Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
Tagged: መቱ ዩኒቨርሲቲ, ሠመራ ዩኒቨርሲቲ, ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ, ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ, አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ, አሶሳ ዩኒቨርሲቲ, አክሱም ዩኒቨርሲቲ, አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ, አድማስ ዩኒቨርሲቲ, ወለጋ ዩኒቨርሲቲ, ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ, የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ, የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ, ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ, ዲላ ዩኒቨርሲቲ, ጅማ ዩኒቨርሲቲ, ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ
- This topic has 42 replies, 3 voices, and was last updated 1 year, 10 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
June 30, 2019 at 12:48 am #11233SemonegnaKeymaster
ሰሞነኛ የተማሪዎች ምርቃት — በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች (የግል/ የመንግስት) የተማሪዎች ምርቃት።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ። በተመሳሳይ የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎችን አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው በአምስት ኮሌጆች ውስጥ ያስተማራቸውን ተማሪዎች 1 ሺህ 112 በመጀመሪያ ዲግሪ እና 201 በሁለተኛ ዲግሪ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ብርሃኑ የተማሪዎች ምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነት ማገልገል አለባቸው።
”ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እና በኢንጅነሪንግ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚያስተምር በመሆኑ ተማሪዎችም በዚሁ መስክ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን መሥራት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን እንደሚያካሂድና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ተመራቂዎች በበኩላቸው ባገኙት ዕውቀት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሪፖርተር እንደተናገሩት፥ ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመጥቀም ይሠራሉ። ወደ መንግስትም ሆነ ግል ተቋማት በመሄድ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ያገኙትን ትምህርት በተግባር ማስደገፋቸውን ገልጸው በኮንስትራክሽ ዘርፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ የተመረቁ ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት ለማህበረሰቡ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመታት ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 578 ዕጩ መምህራንን በተመሳሳይ ዕለት በዲፕሎማ አስመርቋል።
ከዕውቀት ባለፈ በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሠሩ የኮሌጅ ተመራቂ እጩ መምህራን ተናግረዋል።
ከተመራቂ መምህራን መካከል በሒሳብ ትምህርት ክፍል የተመረቀችው መምህርት ስንቂት ማሙየ እንዳለችው፥ በቀጣይ ዕውቀቷን ለተማሪዎች ከማካፈል በተጨማሪ ሀገራቸውን የሚወዱና በሥነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በኃላፊነት እንደምተሠራ ተናግራለች።
“ሀገራችን ከመምህራን ብዙ ትጠብቃለች፤ እኛ መምህራንም ትውልድን በዕውቀት አንፀን በመቅረፅ ለሀገራቸው እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ አለብን” ብላለች።
በማኅበራዊ ሳይንስ ዕጩ መምህርና በኮሌጁ 3 ነጥብ 8 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው መንግስቱ ማሬ በበኩሉ ቀጣዩ ትውልድ በዕውቀት የዳበረና ማኅበረሰቡን አገልጋይ እንዲሆን በተመደበበት የሥራ ቦታ ተማሪዎቹን እንደሚያበቃ ተናግሯል።
“መመረቅ የመጨረሻ ሳይሆን ለአስተማረችኝ ሀገሬና ወገኔ አገልግሎት መስጠት የምጀመርበት ነው” ያለው ተመራቂው ሲሆን፥ በቀጣይም ዕውቀቱን በማዳበር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን አስረድቷል።
“የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ዕውቀትንና ማኅበራዊ ግብረ-ገብነትን ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ በቀጣይ የሥራ ዘመኔ የምከተለው መርህ ነው” ያለችው ደግሞ በሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ዘርፍ የተመረቀችው መምህርት መሰረት የኔሁን ናት።
የኮሌጁ ዲን አቶ ስንታየሁ ነጋሽ በበኩላቸው ኮሌጁ ከተቋቋመ 38 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው በእነዚህ ዓመታት ከ44 ሺህ በላይ መምህራንን ማስመረቁን ተናግረዋል። በዕለቱ ከተመረቁ 1ሺህ 578 እጩ መምህራን መካከልም 798ቹ ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ ዲኑ ገለጻ፥ ተመራቂዎቹ በትምህርት ቆይታቸው በቂ ዕውቀት ይዘው መውጣት የሚያስችላቸውን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት አግኝተዋል። ምሩቃን በቀጣይ ሙያውን አክብረው በመሥራትና ራሳቸውን ወቅቱ በሚፈልገው ልክ አቅማቸውን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 30, 2019 at 1:10 am #11237AnonymousInactiveከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተመረቁ
—–የአሶሳ ዩንቨርሲቲ በመደበኛና በማታ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሲያሰምር የነበረውን ተማሪዎች ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመረቀ። በኅዳር 2011 ዓ፣ም በተፈጠረው ግጭትና አለመግባባት የመማር ማስተማር ሂደት ተስተጓጎሎ እንደነበር እና ለሦስት ተማርዎች ሕይወት ህልፈት ምክንት መሆኑም ይታወሳል።
ምንጭ፦ DW Amharic
June 30, 2019 at 1:16 am #11238AnonymousInactiveአክሱም ዩኒቨርሲቲ ኤርትራዊያን ተማሪዎችን አስመረቀ
—–አክሱም ዩኒቨርሲቲ ኤርትራዊያን ተማሪዎችን አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው 14 ኤርትራዊያን በመጀመሪ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ናቸው። አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሰጡ ኤርትራዊያን ተመራቂዎች እንዳሉት በቀጣይ የሁለቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ።
በፓለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት የተመረቀው ዮናስ አሸብር እንዳለው የሁለቱ ሀገራት የሕዝብ ለሕህዝብ ግንኙነት ብዙ ዓመታት ያስቆጠረ ነው።
ሀገራቱ በመካከላቸው ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ከ20 ዓመታት መለያየት በኋላ ዳግም ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን አስታውሶ፥ “በቀጣይ የሀገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ድልድይ ሆነን እንሠራለን” ብለዋል።
ከዩኒቨርሲቲው በቢዝነስ ማኔጅመንት የተመረቀው ዮሐንስ ጉዕሽ በበኩሉ፥ በኢትዮጰያ መንግስት የትምህርት ዕድል በማግኘቱ ደስታ እንደተሰማው ገልጾ “የጋራ ባህልና እሴት ያላቸው የኢትዮጰያና የኤርትራን ህዝቦችን ማለያየት አይቻልም” ብሏል።
በቀጣይም የሁሉቱ ሀገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ለማሰቀጠል የበኩልን እንደሚወጣ ተናግሯል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
June 30, 2019 at 8:51 pm #11239SemonegnaKeymasterየተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመርቀዋል
—–አዲስ አበባ – የተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎቻቸውን ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቀዋል።
በዕለቱ ተማሪዎቻቸውን ካስመረቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ መቱ ዩኒቨርሲቲ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። ከተመረቁት ውስጥም 1 ሺህ 112 በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር (በመጀመሪያ ዲግሪ) ያስመረቀ ሲሆን፥ 201 ተማሪዎችን ደግሞ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ነው ያስመረቀው።
ጅማ ዩኒቨርሲቲም በዕለቱ በመጀመሪያ ዙር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 683 ተማሪዎቹን አስመርቋል። ከእነዚህም ውስጥ 341 በድህረ ምረቃ ሲሆን፥ 1 ሺህ 11 ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።
በተመሳሳይ ዲላ ዩኒቨርሲቲም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4 ሺህ 726 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ በዓል ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ በዘንድሮው ዓመት በመላው ሀገሪቱ ከ175 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚመረቁ አንስተዋል። ተመራቂ ተማሪዎች ለሀገራቸው የሚሰሩ ሊሆኑ እንደሚገባም ፕሮፌሰር አፈወርቅ መልእክት አስተላልፈዋል። ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዕለቱ ካስመረቃቸው ተማሪዎቹ ውስጥ 500 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ ነው ያስመረቃቸው።
ወለጋ ዩኒቨርሲቲም በዕለቱ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 682 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ 2 ሺህ 139 ሴቶች ሲሆኑ 1 ሺህ 543 ደግሞ ወንዶች መሆናቸው ተገልጿል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው 295 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ ያስመረቀ2 ሲሆን፥ 8 ተማሪዎችን ደግሞ በ3ኛ ዲግሪ ወይም በዶክትሬት ዲግሪ አስመርቋል።
መቱ ዩኒቨርሲቲም በተለያየ የትምህርት መሰኮች ሲያሰለጥናቸው የነበረውን ከ2 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎቸ በዛሬው ዕለት አስመርቋል። በምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት ግብርና ሚኒስተር ዲኤታና የመቱ ዩኒቨርሰቲ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳኒ ሬዲ መንግስት ለሰው ሀብት ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥው እየሠራ ባለበት መመረቃቸውንና ከተመራቂ ተማሪዎች የሚጠበቀው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ተካልኝ ቃጄላ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ብዙ ፈታኝ የሆኑ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶችን አልፎ ለዚህ መብቃቱን አስታውሰዋል።
