የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች

Home Forums Semonegna Stories የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች

Viewing 11 posts - 46 through 56 (of 56 total)
  • Author
    Posts
  • #16289
    Semonegna
    Keymaster

    በኢትዮጵያ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ተለዩ

    ጎንደር (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ ስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) በመባል መለየታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ዙሪያ ያካሄደውን የምርምር ግኝቶች ላይ መስከረም 29 ቀን 2013 ዓም ከባለድርሻዎች ጋር ተወያይቷል።

    የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ወርቁ ነጋሽ በወቅቱ እንደገለጹት፥ በሀገሪቱ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚል በሦስት ደረጃዎች ተለይተዋል።

    ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ተናግረዋል።

    ጎንደርአዲስ አበባባህር ዳርመቀሌጅማሀዋሳአርባ ምንጭ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ተለይተዋል” ብለዋል ዶ/ር ወርቁ።

    ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ወርቁ፥ “ያደጉ ሀገሮች የእድገት ምስጢርም ከዚህ የመነጨ ነው” ብለዋል። የምርምር (Research) ዩኒቨርሲቲዎቹ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

    ሌሎች 15 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ (Science and Technology) ዘርፍ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ መለየታቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ እውቀትና ክህሎት ያዳበረ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።

    ቀሪዎቹ 23 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የተለዩ መሆኑን ዶ/ር ወርቁ አስታውቀዋል።

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን ተናግረዋል።

    ላለፉት ሶስት አመታት ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በማእከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተመረጡ 1,343 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በትምህርት ጥራት ዙሪያ ጥናትና ምርምር መካሄዱን ገልጸዋል። በምርምር ውጤቶቹ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

    “በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ትምህርት ኮሌጅ መምህራን የተዘጋጀው የምርምር ውጤት ለፖሊሲ አውጪዎች ጠቃሚ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ነው” ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን ናቸው።

    ባለፈው ዓመት ዩኒቨርሲቲው ከ200 በላይ የምርምር ሥራዎችን ማካሄዱን ዶ/ር አሥራት አስታውሰዋል፤ ዘንድሮም በተለያዩ ዘርፎች ምርምር ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያካሄደ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ማሳወቃቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ተሳትፈዋል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ

    የምርምር ልህቀት ማዕከል

    #16454
    Anonymous
    Inactive

    በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት

    የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የገጽ ለገጽ ትምህርት መስጠት መጀመራቸውን ተከትሎ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ለተቋማት፣ ለሠራተኞች፣ ለመምህራንና ለተማሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት የሚከተለው ነው።

    በኮቪድ-19 ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የገጽ ለገጽ ትምህርት (in-class teaching) ለማስቀጠል እንዲቻል በየተቋማቱ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

    ለዚህም እንዲያግዝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የገጽ ለገጽ ትምህርትን ለማስቀጠል ሊከተሏቸው የሚገቡ ፕሮቶኮሎችን በማዘጋጀት ተቋማት በመመሪያው መሠረት እንዲዘጋጁ ሆኗል።

    ይሄንንም ዝግጅት የክትትል ግብረኃይል በማዘጋጀትና በማሰማራት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በአካል ተገኝተው ግምገማ አካሂደዋል። በግምገማው ውጤት መሠረትም ተቋማቱ ያላቸው ዝግጅት ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል መሆኑ በመረጋገጡ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ትምህርትና ስልጠናቸው እንዲመለሱ ጥሪ ተደርጓል።

    በመሆኑም ውድ ተማሪዎች ከወራት ቆይታ በኋላ ወደ ትምህርት ገበታችሁ እንደመመለሳችሁና ትምህርትና ስልጠናው የሚቀጥለው በኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል እንደመሆኑ፥ በተቋማቱ የሚኖራችሁ ቆይታ ኃላፊነት የተሞላበት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ላይ ያተኮረና በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላ እንዲሆን አሳስባለሁ።

    ወደየዩኒቨርሲቲዎቻችሁ ስትመለሱም በአመራሩ የሚሰጣችሁን የጥንቃቄ መመሪያ ሁሉ ተግባራዊ ልታደርጉ ግድ ይላል። ወረርሽኙን ራሳችንን ብቻ በመከላከል ልንወጣው የምንችል ባለመሆኑ ለትምህርታችሁ ትኩረት ከመስጠት ጎን ለጎን ማስክ (የፊት መሸፈኛ ጭንብል) በመጠቀም፣ ንፅህናን በመጠበቅና በመመሪያው ላይ የተቀመጡ ሌሎች ሕግጋትንም ተግባራዊ በማድረግ የራሳችሁንና የጓደኞቻችሁን ሕይወት እንድትጠብቁም አሳስባለሁ።

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሩም ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲ ሲመለሱ መመሪያውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ግንዛቤ በመፍጠርና ከዚህ ቀደም ሲገለፅ እንደነበረው የጥንቃቄ መልዕክቶችን ሁሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማመቻቸት እንዲሁም መመሪያው እንዲተገበር በማድረግ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ።

