-
Search Results
-
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያካሄደውን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀመንበርነት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን በአቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን በመተካት፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አመራሮችን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቀቀ።
ደብረ ብርሃን (አብን) – የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኘበት በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አብን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለሥ በሚያስችለውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ይገኝ ዘንድ ላለፉት ጊዜያት የመጣበትን መንገድ መርምሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ ማሻሽያ መዘጋጀቱን ገለፀው በዚህ ላይ ጠቅላላ ጉባዔው በደንብ ተወያይቶ አቋም እንዲይዝበት ጠይቀዋል።
ጉባዔው በመጀመረያ ቀን ውሎው የአብን መዋቅራዊ ማሻሽያ (reform) አስፈላጊነትና አላማ፣ የንቅናቄው ጥቅል የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የፋይናንስ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት፣ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሪፖርት፣ የተሻሻለው የንቅናቄው መተዳደሪያ ደንብና ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኃላ አፅድቋል።
ጠቅላላ ጉባዔው 5 ተለዋጭ አባላት ያሉት 45 የንቅናቄውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥም መርጦ ያፀደቀ ሲሆን የተመረጡት አባላትም የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጠዋል። በተጨማሪም በሊቀመንበሩ የቀረቡለትን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚዎችን አፅድቋል። በዚህም መሠረት 9ኙ የአብን ሥራ አስፈፃሚ አመራሮች፦
- አቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን – ሊቀመንበር፣
- አቶ የሱፍ ኢብራሂም – ምክትል ሊቀመንበር፣
- አቶ አዲስ ኃረገወይን – የፖሊሲ ስትራቴጂ ኃላፊ፣
- አቶ ጣሂር ሞሐመድ – የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
- ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም – የውጭ ጉዳይ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት
- አቶ ጋሻው መርሻ – የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣
- አቶ መልካሙ ፀጋዬ – የፅሕፈት ቤት ኃላፊ፣
- አቶ ጥበበ ሰይፈ – የሕግ እና ሥነ-ምግባር ኃላፊ፣ እና
- አቶ ክርስቲያን ታደለ – የፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው።
ምንጭ፦ አብን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦
- የህወሓት አመራሮችና አባላት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ህወሓት የሰጠው መግለጫ
- ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ
- ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ መፍርሱን እና ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ንብረት እንዲከፋፈል ምርጫ ቦርድ አጸደቀ
- በኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ― ኦነግ
- በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው! የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫየኢትዮጵያውያን የፍትህ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን የአያሌ ዜጎችን ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የወሰደ ረጅም ጉዞ ነው። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የሁሉንም ተሳትፎ ያማከለና አገዛዙ ከሚቋቋመው በላይ የሆነ ንቅናቄ የታየበት ትግል ተደርጓል። ውጤቱም የዛሬዋን ሁኔታ ወልዷል።
