-
AuthorSearch Results
-
October 24, 2020 at 1:00 am #16454
In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveበሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የገጽ ለገጽ ትምህርት መስጠት መጀመራቸውን ተከትሎ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ለተቋማት፣ ለሠራተኞች፣ ለመምህራንና ለተማሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት የሚከተለው ነው።
በኮቪድ-19 ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የገጽ ለገጽ ትምህርት (in-class teaching) ለማስቀጠል እንዲቻል በየተቋማቱ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
ለዚህም እንዲያግዝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የገጽ ለገጽ ትምህርትን ለማስቀጠል ሊከተሏቸው የሚገቡ ፕሮቶኮሎችን በማዘጋጀት ተቋማት በመመሪያው መሠረት እንዲዘጋጁ ሆኗል።
ይሄንንም ዝግጅት የክትትል ግብረኃይል በማዘጋጀትና በማሰማራት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በአካል ተገኝተው ግምገማ አካሂደዋል። በግምገማው ውጤት መሠረትም ተቋማቱ ያላቸው ዝግጅት ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል መሆኑ በመረጋገጡ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ትምህርትና ስልጠናቸው እንዲመለሱ ጥሪ ተደርጓል።
በመሆኑም ውድ ተማሪዎች ከወራት ቆይታ በኋላ ወደ ትምህርት ገበታችሁ እንደመመለሳችሁና ትምህርትና ስልጠናው የሚቀጥለው በኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል እንደመሆኑ፥ በተቋማቱ የሚኖራችሁ ቆይታ ኃላፊነት የተሞላበት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ላይ ያተኮረና በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላ እንዲሆን አሳስባለሁ።
ወደየዩኒቨርሲቲዎቻችሁ ስትመለሱም በአመራሩ የሚሰጣችሁን የጥንቃቄ መመሪያ ሁሉ ተግባራዊ ልታደርጉ ግድ ይላል። ወረርሽኙን ራሳችንን ብቻ በመከላከል ልንወጣው የምንችል ባለመሆኑ ለትምህርታችሁ ትኩረት ከመስጠት ጎን ለጎን ማስክ (የፊት መሸፈኛ ጭንብል) በመጠቀም፣ ንፅህናን በመጠበቅና በመመሪያው ላይ የተቀመጡ ሌሎች ሕግጋትንም ተግባራዊ በማድረግ የራሳችሁንና የጓደኞቻችሁን ሕይወት እንድትጠብቁም አሳስባለሁ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሩም ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲ ሲመለሱ መመሪያውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ግንዛቤ በመፍጠርና ከዚህ ቀደም ሲገለፅ እንደነበረው የጥንቃቄ መልዕክቶችን ሁሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማመቻቸት እንዲሁም መመሪያው እንዲተገበር በማድረግ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ።
መምህራን ከተማሪዎቹ ጋር ሰፊ ጊዜ የምታሳልፉ እንደመሆኑ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ተማሪዎች እንዳይዘናጉ የማድረግና የጥንቃቄ መመሪያውን እንዲያከብሩ የማስገንዘብ ኃላፊነት አለባችሁ።
የአስተዳደር ሠራተኞችም ተማሪዎች በግቢ ውስጥ የሚኖራቸው መስተጋብር ጥንቃቄ አልባ እንዳይሆን፤ የእናንተም አበርክቶ ከፍተኛ ነውና እናንተ ጠንቃቃ ሆናችሁ ተማሪዎችንም እንድታነቁ ይሁን።
በያዝነው ዓመት የሚኖረንን የትምህርትና ስልጠና ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀምና ትምህርትና ስልጠናው በታቀደው ጊዜ እንዲከናወን ለማስቻል ከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊና መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስና እንደ ጤናችን ሁሉ ሰላማችንንም ማስጠበቅ ኃላፊነታችንና ግዴታችንም ጭምር ነው።
ለዚህም የትምህርትና ስልጠና ማኅበረሰቡ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ጤናችሁንና ሰላማችሁን በመጠበቅ፣ ውድ ጊዜያችሁን ለእውቀት ሸመታ፣ ማኅበረሰባችሁን በሚጠቅሙ እና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር እንዲሆን ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ።
ዓመቱ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎችን የምንከውንበት ውጤታማና ሰላማዊ የመማር-ማስተማር ጊዜ የምናሳልፍበት እንዲሆን ከምንጊዜውም በላይ በጋራና በትጋት እንሠራለን!
ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ምSeptember 24, 2020 at 1:21 pm #16085In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
SemonegnaKeymasterትምህርት እንደሚጀመር ከሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተሰጡ ማብራሪያዎች
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ትምህርት እንደሚጀመር ሲያሳውቅ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተቋረጠውን ትምህርት የሚያስቀጥሉበት አቅጣጫን አስቀምጧል።
ከሁለቱም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መቼ እና እንዴት ትምህርት እንደሚጀመር የተሰጡት መረጃዎች የሚከተሉት ናቸው።
ትምህርት ሚኒስቴር
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በሦስት ሳምንታት ውስጥ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ተወስኗል።
የዓለም የጤና ድርጅትና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ መሠረት ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በመድኃኒት ማጽዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ማጽጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለሌላ አገልግሎት (ለምሳሌ፥ ለለይቶ ማቆያነት) ውለው የነበሩ ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን የማስተካከያ ሥራ ሊሠራላቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
እንደየ ትምህርት ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት በፈረቃ እና አንድ ቀን በመዝለል ተራ ሊያስተምሩም ይችላሉ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪ ማስተማር የሚችሉ መሆንም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
የተቀመጠው መስፈርት እንዳለ ሆኖ፡-
- በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም፤
- በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም፤
- በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሦስተኛ ዙር ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም
ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ መቅረቡ ይታዋሳል፡፡
በዚህ መሠረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሦስት ሳምንታት ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ትምህርት መጀመር ይችላሉ ተብሏል፡፡
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከልን የዩኒቨርሲቲዎችን እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን ከተቋረጠበት ለማስቀጠል በመሪዎች ደረጃ በተካሄደው ስብሰባ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዚህም መሠረት፥ በዓለም የጤና ድርጅት መስፈርትና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የየኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያ መነሻ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የማስተማርና የማሰልጠን ተግባራት ዝርዝር መመሪያ እንዲያዘጋጅና ተገቢውን ውይይት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በማድረግና ግንዛቤ በማሳደግ፣ የተቋማትን ዝግጁነት በማረጋገጥ፣ አግባብነት ያለውን የትምህርትና ሥልጠና መርሀግብር በማዘጋጀት ተማሪና ሰልጣኝ መቀበል የሚችሉ መሆኑን፤ ለዚህም ተቋማት ቀሪ የመስከረም ወር ቀናትንና የጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንትን የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን ለማከናወን እንዲጠቀሙ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ስለሆነም፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እስከ ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት መጨረሻ የተቋማትን የዝግጅት ምዕራፍ አፈፃፀም በአካል እየተገኘ ገምግሞ በቂ የኮቪድ-19 መከላከያ ዝግጅት ላደረጉት የመንግሥትና የግል ዪኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪና ሰልጣኝ እንዲቀበሉ የሚፈቅድ ይሆናል። በቂ ዝግጅት ያላደረጉ ተቋማት፣ ዝግጅታቸውን እስከሚያጠናቅቁ ድረስ ክትትል ይደረጋል። ያለ በቂ ዝግጅትና ያለሚኒስቴሩ የመስክ ምልከታና ፈቃድ ተማሪዎችን ወይም ሰልጣኞችን ተቀብሎ መገኘት አግባብነት አይኖረውም።