በተመሳሳይ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ 714 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሓ ግብሮች አስመርቋል። ከነዚህ ውስጥ 930 ሴት ተመራቂዎች መሆናቸው ታውቋል። ዩኒቨርሲቲው አሁን ለ6ኛ ጊዜ እያስመረቀ ሲሆን ከተመሰረተበት ከ2004 ዓም ጀምሮ አጠቃላይ 12 ሺ 450 ተማሪዎችን አስመርቋል። በዕለቱ በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል። ፕሮፌሰር ሂሩት ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ እንድትወጣ የተማረው ሀይል ዋነኛ አካል ነው ብለዋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ
July 1, 2019 at 12:45 am #11240AnonymousInactiveዲላ ዩኒቨርሲቲ እና መቱ የኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከሰባት ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
—–ዲላ/ መቱ – ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 4 ሺህ 726 ተማሪዎችን አስመረቀ። መቱ የኒቨርሲቲም በበኩሉ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያስተማራቸውን 2 ሺህ 323 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ዩኒቨርሲቲው በተያዘው ዓመት 4 ሺህ 216 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ ቀሪዎቹን በሁለተኛ ዲግሪ ለምረቃ ማብቃቱን ተናግረዋል። ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ 1 ሺህ 561 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ከ50 በላይ አነስተኛና 12 መካከለኛ ምርምሮች መካሄዳቸውን አስረድተዋል፤ የጥናት ውጤቶችንም ለማህበረሰቡ ጥቅም ለማዋል ጥረት መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። በአከባቢው የሚገኘውን የይርጋጨፌ ተፈጥሯዊ ቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የምርምር ማዕከል ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የቡና ሳይንስና ምጣኔ ሃብት መርሐ ግብር ለመክፈት የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻን ጨምሮ ሌሎች ዝግጀት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ “የዛሬ ስኬታችሁ የመጨረሻ ግባችሁ አይደለም” በማለት ምሩቃን ራሳችሁን ለተሻለ ስኬት እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕዝቡን አኗኗር ለመለወጥ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የትምህርት ጥራትን ጨምሮ በመስኩ የሚስተዋሉ ድርብርብ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
ከተመራቂዎች መካከል ከጤና መኮንን ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ጸዮን ሙላት ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ መሆኗን አስረድታለች። “የጤና ሙያ ህብረተሰቡን በጥንቃቄ ማገልገልን የሚጠይቅ ነው” ያለችው ተመራቂዋ፣ በምትሰማራበት የሙያ መስክ ሕዝብና መንግስት በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።
በተመሳሳይ መቱ ዩኒቨርስቲ በመቱና በደሌ ካምፓሶች በተለያዩ የሙያ መስኮች ያስተማራቸውን 2 ሺህ 323 ተማሪዎች ትናንትና ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በመጀመርያ ዲግሪ አስመርቋል። ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 988 የሚሆኑት ሴት ምሩቃን መሆናቸው ታውቋል።
የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታና የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳኒ ረዲ በተጀመረው አገራዊ የለውጥና የእድገት ጉዞ ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት በሚሰማሩበት የሙያ መስክ ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በነርሲንግ ትምህርት የተመረቀው አንዋር ታጁዲን እንዳለው በተቀጣሪነትም ይሁን በግል ሥራ ፈጠራ ቀስሞ የወጣውን ዕውቀት ወደ ተግባራ ለመቀየር ተዘጋጅቷል።
በማኔጅመንት እንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት መስክ የተመረቀው ቴዎድሮስ ፍስሃ፥ ለግል ሥራ ፈጠራ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስረድቷል።
በሕግ ትምህርት የተመረቀች ፈትያ አብዱልመጂድ በበኩሏ፥ በተማረችበት የሙያ መስክ ኅብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።
ከተመራቂዎቹ ውስጥ 2 ሺህ 52 የሚሆኑት በመቱ ዋናው ግቢ የተቀሩትን ደግሞ በበደሌ ግብርናና ደን ሳይንስ ኮሌጅ በተፈጥሮና ኮምፒዩቲሽናል ሳይንስ፣በጤና፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስና በምህንድስና መስኮች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።
ምንጭ፦ ኢዜአ
July 3, 2019 at 11:29 pm #11282AnonymousInactiveክብርት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት በዓል ላይ ያስተላለፉት መልዕክት
