Search Results for 'ዲያስፖራ'

Home Forums Search Search Results for 'ዲያስፖራ'

Viewing 10 results - 1 through 10 (of 10 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት በጋራ ለመመከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን ከሕዝባቸው ጎን በቆራጥነት በመቆም የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ይህ የህልውና ጦርነት በውጭ ሀገር የምንገኘውን ኢትዮጵያውያን እንቅልፍ የነሳና ሀገራችን እንደ ሀገር እንዳትቀጥል በወያኔ ጁንታ ቡድን፣ በአልሸባብ፣ እና በሸኔ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በቅንጅት የከፈቱብን ጦርነት ብሔራዊ ክብራችንና የሚነካ የሀገራችንን ሰላም የሚያውክ በመሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል።

    ስለዚህ መንግሥት በሆደ ሰፊነት ቀደም ሲል የወሰዳቸውን ቁርጠኛ የሰላም ፍላጎቶቹን በማድነቅ የሰላም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ሙሉ ድጋፍ ስንሰጥ መቆየታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀቱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከሰላም ይልቅ ጦርነትንና እልቂትን መርጠው የከፈቱብንን የአጥፍቶ መጥፋት ጦርነትን በጥብቅ አውግዘን መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የአሸባሪውን ጁንታ ቡድን እንዲሁም አልሸባብና ሸኔን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሕልውናና ለሕዝባችን ሰላምና ጥቅም ስንል ከመንግሥትና እንዲሁም ከመከለከያ ሠራዊታች ጎን በመቆም የዜግነት ድርሻችንን ለመወጣት የትግባር ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።

    በእርግጥ ዲያስፖራው ዛሬም ነገም ለሀገሩ ለወገኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ቢሆንም በሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው ሀገር የማዳን ዘመቻ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ እምነት ሳንከፋፈል ከስሜታዊነትና ከኩሪፊያ በመውጣት ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ነገር ለማምጣት፣ የተሻለችውን ኢትዮጵያ ለማየት ትግሉን የሚጠይቀውን ማንኛውንም ድጋፉ እንድናደርግ ምክር ቤታችን በድጋሚ በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ጥሪ ያቀርባል።

    መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን፣ ውስጣዊ ችግሮቻችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት ግጭቶችና የጦርነትን ውድመት እንዳይቀጥል በቁርጠኝነት ተነሳስቶ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መሠረት ለመጣል ፖለቲካዊ ችግሮችን በአግባቡ ፈትሾ ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድርድር ማድረግ፤ በሀገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ቡድኖች ወደ ዘላቂ ሰላም የጠረንጴዛ ድርድር እንዲቀመጡ ወስዶት የነበረውን የሰላም ጥረት አሁንም ወደፊትም እንዲቀጥል ምክር ቤታችን መደገፉን ይቀጥላል።

    ነገር ግን ከጦርነት በተሻለ ሰላምን መምረጥ ትርፋማነቱ ቢያዋጣም አሸባሪውና ጎጠኛው የጁንታው ቡድን የአማራና አፋርን ሕዝብ በመውረር የትግራይን ሕዝብ አግተው በሰላማዊ ሕዝብና በመሠረተዊ የልማት ተቋማት ላይ ያደረሱትን መጠነ ሰፊ ውድመት መልሰን ለማቋቋም እርብርብ በምናደርግበት ወቅት የሀገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ለሦስተኛ ዙር የተከፈተብን ታሪክ ይቅር የማይለው ጦርነት በእጅጉ አስቆጥቶናል። ስለዚህ፦

    1ኛ የአማራና የአፋር ክልልን በመውረር ሲዋጉና አመራር ሲሰጡ የነበሩትን እንዲሁም እድሚያቸው ለውትድርና ሞያ ያልደረሱ የትግራይ ህፃናትን በመመልመል ለጦርነት ያሰልፉትን የወያኔ ጁንታ አመራሮች ተለይተው በጦር ወንጀለኝነትና በሀገር ክህደት ክስ ተመሥርቶባቸው በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥትን እንጠይቃለን።

    2ኛ ሀገራችን በገጠማት የሰላም ማጣት ችግርና ተገዳ ከገባችበት የህልውና ጦርነት በተጨማሪ የሕዝብ ሞትና የሥነ ልቦና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የሐሀት ቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በሚያደርጉ ቅጥረኛ ሚዲያዎች፣ አለአግባብ ለመበልፀግ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈፅሙ ነጋዴዎች፣ በተለይ የመንግሥት ሙሰኞችና ሌቦች ላይ ያለምንምንም ይቅርታ ጠንካራ እርምጃ መንግሥት እንዲወስድ እናሳስባለን።

    3ኛ መንግሥት የሚቻለው ሁሉ ጥረት በማድረግ ለሀገር ጠቀሜታ ሲል ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ አካሄዶችና አዳዲስ ስልቶችን (strategies) መንደፍ አለበት። በተለይ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ የሚያውኩትን የሚዲያ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለድፕሎማቶቹን ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጥና ለተግባራዊነቱም ልዩ ክትትል እንዲያደርግ በጥብቅ እናሳስባለን።

