-
AuthorSearch Results
-
April 19, 2021 at 12:56 am #19091
In reply to: ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች
AnonymousInactiveከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሀገራችን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ የተሰጠ መግለጫ
በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት በንጹሃን ዜጎች ላይ የህይወት እና ንብረት አደጋ ባደረሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ትግራይ ክልል ውጤታማ ሕግ የማስከበር ተልእኮውን በጀግንነት በመፈጸም ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ።
እነዚህ ሆን ተብሎ የሠራዊታችንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልእኮ ለማስተጓጎል ታስበው የተሠሩ የጥፋት ሴራዎች፣ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን እና በመከላከያ ሠራዊታችን የተቀናጀ ሥራ ሊከሽፉ ችለዋል።
አንደኛ በመተማ መስመር ለዘመናት አብረው በኖሩ የቅማንት እና የአማራ ተወላጆች መካከል የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን የፈዴራል እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ እና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተቀናጀ ሥራ በመሥራት የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ።
ሁለተኛ፥ በወለጋ ቡሬ መስመር፣ በጊዳ አያና፣ አንገር ጉቴ አዋሳኝ አከባቢዎች ለረዥም ጊዜ አብሮ በኖሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችን ሆን ብሎ ለማጋጨት ታስቦ የተደረገው ሙከራ በአከባቢው ኅብረተሰብ ትብብር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተችሏል።
ሦስተኛ፥ የሀገራችንን የገቢ እና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴን ለመገደብ በማሰብ፣ በሱማሌ እና የአፋር ኢሳ ሕዝቦችን ለማጋጨት የተሴረው ሴራ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን የተቀናጀ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር ለመዋል ችሏል።
አራተኛ፥ ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች በተለይም በዚህ ሁለት ሶስት ቀን በአጣዬ ከተማ እና በአከባቢው በታጠቁ ኃይሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ በዚህ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ይመኛል።
በዚህ የጸጥታ ችግር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና መሣርያ ይዘው በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ የከፈቱ፣ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ የገደቡ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ሠራዊታችን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን እየገለጽን፤ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የኅብረሰተሰቡን ሰላም በማወክ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።
በዚህም መሠረት፥ በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልል እና ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል። ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ሥራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥራን ይሠራል።
በዚህም መሠረት የአከባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል የሚከተሉት ክልከላዎች የተደረጉ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል።
1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ፣ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
2ኛ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግሥት ተቋማትን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጠልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ከላይ የተዘረዘሩትን እና ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለኅብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ድርጅት፣ የመንግሥት መዋቅር እና በድኖች ላይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ መታወቅ አለበት።
በመጨረሻም መላው ኅብረተሰባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሰለፍ ለገሀራችን ሰላም እና ደህንነት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ሚያዝያ 10፥ ቀን 2013 ዓ.ም.March 28, 2021 at 2:31 am #18804In reply to: ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች
AnonymousInactiveከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ባካሄደው የአንድ ሳምንት የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ።
ኮሚሽኑ የፀጥታ ሥራውን በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ የጋራ በማድረግ በተግባር ምዕራፉ የመጀመሪያ ሳምንት ባካሄደው ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሂደት ባከናወናቸው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባራት
- በተደራጀ መንገድ ታቅደው የሚፈፀሙ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች፣
- የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም አፈና እና ግድያ፣
- የተሽከርካሪ ስርቆት፣
- ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን መቀነስ መቻሉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ እንደገለፀው በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 359 ተጠረጣሪዎች ተከታትሎ በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥ
ትግራይ ላይ በተፈፀመው የጁንታው ጥቃት የተሳተፉና በተለያየ መንገድ አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በተለያየ የወንጀል ተገባር ሲሳተፉ በተገኘ የሕዝብ ጥቆማ 135 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰባት የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በማጣራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ በዘረፋና በግድያ ከተወሰዱ 10 ራይድ ተሽከርካሪዎች ስምንቱ እንደተያዙና የሁለቱ አካላቸው እንደተፈታ ፖሊስ ደርሶበት በቁጥጥር ስር አውሎ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እና የንግድ ስር-ዓቱን ለማዛባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በዚህ ኦፕሬሽን በቀጥጥር ስር አውሎ ከእነሱም ብዛት ያላቸው ሸቀጦችና ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባካሄደው በዚህ የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ንብረቶች መካከል በዝርፊያ የተወሰደ አንድ ሲኖ-ትራክ ከባድ መኪናንና ከግለሰቦች የተነጠቁና ከድርጅቶች የተዘረፉ ባርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመያዝ ለባለ ንብረቶቹ ተመላሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ሐሰተኛ መታወቂያ በመቀያየርና በመጠቀም በተለያዩ የተሽከርካሪ መሸጫ ድርጅቶች እየተቀጠሩ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች በማሰረቅ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች መያዛቸውንም ጨምሮ ገልጿል።
በመጨረሻም ኮሚሽኑ ይህ ከጅምሩ ውጤት ያስመዘገበ የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፆ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው የከተማው ህዝብ ለሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መረጃዎችን ባለመቀበልና ሀሰተኛ መረጃዎችንም ባለመጋራት እንዲሁም ለፖሊስ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት እንደተለመደው መረጃ በመስጠት እንዲተባበር እየጠየቀ ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት የከተማው ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ኮሚሽኑ ሌሎች የፀጥታ ሀይሎችንም በመወከል የላቀ ምስጋና ያቀርባል።
የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ምMarch 19, 2021 at 12:44 am #18664In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
ባልደራስ እና አብን ትብብርን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫየሀገራችን ሕዝብ ለዘመናት በተጫኑበት ኢዲሞክራሲያዊና አምባገነን አገዛዞች የተነሳ፥ በነፃነት እጦት፣በስቃይ እና በመከራ ኑሮውን እንዲገፋ ተደርጓል። ጭቆናን አስወግዶ የሚፈልገውን ፍትህ እና እኩልነት እውን ለማድረግ ከፍትኛ ዋጋ መክፈሉም እሙን ነው።
ይሁንና የሀገራችን የለውጥ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ ጅማሮው ሳይሳካ፥ ለቀጣዩ ዴሞክራሲያዊ ትግል ተስፋ ሊሆን የሚችል መሠረታዊ የትርክትና የመዋቅር ክለሳ እንኳ ሳይደረግ አምባገነንነትና ዘረኝነት የእጅ ለውጥ ብቻ እያደረጉ የሚፈራረቁባት ሆናለች። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለፈው ሕዝባችን አሁንም ዲሞክራሲን፣ እኩልነትንና ዘላቂ ሰላምን በመሻት ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል አጠንክሮ እንደቀጠለ ይገኛል።
የዚህ ዓይነት መልክና ይዘት ተላብሶ የተደራጀው የተፎካካሪ ኃይል ለሰርጎ ገቦች የተጋለጠ፣ በተፈጥሮው ደካማና ተሰባሪ ከመሆኑም በላይ የአምባገነኑን ሥርዓት ራዕይ አቀንቃኝ እስከመሆን ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በተጨማሪ የተቃውሞው ጎራ እርስ በርሱ በፍረጃና በሴራ መጠላለፍ ምክንያት በቁርሾ እንዲሞላ በማድረግ የጋራ ሀገራዊ ስምሪት መውሰድ እንዳይችል አድርጎት ቆይቷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ አምባገነኖችን በጋራ መታገል ጥረት ከማድረግ ወርደው በመናኛ ፍላጎቶችና በጥቃቅን ልዩነቶች ዙሪያ ታጥረው ሲሻኮቱ በመካከል የባከነው ጊዜ እና የሰው ህይወት የሚያስቆጭ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሀገራችንን ለእድሜ ልክ ዝቅታ የዳረጋት የጥላቻ ትርክት፣ ትርክቱን መሠረት አድርገው የተደነገጉ ሕግጋትና የተዘረጉ መዋቅሮች ተከልሰው መላ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት፣ በወንድማማችነት፣ በፍትህና በሰላም የሚተዳደሩነት ዘላቂ ሥርዓት በማስፈን በተለምዶ “መንታ ቅኝት” ያለው የትግል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የአብን ስትራቴጂክ ግብ መላውን ኢትዮጵያዊ የፍትሀዊ አማካኝ ተጠቃሚ በማድረግ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ማዕቀፍ እንዲፈጠር ሲሆን የድርሻውን ለማበርከት አበክሮ እየሠራ ያለ ንቅናቄ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ደግሞ የኢትዮጵያዊ ኅብር ዓይነተኛ መገለጫ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ከከፋፋይና ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ ለማድረግና ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል በሚል የተደራጀ ስለመሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ የኗሪዎቿ መሆኗን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የጋራ ትግል መነሻ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ፍትህንና እኩልነትን በማስፈን ላይ የተመሠረተ ሲሆን፥ አንዳች ቅቡልነት ያለው መርህ ወይም ምክንያት ማጣቀስ የማይችሉ ኃይሎች ከተማዋ የአንድ ንጥል ብሔር ንብረት መሆኗን በይፋ በመግለፅ የማታገያ አጀንዳ በማድረግ ሕዝቡ በነሱ ፍቃድና ይሁንታ መኖር እንዳለበት አድርገው ያወጁት ያልተገራ ፍላጎት የጋረጠበትን የህልውና ስጋት መቀረፍ እንዳለበት አብን እና ባልደራስ የጋራ ፖለቲካዊ አቋም ወሰደዋል።
የሀገራችን ኢትዮጵያ መድናና የመላ ሕዝቧ ሰላማዊ መኖሪያ ሆና ዘመናትን የተሻገረችው አዲስ አበባ መደበኛና ነባር ምልከታ ሊቸራት ሲገባ ከልቦለድ የመነጨ የዘረኞች “የልዩ ጥቅም”ቀንበር ጊዜ በረዘመ ቁጥር የሕግና የፖለቲካ ቋጠሮው እየጠበቀ መምጣቱና ይዘቱ “በኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በአዲስ አበባ መስተዳደር ስምምነት” እንደሚወሰን በተሻሻለው ቻርተር መደንገጉ ከተማዋንና ሕዝቧን ከአንድ ወገን በተሰባሰበ የፖለቲካ ኃይል ይሁንታ፣ ፍፁም ቁጥጥርና ጥበቃ ስር ለማዋል የተወሰነ መሆኑን ያሳያል። አብን እና ባልደራስ ይሄን አምባገነናዊ፣ ፍትህ አልቦ፣ ዘረኛ፣ አግላይና በመጨረሻም የግጭትና የብሔራዊ ደህንነት አደጋ የሆነ አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ ተሰልፈው ለመታገል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ትብብሩ በቀጣይ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት ለምንፈልገው የሀገራዊ በጎ ኃይሎች ጥምረት እርሾ ሆኖ እንዲያገለግል የታለመ ነው። አስቻይነት የሌለውና በሕግ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ጉዳይ በነባራዊ ተግዳሮቶች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን በማረጋገጥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመሳሳይ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዬች ባስተናገደበት ሁኔታ ትብብሩ ለህጋዊ እውቅና ሲቀርብ በመፍቀድና በመመዝገብ እንዲያፀድቀው የሚቀርብ ይሆናል።
በዚህ መነሻነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ትግል በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮችን የጋራ ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ በጋራ የምንሠራበት የፖለቲካ ትብብር ፈጥረን ለመሥራት መወሰናችንን ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ለመላው አማራ ሕዝብና ለአዲስ አበባ ሕዝብ ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው። ሌሎች ፓርቲዎችን ጨምሮ በሁለቱ ፓርቲ አመራሮች መሃከል ለወራት ሲካሄድ የነበረው ረዥምና አድካሚ ድርድር ፍሬ አፍርቶ መጪውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የአብን እና የባልደራስ ትብብር አሸናፊ ሆኖ መውጣት የሚያስችላቸውን የጋራ ስልቶች ቀይሰው በይፋ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
አብን እና ባልደራስ፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ሕዝብ በበደል ውስጥ አምጠው የወለዷቸው የቁርጥ ቀን ልጆቹ እንደመሆናቸው መጠን በተባባረ ክንድ በሕዝባችን ላይ የተጫነውን የመከራ ቀንበር እንዲወርድ ከመቼውም ግዜ በላይ በጋራ ትብብር ለመታገል በቁርጠኝነት ተሰልፈዋል።
አብን በጽንፈኞች የተሳሳተ ትርክት መነሻነት በአማራ ሕዝብ ላይ በተከታታይ የሚደርሰው ግፍ ድምጽ በመሆን በመጀመሪያው ረድፍ ሆኖ ትግሉን እየመራ ይገኛል። አብን የሀገራችን ኢትዮጵያን ደህንነት ለማረጋገጥና ህልውናዋን ለማስቀጠል አንድ ወሳኝ አምድ የሆነው የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ተፈርጆ የሚጠቃበትን የፅንፈኞች ስሁት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያስችል ልዩ ማዕቀፍ ሆኖ የተደራጀ ሲሆን ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስሪቱ በኢትዮጵያዊነት፣ ምልከታውም በወንድማማችነት፣ በፍትህና በዴሞክራሲ የተቃኘ ስለመሆኑ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው።
ከላይ በሰፊው እንደተመላከተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ላይ የተጋረጡ የህልውና አደጋዎችን ለመከላከል፣ የከተማዋ ሕዝብም ራሱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመረጣቸው እንደራሴዎቹ የመተዳደር መብቱን ለማስከበር ባሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በብቃትና በንቃት በነሳተፍ አያሌ መስዋዕቶችን በመክፈል የቀጠለ መሆኑን ራሱ ሕዝቡ በተግባር ኖሮ ያረጋገጠው ሀቅ ነው። ከላይ በተጠቀሱት መሠረታዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ግቦች ዙሪያ ሁለቱ ድርጅቶች በፅኑ የሚጋሯቸውን አቋሞች መሠረት በማድረግ ቀጣይ ለሚደረገው ጠንካራና የተቀናጀ የሕዝብ ትግል ወሳኝ የማታገያ አጀንዳ እንዲሆኑ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ በተለይም የአማራ ሕዝብና የአዲስ አበባ ሕዝብ የተደቀነባቸውን የህልውና አደጋ በትብብር ከመታገል ውጭ ሌላ ተጨባጭ የመፍትሄ አማራጭ እንደሌለ መተማመን ላይ ደርሰዋል።
ከዚህ ቀደም በጋራ አብረውን ለመሥራት ንግግር ጀምረው ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች በትብብሩ ለመዝለቅ ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ጊዜው አለመርፈዱን ተገንዝበው በጎ ፍላጎት ካሳዩን ከግማሽ መንገድ ባላይ ተጉዘን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
የፈጠርነው ትብብር አርአያ መሆን የሚችልና ከትላንት ለተሻለ አዲስ የፖለቲካ ባህል ማሳያ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ ከምርጫ በኃላም ትብብሩ ጎልብቶ፤ የሀገራችንን ሕዝብ ለዘመናት የቆየ የፍትህ ትግል ዳር ለማድረስ እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያዊ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍነት የሚመጥን አመራር ለመስጠት ለመፍጠር ከወዲሁ አብረን መቆም ጀምረናል።
አብን እና ባልደራስ የአዲስ አበባ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረው ከሚቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ትብብር በመፍጠር የከተማዋ ሕዝብ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ተወክሎ እንደሁሉም ሕዝብ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ትግል የማሳለጥ ሚና እንደሚኖረው ለማሳወቅ እንወዳለን።
አዲስ አበባ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባች፣ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ ብትሆንም፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተነሱ ተረኞች ከተማይቷን በልዩ ጥቅም ስም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቸኛ ንብረት ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጋራ አጥብቀን እናወግዛለን። በከተማይቱ እና ነዋሪዎቿ ላይ የተደቀነውን ይህ አደጋ ለመከላከል ባልደራስ በዋነኛነት እያካሄደ ያለውን ትግል አብን የሚያድንቅ እና በሙሉ ልብ ከጎኑ እንደሚሰለፍ ቃል ይገባል። በአንጻሩም ባልደራስ ፓርቲ በጽንፈኞች ሴራ ዒላማ እንዲሆን በተደረገው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና በደል ለማስቀረት በቁርጠኝነት አብን ለሚያደርገው ትግል ክብርና እውቅና እንደሚሰጥ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ስምምነታችን የተበላሸውን የሀገራችንን ፖለቲካ ባሕል በማስተካከል፣ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል አብሮ መቆም እንደሚገባ ከማሳየት ባሻገር፥ ሌሎች ለተመሳሳይ አላማ ያነገቡ ፓርቲዎችም ይህን ፈለግ ተከትለው የትብብሩ አካል እንዲሆኑ ፅኑ ፍላጎት አለን።
በመጨረሻም በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ጽንፈኛ ኃይሎች በሚፈጽሟቸው የሽብር ድርጊቶች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ለማስቆም በየእርከኑ ያሉ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች ተግተው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን።
በተለይ ችግሩ ተባብሶ በሚገኝባቸው የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል እና አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ችግሩን የሚመጥን ኃላፊነት በመውሰድ ንፁኃንን ከጥቃት እንዲከላከሉና ወንጀለኞችን ለሕግ እንዲያቅርቡ በአፅንኦት እንጠይቃለን።
መሠረተ-ቢስ በሆነ ክስ ተወንጅለው ለእስር የተዳረጉትንና የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን የተነፈጉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እናሳስባለን። ትህነግ በለኮሰው ጦርነት በትግራይ ክልል ሕግ ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የንጹኃን ዜጎቻችንን ደህንነት እና የሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ልዩ ትኩረት እንዲደረግና የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እንወዳለን።
መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም.