ስለሆነም፥ የ2012 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎችና የስልጠና አጠናቃቂዎች እንዲሁም በሌሎች የትምህርትና ሥልጠና እርከን የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ በሚዲያ በሚታወጀው የተማሪና ሰልጣኝ ቅበላ መርሀግብር መሠረት በየተቋሞቻቸው ጥሪ የሚደርግላቸው መሆኑን፤ እስከዚያው ድረስ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገልጸዋል። አያይዘውም ትምህርት/ስልጠና በሚጀመርበት ጊዜ የተጣበበ የትምህርትና ስልጠና ጊዜ የሚኖር በመሆኑ፥ ተማሪዎች/ሰልጣኞች ቀጣይ ጊዜያቸውን ለንባብና ለተያያዥ ዝግጅቶች እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመሆኑ፥ ሁሉን አቀፍ ጥንቃቄ እየተደረገ የትምህርትና ስልጠና ተግባራትን በጋራ ሆነን እንወጣዋለን በማለት ዶ/ር ሳሙኤል መግለጫቸውን ቋጭተዋል።
September 22, 2020 at 12:28 am #15979In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን መቀበል ከመጀመራቸው በፊት የተቋማቱ ዝግጁነት እንደሚረጋገጥ ተገለጸ
አዲስ አበባ (የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመክፈት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ መጀመሪያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከል የትምህርትና ስልጠና ተቋማት መልሶ የመክፈት ሂደትና ዝግጅት በሚል ርዕስ ምክረ-ሃሳብ አቅርበዋል።
በ2012 ዓ.ም የተቋረጠዉን ትምህርት በልዩ ዕቅድ ለማጠናቀቅ በሚሠሩ ሥራዎችና ትምህርት ሲጀመር ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲሁም ቀደም ተብለው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ምን መምሰል እንዳለባቸው በምክረ-ሃሳባቸው ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በጉባኤው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ‘መቼ እንክፈት?’ ለሚለው ትክክለኛ መልስ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በዓለም የጤና ድርጅት መለኪያ መስፈርት መሠረት ደረጃውን ጠብቆ በተዘጋጀ ዝርዝር በጥልቀት የዝግጅት መጠኑ ተፈትሾ ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል። በዚያ መሠረት የተቋማት ዝግጅት ይፈተሻል፤ በዳሰሳውም መሠረት መቀበል እንደሚችሉ ፍቃድ ይሰጣል ሲሉ አብራርተዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለፁት፥ ቅድሚያ ለተመራቂዎች [ቅድሚያ] በመስጠት፣ ተማሪዎችን በመከፋፈል በትንሽ ቁጥር ይጀመራል። ይህም ከሚታዩ ነገሮች እየተማርን የተማሪ ቁጥር ለመጨመር ዕድል ይሰጠናል ብለዋል። ዝርዝር አፈጻጸሙ በምን እንደሚመራ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ፕሮቶኮል ይዘጋጃልም ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንደመሆናቸው የክልል መንግሥታት ሥራ ይጠበቅባቸዋል። አማራጭ የለይቶ ማቆያ (quarantine) ቦታዎችን ማዘጋጀትም ግድ ስለሚላቸው እዚያ ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሠራል ብለዋል። ተማሪዎችን በማጓጓዝ ሂደት ችግር እንዳያጋጥም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንሠራበታለን ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የሚያስችል እቅድ ካሁኑ አዘጋጅተው ከአስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን ጋር በመወያየት የጋራ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል። የበፊቱን አሠራር ይዘን መቀጠል አንችልም፤ ዝግጅታችንን፣ ተጋላጭነታችንን አውቀን ተማሪ እንቀበላለን። አንድ ብሎክ ወይም አንድ ካምፓስ ኮቪድ-19 ቢያጋጥም ምን እናደርጋለን ከሚለው ጀምሮ በዝርዝር መሥራት እና እያንዳንዱ እቅድ ያለተማሪዎች እገዛ ተፈፃሚ ስለማይሆን ወደእነሱ ለማስረፅ መሥራት የግድ ይለናል ብለዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት፥ ጊዜው የተማሪዎች ሕብረት ኃላፊነት የሚፈተንበት ነው። የተማሪዎች ሕብረት አባላት የመፍትሄ ሃሳብ ሆናችሁ ለተፈፃሚነቱ ከዩኒቨርሲቲያችሁ ጋር በትብብር እንድትሠሩ ከእናንተ ይጠበቃል። ሰላማችሁን ማስጠበቅና ለደህንነታችሁ ዘብ መቆም ለትምህርታችሁ ቀጣይነት ዋስትና ነው ሲሉ አብራርተዋል። ዩኒቨርሲቲዎች መከፈታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ተመልሰው እንዳይዘጉም ጭምር የተማሪዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን አስመልክቶም የትኞቹ በዩኒቨርሲቲዎች ይቅረቡ የትኞቹ በተማሪዎች ይሟሉ የሚለውን ከተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለይቶ መወሰን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ውይይቱ ተቋማት የት ላይ እንደሆኑ ለይተን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ለመያዝ ታስቦ የተካሄደ ነው ብለዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎች በአሁኑ ጊዜ ቁርጠኝነት የሚፈልግ የለውጥ ሥራ እየሠራን እንደሆነ መገንዘብ እና በዚያው መጠን መፍጠን ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት የመመለስ ሂደት ባለድርሻ አካላትን በተገቢው መንገድ የማቀናጀት ኃላፊነት ተወስዶ መሠራት ያለበት ጉዳይ ነውም ብለዋል።
ተማሪዎችን ከመመለስና የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ከማዘጋጀት አንፃር የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥታት እያንዳንዱ የራሱን ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል። እንደከፍተኛ ትምህርት ዓለም-አቀፋዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ምርምር ላይ የተገኘውን እውቀት ተጠቅመን ለሀገር የሚውል አድርገን መጠቀምም ይገባናል ብለዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ሥራውን በማስፈፀም ሂደት ኃላፊዎች የግንኙነት (communication) ክፍተት እንዳይኖር በመነጋገር ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመው አመራር የሁሉ ነገር ቁልፍ እንደመሆኑ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ነገ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፤ ከዚያም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተቋማቱን ለመክፈት ያበቃሉ ተብለው የተቀመጡ ዝርዝሮችን በመያዝ በዩቨርሲቲዎች በመገኘት ብቁ መሆን አለመሆናቸው ታይቶ አስፈላጊውን መስፈርት ካሟሉ ብቻ እንዲከፍቱ ይደረጋል ብለዋል – ዶ/ር ሳሙኤል።
ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ወደኋላ የቀራችሁ ዩኒቨርሲቲዎች ካላችሁ ፈጥናችሁ ዝግጅታችሁን አጠናቅቁ ብለው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ጉዳዩንም እንደፕሮጀክት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለባቸው አስበዋል።
ከተሳታፊዎች የተለያዩ ስጋት ናቸው ተብለው የተነሱ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ለመፍታት እንደሚሠራ ተገልጿል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
July 26, 2020 at 1:36 am #15191In reply to: ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
SemonegnaKeymasterአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።
ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 21, 2020 at 1:38 am #15139In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ900 ተማሪዎች የትምህርት መከታተያ ሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ድጋፍ አደረገሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በመጪው የትምህርት ዘመን በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፀጋዬ ደዮ በተቋሙ በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ላይ እንዳሉት፥ በ2013 የትምህርት ዘመን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዘኛ ቋንቋና ሥነ-ልሳን በተጨማሪ በሶሻል አንትሮፖሎጂ (social anthropology) ዘርፍ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል።
እንዲሁም በጤና ሣይንስ ኮሌጅ የትምህርት ዘርፍ በሥነ ተዋልዶ፣ ሥነ ምግብ፣ ማኅበረሰብ ጤና፣ እናቶችና ሕፃናት ጤና የትምህርት ዘርፎች እንደሚከፈቱም አስታውቀዋል።
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በሚጀምራቸው ዘጠኝ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በእያንዳንዱ የትምህርት ዘርፍ እስከ 15 የሚደርሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርና ይህም ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ ለውጥ መሆኑን ዶ/ር ፀጋዬ ገልጸዋል።
