Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
Tagged: መቱ ዩኒቨርሲቲ, ሠመራ ዩኒቨርሲቲ, ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ, ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ, አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ, አሶሳ ዩኒቨርሲቲ, አክሱም ዩኒቨርሲቲ, አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ, አድማስ ዩኒቨርሲቲ, ወለጋ ዩኒቨርሲቲ, ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ, የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ, የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ, ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ, ዲላ ዩኒቨርሲቲ, ጅማ ዩኒቨርሲቲ, ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ
- This topic has 42 replies, 3 voices, and was last updated 1 year, 10 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
July 15, 2019 at 12:12 am #11389AnonymousInactive
ፖለቲካ ብቻ ስናመነዥክ ለሁለት መቶ ሺህ አዲስ ተመራቂዎች የሚሆኑ የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩን ዘንግተነዋል
—–ያሳስበኛል!
(ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ)ዘንድሮ ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ 175 ሺህ ወጣቶች ተመርቀዋል። ከግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የሚመረቁት ሲደመሩበት ከ200 ሺህም በላይ ነው – ተመራቂው።
ሀገሪቱ ፖለቲካ እያመነዠከች ኢኮኖሚዋ ዘጭ ብሏል። የጠየቅኋቸው ባለሀብቶች ሁሉ “ሥራ ቀዝቅዟል” ሲሉ ነው የምንሰማው። ብዙ ኩባንያዎች ሠራተኛ ቀንሰዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የብዙ አምራቾችን እጅ ሥራ-ፈት አድርጎታል። የዋጋ ግሽበቱ ከተጠበቀውም በላይ ሆኖ ኑሮ ጣራ ወጥቷል።
በዚህ ወቅት ይህን ያህል ተመራቂ ወደገበያው ሲወጣ (ወደ ሥራ መፈለጉ ሲገባ) ገበያው ግን ያሉትንም የሚያደርግበት ስላጣ አቅርቦት ከፍላጎት ልቆ ፈላጊ ከተፈላጊ ጋር ተላልፏል። ይህ ደሞ የሥራ አጡን ቁጥር እንዳያንረው ያሰጋል። በበኩሌ ፊዚክስ (physics) ተምሮ የእንጨት ሥራ (woodwork) የሚሠራውን ሰው ሥራ አገኘ ለማለት ይቸግረኛል። ይልቅስ ሀገራዊ ኪሳራ ከዚህ እንደሚጀምር ነው የሚገባኝ። ኢንጂነሪንግ (engineering) ተመርቃ አንድ ቢሮ ፀሀፊ (secretary) ሆና ያገኘኋት ልጅና ኢንጂነሪንግ ተመርቆ ቡና ጠጡ እየሠራ ስኬታማ ሆንኩ ብሎ በኔው ቲቪ የቀረበ ወጣት ካየሁ ወዲህ የሀገራችን ትምህርትና የሰው ሀብት ገበያው ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ መሆኑ ገብቶኛል።
• ሠመራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ስያስተምር የቆየውን 1800 ተማሪዎችን አስመረቀ
አሁንም ግራ የገባኝ ይኸው ነው። ተመራቂ ተማሪ አሸዋ በሆነበት በዚህ ዓመት ይህን ኃይል ማካተት (accommodate ማድረግ) የሚችል ኢኮኖሚ አለመፈጠሩ እያደር ወዴት ሊመራን ይሆን? እንደህንድ የተማረ ኃይል ኤክስፖርት እናድርግ እንዳንል ሀገሪቱ ከህዝቧ 63 ምናምን ፐርሰንት ዘመናዊ ትምህርት ያልተማረ (illiterate) ሆኖባት ገና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተማሩ ሰዎች ትሻለች። እዚህ ደግሞ የተማሩትን የሚቀጥር ኢኮኖሚ የላትም። ወዲህ የትምህርት ጥራቷ መውደቅ እንኳን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ማምረት ቀርቶ ለራሷም የሚመጥን አዋቂ እያፈራላት አይደለም። ነገሩ ሁሉ ቁጭ ብለው ሲያስቡት እንደሊማሊሞ አድካሚ ነው። ምን ይሻለን ይሆን? ተምሮ ተምሮ መጨረሻው አራት ኪሎ የሥራ ማስታወቂያ ሰሌዳ ሲያስስ ውሎ መመለስ? ወይም የተገኘውን እየሠሩ ነፍስን ለማቆየት ሲባል ዕውቀትን ማርከስ? ወይስ የወላጅ ጥገኛ ሆኖ መኖር?
ያሳስበኛል። ለዚህ ነው ፖለቲካ ዳቦ የሚያስጋግር ፋታ ይሰጥ እንደሁ እንጂ ዳቦ አይሆንም ብዬ የማስበው። አገር ፖለቲካ ስታመነዥክ ዜጋ ኑሮን መግፋት ካቃተው፣ ወጣት ሥራ አጥቶ ተስፋ ከቆረጠ፣ ኢኮኖሚው አስታዋሽ አጥቶ ዘመን ከባተ አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ኮላቶራል ዳሜጅ (collateral damage)!!
