-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓረብ ሊግ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ቁልፍ ጉዳዮችን ሳያገናዝብ ለአንድ ወገን ያደላ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አወገዘ።
የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፥ የዓረብ ሊግ የሕግ አስፈፃሚ ምክር ቤት የካቲት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ የደረሰበት ውሳኔ የሚያሳዝን ሆኖ ያገኘው መሆኑን እና ኢትዮጵያ ውሳኔውን በፍጹም የማትቀበለው መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ የሱዳን መንግሥት በዓረብ ሊግ ለቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ድጋፍ ላለመስጠት የወሰደውን አቋም እንደምታደንቅ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ሱዳን የተቀነባበረውን እና የዓረብ ሊግን አቋም ባለመደገፍ የምክንያታዊነት እና የፍትሕ ድምፅ መሆኗን ዳግመኛ ማረጋገጧን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ለተመሠረተው እና የሁሉም ወገን አሸናፊነትን መሠረት ላደረገው የሱዳን አቋም ወደር የለሽ አድናቆቷን ገልጻለች።
ኢትዮጵያ ከዓረብ ሊግ ሀገራት ሕዝቦች እና መንግሥታት ጋር በጋራ እሴት፣ ባሕል እና ልማድ ላይ የተመሠረተ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት እንዳላት በመግለጫው ተጠቁሟል።
የዓረብ ሊግ የተለያዩ ሉዓላዊ ሀገራትን ያቀፈ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የሁሉንም ወገን ፍላጎት ያካተተ እና ሚዛናዊ መስመር መያዝ እንደሚጠበቅበት በመግለጫው ተጠቅሷል።
ከዚህ መስመር በተቃረነ መልኩ የሚሠራ ከሆነ ግን የሊጉ ተዓማኒነት እና በዚህ እጅጉን በተሳሰረ ዓለም ውስጥ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ትብብርን ለማምጣት ያለው አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንደሚሆን ተገልጿል።
በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ እንደነበረው ሁሉ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን “የአሁኑን እና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የዓባይን ውኃ ሃብት የመጠቀም መብት አለኝ” የሚለውን የዘለቀ እና የማይናወጥ አቋም በድጋሚ ገልጻለች።
የዓባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ በሌሎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሳይደርስ ውኃውን በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም መርህን ተከትላ እንደምትሠራ ተገልጿል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አሠራር ላይ መሠረታዊ መፍትሔ የሚሰጠውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነትን ተከትላ እንደምትሠራም ማረጋገጧ ተገልጿል።
የዓረብ ሊግ እውነተኛውን መንገድ ተከትሎ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የዘለቀ እና የጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ እንደሚሠራ ኢትዮጵያ እንደምትተማመን በመግለጫው ተጠቅሷል።
ወዳጅነትን ማጠናከር እና ለጋራ ግቦች ተቀራርቦ መሥራት የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑም ነው የተገለጸው።
-
- የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ያወጣውን መግለጫ (እንግሊዝኛ) ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ደብረ ታቦር (ሰሞነኛ) – “የኪነጥበብ (የአዝማሪ) ሚና ትናንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ የሰላም እና የኪነጥበብ መድረክ በርከት ያሉ ታዳሚዎች በተገኙበት በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ።
በአዝማሪ ላይ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚሉት የአዝማሪዎች አገልግሎት በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ አዝማሪዎች ዘፈንን ከሚከውኑበት ሰውን የማዝናናት ተለምዷዊ ተግባር ባሻገር በኢትዮጵያ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ነበራቸው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ Kimberlin (1983) እንደሚገልፁት፥ ዘፈን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አኗኗር፣ ይትብሃልና ሕይወት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ እንደ Ashenafi (1971) እና Teclehaimanot (1986) ትንታኔ አዝማሪዎች ዋና ሥራቸው ማዝናናት ቢሆንም በተጨማሪ ግን ዜናና ታሪክ ነጋሪዎች፣ ሃያሲዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣ መዝጋቢዎች፣ አዝማቾች፣ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ ያደረገው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “የኪነጥበብ (አዝማሪ) ሚና ትናንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ ታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የግማሽ ቀን መርሐ-ግብር አካሂዷል።
ሰላም ኢትዮጵያ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ በንግግራቸውም እንደገለፁት ኪነጥበብ ለዕድገት ወሳኝ መሆኑንና፣ ኪነጥበብንና ባህልን ያላካተተ ዕድገት ሙሉ ሊሆን እንደማይችል እና ይህ ሰላምና ባህልን አጣምሮ የያዘ መድረክ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለው ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ “የኪነጥበብ (አዝማሪ) ሚና ትናንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን ከውይይቱ በተጨማሪ በመድረኩ የቀረቡት ልዩ ልዩ የኪነጥበብ ሥራዎች ድምቀት ሰጥተውታል።
በመርሐ-ግብሩ መጨረሻ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የም/ማ/አ/ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንበሩ ተሾመ ባህሉንና ትውፊቱን የማያውቅና እነዚህን ሀብቶቹን የማያለማ ማኅበረሰብ ሁልግዜም አያድግም፤ በመጤ ባህሎች የራሱን ወርቃማ የሆኑ ሀብቶቻችንን እያጣንሁልግዜ የውጭ ናፋቂ እየሆንን፤ ስልጣኔ የሚመስለን የሌሎቹ ነው። ግን እኛ ወርቃማ የሆነ ጥበብ አለን፤ እናም ይኸ ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ለሆነው ባህል ሁላችንም የበኩላችንን ድጋፍ ማድረግ፣ መስመር ማሳየት፣ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት ባለሙያዎችን አይዟቹህ ማለት አለብን ሲሉ ገልጸዋል። ባለሙያዎችን ለወደፊቱ እንዴት እንደግፋቸው? እንዴት እናበረታታቸው? የውጭና የውስጥ ሀይሎችን እንዴት እናስተሳስራቸው የሚለውን ለቀጣይ የሁላችንም የቤት ሥራ መሆን አለበት ያሉ ሲሆን በመጨረሻም ለመርሐግብሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን አካላት በሙሉ አመስግነዋል – ዶ/ር መንበሩ ።
ማጣቀሻዎች፦
- Ashenafi Kebede: The music of Ethiopia: its development and cultural setting. Dissertation, Wesleyan University. (1971)
- Cynthia Tse Kimberlin: “The Music of Ethiopia“, in Music of Many Cultures, E. May, ed., Berkeley, Los Angeles: University of California Press. (1983).