—–ክብርት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምርቃት በዓል ላይ በመገኘት ለ2011 ዓ.ም. ምሩቃን (Class of 2019) “የዓመታት ልፋታችሁ ውጤት ለሚታዩበት ዕለት እንኳን በቃችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምሩቃኑ ሚዛናዊና ምክንያታዊ በሆነ አስተሳሰብ በመመራት አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ፈታኝ ሁኔታ ለመታደግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ፕሮፌሰር ሂሩት ጥሪ አቅርበዋል።
መማር ማለት እውቀት መሰብሰብ ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፥ የተማረ ሰው በእያንዳንዱ በሚያጋጥመው ነገር ላይ ጠለቅ ያለ ዕይታ ያለውና ለሁሉም ነገር በቂ ምርምር በማድረግ ሚዛናዊና ምክንታዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ለአገርና ለወገናቸው እንዲሰሩበትም አስገንዝበዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃይማኖት ዲሳሳ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ከ3ኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች (3rd Generation Universities) አንዱ ሲሆን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ 2,711 ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማስመረቁን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግሮች ተቋቁሞ የመማር ማስተማር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በአግባቡ በመፈፀም ለዚህ እለት እንዲበቃ ትብብርና ድጋፍ ላደረጉት የአካባቢው ህብረተሰብ፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ የጸጥታ ኃይሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ተመራቂ ተማሪዎችም በቀሰሙት ዕውቀት እና ክህሎት ህብረተሰባቸውን ከማገልገል ባሻገር ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 7, 2019 at 3:43 am #11321AnonymousInactiveጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስመረቀ
—–ጂጂጋ (ሰሞነኛ) – ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸው 2 ሺህ 107 ተማሪዎች አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 101 በሁለተኛ የዲግሪ መረሀ ግብር የተማሩ ናቸው።
በምረቃ ሥነ ስርዓት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አመራር አባል ዶክተር አብዲቃድር ኢማን ባስተላለፉት መልዕክት “ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው በንድፍ ሀሳብና በተግባር የቀሰሙትን ዕውቀት ለህብረተሰብ ለውጥ እና እድገት ማዋል ይጠብቅባቸዋል” ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ኢልያስ ኡመር በበኩላቸው ተቋሙ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ች በ ምህንድስና፣ በጤና ሳይንስ፣ በግብርና፣ በሕክምና እና በሌሎችም የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ዩኒቨርስቲው ከመደበኛው ሥራው ሳይወሰን በክልሉ ሰባት ከተሞች ማዕከላትን ከፍቶ ለማ ኅበረሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና አስተዳደር ተመራቂ ወጣት አብዲ መሀመድ በሰጠው አስተያየት፥ ከዩኒቨርስቲው በቀሰመው ዕውቀት ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሥራ ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል።
ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምራቸው ከ24ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነስርዓት ወቅት ተገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
July 7, 2019 at 4:16 am #11322AnonymousInactiveድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ 2ሺህ 880 ተማሪዎችን አስመረቀ
—–ድሬ ዳዋ (ሰሞነኛ) – ድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 880 ተማሪዎች አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው በምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ በጥበብና በሰብዓዊ ተግባራት አርአያ ናቸው ላላቸው ሁለት ሰዎችም የክብር ዶክተሬት ሰጥቷል።
ዩኒቨርሲቲው ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ አስተምሮ ካስመረቃቸው መካከል 63ቱ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮ አረጋዊያንን በመደገፍና በመጦር ተግባር ለተሰማሩት ለወ/ሮ አሰገደች አስፋውና ለታዋቂው ለክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ መሐመድ ቢራ (አሊ ቢራ) የክብር ዶክተሬት ሰጥቷል።
በምረቃው ላይ በከፍተኛ ማዕረግ ለተመረቁ ተማሪዎች የተዘጋጁትን የወርቅ መዳሊያና የዋንጫ ሽልማቶች የሰጡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው።
አቶ ፍቃዱ በምረቃው ላይ እንዳሉት ሀገሪቱን ወደ ቀድሞ የስልጣኔና የዕድገት ማማ ለማድረስ ቁልፍ ሚና ላለው የትምህርት መስክ መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
በቀጣይም የትምህርትና የስልጠና ዘርፍ ጥራትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት መደረጉን ነው የተናገሩት።