ፖለቲካው ሲፈተፈት ኢኮኖሚውም አስታዋሽ አይጣ።
ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑJuly 15, 2019 at 3:32 am #11394AnonymousInactiveዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በቡራዩ ካምፓስ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በካምፓሱ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ
—–ቡራዩ (ሰሞነኛ)– ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም, ለመጀመሪያ ጊዜ በቡራዩ ገፈርሳ ካምፓስ በአካውንቲንግና ፋይናንስ በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሕጻናትን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳውና የሴኔት አባላት እንዲሁም የቡራዩ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ ተረፈ ንጋቱ በክብር እንግድነት በተገኙበት አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በ36ኛው ዙር በተለያዪ ካምፓሶች ከ1500 በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃል። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ገፈርሳ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ 18 ተማሪዎችን በዲግሪ እና በመዋዕለ ሕፃናት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን አስመርቋል። በዕለቱ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የተጀመረው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙሮች እና በአካባቢው አባ ገዳዎች ምርቃት ነው።በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ተፈራ ንጋቱ ባደረጉት ገለጻ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በገፈርሳ ካምፓሱ ከተማሪ ብዛት ይልቅ የትምህርት ጥራት ላይ አተኩሮ በመንቀሳቀሱ ሊመሰገን እንደሚገባው ጠቅሰው የዛሬ ተመራቂዎች ዛሬ ተመርቃችሁ የጨረሳችሁ ሳይሆን ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግራችሁ በመሆኑ በርቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በገፈርሳ ካምፓሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ ካምፓሱ ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተመሰረተና በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት፣ በአኒማል ፕሮዳክሽን ቴክኖሎጂ እና በሆርቲካልቸር በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በሌላ በኩል ዩኒቲ አካዳሚ ቡራዩ ካምፓስ በመጪው ዓመት መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል አካዳሚውን በማስፋፋት የቡራዩ ሕብረተሰብ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የማስፋፋት ሥራ እየሰራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተመራቂ ወላጆች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በዕለቱ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያና የፕሬዚዳንቱን ዋንጫ ሸልመዋል።
ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ውጭ በደሴና በአዳማ የስልጠና መስኮችን በመለየት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለሕብረተሰቡ በመስጠት ላይ ይገኛል።
ምንጭ፦ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
July 27, 2019 at 1:34 am #11512SemonegnaKeymasterሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ
—–ፍቼ (ሰሞነኛ) – ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ ሀምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት አስመርቋል። በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
በምርቃት መርሀግብሩ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕት ‛ከጀግናው ጀነራል ታደሰ ብሩ መገኛና ከየዋኋ እናት አበበች ጎበና አገር የምትመረቁ ተማሪዎች በጀግንነት ሀገርን ማሻገር፣ በየዋህነት ሁሉን ማቀፍ መርሀችሁ ሊሆን ይገባል’ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት በበኩላቸው ‛መማር ለራስ ብቻ መኖርና መለወጥ ሳይሆን ለሀገራችን ህዝብ ችግር መፍትሄ መፈለግ ነው’ በማለት የዕለቱ ተመራቂዎች የሀገራቸውን ችግር የሚፈቱ ብርቱ ዜጎች እንዲሆኑ አበክረው ተናግረዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ግርማ አመንቴ ሲሆኑ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ‛በዓለም ላይ ያለምንም ድንበር ከሀገራችሁ ጀምሮ በየትኛዉም ቦታ የመሥራትና ማንኛዉንም ዕድሎች በመለየትና በመጠቀም በምክንያታዊነት፤ ከስሜታዊነት የወጡ ዉሳኔዎችን በመዉሰድ ለዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ የምታደርጉ ዜጎች ለመሆን ራሳችሁን ማዘጋጀት ይጠበቅባችኋል’ ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ለሦስት ዓመታት በሁለት ኮሌጆች፥ ማለትም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።
በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
July 30, 2019 at 1:47 pm #11539AnonymousInactiveአድማስ ዩኒቨርስቲ 6 ሺህ 8 መቶ 48 ተማሪዎችን ተማሪዎች አስመረቀ
—–አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)፦ አድማስ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 6 ሺህ 8 መቶ 48 ተማሪዎች ተማሪዎች ሐምሌ 14 ቀን 2011ዓ.ም. አስመረቀ።
ዩኒቨርስቲው በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተከናወነ ሥነ-ስርዓት ያስመረቃቸው ተማሪዎች በዲግሪና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ዲፕሎማ በመደበኛና ተከታታይ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ናቸው። የዩኒቨርስቲው ሬጅስትራር ኃላፊ አቶ ተፈሪ ክብረት እንደገለጹት ተመራቂዎቹ 3 ሺህ 121 በዲግሪ፣ 1 ሺህ 668 በደረጃ-3፣ እና 2 ሺህ 59 በደረጃ-4 በቴክኒክና ሙያ የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው።
