቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ለማ ጉዲሳ፥ ተማሪዎች በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውን በተማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። “የሲቪል ሰርቪሱን ሀገልግሎት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድርግ በተማሩት የትምህርት መስክ የበለጠ መሥራት ይኖርባቸዋል” ሲሉም አመልክተዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው እንደ ኦንላይን (online) ያሉ የተለያዩ አማራጭ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ምሩቃን ተማሪዎች ማሟላት ያለባቸውን እንዲያሟሉ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ምሩቃኑ በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማሩ ሀገራዊ ለውጡንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ሀገልግሎት በመስጠት ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም ነው ያስገነዘቡት። ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣትና ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ከዛሬው ተመራቂዎች መካከል ብቸኛ የዶክትሬት ተመራቂ የሆኑት ዶ/ር ሰይፉ ተሾመ በበኩላቸው፥ በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በተሻለ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። “ሁላችንም በመተባበር ለሀገራችን ብልጽግና በአንድነትና በመተባበር መሥራት አለብን” ብለዋል።
ሌላዋ ተመራቂ መሠረት መልኬ በበኩሏ፥ በምትሰማራበት የሥራ መስክ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ እድገት የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግራለች። በሀገሪቱ በሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩሏን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጻለች።
የዛሬ ምሩቃንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በቅድመ ምረቃ እና ድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል።
ዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴም ለ300 አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች በኮሮና ቫይረስ የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቀነስ የምግብ እና የዘይት ድጋፍ አድርጓል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
August 25, 2020 at 2:40 pm #15567AnonymousInactiveለመጪው የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ከነሐሴ 20 ጀምሮ ምዝገባ እንደሚጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)፦ የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ምዝገባ ከነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚጀመር ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ትምህርት ቤቶች የቀጣይ ዓመት የትምህርት ምዝገባን ከነሐሴ 20 ጀምረው ማካሄድ ይችላሉ ብሏል።
የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀረጓ ማሞ፥ ትምህርት ቤቶች ምዝገባውን ሲያካሂዱ ኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ 19) ለመከላከል በዓለም የጤና ድርጅት እና በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር የተቀመጡ ቅድመ ዝግጅቶችንና መከላከያ መንገዶችን በሚገባ በመተግበር መሆን እንዳለበት አሳስቧል።
ትምህርት የሚጀመርበት ቀን በቀጣይ እንደሚወሰንና ይፋ እንደሚደረግም የገለፁት ዳይሬክተሯ፥ የቀጣዩ ዓመት የትምህርት ሂደት ስኬታማ እንዲሆንም ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆችና መላው የትምህርት ማኅበረሰብ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ የሚተላለፉትን ገዢና አስፈላጊ መልዕክቶች ብቻ በመከታተልና ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችልባቸውን መንገዶች ከውዲሁ በማስወገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
አካላዊ ርቀትን ጠብቆ ለማስተማር፣ የንፅህና መጠበቂያዎችን ከማዘጋጀትና መሰል የኮሮና ቫይረስን የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ቀድመው ዝግጅት የሚደረግባቸው ተግባራትም እንደሆኑ አክለው ገልጸዋል።
በምን ዓይነት መልኩ ትምህርት መጀመር እንዳለበት የተለያዩ አማራጮችን ለማመላከት ሰፊ ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን፥ ውሳኔዎች ላይ ሲደረሱ በቀጣይ ይፋ ይደረጋሉ።
የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጊዜን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርብ የሚያሳውቅ ሲሆን ተማሪዎች ራሳቸውን እያዘጋጁ እንዲቆዩ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
በመጪው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረገ ነው?
በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታወቋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት፥ የቀጣዩ ዓመት ትምህርት ምዝገባ ከነገ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች እንደሚጀመር እና ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቅደመ ዝግጅቶችንና ተግባራትን በተገቢው መንገድ በመተግበር ምዝገባ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
የበሽታው ሁኔታ እየተስፈፋ ቢሆንም የትምህርት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊ ሆኑ መገኘቱን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ወደ መማር ማስተማር ተግባር በሚገባበት ወቅት ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠራ ገልጸው፥ የፊት መሸፈኛ ጭንብል (face mask)፣ የእጅ ማፅጃ (sanitizer) እና መሰል አቅርቦቶችን ከባላድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይከሰት ተማሪዎች የፊት መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና እጅን በተደጋጋሚ በመታጠብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛ ሴሚስተር ያለፋቸውን ትምህርቶች ማካካሻ ለመስጠት መታሰቡንም ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬሽን (EBC) ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
August 30, 2020 at 10:21 pm #15644SemonegnaKeymasterበሁለቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የልህቀት ማዕከላት የሚሹትን ትኩረት ለይቶ ለመደገፍ ያለመ ጉብኝት ተካሄደ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ዳይሬክተር ጄኔራሎች፣ ከፍተኛ አማካሪዎች እና ሌሎች ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና በአዳማ ሳይንስና ቴክሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱ በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በአካል በመገኘት ዩኒቨርሲቲዎቹ የልህቀት ማዕከላት ሆነው ከተፈጠሩ ጊዜ አንስቶ ‘የመንግሥትን ተልዕኮ ተሸክመው የት ደርሰዋል? ምን ውጤት አስመዝግበዋል? ያጋጠማቸው ማነቆ ካለስ ምንድን ነው?’ የሚሉትን ጉዳዮች ለመለየትና መፍትሄ ለማስቀመጥ እንደተካሄደ ተገልጿል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ የጉብኝቱ ዓላማ በሀገራችን 16 የተለያዩ የልህቀት ማዕከላትን የያዙት አዲስ አበባ እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋቋሙለት ዓላማ አንፃር የሚገባቸውን ያህል እየሠሩ ነው ወይ የሚለውን ለማየት፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመለየትና በዚያው መጠን ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች ሐምሌ 2006 ዓ.ም መንግሥት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም እንዲሆኑ አድርጎና ተጠሪነታቸውን በወቅቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አድርጎ ሲያዋቅራቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስርጸት ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው በልዩ ሁኔታ የተመሠረቱ ሲሆን፤ ከመማር-ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር ልህቀት ማዕከልነት (centers of excellence) በኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ትስስር (industry-university linkages) እና በኢንኩቤሽን ማዕከልነት (incubation centers) እንዲያገለግሉ ታስበው ነው ብለዋል።
በልህቀት ማዕከላቱ ተማሪዎች ተምረው ሲወጡ ኢንዱስትሪውን በቀጥታ መቀላቀል የሚችሉበት አቅም እንዲያፈሩ ታልሞ መሠራት እንዳለበት ጠቁመው፥ ይህ እውን እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራዎች ጋር አገናዝበን በቋሚነት በዕቅድ እንድናግዛቸው እንሠራለን ብለዋል ፕ/ር አፈወርቅ። የልህቀት ማዕከላት በሀብት መደገፍ እንዳለባቸው ገልጸው፥ ነገር ግን ከመንግሥት ቋት ብቻ ሊሆን ስለማይቻል ሀብቶች ማፈላለግ ላይ በጋራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው፥ የተደራጀ ተቋማዊ አሠራር በመፍጠርና ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ተቋማቱን ወደ ትክክለኛ የልህቀት ማዕከልነት መለወጥ ይቻላል ብለዋል። በአከባቢያቸው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የሀገራችን የቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ ሳይንስና ምርምር ተቀባይ ብቻ ሆኖ መቀጠል የለበትም ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል፥ መሪ እንዲሆኑ ሀብት አፈላልጎ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ፈጥሮ መሥራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ በሁሉም የልዕቀት ማዕከላት የሰው ኃይል ችግር መፍታት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለሀገር ብልጽግና ካላቸውም ፈይዳ አንጻር በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንዲሚደረግላቸውም ገልፀዋል።
ቡድኑ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ጉብኝት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳ በዩኒቨርሲቲው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የገለፁ ሲሆን፤ ዓለምአቀፍ እውቅና ለማግኘት የሚያግዙ የአሠራር ሂደቶችን ተከትለው ለመሥራት እየጣሩ መሆኑን ገልፀው፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢያግዘን ያሏቸውን ተግዳሮቶች አቅርበው ውይይቶች ተካሂደው የመፍትሄ ኃሳቦችም ተጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ያሉ የልህቀት ማዕከላት፣ ቤተ-ሙከራዎች እና የግንባታ ሥራዎችም ተጎብኝተዋል።
በተመሳሳይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ሲካሄድ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ ዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከተሰየመበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተሰሩ ሥራዎችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን፥ እንዲሁም የተፈጠሩ ትስስሮችን (partnerships) እና አጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ያለውን የሰው ሀብትና ተማሪዎች መረጃ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል። በዩኒቨርሲቲው ልዩ ነው ያሉትን የደብል ሜጀር እና ፋስት ትራክ የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታንም ጨምረው አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፥ በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው 161 የሦስተኛ ዲግሪ (doctoral) ተማሪዎች አሉ።
በሁለቱ ጉብኝቶች ከተነሱት ዋና ዋና ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች ውስጥ የግዥ ሥርዓት ችግሮች፣ የተሽከርካሪዎች እጥረት፣ ብቁ መምህራን ከገበያ ላይ በቀላሉ ያለማግኘት፣ በፋይናንስ ምክንያት የግንባታ ሥራዎች መዘግየት ይገኙበታል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ ማጠቃለያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፥ የልህቀት ማዕከላት ሲባል አንድ ተቋም በአገሪቱ መሪ የሆነ የቴክኖሎጂ ማዕከል መሆን ማለት ነው። ይሄንን ደግሞ ከኢንዱስትሪ ጋር ትስስር በመፍጠር፣ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና (TVET) ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ኢንዱስትሪውን የሚመጥን፣ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ያሟላ ሰልጣኝ ለገበያ የሚያቀርብ፣ ተግባራዊ ምርምሮች የሚካሄዱበት መሆን ሲቻል ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ እንፈልጋለን ብለው ያቀረቧቸውን በመውሰድ እንሠራበታለን ሲሉም ዶ/ር ሙሉ አክለዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ ዘመናዊ የሳይንሳዊ አስተሳሰቦች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተገናኝተው ለሀገር ብልጽግና የሚውሉባቸው እንደመሆናቸው አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የልህቀት ማዕከላት በቡድኑ የተጎበኙ ሲሆን፤ በጉብኝቱም ዩኒቨርሲቲዎቹ የተለያዩ የሀገር ሀብት የሆኑና ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች ተቋማት የሌሉና በተለይ ለምርምር ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እንደ ኤሌክትሮማይክሮስኮፕ ያሉ መሣሪያዎች መኖራቸው ተመልክቷል። ይሄንንም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በጋራ ለመጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ማመቻቸት ያስፈልጋል ተብሏል። በቀጣይም ተቋማቱ የተፈጠሩበትን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ እና ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲቻላቸው የሚያግዙ የታቀዱ ድጋፍና ክትትሎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ይካሄዳሉ ተብሏል።
አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የልህቀት ማዕከላት፦
- Sustainable Energy
- Mineral Exploration, Extraction and Processing
- Nano Technology
- Bioprocessing and Biotechnology
- Construction Quality and Technology
- High Performance Computing and Big Data Analysis
- Artificial Intelligence and Robotics
- Nuclear Reactor and Technology
አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የልህቀት ማዕከላት፦
- Space Technology Institute
- Institute Of Pharmaceutical Science
- Institute Of Water Resource and Irrigation Engineering
- Electrical System and Electronics
- Advanced Manufacturing Engineering
- Advanced Material Engineering
- Urban Housing and Development
- Transportation and Vehicle
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
September 8, 2020 at 1:11 am #15770AnonymousInactiveየመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እያጤነ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲአ አበባ (ትምህርት ሚኒስቴር) – የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቴዎስ የ2013 ዓ.ም የትምህርት ሂደትን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ከትምህርት ቤቶች አከፋፈት ጋር ተያይዞ ባሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ከ42,000 በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይማሩ የነበሩ ከ26 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል።
