-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሳይንስ ሳምንትን ከጥቅምት 25 ቀን እስከ ህዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት ያከብራል።
የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ዓላማዎችና መሪቃል ይከበራል። የኢትዮጵያው የሳይንስ ሳምንት ሲከበር የተባበሩት መግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) በየዓመቱ ኖቬምበር 10 ቀን የሚያከብረውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ባማከለ ሁኔታ ይፈፀማል።
ይህ ሀገራዊ የሳይንስ ሳምንት ሲከበር ዋና ዓላማው ሳይንሳዊ አስተሳሰብንና አሠራርን፣ የሳይንስ ባህል ግንባታ ሥራዎቻችንን ለማሳወቅና እንዲሁም በተለያዩ ሳይንሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በቀጣይም የወጣቱን ትውልድ የሳይንስ ፍላጎት ለማሳደግ እንዲያግዝ ሳይንስ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሳይንስን፣ ሳይንሳዊ እንቅስቃሴዎችን እና የሳይንሳዊ ጥናቶችን ለሕዝብ ለማስተዋወቅም ያለመ ነው።
በሳይንስ ሳምንት ከሚከናወኑ ዝግጅቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
- ከጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል በSTEM (Science, Technology, Engineering, and Mathematics) ዘርፎች ውድድር ይካሄዳል። ተማሪዎቹ በአራቱ የትምህርት ዘርፎች ለውድድር በሚያቀርቡት ፈጠራ ላይ ተመሥርቶ በሚሰጠው ዳኝነት አሸናፊዎች እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ተሸላሚ ይሆናሉ።
- ሐሙስ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶችና ሙያ ማኅበራት ጋር በሒልተን ሆቴል ምክክር ያደርጋል:: በምክክር መድረኩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሳይንስ ሥራዎችና የትኩረት አቅጣጫ፣ የሙያ ማኅበራት ሚና ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና፤ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት ዕይታ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶች የሳይንስ ሥራዎች ትኩረትና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር “ለኢትዮጵያ ግብርና አገር በቀል እይታ” በሚል የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ ይካሄዳል።
- አርብ ጥቅምት 28 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ሳይንስ ለልማትና ብልፅግና በሚል ርዕስ የተለያዩ ባድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሀገራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር ወርክሾፕ ይካሄዳል።
- እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የአረንጓዴ ቀን (Green Day) ይከበራል። በዕለቱ ባለፈው ክረምት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተተከሉ ችግኞችን ቦታቸው ድረስ በመገኘት የመንከባከብ ሥራዎች ይሠራሉ። እፅዋቱ ባሉበት ደረጃ በሚሠሩ የእንክብካቤ ሥራዎች ላይም በተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ሳይንሳዊ ገለፃ ይቀርባል።
- ሰኞ ሕዳር 01 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የባዮዳይቨርሲቲ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute) ጋር በመተባበር “ሰውና ሥነ ምህዳር (Man and Biosphere)” በሚል ርዕስ ትምህርታዊ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል። በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጥሮ ሳይንስና ግብርና ኮሌጆች በርዕሱ ላይ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።
- ማክሰኞ ሕዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biotechnology Institute) ጋር በመተበባር “ባዮቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ በዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርታዊ ገለፃ ይቀርባል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ ሳይንሳዊ ገለፃዎችና ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ስለሆነም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. በሚጀምረው የሳይንስ ሳምንትን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተውት ለህብረተሰቡ የሚመጥኑና ሳይንሳዊ ግንዛቤዎችን የሚፈጥሩ ሥራዎችን በመሥራት የሳይንስ ሳምንት አከባበር አካል እንዲሆኑ እንጋብዛለን።