    በመጨረሻም ምክር ቤቱ ወደፊት ከሚያደርጋቸው የድጅታል ዲፕሎማሲ ትግል በተጨማሪ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ በሚደረገው የህልውና ጦርነት የዘማቹ ሠራዊት ደጀን በመሆን ጠንካራ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እናረጋግጣለን።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት (ኢዳተም)

    Semonegna
    Keymaster

    “የአማራ ባንክ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ባለአክሲዮን እንዲሆኑ አስችሏል” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)

    አዲስ አበባ (አሚኮ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አማራ ባንክ መከፈቱንና መይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክተው ለባንኩ ባለድርሻ አካላት እና ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

    ዶክተር ደሴ ይናገር አማራ ባንክ አጀማመሩ ከሌሎች ባንኮች የተለየ የሚያደርገው ጉዳዮች እንዳሉት አስረድተዋል። የባንኩ አክሲዮን በስፋት በገጠርም በከተማም የተሸጠ መሆኑ፤ በባለ አክሲዮን ብዛት ትልቅ ባንክ መሆኑ ልዩ ባንክ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

    ዶክተር ይናገር የባንኩ እውን መሆንን ያሳኩ አደራጆች እና የባንኩ የሥራ አመራር ሊመሰገኑ እንደሚገባም ነው የገለጹት። በተለይ የአማራ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ መላኩ ፋንታ በባንክ ምሥረታ ሂደት አሰልቺውን ጉዞ በተለይም ከተቀመጡት መስፈርቶች አንድ እንኳን ቢጎድል መሳካት የማይችለውን ሂደት በማሳካት ያከናወኑት ሥራ ትልቅ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት። አቶ መላኩ ከበርካታ የሕይወት ውጣውረድ እና እስር በኋላ ተቋም መርተው ለሕዝብ የሚጠቅም ባንክ ማቋቋም በመቻላቸው እሳቸው እና የሚመሩት አደራጅ እና የሥራ አመራር ቦርዱ ምሥጋና አቅርበዋል።

    በአማራ ባንክ ምሥረታ ላይ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ እና ባንኩ እውን እንዲሆን ያደረጉት ተሳትፎ የሚመሰገን እንደሆነም ነው ዶክተር ይናገር የገለጹት።

    በባንክ ምሥረታ በአንድ ቀን 72 ቅርንጫፍ ለመክፈት ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም ተሠርቶ ካልሆነ የማይቻል እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ይናገር ደሴ፥ ለዚህ ውጤት የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄኖክ ከበደ እና የሥራ አጋሮቻቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትልቅ በመሆኑ ሊመሰገኑ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

    ኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ አቅም ገና ያልተነካ በመሆኑ አሁን የተከፈተውን አማራ ባንክ ጨምሮ አዳዲስ እየተከፈቱ ካሉ ባንኮች በተጨማሪ ከተሳካ የሌሎች ሀገር ባንኮች እንዲገቡ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት። ይህም የሀገርን ልማት በማፋጠን የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት። ባልተነካው የሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ እና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የአማራ ባንክ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ዶክተር ይናገር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

    አርሶ እና አርብቶ አደሮች የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የባንክ ባለአክሲዮን እንዲሆኑ ማስቻል አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ረገድ አማራ ባንክ ሰፊ የአክሲዮን ሽያጭን በገጠር በመሸጥ የሚስተካከለው እንዳልተገኘም ነው የጠቆሙት። ባለአክሲዮኖቹም በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ መሆናቸው ባንኩን ልዩ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል። ይህም ባንኩን የመላው ኢትዮጵያዊያን ባንክ እንደሚያደርገው ዶክተር ይናገር አስረድተዋል።

    አማራ ባንክ በአገልግሎት አሰጣጡ እና በፍትሐዊ አሠራሩ ልቆ ከወጣ የውጭ ባንኮች ቢገቡ እንኳን ተወዳዳሪ መሆን ስለሚችል ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ባንኩ ቁጠባን በማበረታታት ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፤ ለባንኩ መንግሥት የሚያደርገው እገዛ እንደተጠበቀ ሆኖ ባንኩ ኢትዮጵያዊያንን ሊያገለግል እንዲችል የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን በስፋት ገቢራዊ ማድረግ እንዳለበት ነው ዶክተር ይናገር የተናገሩት። አማራ ባንክ ዘመኑ የቴክኖሎጅ በመሆኑ በቴክኖሎጅ ዘርፍ ልቆ እንደሚወጣም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ አሚኮ

    Anonymous
    Inactive

    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
    ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣
    ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሉች፤
    የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻችን፤
    በመላው ዓለም ለምትገኙ ሰላም ወዳድ ኃይሎች በሙሉ !