- Teclehaimanot G. Selassie: A brief survey study of the Azmaris in Addis Ababa. Proc. of the International Symposium on the Centenary of Addis Ababa. (1986).
ምንጭ፦ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ጠብቀው ከመሥራትና ማህበረሰቡን ከማስተማር ይልቅ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ የሚሠሯቸውን የዘገባ ስህተቶች እና አባባሽ ይዘቶች እንዲያስተካክሉ በቃልና በደብዳቤ እያሳወቅኩ ነው ይላል።
ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚፅፉት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ “የክልል መገናኛ ብዙሃን ወገንተኝነት እና ለገዥው ቡድን አጎብዳጅነት” እንደሚታይባቸው አንስተው፤ ብዙ ፖለቲካዊ ዘገባዎችን እና ትርክቶችን በተዛባ መልኩ የሚያቀርቡ እንደሆኑ ነው የገለጹት።
ዘውግ-ተኮር የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው ያለመዘገብ፣ ሀቅን እንዳለ ያለማቅረብና ሚዛናዊ አለመሆን እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፥ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ግጭት በሚስተዋልበት ወቅት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዳይዘግቡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስህተት የሚፈጽሙት ባለማወቅ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ ዓይነት ስህተት እንዲወጡ መጀመሪያ በማስተማር የተለየ ሁኔታ ሲያጋጥም በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ የሕዝብ ማስተማሪያ አልያም የጦር መሣሪያ የመሆን ዕድል ስላላቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሀሳባቸውን በመስጠት፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣልም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ሃይማኖት ጌታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ “ፅንፍ ይዞ እየተጓዘ” መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ለግጭት አባባሽ እየሆነ ነው ይላሉ።
በተለይ አንዳንድ “የፅንፍ ፖለቲካ” የሚያራምዱ ግለሰቦች የራሳቸውን መገናኛ ብዙሃን በመክፈት የሚፈልጉትን “ፅንፈኛና የጥላቻ አጀንዳ” እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል። በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በኩል ደግሞ “ሕዝብ ሲሞት እና ጉዳት ሲደርስበት ተከታትሎ ከመዘገብና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ መንግሥትን እየጠበቁ የመዘገብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል” ነው ያሉት።
መገናኛ ብዙሃኑ አስቀድመው የስጋት ትንተናዎችን በሚዛናዊነት በማቅረብ ግጭትን የመከላከል ሚና እየተወጡ አይደለም ያሉት አቶ ሃይማኖት፥ ብሮድካስት ባለስልጣንም ለመገናኛ ብዙሃኑ የተሰጣቸው ነጻነት እንዳይታፈን ጥንቃቄ በማድረግ፤ በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ባሉት ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደወሰን አንዱዓለም “የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ በተረበሸ ቁጥር መገናኛ ብዙሃኑም አብረው መታመማቸው ከፍተኛ ችግር አስከትሏል” ነው ያሉት።
አብዛኛው መገናኛ ብዙሃን ሕዝብን ከሕዝብ፣ ክልልን ከክልል፣ መንግሥትን ከሕዝብ የሚያራርቁ ዘገባዎችን እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች የሕይወት መልኮችን ትተው ፖለቲካ ላይ ብቻ የመጠመድ ችግር ይታይባቸዋል ነው ያሉት።
ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃኑን ሥራዎች መዝኖ እርምጃ ለመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፖለቲካዊ መስፈርት በመቀየር ሙያዊ መመዘኛ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፥ በመስፈርቱ መሠረት ድክመትና ጥንካሬ ተለይቶ እንዲያስተካክሉት ለተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ደብዳቤ መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።
“ሀገሪቱ ለውጥ ላይ ናት በሚል መገናኛ ብዙሃኑ የነውጥ አራጋቢ ሆነው እንዲቆዩ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ የፖለቲካ ሁኔታ በተረበሸ ቁጥር ሚዲያው አብሮ መረበሽ እንደለሌበትና በቅርቡ በሚወጣው የመገናኛ ብዘሃን አዋጅ ግልፅ ድንበር እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ አመራሮች በቦርድም ሆነ በሚዲያ መሪነት እንዳይሰየሙ በረቂቅ አዋጁ መቀመጡን አንስተው፥ መገናኛ ብዙሃኑ ከባለሥልጣኑ ጋር እንደ ‘አይጥ እና ድመት’ ከሚተያዩ እርስ በራሳቸው የሚተራረሙበት፣ የሚነጋገሩበትና የሚደጋገፉበት የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል መቋቋሙንም ነው የገለጹት።
“በልቅነት እየሠሩ ያሉትን ለማረም ሲባል በነጻነት ላይ ያሉት መጎዳት የለባቸውም” ያሉት አቶ ወንደወሰን፥ ችግሩን ለማረምና ሁለቱን ለመለየት ከውይይትና ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በቀጣይ በሕግ የተጠና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