የ2013 ዓመት ትምህርትን ለመጀመር የሚስችሉ ሁኔታዎችን ለመቃኘት የጥናት ቡደን ተቋቁሞ ጥናት እያደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። በጥናቱ መሠረት ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪዎችን ለማስተማር የሚያስችል አቅም ስለመኖርና አለመኖራቸው ልየታ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የተማሪዎችን ርቀት ለማስጠበቅ በአንድ ወንበር አንድ ተማሪ እንዲቀመጥ የሚደረግ ሲሆን በፈረቃ ትምህርት መስጠት፣ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባት፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ለማስተማሪያነት መጠቀም እንደ አማራጭ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተገልጿል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ አንዳንድ ክልሎች አስቀድመው ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን የገነቡ ቢሆንም፥ ሁሉም ክልሎች በየትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ክፍሎችን እንዲገነቡ እየተደረገ ነው።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ በቂ የንጽህና ወሃ እንዲኖር ማድረግ፣ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘርና ማስክ የማቅረብ ሥራዎችም እንደሚሠሩ በተሰጠው መግለጫ ላይ ተነስቷል።
የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ያለበት ሁኔታ እየተገመገመ ደረጃ በደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እየተጤኑ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሚሊዮን ማቴዎስ ለስኬቱ ወላጆችና ባለድርሻ አካላት ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
ከኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ዜና ሳንወጣ፥ ሚኒስቴሩ በቀጣይ ተማሪዎች በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፁ ሆነው እንዲወጡ በትኩረት እንደሚሠራ በ10 ዓመቱ ዕቅድ ውይይት ላይ አስታውቋል።
በውይይቱ ወጣቶች አሁን እየታዩ ባሉ አላስፈላጊ ድርጊቶች እና እንቅስቃሴዎች ውስጥ ገብተው መገኘታው በተማሪዎች የሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ በትኩረት ያለመሥራት አንዱ ምክንያት መሆኑ ተነስቷል።
በዕቅዱ ውስጥ ተማሪዎች ከመማር ማስተማር ባሻገር በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፁ ብቁ ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮች እንደሚዘረጋ ተጠቁሟል።
ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ብዝሃነትን የሚያስተናግዱ፣ ለወንድማማችነት ትኩረት የሚሰጡ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፁ ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮች በ10 ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ተካትተዋል።
ለማኅበረሰቡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የትምህርት ቤቶችን ሕግና ደንብ የሚያከብሩ፣ በበጎ ምግባራቸው ማኅበረሰቡ የሚረከባቸው ተማሪዎችን መፍጠር በ10 ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ በትኩረት ይሠራባቸዋል ተብሏል።
ምንጭ፦ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
September 16, 2020 at 12:02 am #15861SemonegnaKeymasterቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 70 አዳዲስ የድኅረ-ምረቃ ትምህርት ክፍሎችን ሊከፍት ነው
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በሁለተኛ እና ሦስተኛ ድግሪ 70 አዳዲስ ትምህርት ዓይነቶችን ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ይህም ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት ዓይነቶች 101 እንደሚያደርሰው ተጠቁሟል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታምሩ አኖሌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንዳሉት በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው አዲስ ከሚከፈቱት 19 የሦስተኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ውስጥ የገዳ እና የአስተዳደር ጥናት አንዱ ነው።
ቀሪዎቹ የተለያዩ የሁለተኛ ዲግሪ መርሀግብሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በሦስተኛ ዲግሪ ይሰጥ የነበረውን አንድ መርሀግብር ወደ 20 ከፍ ሲያደርገው የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከ30 ወደ 81 የትምህርት ክፍሎች እንደሚያሳድገው ዶ/ር ታምሩ አመላክተዋል። የትምህርት ክፍሎችን ፍላጎት ከመለየት አንስቶ የየሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ቀረጻና ትችት እንዲሁም የሰው ኃይልና ግብዓት የማሟላት ሥራዎች በጥንቃቄ መከናወናቸውንም በማከል አስረድተዋል።
የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም ዶ/ር ታምሩ ገልጸዋል። የመምህራን እጥረት እንዳይከሰት ረዳት ፕሮፈሰርና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው 73 የውጭና 43 የሀገር ውስጥ መምህራን ቅጥር መፈጸሙንም አስታውቀዋል።
ለመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ የሆኑ በተለይ ለኢንጅነሪግና ለተፈጥሮ ሳይንስ ቤተ-ሙከራና ቤተ-መጽሐፍት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ መደራጀቱን ገልጸዋል። ይህም ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለማድረስ እገዛ ከማድረግ ባለፈ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው ለተለያዩ የተግባር ትምህርቶች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎችን በመውሰድ የሚያወጣውን ውጭ እንደሚያስቀር አስረድተዋል።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) አቋቁሞ ከኢትዮጵያ ምርጥ አምስት እንዲሁም ከአፍሪካ ምርጥ 10 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አንዱ ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ ናቸው።
በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የገዳ ሥርዓት እንዲካተት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደሚ ሚናውን ከመወጣት ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ከኮመን ኮርስ (common course) እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የገዳ ሥርዓት ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
“ዩኒቨርሲቲው በስሩ ባሉት ስምንት ኮሌጆችና በአንድ ኢንስትቲዩት ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል” ብለዋል ዶ/ር ጫላ።
ምንም እንኳን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ለጊዜው ቢቆምም በቀጣይ ዓመታት የተማሪዎችን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ከፕሬዝዳንቱ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን
September 19, 2020 at 2:18 am #15927AnonymousInactiveበ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ የፊደል ገበታ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ተሰጠ
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከጉራጌ ዞን አስተዳደር በጋራ በመሆን የጉራጊኛ የፊደል ገበታ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ለማስተማር በዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች ለተዉጣጡ መምህራን ስልጠና የሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት፣ የሚዲያና የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የፊደል ገበታዉ ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች መስጠት አጋዥ መሆኑ ተገልጿል።
በስልጠናዉ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል የሱፍ እንዳሉት፥ የሀገራችን ሕገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በቋንቋቸዉ የመናገር፣ የመፅሀፍ፣ ቋንቋቸዉን የማሳደግ መብት እንዳላቸዉ አስፍሯል። የቤተ-ጉራጌ ህጻናትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ እንዲማሩ ለማድረግ ይሁንታ ያገኘዉን የጉራጊኛ የፊደል ገበታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሄደበት ያለዉን መንገድ አበረታች ተግባር እንደሆነም አስታዉቀዋል። የጉራጊኛ የፊደል ገበታ የትምህርቱን መስክ መሣሪያ በማድረግና ወደ መሬት ለማውረድ የሰልጣኝ መምህራን ሚና የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል።
ለህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መስጠት አስፈላጊዉን የቤተሰብ ድጋፍ በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችላቸዉን ዕድል ለማስፋትና ሳይንሱን ይበልጥ ለመረዳት፥ እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የሚያስችላቸዉ ተመራጭ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ እንደሆነም አስታዉቀዋል።
በስልጠናዉ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ እንዳሉት፥ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት፣ የሚዲያ እና የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ለማድረግ የምሁራን ሚና የጎላ ነዉ። ቋንቋ የአንድ ማኅበረሰብ የማንነት መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ዜጎች የራሳቸዉ ቋንቋ እንዲማሩ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ተደንግጓል ብለዋል።
ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ መማር እንዲችሉ ለማድረግና የጉራጊኛ ቋንቋ በማልማት የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት ከቁጭት ባሻገር ወደ ተግባር አለመገባቱም አስታዉሰዉ፥ የተለያዩ ምሁራን መጽሐፍ በማዘጋጀት በጥናትና ምርምር ሁሉም የበኩሉን ቢያበረክትም ዉጤታማ እንዳልሆነም አንስተዋል።
ቋንቋዉን ለማልማት የኮምፒዩተር ቀመር (ሶፍትዌር) በመቅረጽ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ እና የተለያዩ ዕቅዶችን በማቀድ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ምሁራን እያደረጉት ያለዉን ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።
በስልጠናዉ የተሳተፉ አንዳንድ መምህራን በሰጡት አስተያየት፥ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን የበኩላቸዉን ሚና እንደሚወጡም አስረድተዋል።
በስልጠናዉ ያገኙት እዉቀት በመጠቀም የጉራጊኛ የፊደል ገበታዉ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ከማስተማር በተጨማሪ በሁሉም የትምህርት ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ቢሰጥ መልካም ነዉ ብለዋል።
በመጨረሻም ከሁሉም ወረዳዎች ከሚገኙ ሁለት ሞዴል ትምህርት ቤቶች አራት አራት መምህራን ስልጠና ተሰጥቷል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።
September 22, 2020 at 12:28 am #15979AnonymousInactiveየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን መቀበል ከመጀመራቸው በፊት የተቋማቱ ዝግጁነት እንደሚረጋገጥ ተገለጸ
አዲስ አበባ (የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመክፈት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ መጀመሪያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከል የትምህርትና ስልጠና ተቋማት መልሶ የመክፈት ሂደትና ዝግጅት በሚል ርዕስ ምክረ-ሃሳብ አቅርበዋል።