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ዙሪያ መለስ ውይይት በማድረግና፤

    • የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መሠረት ለመጣልና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ ሥልጣን የሚይዝ ሥርዓት ለመፍጠር የተደረገውን 6ኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሂደት በመገምገም፤
    • የታላቁን የአባይ ግድብን በማጠናቀቅና እንደ ሀገር የተፈጥሮ ፀጋችንን ተጠቅመን የመልማት መብታችንን ለማረጋገጥ በተያያዝነው ጥረት ረገድ የተጋረጡብንን ተግዳሮቶች በመገንዘብ፤
    • ሕዝባችን በሰላምና ደህንነት እጦት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና መረን በለቀቀ የኑሮ ውድነት እየደረሰበት ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ግምት ውስጥ በማስገባት፤
    • ከሁሉም በላይ ሀገራችን ከውስጥ በከሃዲያንና እኩያን ኃይሎች ቅንጅት፣ ከውጭ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻቸው አይዞህ ባይነትና ድጋፍ የተደቀነባትን የህልውና ስጋት ተቀዳሚ ትኩረት በመስጠት፤

    የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የደረሰባቸውን አቋሞች ለተከበረው ሕዝባችን፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በአጠቃላይም ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ይወዳል።

    1. ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ

    አብን እንደ ድርጅት የመጀመሪያው አብይ የፖለቲካ ተመክሮው በሆነው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ ሲያቅድ፥ ገና ከመነሻው ሀገራችን የምትገኝበትን የፖለቲካ አውድ በመገምገም በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለሀገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዴሞክራሲያዊ ተመክሮ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር እንደሆነ በይፋ አሳውቋል።

    አብን ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ዘመቻውን ስትራቴጂክ ግቦችና ማስፈፀሚያ ስልቶችን በዝርዝር በመንደፍ፣ አማራጭ ፖሊሲዎቹን በማኒፌስቶ በመሰነድና ሙሉ ድርጅታዊ ኃይሉን በማንቀሳቀስ በምርጫ በሚሳተፍባቸው በአማራና ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች 510 እጩዎችን በማቅረብ ሰፊውን መራጭ ሕዝብ ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።

    በዚህም መሠረት የምርጫ ዘመቻው ከነተግዳሮቶቹ ተጠናቅቆ፣ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ፓርቲያችን በሚወዳደርባቸው ክልሎች ድምፅ ተሰጥቶና በከፊል ጊዜያዊ ውጤት ተገልጾ በድኅረ ምርጫ ሂደት ላይ እንገኛለን።

    ፓርቲያችን በመላ ሀገሪቱ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በምርጫው ሂደት የተፈፀሙትን አበይት ጥሰቶች በማሰባሰብና በዝርዝር ቅሬታዎችን በመሰነድ በህግ አግባብ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል። የምርጫ ቦርድ ከተጣለበት ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ ከሰው፣ ከፋይናንስ፣ ከተመክሮና ከሎጂስቲክ አቅም ውሱንነት ቢታይበትም በአጠቃላይ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ አንፃራዊ አዎንታዊነት እንዳሳየ እናምናለን። በቦርዱ የበላይ አመራር የታየው ገለልተኝነት፣ ግልፅነትና ፍትሃዊነት መንፈስ እንደ ተቋም የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም እንገነዘባለን።

    የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሕዝባችን ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ በምርጫው ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ላሳየው ፅናት ልባዊ አድናቆቱን በመግለፅ፣ የመራጩ ድምፅ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ህጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የሕዝባችንንም ሀቀኛ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል ለማሳወቅ ይወዳል።

    በሌላ በኩል 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሥርዓቱን እውነተኛ ባህርይ በተግባር መፈተንና ማጋለጥ መቻሉን ትልቁ ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በምርጫው ሂደት የታየው ጎዶሎነትና ክፍተት ከምርጫ ውጤት አኳያ የምንመዝነው ከሆነ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የሃሳብ ብዝሃነት የማያመለክት መሆኑን መናገር ይቻላል።

    አብን እንደ ድርጅት በምርጫ በመሳተፉ ምን አገኘ፣ አሳካ የሚለውን ስንገመግም አንዳንድ ተስፋ ሰጭ ነገሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም። ከሁሉም በላይ የሕዝባችን እውነተኛ ወኪል ስለመሆናችን ሕዝባችን የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁሞ በሰጠን የመተማመኛ ድምፅ በቂ ማረጋገጫ አግኝተናል። ይህም የመጪው ዘመን ፓርቲ መሆናችንን ይመሰክራል። በሐገር አቀፍ ድረጃ በተሻለ ሕዝብን የማስተባበር አቅም እንዳለንና ጠንካራ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል መሆናችንን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠናል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የምርጫው ሂደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ይገነዘባል። በቀጣይም ከሂደቱ ያገኛቸውን ተመክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካችን ሁነኛ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።

    1. ብሔራዊ ደህንነትን በተመለከተ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት፣ በሕዝብ ጥቅምና ክብር፣ በሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ረገድ ግልፅና የማያሻማ አቋም ያራምዳል። በገዥው ፓርቲ ግልፅ ፍረጃ፣ ወከባና ጥቃት እየደረሰበትም ቢሆን የፖለቲካ ማዕከሉ እንዲረጋጋና በአፍሪካ ረዥሙንና ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ያደረገች ሀገር ተመልሳ ወደ ቀውስ እንዳትገባ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

    አብን ወቅታዊው የሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት ከጊዜ ጊዜ እየከፋና እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ይገነዘባል። የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ከተቻለ ኢትዮጵያን ለየዘውጉ አምበሎች በታትኖ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት፤ ካልሆነ ደግሞ ውስጣዊ አንድነት የሌላት፣ ደካማና ፍላጎታቸውን ያለማንገራገር የምትቀበል አድርገው ለማሽመድመድ እየተረባረቡ ይገኛሉ።

