Search Results for 'ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 21 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬታቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ

    ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያ (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 16 ቀን፥ 2015 ዓ.ም ባካሄደው የተማሪዎች ምረቃ ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል። በዕለቱ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በሥራ መደራረብ ምክንያት በምረቃ ዕለቱ ተገኝተው ባለመቀበላቸው፥ ኅዳር16 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል።

    በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመጀመሪያዋ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ናት።

    የክብር ዶክተር መዓዛ ብሩን ለክብር ዶክትሬት ሽልማት ያበቋቸው ሥራዎች በዝርዝር:-

    • በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ (ሸገር ኤፍ ኤም 1) መሥራች እና ባለቤት፤
    • የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ማሰራጫ ድርጅት መሥራችና ባለቤት፤
    • በእንግዶች ምርጫዋ፤ በምርምር በተደገፈ የመጠይቅ ዘይቤዋ፣ በትህትናዋ፣ በአነጋገር ለዛዋ በቀጥታ አዘጋጅታ ከምታቀርባቸው መርሃ ግብሮች (የቅዳሜ ጨዋታ እና ሸገር ካፌ) በተጭማሪ በተለያዩ የሸገር ሬዲዮ መርሃ ግብሮች እንዲሁም በሌሎች ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን መርሃ ግብሮች ላይ አሻራ የተወች እና ባጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች አርአያ የሆነች፤

    ምናልባት ከሁሉ በላይ ታዋቂ የሆነችበትና አምሳያ የሌለው የላቀ አስተዋፅኦ ተብሎ ሊወሰድ ከሚችሉት ሥራዎቿ ውስጥ አንዱ፥ በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸውን በርካታ ባለታሪክ ምሁራን፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፤ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይውት ታሪክ፣ ሥራ፣ አስተሳሰብ እና ለሌሎች አርአያ የሚሆነውን የሕይወት ፍልስፍናቸው በራሳቸው አንደበት ተሰናድቶ ለታሪክ እንዲቆይ ማድረጓ ነው። በዚህም ለኢትዮጵያውያን በዓይነቱ ተወዳዳሪ የሌለውና ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የሚሄድ የታሪክ የድምጽ መዘክር አበርክታለች ማለት ይቻላል። የጨዋታ እንግዳ መሰናዶ እንግዶቿ ያካበቱት ልምድ፤ አበርክቶታቸው፤ ያልተጻፉ ሃገራዊ ጉዳዮች እና ሚስጥሮች ከኃላፊ ባለታሪኮቹ ጋር እንዳያልፉ፤ በመቅረጸ-ድምጽ ተሰንቀው በሰፊው እንዲታወቁ እና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ አድርጋለች። በእርግጥም ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ከየተደበቁበት ፈልጋ ቃለ መጠይቅ ካደረገቻቸው ጉምቱ እንግዶች መካከል ጥቂት የማይባሉት አሁን በመሃከላችን አይገኙም፤ ታሪካቸው ግን ህያው ሆኗል።

    ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የተወለደች ሲሆን፥ ዘጠኝ ዓመት ገደማ እስኪሆናት በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው ሂርና ከተማ አደገች። ሂርና ሳለች ጎረቤቶቿ የኦሮሞ፣ የሃረሪና የሶማሌ እንዲሁም የየመን ተወላጆች ስለነበሩ በተለያዩ ባሕላዊ ዕሴቶች እና እርስ በእርስ ትስስር የዳበረ አስተዳደግ ነበራት። ይህም ለሥነ-ጽሁፍ ከነበራት ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ ለዛሬው ማንነቷ መሠረት ሆኗታል።

    • ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ወላጆቿ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የቅድስተ ማርያም የልጃገረዶች ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት አሰገቧት።
    • 1967 ዓ.ም. የሁለትኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች በእድገት በሕብረት ዘመቻ ወደ ውቅሮ፥ ትግራይ ተልካ ለስድስት ወራት አገልግላለች።
    • በ1970 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች።
    • ከሬዲዮ ሥራ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለች በአጋጣሚ ሲሆን፥ በወቅቱ ተወዳጅ ከነበረው የእሁድ ፕሮግራም ጋር ለነበራት ለስምንት ዓመታት ያክል የቆየ ትስስር ምክንያት ሆኖታል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ በቋሚነት የተመደበችበት ሥራዋ በባህል ሚኒስቴር ስር የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢነት ነበር።
    • በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ተሳትፎዋን ሳታቆም በባህል ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ አግልግሎት ክፍል አገልግላለች።
    • ከዚያም በብሔራዊ ባንክ የብሪቱ መጽሄት ዋና አዘጋጅ በመሆን የፋይናንስ ዜናዎችን እና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ እና በአርትኦት አገልግላለች።
    • በ1984 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅላ የፕሬስ እና ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር በመሆን ለአራት ዓመታት ሠርታለች።
    • ከዚያም በግል በአማካሪነት እና በሕዝብ ግንኙነት እና ማስታወቂያ ስትሠራ ከቆየች በኋላ፤ በ1987 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ1 የሬዲዮ ጣቢያን የአየር ሰዓት በመጠቀም የቅዳሜ ከሰዓት የጨዋታ መርሀ ግብርን ከባለቤቷ ከአርቲስት አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዋ አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ጋር የማዘጋጀት ዕድል አግኝታ መርሀ ግብሩን ለስምንት ዓመታት ያክል ስታቀርብ ቆይታለች።
    • በመጨረሻም በ2000 ዓ.ም. አንጋፋና ተወዳጅ የሆነውን ሸገር ኤፍ ኤም1ን እዉን ለማድረግ በቅታለች።