በተጨማሪም ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የሳይንስ ሳምንት፣ በየዘርፋቸው ሳይንስ ለአገር ልማትና ብልፅግና ያለውን ፋይዳ የሚያሳዩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ በበዓሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንጋብዛለን።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ጠብቀው ከመሥራትና ማህበረሰቡን ከማስተማር ይልቅ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ የሚሠሯቸውን የዘገባ ስህተቶች እና አባባሽ ይዘቶች እንዲያስተካክሉ በቃልና በደብዳቤ እያሳወቅኩ ነው ይላል።
ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚፅፉት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ “የክልል መገናኛ ብዙሃን ወገንተኝነት እና ለገዥው ቡድን አጎብዳጅነት” እንደሚታይባቸው አንስተው፤ ብዙ ፖለቲካዊ ዘገባዎችን እና ትርክቶችን በተዛባ መልኩ የሚያቀርቡ እንደሆኑ ነው የገለጹት።
ዘውግ-ተኮር የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው ያለመዘገብ፣ ሀቅን እንዳለ ያለማቅረብና ሚዛናዊ አለመሆን እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፥ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ግጭት በሚስተዋልበት ወቅት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዳይዘግቡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስህተት የሚፈጽሙት ባለማወቅ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ ዓይነት ስህተት እንዲወጡ መጀመሪያ በማስተማር የተለየ ሁኔታ ሲያጋጥም በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ የሕዝብ ማስተማሪያ አልያም የጦር መሣሪያ የመሆን ዕድል ስላላቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሀሳባቸውን በመስጠት፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣልም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ሃይማኖት ጌታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ “ፅንፍ ይዞ እየተጓዘ” መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ለግጭት አባባሽ እየሆነ ነው ይላሉ።
በተለይ አንዳንድ “የፅንፍ ፖለቲካ” የሚያራምዱ ግለሰቦች የራሳቸውን መገናኛ ብዙሃን በመክፈት የሚፈልጉትን “ፅንፈኛና የጥላቻ አጀንዳ” እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል። በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በኩል ደግሞ “ሕዝብ ሲሞት እና ጉዳት ሲደርስበት ተከታትሎ ከመዘገብና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ መንግሥትን እየጠበቁ የመዘገብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል” ነው ያሉት።
መገናኛ ብዙሃኑ አስቀድመው የስጋት ትንተናዎችን በሚዛናዊነት በማቅረብ ግጭትን የመከላከል ሚና እየተወጡ አይደለም ያሉት አቶ ሃይማኖት፥ ብሮድካስት ባለስልጣንም ለመገናኛ ብዙሃኑ የተሰጣቸው ነጻነት እንዳይታፈን ጥንቃቄ በማድረግ፤ በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ባሉት ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደወሰን አንዱዓለም “የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ በተረበሸ ቁጥር መገናኛ ብዙሃኑም አብረው መታመማቸው ከፍተኛ ችግር አስከትሏል” ነው ያሉት።
አብዛኛው መገናኛ ብዙሃን ሕዝብን ከሕዝብ፣ ክልልን ከክልል፣ መንግሥትን ከሕዝብ የሚያራርቁ ዘገባዎችን እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች የሕይወት መልኮችን ትተው ፖለቲካ ላይ ብቻ የመጠመድ ችግር ይታይባቸዋል ነው ያሉት።
ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃኑን ሥራዎች መዝኖ እርምጃ ለመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፖለቲካዊ መስፈርት በመቀየር ሙያዊ መመዘኛ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፥ በመስፈርቱ መሠረት ድክመትና ጥንካሬ ተለይቶ እንዲያስተካክሉት ለተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ደብዳቤ መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።
“ሀገሪቱ ለውጥ ላይ ናት በሚል መገናኛ ብዙሃኑ የነውጥ አራጋቢ ሆነው እንዲቆዩ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ የፖለቲካ ሁኔታ በተረበሸ ቁጥር ሚዲያው አብሮ መረበሽ እንደለሌበትና በቅርቡ በሚወጣው የመገናኛ ብዘሃን አዋጅ ግልፅ ድንበር እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ አመራሮች በቦርድም ሆነ በሚዲያ መሪነት እንዳይሰየሙ በረቂቅ አዋጁ መቀመጡን አንስተው፥ መገናኛ ብዙሃኑ ከባለሥልጣኑ ጋር እንደ ‘አይጥ እና ድመት’ ከሚተያዩ እርስ በራሳቸው የሚተራረሙበት፣ የሚነጋገሩበትና የሚደጋገፉበት የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል መቋቋሙንም ነው የገለጹት።
