-
Search Results
-
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!
(ያሬድ ኃይለማርያም*)
በ1994 እ.ኤ.አ. ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በዋናነት የመሩት ሁለት ሬድዮ ጣቢያዎች ነበሩ። አንዱ በመንግሥት ስር የነበረው ሬድዮ ሩዋንዳ (Radio Rwanda) የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው እና ዋናው የእልቂቱ አነሳሽና ቀስቃሽ የነበረው Radio Télévision des Milles Collines (RTLM) ተብሎ የሚጠራው ጣቢያ ነበር። ይህ ጣቢያ በወቅቱ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ስለነበር በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን እና የቀኝ አክራርሪ የሆኑትን የሁቱ ኢንተርሃሞይ ሚሊሻዎችን (Interahamwe militia) በቀላሉ ወደ ጥላቻ በመንዳት በመምራት እና እልቂት እንዲፈጽሙም በማነሳሳት ትልቅ ሥራ ሠርቷል። ይህ ጣቢያ ከእልቂቱም በፊት ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል ጥላቻን ሲሰብክ ቆይቷል።
ዛሬ ደግሞ ተራው የእኛ በሚመስል ሁኔታ እጅግ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ለዓመታት ጥላቻን ለኦሮሞ ወጣቶች እና ለኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ሲሰብክ የነበረው OMN የተባለው ሚዲያ የወንድማችንን ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ባስተላለፋቸው ተከታታይ የአመጽ እና የእልቂት ጥሪዎች እና ቅስቀሳዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል። ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ልክ የሩዋንዳው RTLM እንዳደረገው ሁሉ ጥሪው ክልሉ ውስጥ ላሉ ሥራ-አጥ ወጣቶች እና በሽኔ ስም ለሚጠሩት ሚሊሺያዎች ነበር። በዚህም እጅግ ለመስማትና ለማየት የሚሰቀጥጡ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲፈጸሙ ተደርጓል። ሰዎች እቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከነቤተሰቦቻቸው በእሳት ጋይተዋል፤ ህጻናት፣ ሴቶች እና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በስለት እና በቆንጨራ ተቆራርጠው ተገድለዋል፤ እናት ከህጻን ልጇ ጋር በአንድ ገመድ ታንቃ ተገድላለች፤ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል፤ ብዙዎች ከቤታቸው ሸሽተው በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ተደብቀዋል።
አንዳንድ እማኞች በመገናኛ ብዙኃን ምስክርነታቸውን እንደሰጡት እና እኛም ማረጋገጥ እንደቻልነው ለጥቃት የተሰማሩት ኃይሎች በቂ ዝግጅት ያደረጉ፣ የተለያዩ የጥቃት መሣሪያዎችን የያዙ እና የጥቃት ዒላማ የሆኑ ሰዎችን ስም እና አድራሻም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ ተችሏል። ነገሩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በክልሉ ውስጥ ያሉ የክልሉ ታጣቂ ኃይሎች ይህ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ድርጊቱን ለማቆም አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው። በአሜሪካ ድምጽ (ቬኦኤ) እና አንዳንድ ሚዲያዎች እንደተዘገበውም በተወሰኑ ቦታዎች የመንግሥቱ ታጣቂዎች ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ጥቃት ሲፈጸም እያዩ ዝምታን መርጠው መቆየታቸው ነው። በሩዋንዳም የዘር ማጥፋት ጥቃት ሲፈጸም የሆነው ይሄው ነበር። እነዚህ ኃይሎች በምንም መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል የበቀሉ እንክርዳዶች ናቸው። በመሆኑም እንዲህ ያሉ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ ቡድኖችን እና ነገሩን በቸልታ ሲያዩ በነበሩ የክልሉ ኃላፊዎች ላይ በቂ ምርመራ ሊካሔድ እና በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።
OMN አዲስ አበባ ያለው ጽሕፈት ቤቱ ቢዘጋም ተመሳሳይ የእልቂት ጥሪዎችን ከሀገር ውጭ ባሉ ባልደረቦቹ በኩል ሲያስተላልፍ ቆይቷል። ዛሬ ደግሞ ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ አየር ላይ ያዋላቸውን እና በዩቲዩብ (YouTube) የተላለፉ ዝግጅቶቹን ከአየር ላይ እያወረደ እና መረጃዎችን ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፦
(፩ኛ) የእነዚህ የእልቂት ጥሪዎች ቅጂዎቻቸው ጣቢያው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት እጅ ስለሚገኙ እና የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲውም የእነዚህ ቅስቀሳዎች ቅጂ እንዳለው ባለሥልጣኑ ስለተናገሩ ጣቢያው መረጃ ለማጥፋት እያደረገ ያለው ጥረት ይሳካል ብዬ አላምንም። ነገር ግን እነዚህ መረጃዎች በመንግሥት በኩል በቂ ጥበቃ ተደርጎላቸው በክልሉ ውስጥ ለተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ያላቸው አስተዋጽኦ በአግባቡ ሊመረመር ይገባል፤
(፪ኛ) በOMN የተላለፉ የዘር ተኮር ቅስቀሳ ቪዲዮዎች እና ዘገባዎች በእጃችው ላይ የሚገኝ እና ጉዳዩ የሚያሳስባችው ግለሰቦች፤ እንዲሁም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና አንዳን አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፍ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ያላችሁ ሰዎች በዚህ የኢሜል አድራሻ end.empunity.eth@gmail.com እንድታቀብሉን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
ዘር ተኮር ጥቃት ይቁም!