ተመራቂዎቹ በዲግሪ በአካዉንቲንግና ፋይናንስ፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት፣ በሆቴል ማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት እና በኮምፒዩተር ሳይንስ የተመረቁ ሲሆን በቴክኒክና ሙያ ደግሞ በኢንፎርሜሽን ኮምኒኬሽን ቴክኖልጂ፣ ሆቴሌና በቢዝነስ ፋይናንስ ዘርፎች የሰለጠኑ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋይ እንደገለጹት ዩንቨርስቲው በአገሪቷ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በምታደርገው ጥረት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ዩኒቨርስቲው እያደረገ ያለውን የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘም፥ አድማስ ዩኒቨርሲቲ መቐለ ካምፓስ ሰኔ 29 ቀን 2011ዓ.ም. በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በድግሪና በቴክኒክና ሙያ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺሕ 300 ተማሪዎች አስመርቋል። በተመሳሳይ መልኩ ዩኒቨርስቲው 1 መቶ 41 በድግሪ እና 302 ደግሞ በደረጃ-4 በቴክኒክና ሙያ በቢሾፍቱ ካምፓስ የሰለጠኑ ተማሪዎችን አስመርቋል።
አድማስ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮን ተመራቂዎችን ጨምሮ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከ70 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና እርከኖች አስመርቋል።
በአሁኑ ወቅትም በውጭ ሶማሌላንድና ፑንትላንድ በሚገኙት ካምፓሶቹ ያሉትን ጨምሮ በጠቅላላው ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው።
July 30, 2019 at 9:33 pm #11544AnonymousInactiveዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ አስመረቀ
የትምህርት ጥራትን ማጠናከርና ማሻሻል ቀጣይነት ያለዉ ሥራ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ማህበረሰቡ የበኩላቸዉን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ተባለ።
ይህን ያሉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ባስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
ሚኒስትሯ አክለውም ከፍተኛ ትምህርትን የማስፋፋት፣ የጥራትና ፍትሀዊነት ሂደት ዉስጥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። በተለይም ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር መንግሥት ባዘጋጀዉ የሕግ ማዕቀፍ በመደገፍ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋቁመዉ ለዜጎች ሰፊ የትምህርትና የሥራ ዕድል ከፍተዋል። እነዚህ ተቋማት በትምህርት ፈላጊዎች እንደጥሩ አማራጭ ስለታዩና ተቀባይነትም ስላገኙ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ብዛት ከ200 በላይ ደርሷል፤ በዚህም በከፍተኛ ትምህርት ከሚማሩት ጠቅላላ ተማሪዎች ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑትንም ያስተናግዳሉ ብለዋል።
ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ36ኛ ጊዜ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት በዚህ ዝግጅት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማኅበረሰብ አገልግሎትና በጥናትና ምርምር ላይ እያሳዩ ያሉት መልካም ጅምር ሊበረታታ ይገባል ሲሉ ፕሮፌሰር ሂሩት ጨምረው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉት፥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በሄደ ቁጥር የሚፈለገዉ የሰዉ ኃይልም በቁጥርና በጥራት እየጨመረ ይሄዳል። ለዚህም የወቅቱን የእድገት እርምጃና የሥራ ገበያ ፍላጎት የሚመጥን የማስተማር፣ የምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ማስፋፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል። አክለውም፥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሄንን ተገንዝበው የፕሮግራም አድማሳቸውንና አገልግሎታቸውን የአገሪቱን የአሁንና መፃኢ የሰው ኃይል ፍላጎት ባገናዘበና ጥራቱን ባስጠበቀ መልኩ በማሻሻል አጋርነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ አስምረውበታል።
ሚኒስትሯ በቆይታቸውም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘጉ ተመራቂዎች የሜዳሊያና ዋንጫ፣ እንዲሁም የሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕስ ባለቤት በሆኑት በሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስም በተሰየመው የሕይወት ዘመን አገልግሎት ሽልማት ዘርፍ ተሸላሚ ለሆኑ 4 ግለሰቦች የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡
ዶ/ር አረጋ ይርዳዉ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፥ ተማሪዎች በቆይታው ያካበበቱትን ዕውቀትና ልምድ ለአገራቸው በሚጠቅም መልኩ ሊያውሉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአገራችን የመጀመሪያው የግል ዩኒቨርሲቲ በመሆን በመንግሥት ዕዉቅና ተሰጥቶት ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችና መስኮች ለዜጎች ተደራሽነትንና ህትሃዊነትን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
August 9, 2019 at 5:08 am #11648AnonymousInactiveጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በማታው መርሀ ግብር ያስተማራቸውን ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል
—–ጋምቤላ (ሰሞነኛ) – ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎቹን አስመርቋል። በዕለቱ የምርቃት መርሀ ግብር ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተመራቂዎቹን በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያካበታችሁት ዕውቀት ወገንና ሀገርን ወደፊት የሚያራምድ፣ እድገታችንን አጠናክሮ በሕዝቦች መካከል ኢኮኖሚያዊ እድገትና ትስስር ፈጥሮ ፍቅርንና መቻቻልን የሚያሰፍን እንዲሆንም መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህም ዕለት ተዕለት በዕውቀት ላይ ዕውቀትን መጨመርና ሁልጊዜም ለአዳዲስ ጠቃሚ ነገሮች ተማሪ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።
“መማራችሁ አዳዲስ አስተሳሰቦችንና አሰራሮችን በማፍለቅ ለራስና ለወገን የሚበጁ ተግባራትን ለማከናወን በመሆኑ አሁንም በጥረታችሁ ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባችኋል” ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከተናገሩት
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገርን የመቀየር አቅም ስላለቸው በተማሩበት ዘርፍ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በኃላፊነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ለተከታታይ ዓመታት በመደበኛና በማታው መርሀ ግብር ሲያስተምራቸው የቆየውን 790 ተማሪዎችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