«በ1950ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ጋሽ ጥላሁንን፤ አለማየሁ እሸቴን እና ታምራት ሞላን የመሳሰሉ እንቁዎች ሰምቼ ከሙዚቃ ፍቅር ያዘኝ» ድምፃዊ የግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም የሙዚቃ አቀናባሪ አንጋፋዉ አርቲስት አያሌዉ መስፍን። ከሁሉ ከሁሉ የአዲስ አበቤ ፍቅረኛሞች ቀጠሮአቸዉ አያሌዉ መስፍን ሙዚቃ ቤት ጋር እንደነበር የሚያስታዉስ ያስታዉሰዋል።
ድምፃዊ የግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም የሙዚቃ አቀናባሪ ነው፤ አንጋፋዉ አርቲስት አያሌዉ መስፍን። ወሎ የሙዚቃ ባለ ኃብቶችን የሙዚቃ ምሁራንን፤ ያፈራች ሃገር መሆንዋ አብዛኞች ይመሰክሩላታል። ወሎ ካፈራችዉ አያሌዉ መስፍን ከመሳሰሉ ከያኒዎች መካከል በባህል ሙዚቃ ገናና ስምን የተከለዉ የማሲንቆዉ ቀንድ፤ በማሞካሸት የጥበብ ጀማሪ አሰፍዬ አባተ ይባል የነበረዉ፤ አንጋፋዋ ድምፃዊ ማሪቱ ለገሰ፤ አለማየሁ እሸቴ፤ ኃብተሚካኤል ደምሴ ከአብዛኞቹ የጥበብ እንቁዎች እጅግ ጥቂቶቹ ናቸዉ።
ወሎ ከያኒዎችን ብቻ ሳይሆን አራቱን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች ያፈራች እንደሆነችም ይነገርላታል። «በ 50 ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ጋሽ ጥላሁንን፤ አለማየሁ እሸቴን እና ታምራት ሞላን የመሳሰሉ እንቆዎች ሰምቼ ከሙዚቃ ፍቅር ያዘኝ» ያለን አንጋፋዉ አርቲስት አያሌዉ መስፍን፤ ስለአገር ፍቅር ስለፍትህ፤ ስለአንድነት ስለፍቅር አዚሞአል፤ ገጥሞአልም። በተለይ በሙዚቃዎቹ ከኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ጋር በጋራ የሃገር ድንበርን ማስከበሩ ይነገርለታል። በደረሳቸዉ ግጥሞች በርካታ ከያንያን ተወዳጅ ዜማቸዉን ለአድማጭ ጆሮ አድርሰዉ ታዋቂ ሆነዋል። ከሁሉ ከሁሉ የአዲስ አበቤ ፍቅረኛሞች ቀጠሮአቸዉ አያሌዉ መስፍን ሙዚቃ ቤት ጋር እንደነበር የሚያስታዉስ ያስታዉሰዋል።
ምን እሱ ብቻ! እንዲህ እንደአሁኑ የእጀታ ስልክ (ሞባይል) ኖሮ፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሞላ ጎደል ተስፋፍቶ «ሜሴጅ አድግ አድርጊልኝ» በማይባልበት በዝያ ዘመን ከክፍለሃገር የመጡ ኢትዮጵያዉያን አያሌዉ ሙዚቃ ቤት መገናኛቸዉ ነበር። የመዲናዋም ወጣቶች ቢሆኑ በአያሌዉ ሙዚቃ ቤት በራፍ ግራና ቀኝ ከቆመዉ ነጎድጓድ ድምፅን ከሚተፋዉ አምፕሊፋየር «አልያም የድምፅ ማጉያ » በተለይ አዲስ ሙዚቃ ተለቀቀ ከተባለ አካባቢዉ ላይ ቆመዉ ማድመጫቸዉ ነበር፤ የሆነ ሆነና አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አያሌዉ መስፍን የት ይሆን? የሙዚቃዉን መድረክ ተዉዉ እንዴ?
◌ ስለአገር ፍቅር ስለፍትህ፤ ስለአንድነት ስለፍቅር አዚሟል
አዘጋጆች፦ አዜብ ታደሰ እና ተስፋለም ወልደየስ (ዶይቸ ቬለ)
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ‹‹ምን አለሽ?›› የአምለሰት ሙጬ ፊልም ምን ነገር ይኖረው ይሆን?
- የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ የማስፈጸሚያ ሰነድ እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ
- አውታር ― የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን በቀላሉ ለማግኘት የተዘጋጀ የስልክ መተግበሪያ
- ምን ልታዘዝ ― በቀልዳ ቀልድ ለዛ የተዋበውና ፖለቲካዊ ሥላቅ ዘውግ ያለው ድራማ
- ከህመሜ እስከ ስደቴ ከጎኔ ላልተለየው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለመገናኘት አበቃን – አርቲስት ፋሲል ደመወዝ
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ዓላማው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉን በኢፌዴሪ ጠቅላይ የሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። አቶ ንጉሱ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ላይ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) በሰጡት መግለጫ በክልሉ መንግስት ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል።
በተደራጀ ሁኔታ በመንግስት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረው የተደራጀ እንቅስቃሴ ከሽፏል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ።
የአማራ ክልል ወደ መረጋጋት እየመጣ ባለበትና እና ሕዝቡ ቀደም ሲል ያነሳ የነበረውን የህግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ባለበት ወቅት የተሰነዘረው ጥቃት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ላይ የተሞከረ ነው ብለዋል።
ሙከራው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት ይህን መሰሉን ተግባር የመግታት ሥራ እንደሚሠራና ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጸረ-ህገ መንግስትና መፈንቅለ መንግስቶች እንዲሁም በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፥ ክልሉን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ቴለቭዥን ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉትን አጭር ቃል ምልልስ እዚህ ጋር በመጫን ያዳምጡ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ!
