Home › Forums › Semonegna Stories › የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Tagged: Daniel Bekele, Ethiopian Human Rights Commission, ስንታየሁ ቸኰል, ክርስቲያን ታደለ, የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ, የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን, ፍሬው በቀለ
- This topic has 15 replies, 2 voices, and was last updated 2 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 24, 2019 at 1:40 pm #12402AnonymousInactive
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስ አበባ፥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ስር በአደራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጐብኝተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ስር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ኃይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሆኔታቸውንም ተመልክተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍሉ በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል።
በሌላ በኩል “ታሳሪዎቹ ከ 3–4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰርት ሊቀርብ ይገባል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
“ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማታሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ለጉዳዮቹ ሁሉ ሕጋዊ እልባት ለማግኘት ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ኮሚሽኑ ክትትሉን እየቀጠለ መሆኑን አሳውቀዋል።
ጉብኝቱ በዓለም ዓቀፍ የእስር ቤቶች ጉብኝት ደረጃ መሠረት ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የተደረገ ሲሆን የፖሊስ ኮሚሸኑ አመራሮች እና የጥበቃ ክፍል ኃላፊዎች ለዋና ኮሚሸነሩ ጉብኝቱ በማመቻቸት ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ዋና ኮሚሸነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምንጭ፦ የኮሚሽኑ ፌስቡክ ገጽ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 11, 2020 at 7:17 pm #15371AnonymousInactiveወላይታ ዞን ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም ሊቆጠቡ ይገባል!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – ወላይታ ዞን ውስጥ በአንዳንድ ከተሞች ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረጉት ተቃውሞዎች የፀጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝነት አጠያያቂ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
የተለያዩ ምንጮች እንደጠቆሙት የተቃውሞ ሰልፉ የተቀሰቀሰው ሰኞ ዕለት በፌዴሬሽኑ ውስጥ አዲስ የክልል መንግሥት መመሥረትን በተናጠል ለማወጅ በፈለጉ በርካታ ከፍተኛ የዞኑ ባለስልጣናት እስርን ተከትሎ ነው። የመንግሥት ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ግን ታሳሪዎቹ በአካባቢው አለመረጋጋት ለመፍጠር ሲያሴሩ ተይዘዋል ብለዋል።
የኮሚሽኑ የመረጃ ምንጮች እንዳስረዱት የባለስልጣናቱን እስር ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፈኞች በዞኑ ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ወደ ጎዳናዎች የወጡ ሲሆን፥ በዞኑ ዋና ከተማ በሶዶ አንድ ሰው እንዲሁም በቦዲቲ ከተማ አምስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል ።
በሰኞው እስር ወቅት በጠቅላላው 178 ሰዎች የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሆናቸው እና በወላይታ ሶዶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ በቁጥጥር ስር የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ እንደገለጹት፥ “የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፎችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፤ እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎች ቀድሞውኑን የነበረ ውጥረትን ያባብሱ እንደሆን እንጂ መፍትሔ አይሆኑም” ብለዋል።
አቶ አሮን አያይዘውም በግጭቱ ወቅት የተከሰተው የ6 ሰልፈኞች አሟሟትን እና የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ፈጣን ምርመራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም የታሳሪዎችን መብቶች ማክበርና በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለስረ-ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንጻርም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት በክልሉ ውስጥ ለተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ወቅታዊና ሰላማዊ መፍትሔ በሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።
ወላይታ ዞን ውስጥ በተቀሰቀሰው ግጭት የተከሰተው ምንድን ነው?
ባለፈው እሁድ (ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ መልስ አልተሰጠንም በሚል በተነሳ የተቃውሞ ሰልፍ፥ በነጋታው (ነሐሴ 4 ቀን) በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የጠቀሳቸው የቦዲቲ ከተማ የጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተመስገን ሕሊና ነሐሴ 4 ቀን በቦዲቲ ከተማ ቢያንስ ስድስት ሰዎች የጸጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ መገደላቸውን ተናግረዋል። ለሌሎችም (ለተጎዱ ሰዎች) የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ መስጠታቸውን የተናገሩት አቶ ተመስገን፥ የጥቃቱ ሰለባዎች ጭንቅላታቸው፣ ሆዳቸውንና ደረታቸው ላይ መመታታቸውን ገልጸዋል። ከሞቱት መካከል የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት እንደሚገኝበትና የቆሰሉትም በቁጥር እንደሆኑ አክለው ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የጤና መኮንን ደግሞ፥ በሶዶ ከተማ አራት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተተኩሶባቸው የተገደሉ ሰዎች ማየታቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ105 በላይ መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ ለዶይቼ ቬለ የአማረኛ ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል።
August 13, 2020 at 11:53 am #15396SemonegnaKeymasterበአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት የታዩ ክፍተቶች አፋጣኝ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ‹COVID-19› በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 3/2012 ማወጁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀ ወዲህ በመላው ሀገሪቱ ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ ካለመሆኑም በላይ የቫይረሱን ስፋት እና የስርጭት መጠን መሠረት በማድረግ በየጊዜው በአስፈጻሚው አካል የሚወጡ መመሪያዎችም በጥናት ያልተደገፉ እና ለሕግ አስከባሪው ኃይል የተለጠጠ የማስፈጸም ሥልጣን የሚሰጡ ሆነው ታይተዋል። በዚህም ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር ሳምንታት የታዩት የዐዋጁ አፈጻጸም ሂደቶችም ሆኑ የመመሪያ አወጣጥ ሂደቱ ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በጽኑ ያምናል።