“በልቅነት እየሠሩ ያሉትን ለማረም ሲባል በነጻነት ላይ ያሉት መጎዳት የለባቸውም” ያሉት አቶ ወንደወሰን፥ ችግሩን ለማረምና ሁለቱን ለመለየት ከውይይትና ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በቀጣይ በሕግ የተጠና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በጥቅምት ወር ሁለተኛ ሳምንት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች 78 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እና ግጭት በመቀሰቀስ የተጠረጠሩ 409 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ (ፋና) – ከጥቅምት 11 ቀን፣ 2012 ዓ.ም. ክስተት ጋር ተያይዞ ግጭት በመቀስቀስ የተጠረጠሩ 409 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥቅምት 20 ቀን፣ 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ላይ በወቅቱ በነበረው ግጭት የ78 ዜጎች ሕይወት ማለፉን አንስተዋል።
በወቅቱ በግጭቱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የፀጥታ መዋቅሩ በሙሉ አቅሙ መሥራቱንም ነው የገለፁት። የጸጥታ አካላት ችግሮች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለማረጋጋት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ችግሩን ለማርገብ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ላደረጉት አስተዋፀኦ መንግሥት ምስጋናውን አቅርቧል።
በሀገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በተፈጠሩ ተመሳሳይ ግጭቶች ከተጠረጠሩ 3 ሺህ 221 ግለሰቦች መካከል ከ2 ሺህ በላዩ ለሕግ መቅረባቸውን አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግርዋል።
የህብረተሰቡን ደኅንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ክስተቶች እየሰፉ በመምጣታቸው ሰላምን የማስከበር ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጠው መንግሥት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን አንስተዋል፡፡ ማንም ከሕግ በላይ ስላልሆነ በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ አካል ላይ ተጠያቂነት እንደሚረጋገጥም አስታውቀዋል።
አቶ ንጉሱ ጥላሁን በመግለጫቸው፥ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ከለውጡ ትሩፋቶች መካከል አንደኛው የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት መሆኑን አንስተዋል። ሆኖም አንዳንድ መገናኛ ብዙኃንና የማህበረሰብ አንቂዎችን ነጻነት ሽፋን በማድረግ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ መረጃዎችን እያሰራጩ በመሆኑ የመቆጣጠር ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ከኢህአዴግ ውህደት ጋር በተያያዘም አቶ ንጉሱ በመግለጫቸው በሀገሪቱ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት ታስቦ የመጡ ሃሳቦች ሆን ተብሎ ባልተገባ መንገድ እየተተረጎሙ ለሕዝብ ማደናገሪያነት እየዋሉ ነው ብለዋል – አቶ ንጉሱ ጥላሁን። ሃሳቡ ፓርቲው ለበርካታ ዓመታት ሲመክርበት የቆየ፣ በጥናት የተደገፈና የበርካታ የሰለጠኑ ሀገራት የተቀመረበት አሁን ለደረስንበት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የሚመጥን ሃሳብ ነው ብለዋል። ከዚያም ባለፈ የአገሪቱን ህዝቦች ከባለቤትነትና ደጋፊነት ወደ እኩልነትና በአንድ ድምጽ ወደ መወሰን የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሀገር የማዳን ጥሪ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነትባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሥርዓት አልበኞች በተወሰደ የጥፋት እርምጃ የማይተካ የዜጎቻችንን ሕይወት አጥተናል፣ የብዙዎች አካል ጎድሏል፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩት ንብረት ወድሟል እዲሁም በተዘጉ መንገዶች ምክንያት ዜጎች ተንገላተዋል፤ የሀገሪቷ የኢኮኖሚ እቅስቃሴም ተስተጓጉሏል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዜጎች ሕይወት ላይ በደረሰው ጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል። ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል። የተፈጸመውን ሕገ ወጥ እና አሳፋሪ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል!
የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረጉ የሥርዓት አልበኞች ሙከራዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ መጥቷል። የመንግሥት እነዚህን ሙከራዎች አስቀድሞ የመተንበይ፣ ሲከሰቱም አፋጣኝ እና ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅሙ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እየታየበት አይደለም። በዚህም ምክንያት የዜጎች ሕይወት በተደጋጋሚ አደጋ ላይ ወድቋል፤ አሁንም እየወደቀ ይገኛል። በቁጥር ቀላል የማይባሉ ዜጎች በሀገራቸው ደኅንነታቸው ተጠብቆ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት እና የመኖር መብታቸውን መጠቀም የማይችሉበት ብቻ ሳይሆን በማያቋርጥ ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የተገደዱበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከዚህም አልፎ በዕምነት ተቋማት እና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለመተማመን ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ የማይታረም ከሆነ የሽግግር ሂደቱ ተጨናግፎ ወደማንወጣው ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል።
መንግሥት የችግሩን ጥልቀት እና ሕግ የማስከበር ድክመቱን በሚገባ ፈትሾ በአስቸኳይ ክፍተቶቹን እንዲያስተካክል እና የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ እና ጥፋተኞችን ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቀን እናሳስባለን።
መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ የጋራ ሀገራችንን ከጥፋት አፋፍ ለማዳን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የሚገባን ወቅት ላይ መሆናችንን ተገንዝበን ልዩነቶቻችንን አቻችለን በአንድነት እንድንቆም እና ሀገራችን ከተደቀነባት ከባድ አደጋ እንድንታደግ ከአደራ ጭምር ጥሪ እናስተላልፋለን።
የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
ምንጭ፦ ኢዜማ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ (ህወሃት እየፈጠረ ያለው ተግዳሮት)
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
- “ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል” በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
- ጥፋተኞች ለሕግ ይቀርባሉ፤ ሰላምን ለማስፈን እንተጋለን ― አዲስ የተሾሙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው
- ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስ አበባ፥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ስር በአደራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጐብኝተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ስር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ኃይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሆኔታቸውንም ተመልክተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍሉ በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል።
በሌላ በኩል “ታሳሪዎቹ ከ 3–4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰርት ሊቀርብ ይገባል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
“ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማታሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ለጉዳዮቹ ሁሉ ሕጋዊ እልባት ለማግኘት ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ኮሚሽኑ ክትትሉን እየቀጠለ መሆኑን አሳውቀዋል።
ጉብኝቱ በዓለም ዓቀፍ የእስር ቤቶች ጉብኝት ደረጃ መሠረት ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የተደረገ ሲሆን የፖሊስ ኮሚሸኑ አመራሮች እና የጥበቃ ክፍል ኃላፊዎች ለዋና ኮሚሸነሩ ጉብኝቱ በማመቻቸት ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ዋና ኮሚሸነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምንጭ፦ የኮሚሽኑ ፌስቡክ ገጽ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።
—–አዲስ አበባ (ማኅበረ ቅዱሳን) – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ዓርማ አድርጋ ስትጠቀምበት የኖረችውን እና አሁንም የምትጠቀምበትን ባንዲራ ለበዓል ይዛችሁ ወጥታችኋል፤ በቤተ ክርስቲያን ጣሪያ እና ጉልላት ላይ ቀብታችኋል በማለት ምእመናንን የሚያዋክቡ፣ ወጣት ክርስቲያኖችን የሚያስሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ።