    መምህራን ከተማሪዎቹ ጋር ሰፊ ጊዜ የምታሳልፉ እንደመሆኑ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ተማሪዎች እንዳይዘናጉ የማድረግና የጥንቃቄ መመሪያውን እንዲያከብሩ የማስገንዘብ ኃላፊነት አለባችሁ።

    የአስተዳደር ሠራተኞችም ተማሪዎች በግቢ ውስጥ የሚኖራቸው መስተጋብር ጥንቃቄ አልባ እንዳይሆን፤ የእናንተም አበርክቶ ከፍተኛ ነውና እናንተ ጠንቃቃ ሆናችሁ ተማሪዎችንም እንድታነቁ ይሁን።

    በያዝነው ዓመት የሚኖረንን የትምህርትና ስልጠና ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀምና ትምህርትና ስልጠናው በታቀደው ጊዜ እንዲከናወን ለማስቻል ከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊና መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስና እንደ ጤናችን ሁሉ ሰላማችንንም ማስጠበቅ ኃላፊነታችንና ግዴታችንም ጭምር ነው።

    ለዚህም የትምህርትና ስልጠና ማኅበረሰቡ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ጤናችሁንና ሰላማችሁን በመጠበቅ፣ ውድ ጊዜያችሁን ለእውቀት ሸመታ፣ ማኅበረሰባችሁን በሚጠቅሙ እና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር እንዲሆን ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ።

    ዓመቱ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎችን የምንከውንበት ውጤታማና ሰላማዊ የመማር-ማስተማር ጊዜ የምናሳልፍበት እንዲሆን ከምንጊዜውም በላይ በጋራና በትጋት እንሠራለን!

    ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ
    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
    ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም

    ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት

    #19566
    Anonymous
    Inactive

    5ኛው “ሀገረሰባዊ ዕውቀት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት” ሀገራዊ ዓውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

    አርባ ምንጭ (አምዩ) –  የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አምዩ) የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 5ኛው “ሀገረሰባዊ ዕውቀት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት” ሀገራዊ ዓውደ ጥናት ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል።

    በዓውደ ጥናቱ “የአሪ ብሔረሰብ ባህላዊ የተፈጥሮ ሀብት ዕውቀት፣ እሳቤዎችና ክዋኔዎች፣” “ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ፣” “ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በጋሞ ሕዝብ፡- የኦቾሎ ደሬ ተሞክሮ” እና “ሀገር በቀል ዕውቀት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፡- የጋሞ እና ኮንሶ ጥብቅ ደኖች” የሚሉ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ክዋኔና እሳቤዎች ለአካባቢ ጥበቃና ለግጭት አፈታት ያላቸውን ሚና የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ጥናታዊ ጽሑፎቹ በዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩትና በሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህራንና ተመራማሪዎች የተሠሩ ናቸው።

    በጽሑፎቹ እንደተመለከተው ሀገር በቀል ዕውቀት፣ እሳቤዎችና ክዋኔዎች የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም ግጭቶችን በመከላከልና በመፍታት ረገድ ለበርካታ ዘመናት አዎንታዊ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ዘመናዊነትና ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ለውጦች፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በፌዴራልና በአካባቢ አስተዳደር በቂ ትኩረት አለማግኘትና ሌሎችም ምክንያቶች ለሀገር በቀል እሴቶቹ አደጋ የጋረጡ ሆነዋል። ተመራማሪዎቹ በጥቆማቸው ከመንግሥት አካላት ተገቢው ትኩረትና ዕውቅና እንዲሰጠው፣ ማኅበረሰብ መር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲጠናከር እንዲሁም የምርምር፣ የካርታና ዶኪዩሜንቴሽን ሥራዎች እንዲሠሩ ሃሣብ አቅርበዋል።

    የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕክምና፣ በግብርና፣ በግጭት አፈታት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በሌሎችም በርካታ መስኮች የእምቅ ባህልና ዕውቀት ባለቤት መሆኗ ለማኅበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ለመስጠት የሚያስችል ነው። በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እንዲሁም ምርምሮች እንዲካሄዱ ድጋፍ በማድረግ ሀገር በቀል ዕውቀትና ክዋኔዎች ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ በትኩረት ይሠራል።

    ዓውደ ጥናቱ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የክልሉና የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች እንዲሁም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት ያቀዷቸውን ሥራዎች የሚያጠናክር መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አርባ ምንጭ እና አካባቢው በርካታ ባህላዊ እሴቶችን ያቀፈ በመሆኑ ለዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ሀገር በቀል ዕውቀት ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር ተጣምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገርና ለሀገር ልማት እንዲውል ለሀገር በቀል ዕውቀት ያለንን የተሳሳተ ግንዛቤ ማረም ብሎም በምርምር ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አህመድ ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን ከማካሄድ ባሻገር የሥነ-ጥበብ ዘርፍን ለማሳደግ አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ሀገራዊ የትርጉምና የተርጓሚነት ሙያ ጉባዔ ማዘጋጀቱን አስታውሰው መሰል መድረኮች ልምድና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም፣ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ሙያዊ አቅምን ለመገንባት ፋይዳ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

    የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በዓውደ ጥናቱ ተሳትፈዋል።

    ምንጭ፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

    ሀገረሰባዊ ዕውቀት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ዓውደ ጥናት

    #19674
    Anonymous
    Inactive

    በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ዙሪያ ጥራትን ማስጠበቅ ያስችላል የተባለ ረቂቅ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተዘጋጀ
    በ2014 ዓ.ም. ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመንገድ ደህንነት ትምህርት ይሰጣል

    አዲስ አበባ (ትምህርት ሚኒስቴር) – በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ዙሪያ ጥራትን ማስጠበቅ ያስችላል የተባለ ረቂቅ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተዘጋጀ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማዕከላትን ለማቋቋም የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ያላቸውን ፍላጎት እና የቤተ ሙከራ ኬሚካሎች አጠቃቀም እንዲሁም አወጋገድ ሥርዓት ዙሪያ ጥናታዊ ዳሰሳ ግኝት ቀርቦ ውይይት መካሄዱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

    መድረኩ የማዕከሉ አምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ እና ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻፀም ለመገምገም ያለመ ነበር፡፡

    በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማዕከል የሥነ ህይወት ትምህርት ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታዬ ሞላልኝ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅዱ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ የሂሳብ፣ የሳይንስ፣ የምህንድስና ትምህርቶችን ከጥበብ እና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለመስጠት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

    ቤተ ሙከራ ተማሪዎች በፅንሰ ሃሳብ የተማሩትን የትምህርት ይዘት በተግባር ሙከራ አስደግፈው ይበልጥ ትምህርቱን በቀላሉ እንዲረዱ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ በክልል ደረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስምንት የስልጠና ማዕከላት እንደሚቋቋሙ አቶ ጌታዬ ተናግረዋል፡፡

    በትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራ ኬሚካሎች አጠቃቀምና አወጋገድ ሥርዓት ዙሪያ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ከቀረበው ጥናታዊ ዳሰሳ ለማወቅ ተችሏል፡፡

    በመድረኩ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

    ከዚህ ቀደም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በጥበብና ሂሳብ ዘርፍ የሚቀርቡትን የተማሪዎችን የፈጠራ ውጤቶች በአግባቡ መምራት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ መዘገጀቱንም ሚኒስቴሩ አስታውሷል።

    ከትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ በ2014 ዓ.ም ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመንገድና ትራንስፖርት ደህንነት ትምህርት እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር ሰኔ 7 ቀን፥ 2013 አስታውቋል።

    የትምህርት ሚኒስቴርና የትራንስፖርት ሚኒስቴር በትብብር ያዘጋጁት “የመንገድ ደህንነት ለሁሉም” በሚል የመንገድ ደህንነት ሥርዓተ ትምህርት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሳምንቱ ውስጥ ተካሂዷል።

    የመንገድ ደህንነት ሥርዓተ ትምህርት ከቅደመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል፣ እንዲሁም በጎልማሶች ትምህርት እንዲካተት ተደርጎ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተቀረፀ ሲሆን በ2014 ወደ ሥራ ይገባል።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ) በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ትግበራ የሚገባው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት፣ የትምህርት ጥራትን ታሳቢ ያደረገና ባለፉት ዓመታት የታዩ ችግሮችን ነቅሶ ያወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

    በቀጣይ ዓመት ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመንገድ ደህንነት ትምህርት ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለፁት ሚኒስትሩ፥ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የትራፊክ ደህንነት ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል።

    የትራንስፖርት ሚነስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ አጠቃቀምን ባህል ለማድረግና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገለፀዋል።

    የመንገድ ደህንነት ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ከማምጣቱም በላይ የመንገድ አጠቃቀምን ባህል ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

    ሥርዓተ ትምህርቱ ዜጎች የመንገድ ትራፊክ ሕግና ደንብን በአግባቡ አውቀው ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና ሌሎችንም እንዲያሳውቁ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል። በዝግጅቱም የመንገድ ደህንነት ትምህርትን ለማስተማር  የሚያስችሉ ቋሳቁሶችን ትምህርት ሚኒስቴር ከትራንስፓርት ሚኒስቴር ተረክቧል።

    በበ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ተግባራዊ በሚደረገው የመንገድና ትራንስፖርት ደህንነት ትምህርት ላይ በ11 የትምህርት ዓይነቶች የመንገድ ደህንነት ትምህርት የሚተገበር ሲሆን ከ34 ሚሊዮን  በላይ ተማሪዎችን ለመድረስ ያስችላል።

    ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር

    የመንገድ ደህንነት ትምህርት

    #49776
    Semonegna
    Keymaster

    ከ350 በሚበልጡ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን
    የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በ2014 በጀት ዓመት የሥነ-ሥርዓት ጥሰት በፈጸሙ ከ350 በላይ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ ከአረጋገጣቸው 10 ሺህ የትምህርት ማስረጃዎች 505 ቱ ሀሰተኛ ናቸው ብሏል።

    የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር ዶ/ር አንዷለም አድማሴ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በ2014 በጀት ዓመት ከየትኛውም በጀት ዓመት የበለጠ የትምህርት ጥራትን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን የማጽዳት ሥራ ተከናውኗል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ገምግሞ አቅጣጫ ካስቀመጠ ጊዜ ጀምሮ ከ350 በላይ በሚሆኑ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ወስዷል።

    መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየወሰዳቸው ካሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ውስጥ ሕገ-ወጥ የትምህርት ተቋማትን መቆጣጠር አንዱ ተግባር ነው ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ አሁን ላይ የትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ትርፍን ብቻ አላማ ያደረጉ ሕገ ወጥ የግል የትምህርት ተቋማት መስፋፋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

    ተቋምና ፕሮግራም መዝጋት አማራጭ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጣቸው በትውልድ ህይወት የሚነግዱ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

    እንደ ዶ/ር አንዷለም ገለጻ፥ በርካታ ዜጎች እውቅና በሌለው የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገንዘባቸውን ከፍለው ከተማሩ በኋላ ባለስልጣኑ ማረጋገጫ ሲሠራላቸው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሆንባቸው ለተመሰቃቀለ ህይወት እየተዳረጉ ነው። በተቋማት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ በ355 የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ከፕሮግራም መዝጋት እስከ ተቋሙን ሙሉ በሙሉ እስከ መዝጋት የደረሰ የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል። ለዚህም መገናኛ ብዙኃን የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

    የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ሥራ በበጀት ዓመቱ በትኩረት ከተሠራባቸው መካከል መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር አንዷለም፤ በዘርፉ የጤና ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን ለሚቀጥሯቸው ሠራተኞች ቅጥር ከመፈጸማቸው በፊት የትምህርት ማስረጃቸው በባለስልጣኑ እንዲረጋገጥ የሚያደርጉበት አግባብ ለሕገ-ወጥ የትምህርት ማስረጃ ቁጥጥር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። ዕድገትና ቅጥር ሲያከናውኑም በሙሉ ሳያስፈትሹ እንደማያከናውኑ ተናግረዋል።

    ዋና ዳይሬክተሩ የትምህርት ማስረጃ ሲረጋገጥ በቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች ተገደው የሚመጡ አካላትን የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥና ከውጭ ሀገር የተገኘ የትምህርት ማስረጃን አቻ ግምት በመስጠት በሁለት መልኩ የሚረጋገጥ ነው ብለዋል። የማረጋገጥ ሥራ የሚጀምረው ከሀገር አቀፍ ፈተናዎች እንደሆነና በወቅቱ ከነበረው የመቁረጫ ነጥብ በመጀመር እያንዳንዱ የትምህርት ማስረጃ ተፈትሾ እስከ ዲፕሎማና ዲግሪ እንደሚረጋገጥም ጠቁመዋል።

    በ2014 በጀት ዓመት የጤና ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽንን ሳያካትት ተገደው ከመጡ ከ10 ሺ በላይ የትምህርት ማስረጃዎችን ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ ከተረጋገጡት የትምህርት ማስረጃዎች 505 የሚሆኑት ትክክለኛ ያልሆኑ የትምህርት ማስረጃዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።

    ፈቃድ ሳያገኙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዱ ያሉ ትውልድን እያቀጨጩ የሚገኙ ሕገ-ወጥ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደት ሕብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርግም ዶ/ር አንዷለም ጥሪ አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን

    #51040
    Semonegna
    Keymaster

    አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመደበኛና በርቀት ትምህርት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

    አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በድኅረ ምረቃ 210 እንዲሁም በቅድመ-ምረቃ 1,850 ተማሪዎችን መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም. አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝደንት አቶ ዘሪሁን መስፍን፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብት በመጠቀም ወቅቱ የሚጠይቀውን ችግር የሚፈታላት የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋታልና ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት በመጠቀም የሀገራቸውን ችግር እንዲፈቱ አሳስበዋል።

    “ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ በሥራ ዕድሜ የሚገኝ የሠው ኃይል፣ አኩሪ ታሪክና ባህል ያላት ውብ ሀገር ናት፤ እነዚህን ገፀ በረከቶች ወደ ውጤት በመቀየር የሀገራችን ሕዝቦች ካሉባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች መታደግ ወቅቱ የሚጠይቀው የተማሩ ዜጎች የዕለት ተዕለት ተግባር እንደሚሆን ይጠበቃል፤ በመሆኑም በቀጣይ እናንተ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጃችን በዛሬው ዕለት ትምህርታችሁን በሚገባ ተከታትላችሁ ያጠናቀቃችሁ የዕለቱ ተመራቂዎቻችን ያገኛችሁትን ዕውቀትና ክህሎት በምትሠማሩበት የሥራ መስክ በአግባቡና ኃላፊነት በተሞላበት ጭምር ለሀገራችሁና ለሕዝቦቿ እንደምታበረክቱ የፀና እምነት አለኝ” ብለዋል።