ተመራቂዎቹ በቀሰሙት ዕውቀት ስራን ሳይንቁና ሳይጠብቁ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን ለመለወጥ በቁርጠኝነት ሌት ተቀን እንዲሰሩም አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው፥ ተማሪዎች ብዝሃነትን በማክበር በቀሰሙት ዕውቀት ለሀገር ዕድገት፣ ለሰላምና አንድነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በ1999 ዓ.ም. የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ፥ በአሁን ወቅት በ6 ኮሌጆች፤ በ41 የትምህርት መስክ ከ13 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
July 8, 2019 at 12:11 am #11331AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 6 ሺህ 824 ተማሪዎችን አስመረቀ
—–አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ42 የትምህርት ዘርፎች በመደበኛና በተከታታይ መርሃ ግብር ያስተማራቸውን 6 ሺህ 824 ተማሪዎችን ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል።
በመጀመሪያ፣ በማስተርስና በዶክትሬት ዲግሪ ከተመረቁት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 180 የሚሆኑት ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሌላንድ፣ ሶማሊያና የመጡ ናቸው። እነዚህ የውጭ ዜጎች በዩኒቨርስቲው የተማሩት የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው ነጻ የትምህርት እድል አማካኝነት ነው።
በምረቃው ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ዩኒቨርሲቲው ትኩረቱን በሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ላይ በማድረግ ዘንድሮ 29 ተማሪዎችን በዶክትሬት ዲግሪ ማስመረቁን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የአንድ ፓርቲ አገልጋይ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ለመቀየር በርካታ የገጽታ ግንባታ ታገባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰው፥ ዩኒቨርሲቲው ለሁሉም ዜጎች ክፍት የሆነ የምሁራን መፍለቂያ አምባና የእውቀት ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተቋቁሞ ሥራ ላይ በቆየባቸው ባለፉት 25 ዓመታት ከዲፕሎማ አንስቶ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃዎች ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።
በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን በድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ያደረገው የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፥ የቅበላ አቅሙን በማሳደግ በስድስት የትምህርት ዘርፎች በዶክትሬት ደረጃ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል።
ዘንድሮ ከተመረቁት መካከል በ25 የእውቀት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ እና በቅድመ ምረቃ ደግሞ በ11 ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ይገኙበታል።
በምረቃው ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረኢየሱስ እንዳሉት፥ መንግስት የጀመረውን አካባቢን የመንከባከብ ተግባር በጋራ እውን በማድረግ ኢትዮጵያን ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ምቹ የመኖሪያ ስፍራ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ተማራቂ ተማሪዎችም አገራቸውን ወደፊት ለማራመድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
መንግስት በተለይ በመጪው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የያዘውን እቅድ ለማሳካት ተመራቂዎች የአካባቢያቸውንና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ በማስተባበር ችግኝ እንዲተክሉ ጥሪ አቅርበዋል። የሚተከሉት ችግኞችም የምርቃታችሁ ማስታወሻ ይሆናሉ ሲሉም አክለዋል።
በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን የፈጸመው ተስፋዬ አባተ በተመረቀበት ሙያ አገሩን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሮ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረበውን የችግኝ ተከላ ጥሪ በመቀበል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል። “ከዚህም ባለፈ በክረምት በበጎ ምግባር አገልግሎት ላይ በመሰማራት የሚጠበቅብኝን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ” ብሏል።
July 8, 2019 at 12:27 am #11332AnonymousInactiveሰብዓዊነትን በመላበስ ሀገራቸው እንደሚያገለግሉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ
—–ሀዋሳ – ከተማሩት ሙያ በተጨማሪ ሰብአዊነትን በመላበስ ሀገራቸው እንደሚያገለግሉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ።
ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚመረቁት የኮሌጁ ተማሪዎች አነቃቂ ንግግሮችን ከሚያደርጉ ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ቆይታ በማድረግ ልምድ ተለዋውጠዋል።
ለዚሁ በተዘጋጀው መድረክ ከተሳተፉት መካከል በኮሌጁ ጤና መኮንን ተመራቂና የምረቃ ኮሚቴ አስተባባሪ እንግዳሸት ዜና እንዳለው፥ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርቱ ባሻገር ተጨማሪ ክህሎቶችን ለመገብየት የሚያስችሉ ናቸው። በተለያዩ ዘርፎች ሃገራቸውን የሚያገልግሉና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመጋበዝ ልምዳቸውን ለመካፈል መድረኩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጿል። ከተማረው ሙያ በተጨማሪ ሰብአዊነትን በመላበስ ሀገሩን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