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያንን ተቀማጭ ገንዘብ ከንግድ ባንክ አውጥታችሁ እኛ በምንፈልገው ባንክ አስቀምጡ በማለት የሚያስገድዱ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀው 38ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጠናቀቀበት ዕለት ነው።
ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው፣ የሐሰት ታሪክ ፈጥረው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚነዙ አቀጣጣዮችን (‘አክቲቪስት’/ ‘activist’ ነን ባዮች) እና ፖለቲከኞችን እኩይ ድርጊት መቃወም እንደሚገባ ጉባኤው በመግለጫ አሳውቋል።
ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።
የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም ጉባኤው አሳስቦ አገራዊ ለውጡ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው እኩይ ተግባር ቤተ ክርስቲያንን እያሳዘናት እና እያሳሰባት መሆኑንም አስገንዝቧል።
በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን ጥፋት በሰላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ እንደሚኖርበትም አሳስቧል።
የጥምቀት እና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ነጥቀው፣ አንዳንድ ጊዜም ቆርሰው ለሌሎች የሚሰጡ አካላትን እኩይ ድርጊት አጥብቆ የተቃወመው መግለጫው በአገር ውስጥም በውጭም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እኩይ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥበብ እና በትዕግሥት ማሳለፉ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጧል።
ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ አድናቂዎች ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፈ የመጣው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። ቁራኛዬ ፊልም ሦስት ሽልማቶችን ሲያገኝ፥ ድምጻዊ ቸሊና እና ዘመን ተከታታይ ድራማ ሁለት፣ ሁለት ሽልማቶችን አግኝተዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ እጅግ መቀዛቀዝ፣ የሙዚቃ አልበምም ህትመት መፍዘዝ፣ ፊልም ሠሪዎችም ሥራዎቻችውን ተመልካቾች ፊታቸውን ባዞሩባቸው ወቅት እንደ አንድ የኪነጥበብ አባልና የሚዲያ ባለሙያ አቅማቸው በፈቀደ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት፣ እንዲሁም አድማጭ እና ተመልካቹን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማነቃቃት በማሰብ ነበር ጋዜጠኛ ብርሀኑ ድጋፌ እና ባልደረቦቹ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ላይ “ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት” ሥነ ሥርዓትን የየጀመሩት።
በእርግጥ ኪነ-ጥበብና ኢትዮጵያ ሀገራችን በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው መንገድ እጅግ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቁርኝት ቢኖራቸውም ቅሉ የኪነ ጥበብ ሙያዉን እንደተከበረ ሙያ ባለሙያዉንም የተከበረ ሙያ እንዳለው ቆጥሮ ወቅት ጠብቆ በተገደበ የጊዜ ኡደት ለሙያውና ለባለሙያው ተገቢውን ዕውቅና፣ ብሎም ክብር የሚሰጥ ቋሚ ተቋም ባለመኖሩ ያለመኖሩን በማስገንዘብ የሥነ ስርዓቱ ሀሳብ ጠንሳሾች “ለምን እኛ የቻልነውን አናደርግም?” በሚል ነበር የኪነ ጥበብ ሰዎችን በዓመት አንድ ጊዜ እያሰባሰቡ ለማወያየት፣ በዓመቱ በሙያውና በሙያቸው ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉትን “በጎ ሥራ ሠርታችኋል! ይበል!” ለማለት ለዛ የኤድማጮች ምርጫ ሽልማትን በ2003 ዓ.ም የጀመሩት።
በ2003 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ ሽልማት ‘የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ’፣ ‘ምርጥ ተዋናይት’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ፊልም’ እና ‘የዓመቱ ምርጥ አልበም’ በሚሉ አምስት ዘርፎች (ዘውጎች) ኢትዮጵያውያን የኪነ ጠበብ ሰዎች ተመርጠው የተሸለሙ ሲሆን ሽልማቱም ያገኙትም ከያኒት ዘሪቱ ከበደ “አርቴፍሻል” በሚለው ነጠላ ሙዚቃዋ፣ ተዋናይት ሰሃር አብዱልከሪም “ያንቺው ሌባ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣ ጋሽ አበበ ባልቻ “ሄሮሺማ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣ “ሄሮሺማ” ፊቸር ፊልም በምርጥ በፊልምነት፣ እንዲሁም ከያኒ ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) በመጀመሪያው አልበሙ በአምስቱ የተዘረዘሩት ዘርፎች አሸናፊዎች ሆነው የሥነ ሥርዓቱ የበኩር ተሸላሚዎች ሆኑ።