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያካሄደውን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀመንበርነት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን በአቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን በመተካት፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አመራሮችን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቀቀ።
ደብረ ብርሃን (አብን) – የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኘበት በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አብን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለሥ በሚያስችለውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ይገኝ ዘንድ ላለፉት ጊዜያት የመጣበትን መንገድ መርምሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ ማሻሽያ መዘጋጀቱን ገለፀው በዚህ ላይ ጠቅላላ ጉባዔው በደንብ ተወያይቶ አቋም እንዲይዝበት ጠይቀዋል።
ጉባዔው በመጀመረያ ቀን ውሎው የአብን መዋቅራዊ ማሻሽያ (reform) አስፈላጊነትና አላማ፣ የንቅናቄው ጥቅል የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የፋይናንስ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት፣ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሪፖርት፣ የተሻሻለው የንቅናቄው መተዳደሪያ ደንብና ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኃላ አፅድቋል።
ጠቅላላ ጉባዔው 5 ተለዋጭ አባላት ያሉት 45 የንቅናቄውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥም መርጦ ያፀደቀ ሲሆን የተመረጡት አባላትም የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጠዋል። በተጨማሪም በሊቀመንበሩ የቀረቡለትን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚዎችን አፅድቋል። በዚህም መሠረት 9ኙ የአብን ሥራ አስፈፃሚ አመራሮች፦
- አቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን – ሊቀመንበር፣
- አቶ የሱፍ ኢብራሂም – ምክትል ሊቀመንበር፣
- አቶ አዲስ ኃረገወይን – የፖሊሲ ስትራቴጂ ኃላፊ፣
- አቶ ጣሂር ሞሐመድ – የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
- ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም – የውጭ ጉዳይ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት
- አቶ ጋሻው መርሻ – የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣
- አቶ መልካሙ ፀጋዬ – የፅሕፈት ቤት ኃላፊ፣
- አቶ ጥበበ ሰይፈ – የሕግ እና ሥነ-ምግባር ኃላፊ፣ እና
- አቶ ክርስቲያን ታደለ – የፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው።
ምንጭ፦ አብን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦
- የህወሓት አመራሮችና አባላት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ህወሓት የሰጠው መግለጫ
- ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ
- ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ መፍርሱን እና ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ንብረት እንዲከፋፈል ምርጫ ቦርድ አጸደቀ
- በኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ― ኦነግ
- በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው! የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
በኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ሊደረግበት ይገባል
