Search Results for 'ትግራይ ክልል'

Home Forums Search Search Results for 'ትግራይ ክልል'

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 70 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ― አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለ

    ትኩረት ለትግራይ!!!
    ትኩረት ለአስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ!
    ትኩረት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር!

    ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ፥ መንግሥት በትግራይ ክልል ሲያካሄድ የቆየውን ሕግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ማለትም የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የሕክምና እና የመድኃኒት፣ የደህንነት፣ ባንክ፣ ትራንስፖርት የመሳሰሉት አገልግሎቶች አሁንም ያለመሟላት እና ከፍተኛ የሆነ የሕግና ሥርዓት ያለመከበር ስጋት እንዲሁም ጥቃት ያለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ከታማኝ ምንጮች አረጋግጧል። ጊዜያዊው የክልሉ አስተዳደር ሁኔታዎችን ለማስተካከል እየጣረ ያለበትን ጥረት ብንረዳም፥ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነውና የሁላችንንም ኢትዮጵያውያን ርብርብ እና እገዛ እንደሚጠይቅ ተረድተናል። ሁኔታዎች ከእስከአሁኑም በላይ ተባብሰው ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆኑ በፊት አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።

    በመሆኑም፦

    1. በክልሉ ባለፈው ክረምት ወቅት በአዝርዕት ላይ በደረሰው የበረዶ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የጎርፍ አደጋ እና የበረሀ አንበጣ ወረርሽኝ የተነሳ ጉዳት የደረሰ እንደነበርና ከዚህም የተረፈውን በነበረው ጦርነት ምክንያት በበቂ ሁኔታ መሰብሰብ ባለመቻሉ እና በተያያዥ ምክንያቶች ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎቻችን አስቸኳይ የህይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመረዳታችን፥ ነገ ዛሬ ሳይባል በአስቸኳይ የምግብና የመጠጥ እርዳታ የሚደርስበትን መንገድ እንዲመቻች፥ ለዚህም ለሚመለከታቸው አካላትና መላው የኢትዮጵያ ዜጎችን ጥሪ እናቀርባለን።
    2. ለሕክምና ተቋማት የመድኃኒት፣ የሕክምና መሳሪያዎች፣ ባለሙያ እና ጥበቃ በማሟላት ማስቀረት የሚቻሉ የጤንነት ችግሮች እንዲቀረፉ እና በተለይ ሕጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች እንዲረዱ እንጠይቃለን።
    3. ጊዜያዊው የክልሉ መንግሥት እስከታችኛው የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅር መልሶ ለማዋቀር እየሠራ እንደሆነ ብንገነዘብም፥ በዘላቂነት ሥራው እስኪሳካ ከነዋሪው እና ከሌሎች እትዮጵያውያን የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ሰላምና ማረጋጋቱን ለማገዝ የሚችል ግብረ-ኃይል በማሰማራትም ጭምር ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ዜጎቻችን ላይ ያለውን የደህንነት፣ የዝርፊያና የመደፈር… ስጋት በአፋጣኝ እንዲያስቆም እንጠይቃለን።
    4. በክልሉ እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችና በማከፋፈል ሊያግዙ የሚችሉ በጎ ፈቃደኞች መሰማራት እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እናሳስባለን።
    5. የምግብ እና ሕክምና አገልግሎት ማድረስ የማይቻልባቸው ቦታዎች ካሉም ሰላማዊ ዜጎች በተለይ ሴቶች፣ ሕፃናት እና አቅመ ደካሞች ከአካባቢው ተጓጉዘው ወደሌሎች አቅርቦት ሊደርስላቸው ወደሚችሉበት የትግራይ ክልል ከተሞች ወይም ወደ አቅራቢያ የሀገራቸው ክልሎች በማድረስ የህይወት አድን ሥራዎች እንዲሠሩ አበክረን እንጠይቃለን።
    6. በሰላማዊ ሰዎች እና ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የደረሰው አካላዊ ጥቃት፣ ዘረፋ እና የሞራል ድቀት በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን።
    7. በቀጥታ ከሕግ ማስከበር እርምጃው ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ በተለያዩ ተቋማት ላይ የደረሰውን ዝርፍያ እና የንብረት ውድመት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን።
    8. በሀገርም ውስጥ በውጭም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው እየተጎዱ ያሉት ንጹኃን ዜጎቻችን ናቸውና ይህ ስቃይ እና ስጋት አብቅቶ ወደ ማቋቋም ለመሸጋገር ይቻል ዘንድ በሁሉም ዘርፍ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ታደርጉ ዘንድ እንጠይቃለን።
    9. የመንግሥት የሚመለከታችሁ አካላት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ፣ የሚድያ፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ያላችሁን መዋቅር በመጠቀም ቅድምያ ህይወት ለማዳን እና ሰብዓዊነትን በማስቀደም በአንድነት እንድንቆም እንለምናችኋለን።

    ኦባንግ ሜቶ
    ዋና ዳይሬክተር፥ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
    ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
    ትግራይና አማራ ክልል፡ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል
    አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እና ድጋፍ ሊቀርብ ይገባል

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ፣ በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎች ደኅንነት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአሳሳቢና ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ በሚችል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገለጸ። ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 6 እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም.  በጎንደር እና በዳንሻ በመገኘት እንዲሁም፣ ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በትግራይ ክልል፣ ደቡባዊ ዞን፣ ጨርጨር ወረዳ በሚገኙት ኡላጋ እና ቢሶበር መንደሮች በመጓዝ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ተጎጂዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ያደረገውን ክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

    በተጨማሪም የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ከጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ ዙር የመስክ ምልከታ ወደ መቀሌ ከተማ እና ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፥ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብዓዊ ቀውስ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በመመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ሥራው እንደተጠናቀቀ ተጨማሪ ሪፖርቱን ይፋ የሚደረግ መሆኑን ኮሚሽኑ አክሎ አሳውቋል።

    የአሁኑ ክትትል በዋነኛነት በተካሄደባቸው በዳንሻ፣ በሁመራ፣ በቢሶበር እና በኡላጋ ጦርነቱ የሲቪል ሰዎችን ሞትና አካላዊ ጉዳት አስከትሏል፤ የሲቪል ሰዎችን መኖሪያና የንግድ ቦታዎች ለዝርፊያና ለተለያዩ ጉዳቶች አጋልጧል፤ እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመትና የኤሌክትሪክ እና የውሃ የመሳሰሉ አገልግሎቶች አለመመለስ፣ በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና በተፈናቃናዮች ላይ የበለጠ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል የሚያሰጋ ነው። በቢሶበር እና በኡላጋ  31 ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፤ 104 መኖሪያ ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ እንዲሁም የአካባቢው ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በተመሳሳይ መልኩ በሁመራ እና በዳንሻ የሲቪል ሰዎች ንብረት የሆኑ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶችን ጨምሮ የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ውድመት እና ዝርፊያ ደርሷል። ሲቪል ሰዎች በብሔራቸው ምክንያት ወይም በአካባቢዎቹ የፀጥታ መጓደል ምክንያት ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በእነዚህ አራት ከተሞች ያለው የፀጥታ ስጋትና  የፍትህ አካላት ወደ መደበኛ ሥራቸው አለመመለስ፣ የሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ጥበቃ ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል።

    ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሲያስረዱ፥ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ምርመራውና ክትትሉ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የነዋሪዎቹንም ሆነ ከትግራይ ክልል ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት እንዲጨምርና የመቋቋም አቅማቸውን በአስከፊ ሁኔታ እንዲፈተን አድርጓል” ብለዋል። የኮሚሽኑ ምርመራ ቡድን የጎበኟቸው ተጎጂዎች በአብዛኛው በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው አሊያም አንድ ዙር ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው መሆኑን በሪፖርቱ እንደተመለከተ ጠቅሰው፥ “በአካባቢዎቹና በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት የሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው” በማለት ገልጸዋል።

    ሙሉውን ሪፖርት እዚህ ጋር (ማስፈንጠሪያ) በመጫን ማግኘት ይቻላል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

    The security situation of civilians and IDPs in Tigray region የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል ― ኢሰመኮ

    Anonymous
    Inactive

    የህወሓቶች እብሪት ― የህወሓቶች ውድቀት ― እንደሀገር፣ እንደዜጋ የሚያስተምረን ትምህርት
    (አቶ ነአምን ዘለቀ)

    ጆርጅ ሳንታያና (George Santayana) የተባለው ፈላስፋ “ታሪክን የማያስተውሱ ታሪክን በመድገም ይረገማሉ” (‘Those who cannot remember the past are condemned to repeat it.’) እንዳለው፥ አምባገነኖች ከሂትለት እሰከ ሳዳም ሁሴን – ካለፈው መማር ሳይችሉ ያንኑ ሲደጋግሙ ኖሩ። የህወሓቶች እብሪት፣ ትእቢት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የነበራቸው ንቀት የዚሁ እብሪተኞች ካለፈው ለመማር አለመቻልና የፍትህን ማዕከላዊነት ጥሎ ልከኝነት ረግጦ የመራመድ ቅጥያ ውጤት ነው።

    ለ27 ዓመታት ፍጹም ሊባል በሚችል የበላይነት የመንግሥት፣ የኢኮኖሚ፣ የወታደራዊና የደህንነት ቦታዎች ላይ የአንበሳ ድርሻውን ይዞ የነበረው ህወሓት፥ ከ2018ቱ (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጥር) ለውጥ በኋላ በእኩልነት ለመኖር የተሰጠውን ዕድል መቀበል እንዳልቻለ ግልጽ የነበረው የዛሬ ሁለት ወር ተኩል ገደማ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን እዝ ሠራዊት አባላት ላይ ያደረሰው መብረቃዊ ጥቃትና ጭካኔያዊ እርምጃ ያን ተከተሎ በተደረገው ሕግን የማስከበር ወታደራዊ ዘመቻ የተጀመረ ሳይሆን ከሁለት ዓመት ተኩል ጀምሮ አንደ ነበር ግልጽ ነው ።

    ያ የነበረውን ሁለንተናዊ የበላይነት ሲያጣ የሞት ሞት ሆነበትና እንዴት ያድርገው!? መላ ቅጡ ጠፋው። ከጅምሩም የያዙትን ስልጣን ለፍትህ፣ በልከኝነት፣ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን በሀገርና በሕዝብ ኪሳራ የራሳቸውን፥ አለፍ ሲልም የአንድ ብሔር ሊሂቃን የበላይነት ለማረጋገጥ የተቀሙበት የዘረፋ፣ የዘረኝነትና የመንግሥታዊ ሽብር መሣሪያቸው ነበር። ህወሓቶች ስለራሳቸው ልዩ መሆን፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ጀግንነት፣ ብቃትና ክህሎት ራሳቸው በፈጠሩት የሀሰት ትርክት በእብሪትና በትእቢት የተወጠረው አእምሮአቸው አዲሱን የኢትዮጵያ የለውጥ መንገድ እንዲሁም ከለውጡ ጋር ተከትሎ የመጣውን ነባራዊ እውነታ ሊቀበሉ አልቻሉም።

    እነ ስዩም መስፍን ኢትዮጵያን “ሶርያና የመን እናደርጋታለን” ብለው በአደባባይ አወጁ። እነ ጌታቸው ረዳ “ትግራይ ሀገር መንግሥት መሆን እንዳለባትና እና በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር ሶማሌላንድ ከሞቃድሾ ጋር እንዳላት ግንኙነት ነው የምንፈልገው” በማለት በድፍረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሩ። “ተራራን ያንቀጠቀጥን”፣ “የደርግን ሠራዊት የደመሰስን”፣ “ከወርቅ ሕዝብ የተገኘን”፣ “ኢትዮጵያን እንደ አዲስ የሠራን”፣ “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያረጋገጥን”፣… ብለው ለአስርት ዓመታት የሰበኩት ህወሓቶች የሀሰት ትርክቶቻቸውንም አብጠው አብጠው በአምሮአቸው ውስጥም ተገንብተው፣ ጠጥረውና ደድረው እውነታን ለማየት የማያስችል ግርዶሽ ሆነው ቆዩ። በርካታ የትግራይን ወጣቶችንም በዚሁ ትርክት እወናበዱ። መሬት ላይ ካለው ከነባራዊው እውነታ ጋር ፍጹም በተቃራኑ ቆሙ። እውነታውን ተቀብለው ለመሄድም በትዕቢት፣ በእብሪት፣ በዘረኝነት የተተበተበው ልቦናቸውና ህሊናቸው ፈጽሞ አልፈቅድላቸው አለ።

    በመሆኑም ህወሓቶች ማድባትና መዘጋጀት ጀመሩ። ለሁለት ዓመታት ሲደራጁ፣ ሲዘጋጁ ቆይተው ማዕከላዊ መንግሥቱን ዳግም ለመቆጣጠር፥ ይህ ካልሆነም ኢትዮጵያን አተራምሰውና በታትነው “የትግራይን ሀገር መንግሥት” ለመመሥረት “በመብረቃዊ ጥቃት” በሰሜን እዝ ላይ ክህደትና ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ፈጸሙ። በስልጣን ዘመናቸውም ግፍና መከራ ለሕዝብ ሲሰፍሩ ኖሩ። በሰፈሩት ቁና መስፈር አይቀርምና የሚሊዮኖች እምባ፣ የብዙ ሺዎች ደም፣ ዋይታና ሰቆቃ፣ በህወሓቶች ግፍ የተሰደዱ የአስር ሺዎች ኢትዮጵያውያውን መከራ ፈጽሞ ይሆናል ብለው ባልጠበቁትና ባልተዘጋጁበት የበስተርጅና እድሜያቸው፣ በመጦሪያ ዘመናቸው እጅግ የመረረ ዋጋ ጠየቃቸው። በመጨረሻም መራሩን ውድቀትና ውርደት አከናነባቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብም ‘አክ እንትፍ!’ እንዳላቸው ሊከሰትላቸው ፈጽሞ ሳይችል ቀርቶ በስተርጅና እድሜያቸው ለውድቀትና ለውርደት፣ ገሚሶቹ ደግሞ በመደምሰስ ፍጻሜያቸው ባጁ።

    የኢትዮጵያ አምላክም በእነዚህ ግፈኞች ላይ መብረቃዊ ጥቃት ያደረሰ ይመስለኛል። ስልጣንና ሀብት ደደብና ደነዝ አድርጎ ለውርደት ከዳረጋቸው ከህወሓቶችና ካለፉ አምባገነኖች ታሪክ ለመማር ያልቻሉ፥ አሁንም በያዙት ስልጣን መከታ በማድረግ በሕዝብ ጫንቃ ለመናጠጥ የሚሞክሩ፣ ፍትህን፣ ሰላምን፣ ለሀገር የሚበጀውን፣ የዜጎችን ህይወት የሚለውጥ ተግባር ላይ ከማተኮርና ከመትጋት ይልቅ ሕዝብን ከሕዝብ የሚከፋፍሉ፣ የብሔር ካርድ ለስልጣን ማጠናከሪያ የሚመዙ፣ የሕዝብ ሰላም የሚያውኩና ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚደነፉ፣ በየመድረኩም የሚፎክሩ አፍራሽ በየብሔሩ ስም የተደራጁ ኃይሎችና ቡድኖች በገዢው ፓሪቲ የሚገኙ እንዳንድ መሪ ካድሬዎች ከዚህ ታሪክ ይማሩ ይሆን?