በዚህ መልኩ የተጀመረው ለዛ የአድማጮች ምርጫ በየዓመቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ሃምሌ ድረስ የሚወጡ የኪነ ጥበብ ሰዎችንና ሥራዎችን በአድማጮች ምርጫ አወዳድሮ ዕውቅና እየሰጠ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሳታፊዎችን እያበዛ፣ በባለሙያዉም፣ በመራጭነት በሚሳተፈውም ይሁን በየበይ ተመልካችነት በሚከታተለው ኢትዮጵያዊ ዘንድም ተወዳጅነት እያተረፈ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። በዘጠነኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች ሽልማት ያገኙት የሚከተሉት ናቸው።
- ምርጥ ነጠላ ዜማ፦ “ቢልባ” (ጃንቦ ጆቴ) [ኦሮምኛ ሙዚቃ]፣
- ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፦ ቸሊና የሺወንድም (“ቸሊና” በተባለው የሙዚቃ አልበሟ)፣
- ምርጥ የሙዚቃ አልበም፦ “ቸሊና” (ቸሊና የሺወንድም)፣
- ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ፦ ከእሁድ እስከ እሁድ (ጎሳዬ ተስፋዬ)፣
- ምርጥ ሙዚቃ/ዘፈን፦ “ሰርካለሜ” በድምጻዊ ዚጊ ዛጋ (በኃይሉ ታፈሰ)፣
- ምርጥ ተዋናይት፦ የምስራች ግርማ ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣
- ምርጥ ተዋናይ፦ ዘሪሁን ሙላት ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣
- ምርጥ ፊልም፦ ቁራኛዬ
- ምርጥ ተዋናይት በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ሀና ዮሐንስ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
- ምርጥ ተዋናይ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ አበበ ባልቻ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
- ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ደርሶ መልስ በፋና ቴሌቪዥን፣ እና
- “የ2010 ዓ.ም የኪነ ጥበባ በለውለታ” የክብር ተሸላሚ፦ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ደማቅ አሻራቸውን ያስቀመጡትን የቀድሞዎቹን አይቤክስ ባንድ እና ሮሃ ባንድ ከመሠረቱት አባላት አንዱ የሆኑት ጂዮቫኒ ሪኮ (Giovanni Rico)
አዲስ አበባ (ኢትዮ ቴሌኮም) – ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አንድ መቶ ሴቶች በፋሽን ዲዛይን የሙያ መስክ ነፃ የትምህርት ዕድል መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰጠ።
ኢትዮ ቴሌኮም በትምህርት ዘርፍ ከሚያደርጋቸው የማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች መካከል ይህ የትምህርት ዕድል የተመቻቸው ሴቶች በትምህርት፣ በሥራ እንዲሁም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ መስኮች ከወንዶች ያነሰ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን ከግምት በማስገባት ሴቶችን ማስተማር እና በሥራ ማሰማራት ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ፣ ብሎም ለሀገር ያለውን ከፍተኛ ሚና በመገንዘብ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም የዚህ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሴቶችን በመመልመል ሂደት ውስጥ በዋነኝነት የኢኮኖሚ አቅምን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲሆን በተለይም ከፍለው መማር የማይችሉ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት አድርጓል።
ነፃ የትምህርት ዕድል ፕሮጀክቱ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰልጣኝ ተማሪዎች፣ የኢትዮ ቴሌኮም አስተዳደር (management) እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ባደረጉት ንግግር ተቋማት ገቢያቸውን ከማሳደግ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ የሕብረተሰቡን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ተቋማዊ አሠራር በማጠናከር፣ እቅድ በማውጣት እና አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ አመራሩና ሠራተኛው ጠንካራ፣ አዎንታዊና በተግባር የሚገለጽ አመለካከት በማዳበር በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል። በዚህ ረገድ ቀደም ሲል በትምህርት፣ በጤና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና በሌሎች የሕብረተሰብ ችግሮች እና ፍላጎቶች ዙሪያ ሲሠራ ቆይቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል።
የነፃ ትመህርት ዕድሉን ያገኙ ሴት ሰልጣኞች የፋሽን ዲዛይን ሙያ ፍላጎት ኖሯቸው በአቅም እጥረት ሳይሰለጥኑ ቢቆዩም በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት ዕድሉን ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው እንዲሁም ይበልጥ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማድረጉን ገልጸዋል።
የዕድሉ ተጠቃሚ ሴቶችም በሚያገኙት የፋሽን ዲዛይን ሙያ ዕውቀት ታግዘው በቀጣይ ለራሳቸው የገቢ ምንጭ የሚፈጥሩ፣ ለቤተሰባቸው አጋዥ፣ ለአካባቢያቸው ምሳሌ እንዲሁም ለሀገራቸው ኩራት እንደሚሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም ያምናል። ሀገራችንም በሀገራዊ ምርቶች እና አገልግሎቶች ወደ ፊት ለመራመድ ከፍተኛ ጥረት የምታደርግበት ወቅት በመሆኑ በዚህ የሙያ ዘርፍ መሰልጠን የወደፊት ብሩህ ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ኢትዮ ቴሌኮም ሙሉ እምነት አለው።