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫከምዕራብ ኦሮሚያ (የወለጋ ዞኖች) ቴሌፎንና ኢንተርኔትን የመሳሰሉት የመገናኛ አገልግሎቶች በመንግሥት ከተቋረጡ አንድ ወር አለፈ። ከዚህም የተነሳ የዕለት ተዕለት ክስተቶችን በጊዜዉ ከነበቂ መረጃ ጋር ማግኘት አዳጋች ቢሆንም እንኳ የመንግሥት ወታደሮችና ታጣቂዎች በሰላማዊ (ትጥቅ-አልባ) ዜጎች ላይ እያካሄዱ ባሉት ግድያ የሰዎች ሕይወት እንደቅጠል እየረገፈ መሆኑ መተለያየ መንገድ እየተሰማ ነዉ። በተለይም በሁለት ዞኖች (ምዕራብ ወለጋ እና ቄሌም ወለጋ) ዉስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች በሕዝቡ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ግድያና ጭፍጨፋ በቃላት መግለጽ እንኳን ይከብዳል። የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የጦር ወንጀል የሚሉት ቃላቶችም በትክክልና በበቂ ሁኔታ ልገልጹት አይችሉም። በደቡብ ኦሮሚያ (በጉጂ ዞኖች) ያለዉ ሁኔታም እምብዛም ከዚህ የተለየ አይደለም። በዚህ መልኩ ከአንድ ዓመት በላይ በወታደራዊ አስተዳደር (ኮማንድ ፖስት) ሥር በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለዉን እሮሮና ስቃይ በተለያዩ ጊዜያት ገልጸን መፍትሄ እንድፈለግለት ብንወተዉትም እስካሁን የሕዝባችን ኡኡታና ችግሩ ተገቢዉን ተሰሚነት ሊያገኝ አልቻለም።
ባሁኑ ጊዜ በተጠቀሱት ቦታዎች በተለይና በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ባጠቃላይ በሰላማዊ (ትጥቅ-አልባ) ዜጎች ላይ የሚፈጸም ግድያና ጭፍጨፋ፣ የጅምላ እስር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ መባረር፣ ባጠቃላይ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣና የጦር ወንጀል (war crime) ከመቼዉም ጊዜ ባላይ ዘግናኝና ከባድ ሆኗል። በነፃና ገለልተኛ አካል የሚደረግ ምርመራ፣ እንዲሁም አስቸኳይ መፍትሄ የሚፈልግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነዉ ብለንም እናምናለን።
ሆን ተብሎ በዶ/ር አብይ አህመድ በሚመራዉ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰላማዊ ሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለዉን ይህንን እሮሮና ሰቆቃን እጅግ አጥብቀን እናወግዛለን። ይህ እሮሮና መከራ ባስቸኳይ እንድቆምም አበክረን እንጠይቃለን። ይህ ችግር ባስቸኳይ ካልተገታ በስተቀር ከዚህም ወደባሰ ሁኔታ አድጎ ከማንም ቁጥጥር ዉጪ ልሆን እንደሚችል ስጋታችን እየጨመረ መሆኑንም አሁንም በድጋሚ አስረግጠን ልንገልጽ እንወዳለን። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ዉድመትን ጨምሮ እስካሁን ለደረሱትና በቃጣይም ልደርሱ ለሚችሉት ጉዳቶች ሁሉ ተጠያቂዉ የኢትዮጵያ መንግሥት (የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር) መሆኑንም ግልጽ እናደርጋለን።
በመጨረሻም መፍትሄ ይሁን ዘንድ የሚከተሉት እርምጃዎች እንድወሰዱ ኦነግ በአጽንኦት ይጠይቃል፦
- በግድያና ጭፍጨፋ፣ በእስራት እና በማንኛዉም መልኩ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በመንግሥት እየተካሄደ ያለዉ ይህ እሮሮና ማሰቃየት ባስቸኳይ እንዲቆምና ይህንን እያካሄዱ ያሉት የመንግሥት ኃይሎች (ወታደሮች) ወደ ካምፕ እንዲመለሱ፤
- ያሉት ችግሮች በዉይይትና በሰላም መፍትሄ የሚያገኙበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያመቻች፤
- ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸዉ እና ቀዬአቸዉን ለቆ ለመሸሽ የተገደዱ ሰዎች ወደ ቀዬአቸዉ ተመልሶ ስላማይ ኑሮዋቸዉን እንዲኖሩ፣ ከደረሰባቸዉ ጉዳት የሚያገግሙበት እገዛም እንዲደረግላቸዉ። ያለምንም ጥፋትና ህጋዊ ዉሳኔ በተለያዩ ቦታዎች የታሠሩት እንዲፈቱ እና በኢፍትሃዊ መንገድና በተለያዩ ሴራዎች ከትምህርት ገበታቸዉ የተለዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸዉ የሚመለሱበት ሁኔታ ባስቸኳይ ተመቻችቶላቸዉ እንዲመለሱ እንዲደረግ፤
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለዉን ግፍና ሰቆቃ፣ በዚህም እየደረሰ ያለዉን ጉዳት በተመለከተ በነፃና ገለልተኛ አካል አስፈላጊዉ ምርመራ (international investigation) እንዲደረግበት።
ድል ለሰፊዉ ሕዝብ!