August 10, 2019 at 8:47 pm #11662AnonymousInactiveአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 1,859 ተማሪዎችን አስመረቀ
—–አዳማ (ሰሞነኛ) – አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 353 ሴት ተማሪዎችን ጨምሮ 1859 ተማሪዎችን አስመረቀ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ምሩቃኑ በተማሩበት መስክ ጠንካራ ሠራተኛ በመሆን የአገልጋይነት ስሜት በመላበስ የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም በዩኒቨርሲቲ የሚታዩ በዘርኝነት የሚከሰቱ መጠፋፋቶች ኋላ ቀር አስተሳሰብ በመሆናቸው ይህ ትውልድ መፍቀድ የለበትም ብለዋል።
ናዝሬት የቴክኒክ ኮሌጅ በሚል ከ20 ዓመታት በፊት የተቋቋመውና ከ14 ዓመታት በፊት ወደ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በልዩ የመግቢያ ፈተና ተማሪዎችን የሚቀበል ሲሆን፥ በየዓመቱ 5,000 የሚሆኑ ትምህርት ፈላጊዎች የመግቢያውን ልዩ ፈተና ቢፈተኑም ፈተናዉን አልፈው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለለማር ዕድሉን የሚያገኙት 1,500 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው ተገልጻል።
ዩኒቨርሲቲው የምርምር እና የጥናት የልህቀት ሥራዎችን የሚያካሂድበት 8 የልህቀት ማዕክላት (center of excellence) እንዳሉትና፤ በዩኒቨስቲው የሚገኘው ቤተ ሙከራ (laboratory) ለዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ተነግሯል።
ምሁራን በዘርፉ ላይ ምርምር እና ጥናት ሊያካሂዱበት የሚችል በዓይነቱ ለየት ያለ የምርምር ማዕከል (research center) በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየተገነባ እንደሚገኝም ተነግሯል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 26, 2019 at 6:07 pm #11762SemonegnaKeymasterሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለ25ኛ ጊዜ አስመረቀ
—–አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥኖ ሀምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም አስመረቀ። በያዝነዉ 2011 ዓ.ም ለ25ኛ ጊዜ በቀን እና ማታው መርሀ ግብር ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ወንዶች 177 ሴቶች 69 በድምሩ 246 ሰልጣኞች፤ እንዲሁም በአጫጭር ፕሮግራም ወንድ 480 ሴት 532 በድምሩ 1012፣ በአጠቃላይ ወንድ 657 ሴት 601 በድምሩ 1258 ሰልጣኞች ተመርቀዋል።
የሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ትምህርት በማቋረጣቸዉ እና የ10ኛ ክፍል ትምህርትን ባለማጠናቀቃቸዉ በመንግስት የተቀመጠዉን ዝቅተኛዉን መግቢያ መመዘኛ ማሟላት ባለመቻላቸዉ በመደበኛ ስልጠና ፕሮግራም መግባት ለማይችሉ አጫጭር ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበርና ድጋፍ በማግኘት የሚሰጣቸዉ አጫጭር ስልጠናዎች አንዱ Save the Children እና SNV ከተባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሴቶችና የወጣቶች የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ላይ ያተኮረ Livelihood Improvement of Women and Youth/LI-WAY/ የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረፅ በልብስ ስፌት፣ ምግብ ዝግጅት እና በተለያዩ የቴክኒክ እና ሙያ የስልጠና ዘርፍ ያሰለጠናቸዉን የመጀመሪያ ዙር አስመርቋል።
በምርቃቱ መርሀ ግብር ላይ የፌደራል ቴክኒክ ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸዉ ነጋሽ፣ የጃፓን አምባሳደር በኢትዮጵያ ሚስተር ዳይሱኬ ማትሱናጋ (Daisuke Matsunaga)፣ የሰላም ሕፃናት መንደር መሥራች ወ/ሮ ፀሀይ ሮሽሊ (Tsehay Röschli)፣ ከሰላም ጋር የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ የሰላም ቦርድ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።
በዕለቱ የማነቃቂያ ንግግር በአቶ ደምረዉ መታፈሪያ የተደረገ ሲሆን በመርሀ ግብሩ የተለያዩ የሰላም የአጋር ድርጅቶች ንግግር አድርገዋል። በተጨማሪም በስልጠናዉ ዘርፍ የላቀ ዉጤት ላስመዘገቡ ሰልጣኞች እና አሰልጣኞች ሽልማት ተሰጥቷል። በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ የፎቶ ፕሮግራም እና ችግኝ በመትከል ፕሮግራሙ ተጠናቋል።
ምንጭ፦ ሰላም የሕፃናት መንደር
July 26, 2020 at 1:36 am #15191SemonegnaKeymasterአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።
ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
August 1, 2020 at 1:38 am #15243SemonegnaKeymasterደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ፤ ለመጪው የትምህርት ዘመን የቅድመ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።
ደብረ ብርሀን (ኢዜአ/ሰሞነኛ) – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በ2ኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 61 ተማሪዎች ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ አንዳርጌ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በትምህርት ዘርፉ ላይ በርካታ እንቅፋቶች አጋጥመዋል። የመማር ማስተማሩ እንዲቋረጥ በመደረጉም ተማሪዎችን አቅም በፈቀደ መንገድ በቴክኖሎጂ ለማገዝ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይም የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቴክኖሎጂ እንዲከታተሉ በማድረግ ለምረቃ ቀናቸው ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ያስመረቃቸው ተማሪዎችም በቀን፣ በማታ እና በሳምንታዊ የትምህርት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ተከታትለው ማጠናቀቅ የቻሉ መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹ በጤና፣ በግብርና እና ተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ቀመር እና የቢዝነስ የትምህርት መስክን ጨምሮ በ21 የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከልም 52ቱ ሴቶች መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ አስታውቀዋል።
አሁን ላይ ሀገሪቱ የተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች ውስጥ መሆኗን አመልክተው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ ከገጠማት ችግር ፈጥና እንድትወጣ በቆይታቸው ወቅት ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዶ/ር ደረጀ አሳስበዋል።