    ከዚህ አንፃር የብልጽግና አገዛዝ የሀገሪቱን፣ የዜጎችና የመንግሥቱን ሰላምና ደህንነት፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ክፍተቶች እየተስተዋለበት ነው። በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ከአፈናና ጭቆና መንበሩ የተባረረውና በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ እና አፋር ልዩ ኃይልና ሕዝባዊ ሚሊሺያ ድባቅ የተመታው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊሆን በቅቷል።

    አብን ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልፅ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀርባል።

    መንግሥት ልዩ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤ በተለይም አሸባሪው የትህነግ ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን፤ በአጠቃላይም የትግራይን ሕዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ሁኔታ አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል። የትግራይ ሕዝብ በመካከሉ ለሚገኙ ተማሪ ልጆቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።

    አብን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሀገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሀገራችን ስለገጠማት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል።

    በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል ዳግም በዲፕሎማሲው አውድማ እንዳይነጠቅ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀርባል።

    በተለይም ደግሞ በፀረ – ኢትዮጵያው ጎራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተሰነዘረበት የአማራ ሕዝብ የሚገኝበትን ወቅታዊ የስጋት ደረጃ በውል ተገንዝቦ የበኩሉን ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርግ፣ የአማራ ዲያስፖራ በሕዝባችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ሁለገብ የሃሳብ፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።

    አብን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ መላው የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ አኩሪ የነፃነት ታሪክ ያላት ሀገር በእኩያን ኃይሎች የተከፈተባትን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት ለመመከት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ ረገድ በአካባቢው ጉዳይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለምአቀፍ ተቋማት በአፍራሽ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳይደለሉና የችግሩን ዙሪያ ገብ በፍትሃዊነት በመገምገም እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርባል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ላይ የተደቀነውን ፅኑ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም የሀገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን በአፅንኦት ለመግለፅ ይወዳል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
    ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም

    ምንጭ፦ አብን

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ

    Semonegna
    Keymaster

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) በትብብር ለመሥራት ስምምነት አደረገ

    ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካን ሀገር ካምብሪጅ ከተማ ከሚገኘው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) ከተሰኘው ዕውቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።

    ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡትን ውል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችላቸውን የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ማከናወንም ጀምረዋል።

    በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ሐብቴ ዱላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር የሚኖረው የትብብር ሥራ በዋናነት በኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የሚሰጡትን የትምህርት ፕሮግራሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የቤተ-ሙከራ ትምህርት ለማስደገፍ የሚያስችልና በመምህራንና በተማሪዎች የሚሠሩትን የምርምር ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

    እንዲሁም የትብብር ሥራው የኮሌጁን የመማር-ማስተማር ሥራ ለማዘመንና ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን ለማስጠበቅ የሚያግዘው ከመሆኑም ባሻገር በምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶ/ር ሐብቴ አስረድተዋል።

    በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኮርአብዛ ሸዋረጋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፥ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባው ውል መሠረት በያዝነው የ2012 የትምህርት ዘመን ከሁለተኛው መንፈቀ-ዓመት /ሴሚስተር/ ጀምሮ ዓመታዊ ክፍያው ከ160 ሺህ በላይ የሆነውን የኦንላይን ትምህርት በነጻ በመስጠት የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅን ተጠቃሚ ማድረግ ይጀምራል። ለዚህም ዕቅድ ተግባራዊነት ኢንሰቲትዩቱ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።

    በዚህም መሠረት ድጋፍ ሰጪው ቡድን የኦንላይን ትምህርቱን ለመስጠት ወሳኝ የሆኑት የቤተ-ሙከራ ዕቃዎችን ይዞ በመምጣት ለዩኒቨርሲቲው በእርዳታ አበርክቷል። የተበረከቱት ዕቃዎች እስካሁን ድረስ በንድፈ-ሐሳብ /theory/ ብቻ ሲሰጡ የነበሩትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ /artificial intelligence/፣ ሮቦቲክስ /robotics/ እና ተዛማጅ የትምህርት ዓይነቶች የማስተማር ዘዴ በተግባር የታገዘ አንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አቶ ኮርአብዛ ገልጸዋል።

    ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከታቸውን የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል ከኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅና ከኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለተውጣጡ 10 መምህራን ከጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ያዘጋጀውን በኮምፒዩተር ፕሮግራም ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በመጨረሻም ዶ/ር ሐብቴ አክለውም፥ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመሥራት እንዲችሉ በማገናኘቱ ሥራ በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ እንደነበረ በመግለፅ ይህንን የዜግነት ግዴታቸውን ለተወጡት የዲያስፖራ አባላት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።

    ምንጭ፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ዘንድሮ ለሰባተኛ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን የሸለመው የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) ተካሂዷል።

    በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማንን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

    ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በዘጠኝ ዘርፎች 291 ሰዎች ከሕዝብ ዘንድ ተጠቁመው የነበረ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 27ቱ ተመርጠው ለመጨረሻ ዕጩነት (በዘጠኝ ዘርፎች፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ ሦስት ሦስት ዕጩዎች) ቀርበው ኢትዮጵያውያን አሸናፊዎችን እንዲመርጡ ተደርጎ ነበር

    ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በእያንዳንዱ ዘርፍ ከቀረቡት ዕጩዎች ውስጥ የመጨረሻ ተሸላሚዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት አሸናፊዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

    በመምህርነት ዘርፍ

    • ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል

    በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)

    • ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በ አትክልት ምርምር ፕሮፌሰር፣ የጎለሌ ዕፅዋት ማዕከል የበላይ ኃላፊ፣ በሀገረ እንግሊዝ የተከበረው KEW International ሜዳል ተሸላሚ)

    በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ

    • አቶ በዛብህ አብተው (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የስፖርት ፎቶግራፍ አንሺ)

    በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)

    • አቶ አብድላዚዝ አህመድ

    በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ

    • አቶ ነጋ ቦንገር (የነጋ ቦንገር ሆቴል፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ የንግድ ተቋማት ምሥራች እና ባለቤት)

    በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት

    • አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ

    በቅርስና ባህል ዘርፍ

    • አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)

    በሚዲያና ጋዜጠኝነት

    • አቶ አማረ አረጋዊ (ሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር በስሩ የሚታተመው ሪፖርተር ኢትዮጵያ (የአማርኛ እና የእንግሊዝኛ) ጋዜጣ መሥራች)

    በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች

    • አቶ ኦባንግ ሜቶ (ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) መሥራች እና ሊቀ-መንበር)

    የሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ የክብር ተሸላሚዎች

    • የጋሞ ሽማግሌዎች (በቡራዩ የተከሰተውን ግድያ በመቃወም በአርባ ምንጫ የተቃውሞ ሠልፍ ላይ፣ በቁጣ ንብረት ለማውደም የቃጡ ወጣቶች እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ አንደ አካባቢው ባሕል ሣር ይዘው በአካላቸው ቆመው ንብረቱን ከጥፋት የተከላከሉት የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ነበሩ።)

    በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎችን እንኳን ደስ አላቸሁ ብለዋል። ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቷ፥ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚዎች ለነገው ትውልድ ተረካቢዎች አርዓያ የሚሆን ሥራ በመሥራታቸው ሊደነቁ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    በ2005 ዓ.ም. በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተቋቋመው የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵይውያን በጎ ሥራን የሠሩ እና ለሌሎች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ማበረታታት እና ዕውቅና መስጠት ነው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    The 7th edition of Bego Sew Award የበጎ ሰው ሽልማት


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊው የበጎ ሰው ሽልማት ከግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዕጩዎችን ሲጠቁሙ እንደነበር ይታወሳል።

    በዚህ በተጠቀሰው የጊዘ ገደብ ውስጥም በ አጠቃላይ 291 ሰዎች ተጠቁመው 27 ዕጩዎች ለዳኞች ውሳኔ ቀርበዋል ለመጨረሻው የዳኞች ውሳኔ መቅረባቸውን የበጎ ሰው ሽልማት አስተባባሪዎች በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

    እንደወትሮው ሁሉ በሽልማቱ ዕጩዎች የተጠቆሙባቸውና ሽልማት የሚያሰጡት አስር የተለያዩ ዘርፎች ናቸው። በእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ የቀረቡት ዕጩዎች የሚከተሉት ናቸው።

    በመምህርነት ዘርፍ

    1. ፕሮፌሰር ሽታዬ ዓለሙ ባልቻ (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ)
    2. ወ/ሮ ህይወት ወልደመስቀል
    3. ዶ/ር መስከረም ለቺሳ ደበሌ (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ሥነ-ባህሪ ኮሌጅ)

    በሳይንስ (ህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ)

    1. ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ
    2. ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ
    3. ዶ/ር ታደለች አቶምሳ

    በኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና በፎቶ ግራፍ ዘርፍ

    1. አቶ ሚካኤል ፀጋዬ
    2. አቶ በዛብህ አብተው
    3. አቶ ዳኜ አበራ

    በበጎ አድራጎት (እርዳታ እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች)

    1. ዶ/ር ጀምበር ተረፈ
    2. አቶ አብድላዚዝ አህመድ
    3. አቶ ላሌ ለቡኮ

    በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ

    1. አቶ ዳንኤል መብራቱ
    2. አቶ ክቡር ገና
    3. አቶ ነጋ ቦንገር

    በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት

    1. አቶ በትሩ አድማሴ (ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩ)
    2. ዶ/ር አሚር አማን (የአሁኑ የጤና ሚኒስትር)
    3. አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ

    በቅርስና ባህል ዘርፍ

    1. አቶ አብዱልፈታህ አብደላ (የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የባህላዊ ዳኝነትና የፍትህ ሥርዓቶችን በመጻፍ የሚታወቁ)
    2. አርሶ አደር አቶ አድማሴ መላኩ (በምስራቅ ጎጃም ዞን በጮቄ ተራራ አካባቢ የሚገኘውን ‹‹አባ ጃሜህ›› ደን ለ52 ዓመታት በግል ተነሳሽነት ሲጠብቁና ሲንከባከቡ የነበሩ)
    3. ሳሙኤል መኮነን (ከጎንደር)