ከበርካታ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ እንዳየነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማዋለድ ከባድ ምጥ ያለበት የጭንቅ ጊዜ ማሳለፍ የግድ መሆኑን ነው። በኢትዮጵያችንም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው። በእንደዚህ ዓይነት አስጨናቂ ወቅት ይህን ሂደት እንደአንድ ከባድ ታሪካዊ ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ የመኖራቸውን ያህል ግርግር ፈጥረውና የራሳቸውን ፍላጎት በኃይል ለመጫን የሚፍጨረጨሩ ቡድኖችና ግለሰቦች መኖራቸውን በየእለቱ በየቦታው የምናየው አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።
ፓርቲያችን ከተመሠረተ ጀምሮ ለሀገር ሠላምና ለሕዘብ መረጋጋት የራሱን ያልተቆጠበ አሥተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። በእኛ ዕምነት የተያዘው የሽግግር ሂደት ለአንድ ወገን የማይተውና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነ እናምናለን። ያም ሆኖ በዚህ ፈታኝ ወቅት የመንግሥት ሚና ትልቅና ከፍተኛ እንደሚሆን እንገነዘባለን።
ፓርቲያችን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሠቱ ፈታኝ ሁኔታዎችንና የመንግሥትን ምላሽ በመገምገም በሚከተሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ይገልፃል።
- የየትኛውም በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ተግባር የሀገራችን ሕጎ እና ሀገራችን ያፀደቀቻቸውንና የተቀበለቻቸውን ድንጋጌዎች ባከበረ መልኩ ብቻ እንዲሆን ማድረግ የሚገባን ዛሬ ነው። ዜጎች በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ካልተረጋገጠላቸው እና ከሕግ በታች መሆናቸውን ካልተረዱ ማንም እየተነሳ የፈለገውን አድርጎ “አልጠየቅም” የሚል ማንአለብኝነት ከሠፈነ መቼም ማቆሚያ ወደማይኖረው የሁከት ዓለም ጅው ብሎ እንዳይገባ ያሠጋል።
- የሁሉም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በነፃነት እና በሠለጠነ መንገድ መግለፅ፣ በሥልጣን ላይ ያለውንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን መተቸት፣ ማጋለጥ አልፎም በምርጫ ከሥልጣን ማውረድ የተለመደና ተገቢም ሊሆን ይችላል። ሀገርን የሚያዋርድ ተግባር መፈፀም ግን ለማንም ያልተፈቀደ የሀገር ከህደት ወንጀል መሆኑ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል። በሕዝብ፣ በሃይማኖቶች፣ በብሔረሰቦች፣ በሰንደቅ ዓለማና በመሳሰሉት የአገር መገለጫዎች ላይ የሚፈፀም ማንኛውም የነውር ተግባር አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚያስከትል መሆን አለበት።
- ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚሠጠው ትኩረት ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየና ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚጠብቃቸው መሆን እደሚገባው እናምናለን። በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርስቲ ግቢዎች የተከሠቱ ችግሮች የሕዝባችንን ልብ ሰብረው ያለፉ ክስተቶች ናቸው። ከሁሉም በላይ በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የተደረገው እገታ ውሉ የጠፋና የመንግሥትን የተማሪዎችን ህይወት የመጠበቅ ኃላፊነት አለመወጣት ያጋለጠ ነው። ከዚህ ቀደም መንግሥት ስለለተማሪዎቹ እገታ ወቅቱን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለተማሪዎቹ ቤተሰቦች እና ለሕዝብ እንዲሰጥ ኢዜማ መጠየቁ ይታወሳል። ሆኖም መንግሥት ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ከፍተኛ ክፍተት ታይቶበታል። ከዚህ አንጻር መንግሥት ተማሪዎቹን ከእገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ እና የሕዝብን ልብ እንዲያሳርፍ አበክረን እንጠይቃለን።
- “በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸም ግፍ ለየትኛውም አካባቢ ለሚገኝ ሰላም ጠንቅ ነው” እንዲሉ፥ ለተማሪዎቻችን የመቆም ጉዳይ የአንድ ወገን ወይም የአንድ ክልል ጉዳይ ሊሆን አይገባውም። የሁላችንንም ተናብቦ መሥራት ግድ ይላል። ከዚህ አንጻር የታገቱ ልጆቻችንን በሰላም ለማስለቀቅ ሕግ እና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች በሕዝባችን የሚደረጉ ሀቀኛ ጥረቶችን እንደግፋለን።
- ሀገርን እና ሕዝብን የማወክ አንድ አካል የሆነው የሞጣ መስጂዶችን የማቃጠል ድርጊት በአጥፊዎቹ ላይ አስተማሪ ርምጃ ተወስዶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ መስጂዶቹን አድሶና ምዕመናኑን ክሶ ወደቀድሞው ሰላማዊ አገልግሎት ለመመለስ የሚደረጉትን የአብሮነት እንቅስቃሴዎችን እንደግፋለን።
