-
Search Results
-
ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ
(የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮን በተመለከተ)
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ፌዴራዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 87 በተደነገጉ ግልጽ መርሆዎች መከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1100/2011 በተሰጡት ግዳጆች መሠረት ዝርዝር ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ደንቦች እና መመሪያዎችን በማውጣት፥ በሀገራችን ላይ የተቃጡ የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን በመመከት የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስከብሯል። የሕዝብንም ሰላም በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።
መከላከያ ሠራዊቱ የአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሰላም የእኛም ሰላም ነው በሚል መርህ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ ዛሬም ግዳጁን በአስደናቂ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ የዓለም ሕዝቦችና የቀጠናችን ብሎም የሀገራችን ዋነኛ ጠላት የሆነውን አሸባሪነት ለመዋጋት በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የመሸገውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በመመከት ቀጠናችን ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ እንዲሆን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ነው።
በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አለመረጋጋቶችን ከሌሎች የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች፣ ከክልል መስተዳድሮች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና በዋነኝነት ከሕዝባችን ጋር በመተባባር ችግሩን ለመቅረፍ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲመጣ ሠርቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚህ ተግባሩ ሠራዊታችን በደረሰበት ቦታ ሁሉ ሕዝብ ከፍተኛ የሰላም አየር የሚተነፍስ እና እፎይታ የሚሰማው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህያው ምስክር ናቸው።
ከእነዚህ የሠራዊቱ አኩሪ ድሎች የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ ሠራዊታችን ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል በአንድ ጊዜ ግዳጆችን መወጣት የሚችል፣ ለፈተናዎች የማይበገር፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝቦች ሰላም ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ የማይል ሕዝባችን የሚመካበት ሠራዊት መሆኑን ነው።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥
የመከላከያ ሠራዊታችን የተጋድሎና የአሸናፊነት ገድሉ በወታደራዊ ስምሪት እና የግዳጅ አፈጻጸም ላይ ብቻ ሳይገደብ የሕዝብ ችግር ችግሬ ነው የሚል የሕዝቦች ደህንነትና ኋላ ቀርነት የሚያንገበግበውና የሚቆጨው ያለውን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይል፣ የሕዝባችን አለኝታ የሆነ የልማትና የሰላም ሠራዊት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነትና የጥንካሬ መለያ የሆነውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ሠራዊቱ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ ከወር ደመወዙ በማዋጣት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አስተዋጽኦ ከማበርከት አልፎ፤ በግድቡ ላይ ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ለመመከት ሌት ተቀን ዘብ ቆሞ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
መከላከያ ሠራዊታችን ከራሱ በፊት ለሕዝቡና ለሀገር የሚለውን እሴት መሠረት በማድረግ የሀገራችን ሕዝቦች ለገጠማቸው ሰው-ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን አብነት የሚሆን ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።
በጎርፍ አደጋ ዜጎች የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቀነስ፣ በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ፣ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተሰማርቶ በማገዝ፣ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን ኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል፣ ከደመወዙ ቀንሶ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ፣ ገበታ ለሀገር ፕሮጀከት እውን እንዲሆን የወር ደመወዙን በማዋጣት እና በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ ከሕዝቡ ጋር በመሆን በመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረ ተግባሩን ከመጀመሪያውኑ ሠራዊቱ የታነጸበት መሠረታዊ ባህሪው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሃቅ ነው።
መከላከያ ሠራዊታችን ሀገራዊ ግዳጆቹን ሲወጣና ሕዝባዊ ተግባራቱን ሲያከናውን የሚገጥሙትን ችግሮች ሁሉ በመቋቋም ፈተናዎችን በጽናት ተጋፍጦ በማለፍና ውድ ህይወቱን መስዋዕት በማድረግም ጭምር መሆኑ በሕዝባችን የሚታወቅ ሃቅ ነው።
ይሁን እንጂ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሰላም የማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን በጀግንነትና በቁርጠኝነት እየተወጣ ባለበት በዚህ ሰዓት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የማይፈልጉ ቡድናዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሠራዊቱን ስምና ዝና በማጠልሸት በመርህና በሕግ ላይ ያልተመሠረተ የትችት ናዳ በማውረድ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፥ ሠራዊቱ ይህን የፀረ-ሰላም ኃይሎች አጀንዳ በውል በመገንዘብ ትኩረቱን ግዳጁ ላይ ብቻ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥
ሰሞኑን በተለያዩ የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ የአቋም መግለጫ በሚል ርዕስ ስር መግለጫ ያወጣው አካል ሠራዊቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች የተካተቱበት ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ አሰራጭቷል።
በዚህ መግለጫ 1ኛ ተራ ቁጥር ላይ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 87(5) ድንጋጌ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ አኳኋን እንደሚያከናውን የተደነገገውን መርህ በሚጥስ መልኩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ተወያይተው ከሚሰጡት መፍትሄ ውጭ መከላከያ የአደረጃጃት፣ የስምሪትና የቁጥጥር ተግባሩን መፈጸም አይችልም በማለት መከላከያ በተቋማዊ ዕቅዱ እንዲሁም ወቅታዊና ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መነሻ አድርጎ ግዳጁን እንዳይፈጽም በሚገድብ አኳኋን የተዛባ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል።
በዚህ መግለጫ ተራ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ በዝምታ እንዳለፈና የሕገ-ወጥ የፖለቲካ ኃይሎች ጥቅም አስጠባቂ ኃይል መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት በመግለጫ ላይ ተካቷል።
እውነታው የመከላከያ ሠራዊታችን የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተሰማርቶ አስፈላጊ ተገቢና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ይህንን በተጻረረ መልኩ ሠራዊቱ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ነው በማለት የመከላከያ ኃይሉን የማይመጥን፣ ተቋሙ ለሀገርና ለሕዝብ የከፈለውን እና እየከፈለ ያለውን ክብር መስዋዕትነት የሚያንኳስስ ሀገራዊ ተልዕኮውን እና አኩሪ ታሪኩን የሚያጠልሽ መልዕክት ይህ አካል ባወጣው መግለጫ ተስተጋብቷል።
ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይህ አካል መከላከያን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ በማስተጋባት ፍጹም የሠራዊቱን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በማራከስ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።
ይህ ተግባር መከላከያ ሠራዊቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከክልሉ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ጥረት በሚያደርግበት የክልሉ ሕዝብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ትርጉም ባለው ደረጃ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እያስመሰከረ ባለበት እና አጠቃላይ በክልሉ ያለውን ስምሪት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዓላማ አድርጎ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁነቱን ባረጋገጠበት ወቅት የሠራዊቱን ተልዕኮ የሚገድብ መግለጫ ማውጣቱ አግባብነት የጎደለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ መግለጫ የሠራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል ሀገራዊና ክልላዊ ተግባሮቹንም በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደናቅፍ ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ነው።
ከዚህ በፊትም እነዚህ አካላት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ ላይ የነበሩ ቢሆንም ለሕዝቦች ክብር እና ጥቅም ሲባል በከፍተኛ ኃላፊነት መንፈስ ለማለፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። መላው የሀገራችን ሕዝቦች እንደሚገነዘቡት የመከላከያ ሠራዊታችን የማንም ፖለቲካ ኃይል፣ ክልል ወይንም ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብርላቸው፣ ሰላምና ደህንነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው የገነቡት ጠንካራ፣ ብሔራዊና ሀገራዊ ተቋም ነው።
ስለሆነም የሠራዊቱን አደረጃጀት፣ ስምሪትና የግዳጅ አፈጻጸም የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሠራዊቱ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠለትን መርህና በአዋጅ የተሰጠውና ግዳጅና ተልዕኮ መሠረት በማድረግ ተግባራቱን በራሱ የሚወስን እንጅ የሠራዊቱን አጠቃላይ ተልዕኮ እኔ ነኝ የምወስንልህ በሚል አግባብ ይህ አካል የሰጠው መግለጫ የሠራዊቱን ገለልተኝነት የሚጋፋ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ ወቅት የሀገራችን ሕዝቦች እንደ ሀገር የገጠማቸውን ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በመመከት ሰላማቸውን ለማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የሀገራችንን እድገት የማይፈልጉ አካላት በተለይ ከሕዳሴ ግድባችን ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ በሚጻረር መልኩ በእጅ አዙር እና በቀጥታ ጥቃት የሚፈጽሙበትና አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሀገራችንን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት ዓላማ አድርገው በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ እና የማፈናቀል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል።