በ2012 ዓ.ም የተቋረጠዉን ትምህርት በልዩ ዕቅድ ለማጠናቀቅ በሚሠሩ ሥራዎችና ትምህርት ሲጀመር ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲሁም ቀደም ተብለው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ምን መምሰል እንዳለባቸው በምክረ-ሃሳባቸው ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በጉባኤው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ‘መቼ እንክፈት?’ ለሚለው ትክክለኛ መልስ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በዓለም የጤና ድርጅት መለኪያ መስፈርት መሠረት ደረጃውን ጠብቆ በተዘጋጀ ዝርዝር በጥልቀት የዝግጅት መጠኑ ተፈትሾ ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል። በዚያ መሠረት የተቋማት ዝግጅት ይፈተሻል፤ በዳሰሳውም መሠረት መቀበል እንደሚችሉ ፍቃድ ይሰጣል ሲሉ አብራርተዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለፁት፥ ቅድሚያ ለተመራቂዎች [ቅድሚያ] በመስጠት፣ ተማሪዎችን በመከፋፈል በትንሽ ቁጥር ይጀመራል። ይህም ከሚታዩ ነገሮች እየተማርን የተማሪ ቁጥር ለመጨመር ዕድል ይሰጠናል ብለዋል። ዝርዝር አፈጻጸሙ በምን እንደሚመራ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ፕሮቶኮል ይዘጋጃልም ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንደመሆናቸው የክልል መንግሥታት ሥራ ይጠበቅባቸዋል። አማራጭ የለይቶ ማቆያ (quarantine) ቦታዎችን ማዘጋጀትም ግድ ስለሚላቸው እዚያ ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሠራል ብለዋል። ተማሪዎችን በማጓጓዝ ሂደት ችግር እንዳያጋጥም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንሠራበታለን ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የሚያስችል እቅድ ካሁኑ አዘጋጅተው ከአስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን ጋር በመወያየት የጋራ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል። የበፊቱን አሠራር ይዘን መቀጠል አንችልም፤ ዝግጅታችንን፣ ተጋላጭነታችንን አውቀን ተማሪ እንቀበላለን። አንድ ብሎክ ወይም አንድ ካምፓስ ኮቪድ-19 ቢያጋጥም ምን እናደርጋለን ከሚለው ጀምሮ በዝርዝር መሥራት እና እያንዳንዱ እቅድ ያለተማሪዎች እገዛ ተፈፃሚ ስለማይሆን ወደእነሱ ለማስረፅ መሥራት የግድ ይለናል ብለዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት፥ ጊዜው የተማሪዎች ሕብረት ኃላፊነት የሚፈተንበት ነው። የተማሪዎች ሕብረት አባላት የመፍትሄ ሃሳብ ሆናችሁ ለተፈፃሚነቱ ከዩኒቨርሲቲያችሁ ጋር በትብብር እንድትሠሩ ከእናንተ ይጠበቃል። ሰላማችሁን ማስጠበቅና ለደህንነታችሁ ዘብ መቆም ለትምህርታችሁ ቀጣይነት ዋስትና ነው ሲሉ አብራርተዋል። ዩኒቨርሲቲዎች መከፈታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ተመልሰው እንዳይዘጉም ጭምር የተማሪዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን አስመልክቶም የትኞቹ በዩኒቨርሲቲዎች ይቅረቡ የትኞቹ በተማሪዎች ይሟሉ የሚለውን ከተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለይቶ መወሰን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ውይይቱ ተቋማት የት ላይ እንደሆኑ ለይተን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ለመያዝ ታስቦ የተካሄደ ነው ብለዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎች በአሁኑ ጊዜ ቁርጠኝነት የሚፈልግ የለውጥ ሥራ እየሠራን እንደሆነ መገንዘብ እና በዚያው መጠን መፍጠን ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት የመመለስ ሂደት ባለድርሻ አካላትን በተገቢው መንገድ የማቀናጀት ኃላፊነት ተወስዶ መሠራት ያለበት ጉዳይ ነውም ብለዋል።
ተማሪዎችን ከመመለስና የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ከማዘጋጀት አንፃር የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥታት እያንዳንዱ የራሱን ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል። እንደከፍተኛ ትምህርት ዓለም-አቀፋዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ምርምር ላይ የተገኘውን እውቀት ተጠቅመን ለሀገር የሚውል አድርገን መጠቀምም ይገባናል ብለዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ሥራውን በማስፈፀም ሂደት ኃላፊዎች የግንኙነት (communication) ክፍተት እንዳይኖር በመነጋገር ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመው አመራር የሁሉ ነገር ቁልፍ እንደመሆኑ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ነገ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፤ ከዚያም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተቋማቱን ለመክፈት ያበቃሉ ተብለው የተቀመጡ ዝርዝሮችን በመያዝ በዩቨርሲቲዎች በመገኘት ብቁ መሆን አለመሆናቸው ታይቶ አስፈላጊውን መስፈርት ካሟሉ ብቻ እንዲከፍቱ ይደረጋል ብለዋል – ዶ/ር ሳሙኤል።
ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ወደኋላ የቀራችሁ ዩኒቨርሲቲዎች ካላችሁ ፈጥናችሁ ዝግጅታችሁን አጠናቅቁ ብለው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ጉዳዩንም እንደፕሮጀክት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለባቸው አስበዋል።
ከተሳታፊዎች የተለያዩ ስጋት ናቸው ተብለው የተነሱ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ለመፍታት እንደሚሠራ ተገልጿል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
September 24, 2020 at 1:21 pm #16085SemonegnaKeymasterትምህርት እንደሚጀመር ከሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተሰጡ ማብራሪያዎች
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ትምህርት እንደሚጀመር ሲያሳውቅ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተቋረጠውን ትምህርት የሚያስቀጥሉበት አቅጣጫን አስቀምጧል።
ከሁለቱም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መቼ እና እንዴት ትምህርት እንደሚጀመር የተሰጡት መረጃዎች የሚከተሉት ናቸው።