- ከዴሞክራሲና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች
- አቶ አዲሱ አረጋን ነጻ ያወጣችው የእስክንድር ፌስታል
- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተቀሰቀሰ ረብሻ የአንድ ተማሪ ህይወት አለፈ
- ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል
Topic: የጉራጌ ሕዝብ ከ158 ዓመታት በፊት…
የጉራጌ ሕዝብ አውራጃውን ከራሱ በተወለዱ አበጋዞች ያስተዳድር የነበረው ኦሮሞ በገዳ መተዳደር ከመጀመሩ ቢያስ ከ208 ዓመታት በፊትና ኦሮሞ ደቡብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅና መካከለኛው ኢትዮጵያን መውረር ከመጀመሩ ከ200 በላይ ዓመታት በፊት ነበር።
የጉራጌ ሕዝብ ከ158 ዓመታት በፊት…
(አቻምየለህ ታምሩ)ሰማዩም ምድሩም የኛ ነው የሚሉን ኦነጋውያን የሚይዙት ቅጣምባሩ ጠፍቷቸዋል። ከሰሞኑ ደግሞ ባሰራጩት በምስል የታገዘ ዜና በጉራጌ ምድር ከ158 ዓመታት በፊት ተቋርጦ ነበር ያሉን የገዳ ስርዓት ማስጀመራቸውን ነግረውናል። እንዲህ ዓይነት ዜና ሲሰማ ዝም ማለት ተገቢ ባለመሆኑ ከ158 ዓመታት በፊት የጉራጌ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር ስለነበረው ግንኙነት፣ የነበረውን የውስጥ አስተዳደር ታሪክና “ገዳ” የሚባለው የወረራና የዘመቻ ስርዓት ወደ በአካባቢው በደረሰበት ወቅት ስለተከተሉ ሁኔታ ሳነብ ከተማርሁት የሚከተለውን ጀባ ብያለሁ።
የጉራጌ ምድር ከጥንት ጀመሮ የኢትዮጵያን መንግሥት ያቆሙ ዋና ዋና የጦር መሪዎችን ያፈራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አውራጃ ነበር። ተመዝግቦ ከምናገኘው ታሪክ ብንነሳ እስከ ሞቃድሾ ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት ባስተዳድሩት ዐፄ ዐምደ ጽዮን [እ.ኤ.አ. ከ1314 ዓ.ም.–1344 ዓ.ም. ድረስ የነገሡ] ዜና መዋዕል ውስጥ ጉራጌ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር ቅርብ ቁርኝት የነበረው ሕዝብ እንደነበር ተጽፎ እናገኛለን። በዘመኑ የጉራጌ አውራጃ የውስጥ አስተዳደር ይመራ የነበረው በጉራጌ ተወላጅ አበጋዞች ነበር።
ጉራጌ አውራጃውን ከራሱ በተወለዱ አበጋዞች ያስተዳድር የነበረው ኦሮሞ በገዳ መተዳደር ከመጀመሩ ቢያስ ከ208 ዓመታት በፊትና ኦሮሞ ደቡብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅና መካከለኛው ኢትዮጵያን መውረር ከመጀመሩ ከ200 በላይ ዓመታት በፊት ነበር። የኦሮሞ ብሔርተኛው ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን “The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia” በሚል ባሳተመው መጽሐፉ ገጽ 158 ላይ እንደጻፈው ኦሮሞ በገዳ መመራት የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1522 ዓ.ም. እንደሆነና የመጀመሪያው ገዳ “ገዳ መልባ” እንደሚባል ነግሮናል። ጉራጌ ግን ኦሮሞ ገዳ ከጀመረበት ከ1522 ዓ.ም. በመቶዎቹ በሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ቆዬት ብዬ የማቀርብላችሁ ከገዳ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላው የራሱ የውስጥ አስተዳደር ስርዓት ነበረው።
የጉራጌ ምድር ክርስትና ቀድሞ በሰፊው ከተሰበከበትና ከጸናበት የኢትዮጵያ አውራጃዎች አንዱ ነበር። በወቅቱ የተጻፈው ድርሳነ ዑራኤል ይህንን ያረጋግጣል። ከድርሳነ ዑራኤሉ በተጨማሪ ራሳቸው የጉራጌ ተወላጆችም ይህንን ታሪክ ጽፈዋል። የጨቦ ኡዳደ ኢየሱስ ሕዝብ ታሪክ ጸሐፊው አቶ ምስጋናው በላቸው “የጨቦ ኡዳደየሱስ ሕዝብ አጭር ታሪክና ባሕል” በሚል በመጋቢት 1985 ዓ.ም. ከጀርመን በጻፉት የታሪክ መጽሐፋቸው ገጽ 66 ላይ እንደጻፉት አይመለል በሚባለው የጉራጌ ምድር የሚኖረው «ክስታኔ» የሚባለው ሕዝብ መጠሪያ «ክስተነ» ከሚል ከቦታው ቋንቋ የመጣ መሆኑንና ትርጉሙም ክርስቲያን ማለት እንደሆነ ነግረውናል። አይመለል የመጀመሪያዎቹ ክስታኔዎች ወይንም ክርስቲያኖች የሰፈሩበት ምድር ነው።
