-
AuthorSearch Results
-
August 30, 2020 at 12:33 am #15626
In reply to: ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
SemonegnaKeymasterባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 7520 ተማሪዎች በበይነ-መረብ አስመረቀ
(ባሕር ዳር) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምርቃ መርሀ-ግብር በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛውና በተከታታይ መርሀ-ግብር 2254 ተማሪዎች፣ በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ-ግብር 40 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲ መርሀ-ግብር 41 ተማሪዎች፣ በምስክር ወረቀት መርሀ-ግብር 642 ተማሪዎች በድምሩ 7520 ተማሪዎችን በበይነ-መረብ በመታገዝ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። ከተመራቂ ተማሪዎቸ መካከል 2345 ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል አምስቱ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ፣ እንዲሁም የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክዕት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ዓለምን ባስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ ተግዳሮት ሳይደናቀፉ የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ለተመረቁ ተማሪዎች አድናቆታቸውን ገልፀው ወደ ቀደምት ትልቅነታችን እና ጥበብ ለመመለስ እና አሁን የጀመርናቸውን የአባይ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት የጋራ መድኃኒት ስለሚያስፈልገን ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም በጋራ መሥራት እንደሚገባን አሳስበዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን (ኮቪድ-19) ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዩኒቨርስቲዎች ሕይወትን ለመታደግ የእውቀት እና የሕዝብ ተቋምነታቸውን ማስመስከራቸውን ጠቅሰው ለዚህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በማምረት እና በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን በማበርከት ሕበረተሰቡን ከወረርሽኙ እየታደገ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ገልፀዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከትምህርት እንዳይለዩ በዩኒቨርሲቲው የICT ባለሙያዎች የበለፀገ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት (learning management system) ለአማራ ክልለዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ማበርከቱን አውስተዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንዳሉት መማር ትርጉም የሚኖረው የሕበረሰተቡን ኑሮ ማሻሻልና ለችግሮቹ መፍቻ የሚሆን አዳዲስ አሠራሮችንና ሀሳቦችን መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቁመው የሀገራችን ችግር የሚፈታው የችግሮችን ስፋትና ጥልቀት በሚረዱ ምሁራን በመሆኑ የምንግዜም ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አክለውም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የልሕቀት ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ትጋት አድንቀው፤ በእምቦጭ ዙሪያ ብዙ ሥራ መሥራት የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። ከአባይ ፏፏቴ ጀምሮ እስከ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ድረስ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግ የሚቻልበትን ምርምር በመሥራት መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማሳየትም ከዩኒቨርሲቲው እንደሚጠበቅ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል።
የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን ጥቂት ተማሪዎች አዳራሽ ውስጥ በአካል በመገኘት፥ አብዛኛዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው በአማራ ቴሌቪዥን ከጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቀጥታ ስርጭት፣ በፌስቡክ (Facebook) እና ዩቲዩብ (YouTube) የተላለፈውን ታድመዋል።
ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
August 25, 2020 at 2:40 pm #15567In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveለመጪው የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ከነሐሴ 20 ጀምሮ ምዝገባ እንደሚጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)፦ የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ምዝገባ ከነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚጀመር ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ትምህርት ቤቶች የቀጣይ ዓመት የትምህርት ምዝገባን ከነሐሴ 20 ጀምረው ማካሄድ ይችላሉ ብሏል።
የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀረጓ ማሞ፥ ትምህርት ቤቶች ምዝገባውን ሲያካሂዱ ኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ 19) ለመከላከል በዓለም የጤና ድርጅት እና በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር የተቀመጡ ቅድመ ዝግጅቶችንና መከላከያ መንገዶችን በሚገባ በመተግበር መሆን እንዳለበት አሳስቧል።
ትምህርት የሚጀመርበት ቀን በቀጣይ እንደሚወሰንና ይፋ እንደሚደረግም የገለፁት ዳይሬክተሯ፥ የቀጣዩ ዓመት የትምህርት ሂደት ስኬታማ እንዲሆንም ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆችና መላው የትምህርት ማኅበረሰብ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ የሚተላለፉትን ገዢና አስፈላጊ መልዕክቶች ብቻ በመከታተልና ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችልባቸውን መንገዶች ከውዲሁ በማስወገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
አካላዊ ርቀትን ጠብቆ ለማስተማር፣ የንፅህና መጠበቂያዎችን ከማዘጋጀትና መሰል የኮሮና ቫይረስን የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ቀድመው ዝግጅት የሚደረግባቸው ተግባራትም እንደሆኑ አክለው ገልጸዋል።
በምን ዓይነት መልኩ ትምህርት መጀመር እንዳለበት የተለያዩ አማራጮችን ለማመላከት ሰፊ ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን፥ ውሳኔዎች ላይ ሲደረሱ በቀጣይ ይፋ ይደረጋሉ።
የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጊዜን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርብ የሚያሳውቅ ሲሆን ተማሪዎች ራሳቸውን እያዘጋጁ እንዲቆዩ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
በመጪው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረገ ነው?
በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታወቋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት፥ የቀጣዩ ዓመት ትምህርት ምዝገባ ከነገ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች እንደሚጀመር እና ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቅደመ ዝግጅቶችንና ተግባራትን በተገቢው መንገድ በመተግበር ምዝገባ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
የበሽታው ሁኔታ እየተስፈፋ ቢሆንም የትምህርት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊ ሆኑ መገኘቱን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ወደ መማር ማስተማር ተግባር በሚገባበት ወቅት ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠራ ገልጸው፥ የፊት መሸፈኛ ጭንብል (face mask)፣ የእጅ ማፅጃ (sanitizer) እና መሰል አቅርቦቶችን ከባላድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይከሰት ተማሪዎች የፊት መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና እጅን በተደጋጋሚ በመታጠብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛ ሴሚስተር ያለፋቸውን ትምህርቶች ማካካሻ ለመስጠት መታሰቡንም ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬሽን (EBC) ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
August 24, 2020 at 2:29 am #15538In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveበኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፣
ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና ያመለጡን ዕድሎች በብሔራዊ መግባባት መነፅር ሲታይ
መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)
ለብሔራዊ መግባባት ውይይት የቀረበ ጥናት
ነሐሴ 2012አብዛኛዎቹ የሀገራችን የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በአስረኛው ምዕተ ዓመት የንግስት ሳባ እና የንጉሥ ሰለሞን ግንኙነት በሚባለው ጊዜ ይጀምራል ይላሉ። ይህ ለአንዳንዶቹ የሚታመን ታሪክ ተደርጎ የሚወሰደው፤ ለሌሎች ደግሞ ተረት እንደነበረ የሚነገረው ክስተት የማስመሰያ ትርክቱ የእስራኤል አምላክ የቀባቸው ገዥዎች ተብሎ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ንጉሦቹ ቅቡልነትን አግኝተውበታል። በትርክቱም ሀገሪቷን እስከ 1966 ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ያለ ብዙ ጭንቀት ገዝተውበታል።
የዛሬይቱ ሰፊዋ ኢትዮጵያ እንደ ሕብረ ብሔራዊ የነገሥታት መንግሥት (multi-ethnic empire state) የተፈጠረችው በ2ኛው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ግማሽ፤ የዘመነ መሳፍንት ከሚባለው ዘመን በኋላ ስለሆነና ዛሬም በጣም ሰፊ ቀውስ ውስጥ የከተተን ታሪካዊ ዳራም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ፥ ጽሑፌም ከዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ጋር በተፈጠሩ ችግሮች ላይ ያተኩራል።
የዘመነ መሳፍንትን ክስተት በመለወጥ የተጀመረው የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሕልም በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ከሦስት እጥፍ በላይ የሰፋች ኢትዮጵያን መፍጠር ችሎዋል። ይህ የታሪክ ክስተት የሦስት ምኞቶች ዉጤት ነበር። እነዚህም፡-
1ኛ/ ተበታትና የነበረችውን የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማሰባሰብ የታለመ ምኞት፣
2ኛ/ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን ጨምሮ ሰፊውን የደቡብ ክፍል የማስገበር ምኞት፣
3ኛ/ አፍሪካን ለመቀራመት የመጡትን የአውሮፓ ሀገሮች ጋር የመፎካከር ምኞት ነበሩ።እነዚህን ሦስት ምኞቶች ለማሳካት የመጀመሪያ የሆነውን ሙከራ የጀመሩት እንደምታውቁት አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ። ቴዎድሮስ ሕልሞቹን ለማሳካት ጠንካራና ሰፊ ሠራዊት ማደራጀት ነበረባቸው፤ ለዚህም ሰፊ መሬት የያዙትን ቄሶች መሬት መቀማትና ዘመናዊ መሣሪያን ከክርስቲያን አውሮፓ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነበር። የአዉሮፓ መሪዎችን ማሳመን ሲያቅታቸው ደግሞ ሙያው የሌላቸውን አውሮፓዊያንን ሳይቀር በቤተ መንግሥታቸው ሰብስበው ከባድ የጦር መሣሪያ ውለዱ እስከማለት ደርሰዋል። ይህም ምኞታቸዉ ይሳካ ዘንድ በነበራቸዉ የጦር መሣሪያ የአካባቢ ገዥዎችንም ለማንበርከክ ተንቀሳቅሰዋል።
ቄሶችን ለመግፋት ያደረጉት ሙከራ እግዚአብሔርን የካዱ ንጉሥ ተብሎ ተሰባከባቸዉ። የአውሮፓውያንን ዘመናዊ መሣሪያ ለማግኘት ገደብ ያለፈ ጉጉታቸው ከእንግሊዘኞች ጋር ያለጊዜ አላተማቸው። የየአከባቢውን ገዥዎች በጉልበት ለማንበርከክ እጅና አንገት በመቁረጥ የገፉበት ሙከራ ከእንግሊዞች ጋር ለመዋጋት የቁርጥ ቀን ሲመጣ፥ የትግራይ፣ የወሎ፤ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጎንደር ገዥዎች ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ካዷቸው። በአጭሩ የየአከባቢዉ ገዥዎች በእንግሊዞች እጅ መሞታቸውን ሲሰሙ ከማዘን ይልቅ ተገላገልን ያሉ ይመስላል። ለዚህም ይመስለኛል ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሴር ባህሩ ዘውዴ የቴዎድሮስን ሚና በተሻለ የታሪክ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ ሲሞክር፥ “የተወናበዱ የለዉጥ ነቢይ” (“confused prophet of change”) ያላቸዉ።
በዚህ የቴዎድሮስ የታሪክ ሚና ላይ ብዙ ሰው ልብ የማያደርገውን የታሪክ ማስታወሻ አስቀምጬ ልለፍ። ይኼውም ቴዎድሮስ በጊዜው ለነበሩ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ፥ “አባቶቼ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር “ጋሎችን” በሀገሬ ላይ ለቆ፣ እነሱ ጌቶች ሆነው፣ እኛ የእስራኤል ልጆች የነሱ አሽከሮች ሆነን እንኖር ነበር። አሁን እግዚአብሔር ከትቢያ አንስቶኝ የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎኛል። እናንተ ከረዳችሁኝ በጋራ እየሩሳሌምንም ነፃ ልናወጣ እንችላለን” ማለታቸዉ ነዉ (ትርጉም የኔ ነው)። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ልበል፦
1) “ጋሎቹ” የሚባሉት በዘመነ መሳፍንት የጎንደርን ቤተ መንግሥት በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበሩ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውና እየሩሳሌም በጊዜው በእስላሞች እጅ የነበረች መሆንዋን ነው።