ትምህርት ሚኒስቴር
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በሦስት ሳምንታት ውስጥ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ተወስኗል።
የዓለም የጤና ድርጅትና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ መሠረት ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በመድኃኒት ማጽዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ማጽጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለሌላ አገልግሎት (ለምሳሌ፥ ለለይቶ ማቆያነት) ውለው የነበሩ ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን የማስተካከያ ሥራ ሊሠራላቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
እንደየ ትምህርት ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት በፈረቃ እና አንድ ቀን በመዝለል ተራ ሊያስተምሩም ይችላሉ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪ ማስተማር የሚችሉ መሆንም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
የተቀመጠው መስፈርት እንዳለ ሆኖ፡-
- በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም፤
- በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም፤
- በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሦስተኛ ዙር ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም
ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ መቅረቡ ይታዋሳል፡፡
በዚህ መሠረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሦስት ሳምንታት ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ትምህርት መጀመር ይችላሉ ተብሏል፡፡
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከልን የዩኒቨርሲቲዎችን እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን ከተቋረጠበት ለማስቀጠል በመሪዎች ደረጃ በተካሄደው ስብሰባ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዚህም መሠረት፥ በዓለም የጤና ድርጅት መስፈርትና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የየኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያ መነሻ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የማስተማርና የማሰልጠን ተግባራት ዝርዝር መመሪያ እንዲያዘጋጅና ተገቢውን ውይይት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በማድረግና ግንዛቤ በማሳደግ፣ የተቋማትን ዝግጁነት በማረጋገጥ፣ አግባብነት ያለውን የትምህርትና ሥልጠና መርሀግብር በማዘጋጀት ተማሪና ሰልጣኝ መቀበል የሚችሉ መሆኑን፤ ለዚህም ተቋማት ቀሪ የመስከረም ወር ቀናትንና የጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንትን የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን ለማከናወን እንዲጠቀሙ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ስለሆነም፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እስከ ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት መጨረሻ የተቋማትን የዝግጅት ምዕራፍ አፈፃፀም በአካል እየተገኘ ገምግሞ በቂ የኮቪድ-19 መከላከያ ዝግጅት ላደረጉት የመንግሥትና የግል ዪኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪና ሰልጣኝ እንዲቀበሉ የሚፈቅድ ይሆናል። በቂ ዝግጅት ያላደረጉ ተቋማት፣ ዝግጅታቸውን እስከሚያጠናቅቁ ድረስ ክትትል ይደረጋል። ያለ በቂ ዝግጅትና ያለሚኒስቴሩ የመስክ ምልከታና ፈቃድ ተማሪዎችን ወይም ሰልጣኞችን ተቀብሎ መገኘት አግባብነት አይኖረውም።
ስለሆነም፥ የ2012 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎችና የስልጠና አጠናቃቂዎች እንዲሁም በሌሎች የትምህርትና ሥልጠና እርከን የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ በሚዲያ በሚታወጀው የተማሪና ሰልጣኝ ቅበላ መርሀግብር መሠረት በየተቋሞቻቸው ጥሪ የሚደርግላቸው መሆኑን፤ እስከዚያው ድረስ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገልጸዋል። አያይዘውም ትምህርት/ስልጠና በሚጀመርበት ጊዜ የተጣበበ የትምህርትና ስልጠና ጊዜ የሚኖር በመሆኑ፥ ተማሪዎች/ሰልጣኞች ቀጣይ ጊዜያቸውን ለንባብና ለተያያዥ ዝግጅቶች እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመሆኑ፥ ሁሉን አቀፍ ጥንቃቄ እየተደረገ የትምህርትና ስልጠና ተግባራትን በጋራ ሆነን እንወጣዋለን በማለት ዶ/ር ሳሙኤል መግለጫቸውን ቋጭተዋል።
September 25, 2020 at 4:03 pm #16096AnonymousInactiveወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለ15 ኛ ዙር 3,608 ተማሪዎችን አስመረቀ
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በትምህርታቸው የላቁ ተማሪዎችን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ተረከበወለጋ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በተከታታይና በርቀት መርሀግብር በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 3,608 ተማሪዎች መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም አስመረቀ።