ክስታኔ፣ ጉራጌ በመባል በወል ከሚጠሩት የቤተ ጉራጌ ማኅበረሰቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን ሶዶ ጉራጌ እየተባለም ይጠራል። የክስታኔ ሕዝብ ቋንቋ ክስታኒኛ ይባላል። አቶ ምስጋናው በላቸው በመጽሐፋቸው ገጽ 63 እንደነገሩን በጨቦ ምድር ብቻ ከግራኝ ወረራ በፊት 40 ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት የነበሩ ሲሆን ከወረራው በኋላ የተረፉት ግን 13 ስደተኛ ታቦቶች የተዳበሉበት ታሪካዊው የዋሻ ሥላሴ ቤተክርስቲያንና በወንጭት ደሴት ላይ የነበረው የቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ብቻ መሆናቸውን ነግረውናል። አቶ ምስናጋው ጨምረው እንደጻፉት የዋሻ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የተሠራ መሆኑን ከጉራጌ ታሪክ አዋቂ አባቶች አገኘሁት ያሉትን ታሪክ ነግረውናል። ይህ የጉራጌ ሕዝብ ክርስትናን ከተቀበሉ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገዶች መካከል መሆኑን ያሳየናል።
ጉራጌ የኢትዮጵያን ሰለሞናዊ መንግሥት በሸዋ ምድር ካቆሙ የኢትዮጵያ ዋና ዋና ነገዶች መካከል ቀዳሚው ስለመሆኑ ሌላው ማስረጃ በዐፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት የተጻፈው ድርሳነ ዑራኤል ነው። በዘመኑ ድርሳነ ዑራኤል እንደተጻፈው እግዚአብሔር መስፍንነት ከጉራጌ፥ ከመንዝና ከወረብ እንዳይወጣ ለአጼ ናዖድ [የንግሥና ዘመናቸው እ.ኤ.አ. ከ1494–1508 ዓ.ም. ድረስ ነው] ቃልኪዳን ገባለት ይለናል። ይህ በድርሳነ ዑራኤሉ ከገጽ 311–315 ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን ሙሉው ቃል እንዲህ ይነበባል፦
“ወእምድኅረ፡ ዝንቱ፡ ወሀቦ፡ ለናዖድ፡ እግዚእነ፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ ኪዳነ ምሕረት፡ ከመ፡ ኢይጥፋእ ምስፍና፡ ወምልክና፡ በምድረሸዋ፡ ወመንዝህ ወበሀገረ፡ ጐራጌ፡ ዘይብልዎ ምድረ፡ ወረብ፡ ወምሁር።”
ትርጉም፦
“ከዚሀ፡ በኋላ፡ ጌታ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ከምድረ፡ ሸዋ፡ ምሁርና፡ ምድረ፡ ወረብ፡ ከሚባለው ከጐራጌ፡ አገር፡ ከመንዝም፡ አገዛዝና፡ መስፍንነት፡ አንዳይጠፋ፡ ለናዖድ፡ ቃል፡ኪዳን፡ ሰጠው።”
በድርሳኔ ዑራኤሉ እንደተገለጠው የጉራጌ ሕዝብ በዘመኑ የኢትዮጵያ መስፍን ሆነው እንዲሾምላቸው ከተወሰነላቸው ሦስት የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነበር። በዚህ መልክ እስከ መካከለኛው ዘመን የማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ዋልታ የነበረው ጉራጌ ከግራኝ ወረራ በኋላም ለኢትዮጵያ ቤተመንግሥት በጣም ቅርብ ነበር። ከግራኝ ወረራ በኋላ ዋናኞቹ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ራሶች ጉራጌዎች ነበሩ።
ከግራኝ ወረራ በኋላ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን ከነበራቸው አራጊ ፈጣሪ ጉራጌዎች መካከል በዐፄ ያዕቆብ [እ.ኤ.አ. ከ1597 ዓ.ም.–1603 ዓ.ም.፤ እንዲሁም ከ1604 ዓ.ም.–1607 ዓ.ም. ድረስ የነገሡ] እና በዐፄ ዘድንግል [ እ.ኤ.አ. ከ1603 ዓ.ም.–1604 ዓ.ም. ድረስ የነገሡ) ዘመናት የነበሩትን ራስ ዘሥላሴን ለአብነት መጥቅስ ይቻላል። የጉራጌ ተወላጁ ራስ ዘሥላሴ ዐፄ ዘድንግል “መልከ ሐራ” በሚል ያቋቋሙትን የንጉሥ ሠራዊት ይመሩ ነበር። ዐፄ ሰርጸ ድንግል እ.ኤ.አ. በ1597 ዓ.ም. ከሞቱ በኋላ ደግሞ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያን የገዙት ራስ ዘሥላሴ ነበሩ ማለት ይቻላል።
ራስ ዘሥላሴ በዐፄ ሰርጸ ድንግል ዘመን «ቁርባንና ሚዛን» የተባለው ደምብያ የሰፈረው ሠራዊት መሪ ነበር። ዐፄ ዘድንግል ለወታደሩ አመጽ ምክንያት የሆነ ገባሩን ነጻ የሚያወጣ አዋጅ አውጀው ነበር። ይህ አዋጅ ወታደሩንና ገባሩን ወይም ዜጋውን እኩል ያደረገ አዋጅ ነበር። በዚህ ምክንያት ራስ ዘሥላሴና ቁርባንና ሚዛን የተባለው ሠራዊት በንግሡ ላይ አምጾ ደምብያ ውስጥ ባርጫ ከተባለ ስፍራ ዐፄ ዘድንግልን ገደሉት። ጣሊያናዊው የታሪክ ተመራማሪ ኮንቲ ሮሲኒ (Carlo Conti Rossini) ያሳተመው በዘመኑ የተጻፈው ታሪከ ነገሥት መንግሥት በጉራጌው በራስ ዘሥላሴ እጅ ገብቶ ነበር ይላል። ኮንቲ ሮሲኒ ያሳተመው ታሪከ ነገሥት ውስጥ የሚገኘው ይህ ታሪክ የሚከተለውን ይመስላል፦
“ወበውዕቱ ፩ ዓመት ተጻልዕዎ ሐራሁ ለሐጼ ዘድንግል እለ ይብልወሙ ቁርባን፥ ወሚዛም ወእርስ ዘሥላሴ በምክንያተ ዝንቱ አዋጅ ዘአንገረ ውእቱ እንዘ ይብል ሰብእ ሐራ፤ ወገብራ ምድር። እስመ ዓመፁ ኩሉ ዜጋሆሙ ወቀተልዎ በኵናት ማዕከለ ደምብያ ዘውእቱ ባርጫ [1604 ዓመተ ምኅረት] ። […] ወእምድኅረ አዘዘ እራስ ዘሥላሴ ከመ ያንስእዎ ለሐጼ ዘድንግል ወአንሥእዎ ወወሰድዎ ውስተ ደሴተ ዳጋ ወቀበርዎ ህየ። ወነበረት መንግሥት በዕዴሁ ለጉራጌ ራስ ዘሥላሴ።” [ምንጭ፦ C. Conti Rossini, C. (1893). Due squarci inediti di cronica etiopica. Rendiconti della reale accademia dei Lincei. Classe di Scienze Morali, Storiche e Filologiclre; Page 807.