    ቀጣይ ዘመናችሁ የፍቅር፣ የመከባበርና የአንድነት ጉዞ እንዲሆን በመመኘት በሄዳች ሁበት ሁሉ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጃችንን በአግባቡ በመወከል አምባሳደሮቻችን እንድትሆኑ ሲሉም አደራ አስተላልፈዋል።

    የአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የቦርድ አባል ዶክተር ብርሃኔ አስፋው በበኩላቸው ለተመራቂ ተማሪዎች በባስተላለፉት መልዕክት፥ የትምህርት ፍላጎታችሁን ለማሳካትና የሚፈለገው ርቀት ላይ ለመድረስ አሁንም አልረፈደም ሲሉ የትምህርት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

    በየጊዜው ራስን በማሳደግ ሁልጊዜ በማንበብ ለቀጣይ ከፍተኛ ትምህርት ተግታችሁ ተገኙ ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎች አሳስበዋል።

    ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዜና ሳንወጣ፥ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ናቸው።

    ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአቅም ግንባታ፣ በጋራ ፕሮጀክት ቀረጻና ትግበራ፣ በሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን፣ ጉባኤዎችን ማዘጋጀትና የምርምር ሥራዎችን በጋራ መሥራት የሚያስላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

    ከተመሠረተ 80ኛ ዓመቱን የያዘው ኢዜአ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ” ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስገንብቶ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ስቲዲዮ ሥራ ለማስጀመር እየሠራ መሆኑን አቶ ሰይፈ ገልጸዋል። የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ ሥራ ለማስገባት የድርጊት ማስፈጸሚያ እቅድ መፈረሙን አመልክተዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደ ፊት ለማራመድ የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት መሆኑንና ኢዜአ ይሄን ሥራ በሙያው ማገዝና መደገፍ አለበት ብለዋል።

    ተቋማቱ በተለይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ጭምር በውድድር ተቀብሎ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ እየሠራ ያለውን ሥራ ለማስተዋወቅ በጋራ ይሠራሉ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው።

    ኢዜአ በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ግብ አስቀምጦ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአቅም ግንባታ፣ በጋራ ፕሮጀክት ቀረጻና ትግበራ፣ በሚዲያ አገልግሎትና ሽፋን፣ ኮንፈረንሶች ለማዘጋጀትና የምርምር ሥራዎችን በጋራ መሥራት የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።

    የመግባቢያ ሰነዱን ወደ ተግባር ለመቀየር ኢዜአ ከዩንቨርስቲው የኢንፎርሜሽን፣ ኮምዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ቡድን ጋር ፕሮጀክት በመቅረጽ በጋራ መሥራት መጀመሩን ጠቁመዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

    አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ

    #51329
    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን አስረከበ

    ባሕር ዳር – የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ነሐሴ 21 ቀን፥ 2014 ዓ.ም የተማሪዎችን ምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በማኅበረሰብ አገልግሎት ጉልህ አስተዋፅዖ ላበረከቱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ) የሰሜን ወሎ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለሆኑት ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማት ለተወካያቸው መስጠቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን ብፁዕ አባታችን በአሁኑ ሰዓት የሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን ጨርሰው በመመለሳቸው መስከረም14 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ሕንፃ ተገኝተው የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

    የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የዕለቱ የክብር እንግዳ በሆኑት በብፁዕ አቡነ አብርሃም ፀሎትና ቡራኬ ተጀምሯል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት በጭንቅ እና በመከራ ወቅት ሀይማኖትና ዘር ሳይለዩ የከበረ ሥራን ሠርተው የከበሩትን ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በማክበራችን እኛም ብዙ አትርፈናል ሲሉ ተናግረዋል። በወቅቱ አቅም ያላቸው በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው በሚሸሹበት ወቅት በጦርነት፣ በችግር እና መከራ ውስጥ ወደ ሚገኘው ሕዝባቸው ጋር በመሄድ የመከራው ቀንበር እንዳይሰማቸው ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመጣውን ክፉ ቀን እንዲያልፍ በማድረጋቸው ታሪክ የማይረሳው ሥራን ሠርተዋል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

    የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ እንዲሁም ዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀይማኖት፣ ዘር እና ቀለም ሳይለይ በሥራቸው ብቻ መዝኖ ለብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የክብር ዶክትሬት በመስጠቱ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ስም ምስጋና አቅርበዋል። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በዚያ ሽብር እና ጭንቅ በነገሰበት ወቅት ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ አማኝ እና ኢ-አማኝ ሳይሉ ሁሉንም የሰው ዘር በእኩል ዓይን በማየት የመከራውን ቀን ከሕዝባቸው ጋር ያሳለፉትን ድንቅ አባት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዕውቅና ሽልማት በመስጠቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መደሰቷን ተናግረዋል።