    በሚዲያና ጋዜጠኝነት

    1. አቶ በልሁ ተረፈ
    2. አቶ አማረ አረጋዊ
    3. ወ/ሮ አንድነት አማረ

    በኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች

    1. አቶ ኦባንግ ሜቶ
    2. አርቲስት ታማኝ በየነ
    3. ፕሮፌሰር ፀጋዬ ታደሰ

    በተጠቀሱት የሽልማት ዘርፎች ከእያንዳንዳቸው አንደኛ ሆነው የሚመረጡት ዕጩዎች በተመረጡበት ዘርፍ የ2011 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ተብለው ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል (ካዛንችስ፣ አዲስ አበባ) አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ይሸለማሉ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የበጎ ሰው ሽልማት


    Semonegna
    Keymaster

    ባለፉት ስድስት የሽልማት መርሀግብሮች አገራችን የምትኮራባቸውን የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ላከናወኑ ሰዎች እውቅና የተሰጠው ከሕዝብ በቀረበ ጥቆማ መሠረት ሲሆን፥ የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም ለአገራቸው እድገት አርአያነት ያለው አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች ዕውቅና የሚያገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–ሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም የዕጩዎች ጥቆማ ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደጀመረ እና እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንደሚከናወን የሽልማት አስተባባሪ ኮሚቴው አስታወቀ።

    ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለአገርና ለሕዝብ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባርን ያከናወኑ ሰዎችን ዕውቅና የሚሰጠው የበጎ ሰው ሽልማት ሰባተኛው መርሃ ግብር ነሀሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ይካሄዳል።

    ሽልማቱም በመምህርነት፣ በሳይንስ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በበጎ አድራጎት ሥራ፣ በቢዝነስ ሥራ ፈጠራ፣ በመንግስት የሥራ ተቋማት ኃላፊነት፣ በቅርስና ባህል፣ በማኅበራዊ ጥናት፣ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፎች እና ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎችን የሚያካትት እንደሆነ ኮሚቴው ገልጿል።

    ለእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ ሦስት ዳኞች ተመርጠው ምርጫው የሚከናወን ሲሆን ዳኞቹም የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና በታማኝነት ምርጫውን ያከናውናሉ ተብለው የታመነባው እንደሆኑ በመግለጫው ወቅት ተጠቅሷል።

    ኮሚቴው እንደገለፀው፥ ባለፉት ስድስት የሽልማት መርሀግብሮች አገራችን የምትኮራባቸውን የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ላከናወኑ ሰዎች እውቅና የተሰጠው ከሕዝብ በቀረበ ጥቆማ መሠረት መሆኑን ገልፆ፥ መርሀግብሩን ለዚህ ያበቃው በሂደቱ የሕዝብ ተሳትፎ በመኖሩ ስለሆነ ይህም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

    የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማ ለአገራችን መልካም የሠሩ፣ አገራዊ ተልዕኳውን በብቃት የተወጡ፣ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጪ ተግባራትን ያከናወኑ፣ የአገሪቱን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል እንዲጠበቅና የሀገራቸው ስልጣኔ ከፍ እንዲል የሠሩ ኢትዮጵያዊያንን በማበረታታት ዕውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሥራዎችን ለሀገራቸው ማበርከት እንዲችሉ ማስቻል ነው።

    ይህንን የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማ ከግምት ውስጥ በማስገባት ህብተረሰቡ ጥቆማውን ከግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በስልክ፣ በቫይበር (Viber)፣ በቴሌግራም (Telegram)፣ በኋትሳፕ (WhatsApp)፣ በኢሜይል (e-mail)፣ በፖስታና በአካል በመቅረብ መጠቆም እንደሚቻል ኮሚቴው ያሳወቀ ሲሆን፥ ለዚህም አገልግሎት በስልክ ቁጥር 0940140813begosewprize@gmail.com እና ፖስታ ሳጥን ቁጥር 150035 አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ መጠቀም ይቻላል ተብሏል።

    የዘንድሮው የሽልማት ፕሮግራም ለአገራቸው እድገት አርአያነት ያለው አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች ዕውቅና የሚያገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የበጎ ሰው ሽልማት


    Semonegna
    Keymaster

    መቀዛቀዝ የታየበትን የህዝባዊ ተሣትፎ ለማነቃቃት የተለያዩ መድረኮችን በቀጣይነት እንደሚያዘጋጅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ገልጸዋል።

    አዲስ አበባ (ዋልታ)– የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለፉት 6 ወራት 484 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል።

    ጽህፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ሲሆን በቀጣይ የተጠናከረ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚንቀሳቀስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር እና የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።

    መቀዛቀዝ የታየበትን የህዝባዊ ተሣትፎ ለማነቃቃት የተለያዩ መድረኮችን በቀጣይነት እንደሚያዘጋጅ የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ገልጸዋል።

    ቪዲዮ፦ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ድጋፍ ዙሪያ ከኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ጋር የተደረገው ውይይት