በአካውንቲንግና ፋይናስ የትምህርት ዘርፍ 3.91 በማምጣት የተመረቁት አቶ ገብረሀና ደበበ በበሰጡት አስተያየት በተመረቁበት ዘርፍ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በእናቶች እና ሕፃናት ጤና የተመረቁት ወ/ሮ ዘነቡ አጎናፍር በበኩላቸው፥ ሕብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።
ሐምሌ 21 ቀን በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት በኮሮና ቨይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተወካይ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት ብቻ ተገኝተው የምረቃ መረሐ ግብሩን ተከታትለዋል።
ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ ዩኒቨርሲቲው ለ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል።
የ2013 ዓ.ም. የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀርቦ ነበር። በፕሬዝዳንቱ የቀረበው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በ5 ዋና ዋና ዘርፎች ተከፍለዋል። በአስተዳደር፣ በፕ/ጽ/ቤት፣ በአካዳሚክ፣ በጥናትና ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት እና በቢዝነስና ልማት ዘርፍ የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን በጥልቀት የመረመረ እቅድ እንደነበረ ለማየት ተችሏል።
ዶ/ር ንጉስ ታደሰ እንዳቀረቡት፥ በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ዝርዝር እና የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳን አስቀምጠዋል። የቀጣይ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮች ተለይተው ጥናት ተካሂዷል ብለዋል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ያለው የግንባታ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱና እያለቁ መሆናቸውንም ዶ/ር ንጉስ ገልጸዋል።
በዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ላይ መከናወን አለባቸው ከተባሉት ዋና ዋና ተግባራት መካከል፥ ለሀኪም ግዛው መታሰቢያ ሆስፒታልና ለአዲሱ ማስተማሪያ ካምፓስ የውስጥ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲ (applied university) ደረጃን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል (center of excellence) የሚያዘጋጅ ቡድን ማዋቀርና ወደ ሥራ ማስገባት፤ የምኒልክ የቴክኖሎጂ ካምፓስን የዲዛይን፣ የካሳ ክፍያና ሌሎች ሥራዎች መሥራት፣ የአካዳሚክ አመራሩን መገምገምና ጊዜያቸው ያጠናቀቁ አመራሮች በአዲስ መተካት፣ የተጀመሩትን የጥናትና ምርምር ሥራ ማስቀጠል፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተዘጋጀውን የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ በቁሳቁስና በሰው ኃይል ማሟላት እና በ2013 ዓ.ም ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት ማድረግና የተስተጓጎለውን ትምህርት በአጭር ጊዜ ለማካካስ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
በመቀጠልም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በዕቅዱ ላይ ቢካተቱ ያሏቸውን ሀሳቦችና ትኩረት የሚያሻቸውን ነጥቦች ላይ ሀሳብና አስተያየት ሰጥተዋል።
የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው፥ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዙ ምርምሮች እየተካሄዱ እንደሆነና የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርን ለ3ኛ ጊዜ ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቀድሞ ይከናወኑ የነበሩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።
የአስተዳርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ አጅቤ እንዳሉት፥ በዝግጅት ምዕራፍ እቅድ በየሥራ ዘርፉ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ተግባራትን እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ተወያይቶ ለተግባራዊነቱ እንዲሰራ ሁሉም አመራር የሚጠበቅበትን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ምንጮች፦ ኢዜአ/ ዩኒቨርሲቲው
August 9, 2020 at 1:39 am #15349AnonymousInactiveወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎችን አስመረቀ
ደሴ (ኢዜአ/ወ.ዩ.) – ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.) በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ (Masters program) ያሰለጠናቸውን 350 ወንድ 69 ሴት በድምሩ 419 ተማሪዎችን ነሐሴ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ተማሪዎቹ ባሉበት ቦታ በኦንላይን (online) አስመረቀ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ቢያስመርቁም ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በወቅታዊ የወረርሽኝ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሥራ ቢቋረጥም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ተማሪዎችን በማስተማር የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ መደረጉን አስታውቀዋል።
ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታ እና ሳምንታዊ መረሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን አመልክተው ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁት መካከል 69 ሴቶች እንደሚገኙበት ዶ/ር አባተ ገልጸዋል።
ዶ/ር አባተ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ዓለም በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በተናወጠበት እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተከሄደበት ዓመት መመረቃቸው ታሪካዊና ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። አያይዘውም፥ ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ዕቅዱን በአዲስ መልክ በማዋቀር ሀገር-በቀል እውቀቶችን ከምርምር ጋር በማቀናጀት ለውጥ በሚያስመዘግብ መልኩ ለመሥራት የተዘጋጀ በመሆኑ፥ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በሚሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምረው አዳዲስ ምርምሮችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመሥራት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።