    አቡነ ኤርምያስ በበኩላቸው የተሰጠኝ የክብር ዶክትሬት ለእኔ ሳይሆን በሁለቱም ወገን በጦርነቱ ወቅት ቆስለው በየጫካው የወደቁ ወገኖችን ቁስል በማጠብ እና ከልጆቻቸው ጉሮሮ ቀንሰው ለቁስለኞች በማብላት ትልቅ ፍቅር ላሳዩን እናቶች እና በጸሎት ሲጠብቁኝ ለነበሩት ለብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ከጎኔ ሆነው በምክር ለረዱኝ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሀዋርያዊ ተልዕኮ ዘወትር ለሚፋጠኑት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ድልድይ ሆነው ላገናኙኝ የመስጊድ ኮሚቴ አባላት፣ ሰብዓዊ ግዴታቸውን ለተወጡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ወሎ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚዳንቶች መምህራን እና ሠራተኞች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    አቡነ ኤርምያስ

    #54180
    Semonegna
    Keymaster

    ናሽናል አቭዬሽን ኮሌጅ የአቭዬሽንና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው

    ናሽናል አቭዬሽን ኮሌጅ በአገራችን በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአቭዬሽንና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቀጣይነት ለማረጋገጥና ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሠራ እንደሆነ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ተናገሩ። ኮሌጁ ያሰለጠናቸውን 277 ተማሪዎች ኅዳር 3 ቀን፥ 2015 ዓ.ም አስመርቋል።

    የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ኅዳር 3 ቀን በተካሄደው የተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ብዛት ያለው የሰው ኃይል፣ አኩሪ ታሪክና ባህል ያላት ውብ ሀገር ናት። እነዚህን ገፀ-በረከቶች ወደ ውጤት በመቀየር የሀገራችን ሕዝቦች ካሉባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች መታደግ ወቅቱ የሚጠይቀው ነው። ከዚህ አኳያ የተለያዩ ክህሎቶችና ዕውቀቶች የቀሰሙ ተመራቂዎች ኢትዮጵያን ለማበልጸግ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል።

    ኮሌጁ በሀገሪቷ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የራሱን ኃላፊነት እየተወጣና በትምህርት አሰጣጥ ሂደት ጥራትን መሠረት አድርጎ እየሠራ የሚያስመስግነው ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ተመራቂ ተማሪዎቹ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በሚሠሩበት የሥራ መስክ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለሀገራቸውና ለሕዝቦቿ እንደሚያበረክቱ የፀና ዕምነት አለኝ ብለዋል።

    ኮሌጁ ካናዳ ከሚገኘው ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) እና እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ኢንስቲትዩት ኦፍ ኮሜርሽያል ማኔጅመንት (ICM) ባገኘው ዕውቅና መሠረት ከአቭዬሽን፣ ቱሪዝምና ሆቴል ሙያ ጋር በተገናኘ ደረጃውን ያሟላ ዓለም አቀፍ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቅሷል። ኮሌጁ ለዘጠነኛ ጊዜ በአቭዬሽን፣ በቱሪዝም፣ በሎጀስቲክስና ቢዝነስ በሁለተኛና በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በሰርተፍኬት ያሰለጠናቸውን 277 ተማሪዎችን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) አዳራሽ በልዩ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል።

    ናሽናል አቭዬሽን ኮሌጅ የናሽናል አየር መንገድ እህት ኩባንያ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች መካከል ግንባር ቀደም መሆኑንም የኩባንያው ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ ብሩ ገልጸዋል።

    አየር መንገዱ በሀገራችን በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአቭዬሽንና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቀጣይነት ለማረጋገጥና ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ ቁልፍ የሆነውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ናሽናል አቭዬሽን ኮሌጅን በማቋቋም የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል።

    በአሁኑ ጊዜም መንግሥት የያዘውን የትኩረት አቅጣጫ በመከተል ግንባር ቀደም የስልጠና ተቋም በመሆን ለበለጠ ስኬት ራሱን አዘጋጅቶ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተው፥ ናሽናል አቭዬሽን ኮሌጅ ከተመሠረተበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከአራት ሺ በላይ ምሩቃንን ከሀገር አልፎም ለዓለም አበርክቷል ብለዋል።

    ናሽናል አቭዬሽን ኮሌጅ የሚሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በምታካሄደው የልማት የትኩረት አቅጣጫ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ እና ዓለም አቀፍ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ቱሪዝም በሚፈልገው ደረጃ የተወጠነ በመሆኑ የኮሌጃችን ፍሬ የሆኑት ተመራቂዎች በሄዱበት ሁሉ ስኬትማ እንደሆኑ ተገልጿል።

    ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት የአገር ግንባታ እየተሳተፈ ቢሆንም ብቻውን በሚያደርጋቸው ጥረቶች የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት አዳጋች መሆኑን ገልጸው፥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለኢንዱስትሪው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ቢያደርጉ የሚፈለገው ግብ ላይ መድረስ እንደሚቻልም አመልክተዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (አዲስ ዘመን)

    ናሽናል አቭዬሽን ኮሌጅ

    #56101
    Semonegna
    Keymaster

    ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱን ገለጸ

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና ገለጹ።

    መንግሥት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከመዋቅር ጀምሮ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

    ለአብነትም 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ብሔራዊ ፈተና በ12ኛ ክፍል እንዲሰጥ ከማድረግ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች በ3 ዓመት ይመረቁ የነበረውን ወደ 4 ዓመት እንዲያድግ መደረጉን አስታውሰዋል።

    ባለፉት ዓመታት በተለይ በትምህርት ፍኃዊነትና ተደራሽነት ላይ በርካታ ሥራ የተሠራ ቢሆንም በትምህርት አግባብነትና ጥራት ላይ የተሳካ ወይንም አጥጋቢ ሥራ ባለመሠራቱ ውጤት ሊመዘገብ አልተቻለም ብለዋል። ለዚህም በቅርቡ የወጣው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ችግር ምን ላይ እንዳለ በግልጽ አሳይቷል ብለዋል።

    በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ለመምህራን ምዘና ተሰጥቶ በርካቶቹ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን አውስተው፤ ይህ ለትምህርት ጥራት ችግሩ ዓይነተኛ አስተዋፆኦ እንዳለው ነው ያስረዱት። ለተማሪዎቹ ዝቅተኛ ውጤት መመዝገብ መምህራንን ጨምሮ አጠቃላይ የትምህርት ማኅበረሰቡ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ችግሩን በጋራ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

    መንግሥት የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አለመኖር ለትምህርት ጥራት መጓደል አንዱ ምክንያት መሆኑን በመረዳት ችግሩን ለማቃለል ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሙን ገልፀዋል። ጨምረውም፥ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ለማከም ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

    ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን ትምህርት ዋነኛ ምሰሶ በማድረግ የትምህርት አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ አማካሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎችን ማፍራት ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የሚያስችል የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱን ነው የተናገሩት። ፍኖተ-ካርታው በቀጣይ ለትምህርት ሚኒስቴር እንደሚቀርብም ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና የገለጹት።

    መንግሥት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመምህራን ሙያ በማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀው፥ የመምህራን ዕውቀትንና አቅምን ማጎልበት ደግሞ ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ሥራ መሆኑን አመላክተዋል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ

    #56105
    Semonegna
    Keymaster

    ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጆርናል ለማስጀመር በምሁራን አስገመገመ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በማስተማርና በምርምር ሥራዎቻቸው ዕውቅናን ያተረፉ ፕ/ር አማረ አስግዶም እና ፕ/ር ያለው እንዳወቅ እንዲሁም በኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ምርምርና ስርጭት (research and dissemination expert) ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ተስፋማርያም ሽመክት፣ ብሎም የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በተገኙበት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ‘ኮተቤ የትምህርት ጆርናል’ (Kotebe Journal of Education, KJE) የተሰኘውን ጆርናል ለማስጀማር ዝግጅቱን አጠናቆ ለዚሁ ዓላማ የተሰነዱ ፖሊሲንና መመሪያን የካቲት 16 ቀን፥ 2015 ዓ.ም አስገምግሟል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በአዋጅ ከተቋቋመ እነሆ አንድ ዓመት ከጥቂት ወራት በሆነ ጊዜ ውስጥ በርካታ የማቋቋም ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ። ከእነዚህም አንዱ ዩኒቨርሲቲው የሚታወቅበት የራሱ መለያ ጆርናል እንዲኖረው ማስቻል ነው። ጆርናል ምሁራን ጥናትና ምርምሮቻቸውን ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ለሶስተኛ ወገን ተጠቃሚ የሚያደርሱበት ድልድይ ነው። ለዩኒቨርሲቲ ይህ ድልድይ አንዱ የሀገራዊነት እና ከዚያም ባሻገር መለኪያ ነውና በጥንቃቄ የምንይዘው ነው ብለዋል። በመሆኑም ይህንኑን እውን ለማድረግ ስንሠራ ቆይተን የሚተገበርበትን አሠራር (ፖሊሲ እና የአሠራር መመሪያ) ቀርፀን ለዛሬ ማስጸደቂያ ቀን (validation) አድርሰናልና፤ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ በሙሉ ትልቅ አክብሮት አለኝ ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    በመልዕክታቸው አያይዘውም ፕሬዝዳንቱ ‘ኮተቤ የትምህርት ጆርናል’ (KJE) በዓይነቱ ለየት ያለ፣ ሀገራችንን፣ ተቋማችንን እና ትውልዱን የሚያሻግር እንዲሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲታተም ለዚሁ ሥራ አመራርነት ለተሠየመው ቲም አደራ ብለዋል።