- በቅርቡ የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በተወሰኑት አካባቢዎች በተለይም በአቦምሳ የከተራ በዓል ሳይከበር የቀረበትን ሁኔታ ታዝበናል። የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዳይከበር እንቅፋት የሆኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ እንጠይቃለን።
- ኢዜማ የምርጫ ወረዳዎችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንደዚሁም ሕዝባዊ ውይይቶች በሚያካሄድበት ጊዜ ጥቂት ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ግርግር ሕዝብን የሚወክል እንዳልሆነ ብንረዳም በአጠቃላይ የፖለቲካ ድባቡ ላይ የሚፈጠረው የስሜት መሻከር ያሳስበናል። በተለይም ወደምርጫ ለመግባት ዝግጅት እያደረግን ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት ሕዝቡ ሕገመንግሥታዊ የሆነውን የመሰብሰብ መብቱን መጠቀም የማይችልበት ሁኔታ ይታያል። ባሳለፍነው ሳምንት በተከሠቱ በተለይ የጎንደር እና የሸዋሮቢት ድርጊቶችን ተከታትሎ አጥፊዎችን እንዲቀጣ አቤቱታችንን ለመንግሥት አቅርበናል። ኢዜማ ላይ የሚከሠቱ ችግሮች ሁለት ገጽ አላቸው አንደኛው ከመንግስት መዋቅር የሚመጣ ሲሆን ሁለተኛው ከዚያ ውጭ የሆኑ ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ነው። “ባለጌና ጨዋ በተጣሉ ጊዜ ለጊዜውም ቢሆን ባለጌ ያሸነፈ ይመስላል” የሚል የቆየ የሀገራችን ብሂል አለ። ይህም ጨዋው በሕግ ስለሚያምንና የሕግ አስከባሪ ባለጌውን ይቀጣል፤ ብሎ በማመን ነው። በእኛ መዋቅርም የሚታየው ይሄው ሕግን የማክበር ጉዳይ ነው፤ ይህም ቢሆን ልክ አለው፤ ከገደብ ያለፈ ነውር ሲፈፀም አመራሩም፣ አባሉም፣ ደጋፊውም ራሱን፣ ፓርቲውንና ሀገሩን የመጠበቅ ተፈጥሯዊ መብት አለው። ኢዜማ ሀገርንና ሕዝብን ለድርድር አያቀርብም። ይህንንም ደግመን ደጋግመን ተናግረናል! መንግሥት በራሱ ውስጥም ሆነ ከራሱ ውጭ ያሉትን ሥርዓት አልበኞች በሕግ ሊቀጣ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ራሱን ወደመከላከልና ሰላሙን ወደ ማስጠበቅ ሊገፋ ይችላል። ይህም በየትኛውም መመዘኛ ስህተት ሊሆን አይችልም።
በመጨረሻም የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን መጠበቅ ለሁላችንም የሚጠቅም ሀገር እና ሕዝብን የሚታደግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አውቀን እንድንጓዝበት መልዕክታችንን እያስተላለፍን ሥርዓት አልበኝነትን በጋራ በቃ የምንልበት ጊዜው ዛሬ መሆኑን በአፅንኦት እንገልፃለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት ጥር 16 እና 17 ቀናት 2012 ዓ.ም. 5ኛ መደበኛ ጉባዔውን በማካሄድ የንቅናቄያችንን አጠቃላይ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ፣ የምርጫ ዝግጅት፣ የታሠሩ የአብን አመራሮችና አባለትን፣ የታገቱ አማራ ተማሪዎችን እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔ እና አቅጣጫ በማስቀመጥ አጠናቋል።
በአገራችን ኢትዮጵያ አማራ-ጠል የተሳሳተ ትርክት በፈርጣጭ ብሔርተኞች መቀንቀን ከጀመረ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያሳለፈ ቢሆንም፥ ለሦስት አስርት ዓመታት መዋቅርና ሕግ ሆኖ አማራን እንደ ሕዝብ ለመጨቆን ሥራ ላይ ውሏል። የአማራ ሕዝብ የተገንጣይ ብሔርተኞች የተሳሳተ ትርክት እንዲቆም ብሎም ኢትዮጵያዊያን በሰላምና በአንድነት ተከባብረው እንዲኖሩ ሲታገል ቆይቶ በ2010 ዓ.ም. ለውጥ እንዲመጣ ቢያድርግም ለውጡን እንመራለን እና እናሻግራለን የሚሉት “ተረኛ ነን” ባዮች የቆየውን ትርክት ለማስቀጠል በሚያደርጉት ልፊያ ሕዝባችን በተደጋጋሚ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።
የአማራ ሕዝብ በሰላምና በመተሳሰብ እሴቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ተዋዶና ተከባብሮ የኖረ ወደፊትም የሚኖር ሕዝብ መሆኑ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ሀቅ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያዊያንን የቆየ እሴት የማይወክሉ ብሎም እንቆምለታለን ብለው የሚምሉለትን ሕዝብ ዓላማና ፍላጎት የማያውቁ ተገንጣይ የፖለቲካ ቡድኖች በሚያቀነቅኑት የአማራ-ጠል ትርክትና እንቅስቃሴ የተነሳ የአማራ ሕዝብ ለከፍተኛ ጭቆና ተዳርጎ ቆይቷል። የአማራ ሕዝብ ትግል የኅልውናና ፀረ-ጭቆና መሆኑ የታወቀ ሲሆን፥ ባለፉት ዓመታትም ጭቆናን ሲታገል የነበረው አንደኛው ጨቋኝ በሌላኛው ጨቋኝ እንዲቀየር አልነበረም፤ አይደለምም። ሆኖም ግን “የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት መንሳት” የሚለው ትህነጋዊ ትርክት በተረኛ መንግሥት ነን ባይ ቡድኖችና ተቀፅላዎች በመተካቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት በ5ኛ መደበኛ ጉባዔው በሚከተሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔና አቅጣጫ አስቀምጧል።