መከላከያ ሠራዊት ከሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ የደህንነት ስጋቶችን ለመመከት የሚያስችል ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ባለበት እና በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ለማስቆም አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና መልክዓ ምድራዊ ቦታዎች ዘልቆ ሰፊ ስምሪት በማድረግ፣ ክቡር መስዋዕትነትን በመክፈል የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ጥረት በሚያደርግበት በዚህ ወቅት መግለጫውን ያወጣው አካል የሠራዊቱን ወርቃማ ዕድል በሚያጎድፍ መልኩ ሠራዊቱን በሚመለከት ያሰራጨው መልዕክት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ጉዳዩ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በቀጥታ የሚቃረን፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስምሪት እና ተልዕኮ በምንም መልኩ በአንድ አካል ወይም ቡድን ስር የማይወድቅ ሕጋዊና ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ አግባብ ብቻ የሚመራ መሆኑን እያስታወቅን፤ መግለጫውን ያወጣው አካል ስህተቱን በይፋ እንዲያርም አጥብቀን እንጠይቃለን። ማንኛውም አካል የሠራዊቱን ተልዕኮ በሚያደናቅፍ አግባብ መግለጫ ከመስጠት እና አላስፈላጊ መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብም እናሳስባለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሀገርና ሕዝብ የሰጠንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በገባነው ቃልኪዳን መሠረት ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በመሆን፣ ክቡር የሆነውን ህይወታችንን በመክፈል ጭምር የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ የምንገኝ መሆኑን ለመላው ሕዝባችን እያረጋግጥን የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም እንደወትሮው ሁሉ ከጎናችን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መላው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት፥
እኛ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በተጋድሎና በድል የደመቀ አንፀባራቂ ታሪክ ያለን ሠራዊት ነን። በከፍተኛ ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ፅናት ምድራዊ ፈተና ተቋቁመን እና ጥሰን በማለፍም ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሰላም፣ ደህንነትና ልማት ስንል ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት እየከፈልን አልፈናል። በቀጣይም ከዚህ ጉዟችን ሊያደናቅፉን የሚጥሩ፣ ከተልዕኳችን ሊገድቡን ከሚሞክሩና አንድነታችንን ሊሸረሽሩ በሚታክቱ ማንኛውም ዓይነት ኃይሎች ሴራ ሳንገታ ደማቅ ታሪክ መሥራታችንን እንቀጥላለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያበቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ እየደረሰ ያለው የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን እና ወንበራ በተባሉ ወረዳዎች ታጣቂዎች በሰላማዊ ሕዝቦች ላይ ጉዳት እያደረሱ አንደሆነ ነዋሪዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች አመለከቱ። የአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ኃላፊዎች በታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ይናገራሉ።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን እና እና ወንበራ ወረዳዎች በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ሰሞኑን በወረዳዉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ሕብረተሰቡን ለሞት፣ ለስደት እና ለአካል ጉዳት እየዳረጉት እንደሆነ ነዋሪዎቹና ቤተሰቦቻቸው የተጎዱባቸው ግለሰቦች አመልክተዋል። ለሥራ በተንቀሳቀሱበት ባለፈው እሁድ (መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም.) ስድስት ዘመዶቻቸው እንደተገደባቸው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጓዋንጓ አካባቢ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል በስልክ ተናግረዋል። የግልገል በለስ ነዋሪ የሆኑና ለደህንነታቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ በበኩላቸው፥ “መተከል ዞን ውስጥ ቡለን እና ወንበራ አካባቢዎች የሚፈፀመው ጥቃት እጅግ ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ነው” ብለዋል፡፡
ግጭቱ እንዲባባስ ከመንግሥት መዋቅሩ መረጃ የሚያደርስ አካል ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ለዚህም ምክንያታቸው ታጣቂው ኃይል ባለበት አካባቢ የፀጥታ ኃይሉ ሲንቀሳቀስ ቀድመው ከቦታው እንደሚሰወሩ አብራርተዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪና የአማራ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው “የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከክልሉ ውጪ ያሉ የአማራ ክልል ተወላጆችን መብት እያስጠበቀ አይደለም” ሲሉ ይከስሳሉ። የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ እንደገለፁት “ፀረ-ሰላም” ያሏቸውን አካላት ለመደምሰስና በቁጥጥር ስር ለማዋል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በጋራ እየተሠራ ነው። ችግሩ የተፈጠረበትን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑን ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ለማነጋገር ብሞክርም “መረጃ በስልክ አንሰጥም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከባሕር ዳር ጋዜጠኛ ዓለምነው መኮንን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አነጋግሮ ተከታዩን ዘገባ ለዶይቼ ቬለ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ልኳል።
-
- ዘገባውን ለማዳመጥ እዚህ ጋር ይጫኑ።
በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን የተፈጠረው ምንድን ነው?
ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ውስጥ ኤጳር በምትባል ቀበሌ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ‘ጸረ-ሰላም’ ያሏቸውኃይሎች (ታጣቂዎች) በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የአፈናና የግድያ ወንጀል ከመፈጸማቸው በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