ትርጉም፦
“በአንድ ዓመት ውስጥ ቁርባንና ሚዛን የተባሉት ወታደሮች እንዲሁም ራስ ዘሥላሴ “ሰው ነጻ ነው፤ ምድር ገባር ነው” በሚለው አዋጅ ምክንያት ዐፄ ዘድንግልን ተጣሉት። ዜጎች [ንጉሡን ደግፈው አመጹ]። በደምብያ መካከል ባርጫ ውስጥ በጦር ወግተው ገደሉት። ከዚህ በኋላ ራስ ዘሥላሴ ዐፄ ዘድንግልን እንዲያነሱት አዘዘ፤ አንስተው በዳጋ ደሴት ቀበሩት። መንግሥት በጉራጌው በራስ ዘሥላሴ እጅ ነበረች።”
ከዚህ የምንረዳው በዘመኑ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት አራጊ ፈጣሪ የነበሩት የጉራጌ ተወላጁ ራስ ነበሩ።
ወደ ውስጥ አስተዳደሩ ስንመጣ የጉራጌ ሕዝብ አውራጃውን የሚያስተዳድረው ከተወላጆቹ በሚመረጡ አበጋዞች ነበር። የጨቦ ተወላጁ አቶ ምስጋናው በላቸው የጉራጌ ሕዝብ አካል የሆነውን የጨቦ ሕዝብ የውስጥ አስተዳደር በሚመለከት “የጨቦ ኡዳደየሱስ ሕዝብ አጭር ታሪክና ባሕል” በሚለው መጽሐፋቸው ከገጽ 85–89 የሚከተለውን ጽፈዋል፤
“አበጋዙ የሕዝቡ ጠቅላይ አስተዳዳሪ ሆኖ እንደ አባት የሚታይ መሪ ነው። አበጋዙ እንደኃላፊነቱ ሥፋትና የሥራው ክብደት ከእጩነት አስንቶ እስከተሾመበት ድረስ በጥልቅ ተጠንቶ የሚመረጥበት ሁኔታ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። ይህም የሚሆነው በየሁለት ዓመት ግፋ ቢል በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ነው። የአንድ አበጋዝ የአገልግሎት ዘመኑ ለሁለት ዓመት ብቻ ሲሆን በዚሁ ሁለት ዓመታት ውስጥ ዳኝነቱና ተወዳጅነቱ ከፍ ያለ ምስክርነት ካገኘ ያለ ምንም ተቃውሞ አንድ ዓመት ተመርቆለት ለሦስት ዓመታት ያስተዳድራል። ድጋሚ መመረጥ የለም።…
አበጋዝ ሲመረጥ በጊዜው ሥልጣን ላይ ያለው የአመራር አካል ሥልጣን ከመልቀቁ ከብዙ ወራት በፊት አበጋዝ መመረጥ የሚገባው ሰው ስም ከየጎሣው በሚስጥር ይጠየቃል። አበጋዝ መሆን ይችላል ተብሎ ከየጎሳው ከየአካባቢው የተጠቆመውን አዛውንት የእያንዳንዱን ሁኔታ ማለት ባኅሪው፣ ተቀባይነቱና የማስተዳደር ችሎታውን በሚስጥር አጥንቶ አበጋዝ ይሆናል ብሎ ያመነበትን ለጠቅላላው የሕዝብ ጉባዔ ያቀርባል።
ሕዝቡ ካመነበት በኋላ የሹመቱ ሥነ ስርዓት የሚፈጸምበትን ቀን ራቅ አድርጎ ይቀጥራል። ቀጠሮው ራቅ የሚለው በሕዝቡ ጥያቄ ሆኖ እንደተለመደው በስርዓተ ሹመቱ ቀናት ሕዝቡ በፈቃዱ የሚደሰትበትን የእርድ በሬዎች፣ የሚበላና የሚጠጣውን ከየጎሳውና ከየአካባቢው አጠራቅሞ ለማምጣት እንዲመቸው ብሎ ነው። የተሿሚው ጎሳ አብዛኛውን ያቀርባል።
በስርዓተ ንግሡ ቀን አበጋዙ በሻሽ ጥምጥም ዘውድ ሰሠርቶላቸው፣ የአበጋዙ ባለቤት በፀጉራቸው ጉንጉን ዘውድ ተሠርቶላቸው አበጋዙ በሠንጋ ፈረስ፣ ባለቤታቸው “እቴ” ተብለው [እቴጌ ማለት ይመስላል] በሰጋር በቅሎ ላይ ተቀምጠው በጎሳቸው እጀብና ሆታ ሰንበት ወራቡ ሲደርሱ እዚያ ተሰብስቦ የሚጠብቃቸው ሕዝብ በዘፈንና በእልልታ ይጠብቃቸዋል። ሰንበት ወራቡ የመጀመሪያ ስርዓተ ንግሥ የሚፈጸምበት ቦታ ነው። እዚያ ቦታ ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ አበጋዙና “እቴ” የሚቀመጡበት በሦስት ድርብ የተሰራ የእንጀራ መደብ ይዘጋጃል። እንጀራ ላይ የሚቀመጡበት ምክንያት እነሱ በሚያስተዳድሩበት ክልል ጥጋብ እንዲሆን ተመኝተው ነው ተብሎ ይታመናል።
ተሿሚዎቹ የክብር ሥፍራቸውን ከያዙ በኋላ በገንዙና በአባጅልባዎች አማካኝነት ሕዝብ በተሰበሰበበት ሥርዓተ ንግሡ ይፈጸማል። ወዲያውኑ ቃለ መሐላ ሲፈጸም ወይፈኖች፣ በሬዎች ታርደው ፈንጠዝያው ይቀጥላል። ይህ የደራ ድግስ በየደረጃው እየተበላ አምስት ቀን ይቆያል። በአምስተኛው ቀን አበጋዙና “እቴዋ” ዋሻ ሥላሴ ቤተክርስቲያን እንደዚያ ታጅበው ሄደው የመጨረሻ ሥርዓተ ንግሥ ከተፈጸመ በኋላ አበጋዙ ወደ ጅሎት ቦታው ተመልሶ አገልግሎቱን ከፈጸመው አበጋዝ መንበሩን ይረከባል። አንዴ አበጋዝ ሆኖ የተመረጠ አዛውንት መንበሩንና አስተዳደሩን በፍቅርና ራሱ ቃለ ቡራኬ ሰጥቶ ለአዲሱ አበጋዝ ሲያስረክብ በትረ መንግሥቱ [በእጁ ይይዘው የነበረው ዘንድ] ለክብሩ ሲባል በእጁ ይቀራል። የአገልግሎቱ ዋጋም ዕድሜውን ሙሉ አበጋዝ ተብሎ መጠራት ሆኖ ይኸው የማዕረግ ስሙና የሚይዘው አንድ ነበሩ።”