2) ከዚህ አንጻር ማስታወስ የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ አፄ ቴዎድሮስ የብሔረሰብ (የዘር) ፖለቲካን በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው።ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ለሦስት ዓመታት በተክለጊዮርጊስ እና ካሣ (አማቾች የነበሩ ይመስለኛል) ከተካሄደው የሥልጣን ትግል በኋላ በአሸናፊነት የወጡት አፄ ዮሐንስ (ካሣ ምርጫ) ነበሩ። አፄ ዮሐንስ ከሀገር ውስጥ ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ ገዢዎች ጋር እየተጋጩ፥ ከውጭ ደግሞ ከጣሊያኖች፣ ከግብፆችና ከሱዳን መሐዲስቶች (ደርቡሾች ) ጋር ሲዋጉ በመጨረሻ በመሐዲስቶች እጅ ወድቋዋል።
በአጭሩ ዮሐንስ ለትግራይ ሊሂቃን የኢትዮጵያ ማዕከል ነበርን፤ የአክሱም ሀቀኛ ወራሾች እኛ ነን የሚለውን የፖለቲካ ስሜት መፍጠር ቢችሉም፥ በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተለየ ሚና መጫወት አልቻሉም።
በማያሻማ ቋንቋ፥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዋናነት የተፈጠረችውና የዛሬው የታሪክ ጣጣችንም በዋናነት የተፈጠረው በአፄ ምኒልክ ነው። ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስን የሱዳን መሐዲስቶች እስኪገድሉላቸው ድረስ ከአውሮፓ መንግሥታት፥ በተለይም ከጣሊያን በገፍ ባገኙት የጦር መሣሪያ እነራስ ጎበና የመሳሰሉ የኦሮሞ የጦር መሪዎችን በመጠቀም በጊዜው ጠንካራ የሚባል ግዙፍ ሠራዊት መገንበት ችለዋል። ይህንን ግዙፍ ሠራዊትን ከዮሐንስ ጋር በመዋጋት ከማድከም ይልቅ፥ በአንድ በኩል ዮሐንስን እየገበሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የነበረችውን ኢትዮጵያ ሦስት እጅ እጥፍ የሆነ ሰፊ ግዛት መፍጠር ችሎዋል። በዚህም መጀመሪያ ሳይጠቀለሉ የቀሩትን የሸዋ ኦሮሞዎችን ጠቅልለው ያዙ። ከዚያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) በ1876 ጉራጌን ብዙ ሕይወት ከጠየቀ ጦርነት በኋላ አስገበሩ። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የምኒልክን የመስፋፋት ጦርነቶች እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል። ይኸውም በምኒልክና ጀኔራሎቹ ብዙ የግዛት መስፋፋት ጦርነቶችን ቢወጉም ሦስቱ ወሳኝ ጦርነቶች ነበሩ።
አንደኛው በምዕራብ በኩል በእማባቦ (ዛሬ ሆሮ ጉዱሩ በሚባለው ላይ በጎበና መሪነት እ.አ.አ በ1882 የተዋጉት ጦርነት ነበር። ይህ ጦርነት ኦሮሞን ጨምሮ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ዕድልና የጎጃም መሪዎች ከሸዋ ጋር የነበራቸውን ፉክክር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወሰነና የሸዋንም የበላይነት ያረጋገጠ ነበር።
ሌላው የምኒልክ ጦርነት በአርሲ ላይ እ.አ.አ በ1886 የተደመደመዉ ነው። አርሲዎች ከሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች በተለየ መንገድ ለአምስት ዓመታት በጀግንነት ተዋግተዋል። በመጨረሻም በራሳቸው በምኒልክ በተመራ ጦር የአውሮፓ መሣሪያ በፈጠረው ልዩነት ሊሸንፉ ችለዋል። ተመሳሳይ የመከላከል ጦርነት እንዳይገጥማቸው ይመስላል ምኒልክ ዛሬ አለ፣ የለም የሚባለውን የአኖሌ ዓይነት የጭካኔ በትር በአርሲዎች ላይ አሳርፈዋል። እዚህ ላይ ዛሬ እየተነጋገርንበት ላለው የብሔራዊ መግባባት መሳካት፥ የለም ከሚለው አጉል ክርክር ወጥተን የትናንትናውን የታሪክ ቁስላችንን በሚያክም መልኩ እንድናስተካክል መምከርን እወዳለሁ።
ሦስተኛው የምኒልክ ትልቁ ጦርነት አሁንም በእሳቸው የተመራውና እ.አ.አ በ1887 የተካሄደው የጨለንቆ ጦርነት ነበር። የዚህ ጦርነት ውጤት በጊዜው የሀብታሟ የሐረር ከተማ መንግሥት (the Harari city-state) ጨምሮ ምስራቅ ኢትዮጵያ ያለ ደረሰኝ ምኒልክ እጅ የገባበት ሁኔታን ፈጥሯል። ከዚህም በኋላ ከፋን፣ ወላይታን፣ ወዘተ ለመያዝ ብዙ ደም የፈሰሰባቸው ጦርነቶች ነበሩ። እንደሚባለው በእንግሊዝ ተስፋፊዎችና በምኒልክ ኢትዮጵያ መካከል የመምረጥ ዕድል የገጠማቸው የቦረና ኦሮሞዎች፥ ‘ማንን ትመርጣላችሁ?’ ሲባሉ፥ የፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ፊትን አይተው፥ የእኛኑ ፊት የሚመስለው ይሻላል ብለው በሪፈረንደም (referendum) እየሰፋ በመጣው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ግዛት ውስጥ የተቀላቀሉበት ሁኔታም እንዳለ ይነገራል።
እ.አ.አ በ1889 አፄ ዮሐንስ በመሐዲስቶች ሲገደሉ፥ ኦሮሞን ጨምሮ አብዛኛው ደቡብን የተቆጣጠሩት ምኒልክ ለሰሜኑ ወንድም መሪዎች ፈረንጆች እንደሚሉት “ካሮትና ዱላን ማስመረጥ” (carrot-and-stick approach) ብቻ በቂ ነበር። የሰሜኑ መሪዎች ምርጫም በማያሻማ መንገድ ካሮት ነበር። ስለካሮቱም በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኦሮሞ አከባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ የተገኘውን እጅግ በጣም ሰፊ ግዛት ዉስጥ በታናሽ ወንድምነት ሹማቶችን መቀራመት ነበር።
በብሔራዊ መግባባታችን ውይይት አንፃር በምኒልክ በተፈጠረው ሰፊ አፄያዊ ግዛት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ወደ ማንሳቱ ልለፍ። አንደኛው ችግር ከላይ እንዳነሳሁት፥ በጉልበት የግዛት ፈጠራ ላይ አኖሌን የመሳሰሉ የታሪክ ጠባሳዎች መፈጠራቸው። ሁለተኛውና ዋናው ነገር ግን ከማቅናቱ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካል ኤኮኖሚው ነው። ይህም በነፍጥ ላይ የተመሠረተዉ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ዛሬም እያወዛገበን ያለው የነፍጠኛ ሥርዓት በሚባለው ላይ የተመሠረተዉ ነዉ። ለማቅናት የተሰማራው የፊውዳሉ ሥርዓት ሠራዊት የገባር ሕዝቦችን ነፃነት ቀምተዋል፤ መሬታቸዉን ዘርፈዋል፤ ሕዝቦችን በገዛ መሬታቸው ላይ ጭሰኛና አሽከር አድርገዋል፤ ቋንቋቸውን አፍነው በ’ስማ በለው’ ገዝቷቸዋል። በአጭሩ፥ እጅግ በጣም ዘግናኝና ጨካኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ጭነውባቸዋል። አንዳንዱ ነፍጠኛ በሃያ ሺዎች የሚቆጠር ጋሻ መሬትም ነበረው። ወረ-ገኑ የመሳሰሉ የቤተ መንግሥት መሬቶች እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት ይዞታም በፍጹም የተለያዩ መሆናቸው ነው። አነሰም በዛ የሰሜኑ ገበሬ የዘር ግንዱን ቆጥሮ መሬት ያገኛል። መሬት አያያዙም የወል ነበር። ሌላው ቢቀር የሚገዛውም በራሱ ቋንቋ ነበር። በደቡቡ ያለው ግን የመሬት ሥርዓቱ የግል ሆኖ፥ ጭሰኝነት እጅግ የተንሠራፋበት ነበር። ሲሶ ለነጋሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ፣ ሲሶ ለአራሽ የሚባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የመሬት ፖሊሲ እጅግ በጣም ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሥራ ላይ የዋለው በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ነው።
በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን “መሬት ላራሹ” እና “የብሔረሰቦች እኩልነት” የተባሉ ሕዝባዊ መፈክሮች የተወለዱት ከዚሁ ጨቋኝ ሥርዓት ነበር። ዛሬ የታሪክ ክለሳ ውስጥ ብንገባም፥ በእውነቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራክ የወጡ ወጣቶች፥ እንዲያውም በወቅቱ ‘አማራ’ ከሚባለው ክፍል የሚበዙ ይመስለኛል፤ መፈክሮቹን በጋራ አስተጋብተዋል።
ለማንኛውም ከብሔራዊ መግባባታችን አንፃር አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ። ‘ነፍጠኛ’ የሚባለው ሥርዓት ገዝፎ የነበረ ሥርዓት መሆኑና፥ ይህም ሥርዓት ከደቡቡ አርሶ አደር የተሻለ ኑሮ የማይኖሩትን፥ ቢፈልጉ እንኳን የደቡቡን ገበሬ ለመዝረፍ አቅሙም ሆነ ዕድሉን ያልነበራቸውን የአማራ አርሶ አደርን አይጨምርም፤ መጨመሩም ጩቡ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ አንዳንድ የአማራ ሊሂቃን “እኔም ነፍጠኛ ነኝ” የሚለውን መፈክር ሲያሰሙ፥ ጥቅሙ ኦሮሞን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ከአማራ ሕዝብ ጋር ከማጋጨት የዘለለ የፖለቲካ ትርፍ የሚኖረው አይመስለኝም። ስለሆነም የምንችለውን ያክል ሁላችንም ከሁለቱም ጩቡዎች እንጠንቀቅ ዘንድ አደራ እላለሁ።
ወደ ሌሎች ነጥቦች ከማለፌ በፊት በዋናናት በምኒልክ የተፈጠረችዉ ኢትዮጵያን ለማስተካከል ያቃታቸዉና መሪዎች ማለፍ ያልቻሉት የታሪክ ፈተና ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በንጽጽር እንደ ታሪክ ቁጭት ማንሳትን እወዳለሁ። አፄ ቴዎድሮስ የሞቱት እ.አ.አ በ1868 ነበር። ጃፓንን ከታላላቅ የዓለም መንግሥታት ተርታ ያሰለፏት መጅ (Meiji) የሚባሉ የንጉሣውያን ቤተሰብ ወደ ሥልጣን የተመለሱት (The Meiji Restoration) በዚሁ ዓመተ ምኅረት ነበር። የጃፓን ንጉሣዊ ቤተሰቦች በሰላሳ ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ የበለፀገች ታላቋ ጃፓንን ፈጠሩ። የጃፓኖች የሀገር ፍቅር ግንባታቻውም ባዶ አልነበረም። ትዝ እስከሚለኝ ድረስ አንድ የጃፓን ወታደር ንጉሤ የጃፓንን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሸነፍ አልነገሩኝም ብሎ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ በፊሊፕንስ ይሁን፤ በኢንዲኔዢያ ጫካ ውስጥ ተገኝቷል። ለሀገር ፍቅር ሲባል እራስን በራስ ማጥፋት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በትናንሽ አይሮፕላኖችን የአሜሪካን መርከቦች ውሰጥ እየጠለቁ አጥፍቶ መጥፋትን የጀመሩት የጃፓን ካሚከዞች (Kamikaze) የሚበሉ ነበሩ። የኢትዮጵያ መሪዎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ (እ.አ.አ 1868-1900) ድረስ ሀገሪቷን ከዓለም ጭራነት አላላቀቋትም። በነገራችን ላይ ጃፓንና ኢትዮጵያ በ1868 ላይ ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ።
ሌላው ንጽጽሬና የታሪክ ቁጭታችን መሆን ያለበት፥ ታላቋ ጀርመንን የፈጠሩት ቢስማርክ (Otto von Bismarck) እና ምኒልክ የአንድ ዘመን ሰዎች ነበሩ። ምንም ይሁን ምን እነ ቢስማርክ ዓለምን ሁለት ጊዜ ጦርነት ውስጥ መክተት የቻለች ኃያሏን ጀርመን ሲፈጥሩ፥ የኢትዮጵያ ገዥዎች ግን ኋላቀር ኢትዮጵያን ትተውልን ሄደዋል። በነገራችን ላይ ሀገር ትፈርሳለች ተብሎ ስለተሰጋ፥ የምኒልክ ሞት ለሕዝብ ይፋ የሆነው ከዓመታት በኋላ ነበር ይበላል።
በአጠቃላይ ከብሔራዊ መግባባት ፈጠራችን አንፃር መረሳት የሌለበት ቁመነገር፥ በምኒልክና ጣይቱ የተመራው የአድዋው የጋራ ድል እንኳ ያልፈቱት የሚጋጩ ሦስት አመለካከቶች ዛሬም ከእኛ ጋር መኖራቸዉ ነዉ።
አንደኛው፥ የሀገራችን ሀገረ-መንግሥት ግንባታ አንድ የነበሩና የተበታተኑ ሕዝቦችን አንድ ላይ መልሶ ያመጣ ነዉ የሚላዉ አመላካከት (reunification)፤
ሁለተኛው፥ በአንድ ላይ ያልነበሩ ሕዝቦችን ወደ አንድ ማምጣት ነዉ የሚለዉ አመላካከት (unification and/or expansion)፤
ሦስተኛው፥ ነፃ ሕዝቦችን ጨፍልቆ በኃይል ማቅናት ነዉ የሚላዉ አመላካከት (colonial thesis) ናቸው። የበለጠ ግልፅ ለማድረግ፥ የኢትዮጵያ አንድነት አጥባቂዎች ነን የሚሉ በዋናነት የምኒልክን ኃጢአቶች አይቀበሉም። እንደሚሉት እምዬ ምኒልክ በዓለም ከተደረጉት የሀገር ግንባታዎች ምን የተለየ ነገር ሠራ የሚለውን ሐሳብ ያራምዳሉ። ከዚያም አልፈዉ ምኒልክ የሠራዉ ሥራ ተለያይተዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ ግዛቶችን መመለሰ ነበር ይላሉ። በአንፃሩ የኢትዮጵያ አንድነትን የማያጠብቁ ብሔረተኞች ደግሞ የአቶ ሌንጮ ለታን አባባል ለመጠቀም (አሁን አቋማቸዉ ያ መሆኑን አላዉቅም)፥ ሲያንስ “ኢትዮጵያዊ ለመሆን እንደራደራለን ሲበዛ ደግሞ ነፃ መንግሥታትን እስከ መፍጠር ድረስ እንሄደለን” የሚሉ ናቸው። በጥቅሉ እነዚህ አመለካከቶች በፖለቲካችን ለሚጋጩ ሕልሞቻችን መሠረት የሆኑና ካልተገደቡ የሥልጣን ሕልሞች ጋር ተደምሮ የብሔራዊ መግባባት ጥረታችንን የሚያወሳስቡ አመለካከቶች መሆናቸውን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል።በእነምኒልክ የተፈጠረችዉን ኢትዮጵያን ለማስተካከል የተደረጉ ሙከራዎችና ያመለጡን ዕድሎች፡-
1) የልጅ ኢያሱ ሙከራ
ልጅ ኢያሱ የምኒልክ ልጅ ልጅ ሲሆን፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩ ዕድል የነበረውና ያንንም ልዩ ዕድል አውቆ ለመጠቀም ሲሞክር በወጣትነት ዕድሜው ላይ የተቀጨ መሪ ነበር። በብሔር ግንዱ ኦሮሞና አማራ የነበረ፣ በሃይማኖት ጀርባዉ ክርስቲያንና ሙስሊም የነበረ ሰዉ ነዉ። ከወሎም በመወለዱ፣ ትግራይንና ሸዋን ለማገናኘት የተሻለ ድልድይ ለመሆን ይችል ነበር። የሚገርመው ግን፥ የልጅ ኢያሱ ወንጀሎች የሚመነጩት እነዚህኑ አዎንታዊ እሴቶችን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለመጠቀም መሞከሩ ነበር። ለምሳሌ አንዳንድ የታሪክ ማስታወሻዎች እንደሚያስረዱት፥ አርሲዎች እንደልጃቸው ይመለከቱት ነበር ይባላል። ከሱማሌዎችና ከአፋሮች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው በቂ የሆነ የታሪክ ማስረጃ አለ። ከጎጃሙ ራስ ኃይሉና ከወለጋው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ጋር የጋብቻ ዝምድና እንደነበረው ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያንን ለማሠራት የሚጥረውን ያክል (ለምሳሌ የቀጨኔውን መድሃኔዓለምን እሱ ነው ያሠራው ይባላል) መስግዶችን ያሠራ ነበር። ከሥልጣን ላወረዱት የሸዋ ሊሂቃን ግን፤ አንዱና ትልቁ የልጅ ኢያሱ ወንጀል መስጊዶችን ማሠራቱ ነበር። የመጨረሻው ትልቁ ወንጀል ደግሞ ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያንዣበቡ የቅኝ ገዥ ኃይሎች ከሰሜንና ምስራቅ ጣሊያን፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በምስራቅ እንግሊዝ፣ በምስራቅ ፈረንሳይ የሦስትዮሽ ስምምነት (tripartite treaty) የሚባለውን እ.አ.አ በ1903 ፈርሞ የምኒልክን ሞት ይጠብቁ ከነበሩት መራቅና በአንደኛው የዓለም ጦርነት በአከባቢያችን ግዛት ካልነበራቸው ከነጀርመንና ቱርክ ጋር ለመደጋገፍ መሞከሩ ነበር።
በጥቅሉ ከሁሉም በላይ ወንጀሎቹ ሰፊዋን ኢትዮጵያን የፈጠርን እኛ ነን የሚሉትን የሸዋ ልሂቃንን መጋፋቱ ነበር። በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኢያሱ ወንጀሎች የሸዋ ልጅ አለመሆኑ (የኢያሱ አባት ወሎ ነው)፣ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አለመሆኑ (አባቱ የግድ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት መሐመድ ዓሊ ነበሩና) እንዲሁም የአውሮፓ የቅኝ ገዥ ኃይሎችን ማስቀየሙ ናቸው።