ቢቢሲ በበኩሉ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጠይቆ እንደተረዳው፥ በተለያዩ ጊዜያት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሚፈጸመው ጥቃት የተነሳ የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በስጋት ውስጥ ሆነው እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። [ለምሳሌ ያህል፥ ሰኔ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልሉ ዳንጉር ወረዳ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልሉ መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ከ30 ሰዎች በላይ መሞታቸውን የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲልን ጠቅሶ የቢቢሲ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍልዘግቦ ነበር።]
በሚፈጸሙት ጥቃቶችም በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው መገደቡንና ክስተቱም ሁሉም በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረጉ በአካባቢዎቹ ባለው ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ ተናግረዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ የጤና እና ግብርና ባለሙያዎችን ለማፈን ከመሞከራቸውም በላይ፥ በመንግሥት መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ወደ ሌላ ወረዳ መሸሻቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ በወጣው መረጃ መሠረት የአካባቢው ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ ልዩ ኃይል በጋራ በመሆን ወደ ወረዳዎቹ በመግባት ጥቃቱን ለማስቆምና ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ገለጻ ከሆነ በወረዳዎቹ ጉዳት እያስከተለ ያለው ጥቃት የሚፈጸመው ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ባልፈለጉት “የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን አባላት” መሆኑንና በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስካሁን የታገቱ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በተመለከከተ “በቁጥር ደረጃ በዝርዝር አልተለየም” ያሉት ኮማንደር ነጋ፥ መረጃው ተሰባሰቦ ሲያልቅ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ በክልሉ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ ‘ጸረ-ሰላም’ ያሏቸው ኃይሎች ከውጪ ሀገር ጭምር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃ መገኘቱን ጠቅሰው፥ “ወጣቶችን ለመመልመል እንደሚንቀሳቀሱም” ጨምረው ተናግረዋል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከቀናት በፊል መልካን በሚባል ቀበሌ 30 ሰዎችን አፍነው የነበረ ሲሆን፥ አሁን እነሱን መልቀቃቸውን አመልክተው፤ የያዟቸውን ሰዎች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በተለያዩ ጊዜያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንነታቸው ያልተገጹ ቡድኖች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው ባሻገር በተደጋጋሚ ሰዎችን እያገቱ እንደሚወስዱ ሲዘገብ ቆይቷል። እየደረሰ ያለውን የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት፣ የሰውና የንብረት ጉዳት፣ እንዲሁም ተደጋጋሚ የስዎች መታገት ለማስቆም የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ከሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠርና ድርጊቱን ለማስቆም እየጣሩ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጮች፦ ዶይቼ ቬለ ራድዮ እና ቢቢሲ ራድዮ የአማርኛ ዝግጅት ክፍሎች
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጊዜያዊ ውጤትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም
ሀዋሳየደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የሲዳማ ዞን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሕዝብ ውሳኔ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሂዷል።
የሕዝበ ወሳኔው አፈፃፀም ተአማኒ፣ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ አንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ሕዝብ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ዕለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ቦርዱ የሕዝበ ውሳኔውን ጥያቄ የማስፈፀም ኃላፊነቱን መወጣት የጀመረው ሂደቱ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ተአማኒ እንዲሆን እንዲሁም በሲዳማ ዞን እና በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ ዜጎች ያለ አድልዎ ፍላጎታቸውን የሚገልፁበት አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ አፈፃፀም መመሪያ በማጽደቅ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ የሕዝብ ወሳኔውን የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የክልሉ እና የዞን መስተዳደር አካላት እንዲደርስ ለሕዝብም ይፋ እንዲሆን ተደርጓል። ቦርዱ በሕዝብ ውሳኔው እቅድ አፈፃፀም ከክልሉና የዞኑ መስተዳደር አካላት ጋር በርካታ ውይይት እና ስምምነቶችን አድርጓል። በዚህም መሠረት ለሕዝብ ውሳኔ ማስፈፀሚያ የሚያስፈለገውን በጀት በክልሉ መንግሥት እንዲፈቀድ ተደርጓል። ሕዝብ ውሳኔው በሰላማዊ ሁኔታ ለማስፈፀም አስፈላጊ ሁኔታዎችን የክልሉ ምክር ቤት አስቀድሞ እንዲፈጽም በጠየቀው መሠረት የሕዝቡ ውሳኔ የሲዳማ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ የሚል ከሆነ በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች መብት ጥበቃንና አዲስ በሚፈጠረው እና ነባሩ ክልል መሃከል የሚኖረውን የሃብት ክፍፍል የሚወሰንበት አስተዳደርና በሕግ ማእቀፍ አውጥቶ አቅርቧል።
በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት በቦርዱ ባለሞያዎች የመስክ ጥናት አካሂደው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን መረጃ አደራጅተዋል። በዚህም መሠረት ለሕዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ 1692 ምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን ከድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በኋላ ተጨማሪ 169 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል። የሕዝብ ወሳኔው አፈፃፀም ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲያስችል የክልሉ፣ ከዞኑ፣ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም የፌደራል የጸጥታ ተቋማት እና አስተዳደር ተቋማት የሕዝበ ውሳኔው ፀጥታ ዕቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል። የዕቅዱንም አፈጻጸም ቦርዱ በጋራ ሲከታተል ቆይቷል። ከቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት እስከ ድኅረ ሕዝበ ውሳኔ የነበረው የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ በዚህ ዕቅድ መሠረት በጋራ ኮሚቴ በየጊዜው እየታየ ሰላማዊ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ተችሏል።
ሕዝበ ውሳኔውን በገለልተኝነትና በሕግ መሠረት የሚያስፈፅሙ 6843 አስፈፃሚዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች በመመልመል በዞኑ ያሰማራ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዴት እንደሚያስፈጽሙ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናውም ቀድመው የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ 20 አሰልጣኞች ለ5 ቀናት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች የታተመ የማስፈጸሚያ መመሪያ (manual) እንዲኖራቸው ተደርጓል።
የመራጮች ምዝገባ በዞኑ እና በሀዋሳ ከተማ መስተዳድር ለሚኖሩ ማንኛውም ሕጋዊ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ዜጎች ክፍት ሆኖ ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 06 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ምዝገባው ተካሂዶ 2,280,147 ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበዋል።
የድምጽ ሰጪዎች ሕዝበ ውሳኔው ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲመዘገቡ ለመቀስቀስ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የምዝገባ መስፈርቶችን የሚገልጹ እንዲሁም ስለድምጽ አሰጣጡ የሚያብራሩ መልእክቶች ተላልፈዋል። በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የዜጎች መብት እንዳይገደብ እና የሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው የቦርዱ አመራር አባላት በሀዋሳ፣ በይርጋለም፣ በወንዶ ገነት፣ በበሌላ፣ በመዘዋወር የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ክትትል በማድረግ የታዩ ጉድለቶች እና የአሠራር ዝንፈቶች እንዲስተካከሉ ያደረጉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዜጎች በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እንዲሁም በድምጽ መስጠት ሂደቱ የታዘቧቸውን ግድፈቶች በቀጥታ ለቦርዱ ለማሳወቅ እንዲችሉ የቀጥታ የስልክ መስመሮች ተዘጋጅተው ለመገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያ ይፋ ተደርጓል። በደረሱት ጥቆማዎችም መሠረት የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲሁም መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።
በቦርዱ አባላት በተደረጉ ጉብኝቶች እና ቀደም ብሎ ከዞኑ እና ከክልል መስተዳድር ተቋማት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ግንኙነቶች በሕዝበ ውሳኔው ሂደት በርካታ ማስተካከያዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም ጥቂቶቹ፦
- የአካባቢ ሚሊሻ አባላት የምርጫ ጣቢያዎችን ጸጥታ አጠባበቅ ምንም አይነት ሚና እንዳይኖራቸው ተደርጓል፤
- በሕዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፤
- በሕዝበ ውሳኔው መራጮች ምዝገባ እና ድምጽ መስጠት ሂደት ሁለቱም አማራጮችን የሚወክሉ ወኪሎች አንዲገኙ ጥረት ተደርጓል፤
- የተጓደሉ የሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በፍጥነት እንዲሟሉ ተደርጓል።
የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊነት እና ግልጽነቱን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለወደፊት መሻሻል ላለባቸው አሠራሮች ትምህርት ለመውሰድ ለ128 የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች እና 74 የአገር ውስጥና የውጪ ሚዲያ ጋዜጠኞች ሂደቱን እንዲታዘቡና እንዲዘግቡ የሚያስችል እውቅና ተሰጥቷል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የኮሚሽኑ 20 ታዛቢዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ተደርጓል። በኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ፍቃድ የተሰጣቸው የአሜሪካን መንግሥት ወኪሎችና ዲፕሎማቶች ሕዝበ ውሳኔን እንዲታዘቡ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጓል።
የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት እስከ ድምጽ መስጫው ቀን ባሉት ጥቂት ቀናት ቦርዱ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን ያሰራጨ ሲሆን በዚህም ሂደት 3000 የድምጽ መስጫ ሳጥኖች እና 2.5 ሚሊዮን በላይ (መጠባበቂያን ጨምሮ) የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲሁም የተለያዩ ቅጾችና ቁሳቁሶች ስርጭት ተከናውኗል።
በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ጸጥታ እና ደኅንነት አስመልክቶ ቦርዱ ሂደቱን በሚመራበት ወቅት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ በሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመስክ ጉብኝት አድርጓል። ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘ እና ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማኅበረሰብ ክፍሎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማዳመጥ የቦርድ አመራር አባላት በቦታው በመገኘት የመስክ ቅኝቶችን አድርገው ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል። ከውይይቱም በተጨማሪ የሲዳማ ዞን እና የደቡብ ክልል የጸጥታ አካላት፣ የፌደራል ፓሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊትን ያካተተ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ የሚያይ መድረክ በማቋቋም ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ተደርጓል።
ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የተከናወነው የድምጽ መስጠት ሂደት ሰላማዊ እና ጉልህ የሎጄስቲክስ ችግር ያልታያበት ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሰልፎች ከመኖራቸው በስተቀር በታቀደበት ሁኔታ ተጠናቋል። በዕለቱ የቦርድ አመራር አባላት የመስክ ጉብኝቶችን ያካሄዱ ሲሆን የምርጫ ቆጠራውም በዕለቱ ተጠናቆ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተለጥፏል። በዕለቱ ከመራጮች የሚመጡ ጥቆማዎችንም መሠረት በማድረግ የተለያዩ እርምት እርምጃዎች ሲከናወኑ ውለዋል።
በዚህም መሠረት በአጠቃላይ ከተመዘገበው 2,280,147 መራጭ 2,277,063 ሰው ድምጹን ሰጥቷል። ይህም የምርጫ ቀን የድምጽ መስጠት ተሳትፎ (voter turnout) 99.86 በመቶ መሆኑን ያሳያል። ሲዳማ በነባሩ ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ጎጆ ምልክትን የመረጠ ሰው ብዛት 33,463 ሲሆን የሲዳማ በክልልነት መደራጀትን ሻፌታን የመረጠ ሰው ብዛት 2,225,249 ነው። በውጤቱም ሻፌታ የመረጠው 98.51 % ሲሆን ጎጆን የመረጠው 1.48 % ነው። ። በሂደቱ የዋጋ አልባ ድምጽ ቁጥር 18,351(0.01%) ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47/2/ እና /3/ ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱ ክልል የመቋቋም መብት አለው በማለት በሚደነግገው መሠረት፥ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተፈጽሟል። የዞኑ ነዋሪዎች በነፃ ፈቃዳቸው በሰጡት ውሣኔ መሠረት ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምፅም በዚህ ውሳኔ አግኝቷል።
የሕዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው። ሕዝበ ውሳኔው ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደረጉበት እና በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ነው ብሎ ቦርዱ ያምናል። በውጤቱ መሠረትም በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 47/3/መ ላይ እንደተጠቀሰው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የሕዝቡን ድምጽ ባከበረ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲሁም ሽግግሩን ጊዜን በጠበቀ ሁኔታ በማከናወን የስልጣን ርክክቡን በአግባቡ አከናውነው ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያስፈጽሙ ቦርዱ የጸና እምነት አለው።
ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
የሕዝበ ውሳኔው አፈፃፀም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆኑ በዚህ ሂደት የተገኘ በጎ ውጤት ሲሆን፥ ለዝግጅት ከነበረው አጭር ጊዜም አንጻር የቦርዱ አፈጻጸም የተሳካ ነው ብሎ ያምናል። የአፈፃፀም ሂደቱ ጠቃሚ ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ያህል ተግዳሮቶች የነበሩበት በመሆኑ ለቀጣይ ትምህርት ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤- የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ (የአነስተኛ ቡድኖች መብት ጥበቃ፤ የሀብት ክፍፍል) በቦርዱ የቀረበው ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት የተሰጠው ምላሽ መዘግየት፤
- የሕዝበ ውሳኔው ቅስቀሳ ሂደት የአንድን ወገን አማራጭ ብቻ የቀረበበት መሆኑ እና የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት እንዲታዘቡ የክልሉ መንግሥት ወኪሎች እንዲመድብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም አለመመደቡ፤
- የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ለመወሰን የሚያስፈልገው የሕዝብ ቁጥር የተሟላ መረጃ አለመኖር፤
- በተወሰኑ የሀዋሳ ከተማን የገጠር አካባቢ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የማይመለከታቸው ሰዎች መገኘት፣ በድምፅ ሰጪዎች ላይ በአንዳንድ ጣቢያዎች ተፅእኖ የማሳደር ሁኔታ መታየት፤
- በአንዳንድ ቦታዎች በድምፅ ሰጪዎች ብዛት ምክንያት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መጨናነቅ መከሰቱ፤
- በሕዝበ ውሳኔው ውጤት አገላለጽ ላይ ከሀዋሳ ከተማና ከዞኑ መስተዳድር ተቋማት ኃላፊዎች በቦርዱ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት አስቀድሞ የመገመት (projection) እና የመግለጽ ችግር መታየቱ፤
- በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ የተቀመጠን የምርጫ ጣቢያ መክፈቻ እና መዝጊያ ሰዓት አለመጠበቅ እንደዋና ተግዳሮት የሚጠቀሱ ሲሆን (ማለትም የክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ የደቡብ እዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት) የሕዝበ ውሳኔ ቁሳቁስ ማጓጓዝ፣ የአካባቢ ጸጥታ እና ደኅንነትን በመጠበቅ፣ የአስፈጻሚዎች ስምሪትን እንዲሁም ድምጽ የተሰጠባቸውን ሰነዶችን ጥበቃ በማድረግ እጅግ የሚመሰገን ድጋፍ ማድረጋቸው እና በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ከፍተኛ ቅንጅት መኖሩ እንደትልቅ ስኬት የሚነሳ ነው።
ምስጋና
በሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ሕዝበ ውሳኔ እስካሁን በአገራችን ከነበረው ልምድ የተለየ እና መጀመሪያው ቢሆንም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ ሊፈጸም ችሏል። ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ስኬታማ ለማድረግ ቦርዱ ከተለያዩ አካላት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ድጋፍ አግኝቷል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚከተሉት ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናውን ያቀርባል።- በሕዝበ ውሳኔው በሰላማዊ እና ሥነ ሥርዓት ባለው ሁኔታ ለተሳተፉት የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች በሙሉ፣
- ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው በመሄድ ባልተሟላ አንዳንዴም በአስቸጋሪ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔውን ላስፈጻሙ የሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች እና ሥራውን በማስተባበር ለደከሙ የቦርዱ ሠራተኞች፣
- ለሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች ምልመላ ድጋፍ ያደረጉልን፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ፣ ለአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ፣
- ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስዳድር እና የርዕሰ መስተዳድሩ ሕህፈት ቤት፣
- ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት፣
- ለሲዳማ ዞን አስተዳደር፣
- ለሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣
- ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሃገር መከላከያ ሠራዊትና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደቡብ እዝ፣
- ለፌደራል ፓሊስ፣
- ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፓሊስ ኮሚሽን፣
- ለሲዳማ ዞን ፓሊስ፣
- ለሀዋሳ ከተማ ፓሊስ፣
- ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣
- ሕዝበ ውሳኔውን ለመታዘብ ለተሳተፉ ሲቪል ማኅበራት፣
- የተለያዩ እገዛዎችንን ላደረጉልን የአሜሪካን የልማት ድርጅት (USAID/IFES) እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP)፣
- ለአዲስ ፓርክ
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትህ እና ነፃነት ጥያቄ በግድየለሽነት በሚንቀሳቀሱ ሰዎችና ተግባራቸው እንዳይጠለፍ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል!የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ይገባናል በሚል ሁሉንም አገዛዞች ሲታገል የቆየ ሕዝብ መሆኑ ሃቅ ነው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንኳን ፍትሃዊ እና የሁሉንም ዜጎች ነፃነት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል በትግል የተገኙ አራት ዕድሎች መክነውብናል። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች እና የዜጎች አልገዛም ባይነት እና እምቢተኝነት ትንቅንቅ የሚቋጨው ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭ ሆኖ የሚመርጠው እና የሚቆጣጠረው መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው።
የሩቁን ትተን በ2007 ዓ.ም. እንኳን ብናይ፣ በሙሉ ድምጽ ተመርጫለሁ ብሎ ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረዉ ገዢ ቡድን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ስብርብሩ የወጣው በዜጎች የጋለ የዴሞክራሲ ጥያቄ እና የተባበረ ትግል ነው።
ይህ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተባበረ ክንድ የተሰበረ አምባገነናዊ አሠራርና አስተሳሰብ መልክ እና ቅርፁን በመቀያየር የተገኘውን የለውጥ ጭላንጭል ድርግም አድርጎ በማጥፋት ጥለነዉ ወደመጣነዉ ጨለማና ወደራሱ የአገዛዝ አቅጣጫ ሊጠልፈው እንደተዘጋጀ ከበቂ በላይ ምልክቶችን አይተናል።የኢትዮጵያን ሕዝብ ትዕግስት፣ አስተዋይነት እና አርቆ አሳቢነት የመረዳት ችሎታ ያነሳቸው ጥቂት ፅንፈኞች ሀገራችን የምትጠብቀውን ተስፋ ሊነጥቋትና እነሱም አጥፍተው ሊጠፉ የተዘጋጁ ይመስላል። በእንደዚህ ዓይነት አቅላቸውን በሳቱ የአገዛዝ ቡድኖች እጅ መውደቅ ለአገራችን የመጀመሪያ ባይሆንም ይህ አሁን የገጠመን አጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መቆምን እና መታገልን የሚያሻ መሆኑን ማሳሰብ እንወዳለን። በተደጋጋሚ እንዳልነው አሁን ያገኘነውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ሀገራዊ መረጋጋት በእጅጉ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ በተፃራሪ የአንድ ወገን አሸናፊነት ተረክ መፍጠር ያገኘነውን ዕድል አደጋ ላይ የሚጥል እና ለማንም የማይጠቅም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንሸጋገርበትን መደላድል ለመፍጠር ሰላም እና መረጋት ለማስፈንና ተቋማትን ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ቢሆንም በገዢው ፓርቲ ውስጥም ይሁን ከዚያ ውጪ ለውጡ የጋራ ትግል ውጤት መሆኑን የዘነጉ ቡድኖች የሚሠሩትን ነውረኛ አካሄድ በማየት በሚከተሉት 7 ነጥቦች ላይ ያለውን አቋም ይገልጻል።
- የአማራ እና የቅማንት ሕዝብ ብዙ መከራዎችን በጋራ ያሳለፈ ድንበር የሌለው አንድ ሕዝብ ዛሬ በአስተዳደር ወሰን እና በማንነት ጉዳዮች የሚነሱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን የሚያስተናግደው በክፋት በተዋቀረው ፌደራላዊ አሠራር መሆኑን ተገንዝበን ለዘላቂ ሰላም እና ለሕዝብ አብሮ መኖር በትዕግስት እንድንሠራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ግጭቶች ባሉበት አካባቢ የሚኖረውም ሕዝብ፤ በመሀከሉ ያለውን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እና ሰላሙን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ እኩይ ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን በሕዝባችን አንድነት ስም እንማጸናለን።
- ኢሕአዴግ በጌታ እና ሎሌ አደረጃጀት የተዋቀረ ከዚህም ሲያልፍ መንግሥትነት የሚያስገኘውን የሥልጣን ጥቅም በመቀራመት ጎን ለጎን ሲጓተቱ የነበሩ ቡድኖች ስብስብ መሆኑን ለምናውቅ ሁሉ የዛሬው እሽኮለሌ አያስደንቀንም። ሆኖም ግን ሕዝባችንን በእነሱ ጦስ ወደእልቂት ለመክተት የሚያደርጉትን የትንኮሳ አካሄድ እንዲያቆሙ በኢሕአዴግ ውስጥ የተሰባሰቡ የብሔር ድርጅቶችን በጥብቅ እናሳስባለን።