    ከስልጣን ጋር በሚመጣ እብጠትና ማን አለብኝነት ብዙ ርቀት የማያስኬድ መሆኑን ማጤን ትልቅ አስተውሎ ነው። ከፋፋይና ሕዝብን በጭንቀት ውስጥ እንዲኖር ከሚያደርጉ የማኅበራዊ ሚዲያዎችና በየሚዲያው ከሚሰነዘሩ መርዛማና ከፋፋይ አሰተያየቶች ለመሰንዘር ከመሽቀዳደም በጎ በጎውን፣ ለሀገር የሚበጀውን፣ ለሕዝብ ተስፋ የሚሆንውን፣ ለሥራ-አጡ ሥራ የሚፈጥረው፣ ኢትዮጵያን የሚያለማውን፣ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያቀራርቡ ተግባራት ላይ ማተኮርና መትጋት በኃላፊነት ላይ ለሚገኙ እነዚህ የገዥው ፓርቲ መሪ ካድሬዎች ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል።

    የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም፣ የሕግ የበላይነትና ፍትህን ያማከለ ብሎም ለእያንዳዱ ዜጋ በየትኛውም ክልልና ቦታ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ/ት የደህንነት ዋስትናው የሚጠበቅበት፣ ሠርቶ ለፍቶ በሰላም መኖሩ የሚረጋገጥበት፣ የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩ እንቅስቃሴዎች ላይ በማተኮር ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ ሠርቶ ጊዜው ሲደርስ ስልጣን ማስተላለፍ መሆን ይገባዋል። ስልጣንን ለማቆየት የብሔር ካርድ በየዕለቱ መምዘና ህወሓቶች እንዳደረጉት የሕዝብም አብሮነት የሚሸረሽሩ፣ ብሔር ለብሔር የሚያጋጩ ተግባራት ላይ መጠመድ ዋና ሥራ ሆኖ መቀጠል የለበትም። ከሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ከሙስጠፋ ኦማርና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከሌሎችም ሊማሩ ይገባል።

    ሕዝብ በአግባቡና በቅጡ ማገልገል ቅድሚያ መስጠቱ በህወሓቶች ውድቀትና ውርደት ዋዜማ ትልቁ ትምህርት ይህ እንደሆነ መቀበል ብልህነት ነው ። ለሀገርና ለሕዝብም ብቸኛው መንገድ የሕዝብን ሰላም፣ ደህንነት፣ ፍትህ፣ መብቶችና ጥቅሞች እንዲሁም አስከፊውን ድህነት ለማስወገድ አካታችና ዘላቂ ልማትን ማስቀደም መሆን አለባቸው። የህወሓቶች ውድቀት ዋዜማ እንደ ሀገር ምን እንማራለን ለሚለው አንዱ አስተምሮና አስተውሎ ይህ ይመስለኛል።

    አቶ ነአምን ዘለቀ

    የህወሓቶች እብሪት ― የህወሓቶች ውድቀት

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ለሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ካልታገለ እንደ ብልጽግና መቆም አይችልም!

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ አቋም
    ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.
    ባህር ዳር

    ስናጠፋ የሚገስጸን፣ ስናለማ የሚያግዘን ሕዝብ እንዳለን እናምናለን። በሕዝባችን ስብራት ላይ ተደማሪ ስብራት መሆን ስለማንፈልግ ከሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በመነጨ ቅን ልቦናና ፍላጎት የሕዝባችንን ድምጽ ለማክበርና ለማስከበር ተዘጋጅተናል። የብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ማቅ እና ድሪት አውልቆ የሕዝብን ሀቀኛ ፍላጎትና እውነተኛ መሻት የሆነውን መካከለኛ አማራጭና የወሳኝ ኩነቶች ወሳኝነት ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚበጀውን የፕራግማቲዝም (pragmatism) ድርና ማግ ተጎናጽፎ ነው። በብልጽግና እምነት ቋሚና የማይለወጥ እውነት የለም፤ ሁሉም ነገር ቋሚ ሊሆን አይችልም። በብልጽግና እምነት የማይለወጥ መሠረታዊና ቁሳዊ የሆነ ነገርም አይኖርም። ከብልጽግና ርዕዮተዓለማዊ እምነት አኳያ ቋሚና የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ እሱም ኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።

    መደመርን መንገዳችን፣ ብልጽግናን መዳረሻችን አድርገን ስንነሳ መደመር የሚፈልጉ ዜጎቻችንን ልንቀንሳቸው አንችልም። ዛሬ በማይካድራ፣ በዳንሻ፣ በዓላማጣ፣ በጥሙጋና በዋጃ ባጠቃላይ በራያ ዋጃ ዓላማጣና ኮረም እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ያሰማችሁትን የ‘አማራ ነን’ ድምጽ በአክብሮት የምንቀበለውና በጽናት የታገልንለት ወደፊትም የምንታገልለት የመደመር ኅብረብሔራዊ ፌዴራላዊ ትርጉም ያለው የቆየ ግን በእብሪት የተገፋና መልስ የተነፈገው የዜጎች ጥያቄ ነው።

    ሁሉም የብልጽግና ቤተሰቦችና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኃይሎች እንዲረዱት የምንፈልገው ቁምነገር አለ።

    በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም።

    ክልላዊ ወሰናችንንና ፌዴራላዊ መብታችንን በመጋፋት በግፍ ተጠቃን እንጂ ማንንም አላጠቃንም።

    በጭካኔና ያለርህራሄ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመብን እንጂ በማንም ላይ የግፍ አጸፋ አልመለስንም። በደም ፍላት ስሜት ተገፍትረው ግፍ ለመፈጸም የቃጡና የሚቃጡ በውስጣችን ያሉ ስሁታንንም ያለርህራሄ ታግለናል፤ እየታገልንም እንገኛለን።

    ከልክ በላይ በተወጠረ እብሪት በትምክህተኝነት ስሜትና በተስፋፊነት ልክፍት ተወጥረው ሕዝባችንን፣ መሬታችንን፣ ታሪካችንን፣ መልካም ስማችንን፣ የ30 ዓመት ሁሉአቀፍ ክልላዊ እድገታችንን፣ እድሜያችንንና ሥነ-ልቦናችንን በግፍ ተዘረፍን እንጂ የማንንም ቅንጣት አልዘረፍንም።

    የወሰን፣ የማንነትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቂያችንን በሕግና በሥርዓት አቀረብን እንጂ እንደ ትሕነግ በማን አለብኝነት ‘ዘራፍ’ አላልንም።

    የተገፋን፣ የተበደልንና የተጨፈጨፍን ቢሆንም ለፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ አልፈጠርንም።

    የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የሀገር ሉአላዊነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ቁርጠኛ አጋርነታችንን በክቡር መስዋዕትነት አረጋገጥን እንጂ ሀገራችንና ሕዝባችንን በመካድ አልወጋንም። ሀገርና ሕዝብ ክደው በወገን ላይ የጭካኔ አፈሙዝ ያዞሩትንም የታሪክ ማፈርያዎች እንደሆኑ እንረዳለን።

    በሰላማዊ መንገድ እጅ የሰጡና የተማረኩ የትሕነግ ተዋጊ ኃይሎችን በወንድማማች መንፈስ ቁስላቸውን ጠረግን፣ እንዲያገግሙ በፍቅር ተንከባከብን እንጂ እንደጠላት አልገፋናቸውም። በተለመደው አማራዊ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት እልፍኛችንን ለቀን፣ ከአልጋችን ወርደን የምርኮኛነት ስሜት እንዳይሰማቸው አስተናገድናቸው እንጂ በግፍ አላሸማቀቅናቸውም።

    እብሪተኛው የአፓርታይድ ቡድን በፈጸመብን ሴራ እስከአሁኗ ሰዓት ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በስጋትና በጭንቀት የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ነው። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አሁንም በስደት ላይ ይገኛሉ። በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን የሚፈሰው የአማራ ደም ዛሬም አልቆመም። በሌሎችም አካባቢዎች የስጋት ጅረት አልተገደበም። በማይካድራና በሁመራ በየቦታው የተጣሉ አስከሬኖች ‘በክብር ቅበሩኝ’ ጥሪ ቢያስተጋቡም የንጹሃኑ በድኖች ግን ዛሬም ድረስ ተለቅመው አላለቁም።

    ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ ጥንተ ጠላት የሆነው ትሕነግና ጽንፈኛ ወዳጆቻቸው ከትክክለኛው ወቅታዊ አውድ ፍጹም የሚቃረን ሙግትና ትንታኔ ሲሰጡ ልማዳቸው መሆኑን ብናውቅም ለአንድ አንድ የትግል አጋሮቻችንና ደጋፊዎቻችንን ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን።

    1. ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አረመኔውና የአፓርታይድ ሥርዓት አቀንቃኙ ትሕነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የተጠናና የተደራጀ ሁሉ-አቀፍ ጥቃት ሲፈጽም የወራሪነት፣ የተስፋፊነትና የጨፍጫፊነት አድማሱን በማስፋት በ24 ሰዓት ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ የአማራ ክልል አቅጣጫዎች ጎንደርንና ወልድያን የመቆጣጠር ግብ አስቀምጦ ነው። ይህንን እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ከ3 ዓመት ያላነሰ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ትሕነግ ያስቀመጠውን የወራሪነት ግብ በመቀልበስ ሀገርና ሕዝብን ለመታደግ በወትሮ ዝግጁነት መፈጸሙ የአማራን ሕዝብ ሊያስመሰግነው ሲገባ፥ በጥርጣሬ እንድንታይ የሚያደርግ በፍጹም አይሆንም። የተከፈተብንን የግፍ ጦርነት ተከላክለንም፣ አጥቅተንም ጦርነቱን መቀልበሳችንና በግፍ ተነጥቀን የነበረውን ተፈጥሯዊ መብታችንን በእጃችን ማስገባታችን (repossession right) የተፈጥሮን ሕግ የሚቃረን ሳይሆን በእብሪተኞች የማይታረቅ ተቃርኖ መቃብር ላይ የተረጋገጠ ድል ነው። ስለሆነም እርስት ለማስመለስ ያልታገለን ይልቁንም ላለፉት 30 ዓመታት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየን ሕዝብና መንግሥት እርስት ለማስመለስ እንደተዋጋ አድርጎ ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አመክንዮ የጎደለው ድምጽ ማሰማት ነውር ነው እንላለን። በእርግጥ እርስት ማስመለስ የሚለው ትችት ለባለእርስቶች የተወረወረ የበላ-ልበልሀ ክርክር መሆኑ የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ፍትሀዊነት ያረጋገጠ ሀቅ በመሆኑ ሀሳቡን ደጋግማችሁ ለተጠቀማችሁ ሁሉ ምስጋና እናቀርብላችኋለን።
    2. እንደ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ሕዝብ ሀቅ ይታወቃል። የአማራ ሕዝብ ሀቅ ዛሬም በአደባባይ በሕዝባዊ ሰልፍ በይፋ እንደሚታየው የማንነት፣ የወሰን፣ በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት ፍትሀዊ ጥያቄ ነበር። ከ500ሺ ሕዝብ በላይ የተፈናቀለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተገደለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተሰወረባቸው እነዚህ አካባቢዎች ዛሬም የተረጋገጠ የጅምላ መቃብር የተገኘባቸውና የአፓርታይድ ሥርዓት በተጨባጭ የተፈጸመባቸው የትሕነግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ጭካኔ ማረጋገጫ የግፉአን መቀበርያ አጽመ እርስቶች ናቸው።

    በግፍ የተጨፈጨፉ የንጹሀን ወገኖቻችን አስከሬኖች ተለቅመው በክብር ባላረፉበት በዚህ ወቅት የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት የወንበዴውን ቡድን ወንጀል ለመደበቅና ለማድበስበስ እየተፈጸመ የሚገኝ ሌላኛው የትሕነግ ሸፍጥ ማምለጫ መንገድ ሲሆን፥ የአካባቢውን ነባራዊ ሀቅ በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት የሚራመዱ የተሳሳቱ ሀሳቦች የሞራል ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው።

    ስለሆነም የሕግ የበላይነት ለማስከበር፣ የሀገር ሉአላዊነት ለማጽናት በተደረገ ሁሉ አቀፍ የትግል ጀብዱ በታሪክ አጋጣሚ ወደባለእርስቱ የገቡ አካባቢዎች (repossessed lands) ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በሥርዓቱና በአግባቡ በቀጣይ ማየት ይቻላል የሚል እምነት አለን። ግን ደግሞ የትሕነግን የአፓርታይድነት የወንጀል ፈለግ (criminal scene) መፈተሽና መመርመር፣ ለትግራይና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማጋለጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለን። ስለሆነም:-