እ.አ.አ በ1916 በመስቀል ቀን ኢያሱን ለማውረድ ሁሉም መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ተሰለፉ። ቄሶቹ ኢያሱ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አይደለም በማለት በማውገዝ፣ የሸዋ ሊሂቃን ሠራዊታቸውን በመሳለፍ፣ የአውሮፓዊያኑ መንግሥታት ምክርና ጥበባቸውን ይዘው ተሰለፉ። የአውሮፓዊያኑ ጥበብ የሚገርም ነበር፤ ኢያሱ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የእስልምና ምልክት የሆነውን ግማሽ ጨረቃ ለጥፎ ለቱርኮች ዲፕሎማት ሲሰጥ የሚያሳይ ፎቶ ሾፕ የሆነ ሥዕል (ፎቶ ሾፕም፣ የባንድራ ፖለቲካም በልጅ ኢያሱ ዘመንም ነበር) መፈንቅለ መንግሥት እንድያከሄዱ የሸዋ ሊሂቃንን መርዳት ነበር። እዚህ ላይ ለታሪክ ትዝብት አንድ ነገር ልብ በሉልኝ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሳስተምር፥ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ችግሮቻችንን በሚመለከት ፈተናም ፈትኜበታለሁ፤ የሸዋው ጦር መሪ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የመፈንቅለ መንግሥቱም መሪ ነበሩ፤ ልጅ ኢያሱን ሲያወርዱ ባስተላለፉት መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል።
“He claims that he eats flesh of cattle slain by Muslims in order to extend frontiers and to win hearts. But these Somali and Muslims have already been brought to heel [and do not need such diplomacy]”
በጥሬው ሲተረጎም፥ ግዛትን ለማስፋፋትና ልቦችን ለመሳብ ብዬ በሙስሊም የታረደውን የከብት ሥጋ እባላለሁ ይላል። ነገር ግን እነዚህን ሱማሌዎችና ሙስሊሞችን ቀድሞውኑ ስላንበረከክን እንዲህ ዓይነቱ ዲፕሎማሲ አያስፈልጋቸውም።
ይህንን የሀብተጊዮርጊስን ንግግር በሚመለከት ሰፊውን ትንተና ለናንተ ትቼ፥ በዚህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን አስተካክሎ በሰፊ መሠረት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ፥ ልጅ ኢያሱን ለሥልጣን ተብሎ በተጠነሰሰው ሤራ መውረዱን እንዳትረሱት አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ያመለጠንን ዕድል ትርጉም ግን ለታሪክ መተውን አመርጣለሁ።
2) ኢያሱን በወሳኝነት የተኩት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ
የሀገራችንን ሀገረ-መንግሥት ግንባታን በተሻለ መሠረት ላይ ለመገንባት ረጅም ጊዜ (ለ60 ዓመታት ገደማ አገሪቷን መርተዋል) በልጅነታቸው የተሻለ የፈረንጅ ዕውቀት የቀመሱና ከማንም የበለጠ ተደጋጋሚ ዕድል ያገኙ ነበሩ። ነገር ግን በእኔ ግምት ታሪክ የሰጣቸዉን ዕድል አልተጠቃሙበትም። ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ የታሪክ ሚዛን ላይ ቢያስቀጣቸውምና እኔም ቢሆን በዘመናዊ ትምህርትና በመሳሰሉት ላይ የነበራቸውን አሻራ ቀላል ነው ብዬ ባላስብም፥ ንጉሡ ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ የግል ዝናንና ሥልጣንን ማዕከል ማድረጋቸው ኢትዮጵያዉያንን የ20ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች ማድረግ አልተቻላቸውም። ስለዘር ግንዳቸው ሀሜቱ እንዳለ ሆኖ፥ ከኢያሱ በተሻለ ደረጃ ኦሮሞም፣ ጉራጌም አማራም ነበሩ። ይህንን ስረ ግንድ አልተጠቀሙም። በተለይ ኦሮሞ ከሚባል ሕዝብ ሲሸሹ እንደኖሩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለማንኛዉም፤ አንድንድ ወሳኝ ነገሮችን እንመልከት።
አምቦ 2ኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የሰማሁት ይመስለኛል፤ አንድ ጋዜጠኛ ካነበቡት መጽሐፍት ዉስጥ የትኛውን እንደሚያደንቁ ሲጠይቃቸው፥ ቀልባቸውን በጣም የሳበውና ብዙ ጊዜ ደጋግመው ያነበቡት በኒኮሎ ማኪያቬሊ (Niccolò Machiavelli) የተፃፈውን “The Prince” የተባለውን እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ንጉሡ አብዘኛዉን የሕይወት ዘመናቸዉን የተመሩት በማኪያቬሊ ምክር ነበር ብዬ እጠረጥራለሁ። በማክያቬሊ ትምህርት በመመራትም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን አንድ በአንድ አስወግደው ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1930 ጥቁር ማክያቬሊ ፈላጭ ቆራጭ ንጉሥ ሆነው ወጡ።
እንደ ሀብተጊዮርጊስ ዓይነቱን እግዚአብሔር በጊዜ ሲገላገልላቸው፣ እንደ ጎንደሩ ራስ ጉግሳና ባለቤታቸው ንግስት ዘዉድቱን ያስወገዱበት የፖለቲካ ጥበብ፣ በጊዜው በርግጥም አስደናቂ ነበር። ይህ የንጉሡ ጥበብ፤ አርባ ዓመታትን ቆጥራ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የመጣቸውን ጣሊያንን ለመከላከል አልረዳም። መንግሥታቸዉንም፤ ሀገሪቷንም ለክፉ ቀን አላዘጋጁም።
አድዋ ላይ ታሪካዊ ድል ያስገኙ ጀግኖችም የሉም። አንድ ለታሪክ የተረፉት ደጀዝማች ባልቻ ሣፎም በንጉሡ ዉሰኔ እስር ቤት ነበሩ። እዚህም ላይ አንድ የታሪክ ትዝብት አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለሁ። ኃይለ ሥላሴ ለሥልጣናቸዉ ብሎ የገፏቸው ብዙ የአከባቢ መሪዎች፥ ከትግራዩ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ጀምሮ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጅማ፣ የወለጋ ገዥዎች የጣሊያን ባንዳ ሆኑ። ከሚታወቁት ውስጥ ለታሪክ ‘ተፈሪ ሌላ፣ ሀገር ሌላ’ ብለው ሲዋጉ የሞቱት ደጃዝማች ባልቻ ብቻ ነበሩ። በንጉሡ ስህተት ሀገሪቷ ውድ ዋጋ ከፍላለች። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ጠዋትና ማታ ባንዳ፣ ባንዳ ሲሉ፥ ግብፅ ሱዳንን ይዛ የምር ከመጣች ሰው ያላሰበውን አሳስበው ለኪሳራ እንዳይዳርጉን የሚፈራው።
ያም ሆነ ይህ፥ ኃይለ ሥላሴ ለጦርነት ያላዘጋጇትን ሀገር በክፉ ቀን ጥለው ሸሹ። ሐረርጌ ላይም የጂቡቲን ባቡር ሲሳፈሩ ከጦር ሜዳ መሸሻቸውን ለመሸፈን፥ ‘የት ይሄደሉ?’ ብሎ ለጠያቀቸዉ የፈንሳይ ጋዜጠኛ፡ “Je ne suis pas né soldat” (“ወታደር አይደለሁም”) ብለው ያለፉት። ለሳቸዉም ፍትሃዊ ለመሆን፥ የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ቢክዷቸውም በዓለም መንግሥታት ማኅበር ላይ የሚያስመካ ሥራ ሠርተዋል። ሆኖም ከጦር ሜዳ የመሸሻቸው ጉዳይ እስከ መንግሥታቸው ፍፃሜ ድረስ እንደ ጥቁር ነጥብ ስትከታላቸዉ ኖራለች። የአርበኞችም ሆነ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዋናው የተቃውሞ መፈክርም ይህች የሽሸት ጉዳይ ነበረች። ከጣሊያን ወረራ በኋላም ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ምክንያት፥ ጋዜጣቸውን “አዲስ ዘመን” ብለው እንደሰየሙ፥ በእርግጥም አዲስ ዘመን፤ ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ይፈጠራሉ ብሎ የጠበቁ ብዙ መሆናቸውን ብሎ መገመት አስቸጋሪ አይመስለኝም።
ለአምስት ዓመታት በእንግሊዝ ሀገር በስደት ሲኖሩ ስለራሳቸው ስህተትም ሆነ የሰለጠነው ዓለም ንጉሦች እንዴት ሕዝቦቻቸውን እንደሚመሩና በዚያም ምክንያት በሕዝቦቻቸው ዘንድ ተከብረው እንዴት እንደሚኖሩ ተምረዋል ብሎ መጠበቅ ይቻል ነበር። ከሁሉም በላይ በጣሊያን ወረራ ምክንያት እሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ከገጠመው ውርደትና ኪሳራ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅም ነበር። ከሁሉም አልተማሩም። በባሰ ሁኔታና ፍጥነት ወደ ድሮአቸው ተመለሱ። ለዓቢይነት፥ አስተዳደራቸውን የተቃወሙ የራያ ገበሬዎችን (ቀዳማይ ወያኔ የሚባለዉ ነዉ) ከየመን በመጡ የእንግሊዝ አይሮፕላኖች አስደበደቡ። የሪፐብሊካን አስተሳሰብ ነበራቸው የሚባሉትን አርበኛ ደጃዝማች ታከለን (ደጃዝማች ታከለ ወልደሀዋርያት) አሰሩ። እኚህ ሰው ከተደጋጋሚ እስር በኋላ በመጨረሻም ሊይዟቸው ከተላኩ የንጉሡ ወታደሮች ጋር ሲዋጉ ሞቱ። ሌላው ስመጥር አርበኛ የነበሩ በላይ ዘለቀንም ያለርህራሄ ሰቀሉ።
የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ግልፅ ደብዳቤ እንኳን (አምባሳደር ብርሃኑ፤ በአሜሪካ አምባሳደር የነበሩና ንጉሡ የገፉበት መንገድ ዉሎ አድሮ ንጉሡንም ሆነ ሀገሪቷን ለዉርደት እንደሚያበቃ የመጀመሪያ የማስጠንቃቂያ ደወል በአደባባይ የሰጡ ባለስልጣን ነበሩ) አሠራራቸውን አላስለወጧቸውም።
በፖለቲካ ሥርዓታቸው ላይ በተከታታይ ቦንቦች ፈነዱ። የመጀመሪያዉ ትልቁ ቦንብ በራሳቸው ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈነዳው የነመንግሥቱ ንዋይ ያውም የእሳቸውን ክብርና ሞገስ ለመጠበቅ ከፈጠሩት የክብር ዘበኛ ጦር ነበር። ንጉሡ ከክስተቱ ከመማር ይልቅ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን በሞት ቀጡ፤ የታናሽ ወንድማቸውን ሬሳ እኔን ያየህ ተቀጣ በሚመስል መንገድ በስቅላት ቀጡ። የበሉበትን [ወጭት] ሰባሪዎች ናቸው ብለውም በአዝማሪ አዘለፏቸው።
ማን እንደመከራቸው ባይታወቅም ትልቁን የመንግሥታቸውን የዲፕሎማሲ ውጤትን ያበላሸውና ለትልቅ ኪሳራ ያበቃንን የኤርትራን ፌዴሬሽንን አፈረሱ። ውጤቱም ሁላችንም እንደምናውቀው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር መፈጠር ሆነ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ኦሮሞዎች የሜጫና ቱለማ ልማት ማኅበር በመፍጠራቸው ጠገቡ ተብሎ መሪዎቹ እነ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር ተሰቀሉ፤ ኃይለማርያም ገመዳ እስር ቤት ውስጥ በተፈፀመበት ድብዳባ ሞተ። ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሞት ተፈርዶባቸው በአማላጅ ወደ ሐረርጌ በግዞት ተላኩ። እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ አልነበራቸውም። ውጤቱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን መፍጠር ሆነ። በነገራችን ላይ በእነ ኤሌሞ ቅልጡ በኦነግ ስም የመጀመሪያዋ ጥይት የተተኮሰችው ጀኔራል ታደሰ ብሩ የታሰሩበት ሥፍራ ሐራርጌ ዉስጥ ነበር። በዚሁ ጊዜ ሰፋፊ ማኅበራዊ ፍትህን የሚጠይቁ ተከታታይ ጥያቄዎችም መቅረብ ጀመሩ። እ.አ.አ በ1965 የንጉሡ ፊውዳላዊ ሥርዓት የተመሠረተበት ላይ በመሬት ላራሹ ሰልፍ ድንገተኛ የፖለቲካ ቦንብ ፈነዳ። ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ እስከዛሬ ኢትዮጵያን እያመሰ ያለው በእነ ዋለልኝ መኮንን የብሔረሰቦች ጥያቄ ታወጀ። ይህችኛውን ንጉሡና ሥርዓቱ በቀላሉ የተመለከቷት አይመስልም። ንጉሡ የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ፥ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዝደንት የነበረውን ጥላሁን ግዛዉን በማሰገደል “ልጆቼ” ከሚሏቸው ተማሪዎች ጋር ደም መቃባት ዉስጥ ገቡ። በዚህም የታሪክ ጎማው ወደፊት እንዳይሽከረከር ጣሩ።
አሳዛኙ ጉዳይ መካሪዎቻቸውም ሆኑ እሳቸው አስተዳደራቸው ለሃያኛዉ ክፍለ ዘመን የማይመጥን መሆኑን፣ በጣም እወዳታለሁ የሚሏትም ኢትዮጵያ በታሪክ ፍራሽ ላይ ተኝታ የምትሸሞነሞን ሀገር መሆኗን አልተረዱም። የኤርትራ ግንባሮች ጥይትም ከረጅም ዘመን እንቅልፋቸው አላነቋቸውም። የባሌና የጎጃም ሕዝብ አመፅም አልቀሰቀሳቸውም። ለዓመታት የቆየው የተማሪዎች ንቅናቄ ጩኸትም አላነቃቸውም። ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በቀጥታ የወጡ የመኢሶንና የኢህአፓ የሶሻሊስት አብዮት ደወልም አላነቃቸውም። በመጨረሻም በመቶ ሺዎች የሚቆጠረው የወሎ ሕዝብ እልቂት እንኳን ከእንቅልፋቸዉ አላበነናቸውም።
በነገራችን ላይ፥ ብልጡ ደርግ በጠዋቱ ሊያወርዳቸው፣ ማታ ያሳየው የወሎ ሕዝብ እልቂት፥ በአንድ በኩል የንጉሡ ውሻ በጮማ ሥጋ ሲጫወት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃብ በተረፈረፈ ሕዝብ ውስጥ ሕፃን ልጅ የሞተች እናቷን ጡት ስታጠባ የሚያሳየዉን የጆናታን ዲምበልቢ (Jonathan Dimbleby, “The Unknown Famine”) ፊልም ነበር። ያንን ፊልም ደርግ በቅድሚያ ንጉሡና የኢትዮጵያ ሕዝብን እንዲያዩ ስለጋበዘ ቴሌቪዥን ያልነበረን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አካባቢዎች ያሉትን ቡና ቤቶችን አጣብበን ስንመለከት ነበር። የንጉሡ ደጋፊዎች እንኳ ጃኖሆይ እንዲህ ጨካኝ ነበሩ እንዴ? የሚሉትን ይዘን ወደ ዶርማችን እንደገባን ትዝ ይለኛል። ምናልባት ከእንቅልፋቸው የነቁት በማግስቱ የደርግ አባላቱ በኩምቢ ቮልስዋገን ከቤተ መንግሥታቸው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሲወስዷቸው በሠሩባቸው ድራማ ይመስለኛል። ብልጣብልጦቹ ደርጎች የተጠቀሙት ቮልስ መጀመሪያ መስኮቷ ዝግ ነበር ይባላል።
ንጉሡ ከውጭ ብዙ ሰው ሲጮህ ተመልክተው፥ “እናንተ ልጆች የሚወደን ሕዝባችን ንጉሤን የት እየወሰዳችሁ ነው እያለ ነዉ” ሲሉ፥ ብልጦቹ ደርጎችም መስኮቱን ከፍተው የሕዝቡን ድምፅ ሲያሰሟቸው ጩኼቱ “ተፈሪ ሌባ፤ ተፈሪ ሌባ” የሚለውን ሰምተው፥ “አይ ኢትዮጵያ ይኼን ያክል በድዬሻለሁ እንዴ?” አሉ ይባላል። በዚህ ሽኝታቸው ድሮ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ዳቦ የሚጥሉላት ለማኝ ዳቦዋን ስትጠብቅ፥ ‘ንጉሡ ወረዱ፤ ንጉሡ ወረዱ’ ሲባል ሰምታ፥ ‘ለዚህ ያበቃኸኝ አንተ ነህ!’ ብላ በቮልሷ አቅጣጫ የወረወረችው ዳቦ ብቻ ነበር ይባላል። የንጉሡ ሬሳም ከ17 ዓመታት በኋላ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ሽንት ቤት ሥር ተቆፍሮ እንደተገኘ ይታወቃል። እዚህ ላይ ልብ አድርገን ማለፍ ያለብን የፖለቲካ ቁም ነገር ለ60 ዓመታት ገደማ (የአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ እንዳለ ሆኖ) በፈላጭ ቆራጭነት ኢትዮጵያን ሲገዙ የሀገረ መንግሥታቸው ግንባታ ፕሮጀክት በአጉል ምክርም ይሁን በራሳቸው ገታራ አቋም ከሽፎ ሽኝታቸው በለማኟ ዳቦ፣ ቀብራቸው ደግሞ በአሳደጓቸው ወታደሮች ሽንት ቤት ሥር መሆኑ ነው።
3) አብዮቱ እና የደርግ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ
አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሕዝባዊ አብዮቱ ልዩ ዕድል ፈጥሮ ነበር። አብዮቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የመጡ የአዲሱ ትዉልድ ምሁራን ድጋፍና ተሳትፎ ነበረው። እንደ አብዮቱ መሪ ወደፊት የመጣውን መንግሥቱ ኃይለማርያምም ‘ቪቫ መንግሥቱ፣ ቪቫ መንግሥቱ!’ ብለን ተቀብለን ነበር።
የኢትዮጵያ አብዮትን አብዮት ያደረገው የጭሰኝነት ሥርዓትን ያስወገደውና የደርግ እርምጃ (ውለታው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቢሆንም) እስከዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አለው ብዬ ባምንም፥ ነገሮችን በቶሎ የሚያዩ ወጣቶች “ተፈሪ ማረኝ፤ የደርጉ ነገር አላማረኝ ” ማለት የጀመሩት ብዙዉም ሳይቆዩ ነበር። በአጭሩ ለማስቀመጥ፥ የደርግ የሥልጣን ፍቅር፣ የመኢሶንና የኢህአፓ አሳዛኝ ክፍፍል፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት የተናጠል የፖለቲካ ፕሮጀክቶች በአብዮቱ መፈንዳት የተፈጠረውን ልዩ ታሪካዊ ዕድል አምክኖታል።