ተመራቂዎች በትምህርት ቆታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ ዶ/ር አባተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 2 ቀን ያስመረቃቸው ተማሪዎች 12ኛ ዙር ሲሆኑ፥ በሕግ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ቢዝነስ እና ምህንድስና የሰለጠኑ ናቸው።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ምሩቃን በቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት በታማኝነት እኩል ሕብረተሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ የአንድነትና የሰላም እሴት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍም በእውቀት ላይ የተመሠረተ እገዛ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ አበበ አመልክተዋል።
ከተመራቂዎች መካከል መላኩ በላይ በሰጠው አስተያየት ምንም እንኳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በትምህርቱ ዘርፍ ጫና ቢያሳድርም፥ በቴክኖሎጂ ታግዘው በዕለቱ ለመመረቅ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በተማረበት ሕክምና እና ጤና ሳይንስም ሕብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ጠቁሞ፥ “በተለይ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻዬን እወጣለሁ” በማለት አክሏል።
ሌላዋ የፕሮጀክት አመራር (project management) ተመራቂ ገነት ኪሮስ በበኩሏ፥ በሙያዋ ሕዝቡን በማገልገል የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግራለች። ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን የሚያስጨንቅበት ቢሆንም በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ታግዛ ለዚህ በመብቃቷ መደሰቷን ገልጻለች።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.)
August 24, 2020 at 3:36 am #15543AnonymousInactiveድሬዳዋ፣ መዳ ወላቡ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ከ460 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች በድኅረ ምረቃና በቅድመ መደበኛ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 118 ተማሪዎች አስመረቀ። ከተመራቂዎች መካከል 56ቱ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ሲሆኑ፥ 23 ተማሪዎች ደግሞ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሰለጠኑ የሕክምና ዶክተሮች እንዲሁም በቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት 39 ተማሪዎች በኪነ ህንፃ በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸው ናቸው።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ ተመራቂዎች ሃገራችን በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ውስጥ ሆና የተመረቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተለይም የሕክምና ተመራቂዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በተጀመረው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሌሎችም በተመረቁበት ሙያ የሀገሪቱን እድገት በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት በመሰማራት በ2012 በጀት ዓመት 38 የምርምር ሥራዎች ፀድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውንና ሃያ ሰባቱ መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተያያዘ፥ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል ያለበትን የግንባታ ደረጃና የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በዩኒቨርስቲው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችንና የSTEM ማዕከሉን ጎብኝተዋል።
ከተማሪዎች ምረቃ ዜና ሳንወጣ፥ መዳ ወላቡ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 345 ተማሪዎች ነሐሴ 16 ቀን 2012 አስመርቀዋል።
የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አህመድ ከሊል በምረቃው ሥነ-ሥርዓት እንደተናገሩት፥ ተቋሙ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ቢያስመርቅም ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። ሆኖም እንደ “ኦንላይን” ያሉ የተለያዩ አማራጭ በመጠቀም ምሩቃን ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን እንዲያሟሉ ማድረጉንም ገልጸዋል።
መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በዕለቱ በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያስመረቃቸው 208 ተማሪዎች አምስተኛው ዙር ሲሆኑ፥ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ ቋንቋና ሥነ ጽሁፍ፣ ሕክምናና ጤና ሳይንስ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ቢዝነስና ምህንድስና የተማሩ ናቸው።
ዶክተር አህመድ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ግንዛቤ ከማስጨበጡ በተጓዳኝ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የመደገፍና ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉና ኮሮናን በመከላከሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከተመራቂዎች መካከል መሐመድ አህመድ በሰጠው አስተያየት፥ ኮሮና ቫይረስ በትምህርቱ ዘርፍ ጫና ቢያሳድርም በቴክኖሎጂ ታግዘው ለምርቃት በመብቃቱ መደሰቱን ገልጾ፥ በሰለጠነበት ሙያ ሕብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። ሌላው የእለቱ ተመራቂ ጣህር መሐመድ በበኩሉ በሙያው ሕዝቡን በማገልገል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጿል።
በ1999 ዓ.ም 742 ተማሪዎች ተቀብሎ ሥራ የጀመረው መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ ከ24ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች እንዳሉት ተመልክቷል።
በተመሳሳይ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ ርቀትና ተከታታይ የትምህርት መረሃ ግብር ያሰለጠናቸው 137 ተማሪዎች አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አደም ቦሪ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት እንደገለጹት፥ ያስመረቋቸው ተማሪዎች ኮሮና ቫይረስ ጫና ቢፈጥርባቸውም አማራጭ የመገናኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው።