      • ላለፉት 50 ዓመታት የዜጎች ማጎርያና ማሰቃያ የሆኑ ከመሬት በታች የተሰሩ ዋሻዎች (underground torching caves) ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው።
      • ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጅምላ መቃብሮች ታስሰው ላለፉት 50 ዓመታት እንደ ሕዝብ የተፈጸመብንን ግፍና ጭካኔ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን።
    1. በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ግፈኛና ግፍን ነቅሎ በአዲስና በተረኛ ግፈኛና ግፈኝነትን ማጽናት አይደለም። ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ችግር ከግፈኞች አልነበረም። እንደሀገር ግፈኞችን መቅበር የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በየታሪክ ምዕራፉ ግፈኞችን መቅበር የምትችል ሀገር ግፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ግን አልቻለችም። ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ ግፈኝነትን በጽናት በሚታገልበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ የየበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ እየጠየቅን፥ በእኛ በኩል እብሪተኝነትም ሆነ ግፈኝነት የሕዝባችንን ክብር ዝቅ ስለሚያደርገው በጽናትና በታማኝነት የምንታገለው መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።
    2. በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሕግ የበላይነት የምናስከብር መሆኑን እያረጋገጥን፤ በቤንሻንጉል ክልል በሕዝባችን ላይ ተደጋጋሚ ግፍ የሚፈፅሙ የእብሪተኞች ቅሪት ዓላማና ፍላጎት በድል እንደሚቋጭ ሳንጠራጠር የተጀመረውን ሕግ የማስበር ሥራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ጎን ለጎንም የተፈናቃይ ወገኖቻችንን መሠረታዊና ወቅታዊ ፍላጎት እንዲሟላ ከማድረግ ባሻገር የሕዝባችንን እንቅፋት በሕግ አግባብ ተጠራርጎ መጥፋቱ ከተረጋገጠ በኋላ ዜጎቻችንን ተመልሰው በቀያቸው ላይ እንዲሰፍሩ የሚደረግ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን።

    በመጨረሻም በትሕነግ መራሹ እብሪተኛ አፓርታይድ እርምጃ ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመባችሁ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የማይካድራና የሁመራ ሰማዕታት ሁልጊዜም በሕዝባችን ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ክብር አላችሁ።

    የሕግ የበላይነት ለማስከበር በተፈጸመው እልህ አስጨራሽ ግብ ግብ ክቡር መስዋዕትነት የፈጸማችሁ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የአባቶቻችን ልጆች ስለሆናችሁ ኮርተንባችኋል፤ ለዘላለምም እንኮራባችኋለን።

    የኦነግ ሽኔንና የጉሙዝ አማጺ ቡድንን ለመደምሰስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ስምሪት ወስዳችሁ ታሪካዊ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የምትገኙ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች፣ የኦሮምያና የቤንሻንጉል ክልል ሀቀኛ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጀግንነታችሁን ስንዘክር በአማራ ሕዝብ አክብሮትና ትህትና ነው።

    ድል ከኢትዮጵያና ከአማራ ሕዝብ አብራክ ለተገኙ ታሪካዊ ጀግኖቻችን!!!
    ውርደት በእብሪትና በትዕቢት ተወጥረው ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለሚወጉ ጠላቶቻችን!!!
    ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ!!!
    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    ማይካድራ ውስጥ ሲቪል ሰዎች ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው ― ኢሰመኮ

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
    ትግራይ፡ የማይካድራ ሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው
    የተጎዱትን ማቋቋም እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይገባል

    በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ  የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል (atrocious crime of massacre against civilians) መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

    ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀ ጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተሞች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ነው። ይህ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime)  ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ስለሆነ፥ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል።

    በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፥ በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ ሀገር መከላከያ ሠራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር በተለይ “አማሮችእና ወልቃይቴዎች” ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል። ኢሰመኮ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን ባገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ ተመልክቷል።

    ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል።

    የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል” ብለዋል። አክለውም “የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፥ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።

    የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርትን እዚህ ጋር በመጫን ማግኘት ይቻላል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
    ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ማይካድራ ጭፍጨፋ

    Anonymous
    Inactive

    ሰላም ነሺው የክህደት ቡድን ላይ የሚወሰደው ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ
    (ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ)

    የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፥

    በትግራይ ክልል የጀመርነው ሕግን የማስከበር ርምጃ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጠናቅቋል። አሁን በመጨረሻውና በሦስተኛው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

    እየወሰድን ያለነው ሕግን የማስከበር እርምጃ ሦስት ምዕራፎች እንዳሉት ቀደም ብለን የገልጸን ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ፥ በገዛ ወገኑ የተጠቃውን የመከላከያ ሠራዊታችንን አሰባስበንና አጠናክረን፣ ተቋርጦ የነበረውን የእዝ ሰንሠለቱን ወደ ቦታው መልሰን ግዳጁን እንዲወጣ ማስቻል ነበር። በዚህም መሠረት ሠራዊቱ በከፍተኛ እልህ፣ ቁጭትና ወኔ ከገጠመው አደጋ በፍጥነት አገግሞ፣ የሕዝቡን ከፍተኛ ድጋፍ በልቡ ይዞ የሀገር ክህደት የፈጸመውን የህወሓት ቡድን ለሕግ ለማቅረብ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተንቀሳቅሷል።

    የእርምጃው ሁለተኛ ምዕራፍ ዋና ዓላማ፥ የህወሓትን ጁንታ ከየአካባቢው እያስለቀቀ፣ አቅሙንም ከጥቅም ውጭ እያደረገ፣ ሕዝቡን ከዚህ የክህደት ቡድን ይዞታ ነጻ በማድረግ፣ የመሸገበትን የመቀሌ ከተማ መክበብ ነበር። ከመቀሌ ውጭ ያለውን ህወሓት የያዘውን ቦታ ነጻ በማውጣት፤ የተዘረፉ ትጥቆችንና ካምፖችን መልሶ በመያዝ፤ የክህደት ቡድኑ የዘረፋቸውን ስትራቴጂያዊ የሆኑ መሣሪያዎችን ለውድመት ሳያውላቸው በፊት ከጥቅም ውጭ ማድረግ፤ በግዳጅ የያዛቸውን የሠራዊታችን አባላት ማትረፍ፤ የተሠውትን መቅበር እና አደጋ የሚደርስባቸውን ዜጎች መታደግ የሁለተኛው ምዕራፍ እርምጃ ዝርዝር ዓላማዎች ነበሩ።

    በዚህ መሠረት በዳንሻ፣ ሑመራ፣ ሽሬ፣ ሽራሮ፣ አክሱም፣ አድዋ፣ አዲግራት፣ አላማጣ፣ ጨርጨር፣ መሖኒ፣ ኮረምና በሌሎችም ቦታዎች በተወሰደ እርምጃ ሠራዊታችን ሕዝብ እየታደገና ድል እያደረገ ተጉዟል። ሕዝብ ለመታደግ በነበረው ዓላማ በተቻለ መጠን ሕግ የማስከበር እርምጃው በከተሞች አካባቢ ጥፋት እንዳያስከትሉ እና ሰላማዊ ዜጎች ዒላማ እንዳይሆኑ፤ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የሀይማኖት ቦታዎች፣ የሕዝብ መገልገያዎች፣ መሠረተ ልማቶች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመሳሰሉት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ምንም እንኳን የክህደት ቡድኑ የጥፋቱ ደረጃ ሰፊ እንዲሆን ቢፈልግም፥ በሕግ ማስከበር እርምጃችን ወቅት፥ የአየር ኃይል አውሮፕላኖቻችን ለሕዝቡ በነበራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ወደ ዒላማዎቻቸው የቀረበ አንድም ሰው እንኳን ከገጠማቸው የታጠቁትን ትጥቅ ይዘው እስከ መመለስ ደርሰዋል።

    በዚህም፥ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማው ቡድኑ በሀይማኖት ተቋማትና በቅርሶች አካባቢ ተኩስ እንዲኖር የነበረውን ፍላጎት፣ በሠራዊቱ ተልዕኮን በጥበብ የማከናወን ችሎታ አማካኝነት የቡድኑ ፍላጎት ሊመክን ችሏል። ነጻ በወጡ አካባቢዎች በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ሕዝቡን መልሶ እንዲደራጅ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ አማካኝነት የተጎዱ ወገኖቻችን እንዲደገፉ፣ ሕዝቡ የተፈጸመውን ነገር በትክክል እንዲረዳና ራሱን የሂደቱ አካል ለማድረግ ተችሏል። የተበላሹና የተበጣጠሱ ማኅበራዊ ተቋማትን፣ የመገናኛና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመጠገን፣ ሕዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል።

    ሁለተኛው የርምጃው ምዕራፍ ሕዝቡን የታደገ፣ የጁንታውን አከርካሬ ሰብሮ አቅሙን ወደ መቀሌ ማጥበብ ተችሏል።

    አሁን የቀረው ጉልበት መቀሌ ላይ ያደራጀው ምሽግ እና አልፎ አልፎ የሚያሰማው ከንቱ ፉከራ ነው። በዚህ ሕግን የማስከበር እርምጃ ወቅት ሕዝባችን ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ህወሓት ስለ መከላከያ ሠራዊቱ የነዛው ፕሮፓጋንዳም ስሕተት መሆኑን የትግራይ ሕዝብ በዓይኑ ለማየት ችሏል። የሠራዊቱን ደግነትና ከጥፋት ለመታደግ የከፈለውን መስዕዋትነት ሕዝቡ ራሱ መመስከር ጀምሯል። በየአካባቢው ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ ለሠራዊቱ በማብላት፣ የክህደት ቡድኑ የሚሄድባቸውን መንገዶች በመጠቆም፤ የተደበቁ መሣሪያዎችንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በማጋለጥ ከሠራዊቱ ጎን ሆኖ የሚያስደንቅ ተጋድሎ ፈጽሟል። በዚህም የትግራይ ሕዝብ ቀድሞም በህወሓት የጥፋት መንገድ ምን ያህል እንደተንገሸገሸ በግልጽ አሳይቷል።

    ሠራዊቱ ሽሬ በገባበት ጊዜ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በሆታ ከመቀበሉም በላይ፣ ጁንታው ያስታጠቀውን ከ200 በላይ መሣሪያ ሰብስቦ ለመከላከያ አስረክቧል። ሠራዊታችን አክሱም በደረሰም ጊዜ ሕዝቡ ራሱ በክህደት ቡድኑ ቁጥጥር ሥር የዋሉ የሠራዊት አባላትን ነጻ አድርጎ፣ የቆሰሉትን አክሞና ተከባክቦ፣ በክብር ለመከላከያ ሠራዊቱ አስረክቧል። የአክሱም ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊቱ ከእርሱ ጋር እንዲሆን ከመጠየቁም በላይ አብሮ ተሰልፎ የሕግ ማስከበሩ ዳር እንዲደርስ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በተመሳሳይ ሠራዊታችን አዲግራት ሲገባ፣ ሕዝቡ ራሱ የተደበቁትን የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት እየያዘ ለመከላከያ አስረክቧል።

    በተቃራኒው የቆመው የክህደት ቡድን ስንትና ስንት የሀገር ሀብትና ጉልበት የፈሰሰባቸውን መሠረተ ልማቶችን እያፈረሰ፣ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ከጥቅም ውጭ እያደረገ፣ መንገዶችና ድልድዮችን እየደረማመሰ ሸሽቷል። የታሪካዊቷ አክሱም የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጭምር ውድመት በማድረስ የቀጣይ ዓመታት የቱሪዝም እንቅስቃሴያችን ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። የክልሉ ነዋሪ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያደርግባቸውን መንገዶች በዶዘር ማፈራረሱ ሳይበቃው፥ የመቀሌ ከተማን ልክ እንደ ጦርነት አውድማ ለማድረግ በመዛት ቅንጣት ታህል ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑን በግልጽ አሳይቷል

    ውድ ኢትዮጵያውያን፥

    አሁን ሕግ የማስከበር ርምጃው ወደ ሦስተኛውና ወሳኙ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ሦስተኛው ምዕራፍ በመቀሌ የሚካሄደውና የክህደት ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ የሚደረግ የመጨረሻው እርምጃ ነው። የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ጥበብ፣ ጥንቃቄና ትዕግስት የሚፈልግ እንደሆነ ግልጽ ነው።

    ይህ የክህደት ቡድን ለምንም ነገር ደንታ እንደሌለው፥ ለሕዝቡ፣ ለታሪኩ፣ ለባህሉ፣ ለቅርሱና ለእምነቱ ቅንጣት ርኅራሄ እንደሌለው በግልጽ አሳይቷል። ሁሉም ነገር ጠፍቶ እርሱ ብቻ ቢተርፍና ከሕግ ቢያመልጥ ደስተኛ ነው። በዚህም የተነሣ በመቀሌ ከተማ ውስጥ የሀይማኖት ተቋማትን፣ ሆቴሎችን፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ የሕዝብ መኖሪያ መንደሮችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ቅርሳ ቅሶችንና መካነ መቃብሮችን ሳይቀር እንደ ምሽግ ተጠቅሞባቸዋል። መጥፋቱ ላይቀር ብዙዎችን ይዞ ለመጥፋት ተዘጋጅቷል። ልክ በአንዳንድ ሀገራት እንደሚታዩት የሽብር ቡድኖች፣ ለሕዝብና ለሀገር ምንም ደንታ የሌላቸው አሸባሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ ይሄ የጥፋት ቡድን መቀሌን እንደ ሕዝብ መኖሪያነት ሳይሆን እንደ ጦር አውድማነት ቆጥሯታል።