ዓለም-አቀፉ የጤና ድርጅት እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስን አስመልክተው በየጊዜው ይፋ ከሚያደርጓቸው መግለጫዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ቫይረሱ ገና በቅጡ ተጠንቶ ያልታወቀ ተለዋዋጭ ባሕርይ ያለው መሆኑ ነው። ከዚህ የተነሣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንዲያስችሉን የምንወስዳቸው እርምጃዎች በበቂ ጥናት ላይ የተመረኮዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከታወቀበት ጊዜ አንሥቶ ፍ/ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው መቆየታቸው የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲገደብ ከማድረጉ በላይ ጉዳያቸው በአፋጣኝ ታይቶ በነጻ መሰናበት እንዲሁም በዋስ መለቀቅ የሚችሉ ዜጎች ያለ አግባበብ በእሥር እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል። በዚሁ ምክንያት አንዳንድ ማረፊያ ቤቶች በመጨናነቃቸው ዜጎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ሆነዋል።
የዐዋጁ አፈጻጸም ሲገመገም የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ ከማንኛውም ጥቃት ነጻ-የመሆን፣ ፍትሕ የማግኘት፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ ያልተመጣጠነ ገደብ ያስቀመጠ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ በጥብቅ ያምናል። ከዚህም በተጓዳኝ በቀጥታ በዐዋጁ ምክንያት ባይሆንም፤ የቫይረሱ መስፋፋት ባስከተላቸው ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የተነሳ በጤና ባለሙያዎች፣ በሴቶች እና ሕጻናት፣ እንዲሁም በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ላይ ዓይነተ-ብዙ የመብት ጥሰቶች እየደረሱ በመሆኑ ትኩረት እና መፍትሔ የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ ያምናል። እንዲሁም በዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት እና በአጠቃላይ ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ከታዩት ጉልህ የመብት ጥሰቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
በትግራይ ክልል ናዕዴር ዓዴት ወረዳ ቀደም ብሎ በክልሉ ታውጆ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማስከበር በሚል አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም መቐለ ከተማ ሰሜን ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው 05 ቀበሌ አካባቢ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሕክምና ላይ ናቸው። በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አንድ የባጃጅ ሹፌር በጸጥታ ኃይሎች በተፈጸመበት ጥቃት አንድ እጁ ላይ በጥይት ጉዳት ደርሶበታል።
በተለያዩ አካባቢዎች “የአፍ መሸፈኛ ጭምብል አላደረጋችሁም” በሚል ምክንያት ፖሊስ ተመጣጣኝ ባልሆነ እርምጃ በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልት እና ለቫይረሱ አጋላጭ በሆነ መንገድ የጅምላ እስር ፈጽሟል። “ዐዋጁን ተላልፈዋል” በሚል ምክንያት ንግድ ቤቶች የሚታሸጉበት እና በሰዓት ገደብ እንዲዘጉ የሚደረጉበት ሂደት አንድ ወጥ አለመሆኑ አድሎአዊ እና ሕገ-ወጥ ለሆነ አፈጻጸም አጋልጧል።
ቫይረሱን ግንባር-ቀደም ሆነው እየተከላከሉ ላሉት የጤና ባለሙያዎች በቂ ራስን የመከላከያ ግብዓቶች እየቀረቡ ባለመሆኑ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እንዲሰሩ በመደረጋቸው ለቫይረሱም ተጋላጭ ሆነዋል። በጤና ሚንስቴር ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሠረት እስከአሁን ድረስ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋም ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። “ንክኪ አላቸው” በሚል በየጊዜው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚደረጉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ነው።
በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሀገር ውስጥ በረራ ሊያደርጉ የነበሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች “ዓለም-አቀፍ በረራ አድርጋችኋል” በሚል ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለአስራ ስድስት ቀናት ያህል እንዲገቡ፣ ለተወሰኑ ቀናትም ቤተሰብ ያሉበትን እንዳያውቅ ተደርጓል። ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም የቫይረሱን መከላከያ ሥራዎች ሽፋን በማድረግ በአባላትና አመራሮቻቸው ላይ ልዩ ልዩ ተጽዕኖዎች እየደረሱባቸው ነው። ለአብነት፥ ወደ ደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ ለቤተሰባዊ ጉዳይ የሄዱትን አንድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አባል ወደ ከተማዋ ለሚገቡ ሌሎች ሰዎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ በማይሆን አሰራር ከግንቦት 9 – 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ ተለቀዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ፖሊስ ጣልቃ በመግባት እንዲቆም ተደርጓል።
የቫይረሱ ስርጭት ባስከተለው ተጽዕኖ የዜጎች የሥራ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ከመውደቁም በላይ፥ አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኞቻቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ እና አስገዳጅ ፈቃድ ያለክፍያ እንዲወጡ ተደርጓል።
የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ይፋ ባደረገው መረጃ በተለይም በጅቡቲ በኩል የሚገቡ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከሚደርስባቸው መገለል በተጨማሪ በአንዳንድ ከተሞች የማደሪያ እና የምግብ አገልግሎት እንዳያገኙ፣ መኪና እንዳያቆሙ ክልክላ ይደረግባቸዋል።
መንግሥት ቀዳሚ ትኩረቱን በሽታውን በመከላከል እና ተያያዥ ሥራዎች በማድረጉ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን የመሳሰሉት ልማዳዊ ጎጂ ድርጊቶች እየተበራከቱ እና እየተስፋፉ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ብቻ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 101 ያህል ህጻናት የመደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም መሰል የመብት ጥሰቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በመሆኑም፥ ዐዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እና በየደረጃው ያለው ግብረ-ኃይል ለእነዚህ የመብት ጥሰቶች እና የአፈጻጸም ችግሮች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ በትኩረት እንዲሠራ ኢሰመጉ ያሳስባል። መንግሥት በዐዋጁ አፈጻጸም ምክንያት ሊጎዱ ለሚችሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች፣ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እርዳታ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ቫይረሱን ከፊት ሆነው እየተከላከሉ ላሉ የሀገራችን የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ አሁን ካለበትም ደረጃ የከፋ የሚሆንበትም ጊዜ ሳይጠበቅ አስፈላጊ የሆነውን ራስን የመከላከያ ግብዓት በበቂ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲያገኙ መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ሕክምና ላይ የሚገኙ ዜጎች የምግብ አገልግሎት፣ የመኖሪያ እና የንፅህና መስጫ ስፍራ ጽዳት፣ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን ጨምሮ የሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦትና የመሳሰሉ የአገልግሎት ችግሮች መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው መንግሥት በትኩረት ችግሮቹን እንዲያስተካከል ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል። በየጊዜው ዐዋጁን በመተላለፍ ተይዘው እንደ ትምህርት ቤት ባሉ መሠረተ ልማቶች ውስጥ የታሰሩ ዜጎች የሚቆዩበት ሥፍራ እንደ ምግብ፣ አልጋ፣ መጸዳጃና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ለመስጠት በሚያስችል መልኩ መደራጀታቸውን እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ያሳስባል።