“ዩኒቨርሲቲዎች የልህቀት ማዕከላት እንጂ ድንጋይ የሚወረወርባቸው አይደሉም፤ ከሁሉም በላይ ሃገርን ማስቀደም ይገባል” ብሏል። ወጣቱ በሰከነ መንፈስ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባና ከተጋባዥ እንግዶች ያገኘውን ልምድ በተግባር እንዲያረጋግጥም መልዕክቱን አስተላልፏል።
July 8, 2019 at 12:29 am #11333AnonymousInactiveየኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከ 3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ
—–አዲስ አበባ – ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያስተማራቸውን 3 ሺህ 282 ተማሪዎች ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመረቀ።
በአዲስ አበባ ኮከብ አዳራሽ በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር እንዳወቅ አብጤን ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት ተገኝተዋል።
ትምህርታቸውን አጠናቀው ዛሬ ለምረቃ የበቁት በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን በዲፕሎማና በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል።
ታሪክና ቅርስ አስተዳደር፣ ቋንቋና ሥነ-ጹሁፍ፣ ሥነ-ዜጋ፣ የቢዝነዝ አስተዳደር፣ የሕብረተሰብ ሳይንስ፣ ስፖርት ሳይንስ፣ ከተማ መሬት አስተዳደር፣ ጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥናት ከስልጠና መርሃ ግብሮቹ መካከል ናቸው።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው፤ ዩኒቨርሲቲው በአዲስ መልክ ሜትሮፖሊታን ሆኖ ከተቋቋመ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ሲያስመርቅ በአጠቃላይ ለ60 ጊዜ ተማሪዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል።
July 11, 2019 at 2:37 am #11354AnonymousInactiveአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ32ኛ ጊዜ 6,857 ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል
—–አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ ምረቃና በድኅረ ምረቃ ያሰለጠናቸውን 6,857 ተማሪዎች ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. አባያ ካምፓስ በሚገኘው አዳራሽ እና ሰኔ 30 ቀን2011 ዓ.ም. በሣውላ ካምፓስ በድምቀት አስመርቋል። ከተመራቂዎች መካከል 4,434 ወንዶች ሲሆኑ 2,423 ሴቶች ናቸው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ተመራቂዎች የሥራ ዓለምን ሲቀላቀሉ ከዩኒቨርሲቲው በገበዩት እውቀት፣ ክህሎትና መልካም ሥነ-ምግባር መንግሥትና ህዝብ የአገሪቱን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እያደረገ ባለው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንዲሁም ራሳቸውን፣ ወገናቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች በተለያየ መልኩ ወደ ሥራው ዓለም ሲቀላቀሉ በአገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በአሁኑ ጊዜ በአገራችን መልካም ተስፋ እየታየ ቢሆንም ተስፋውን የሚያደበዝዙ ችግሮች ይስተዋላሉ ያሉት ዶ/ር ይናገር፥ ችግሮች እንዳይከሰቱና ከተከሰቱም በሰከነ ሁኔታ እንዲፈቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚሠራጩ ሀሰተኛ ወሬዎች ቦታ ሳይሰጡ ለአገራችን አንድነትና አብሮነት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የዕለቱ እንግዳና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል ዶ/ር አብርሃም አላኖ በበኩላቸው የአንድ አገር ልማት ያለ ትምህርት መስፋፋት እውን ሊሆን እንደማይችል መንግሥት ተረድቶ ለከፍተኛ ትምህርት ፍትሃዊ መስፋፋትና ተደራሽነት በትኩረት ሲሠራ የቆየ በመሆኑ በዘርፉ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል። መንግሥትና የዘርፉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር አብርሃም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በአገሪቱ ከሚገኙ የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በሁሉም መስኮች ቀዳሚ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
አገራችን ኢትዮጵያ በዕድገት ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን ያወሱት የክብር እንግዳው ከለውጡ ጋር ተያይዞ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ ከፍተኛ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች የተጋረጡ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የዕለቱ ተመራቂዎች ምክንያታዊ በመሆንና ከግለኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ለማኅበረሳባችን ለውጥ ብሎም አገሪቱ ከገጠማት ፈተና እንድትወጣና የተጀመረው ለውጥ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 4 ነጥብ በማምጣት የሜዳልያና ዋንጫ ተሸላሚ የሆነው የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተመራቂ እስማኤል ፈድሉ በሰጠው አስተያየት ጠንክሮ መሥራቱና ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ ለስኬት እንዳበቃው ገልጿል። ማንኛውም ሰው በተሰማራበት መስክ ዓላማ በመሰነቅ በቁርጠኝነት ከሠራ ውጤታማ መሆን ይችላል ያለው ተሸላሚው አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ ጅምር በመሆኑ የትምህርት ደረጃውን በማሻሻል አገሩን በታማኝነትና በቅንንት እንደሚያገለግል ተናግሯል።