    በዚህ ቡድን ምክንያት እንዲሞቱ የተገደዱት ነዋሪዎች ዜጎቻችን እንደመሆናቸው መጠን እና የሚወድመውንም ከተማ ነገ መልሶ ለመገንባት ዞሮ ዞሮ የእኛው ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን በመቀሌ የሚኖረን የሕግ ማስከበር እርምጃችን፥ ጉዳትን እጅግ በቀነሰ መልኩ መከናወን እንዳለበት እናምናለን። ስለዚህም፥ የመቀሌ ከተማን ከከፋ ጉዳት ታድገን ዘመቻውን በድል የምናከናውንበትን መንገድ እንደምንከተል ለመግለጽ እወዳለሁ። መንግሥት ይሄንን የሚያደርገው በዚህ የክህደት ቡድን የተነሣ ሕዝብና ሀገር እንዳይጎዳ ከመፈለግ ነው።

    በመሆኑም፥

    አንደኛ፡- የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች፥ በጀመርነው ሕግን የማስከበር እርምጃ ቁልፍ ተዋናዮች እንድትሆኑ፣ ከሠራዊታችን ጎን በመቆም ይሄንን የክህደት ቡድን አባላት ለፍርድ በማቅረብ ወሳኝ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን። ለጥቂት ስግብግብ ጁንታዎች ሲባል አንድም ሰው መሞት፣ አንዲትም ንብረት መውደም የለበትም።

    ለዚህም የእናንተ ትብብር አይተኬ ሚና የሚጫወትና ብዙ ጉዳቶችን እንደሚያቀል እሙን ነው።

    ሁለተኛ፡- የክህደት ቡድኑን ዓላማ በማስፈጸም ላይ ያላችሁ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት፥ አሁንም ቢሆን እጃችሁን በሰላም ለመስጠት ጊዜው አልረፈደም። ሕግ የማስከበር እርምጃው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መሆናችንን ተረድታችሁ የማያዳግመውን ዕድል እንድትጠቀሙበት፤ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ ባለው በ72 ሰዓታት ውስጥ እጃችሁን በሰላም ለመንግሥት እንድትሰጡ የመጨረሻ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።

    ሦስተኛ፡- የጁንታው አባላት፥ የጥፋት ጉዟችሁ ጀንበሯ እየጠለቀች መሆኑን አምናችሁ፣ ከማትወጡበት ቅርቃር ውስጥ መግባታችሁን ተገንዝባችሁ በቀጣይ 72 ሰዓታት ውስጥ እጃችሁን በሰላም እንድትሰጡ እንጠይቃችኋለን፤ የመጨረሻዋን ዕድል ተጠቀሙበት። ተጨማሪ የሕዝብ እልቂት ከመፍጠርና ከተማ ከማውደም ተቆጥባችሁ ከታሪክ ውግዘት እንድትድኑ ጥሪ እናቀርባለን።

    በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው የምንፈልገው ነገር ቢኖር፥ ሦስተኛውን ምዕራፍ የሕግ ማስከበር እርምጃ ከማከናወን ጎን ለጎን በጥፋት ቡድኑ ምክንያት ቀያቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሸሹ ወገኖቻችንን ለመመለስ፤ የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም፤ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን፤ ነጻ የወጡ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች ወደ መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በሁሉም ረገድ ዝግጅት አድርገናል። ወደ ትግበራ ስንገባ ከእጃችን እንዳያጥር እና ዓይናችንን ወደ ሌሎች እንዳናማትር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን። እኛ ኢትዮጵያውያን የቆየና የዳበረ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል ስላለን፣ የማንንም የውጭ እጅ ሳንጠብቅ ወገኖቻችንን እኛው ልናቋቁማቸው ይገባል። ለዚህም በመንግሥትና በተለያዩ የማኅበረሰብ አንቀሳቃሾች አማካኝነት የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንድትቀላቀሉ ስል ጥሪ አቀርባለሁ።

    ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
    ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
    ኅዳር 13 ቀን 2013 ዓ.ም

    ሰላም ነሺው የክህደት ቡድን ላይ የሚወሰደው ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ (ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ)

    Anonymous
    Inactive

    የሀገር ክህደት ወንጀል በፈጸሙ 76 ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ላይ
    የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱ ተገለፀ ― የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
     

    አዲስ አበባ (የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን) – በትግራይ ክልል በሚገኘው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም ሀገር የማፍረስ ሴራ አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩና የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ የጁንታው ህወሓት ወንበዴ ቡድን የበላይ አመራሮችን አድኖ ለሕግ ለማቅረብ ከሳምንት በፊት ማለትም ህዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደወጣባቸው መገለፁ ይታወቃል።

    በተመሳሳይም ከጁንታው የህወሓት ቡድን አባላት ጋር እየተገናኙ ሀገር በማፍረስ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ የሀገር ክህደት ወንጀል በፈፀሙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት እንዲሁም በፖሊስ አመራሮች ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ያስታወሰው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ፥ ከጁንታው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እጃቸውን ባስገቡና በሀገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽኑ ገልጿል።

    በዚህም መሠረት በሀገር መከላከያ ሠራዊት በሥራ ላይ ያሉና በጡረታ የተሰናበቱ ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት የተጣለባቸውን ሕዝባዊና ሀገራዊ አደራና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና የጁንታው የህወሓት ቡድን የሴራ አካል በመሆን የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችንም አድኖ ለሕግ ለማቅረብ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጠባቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

    የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣልና ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ውስጥ በመሳተፍ የሚፈለጉትና የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው በሥራ ላይ ያሉና በጡረታ የተሰናበቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው።

    1. ሜጀር ጀነራል ማህሾ በየነ
    2. ሜጀር ጀነራል ሀለፎም እጂጉ
    3. ብርጋዴል ጀነራል ፍትዊ ፀሃዬ ገብረእግዚአብሔር
    4. ብርጋዴል ጀነራል ግደይ ሀይሉ ገብረእግዚአብሔር
    5. ብርጋዴል ጀነራል ወልደጊዮርጊስ
    6. ብርጋዴል ጀነራል አብዲሳ ፍላንሳ
    7. ብርጋዴል ጀነራል ጉሽ ገብሬ
    8. ብርጋዴል ጀነራል ከበደ ፍቃዱ
    9. ብርጋዴል ጀነራል ገብረጊዮርጊስ
    10. ብርጋዴል ጀነራል ህንፃ ወልደጊዮርጊስ
    11. ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳይ
    12. ኮሎኔል ንጉሴ ገብሩ
    13. ኮሎኔል መብራቱ አሰፋ /አልማዝ/
    14. ኮሎኔል ዘገየ ንጉስ
    15. ኮሎኔል ያለም
    16. ኮሎኔል መብራቱ ተድላ
    17. ኮሎኔል ነጋሽ መብራቱ
    18. ኮሎኔል ተክሉ በላይ
    19. ኮሎኔል ጥጋቡ መለስ
    20. ኮሎኔል ግርማ ተካ
    21. ኮሎኔል ሙሉጌታ ገብረክርስቶስ ነጋሽ
    22. ኮሎኔል አራሞ ገብረመድህን
    23. ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረመድህን
    24. ኮሎኔል ግርማል አለማየሁ
    25. ኮሎኔል ነጋሽ አለፎም
    26. ኮሎኔል ተስፋዬ ምሩፅ
    27. ኮሎኔል ካሳየ አሰፋ
    28. ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ ስዩም
    29. ኮሎኔል ኪሮስ ሓጎስ ገ/ዝጋብሔር
    30. ኮሎኔል ሙርፅ ገብረሊባኖስ አብርሃ
    31. ኮሎኔል ሓ/ስላሴ ኪሮስ ተስፋይ
    32. ኮሎኔል ምሩፅ በርሔ /ተወርወር/
    33. ኮሎኔል ኃይለሥላሴ አሰፋ
    34. ኮሎኔል ደርበው ኃጎስ
    35. ኮሎኔል ወልዴ ሀጎስ
    36. ኮሎኔል ንጉሴ አማረ
    37. ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ
    38. ኮሎኔል ባራኪ /ወዲ ራያ/
    39. ኮሎኔል ከበደ ገብረሚካኤል
    40. ኮሎኔል ፀጋ ብርሀን ገብረእዜር
    41. ኮሎኔል ዘሩ ሀ/መለኮት
    42. ኮሎኔል ኃይለ መዝገብ
    43. ኮሎኔል አርአያ ገብሩ ግደይ
    44. ኮሎኔል የማነ ገብረሚካኤል
    45. ኮሎኔል ዘሩ መረሳ
    46. ኮሎኔል ልጃለም ገብረህይወት
    47. ኮሎኔል ፍሰሀ ግደይ
    48. ኮሎኔል ገብረመስቀል ወልደገብርኤል
    49. ኮሎኔል ወልዱሀጎስ ገብሩ
    50. ኮሎኔል ገብረሚካኤል ሀጎስ
    51. ኮሎኔል ስብሀቱ መብራቱ
    52. ኮሎኔል ጣሰው ወ/ጊዮርጊስ
    53. ኮሎኔል ገብረእግዚያብሔር አለምሰገድ
    54. ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ
    55. ኮሎኔል ተክለ በላይ
    56. ሌተናል ኮሎኔል ተወልደ አብርሃ ወልደሚካኤል
    57. ሌተናል ኮሎኔል ሙዘይ ተሰማ ስዩም
    58. ሌተናል ኮሎኔል ሀዲሽ ገብረፃድቅ አለማየሁ
    59. ሌተናል ኮሎኔል ፍስሃ በየነ ገብረኪዳን
    60. ሌተናል ኮሎኔል ምሩፅ ወልደአረጋይ ገብረመስቀል
    61. ሌተናል ኮሎኔል ሙሩፅ በርሀ ኣበራ
    62. ሌተናል ኮሎኔል ፀሀዬ ሀጎስ
    63. ሌተናል ኮሎኔል ሀጎስ ኪሮስ
    64. ሌተናል ኮሎኔል ገብረ ህንፃ ሀዲሽ
    65. ሌተናል ኮሎኔል ፈለቀ አይጠገብ
    66. ሻለቃ አስገዶም መስፍን
    67. ሻምበል ባሻ ሙእዝ መልካም
    68. ሻምበል አርአያ ተክለሀይማኖት
    69. ሻምበል ተስፋ ህይወት

    ናቸው። ከላይ ስማቸው የተዘረዘረው ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እሴቶች መካከል ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም የሚለውን ወደ ጎን በመተው የወንበዴው ጁንታ ህወሓት የጥፋት ቡድን የሴራ አካል በመሆን በወንጀል የሚፈለጉ መሆናቸውን ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው አሳውቋል።

    በመሆኑም መላው የሀገራችን ሕዝቦች፥ በተለይም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና ሚሊሻዎች እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ የሀገራችን የፖሊስ ሠራዊና የደህንነት ተቋማት እነዚህን የጁንታውን የህወሓት የጥፋት ቡድን ተፈላጊዎች አድኖ ለሕግ ለማቅረብ እየተደረገ ባለው ጥረት በያላችሁበት የድርሻችሁን እንድትወጡ በማለት ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። በቀጣይም በጁንታው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እንዲሁም በሀገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉትንና በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራውም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ መረጃዎችን በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለሕብረተሰቡ ይፋ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

    የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ

    Anonymous
    Inactive

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወሰነ።

    ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲመለስ የተሰጠውን በቂ ዕድል መጠቀም ባለመቻሉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወስኗል።

    ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት ፈጽሟል። በተጨማሪም በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

    የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 12 በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም፡

    (1) በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤

    (2) ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፤

    (3) የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ እንደሚቆጠር ተደንግጓል። ከዚህ ድንጋጌ አንጻር ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል።

    በዚሁ መሠረት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 (1) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጆቹ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም ሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ መስጠት ያለበት ሆኖ በመገኘቱ፥ ጥቅምት 28 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትንን ውሳኔዎች አሳልፏል።

    1. ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14 (2) መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣጣመ መልኩ አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤
    2. ሕገ-ወጡን የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የተቀመጡት ስልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል። በዚሁ መሠረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል። በተጨማሪም ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች ይኖሩታል። በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤

    ሀ) አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤

    ለ) የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤

    ሐ) ሕግና ሥርዓት መገበሩን ያረጋግጣል፤

    መ) አግባብ ባለው ህግ መሠረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤

    ሠ) የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤

    ረ) በፌዴራል መንግሥቱ ሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል።

    1. ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ስለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ በማለት ወስኗል።

    በመጨረሻም፥ መላው የትግራይ ሕዝብና የሀገራችን ሕዝቦች ሕገ-ወጡ ቡድን የፈፀመውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ የሀገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር በሚል መርህ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ መንግሥት እና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን እኩይ ዓላማ ይዘው እርስ በርሳችንን በማጋጨት ሀገራችንን ለመበታተን ሌትተቀን የሚሠሩ ኃይሎችን ነቅተን በመጠበቅና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዘብ እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል።

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

    Semonegna
    Keymaster

    በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    አዲስአበባ
    ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም

    በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት የተለያዩ የፖለካ አካላት ወደ ሀገር መግባታቸው፣ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ችግሮች እንዳያጋጥማቸውና ደህንነታቸውን በመጠበቅና የፈለጉትን ሀሳብ እንዲገልጹ በቂ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

    በፌደራልና በክልል የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መንግሥት ባደረገላቸው ምኅረትና ይቅርታ እንዲፈቱ መደረጋቸውን እንደ ትልቅ ሥራ መወሰድ አለበት ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ሚዲያዎችም የተለያየ ሀሳብ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉና ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመንግሥት እንዲያደርሱ ነፃነታቸውን በመጠበቅ በኩል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

    ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተቀዛቅዞ የነበረ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና የተጀመረ የልማት ሥራ እንዲቋጭ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነትና በሌሎች የጸጥታ አካላት የተከናወኑ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን በበጎ የሚወሰዱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

    በሌላ በኩል ግን በሰላማዊ መንገድ ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት መካከል ሰላማዊ መንገዱን በመተው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ አካላት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በተለይ የኦኔግ ሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ሕብረተሰቡን በመግደል፣ በማገት፣ ንብረት በማውደምና ሌሎች የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።