የታገቱ አማራ ተማሪዎችን በተመለከተ፡-
በደንቢዶሎ ዩንቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ አማራ ተማሪዎች ታግተው ከጠፉ ሁለት ወራት አልፈውታል። ይህ የአሸባሪነት ተግባር በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠውና የታገቱ ልጆች እንዲለቀቁ አብን መጠየቁ ይታወሳል። የአማራ ሕዝብ እና ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይህን ነውረኛ የአሸባሪነት ተግባር አውግዞ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በትዕግስት ሲጠይቅ ቆይቷል። የአብን ብሔራዊ ምክር ቤት በዚህ የአሸባሪነት ተግባር የታገቱ አማራ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ አሸባሪዎችም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እያሳሰበ፤ ለታገቱ አማራ ተማሪዎች ድምፅ ለማሰማት በተለያዩ ከተሞች በአማራ ወጣቶች የተጠራውን ሰልፍ አብን የሚደግፍ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሰላማዊ ሰልፉም ከየትኛውም ጥቃትና ጥፋት ነፃ በሆነ መንገድ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃና ከለላ የማድረግ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ እናሳስባለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ “ክልል” መንግሥትና ማዕከላዊ መንግሥቱ ላሳዩት የበዛ ቸልተኝነት ተጠያቂነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጊቱን ላልተገባ የፖለቲካ ቁማር ከማዋል ተቆጥበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በጥብቅ እናሳስባለን። መላው የአማራ ሕዝብ ቀጣይ በልጆቹ ዙሪያ መንግሥት የሚሰጠውን ምላሽ እየተከታተለ ለቀጣይ ትግሎችም ራሱን እንዲያዘጋጅ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
የፖለቲካና የኅሊና እስረኛ የሆኑ የአብን አመራርና አባላትን በተመለከተ፡-
የአማራ “ክልል” ከፍተኛ አመራሮች እና የፌዴራል የጦር መኮንኖች ግድያ ተከትሎ “የክልሉ”ም ሆነ ማዕከላዊ መንግሥት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ከመሆኑም በላይ ካላንዳች የፖለቲካ ትርፍ ስሌት ኃቁን በወቅቱ ለሕዝብ ማቅረብ ሲገባቸው፤ በሕዝብ ላይ የደረሰውን አሳዛኝ በደል እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ይባስ ብሎ ንጹሃን የንቅናቄያችን አመራሮችና አባሎቻችንን በታሪክ አጋጣሚ መንግሥት የመሆን ዕድል የገጠመው ቡድን ለአማራ ሕዝብ ካለው የተሳሳተ የጥላቻ አመለካከት በመነሳት በግፍ አግቷቸው እንደሚገኝ ይታወቃል። ገዢው መንግሥት የንቅናቄያችንን አመራሮችና አባላት በቂ ባልሆነ ማስረጃ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ብቻ ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ አቆይቷቸዋል።
የአማራን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ብሎም የአገርን ኅልውና ግምት ውስጥ በማስገባት ያለአግባብ የታሰሩ የአብን አመራሮችና አባላት በውይይት እንዲፈቱ ከ7 ወራት በላይ ኃላፊነት በተሞላበት እጅግ ከፍተኛ ትዕግስት የጠየቅን ከመሆኑም በላይ ጓዶቻችን ያልተገባ መስዋዕትነት እየከፈሉ ይገኛሉ። ይህንንም አስመልክቶ ንቅናቄያችን ለሕዝብና ለመንግሥት በተከታታይ ያሳወቀ ቢሆንም ከመንግሥት በኩል ፍትህ በመነፈጉ ምክንያት ለሕዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ቀጣይ የሰላማዊ ትግል አማራጮችን ለመጠቀም ተገደናል። ስለሆነም መንግሥት ያለአግባብ በአፈሳ የፈፀመውን እስር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ክሳቸው ተቋርጦ በአንድ ወር ውስጥ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እያሳሰብን፤ በተቀመጠው ጊዜ የማይፈቱ ከሆነ በየደረጃው ያሉ የንቅናቄያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ሕዝባችንን በማስተባበር እንደሚከተለው በተገለጸው የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት ሁሉንም የሰላማዊ ትግል አማራጮች እንተገብራለን።