በዐዋጁ ድንጋጌ መሠረት የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት ተዘግተው ተማሪዎች እና መምህራን በአካል ተገናኝተው ትምህርት የሚሰጥበት ሂደት ተቋርጧል። ሆኖም ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው ትምህርት እንዲከታተሉ እየተደረገበት ያለው መንገድ ጥራቱን በጠበቀ፣ ተማሪዎች ትምህረቱን ለማስተላለፍ የሚረዱትን ነገሮች የማግኘት አቅማቸውን ታሳቢ ያደረገ እና የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን ፍትሐዊ እድል ለመስጠት በሚያስችል መልኩ እንዲሰጡ መንግሥት እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርማሪ ቦርድም ሁኔታዎቹን በየጊዜው እየተከታተለ፣ በዐዋጁ ይዘት እና አፈጻጸም ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን በአግባቡ እንዲስተካከሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን። መንግሥት ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን አስመልክቶ በየደረጃው የሚሠሩ ሥራዎች ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ እና የሲቪል ማኅበረሰቡንም ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።
ከዚህ በኋላ የሚወጡ መመሪያዎች የበሽታውን ባህርይ ታሳቢ ያደረጉ፣ በበቂ ጥናት እና መረጃ ላይ የተመሠረቱ፣ ለሕግ አስከባሪ ኃይሎች የሚሰጡት ሥልጣን ውስን እንዲሆን፣ ብሎም ክልከላ የተደረገባቸውን ነገሮች በግልጽ የሚያመላክቱ እንዲሆን ኢሰመጉ በጥብቅ ያሳስባል። ዐዋጁን በማስፈጸም ወቅት የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ሚና የጤና ባለሙያዎችን የማገዝ እንዲሆን ቅጣት እንኳን አስፈላጊ ቢሆን ሕይወትን የማዳን ዓላማ እንጂ የባሰ አደጋ ውስጥ በማይከት ሁኔታ መሆን ስለሚገባው፤ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ የሚያሳስብ ድንጋጌ በያዘ መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኢሰመጉ ያሳስባል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉ የመሬት ወረራን ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ የሕግ ማስከበርና የቤት ማፍረስ እርምጃዎች ያለንበት ወቅት ክረምት እንደመሆኑ እና ዜጎችን ለበሽታውም ስርጭት የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ በጥንቃቄ እና ወጥነት ባለው እንዲታዩ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!
ምንጭ፦ ኢሰመጉ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ 1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር ከ404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት መስከረም 29 ቀን 1984 ዓ.ም. በአባላት የተመሠረተ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ ተሟጋች ተቋም ነው።August 21, 2020 at 12:40 am #15495AnonymousInactiveኢሰመኮ (ጋዜጣዊ መግለጫ) ― ኦሮሚያ፡ የሞት እና አካል ጉዳት አደጋ በተቃውሞ ሰልፎች
አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ምክንያት የሚከሰተው የሰዎች ሕይወት መጥፋት በእጅጉ እንደሚያሳስበው እየገለጸ፥ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪውን ያቀርባል።
በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በተለይም በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሀሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ የሞት ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ ደርሶታል፡፡ የሞት ጉዳቶቹ የደረሱት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
“የመንግሥት አካላት የዜጎችን በሰላማዊ መልኩ ተቃውሞ የማሰማት መብት ማረጋገጥ እንዳለባቸው እና ሕግ የማስከበር ሥራ ተመጣጣኝነት እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው”የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ ገልፀዋል።
“የኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት የተከሰቱ አሳዛኝ ግድያዎች ከፈጠሩት ሰቆቃ አሁንም ፈጽሞ አላገገመም። እነዚህ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አዝማሚያዎች እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም” በማለት አክለው ገልጸዋል።
እስካሁን በአንዳንድ ሚዲያዎች የወጡ ሪፖርቶች እና በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ መረጃዎች የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በሚመለከት የተለያየ አሃዝ አስቀምጠዋል። ኢሰመኮ የደረሰውን ሞትና ጉዳት መጠን ለማረጋገጥ ከየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ምስክሮች፣ ሆስፒታሎች እና የአስተዳደር አካላት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።
ኢሰመኮ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ጉዳዩን ለማጣራት በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ መንግሥት (ሰኔ 1986 ዓ.ም.) አዋጅ ቁጥር 210/1992 ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዲሠራ ሰኔ 27 ቀን 1992 ዓ.ም. የተመሠረተ ተቋም ነው።ተመሳሳይ ዜናዎች
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
- የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መግለጫ ― ሀገራችን ካጋጠማት ፈተና እንድትወጣ በሰላማዊ ትግላችን እንድንቀጥል የቀረበ ጥሪ
- በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት የታዩ ክፍተቶች አፋጣኝ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል! ― የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ
- ፖሊስ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ቀድሞ የሕግ የበላይነትን እራሱ ሊያከብር ይገባል! ― ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
- ወላይታ ዞን ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም ሊቆጠቡ ይገባል! ― የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
September 18, 2020 at 3:30 pm #15917AnonymousInactiveበቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል የተከሰተውን ግድያ እና መፈናቀል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ
አሶሳ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን /ኢሰመኮ/ (ኮሚሽኑ) በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ አሳስበውታል።