የትምህርቱ ዓላማ ዩኒቨርሲቲው አቅምና ዕውቀትን ከማጐልበትና ከማሻገር በተጓዳኝ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ ለማመቻቸት ነው ብለዋል። በተለይ በትምህርት ጥራት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንዲወገዱ የትምህርት መርሃ ግብሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የውጭ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶ/ር የሺመቤት ቦጋለ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ለሚጀምረው የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በቂ የሰው ኃይልና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። መረሃ ግብሩ በትምህርት ተግባቦት ቴክኖሎጂ በቤተ ሙከራዎችና በኢንተርኔት በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተ መጽሕፍትን አደራጅተናል ብለዋል።
የሚጀምረው መረሃ ግብር የተቋሙ መምህራንና ተማሪዎች አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የኦሮምኛ ቋንቋ ዲፓርትመንት ኃላፊ ወ/ት ሁርሜ ደገፋ ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለአንድ ቀን በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው ከ100 በላይ መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች ተካፍለዋል።
ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም. ከተቋቋመ ጀምሮ በ33 የትምህርት ዘርፎች ከ4 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱም ተመልክቷል።
ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን በሬዲዮ በመከታተል ላይ ለሚገኙ 900 ተማሪዎች የሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ድጋፍ አደረገ። ድጋፉ ከ700ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ 500 ሬዲዮኖችና 400 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች ናቸው።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት እንደገለጹት፥ ድጋፉ በመቀበያ ችግር ምክንያት የሬድዮ ትምህርት ፕሮግራም መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ድጋፉ የተደረገላቸው መቀሌን ጨምሮ በአምስት የክልሉ ወረዳዎች የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች እንደሆኑ አመልክተው፥ በየቤታቸው ትምህርታቸውን በሬዲዮ ለመከታተል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይቋረጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል – ፕ/ር ክንደያ። ተማሪዎች በሬድዮ የሚተላለፍ ትምህርት በመከታተል ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ፕ/ር ክንደያ አስረድተዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፥ የተደረገው ድጋፍ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። ከዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አይነስውሩ አለም ተስፋዬ በሰጠው አስተያየት የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት መርሃ ግብሩ በተጨማሪ ወቅታዊ የዓለማችን ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችለን ነው ብሏል። በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ድጋፍ ማድረግ ሰብአዊና ዜግነታዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።
July 16, 2020 at 12:05 pm #15097In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveየከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ተሰጥቷቸው የዓመቱን ትምህርት ያጠናቅቃሉ ― የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።
የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አጋማሽ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) በመከሰቱና በፍጥነት በመዛመቱ ምክንያት የዓለም ሀገራት የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተቋርጦ መንግሥታት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ቅድሚያ ሰጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
እንደሚታወቀው ቫይረሱ ወደሀገራችን መግባቱ በምርመራ ከተረጋገጠበት ጀምሮ የሀገራችን መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ እየሠራ ይገኛል። በዚሁ መሠረት የቫይረሱን መስፋፋት ለመቀነስ ሲባል የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የገጽ-ለገጽ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ይታወሳል። ሆኖም ባሉበት ሆነው ከትምህርትና ንባብ እንዳይርቁ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።
የትምህርትና ስልጠና ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ከትምህርትና ስልጠና ተቋማት መከፈት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እያነሱ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተዘጋጅቷል።
አሁን ባለው ሁኔታ ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረው የኦንላይን ትምህርት የሚቀጥል ሆኖ፥ ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ ሌሎች መንገዶችንም በቀጣይ የሚታዩ ይሆናል። ለዚህም ሁሉም ዜጎች የቫይረሱን መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ መሥራት ያስፈልጋል። ስለዚህ ተማሪዎችና መምህራን ባሉበት ሆነው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ሌሎችንም እንዲያስተምሩ ይጠበቃል። ያም ሲሆን የስርጭት መጠኑ ሲቀንስ ቀጣይ የትምህርትና ስልጠና አካሄዶችን ይፋ የምናደርግ ይሆናል።
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የለይቶ ማቆያና ምርመራ ማዕከላት በመሆን በማገልገል ላይ ሲሆኑ፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ እንዲሁም መጠነ ሰፊ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት እያገዙም ይገኛሉ። ስለሆነም ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም የትምህርትና ስልጠና ተቋማቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ የሚቆዩ ይሆናል።
በዚሁ መሠረት ወደፊት በሀገራችን የሚኖረውን የቫይረሱን ስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ ከሚመለከተው አካል በሚሰጠን መረጃ መሠረት ነባር ተማሪዎችን ከተለመደው አካሄድ በተለየ ሁኔታ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ሥራ ተጀምሯል።
ነባር ተማሪዎችን በተመለከተ፡-
ሙሉ በሙሉ ኮርስ ያጠናቀቁ ተመራቂ ተማሪዎች (ለምሳሌ፡- የሕግ፣ የእንስሳት ሕክምና /veterinary medicine/፣ የሕክምና ተማሪዎች ወዘተ)፥ የመጀመሪያ ሴሚስቴር ያላጠናቀቁ ተማሪዎች፣ ሁለተኛ ሴሚስቴር ምንም ያልጀመሩ ተማሪዎች በባች/በደረጃ ተለይተዉ፣ የሴሚስቴሩን ኮርስ እስከ 25% እና 75% ያጠናቀቁ ተማሪዎች የቀሩ ምዕራፎች ተለይተዉ ማካካሻ ትምህርት በማመቻቸት እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ይሆናል።ተግባራዊ ለማድረግም በሁለት ዙር ተከፍለው ወደ ተቋማቱ እንዲገቡ በማድረግ የገጽ-ለገጽ ትምህርት ወስደዉ እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ሆኖ በአጭር ጊዜ ለማካካስ እንዲቻል የኦንላይን ትምህርቱም የሚቀጥል ትምህርት የሚሰጥበት አካዴሚክ ካሌንደር (academic calendar)፣ ቀናትና ሰዓታት ማሻሻያ የሚደረግባቸው ይሆናል። ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲዎች ሲመለሱም በቤተ-መፃሕፍት፣ በመማሪያ፣ መመገቢያ እና ማደሪያ ክፍሎች የሚኖራቸው ቁጥርም የተመጠነ ይሆናል።
በዚሁ መሠረት፡-- ተመራቂ ተማሪዎች እና ተመራቂ ያልሆኑ 4ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ያሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 3፣ 4 እና 5 ሰልጣኞች በመጀመሪያዉ መርሃ-ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
- የ1ኛ ዓመት፣ 2ኛ ዓመት እና ተመራቂ ያልሆኑ የ3ኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 1 እና 2 ሰልጣኞች በሁለተኛዉ መርሃ ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
- የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አዲስ ገቢ ተማሪዎች እና የነባር ተማሪዎች ቀጣይ ዓመት ትምህርቶች የማካካሻ ፕሮግራሞች ከተካሄዱ በኃላ በቀጣይ የሚገለፅ ይሆናል።
በዚሁ አጋጣሚ ተማሪዎች ወደትምህርት የሚመለሱበት ዕለት ተወስኖ እስከሚገለፅ ድረስ ከቫይረሱ ራሳቸውን በመከላከል ባሉበት ሆነው ንባባቸውን እንዲቀጥሉና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዲሁም በአከባቢያቸው ያሉ ወገኖችን እንዲያስተምሩ መልዕክት እናስተላልፋለን።
ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.
ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር)
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርJune 15, 2020 at 10:54 am #14801In reply to: 2ተኛው “አረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
AnonymousInactiveየተፈጥሮ ሳይንስ እና ግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ተገለጸ።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገራችን አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕለት የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ቀን በሚል ችግኝ የመትከል ማዕድ የማጋራትና ደም የመለገስ መርሃ-ግብሮች ተከናውነዋል።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአሰላ ከተማ የሚገኘው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት መርሃ-ግብሩን ያስጀመሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፥ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።
በቅድመ ተከላ፣ በተከላ ወቅትና ድኅረ ተከላ መደረግ ያለባቸውን እንክብካቤዎችን እና ጥንቃቄዎችን በማስተማርና እንዲሁም እንደየአከባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ተስማሚ የሆኑትን ችግኞች እንዲባዙ ጥናትና ምርምር ከማድረግና ማማከር በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ችግኞችን አባዝተው ለአከባቢው ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አያይዘውም በየአከባቢው ያለው የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማኅበረሰቡ እንዲሁም ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን እየተጠነቀቁ በዚሁ ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ማዕድ እንዲያጋሩ እና ደም በመለገስም ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት እንዲታደጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን ሦስቱን ግቢዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን የጎበኙ ሲሆን፥ በጉብኝቱ ከሰባ ዓመታት በፊት በስዊድን ድጋፍ የተቋቋመውና በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የግብርና ምርምር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ እና የጤና ሳይንስ ኮሌጁም የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ለመከላከል የሚያመስገን ሥራ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።
ፕሮፌሰር አፈወርቅ በማዕድ ማጋራት ዩኒቨርሲቲው የሚደግፈውን አፎምያ የአረጋውያን መርጃ ማኅበር የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው የዱቄትና ዘይት ድጋፍ አድርጓል።
ከአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ከድምጻውያን ጋር በመሆን በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ ውስጥ (የካ ተራራ) ችግኞችን ተክለዋል።
ከንቲባው በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዓለም-አቀፍ ስጋት የሆንውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ከመከላከል በተጓዳኝ ነዋሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ችግኞች እንዲተክሉ አሳስበዋል። ችግኝ ከመትከል ባለፈም ችግኞች በየጊዜው መንከባከብም ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ሕብረት ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ሕብረተሰቡ ችግኞች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመረዳት በራሱ ተነሳሽነት መትከልና መንከባከብ ይገባል ብለዋል። ሕብረቱም የተከላቸውን ችግኞች ለመንከባከብም ቃል ገብተዋል።
በሥፍራው ተገኝቶ አረንጓዴ አሻራ በማኖሩ ደስተኝነቱን የገለጸውና ተግባሩ መቀጠል አለበት ያለው ድምፃዊ ነዋይ ደበበ ነው።
”ንጹህ አየር ለሰው ልጅ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ችግኝ መትከል ግዴታ ነው። በዚህም ቦታ ተገኝቼ አረንጓዴ አሻራ በማኖሬ ደስተኛ ነኝ” ሲል የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ተናግሯል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰባት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከሚተከሉት መካከል ለጥምር ግብርና የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች ይገኙበታል።
ምንጮች፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 8, 2020 at 12:52 am #14425In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveየጤና ሳይንስ ምሩቃን በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ከሀገር ውጭ ሲወጡ ደግሞ በተማሩበት የሙያ መስክ ጥራት ያለውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ የሚያበቃ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና የስልጠና ፕሮግራም ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የጤና ሳይንስ ትምህርቶችን ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር Jhpiego ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር የጤና የሰው ኃይል ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም (Health Workforce Improvement Program /HWIP/) ላይ የቪዲዮ ውይይት (webinar) አድርጓል።
በውይይቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጤና ሳይንስ የሚመረቁ ምሁራን በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ከሀገር ውጭ ሲወጡ ደግሞ በተማሩበት የሙያ መስክ ጥራት ያለውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ የሚያበቃ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና የስልጠና ፕሮግራም ደረጃ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው እንዲህ ዓይነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እገዛም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በጤና ዘርፍ በየዓመቱ መሰልጠን ያለባቸውን ቁጥር አጥንቶ መመጠን፣ ኢ-ለርኒንግን (e-learning) ማጠናከር፣ የትምህርት መርሃግብሮች ዕውቅና አሰጣጥ (programs accreditation) ላይ መሥራት፣ የመርሃግብር ደረጃ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎች ይጠበቃል ብለዋል።
የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው ሆስፒታል እና የጤና ማዕከላት ሲኖራቸው የሌላቸው ደግሞ ተማሪዎቻቸውን በአከባቢያቸው ከሚገኙ የጤና ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ያሰለጥናሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ስለሆነም በጤና ዘርፍ ያሉ አመራሮችን፣ መምህራንን እና የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባትና ግብዓት ማሟላት ለጥራት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ የ5 ዓመት መሆኑን እና በጤና ዘርፍ የሚወጡ ተማሪዎች ጥራት እንዲኖራቸው መሥራትና፣ ለጤና ዘርፍ ትምህርት ጥራት የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ግብዓቶችንና ቴክኒካዊ ምክረሃሳቦችን በማቅረብ ተግባራዊ እንዲረግ መሥራት ዋና ዓላማቸው መሆኑን የገለፁት የJhpiego ዳይሬክተር ዶ/ር ተግባር ይግዛው የጤና ሳይንስ ትምህርትን ጥራትን ለመደገፍ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የ39.5 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክቱን ተግባዊ ለማድረግም በጤና ትምህርት ዘርፍ በሚደረጉ ድጋፎች ላይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በተለይ ለጾታ እኩልነት ቦታ እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።
ዶ/ር ተግባር ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ውስጥ የሚከሰቱትን ወሳኝ የሰው ኃይል ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ መንገዶችን ለማመቻቸት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ስምምነት የሚሠራ መሆኑን ገልጸው፥ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራትም የኢትዮጵያን የጤና ባለሙያዎች ጥራት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ብቃት ለማሻሻል እና የጤና የሰው ኃይል አስተዳዳሪዎች ችሎታን ለመገንባት በተቋም እና ግለሰቦች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ብለዋል።
በውይይቱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ቢሠራበት የሚሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል። በዚህም በሚኒስቴሩ በኩል ከድርጅቱ ጋር በጋራ የሚሠራባቸው መስኮች ተለይተው እና የትግበራ ዕቅድ አውጥተው ወደሥራ እንደሚገቡ ተጠቁሟል።
በውይይቱ ዩኒቨርሲቲዎችን ዓለምአቀፋዊ ማድረግ ላይ የሚሠራውን ሥራ ለማገዝ ዕውቅና መስጠት (accreditation) መጀመር እንዳለበትና በተለይ የሕክምና ትምህርት ላይ ቀድሞ መጀመር ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑም ተመላክቷል።
April 20, 2020 at 11:56 pm #14230In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveየከፍተኛ ትምህርትን በቴክኖሎጂ በመታገዘ ማስቀጠልን አስመልክቶ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ በቴክኖሎጂ በመታገዘ የከፍተኛ ትምህርትን ለማስቀጠል መወሰኑን መግለፁ ይታወቃል። ይሄንንም ተከትሎ በትግበራው ዙርያ ከስጋትና ከመረጃ ጉድለት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። አፈፃፀሙ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህን ሚኒስቴሩ ይህን ፅሑፍ (ማብራሪያ) አዘጋጅቷል።
የተነሱት ጥያቄዎች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን የተመለከቱ፣ የኢንተርኔት ዋጋ ውድ መሆን ፣ የኔትወርክ ችግር መኖርን፣ የመብራት አለመኖርና መቆራረጥን፣ ሁሉም ተማሪዎች ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ አቅም ሳይኖራቸው ትግበራው የሚያስከትለውን ኢ-ፍትሃዊነት እና ቢተገበር ውጤታማ ላይሆን ይችላል ከሚል ስጋት የሚነሱ ናቸው።
ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት የሰው ልጆችን ህልውና በሚፈታተኑ አስቸጋሪ ወረርሽኞች ውስጥ አልፋለች። ከነዚህም አንዱ በዘመናችን ያጋጠመን ኮቪድ-19 ነው። ቫይረሱ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም መዛመት ከመቻሉ ጋር ተያይዞ የበርካታ አገራትን ዜጎች ከቤት ውጭ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ገድቧል። በሁሉም ዘርፎች ዓለምን ለቀውስ ዳርጓል።
ታዲያ ይህ ቫይረስ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ሲል መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል። ከነዚህም አንዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ወደየቤተሰቦቻቸው መመለስ ነው።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቫይረሱ መቼ በቁጥጥር ስር ውሎ እነዚህ ተማሪዎች ወደቀድሞ እንቅስቃሴያቸው እንደሚመለሱ ስለማይታወቅ ትምህርትን ከማስቀጠል አንፃር የተለያዩ አማራጮችን መመልከት አስፈልጓል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ስንመለከት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ/ UNESCO) በቀውስና አደጋ ጊዜ ስለትምህርት ማስቀጠል “Education Response in Crises and Emergencies” ሲያስረዳ፥ በችግር ጊዜ ትምህርት ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ አገራት የተለያዩ የትምህርት ማስቀጠያ መንገዶችን ተከትለው እንዲሰሩ ያስቀምጣል። በተለይም “Education 2030 Incheon Declaration and Framework for Action“ ላይ በተለያዩ የአደጋ ጊዜዎች በመደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ መንገዶችን በመጠቀም ተለዋጭ የመማር-ማስተማር ዘዴዎችን በመተግበር አካታችና ፍትሃዊ ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ስለሆነም ይህ በትምህርት ላይ የነበሩና በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎቻችንን በተቻለ መጠን በሚቻለው ሁሉም አማራጭ ንባቦችን እንዲያገኙ በማድረግ እያነበቡ እንዲቆዩና ከትምህርታቸውም እንዳይቆራረጡ ማድረግን ግብ አድርጎ እየተሠራ ያለ ተግባር ነው። ስለዚህ እንደሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ባለን አቅም፣ ሀብትና ግብዓት የከፍተኛ ትምህርቱን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማስቀጠሉ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር በመሆኑ ውሳኔው ተላልፏል።
በዚህም የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን በተመለከተ፡
የሁለተኛ ሴሚስተር የሁሉም ትምህርት ዓይነቶች ሞጁሎች (modules)፣ አጋዥ ንባቦች እና ሌሎችም በየትምህርት ዓይነቱ ተሰንደው የሚገኙባቸው ድረ-ገፆችን (ዌብሳይቶችን) የማሟላት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በዚህም፦
-
- የተዘጋጁ የኮርስ ማቴሪያሎችና አጋዥ የትምህርት መጽሃፍቶች ተደራሽ የሚሆኑበት የዲጂታል ላይብረሪ ዝግጁ ተደርጓል። (http://ndl.ethernet.edu.et/) አስፈላጊ በሆኑ የትምህርት ይዘቶች እየበለፀገ ይገኛል።
- እንዲሁም በርካታ ይዘቶችን የያዘዉ የ TechIn ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ዝግጁ ሆኗል (http://library.techin.et/)
- የኦንላይን ትምህርት መስጠት የሚያስችል የLearning Management System/MOOCS ዝግጁ ተደርጓል። (https://courses.ethernet.edu.et/)
እንዲሁም ተማሪዎች ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በስልክም ይሁን በላፕቶፕ እንዲሁም በታብሌት ወደእነዚህ ዌብሳይቶች ገብተው በሚያነቡበት ጊዜ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ከኢትዮ ቴሎኮም ጋር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
እንደተገለፀው ወረርሽኙ መቼ እንደሚገታ አይታወቅም። ነገር ግን ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑ ተረጋግጦ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እስከሚመለሱ ድረስ በተለያዩ ድረ-ገፆች (ዌብሳይቶች) ለንባብ የቀረቡላቸውን ግብዓቶች (ማቴሪያሎች) እያነበቡ ይቆዩና ሲመለሱ እንደየተቋማቱ ተጨባጭ ሁኔታ ቀሪ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት ፕሮግራም ይቀይሳሉ።
የምረቃ እና ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎችን በሚመለከት
አብዛኞቹ የማስተር (MSc, MA, MPH…) እና የፒኤችዲ (PhD) ተማሪዎች በምርምር ላይ እንደመሆናቸው ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ትምህርቱን በኦንላይን ለማስቀጠል እንዲያመቻቹ ሆኗል። በዚህም ለመማር-ማስተማሩ የሚያግዙ ግብዓቶች (ማቴሪያሎች) በኦንላይን፣ በኢ-ሜይል እና ሌሎች ዘዴዎች ለተማሪዎች እንዲቀርቡ እየተሠራ ይገኛል። ምርምሮቻቸውን ያላጠናቀቁና ዳታ ለማሰባሰብ የግድ መውጣት ከሚያስፈልጋቸው ውጭ ያሉት በሙሉ የመመራቂያ ጽሁፋቸዉን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እንዲያቀርቡ ይመቻቻል።
የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸዉ ጋር የሚገናኙበት የኦንላይን የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማድረግ፣ ማንኛዉንም ሰነዶችን ማጋራት ሌሎችንም የቨርቹዋል (virtual) ግንኙነቶች ማድረግ የሚያስችል የ Office 365 Teams ቴክኖሊጂ ዝግጁ ተደርጓል። በተጨማሪም በሃገር ዉስጥ የተሠሩ የ Thesis and Dissertations ሰነዶች ለማጣቀሻ እንዲሆኑ በ<https://nadre.ethernet.edu.et/> ዝግጁ ሆነዋል።
በተጨማሪም አብዛኞቹ የ Educational Private አገልግሎቶች ከኢተርኔት ዳታ ማዕከል የሚሰጡ ስለሆነ፣ ለዳታ ማዕከሉ ለጊዜዉ ያልተቆጠበ የኢንተርኔት ባንድዊድዝ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲያቀርብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመነጋገር ላይ ይገኛል።
ይህ አቅጣጫ እንዳለ ሆኖ ዩኒቨርስቲዎች እንደየትምህርት ክፍላቸውና የትምህርት ዓይነቶቹ እንደሚያስፈልጓቸው ተጨማሪ ሁኔታዎች እያዩ ሌሎች የመገናኛ ፕላትፎርሞችንም የሚያቻቹ ይሆናል።በመጨረሻም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሁን በዓለማችን ያጋጠመውን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሁሉም ዘርፍ ያለውን የሀገራችንን እና የዜጎቿን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እና በተቻለ መጠን ሁሉ ትምህርትን ተደረሽ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትክክለኛ የTelegram Channel <https://t.me/MinistryoSHE>ነው። ይቀላቀሉ! በሌላ አማራጭ ትክክለኛ መረጃ ያግኙ።
January 18, 2020 at 11:44 pm #13337In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactive- በሥራ ላይ ያለው ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ይቀየራል።
- በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት አስፈላጊ ነው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጋጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ላይ እንደገለፁት ከ2012-2014 የትምህርት ዘመን በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የአስር ዓመታት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቷል።
በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት መቀየር ያስፈለገው በፍኖተ ካርታው ምክረ-ሃሳቦች መሠረት ችግሮች ስላሉበት ነው። በመሆኑም በመጭዎቹ ዓመታት በአዲስ የሚተካው ሥርዓተ-ትምህርት የተማሪዎችን ሥነ-ምግባር ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቃዋል።
በአውደ-ጥናቱም ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች፣ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ሃላፊዎች፣ ከሁለተኛና ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን፣ የመምህራን ኮሌጆችና ከአምስቱ የመምህራን ማሰልጠኛ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው ሥርዓተ-ትምህርቱ እየተዘጋጀ ያለው ከፍኖተ ካርታው በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ጥቆማዎች (recommendations an suggestions) እንዲሁም የካንብሪጅ ኢንተርናሽናል አሰስመንትን (Cambridge Assessment International Education) ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻዎች በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ተጨማሪ አስተያየት መሠረት ነው።
በምክክር መድረኩም የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ፣ የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት መርህ አቅጣጫ (position papers) እና ሌሎችም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ሰለሞን መግለፃቸውን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።
ከሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ደግሞ፥ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት፣ ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሒዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም “በዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በተሟላ ሁኔታ ተተገብረው ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባር የተላበሱ ምሩቃን አፍርተን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እያለፍን የሀገራችንን የማስፈጸም አቅም በመገንባት በብልጽግና ከፍታ ላይ ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ላይ የተቀመጡ ምክረ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ በነባሩ የትምህርት ሥርዓት ላይ ያለውን ጉድለት ለመሙላት እና ለማሻሻል አዳዲስ የለውጥ ኃሳቦችን በማካተት ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ትግበራ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፥ ከነዚህም መካከል የከፍተኛ ትምህርትን ሥርዓተ ትምህርት የማሻሻል፣ የትምህርት አሠጣጥ ሥነ-ዘዴዎቹንና የትምህርቶቹንም ይዘት የመከለስና የኮርስ ካታሎግ (course catalog) የማዘጋጀት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንን በተልዕኮና በልህቀት ለይቶ የማደራጀት እንዲሁም አዳዲስ የሕግና የአሠራር ማዕቀፎችን የማውጣትና ነባሮቹንም የመከለስ ሥራዎች ይገኙበታል ብለዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ሂሩት ገለፃ፥ የምክክር መድረኩ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ሚኒስቴሩ በሚያከናውናቸው የለውጥ ሥራዎች ላይ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ስለሚያምንና በተለይም በቂ ግንዛቤ ያለውና የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ለለውጥ ሥራዎቻችን ስኬት ቁልፍ ስለሆነ ነው ሲሉ አስቀምጠዋል።
ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መድረክ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጉዳዮች፣ በፍኖተ ካርታ ምክረ-ሃሳብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሴክተር የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እንዲሁም በሰላማዊ መማር ማስተማር ዙሪያ የተሠሩ አንኳር ሥራዎች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።
በመጨረሻም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የልህቀት ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴን የሚጎበኙ ይሆናል።
ምንጮች፦ የትምህርት ሚኒስቴር/ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
January 17, 2020 at 2:21 am #13311In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveበዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተፈጠረው የሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ከ640 በላይ ተማሪዎች፣ 40 መምህራን እና ከ240 በላይ የአስተዳደር ራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ (ኢብኮ) – ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በነበሩ ከ640 በላይ ተማሪዎች፣ 40 መምህራን እና ከ240 በላይ የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንደተወሰደ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
በዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረ የሰላም እጦት 35 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ጥለው መውጣታቸውን የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፥ እነዚህን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል። የተማሪዎችን አደረጃጀት በኅብረ ብሔር ለማሰባጠር መታሰቡንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም ባጡባቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር ግምገማ እና ምክክር እያደረገ ይገኛል።
በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማጣራት የተዋቀረው ኮሚቴ ባደረገው የመስክ ምልከታ ያዘጋጀው ሪፖርት በመድረኩ ላይ ቀርቧል። በቀረበው ሪፖርትም የዩኒቨርሲቲዎች የሰላም መታወክ የፖለቲካ አመራሮች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንዳለ ተገልጿል።
በተለያዩ ክልሎች ባሉ የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮች የሚወጡ መግለጫዎች እና ከግቢ ውጭ ተማሪዎችን ሰብስቦ ተልእኮ የመስጠት ሥራዎች ለመማር ማስተማሩ መታወክ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቁሟል። ተልእኮ የተቀበሉ ተማሪዎች መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቦና፣ አካላዊ፣ የሕይወት እና ንብረት ጉዳት በማድረስ ግጭት እንደሚያነሳሱም ተጠቁሟል። በሚዲያዎች፣ በሶሻል ሚዲያዎች እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተጋነኑ እና የተዛቡ መረጃዎች መሰራጨት፣ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ችግሮችን ውጫዊ ማድረግ ወይም ቸልተኝነትም ሌላው ለዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እጦት የተነሣ ተግዳሮት ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ያለው በቤተ ዘመድ የተሳሳበ የሠራተኛ አደረጃጀት እንዲሁ እንደ አንድ ችግር ተጠቅሷል።
ችግር የፈጠሩ እና ምንም ዓይነት የሕግ እርምጃ ሳይወሰድባቸው በነፃ የሚለቀቁ እና እንዲማሩ የሚፈቀድላቸው ተማሪዎችም በዩኒቨርሲቲዎች ለሚታየው የሰላም እጦት ሌላው ምክንያት መሆናቸው ተጠቁሟል።
በዩኒቨርሲቲ አመራሩ በኩል ውጫዊ ማስፈራሪያዎችን በመፍራት ውሳኔ ሰጭነት ላይ የሚታየውን ማፈግፈግ እንዲሻሻል እና ጠንካራ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
October 18, 2019 at 11:37 am #12296In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
AnonymousInactiveየሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲ ስለሚገቡ አዲስ ተማሪዎች እና የሚደረግላቸውን አቀባበል በተመለከተ የሰጠው መግለጫ