ደርግ መሃይምነትና የሥልጣን ፍቅር ስለተደባለቀበት፥ የሶሻሊስት አብዮቱን እንደሰው ማሰርና መግደል ወሰደው። በዚህ ሶቭዬት ህብረት ድረስ ሄዶ የሌኒን ሐውልት አይተው የመጡት ባለሥልጣኖቹ ስለሶሻሊዝም የተማርነው ከበሰበሰ ከቡርዧ ቤተ መፃሕፍት ሳይሆን ከምንጩ ከሌኒን ሀገር ነው እያሉ ተዘባበቱ። ካደሬዎቻቸው ድንቅ የሶሻሊስት ዕውቀታቸውን ከፍተኛነት ለማሰየት በሚመስል መንገድ የስታሊን ቀይ በትር ሥራ ላይ ይዋል አሉ። ደርግ የሱማሌ ወረራን፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ አንድነት እንዲነግድ ልዩ ሁኔታ ስለፈጠሩለት “አብዮታዊት እናት ሀገር፥ ወይም ሞት!” አለ።
ከኤርትራ ግንባሮች እስከ ኢህአፓ እና መኢሶን (ኢጭአት/ ኦነግን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች እዚህ መሃል ናቸው) የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነትና የአብዮት ጠላቶች ሆነው ልዩ ልዩ ስሞች ተለጣፈበቸው። በአጭሩ የኢህአፓና መኢሶን መከፋፈልም ደርግን ብቻኛ የሀገር አንድነትና የአብዮት ተወካይ አደረገው። ሌሎች ዝርዝሮችን ትቼ ለኢትዮጵያ አንድነትና አብዮት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ላንሳ።
የደርግ የመጀመሪያው ሊቀ መንበር አማን አንዶም የሚባሉ ኤርትራዊ ጀኔራል ነበሩ። የደርግ ሊቀ መንበር ተብሎ ከደርግ ውጭ የተመረጠትም ለኢትዮጵያ አንድነት ብሎ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ ሄዶ ካልተዋጋሁ ብሎ ንጉሡን ያስቸገሩ መኮንን ስለነበሩ ነዉ። በወታደሮቹ ዘንድም ተወዳጅ ስለነበረ በራሳቸው በደርግ አባሎቹ ጥያቄ መጀመሪያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከዚያም ከደርግ ውጭ የደርግ ሊቀ መንበር የሆነው የተመረጡትና በአደባባይ እስከሚታወቀውም በኢትዮጵያ አንደነት ላይም (መቼም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ልዩ ፍቅር አለን የሚሉ ብዙ ቢኖሩም፥ ፍቅራቸውን የሚለካልን መሣሪያ በሜዲካል ሳይንስ እስካሁን አልተፈጠረልንም) ምንም ዓይነት ጥያቄ ያልነበራቸውና የኤርትራን ችግር በሰላም ለመፍታት አሥመራ ድረስ ሄዶ ሕዝቡን ያወያዩ ነበሩ። ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አለኝ የሚሉ እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን ጠረጠሯቸዉ፤ በታንክ እቤታቸው ውስጥ ገደሉት። በእኔ ግምት ውጤቱ የኤርትራና የኢትዮጵያን አንድነት መግደል ነበር። በዚህም ኤርትራ የደም ምድር ሆነች። ዛሬ እንዲህ ልንሆን የፈሰሰው የሰው ደም ዋጋም ሆነ ለጠፋው ሀብትና ንብረት ሂሳብ ለፈረደበት ታሪክ መተው ይመረጣል።
የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን ልታመጡብኝ ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁለተኛውን የደርግ ሊቀ መንበር የነበሩትን ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ከደጋፊዎቻቸው የደርግ አባላት ጋር ረሸናቸው።
ኮሎኔል አጥናፉ አባተንም ቅይጥ ኢኮኖሚ ልታመጣብን ነው ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም በፀረ-አብዮታዊነት ረሸነዉ። በነገራችን ላይ የመጨረሻ ጭንቅ ሲመጣ መንግሥቱ ኃይለማርያም የአጥናፉን ቅይጥ ኢኮኖሚ ላይ ለመንጠላጠል ሞክሮ ነበር።
በዛሬው የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላቸው ጀኔራል ታደሰ ብሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሞት ተፈርዶባቸው ተረሸኑ። እኔ መከታተል እስከቻልኩ ድረስ ታደሰ ብሩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ፍጹም ጥያቄ ያልነበራቸው፤ ለኢትዮጵያ ብሎ ከሰላሌ ጫካ እሰካ ሞቃዲሾ ድረስ ተወስደው የታሰሩ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን ብለው ሲመጡ ከነሱ ጋር እየተዋጉ የመጡ አርበኛ ነበሩ። ከተራ ወታደርነት እስከ ጀኔራል ማዕረግ ድረስ ሀገራቸውን ያገለገሉም ነበሩ። እግር ጥሏቸው አብዮቱ ውስጥ የገቡት መንግሥቱ ኃይለማርያም ያላርህራሄ ገደሏቸዉ። በነገራችን ላይ ከጀኔራል ታደሰ ብሩ ጋር በፀረ አንድነት ክስ የተገደለ፣ ብዙ ሰው የማያስታውሰው መለስ ተክሌ የሚባል በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪ መሪዎች አንዱ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ነበር (በጊዜዉ ከነበረዉ አቋም ተነስቼ፥ ይህ ሰው ቢቆይ ኖሮ የትኛው ድርጅት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ዶክተር አረጋዊን ደግሜ መጠየቄን አስታውሳለሁ)። ይህ ሰዉ ሌላ ተከታይ ቢያጣ ለሩብ ምዕተ ዓመት አከባቢ የምኒልክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥሮ በፈላጭ ቆራጭነት ሀገሪቷን የገዛው ለገሠ ዜናዊ ስሙን አንስቶ ትግራይ በረሃ ገብቷል። ይህም ደርግ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ያመጣብን የታሪክ ዕዳ ነው።
በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳልነበራቸው በተሻለ የማውቃቸውን የመኢሶን መሪዎችን ላንሳ። ለሥልጣን ተብሎ በደርግና ብዙ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ዘንድ እንደ ኦሮሞ ድርጅት፥ በኦሮሞ ደግሞ እንደነፍጠኛ ድርጅት የሚታየው መኢሶን በዘመኑ በየትኛውም ሚዛን የተሻለ ትምህርት የነበራቸው መሪዎች ነበሩት፤ በስብጥራቸውም ኤርትራዊ የዘር ግንድ አላቸው ከሚባሉት ኅሩይ ተድላ እና አበራ የማነአብ እስከ ሲዳማው እሼቱ አራርሶ የነበሩበት ነው። ሽኩሪ የሚባል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብረን የነበርነው ልጅ በስተቀር ሰፊ ተሳትፎ እንደልነበራቸዉ የማዉቀዉ የሱማሌ ምሁራንን ብቻ ነበር።
የመጀመሪያዉ የመኢሶን ሊቀ መንበር የሰሜን ሸዋ አማራ ከሚባለው የተወለዱ፥ ዶ/ር ወርቁ ፈረደ፣ ሁለተኛው ኃይሌ ፊዳ፣ ሦስተኛው የወሎ አማራ ከሚባለው የመጡ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ነበሩ። ሕብረ ብሔር ነን፤ ለሀገረ- መንግሥት ግንባታው የተሻለ ግንዛቤም እዉቀትም አለን ለሚሉ የመኢሶን ምሁራንም ደርጎች ርህራሄ አላደረጉም። በተለይ የመጀመሪያው የኦሮሞ የምሁር ትዉልድ የሚባሉት ኃይሌ ፊዳን ጨምሮ አብዱላህ ዩሱፍ፣ ዶ/ር ከድር መሀመድ፣ ዶ/ር ተረፈ ወልደፃዲቅ፣ ዶ/ር መኮንን ጆቴ የመሳሰሉት ሕበረ ብሔር በሚባለው መኢሶን ውስጥ አልቀዋል። በእኔ እምነት ብዙዎች ሊቀየሙኝ ቢችሉም፥ እንደስማቸው በኢትዮጵያ ምድር ሕብረ ብሔር የነበሩ ድርጅቶች መኢሶንና ኢህአፓ ብቻ ነበሩ። አላስፈላጊ ክርክር ዉስጥ ሳልገባ፥ እኔ እስከ ማምነው ድረስ ኢሠፓ የወታደሮች ፓርቲ ነበር። የኢህአዴግን ምንነት ለብልጽግና አበላት እተዋለሁ። የብልጽግናን ምንነት ደግሞ የታሪክ ፈተናዉን ሲያልፍ ብንነጋገርበት የተሻለ ይመስለኛል።
ደርግ ሕበረ ብሔር ድርጅቶችን በቀላሉ አንድ በአንድ ቀርጥፎ በላቸው። ኢህአፓን ቁርስ አደረገ፤ መኢሶንን ምሳ አደረገ:: ብሔር ሆኖ ለመውጣት ገና ዳዴ የሚሉትን ወዝሊግንና ማሌሪድን እራት አደረጋቸው። ከደርግ ዱላ የተረፉት በደርግ አስተዋጽኦ ጭምር በተሸለ ሁኔታ ኃይል ሆነዉ የወጡት የብሔር ንቅናቄዎች ናቸው። ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) ወደ ኦነግ ተጠቃልሎ ገብቶ ዛሬ የምናውቀው ኦነግን ፈጠረ። የሱማሌ ድርጅቶች ኦብነግ ዓይነትን ፈጠሩ። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ቢያንስ ዋናው ክንፍ ዛሬ ሲአን (የሲዳማ አርነት ንቅናቄ) የሚለው ሆነ። አፋሮችም የአፋር ግራ ክንፍ አርዱፍ እያሉ በሕይወት ያሉ ድርጅቶች አሏቸው። በጣም የተሳካላቸው የብሔር ንቅናቄዎች በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ደርግን ለሁለት ቀብረው መንግሥታት ሆኑ።
የደረግ ዘመንን ስናጠቃልል መረሳት የሌለባቸው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች፥ ለሥልጣን ብሎ ደረግ ባካሄዳቸው ጦርነቶች፡-
የሀገረ-መንግሥት ግንባታውን የበለጠ አወሳስቦ መሄዱን፣
ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በፃፉት መጽሐፍ በትክክል እንዳስቀመጡት፥ ደርግ ትቶት የሄደው በደም እምባ የታጠበች ሀገር መሆንዋን፣
በሀገር አንድነት ስም ባካሄደው ትርጉም-የለሽ ጦርነት የባከነው የሀገር ሀብት ብቻ ሳይሆን በዓለም ትልቋ ወደብ-አልባ ሀገር ኢትዮጵያን ትቶ መሄዱን ነዉ።ደርግ ለ17 ዓመታት የተጫወተዉ የአጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካን እንደ ኑዛዜም፣ እንደ ቁጭትም የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ (ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርምም ሆነ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ እድፋቸውን ከታጠቡበት በጣም ይሻላል) በፃፉት መጽሐፍ ልዝጋ።
የኢህአፓ ወጣቶችን የትግል ስሜት፣ የመኢሶን መሪዎች ዕውቀትና የእኛን የወታደሮቹን የሀገር ወዳድነት ብንጠቀምበት ኖሮ ሀገራችን እንዲህ አትሆንም ማለታቸውን እስር ቤት ሆኜ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ምክራቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይም የሚሆን ይመስለኛል። በነገራችን ላይ በታሪክ አጋጣሚ ወደ አስር ወሮች ገደማ በኢህአዴግ እስር ቤት የተኛሁበት አልጋ ኮ/ል ፍስሃ ደስታ ይተኙበት እንደነበረ ሰምቻለሁ።
4) የኢህአዴግ ዘመን የሀገረ-መንግሥት ግንባታ
ለአራተኛ ጊዜ የሀገራችን ፖለቲካን ማሰልጠንና የተሻለ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል ያመለጠን የኢህአዴጉ ዘመን ነው (ይህ የመለስ እና የኃይለማርያም ዘመንን ይጨምራል)። የኢህአዴግ ዘመን ሌላው ቢቀር የብሔረሰቦች ጥያቄን ለሁሉም ሕዝቦች ተቀባይነት ባለው መንገድ ይመልሳል ብሎ (እኔን ጨምሮ) የጠበቁ ብዙ ናቸው። ይህም ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የተሻለ ዕድል ይፈጠራል ተብሎም ተገምቶ ነበር።
ገና የሽግግር መንግሥቱ ሲመሠረት፥ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንደግል ሠርጋቸው የፈለጉትን ጠርተው፣ ያልፈለጉትን በመተው የሠሩት የፖለቲካ ቲያትር ጫካ ሆነው ስደግፋቸው ከነበሩት የኢህአዴግ መሪዎች ተለየሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ብዙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጓደኞቼ በዚህ ጊዜ የተለዩዋቸዉ ይመስለኛል። ኢህአዴግ መጀመሪያ በጦርኛነት፤ ቀጥሎ ደግሞ በዘመኑ ቋንቋ የሽብርተኝነት ታርጋ እየለጠፈ ለ27 ዓመታት ሕዝብና ሀገርን አመሰ። ዝርዝር ነገሮች ውስጥ ሳልገባ፥ በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች፤ በሲዳማ፣ በሀዲያ፤ በወላይታ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ ቁጥራቸውን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንኳ የማያውቁት ሕይወት ጠፋ። የአፍሪካ መዲና የምትባለው አዲስ አበባ/ፊንፊኔም ሆነች የኢህአፓን ጠበል በቀመሱ ብአዴኖች የሚመራው የአማራ ክልልም ውሎ አድሮ ከኢህአዴግ ዱላ አልተረፉም።
በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም (ነገርየው መሬት ላይ ሲፈተሽ፥ የአብዮታዊነትም የዴሞክራሲያዊነትም ባህርይ አልነበረውም) የተተበተበው የሞግዚት አስተዳደር እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት ሊሆን አልቻለም። የሕዝቦችን እራስን በራስ ማስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት ያልነበረው፥ ጆርጅ ኦርዌል የእንስሳት እርሻ (George Orwell, “Animal Farm”) በሚለዉ መጽሐፉ ላይ፥ ሁሉም እንስሶች እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንስሶች የበለጠ እኩል ናቸው “All animals are equal, but some are more equal than others” ከሚለው ያለፈ የፖለቲካ ፋይዳ አልነበረውም። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተብዬዎቹም ከ97ቱ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ይቅርና ቅርጫ እንኳ ሊ ሆኑ አልቻሉም። ዉጤቱም ዴሞክራሲያዊ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል መጨናገፉ ብቻም ሳይሆን ለ27 ዓመታት ውድ የሕይወት ዋጋ ጭምር ሲያስከፍለን ኖሯል። በዚህም ምክንያት የታሪክ ጣጣችንን አስተካክለን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የመፍጠር ተስፋችን ሕልም ሆኖ ቀርቷል።
5) በማምለጥ ላይ ያለ አዲስ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ
አሁን እየገጠመን ያለውን የታሪክ ፈተናን ለማለፍ፥ ጨክነን በቁርጠኝኘት ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መግባት ወይም ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ-መንግሥት የምታበቃበት የሚጨምር ቀውስ ውስጥ መግባት ይመስለኛል። እዚህ ላይ የሌሎች ሀገሮችን ፖለቲካ በድኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን ብቻ እንኳን በመቀኛት ብጀምር፥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በቁርጠኝነት የሠሩት ተሳክቶላቸዋል። ያንን ያልቻሉት ወይ ፈርሰዋል ወይም አሁንም በቀውስ ውስጥ እየዳከሩ ነዉ። ቅኝታችንን በላቲን አሜሪካ ብንጀምር፥ ቀዉስ ገጥሟቸዉ አነ አርጀንቲና፣ ቺሌ፣ ፔሩ፣ ኒካራጓ፣ ኮሎምቢያ የመሰሰሉ ሀገሮች በተለያየ ደረጃ ፖለቲካቸውን ያስተካከሉ ሀገሮች ናቸው። ከ60 ዓመታት በላይ ለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ሳትበገር በአሜሪካ አፍንጫ ሥር የኖረችው አስደናቂዋ ሶሻሊስት ኩባና በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አሁን በሁለት ፕሬዝዳንቶች የምትገዛዋ ሶሻሊስት ቬኔዙዌላም በዚሁ ክፍለ ዓለም ይገኛሉ። በአውሮፓ ፖርቹጋል፣ ስፓኝ፣ ግሪክ፣ ፖለቲካቸዉን ማስተካከል ችለዋል። ዩጎዚላቪያ ውድ ዋጋ ብትከፍልም ከመፍረስ አልደነችም። ሶቭዬት ህበረትና (ግማሽ አውሮፓ ነች) ቼኮዝላቫኪያ በሰላማዊ መንገድ ፈርሰዋል። በኤዥያ፥ ኔፓል የፓለቲካ ችግርዋን በብሔራዊ መግባባት ስትፈታ፥ፓኪስታን፣ ቬየትናም፣ ካምቦዲያና ላኦስ ደግሞ ችግሮቻቸውን በጦርነት ፈተዋል። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን አሁንም እየቀወሱ ነው። ወደ አፍሪካችን ስንመጣ፥ ደቡብ አፍሪካና ጋና ከመሳሰሉት በስተቀር አብዘኛዎቹ በይስሙላ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ አምባገነን መንግሥታት ሲሆኑ፥ የአፍሪካ ሕብረትም የዲክታተሮች ማኅበር (trade union of dictators) ከመሆን አላለፈም (በኢህአዴግ ጊዜ የተከሰስኩበት አንዱ ወንጀሌ የአፍሪካ መሪዎችን ተሰደብክ የሚል ነበር)። ሱማሊያና ሊቢያ ፈረንጆች የወደቁ መንግሥታት (failed states) የሚሏቸው ሲሆኑ፤ ሩዋንዳ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ሌላ ቦንብ የምትጠብቅ ይመስለኛል።