    ከዚሁ ጋር በተያያዘም ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ከንቅናቄ መድረኮች አንዱ የሆነው ሁሉም የዳያስፖራ አካላት የሚገኙበት መድረክ በራስ ሆቴል መድረክ አዘጋጅቶ ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር በቀጣይነት እና በተሻለ ሁኔታ ግድቡን ሊደግፉ በሚችሉበት መንገድ ላይ ውይይት አድርጓል።

    ዳያስፖራው ባለፉት ሰባት ዓመታት 46 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን ሃገሪቱ ካላት ዲያስፖራ ቁጥር አንጻር ድጋፉ አነስተኛ መሆኑ ተጠቁሟል። በመሆኑም በተለይም በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ ዲያስፖራዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ድጋፍ ስላላደረጉ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ የዳያስፖራ ማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም አስታውቋል።

    ለዚህም ዳያስፖራው ለህዳሴው ግድብ አዲስ የዳያስፖራ ተሳትፎ ንቅናቄ ለመፍጠር እና በዳያስፖራው ዘንድ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያለውን ብዥታ ለማጥራት መድረክ ፈጥሮ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደነበርና፣ የራስ ሆቴሉ ውይይትም የዚሁ ዋነኛ አካል እንደነበር ተገልጿል። በተመሳሳይ ሁኔታም በዕለቱ የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች የሚሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በካፒታል ሆቴል ተካሂዶ ነበር።

    ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን ከአራት ዓመት በኋላ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

    ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦  

    ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አባባ – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሁለት ወር በፊት ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የትረስት ፈንዱ እንዲቋቋም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው እንደነበረ ይታወሳል።

    በይፋ የተቋቋመው ትረስት ፈንድ ጥቅምት 12 ቀን ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ በይፋ ሥራ እንዲጀምር ላደረጉት ትጋትና ጥረት አባላቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም አመስግነዋል።

    በአሁኑ ወቅት በትረስት ፈንዱ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንዳለና ከዚህም በኋላ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

    ———————————————-

    ———————————————-

    የትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤቱ የፈንዱን አቅምና ውጤታማነት ለማሻሻል በትጋት መሥራት እንዳለበትም ዶክተር አብይ ተናግረዋል።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የሚሰጡትን የተወሰነ ገንዝብ በአንድ ወይም በሁለት ጊዜ ጠቅልለው በመክፈል በጣም ወሳኝ ለሚባሉ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንዲያፋጥኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

    በቀን ከአንድ ዶላር በላይ መስጠት ለሚችሉ ዜጎች ድጋፋቸውን በፍጥነት እንዲያድርጉና ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ከትረስት ፈንድ ምክር ቤቱ ጋር ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ዶክተር አብይ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

    የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ የተመረጡ ሲሆን ስም ዝርዝራቸው በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም መጠቆማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የላከው መግለጫ ያስረዳል።

    ፈንዱ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማቀናጀትና የልገሳውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የባንክ ሒሳብ ቁጥሩም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000255726725 (አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ) ነው። ከዚህ የባንክ የሒሳብ ቁጥር በተጨማሪ ተቋሙ በኢንተርኔትም ገንዘብ እንደሚያሰባስብና ኦፊሴላዊ ድረ ገጹም “https://www.ethiopiatrustfund.org” እንደሆነ ክስር በተመለከተው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

    በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀን ቢያንስ 1 የአሜሪካ ዶላር በመለገስ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ተቋም ምክር ሰጪ ካውንስል መግለጫ (ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም)

    የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዳያስፖራ ፈንድ ተቋም ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም (October 22, 2018) ለሕዝብ መዋጮ መሰብሰቢያ ይከፈታል።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፈንድ ተቋም ምክር ሰጪ ካውንስል (ኢዲቲኤፍ) ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም (October 22, 2018) ለሕዝብ መዋጮ መሰብሰቢያ ያዘጋጀዉን ዝግጅት ለሕዝብ ይፋ አድርጎ ሥራዉን በኦፊሴላዊ ድረ-ገጽ https://www.ethiopiatrustfund.org እንደሚጀምር በደስታ ያስታዉቃል።

    ባለፉት ሳምንታት ካውንስሉ የዲያስፖራ ፈንዱን ሕጋዊና መንግስታዊ ደንቦችን በተከተለ መንገድ ፈንዱን ለመመስረት በትጋት ሠርቷል።

    የፈንዱ ካውንስል ምክር ቤት በዓለም ያሉ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በቀን 1 ዶላር ለህዝብ አርዳታ አዋጡ ያሉትን ጥሪ ተመልከቶ መዋጮ ለመስጠትና ፈንዱን በስራ ላይ ለማዋል ከፍ ያለ ጉጉት አንዳላቸው ይገነዘባል።

    ይህን ፍላጎት ለሟሟላትና ፈንዱን በሥነ ስርዓት ሥራ ማስጀመር ምክር ቤቱ ለትርፍ ያልተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማቋቋም የባንክ ሂሳብ ቁጥር መክፈት ከኢንተርኔት ክፍያ ስርዓቶች እና ሌሎች የፋይናንስ መድረኮችን ጋር መደራደር አና የተለያዩ ደንቦችን ሟላትና አስተዳደራዊ እና የአፈፃፀም ሂደቶችን ለመቆጣጠር እና ግልጽነትን ለማረጋገጥ ምክር ቤቱ እነዚህን ሥራዎች በፍጥነት መወጣት ችሏል።