-
- የካቲት 22/2012 ዓ.ም፡- በተመረጡ የአገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል፤
- የካቲት 26 እና 27/2012 ዓ.ም፡- አድማ ይደረጋል፤
- ከመጋቢት 3/2012 ዓ.ም ጀምሮ አመራሮቻችን እና አባሎቻችን እስከሚፈቱ ድረስ ለተከታታይ ቀናት ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲካሄድ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ የወሰነ ሲሆን ለዚህም ከወዲሁ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ከዩኒቨርሲቲዎች ስለተፈናቀሉ ተማሪዎች፡-
መንግሥት አገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች በሰላም ትምህርታቸውን መከታተል ካለመቻላቸውም በላይ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና የሞት አደጋ ገጥሟቸዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የዩኒቨርሰቲ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ይህ በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸም በደል አማራ ላይ የእውቀት ሽግግር እንዳይኖር ሲደረግ የኖረው መንግሥታዊ ጭቆና መገለጫ መሆኑን አብን ይገነዘባል። ስለዚህ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተማሪዎቹ ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትን መንገድ በአስቸኳይ እንዲያመቻች አብን ያሳስባል።
አገራዊ ምርጫን በተመለከተ፡-
ንቅናቄያችን ያዘጋጀው የምርጫ ማኒፌስቶ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን ምክር ቤቱም ተጨማሪ ጉዳዮች ተካተውበትና በተለያዩ አካላት ውይይት እንዲደረግበት እንዲሁም ንቅናቄያችን በቅርቡ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲፀድቅ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በመጨረሻም በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያለ መላው የአማራ ሕዝብና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ቡድን የሚፈጸምን ኢ-ሰብአዊና የአሸባሪነት ተግባር ተባብሮ እንዲያወግዝ ብሎም ለፍትኅ፣ እኩልነትና ነጻነት እንዲሁም የሕግ የበላይነት መረጋጋጥ እንዲታገል ንቅናቄያችን ጥሪውን ያስተላልፋል።
አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል!
የአማራ ብሔራዊ ነቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት፤
ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስ አበባ፥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ስር በአደራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጐብኝተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ስር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ኃይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሆኔታቸውንም ተመልክተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍሉ በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል።
በሌላ በኩል “ታሳሪዎቹ ከ 3–4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰርት ሊቀርብ ይገባል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
“ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማታሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ለጉዳዮቹ ሁሉ ሕጋዊ እልባት ለማግኘት ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ኮሚሽኑ ክትትሉን እየቀጠለ መሆኑን አሳውቀዋል።
ጉብኝቱ በዓለም ዓቀፍ የእስር ቤቶች ጉብኝት ደረጃ መሠረት ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የተደረገ ሲሆን የፖሊስ ኮሚሸኑ አመራሮች እና የጥበቃ ክፍል ኃላፊዎች ለዋና ኮሚሸነሩ ጉብኝቱ በማመቻቸት ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ዋና ኮሚሸነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምንጭ፦ የኮሚሽኑ ፌስቡክ ገጽ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