የጉራጌ ሕዝብ የውስጥ አስተዳደር በዚህ መልክ የተገለጸውን ይመውላል። አበጋዞቹ በሕዝብ ፊት ሥርዓተ ንግሥና ከፈጸሙ በኋላ የሥርዓት ንግሥናው ፍጻሜ የሚሆነው አበጋዙና እቴዋ በጥንታዊው ዋሻ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የመጨረሻውን ሥርዓተ ንግሥ ከፈጸሙ በኋላ ነው። በዚህ መልክ አውራጃውን ሲያስተዳድር የኖረው የጉራጌ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት የተቋረጠው በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ነው። በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ከማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት የተቋረጠው የጉራጌ ሕዝብ በተለይም የጨቦ ክስታኔና ምሑር ሕዝብ በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ክሥታኔና ምሑር የነበረውን ቋንቋውን በአባገዳዎች ተገዶ እንዲተውና ኦሮምኛ እንዲናገር በመገደዱ ብዙ ስቃይ እንደደረሰበት አቶ ምስጋናው በመጽሐፋቸው አትተዋል። አቶ ምስጋናው በመጽሐፋቸው ገጽ 50 ላይ እንደጻፉት ኦሮሞ በገዳ ስርዓት እየተመራ የጉራጌን ምድር ሲወር የነበረውን ጥፋት እንዲህ ይገጹታል፦
“በዚህ ጊዜ [ኦሮሞ ወደ ጉራጌ ምድር በተስፋፋበት ወቅት ማለታቸው ነው] ስለ ቋንቋ የነበረው እምነት ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ” የሚል ሆነ። ትርጉሙም ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” ማለት ነው።”
እንግዲህ! ኦነጋውያን በጉራጌ ምድር ከ158 ዓመታት በፊት ነበረ ያሉትን ገዳ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ያሉት ገዳ የሚባለው የወረራ ስርዓት ሳይመሰረት የራሱ የውስጥ አስተዳደር የነበረውን የጉራጌ ሕዝብ “ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” እያሉ አባገዳዎች የጉራጌን ሕዝብ ያጠፉበትን፣ ከርስቱ ያፈለሱበትን የወረራና የጦርነት ስርዓት መልሰው ለመትከል ነው። አባገዳዎች ወደ ጉራጌ ምድር ብቻ ሳይሆን ወደ ምዕራብ፣ መካከለኛውና ደቡብ ኢትዮጵያ የተስፋፉት “ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” እያሉ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት እየፈጸሙ ነው። ኦነጋውያን በጉራጌ ምድር መልሰው ሊተክሉ እየፈለጉት ያለው የገዳ ስርዓትም “ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” እያሉ አባገዳዎች ዘር ያጠፉበትን፣ ባላመሬቱን ከርስቱ ያለፈሉበትን የወረራና የዘር ማጥፋት ስርዓት ነው።
የጨቦ ተወላጁ አቶ ምስጋናው በላቸው በመጽሐፋቸው ገጽ 66 እንደነገሩን አባገዳ አካባቢውን ከወረረው ጀምሮ የነበረው ስቃይ፣ ጭቆና መከራ ተወግዶ በጨቦ ምድር ፍቅርና ሰላም የወረደው ዳግማዊ ምኒልክ ሲደርሱላቸውና ከአባገዳ ባርነት ሲያላቅቋቸው እንደሆነ ጽፈዋል። «የሰላሙ ዘመን» ያሉት የዐፄ ምኒልክ ፀሐይ በጨቦ ምድር መውጣት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የጨቦ ካህናት ከዐፄ ምኒልክና ራሶቻቸው ጋር እየዞሩ በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የጥንቱን ወንጌል የማስፋፋት ተግባራቸውን በመቀጠል እስከ ዳር አገር ድረስ እየዞሩ ክርስትና መነሳት የሚፈልገውን ክፍል እንዳጠመቁና ከመሀል ኢትዮጵያ እስከ ኖኖና ጡቁር ምድር ድረስ በመሄድ አዳዲስ አማኞችን ያጠምቁት የጨቦ ቄሳውስት እንደነበሩ አውስተዋል።
ባጭሩ የጉራጌ ሕዝብ ለሺህ ዘመናት የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ዋልታ የነበረ፣ የራሱ የሕዝብ አስተዳደር ስርዓት የነበረው ሠራተኛ ሕዝብ እንጂ ገዳ የሚባል ከዲሞክራሲ ጋር የስናፍጭ ቅንጣት ታህል ግንኙነት የሌለው የወረራ፣ የጦርነት፣ የመስፋፋት ዘመቻና የዘር ማጥፋት የተካሄደበት ስርዓት ባለቤት አልነበረም!
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ አፅም ከሀገረ እንግሊዝ ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ኢትዮጵያ ተጠየቀ። በተጨማሪም ለንደን ከተማ ውስጥ በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም (Victoria and Albert Museum) የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድን መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በለንደን ጉብኝት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም በለንደን የዊንዶዘር ቤተመንግስት (Windsor Castle) የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን መካነ መቃብር እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፄ ሃይለስላሴ ይጸልዩበት የነበረውን ወንበር ጎብኝተዋል።