    በተማሪዎች ጠለፋ ላይም በመሰማራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ አካባቢ የኦኔግ ሸኔ አባላትና ህወሓት በተቀናጀ መንገድ የሕዝብ ግዲያ በመፈጸም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር ለማየት ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ።

    ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም የህወሓት ጽንፈኛው ኃይል ከእነዚህ ከፍተኛ ጥፋቶች ኋላ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበረ በተለያዩ ጊዜ ባደረግናቸው ምርመራዎች ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

    የህወሓት ጽንፈኛ ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመሥራት ያለመፈለግ፣ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማከናወን፣ የሠራዊት አባላትን ለውጊያ በሚመጥን መንገድ ማዘጋጀት፣ የፌደራል መንግሥትን ሕገ-ወጥ ነው በማለት ባገኘው ሚዲያ በሙሉ ማሰራጨትና ሌሎች ለጸጥታ ሥራ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያከናውን መቆየቱንም ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።

    በአጠቃላይ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንና የኦኔግ ሸኔ ታጣቂው ኃይል በተደራጀ መንገድ ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ለሁለት ዓመታት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍል ሲያተራምሱ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ እንደተቻለም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ተናግረዋል።

    በሁሉም አካባቢ የተፈጸሙ የጸጥታ ችግሮች ሲያደራጁና ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን ምርመራዎቻችንና የተለያዩ መረጃዎቻችን አረጋግጧል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ የተለያዩ ፍንዳታዎችን በመፈጸም፣ የግድያ ሙከራዎችን ማከናወን፣ ንብረት ማውደም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና በቤተ-እምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበራቸውም ኮሚሽነር ጄነራሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

    አሁንም በትግራይ ክልል ጦርነት ከፍተው ባሉበት ወቅት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎችና ትላልቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ለማድረስ ያሰማሩት ኃይል እንዳለ ተደርሶበታል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ይሄ ኃይል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ባደረጉት ስምሪት ግማሹ የተያዘ ሲሆን ግማሹ ደግሞ በቅርብ ቀን ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን ተነግሯል።

    የፌደራል ፖሊስ ባለው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሠረት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢ በመሰማራት የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታን የሚጠብቅ ኃይል መሆኑን በመግለጽ በትግራይ ክልልም በ22 ትልልቅ ተቋማት ላይ በመሰማራት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው ብለዋል።

    የፌደራል ፖሊስ አባላት ኤርፖርቶችን፣ ዲፖዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያዎችን፣ ቴሌኮምን፣ ቤተ መንግሥትን፣ ትላልቅ ግድቦችንና ኬላዎችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን በመጠበቅ ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሲሰጡ መቆየታቸውንና በትግራይ ውስጥ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ከሕብረተሰቡ ጎን በመሰለፍ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።

    የፌደራል ፖሊስ ኃይል ሕብረተሰቡን ሲያግዝ በነበረበት ወቅት ህወሓት ከፍተኛ ኃይል በመመደብ ጥቃት እንደሰነዘረባቸውና የንብረት ዝርፊያ መፈጸሙን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በአንዳንድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ላይ ሆነው ሊወረው የመጣውን ኃይል ተከላክሏል ብለዋል።

    መውጫና መግቢያ መንገዶችን ለሠራዊቱ በማሳየት የትግራይ ሕዝብ ሊያጠቃው የመጣውን አካል መከላከል መቻሉና ከሰሜን እዝ ጋር በመሆን ጽንፈኛውን ተዋጊ ኃይል በመመከትና በመምታት የራሱን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ተብሏል።

    ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የፈፀመው ይሄ አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ፣ ሕግና ህሊና ይቅርታ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ኮሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው፥ ሠራዊቱንና ሕዝቡን የደፈሩበት ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።

    ለውጊያ ሳይሆን ለጥበቃ ሥራ የተሰማራ የፌደራል ፖሊስ ኃይል በታጠቀና ለውጊያ በተዘጋጀ ኃይል ተከቦ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አጅግ አሳፋሪ መሆን በመግለጽ ሕግ የማስከበር ሂደታችን በድል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የፌደራልና የክልል ፖሊስ እንዲሁም ሕዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው የሚኒሻ አባላት በጋራ በመደራጀት አካባቢያቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፤ ለተለያየ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ሃይሎችን በየአካባቢው በቂ ጥናት በማድረግ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

    በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጥፋት ሙከራዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሠራዊቱ በአንድ ረድፍ በመሰለፍ ይህንን ችግር ለመከላከል ላሳየው ከፍተኛ ጽናት አድናቆታቸውን በመግለጽ አሁንም ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮች ተረባርበን አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መከላከል አለብን ብለዋል።

    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መፈጸም ከሠራዊቱ አባላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ወያኔ የሚሠራጩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በጋራ መከላከል እንዳለበትና በየቀኑ ከመንግሥት የሚሰጠውን መግለጫ ብቻ መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

    መንግሥት ለሚያቀርበው ጥሪ ሕብረተሰቡ በቂ ዝግጅት በማድረግ እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተሰማራ ኃይል በመከታተል መጠቆምና ማጋለጥ እንዳለበትም ኮሚሽነር ጄነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።

    በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተሰጡ አድራሻዎች መሠረት በዚህ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ1,500 በላይ የሚደርሱ ጥቆማዎች መድረሳቸውንና በዚህም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ በሌሎችም መሰል ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

    የተጀመረው ጸረ-ሰላም ኃይልን የማጥራት ሂደት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ግንባታ በማዞር ጥረት የምናደርግበት ጊዜ እንዲሆንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ተመኝተዋል።

    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!

    በቅርቡ በወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ፣ ባለፈው ሳምንት በጉራፈርዳ በአማራ ዜጎቻችን ላይ የተካሄደው ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በጽኑ እንደሚያወግዝ ይገልጻል። እንዲሁም ይህንን ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ኃይሎች ለሕግ እንዲቀርቡ ፓርቲያችን አበክሮ ይጠይቃል።

    ይህ የዘር ፍጅት እየተባባሰ በመምጣቱ እና ማቆሚያው ባለመታወቁ መንስ ዔውም የአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ዳተኝነት መሆኑን የተገነዘበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዚህ የዘር ፍጅት አስፈጻሚው የመንግሥት አካልን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወቃል።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት በፓርላማው የተነሳበትን ተጠያቂነት መሠረት በማድረግ እና ህወሓት በሰሜኑ እዝ ላይ በከፈተው ጥቃት በህወሓት ላይ ጦርነት አውጇል

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጠየቁት መሠረት እና ከጦርነቱ ጎን ለጎን ህወሓት በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ እና አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል።

    ልክ በህወሓት ላይ እንደሚካሄደው ጦርነት የዘር ፍጅት እየፈጸመ በሚገኘው በኦነግ ሸኔ እና በኦሮሞ ጽንፈኞች እና ተመሳሳይ ተግባር በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በሚፈጽሙት ሁሉ ላይ መደረግ ያለበት የዘገየ እርምጃ እንደሆነ የባልደራስ እምነት ነው። ይህም በሽብርተኝነት የመፈረጁ እርምጃ በዘር ፍጅት ላይ በማስፈጸም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉትን ማጠቃለል ይኖርበታል።

    ሀገራችንን ለዚህ ሁሉ የዘር ፍጅትና ትርምስ ውስጥ የከተታት ህወሓት እና ኦነግ ያዘጋጁት ሕገ-መንግሥት ለሀገር አንድነት እና ስጋት ምንጭ ስለሆነ ሊታገድ ይገባል። ከጦርነቱ በኋላ መንግሥት ሕገ-መንግሥቱ የሚታገድበትን እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚስማሙበት አዲስ ሕገ-መንግሥት እንዲዘጋጅ ሁኔታዎችን ሊያመቻች እንደሚገባ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል።

    በመጨረሻም፥ አሁን በሀገራችን በህወሓት ላይ የሚደረገው ጦርነት ተገቢ እንደሆነ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል። ዳሩ ግን ወንድም በሆነው በትግራይ ሕዝብ ላይ እልቂት እንዳይፈጸም ፓርቲያችን ማሳሰብ ይወዳል። በጦርነቱ ላይ ለሚሳተፉት የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፓርቲያችን ልዩ ክብር አለው። ጦርነቱንም የሚመሩ ባለስልጣናት ከእልህ እና ከቂም በቀል በራቀ ሕግን በማስከበር ብቻ እንዲመሩ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በሂደቱ መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊታችን እና ለአማራ ልዩ ኃይል አክብሮት እና እድናቆቱን ዳግም እየገለጸ፥ ሌሎችን ሀገራዊ ጉዳዮችን ከጦርነት ጎን ለጎን የሚፈቱበትን አማራጭ ላይ ሁሉም ስለኢትዮጵያ ያገባኛል የሚል ኃይል እንዲሳተፍ ያሳስባል።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
    ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    የሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ሙሉ ትኩረታችንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ላይ እናድርግ!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    በሀገራችን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መንግሥታዊ ድጋፍ አግኝቶ በተግባር ላይ የቆየው ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ በዜጎች እና ማኅበረሰቦች መካከል የጥላቻ እና ያለመተማመን ስሜት እንዲሰፍን ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው አገዛዝ በስልጣን ላይ ለመቆየት የጥላቻ እና አለመተማመን መስፈኑን እንደአንድ መሣሪያ ሲጠቀመው ቆይቷል። ይህን ለረጅም ጊዜ በመንግሥት መዋቅር ጭምር እየተደገፈ የተሠራው ማንነትንን መሠረት ያደረገ መከፋፈል፣ የጥላቻ እና የእርስ በርስ አለመተማመን አሁንም ድረስ በየአካባቢው ተንሰራፍቶ፤ ዜጎች በሀገራቸው በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው ደህንነታቸው ተጠብቆ የመኖር፣ የመሥራት እና ሀብት የማፍራት ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና ያለውን ሰብዓዊ መብታቸውን እየገፈፈ ነው።

    ይህ መከፋፈል፣ የእርስ በርስ ጥላቻ እና አለመተማመን ከሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ውጪ የፖለቲካ አመለካከታቸውን በኃይል ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት እንደአጋጣሚ ወስደው እየተጠቀሙበት እንደሆነ ግልፅ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት መዋቅርም ሙሉ በሙሉ ከዚህ ችግር ያልጸዳ ብቻ ሳይሆን አደጋ በደረሰባቸው ቦታዎች የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከአጥፊዎች ጋር በትብብር እየሠሩ ከአደጋ መጠበቅ የሚገባቸውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛል።

    የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እንዲሁም አንድነትን የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸው የደህንነት መዋቅሮች የደህንነት ስጋት ያለባቸው ቦታዎችን በአግባቡ ተንትኖ ደረጃቸውን መለየት እና በዚያም ልክ ተዘጋጅቶ የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት እና የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ ላይ በተደጋጋሚ ክፍተት እንዳለባቸው አይተናል። የንፁሃንን ሕይወት የቀጠፉ እና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶች መደጋገማቸው ከተፈፀሙ በኋላ የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎችም አጥጋቢ እንዳልሆኑ በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህን ጉድለቶችን ሙሉ ለሙሉ ማረም እና አስተማማኝ የሆነ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የረጅም ጊዜ ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም፥ ክፍተቱ እያስከተለ ያለው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ጥፋት የማስተካከያ እርምጃዎች ከማንኛውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ትኩረት ቅድሚያ ተሰጥቶዋቸው እንዲሠሩ የሚያስገድድ ነው።

    ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ አባል የነበሩ ሰዎች በሀገር እና ዜጎች ላይ ላደረሱት ጥፋት ሁሉ ይቅርታ ጠይቀው፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊያንም ተቀብሎት፤ ሀገር አቀፍ ለውጥ ሂደት ጅማሮ ውስጥ መግባታችን ይታወቃል። የነበረውን ስልጣን የበላይነት ያጣው ህወሓት በተለያየ ጊዜ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከአጠቃላይ የለውጡ መንፈስ ውጪ ከመሆን አልፈው፤ የሀገር ሰላም እና አንድነትን በተደጋጋሚ አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የፌደራሉን መንግሥትና የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በቀጥታ በመቃወም ራሱ አስመራጭ፣ ተመራጭ፣ ታዛቢ እና ቆጣሪ የነበረበት ሕገ-ወጥ የክልል ምርጫ አድርጓል። በዚህም የተነሳ የፈደራል መንግሥት ከክልሉ ጋር ያለዉን ቀጥተኛ ግንኙነት ማቋረጡን እናስታውሳለን። “ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም!” የሚል አደገኛ ቅስቀሳ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ ፍፁም ሥርዓት አለበኝነት እንዲነግሥ በባለስልጣናቱ እና በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል። በሀገሪቱ በተለያየ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን ቢያንስ በእርግጠኝነት የምናውቀውን የሚዲያ እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የብዙ ንጹሀን ሕይወት እንዲቀጠፍ ተባባሪ ሆኗል።

    በሀገራችን የመከላከያ ሠራዊት ላይም በተደጋጋሚ ሥራዉን የማደናቀፍ እና የሚገባዉን ክብር የመንፈግ ድርጊቶች ፈጽሟል። የሠራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ መንገድ በመዝጋት እና በማዘጋት እንዲሁም በመከላከያ ሕግ እና ደንብ መሠረት የሚፈጸሙ የከፍተኛ የጦር ኃይል አመራር ሹመቶችን ባለመቀበል አስተጓጎሏል። ህወሓት የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የትግራይን ሕዝብ እንደከለላ በመውሰድ እና ያከማቸውን ገንዘብ እና የኃይል አቅም በመጠቀም በማንአለብኝነት የፈፀማቸው ድርጊቶች እያደር የብዙ ዜጎችን ሕይወት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ አደጋ ውስጥ እየከተቱ መጥተው መንግሥት ያለውን ኃይልን ተጠቅሞ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተገደደበት ደረጃ ላይ መድረሱን እንገነዘባለን።

    ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እራሱን ለመከላከል እና ለሀገር አንድነትና ሰላም ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ ስጋት ሲደቅን የነበረው ህወሓት ላይ መውሰድ የጀመረው እርምጃ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም ኃይልን ተጠቅመው የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት ላይ አደጋ በመጣል የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በሙሉ ሥርዓት የሚያሲዝ እና ከአሁን በኋላ የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት ከሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ውጪ ለመንቀሳቀስ ያሉ አማራጮችን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚዘጋ መሆን ይኖርበታል።

    በሁሉም አካባቢዎች ችግር ሲያጋጥም አሰስፈላጊውን መስዕዋትነት እየከፈለ የሚጠብቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን በዚህ ወቅት ከውጭ ጠላቶች ሀገርን የመከላከል እና ከሀገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች ሀገርን የመታደግ ድርብርብ ከባድ ኃላፊነቶችን እንደተሸከመ እንረዳለን። ምንም እንኳን ተደራራቢ እና አስቸጋሪ ኃላፊነት ቢሆንም የተቋቋመበት ኃላፊነት እና የተሰጠው ሕገ-መንግሥታዊ ግዳጅ በመሆኑ እንደሚወጣው እናምናለን። በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን አንድነት እና ሰላምን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች የኢዜማ አባላት እና አመራር ሙሉ በሙሉ ከጎኑ እንደሚቆም ለማረጋገጥ እንወዳለን።

    በመሆኑም፦

    1. መከላከያ ሠራዊቱ እና ሌሎች የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የሁሉንም ዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበረ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶች እና በዕድሜ የገፉ አረጋውያን ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ ልናሳስብ እንወዳለን። የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላምን እና አንድነትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ በተቻለው አቅም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ በሁሉም አካባቢዎች መደበኛ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚቀጥልበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል።
    2. የትግራይ ሕዝብ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሀገር ሰላም እና አንድነትን የማረጋገጥ እርምጃ መሆኑ በማወቅ ለረጅም ጊዜ የስጋት ድባብ በመፍጠር እንደሽፋን እየተጠቀመ ሲበዘብዘው እና በስሙ ሲነግድ የነበረው ህወሓትን በፍፁም ሳይተባበር ከአብራኩ ከወጣው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለሀገር ሰላም እና አንድነት ከአባት እና እናቶቹ የወረሰውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያረጋግጥ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    3. የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል አባላት ህወሓት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማድረግ በኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ መዳከም እንዲፈጠር በሚያደረገው ሀገርን የማፍረስ ዘመቻ ላይ እንዳይሳተፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆምም ሕዝቡን ከስጋት እና ከአደጋ እንዲጠብቅ እንጠይቃለን።
    4. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚወሰደው እርምጃ የዜጎችን ደህንነት እና የሀገር ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ መሆኑን በመረዳት አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ለሰላም እና ደህንነት እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ከማድረግ እንዲቆጠብ፣ በሁሉም አካባቢ ስጋት የገባቸውን ሰላማዊ ዜጎች ከለላ እና ማበረታቻ በመስጠት እንዲሁም አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ለሰላም እና ደህንነት መከበር ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ትብብር እንዲያደርግ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    5. አሁን እንደ ሀገር የተደቀነብን አደጋ ማንንም ከማንም የማይመርጥ የህልውና አደጋ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን አደጋ የሚመጥን መፍትሄ በማፈላለግ ረገድ የተማረው ማኅበረሰብ ሚና ትልቅ እንደሆነ እሙን ነው። የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ከዳር ቆሞ አስተያየት ሰጪና ተቺ ከመሆን ወጥቶ ወደመሀል በመግባት ሊመጡ የሚችሉ የፖለቲካ መፍትሄዎችን በመጠቆም፤ እንዲሁም በቀጥታ ድጋፉን የሀገር አንድነትን እና ሰላምን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጎን በማሰለፍ ያለበትን ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት እንዲወጣ በዚህም በታሪክ ከሚመጣበት ወቀሳ እንዲድን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
    6. አሁን እየተተገበረ ላለው ሀገራዊ ግዳጅ ጥሪ ተደርጎላችሁ የምትሳተፉ ኃይሎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ስር ብቻ ተልኮውን እንድትፈፅሙ እና በተሰጣችሁ ሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ እንድታተኩሩ እናሳስባን። ኢዜማ ለሀገራዊው ጥሪ በፍጥነት ለሕይወታችሁ ሳትሳሱ ምላሽ ለሰጣችሁ ሁሉ ምስጋናውን እያቀረበ በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት በይፋ ከመንግሥት ከተሰጠ ተልዕኮ ወጪ የሆነ ለሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ እንቅፋት የሚሆን ተግባር እንዳትፈፅሙ ስንል እናሳስባለን። በተለይም ኢ-መደበኛ በሆነ አደረጃጀት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የገባንበትን ችግር የበለጠ የሚያወሳስብ እጅግ አደገኛ ተግባር እንደሆነ ልናሳስብ እንወዳለን። ስለዚህም አሁን የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማስከበር የተገባው በሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ አተኩረን በመንቀሳቀስ በፍጥነት የሕዝብን ጭንቀት በመቋጨት ሌሎች የዴሞክራሲ እና የይገባኛል ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገዶች ወደፊት የሚፈቱበት መንገድን እንድናመቻች በአፅንዖት እናሳስባለን።
    7. ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅእኖ ያላገገመው የኢኮኖሚ እንቀውሰቃሴ የአንበጣ መንጋ ጥቃት ተጨምሮበት ኅብረተሰባችን ምን ያህል ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ ለመገመት የሚከበድ አይደለም። በዚህ አስቻጋሪ ሁኔታ የተቀሰቀሰው ግጭት ሊፈጥር የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በመክተት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የእርዳታ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ዜጎች ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ ለማሳሰብ እንወዳለን።
    8. በተደጋጋሚ እንደገለፅነው የዜጎችን ደህንነትና ያለስጋት የመኖር መብት የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት የመንግሥት ነው። መንግሥት በተደጋጋሚ ይህን ኃላፊነቱን መወጣት ሳይችል በመቅረቱ ዜጎች ውድ የሆነውን ሕይወታቸውን ሲያጡ ቆይተዋል። በሀገር ውስጥ የሚፈፀሙ በተለይም ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በማንም ይፈፀሙ በማን የማስቆም እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ መንግሥት ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆን አይችልም። ጠመንጃ ደግነው ጥይት ተኩሰው ሰው ከሚገድሉት ነብሰበላዎች እኩል እነዚህን ኃይሎች በተለያየ መንገድ የሚያበረታቱ ከጎናችሁ ነን የሚሉ በተለይም በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ንፁሃን ላይ ለሚደርስ ጥቃት ድጋፍ ሲሰጡ የሚታዩ ኃይሎች ላይ መንግሥት አስተማሪ የእርምት እርምጃ በመውሰድ እንዲያስቆም እናሳስባለን። ምንም እንኳን ሰላምን የማረጋገጥ ኃላፊነት በዋናነት የመንግሥት ቢሆንም መንግሥት ብቻውን የሚፈፅመው አይደለም። ማኅበረሰቡን ያላስተባበረ እና ያላካተተ የሕግ ማስከበር እርምጃ ውጤታማ እንደማይሆን በተደጋጋሚ ታይቷል። ስለሆነም መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን መላውን ማኅበረተሰብ ባሳተፈ መልኩ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ በየቀበሌው የፀጥታና አካባቢ ጥበቃ ሥርዓት እንዲዘረጋ ለማሳሰብ እንወዳለን። በተለይም መንግሥት በተደጋጋሚ በመግለጫ ጭምር የችግሩ አካል እንደሆኑ የሚገልፃቸው የመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችን ወደ ተጠያቂነት በማምጣት ራሱን እንዲያጠራ አፅንኦት ሰጥተን እናሳስባለን። ለዚህም ኅብረተሰቡን የመፍትሄው አካል ማድረግ ወሳኝ ነው። መንግሥት በቅርብ ጥቃት የተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደመደበኛ ሕይወታቸው የሚመለሱበት ሁኔታን በአፋጣኝ እንዲያመቻች እንዲሁም ሌላ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን። ተመሳሳይ ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች ሊፈጸሙ የሚችሉባቸው ቦታዎችን አስቀድሞ በመለየት በልዩ ትኩረት ጥበቃ እንዲደረግም እናሳስባለን። በተለይም የክልል አስተዳደሮች በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ የመጀመሪያ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
    9. ኢዜማ በክልል የተደራጀው ልዩ ኃይል በምንም መስፈርት ሕጋዊ ነው ብሎ እንደማያምን እና ለዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል። ይህ አደረጃጀት በሀገር አንድነት ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ተጨባጭ አደጋ ማሳያ በትግራይ ክልል ሰሞኑን የተከሰተው ክስተት አንዱ እና ዋነኛው ነው። በዘውግ ላይ የተመሠረተው የሀገራችን ፖለቲካ አንዱን የዘውግ ማንነት ከሌላው ለመከላከል ወይም ሌላውን ለማጥቃት በሚዋቀረው የልዩ ኃይል እየተደገፈ የሀገራችንን ሕዝብ ወደበለጠ ስቃይ እና የጭንቅ እየከተታት ይገኛል። ሕዝቡም እርስ በእርሱ በጠላትነት እንዲተያይ የሚያደርግ እኩይ አደረጃጀትም መሆኑን በተደጋጋሚ በተግባር ለማየት ችለናል። ስልዚህም በየክልሉ በስፋት የተደራጀውን ልዩ ኃይል ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ ወይንም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚቀላቀልበትን አሠራር እንዲዘረጋ እንጠይቃለን።
    10. በሁሉም አካባቢ የምትገኙ የኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች በተለመደው ሥነ-ምግባር በየአካባቢያቹ ሰላም እና ደህንነትን ለማስከበር በንቃት ማኅበረሰቡን በማስተባበር እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንድትሠሩ እናሳስባለን።

    በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚጠበቀው የሁሉም ዜጎች እኩል መብት የሚከበርበት እና ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲመሠረት እንደሆነ በፅኑ እናምናለን። የሀገራችን አንድነት እና ሰላም ተጠብቆ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር አንድነት እና ሰላም ተባብረው ለመሥራት ፈቃደኛ እና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ ተቀራርበው እንዲሠሩ የሚያስችል ከምር የሚወሰድ የውይይት መድረክ መዘጋጀት አለበት። ይህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎች ግን ሁሉም የሕግ የበላይነትን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሙትን የቃልኪዳን ሰነድ የሚያከብሩ መሆን አለባቸው። የደህንነት እና የፍትህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት መቻላቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ውጤታማ እንዲሆን የማይተካ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም መንግሥት ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ ስልጣኑን አረጋግጦ እውነተኛ እና ለውጥ ማምጣት የሚችል ውይይት እንዲጀመር መንገድ የመጥረግ ሥራውን በአፋጣኝ አጠናቆ ሁላችንም ትኩረታችንን ወደዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንድናዞር አበክረን ጥሪ እናደርጋለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም

    የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ትኩረታችንን ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ እናድርግ!

    Anonymous
    Inactive

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ

    • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት
    • የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት
    • የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ
    • የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ
    • የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት
    • የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
    • የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ።

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንዳሉት፥ በጥቃቱ የተነሳ የተፈናቀሉ 200 ያህል አባወራዎችን የማረጋጋትና ሥራ እየተሠራ ነው።

    በተፈጸመው ጥቃት 23 ወንድ እና 9 ሴቶች በድምሩ 32 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፥ 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

    በጥቃቱ የመኖሪያ ቤቶችና አንድ ትምህርት ቤት እንደተቃጠለ ተናግረው፥ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

    የጥቃት ድርጊቱን የፈጸመው አካል ኦነግ ሸኔ መሆኑን ገልጸው፥ ከጀርባ በመሆን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እየደገፈው እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለይም ቡድኑ የታጠቃቸው እንደ ስናይፐርና ብሬል ያሉ የጦር መሳሪያዎች ህወሓት ያስታጠቀው እንደሆነ ገልጸዋል። ከኦነግ ጀርባ በመሆን ህወሓት በህብረተሰቡ ላይ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነም አክለዋል።

    ጥቃት የተፈጸመበት ቀበሌ ከወረዳ ከተማ በ75 ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሆኑን ገልጸው፥ ህወሓት በብሔሮች መካከል ግጭት ለመፍጠር በስሌት የፈጸመው ተግባር ስለመሆኑ ተናግረዋል።

    ከድርጊቱ ፈጻሚዎች መካከል የተወሰኑት መያዛቸውን ተናግረው ቀሪዎቹን ለመያዝ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም ከሕብረተሰቡ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት

    በተያያዘ ዜና፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ መንግስት የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት ምሁራንና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።

    “በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልፃለሁ።

    የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት አቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።

    ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።

    መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።

    የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።

    ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።

    መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።

    ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።”

    • የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት

    የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት የሚከተለውን ብለዋል።

    “በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ሀዘን እየገለፅኩ፥ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ።

    በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ሲል ብሔርን፣ ሀይማኖትን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የማድረስ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።

    በተለይ የአማራን ማኅበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው። ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ በመሆኑ፥ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በዘላቂነት ለማበጀት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግሥትና ሕዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል።”

    • የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ

    ይህንን ጥቃት ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ብሏል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያንብቡ።

    • የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ፥ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን እንደማይችል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።

    • የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት በተገደሉት እና ጉዳት በደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን” በማለት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ፓርቲው በዚሁ መልዕክቱ፥ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአንድነት በመቆም የዘውግ ፖለቲካ ያመጣብንን በሕይወት የመኖር እና እንደ ሀገር የመቀጠል አደጋ ልንታገለው እንደሚገባና፤ ኢዜማ አጠቃላይ የሀገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ በቀጣይ ቀናት መግለጫ እንደሚሰጥ አመላክቷል።

    በማስከተልም፥ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሐዘን ሲሆን፤ የጥቃቱ ዓላማም ሀገርን የማፍረስ መሆኑን ተረድተን ሀዘናችንን በጋራ በመግለፅ በአንድነት እንድንቆም እንጠይቃለን ሲል መልዕክቱን ቋጭቷል።

    • የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ካወገዘ በኋላ፥ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሱት ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ናቸው ማለቱን በከፊል በማስተባበል፤ ይልቁንስ ኦነግ ሸኔ የሚባል ቡድን በአካል እንደሌለ ገልጿል። የኦነግን ሙሉ መግለጫ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።

    • የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ

    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ደግሞ በሰጠው መግለጫ፥ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ዘር-ተኮር ጥቃት የፌደራል መንግሥቱን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ  ግንባር ቀደም ተጠያቂ እንደሆነ አትቷል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር ያገኙታል።

    በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር

    Anonymous
    Inactive

    የወቅቱ አብይ ጥያቄ – የህወሓትን ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ በጋራ ቆመን፣ በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ነው
    አቶ ነአምን ዘለቀ

    ሰላም ወገኖቼ፥

    የወቅቱ አብይ ጥያቄ ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ኢትዮጵያዊነት ከህወሓት ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ በጋራ ቆመን፣ ከዳር እሰክዳር በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ነው። መሆን ወይንም አለመሆን ነው ለእያንዳዱ ዜጋ የቀረበው ጥያቄ!

