-
Search Results
-
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ እየደረሰ ያለው የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን እና ወንበራ በተባሉ ወረዳዎች ታጣቂዎች በሰላማዊ ሕዝቦች ላይ ጉዳት እያደረሱ አንደሆነ ነዋሪዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች አመለከቱ። የአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ኃላፊዎች በታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ይናገራሉ።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን እና እና ወንበራ ወረዳዎች በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ሰሞኑን በወረዳዉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ሕብረተሰቡን ለሞት፣ ለስደት እና ለአካል ጉዳት እየዳረጉት እንደሆነ ነዋሪዎቹና ቤተሰቦቻቸው የተጎዱባቸው ግለሰቦች አመልክተዋል። ለሥራ በተንቀሳቀሱበት ባለፈው እሁድ (መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም.) ስድስት ዘመዶቻቸው እንደተገደባቸው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጓዋንጓ አካባቢ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል በስልክ ተናግረዋል። የግልገል በለስ ነዋሪ የሆኑና ለደህንነታቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ በበኩላቸው፥ “መተከል ዞን ውስጥ ቡለን እና ወንበራ አካባቢዎች የሚፈፀመው ጥቃት እጅግ ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ነው” ብለዋል፡፡
ግጭቱ እንዲባባስ ከመንግሥት መዋቅሩ መረጃ የሚያደርስ አካል ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ለዚህም ምክንያታቸው ታጣቂው ኃይል ባለበት አካባቢ የፀጥታ ኃይሉ ሲንቀሳቀስ ቀድመው ከቦታው እንደሚሰወሩ አብራርተዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪና የአማራ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው “የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከክልሉ ውጪ ያሉ የአማራ ክልል ተወላጆችን መብት እያስጠበቀ አይደለም” ሲሉ ይከስሳሉ። የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ እንደገለፁት “ፀረ-ሰላም” ያሏቸውን አካላት ለመደምሰስና በቁጥጥር ስር ለማዋል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በጋራ እየተሠራ ነው። ችግሩ የተፈጠረበትን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑን ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ለማነጋገር ብሞክርም “መረጃ በስልክ አንሰጥም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከባሕር ዳር ጋዜጠኛ ዓለምነው መኮንን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አነጋግሮ ተከታዩን ዘገባ ለዶይቼ ቬለ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ልኳል።
-
- ዘገባውን ለማዳመጥ እዚህ ጋር ይጫኑ።
በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን የተፈጠረው ምንድን ነው?
ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ውስጥ ኤጳር በምትባል ቀበሌ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ‘ጸረ-ሰላም’ ያሏቸውኃይሎች (ታጣቂዎች) በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የአፈናና የግድያ ወንጀል ከመፈጸማቸው በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
ቢቢሲ በበኩሉ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጠይቆ እንደተረዳው፥ በተለያዩ ጊዜያት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሚፈጸመው ጥቃት የተነሳ የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በስጋት ውስጥ ሆነው እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። [ለምሳሌ ያህል፥ ሰኔ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልሉ ዳንጉር ወረዳ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልሉ መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ከ30 ሰዎች በላይ መሞታቸውን የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲልን ጠቅሶ የቢቢሲ ራድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍልዘግቦ ነበር።]
በሚፈጸሙት ጥቃቶችም በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው መገደቡንና ክስተቱም ሁሉም በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረጉ በአካባቢዎቹ ባለው ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ ተናግረዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ የጤና እና ግብርና ባለሙያዎችን ለማፈን ከመሞከራቸውም በላይ፥ በመንግሥት መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ወደ ሌላ ወረዳ መሸሻቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ በወጣው መረጃ መሠረት የአካባቢው ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ ልዩ ኃይል በጋራ በመሆን ወደ ወረዳዎቹ በመግባት ጥቃቱን ለማስቆምና ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ገለጻ ከሆነ በወረዳዎቹ ጉዳት እያስከተለ ያለው ጥቃት የሚፈጸመው ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ባልፈለጉት “የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን አባላት” መሆኑንና በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስካሁን የታገቱ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በተመለከከተ “በቁጥር ደረጃ በዝርዝር አልተለየም” ያሉት ኮማንደር ነጋ፥ መረጃው ተሰባሰቦ ሲያልቅ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ በክልሉ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ ‘ጸረ-ሰላም’ ያሏቸው ኃይሎች ከውጪ ሀገር ጭምር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃ መገኘቱን ጠቅሰው፥ “ወጣቶችን ለመመልመል እንደሚንቀሳቀሱም” ጨምረው ተናግረዋል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከቀናት በፊል መልካን በሚባል ቀበሌ 30 ሰዎችን አፍነው የነበረ ሲሆን፥ አሁን እነሱን መልቀቃቸውን አመልክተው፤ የያዟቸውን ሰዎች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በተለያዩ ጊዜያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንነታቸው ያልተገጹ ቡድኖች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው ባሻገር በተደጋጋሚ ሰዎችን እያገቱ እንደሚወስዱ ሲዘገብ ቆይቷል። እየደረሰ ያለውን የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት፣ የሰውና የንብረት ጉዳት፣ እንዲሁም ተደጋጋሚ የስዎች መታገት ለማስቆም የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ከሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠርና ድርጊቱን ለማስቆም እየጣሩ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጮች፦ ዶይቼ ቬለ ራድዮ እና ቢቢሲ ራድዮ የአማርኛ ዝግጅት ክፍሎች
2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።
አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር፣ ሚኖሶታ ግዛት ካደረገው ቡክስ ፎር አፍሪካ (Books for Africa) ከተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር ባደረገው ግንኙነት፥ በዕርዳታ ያስመጣቸውን የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ እና ስነ-ፅሁፍ መጽሐፎችን በይልማና ዴንሳ ወረዳ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች አከፋፍሏል።
የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑት አዴት ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ብርአዳማ ከተማ አካባቢ ደግሞ በሰከላል ጃንባራ መድኃኔዓለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በስማርጋ ቀበሌ የሚገኘው ቼመን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በአይቫር ቀበሌ የሚገኘው መጣቅር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ እርዳታው ለሌሎችንም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ያካተተ እንደነበር ታውቋል። መጽሐፎቹ ለመምህራን እና ለተማሪዎች ማጣቀሻነት የሚሆኑ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል እና ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል እንዲሁም ለጎልማሶች ትምህርት የሚያገለግሉ እንደሆኑ ማወቅ ተችሏል። በዕለቱም ከ10 ካርቶን በላይ የሚሆኑ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የሥነ-ፅሑፍ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መጽሐፎች ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ቦታው ድረስ በመሄድ ለርዕሳነ መምህራን ርክክብ ተፈፅሟል።
በርክክቡ ወቅት በሰከላል ጃንባራ መድኃኔዓለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አዱኛ አጥናፉ እንዳሉት፥ የተደረገላቸው የመጽሐፍ እርዳታ በገንዘብ ሊተመን የማይችልና የተማሪዎችን ብሎም የመምህራንን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ ነው ብለዋል። ይህም የተማሪዎቻቸውን በሀገር ደረጃ የመወዳደር አቅም የሚያጎለብት በመሆኑ የመጽሐፍ እርዳታው ለትምህርት ቤቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። ርዕሰ መምህሩ አክለውም በትምህርት ቤታቸው ያሉባቸውን፦ (1ኛ) ለሳይንስ ትምህርቶች የሚያገለግሉ ኬሚካሎች፣ (2ኛ) በፀሀይ የሚሰራ የኃይል ማመንጫ ችግር ለመቅረፍ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ካደረገው የመጽሐፍ እርዳታ በተጨማሪ በይልማና ዴንሳ ወረዳ ውስጥ ለሚገኙ ከስድስት በላይ የችግኝ ጣቢያዎች ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ በሰው የሚገፉ ጋሪዎች፣ አካፋዎች ፣የመጎንደያ መቀሶች፣ የአሸዋ መንፊያ ወንፊቶችና መጋዞችን ለጣቢያዎቹ አበርክቷል። የይልማና ዴንሳ ወረዳ የስማርጋ ችግኝ ጣቢያ ሠራተኛና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ዳሳሽ ላቃቸው እንዳሉት፥ ችግኝ ጣቢያው በዓመት ከ80 ሺህ በላይ የተለያዩ አገር በቀል ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በነፃ እንደሚያቀርብ ገልፀው፥ እስካሁን ባለው የሥራ ሂደት ምንም ዓይነት የቁሳቁስም ሆነ የግብዓት ችግር እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል።
የመጽሐፍ ድጋፉ በጎንደር አካባቢ ለሚገኙ የወረዳ የመንግስት ትምህርት ቤቶችም የተደረገ ሲሆን መጽሐፎች ተመሳሳይ ይዘት ያለቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ አቶ አየነው በላይን በመተካት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።
ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ቴክሳስ (The University of North Texas) ተከታትለዋል። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ አት ኦስተን (The University of Texas at Austin) እና በሌሎችም በተመራማሪነት ማገልገላቸውም ታውቋል። የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአሜሪካና ካናዳ ማቅረባቸውም በግለ ታሪካቸው ተብራርቷል።
ዶክተር መሐሪ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሙያ ማኅበራት አባል መሆናቸውም ነው የተገለጸው። የአሜሪካ የስታትስቲክስ ማኅበር (American Statistical Association)፣ የአሜሪካ የትምህርት ጥናት ማኅበር (American Educational Studies Association)፣ የተቋማዊ ጥናት ማኅበር፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥናት ማኅበር፣ የደቡብ ምዕራብ የትምህርት ጥናት ማኅበርና የቴክሳስ የትምህር ጥናት ማኅበር አባል እንደሆኑም ነው የተገለጸው።
ከ13 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና የተለያዩ ትምህርቶችን በማስተማር እንደቆዩም ተገልጿል፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ማገልገላቸውም ነው የተነገረው።
ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስን ልምዳቸውንና የአመራር ብቃታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሄድ በጀመረው መደበኛ ጉባኤው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟቸዋል።■
ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የበላይ ባለ ኮኮብ 5 ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ፕላን በዘርፉ ባለሙያዎች ተገመገመ። የፕሮጀክቱ ዲዛይንና አማካሪ የሆኑት አቶ ነቢዩ ሰለሞን እንዳብራሩት፥ ሆቴሉ በ3,690 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ፣ 3 ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ 120 የመኝታ ክፍሎች፣ 2 ሬስቶራንቶች፣ ባር፣ ጂም እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች እንደሚኖሩት፣ ዲዛይኑ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ህንጻ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ መኮንን በበኩላቸው በቀረበው ዲዛይን መሠረት ገንቢ አስያየት በመስጠት ሆቴሉ ከታሰበው በላይ ተሻሽሎና ዳብሮ እንዲሠራ ባለሙያዎች የድርሻቸውን አንዲወጡ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቡና ስኒ በዲዛይኑ ላይ መካተቱ ከደብረብርሃን ጋር ምን ያገናኘዋል? የሠራተኞች ማረፊያ ክፈል፣ ሕፃናት መዝናኛ፣የመዋኛ ገንዳ መካተት አለበት የሚሉና እና ሌሎችም በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በመድረኩ ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከህንጻ ሹም፣ ከህንጻ ዲዛይን አማካሪዎች፣ ከባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የበላይ ባለ 5 ኮኮብ ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት የመሠረት ድንጋው ሲጣል መገለጹ የሚታወስ ነው።
ምንጮች፦ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው?
ባሕር ዳር – በጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ አራት ማስወገጃ መንገዶች በአማራጭነት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ምክረ-ሐሳብ ይቀርባል። ከእነዚህ ማስወገጃ መንገዶች እስካሁን ሁለቱ (የሕዝብ ጉልበት እና ማሽነሪዎች) ጣና ሐይቅ ዙሪያ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው።
ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው? ስንል የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣንን ጠየቅን።
በዚህ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሁለት ማሽኖች ብቻ እንደሆኑ የነገሩን በአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ሥርዓተ ምኅዳር ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘው ሁለቱ ማሽኖች ካናዳና እሥራኤል ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በአማጋ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ድጋፍ የተገዙ ናቸው ብለዋል።
“በባሕር ዳር እና ጎንደር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) እየተዘጋጁ ያሉ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች መኖራቸውን አውቃለሁ” ያሉት አቶ መዝገቡ፥ እስካሁን ድረስ ግን ከተቋማቸው ጋር ርክክብ ፈፅመው ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ገልጸዋል።
አብመድ የተሰሩት ማሽኖች ለምን ርክክብ ተፈፅሞ አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም ሲል ሁለቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አነጋግሯል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ከሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር የሠራው የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት ቢመረቅም ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ጊዜ ድረስ አገልግሎት አይሰጥም።
“ማሽኑ አገልግሎት ለመስጠት ምንም ዓይነት ችግር የለበትም፤ በቅርቡም ለሦስት ወራት ያክል የሙከራ ትግበራ ከተደረገ በኋላ ከሚመለከተው አካል ጋር ርክክብ ይደረጋል” ያሉት የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ የዘገየው ማሽኑን ለማንቀሳቀስ የሚሠራ ራሱን የቻለ የሰው ኃይል አደረጃጀት ባለመኖሩ ቅጥርና ምልመላ ለመፈፀም ጊዜ በመውሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሙላት ኢንዳስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር ለባለሙያዎቹ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ያስታወቁት ዶ/ር ሰይፉ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገቡም ገልፀውልናል። ማሽኑን በዘላቂነት ለማስተዳደርና ሥራውን ለማስተባበር ራሱን የቻለ ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።
በጎርጎራ ወደብ አካባቢ የሚገኘው ሌላው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአረም ማስወገጃ ማሽንም ከአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ጋር ርክክብ ያልተፈፀመበት ማሽን ነው። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ኢንጅነር ሰለሞን መስፍን “ለአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ርክክብ እንዲፈፀሙ ደብዳቤ ልከናል” ብለዋል። የተዘጋጀው ማሽን አገልግሎት ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ማሽኑን የሚያንቀሳቅስ የሰው ኃይል (ኦፕሬተር) ማዘጋጀት የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ድርሻ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በበኩሉ ማሽኖቹን ለመረከብና የሰው ኃይል ለመቅጠር በተግር ሲሠሩ ማየት እፈልጋለሁ ብሏል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጅነሪንግ የተዘጋጀው ማሽን ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህ ሳምንት ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የተገዛ ሌላ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጣና ሐይቅ ላይ ደርሶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ምንጭ፦ አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-