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/March 10, 2021 at 1:04 am #18520In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት የሕልውና አደጋ በአቶ ልደቱ አያሌው እይታ
ስንብት፥ ለመሰንበት
ልደቱ አያሌው
የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም.ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሕልውና አደጋ ውስጥ ትገኛለች። ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የአቅምና የቅንነት ድክመት ያለበት በመሆኑ ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ከማቃለልና ከመፍታት ይልቅ፥ የበለጠ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። በዚህም ምክንያት ሀገራችን ሕልውናዋን የሚፈታተን አሳሳቢ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከመግባቷም በላይ፥ ከኤርትራና ከሱዳን መንግሥታት ግልጽ ወረራ ተፈጽሞባታል። ከታሪኳና ከማንነቷ በተቃራኒም ይህንን ግልጽ ወረራ ለመቀልበስ የሚያስችል አቅምና ወኔ ያጣች ደካማ ሀገር ሆናለች። ይህ ክስተት ሀገሪቱ ምን ያህል በሂደት ውስጣዊ አንድነቷ እየተዳከመ እንደመጣና ወደ መበታተን አደጋ ውስጥ እየገባች ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው።
ብልጽግና ፓርቲ እያራመደ በሚገኘው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ምክንያትም ሀገራችን ለከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ተጋላጭ በመሆን ብሔራዊ ጥቅሞቿንና ሉዓላዊነቷን በአግባቡ ማስከበር የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብታለች። ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉም ሀገራዊ ሕልውናችንን በሚፈታተን መጠን ኢኮኖሚያችን ወደ ጥልቅ ቀውስና ኪሣራ ውስጥ እየገባ ይገኛል።
ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በብዙ የሕይወት መሥዋዕትነት የተገኘውና የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ተጀምሮ የነበረው የለውጥ ሂደት በአመራር ድክመትና በአምባገነናዊ ባህርይ ምክንያት እንዲከሽፍ በመደረጉ ነው። በሥልጣን ላይ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ ለለውጡ መምጣት ምክንያት የሆኑትን ፖለቲካዊ ችግሮች ሕጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ አግባብ ከመፍታት ይልቅ አማራጭ ሀሳቦችን በማፈን፣ በፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድና የፈጠራ ክስ በመመሥረት፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ተቀናቃኞቹን በማሰርና ‘ለሕልውናዬ ስጋት ናቸው’ ብሎ የሚፈራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ሕጋዊ ዕውቅና በመሠረዝ ጭምር ካለፈው የ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ ሥርዓት የባሰ እንጂ የተሻለ አለመሆኑን በተግባር አሳይቷል። ባጭሩ፥ ሀገራችን ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ ወይም በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እየተመራች ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ የባሰ ቀውስ የመሸጋገር እንጂ ወደ በጎና የተሻለ ሥርዓታዊ ለውጥ የመሸጋገር ዕድል እንደሌላት በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ ሆኗል።
እኔም ሆንኩ አባል የሆንኩበት ፓርቲ፥ በአንድ በኩል የተጀመረው የለውጥ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ ምን ዓይነት መዋቅራዊ ለውጦች በቅደም ተከተል መካሄድ እንዳለባቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት የተጀመረው የለውጥ ሂደት ከከሸፈ በሀገራችን አጠቃላይ ሕልውና ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ምን ያህል ከባድና አደገኛ እንደሚሆን የሚያሳስብ የሀሳብ ትግል ላለፉት ሦስት ዓመታት ስናካሂድ ቆይተናል።
ነገር ግን የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካ በዕውቀት፣ በምክንያታዊነትና በሐቀኝነት የሚካሄድ ሳይሆን ብሔርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ሤረኝነት፣ ጥላቻና ውሸት የነገሠበት በመሆኑ ጩኸታችን የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። ሆኖም ቀደም ብለን ስናቀርበው የነበረው ስጋት ከተራ ሟርተኝነት ሳይሆን፥ ከተጨባጭ የፖለቲካ ግምገማ፣ ግንዛቤና ትንታኔ የመነጨ ስለነበር እንደፈራነው የለውጥ ሂደቱ ከሽፎ አሁን ሀገሪቱ ወደባሰና ውስብስብ የሕልውና አደጋ ውስጥ ገብታለች።
የለውጥ ሂደቱን መክሸፍ ተከትሎ ሀገራችን ወደ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት የገባችና በውጭ ኃይሎች ወረራ ሥር የወደቀች ቢሆንም፥ ግብዞቹ የብልጽግና አመራሮችና የእነርሱ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆኑ ተከታዮቻቸው ግን ዛሬም ጭምር ሀገሪቱ ወደላቀ የብልጽግና ጎዳና እየገሰገሰች እንደሆነ ሊነግሩን ሲደፍሩ እያየን ነው። ብልጽግና ፓርቲ የከሸፈን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የሚካሄድ ሀገራዊ ምርጫ፥ የተጨማሪ ቀውስ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የፖለቲካ ችግሮች የሚያስገኘው ምንም ዓይነት አዎንታዊ ፋይዳ የሌለ መሆኑን መገንዘብ ተስኖት የሥልጣን ቅቡልነት ልባስ ለመደረብ ሲል ብቻ ትርጉም የለሽ ምርጫ ለማካሄድ እየተጣደፈ ይገኛል። ይህም ሀገሪቱ ወደባሰና ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ የፖለቲካ ቀውስ ልትገባ ትችላለች የሚል ተጨማሪና ምክንያታዊ ስጋት ፈጥሯል።
በእኛ በኩል ውጤታማ ሽግግር ባልተካሄደበትና አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በችኮላ ወደ ምርጫ ውስጥ መግባት አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው የሚል የጠነከረ አቋም ያለን ቢሆንም፥ ምርጫው መካሔዱ የማይቀር ከሆነ ግን ቢያንስ በምርጫው ሂደት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ ለመቀነስ በሚያስችል አግባብ በምርጫው ተሳታፊ ለመሆን በዝግጅት በማድረግ ላይ ነበርን።
ነገር ግን ከሁሉም ነገር በላይ ሀሳብን አብዝቶ የሚፈራውና ከሀገሪቱ ደኅንነት በላይ ለራሱ የሥልጣን የበላይነት ሰፍሳፋ የሆነው የወቅቱ መንግሥት በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሂደት ተሳትፎ እንዳይኖረን ስለፈለገና ስለወሰነ በሕገ-ወጥ መንገድ ፓርቲያችን እንዲሰረዝና ከትግሉ ሜዳ እንዲወገድ አድርጓል።
በእኔ ላይም በባለቤትነት በሚቆጣጠራቸውና ለልዩ ተልዕኮ ባቋቋማቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ቅጥረኞቹን አሰማርቶ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ፣ የዛቻና ማስፈራራት ድርጊት በመፈጸም፣ የፈጠራ ክስ በመመሥረትና በሕገ-ወጥ መንገድ በማሰር የትግል ተሳትፎዬን ለመገደብ ሞክሯል። ይህም አልበቃ ብሎት በፖለቲካ መድረኩ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወትም እንዳልኖር ስለፈለገ፥ ያለምንም ሕጋዊ ድጋፍ ያለብኝን ከፍተኛ የልብ ሕመም ወደውጭ ሀገር ሄጄ እንዳልታከም እገዳ ጥሎብኛል። ይህ ሕገ-ወጥ እገዳ እንዲነሳልኝ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትንና ባለሥልጣናትን ለማነጋገርና ለመማጸን ያደረግኩት ጥረትም ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማድረግ የነበረኝ ቀጠሮ በመስተጓጎሉ በእያንዳንዱ ሰዓትና ዕለት ሕይወቴ ለዕልፈት ሊጋለጥ በሚችልበት አደጋ ውስጥ እገኛለሁ። በዚህ ድርጊቱም የወቅቱ መንግሥት አምባገነናዊ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ኢ-ሰብአዊ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በርግጥም ሥርዓቱ ከግለሰብ ግድያ ጀምሮ እስከ የሕዝብ ጅምላ ጭፍጨፋ ከሚደርስ ቀውስ የፖለቲካ ትርፍ ለመቃረም የሚጥር ኃይል በመሆኑ በእኔ ላይ ይህንን ማድረጉ እምብዛም አያስደንቅም።
ሰሞኑን የምገኝበትን አሳሳቢ የጤና ሁኔታ በተመለከተ ከሐኪም ጋር ባደረግሁት ምክክርም ለሕመሜ አስተማማኝ ሕክምና እስካገኝ ድረስ በአካሌም ሆነ በአዕምሮዬ ላይ ምንም ዓይነት ጫናና ውጥረት የሚፈጥር ሥራ እንዳልሠራና በቂ ረፍት እንዲኖረኝ ከባድ ማስጠንቀቂያና ምክር ተሰጥቶኛል። ጤናዬ ከሚገኝበት አሳሳቢ ደረጃ (risk) አኳያ በሕይወት ለመሰንበት የምፈልግ ከሆነ፥ ለጊዜው ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ይህንን ማድረግ እንደሆነ ተነግሮኛል።
ሀገራችን የምትገኝበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በእኔ በኩል አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ አግኝቼና ጤናዬ ተስተካክሎ በትግሉ ሂደት የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረኝ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረኝና አሁንም ያለኝ ቢሆንም የሕክምና እርዳታ እንዳላገኝ ራሳቸውን በፈጣሪ ቦታ ሊተኩ በሚፈልጉ ገዥዎች በመከልከሌ ምክንያት ይህንን ምኞቴን ማሳካት የማልችልበት እንቅፋት ገጥሞኛል። ስለሆነም ተገቢውን የሕክምና እርዳታ አግኝቼ ጤናዬ እስኪመለስ ድረስ በሕይወት የመሰንበት ዕድሌን ለመሞከር ስል ከማንኛውም ዓይነት የትግል እንቅስቃሴ (ገንዘብ ወይም ምክር ከማዋጣት ባለፈ) ራሴን ለጊዜው ለማቀብ የተገደድኩ ስለመሆኑ በከፍተኛ ቁጭትና ሐዘን እገልጻለሁ።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰማኝ ቁጭትና ሐዘን ልብን የሚሰብር የሆነብኝ ያለምክንያት ሳይሆን፥ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕልውና አደጋ ውስጥ በገባችበትና ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ከአቅሜ በላይ በሆነ የጤና ችግር ምክንያት ራሴን ከትግሉ ሜዳ ለማግለል መገደዴ ያልጠበቅሁትና ከፍላጎቴ ውጭ የሆነ መጥፎ ገጠመኝ ስለሆነ ነው።
የሆነው ሆኖ ይህንን መጥፎ አጋጣሚ እንደ አንድ ጊዜያዊ ስንብት ልቁጠረውና ስለ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ሕዝቡ ግንዛቤ ሊወስድ ይገባዋል ብዬ በማምንባቸው በሚከተሉት ስምንት ነጥቦች ዙሪያ የሚሰማኝን በመግለጽ ለመሰናበት ልሞክር።
- ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለንም
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለገጠማት የሕልውና አደጋ በአስተሳሰብና በመዋቅር ደረጃ ዋናዎቹ ተጠያቂ ምክንያቶች የጽንፈኝነት ፖለቲካ፣ ብሔርተኝነትና የፖለቲካ አመራር ድክመቶች ናቸው። ስለሆነም ለወቅቱ የለውጥ ሂደት መክሸፍ ዋናው ተጠያቂ የእነዚህ መዋቅራዊ ድክመቶች ሰለባ የሆነው የቀድሞው ኢሕአዴግ፣ የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ ነው።
ብልጽግና ፓርቲ በእጁ የገባውን ወርቃማ የለውጥ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ሳይችል የቀረበት ተጨማሪ ምክንያትም ፓርቲው ከሀገሪቱ ጥቅምና ደኅንነት በላይ ለራሱ የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ውስጣዊ አንድነቱን በማዳከሙና ወደ የእርስ በርስ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ በመግባቱ ነው። የፓርቲው ውስጣዊ ክፍፍል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ላሉ የእርስ በርስ ግጭቶችና በትግራይ ክልል ለተከሰተው ጦርነት ዋናው ምክንያት ሲሆን፥ ውስጣዊ ችግሩ አሁንም የተሻለ ትኩረት አግኝቶ ካልተፈታ በስተቀር ሀገሪቱን ለባሰ ቀውስና ጦርነት የሚዳርጋት ይሆናል። የራሱን ውስጣዊ ችግር መፍታት ያልቻለና ከራሱ የፖለቲካ ሥልጣን በላይ የሀገሪቱን ጥቅም ማስቀደም የተሳነው ደካማ ገዥ ፓርቲ የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ ሊያደርግም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት አይችልም።
ቀደም ሲል ብልጽግና ፓርቲ ይህንን መሠረታዊ ድክመቱን አምኖ በመቀበልና በማረም ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት ይችላል የሚል ግምት (ምናልባትም የሞኝነት) የነበረን ቢሆንም ግምታችን ስህተት እንደነበር ያለፉት ሦስት ዓመታት ሂደት በተግባር አሳይቶናል። በዚህም ምክንያት ብልጽግና ፓርቲ እንደ ፈጣሪውና አሳዳጊው ህወሓት ሁሉ፥ ከመሞት መዳን ያለመቻል መዋቅራዊ ችግር ያለበት ግትርና ጀብደኛ ድርጅት እንደሆነ መገንዘብ ችለናል። ምክንያቱም ብልጽግና ፓርቲ አምባገነን የሆነው አምባገነን እንዲሆን ያስገደዱት ነባራዊ ሁኔታዎች ስላሉ ሳይሆን በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ አምባገነን መሆንን የመረጠ ድርጅት ስለሆነ ነው።
ከይቅርታ ጋር፥ እዚህ ላይ በከፍተኛ ድፍረትና ርግጠኛነት ልናገር የምችለው፥ የ21ኛዋን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን የማክያቬሊ የፖለቲካ ሤራ ስልት (conspiracy theory) እና የንግርት አምልኮት ለመግዛት እየሞከረ ያለው ብልጽግና ፓርቲ አሁን በያዘው አቅጣጫ መጓዝ ከቀጠለ ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን የማፍረስ እንጂ ወደ ዘላቂ ለውጥ የማሸጋገር ሚና ከቶውንም ሊኖረው አይችልም። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ የገባንበትን ከባድ ጦርነት፣ በኤርትራናና በሱዳን መንግሥት የተፈጸመብንን ወረራ፣ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብጽና ከሱዳን ጋር የገባንበትን ፍጥጫ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየተፈጸመ የሚገኘውን የሕዝብ መፈናቀልና የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በገዥው ፓርቲና በበርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚታየውን ፍጥጫ፣ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እየደረሰብን ያለውን ከባድ ተጽዕኖ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለብን ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ፣ ከፊታችን እየመጣ ያለውን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና ሌሎች ተመሳሳይ ፈተናዎቻችንን በጥቅሉ ደምረን ስናያቸው እንኳንስ ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን ሆኖ ሁላችንም ተባብረን በአንድነት ብንቆም የወቅቱን የሀገሪቱን ፈተና በቀላሉ መወጣት አዳጋች ነው። ስለሆነም የውስጥ ችግራችንን ፈተን በአንድነት እስካልቆምን ድረስ በብልጽግና ፓርቲ የተናጠል ጥረት ችግራችን ፍጹም ሊፈታ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል።
- ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰብና በሞራል ዝቅታ ላይ የምንገኝበት ነው
የምንገኝበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጭካኔን፣ ጅምላ ግድያን፣ የሤራ ፖለቲካን፣ የጥላቻ ንግግርን፣ ውሸትንና የግለሰብ አምልኮትን እየተለማመድን የምንገኝበት ነው። እነዚህን እኩይ ተግባራት በፊት አውራሪነት እያለማመደን የሚገኘው መንግሥት ሲሆን፥ ጋሻጃግሬዎቹ ደግሞ ሀይማኖተኛ፣ ብሔርተኛና ምሁራን ነን ባይ “ልሂቃን” መሆናቸውን እያየን ነው።
በርግጥም ወቅቱ የ“ዝቅታችን” ወቅት ነው። ለአንድ “ህወሓት” የተባለ አምባገነናዊ የሆነና በሕዝብ ትግል ከሥልጣን ለተወገደ ኃይል ባለን ገደብ የለሽ ጥላቻ ምክንያት ዓይነልቦናችን ታውሮ የዛሬ ገዥዎቻችን በሕዝብና በሀገር ላይ እየፈጸሙት ያለን የዛሬ ግፍና በደል ፈጽሞ ማየትና መረዳት ተስኖናል። የወቅቱ ገዥዎቻችን ለራሳቸው የሥልጣን የበላይነት ሲሉ በሀሰትና በአስመሳይነት በጥብጠው የሚግቱንን ሥልታዊ ፕሮፓጋንዳ፣ በሀገር ጥቅምና በሕግ ማስከበር ሰበብ እየፈጸሙት ያለን በውጤቱ ሀገር በታኝ የሆነ የሤራና የበቀል ተግባር መገንዘብ ተስኖን እንደ ሕዝብ የአዲስ አምባገነናዊ ኃይል አዋላጅና ወላጅ ሆነናል። እወደድ ባይና ደካማ በሆነው የብልጽግና ፓርቲ አመራርና ተከታዮቹ በሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለው የጋራ አጀንዳ፥ በዋናነት ህወሓትን በመጥላትና በመበቀል ዙሪያ የተቃኘ ቢሆንም፥ ዋናውና የጋራ መገለጫቸው የሆነው ባሕርያቸውና ግብራቸው ግን የህወሓት አውዳሚ አመለካከትና ውርስ (legacy) አራማጅና አስቀጣይ መሆን ነው። እነዚህ ግብዝ ኃይሎች በህወሓት መንገድ መጓዝ ህወሓት በከፋፋይ አጀንዳው ያዳከማትን ሀገር ለይቶላት እንድትፈርስ ከማድረግ ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ መገንዘብ ተስኗቸዋል። ይህም በራሱ ኢትዮጵያውያን ከሌሎችም ሆነ ከራሳችን ያለፈ ስህተትና ውድቀት የመማር አቅማችን እጅግ አናሳ መሆኑን ያሳያል።
በአጠቃላይም ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በራሳችን ታሪክ፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ሰላም፣ የወደፊት ዕድገትና ጥቅም ላይ ራሳችን ጦርነት ያወጅንበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል። በአጭሩ የራሱን ፍላጎትና ዘለቄታዊ ጥቅም የማያውቅ ግብዝ ሕዝብ ሆነናል። ከገባንበት ዝቅጠት ጥልቀትና ስፋት አኳያም አንዳንዶች “ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተጨራርሰን ከምንጠፋ በስምምነት ተለያይተን መኖር የምንችልበት ዕድል ይኖር ይሆን?” ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ የተገደዱበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያውያን እንደ “ሕዝብ” በዚህ ዓይነት የአስተሳሰብና የሞራል ዝቅታ ላይ እንደምንገኝ ተገንዝበን ስክነትና ብስለት ወደተላበሰ የፖለቲካ አቅጣጫ በፍጥነት ካልገባን በስተቀር ሀገራችንን ከገጠማት የመፈራረስ አደጋ ልንታደጋት አንችልም። እጅግ አማላይና መሠሪ በሆነው የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ ስልት ሰለባ በመሆን፣ ወይም በአድር ባይነት፣ ወይም በጥቅመኝነትም ሆነ በማንኛውም ሌላ ምክንያት የወቅቱን ሥርዓት እየደገፍን የምንገኝ ዜጎች በታሪክና በትውልድ ፊት የየራሳችን የተጠያቂነት ድርሻ እንደሚኖርብን ተገንዝበን፥ ሥርዓቱን መቃወምና መታገል ቢያቅተን እንኳን ቢያንስ ዝም በማለት የሀገሪቱ ጥፋትና ውድቀት ቀጥተኛ ተጋሪ ከመሆን ልንቆጠብ ይገባል።
- በይስሙላ ምርጫ የሚፈታ ችግር የለንም
ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ውጤታማ የሽግግር ሂደት ባላካሄድንበት ሁኔታ የሚካሄደው የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ ሂደትም ሆነ ውጤት የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ የበለጠ የማባባስ እንጂ የመፍታት አንደምታ አይኖረውም። ምርጫው ሳይጀመር ያለቀና ውጤቱም ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ ማስገባት ወይም አምባገነናዊነትን ማጽናት መሆኑ አስቀድሞ የታወቀ ነው። ይህ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በማንኛውም መንገድ አሸናፊ ሆኖ በሥልጣን ላይ ለመቀጠል ወስኖና ተዘጋጅቶ የገባበት ምርጫ ስለሆነ፥ የዚችን ደሃ ሀገር በጀት ከማባከን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በአጭሩ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንደማይሆን ሳይሆን እንዳልሆነ የቅድመ ምርጫው ሂደት በማያሻማ ሁኔታ አሳይቷል። የወቅቱ የፖለቲካ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በአንጻራዊነት ነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነትና በእኩልነት ምርጫ የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅን ለማስፈን፣ ብሎም ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ በሚያስችል ሁሉን አቀፍ በሆነ የሽግግርና የሀሳብ ግብይት ሂደት (national dialogue) ነው እንጂ በተለመደው ዓይነት የታይታ የምርጫ ግርግር አይደለም።
ወደ መዋቅራዊና ዘላቂ ለውጥ ለመግባት ከተፈለገ መፍትሔው የችኮላ ምርጫ ማካሄድ ሳይሆን በቅድሚያ ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በመላው ሀገሪቱ የታሠሩ የፖለቲከኛ እስረኞችን መፍታት፣ ዜጎች ላይ የሚደረግ አፈናና ግድያን ማስቆም፣ የሀገሪቱ ሕግጋትና ተቋማት ሀገር ጠቀም በሆነ አግባብ እንዲሻሻሉ ማድረግና ቢያንስ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት የታየው ዓይነት የዕርቅና የመቻቻል መንፈስ በሀገሪቱ እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል።
- ልዩ ትኩረት አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ
በተግባር እየተፈጸመ ከሚገኘው ግልጽ ድርጊት እንደምንረዳው ብልጽግና ፓርቲ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ ሳይሆን በአፈናና በኃይል በሥልጣን ላይ ለመቀጠል የወሰነ አምባገነን ኃይል ነው። ገዥው ፓርቲ የሚጠላቸውንና የሚፈራቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካ መድረኩ በማስወገድና የፓርቲ አመራሮችን በማሰር በወሰደው እርምጃ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንዳልሆነ ከወዲሁ በተግባር አረጋግጧል። ሆኖም ምርጫው በታሰበበት ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሂደቱ ከማግለል ይልቅ አቅማቸውና ሁኔታው በፈቀደላቸው መጠን በምርጫው ተሳታፊ ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል እላለሁ።
ነገር ግን በቂ ዝግጅት አድርገውና የገዥውን ፓርቲ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በብቃት ተቋቁመው በሀገር ደረጃ መንግሥት ለመሆን በሚያስችል መጠን ምርጫውን ለማሸነፍ የሚኖራቸው ዕድል እጅግ ጠባብ መሆኑን በመገንዘብ ሙሉ ትኩረታቸውን አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አዲስ አበባ ከተማን አሸንፎ ለመረከብም አንድነት ተኮር የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመተባበር ጉዳይ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀርብበት የማይገባና ምትክ የለሽ እርምጃ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ግለሰብን በመጥላት የሀገርን ጥቅም ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ከማንኛውም ኃላፊነት ከሚሰማው ፓርቲ የማይጠበቅ ተግባር ቢሆንም ምናልባት የእኔ ለጊዜውም ቢሆን ከምርጫውና ከትግሉ ሂደት ገለል ማለት ለተቃዋሚው ጎራ መተባበር አንድ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።
የአንድነት ኃይሉ ምንም ዓይነት ድምጽ ሊባክን በማይችልበት ሁኔታ እርስ በርስ ላለመፎካከር አስቀድሞ ካልተስማማ በስተቀር፥ ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ (በፓርቲም ሆነ በግል የሚወዳደሩ) አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል እንደሚኖራቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል ካገኙም የአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ሕልውና አደጋ ውስጥ እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በምርጫ 97 ሲሆን እንደታየው “ምርጫው ስለተጭበረበረ ያሸነፍነውን ወንበር ወይም ምክር ቤት አንረከብም” በሚል የተሠራው ታሪካዊ ስህተት በዘንድሮውም ምርጫ እንዳይደገም ፓርቲዎች ከወዲሁ በጉዳዩ ላይ መተማመንና መወሰን ይኖርባቸዋል።
- መፍትሔው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት መፍጠር ነው
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በሁለት የጎረቤት ሀገራት (በኤርትራና ሱዳን) ሉዐላዊነቷ ተደፍሮ የግዛት ወረራ ተፈጽሞባታል። ይህ ወረራ ከማንኛውም ውስጣዊ ችግሮቻችን በላይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠውና በአስቸኳይ ሊቀለበስ የሚገባው ነው። ይህንን ማድረግ ሳንችል ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገርና ሕዝብ የነጻነት ታሪክም ሆነ ሉዐላዊ ሕልውና አለን ብለን መናገር አስቸጋሪ ይሆናል። የወቅቱ መንግሥት በሀገር ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ ማስቆምም ሆነ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበር ስላለመቻሉ የሚያቀርበው ማንኛውም ምክንያትም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የወቅቱ መንግሥትም ሆነ መንግሥትን በዋናነት የሚመሩት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እነዚህን ሁለት ቁልፍና መሠረታዊ የአንድ መንግሥት ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት ስላልቻሉ ከእንግዲህ የሚኖራቸው ብቸኛ አማራጭ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ሀገራዊ የሀሳብ ግብይት ሂደት (national dialogue) መጀመርና ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት ማካሄድ ነው።
የወቅቱ መንግሥት ቀደም ሲል በኢሕአዴግ ስም፣ አሁን ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ስም ሕዝባዊ ይሁንታ ሳይኖረው ለ30 ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለ ኃይል ነው። ይህ መንግሥት የሀገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ካለመቻሉም በላይ ይበልጥ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። ስለሆነም የወቅቱ ብልጽግና ፓርቲ በአንድ በኩል የሀገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር ባልቻለበት ሁኔታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ አካሒዶ የሕዝብ እውነተኛ ውክልና ለማግኘት በሐቅ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን በቋሚ ርስትነት ይዞ ሊቀጥል አይገባውም።
ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ከግለሰብ በላይ የሆነ ሚና አለኝ ብሎ የሚያምንና ድክመቱ የኔ ሳይሆን የመሪዎቼ ወይም የመሪዬ ነው ብሎ የሚያስብ ከሆነም ሀገሪቱ ለይቶላት ከመፍረሷ በፊት መሪዎቹን ወይም መሪውን የመቀየር ርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን ለሀገሪቱ ውድቀት ፓርቲውም እንደ ድርጅት ተጠያቂ ይሆናል።
ከዚህ ውጭ በአንድ ሀገር የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና የውጭ ወረራን መከላከል ያልቻለ ማንኛውም መንግሥት በሥልጣን ላይ መቀጠል የሚችልበት ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት የለም። ከዚህ በተጻራሪ የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ መከላከል ያልቻለ መንግሥት፥ “ሌላ አማራጭ የለንም” በሚል ሰበብ በሥልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችለው ኢትዮጵያ ሕልውናዋን ከጥፋት አድኖ የሚያስቀጥላት ትውልድና ዜጋ ያልፈጠረች መካን ሀገር መሆኗን አምነን ከተቀበልን ብቻ ይሆናል።
በተጨማሪም በቅርቡ ትግራይ ክልል ውስጥ የገባንበት ጦርነት የሀገሪቱን አንድነት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ የሚጥልና ከኛ ዘመንም አልፎ ምናልባትም ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ጣጣ የሚያስከትል አሳሳቢ ክስተት ነው። ስለሆነም ይህ ችግር በዘላቂነት በጦርነት ሊፈታ እንደማይችል በመገንዘብ ከሥልጣን ጥያቄ፣ ከበቀል፣ ከስሜትና ከጀብደኝነት በራቀ አተያይ ለችግሩ አስቸኳይ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል።
- ሀገሪቱን ከሕልውና አደጋ መታደግ የሚችል ጠንካራ ፓርቲ መፈጠር አለበት
ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም በሀገሪቱ በጎ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ የምንመኝና የምንፈልግ ቢሆንም ይህንን የሁልጊዜ ምኞታችንን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራና ለመርህ ታማኝ የሆነ ፓርቲ መፍጠር እስካሁን አልቻልንም። ዛሬም እንደ ትናንቱ የሥርዓቱን ድክመቶችና ጥፋቶች ስንቆጥር የምንውል የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ብንኖርም ያለጠንካራ ፓርቲ መኖር ሀገሪቱን ከጥፋት መታደግም ሆነ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል መገንዘብ የቻልን አይመስልም። በምሬት፣ በጩኸትና በውግዘት ብቻ ሊመጣ የሚችል ዘላቂ ለውጥ እንደማይኖር ተገንዝበን ለመጭው ትርጉም የለሽ ምርጫ ከምንሰጠው ትኩረት በላይ ለሀገሪቱ ችግሮች የሚመጥን ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ በመፍጠር ሥራ ላይ ማተኮር አለብን። በተለይም አንድነት ተኮር የሆነው የፖለቲካ ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ በተዳከመበትና በተበታተነበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል አስተማማኝ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል በመገንዘብ አዲሱ ትውልድ ዋና ተዋናይ የሚሆንበት ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ መፍጠር ቀዳሚና ለነገ የማይባል አጀንዳችን መሆን ይገባዋል እላለሁ። ይህንን ማድረግ ካልቻልን “አማራጭ የለም” በሚል ሰበብ አምባገነኖችና የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ፓርቲዎች ወይም መሪዎች ሁልጊዜም በሥልጣን ላይ የሚቀጥሉበትን ዕድል እንፈጥራለን።
- የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ለሰላም
የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ በብዙ ውጥረቶች የተሞላና በቀላሉ ተሰባሪ ነው። በዚህ ምክንያት ውጤታማ በሆነ የሽግግር ሂደት ሳይታለፍ የሚካሄደው መጪው ምርጫ ሀገራችንን ወደ ባሰ ግጭትና ትርምስ ሊያስገባ የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ። ይህ ስጋት በቂ መነሻ ምክንያት ያለው መሆኑን በመረዳት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የምርጫ ሂደቱ ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዳያመራ የማድረግ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን በመገንዘብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበትና የሰከነ ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ሊያካሒዱ ይገባል። አሁን ከምንገኝበት እጅግ ከባድና ውስብስ የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር የሰላም እጦት የሀገሪቱን ሕልውና የሚፈታተን አደጋ ይዞብን ሊመጣ ስለሚችል፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫውን አሸናፊ ለመሆን ከመሥራት በላይ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።
በአግባቡ ካልተጠቀምንበትም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለው ማኅበራዊ ሚዲያ የብሔራዊ ደኅንነታችን ዋና የአደጋ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ይህንን እውነታ በመገንዘብ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎቻችን በምርጫው ወቅት የሚኖራቸው ሚና ለሰላም ቅድሚያ በሚሰጥ የኃላፊነት ስሜት ሊካሄድ ይገባዋል። በአጠቃላይ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በውስጥም በውጭም ከፍተኛና አሳሳቢ ውጥረት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል።
- ሕገ-መንግሥቱ ሳይሻሻል የፖለቲካ ችግራችን አይፈታም
የወቅቱ የሀገራችን የፖለቲካ ችግር የሀገራዊ ብሔርተኞችንና የንዑስ ብሔር ብሔርተኞችን የተካረረ የፖለቲካ ቅራኔ በአንጻራዊነት በሚያቻችል አግባብ የወቅቱን ሕገ-መንግሥት ከማሻሻል ባነሰ ሌላ የመፍትሔ ርምጃ ሊፈታ አይችልም። ሕገ-መንግሥቱ እስካልተሻሻለ ድረስ ከማንነት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የተነሱትም ሆነ ወደ ፊት ባልተቋረጠ ሁኔታ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች የሀገሪቱን ሰላምና ሕልውና እያወኩ መቀጠላቸው አይቀርም። ይህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስም የሀገሪቱ ሰላም፣ አንድነት፣ ሕልውናና የኢኮኖሚ እጥረት በዘላቂነት መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም።
ከዚህ ግንዛቤ ጋር በተያያዘ በኔ በኩል ለውይይት መነሻ የሚሆን የሕገ-መንግሥት አማራጭ ረቂቅ ሰነድ በመጽሐፍ መልክ በማሳተም ላይ እገኛለሁ። የሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ለሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፈታት የሚኖረውን ምትክ የለሽ አዎንታዊ አስተዋዕፆ የምትገነዘቡ መገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ዜጎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት በማድረግ ትችት እንድታቀርቡበትና እንድታዳብሩት፣ ከተቻለም ሰነዱን በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሂደት የጋራ የትግል አጀንዳ አድርጋችሁ እንድትጠቀሙበት በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም ከአቅም በላይ በሆነ የጤና ምክንያት ቢሆንም ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ለጊዜውም ቢሆን ከትግል ተሳትፎዬ ለመታቀብ በመገደዴ፥ የትግል አጋሮቼንና የዐላማ ደጋፊዎቼን ሁሉ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይህንን የምለው ከእኔ ብዙ እንደምትጠብቁና ለእኔ ለራሴ እንደሆነብኝ ሁሉ ለእናንተም ይህ ክስተት ድንገተኛ መርዶ እንደሚሆንባችሁ ስለምገነዘብ ነው። ወደፊት የጤና ሁኔታዬ ተሻሽሎ እስከመጨረሻው በፖለቲካ ሂደቱ ለመቀጠል ለራሴ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም ፈጣሪ ዕድል እንደሚሰጠኝ ተስፋ እያደረግኹ ሀገራችን ኢትዮጵያ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማት ያለኝን ልባዊ ምኞት በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ።
ልደቱ አያሌው
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
March 9, 2021 at 2:07 am #18505In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ
አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አድርገዋል።
በጉብኝቱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገብረመድኅን፣ ሜ/ጀነራል ገብረመድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተው ታሳሪዎችን አነጋግረዋል። እንዲሁም ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል። ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል። የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው፣ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች አሉ። አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል። ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል። በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው ደረጃ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች ላይ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የወንጀል ምርመራውን በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ እና የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
February 14, 2021 at 4:44 am #18207In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ወረራ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ
“ከድንበሩ ቆሞ ጌታ ካልመለሰው፥
መሬትም ይሄዳል እግር አለው እንደ ሰው።”የሀገራችን ዳር ድንበር በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ደምና አጥንት ተለስኖ የተሠራ የማይነቃነቅ አምድ እንጂ፥ እንደ ሰንበሌጥ አጥር ማንም በፈለገው ጊዜ እየጣሰው የሚገባ ድንበር አይደለም። ሀገሩንና ድንበሩን የማያስከብር ሕዝብ ለባርነት እንደተዘጋጀ ይቆጠራል። ለአንድ ዜጋ ሀገርና ድንበር የክብሩ ከፍተኛ መገለጫው ነውና።
ኢትዮጵያ ሀገራችን በትግራይ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን እንዲሁም በመተከል በኦሮሚያ ክልል ጽንፈኞችን ለማጽዳት ከፍተኛ ግብግብ በምታደርግበት ወቅት፣ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ ጦሯን ማስፈሯንና በአካባቢው በነበሩ ኢትዮጵያውን ገበሬዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን የተለያዩ የዜና አውታሮች የዘገቡት ሃቅ ነው። አሁን በቅርቡ ደግሞ በምዕራብ አርማጭሆ በደለሎ የገበሬዎችን የእርሻ ምርት ማቃጠሏን በከፍተኛ ቁጭት ሰምተናል። ይህ የሱዳን ድፍረት ማንኛውንም ኢትዮጵያጵያዊ ዜጋ እጅግ የሚያስቆጣ እርምጃ በመሆኑ ሁላችንንም እንቅልፍ የሚነሳ ድፍረት ነው ይላል ኢሕአፓ።
የድንበር ውዝግቡ ለረዥም ጊዜ እልባት ሳያገኝ የቆየ መሆኑ ቢታወቅም፥ ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ድንበሯን አልፋ አንድ ጋት መሬት ከሱዳን ፈልጋ አታውቅም። ሱዳን ግን አጋጣሚ እየጠበቀች በተደጋጋሚ ከመተንኮስ ቦዝና አታውቅም። በሰላማዊ ጊዜም ከብቶቿን ወደ ኢትዮጵያ መሬት አሻግራ እንዲግጡ በመድረግ፣ ለእጣን የሚሆን ሙጫ በመሰብሰብ፣ ለቤትና ለማገዶ የሚሆን እንጨት እየቆረጠች በመውሰድ የምትፈጽማቸውን ድርጊቶች ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች በመቃወማቸው በተደጋጋሚ ስትጋጭ ኖራልች። ኢሕአፓ በአካባቢው በሚንቀሳቀስበት ጊዜም ይህን ለማስቆም ለሱዳን መንግሥት ገበሬዎቻቸው ድንበራችንን እየተሻገሩ የሚያደርጉትን የጥሬ ሀብት ስብሰባና የከብት ግጦሽ እንዲያስቆሙ በተደጋጋሚ ጠይቆ አሻፈረኝ ስላሉ፤ የአካባቢውን የምዕራብ በጌምድርን (መተማ፣ ቋራ፣ ጫቆ) ሕዝብ አስተባብሮ የሱዳንን ጦር በመውጋት ድል አድርጎ የኢትዮጵያን ድንበር አስከብሮ አንደነበረ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት ሱዳን የነበሩ የድርጅቱ አባሎች ለእስርና እንግልት ተዳርገዋል፤ የተወሰኑትንም ለህወሓት በማስረከብ ለሰቆቃ/ግርፋትና እስር እንዲዳረጉ አድርገዋል። ገዳሪፍ የነበረውን የድርጅቱን ጽሕፈት ቤት በርብረው የድርጅቱን ንብረቶች ወስደዋል። ከህወሓት ጋር በመተባበር ኢሕአፓን ከበው ወግተዋል። ህወሓትንም አጅበው አዲስ አበባ አስገብተው ተመልሰዋል።
ህወሓት እና የሱዳን መንግሥት ከመጀመሪያ ጀምረው የጠበቀ ወዳኝነት እንደነበራቸው ይታወቃል። በደርግ ዘመን ህወሓት ጉልበት ያገኘውና የኢትዮጵያን ጦር አሸነፍኩ ያለው ሱዳን ከፍተኛ መከታና ደጀን ሆና ስለረዳቻቸው ጭምር ነው። ለዚህ ውለታ ሱዳኖች ድንበራችን ጥሰው በደለሎ በኩል ገብተው ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን አፈናቆለው ለረዥም ዓመታት ሲያርሱ ኖረዋል። የአካባቢው ገበሬዎች ድርጊቱን በመቃወም ሲከላከሉ፣ የህወሓት ካድሬዎች “መንግሥትና መንግሥት ይነጋገራል እንጂ ገበሬውን አያገባውም” በማለት ኢትዮጵያውያንን ገበሬዎችን ያስሩና ያንገላቱ ነበር። እውነታው ግን ሱዳን እንደፈለገች የኢትዮጵያን መሬት እንድትጠቀም በነአባይ ፀሐዬ የተሸረበ ሤራ መሆኑ ነው። የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የህወሓትን አሸባሪ ቡድን ለማፅዳት ጦርነት እያደረገ በነበረበት ወቅት ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን ከማሳቸው ያፈናቀለችው የወዳጇ የህወሓት መመታት ስለከነከናትና በአጋጣሚውም የረጅም ጊዜ ምኞቷን ለማሳካት የወሰደችው እርምጃ ነው።
ሱዳን ድንበራችንን የጣሰችበት ሌላው ምክንያት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ ለማደናቀፍ እንዲቻል ከሱዳን ጀርባ ተጫማሪ ገፊ ኃይል ሊኖር እንደሚችል መገመት አይቸግርም። ከዚህ በተጨማሪ ህወሓትና የውጭ ደጋፊዎቻቸው ትግራይ ውስጥ የሚደረገውን የሀገር አፍራሹን ቡድን የማጽዳት ዘመቻ ቀጣናዊ መልክ ለማስያዝ የሚጥሩትን እውን ለሜድረግ ሱዳን የጦስ ዶሮ ሆና መቅረቧ አጠራጣሪ አይደለም እንላለን።
በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ውስጥ የተጎዳው ሕዝባችን አስፈላጊው እርዳታ እንዲደርሰው መንግሥት እስካሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ በተጠናከረ መልክ እንዲቀጥልና የዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶችም እርዳታና ድጋፋቸውን በመንግሥት በኩል ለሕዝቡ የሚደርስበትን መንገድ እንዲያመቻች እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን መሬታችንን ለቃ እስክትወጣ ድረስ የሱዳንን ትንኮሳ ጥንቃቄ በተሞላበት በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመያዝ ከፍጻሜ ለማድረስ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይኖርበታል። ድንበራችን በቋሚነት የሚከለልበትንም መንገድ እንዲያመቻች እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበርና የሀገሩን አንድነት ለማስጠበቅ ሊፋለም እንደሚችል ግልጽ መሆን አለበት። ሕዝባችን በተደጋጋሚ እንዳስመሰከረው ሱዳን ከሀገራችን ክልል እስክትወጣ ድረስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ በመሆን፥ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንደሚቆም አንጠራጠርም። ኢሕአፓም በማንኛውም መንገድ ከሕዝባችን ጎን ዘብ ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። አባቶቻችን ስለሀገርና ድንበር ሲነሳ እንደ እግር እሳት ሲያንግበግባቸው፦
“ከደንበሩ ቆሞ ጌታ ካልመለሰው፥
መሬትም ይሄዳል እግር አለው እንደ ሰው”ይሉ ነበር።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ጥር 29 ቀን፥ 2013 ዓ. ም.January 19, 2021 at 5:34 pm #17532In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ― አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ
ትኩረት ለትግራይ!!!