በዕለቱ የተመረቁት 3608 ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ከመከሰቱ በፊት ትምህርታቸውን የጨረሱና በበየነ መረብ ትምህርታቸውን በመከታተል ያጠናቀቁ ናቸው። ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 1,139 ተማሪዎች በአካል ተገኝተው ምርቃታቸው ላይ የተካፈሉ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ ተመራቂዎች ቤታቸው ሆነው በበየነ-መረብ እና በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ኔትወርክ (ኦ.ቢ.ኤን) በቀጥታ ሰርጭት ምርቃታቸውን ተከታትለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀሰን ዩሱፍ በምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፥ ተማሪዎቹ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተሰጣቸውን ስልጠና በአግባቡ በማጠናቀቃቸው ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ስምንቱ በሦስተኛ፣ 1,153ቱ በሁለተኛና ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ የተሰጣቸውን ትምህርት ያጠናቀቁ ናቸው።
ክቡር ዶ/ር ሀሰን_ዩሱፍ በምረቃው መርሀግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ተመራቂዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ፥ ብዙ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን በማለፍ ተመራቂዎች ለዚህ በመብቃታቸው እጅግ የሚያኮራ እና የሚያስደስት ነው ብለዋል። ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ማኅበረሰቡን በታሞኝንት፣ በቅንንትና፣ በጥሩ ሥነ ምግባር እና ሀቀኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ክቡር ዶ/ር አበራ ዴሬሳ፥ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባልና የዕለቱ የክብር እንግዳ፥ በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር አድርገዋል። ተመራቂዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ፤ እንኳን ለዚህ ታሪካዊ ቀን አበቃችሁ ብለዋል። በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተጽዕኖ በመቋቋምና በኢንተርኔት ትምህርታችሁን በመከታተል ለዚህ በመብቃታችሁ ጥንካሬያችሁን ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል። በትምህርታችሁ ሂደት ያሳያችሁትን ጥንካሬ በተግባር ሥራው አለምም እንድትደግሙና ማኅበረሰቡን በተሰማራችሁበት የሥራ መስክ ሁሉ በቅንነትና በታማኝንት እንድታገለግሉ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 14 አመታት ከ44 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለሀገሪቱ እድገት ሁነኛ አስተዋጽዖ ያበረከተ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም ክ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ድግሪ መርሀግብር በ159 የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
በሌላ ዜና፥ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ሊባኖስ ወረዳ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም ተረከበ። ትምህርት ቤቱን ለዩኒቨርሲቲው ያሰረከቡት የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኃይሉ ናቸው።
አቶ ፀጋዬ በወቅቱ እንዳሉት ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በወረዳው ሸረሮ ከተማ የተረከበው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀደም ሲል በመሰናዶ ትምህርት ቤትነት ሲያገለግል የነበረ ነው። ትምህርት ቤቱ 420 ተማሪዎችን በአዳሪና ተመላላሽ በመደበኛነት ለማስተማር የሚያስችለውን ቁሳቁስና በጀት በማሟላት ዘንድሮ ሥራ እንደሚጀምር ተመልክቷል።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ኘሬዚዳንት ዶ/ር ፀጋዬ ደዮ በተረከቡት ትምህርት ቤት ከስምንተኛ ወደ ዘጠነኛ ክፍል በከፍተኛ ውጤት የሚያልፉ ተማሪዎችን ከዞኑ 13 ወረዳዎች ተቀብለው እንደሚያስተምር ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ በቂ ቤተ-መፃሕፍት፣ ቤተ-ሙከራና ሌሎች ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ሥራዎችን በማከናወን ለሌሎች ትምህርት ቤቶች አርአያ ተደርጎ እንደሚመቻች ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተጨማሪም ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስን በመከላከል በትምህርታቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ 3,200,000 ብር ግምት ያለው የማመሳከሪያ መፃሕፍትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለዞኑ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቅርቡ መስጠቱንም አስታውሰዋል። የሚደረገው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን በመጠበቅ በሥነ-ምግባር የታነፀ ሥራ ወዳድ ትውልድ ለማፍራት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በዞኑ ይህን መሰል ትምህርት ቤት ከፍቶ አገልግሎት መስጠቱ ለዞኑ ደግሞ ጎበዝ ተማሪዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን የገለፁት የዞኑ ወላጅ መምህራን ሕብረት አባል ወ/ሮ ሌሊሴ ባልቻ ናቸው። ተማሪዎች በተፈጠረላቸው ምቹ ዕድል ለመጠቀም በርትተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያነሳሳ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላው አስተያየት የሰጠው የሸረሮ ከተማ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ መገርሣ ሁንዴ፥ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የተረከበው ትምህርት ቤት በተሻለ አቅምና ቁሳቁስ ተደራጅቶ የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው ገልጿል።
ሰላሌ ዩኒቨርስቱ በማኅበረሰብ አገልግሎት ለአካባቢው ነዋሪዎችና ተማሪዎች የሚጠቅሙ ኘሮጀክቶች ነድፎ ዘንድሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ከዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ኘሬዚዳንት ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
ምንጮች፦ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
-
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.