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)
ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም.አጣዬ፣ ማጀቴ እና ካራቆሬ በሚባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እንደተናገሩት፥ ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት ኃይሎች በሚገባ ዝግጅት ያደረጉ፣ በቁጥር ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ከ አካባቢዎች የሕግ አስከባሪ ፖሊሶች ቁጥር ጋር ሲነጻጸሩ እጅጉን የበዙ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– በወገኖቻችን ላይ በታጠቁ ኃይሎች እየደረሰ ያለውን ጥፋት የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት በአስቸኳይ ሊያስቆሙ ይገባል፤ ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ።
በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች በአጣዬ፣ በካራቆሪ፣ በማጀቴና አካባቢው በሚኖሩ ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና ሰቆቃ መንግስት በአፋጣኝ ሊያስቆም ይገባዋል በማለት ድምፃቸውን በሰላማዊ ሰልፍ በመግለፅ ላይ ናቸው።
አጣዬ፣ ማጀቴ እና ካራቆሬ በሚባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እንደተናገሩት፥ ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት ኃይሎች በሚገባ ዝግጅት ያደረጉ፣ በቁጥር ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ከ አካባቢዎች የሕግ አስከባሪ ፖሊሶች ቁጥር ጋር ሲነጻጸሩ እጅጉን የበዙ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በታጠቁ ኃይሎች የመቁስል አደጋ የደረሰባቸው መገኖቻችን ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ የተዘጉ መንገዶችን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስከፍትም ጠይቀዋል።
ሰልፉ እስካሁን በሰላማዊ አግባብ ተካሄዶ የተጠናቀቀ ሲሆን በአጣዬ ከተማ በህብረተሰቡ ላይ ጥቃት እያደረሰ የሚገኘው ኦነግ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢያለ ገልጸው ችግሩ ከዞኑ አቅም በላይ በመሆኑ መከላከያ ሠራዊት ገብቶ አካባቢውን እንዲያረጋጋ ድጋፍ የተጠየቀ ቢሆንም በወቅቱና በፍጥነት ባለመግባቱና ከገባም በኋላ እርምጃ እንድወስድ አልታዘዝኩም በማለቱ ችግሩ እየተባባሰ መሄዱን ተናግረዋል።
በአጣዬ ከተማ የኦነግ (የኦሮሞ ነጻ አዉጪ ግንባር) የታጠቀ ኃይል ባደረሰው ጥቃት በሰው ህይወት እና ንብረት እንድሁም በሀይማኖት ተቋማት ላይ ውድመት መድረሱን ኃላፊው ገልጸዋል።
ጥቃቱን እየፈጸመ ያለው ኃይል በተለየ መንገድ ስልጠና የወሰደ በመሆኑ ይህን አካል መደምስ ካልታቻለ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር አስቸጋሪ በመሆኑ የክልሉና የፌዴራል መንግስትን የተቀናጀ መፍትሄ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በሚያዋስኑ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሰላማዊ ግኑኙነት መኖሩን ጠቁመው፥ በከሚሴ ልዩ ዞን ዙሪያ የተፈጠረውን ክስተት ለመፍታት በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት አካል የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት (አብመድ) ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እንደዘገበው፥ ወደ አጣየ፣ካራቆሬ እና ማጀቴ መከላከያ ገብቷል፤ ሁኔታውም ከሌሎች ቀናት ይልቅ በአንጻራዊ መሉ እሁድ (መጋቢት 29 ቀን፥ 2011 ዓ.ም.) እየተረጋጋ መምጣቱን፤ ተጨማሪ ፀጥታ አስከባሪ ኃይልም እየገባ መሆኑን የአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አለበል አማረ አስረድተዋል።