ትኩረት ለአስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ!
ትኩረት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር!ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ፥ መንግሥት በትግራይ ክልል ሲያካሄድ የቆየውን ሕግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ማለትም የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የሕክምና እና የመድኃኒት፣ የደህንነት፣ ባንክ፣ ትራንስፖርት የመሳሰሉት አገልግሎቶች አሁንም ያለመሟላት እና ከፍተኛ የሆነ የሕግና ሥርዓት ያለመከበር ስጋት እንዲሁም ጥቃት ያለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ከታማኝ ምንጮች አረጋግጧል። ጊዜያዊው የክልሉ አስተዳደር ሁኔታዎችን ለማስተካከል እየጣረ ያለበትን ጥረት ብንረዳም፥ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነውና የሁላችንንም ኢትዮጵያውያን ርብርብ እና እገዛ እንደሚጠይቅ ተረድተናል። ሁኔታዎች ከእስከአሁኑም በላይ ተባብሰው ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆኑ በፊት አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።
በመሆኑም፦
- በክልሉ ባለፈው ክረምት ወቅት በአዝርዕት ላይ በደረሰው የበረዶ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የጎርፍ አደጋ እና የበረሀ አንበጣ ወረርሽኝ የተነሳ ጉዳት የደረሰ እንደነበርና ከዚህም የተረፈውን በነበረው ጦርነት ምክንያት በበቂ ሁኔታ መሰብሰብ ባለመቻሉ እና በተያያዥ ምክንያቶች ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎቻችን አስቸኳይ የህይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመረዳታችን፥ ነገ ዛሬ ሳይባል በአስቸኳይ የምግብና የመጠጥ እርዳታ የሚደርስበትን መንገድ እንዲመቻች፥ ለዚህም ለሚመለከታቸው አካላትና መላው የኢትዮጵያ ዜጎችን ጥሪ እናቀርባለን።
- ለሕክምና ተቋማት የመድኃኒት፣ የሕክምና መሳሪያዎች፣ ባለሙያ እና ጥበቃ በማሟላት ማስቀረት የሚቻሉ የጤንነት ችግሮች እንዲቀረፉ እና በተለይ ሕጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች እንዲረዱ እንጠይቃለን።
- ጊዜያዊው የክልሉ መንግሥት እስከታችኛው የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅር መልሶ ለማዋቀር እየሠራ እንደሆነ ብንገነዘብም፥ በዘላቂነት ሥራው እስኪሳካ ከነዋሪው እና ከሌሎች እትዮጵያውያን የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ሰላምና ማረጋጋቱን ለማገዝ የሚችል ግብረ-ኃይል በማሰማራትም ጭምር ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ዜጎቻችን ላይ ያለውን የደህንነት፣ የዝርፊያና የመደፈር… ስጋት በአፋጣኝ እንዲያስቆም እንጠይቃለን።
- በክልሉ እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችና በማከፋፈል ሊያግዙ የሚችሉ በጎ ፈቃደኞች መሰማራት እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እናሳስባለን።
- የምግብ እና ሕክምና አገልግሎት ማድረስ የማይቻልባቸው ቦታዎች ካሉም ሰላማዊ ዜጎች በተለይ ሴቶች፣ ሕፃናት እና አቅመ ደካሞች ከአካባቢው ተጓጉዘው ወደሌሎች አቅርቦት ሊደርስላቸው ወደሚችሉበት የትግራይ ክልል ከተሞች ወይም ወደ አቅራቢያ የሀገራቸው ክልሎች በማድረስ የህይወት አድን ሥራዎች እንዲሠሩ አበክረን እንጠይቃለን።
- በሰላማዊ ሰዎች እና ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የደረሰው አካላዊ ጥቃት፣ ዘረፋ እና የሞራል ድቀት በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን።
- በቀጥታ ከሕግ ማስከበር እርምጃው ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ በተለያዩ ተቋማት ላይ የደረሰውን ዝርፍያ እና የንብረት ውድመት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን።
- በሀገርም ውስጥ በውጭም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው እየተጎዱ ያሉት ንጹኃን ዜጎቻችን ናቸውና ይህ ስቃይ እና ስጋት አብቅቶ ወደ ማቋቋም ለመሸጋገር ይቻል ዘንድ በሁሉም ዘርፍ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ታደርጉ ዘንድ እንጠይቃለን።
- የመንግሥት የሚመለከታችሁ አካላት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ፣ የሚድያ፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ያላችሁን መዋቅር በመጠቀም ቅድምያ ህይወት ለማዳን እና ሰብዓዊነትን በማስቀደም በአንድነት እንድንቆም እንለምናችኋለን።
ኦባንግ ሜቶ
ዋና ዳይሬክተር፥ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያJanuary 19, 2021 at 12:30 am #17495In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ትግራይና አማራ ክልል፡ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል
አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እና ድጋፍ ሊቀርብ ይገባልየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ፣ በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎች ደኅንነት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአሳሳቢና ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ በሚችል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገለጸ። ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 6 እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጎንደር እና በዳንሻ በመገኘት እንዲሁም፣ ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በትግራይ ክልል፣ ደቡባዊ ዞን፣ ጨርጨር ወረዳ በሚገኙት ኡላጋ እና ቢሶበር መንደሮች በመጓዝ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ተጎጂዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ያደረገውን ክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
በተጨማሪም የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ከጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ ዙር የመስክ ምልከታ ወደ መቀሌ ከተማ እና ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፥ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብዓዊ ቀውስ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በመመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ሥራው እንደተጠናቀቀ ተጨማሪ ሪፖርቱን ይፋ የሚደረግ መሆኑን ኮሚሽኑ አክሎ አሳውቋል።
የአሁኑ ክትትል በዋነኛነት በተካሄደባቸው በዳንሻ፣ በሁመራ፣ በቢሶበር እና በኡላጋ ጦርነቱ የሲቪል ሰዎችን ሞትና አካላዊ ጉዳት አስከትሏል፤ የሲቪል ሰዎችን መኖሪያና የንግድ ቦታዎች ለዝርፊያና ለተለያዩ ጉዳቶች አጋልጧል፤ እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመትና የኤሌክትሪክ እና የውሃ የመሳሰሉ አገልግሎቶች አለመመለስ፣ በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና በተፈናቃናዮች ላይ የበለጠ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል የሚያሰጋ ነው። በቢሶበር እና በኡላጋ 31 ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፤ 104 መኖሪያ ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ እንዲሁም የአካባቢው ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በሁመራ እና በዳንሻ የሲቪል ሰዎች ንብረት የሆኑ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶችን ጨምሮ የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ውድመት እና ዝርፊያ ደርሷል። ሲቪል ሰዎች በብሔራቸው ምክንያት ወይም በአካባቢዎቹ የፀጥታ መጓደል ምክንያት ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በእነዚህ አራት ከተሞች ያለው የፀጥታ ስጋትና የፍትህ አካላት ወደ መደበኛ ሥራቸው አለመመለስ፣ የሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ጥበቃ ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሲያስረዱ፥ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ምርመራውና ክትትሉ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የነዋሪዎቹንም ሆነ ከትግራይ ክልል ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት እንዲጨምርና የመቋቋም አቅማቸውን በአስከፊ ሁኔታ እንዲፈተን አድርጓል” ብለዋል። የኮሚሽኑ ምርመራ ቡድን የጎበኟቸው ተጎጂዎች በአብዛኛው በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው አሊያም አንድ ዙር ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው መሆኑን በሪፖርቱ እንደተመለከተ ጠቅሰው፥ “በአካባቢዎቹና በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት የሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው” በማለት ገልጸዋል።
ሙሉውን ሪፖርት እዚህ ጋር (ማስፈንጠሪያ) በመጫን ማግኘት ይቻላል።
January 14, 2021 at 2:46 am #17412In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveየህወሓቶች እብሪት ― የህወሓቶች ውድቀት ― እንደሀገር፣ እንደዜጋ የሚያስተምረን ትምህርት
(አቶ ነአምን ዘለቀ)ጆርጅ ሳንታያና (George Santayana) የተባለው ፈላስፋ “ታሪክን የማያስተውሱ ታሪክን በመድገም ይረገማሉ” (‘Those who cannot remember the past are condemned to repeat it.’) እንዳለው፥ አምባገነኖች ከሂትለት እሰከ ሳዳም ሁሴን – ካለፈው መማር ሳይችሉ ያንኑ ሲደጋግሙ ኖሩ። የህወሓቶች እብሪት፣ ትእቢት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የነበራቸው ንቀት የዚሁ እብሪተኞች ካለፈው ለመማር አለመቻልና የፍትህን ማዕከላዊነት ጥሎ ልከኝነት ረግጦ የመራመድ ቅጥያ ውጤት ነው።
ለ27 ዓመታት ፍጹም ሊባል በሚችል የበላይነት የመንግሥት፣ የኢኮኖሚ፣ የወታደራዊና የደህንነት ቦታዎች ላይ የአንበሳ ድርሻውን ይዞ የነበረው ህወሓት፥ ከ2018ቱ (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጥር) ለውጥ በኋላ በእኩልነት ለመኖር የተሰጠውን ዕድል መቀበል እንዳልቻለ ግልጽ የነበረው የዛሬ ሁለት ወር ተኩል ገደማ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን እዝ ሠራዊት አባላት ላይ ያደረሰው መብረቃዊ ጥቃትና ጭካኔያዊ እርምጃ ያን ተከተሎ በተደረገው ሕግን የማስከበር ወታደራዊ ዘመቻ የተጀመረ ሳይሆን ከሁለት ዓመት ተኩል ጀምሮ አንደ ነበር ግልጽ ነው ።
ያ የነበረውን ሁለንተናዊ የበላይነት ሲያጣ የሞት ሞት ሆነበትና እንዴት ያድርገው!? መላ ቅጡ ጠፋው። ከጅምሩም የያዙትን ስልጣን ለፍትህ፣ በልከኝነት፣ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን በሀገርና በሕዝብ ኪሳራ የራሳቸውን፥ አለፍ ሲልም የአንድ ብሔር ሊሂቃን የበላይነት ለማረጋገጥ የተቀሙበት የዘረፋ፣ የዘረኝነትና የመንግሥታዊ ሽብር መሣሪያቸው ነበር። ህወሓቶች ስለራሳቸው ልዩ መሆን፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ጀግንነት፣ ብቃትና ክህሎት ራሳቸው በፈጠሩት የሀሰት ትርክት በእብሪትና በትእቢት የተወጠረው አእምሮአቸው አዲሱን የኢትዮጵያ የለውጥ መንገድ እንዲሁም ከለውጡ ጋር ተከትሎ የመጣውን ነባራዊ እውነታ ሊቀበሉ አልቻሉም።
እነ ስዩም መስፍን ኢትዮጵያን “ሶርያና የመን እናደርጋታለን” ብለው በአደባባይ አወጁ። እነ ጌታቸው ረዳ “ትግራይ ሀገር መንግሥት መሆን እንዳለባትና እና በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር ሶማሌላንድ ከሞቃድሾ ጋር እንዳላት ግንኙነት ነው የምንፈልገው” በማለት በድፍረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሩ። “ተራራን ያንቀጠቀጥን”፣ “የደርግን ሠራዊት የደመሰስን”፣ “ከወርቅ ሕዝብ የተገኘን”፣ “ኢትዮጵያን እንደ አዲስ የሠራን”፣ “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያረጋገጥን”፣… ብለው ለአስርት ዓመታት የሰበኩት ህወሓቶች የሀሰት ትርክቶቻቸውንም አብጠው አብጠው በአምሮአቸው ውስጥም ተገንብተው፣ ጠጥረውና ደድረው እውነታን ለማየት የማያስችል ግርዶሽ ሆነው ቆዩ። በርካታ የትግራይን ወጣቶችንም በዚሁ ትርክት እወናበዱ። መሬት ላይ ካለው ከነባራዊው እውነታ ጋር ፍጹም በተቃራኑ ቆሙ። እውነታውን ተቀብለው ለመሄድም በትዕቢት፣ በእብሪት፣ በዘረኝነት የተተበተበው ልቦናቸውና ህሊናቸው ፈጽሞ አልፈቅድላቸው አለ።
በመሆኑም ህወሓቶች ማድባትና መዘጋጀት ጀመሩ። ለሁለት ዓመታት ሲደራጁ፣ ሲዘጋጁ ቆይተው ማዕከላዊ መንግሥቱን ዳግም ለመቆጣጠር፥ ይህ ካልሆነም ኢትዮጵያን አተራምሰውና በታትነው “የትግራይን ሀገር መንግሥት” ለመመሥረት “በመብረቃዊ ጥቃት” በሰሜን እዝ ላይ ክህደትና ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ፈጸሙ። በስልጣን ዘመናቸውም ግፍና መከራ ለሕዝብ ሲሰፍሩ ኖሩ። በሰፈሩት ቁና መስፈር አይቀርምና የሚሊዮኖች እምባ፣ የብዙ ሺዎች ደም፣ ዋይታና ሰቆቃ፣ በህወሓቶች ግፍ የተሰደዱ የአስር ሺዎች ኢትዮጵያውያውን መከራ ፈጽሞ ይሆናል ብለው ባልጠበቁትና ባልተዘጋጁበት የበስተርጅና እድሜያቸው፣ በመጦሪያ ዘመናቸው እጅግ የመረረ ዋጋ ጠየቃቸው። በመጨረሻም መራሩን ውድቀትና ውርደት አከናነባቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብም ‘አክ እንትፍ!’ እንዳላቸው ሊከሰትላቸው ፈጽሞ ሳይችል ቀርቶ በስተርጅና እድሜያቸው ለውድቀትና ለውርደት፣ ገሚሶቹ ደግሞ በመደምሰስ ፍጻሜያቸው ባጁ።
የኢትዮጵያ አምላክም በእነዚህ ግፈኞች ላይ መብረቃዊ ጥቃት ያደረሰ ይመስለኛል። ስልጣንና ሀብት ደደብና ደነዝ አድርጎ ለውርደት ከዳረጋቸው ከህወሓቶችና ካለፉ አምባገነኖች ታሪክ ለመማር ያልቻሉ፥ አሁንም በያዙት ስልጣን መከታ በማድረግ በሕዝብ ጫንቃ ለመናጠጥ የሚሞክሩ፣ ፍትህን፣ ሰላምን፣ ለሀገር የሚበጀውን፣ የዜጎችን ህይወት የሚለውጥ ተግባር ላይ ከማተኮርና ከመትጋት ይልቅ ሕዝብን ከሕዝብ የሚከፋፍሉ፣ የብሔር ካርድ ለስልጣን ማጠናከሪያ የሚመዙ፣ የሕዝብ ሰላም የሚያውኩና ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚደነፉ፣ በየመድረኩም የሚፎክሩ አፍራሽ በየብሔሩ ስም የተደራጁ ኃይሎችና ቡድኖች በገዢው ፓሪቲ የሚገኙ እንዳንድ መሪ ካድሬዎች ከዚህ ታሪክ ይማሩ ይሆን?