በዚህ የአፍሪካ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ውስጥ አንዱ የሚገርመኝ ላለፉት 60 ዓመታት ፖለቲካቸውን ማስተካከል አቅቷቸው በቀውስ ሲናጡ የኖሩ ሁለት ሀገሮች፥ በተፈጥሮ ፀጋ እጅግ ሀብታሟ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑቢሊክና የሦስት ሺህ ዓመታት ዕድሜ አለኝ የምትለዋ ድሃዋ ኢትዮጵያ መሆናቸው ነው። ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ይህንኑ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቆቅልሾችን የተከታተለ፣ ያጠና፣ ያስተማረና ብዙ ጽሑፎችን የፃፈበት ጆን ማርካከስ (John Markakis) የሚባል ፈረንጅ፥ የታሪክና ፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሴር “Ethiopia: The Last Two Frontiers” (የኢትዮጵያ፥ የመጨረሻዎቹ ሁለት ድንበሮች) ብሎ ፅፏል። ምሳ ጋብዞኝ መፅሐፉን ለዶ/ር ዓቢይ ስጥልኝ ብሎኝ፥ ዶ/ር ዓቢይ ያንብበው አያንብበው ባላውቅም፥ እሳቸውን ማግኘት ለሚችል ለኦፒድኦ ባለሥልጣን ልኬላቸው እንደነበርም አሰታዉሰለሁ። መፅሐፉ በአጭሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የንጉሦቹ ሞዴል (the Imperial model) ፣ የደርግ የሶሻሊስት ሞዴልና የኢህአዴጉ ፌዴራሊስት ሞዴል በሙሉ ከሽፈዋል ይላል። የከሸፉበትም ዋናዉ ምክንያት የባለጊዜ ገዥዎችን ሥልጣን ለማሳካት የተገፋበት መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እኩልነት ያላጎናፀፈና የልማት ጥማታቸውንም ያላረካ በመሆኑ ነው ይላል።
ይህ የፈረንጅ ምሁር እንዳለው፥ ፖለቲካችንን ማሰልጠን ባለመቻላችን ሚሊየኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሚሊዮኖች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሚሊዮኖችም ተሰደዋል። እኔም ከላይ ባነሳሁት ከዚሁ ምሑር ዕይታ ተነስቼ ሀገራችን ስለገባችበት የፖለቲካ ቅርቃርና በብሔራዊ መግባባት አንፃር ከቅርቃሩ ለማውጣት በሌኒን ቋንቋ ምን መደረግ አለበት (What is to be done?) የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ የሀገራችን ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ ልመልስ።
- መሠረታዊ ችግራችን በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎቻችን ሀገርን የመምራት ሕልማቸው፤ ሥልጣንን ጨምድዶ ከመቆየት ሕልማቸው ጋር ሁሌ ስለሚጋጭባቸው ነው። ለሕዝብ አለን ከሚሉት ፍቅር የሥልጣን ፍቅራቸው ስለሚበልጥባቸው ነው። ለዚህ ነው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የሚወደንና (ሕዝቡ ምን ያከል እንደሚወደቸዉ እንዴት እነዳወቁ ባናዉቅም) የምንወደው ሕዝባችን ሲሉ ኖረው ለ60 ዓመታት ገደማ የገዟትን ኢትዮጵያ ለ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ሳያበቁ ከዓለም ሀገሮች ጭራ ደረጃ ትተዋት የሄዱት። የሕዝብ ፍቅራቸውንም ደረጃ በረሃብ በመቶ ሺህዎች ያለቀው የወሎ ሕዝብ ይመሰክራል። ይህን የመሳሰሉ የመሪዎቻችን ባዶ የሕዝብና የሀገር ፍቅር፥ የንጉሡ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት የመለስ ዜናዊ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገቡ ዜጎችን እፈጠራለሁ ወ.ዘ.ተ መሸፈን አይችልም። ለዚህ አሁን ያሉ መሪዎቻችንም ሆኑ ተስፈኛ መሪዎች ይህንን የታሪክ እውነታ በውል እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ።
- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የተቀሩት ልሂቃን በተለያየ ደረጃ የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን ይዘው መጓዛቸው ነው። ከመኢሶንና ኢህአፓ ዘመን እስከዛሬ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና መሪዎቻቸው ይህንን እውነታ በውል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የሕልሟን ጉዳይ በፈንጆቹ አባባል ከዜሮ ድምር ፖለቲካ (zero-sum game politics) የመውጣቱን ጉዳይና የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸዉን በገደብ የማድረጉን ነገር በጥብቅ እንዲያስቡበት እመክራለሁ። ዋና ጉዳያችን ሥልጣን ሆኖ ከፊንፊኔ እስከ መቀሌ ባንዳ፣ ባንዳ እየተባባሉ መካሰሱ ሕዝባችንን ከማደናገር በላይ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የለውም። ዛሬ በአሜሪካና በአውሮፓ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ በአንድ እጅ እስክንድር ነጋ ይፈታ፣ በሌላ እጅ ጃዋር ሽብርተኛ ነው የሚሉት መፈክር ዓይነቶቹ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታችንም ሆነ ለብሔራዊ መግባባት ሥራችን ብዙ የሚጠቅሙ አይመስሉኝም። በእኔ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ስላስቸገረኝ ነበር በ2008 በፃፍኩት መፅሐፍ ላይ ለቡዳ ፖለቲካችን መላ እንፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚጋጩ ሕልሞች ሊታረቁ ወይስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ በሚል ግልፅ ጥያቄ የደመደምኩኝ። ለእኔ መፍትኼው ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ፈጠራ የሚሆን አዲስ ማኅበራዊ ውል (new social contract) ከመፈራረም ውጭ የተሻለ የማጂክ ፎርሙላ ያለን አይመስለኝም። ይህንን እውነታ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ያሉ የብልጽግና ወንድሞቻችንም ሆኑ ከአዲስ አበባ/ፍንፍኔም እስከ አውሮፓና አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ግፋ በለው የሚሉ ሁሉ እንዲረዱልኝ አደራ እላለሁ። በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ቀውስ በሁሉም በኩል ላለቁትም የተሻለ የሐዘን መግለጫ የሚሆነውና ዕንባቸውን የሚያብሰው የችግሮቻችን ምንጭ አዉቀን ዘለቂ መፍትኼ ስንፈልግ ይመስለኛል።
- ከላይ ካነሳኋቸው ሁለት ነጥቦች ጋር ተያይዞ ሺህ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እየተባለ በሕዝብ ላይ የሚሠራዉ የፖለቲካ ትያትር መቆም አለበት።
የንጉሡ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የደርግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የኢህአዴግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ ሲያንሱ በዴሞክራሲ ስም የተቀለዱ ቀልዶች፣ ሲበዙ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተሠሩና ታሪክ ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ነበሩ። በሰለጠነው ዓለም የሕዝብን ድምፅ ከመስረቅ በላይ ወንጀል የለም። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን አስታውሼ ልለፈው። በ“ኢህአዴግ-1” ዘመን አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉትና በዝረራ ያሸንፋል” ብሎ ሲያስቸግረኝ፤ አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዞች አሉት፤ አንደኛው ምርጫ ቦርድ ነው። ሁለተኛው ጠመንጃችሁ ነው። ሁለቱን ምርኩዞቻችሁን አስቀምጣችሁ ተቃዋሚዎችን ካሸነፋችሁ፥ እኔ በግሌ እናንተ የምትሉትን 20 ና 30 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለሃምሳ ዓመታት እንድትገዙን እፈርምልሀለሁ” እንዳልኩት አሰታዉሰለሁ። በ“ኢህአዴግ-2” ጊዜ ደግሞ ዶ/ር ዓቢይ በጠሩት ድንገተኛ ስብሰባ ላይ ገለልተኛ የሆነው ጠቋሚ ኮሚቴ ስምንት ሰዎች አጣርቶ ስላቀረበ አራት ሰዎች መመረጥ ስላለባቸው በተጠቆሙት ሰዎች ላይ አስተያየት ስጡ አሉን። ሌሎች ስብሰባው ላይ የተገኙ የየድርጅት መሪዎች ያሉትን ብለዋል፤ እኔ ጨዋታው ስላላማረኝ፥ “አብዛኛዎቹን ዕጩዎች ብዙዎቻችን አናዉቃቸውምና ከየት እንደመጡ እንኳ ለማወቅ የ24 ሰዓት ጊዜ ስጡኝ” ብዬ አጥብቄ ጠየኩኝ። ዶ/ር አቢይ ‘አይቻልም’ አሉ። ነገ የምናገረው እንዳይጠፋኝና ለታሪክም ቢሆን ተአቅቦ (reservation) መዝግቡልኝ ማለቴ ትዝ ይለኛል። ምስክሮችም አሉኝ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች የምርጫ ጊዜውን ሰሌዳ ለማስተላለፍ በጠሩት የምክክር ስብሰባ ላይ እንደተናገርኩኝ፥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት (divine intervention) ነው እንዳልኩኝ ምርጫው ባይተላለፍ ኖሮ የአዲሱ ምርጫ ቦርድ አካሄድ ሌላ ከበድ ቀውስ ሊያስከትል ይችል እንደነበረ ዛሬ ላይ ሆኜ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይህንኑ ደግም ብዙ ጊዜ በታጋይነቷ ለምናውቃት ክብርት ብርቱካንም ጭምር መናገሬን አስታውሳለሁ።
ስለሆነም የሚመጣውን ምርጫ አዲስቷን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ እንድትወለድበት ካላደረግን፥ የንጉሥ የማክያቬሊ ምክር፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የጆሴፍ ስታሊን ቀይ በትር፣ የመለስ ዜናዊ፣ የሊቀ መንበር ማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውሰት፣ ኢትዮጵያን ለመለወጥ የታሪክ ፈተናውን ለማለፍ እንዳላስቻላቸዉ፥ የዶ/ር ዓቢይም የመደመር የፖለቲካ ቀመር አዛውንቱ የፈረንጅ ምሁር የሚለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጨረሻ ሁለት ድንበሮችን የሚያሻግረን አይመስለኝም። እሱን ካልተሻገርን ደግሞ ሁሌም እንደምለው ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ የምትፈጠር አይመሰልኝም።
ከማጠቃለሌ በፊት የብሔረታዊ መግባባቱ የፖለቲካ ጥረታችን ይሳካ ዘንድ መፍትሄ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮች ላስቀምጥ፦
- ያለ ሀገራዊ ስምምነት በዋናነት በአንድ ቡድን ሕልምና ፍላጎት (በተለይ የአንድ ቡድን ፍኖተ-ካርታ /road map/) የመመረቱ ጉዳይ ለዉጡን አጣብቂኝ ዉስጥ ማስገበቱን የማወቅ ጉዳይ፤
- ለውጡን ለማምጣት በዋናነት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ኃይሎች (ለምሳሌ እንደ ኦሮሞ ቄሮ ዓይነቶቹ) ወደ ዳር የመገፋታቸው ጉደይ፤
- ለውጡን እየመራ ያለው ከራሱ ከኢህአዴግ የወጣ ቡድን ቢሆንም፥ በለውጡ ምንነት፣ ፍጥነት፣ ስፋትና ጥልቀት ላይ የተለያዩ የኢህአዴግ ክንፎች ስምምነት ማጣታቸውና በዚህም ምክንያት እያመጣ ያለው አደገኛ ሁኔታ፤
- በሚጋጩ ሕልሞቻችን ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት መፍትሄ ያላገኘንለት የመከፋፈል ፖለቲካችን (political polarization) ጉዳይ፤
- ዴሞክራሲያዊ ለውጡ ለአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የፓለቲካ ኃይሎች ተቀባይነት ያለዉ፣ ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የጋራ ፍኖተ-ካርታ (roadmap) የመቀየስ አስፈላጊነት ጉዳይና፤ የተቀየሰዉን በጋራ ሥራ ላይ የማዋል ጉደይ፤
- ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማለት በእርግጥም በሕዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ጨዋታ መሆኑን የመረዳት ጉዳይ፤
- ሀገራችን እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፈድራል ሥርዓት ያስልጋታል ስንል፥ ከሕልሞቻችን በሻገር በሕዝቦቻችን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፖሊቲካ ሥርዓት መሆኑን የማረጋገጥ ጉዳይ፤
- ብሔራዊ መግባባቱ በተሻለ መንገድ የሚሳካው፥ በደቡብ አፍሪካ እና ኮሎምቢያ በመሰሰሉት ሀገሮች እንዳየነው የፖለቲካ እስረኞችንና የጫካ አማፅያንን መጨመርን የማስፈለጉ ጉዳይ፤
- የተሳካ ብሔራዊ እርቅን ለመምጣት ከሥልጣን በሻገር የምር የፖለቲካ ቁረጠኝነት (political will) የማስፈለጉ ጉዳይ፤
- ስለኢትዮጵያ አንድነት ያለን ግንዘቤ ከፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ እይታ የሰፋና ለሀገሪቷ ያለን ፍቅርም ገደብ የማድረጉ ጉደይ ናቸዉ።
በመደምደሚያዬም፥ እዚህ ያደረሰንን የሀገራችንን ፖለቲካ ጉዞ ታሪክ ወደኋላ እያየሁ፥ የወደፊቱን የሀገራችንን ዕጣ ፈንታንም እያማተርኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለሁላችንም የታሪክ የግርጌ ማስታወሻ ልተዉ።
በቅርብ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን የሚያፈርሷት እኛን ቀድሞ ሲያፈርሱ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይፈቀድላቸውም’ ሲሉ አዳምጫለሁ። ሀገርን ለመፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች መጀመሪያኑ ፈቃድ ይጠይቃሉ፤ አይጠይቁም የሚለዉን ክርክር ውስጥ ሳልገባ፥ በጨዋ ቋንቋ ንግግራቸውን አልወደድኩላቸውም። ንግግራቸውንም ተከትሎ የኢሳት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ተንታኞች የሚታወቁ የአዛውንት ምሁርን በመጥቀስ (ይህኑን ምሁር መንግሥቱ ሀይለማርያምም ያዉቃል ብለን ስለተሠሩ የንጉሡ ባለስልጣኖች ምክር ጠይቀነዉ፥ ጠመንጃዉ በእናንተ እጅ ነዉ፤ የምን ምክር ትጠይቁናላችሁ ብሎኛል ማለቱን አንብቤአለሁ) ዶ/ር ዓቢይ ጥሩ ይዘዋል፤ ሕጉንም ሰይፉንም እየተጠቀሙ ነው ያሉት የበለጠ ሥጋት ፈጥሮብኛል። እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁላችንም ደጋግመን ማሰብ ያለብን ጨዋታው ከተበላሸ አብዛኛው ዓለምን በሰዓታት ውስጥ ወደ አመድነት የሚለወጥ ወይም ሕይወት-አልባ ሊያደርግ የሚችል የኒዩክሊየርር መሣርያ የታጠቀ፣ ነፍሷን ይማርና የሶቭዬት ህብረት ሠራዊት ዓይኑ እያየ ሀገራቸው መበቷን ነው። የሀገራችንን ፖለቲካ በጋራ አስተካክለን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ።
ዋቢ መፃሕፍት:
- Bahiru Zewde (1991) A History of Modern Ethiopia, 1885 -1991.
- Gebru Tareke (1996) Ethiopia: Power and Protest, Peasant Revolts in the Twentieth Century.
- John Markakis, (2011) Ethiopia: The Last Two Frontiers.
- Merera Gudina, (2002) Ethiopia: Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy, 1960-2000.
- Teshale Tibebu, (1995), The Making of Modern Ethiopia, 1896-1974.