ኮሚሽኑ ከክልሉ ከመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት ነው። ኮሚሽኑ በጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲሁም ከጳጉሜ 2 አስከ መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም. መካከል ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግሥት ለማረጋጥ ችሏል።
በቦታው ላይ ከሚገኝ አንድ መንግሥታዊ ምንጭ መረዳት እንደተቻለው፥ ቢያንስ በሁለት ዙር በደረሱ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን፤ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጥ ችሏል።
የክልሉ መንግሥት እንደጠቆመው ከተፈናቃዮቹ መካከል 300 ያህል የሚሆኑት ወደ ቀያቸው የተመለሱ ሲሆን፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር አካባቢውን ለማረጋጋት እየሠሩ ነው።
ስለሆነም ኮሚሽኑ፡-
- በክልሉ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ሙሉ በሙሉ ያወግዛል፤
- በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያበረታታል፤
- በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥትና እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ማለትም፡ በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ በዓለምአቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች የተደነገጉትን በህይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ ይጠይቃል፤
- በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ ያሳስባል፤
- የሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት አካላት ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ህይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጥሪ ያቀርባል፤
- ኮሚሽኑ በተለይም መሰረታዊ የሆነው በህይወት የመኖር መብት ይረጋገጥ ዘንድ የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት አካላት እንዲሠሩ ያሳስባል።
በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉ እና ከማንኛውም ዓይነት የሁከት ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪውን ያቀርባል፤ እንዲሁም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት እና ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ሌሎች አግባብነት ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የተቀመጡ መብቶችን እና ግዴታዎችን እንዲያከብሩ ኮሚሽኑ እየጠየቀ፥ በቀጣይም ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተለው ይገልፃል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን /ኢሰመኮ/
September 28, 2020 at 7:32 pm #16143SemonegnaKeymasterመንግሥት የሰዎችን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህነነትና ነጻነት የመጠበቅ እና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ይጠብቅ!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ – ኢሰመጉ-
መንግሥት በቤንሻንጉል ክልል የሰዎችን በሕይወት የመኖርና የአካል ደህንነት መብት ይጠብቅ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 14 ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና ነጻነት መብት እንዳለው በግልጽ ይደግጋል። ይሁንና፥ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፥ መተከል ዞን፥ ጉባ፣ ዲባጢ፣ ቡለን እና ወንበራ ወረዳዎች ውስጥ ከባለፈው ጳጉሜ ወር ጀምሮ ማንነቸታው ባልታወቁ አካላት ሲደርስ የነበረው ጥቃት፤ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም በዳንጉር ወረዳ፣ በንገዝ ቀበሌ ዳግም ተከስቶ የበርካታ ንጹኃን ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ እንዲሁም የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ከቦታው ካሉ እማኞች ለመረዳት ችሏል። ጥቃቱ እየደረሰባቸው ያሉ ወረዳዎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ኮማንድ ፖስት ስር ተይዘው የጸጥታ ማስከበር እርምጃዎች እየተሠሩ ያሉ ቢሆንም፤ አሁንም ግን ተጨባጭ ስጋቶች እንዳሉ ኢሰመጉ ለማወቅ ችሏል።
በመሆኑም፥ ኢሰመጉ መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይህ መሰሉ ጥቃት ዳግም እንዳይከሰት መንግሥት አስፈላጊና ሕጋዊ የሆኑ የአጭር እና የረዥም ጊዜ እርምጃዎችን በአስቸኳይ እንዲወስድ ማሳሰቡ አይዘነጋም። ስለሆነም፥ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መንግሥት በከፍተኛ ትኩረት በመመልከት የሰዎችን በሕይወት እና በሰላም የመኖር፣ የአካል ደህነነትና ነጻነት የመጠበቅ ሰብዓዊ መብት በምልዓት እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ዳግም ጥሪውን ያቀርባል። የችግሩ ስፋት ተባብሶ ከዚህም የባሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ከመድረሱ በፊት፥ የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት፣ የአዋሳኝ ክልሎች መንግሥታት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እንዲሠሩ ኢሰመጉ ያሳስባል።
በተጨማሪም፥ መንግሥት በእስካሁኑ ሕገ-ወጥ ድርጊት የተሳተፉ አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርብ፣ ለተጎጂዎች ተገቢውን ካሳ እንዲሰጥ እና የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መጣራት የሚቻልበት ሁኔታ እንዲያመቻች ኢሰመጉ በጥብቅ ያሳስባል።
-
መንግሥት የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነጻነት ይጠብቅ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 32 (1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር መብት እንዳለው በግልጽ ያስቀመጠ ቢሆንም፤ ዜጎች ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ለንግድና ለተለያዩ ጉዳዮች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ተገድቧል። ከመስከረም 11 እስከ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት መነሻቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አድርገው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ጫንጮ እና ገብረ ጉራቻ ከተሞች ላይ ሲደርሱ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና ጸጥታ ኃይሎች ታግደው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መደረጋቸውን ኢሰመጉ በየአካባቢዎቹ ከሚገኙ ከመረጃ ምንጮቹ ለመረዳት ችሏል። በእነዚህ ቀናት በነበረው እንቅስቃሴ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ከነበሩ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች መካከል አብዛኛዎቹ በአቅራቢያ ወዳሉ ከተሞች ተመልሰው ለማደር በመገደዳቸው፤ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልትና ወጪዎች መዳረጋቸውን ኢሰመጉ ለማረጋገጥ ችሏል።
ይህን መሰሉ ድርጊት፥ ከአሁን ቀደምም ተከስቶ ጥቅምት 01 ቀን 2012 ዓ.ም መነሻቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ያደረጉ ከ80 በላይ የሆኑ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ‹‹ወደ አዲስ አበባ መግባት አትችሉም›› በማለት ወደ ደጀንና ባህር ዳር ከተሞች እንዲመለሱ መደረጋቸው ይታወሳል። ይህን አስመለክቶም፥ ኢሰመጉ በወቅቱ ጥቅምት 07 ቀን 2012 ዓ.ም ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት እንየተዳረጉና ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው አላግባብ እየተጣሰ መሆኑን የሚገልጽ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ስለሆነም፤ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይከሰቱ፤ ተጨባጭ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች በሚኖሩ ጊዜ አስቀድሞ ለማኅበረሰቡ በግልጽ በማሳወቅ አስፈላጊና ሕጋዊ የሆኑ እርምጃዎችን ከሕብረተሰቡ ጋር በትብብር በመሥራት ሊፈቱ እንደሚገባ ኢሰመጉ ያምናል።