    የክፋት፣ የነውር፣ የመሰሪነት ጥግ የሆኑት፣ ይህ ነው የማይባል ዘረፋ፣ ዘረኝነትና ግፍ በሚሊዮኖች ዜጎች ላይ የፈጸሙ፣ በእውነቱ ቃላትም የማይገልጻቸው የህወሓት መሪዎች ኢትዮጵያን በበላይነት ካልገዛን ትፈርሳለች የሚል ለዘመናት የቆየ ቅዠት እውን ለማድረግ እየተቅበዘበዙ መሆናቸውን የሰሞኑ ዋና መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል። ከነበራዊ እውነታ ጋር የተጣሉ፣ የሞራልም የእእምሮም በሽተኞች በመሆናቸው የ27 ዓመት የክፋት፣ የዘረፋ፣ የከረፋ ዘረኝነታቸው ውስጥ ፍዳውን ሲያይ የነበሩ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጎች የሚረዳው መሆኑ ግልጽ ነው።

    ከለውጡ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አመራር የነዚህን ጉዶች ባህርይና ለዘመናት የተተበተበ በሽታ በሚገባ ተገንዝቦ፣ ስትራቴጂም ነድፎ ህወሓትን የማዳከም ልዩ ልዩ እርምጃዎችን መወሰድ ይገባው ነበር። ያ ግን አልተደረገም። በተለይም ወንጀለኛውን ጌታቸው አሰፋ ሕግ ፊት እንዲቀርብ የፌደራል መንግሥቱ ሲጠይቅ አናስረክብም ባሉ ጊዜ፥ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎችም ግጭት ለመፍጠር በርካታ የሳቦታጅ ሥራዎች ማደራጀታቸው፣ መቆስቆሳቸው በሚገባ የሚታወቁ ሆነው ሳለ፥ ፈዴራል መንግሥቱ ከጦርነት በመለስ ሁሉንም የመንግሥት ማድረግ አቅም መጠቀምና ህወሓትን አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ነበረበት። በቅርብ ሳምንት በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በአማራ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የተደረገውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በገንዘብና በመሣሪያ ያገዙ፣ በክልሉ ሰፊ መሬት ያላቸው የህወሓት አባል የሆኑ ባለሃብቶች መሆናቸው የክልሉ መንግሥት ባለስልጣን ለኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የተናገረውን ልብ እንበል።

    በመንግሥት አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ተንሠራፍቶ የነበረ ‘የት ይደርሳሉ?’ መሰል የተዛባና አደጋውን የመረዳት የማይመጥን አመለካከት ሳቢያም፣ ህወሓትን የልብ ልብ ሰጥቶ ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት ለመክተት፣ በዚህም የትግራይንም ሆነ የሌላውን ኢትዮጵያዊ በጦርነት እሳት ለመማገድ ዛሬ ላይ የደረሰበት የለየለት እብደት እንዲደርስ ዕድል ባልተሰጠው ነበር፤ አጥፍቶ ከመጥፋትም አይመለሱም። ያ በሀገርና በሕዝብ ላይ የነበራቸውንም ዓይን ያወጣ የጥቂት ዘረኞች የበላይነት፣ ፈልጭ ቆራጭነት እንዳይመለስ አጥተውታልና አዲሱን እውነታ ፈጽሞ ተቀበለው በእኩልነት፣ በአቻነት ሊኖሩ በዘረኝነት፣ በትምክህትና በትእቢት የታጨቀው አእምሮአቸው አይፈቅድላቸውም።

    ለሁለት ዓመት ተኩል የተዘጋጁበት፣ ከጅምሩም ህወሓትና አጋሮቹ እንደ ጊዜ ቦንብ እንዲፈነዳ ቀብሩውት የነበሩት ሰፋፊ የማንነት ስንጥቆች፣ የብሔር ቅራኔዎችን ተጠቅመው ሀገሪቱን በቀውስ ውስጥ ለመክተት፣ ብሎም ለመበታተን ላሰፈሰፉ በየክልሉ ያደፈጡ ጽንፈኞችም ምቹ ሁኔታዎችንም ፈጥሯል። የህወሓት መሪዎች ለበርካታ ዓመታት የነደፉትን መሰሪ ‘ፕላን B’ የሆነውን አባይ ትግራይ-ትግራይ ትግሪኝ፣ ወዘተ… ለመመሥረት የሚችል መስሏቸው እየተንፈራገጡ ይገኛሉ። ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ግልጽ መሆን ያለበት የጦርነት እሳት ኢንዲቀጣጠል፣ ብሎም በመላው ኢትዮጵያ እንዲዛመት ያላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ የሚገኙት መሰሪዎቹ ጸረ-ኢትዮጵያ የህወሓት መሪዎች በጠላትነት የፈረጁት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ መሆን ይገባዋል፤ ወይንም ፈደራል መንግሥቱ፣ የብልጽግና ፓርቲ አይደሉም።

    ይልቅስ ዓይን ቀቅሎ የበላው የሀሰትና የነውር ቋት የሆነው የስዩም መስፍንና ሌሎቹ የህወሓት መሪዎች መሠረታዊ ግብ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ነው። በፍርስራሹም ላይ በዘረኝነት የታጨቀው የትግራይ ትግርኝ ሀገር መንግሥት የመመሥረት ቀቢጸ-ተስፋ እውን የማድረግ ግብ ነው። ይህ ነው አብይ ግባቸው። ለምን ቢባል የህወሓት መሪዎች ኢኮኖሚውን፣ መከላከያውን፣ ደህንነቱን፣ የውጭ ጉዳዩንና ባጠቃላይም በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ላይ በበላይነት የማያሸከረክሩባት፣ ፈላጭ ቆራጭና ሁሉን አድራጊ ፈጣሪ፣ ሌላው የእነርሱ አጎብዳጅ፣ ፈርቶና ተጎናብሶ የማይኖርባት የ27 ዓመቷ ኢትዮጵያ ማስቀጠል የማይችሉበት ነባራዊ ሁኔታን እንዴት ተቀብለው ሊኖሩ ይችላሉ?

    ልብ እንበል፤ ቆም ብለን በቅጡ እናስብ፤ ያቺ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የለችም። ይህን እጅግ መራር እውነታ ሊቀበሉ ሊውጡት ደግሞ ፈጽሞ አልቻሉም። የእነ ስዩም መስፍን “ዓይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ” የለየለት ውሸቶች፣ ማስመሰሎች፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቆመው፣ ሠርተው እንደነበር፣ ለሕዝብ ጥቅም የታገሉና ሲሠሩ እንደነበሩ ለቀባሪው ማርዳት ሙከራዎች ሁሉ ከዚህ ሃቅ የሚመነጭም ጭምር ነው። ይህን ሃቅ አስምረን ግልጽና ፍንትው አድርገን ማየት ቀዳሚው ተግባር ነው። ህወሓት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች የቆመበትና የሠራበት ሁኔታና ጊዜስ መቼ ነበሩ? ብለን ብንጠይቅ፣ እነ ስዩም መስፍን ነጋ ጠባ ሊያጭበረብሩን ከሚሞክሩት ውጭ ማንም አፉን ሞልቶ ሊመሰክር የሚችል ኢትዮጵያዊ የሚገኝ አይመስለኝም። ሀገሪቱን እንደ ቅኝ ተገዢ ሲመዘብሩ፣ በከረፋ ዘረኝነታቸውም ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ የበታችና 3ኛ ዜጋ ሲያንገላቱ፣ ሲገፉ፣ በንቀት ሲመለከቱ፣ ሲዘርፉና ሲገድሉ የነበረው መራራ ታሪክ ሁሉም ያለፈበት የቅርብ ጊዜ አስነዋሪውና አሳፋሪው ትሪካቸውና የእኛም የኢትዮጵያውያን ቁስል ነውና።

    ለምን? ምክንያቱም ከጅምሩም የተነሱበት መሠረት በመሆኑ ለአያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግልጽ መሆን ይገባዋል፤ መወናበድ ማክተም አለበት። ለአወናባጆችና ውዥንብር ነዥዎችም ሰለባ መሆን የለብንም፤ ብዙዎች ከዳር ቆሞው ጉዳዩ የዐቢይ አህመድ እና የህወሓት ጠብ አድርጎ መመልክት በሀገርና በሕዝብ ላይ ትልቅና ከባድ አደጋ፣ እንደ ሀገርና ሕዝብ ለውድቀትም ሊዳርግ የሚችል፣ ይህ ነው ተብሎ ሊገመት የማችል ዋጋ የሚያስከፍል ስህተት ይሆናል። አለፍ ሲልም ቅጥረኞችና ከራሳቸው ጥቅም በላይ ለጋራ ሀገር፥ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ማሰብ የማይችሉ፣ ዐቢይን ሰለጠሉ ኢትዮጵያም ሆነች ሀገረ መንግሥቱ ቢፈርስ፣ በፍርስራሹ ላይ ስልጣን የሚያገኙ የሚመስላቸው እኩዮች “ፓለቲካ ሊያስተምሩን” እንደሚዳዱት የህወሓትና የፌደራል መንግሥቱ/የብልጽግና ጠብና ግጭት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የህወሓት መሪዎች እንቅስቃሴ በሀገራችን ኢትዮጵያና በሕዝብ ሰላም፣ ደህነትና መረጋጋት ላይ የመጣ የህልወና አደጋ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው።

    የዛሬው አብይ ጥያቄ ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ኢትዮጵያዊነት ከህወሓት ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ ማምከን ነው። መሆን ወይንም አለመሆን ነው ለእያንዳዱ ዜጋ የቀረበው ጥያቄ።

    ነአምን ዘለቀ

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የወቅቱ አብይ ጥያቄ የህወሓትን ሀገር አፍራሽ ሴራ በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ነው

    Anonymous
    Inactive

    ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ
    (የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮን በተመለከተ)

    የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ፌዴራዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 87 በተደነገጉ ግልጽ መርሆዎች መከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1100/2011 በተሰጡት ግዳጆች መሠረት ዝርዝር ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ደንቦች እና መመሪያዎችን በማውጣት፥ በሀገራችን ላይ የተቃጡ የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን በመመከት የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስከብሯል። የሕዝብንም ሰላም በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።

    መከላከያ ሠራዊቱ የአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሰላም የእኛም ሰላም ነው በሚል መርህ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ ዛሬም ግዳጁን በአስደናቂ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል።

    ከሁሉም በላይ የዓለም ሕዝቦችና የቀጠናችን ብሎም የሀገራችን ዋነኛ ጠላት የሆነውን አሸባሪነት ለመዋጋት በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የመሸገውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በመመከት ቀጠናችን ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ እንዲሆን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ነው።

    በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አለመረጋጋቶችን ከሌሎች የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች፣ ከክልል መስተዳድሮች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና በዋነኝነት ከሕዝባችን ጋር በመተባባር ችግሩን ለመቅረፍ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲመጣ ሠርቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚህ ተግባሩ ሠራዊታችን በደረሰበት ቦታ ሁሉ ሕዝብ ከፍተኛ የሰላም አየር የሚተነፍስ እና እፎይታ የሚሰማው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህያው ምስክር ናቸው።

    ከእነዚህ የሠራዊቱ አኩሪ ድሎች የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ ሠራዊታችን ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል በአንድ ጊዜ ግዳጆችን መወጣት የሚችል፣ ለፈተናዎች የማይበገር፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝቦች ሰላም ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ የማይል ሕዝባችን የሚመካበት ሠራዊት መሆኑን ነው።

    የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥

    የመከላከያ ሠራዊታችን የተጋድሎና የአሸናፊነት ገድሉ በወታደራዊ ስምሪት እና የግዳጅ አፈጻጸም ላይ ብቻ ሳይገደብ የሕዝብ ችግር ችግሬ ነው የሚል የሕዝቦች ደህንነትና ኋላ ቀርነት የሚያንገበግበውና የሚቆጨው ያለውን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይል፣ የሕዝባችን አለኝታ የሆነ የልማትና የሰላም ሠራዊት ነው።

    የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነትና የጥንካሬ መለያ የሆነውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ሠራዊቱ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ ከወር ደመወዙ በማዋጣት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አስተዋጽኦ ከማበርከት አልፎ፤ በግድቡ ላይ ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ለመመከት ሌት ተቀን ዘብ ቆሞ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።

    መከላከያ ሠራዊታችን ከራሱ በፊት ለሕዝቡና ለሀገር የሚለውን እሴት መሠረት በማድረግ የሀገራችን ሕዝቦች ለገጠማቸው ሰው-ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን አብነት የሚሆን ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።