የፀጥታ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም ከቅዳሜ እና ከእሁድ ረፋዱ (መጋቢት 28–29 ቀን፥ 2011 ዓ.ም.) የተሻለ መሆኑን የተናገሩት ኮሎኔል አለበል፥ ተደራጅቶ ሕዝብን ሰላም እያሳጣ ያለውን ቡድን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተቀናጀ ሥራ እንደሚከናወንም አረጋግጠዋል።
“ገና በጠዋቱ ሀገሪቱ መሪ እያላት ስርዓት አልበኝነት ነገሰ፣ ሕግ ረከሰ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ የሚል ጩኸት ብዙዎች ቢያሰሙም የሽግግር ባኅሪው ነው በሚል ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት አልተቻለም።”
———–ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር ― ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
አለማየሁ ገበየሁ
ፍርድ ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል /Lady Justice/ ተጠሪነቷና ምሳሌነቷ ለፍርድ ቤት ሥራ ብቻ አይመስለኝም። አይኗን ሸፍና ያላጋደለ ሚዛን የያዘችው አስተዳዳሪዎች በሞራል ሕግ ተመርተው ለዜጎች ሁሉ ሚዛናዊ አገልግሎትና ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ነው።
ዶ/ር አብይ አህመድ ደጋግመው ስለሚዛናዊነት ይሰብካሉ። ጋዜጠኞች የተመጣጠነ ዜና እንዲያቀርቡ፣ አክቲቪስቶች ከዋልታ-ረገጥ ሀሳብ ወደ መሃል እንዲመጡ፣ ፖለቲከኞች እኔ ብቻ ነኝ አዳኝህ ወይም የማውቅልህ ከሚለው አባዜ ተላቀው ለሌላውም ሥራ እውቅና እንዲሰጡ ወዘተ…
የሚዛን መንሻፈፍ ግለሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን እየቆየ እንደሚጎዳና ለማይጠገን ቀውስ እንደሚዳርግ የሚገነዘብ ሁሉ በዚህ ሀሳብ ይስማማል። ችግሩ ዶ/ር አብይ እንዳሉት ሁሉም ቀድሞ ጣቱን የሚቀስረው ሌሎች ላይ የመሆኑ አባዜ ነው። ይህ የጣት ቅሰራ ራሳቸው ዶ/ር አብይንም ይመለከታል። አንዱን ትልቅ ጥፋት ሸፋፍነህ ሌላው ላይ ጣትህን ስትቀስር ሚዛናዊነት ይንጋደዳል። አንዱን ትልቅ ጥፋት አላየሁም ብለህ አይንህን ከሸፈንክ ሌላኛው ጥፋት ላይ የአይንህን መጋረጃ ቀደህ ለመጣል ሞራል ታጣለህ።
ከብዙ ምሳሌዎች የተወሰኑትን ብቻ እናንሳ። ገና በጠዋቱ ሀገሪቱ መሪ እያላት ስርዓት አልበኝነት ነገሰ፣ ሕግ ረከሰ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ የሚል ጩኸት ብዙዎች ቢያሰሙም የሽግግር ባኅሪው ነው በሚል ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት አልተቻለም። ከዚህ ይልቅ በቅድሚያ ለውጡ ያመጣቸውን ትሩፋቶች ሳትደባብቁ አሞግሱ ማለት መጣ። ትክክል ነው ሚዛናዊ ለመሆን የበርካታ ባኅሪያት/ ጥሩ ተናጋሪ፣ ትዕግስተኛ፣ ይቅር ባይ፣ ትሁትና የሰላም አጋር/ መሆናቸውን መመስከር ይቻላል። በዚህ ጥሩ ባኅሪ በመታገዝም መንግስታቸው አስደሳች ፖለቲካዊ ድሎች አስመዝግቧል። ይህ ማለት ግን ለውጡ መሳ ለመሳ እየተጓዘ ያለው ከነውጥ ጋር ነው ነው ማለት ስህተት አይደለም። ሕገ-ወጥነት ሀገሪቷን የወረረው ይቅርባይነት ስለበዛ ነው የሚል የቄለ ግምገማ የለኝም – በዚህ ረገድ መንግስታቸው ስትራተጂካዊ ብቃት የለውም የሚለው ሀሳብ የበለጠ ቅርብ ነው። አሁን በቅርቡ እንኳን የሀገራችን ስርዓት አልበኝነት ተግባር ከ8 እስከ 10 ወራት ይቀጥላል በማለት እንደ ዓመታዊ ዕቅድ ነግረውናል። ሕገ-ወጥነትን አምርሮ ከመታገል ይልቅ ከሕገ-ወጥነት ጋር ተቻቻሎ ለመኖር ማሰብ ገራሚ አቋም ነው። በተሸፋፈነች ፍትሃዊ አይን ሚዛናዊነትን እንይ ከተባለ ከዚህም በላይ ነው።
መንግስት ባለበት ሀገር አሥራ ምናምን ባንኮች በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፉ የሽግግር ሂደት ባኅሪው ነው የምትል ከሆነ ሌላውን ሌባ ወይም ሙሰኛ ለመገሰጥም ሆነ ፍርድቤት ለማቆም ይከብዳል። ምክንያቱም ፍ/ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል ስለምትታዘብ። ለተቃውሞ ዱላና ገጀራ አደባባይ ይዞ የወጣ ማኅበረሰብ በቸልታ አልፈህ ያለዱላ ስብሰባ የከተመውን ወጣት በማያሳምን ምክንያት አስረህ የምታሸማቅቅ ከሆነ የሚዛናዊነት መሠረትህ ተናደ ማለት ነው። ይከበር እየተባለ የሚለፈፈው ሕግ ባለመከበሩ ዱላና ገጀራው አድጎ እነሆ ዛሬ የጦር መሣሪያ ይዞ አደባባይ መውጣት ተጀምሯል። በገዛ ፍቃድህ ሚዛናዊ ካልሆንክ ብሎም ቸልተኝነት እንደ ኩይሳ ካሳደግክ ሌሎች አደባባይ የተገተረውን የፍትህ ሚዛን በሌላ ጡንቻ ይሰብሩብሃል። ትርፉና ውጤቱም ይሄው ነው።