ከስልጣን ጋር በሚመጣ እብጠትና ማን አለብኝነት ብዙ ርቀት የማያስኬድ መሆኑን ማጤን ትልቅ አስተውሎ ነው። ከፋፋይና ሕዝብን በጭንቀት ውስጥ እንዲኖር ከሚያደርጉ የማኅበራዊ ሚዲያዎችና በየሚዲያው ከሚሰነዘሩ መርዛማና ከፋፋይ አሰተያየቶች ለመሰንዘር ከመሽቀዳደም በጎ በጎውን፣ ለሀገር የሚበጀውን፣ ለሕዝብ ተስፋ የሚሆንውን፣ ለሥራ-አጡ ሥራ የሚፈጥረው፣ ኢትዮጵያን የሚያለማውን፣ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያቀራርቡ ተግባራት ላይ ማተኮርና መትጋት በኃላፊነት ላይ ለሚገኙ እነዚህ የገዥው ፓርቲ መሪ ካድሬዎች ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል።
የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም፣ የሕግ የበላይነትና ፍትህን ያማከለ ብሎም ለእያንዳዱ ዜጋ በየትኛውም ክልልና ቦታ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ/ት የደህንነት ዋስትናው የሚጠበቅበት፣ ሠርቶ ለፍቶ በሰላም መኖሩ የሚረጋገጥበት፣ የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩ እንቅስቃሴዎች ላይ በማተኮር ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ ሠርቶ ጊዜው ሲደርስ ስልጣን ማስተላለፍ መሆን ይገባዋል። ስልጣንን ለማቆየት የብሔር ካርድ በየዕለቱ መምዘና ህወሓቶች እንዳደረጉት የሕዝብም አብሮነት የሚሸረሽሩ፣ ብሔር ለብሔር የሚያጋጩ ተግባራት ላይ መጠመድ ዋና ሥራ ሆኖ መቀጠል የለበትም። ከሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ከሙስጠፋ ኦማርና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከሌሎችም ሊማሩ ይገባል።
ሕዝብ በአግባቡና በቅጡ ማገልገል ቅድሚያ መስጠቱ በህወሓቶች ውድቀትና ውርደት ዋዜማ ትልቁ ትምህርት ይህ እንደሆነ መቀበል ብልህነት ነው ። ለሀገርና ለሕዝብም ብቸኛው መንገድ የሕዝብን ሰላም፣ ደህንነት፣ ፍትህ፣ መብቶችና ጥቅሞች እንዲሁም አስከፊውን ድህነት ለማስወገድ አካታችና ዘላቂ ልማትን ማስቀደም መሆን አለባቸው። የህወሓቶች ውድቀት ዋዜማ እንደ ሀገር ምን እንማራለን ለሚለው አንዱ አስተምሮና አስተውሎ ይህ ይመስለኛል።
አቶ ነአምን ዘለቀ
December 7, 2020 at 2:54 am #16915In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየአማራ ብልጽግና ፓርቲ ለሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ካልታገለ እንደ ብልጽግና መቆም አይችልም!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ አቋም
ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.
ባህር ዳርስናጠፋ የሚገስጸን፣ ስናለማ የሚያግዘን ሕዝብ እንዳለን እናምናለን። በሕዝባችን ስብራት ላይ ተደማሪ ስብራት መሆን ስለማንፈልግ ከሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በመነጨ ቅን ልቦናና ፍላጎት የሕዝባችንን ድምጽ ለማክበርና ለማስከበር ተዘጋጅተናል። የብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ማቅ እና ድሪት አውልቆ የሕዝብን ሀቀኛ ፍላጎትና እውነተኛ መሻት የሆነውን መካከለኛ አማራጭና የወሳኝ ኩነቶች ወሳኝነት ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚበጀውን የፕራግማቲዝም (pragmatism) ድርና ማግ ተጎናጽፎ ነው። በብልጽግና እምነት ቋሚና የማይለወጥ እውነት የለም፤ ሁሉም ነገር ቋሚ ሊሆን አይችልም። በብልጽግና እምነት የማይለወጥ መሠረታዊና ቁሳዊ የሆነ ነገርም አይኖርም። ከብልጽግና ርዕዮተዓለማዊ እምነት አኳያ ቋሚና የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ እሱም ኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
መደመርን መንገዳችን፣ ብልጽግናን መዳረሻችን አድርገን ስንነሳ መደመር የሚፈልጉ ዜጎቻችንን ልንቀንሳቸው አንችልም። ዛሬ በማይካድራ፣ በዳንሻ፣ በዓላማጣ፣ በጥሙጋና በዋጃ ባጠቃላይ በራያ ዋጃ ዓላማጣና ኮረም እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ያሰማችሁትን የ‘አማራ ነን’ ድምጽ በአክብሮት የምንቀበለውና በጽናት የታገልንለት ወደፊትም የምንታገልለት የመደመር ኅብረብሔራዊ ፌዴራላዊ ትርጉም ያለው የቆየ ግን በእብሪት የተገፋና መልስ የተነፈገው የዜጎች ጥያቄ ነው።
ሁሉም የብልጽግና ቤተሰቦችና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኃይሎች እንዲረዱት የምንፈልገው ቁምነገር አለ።
በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም።
ክልላዊ ወሰናችንንና ፌዴራላዊ መብታችንን በመጋፋት በግፍ ተጠቃን እንጂ ማንንም አላጠቃንም።
በጭካኔና ያለርህራሄ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመብን እንጂ በማንም ላይ የግፍ አጸፋ አልመለስንም። በደም ፍላት ስሜት ተገፍትረው ግፍ ለመፈጸም የቃጡና የሚቃጡ በውስጣችን ያሉ ስሁታንንም ያለርህራሄ ታግለናል፤ እየታገልንም እንገኛለን።
ከልክ በላይ በተወጠረ እብሪት በትምክህተኝነት ስሜትና በተስፋፊነት ልክፍት ተወጥረው ሕዝባችንን፣ መሬታችንን፣ ታሪካችንን፣ መልካም ስማችንን፣ የ30 ዓመት ሁሉአቀፍ ክልላዊ እድገታችንን፣ እድሜያችንንና ሥነ-ልቦናችንን በግፍ ተዘረፍን እንጂ የማንንም ቅንጣት አልዘረፍንም።
የወሰን፣ የማንነትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቂያችንን በሕግና በሥርዓት አቀረብን እንጂ እንደ ትሕነግ በማን አለብኝነት ‘ዘራፍ’ አላልንም።
የተገፋን፣ የተበደልንና የተጨፈጨፍን ቢሆንም ለፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ አልፈጠርንም።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የሀገር ሉአላዊነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ቁርጠኛ አጋርነታችንን በክቡር መስዋዕትነት አረጋገጥን እንጂ ሀገራችንና ሕዝባችንን በመካድ አልወጋንም። ሀገርና ሕዝብ ክደው በወገን ላይ የጭካኔ አፈሙዝ ያዞሩትንም የታሪክ ማፈርያዎች እንደሆኑ እንረዳለን።
በሰላማዊ መንገድ እጅ የሰጡና የተማረኩ የትሕነግ ተዋጊ ኃይሎችን በወንድማማች መንፈስ ቁስላቸውን ጠረግን፣ እንዲያገግሙ በፍቅር ተንከባከብን እንጂ እንደጠላት አልገፋናቸውም። በተለመደው አማራዊ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት እልፍኛችንን ለቀን፣ ከአልጋችን ወርደን የምርኮኛነት ስሜት እንዳይሰማቸው አስተናገድናቸው እንጂ በግፍ አላሸማቀቅናቸውም።
እብሪተኛው የአፓርታይድ ቡድን በፈጸመብን ሴራ እስከአሁኗ ሰዓት ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በስጋትና በጭንቀት የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ነው። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አሁንም በስደት ላይ ይገኛሉ። በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን የሚፈሰው የአማራ ደም ዛሬም አልቆመም። በሌሎችም አካባቢዎች የስጋት ጅረት አልተገደበም። በማይካድራና በሁመራ በየቦታው የተጣሉ አስከሬኖች ‘በክብር ቅበሩኝ’ ጥሪ ቢያስተጋቡም የንጹሃኑ በድኖች ግን ዛሬም ድረስ ተለቅመው አላለቁም።
ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ ጥንተ ጠላት የሆነው ትሕነግና ጽንፈኛ ወዳጆቻቸው ከትክክለኛው ወቅታዊ አውድ ፍጹም የሚቃረን ሙግትና ትንታኔ ሲሰጡ ልማዳቸው መሆኑን ብናውቅም ለአንድ አንድ የትግል አጋሮቻችንና ደጋፊዎቻችንን ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን።
- ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አረመኔውና የአፓርታይድ ሥርዓት አቀንቃኙ ትሕነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የተጠናና የተደራጀ ሁሉ-አቀፍ ጥቃት ሲፈጽም የወራሪነት፣ የተስፋፊነትና የጨፍጫፊነት አድማሱን በማስፋት በ24 ሰዓት ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ የአማራ ክልል አቅጣጫዎች ጎንደርንና ወልድያን የመቆጣጠር ግብ አስቀምጦ ነው። ይህንን እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ከ3 ዓመት ያላነሰ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ትሕነግ ያስቀመጠውን የወራሪነት ግብ በመቀልበስ ሀገርና ሕዝብን ለመታደግ በወትሮ ዝግጁነት መፈጸሙ የአማራን ሕዝብ ሊያስመሰግነው ሲገባ፥ በጥርጣሬ እንድንታይ የሚያደርግ በፍጹም አይሆንም። የተከፈተብንን የግፍ ጦርነት ተከላክለንም፣ አጥቅተንም ጦርነቱን መቀልበሳችንና በግፍ ተነጥቀን የነበረውን ተፈጥሯዊ መብታችንን በእጃችን ማስገባታችን (repossession right) የተፈጥሮን ሕግ የሚቃረን ሳይሆን በእብሪተኞች የማይታረቅ ተቃርኖ መቃብር ላይ የተረጋገጠ ድል ነው። ስለሆነም እርስት ለማስመለስ ያልታገለን ይልቁንም ላለፉት 30 ዓመታት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየን ሕዝብና መንግሥት እርስት ለማስመለስ እንደተዋጋ አድርጎ ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አመክንዮ የጎደለው ድምጽ ማሰማት ነውር ነው እንላለን። በእርግጥ እርስት ማስመለስ የሚለው ትችት ለባለእርስቶች የተወረወረ የበላ-ልበልሀ ክርክር መሆኑ የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ፍትሀዊነት ያረጋገጠ ሀቅ በመሆኑ ሀሳቡን ደጋግማችሁ ለተጠቀማችሁ ሁሉ ምስጋና እናቀርብላችኋለን።
- እንደ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ሕዝብ ሀቅ ይታወቃል። የአማራ ሕዝብ ሀቅ ዛሬም በአደባባይ በሕዝባዊ ሰልፍ በይፋ እንደሚታየው የማንነት፣ የወሰን፣ በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት ፍትሀዊ ጥያቄ ነበር። ከ500ሺ ሕዝብ በላይ የተፈናቀለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተገደለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተሰወረባቸው እነዚህ አካባቢዎች ዛሬም የተረጋገጠ የጅምላ መቃብር የተገኘባቸውና የአፓርታይድ ሥርዓት በተጨባጭ የተፈጸመባቸው የትሕነግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ጭካኔ ማረጋገጫ የግፉአን መቀበርያ አጽመ እርስቶች ናቸው።
በግፍ የተጨፈጨፉ የንጹሀን ወገኖቻችን አስከሬኖች ተለቅመው በክብር ባላረፉበት በዚህ ወቅት የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት የወንበዴውን ቡድን ወንጀል ለመደበቅና ለማድበስበስ እየተፈጸመ የሚገኝ ሌላኛው የትሕነግ ሸፍጥ ማምለጫ መንገድ ሲሆን፥ የአካባቢውን ነባራዊ ሀቅ በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት የሚራመዱ የተሳሳቱ ሀሳቦች የሞራል ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው።
ስለሆነም የሕግ የበላይነት ለማስከበር፣ የሀገር ሉአላዊነት ለማጽናት በተደረገ ሁሉ አቀፍ የትግል ጀብዱ በታሪክ አጋጣሚ ወደባለእርስቱ የገቡ አካባቢዎች (repossessed lands) ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በሥርዓቱና በአግባቡ በቀጣይ ማየት ይቻላል የሚል እምነት አለን። ግን ደግሞ የትሕነግን የአፓርታይድነት የወንጀል ፈለግ (criminal scene) መፈተሽና መመርመር፣ ለትግራይና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማጋለጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለን። ስለሆነም:-
-
- ላለፉት 50 ዓመታት የዜጎች ማጎርያና ማሰቃያ የሆኑ ከመሬት በታች የተሰሩ ዋሻዎች (underground torching caves) ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው።
- ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጅምላ መቃብሮች ታስሰው ላለፉት 50 ዓመታት እንደ ሕዝብ የተፈጸመብንን ግፍና ጭካኔ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን።
- በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ግፈኛና ግፍን ነቅሎ በአዲስና በተረኛ ግፈኛና ግፈኝነትን ማጽናት አይደለም። ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ችግር ከግፈኞች አልነበረም። እንደሀገር ግፈኞችን መቅበር የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በየታሪክ ምዕራፉ ግፈኞችን መቅበር የምትችል ሀገር ግፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ግን አልቻለችም። ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ ግፈኝነትን በጽናት በሚታገልበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ የየበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ እየጠየቅን፥ በእኛ በኩል እብሪተኝነትም ሆነ ግፈኝነት የሕዝባችንን ክብር ዝቅ ስለሚያደርገው በጽናትና በታማኝነት የምንታገለው መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።
- በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሕግ የበላይነት የምናስከብር መሆኑን እያረጋገጥን፤ በቤንሻንጉል ክልል በሕዝባችን ላይ ተደጋጋሚ ግፍ የሚፈፅሙ የእብሪተኞች ቅሪት ዓላማና ፍላጎት በድል እንደሚቋጭ ሳንጠራጠር የተጀመረውን ሕግ የማስበር ሥራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ጎን ለጎንም የተፈናቃይ ወገኖቻችንን መሠረታዊና ወቅታዊ ፍላጎት እንዲሟላ ከማድረግ ባሻገር የሕዝባችንን እንቅፋት በሕግ አግባብ ተጠራርጎ መጥፋቱ ከተረጋገጠ በኋላ ዜጎቻችንን ተመልሰው በቀያቸው ላይ እንዲሰፍሩ የሚደረግ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን።
በመጨረሻም በትሕነግ መራሹ እብሪተኛ አፓርታይድ እርምጃ ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመባችሁ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የማይካድራና የሁመራ ሰማዕታት ሁልጊዜም በሕዝባችን ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ክብር አላችሁ።
የሕግ የበላይነት ለማስከበር በተፈጸመው እልህ አስጨራሽ ግብ ግብ ክቡር መስዋዕትነት የፈጸማችሁ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የአባቶቻችን ልጆች ስለሆናችሁ ኮርተንባችኋል፤ ለዘላለምም እንኮራባችኋለን።
የኦነግ ሽኔንና የጉሙዝ አማጺ ቡድንን ለመደምሰስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ስምሪት ወስዳችሁ ታሪካዊ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የምትገኙ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች፣ የኦሮምያና የቤንሻንጉል ክልል ሀቀኛ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጀግንነታችሁን ስንዘክር በአማራ ሕዝብ አክብሮትና ትህትና ነው።
ድል ከኢትዮጵያና ከአማራ ሕዝብ አብራክ ለተገኙ ታሪካዊ ጀግኖቻችን!!!