ኢትዮ ቴሌኮም ትምህርት ለሀገር እና ለማኅበረሰብ ግንባታ ያለውን አገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ ወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በተጠናከረ መልኩ ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ አስታውቋል።
ምንጭ፦ ኢትዮ ቴሌኮም / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም የኖቤል ሽልማት ለመቀበል የበቁት ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ባበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑ ሽልማቱን የሚሰጠው ኮሚቴ ገልጿል።
በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ዓለምን ያስገረመና ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠለት የቅርብ ወዳጅ ዘመድ ጥየቃ ዓይነት ቃና የነበረው ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሁለት ዓይነት ሀሳቦች ቢስተናገዱም ሚዛን የሚደፋው ጉብኝቱ ሰላምን ለማምጣት መሠረት የተደረገ መሆኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያለውን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ‘ሽልማቱ ይገባቸዋል’ የሚሉ ድምጾች አሸናፊነታቸውን ቀድመው እንዳወጁላቸው ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ በጎረቤት አገሮች መካከል ሰላምንና አብሮነት ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ኖርዌይ ላይ አሸናፊው ይፋ ሲደረግ በኮሚቴው እንደተገለጸው፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እውቅናና ማበረታቻ ያስፈልገዋል።
በእንግሊዝ ኪል ዩኒቨርሲቲ (Keele University) የህግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አወሎ አሎ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ገጭት እንዲያበቃ በማድረጋቸው ሽልማቱ ይገባቸዋል” ማለት ግጭቱ በሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስከተለና የማይተካውን ብዙ ህይወት እንደቀጠፈም ተናግረዋል።”
ከኤርትራ ጋር የወረደው ሰላም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ሙገሳ ያስገኘላቸው ሲሆን ለሁለቱ አገሮች ወንድማማች ህዝቦች ደግሞ ትርጉሙ ከዚህ የላቀ ነበር። በተለይ ተለያይተው የነበሩ ቤተሶች ሲገናኙ ያፈሰሱት የደስታ እምባ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳላት በተጨባጭ የመሰከረ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገር ውስጥ የጀመሯቸው የለውጥ ማሻሻያዎች የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን በመልቀቅ ተጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው አስከመቀበል የዘለቀ ነው።
- ኢትዮጵያና ኤርትራ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ መሠረት ጥሏል።
- በሱዳን የተነሳውን የለውጥ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ የተጀመረው ተቃውሞ በሰላም እንዲጠናቀቅና ተቃዋሚዎች ከወታደራዊ ቡድኑ ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳናውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። በተለይ በሰኔ 2011 ዓ.ም ወደ ሱዳን በማቅናት ሁለቱን አገሮችለማስማማት የጀመሩትን ጥረት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬት እንዲደግፉት በማድረግ ለውጤት እንዲበቃ አድርገዋል።
- ከዚህ ባለፈ ኤርትራና ጂቡቲ ጀርባ የተሰጣጡበትን አለመግባባቶች በሰላም እንዲቋጩና ለጋራ እድገት በጋራ እንዲነሱ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
- በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር በአፍሪካ ቀንድአገሮች መካከል የኢኮኖሚ ህብረት እንዲኖር ያደረጉት ጥረት ለሰላምና ወንድማማችነት ያላቸውን ክፍት ልብ ያሳየ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን የማይደፈረውን ደፈረው ተንቀሳቅሰዋል።
- በዚህም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ተፈርጀው ለእስር የተዳረጉትን አቶ ዳንኤል በቀለን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አድርገው የሾሟቸው ሲሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር አድርገዋቸዋል።
- በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ ውይይት ማድረጋቸው ሌላው ስኬታቸው ነው። በውጭ አገር ተቀምጠው የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር ሲጥሩ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋርም ሰላም በማውረድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ሜዳውን ከፍተውላቸዋል።