በአጠቃላይ ውጤት 3.98 በማምጣትና 43 A+ በማስመዝገብ በ2ኛነት የተሸለመው የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል ተመራቂ ቃለአብ ወንድሙ ታሪኩ በዓላማ መንቀሳቀስና ተግቶ መሥራት ለስኬት ያበቃል ብሏል። ሰሚራ ዲልቦ አወል ከኮኦፕሬቲቭ አካውንቲንግ እና ኦዲቲንግ ትምህርት ክፍል 3.94 ከሴቶች ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት እንዲሁም ተመራቂ ዘሀራ ያሲን አማን ከኮምፒውተር ሣይንስ ትምህርት ክፍል 3.92 በማምጣትና 16A+ በማስመዝገብ ልዩ የወርቅ ሀብል ተሸላሚዎች ሆነዋል።
በዕለቱ ከየትምህርት ክፍላቸው 1ኛ ለወጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሽልማት፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ምሩቃን የወርቅ ሜዳልያ፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ሴት ምሩቃን ልዩ ሽልማት፣ በአጠቃላይ ሴት ምሩቃን መካከል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበች ምሩቅ የአንገት ሐብል ሽልማት እንዲሁም ከአጠቃለይ ምሩቃን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበው ምሩቅ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።
ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
July 12, 2019 at 1:23 am #11362AnonymousInactiveሠመራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ስያስተምር የቆየውን 1,800 ተማሪዎችን አስመረቀ
—–ሠመራ (ሰሞነኛ) – ሠመራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ስያስተምር የቆየውን 1800 ተማሪዎችን የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት አስመርቋል። ክብርት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም በተመሪዎች የምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ በመገኘት ለተመራቂዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ክብርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ለተመራቂዎቹ፣ “በሰው ዘር መገኛ አፋር ሆነን በብሔር ላይ የተመሠረተ ግጭት አያምርብንም ብላችሁ የህይወት ግባችሁ ላይ በማተኮር በወንድማማችነት እና እትማማችነት ሰላማችሁን አስጠብቃችሁ ዓመቱን በማጠናቀቃችሁ አመሰግናችኋለሁ” ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ወቅት በቀጣይ ትውልድ የምንመኘው አንድነቷ በማይናወጥ መሠረት ላይ የተጣለ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገቷ የበለፀገች ሀገር እና ዜጐችዋ የተደላደለ ሕይወት የሚመሩባትን ኢትዮጵያን ነው፤ ይህን የምናሳካው የዛሬው ትውልድ በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በመልካም አስተሳሰብና ሥነ-ምግባር በሀገርና በሕዝብ ፍቅር ታንፆ ሲወጣ ብቻ ነው፤ ለዚህ ደግሞ እናንተ የዛሬ ተመራቂዎች ከፍተኛ አደራ ተጥሎባችኋል ብለዋል ሚኒስትር ሒሩት።
ከተማሪዎች ምርቃት በኋላም በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተካሂዷል።
July 13, 2019 at 5:12 am #11379AnonymousInactiveተመራቂዎች ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግና እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሳሰቡ
—–አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ተመራቂዎች ከፊታቸው ውጣ ውረድ ያለበት ሕይወት ስለሚጠብቃቸው በትጋት ለመወጣት ጥረታቸው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምረቃ እና በድህረ ምረቃ በቀን፣ በማታ፣ በርቀት እና በክረምት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 9,637 ተማሪዎችን ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግስት ባስልጣናት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሙሁራን በተገኙበት በከፍተኛ ድምቀት በሚሊኒየም አዳራሽ አስመርቋል።
ከተመረቁት 9,637 ተማሪዎች ውስጥ በቅድመ ምረቃ 5,876፣ በድህረ ምረቃ 3,761 ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 2,763 ሴቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ምንም እንኳን በቀጣይ የሚጠብቃቸውና መውደቅና መመረቅ ያሉባቸው ሰፊ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም የዛሬውን መመረቅ ልዩ የሚያደርገው የዛሬ ተመራቂዎች ለቀጣይ ሕይወታቸው ስንቅ ይዘው በብዛትና በአንድነት የሚመረቁበት ዕለት መሆኑ ነው። በቀጣይ የሚጠብቃቸውም የትዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የሥራና የሕይወት ዩኒቨርሲቲ ከባድ ፈተና በታላቅ ስብዕና ለማለፍ እንዲሁም በሕይወት የሚገጥማቸውን ችግሮች በጽናት ለመወጣት ጥረትና ትጋት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
”የሕይወት ፈተናን ተጋፍጣችሁ ሌላውን ሕይወት በብቃት ለመወጣት ማንበብና እራስን ማብቃት ወሳኝ ነውም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።