    በጎርፍ አደጋ ዜጎች የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቀነስ፣ በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ፣ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተሰማርቶ በማገዝ፣ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን ኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል፣ ከደመወዙ ቀንሶ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ፣ ገበታ ለሀገር ፕሮጀከት እውን እንዲሆን የወር ደመወዙን በማዋጣት እና በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ ከሕዝቡ ጋር በመሆን በመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረ ተግባሩን ከመጀመሪያውኑ ሠራዊቱ የታነጸበት መሠረታዊ ባህሪው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሃቅ ነው።

    መከላከያ ሠራዊታችን ሀገራዊ ግዳጆቹን ሲወጣና ሕዝባዊ ተግባራቱን ሲያከናውን የሚገጥሙትን ችግሮች ሁሉ በመቋቋም ፈተናዎችን በጽናት ተጋፍጦ በማለፍና ውድ ህይወቱን መስዋዕት በማድረግም ጭምር መሆኑ በሕዝባችን የሚታወቅ ሃቅ ነው።

    ይሁን እንጂ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሰላም የማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን በጀግንነትና በቁርጠኝነት እየተወጣ ባለበት በዚህ ሰዓት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የማይፈልጉ ቡድናዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሠራዊቱን ስምና ዝና በማጠልሸት በመርህና በሕግ ላይ ያልተመሠረተ የትችት ናዳ በማውረድ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፥ ሠራዊቱ ይህን የፀረ-ሰላም ኃይሎች አጀንዳ በውል በመገንዘብ ትኩረቱን ግዳጁ ላይ ብቻ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።

    የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥

    ሰሞኑን በተለያዩ የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ የአቋም መግለጫ በሚል ርዕስ ስር መግለጫ ያወጣው አካል ሠራዊቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች የተካተቱበት ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ አሰራጭቷል።

    በዚህ መግለጫ 1ኛ ተራ ቁጥር ላይ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 87(5) ድንጋጌ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባር ከፖለቲካ ወገንተኝነት  ነጻ በሆነ አኳኋን እንደሚያከናውን የተደነገገውን መርህ በሚጥስ መልኩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ተወያይተው ከሚሰጡት መፍትሄ ውጭ መከላከያ የአደረጃጃት፣ የስምሪትና የቁጥጥር ተግባሩን መፈጸም አይችልም በማለት መከላከያ በተቋማዊ ዕቅዱ እንዲሁም ወቅታዊና ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መነሻ አድርጎ ግዳጁን እንዳይፈጽም በሚገድብ አኳኋን የተዛባ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል።

    በዚህ መግለጫ ተራ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ በዝምታ እንዳለፈና የሕገ-ወጥ የፖለቲካ ኃይሎች ጥቅም አስጠባቂ ኃይል መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት በመግለጫ ላይ ተካቷል።

    እውነታው የመከላከያ ሠራዊታችን የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተሰማርቶ አስፈላጊ ተገቢና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ይህንን በተጻረረ መልኩ ሠራዊቱ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ነው በማለት የመከላከያ ኃይሉን የማይመጥን፣ ተቋሙ ለሀገርና ለሕዝብ የከፈለውን እና እየከፈለ ያለውን ክብር መስዋዕትነት የሚያንኳስስ ሀገራዊ ተልዕኮውን እና አኩሪ ታሪኩን የሚያጠልሽ መልዕክት ይህ አካል ባወጣው መግለጫ ተስተጋብቷል።

    ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይህ አካል መከላከያን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ በማስተጋባት ፍጹም የሠራዊቱን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በማራከስ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።

    ይህ ተግባር መከላከያ ሠራዊቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከክልሉ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ጥረት በሚያደርግበት የክልሉ ሕዝብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ትርጉም ባለው ደረጃ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እያስመሰከረ ባለበት እና አጠቃላይ በክልሉ ያለውን ስምሪት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዓላማ አድርጎ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁነቱን ባረጋገጠበት ወቅት የሠራዊቱን ተልዕኮ የሚገድብ መግለጫ ማውጣቱ አግባብነት የጎደለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል።

    ይህ መግለጫ የሠራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል ሀገራዊና ክልላዊ ተግባሮቹንም በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደናቅፍ ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ነው።

    ከዚህ በፊትም እነዚህ አካላት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ ላይ የነበሩ ቢሆንም ለሕዝቦች ክብር እና ጥቅም ሲባል በከፍተኛ ኃላፊነት መንፈስ ለማለፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። መላው የሀገራችን ሕዝቦች እንደሚገነዘቡት የመከላከያ ሠራዊታችን የማንም ፖለቲካ ኃይል፣ ክልል ወይንም ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብርላቸው፣ ሰላምና ደህንነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው የገነቡት ጠንካራ፣ ብሔራዊና ሀገራዊ ተቋም ነው።

    ስለሆነም የሠራዊቱን አደረጃጀት፣ ስምሪትና የግዳጅ አፈጻጸም የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሠራዊቱ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠለትን መርህና በአዋጅ የተሰጠውና ግዳጅና ተልዕኮ መሠረት በማድረግ ተግባራቱን በራሱ የሚወስን እንጅ የሠራዊቱን አጠቃላይ ተልዕኮ እኔ ነኝ የምወስንልህ በሚል አግባብ ይህ አካል የሰጠው መግለጫ የሠራዊቱን ገለልተኝነት የሚጋፋ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል።

    ይህ ወቅት የሀገራችን ሕዝቦች እንደ ሀገር የገጠማቸውን ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በመመከት ሰላማቸውን ለማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የሀገራችንን እድገት የማይፈልጉ አካላት በተለይ ከሕዳሴ ግድባችን ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ በሚጻረር መልኩ በእጅ አዙር እና በቀጥታ ጥቃት የሚፈጽሙበትና አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሀገራችንን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት ዓላማ አድርገው በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ እና የማፈናቀል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል።

    መከላከያ ሠራዊት ከሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ የደህንነት ስጋቶችን ለመመከት የሚያስችል ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ባለበት እና በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ለማስቆም አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና መልክዓ ምድራዊ ቦታዎች ዘልቆ ሰፊ ስምሪት በማድረግ፣ ክቡር መስዋዕትነትን በመክፈል የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ጥረት በሚያደርግበት በዚህ ወቅት መግለጫውን ያወጣው አካል የሠራዊቱን ወርቃማ ዕድል በሚያጎድፍ መልኩ ሠራዊቱን በሚመለከት ያሰራጨው መልዕክት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

    ጉዳዩ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በቀጥታ የሚቃረን፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስምሪት እና ተልዕኮ በምንም መልኩ በአንድ አካል ወይም ቡድን ስር የማይወድቅ ሕጋዊና ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ አግባብ ብቻ የሚመራ መሆኑን እያስታወቅን፤ መግለጫውን ያወጣው አካል ስህተቱን በይፋ እንዲያርም አጥብቀን እንጠይቃለን። ማንኛውም አካል የሠራዊቱን ተልዕኮ በሚያደናቅፍ አግባብ መግለጫ ከመስጠት እና አላስፈላጊ መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብም እናሳስባለን።

    የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሀገርና ሕዝብ የሰጠንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በገባነው ቃልኪዳን መሠረት ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በመሆን፣ ክቡር የሆነውን ህይወታችንን በመክፈል ጭምር የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ የምንገኝ መሆኑን ለመላው ሕዝባችን እያረጋግጥን የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም እንደወትሮው ሁሉ ከጎናችን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    መላው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት፥

    እኛ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በተጋድሎና በድል የደመቀ አንፀባራቂ ታሪክ ያለን ሠራዊት ነን። በከፍተኛ ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ፅናት ምድራዊ ፈተና ተቋቁመን እና ጥሰን በማለፍም ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሰላም፣ ደህንነትና ልማት ስንል ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት እየከፈልን አልፈናል። በቀጣይም ከዚህ ጉዟችን ሊያደናቅፉን የሚጥሩ፣ ከተልዕኳችን ሊገድቡን ከሚሞክሩና አንድነታችንን ሊሸረሽሩ በሚታክቱ ማንኛውም ዓይነት ኃይሎች ሴራ ሳንገታ ደማቅ ታሪክ መሥራታችንን እንቀጥላለን።

    የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
    ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት

    Anonymous
    Inactive

    የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሃሳብ ሊደገፍ የሚገባው ነው
    የሺዋስ አሠፋ

    ወ/ሮ ሙፈሪሃት የፌደራል መንግሥቱን (ብልፅግና) እና የትግራይ ክልል አስተዳደርን (ህወሓት) መካረር በተመለከተ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገለፁትን አይቼ በግሌ ጥሩ ጅምር ነው – ይበርቱ ብያለሁ። ስድብ፣ ፉከራ እና ይዋጣልን ሀገርን እና ሕዝብን ምስቅልቅል ውስጥ ከመክተት ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም። “እልህ ምላጭ ያስውጣል” እንዲሉ ለራሳችሁም ቢሆን ውስጣችሁን የሚቆራርጥ ከሚሆን በስተቀር አይጠቅምም። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቋራጭ መንገድ የለውም፣ ውይይት/ድርድር ብቻ! በጉልበት/በጠመንጃ የሚሆን ቢሆን ኢትዮጵያን የሚቀድም ባልነበረም ነበር። ልብ በሉ ለውይይት አሻፈረኝ የሚሉ ወገኖች በስተመጨረሻ ቢፈልጉ አያገኙትም፤ ምክንያቱም አይበለው እንጂ ጦርነትም ቢሆን መቋጫው ውይይት/ድርድር ነው።

    በ2009 ዓ.ም ራሳቸው ወ/ሮ ሙፈሪሃት የነበሩበትን የፓርቲዎች ውይይት/ድርድር (ስያሜው ራሱ አወዛጋቢ ነበር) ባስታውሳቸው ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል። ሙከራው የተቀጨው ከጅምሩ ነበር። የቀድሞ ገዢ ፓርቲን ጨምሮ 22 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት ውይይት/ድርድር የመሀል ዳኛ (mediators) ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም በሚለው የጦፈ ክርክር ተደርጎ ኢህአዴግ እና ሌላ አሁን ስሙን የማላስታውሰው አንድ ፓርቲ አያስፈልግም ሲሉ 20 ፓርቲዎች ያስፈልጋል ብለን በከፍተኛ ቁጥር አሸነፍን፣ mediators ሊሆኑ የሚችሉትን ወገኖች የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ መግለጫ (ማለትም፥ CV) እና ዝርዝር ማዘጋጀት ጀመርን።

    በዚህ የተናደዱት የሂደቱ ፊትአውራሪ የነበሩት የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ [የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል] ለሳምንት እንደገና እንየው ብለው በተኑት። በሳምንቱ ራሳቸው አጀንዳውን አንስተው mediators ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም እጅ አውጡ ሲሉ ጠየቁ። ከመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ውጭ ሁሉም አያስፈልጉም አሉ። በሳምንት ልዩነት 20 ለ 2 ውጤቱ ሲገለበጥ ወ/ሮ ሙፈሪሃት እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ይታዘቡ ነበር።  እኔም በጣም ተበሳጭቼ “የተከበሩ አቶ አስመላሽ! ሳምንቱን ሙሉ ሲደልሉና ሲያስፈራሩ ሰንብተው ውጤቱን በጉልበት አስቀየሩት! ይሄ ጉልበት ግን አይቀጥልም፤ ነገ በሌላ ጉልበት ይሰበራል!” ብዬ ትቻቸው ወጣሁ። ሂደቱም ተጨናግፎ ቀረ (በወቅቱ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ዘግቦታል)። ከ3 ዓመታት በኋላ እነአቶ አስመላሽን ወክለው አቶ አዲስዓለም ባሌማ ሁሉን አካታች ውይይት/ድርድር እናድርግ ብለው ሲጠይቁም፣ ያልተገባ ምላሽ ሲሰጣቸውም በተራዬ በትዝብት ተመለከትኩ።

    ዛሬ የመንግሥት አካል ከሆነው የሰላም ሚኒስትር መፍትሄው ውይይት/ድርድር ነው የሚል ተነሳሽነት ሲመጣ አያስፈልግም ብሎ መታበይም ሆነ ተለመንኩ ብሎ ማጣጣል አይገባም። ሚኒስትሯ እንዳሉት፥ ከስሜት ወጥቶ፣ ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በእኔ እምነት ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው፤ ቀጣዩን ታሪክ ለመሥራት መሽቀዳደም ለኢትዮጵያ ውለታ ነውና ማን ይሆን ፈጥኖ ወደ መቀሌ ከተማ ወይም ወደ ወለጋ ጫካዎች ነጭ ባንዲራ ይዞ የሚዘምተው? (የኬንያው Building Bridges Initiative (BBI) ጥሩ መማሪያ ይሆነናል) ወይም ወደአዱ ገነት የሚመጣው? የወጣቶቻችንን ህይወት ከመቀጠፍ፣ የእናቶቻችንን እንባ ከመፍሰስ የሚታደገው? ከፌደሬሽን ምክር ቤት? ከሰላም ሚኒስትር? ከሀይማኖት አባቶች? ከእርቀ-ሰላም ኮሚሽን? ከሀገር ሽማግሌዎች? ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች? ከአባ ገዳዎች? ከጋሞ አባቶች? እናቶች? ከወጣቶች? ከህፃናት?… ማን ይሆን በሞራል ልዕልና እና በመንፈስ ከፍታ ቆሞ ከኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሚጥመለመለውን የጥላቻ አውሎ ነፋስ ገስፆ የሚያስቆመው? እስኪ “እኔ አለሁ” በሉ! (እኔ እንዳልሞክር ፓርቲ ውስጥ መሆን ይሄን ነፃነት አይሰጥም) ግን ኢትዮጵያ የሰው ድሃ አይደለችምና ፍጠኑ። ሰላም!

    የሺዋስ አሠፋ

    አቶ የሺዋስ አሠፋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)  ሊቀ መንበር ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው ሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ነበሩ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ የሺዋስ አሠፋ

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 70 total)