ከዚህም በተጨማሪ፥ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አላግባብ የሚገድቡ የመንገድ መዝጋት እንቅስቃሴዎችን እና እርምጃዎችን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት በትኩረት ተመልክተው ሕጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ኢሰመጉ ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ – ኢሰመጉ
መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ምየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም አቀፍ ጸረ-ሥቃይ ድርጅት (OMCT) አባል፣ የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ኅብረት (Defend Defenders) መሥራች አባል ነው።
November 17, 2020 at 2:16 am #16724AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ኦሮሚያ ክልል፡ የዋስትና መብትን በተቀላጠፈ መንገድ ስለማረጋገጥየኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበታ ልዩ ችሎት ለአራት ወራት ያህል በእስር በቆዩት በአቶ ለሚ ቤኛ እና በአቶ ዳዊት አብደታ ጉዳይ የዋስትና መብታቸውን በማረጋገጥ የሰጠውን ትክክለኛ ውሳኔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እውቅና እየሰጠ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት በተመሳሳይ መልኩ የሌሎችንም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ያቀርባል።
ኢሰመኮ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፥ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸውና የዋስትና ሁኔታውን አሟልተው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ሰዎች በእስር እንዲቆዩ መደረጉ ፍትህን የሚያጓድልና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፥ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸዉ በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ ማሳሰቡ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ስለሚገኙ ሰዎች ሁኔታ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች በማሳወቅ ክትትሉን የቀጠለ ሲሆን፤ በተለያዩ ቦታዎች አበረታች አርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም አሁንም ድረስ በተለይ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው በእስር የሚገኙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የአቶ ልደቱ አያሌው እና የዶ/ር ሁሴን ከድር ጉዳይ አፋጣኝ እልባት የሚሻ መሆኑን ኮሚሽኑ ያሳስባል።
ከሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ በእስር ላይ ለሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ክስ የተመሠረተባቸው ሲሆን፤ አሁንም በድጋሚ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወቃል። በኢሰመኮ ምርመራ መሠረት በአቶ ልደቱ ላይ የቀረቡት ክሶች የዋስትና መብት የማያስከለክሉ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ኢሰመኮ የተመለከተው የጤንነታቸው ሁኔታ ማስረጃዎች የዋስትና መብት ጥያቄውን በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግን አስፈላጊነት ያስረዳል። ስለሆነም የአቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና መብት በአስቸኳይ ሊፈቀድ የሚገባ ነው።
በሌላ በኩል ከሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሁሴን ከድር የአጋርፋ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የዋስትና መብት ፈቅዶላቸዉ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ከመስጠቱም በተጨማሪ፥ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከፖሊስ በቀረበለት የተጠርጣሪው የምርመራ መዝገብ ላይ በሰጠው ውሳኔ ክስ ለማቅረብ የሚያበቃ ማስረጃ አለማግኘቱን ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን ዘግቷል። ይሁንና ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ ፖሊስ ለኮሚሽኑ እንዳሳወቀው በተጨማሪ ወንጀል በመጠርጠራቸው አሁንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሁሴን ከድር አብዛኛውን የእስር ጊዜ የቆዩት በአጋርፋ እስር ቤት ሲሆን፤ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተወስደው አሁንም በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ኢሰመኮ የተረዳ ቢሆንም፤ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ወዲህ ከቤተሰቦቻቸው አለመገናኘታቸው ኮሚሽኑን አሳስቦታል። ስለሆነም ዶ/ር ሁሴን ከድር በአስቸኳይ በቤተሰባቸው ሊጎበኙ የሚገባ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ሊያስከስስ የሚችል አሳማኝ ክስ ካለ በአፋጣኝ ሊቀርብ፣ አሊያም ከእስር ሊለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸው በአስቸኳይ ሊከበር ይገባል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት “የዋስትና መብት በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የተረጋገጠ መሠረታዊ መብት እንደመሆኑ፥ በሕግ በግልጽ ከተመለከቱ ሁኔታዎች በስተቀር የዋስትና መብት በተቀላጠፈ አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ነው።” አክለውም “በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቶች የተከሳሾችን የዋስትና መብት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን እየወሰኑ መሆናቸው የሚበረታታ ተግባር ነው” ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
November 25, 2020 at 7:19 am #16777AnonymousInactiveማይካድራ ውስጥ ሲቪል ሰዎች ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው ― ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
ትግራይ፡ የማይካድራ ሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው
የተጎዱትን ማቋቋም እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይገባልበትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል (atrocious crime of massacre against civilians) መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀ ጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተሞች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ነው። ይህ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ስለሆነ፥ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል።
በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፥ በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ ሀገር መከላከያ ሠራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር በተለይ “አማሮችእና ወልቃይቴዎች” ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል። ኢሰመኮ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን ባገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል” ብለዋል። አክለውም “የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፥ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርትን እዚህ ጋር በመጫን ማግኘት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም.December 23, 2020 at 3:07 pm #17077AnonymousInactiveአሰቃቂ ጭፍጨፋ በመተከል ዞን ― የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፡ የሰዎች ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ ነው።
ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፥ መተከል ዞን፥ ቡለን ወረዳ፥ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው በክልሉ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ገለጸ።
ኢሰመኮ የጥቃቱን ሂደት በተመለከተ ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት እና ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር ሲከታተልና ሲያጣራ ቆይቷል። በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ከሆነችው ቡለን ከተማ 90 ኪ.ሜ. ርቃ የምትገኝ ሲሆን የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ይኖሩባታል። ለቀበሌው የተመደበ የፖሊስ ወይም የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን ኮሚሽኑ በክትትሉ መሠረት ተረድቷል።
ኮሚሽኑ ሁኔታውን እስካጣራበት ጊዜ ድረስ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፥ አብዛኞዎቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን ኢሰመኮ በምልከታ አረጋግጧል። በተጨማሪም ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸውን ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል። በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል። ቢያንስ 18 ያክል ነዶዎች ሲቃጠሉ ማየታቸውን አንድ ተጎጂ አስረድተዋል።
በጨላንቆ እና ዶሼ ቀበሌዎች ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ከአካባቢው ለኮሚሽኑ የተላኩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነም ኮሚሽኑ ተረድቷል።
አካባቢውን በቅርበት እንዲጠብቅ የተመደበው ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማረጋጋት ተግባር ወደቦታው ተልከው የነበሩ አንድ የፌዴራል እና ሁለት የክልሉ አመራሮችን ለማጀብ በሚል አካባቢውን ለቅቆ መሄዱ ታውቋል። ጥቃቱ የጀመረው ይህንኑ ተከትሎ እንደሆነና ሌሊቱን የጀመረው ጥቃት እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ መዝለቁንም ለማወቅ ተችሏል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛው የሺናሻ ተወላጆች ናቸው።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ጥቃቶች ፈጻሚዎቹ ከ”ጫካ” የሚመጡ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፥ በዚህኛው ጥቃት “በስምና በመልክ የሚያውቋቸው” የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸዋል።
ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተደጋጋሚነትና የክልሉን ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ አስመልክቶ የፌዴራሉንና የክልሉን መንግሥታት የተጠናከረ ትብብርና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል፤ ይሁንና ጥቃቶቹ በመልክ እና በስፋት እየተባባሱ መጥተዋል።
ስለሆነም፣ በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለተፈናቀሉ ሰዎች የሕክምና እና ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረቡ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመር ኮሚሽኑ ያሳስባል። በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከር ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.January 2, 2021 at 12:56 am #17232AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
ኦሮሚያ ክልል ― የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተከስቷል፤ አጥፊዎቹ ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸውየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተከሰተ የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባህርያትን የሚያሟሉ መሆናቸውን በምርመራ ሪፖርቱ አመለከተ።
ኢሰመኮ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የባለሙያ ቡድኖቹን ወደ 40 የክልሉ አካባቢዎች የላከ ሲሆን፥ የምርመራውን ግኝቶች ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።
በ59 ገጽ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፥ በዚህ መጠነ ሰፊ ጥቃት የተሳተፉት ብዙ ቁጥር ያላቸው እና ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ፤ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራ እና በመጥረቢያ ተጠቅመው ሰዎችን ደብድበዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማሰቃየት እና በማረድ ጭምር ሰዎችን ገድለዋል። በጥቃቶቹ የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ 500 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ፣ በብሔርና በሀይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሲቪል ሰዎችን፣ ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች በተስፋፋና ለሦስት ቀናት በቆየ ሁከት ማጥቃታቸው፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሚያደርገው የኮሚሽኑ ግኝቶች ያመላክታሉ።
ምንም እንኳን የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው የገጠመውን መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና የፀጥታ አባሎቹንም የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ሁኔታ በመሰማራታቸው ኃላፊነታቸው እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑን መገንዘብ ቢቻልም፤ በተወሰኑ ቦታዎች የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል። በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ፥ ሰልፍ ውስጥ ያልነበሩ፥ በመንገድ ወይም በቤታቸው በር ላይ የተገደሉ፣ ለማሸማገል ጣልቃ የገቡ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአዕምሮ ህመምተኛ ጭምር እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ‘በኢትዮጵያ የሚታየው የግፍና የጭካኔ ወንጀሎች መደጋገም፣ የችግሩን ስር መሠረት ለመፍታት የሚያስችል የተሟላ ብሔራዊ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ ነድፎ በአፋጣኝ በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚያሳይ መሆኑን’ ገልጸዋል።
ሙሉ ሪፖርቱ “መንግስት ያለ አይመስልም ነበር፡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ሪፖርት” በሚል ርዕስ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።
January 14, 2021 at 1:18 am #17408AnonymousInactiveመቆሚያ ያጣው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል (መተከል ዞን) ያሉ ሰዎች እልቂት!
አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ (ኢሰመጉ)የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ መተከል ዞን፣ በቡለን፣ ድባጤ፣ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ እጅግ አሳስቦታል።
ኢሰመጉ ታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል (መተከል ዞን)፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ንጹኃን ሰዎች መገደላቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን አውግዞ፤ መንግሥት በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን የንጹኃን ሰዎች ሰቆቃ ለማስቆም የሚያስችል ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጅ ማሳሰቡ አይዘነጋም።
ሆኖም፤ ከሰሞኑ ይኸው ችግር ዳግም ተከስቶ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ለኢሰመጉ ተናግራዋል። ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ የሚሄድ መኪና ውስጥ የነበሩ ተጓዦች ማንዱራ ከተማ ላይ በታጣቂዎች እንዲወርዱ ተደርጎ አንድ ሰው መገደሉን እና ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ከጥር 2 እስከ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በቡለን እና ጉባ ወረዳዎች፣ ኦሜድላ እና አይነሸምስ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸውን ኢሰመጉ መረጃዎች ደርሰውታል።
በሌላ በኩል፤ ‹‹በድባጤ ወረዳ፣ ቆርቃ ቀበሌ፣ ዳሌቲ በተባለች መንደር ትላንት ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ የኦነግ ሸኔ እና የቤኒን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን፣ እስከአሁን ድረስ እኔ ራሴ ባለሁበት የ82 ሰዎች አስከሬን በፍለጋ መገኘቱን እና የቀብር ቦታዎች እየተዘጋጁ መሆኑን አይቻለሁ›› ሲሉ አንድ የዓይን እማኝ ለኢሰመጉ ተናግረዋል።
ኢሰመጉ በትላንትናው (ጥር 4 ቀን) ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሊበለጥ እንደሚችል፣ በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን እና ከ24 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቆስለው በጋሊሳ ጤና ጣቢያ እና ቡለን ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል።
በመሆኑም፥ መንግሥት ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላትን በአግባቡ አጣርቶ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፤ ለዚህ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለጉ ላይ በብርቱ እንዲሠራ ኢሰመጉ ያሳስባል። ኢሰመጉ ይህ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ሁሉም ግለሰቦች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎች በመንግሥት ላይ ውትወታ እንዲያደርጉ ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)
ጥር 5 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያJanuary 19, 2021 at 12:30 am #17495AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ትግራይና አማራ ክልል፡ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል
አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እና ድጋፍ ሊቀርብ ይገባልየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ፣ በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎች ደኅንነት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአሳሳቢና ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ በሚችል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገለጸ። ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 6 እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጎንደር እና በዳንሻ በመገኘት እንዲሁም፣ ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በትግራይ ክልል፣ ደቡባዊ ዞን፣ ጨርጨር ወረዳ በሚገኙት ኡላጋ እና ቢሶበር መንደሮች በመጓዝ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ተጎጂዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ያደረገውን ክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
በተጨማሪም የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ከጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ ዙር የመስክ ምልከታ ወደ መቀሌ ከተማ እና ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፥ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብዓዊ ቀውስ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በመመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ሥራው እንደተጠናቀቀ ተጨማሪ ሪፖርቱን ይፋ የሚደረግ መሆኑን ኮሚሽኑ አክሎ አሳውቋል።
የአሁኑ ክትትል በዋነኛነት በተካሄደባቸው በዳንሻ፣ በሁመራ፣ በቢሶበር እና በኡላጋ ጦርነቱ የሲቪል ሰዎችን ሞትና አካላዊ ጉዳት አስከትሏል፤ የሲቪል ሰዎችን መኖሪያና የንግድ ቦታዎች ለዝርፊያና ለተለያዩ ጉዳቶች አጋልጧል፤ እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመትና የኤሌክትሪክ እና የውሃ የመሳሰሉ አገልግሎቶች አለመመለስ፣ በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና በተፈናቃናዮች ላይ የበለጠ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል የሚያሰጋ ነው። በቢሶበር እና በኡላጋ 31 ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፤ 104 መኖሪያ ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ እንዲሁም የአካባቢው ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በሁመራ እና በዳንሻ የሲቪል ሰዎች ንብረት የሆኑ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶችን ጨምሮ የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ውድመት እና ዝርፊያ ደርሷል። ሲቪል ሰዎች በብሔራቸው ምክንያት ወይም በአካባቢዎቹ የፀጥታ መጓደል ምክንያት ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በእነዚህ አራት ከተሞች ያለው የፀጥታ ስጋትና የፍትህ አካላት ወደ መደበኛ ሥራቸው አለመመለስ፣ የሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ጥበቃ ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሲያስረዱ፥ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ምርመራውና ክትትሉ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የነዋሪዎቹንም ሆነ ከትግራይ ክልል ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት እንዲጨምርና የመቋቋም አቅማቸውን በአስከፊ ሁኔታ እንዲፈተን አድርጓል” ብለዋል። የኮሚሽኑ ምርመራ ቡድን የጎበኟቸው ተጎጂዎች በአብዛኛው በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው አሊያም አንድ ዙር ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው መሆኑን በሪፖርቱ እንደተመለከተ ጠቅሰው፥ “በአካባቢዎቹና በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት የሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው” በማለት ገልጸዋል።
ሙሉውን ሪፖርት እዚህ ጋር (ማስፈንጠሪያ) በመጫን ማግኘት ይቻላል።
March 9, 2021 at 2:07 am #18505AnonymousInactiveከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ
አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አድርገዋል።
በጉብኝቱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገብረመድኅን፣ ሜ/ጀነራል ገብረመድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተው ታሳሪዎችን አነጋግረዋል። እንዲሁም ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል። ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል። የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው፣ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች አሉ። አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል። ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል። በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው ደረጃ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች ላይ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የወንጀል ምርመራውን በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ እና የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
June 26, 2021 at 3:01 pm #19782AnonymousInactiveበ2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል (ቀዳሚ ሪፖርት)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)በ2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የታዩ ክፍተቶች በተገቢው የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያ ሊታረሙ ይገባል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የክትትል ቡድን በማሰማራት ያጠናቀረውን የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ፤ ክትትሉ በተከናወነባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችና አካባቢዎች የተመለከታቸው ክፍተቶች ተገቢው ትኩረት እንዲያገኙና አስፈላጊውን የሕግና የአተገባበር መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገለጸ።
ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምርጫ 2013 ዓ.ም. ባለ6 ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ በማድረግና ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት እንዲሰጥ ከመወትወት በተጨማሪ፥ በቅድመ ምርጫውና በምርጫው ቀን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን በተመለከተና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ እንዲሁም ምርጫው የአካል ጉዳተኞችን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ያሳተፈና ለእነሱ ተደራሽ የሆነ በማድረግ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም መሠረት 94 ባለሞያዎችን ያካተተው ቡድን በአጠቃላይ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ ከተሞችና በሁሉም ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች በሚገኙ 99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ፥ የአካባቢውን አስተዳደር፣ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን፣ እጩዎችንና አባላት እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ አካላትና ሌሎች ባለድርሻዎችን አነጋግሯል። በዋና ጽሕፈት ቤቱ በተመደቡ ባለሞያዎች አማካኝነት በ7037 የስልክ ቁጥሩ ጥቆማዎችንና አቤቱታዎችን ተቀብሎ አስተናግዷል።
ምርጫው የተካሄደበት አውድ በሀገር ውስጥ የተደራረቡ ችግሮች የገጠሙበት እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ባሉበት፥ በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምርጫው እንዲተላለፍ አስገዳጅ በሆነበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ምክንያት በእስር በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የማይዘነጋ መሆኑንና ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ኮሚሽኑ ገልጿል። ይህ ተግዳሮት እንዳለ ሆኖ፤ ኢሰመኮ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው ዕለት ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት የታየ ቢሆንም፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየ ገልጾ፤ ክትትል ባደረገባቸው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የምርጫው ዕለት ሂደት ያለ የጎላ ችግር በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀና በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር አሳውቋል። በተጨማሪም በምርጫው ሂደት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለተሳተፉና አስተዋጽኦ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ እውቅና ሰጥቶ፤ በቀሪው ሂደትም በሕጋዊና ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲቀጥሉ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።
እነዚህን አዎንታዊና አበረታች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፥ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ከምርጫው ዕለት ጥቂት ቀናት በፊት፣ በምርጫው ዕለትና ከምርጫው ቀን በኋላ የደረሰ የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት፣ ተገቢ ያልሆነ እስር፣ በመራጮች ላይ የደረሰ ማስፈራራት፣ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ ስለደረሰ መጉላላትና ማዋከብ፣ የምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኛ ሰዎች ያለው ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተሳትፎ መጠን በሚመለከት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አስረድቶ፤ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።
በተጨማሪም ጥፋተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ እና ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠውን በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያግዱ፣ የሚገድቡ ወይም የሚያሰናክሉ ሁኔታዎች በተለይም የምርጫ ጣቢዎችን ያለ እንቅፋት የመጎብኘት አስፈላጊነት እና የእስር ቦታዎችን ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የመጎብኘት አስፈላጊነት በሚመለከት ለወደፊቱ ማናቸውም ዓይነት እንቅፋት እንዳይከሰት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱና ሁሉም ሰዎችና ተቋማት ለኮሚሽኑ ሥራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቧል።
ኢሰመኮ ያወጣውን ሪፖርት እዚህ ጋር በመጫን ያግኙ።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
July 3, 2021 at 11:06 pm #19816AnonymousInactiveትግራይ ክልል – የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል
አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 21 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መሰመሮች በመቋረጣቸው፣ በክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውና መንግሥት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ ገለጸ። በክልሉ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስና በትግራይ ክልል ስላለው ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት፣ በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።
ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ሆኖ፣ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የትግራይ አከባቢዎች የመብራት፣ የስልክ እና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ ይገኛል። የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን አባብሶታል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብዓዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ ይገኛል። ይህም በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር ነው።
በተጨማሪም፥ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፥ “በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው። የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። በተጨማሪም ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.