—–አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በ2011 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ 142,840 ተማሪዎች በመደበኛ መርሀ ግብር (regular program) በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል። ምደባቸውም የተማሪዎቹን የትምህርት መስክና የተቋም ምርጫ፣ የተማሪዎቹን ውጤት እና የዩኒቨርሲቲዎችን የቅበላ አቅም ባገናዘበ መልኩ የተካሄደ ነው።
በዚሁም መሠረት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ተቀብለዋል። ቀሪዎቹም እየተቀበሉ ይገኛሉ። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አብዛኞቹ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በተመደቡበት በመገኘት ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል። ነባር ተማሪዎችም ትምህርታቸውን መከታተል ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የ2012 ዓ.ም. የመማር-ማስተማር ሰላማዊ እንዲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ከነዚህም መካከል አንዱ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚረዳ ወላጆችን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የኃላፊነት መውሰጃ የስምምነት ውል እንዲገቡ መደረጉ አንዱ ነው። በዚህም ላይ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል አዲስ ተማሪዎች ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ከመግባታው ቀድም ብሎ እንዲሁም ከገቡ በኃላ፣ ነባር ተማሪዎችም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠናዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደርጓል። በተጨማሪም በያዝነው ዓመትም አዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ተደርጓል።
የመማር-ማስተማር ሥራው የግብዓትም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙትም ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን አቋም እና ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረጉትን ቅድመ-ዝግጅት ለመገምገም ያገዙ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተሳተፉባቸው የመስክ ጉብኝቶች ተካሂደዋል። በቪዲዮ ኮንፈረነስም ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችና የደረሱበትን የዝግጅት ደረጃ የመገምገም እና የማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በውጤቱም ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሰላማዊ ለማድረግ ሊሠሩ የሚገባቸው አስፈላጊ ቅድመ-ዝግጅቶችን ማካሄዳቸው ተረጋግጧል።
ከተማሪዎች ቅበላ ጋር ተያይዞም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች) ሲታይ እንደነበረው ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበት አከባቢ ማኅበረሰብ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የአከባቢው የጸጥታ ኃላፊዎች ጋር በመተባበር ፍፁም ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ቤተሰባዊ አቀባበሎችን ሲያደርጉ ታይቷል፤ እያደረጉም ይገኛሉ። ይህ በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ከተካሄዱ ተከታታይ ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች በኋላ የተገኘ ውጤት ነው።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምደባውን ተግባራዊ ሲያደርግ የተማሪዎችን ምርጫ፣ ውጤት እና የየተቋማቱን የቅበላ አቅም ከማገናዘብ ጎን ለጎን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚያስችሉ አካሄዶችንም ተከትሏል። ይሄው ታውቆ የክልል መንግስታት፣ የዩኒቨርሲቲ ቦርዶችና አመራሮች እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት በጠቅላላ የተቀመጠውን የቅበላና ድልደላ መርህ ተገንዝበው ለአፈፃፀሙ ሁሉም የድርሻቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ እንተማመናለን።ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 13, 2019 at 11:41 pm #11387In reply to: ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
AnonymousInactiveዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ 3,144 ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ
—–ከ23,500 በላይ ተማሪዎችን በዋናው ግቢ፣ በዱራሜ፣ በንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ሆስፒታል እያስተማረ የሚገኘው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ 3,144 ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል።
“አሁን የታየውን የአገራችን የለውጥ ተስፋ ማስቀጠል የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። በመሆኑም በሁሉም ዘርፍ በእውቀትና ክህሎት የበቃ የሰው ሃይል ያስፈልጋታል” የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ በተማሪዎቹ የምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ።
ለዚህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መጀመሪያ ራሳቸውን እየለወጡ በአዳዲስ ሳይንሳዊ ውጤቶች መደራጀት፣ ጊዜውን በሚመጥን መልኩ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ተላብሰው መጓዝ አለባቸው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
*** የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ፕሬዝዳንት ከዩኒቨርሲቲው ኮሌጆችና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር ያዘጋጁት የምክክር መድረክ
የተማረ ሰው ለብዙም ሆነ ለትናንሽ ችግሮች ብዙ መፍትሄ ይፈልጋል፤ አገራችን አሁን ካጋጠሟት ችግሮች እንድትላቀቅ እናንተ የዛሬ ተመራቂዎች በሰበሰባችሁት እውቀትና ክህሎት የመፍትሄ አካል እንድትሆኑ አደራ አለባችሁ ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አየለ ሄገና ናቸው።
በሠላም ተምሳሌትነት የሚታወቀው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ 11,638 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ፥ ከእነዚህ ተመራቂዎች 60%ቱ በግልና በመንግስት ሥራዎች መሰማራታቸውን ዩኒቨርሲቲው በጥናት /tracer study/ እንዳረጋገጠ ጠቁሟል።
የመቀጠር እና የስራ ፈጣሪነት አቅም ለማሳደግ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሥራ ፈጠራ ማዕከል ተቋቁሞ እየተሠራ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ6 ኮሌጆች፣ በ2 ት/ቤቶች በ54 ቅድመ-ምረቃ እና በ7 ድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ትምህርት እየሰጠ ይገኛል።
ከአገር በቀል እውቀቶች ልማት አንጻር ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ሀድይሳ እና ከምባትኛ ቋንቋዎችን በዋና ግቢ እና በዱራሜ ካምፓሶች ማስተማር መጀመሩ ተገልጿል።ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
March 13, 2019 at 11:14 pm #10220SemonegnaKeymasterለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጀ። የአድዋ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት ሰጠ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩት ጥናትና ምርምሮች ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በአገሪቷ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡት የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሚጠበቀው በታች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም እንደ ዋነኛ ምክንያት አስቀምጠውታል። እንዲያውም ለዘርፉ የሚመደበው አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን በመጠቆም።
በተጓዳኝም የምርምር መሠረተ-ልማቶች አለመኖር፣ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ መሆንና መምህራን ለምርምር ትኩረት አለመስጠታቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩት ጥናታ ምርምሮች ቁጥር አነስተኛ መሆነ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ባሏቸው አቅም በአስገዳጅ መልኩ የጥናትና ምርምር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በትምህርት ተቋማቱ ዝቅተኛ ቢሆኑም በሥመ-ጥር ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ምርምሮቻቸውን የሚያወጡ ጉምቱ ምሁራን መኖራቸውንም ዶ/ር ሳሙኤል አልሸሸጉም።