    በአጠቃላይ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የጥንካሬ ተምሳሌትና በዘርፉ ለበርካቶች አርአያ ለመሆኗ ተገቢ ዕውቅና ይሆን ዘንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152 / 2011 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በአርት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት እንዲሰጣቸው ወስኗል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን አስረከበ

    ባሕር ዳር – የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ነሐሴ 21 ቀን፥ 2014 ዓ.ም የተማሪዎችን ምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በማኅበረሰብ አገልግሎት ጉልህ አስተዋፅዖ ላበረከቱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ) የሰሜን ወሎ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለሆኑት ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማት ለተወካያቸው መስጠቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን ብፁዕ አባታችን በአሁኑ ሰዓት የሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን ጨርሰው በመመለሳቸው መስከረም14 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ሕንፃ ተገኝተው የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

    የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የዕለቱ የክብር እንግዳ በሆኑት በብፁዕ አቡነ አብርሃም ፀሎትና ቡራኬ ተጀምሯል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት በጭንቅ እና በመከራ ወቅት ሀይማኖትና ዘር ሳይለዩ የከበረ ሥራን ሠርተው የከበሩትን ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በማክበራችን እኛም ብዙ አትርፈናል ሲሉ ተናግረዋል። በወቅቱ አቅም ያላቸው በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው በሚሸሹበት ወቅት በጦርነት፣ በችግር እና መከራ ውስጥ ወደ ሚገኘው ሕዝባቸው ጋር በመሄድ የመከራው ቀንበር እንዳይሰማቸው ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመጣውን ክፉ ቀን እንዲያልፍ በማድረጋቸው ታሪክ የማይረሳው ሥራን ሠርተዋል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

    የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ እንዲሁም ዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀይማኖት፣ ዘር እና ቀለም ሳይለይ በሥራቸው ብቻ መዝኖ ለብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የክብር ዶክትሬት በመስጠቱ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ስም ምስጋና አቅርበዋል። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በዚያ ሽብር እና ጭንቅ በነገሰበት ወቅት ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ አማኝ እና ኢ-አማኝ ሳይሉ ሁሉንም የሰው ዘር በእኩል ዓይን በማየት የመከራውን ቀን ከሕዝባቸው ጋር ያሳለፉትን ድንቅ አባት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዕውቅና ሽልማት በመስጠቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መደሰቷን ተናግረዋል።

    አቡነ ኤርምያስ በበኩላቸው የተሰጠኝ የክብር ዶክትሬት ለእኔ ሳይሆን በሁለቱም ወገን በጦርነቱ ወቅት ቆስለው በየጫካው የወደቁ ወገኖችን ቁስል በማጠብ እና ከልጆቻቸው ጉሮሮ ቀንሰው ለቁስለኞች በማብላት ትልቅ ፍቅር ላሳዩን እናቶች እና በጸሎት ሲጠብቁኝ ለነበሩት ለብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ከጎኔ ሆነው በምክር ለረዱኝ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሀዋርያዊ ተልዕኮ ዘወትር ለሚፋጠኑት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ድልድይ ሆነው ላገናኙኝ የመስጊድ ኮሚቴ አባላት፣ ሰብዓዊ ግዴታቸውን ለተወጡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ወሎ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚዳንቶች መምህራን እና ሠራተኞች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    አቡነ ኤርምያስ

    Anonymous
    Inactive

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 5117 ተማሪዎች አስመረቀ

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ)– ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መመረቅ የነበረባቸው እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ የዘገዩ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ 4203፣ በሁለተኛ ዲግሪ 759፣ በሦስተኛ ዲግሪ 10፣ በስፔሻሊቲ 40፣ በፒጂዲቲ ቅድመ ምረቃ (post graduate diploma in teaching/PGDT) 105፤ በአጠቃላይ 1623 ሴት፣ 3494 ወንድ ተማሪዎችን፥ በድምሩ 5117 ተማሪዎችን ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በክብር እንግድነት በተገኙበት አስመርቋል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ “የዘንድሮ ተማራቂዎችን እንደተማሪ በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ለዛሬው ቀን በመብቃታቸው ‘ከመወርቅ’ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግሮች በመከራ ጊዜ እንደ ወርቅ ነጥራችሁ በመውጣታችሁና ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል። ዶ/ር ፍሬው አክለወም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆንና በሀገራችን ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግምባር ቀደም እንዲሆን ላገዙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ ላሉ የወጣት አደረጃጀቶችና ለሌሎች አጋር ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተመራቂዎች ዓለምን እየፈተነ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፈው መመረቅ መቻላቸው ታሪካዊ ተመራቂዎች መሆናቸውን አውስተው፤ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገርና ቤተሰብ የጣለባቸውን አደራ በአግባቡ እንዲወጡ፣ በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ጠንክረው በመሥራት ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ‘ሀገሬ ምን አደረገችልኝ?’ ሳይሆን ‘ለሀገሬ ምን አደረኩላት?’ ብሎ ራስን መጠየቅ እና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ጥልቅ ዕውቀት ተጠቅመው በኮሮናቫይረስ ወረርሽ የቀዘቀዘውን ኢኮኖሚ እንዲሻሻል በማገዝ በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላችውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለባሕር ዳር ከተማ ብሎም ለክልሉ እንደ ዓይን ብሌን የሚታይ ግዙፍ የዕውቀት ማዕከል መሆኑንም ተናግረዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በመመረቂያ ፕሮጀክቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት እና የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የወርቅ ዋንጫ ተሸልመዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨረሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ፣ የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተር እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

    የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ባማረው እና በተዋበው የዩኒቨርሲቲው ስታዲየም በፖሊስ ማርሽ ባንድ በቀረበ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መዝሙር እና በሙሉ ዓለም የባህል የሙዚቃ ባንድ በቀረቡ የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜዎች እና ዘመናዊ ሙዚቃዎች በመታጀብ ደምቆ ውሏል።

    ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 5117 ተማሪዎች አስመረቀ

    Anonymous
    Inactive

    ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

    ባህር ዳር (ሰሞነኛ)– የባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹን የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በማድረግ በሙሉ ድምፅ ሹሟል።

    በባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት በከተማው የተቀዳሚ ከንቲባነት የተሾሙት ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በምድረ ፅፍ እና አካባቢ ጥናት (geography and environmental study) ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፤ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአመራር እና መልካም አስተዳደር (leadership and good governance) ከኢትዮጵያ ሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በመቀጠልም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሥራ አመራር (management)  ቻይና ከሚገኘው ኋጆንግ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂያገኙ ዩኒቨርሲቲ (Huazhong University of Science and Technology) ሲሆን፥ ሁሉንም የትምህርት ደረጃዎች በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ናቸው።

    ዶክተር ድረስ ሣህሉ የአማራን ሕዝብና መንግሥት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ባሉ የተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች በውጤታማነት እና በታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል በዞን ደረጃ የምዕራብ ጎጃምዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የዞኑ የሕዝብ ግንኙነትና የከተማ አደረጃጀት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል። በአጠቃላይ የዶክተር ድረስ ሣህሉ የሥራ ልምድ የሚከተለውን ይመስላል፦

    • በምስራቅ ጎጃም ዞን በደባይ ጥላት ግን እና በባሶ ሊበን ወረዳ የደን እርቻ ልማት (agro forestry) እና የመሬት አስተዳደር ባለሙያ በመሆን ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፤
    • በምስራቅ ጎጃም ዞን በባሶ ሊበን ወረዳ የአስተዳደር እና ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በአነደድ ወረዳ የግብርና ኃላፊ፣ የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የሕዝብ ተሳትፎና አደረጃጃት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በጃቢ ጠህናን ወረዳ የመሬት አስተዳደር ጽኅፈት ቤት ኃላፊና የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።
    • የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ፣ የሕዝብ ግንኙነትና የከተማ አደረጃት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፤
    • በአማራ ክልል የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

    ዘገባው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት እና የአማርኛ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ቤት ነው።

    ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ

    Anonymous
    Inactive

    በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ እየደረሰ ያለው የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት

    በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን እና ወንበራ በተባሉ ወረዳዎች ታጣቂዎች በሰላማዊ ሕዝቦች ላይ ጉዳት እያደረሱ አንደሆነ ነዋሪዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች አመለከቱ። የአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ኃላፊዎች በታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ይናገራሉ።

    በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን እና እና ወንበራ ወረዳዎች በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ሰሞኑን በወረዳዉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ሕብረተሰቡን ለሞት፣ ለስደት እና ለአካል ጉዳት እየዳረጉት እንደሆነ ነዋሪዎቹና ቤተሰቦቻቸው የተጎዱባቸው ግለሰቦች አመልክተዋል። ለሥራ በተንቀሳቀሱበት ባለፈው እሁድ (መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም.) ስድስት ዘመዶቻቸው እንደተገደባቸው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጓዋንጓ አካባቢ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል በስልክ ተናግረዋል። የግልገል በለስ ነዋሪ የሆኑና ለደህንነታቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ በበኩላቸው፥ “መተከል ዞን ውስጥ ቡለን እና ወንበራ አካባቢዎች የሚፈፀመው ጥቃት እጅግ ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ነው” ብለዋል፡፡

    ግጭቱ እንዲባባስ ከመንግሥት መዋቅሩ መረጃ የሚያደርስ አካል ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ለዚህም ምክንያታቸው ታጣቂው ኃይል ባለበት አካባቢ የፀጥታ ኃይሉ ሲንቀሳቀስ ቀድመው ከቦታው እንደሚሰወሩ አብራርተዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪና የአማራ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው “የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከክልሉ ውጪ ያሉ የአማራ ክልል ተወላጆችን መብት እያስጠበቀ አይደለም” ሲሉ ይከስሳሉ። የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ እንደገለፁት “ፀረ-ሰላም” ያሏቸውን አካላት ለመደምሰስና በቁጥጥር ስር ለማዋል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በጋራ እየተሠራ ነው።  ችግሩ የተፈጠረበትን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑን ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ለማነጋገር ብሞክርም “መረጃ በስልክ አንሰጥም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከባሕር ዳር ጋዜጠኛ ዓለምነው መኮንን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አነጋግሮ ተከታዩን ዘገባ ለዶይቼ ቬለ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ልኳል።

    በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን የተፈጠረው ምንድን ነው?

    ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ውስጥ ኤጳር በምትባል ቀበሌ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ‘ጸረ-ሰላም’ ያሏቸውኃይሎች (ታጣቂዎች) በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የአፈናና የግድያ ወንጀል ከመፈጸማቸው በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።

    ቢቢሲ በበኩሉ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጠይቆ እንደተረዳው፥ በተለያዩ ጊዜያት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሚፈጸመው ጥቃት የተነሳ የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በስጋት ውስጥ ሆነው እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። [ለምሳሌ ያህል፥ ሰኔ 2 ቀን 2011 ዓ.ም.  በክልሉ ዳንጉር ወረዳ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልሉ መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ከ30 ሰዎች በላይ መሞታቸውን የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲልን ጠቅሶ የቢቢሲ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍልዘግቦ ነበር።]

    በሚፈጸሙት ጥቃቶችም በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው መገደቡንና ክስተቱም ሁሉም በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረጉ በአካባቢዎቹ ባለው ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ ተናግረዋል።

    ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ የጤና እና ግብርና ባለሙያዎችን ለማፈን ከመሞከራቸውም በላይ፥ በመንግሥት መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ወደ ሌላ ወረዳ መሸሻቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

    እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ በወጣው መረጃ መሠረት የአካባቢው ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ ልዩ ኃይል በጋራ በመሆን ወደ ወረዳዎቹ በመግባት ጥቃቱን ለማስቆምና ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

    እንደ ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ገለጻ ከሆነ በወረዳዎቹ ጉዳት እያስከተለ ያለው ጥቃት የሚፈጸመው ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ባልፈለጉት “የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን አባላት” መሆኑንና በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስካሁን የታገቱ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በተመለከከተ “በቁጥር ደረጃ በዝርዝር አልተለየም” ያሉት ኮማንደር ነጋ፥ መረጃው ተሰባሰቦ ሲያልቅ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።

    ምክትል ኮሚሽነሩ በክልሉ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ ‘ጸረ-ሰላም’ ያሏቸው ኃይሎች ከውጪ ሀገር ጭምር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃ መገኘቱን ጠቅሰው፥ “ወጣቶችን ለመመልመል እንደሚንቀሳቀሱም” ጨምረው ተናግረዋል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከቀናት በፊል መልካን በሚባል ቀበሌ 30 ሰዎችን አፍነው የነበረ ሲሆን፥ አሁን እነሱን መልቀቃቸውን አመልክተው፤ የያዟቸውን ሰዎች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

    በተለያዩ ጊዜያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንነታቸው ያልተገጹ ቡድኖች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው ባሻገር በተደጋጋሚ ሰዎችን እያገቱ እንደሚወስዱ ሲዘገብ ቆይቷል። እየደረሰ ያለውን የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት፣ የሰውና የንብረት ጉዳት፣ እንዲሁም ተደጋጋሚ የስዎች መታገት ለማስቆም የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ከሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠርና ድርጊቱን ለማስቆም እየጣሩ መሆኑ ተገልጿል።

    ምንጮች፦ ዶይቼ ቬለ ራድዮ እና ቢቢሲ ራድዮ የአማርኛ ዝግጅት ክፍሎች

    ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን

    Semonegna
    Keymaster

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የመደበኛ እና የተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብር የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎቹን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። የክብር እንግዳና አስመራቂ በመሆን በቪዲዮ ኮንፍረንስ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎች ያስተላለፉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤ ክፍሌ፥ ተመራቂዎች ሀገራቸዉን ከድህነትና ኋላ-ቀርነት ለማላቀቅ በያዙት ሙያ ጠንክረዉ በመሥራት የበኩላቸዉን እንዲወጡ ጥሪያቸዉን በማስተላለፍ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸዉ አስተላልፈዋል ።

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ጋር ተያይዞ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሠረት፥  በበይነ-መረብ (online) አማካኝነት በማስተማር የድኅረ-ምረቃ ትምህርታቸዉን ሲከታተሉ ከነበሩ ከ45 ተማሪዎች ዉስጥ 38 ተመራቂዎች በኤሌክትሪካል ፓወር ኢንጂነሪንግ (electric power engineering)፣ በሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ (public health)፣ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን (business administration)፣ በአካዉንቲንግ እና ፋይናንስ( accounting and finance) በዩኒቨርሲቲዉ ሴኔት ሌጅስሌሽን መሠረት የድኅረ ምረቃ  መስፈርቱን ስላሟሉ መመረቃቸዉን የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ በይፋ በማስታወቅ፤ ተመራቂዎች በተማሩበት መስክ የሰዎች ልጆችን ክብር ጠብቀዉ ሀገራቸዉን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል ።

    ፕሬዝዳንቱ አክለዉም ተመራቂዎች ወደ ብልጽግና ሀገሪቱን ለሚያሸጋግሩት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ለልዩ ልዩ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ በማስተላለፍ በራሳቸዉ እና በዩኒቨርሲቲዉ ማሕበረሰብ ስም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎች እና ለቤተሰቦቻቸዉ አስተላልፈዋል ።

    የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናዉ ካዉዛ፣፥ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ እና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እና የዩኒቨርሲቲዉ የማኔጅመንትና የሴኔት አባላት የምረቃዉን ሥነ-ሥርዓት መታደማቸዉም ተመልክቷል።

    በዕለቱ ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ተሾመ ሊሬ በሰጠው አስተያየት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሀገሪቱ መከፋፈልን የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በመተው፥ በአንድነት ለእድገት መሰለፍ እንደሚባ አመልክቶ በሰለጠነበት ሙያ ሀገሩን ለማገልገል እንደሚጥርም ተናግሯል።

    በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ያለው ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (business administration) ሙያ የተመረቀው መስቀሉ ዳራ ነው። በሰለጠነበት ሙያ ራሱን፣ ብሎም ቤተሰቡንና ሀገሩን በመገልገል የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

    ከተማሪዎች ምርቃት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች እና የዲግሪ መርሀ-ግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች በዚሁ ዕለት (ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም) በበይነ-መረብ (virtual) አስመርቋል። በዕለቱ በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor)፣ በሁለተኛ ዲግሪ (master) እና በሦስተኛ ዲግሪ (doctorate) እና ስፔሻሊቲ ዲግሪ (specialty degree) ትምህርታቸውን ተከታትለው ያሰመረቃቸው ተማሪዎች ቁጠር በአጠቃላይ 4,290 እንደሆነ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት ያገኘንው መረጃ ያመለክታል። በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ናቸው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4,700 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ

    ሐዋሳ (ኢዜአ/HU) – ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በበይነ-መረብ (virtual) ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ ያስቻለቸውን የድኅረ ምረቃ (ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ) ተማሪዎች እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በፊት በእንስሳት ሕክምና እና በሌሎች መርሀ-ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ 4,780 ተማሪዎችን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ።

    ዩኒቨርሲቲው ለ21ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው መካከል 2,866 በመጀመሪያ፣ 1,900 በሁለተኛ እና 12 ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ገልጸዋል።

    ተማሪቂዎችና ቤተሰቦቻቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ምክንያት የተፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ወረርሽኙን ከመከላከሉ ሥራ በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እና የመንግሥትን የልማት እንቅስቃሴ በጥናት ለመደገፍ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን እየተከላከሉ መደበኛ የትምህርት ሥራቸውን ለመጀመር እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።

    ዶ/ር አያኖ በአዲሱ ፍኖተ-ካርታ መሠረት የምርምር ዩኒቨርሲቲ (Research University) ለመሆን ከሚጠበቁት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቀዳሚነት ለማሰለፍ በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር በማዋል የሀገሪቱን ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ተቋሙ በተደራረበ ጫና ውስጥ እያለ ተማሪዎችን ማስመረቁ፥ ምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን አጠናክሮ መቀጠሉ የአመራሩንና የሠራተኞችን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

    በእንስሳት ሕክምና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተመረቀው ዶ/ር ግርማ በዳዳ በሰጠው አስተያየት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ጫና በመቋቋምና ጥናቱ ላይ በመትጋት ለምርቃ መብቃቱን ተናግሯል። ለዚህም ዩኒቨርሲቲውን አመሰግኗል።

    ሌላዋ በሶሻል ሣይኮሎጂ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ ማርታ ማጋ በበኩሏ፥ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርት ማጠናቀቃቸውን ጠቅሳ፤ የምርምር ሥራዋን ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በማካሄድ ለመመረቅ እንደበቃች ገልጻለች።

    ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት መርሀ-ግብር የሚያስተምራቸው ከ43,000 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ ከ7,000 በላይ ሠራተኞች (staff)፣ ሰባት ካምፓሶች፣ ስምንት ኮሌጆችና ሁለት ተቋማት (institutes)፣ እና ከ200 በላይ የትምህርት መርሀ ግብራት (programs) እንዳሉት ድረ-ገጹ ያሳያል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ዩኒቨርሲቲው (HU)

    ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 7520 ተማሪዎች በበይነ-መረብ አስመረቀ

    (ባሕር ዳር) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምርቃ መርሀ-ግብር በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛውና በተከታታይ መርሀ-ግብር 2254 ተማሪዎች፣ በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ-ግብር 40 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲ መርሀ-ግብር 41 ተማሪዎች፣ በምስክር ወረቀት መርሀ-ግብር 642 ተማሪዎች በድምሩ 7520 ተማሪዎችን በበይነ-መረብ በመታገዝ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። ከተመራቂ ተማሪዎቸ መካከል 2345 ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል አምስቱ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ፣ እንዲሁም የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

    በሥነ-ሥርዓቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክዕት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ዓለምን ባስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ ተግዳሮት ሳይደናቀፉ የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ለተመረቁ ተማሪዎች አድናቆታቸውን ገልፀው ወደ ቀደምት ትልቅነታችን እና ጥበብ ለመመለስ እና አሁን የጀመርናቸውን የአባይ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት የጋራ መድኃኒት ስለሚያስፈልገን ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም በጋራ መሥራት እንደሚገባን አሳስበዋል።

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን (ኮቪድ-19) ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዩኒቨርስቲዎች ሕይወትን ለመታደግ የእውቀት እና የሕዝብ ተቋምነታቸውን ማስመስከራቸውን ጠቅሰው ለዚህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በማምረት እና በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን በማበርከት ሕበረተሰቡን ከወረርሽኙ እየታደገ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ገልፀዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከትምህርት እንዳይለዩ በዩኒቨርሲቲው የICT ባለሙያዎች የበለፀገ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት (learning management system) ለአማራ ክልለዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ማበርከቱን አውስተዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንዳሉት መማር ትርጉም የሚኖረው የሕበረሰተቡን ኑሮ ማሻሻልና ለችግሮቹ መፍቻ የሚሆን አዳዲስ አሠራሮችንና ሀሳቦችን መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቁመው የሀገራችን ችግር የሚፈታው የችግሮችን ስፋትና ጥልቀት በሚረዱ ምሁራን በመሆኑ የምንግዜም ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    አክለውም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የልሕቀት ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ትጋት አድንቀው፤ በእምቦጭ ዙሪያ ብዙ ሥራ መሥራት የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። ከአባይ ፏፏቴ ጀምሮ እስከ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ድረስ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግ የሚቻልበትን ምርምር በመሥራት መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማሳየትም ከዩኒቨርሲቲው እንደሚጠበቅ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል።

    የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን ጥቂት ተማሪዎች አዳራሽ ውስጥ በአካል በመገኘት፥ አብዛኛዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው በአማራ ቴሌቪዥን ከጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቀጥታ ስርጭት፣ በፌስቡክ (Facebook) እና ዩቲዩብ (YouTube) የተላለፈውን ታድመዋል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

     