በተለይ በዩንቨርሲቲ ሕይወት ያገኙትንና ያዳበሩትን አብሮ የመኖር ባህል ለትውልድ በማስተላለፍ የተሻለች ኢትዮጰያን ለመመስረት ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በተለይም ለሰው ልጅ ለመማር ወይም ለመላቅ ብዙ ገፊ ምክንያቶች እንዳሉት ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ሕይወትን በትርጉም ለመምራት የሚያስችሉና ማፍቀር፣ መስጠት እንዲሁም ማገልገል ትልቁ መርህ አድርጋችሁ አገራችሁን አገልግሉ ብለዋል።
በመስጠትና በማገልገል መርህም በዘንድሮው ክረምት ብቻ በአዲስ አበባ ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች፣ ከ10 በላይ ሆስፒታሎች እና ከ1000 በላይ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች የማደስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩት ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች የደብተርና ዩኒፎርም ስጦታ መዘጋጀቱንም አውስቷል።
አገሪቷ በችግኝ ተከላ ዘመቻ ላይ መሆኗን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ለመሆን የምንችለው አረንጓዴ ኢትዮጵያን መፍጠር ከቻልን ነው፤ ስንሞት ኢትዮጵያም መሆን የምንችለው ቢያንስ በለምለምና በጥላ ስር ዘላለማዊ እረፍት ማድረግ ስንችል ነው” በማለት ተማሪዎቹ ጠንክረው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ሳይማር ያስተማረውን ህብረተሰብ በማገልገል፣ አርሶ አደሩን ከሞፈርና ከቀንበር የማላቀቅ፣ የጽናትንና የማገልገል ልምድ ዛሬ መጀመር ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። ዜጎች ሳይቸገሩ በሁሉም ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዲኖሩና ለኢትዮጵያ ጽናትና ብልጽግና እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ትምህርት መነሻ እንጂ መድረሻ አይደለም የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እውቀታቸውን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል። ተመራቂዎች አባቶች ያቆዩዋትን ኢትዮጵያ ጉዳይ ለክርክርና ለድርድር እንዳያቀርቡም አክለው አሳስበዋል።
በዘንድሮው የምረቃ በዓል ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የክብር ዶክትሬቶችን፥ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እና ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ካውንስል ኃላፊ እና የዑለማ ኃላፊ ሀጂ ሙፍቲ ሼክ ዑመር እድሪስ ሰጥቷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 13, 2019 at 11:41 pm #11387AnonymousInactiveዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ 3,144 ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ
—–ከ23,500 በላይ ተማሪዎችን በዋናው ግቢ፣ በዱራሜ፣ በንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ሆስፒታል እያስተማረ የሚገኘው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ 3,144 ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል።
“አሁን የታየውን የአገራችን የለውጥ ተስፋ ማስቀጠል የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። በመሆኑም በሁሉም ዘርፍ በእውቀትና ክህሎት የበቃ የሰው ሃይል ያስፈልጋታል” የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ በተማሪዎቹ የምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ።
ለዚህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መጀመሪያ ራሳቸውን እየለወጡ በአዳዲስ ሳይንሳዊ ውጤቶች መደራጀት፣ ጊዜውን በሚመጥን መልኩ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ተላብሰው መጓዝ አለባቸው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
*** የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ፕሬዝዳንት ከዩኒቨርሲቲው ኮሌጆችና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር ያዘጋጁት የምክክር መድረክ
የተማረ ሰው ለብዙም ሆነ ለትናንሽ ችግሮች ብዙ መፍትሄ ይፈልጋል፤ አገራችን አሁን ካጋጠሟት ችግሮች እንድትላቀቅ እናንተ የዛሬ ተመራቂዎች በሰበሰባችሁት እውቀትና ክህሎት የመፍትሄ አካል እንድትሆኑ አደራ አለባችሁ ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አየለ ሄገና ናቸው።
በሠላም ተምሳሌትነት የሚታወቀው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ 11,638 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ፥ ከእነዚህ ተመራቂዎች 60%ቱ በግልና በመንግስት ሥራዎች መሰማራታቸውን ዩኒቨርሲቲው በጥናት /tracer study/ እንዳረጋገጠ ጠቁሟል።
የመቀጠር እና የስራ ፈጣሪነት አቅም ለማሳደግ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሥራ ፈጠራ ማዕከል ተቋቁሞ እየተሠራ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ6 ኮሌጆች፣ በ2 ት/ቤቶች በ54 ቅድመ-ምረቃ እና በ7 ድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ትምህርት እየሰጠ ይገኛል።
ከአገር በቀል እውቀቶች ልማት አንጻር ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ሀድይሳ እና ከምባትኛ ቋንቋዎችን በዋና ግቢ እና በዱራሜ ካምፓሶች ማስተማር መጀመሩ ተገልጿል።ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.