ውርደት በእብሪትና በትዕቢት ተወጥረው ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለሚወጉ ጠላቶቻችን!!!
ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ!!!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲNovember 25, 2020 at 7:19 am #16777In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveማይካድራ ውስጥ ሲቪል ሰዎች ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው ― ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
ትግራይ፡ የማይካድራ ሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው
የተጎዱትን ማቋቋም እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይገባልበትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል (atrocious crime of massacre against civilians) መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀ ጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተሞች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ነው። ይህ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ስለሆነ፥ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል።
በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፥ በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ ሀገር መከላከያ ሠራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር በተለይ “አማሮችእና ወልቃይቴዎች” ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል። ኢሰመኮ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን ባገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል” ብለዋል። አክለውም “የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፥ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርትን እዚህ ጋር በመጫን ማግኘት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም.November 22, 2020 at 2:20 pm #16763In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveሰላም ነሺው የክህደት ቡድን ላይ የሚወሰደው ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ
(ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ)የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፥
በትግራይ ክልል የጀመርነው ሕግን የማስከበር ርምጃ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጠናቅቋል። አሁን በመጨረሻውና በሦስተኛው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።
እየወሰድን ያለነው ሕግን የማስከበር እርምጃ ሦስት ምዕራፎች እንዳሉት ቀደም ብለን የገልጸን ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ፥ በገዛ ወገኑ የተጠቃውን የመከላከያ ሠራዊታችንን አሰባስበንና አጠናክረን፣ ተቋርጦ የነበረውን የእዝ ሰንሠለቱን ወደ ቦታው መልሰን ግዳጁን እንዲወጣ ማስቻል ነበር። በዚህም መሠረት ሠራዊቱ በከፍተኛ እልህ፣ ቁጭትና ወኔ ከገጠመው አደጋ በፍጥነት አገግሞ፣ የሕዝቡን ከፍተኛ ድጋፍ በልቡ ይዞ የሀገር ክህደት የፈጸመውን የህወሓት ቡድን ለሕግ ለማቅረብ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተንቀሳቅሷል።
የእርምጃው ሁለተኛ ምዕራፍ ዋና ዓላማ፥ የህወሓትን ጁንታ ከየአካባቢው እያስለቀቀ፣ አቅሙንም ከጥቅም ውጭ እያደረገ፣ ሕዝቡን ከዚህ የክህደት ቡድን ይዞታ ነጻ በማድረግ፣ የመሸገበትን የመቀሌ ከተማ መክበብ ነበር። ከመቀሌ ውጭ ያለውን ህወሓት የያዘውን ቦታ ነጻ በማውጣት፤ የተዘረፉ ትጥቆችንና ካምፖችን መልሶ በመያዝ፤ የክህደት ቡድኑ የዘረፋቸውን ስትራቴጂያዊ የሆኑ መሣሪያዎችን ለውድመት ሳያውላቸው በፊት ከጥቅም ውጭ ማድረግ፤ በግዳጅ የያዛቸውን የሠራዊታችን አባላት ማትረፍ፤ የተሠውትን መቅበር እና አደጋ የሚደርስባቸውን ዜጎች መታደግ የሁለተኛው ምዕራፍ እርምጃ ዝርዝር ዓላማዎች ነበሩ።
በዚህ መሠረት በዳንሻ፣ ሑመራ፣ ሽሬ፣ ሽራሮ፣ አክሱም፣ አድዋ፣ አዲግራት፣ አላማጣ፣ ጨርጨር፣ መሖኒ፣ ኮረምና በሌሎችም ቦታዎች በተወሰደ እርምጃ ሠራዊታችን ሕዝብ እየታደገና ድል እያደረገ ተጉዟል። ሕዝብ ለመታደግ በነበረው ዓላማ በተቻለ መጠን ሕግ የማስከበር እርምጃው በከተሞች አካባቢ ጥፋት እንዳያስከትሉ እና ሰላማዊ ዜጎች ዒላማ እንዳይሆኑ፤ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የሀይማኖት ቦታዎች፣ የሕዝብ መገልገያዎች፣ መሠረተ ልማቶች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመሳሰሉት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ምንም እንኳን የክህደት ቡድኑ የጥፋቱ ደረጃ ሰፊ እንዲሆን ቢፈልግም፥ በሕግ ማስከበር እርምጃችን ወቅት፥ የአየር ኃይል አውሮፕላኖቻችን ለሕዝቡ በነበራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ወደ ዒላማዎቻቸው የቀረበ አንድም ሰው እንኳን ከገጠማቸው የታጠቁትን ትጥቅ ይዘው እስከ መመለስ ደርሰዋል።
በዚህም፥ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማው ቡድኑ በሀይማኖት ተቋማትና በቅርሶች አካባቢ ተኩስ እንዲኖር የነበረውን ፍላጎት፣ በሠራዊቱ ተልዕኮን በጥበብ የማከናወን ችሎታ አማካኝነት የቡድኑ ፍላጎት ሊመክን ችሏል። ነጻ በወጡ አካባቢዎች በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ሕዝቡን መልሶ እንዲደራጅ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ አማካኝነት የተጎዱ ወገኖቻችን እንዲደገፉ፣ ሕዝቡ የተፈጸመውን ነገር በትክክል እንዲረዳና ራሱን የሂደቱ አካል ለማድረግ ተችሏል። የተበላሹና የተበጣጠሱ ማኅበራዊ ተቋማትን፣ የመገናኛና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመጠገን፣ ሕዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል።
ሁለተኛው የርምጃው ምዕራፍ ሕዝቡን የታደገ፣ የጁንታውን አከርካሬ ሰብሮ አቅሙን ወደ መቀሌ ማጥበብ ተችሏል።
አሁን የቀረው ጉልበት መቀሌ ላይ ያደራጀው ምሽግ እና አልፎ አልፎ የሚያሰማው ከንቱ ፉከራ ነው። በዚህ ሕግን የማስከበር እርምጃ ወቅት ሕዝባችን ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ህወሓት ስለ መከላከያ ሠራዊቱ የነዛው ፕሮፓጋንዳም ስሕተት መሆኑን የትግራይ ሕዝብ በዓይኑ ለማየት ችሏል። የሠራዊቱን ደግነትና ከጥፋት ለመታደግ የከፈለውን መስዕዋትነት ሕዝቡ ራሱ መመስከር ጀምሯል። በየአካባቢው ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ ለሠራዊቱ በማብላት፣ የክህደት ቡድኑ የሚሄድባቸውን መንገዶች በመጠቆም፤ የተደበቁ መሣሪያዎችንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በማጋለጥ ከሠራዊቱ ጎን ሆኖ የሚያስደንቅ ተጋድሎ ፈጽሟል። በዚህም የትግራይ ሕዝብ ቀድሞም በህወሓት የጥፋት መንገድ ምን ያህል እንደተንገሸገሸ በግልጽ አሳይቷል።
ሠራዊቱ ሽሬ በገባበት ጊዜ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በሆታ ከመቀበሉም በላይ፣ ጁንታው ያስታጠቀውን ከ200 በላይ መሣሪያ ሰብስቦ ለመከላከያ አስረክቧል። ሠራዊታችን አክሱም በደረሰም ጊዜ ሕዝቡ ራሱ በክህደት ቡድኑ ቁጥጥር ሥር የዋሉ የሠራዊት አባላትን ነጻ አድርጎ፣ የቆሰሉትን አክሞና ተከባክቦ፣ በክብር ለመከላከያ ሠራዊቱ አስረክቧል። የአክሱም ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊቱ ከእርሱ ጋር እንዲሆን ከመጠየቁም በላይ አብሮ ተሰልፎ የሕግ ማስከበሩ ዳር እንዲደርስ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በተመሳሳይ ሠራዊታችን አዲግራት ሲገባ፣ ሕዝቡ ራሱ የተደበቁትን የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት እየያዘ ለመከላከያ አስረክቧል።
በተቃራኒው የቆመው የክህደት ቡድን ስንትና ስንት የሀገር ሀብትና ጉልበት የፈሰሰባቸውን መሠረተ ልማቶችን እያፈረሰ፣ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ከጥቅም ውጭ እያደረገ፣ መንገዶችና ድልድዮችን እየደረማመሰ ሸሽቷል። የታሪካዊቷ አክሱም የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጭምር ውድመት በማድረስ የቀጣይ ዓመታት የቱሪዝም እንቅስቃሴያችን ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። የክልሉ ነዋሪ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያደርግባቸውን መንገዶች በዶዘር ማፈራረሱ ሳይበቃው፥ የመቀሌ ከተማን ልክ እንደ ጦርነት አውድማ ለማድረግ በመዛት ቅንጣት ታህል ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑን በግልጽ አሳይቷል።
ውድ ኢትዮጵያውያን፥
አሁን ሕግ የማስከበር ርምጃው ወደ ሦስተኛውና ወሳኙ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ሦስተኛው ምዕራፍ በመቀሌ የሚካሄደውና የክህደት ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ የሚደረግ የመጨረሻው እርምጃ ነው። የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ጥበብ፣ ጥንቃቄና ትዕግስት የሚፈልግ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ይህ የክህደት ቡድን ለምንም ነገር ደንታ እንደሌለው፥ ለሕዝቡ፣ ለታሪኩ፣ ለባህሉ፣ ለቅርሱና ለእምነቱ ቅንጣት ርኅራሄ እንደሌለው በግልጽ አሳይቷል። ሁሉም ነገር ጠፍቶ እርሱ ብቻ ቢተርፍና ከሕግ ቢያመልጥ ደስተኛ ነው። በዚህም የተነሣ በመቀሌ ከተማ ውስጥ የሀይማኖት ተቋማትን፣ ሆቴሎችን፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ የሕዝብ መኖሪያ መንደሮችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ቅርሳ ቅሶችንና መካነ መቃብሮችን ሳይቀር እንደ ምሽግ ተጠቅሞባቸዋል። መጥፋቱ ላይቀር ብዙዎችን ይዞ ለመጥፋት ተዘጋጅቷል። ልክ በአንዳንድ ሀገራት እንደሚታዩት የሽብር ቡድኖች፣ ለሕዝብና ለሀገር ምንም ደንታ የሌላቸው አሸባሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ ይሄ የጥፋት ቡድን መቀሌን እንደ ሕዝብ መኖሪያነት ሳይሆን እንደ ጦር አውድማነት ቆጥሯታል።
በዚህ ቡድን ምክንያት እንዲሞቱ የተገደዱት ነዋሪዎች ዜጎቻችን እንደመሆናቸው መጠን እና የሚወድመውንም ከተማ ነገ መልሶ ለመገንባት ዞሮ ዞሮ የእኛው ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን በመቀሌ የሚኖረን የሕግ ማስከበር እርምጃችን፥ ጉዳትን እጅግ በቀነሰ መልኩ መከናወን እንዳለበት እናምናለን። ስለዚህም፥ የመቀሌ ከተማን ከከፋ ጉዳት ታድገን ዘመቻውን በድል የምናከናውንበትን መንገድ እንደምንከተል ለመግለጽ እወዳለሁ። መንግሥት ይሄንን የሚያደርገው በዚህ የክህደት ቡድን የተነሣ ሕዝብና ሀገር እንዳይጎዳ ከመፈለግ ነው።
በመሆኑም፥
አንደኛ፡- የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች፥ በጀመርነው ሕግን የማስከበር እርምጃ ቁልፍ ተዋናዮች እንድትሆኑ፣ ከሠራዊታችን ጎን በመቆም ይሄንን የክህደት ቡድን አባላት ለፍርድ በማቅረብ ወሳኝ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን። ለጥቂት ስግብግብ ጁንታዎች ሲባል አንድም ሰው መሞት፣ አንዲትም ንብረት መውደም የለበትም።
ለዚህም የእናንተ ትብብር አይተኬ ሚና የሚጫወትና ብዙ ጉዳቶችን እንደሚያቀል እሙን ነው።
ሁለተኛ፡- የክህደት ቡድኑን ዓላማ በማስፈጸም ላይ ያላችሁ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት፥ አሁንም ቢሆን እጃችሁን በሰላም ለመስጠት ጊዜው አልረፈደም። ሕግ የማስከበር እርምጃው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መሆናችንን ተረድታችሁ የማያዳግመውን ዕድል እንድትጠቀሙበት፤ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ ባለው በ72 ሰዓታት ውስጥ እጃችሁን በሰላም ለመንግሥት እንድትሰጡ የመጨረሻ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።
ሦስተኛ፡- የጁንታው አባላት፥ የጥፋት ጉዟችሁ ጀንበሯ እየጠለቀች መሆኑን አምናችሁ፣ ከማትወጡበት ቅርቃር ውስጥ መግባታችሁን ተገንዝባችሁ በቀጣይ 72 ሰዓታት ውስጥ እጃችሁን በሰላም እንድትሰጡ እንጠይቃችኋለን፤ የመጨረሻዋን ዕድል ተጠቀሙበት። ተጨማሪ የሕዝብ እልቂት ከመፍጠርና ከተማ ከማውደም ተቆጥባችሁ ከታሪክ ውግዘት እንድትድኑ ጥሪ እናቀርባለን።
በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው የምንፈልገው ነገር ቢኖር፥ ሦስተኛውን ምዕራፍ የሕግ ማስከበር እርምጃ ከማከናወን ጎን ለጎን በጥፋት ቡድኑ ምክንያት ቀያቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሸሹ ወገኖቻችንን ለመመለስ፤ የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም፤ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን፤ ነጻ የወጡ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች ወደ መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በሁሉም ረገድ ዝግጅት አድርገናል። ወደ ትግበራ ስንገባ ከእጃችን እንዳያጥር እና ዓይናችንን ወደ ሌሎች እንዳናማትር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን። እኛ ኢትዮጵያውያን የቆየና የዳበረ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል ስላለን፣ የማንንም የውጭ እጅ ሳንጠብቅ ወገኖቻችንን እኛው ልናቋቁማቸው ይገባል። ለዚህም በመንግሥትና በተለያዩ የማኅበረሰብ አንቀሳቃሾች አማካኝነት የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንድትቀላቀሉ ስል ጥሪ አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ኅዳር 13 ቀን 2013 ዓ.ምNovember 19, 2020 at 3:24 am #16739In reply to: ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች
AnonymousInactiveየሀገር ክህደት ወንጀል በፈጸሙ 76 ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ላይ
የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱ ተገለፀ ― የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንአዲስ አበባ (የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን) – በትግራይ ክልል በሚገኘው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም ሀገር የማፍረስ ሴራ አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩና የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ የጁንታው ህወሓት ወንበዴ ቡድን የበላይ አመራሮችን አድኖ ለሕግ ለማቅረብ ከሳምንት በፊት ማለትም ህዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደወጣባቸው መገለፁ ይታወቃል።