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
August 19, 2020 at 12:07 pm #15482In reply to: ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveየማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ አስር የማዕድን ምርመራ እና ሁለት የማዕድን ምርት ፈቃዶችን ሰጥቷል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የማዕድናት ፍለጋ እና ልማት ለማካሄድ ፈቃድ ለጠየቁና የፈቃድ መውሰጃ መስፈርቶችን አሟልተው ለቀረቡ ለ12 የማዕድን ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰጥቷል። ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ሲሆኑ አስሩ የምርመራ ፈቃዶች ናቸው።
የምርት ፈቃድ የተሰጣቸው የባዛልት እና የዕምነበረድ ማዕድን ምርት ሲሆኑ ሌሎች አስር ኩባንያዎች ደግሞ በደለል ወርቅ፣ ወርቅ እና መሰል ማዕድናት፣ ብረት፣ ማንጋኔዝ፣ ክሮማይት፣ ብር እና ጀምስቶን ማዕድናት ምርመራዎች ናቸው።
ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ለኢንቨስትመንት 270,186,310.00 (ሁለት መቶ ሰባ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ ሶስት መቶ አስር) ብር የተመዘገበ ካፒታልና ለ187 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲሆን፥ የምርመራ ፈቃዶች ደግሞ 131,935,555.00 ብር (አንድ መቶ ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ መቶ ሰላሳ አምስት ሽህ ዘጠኝ አምስት መቶ አምሳ አምስት) ብር የተመዘገበ ካፒታል እና በምርመራ ወቅት በድምሩ ለ293 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ምርመራ ሂደታቸውን በስኬት አጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡም ከሥራ ዕድል ፈጠራ እስከ ውጭ ምንዛሬ ግኝትና ማዳን ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።
የምርመራ ፈቃዱ የውሉ ስምምነት ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ እንደ የፍቃድ ዓይነት ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት የሚፀና ሆኖ፥ የፈቃድ ዘመኑም ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረትና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲያምንበት ሊታደስ የሚችል ነው።
ስምምነቱን በፈቃድ ሰጪው መሥሪያ ቤት በኩል የፈረሙት ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ (የማዕድን ዘርፍ) ሲሆኑ፥ በባለፈቃዶቹ በኩል የፈቃድ ወሳጅ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ለወጠነችው የኢንዱስትሪያዊነት መዋቅራዊ ሽግግር የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈልገውን የማዕድናት ግብዓት ለሟሟላት በሁሉም ዓይነት የዘርፉ ሃብቶቻችን ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል።
ዛሬ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች የምርትም ሆነ የምርመራ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በፌደራልና በክልል የማዕድን አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን መሠረት አድርጎ በጥንቃቄ በትጋትና ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ በማዕድን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተቀባይነት ባለው የአሠራር ዘዴ ለማከናወን በስምምነቱ ውስጥ የተካተተ ሲሆን፥ ተመጣጣኝ ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ቅድሚያ የሥራ ዕድል ለመስጠትና ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን ሥልጠና የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
የአካካቢ ጥበቃን (environmental protection) በተመለከተ የሠራተኞቹን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጤንነትና ደህንነት በማይጎዳና ብክለት በማያስከትል መልኩ የምርት ሥራውን ለማከናወን ውል የተፈፀመ ሲሆን፥ ሥራውን ሲያቋርጥ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ፣ በሰው ሕይወትና ንብረት እንዲሁም ዕፅዋት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ማናቸውም ቅሪቶችና ግንባታዎችን ያስወግዳል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የፕሮጀክቶችን ውልና አፈጻጸም በየጊዜው እየገመገመ በገቡት ውል መሰረት ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑትን የመደገፍና የማበረታታት፣ በውላቸው መሠረት የማይሠሩትን ደግሞ ፍቃድ የመሰረዝና ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዜና ሳንወጣ፥ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዕለቱ አስር ሹመቶችን በሰጡበት ጊዜ፥ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሁነው ተሹመዋል። በዕለቱ የተሰጡት አስር ሹመቶች የሚከተሉት ናቸው።
- ዶ/ር ቀንዓ ያደታ – የመከላከያ ሚኒስትር
- ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
- ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
- ኢንጂነር ታከለ ኡማ – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር
- አቶ ተስፋዬ ዳባ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
- አቶ ዮሐንስ ቧያለው – የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
- አቶ ንጉሡ ጥላሁን – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር
- አቶ እንደአወቅ አብቴ – የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር
- አቶ ፍቃዱ ጸጋ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
- ፕ/ር ሂሩት ወልደማርያም – በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ በመሆን መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅሕፈት ቤት አስታውቋል።
August 16, 2020 at 2:25 am #15429In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveየቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክት ግንባታ ደረጃ 84 በመቶ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ – በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተገነባ ያለውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት /Innovation and Technology Talent Development Institute/ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፌደራልና የክልል ቢሮ አመራሮች ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጎብኝተውታል። ከጉብኝቱ በተጨማሪም አመራሮቹ የአረንጓዴ አሻራቸውን በማዕከሉ ቅጥር ግቢም አኑረዋል።
እንደ የኢኖቬሽን ልማትና ምርምር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ክቡር አቶ ሲሳይ ቶላ ፕሮጀክቱ ባለፉ ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ምክንያቶች መዘግየት አጋጥሞት ነበር። በአሁኑ ወቅት በተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ በተጠናከረ አመራርና ድጋፍ በማጠናቀቅ በ2013 ዓ.ም. ሁለተኛ ሩብ ዓመት መጀመሪያ ወራት ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ለአካባቢው ማኀበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር በሀገራችን የሚገኙ ባለተሰጥኦዎችን አሰባስቦ ተሰጥኦዋቸውን በማጎልበት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩበት ስለሆነ፥ መላ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉትና እንዲሳተፉበት ጥሪ አቅርበዋል። ያለፉ ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ለውጥ ሂደቶች የተነሳ ያጋጠሙ መዘግየቶችን በቀሪ ወራት አካክሶ ሥራ ለማስጀመር የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅም ተመድቦለታል።
ክቡር አቶ ሲሳይ አክለውም ለዓመታት ያጋጠመ የመዘግየት ችግር ተካክሶ በሦስት ወራት ውስጥ አመርቂ የግንባታ ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል። በቀጣይም በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉና መሟላት የሚገባቸው ግብዓቶችን ከግንባታው ጎን ለጎን እየተሟሉ ይገኛል። ለስልጠናና ትምህርት እንዲሁም ተሰጥኦ ማፍለቅና ትግበራ የሚውሉ የቁሳቁስ እገዛና ድጋፍ ከልዩ ልዩ አካላት መገኘት ጀምሯል ያሉት ክቡር አቶ ሲሳይ፥ በቀጣይ የግሉ ዘርፍ፣ ሀገር-አቀፍና ዓለም-አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ልዩ ልዩ ተቋማት እና የመንግሥት አካላትን ትብብር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን ብለዋል።
የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ሥራ ሲጀምር በየደረጃው ካሉ አመራሮች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እንደሚጠበቅ አውስተው፥ ተቋሙ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካና ዘላቂነት እንዲኖረው የአሠራር መመሪያዎችን፣ የትብብር ማዕቀፎችን፣ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትን፣ የተውህቦና የክህሎት መለያ መስፈርቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ቀድሞ የማዘጋጀት ሥራ ከወዲሁ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ለዚህ ሀገራዊ ማዕከል መገንቢያ ቦታ በመስጠት፣ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ክስተቶች ወቅት የተጀመሩ ግንባታዎችና ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላደረጉ የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል። ባለተሰጥኦዎችም ወደፊት ወደተቋሙ መጥተው በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን እገዛና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ሁሉ ትብብራቸው እንዳይቋረጥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ተቋሙን ሥራ ማስጀመር የሚያስችሉትን የግንባታ ሥራዎችን ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንዲቻል በተሰጠ አመራር እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የግንባታ ሥራ ተቋራጩ ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር መስፍን ባልቻ ናቸው። እንደ ኢ/ር መስፍን የቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ ወርክሾፖች፣ የመማሪያ ክፍል እና የማደሪያ ሕንጻዎችን በልዩ ትኩረት ተገንብተው ከ78% እስከ 90% የአፈጻጸም ደረጃዎች ማድረስ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ያለበት አማካይ የአፈጻጸም ደረጃ ከ84% በላይ ነው። ቀሪ የሲቪል ሥራዎችን በማጠናቀቅ የቁሳቁስ ገጠማና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ ለማጠናቀቅ እየተሠራ በመሆኑ በቀጣይ ሦስትና አራት ወራት ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል ብለዋል።
የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ግንባታ ከሦስት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በተሰጠ አምስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በተያዘ የመንግሥት በጀት የተጀመረ ነው። ከመላው ኢትዮጵያ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል እስከ 1000 ባለተሰጥኦዎችን መልምሎና ተቀብሎ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለግን ተሰጥኦዋቸውን በማልማት፣ በማጎልበትና ወደ ተጨባጭ አምራችነት በመቀየር ለሀገራዊ ብልጽግና መሠረት መጣል የሚችል ተቋም መሆኑን መግለጻችን ይታወቃል።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
August 13, 2020 at 11:53 am #15396In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterበአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት የታዩ ክፍተቶች አፋጣኝ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ‹COVID-19› በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 3/2012 ማወጁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀ ወዲህ በመላው ሀገሪቱ ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ ካለመሆኑም በላይ የቫይረሱን ስፋት እና የስርጭት መጠን መሠረት በማድረግ በየጊዜው በአስፈጻሚው አካል የሚወጡ መመሪያዎችም በጥናት ያልተደገፉ እና ለሕግ አስከባሪው ኃይል የተለጠጠ የማስፈጸም ሥልጣን የሚሰጡ ሆነው ታይተዋል። በዚህም ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር ሳምንታት የታዩት የዐዋጁ አፈጻጸም ሂደቶችም ሆኑ የመመሪያ አወጣጥ ሂደቱ ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በጽኑ ያምናል።
ዓለም-አቀፉ የጤና ድርጅት እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስን አስመልክተው በየጊዜው ይፋ ከሚያደርጓቸው መግለጫዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ቫይረሱ ገና በቅጡ ተጠንቶ ያልታወቀ ተለዋዋጭ ባሕርይ ያለው መሆኑ ነው። ከዚህ የተነሣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንዲያስችሉን የምንወስዳቸው እርምጃዎች በበቂ ጥናት ላይ የተመረኮዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከታወቀበት ጊዜ አንሥቶ ፍ/ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው መቆየታቸው የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲገደብ ከማድረጉ በላይ ጉዳያቸው በአፋጣኝ ታይቶ በነጻ መሰናበት እንዲሁም በዋስ መለቀቅ የሚችሉ ዜጎች ያለ አግባበብ በእሥር እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል። በዚሁ ምክንያት አንዳንድ ማረፊያ ቤቶች በመጨናነቃቸው ዜጎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ሆነዋል።
የዐዋጁ አፈጻጸም ሲገመገም የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ ከማንኛውም ጥቃት ነጻ-የመሆን፣ ፍትሕ የማግኘት፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ ያልተመጣጠነ ገደብ ያስቀመጠ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ በጥብቅ ያምናል። ከዚህም በተጓዳኝ በቀጥታ በዐዋጁ ምክንያት ባይሆንም፤ የቫይረሱ መስፋፋት ባስከተላቸው ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የተነሳ በጤና ባለሙያዎች፣ በሴቶች እና ሕጻናት፣ እንዲሁም በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ላይ ዓይነተ-ብዙ የመብት ጥሰቶች እየደረሱ በመሆኑ ትኩረት እና መፍትሔ የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ ያምናል። እንዲሁም በዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት እና በአጠቃላይ ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ከታዩት ጉልህ የመብት ጥሰቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
በትግራይ ክልል ናዕዴር ዓዴት ወረዳ ቀደም ብሎ በክልሉ ታውጆ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማስከበር በሚል አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም መቐለ ከተማ ሰሜን ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው 05 ቀበሌ አካባቢ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሕክምና ላይ ናቸው። በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አንድ የባጃጅ ሹፌር በጸጥታ ኃይሎች በተፈጸመበት ጥቃት አንድ እጁ ላይ በጥይት ጉዳት ደርሶበታል።
በተለያዩ አካባቢዎች “የአፍ መሸፈኛ ጭምብል አላደረጋችሁም” በሚል ምክንያት ፖሊስ ተመጣጣኝ ባልሆነ እርምጃ በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልት እና ለቫይረሱ አጋላጭ በሆነ መንገድ የጅምላ እስር ፈጽሟል። “ዐዋጁን ተላልፈዋል” በሚል ምክንያት ንግድ ቤቶች የሚታሸጉበት እና በሰዓት ገደብ እንዲዘጉ የሚደረጉበት ሂደት አንድ ወጥ አለመሆኑ አድሎአዊ እና ሕገ-ወጥ ለሆነ አፈጻጸም አጋልጧል።
ቫይረሱን ግንባር-ቀደም ሆነው እየተከላከሉ ላሉት የጤና ባለሙያዎች በቂ ራስን የመከላከያ ግብዓቶች እየቀረቡ ባለመሆኑ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እንዲሰሩ በመደረጋቸው ለቫይረሱም ተጋላጭ ሆነዋል። በጤና ሚንስቴር ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሠረት እስከአሁን ድረስ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋም ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። “ንክኪ አላቸው” በሚል በየጊዜው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚደረጉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ነው።
በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሀገር ውስጥ በረራ ሊያደርጉ የነበሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች “ዓለም-አቀፍ በረራ አድርጋችኋል” በሚል ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለአስራ ስድስት ቀናት ያህል እንዲገቡ፣ ለተወሰኑ ቀናትም ቤተሰብ ያሉበትን እንዳያውቅ ተደርጓል። ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም የቫይረሱን መከላከያ ሥራዎች ሽፋን በማድረግ በአባላትና አመራሮቻቸው ላይ ልዩ ልዩ ተጽዕኖዎች እየደረሱባቸው ነው። ለአብነት፥ ወደ ደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ ለቤተሰባዊ ጉዳይ የሄዱትን አንድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አባል ወደ ከተማዋ ለሚገቡ ሌሎች ሰዎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ በማይሆን አሰራር ከግንቦት 9 – 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ ተለቀዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ፖሊስ ጣልቃ በመግባት እንዲቆም ተደርጓል።
የቫይረሱ ስርጭት ባስከተለው ተጽዕኖ የዜጎች የሥራ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ከመውደቁም በላይ፥ አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኞቻቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ እና አስገዳጅ ፈቃድ ያለክፍያ እንዲወጡ ተደርጓል።
የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ይፋ ባደረገው መረጃ በተለይም በጅቡቲ በኩል የሚገቡ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከሚደርስባቸው መገለል በተጨማሪ በአንዳንድ ከተሞች የማደሪያ እና የምግብ አገልግሎት እንዳያገኙ፣ መኪና እንዳያቆሙ ክልክላ ይደረግባቸዋል።
መንግሥት ቀዳሚ ትኩረቱን በሽታውን በመከላከል እና ተያያዥ ሥራዎች በማድረጉ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን የመሳሰሉት ልማዳዊ ጎጂ ድርጊቶች እየተበራከቱ እና እየተስፋፉ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ብቻ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 101 ያህል ህጻናት የመደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም መሰል የመብት ጥሰቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በመሆኑም፥ ዐዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እና በየደረጃው ያለው ግብረ-ኃይል ለእነዚህ የመብት ጥሰቶች እና የአፈጻጸም ችግሮች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ በትኩረት እንዲሠራ ኢሰመጉ ያሳስባል። መንግሥት በዐዋጁ አፈጻጸም ምክንያት ሊጎዱ ለሚችሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች፣ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እርዳታ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ቫይረሱን ከፊት ሆነው እየተከላከሉ ላሉ የሀገራችን የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ አሁን ካለበትም ደረጃ የከፋ የሚሆንበትም ጊዜ ሳይጠበቅ አስፈላጊ የሆነውን ራስን የመከላከያ ግብዓት በበቂ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲያገኙ መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ሕክምና ላይ የሚገኙ ዜጎች የምግብ አገልግሎት፣ የመኖሪያ እና የንፅህና መስጫ ስፍራ ጽዳት፣ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን ጨምሮ የሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦትና የመሳሰሉ የአገልግሎት ችግሮች መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው መንግሥት በትኩረት ችግሮቹን እንዲያስተካከል ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል። በየጊዜው ዐዋጁን በመተላለፍ ተይዘው እንደ ትምህርት ቤት ባሉ መሠረተ ልማቶች ውስጥ የታሰሩ ዜጎች የሚቆዩበት ሥፍራ እንደ ምግብ፣ አልጋ፣ መጸዳጃና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ለመስጠት በሚያስችል መልኩ መደራጀታቸውን እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ያሳስባል።
በዐዋጁ ድንጋጌ መሠረት የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት ተዘግተው ተማሪዎች እና መምህራን በአካል ተገናኝተው ትምህርት የሚሰጥበት ሂደት ተቋርጧል። ሆኖም ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው ትምህርት እንዲከታተሉ እየተደረገበት ያለው መንገድ ጥራቱን በጠበቀ፣ ተማሪዎች ትምህረቱን ለማስተላለፍ የሚረዱትን ነገሮች የማግኘት አቅማቸውን ታሳቢ ያደረገ እና የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን ፍትሐዊ እድል ለመስጠት በሚያስችል መልኩ እንዲሰጡ መንግሥት እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርማሪ ቦርድም ሁኔታዎቹን በየጊዜው እየተከታተለ፣ በዐዋጁ ይዘት እና አፈጻጸም ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን በአግባቡ እንዲስተካከሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን። መንግሥት ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን አስመልክቶ በየደረጃው የሚሠሩ ሥራዎች ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ እና የሲቪል ማኅበረሰቡንም ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።
ከዚህ በኋላ የሚወጡ መመሪያዎች የበሽታውን ባህርይ ታሳቢ ያደረጉ፣ በበቂ ጥናት እና መረጃ ላይ የተመሠረቱ፣ ለሕግ አስከባሪ ኃይሎች የሚሰጡት ሥልጣን ውስን እንዲሆን፣ ብሎም ክልከላ የተደረገባቸውን ነገሮች በግልጽ የሚያመላክቱ እንዲሆን ኢሰመጉ በጥብቅ ያሳስባል። ዐዋጁን በማስፈጸም ወቅት የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ሚና የጤና ባለሙያዎችን የማገዝ እንዲሆን ቅጣት እንኳን አስፈላጊ ቢሆን ሕይወትን የማዳን ዓላማ እንጂ የባሰ አደጋ ውስጥ በማይከት ሁኔታ መሆን ስለሚገባው፤ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ የሚያሳስብ ድንጋጌ በያዘ መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኢሰመጉ ያሳስባል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉ የመሬት ወረራን ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ የሕግ ማስከበርና የቤት ማፍረስ እርምጃዎች ያለንበት ወቅት ክረምት እንደመሆኑ እና ዜጎችን ለበሽታውም ስርጭት የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ በጥንቃቄ እና ወጥነት ባለው እንዲታዩ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!