    Semonegna
    Keymaster

    2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።

    የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።

    ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።

    በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

    በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።

    ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።

    አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።

    ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አረንጓዴ አሻራ

    Anonymous
    Inactive
    • ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲውን የመማር-ማስተማር ሥራ አውከዋል ባላቸው 21 ተማሪዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወሰደ።
    • ዩኒቨርሲቲው “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት አካሂዷል።

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን በማወክ በተለዩና ተጨባጭ ማስረጃ በተገኘባቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ሙሉ በሙሉ መጀመሩንም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።

    የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ፥ አራት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት መታገዳቸውን እና በ21 ተማሪዎች ላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል። ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት በመለየትና በማጣራት በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

    የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከመማር-ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነጽ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም ዶ/ር ዘውዱ ተናግረዋል።

    ባለፉት ሳምንታት ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ቢደረግም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በፖሊ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ፔዳና ይባብ ግቢዎች ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር ተዘግቧል።

    ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ በዩኒቨርሲቲው ፔዳ ግቢ አዳራሽ “ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች፣ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተካሂዷል።

    የኪነ ጥበብ ምሽቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲዉ የዉስጥ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አክሎግ፥ በተማሪዎች አነሳሽነት እና በባህል ማዕከሉ ተባባሪነት ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን አመስግነዉ፤ መሰል ዝግጅቶች በሚኖሩበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደማይለያቸዉ ጠቁመዋል። አክለዉም፥ የዉጭ ሀገራት ተሞክሮዎችን በመጥቀስ መሰል የኪነ ጥበብ ፕሮግራሞች በተማሪዎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ መዘውተር አለባቸው ብለዋል።

    በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ለታዳሚዎች አነቃቂ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዉ የሳይኮሎጅ መምህር አቶ ታምሩ ደለለኝ እንደተናገሩት፥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ሊያስቡባቸው ይገባል ብለዋል። አንደኛው ስብዕናና ክህሎት በማይገነቡ ጊዜያዊ እርካታ ላይ በሚያተኩሩ ክዋኔዎች ለምሳሌ ቲሸርቶችን እያሳተሙ የቀለም ቀን (Color Day)፣ የሕፃናት ቀን (Baby Day)፣ የውሃ ቀን (Water Day) ወይም ሌሎች የመሳሰሉት ላይ ማተኮር ሲሆን፤ ሌላው እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ደግሞ ሰክኖ ከመወያየት ይልቅ አለመግባባትና ግጭት በስፋት መከሰት ናቸው። ከአለመግባባት እና ግጭት ጋር በተያያዘም ተማሪዎች በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ተማሪዎችን እንደ ተማሪ እንዲመለከቷቸውና እርስ-በእርስ እንዲተሳሰቡ መክረዋል። አቶ ታምሩ በመቀጠልም ተማሪዎች ትዕግስትና ማስተዋልን አጥብቀዉ በመያዝ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ስንቅ የሚያገኙበት እንዲሆን እንዲያደርጉት አሳስበዋል።

    በኪነ ጥበብ ምሽቱ “የንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በጎ ሀሳብ አፍላቂ ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይም መሰል ፕሮግራሞች በየ 3 ሳምንቱ እንደሚካሄዱ የዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎች ባህል ማዕከል ኃላፊ ተማሪ ተመስገን ሙሉቀን ተናግረዋል። በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ ታዳሚያን የተገኙ ሲሆን፥ በበመርሃ-ግብሩ መደሰታቸዉን ለመረዳት ተችሏል።

    በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ የግጥም ሥራዎችን ጨምሮ ‘በቃን’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አዝናኝና አስተማሪ ጭዉዉት አንዲሁም ‘ከኛ ጓዳ’ የተሰኘ ተከታታይ የኮሜድ ሥራ ቀርቧል።

    ምንጮች፦ ፋና/ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር፣ ሚኖሶታ ግዛት ካደረገው ቡክስ ፎር አፍሪካ (Books for Africa) ከተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር ባደረገው ግንኙነት፥ በዕርዳታ ያስመጣቸውን የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ እና ስነ-ፅሁፍ መጽሐፎችን በይልማና ዴንሳ ወረዳ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች አከፋፍሏል።

    የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑት አዴት ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ብርአዳማ ከተማ አካባቢ ደግሞ በሰከላል ጃንባራ መድኃኔዓለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በስማርጋ ቀበሌ የሚገኘው ቼመን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በአይቫር ቀበሌ የሚገኘው መጣቅር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ እርዳታው ለሌሎችንም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ያካተተ እንደነበር ታውቋል። መጽሐፎቹ ለመምህራን እና ለተማሪዎች ማጣቀሻነት የሚሆኑ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል እና ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል እንዲሁም ለጎልማሶች ትምህርት የሚያገለግሉ እንደሆኑ ማወቅ ተችሏል። በዕለቱም ከ10 ካርቶን በላይ የሚሆኑ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የሥነ-ፅሑፍ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መጽሐፎች ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ቦታው ድረስ በመሄድ ለርዕሳነ መምህራን ርክክብ ተፈፅሟል።