ለጥናትና ምርምር የሚበጀተውን በጀት በተመለከተም ከአገሪቷ እድገትና ከመምህራኑ አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ እያደገ የሚመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ጆርናሎች ጥራታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጥናት እየተደረገበት መሆኑንም አስረድተዋል። መመሪያውንም በቅርቡ ወደ ሕግ በመቀየር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ጆርናሎች የሚመሩበት ወጥ ሥርዓት በመዘርጋት የእውቅና ደረጃም እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ መውሰድ (ረቂቅ አዋጁን ማውጣትም ሆነ ለጆርናሎች መመሪያ መዘጋጀት) የሚካሄዱትን ምርምሮች ጥራታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፥ በቀጣይም ጥናትና ምርምር ላይ የግሉ ዘርፍ የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ቁጥር 33 ሺህ ደርሷል፤ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺህ 500 የሚሆኑት ናቸው ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው – የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው።
ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ፥ ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት መስጠቱን በትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የአድዋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የዩኒቨርስቲውን ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘብራአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ እንዲውል መሬቱ ተሰጥቷል። በዚህም 131 የአካባቢው አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ላይ ተነስተዋል። ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮችም ካሳ ክፍያ ለመፈፀም 15 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ በበኩላቸው ግንባታውን ለማስጀመር ከፌዴራልና ከትግራይ ክልል መንግሥታት 450 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። ከዚህም የትግራይ ክልል መንግሥት 250 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል መግባቱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ አስተዳደርም በቅርቡ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 16, 2019 at 4:59 pm #9738AnonymousInactiveበአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ የዲያሥፖራ ማህበር አባላት ስልጠና ሰጡ።
—–በውጪ አገራት ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሙሁራንና ተመራማሪዎች /TASFA/ በሚል ተደራጅተው ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።
ከ 08-10/06/2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ በአዲስ አበባ ከተማ ኦሮሞ ባህል አደራሽ የኢፌዲሪ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የህግ ባለሙያዎች እና ከኦሮሚያ ትምህርት፣ ሲቢል ሰርቪስ እና ከተለያዩ ቢሮዎች ለሚሰሩ አመራሮችና ባለሙያዎች የፕሮጀክት ማኔጅሜት ስልጠና በመስጠት ላይ ናቸው።
ፕሮግራሙን የከፈቱት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የሳይንስና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር ኤባ ሚጃና እያንዳንዳችን ያስተማረችንን ድሀ አገራችንን አቅማችን በፈቀደው ብድሯን ለመመለስ ተረባርበን መስራት አለብን ብለዋል።
የማህበሩ አመራሮችና አባላትም በበኩላቸው በራሳቸው ፈቃድና ወጭ መጥተው ያለባቸውን የሙያ ግዴታ ለመወጣት እየሰሩ ሲሆን ይሄን ተግባር በማስፍት ስልጠናው በቴክኖጂ ታግዞ ኦንላይን ትምህርት ጭምር እንደሚሰጥ 1000 ሰልጣኞች ለማሰልጠን ከመንግስት ጋር በመተባበር በታቀደው መሰረትየዛሬው ለ4ኛ ዙር 400 ሰልጣኞች ናቸው ቀጣይም በተመሳሳይ እንሰራለን ማለታቸውን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል፡፡
-
AuthorSearch Results
Search Results for 'የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር'
-
Search Results
-
ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጀ። የአድዋ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት ሰጠ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩት ጥናትና ምርምሮች ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በአገሪቷ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡት የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሚጠበቀው በታች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም እንደ ዋነኛ ምክንያት አስቀምጠውታል። እንዲያውም ለዘርፉ የሚመደበው አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን በመጠቆም።
በተጓዳኝም የምርምር መሠረተ-ልማቶች አለመኖር፣ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ መሆንና መምህራን ለምርምር ትኩረት አለመስጠታቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩት ጥናታ ምርምሮች ቁጥር አነስተኛ መሆነ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ባሏቸው አቅም በአስገዳጅ መልኩ የጥናትና ምርምር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በትምህርት ተቋማቱ ዝቅተኛ ቢሆኑም በሥመ-ጥር ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ምርምሮቻቸውን የሚያወጡ ጉምቱ ምሁራን መኖራቸውንም ዶ/ር ሳሙኤል አልሸሸጉም።
ለጥናትና ምርምር የሚበጀተውን በጀት በተመለከተም ከአገሪቷ እድገትና ከመምህራኑ አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ እያደገ የሚመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ጆርናሎች ጥራታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጥናት እየተደረገበት መሆኑንም አስረድተዋል። መመሪያውንም በቅርቡ ወደ ሕግ በመቀየር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ጆርናሎች የሚመሩበት ወጥ ሥርዓት በመዘርጋት የእውቅና ደረጃም እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ መውሰድ (ረቂቅ አዋጁን ማውጣትም ሆነ ለጆርናሎች መመሪያ መዘጋጀት) የሚካሄዱትን ምርምሮች ጥራታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፥ በቀጣይም ጥናትና ምርምር ላይ የግሉ ዘርፍ የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ቁጥር 33 ሺህ ደርሷል፤ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺህ 500 የሚሆኑት ናቸው ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው – የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው።
ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ፥ ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት መስጠቱን በትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የአድዋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የዩኒቨርስቲውን ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘብራአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ እንዲውል መሬቱ ተሰጥቷል። በዚህም 131 የአካባቢው አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ላይ ተነስተዋል። ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮችም ካሳ ክፍያ ለመፈፀም 15 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ በበኩላቸው ግንባታውን ለማስጀመር ከፌዴራልና ከትግራይ ክልል መንግሥታት 450 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። ከዚህም የትግራይ ክልል መንግሥት 250 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል መግባቱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ አስተዳደርም በቅርቡ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