ምንጭ፦ ኢሰመጉ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ 1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር ከ404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት መስከረም 29 ቀን 1984 ዓ.ም. በአባላት የተመሠረተ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ ተሟጋች ተቋም ነው።August 3, 2020 at 2:22 am #15267AnonymousInactiveጤናችን በእጃችን! ― 1.2 ሚሊዮን ሰዎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚከላከል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ – በግል የንግድ ዘርፍ፣ በመንግሥት እና በመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተመሠረተው ጥምረት ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ለሚቀጥሉት ቀጣይ ወራት የሚሠራ እና እስከ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ሊኖረው የሚችል <ጤናችን በእጃችን!> የተሰኘው ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ። ፕሮጀክቱ የውሃ፣ የሳሙና እና ሌሎች ተመሳሳይ ተግዳሮቶች እጥረት የሚያጋጥማችውን እና በጣም ጥቅጥቅ ያሉ የመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችን ለማገዝ ብሎም ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ የሚያስችል ይሆናል።
የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት አምራች ኩባንያዎች በፕሮጀክቱ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ውስጥ ትርፍን መሰርት ያላደረገ ሥራ ለመሥራት እና ሠራተኞቻቸውን በሥራ መደብ ላይ ለማቆየት ተስማምተዋል። ይህንን ለማካካስ ጥምረቱ ለተሳታፊ ኩባንያዎች ወሳኝ ከሆኑ ጥሬ ዕቃዎች እና ከማምረት ጋር ለተያያዙ የክንዋኔ ወጪዎችን የሚሸፍን ይሆናል።
ጤናችን በእጃችን! ፕሮጀክት በይፋ መጀመርን ተከትሎ ይህ አዲስ ጥምረት የፊት ጭምብሎችን እና ሳሙናዎችን የማምረት እና ማሠራጨት፣ የውሃ ገንዳዎችን መትከል፣ ብሎም የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ለውጥ ፈጣሪ ትምህርቶችን ለ1.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ከፍተኛ ተጋላጭ ተበለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከል ሥራን በሚያጠናክር መልኩ የሚያደርስ ይሆናል።
ዳልበርግ ግሩፕ (Dalberg Group) እና ሮሃ ግሩፕ (Roha Group) የተባሉ የግል ድርጅቶች ተነሳሽነት በመውሰድ በሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የወረርሽኝ የመከላከል ብሔራዊ ምላሽ ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የግል እና የመንግሥት ተቋማት በጋራ በማደራጀት ወደ ሥራ ገብተዋል። የፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜ የሚያስፈልገውን 1 ሚሊዮን ዶላር በሮሃ ግሩፕ በኩል የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው 5 ሚሊዮን ዶላር ከለጋሽ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሰበሰብ ይሆናል። ጥምረቱ የንፅህና መጠበቂያ የሆኑ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ማምረትና በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማከፋፈል በዓይነቱ ለየት ያለ የንግድ ሥራ ሞዴሎችንም ማስተዋወቅ ችሏል።
መንግሥት በበኩሉ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለፕሮጀክቱ የሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስን ያነሳ ሲሆን፥ ዓላማውም የግል ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝላይ ለሚደረገው የመከላከል ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ለማስቻል ነው።
ፕሮጀክቱ እስካሁን ድረስ 15 የሚሆኑ ሀገር በቀል በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ አነጋግሯል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Children) በጎ አድራጊ ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ውስጥ ብሎክን መሠረት ያደረገ የማኅበረሰብ አደረጃጀት ኤጀንሲ በከተማው ውስጥ የሚገኙ 24,934 አካባቢዎችን በመለየት የሚገኙበትን ጊዜያዊ ሁኔታ መረጃ ሰብስቦ አዘጋጅቷል። በተጨማሪም በ10 ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ 121 ወረዳዎች ውስጥ 1,357 የተደራጁ ማዕከላትን በመጠቀም የፊት ጭንብሎችን እና ሳሙናዎችን ለከፍተኛ ተጋላጭ ተበለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚያከፋፍል ይሆናል።
በተጨማሪም ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Children) ለጥምረቱ የቴክኒክ ድጋፍ፣ መመሪያ እና የሕብረተሰቡ ተሳትፎን በተመለከተ ድጋፍ ይሰጣል። የሚሠራጨው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፀደቁ የእጅ መታጠብ፣ የፊት ጭንብል መልበስ እና አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚመለከቱ መልዕክቶችን ያካትታል። የሠራተኞቹን እና የሕብረተሰብ አካላትን ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ ከ260 በላይ የክፍለ ከተማና የወረዳ ቡድን አመራሮችም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
በተያያዘም ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ሙሉ በሙሉ ከመጀመሩ በፊት የፈንድ አስተዳደርና የሥራ ሂደት ለመቆጣጠር የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ለመገምገም ከጥምረቱ ጋር አብሮ የሚሠራ ይሆናል።
“የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማኅበረሰባችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የበኩላችንን ማድረግ በመቻላችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል። ጥምረቱን የተቀላቀሉና ኃላፊነታቸውን በመወጣት አዳዲስ መፍትሄዎችን በማምጣት ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ አብረውን እየሠሩ ያሉትን አጋሮቻችንን እናመሰግናለን” ብለው የጥምረቱ መሥራቾች ተናግረዋል።
አክለውም ይህ ጥምረት ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚያስፈልገውን ቁሳቁሶች ብሎም የባህሪ ለውጥ ትምህርት ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን፥ ሌሎችም በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ተቋማት ይህን ጥምረት በመቀላቀል የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።
ፍሰሃ አለማየሁ የፍሪ ዞን ኢንተርናሽናል (Free Zone International) ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው “የጥምረቱ አባል በመሆናችን የማምረት ሥራችን ሳይስተጓጎል በ ሀ ገራችን ውስጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል እንቅስቃሴ እንድንደግፍ አስችሎናል” ብለው ተናግረዋል።
ጤናችን በእጃችን!
ጤናችን በእጃችን! በዳልበርግ ግሩፕ እና በሮሃ ግሩፕ የተመሰረት የግል እና የመንግሥት ተቋማትን አንድ ላይ የያዘ ጥምረት ነው። በሀገራችን የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ላይ ለውጥ ለማምጣት ሁለቱ ኩባንያዎች የግሉ ሴክተር አቅምን እና ብቃቶችን ለማደራጀት ተነሳሽነት ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል።፡
ጥምረቱ ተጋላጭ የሆኑትን የሕብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ባሉበት ቦታ መፍትሄ ለማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በከፍተኛ አደጋ ላይ ከሚገኙ ንዑስ ምድቦች በተጨማሪ የህብረተሰባችንን ኢኮኖሚያዊ ጤና ለማረጋገጥ አካል የሆኑት የንግድ ድርጅቶችም የዚህ ጥምረት ትኩረት ናቸው። ስለሆነም ጤናችን በእጃችን! የተሰኘው ፕሮጀክት ከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን የሚረዱ አስፈላጊ የንፅህና እና የመከላከያ ምርቶችን በማምረት እና በማሠራጨት ረገድ ልዩ የንግድ ሥራ ሞዴል በማስተዋወቅ የንግድ ተቋማት ይህ አስጨናቂ ጊዜ የፈጠረውን የገበያ እጦት ለመቋቋም የሚያስችላቸው መንገዶችን በማዘጋጀት የንግድ ድርጅቶች ወጪያቸውን ለመሸፈን እና ሠራተኞቻቸውን ለማቆየት የሚያስችል ይሆናል። https://www.tenachinbejachin.org
[caption id="attachment_15265" align="aligncenter" width="600"] ጤናችን በእጃችን! (Tenachin Bejachin!) Initiative[/caption]
August 2, 2020 at 1:41 am #15252SemonegnaKeymasterየኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ስርጭት እጅግ ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል። የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀቡ ይስተዋላል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰብሳቢነት ሥራውን የሚከውነው እና ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን የሚያስተባብረው የሚኒስቴሮች ኮሚቴ፥ ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በወቅታዊው ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። የጤና ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አካሄድ በተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፥ እስከ አሁን [ሃምሌ 25 ቀን] ድረስ በኢትዮጵያ 17,500 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል፣ 84 በመቶው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን፣ ከመመርመራቸው በፊት በቫይረሱ የመያዝ ምልክቶች አልታዩባቸውም። ይህም ምልክት ሳይታይባቸው ቫይረሱን የሚያስተላልፉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ያመላክታል።
የትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ትምህርት ሁኔታዎችን መረጃ አጠቃልሎ አቅርቧል። በዚህም መሠረት፥ ትምህርት ቤቶች [በ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን] ተመልሰው ከመከፈታቸው በፊት ሊተኮርባቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አመላክተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የቫይረሱ የስርጭት መጠን መቀነስ ዋነኛው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምርመራ መጠንን ከፍ ማድረግ የወረርሽኙን አካሄድ ለመረዳት ወሳኝ ተግባር መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል። ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ እንዲካሄድም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ADDIS ABABA (Semonegna) – The Office of Prime Minister – Ethiopia issued a press statement on 1st August 2020 stating that the country will carry out nationwide mass testing of COVID-19 for one month amid the surge of COVID-19 cases in the country, especially in recent weeks. The press statement reads as follows.
Over the past couple of weeks there has been a noticeable increase in the number of positive COVID-19 cases. The ministerial committee overseeing prevention activities and chaired by Prime Minister Abiy Ahmed, met this afternoon to discuss the current status, where the Ministers of Health and Education presented on the international and domestic trends of the pandemic.
According to Ministry of Health reports, there are currently 17,500 positive COVID-19 cases confirmed [in the country] as of date with 70% located in Addis Ababa. While 84% of positive cases are above the age of 50 years, 92% of positive cases showed no symptoms prior to testing, which indicates the presence of many silent spreaders.
The Minister for Education, combining data for primary, secondary and tertiary education, highlighted that a number of issues need to be factored before considering opening schools [for the coming academic year], with declining rate of cases being the key number one factor to enable an opening decision.
Prime Minister Abiy Ahmed emphasized the critical importance of increased testing to understand the trends better for effective decision making, and gave direction for the launch of a one-month nationwide mass testing.
July 26, 2020 at 1:36 am #15191In reply to: ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
SemonegnaKeymasterአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።
ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 21, 2020 at 1:38 am #15139In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ900 ተማሪዎች የትምህርት መከታተያ ሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ድጋፍ አደረገሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በመጪው የትምህርት ዘመን በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፀጋዬ ደዮ በተቋሙ በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ላይ እንዳሉት፥ በ2013 የትምህርት ዘመን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዘኛ ቋንቋና ሥነ-ልሳን በተጨማሪ በሶሻል አንትሮፖሎጂ (social anthropology) ዘርፍ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል።
እንዲሁም በጤና ሣይንስ ኮሌጅ የትምህርት ዘርፍ በሥነ ተዋልዶ፣ ሥነ ምግብ፣ ማኅበረሰብ ጤና፣ እናቶችና ሕፃናት ጤና የትምህርት ዘርፎች እንደሚከፈቱም አስታውቀዋል።
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በሚጀምራቸው ዘጠኝ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በእያንዳንዱ የትምህርት ዘርፍ እስከ 15 የሚደርሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርና ይህም ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ ለውጥ መሆኑን ዶ/ር ፀጋዬ ገልጸዋል።
የትምህርቱ ዓላማ ዩኒቨርሲቲው አቅምና ዕውቀትን ከማጐልበትና ከማሻገር በተጓዳኝ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ ለማመቻቸት ነው ብለዋል። በተለይ በትምህርት ጥራት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንዲወገዱ የትምህርት መርሃ ግብሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የውጭ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶ/ር የሺመቤት ቦጋለ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ለሚጀምረው የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በቂ የሰው ኃይልና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። መረሃ ግብሩ በትምህርት ተግባቦት ቴክኖሎጂ በቤተ ሙከራዎችና በኢንተርኔት በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተ መጽሕፍትን አደራጅተናል ብለዋል።
የሚጀምረው መረሃ ግብር የተቋሙ መምህራንና ተማሪዎች አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የኦሮምኛ ቋንቋ ዲፓርትመንት ኃላፊ ወ/ት ሁርሜ ደገፋ ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለአንድ ቀን በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው ከ100 በላይ መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች ተካፍለዋል።
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም. ከተቋቋመ ጀምሮ በ33 የትምህርት ዘርፎች ከ4 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱም ተመልክቷል።
ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን በሬዲዮ በመከታተል ላይ ለሚገኙ 900 ተማሪዎች የሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ድጋፍ አደረገ። ድጋፉ ከ700ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ 500 ሬዲዮኖችና 400 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች ናቸው።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት እንደገለጹት፥ ድጋፉ በመቀበያ ችግር ምክንያት የሬድዮ ትምህርት ፕሮግራም መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ድጋፉ የተደረገላቸው መቀሌን ጨምሮ በአምስት የክልሉ ወረዳዎች የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች እንደሆኑ አመልክተው፥ በየቤታቸው ትምህርታቸውን በሬዲዮ ለመከታተል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይቋረጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል – ፕ/ር ክንደያ። ተማሪዎች በሬድዮ የሚተላለፍ ትምህርት በመከታተል ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ፕ/ር ክንደያ አስረድተዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፥ የተደረገው ድጋፍ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። ከዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አይነስውሩ አለም ተስፋዬ በሰጠው አስተያየት የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት መርሃ ግብሩ በተጨማሪ ወቅታዊ የዓለማችን ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችለን ነው ብሏል። በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ድጋፍ ማድረግ ሰብአዊና ዜግነታዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።
July 16, 2020 at 12:05 pm #15097In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveየከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ተሰጥቷቸው የዓመቱን ትምህርት ያጠናቅቃሉ ― የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።
የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አጋማሽ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) በመከሰቱና በፍጥነት በመዛመቱ ምክንያት የዓለም ሀገራት የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተቋርጦ መንግሥታት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ቅድሚያ ሰጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
እንደሚታወቀው ቫይረሱ ወደሀገራችን መግባቱ በምርመራ ከተረጋገጠበት ጀምሮ የሀገራችን መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ እየሠራ ይገኛል። በዚሁ መሠረት የቫይረሱን መስፋፋት ለመቀነስ ሲባል የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የገጽ-ለገጽ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ይታወሳል። ሆኖም ባሉበት ሆነው ከትምህርትና ንባብ እንዳይርቁ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።
የትምህርትና ስልጠና ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ከትምህርትና ስልጠና ተቋማት መከፈት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እያነሱ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተዘጋጅቷል።
አሁን ባለው ሁኔታ ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረው የኦንላይን ትምህርት የሚቀጥል ሆኖ፥ ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ ሌሎች መንገዶችንም በቀጣይ የሚታዩ ይሆናል። ለዚህም ሁሉም ዜጎች የቫይረሱን መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ መሥራት ያስፈልጋል። ስለዚህ ተማሪዎችና መምህራን ባሉበት ሆነው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ሌሎችንም እንዲያስተምሩ ይጠበቃል። ያም ሲሆን የስርጭት መጠኑ ሲቀንስ ቀጣይ የትምህርትና ስልጠና አካሄዶችን ይፋ የምናደርግ ይሆናል።
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የለይቶ ማቆያና ምርመራ ማዕከላት በመሆን በማገልገል ላይ ሲሆኑ፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ እንዲሁም መጠነ ሰፊ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት እያገዙም ይገኛሉ። ስለሆነም ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም የትምህርትና ስልጠና ተቋማቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ የሚቆዩ ይሆናል።
በዚሁ መሠረት ወደፊት በሀገራችን የሚኖረውን የቫይረሱን ስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ ከሚመለከተው አካል በሚሰጠን መረጃ መሠረት ነባር ተማሪዎችን ከተለመደው አካሄድ በተለየ ሁኔታ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ሥራ ተጀምሯል።
ነባር ተማሪዎችን በተመለከተ፡-
ሙሉ በሙሉ ኮርስ ያጠናቀቁ ተመራቂ ተማሪዎች (ለምሳሌ፡- የሕግ፣ የእንስሳት ሕክምና /veterinary medicine/፣ የሕክምና ተማሪዎች ወዘተ)፥ የመጀመሪያ ሴሚስቴር ያላጠናቀቁ ተማሪዎች፣ ሁለተኛ ሴሚስቴር ምንም ያልጀመሩ ተማሪዎች በባች/በደረጃ ተለይተዉ፣ የሴሚስቴሩን ኮርስ እስከ 25% እና 75% ያጠናቀቁ ተማሪዎች የቀሩ ምዕራፎች ተለይተዉ ማካካሻ ትምህርት በማመቻቸት እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ይሆናል።ተግባራዊ ለማድረግም በሁለት ዙር ተከፍለው ወደ ተቋማቱ እንዲገቡ በማድረግ የገጽ-ለገጽ ትምህርት ወስደዉ እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ሆኖ በአጭር ጊዜ ለማካካስ እንዲቻል የኦንላይን ትምህርቱም የሚቀጥል ትምህርት የሚሰጥበት አካዴሚክ ካሌንደር (academic calendar)፣ ቀናትና ሰዓታት ማሻሻያ የሚደረግባቸው ይሆናል። ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲዎች ሲመለሱም በቤተ-መፃሕፍት፣ በመማሪያ፣ መመገቢያ እና ማደሪያ ክፍሎች የሚኖራቸው ቁጥርም የተመጠነ ይሆናል።
በዚሁ መሠረት፡-- ተመራቂ ተማሪዎች እና ተመራቂ ያልሆኑ 4ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ያሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 3፣ 4 እና 5 ሰልጣኞች በመጀመሪያዉ መርሃ-ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
- የ1ኛ ዓመት፣ 2ኛ ዓመት እና ተመራቂ ያልሆኑ የ3ኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 1 እና 2 ሰልጣኞች በሁለተኛዉ መርሃ ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
- የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አዲስ ገቢ ተማሪዎች እና የነባር ተማሪዎች ቀጣይ ዓመት ትምህርቶች የማካካሻ ፕሮግራሞች ከተካሄዱ በኃላ በቀጣይ የሚገለፅ ይሆናል።
በዚሁ አጋጣሚ ተማሪዎች ወደትምህርት የሚመለሱበት ዕለት ተወስኖ እስከሚገለፅ ድረስ ከቫይረሱ ራሳቸውን በመከላከል ባሉበት ሆነው ንባባቸውን እንዲቀጥሉና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዲሁም በአከባቢያቸው ያሉ ወገኖችን እንዲያስተምሩ መልዕክት እናስተላልፋለን።
ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.
ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር)
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርJune 28, 2020 at 2:35 am #14974In reply to: ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveየሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ጀመረ
አዲስ አበባ – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ጀመረ። የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በጋራ የጀመሩት የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ፈጠራን በማበረታታት፣ አካታችና አነቃቂነትን መሠረት በማድረግ ፖሊሲዎችን በማሻሻል በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው። ለዚህ ፕሮጀክት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የ11.8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
“ኢትዮጵያን ማስቻል” (Enabling Ethiopia) ፕሮጀክት ሲቀረጽ የሀገሪቱን የ5 ዓመት የሥራ ፈጠራ መሪ ዕቅድ ለማሳካት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበት ነው። ፕሮጀክቱ ሀገሪቱን የሥራ ፈጠራ አጀንዳ እና የኮሚሽኑን አምስት ዓመት ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲያግዝ ሆኖ የተቀረጸ ነው። እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2019 የተጀመረው የኮሚሽኑ የአምስት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ መሪ ዕቅድ በግል ዘርፉና በፌደራል እንዲሁም በክልሎች ደረጃ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተናበበ መልኩ አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ፣ ኢንቨስትመንትን በማመቻቸት በ 2015 (እ.ኤ.አ) 14 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።
በዚህ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለሥራ ፈጠራ ምቹ ምህዳር መፍጠር፣ አስፈላጊ የሰው ኃይል ካፒታልን ማዳበር እና ማክሮ ፖሊሲዎች ሥራ ፈጠራን እንዲያበረታቱ ማስቻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራባቸዋል።
ኢትዮጵያን ማስቻል ለ50 ሺህ ሴቶችና ወጣቶች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሥራ ዕድል በማመቻቸት የመሪ ዕቅዱን አፈጻጸም ያግዛል። በተጨማሪም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጡ ማክሮ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹና አፈጻጸማቸውም ቀልጣፋ እንዲሆን የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ግንባታውን በማገዝ እንዲሁም ሃብት በማሰባሰብ ሥራዎች ላይ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።
ኢትዮጵያን ማስቻል ትኩረት ላልተሰጣቸው የማኅበረሰብ አካላት ማለትም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለሚሠሩት ሥራ ክፍያ የማያገኙ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች፣ ስደተኞችና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ዓላማ ያደረገ ነው። ፕሮጀክቱ የወጣቶችን ክህሎት ከማዳበር በተጨማሪ 200 ለሚሆኑ እምቅ ኃይል ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ህልማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ ያደርጋል።
“ኢትዮጵያን ማስቻል ስሙም እንደሚያመለክተው ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች መልካም አጋጣሚ ነው። በተለይም ትኩረት ያልተደረገባቸው ነገር ግን ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሥራ እንዲኖራቸውና ገቢ እንዲያገኙም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አዳዲስ ዕድሎችን ለማመቻቸት እና ለሥራ ፈጣሪዎች ፣ ለድርጅቶችና ለግሉ ሴክተር እንቅፋቶችን ለማስወገድ ትኩረት ፈጠራ ትብብርና ልህቀትን በመጠቀም ለሴቶችና ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፣ የተከበረ እና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ይተጋል” በማለት ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ገልጽዋል።
ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መሪነት ሲሆን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት አካላት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ነው።
“ይህ ፕሮጀክት በ2030 (እ.ኤ.አ) ለ10 ሚሊዮን ወጣቶች የተከበሩና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ከተቀረጸው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ወጣት አፍሪካ በሥራ ላይ ፕሮጀክት ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር ባለን ትብብር የኢትዮጵያ ወጣቶች እድገት እንዲያስመዘግቡና የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በጉልህ እንዲታይላቸው የሚያደርግ ነው” በማለት አቶ አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገልጸዋል።
- ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው ደንብ ቁጥር 435/2011 መሠረት ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የማስተዳደር ፣ የማቀናጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚፈጠሩ ሥራዎች ዘለቄታ ያላቸው እንዲሆኑ እ.ኤ.አ በ2020 ዓ.ም ሦስት ሚሊዮን ፣ በ2025 ዓ.ም 14 ሚሊዮን ፣ በ 2030 ደግሞ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ በማመቻቸትና ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትል እና አቅም ግንባታ፣ በትብብርና ኢንቨስትመንት፣ በኢኖቬሽንና በመረጃ ትንተና እና ሥርዓት ማበልጸግ ላይ ትኩረት በማድረግ እስከ ሚያዝያ 2012 (እ.ኢ.አ) ድረስ 2.4 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
ስለ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረ-ገጹንና ማኅበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
https://www.jobscommission.gov.et
https://twitter.com/Jobs_FDRE
https://www.facebook.com/JobsCommissionFDRE/- ማስተርካርድ ፋውንዴሽን
ማስተርካርድ ፋውንዴሽን (Mastercard Foundation) ሁሉም ሰው የመማር እና የመበልፀግ ዕድል ሊያገኝ የሚችልበት ዓለም እንዲኖር ይመኛል። ለዚህም ፋውንዴሽኑን ዋነኛ ተልዕኮውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች የትምህርት ልህቀት እና የፋይናንስ አካታችነትን ማሻሻል ነው። በዓለማችን ካሉ ታላላቅ ፋውንዴሽኖች መሐከል አንዱ የሆነው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን አፍሪካ ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደርጋል። እ.ኤ.አ በ2006 በማስተርካርድ ኢንተርናሽናል አማካኝነት ቢመሠረትም በአሁኑ ወቅት ራሱን በቻለ የቦርድ አመራር ስር ይተዳደራል። ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በቶሮንቶ፥ ካናዳ እንዲሁም በኪጋሊ፥ ሩዋንዳ ፅሕፈት ቤቶች አሉት።
ስለ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረገጹንና ማህበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
http://www.mastercardfdn.org
http://twitter.com/MastercardFdnምንጭ፦ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን
June 15, 2020 at 10:54 am #14801In reply to: 2ተኛው “አረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
AnonymousInactiveየተፈጥሮ ሳይንስ እና ግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ተገለጸ።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገራችን አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕለት የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ቀን በሚል ችግኝ የመትከል ማዕድ የማጋራትና ደም የመለገስ መርሃ-ግብሮች ተከናውነዋል።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአሰላ ከተማ የሚገኘው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት መርሃ-ግብሩን ያስጀመሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፥ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።
በቅድመ ተከላ፣ በተከላ ወቅትና ድኅረ ተከላ መደረግ ያለባቸውን እንክብካቤዎችን እና ጥንቃቄዎችን በማስተማርና እንዲሁም እንደየአከባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ተስማሚ የሆኑትን ችግኞች እንዲባዙ ጥናትና ምርምር ከማድረግና ማማከር በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ችግኞችን አባዝተው ለአከባቢው ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አያይዘውም በየአከባቢው ያለው የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማኅበረሰቡ እንዲሁም ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን እየተጠነቀቁ በዚሁ ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ማዕድ እንዲያጋሩ እና ደም በመለገስም ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት እንዲታደጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን ሦስቱን ግቢዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን የጎበኙ ሲሆን፥ በጉብኝቱ ከሰባ ዓመታት በፊት በስዊድን ድጋፍ የተቋቋመውና በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የግብርና ምርምር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ እና የጤና ሳይንስ ኮሌጁም የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ለመከላከል የሚያመስገን ሥራ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።
ፕሮፌሰር አፈወርቅ በማዕድ ማጋራት ዩኒቨርሲቲው የሚደግፈውን አፎምያ የአረጋውያን መርጃ ማኅበር የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው የዱቄትና ዘይት ድጋፍ አድርጓል።
ከአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ከድምጻውያን ጋር በመሆን በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ ውስጥ (የካ ተራራ) ችግኞችን ተክለዋል።
ከንቲባው በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዓለም-አቀፍ ስጋት የሆንውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ከመከላከል በተጓዳኝ ነዋሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ችግኞች እንዲተክሉ አሳስበዋል። ችግኝ ከመትከል ባለፈም ችግኞች በየጊዜው መንከባከብም ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ሕብረት ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ሕብረተሰቡ ችግኞች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመረዳት በራሱ ተነሳሽነት መትከልና መንከባከብ ይገባል ብለዋል። ሕብረቱም የተከላቸውን ችግኞች ለመንከባከብም ቃል ገብተዋል።
በሥፍራው ተገኝቶ አረንጓዴ አሻራ በማኖሩ ደስተኝነቱን የገለጸውና ተግባሩ መቀጠል አለበት ያለው ድምፃዊ ነዋይ ደበበ ነው።
”ንጹህ አየር ለሰው ልጅ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ችግኝ መትከል ግዴታ ነው። በዚህም ቦታ ተገኝቼ አረንጓዴ አሻራ በማኖሬ ደስተኛ ነኝ” ሲል የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ተናግሯል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰባት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከሚተከሉት መካከል ለጥምር ግብርና የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች ይገኙበታል።
ምንጮች፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 11, 2020 at 2:10 am #14775Topic: 2ተኛው “አረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
in forum Semonegna StoriesSemonegnaKeymaster2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።
አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 16, 2020 at 4:06 am #14525In reply to: ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveእናት ባንክ እና ዳሸን ባንክ የብድር ወለድ ስረዛ/እፎይታ እና የአገልግሎት ማሻሻያ አደረጉ
አዲስ አበባ (ፋና/ዋልታ) – እናት ባንክ ለተለያዩ የብድር ዘርፎች የብድር ወለድ ስረዛና የአገልግሎት ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ። ባንኩ በሰጠው መግለጫ ኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝነት በዓለምአቀፍ ደረጃ መሰራጨት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በዓለም ማኅበረሰብ ላይ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን በማድረስ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል።
ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ የንግድ እንቅስቃሴና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑን ነው የገለጸው። በመሆኑም እናት ባንክ ይህንን ጉዳይ በከፋተኛ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪዎቹ የብድር ወለድ ስረዛና የተለያዩ የአገልግሎት ማሻሻያዎችን ማድረጉን ነው ያሳወቀው።
የማሻሻያው ዋና ዓላማም እየተከሰተ ያለውን ችግር በጋራ ለመወጣት፣ በደንበኞች የንግድ እንቅሳቃሴ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ፣ የብድር አመላለስን የተሻለ ለማድረግና የሀገራችን ኢኮኖሚ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ ማስኬድ በሚቻልበት አካሄድ ባንኩ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ታሳቢ ያደረገ ነው ብሏል ።
በዚህም መሠረት የብድር ወለድና አገልግሎት ክፍያን አስመልክቶ በሆቴልና ቱሪዝም የሥራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞች ከግንቦት እስከ ሀምሌ የብድር ወለድ እንዳይከፍሉ መሰረዙን ገልጿል።
ከዚያም ባለፈ የብደር ማራዘሚያ ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ፣ የኦቨር ድራፍት እድሳት ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ፣ ብድራቸውን ከሚጠበቅባቸው የመክፈያ ጊዜ ቀድመው ለሚከፋሉ ደንበኞች ይጣል የነበረው ቅጣት እንዲሁም ውዝፍ የብድር ዕዳን አዘግይቶ ሲከፈል የሚጣል ቅጣት ሙሉ ለሙሉ መነሳቱንም ነው ያብራራው።
በዓለምአቀፍ ባንኪንግ ዙሪያም እናት ባንክ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጾ፥ በዚህም አስመጪዎች እቃ ወደ ሀገር ለማስገባት ለከፈቱት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (LC) አሁን በዓለም ላይ ከተፈጠረዉ ችግር አኳያ አስቀድመዉ ለማራዘሚያ የሚጠየቁት የአገልግሎት ክፍያ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ መደረጉን አንስቷል።
በተያያዘም ከኮቪድ-19 ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ዕቃዎች ለሚያሰመጡ አስመጪዎች ባንኩ ሃምሳ በመቶ (50%) የአገልግሎትና የኮሚሽን ክፍያ መቀነሱን ነው የገለጸው።
እናት ባንክ ማኅብራዊ ኃላፊነትን ለመወጣትና ኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ለብሔራዊ የኮቪድ-19 ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የብር 2 ሚሊዮን ብርድጋፍ ከማበርከቱም ባለፈ የባንኩ ሠራተኞችና የደንበኞች ደኅንነት ከወረርሽኙ ለመጠበቅ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑን ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በተመሳሳይ ዜና፥ ዳሸን ባንክ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያሳድርባቸዉ በጥናት በተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ለመስጠት ወስኗል።
የኮቪድ-19 ስርጭት በተለይ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በመገንዘብ ቀደም ሲል በሌሎች ተጎጂ መስኮች ላይ እንዳደረገው ሁሉ በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞቹ እየደረሰባቸዉ ያለዉን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመጋራት መወሰኑን ለዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን (ዋልታ) በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት በአበባና አትክልት፣ በሆቴልና ማስጎብኘት (ቱሪዝም)፣ በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾች፣ በፋብሪካ ምርት (manufacturing)፣ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እና ትምህርት ተቋማት ዘርፎች ለተሰማሩና በሥራ ላይ ላሉ ደንበኞች እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር (እ.አ.አ.) ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወለድ ቅናሽ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ሰጥቷል።
ባንኩ በአበባና አትክልት ዘርፍ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች ቀደም ሲል በዝቅተኛ ወለድ እያበደረ የነበረ ቢሆንም፥ ዘርፉ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዞ የደረሰበትን የኢኮኖሚ ጉዳት ከግምት ዉስጥ በማስገባት ከ 1 በመቶ እስከ 2 በመቶ ተጨማሪ ቅናሽ አድርጓል።
ከፈረንጆቹ ሰኔ 1 ጀምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ደንበኞች 7 በመቶ የወለድ ምጣኔ ብቻ እንዲከፍሉ ወስኗል። በተጨማሪም ተበዳሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የ6 ወር የብድር እፎይታና እስከ 5 ዓመት የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ፈቅዷል።
በሆቴልና ማስጎብኘት ዘርፍ የተሰማሩ ተበዳሪዎች እ.አ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ የሚከፍሉት የወለድ ምጣኔ ወደ 7 በመቶ እንዲቀንስና ተበዳሪዎቹ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የስድስት ወር የብድር እፎይታ ጊዜና እስከ 5 ዓመት ድረስ የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ እንያገኙ ለማድረግ ወስኗል።
በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾችም እንዲሁ እ.አ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ የወለድ ምጣኔ ቅናሹ ተጠቃሚ ሆነው ለሶስት ወራት 7 በመቶ ብቻ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል። ከዚህም ሌላ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረትም የሦስት ወር የብድር መክፈያ ዕፎይታ ጊዜና እስከ ሦስት ዓመት ያለምንም የብድር ማራዘሚያ ክፍያ እንዲስተናገዱ መደረጉን ባንኩ በመግለጫው አትቷል ።
በፋብሪካ ምርት (manufacturing)፣ በሕዝብ ማመላለሻ አዉቶብስና በትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ ተበዳሪዎችም ጭምር በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ከሰኔ 1 ጀምሮ ለ 6 ወር የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜና እስከ 3 ዓመት ድረስ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ለመስጠት ወስኗል።
በተጨማሪ ዳሸን ባንክ ከላይ ለተጠቀሱትና በቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንሚዳረጉ በጥናት ለተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨማሪ የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ እንዲደረግላቸዉም ወስኗል። ከ17.5 በመቶ እስከ 18 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩና በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞች የ1.5 በመቶ ወለድ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ 16 በመቶና 16.5 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል ብሏል። ከ14 በመቶ እስከ 17 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩ ደግሞ የ1 በመቶ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ ከ13 በመቶ እስከ 16 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተወስኗል ።
ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ዉሳኔዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከታወጀበት ጊዜ በፊት በተበላሸ ብድር ዝርዝር ዉስጥ ይገኙ የነበሩ ብድሮችን እንደማይጨምርም ዳሸን ባንክ አስታውቋል።
ምኝጮች፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት/ ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት
-
AuthorSearch Results
Search Results for 'ትምህርት ሚኒስቴር'
-
Search Results
-
2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።
አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