    በርክክቡ ወቅት በሰከላል ጃንባራ መድኃኔዓለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አዱኛ አጥናፉ እንዳሉት፥ የተደረገላቸው የመጽሐፍ እርዳታ በገንዘብ ሊተመን የማይችልና የተማሪዎችን ብሎም የመምህራንን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ ነው ብለዋል። ይህም የተማሪዎቻቸውን በሀገር ደረጃ የመወዳደር አቅም የሚያጎለብት በመሆኑ የመጽሐፍ እርዳታው ለትምህርት ቤቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። ርዕሰ መምህሩ አክለውም በትምህርት ቤታቸው ያሉባቸውን፦ (1ኛ) ለሳይንስ ትምህርቶች የሚያገለግሉ ኬሚካሎች፣ (2ኛ) በፀሀይ የሚሰራ የኃይል ማመንጫ ችግር ለመቅረፍ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ካደረገው የመጽሐፍ እርዳታ በተጨማሪ በይልማና ዴንሳ ወረዳ ውስጥ ለሚገኙ ከስድስት በላይ የችግኝ ጣቢያዎች ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ በሰው የሚገፉ ጋሪዎች፣ አካፋዎች ፣የመጎንደያ መቀሶች፣ የአሸዋ መንፊያ ወንፊቶችና መጋዞችን ለጣቢያዎቹ አበርክቷል። የይልማና ዴንሳ ወረዳ የስማርጋ ችግኝ ጣቢያ ሠራተኛና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ዳሳሽ ላቃቸው እንዳሉት፥ ችግኝ ጣቢያው በዓመት ከ80 ሺህ በላይ የተለያዩ አገር በቀል ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በነፃ እንደሚያቀርብ ገልፀው፥ እስካሁን ባለው የሥራ ሂደት ምንም ዓይነት የቁሳቁስም ሆነ የግብዓት ችግር እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል።

    የመጽሐፍ ድጋፉ በጎንደር አካባቢ ለሚገኙ የወረዳ የመንግስት ትምህርት ቤቶችም የተደረገ ሲሆን መጽሐፎች ተመሳሳይ ይዘት ያለቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ አቶ አየነው በላይን በመተካት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ቴክሳስ (The University of North Texas) ተከታትለዋል። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ አት ኦስተን (The University of Texas at Austin) እና በሌሎችም በተመራማሪነት ማገልገላቸውም ታውቋል። የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአሜሪካና ካናዳ ማቅረባቸውም በግለ ታሪካቸው ተብራርቷል።

    ዶክተር መሐሪ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሙያ ማኅበራት አባል መሆናቸውም ነው የተገለጸው። የአሜሪካ የስታትስቲክስ ማኅበር (American Statistical Association)፣ የአሜሪካ የትምህርት ጥናት ማኅበር (American Educational Studies Association)፣ የተቋማዊ ጥናት ማኅበር፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥናት ማኅበር፣ የደቡብ ምዕራብ የትምህርት ጥናት ማኅበርና የቴክሳስ የትምህር ጥናት ማኅበር አባል እንደሆኑም ነው የተገለጸው።

    ከ13 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና የተለያዩ ትምህርቶችን በማስተማር እንደቆዩም ተገልጿል፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ማገልገላቸውም ነው የተነገረው።

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስን ልምዳቸውንና የአመራር ብቃታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሄድ በጀመረው መደበኛ ጉባኤው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟቸዋል።■

    ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የበላይ ባለ ኮኮብ 5 ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ፕላን በዘርፉ ባለሙያዎች ተገመገመ። የፕሮጀክቱ ዲዛይንና አማካሪ የሆኑት አቶ ነቢዩ ሰለሞን እንዳብራሩት፥ ሆቴሉ በ3,690 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ፣ 3 ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ 120 የመኝታ ክፍሎች፣ 2 ሬስቶራንቶች፣ ባር፣ ጂም እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች እንደሚኖሩት፣ ዲዛይኑ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

    የደብረ ብርሃን ከተማ ህንጻ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ መኮንን በበኩላቸው በቀረበው ዲዛይን መሠረት ገንቢ አስያየት በመስጠት ሆቴሉ ከታሰበው በላይ ተሻሽሎና ዳብሮ እንዲሠራ ባለሙያዎች የድርሻቸውን አንዲወጡ አሳስበዋል።

    የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቡና ስኒ በዲዛይኑ ላይ መካተቱ ከደብረብርሃን ጋር ምን ያገናኘዋል? የሠራተኞች ማረፊያ ክፈል፣ ሕፃናት መዝናኛ፣የመዋኛ ገንዳ መካተት አለበት የሚሉና እና ሌሎችም በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በመድረኩ ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከህንጻ ሹም፣ ከህንጻ ዲዛይን አማካሪዎች፣ ከባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

    የበላይ ባለ 5 ኮኮብ ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት የመሠረት ድንጋው ሲጣል መገለጹ የሚታወስ ነው።

    ምንጮች፦ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዶክተር መሐሪ ታደሰ

    Semonegna
    Keymaster

    በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር ምክክር ተደረገ

    ባህር ዳር (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ) – የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል በማድረግ ዙሪያ ከዘጠኝ በላይ ከሚሆኑ የባህር ዳር ከተማ ወጣት ማኅበራት ጋር በዩኒቨርሲቲው የጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ምክክር አደረጉ።

    የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮምንኬሽ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የባህር ዳር ወጣቶች በዩኒቨርሲቲው ፀጥታ ጉዳይና የተማሪዎችን ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል። አቶ ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲውም የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርና የወጣቶችን አቅም በመገንባት የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ ጠቁመው ወጣቶችም የባህር ዳር ከተማና የዩኒቨርሲቲው ስም በበጎ እዲነሳ አሁንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት የነበረውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