ከተመራቂዎቹ መካከል 107 ተማሪዎች በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሰለጠኑ ሲሆኑ፥ ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ መደበኛ፣ ርቀትና ተከታታይ ትምህርት የተከታተሉ መሆኑ ተመልክቷል።
ተመራቂዎች ወደ ሥራ ሲገቡ በሰለጠኑበት ሙያ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በቅንነትና ፍትሃዊነት ማገልገል እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር አደም ቦሪ አሳስበዋል።
ከተመራቂዎች መካከል በሁለተኛ ዲግሪ አካውንቲንግና ፋይናንስ የትምህርት መስክ አራት ነጥብ በማምጣት የተመረቀው መሃመድ አሊ በሰጠው አስተያየት፥ ከ17 ዓመታት በኋላ ወደ ትምህርት ተመልሶ የቤተሰብ ኃላፊነትና የሥራ ጫና ተቋቁሞ ለዚህ ውጤት በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በቀጣይም እራሱን የበለጠ በማብቃት በተሰማራበት ሙያ በቅንነትና በትጋት ሀገሩን ለማገልገል እንደሚሠራ ተናግሯል።
August 30, 2020 at 12:33 am #15626SemonegnaKeymasterባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 7520 ተማሪዎች በበይነ-መረብ አስመረቀ
(ባሕር ዳር) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምርቃ መርሀ-ግብር በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛውና በተከታታይ መርሀ-ግብር 2254 ተማሪዎች፣ በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ-ግብር 40 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲ መርሀ-ግብር 41 ተማሪዎች፣ በምስክር ወረቀት መርሀ-ግብር 642 ተማሪዎች በድምሩ 7520 ተማሪዎችን በበይነ-መረብ በመታገዝ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። ከተመራቂ ተማሪዎቸ መካከል 2345 ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል አምስቱ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ፣ እንዲሁም የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክዕት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ዓለምን ባስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ ተግዳሮት ሳይደናቀፉ የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ለተመረቁ ተማሪዎች አድናቆታቸውን ገልፀው ወደ ቀደምት ትልቅነታችን እና ጥበብ ለመመለስ እና አሁን የጀመርናቸውን የአባይ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት የጋራ መድኃኒት ስለሚያስፈልገን ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም በጋራ መሥራት እንደሚገባን አሳስበዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን (ኮቪድ-19) ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዩኒቨርስቲዎች ሕይወትን ለመታደግ የእውቀት እና የሕዝብ ተቋምነታቸውን ማስመስከራቸውን ጠቅሰው ለዚህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በማምረት እና በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን በማበርከት ሕበረተሰቡን ከወረርሽኙ እየታደገ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ገልፀዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከትምህርት እንዳይለዩ በዩኒቨርሲቲው የICT ባለሙያዎች የበለፀገ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት (learning management system) ለአማራ ክልለዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ማበርከቱን አውስተዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንዳሉት መማር ትርጉም የሚኖረው የሕበረሰተቡን ኑሮ ማሻሻልና ለችግሮቹ መፍቻ የሚሆን አዳዲስ አሠራሮችንና ሀሳቦችን መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቁመው የሀገራችን ችግር የሚፈታው የችግሮችን ስፋትና ጥልቀት በሚረዱ ምሁራን በመሆኑ የምንግዜም ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አክለውም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የልሕቀት ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ትጋት አድንቀው፤ በእምቦጭ ዙሪያ ብዙ ሥራ መሥራት የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። ከአባይ ፏፏቴ ጀምሮ እስከ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ድረስ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግ የሚቻልበትን ምርምር በመሥራት መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማሳየትም ከዩኒቨርሲቲው እንደሚጠበቅ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል።
የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን ጥቂት ተማሪዎች አዳራሽ ውስጥ በአካል በመገኘት፥ አብዛኛዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው በአማራ ቴሌቪዥን ከጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቀጥታ ስርጭት፣ በፌስቡክ (Facebook) እና ዩቲዩብ (YouTube) የተላለፈውን ታድመዋል።
ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
August 30, 2020 at 1:16 am #15632AnonymousInactiveሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4,700 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ
ሐዋሳ (ኢዜአ/HU) – ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በበይነ-መረብ (virtual) ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ ያስቻለቸውን የድኅረ ምረቃ (ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ) ተማሪዎች እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በፊት በእንስሳት ሕክምና እና በሌሎች መርሀ-ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ 4,780 ተማሪዎችን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው ለ21ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው መካከል 2,866 በመጀመሪያ፣ 1,900 በሁለተኛ እና 12 ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ገልጸዋል።