- የተቋማትን መኖር እና መጠንከር አስፈላጊ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክንውኖች ከፖለቲካ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ቢሆንም ከሰሞኑ በተለይም የኦዴፓ አደረጃጀት የሰላም፣ የይቅርታ እና የምስጋና ታላቅ በዓል የሆነውን ኢሬቻን መጥለፉ ሳያንስ የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የሚጎትት እና የሚበርዝ በመሆኑ እንዲህ ዓይነትቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም አንጠይቃለን። የሀገር አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሂደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ አዲስ አበባ ለተከበረው ኢሬቻ በዓል ከየቦታው የመጡ የበዓሉ ታዳሚ ኢትዮጵያዊያንን በመንከባከብ ላሳየው አብሮነት እና ወገናዊ ፍቅር እንዲሁም በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላሳየው ትዕግስት ያለንን አክብሮት እና ምስጋና እየገለጽን ወደፊትም ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲታገል የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡
- የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን አፈና እስካሁን በሆደሰፊነት ማለፉ ሊያስመሰግነው ቢገባም ይህን ያልተረዱ ወገኖች ትዕግስቱን እንደፍርሀት፤ ጨዋነቱን እንደ የዋህነት እየወሰዱ ማኅበረሰቡን መተንኮስ እየተለመደ መጥቷል። ይህ የሀገራችንን ሁሉንም ሕዝብ አቅፎ የያዘ፤ ከዚያም በላይ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከል የሆነና ለፌደራል መንግሥቱም ከፍተኛ የሆነ የግብር ገቢ የሚያስገኝ ከተማን በጥንቃቄና በአክብሮት፤ የሚገባውን መብት አክብሮ መያዝ ይገባል። የከተማው ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም እውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን አይቀበልም። ይህንን መብቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅም ራሱን ከቀበሌ ጀምሮ በሁሉም ያስተዳደር እርከን በጠንካራ ሁኔታ አደራጅቶ የራሱን መብት ለማስከበርና የራሱን መሪዎች ለመምረጥ መዘጋጀት ይጠበቅበታል። ኢዜማ ይህንን ራስን የማስተዳደር እንቅስቃሴውን እውን ለማድረግ ከከተማው ሕዝብ ጋር አብሮ ይሠራል፤ የከተማውን ሕዝብም ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ በዜግነቱና በከተማ ነዋሪነቱ ያደራጃል። ከዚህም በተጨማሪ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንደግፋለን፤ በሥነ ሥርዓት እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በጠበቀና ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጎለብት ሁኔታ እንዲካሄድም ጥሪ እናስተላልፋለን።
- በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ያስተዋወቀው አዲስ የደንብ ልብስ ለከተማ የፖሊስ አገልግሎት የሚመች ባለመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውል አጥብቀን እናሳስባለን። የከተማዋ ፖሊስ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እንዲሁም በኮሚኒቲ ፖሊስ ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት እያለው እና የፌደራል ፖሊስ ኃይል በቋሚነት በሚገኝበት ከተማ ውስጥ ተጨማሪ ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ማቋቋም ተቀባይነት የለውም። ይልቁንም የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የከተማዋን ኅብረተሰብ ደኅንነት ማስጠበቅ እና አባላቱ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። በክልሎች የተደራጀው ልዩ ኃይል እና አዲስ አበባ አስተዳደር አቋቋምኩት ያለው ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ለሚደረገው ትግል ትልቅ ተግዳሮቶች ናቸው። ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው እነዚህ አደረጃጀቶች ፈርሰው ወደመደበኛ ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት እንዲካተቱ በድጋሚ ጥሪ እናስተላልፋለን።
- በአማራ ክልል የተከሰቱ የወንድማማች ሕዝብ ግጭቶች ተከትሎ ሁኔታው እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሰፍን ከመስበክ ይልቅ ሥራዬ ብለው ወሬ እየፈበረኩ ግጭቶችን በሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣን በአስቸኳይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እናሳስባለን።
- ላለፉት 27 አመታት ሲሰራበት የቆየው ሀገርን እና ሕዝብን ሆን ብሎ የሚከፋፍልና የሚበትን የዘረኝነት አሠራር ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም የሚቻለው ፖለቲካችንን በማዘመንና በመግራት፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ተደራጅቶ በመታገል በመሆኑ፤ ሌሎች ያደርጉልናል ብሎ ከመጠበቅ ዜጎች በተለይም ለዘብተኛ አመለካከት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ እንድናልፍ ባላችሁ አቅም ሁሉ በሀገራችሁ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ እንድትሆኑ የዘወትር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በአጠቃላይ ሰላምን፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያይ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲገነባ ሕዝባችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ የኢዜማ አደረጃጀቶች በመግባት የጀመረውን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ ከዳር እንዲያደርስ ጥሪያችንን እያቀረብን ሌሎች የማኅበረሰብ መሪዎች ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ መረጋጋት ዘብ መቆም የሚገባቸው ጊዜ ዛሬ መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሀገር አንድነትን ማስቀጠል እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። አሁን ያለንበት የሽግግር ወቅት የሀገር አንድነትን እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን እንዲያረጋግጥ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንደምናደርግ እና አስፈላጊውን መስዕዋትነት ለመክፈልም ወደኋላ እንደማንል በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናችን እንደሚቆም አንጠራጠርም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-