    ከባህር ዳር ከተማ የተወጣጡ የወጣት ማኅበራት ተወካዮች እንደገለጹት፥ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሞባይልና የላፕቶፕ ዘረፋዎች የሚደርስባቸው ተብለው የተለዩ ዋና ዋና የሚባሉ መስመሮች የመንገድ መብራቶቻቸው የጠፉ እና አንዳንዶችም መስመር ሊዘረጋላቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ከመብራት ኃይል እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲሠራ ጠይቀዋል። አክለውም፥ ወጣቶቹ በባህር ዳር ከተማም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተግተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል። በመጨረሻም፥ በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ለተነሱት ጥያቄዎች በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች መላሽ ተሰጥቷል።

    ምንጭ፦ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ተማሪ ሞት ምክንያት የሆነውን ድርጊት የከተማው ነዋሪዎች እና የክልሉ መንግስት አወገዙ።
    —-

    ባሕር ዳር (አብመድ) – በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ተማሪ ሞት ምክንያት የሆነውን ድርጊት የከተማው ነዋሪዎች እና የክልሉ መንግስት አወገዙ። የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ስለ ችግሩ እና ስለ ቀጣይ የተማሪዎች ሰላም ተወያይተዋል።

    ድርጊቱን ያወገዙት ተወያዮቹ ችግር ፈጣሪዎቹን በማጋለጥ ለጸጥታ አካላት እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል። እስካሁን በድርጊቱ የተጠረጠሩ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ነው በውይይቱ የተገለፀው።

    ውይይቱን የተከታተለው ጋሻዬ ጌታሁን እንዳደረሰን መረጃ ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የጸጥታ ስጋት እንዳይደርስባቸው ከጎናቸዉ እንደሚሆኑ ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

    በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እሁድ ግንቦት 18/2011 ዓ.ም የአንድ ተማሪ ህይወት ሲያልፋ ሶስት ተማሪዎች ቆስለዉ በህክምና ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። የችግሩ መንስኤ እስካሁን እንዳልታወቀም ነው ማብራሪያ የተሰጠው።

    የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ሕዝብ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪ ላይ በደረሰዉ የሕይወት መጥፋት ከልብ ከማዘን ባሻገር ድርጊቱን አጥብቀው እንደሚያወግዙት ገልጿል።

    የክልሉ መንግሥት ከሕዝቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ጥቃት አድራሾችን ተከታትሎ ለሕግ እንደሚያቀርብም ነው ያስታወቀው።

    ለሟች ቤተሰቦች፣ ለጓደኞቹና ለዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብም መጽናናትን ተመኝቷል።

    ምንጭ፦ አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው?

    ባሕር ዳር – በጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ አራት ማስወገጃ መንገዶች በአማራጭነት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ምክረ-ሐሳብ ይቀርባል። ከእነዚህ ማስወገጃ መንገዶች እስካሁን ሁለቱ (የሕዝብ ጉልበት እና ማሽነሪዎች) ጣና ሐይቅ ዙሪያ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው።

    ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው? ስንል የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣንን ጠየቅን።

    በዚህ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሁለት ማሽኖች ብቻ እንደሆኑ የነገሩን በአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ሥርዓተ ምኅዳር ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘው ሁለቱ ማሽኖች ካናዳና እሥራኤል ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በአማጋ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ድጋፍ የተገዙ ናቸው ብለዋል።

    “በባሕር ዳር እና ጎንደር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) እየተዘጋጁ ያሉ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች መኖራቸውን አውቃለሁ” ያሉት አቶ መዝገቡ፥ እስካሁን ድረስ ግን ከተቋማቸው ጋር ርክክብ ፈፅመው ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ገልጸዋል።

    አብመድ የተሰሩት ማሽኖች ለምን ርክክብ ተፈፅሞ አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም ሲል ሁለቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አነጋግሯል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ከሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር የሠራው የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት ቢመረቅም ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ጊዜ ድረስ አገልግሎት አይሰጥም።

    “ማሽኑ አገልግሎት ለመስጠት ምንም ዓይነት ችግር የለበትም፤ በቅርቡም ለሦስት ወራት ያክል የሙከራ ትግበራ ከተደረገ በኋላ ከሚመለከተው አካል ጋር ርክክብ ይደረጋል” ያሉት የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ የዘገየው ማሽኑን ለማንቀሳቀስ የሚሠራ ራሱን የቻለ የሰው ኃይል አደረጃጀት ባለመኖሩ ቅጥርና ምልመላ ለመፈፀም ጊዜ በመውሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ከሙላት ኢንዳስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር ለባለሙያዎቹ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ያስታወቁት ዶ/ር ሰይፉ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገቡም ገልፀውልናል። ማሽኑን በዘላቂነት ለማስተዳደርና ሥራውን ለማስተባበር ራሱን የቻለ ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።

    በጎርጎራ ወደብ አካባቢ የሚገኘው ሌላው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአረም ማስወገጃ ማሽንም ከአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ጋር ርክክብ ያልተፈፀመበት ማሽን ነው። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ኢንጅነር ሰለሞን መስፍን “ለአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ርክክብ እንዲፈፀሙ ደብዳቤ ልከናል” ብለዋል። የተዘጋጀው ማሽን አገልግሎት ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ማሽኑን የሚያንቀሳቅስ የሰው ኃይል (ኦፕሬተር) ማዘጋጀት የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ድርሻ እንደሆነም አስታውቀዋል።

    የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በበኩሉ ማሽኖቹን ለመረከብና የሰው ኃይል ለመቅጠር በተግር ሲሠሩ ማየት እፈልጋለሁ ብሏል።

    በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጅነሪንግ የተዘጋጀው ማሽን ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህ ሳምንት ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የተገዛ ሌላ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጣና ሐይቅ ላይ ደርሶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

    ምንጭ፦ አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን


Viewing 15 results - 1 through 15 (of 21 total)