ዶ/ር ሂሩት ካሳው በአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን እንደመረጃ ምንጭነት በመጥቀስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
በጉብኝቱ ወቅትም “የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ማግኘታችን ደስ ብሎናል፤ ይሁን እንጂ ከትውልድ ቦታው ተለይቶ ህይወቱ ያለፈው ልዑል አለማየሁ አፅም በትውልድ ሀገሩ እንዲያርፍ የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ስለሆነ በክብር ወደ አገሩ እንዲመለስ” ሲሉ ዶክተር ሂሩት ጠይቀዋል።
አፅሙ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ ከአባቱ አጼ ቴዎድሮስና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መቀላቀል እንደሚገባውና የዊንዶዘር ቤተመንግስት ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን አቅርቦ በአፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ ልዑካን ቡድኑን በመቀበል ከቡድኑ ጋር የተወያዩት የዊንዶዘር ቤተ-መንግስት ሃላፊ ዶ/ር ማርክ ፓወል በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል። ሂደቱን በተመለከተ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመከታተል እልባት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ሚኒስቴሩ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የልዑካን ቡድኑ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለንደን የሚገኘውን የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ጎብኝቷል። በዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድኑና በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት (Tristram Hunt, PhD) ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅት በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
እ.አ.አ በ2018 የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ለኢትዮጵያ መመለስ እንደማይችል፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻል መገለጹ ይታወቃል። የሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ውሰት የሚለው ቃልም ለኢትዮጵያውያን ከባድ መሆኑን እንደተረዱት ተናግረዋል። በመሆኑም “የተቸገሩት ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ በመሆኑና ምላሽ ለመስጠት ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ” ብለዋል።
“ያለን አማራጭ ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ሊስተካከሉ የሚችሉ አባባሎችን ተጠቅመን የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር፤ ይህን ካላደረግን ግን በሕጉ ላይ ጸንተን ወደፊት የሚሆነውን ነገር መመልከት ይኖርብናል” ሲሉም ዶ/ር ኸንት አክለዋል።
የባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ቅርሶቹ የኢትዮጵያ በመሆናቸው በረጅም ጊዜ ውሰት ሳይሆን በቋሚነት ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ መመለስ የሚችሉበት አማራጭ መፍትሄ ሙዚየሙ ሊያበጅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በኤምባሲውና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል በአስቸኳይ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም፣ ካለው ሕግ ጋር በማይጋጭና የኢትዮጵያን ጥያቄ ሊመልስ በሚችልበት ሁኔታ በመንቀሳቀስ ጉዳዩ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እልባት እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸፀዋል።
በለንደን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ባለው ሙሉ አቅምና ጊዜ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ቅርሶቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ገብሬ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-