በተመሳሳይም ከጁንታው የህወሓት ቡድን አባላት ጋር እየተገናኙ ሀገር በማፍረስ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ የሀገር ክህደት ወንጀል በፈፀሙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት እንዲሁም በፖሊስ አመራሮች ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ያስታወሰው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ፥ ከጁንታው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እጃቸውን ባስገቡና በሀገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በዚህም መሠረት በሀገር መከላከያ ሠራዊት በሥራ ላይ ያሉና በጡረታ የተሰናበቱ ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት የተጣለባቸውን ሕዝባዊና ሀገራዊ አደራና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና የጁንታው የህወሓት ቡድን የሴራ አካል በመሆን የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችንም አድኖ ለሕግ ለማቅረብ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጠባቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣልና ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ውስጥ በመሳተፍ የሚፈለጉትና የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው በሥራ ላይ ያሉና በጡረታ የተሰናበቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው።
- ሜጀር ጀነራል ማህሾ በየነ
- ሜጀር ጀነራል ሀለፎም እጂጉ
- ብርጋዴል ጀነራል ፍትዊ ፀሃዬ ገብረእግዚአብሔር
- ብርጋዴል ጀነራል ግደይ ሀይሉ ገብረእግዚአብሔር
- ብርጋዴል ጀነራል ወልደጊዮርጊስ
- ብርጋዴል ጀነራል አብዲሳ ፍላንሳ
- ብርጋዴል ጀነራል ጉሽ ገብሬ
- ብርጋዴል ጀነራል ከበደ ፍቃዱ
- ብርጋዴል ጀነራል ገብረጊዮርጊስ
- ብርጋዴል ጀነራል ህንፃ ወልደጊዮርጊስ
- ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳይ
- ኮሎኔል ንጉሴ ገብሩ
- ኮሎኔል መብራቱ አሰፋ /አልማዝ/
- ኮሎኔል ዘገየ ንጉስ
- ኮሎኔል ያለም
- ኮሎኔል መብራቱ ተድላ
- ኮሎኔል ነጋሽ መብራቱ
- ኮሎኔል ተክሉ በላይ
- ኮሎኔል ጥጋቡ መለስ
- ኮሎኔል ግርማ ተካ
- ኮሎኔል ሙሉጌታ ገብረክርስቶስ ነጋሽ
- ኮሎኔል አራሞ ገብረመድህን
- ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረመድህን
- ኮሎኔል ግርማል አለማየሁ
- ኮሎኔል ነጋሽ አለፎም
- ኮሎኔል ተስፋዬ ምሩፅ
- ኮሎኔል ካሳየ አሰፋ
- ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ ስዩም
- ኮሎኔል ኪሮስ ሓጎስ ገ/ዝጋብሔር
- ኮሎኔል ሙርፅ ገብረሊባኖስ አብርሃ
- ኮሎኔል ሓ/ስላሴ ኪሮስ ተስፋይ
- ኮሎኔል ምሩፅ በርሔ /ተወርወር/
- ኮሎኔል ኃይለሥላሴ አሰፋ
- ኮሎኔል ደርበው ኃጎስ
- ኮሎኔል ወልዴ ሀጎስ
- ኮሎኔል ንጉሴ አማረ
- ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ
- ኮሎኔል ባራኪ /ወዲ ራያ/
- ኮሎኔል ከበደ ገብረሚካኤል
- ኮሎኔል ፀጋ ብርሀን ገብረእዜር
- ኮሎኔል ዘሩ ሀ/መለኮት
- ኮሎኔል ኃይለ መዝገብ
- ኮሎኔል አርአያ ገብሩ ግደይ
- ኮሎኔል የማነ ገብረሚካኤል
- ኮሎኔል ዘሩ መረሳ
- ኮሎኔል ልጃለም ገብረህይወት
- ኮሎኔል ፍሰሀ ግደይ
- ኮሎኔል ገብረመስቀል ወልደገብርኤል
- ኮሎኔል ወልዱሀጎስ ገብሩ
- ኮሎኔል ገብረሚካኤል ሀጎስ
- ኮሎኔል ስብሀቱ መብራቱ
- ኮሎኔል ጣሰው ወ/ጊዮርጊስ
- ኮሎኔል ገብረእግዚያብሔር አለምሰገድ
- ኮሎኔል ነጋሲ ታደሰ
- ኮሎኔል ተክለ በላይ
- ሌተናል ኮሎኔል ተወልደ አብርሃ ወልደሚካኤል
- ሌተናል ኮሎኔል ሙዘይ ተሰማ ስዩም
- ሌተናል ኮሎኔል ሀዲሽ ገብረፃድቅ አለማየሁ
- ሌተናል ኮሎኔል ፍስሃ በየነ ገብረኪዳን
- ሌተናል ኮሎኔል ምሩፅ ወልደአረጋይ ገብረመስቀል
- ሌተናል ኮሎኔል ሙሩፅ በርሀ ኣበራ
- ሌተናል ኮሎኔል ፀሀዬ ሀጎስ
- ሌተናል ኮሎኔል ሀጎስ ኪሮስ
- ሌተናል ኮሎኔል ገብረ ህንፃ ሀዲሽ
- ሌተናል ኮሎኔል ፈለቀ አይጠገብ
- ሻለቃ አስገዶም መስፍን
- ሻምበል ባሻ ሙእዝ መልካም
- ሻምበል አርአያ ተክለሀይማኖት
- ሻምበል ተስፋ ህይወት
ናቸው። ከላይ ስማቸው የተዘረዘረው ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እሴቶች መካከል ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም የሚለውን ወደ ጎን በመተው የወንበዴው ጁንታ ህወሓት የጥፋት ቡድን የሴራ አካል በመሆን በወንጀል የሚፈለጉ መሆናቸውን ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው አሳውቋል።
በመሆኑም መላው የሀገራችን ሕዝቦች፥ በተለይም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና ሚሊሻዎች እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ የሀገራችን የፖሊስ ሠራዊና የደህንነት ተቋማት እነዚህን የጁንታውን የህወሓት የጥፋት ቡድን ተፈላጊዎች አድኖ ለሕግ ለማቅረብ እየተደረገ ባለው ጥረት በያላችሁበት የድርሻችሁን እንድትወጡ በማለት ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። በቀጣይም በጁንታው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እንዲሁም በሀገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉትንና በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራውም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ መረጃዎችን በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለሕብረተሰቡ ይፋ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
November 18, 2020 at 2:42 am #16733In reply to: ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveበተለያዩ ወንጀል ተግባራት ውስጥ ስለመሳተፋቸው ምርመራ ለመጀመር የሚያስችል በቂ ማስረጃ የተገኘባቸው የህወሓት ድርጅቶች ሀብቶቻቸው ታገዱ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የዘር-ተኮር ጥቃት እና የሽብር ድርጊት እንዲፈጸም የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሰው የትህነት/ ህወሓት ኃይል ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በመመሳጠር እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የተሳተፉ ስለመሆናቸው እና በግብር-ስወራ እና የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ስለመሳተፋቸው ምርመራ ለመጀመር የሚያበቃ በቂ ማስረጃ የተገኘባቸውን ከታች ስማቸው የተጠቀሱትን ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በባንክ ያላቸውን ገንዘብ ጨምሮ ከህዳር 07 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንዲታገዱ አድርጓል።
እግዱ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ድርጅቶቹ ሀብታቸውን ለማሸሽ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆኑ በቂ ማስረጃ የቀረበ በመሆኑ ንበረቶቹ ሳይሸሹ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ማቆየት ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ነው ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አሳውቋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የመመርመር እና ሀብትን የማስመለስ ሥራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ የታገዱት ንብረቶች እንዳይጎዱ እና እንዳይባክኑ ጠብቆ የሚያቆይ የንብረት አስተዳዳሪ የሚሾም ሲሆን፥ አስተዳዳሪው ሥራውን ተቀብሎ ማስተዳደር እስኪጀምር ድረስ የድርጅቶቹ አስተዳዳሪዎች ንበረቱን በሚገባ የመጠበቅ ኃላፊነት እንደለባቸው አስታውቋል።
በቀጣይ የምርመራ እና ክስ ሂደቱን ተከታትሎ ለሕዝቡ እንደሚያሳውቅም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው አትቷል። ሀብታቸው የታገደባቸው የህወሓት ድርጅቶች ከዚህ በታች ስማቸው የተዘረዘሩት ናቸው።
- ሱር ኮንስትራክሽን
- ጉና የንግድ ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ትራንስ ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ሰላም የሕዝብ ማመላለሻ አክሲዮን ማኅበር
- ሜጋ ማተሚያ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤፈርት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤፈርት ኤሌክትሪካል ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤፈርት ዲዛይን እና ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኢዛና ማዕድን ልማት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ቬሎሲቲ አፖራልዝ ካምፓኒስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- መሰቦ ቢውልዲንግ ማቴሪያል ፕሮዳክሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ሳባ ዳይሜንሺናል ስቶን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ
- ሼባ ታነሪ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ኤ.ፒ ኤፍ
- ሜጋ ኔት ኮርፖሬሽን
- እክስፕረስ ትራንዚት ሰርቪስ
- ደሳለኝ ካትሪናሪ
- ሼባ ታነሪ ፋክተሪ አክሲዮን ማኅበር
- ህይወት አግሪካልቸር መካናይዜሽን
- ህይወት እርሻ ሜካናይዜሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- አልመዳ ጋርመንት ፋክተሪ
- መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ
- ደደቢት ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበር
- አዲስ ፋርማሲቲካልስ ፕሮዳክሽን
- ትግራይ ዴቨሎፕመንት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ስታር ፓርማሲቲካልስ ኢፖርተርስ
- ሳባ እምነበረድ አክሲዮን ማኅበር
- አድዋ ፍሎር ፋክተሪ
- ትካል እግሪ ምትካል/ ትግራይ/ ት.እ.ም.ት/
- ብሩህ ተስፋ ፕላስቲክ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ደሳለኝ የእንስሳ መድኃኒት አስመጪና አከፋፋይ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
- ማይጨውፓርትክል ቦርድ ፋክተሪ
ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
November 7, 2020 at 3:21 am #16667In reply to: ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች
AnonymousInactiveየፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወሰነ።
ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲመለስ የተሰጠውን በቂ ዕድል መጠቀም ባለመቻሉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወስኗል።
ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት ፈጽሟል። በተጨማሪም በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።
የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 12 በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም፡
(1) በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤
(2) ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፤
(3) የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ እንደሚቆጠር ተደንግጓል። ከዚህ ድንጋጌ አንጻር ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል።
በዚሁ መሠረት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 (1) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጆቹ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም ሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ መስጠት ያለበት ሆኖ በመገኘቱ፥ ጥቅምት 28 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትንን ውሳኔዎች አሳልፏል።
- ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14 (2) መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣጣመ መልኩ አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤
- ሕገ-ወጡን የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የተቀመጡት ስልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል። በዚሁ መሠረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል። በተጨማሪም ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች ይኖሩታል። በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤
ሀ) አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤
ለ) የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤
ሐ) ሕግና ሥርዓት መገበሩን ያረጋግጣል፤
መ) አግባብ ባለው ህግ መሠረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
ሠ) የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤
ረ) በፌዴራል መንግሥቱ ሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል።
- ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ስለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ በማለት ወስኗል።
በመጨረሻም፥ መላው የትግራይ ሕዝብና የሀገራችን ሕዝቦች ሕገ-ወጡ ቡድን የፈፀመውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ የሀገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር በሚል መርህ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ መንግሥት እና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን እኩይ ዓላማ ይዘው እርስ በርሳችንን በማጋጨት ሀገራችንን ለመበታተን ሌትተቀን የሚሠሩ ኃይሎችን ነቅተን በመጠበቅና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዘብ እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት
-
AuthorSearch Results