ተማሪቂዎችና ቤተሰቦቻቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ምክንያት የተፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ወረርሽኙን ከመከላከሉ ሥራ በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እና የመንግሥትን የልማት እንቅስቃሴ በጥናት ለመደገፍ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን እየተከላከሉ መደበኛ የትምህርት ሥራቸውን ለመጀመር እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር አያኖ በአዲሱ ፍኖተ-ካርታ መሠረት የምርምር ዩኒቨርሲቲ (Research University) ለመሆን ከሚጠበቁት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቀዳሚነት ለማሰለፍ በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር በማዋል የሀገሪቱን ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ተቋሙ በተደራረበ ጫና ውስጥ እያለ ተማሪዎችን ማስመረቁ፥ ምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን አጠናክሮ መቀጠሉ የአመራሩንና የሠራተኞችን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በእንስሳት ሕክምና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተመረቀው ዶ/ር ግርማ በዳዳ በሰጠው አስተያየት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ጫና በመቋቋምና ጥናቱ ላይ በመትጋት ለምርቃ መብቃቱን ተናግሯል። ለዚህም ዩኒቨርሲቲውን አመሰግኗል።
ሌላዋ በሶሻል ሣይኮሎጂ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ ማርታ ማጋ በበኩሏ፥ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርት ማጠናቀቃቸውን ጠቅሳ፤ የምርምር ሥራዋን ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በማካሄድ ለመመረቅ እንደበቃች ገልጻለች።
ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት መርሀ-ግብር የሚያስተምራቸው ከ43,000 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ ከ7,000 በላይ ሠራተኞች (staff)፣ ሰባት ካምፓሶች፣ ስምንት ኮሌጆችና ሁለት ተቋማት (institutes)፣ እና ከ200 በላይ የትምህርት መርሀ ግብራት (programs) እንዳሉት ድረ-ገጹ ያሳያል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ዩኒቨርሲቲው (HU)
August 30, 2020 at 2:29 am #15637SemonegnaKeymasterዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የመደበኛ እና የተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብር የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎቹን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። የክብር እንግዳና አስመራቂ በመሆን በቪዲዮ ኮንፍረንስ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎች ያስተላለፉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤ ክፍሌ፥ ተመራቂዎች ሀገራቸዉን ከድህነትና ኋላ-ቀርነት ለማላቀቅ በያዙት ሙያ ጠንክረዉ በመሥራት የበኩላቸዉን እንዲወጡ ጥሪያቸዉን በማስተላለፍ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸዉ አስተላልፈዋል ።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ጋር ተያይዞ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሠረት፥ በበይነ-መረብ (online) አማካኝነት በማስተማር የድኅረ-ምረቃ ትምህርታቸዉን ሲከታተሉ ከነበሩ ከ45 ተማሪዎች ዉስጥ 38 ተመራቂዎች በኤሌክትሪካል ፓወር ኢንጂነሪንግ (electric power engineering)፣ በሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ (public health)፣ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን (business administration)፣ በአካዉንቲንግ እና ፋይናንስ( accounting and finance) በዩኒቨርሲቲዉ ሴኔት ሌጅስሌሽን መሠረት የድኅረ ምረቃ መስፈርቱን ስላሟሉ መመረቃቸዉን የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ በይፋ በማስታወቅ፤ ተመራቂዎች በተማሩበት መስክ የሰዎች ልጆችን ክብር ጠብቀዉ ሀገራቸዉን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል ።
ፕሬዝዳንቱ አክለዉም ተመራቂዎች ወደ ብልጽግና ሀገሪቱን ለሚያሸጋግሩት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ለልዩ ልዩ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ በማስተላለፍ በራሳቸዉ እና በዩኒቨርሲቲዉ ማሕበረሰብ ስም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎች እና ለቤተሰቦቻቸዉ አስተላልፈዋል ።
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናዉ ካዉዛ፣፥ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ እና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እና የዩኒቨርሲቲዉ የማኔጅመንትና የሴኔት አባላት የምረቃዉን ሥነ-ሥርዓት መታደማቸዉም ተመልክቷል።
በዕለቱ ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ተሾመ ሊሬ በሰጠው አስተያየት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሀገሪቱ መከፋፈልን የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በመተው፥ በአንድነት ለእድገት መሰለፍ እንደሚባ አመልክቶ በሰለጠነበት ሙያ ሀገሩን ለማገልገል እንደሚጥርም ተናግሯል።
በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ያለው ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (business administration) ሙያ የተመረቀው መስቀሉ ዳራ ነው። በሰለጠነበት ሙያ ራሱን፣ ብሎም ቤተሰቡንና ሀገሩን በመገልገል የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።
ከተማሪዎች ምርቃት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች እና የዲግሪ መርሀ-ግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች በዚሁ ዕለት (ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም) በበይነ-መረብ (virtual) አስመርቋል። በዕለቱ በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor)፣ በሁለተኛ ዲግሪ (master) እና በሦስተኛ ዲግሪ (doctorate) እና ስፔሻሊቲ ዲግሪ (specialty degree) ትምህርታቸውን ተከታትለው ያሰመረቃቸው ተማሪዎች ቁጠር በአጠቃላይ 4,290 እንደሆነ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት ያገኘንው መረጃ ያመለክታል። በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ናቸው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.