    የ‘ኮተቤ የትምህርት ጆርናል’ አስመልክቶ የተዘጋጀ ፖሊሲን ያቀረቡት የጆርናሉ ዋና አርታኢ የሆኑት ዶ/ር ሩቂያ ሀሰን፥ የጆርናሉ ዋና ዓላማ ላቅ ባለ ሁኔታ ለተመራማሪዎች ሀገራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ የትምህርት እና የምርምር ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙበትን ተጨማሪ ዕድል መፍጠር መሆኑን ገልፀዋል። የጆርናሉ ተባባሪ አርታኢ ሆነው የተመደቡ ዶ/ር ይታያል አዲስም በበገለጻቸው የሚቀርቡ ጽሑፎች ከዚህ በፊት በማንኛውም ጆርናል ላይ ያልቀረቡና ሳይንሳዊ ሥነ-ዘዴዎችን (guidelines) ያሟሉ ስለመሆናቸው በጥብቅ ዲሲፕሊን ተገምግመውና የተቀመጠላቸውን መስፈርቶችን አሟልተው ሲገኙ ብቻ ለህትመት እንደሚበቁ ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲው የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT) መሠረተ ልማት ቡድን መሪ አቶ ማቲያስ አድማሱ በበኩላቸው፥ ለህትመት የሚቀርቡ ጽሑፎች በኦንላይን ሲስተም ሆነው ጆርናሉ ለህትመት እስኪበቃ ድረስ ያለው ሂደት ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን ይሠራል ብለዋል።

    ምንጭ፦ የዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

    #56753
    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ተቋም ለመሆን እየሠራ ነው

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ተቋም ለመሆን እየሠራ መሆኑ ተገለጸ። አስራ ሰባት (17) ችግር ፈቺ ምርምሮች ተሠርተው ወደ ግምገማ እና ትግበራ ገብተዋል።

    ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ ተቋሙ በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ካሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቶች ቀዳሚው ለመሆን እየሠራ ነው።

    በዚህም 17 የሚሆኑ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑንና ከፊሉ ወደ ትግበራ ማስገባታቸውን፥ እንዲሁም የተቀሩትን ምርምሮች ወደ ትግበራ ለማስገባት በግምገማ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

    ምርምሮቹም በጤና፤ በትምህርት፤ በአገልግሎት አሰጣጥና በፋይናንስ ዘርፍ ግልጋሎት እምርታዊ ለውጥ የሚያመጡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ለአብነት ያህልም በጤናው መስክ፥ የተለያዩ የሕክምና ዘርፉን ሊያዘምኑ ወይም ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ውስን የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች የሚገኙባቸው ሴክተሮች ላይ ተጨባጭ ውጤት ያመጣልም ብለዋል።

    የጭንቅላት እጢ፣ የጡት ካንሰር፣ የቆዳ በሽታ ልየታን ማከናወን የሚችሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች መዘጋጀታቸውንም አብራርተዋል። በአዲስ አበባ ስማርት ሲቲ (smart city) ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው የስማርት ሴኩሪቲ (smart security) ግንባታዎች እየተካሄዱ እንዳሉ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፥ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶች በሚካሄዱባት አዲስ አበባም በሺዎች የሚቆጠሩ የአርተፊሻል ኢተለጀንስ ካሜራዎች መገጠማቸውን አንስተዋል። ካሜራዎቹ የፊት ገፅታን እና የመኪና ሰሌዳ ቁጥሮችን የሚለዩ እና የሚመዘግቡ መሆናቸውን አያይዘው ጠቅሰዋል።

    በፋይናንስ ሴክተር የውይይት መለዋወጫ ሮቦት (ቻትቦት/chatbot) በማዘጋጀት ዘርፉን የሚያዘምኑ ሥራዎች እየተከወኑ እንዳሉ በማብራራትም፤ ቻትቦቶቹ በተመረጡ ሀገርኛ ቋንቋዎች ጭምር ግልጋሎት ይሰጣሉ ብለዋል። የደረቅ ጭነት የተቀናጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ ደግሞ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚንስቴር አበርክቶ መተግበሪያዎቹ ግልጋሎት መስጠት መጀመራውን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አትተዋል።

    በትምህርቱ መስክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አሰጣጥ አገልግሎታቸውን ማዘመን የሚያስችል እና የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ማስቀረት የሚያስችል እጅግ ዘመናዊ የሆነ መተግበሪያ ለምቶ ትግበራ ላይ መዋሉንም ጨምረው ጠቅሰዋል። የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶች በቅልጥፍና እንዲሠሩ እና ለመረጃ ቋትነት ግልጋሎት የሚሰጥ ማዕከል ግንባታም በተቋሙ ውስጥ ተከናውኗል ያሉት ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ፥ የመረጃ ቋት መኖሩ ለተማሪዎችም ይሁን ለመምህራን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Viewing 11 posts - 46 through 56 (of 56 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.