    ካውንስሉ ዓለምአቀፍ ዲያስፖራዎች ማኅበረሰቦች ለፈንዱ ላሳዩት መታገስና የማያወላዉል ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናዉን ያቀርባል።

    ካውንስሉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራን የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ሌሎች ነፃነት ዲሞክራሲ ሰብአዊ መብቶችን እና መልካም አስተዳደርን በኢትዮጵያ ማበልፀግ የሚፈልጉን ሁሉ በቀን 1 ዶላር መዋጮቻቸዉን በአንድ ጊዜ በጠቅላላው 365 የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍሉ ባክብሮት ይጠይቃል። ይህንም በማድረግ አስፈላጊ ፕሮጀክቶችን ባፋጣኝ ለማስጀመር ይቻላል።

    ስለ ፈንዱ ለመማር እና መዋጮ ለማድረግ ወድዚህ ድህረ ገፅ ይሂዱ (ይጫኑ) https://www.ethiopiatrustfund.org/

    ልዩ ማስታወሻ – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በሚል ስም አንዳንድ በግል የተደራጁ ሰዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት እንደሚያደርጉ የፈንዱ ምክር ቤት ይረዳል። ነገር ግን ኦፊሴላዊ የሆነው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 9, 2018 በካውንስሉ የተቋቋመው ኤድቲኤ (EDTF) ብቸኛና መደበኛ በሕግ የታወቀው ነው።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ኢዜአ)፦ መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ልማት ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥሪ ከግምት ያስገባ አዲስ አቅጣጫ እየቀየሰ መሆኑን የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማኅበር አስታወቀ።

    አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ሥራ ለማገዝ፣ እንደዚሁም በውጭ የሚኖረው ዜጋ በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል ማህበሩ አደረጃጀቱን መልሶ በማዋቀር ላይ ነው ተብሏል።

    በሽርክና ወይንም በሌላ መንገድ በመደራጀት በአገሪቱ የልማት እድገት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ዝግጁ መሆናቸውን ኢትዮጵያዊያን የዲያስፖራ አባላት ገልፀዋል።

    በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መዋዕለ ንዋያቸውን በማቀናጀት አገር ውስጥ መሥራት የሚሹ ከሆነ መንግሥት የተለየ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ ባስተለላፉት መልዕክት፤ በውጭ የመኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቱ ልማት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

    በተለይም በስቶክ ማርኬት ወይንም በአክሲዮን ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ አባላት በተናጠልም ሆነ በመደራጀት ወደ አገራቸው ተመልሰው በልማት እንዲሰመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

    ያላቸውን እውቀትና ገንዘብ በማደራጀት መቅረብ ለሚችሉ የዲያስፖራ አባላት መንግሥት የተለየ ድጋፍ እንደሚያቀርብ ነው ዶ/ር አብይ ያረጋገጡት።

    ቪድዮ፦ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ሀገር ውስጥ ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት እና የሚያጋጥማቸው የቢሮክራሲ ችግር

    ኢትዮጵያዊያኑ ዲያስፖራዎች በበኩላቸው መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እያደረገ ያለውን ጥሪ በአዎንታዊ መልኩ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

    በዚህም በተለይም በሽርክና ወይንም በሌላ መንገድ በመደራጀት በአገሪቱ የልማት እድገት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በተደራጀ አግባብ ከጓደኞቻቸው ጋር ተነጋግረው ትልቅ ካምፓኒ ይዘው ለመምጣት ሃሳብ እንዳላቸው የተናገሩት በውጭ የሚኖሩት ወይዘሮ አማኒ መሃመድ ናቸው።

    “የሥራ ሁኔታ እየተመቻቸ ነው፤ ሁሉም ሰው እውቀቱንና ገንዘቡን ኢንቨስት በማድረግ የአገሪቱን እድገት ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልካም ነው። እኔም እንደ አንድ ውጭ አገር እንደሚኖር ዜጋ ወደ ሃገሬ መጥቼ ለመሥራት ትልቅ እቅድ ይዤ እንደምመጣ ተስፋ አደርጋለሁ” ያሉት ደግሞ አቶ አማን አህመድ ናቸው።

    የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማኅበር ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው ማኅበራቸው ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን የዲያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ እየሠራ ነው።

    በተለይ ደግሞ በኢንደዱትሪ ፓርኮች ላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሊኖራቸው የሚችለውን ተሳትፎ ለማጎልበት ፓርኮቹን የሚጎበኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።

    ይህም ዲያስፖራው ስለ ፓርኮቹ በቂ መረጃ እንዲኖረው ትልቅ እድል እንደሚከፍት ገልጸው ማኅበሩ መረጃ ከመስጠቱ ሥራ ጎን ለጎን ሌሎች የውጭ ዜጎችም በዘርፉ እንዲሰማሩ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማኅበር

Viewing 10 results - 1 through 10 (of 10 total)