የቸገረው የከተማ ህዝብ ከሰውነት ተራ ወጥቶ በሠራው ኮንዶሚኒየም አትገባም ተብሎ ገጀራ ሲወደርበት “የባለገጀራዎች ሀሳብ ይለምልም” ብሎ መግለጫ ማውጣት እንዴት ሚዛናዊ ሊሆን ይችላል? በቡራዩና ለገጣፎ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው መፈናቀል፣ እንግልትና አግላይ ርምጃዋች ከልብ ሳታወግዝ ሌላ ታፔላ ለጥፎ አደባብሶ ማለፍ የሚዛናዊነትን ጥያቄ ያስነሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር የሚበትኑ ሀሳቦች ይወገዙ ይላሉ። በሀገሪቱ ያለው ሁለት መንግስት የአብይና የቄሮ ይባላል የሚል ትንታኔ የሚሰጠው ጃዋር የበርካታ በታኝ ሀሳቦች ባለቤት ቢሆንም ውግዘት አይመለከተውም። ኦሮሞ ከቋንቋው ውጭ ሌሎችን ማነጋገር የለበትም፤ ከሌሎች ጋር መጋባትም ማቆም አለበት የሚለው የ“ምሁሩ” በቀለ ገርባ አፓርታይዳዊ አስተያየት ለመመርመርም ሆነ ለመተቸት አልተፈለገም። በተቃራኒው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚንቀሳቀሰው እስክንድር ነጋ ላይ ግልጽ ጦርነት እናውጃለን ተብሏል። ሲጠቃለል ዶ/ር አብይ በበቀለ፣ በኦነግ፣ በጃዋር፣ በሕገወጥ ፖለቲከኞችም ሆነ በእስክንድር ሀሳብ ላይ ሚዛናዊ መሆን አልቻሉም።
ለዚህም ነው ማንኛውም ሚዛናዊ ለመሆን የሚጥር ሰው ለምን የሚል ቀጥተኛ ጥያቄና እንዴት የሚል የጀርባ ምፀት ለማንሳት የሚገደደው። ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ እንዲሰብር ብሂሉ ስለሚያስገድድ? ምንም ቢሆን ዘር ከልጓም ስለሚስብ?… ኢትዮጵያዊነትን መርህ አድርጌያለሁ የሚል መሪ ለጃዋርም ሆነ ለእስክንድር ሀሳቦች እኩል የድጋፍም ሆነ የተግሳጽ መስፈርት ማበጀት ካልቻለ መርሁ ሁሉ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ለራሱ ችግር ይፈጥሩበታል (backfire ያደርግበታል)። ዶ/ር አብይ ከጊዜ ወደጊዜ እየገረጣ የመጣባቸውን ሕዝባዊ እምነት ስር ሳይሰድ ለማከም ከፈለጉ ሚዛናዊነት ከራሳቸው መጀመር ያለባቸው ይመስለኛል። ጥሩ መሪ ደግሞ እንደዛ ነው። መንገዱን የሚያውቅ፣ በመንገዱ የሚሄድ እና መንገዱን የሚያሳይ ስለሚሆን። ባለጊዜ ነን በሚሉ ቡድኖች የሚጊሩ አስከፊና አቀያያሚ ጉዳዮችን አደብ ማስገዛት፣ አቅም ቢያጥር እንኳን በግልጽ ‘አካፋን አካፋ’ በማለት ማውገዝ መጀመር አለባቸው። ከዚህ ከጀመሩ ሌላኛውን ብልሹ ሀሳብና ተግባር ለማረቅ ምቹ መደላድል ይፈጥራል። ይህ አካሄድ ልበ ሙሉነትን በቀላሉ ማትረፍ የሚያስችል ሲሆን፥ ከሁሉም አቅጣጫ በቂ ድጋፍ ያስገኛል። አክባቢዎን በሚያውቋቸው ሰዎች መሙላት ብቻ ሳይሆን ገለልተኛና ሚዛናዊ ሀሳብ የሚሰጡትንም አማካሪዋች ቢያበዙ ጭልጥ ብሎ ከመሳሳትም ያድናል።
አለማየሁ ገበየሁ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በሙስና ወንጀል እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሠረት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት፦
- ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዴ ኢጄታ – በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የማርኬቲንግ ኃላፊ
- ብርጋዴር ጄኔራል ብርሃ በየነ – የሜቴክ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊ
- ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትላ መረሳ – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ ኃላፊ
- ብርጋዴር ጀኔራል ሃድጉ ገብረጊወርጊስ ገብረስላሴ – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ
- ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ተስፋሁን – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የወታደራዊ ምርቶች ኦፕሬሽን ኃላፊ
- ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርዔል ገብረእግዛብሄር – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ የነበሩ
- ኮሎኔል ዙፋን በርሄ ይህደግላ – የመከላከያ ጤና ኮሌጅ ሠራተኛ
- ሌተናል ኮሎኔል አስምረት ኪዳኔ አብርሃ – የጋፋት አርማመንት ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ተወካይ ኃላፊ የነበሩ
- ኮሎኔል አለሙ ሽመልስ ብርሃን – የሜቴክ ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የትራንስፖርት ኃላፊ
- ኮሎኔል ያሬድ ሃይሉ – የሜቴክ በኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት የፕሮጀክት ኃላፊ
- ኮሎኔል ተከስተ ሀይለማሪያም አድሃኑ – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ የነበሩ
- ኮሎኔል አዜብ ታደሰ – የሜቴክ በኮርፖሬት ማርኬቲንግ የሽያጭ ኃላፊ
- ሻለቃ ሰመረ ሀይሌ ሀጎስ – የሜቴክ በደጀን አቪዬሽን የኢንዱስትሪ ኦፕሬሽን ኃላፊ
- ሻምበል ይኩኖአምላክ ተስፋዬ – የሜቴክ በኮርፖሬት ማርኬቲንግና ሽያጭ የፕሮሞሽን ኃላፊ
- ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ ብርሃን – የሜቴክ የአዳማ እርሻ ስራዎች ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ
- ሌተናል ኮሎኔል ሰለሞን በርሄ – የሜቴክ በብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ኃላፊ
- ሻለቃ ይርጋ አብርሃ – የሜቴክ በህብረት ማሽን ቢዩልዲንግ ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ኃላፊ
- ኮሎኔል ግርማይ ታረቀኝ – የሜቴክ በኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የንብረት አስተዳደር ኃላፊ
- ሻምበል ገብረስላሴ ገብረጊዮርጊስ – የሜቴክ የኮርፖሬት ትራንስፎርሜሽን የአቅም ግንባታ ማዕከል ኃላፊ
- ሻምበል ሰለሞን አብርሃ – የሜቴክ በኮርፖሬት ትራንስፎርሜሽን የስልጠና ኃላፊ
- ሻለቃ ጌታቸው ገብረ ስላሴ – የሜቴክ የደን ምንጣሮ ክትትል ኃላፊ
- ሌተናል ኮሎኔል ይሰሃቅ ሀይለማሪያም አድሃኖም – የሜቴክ በኮርፖሬት ኮሜርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን የፕላኒንግና ኮንትሮል ኃላፊ
- ሻለቃ ክንደያ ግርማይ – የሜቴክ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ኃላፊ
- ሌተናል ኮሎኔል አዳነ አገርነው – የሜቴክ በኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የንብረት ክፍል ኃላፊ
- ሻለቃ ጌታቸው አጽብሃ – የሜቴክ ኢንፍራስትራክችርና ኮርፖሬሽን ማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኦፕሬሽን ኃላፊ
- ቸርነት ዳና – የዋይ ቲ ኦ ኩባንያ ባለቤትና ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስር የነበራቸው ደላላ
- አያልነሽ መኮንን አራጌ – ማስረጃ ልታጠፋ ስትል በቁጥጥር ስር የዋለች
በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት፦
- አቶ ጉሃ አጽበሃ ግደይ – የአዲስ አበባ የደህንነት ኃላፊ
- አቶ አማኑኤል ኪሮስ መድህን – የሃገር ውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር
- አቶ ደርበው ደመላሽ – የውስጥ ደህንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩና የኢኮኖሚ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ
- አቶ ተስፋዬ ገብረጻዲቅ – የውስጥ ደህንነት ጥናትና የወንጀል ምርመራ መምሪያ ኃላፊ
- አቶ ቢኒያም ማሙሸት – በውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ የኦፕሬሽን ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ (በዋናነት የግንቦት 7 ጉዳይ ክትትል)
- አቶ ተሾመ ሀይሌ – የአማራ ክልል የደህንነት ኃላፊ የነበሩና የጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር
- አቶ አዲሱ በዳሳ – በሃገር ውስጥ ደህንነት የኦሮሚያ ክልል ደህንነት ኃላፊ
- አቶ ዮሃንስ ወይም ገብረእግዚአብሄር ውበት – የውጭ መረጃ
- አቶ ነጋ ካሴ – በጸረ ሽብር መምሪያ የኦነግ ክትትል ኃላፊ
- አቶ ተመስገን በርሄ – በጸረ ሽብር መምሪያ የኦነግና ኦብነግ ክፍል ዋና ኃላፊ
- አቶ ሸዊት በላይ – በሃገር ውስጥ ደህንነት ኦፕሬሽን መምሪያ የግንቦት 7 ክትትል ምክትል መምሪያ ኃላፊ
- አቶ አሸናፊ ተስፋሁን – በሃገር ውስጥ ደህንነት የአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደህንነት አስተባባሪ
- አቶ ደርሶ አያና – በውጭ መረጃ የአማራ ክልል ክትትል
- አቶ ሰይፉ በላይ – በውስጥ ደህንነት የደቡብ ክልል ክትትል ኦፊሰር
- አቶ ኢዮብ ተወልደ – በውስጥ ደህንነት የደቡብ ክልል ደህንነት ኃላፊ
- አቶ አህመድ ገዳ – በውስጥ ደህንነት የኦሮሚያ ክልል ክትትል ምክትል ኃላፊ
- ምክትል ኮማንደር አለማየሁ ሀይሉ ባባታ – ቀድሞ የፌደራል ፖሊስ የሽብር ወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር የነበረና ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ያገለገለ
- ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሀሰን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
- ዋና ሳጅን እቴነሽ አራፋይኔ – የሽብር ወንጀል መርማሪ
- ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ – የሽብር ወንጀል መርማሪ
- ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
- ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
- ኦፊሰር ገብረማሪያም ወልዳይ
- ኦፊሰር አስገለ ወልደጊዮርጊስ
- ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ
- ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረሐዋርያት – የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት ኃላፊ
- ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተክላይ ኃይሉ – የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሠራተኛ
- ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አቡ ግርማ – የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ኃላፊ የነበረና በዝዋይ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ
- ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አዳነ ሐጎስ – የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሠራተኛ
- ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተስፋሚካኤል አስጋለ – በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ የደህንነት ባለሙያ
- ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብራት መኮንን – የዝዋይ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት ኃላፊ የነበረና የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ጥበቃና ደህንነት ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ
- ረዳት ኢንስፔክተር አለማየሁ ኃይሉ ወልዴ – በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ
- ረዳት ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ አየለ – በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ
- አዳነች ወይም ሃዊ ተሰማ ቶላ
- ጌታሁን አሰፋ ቶላ
- ሙሉ ፍሰሃ