- የደህንነቱንና የፍትህ ዘርፉንም ተአማኒ ለማድረግ በሩን ክፍት በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጡ እያገዙ ነው።
- በአገሪቱ ወደ ኋላ የቀረውን የሴቶች ተሳትፎ ከነበረበት አዘቅት በማውጣት ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸውም አድርገዋል።
- በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። በዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አብሮነቱንና ዕውቅናውን ሰጥቷቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ።
በአጠቃላይ 301 ዕጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትህ እና ነፃነት ጥያቄ በግድየለሽነት በሚንቀሳቀሱ ሰዎችና ተግባራቸው እንዳይጠለፍ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል!የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ይገባናል በሚል ሁሉንም አገዛዞች ሲታገል የቆየ ሕዝብ መሆኑ ሃቅ ነው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንኳን ፍትሃዊ እና የሁሉንም ዜጎች ነፃነት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል በትግል የተገኙ አራት ዕድሎች መክነውብናል። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች እና የዜጎች አልገዛም ባይነት እና እምቢተኝነት ትንቅንቅ የሚቋጨው ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭ ሆኖ የሚመርጠው እና የሚቆጣጠረው መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው።
የሩቁን ትተን በ2007 ዓ.ም. እንኳን ብናይ፣ በሙሉ ድምጽ ተመርጫለሁ ብሎ ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረዉ ገዢ ቡድን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ስብርብሩ የወጣው በዜጎች የጋለ የዴሞክራሲ ጥያቄ እና የተባበረ ትግል ነው።
ይህ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተባበረ ክንድ የተሰበረ አምባገነናዊ አሠራርና አስተሳሰብ መልክ እና ቅርፁን በመቀያየር የተገኘውን የለውጥ ጭላንጭል ድርግም አድርጎ በማጥፋት ጥለነዉ ወደመጣነዉ ጨለማና ወደራሱ የአገዛዝ አቅጣጫ ሊጠልፈው እንደተዘጋጀ ከበቂ በላይ ምልክቶችን አይተናል።የኢትዮጵያን ሕዝብ ትዕግስት፣ አስተዋይነት እና አርቆ አሳቢነት የመረዳት ችሎታ ያነሳቸው ጥቂት ፅንፈኞች ሀገራችን የምትጠብቀውን ተስፋ ሊነጥቋትና እነሱም አጥፍተው ሊጠፉ የተዘጋጁ ይመስላል። በእንደዚህ ዓይነት አቅላቸውን በሳቱ የአገዛዝ ቡድኖች እጅ መውደቅ ለአገራችን የመጀመሪያ ባይሆንም ይህ አሁን የገጠመን አጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መቆምን እና መታገልን የሚያሻ መሆኑን ማሳሰብ እንወዳለን። በተደጋጋሚ እንዳልነው አሁን ያገኘነውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ሀገራዊ መረጋጋት በእጅጉ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ በተፃራሪ የአንድ ወገን አሸናፊነት ተረክ መፍጠር ያገኘነውን ዕድል አደጋ ላይ የሚጥል እና ለማንም የማይጠቅም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንሸጋገርበትን መደላድል ለመፍጠር ሰላም እና መረጋት ለማስፈንና ተቋማትን ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ቢሆንም በገዢው ፓርቲ ውስጥም ይሁን ከዚያ ውጪ ለውጡ የጋራ ትግል ውጤት መሆኑን የዘነጉ ቡድኖች የሚሠሩትን ነውረኛ አካሄድ በማየት በሚከተሉት 7 ነጥቦች ላይ ያለውን አቋም ይገልጻል።
- የአማራ እና የቅማንት ሕዝብ ብዙ መከራዎችን በጋራ ያሳለፈ ድንበር የሌለው አንድ ሕዝብ ዛሬ በአስተዳደር ወሰን እና በማንነት ጉዳዮች የሚነሱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን የሚያስተናግደው በክፋት በተዋቀረው ፌደራላዊ አሠራር መሆኑን ተገንዝበን ለዘላቂ ሰላም እና ለሕዝብ አብሮ መኖር በትዕግስት እንድንሠራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ግጭቶች ባሉበት አካባቢ የሚኖረውም ሕዝብ፤ በመሀከሉ ያለውን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እና ሰላሙን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ እኩይ ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን በሕዝባችን አንድነት ስም እንማጸናለን።
- ኢሕአዴግ በጌታ እና ሎሌ አደረጃጀት የተዋቀረ ከዚህም ሲያልፍ መንግሥትነት የሚያስገኘውን የሥልጣን ጥቅም በመቀራመት ጎን ለጎን ሲጓተቱ የነበሩ ቡድኖች ስብስብ መሆኑን ለምናውቅ ሁሉ የዛሬው እሽኮለሌ አያስደንቀንም። ሆኖም ግን ሕዝባችንን በእነሱ ጦስ ወደእልቂት ለመክተት የሚያደርጉትን የትንኮሳ አካሄድ እንዲያቆሙ በኢሕአዴግ ውስጥ የተሰባሰቡ የብሔር ድርጅቶችን በጥብቅ እናሳስባለን።
- የተቋማትን መኖር እና መጠንከር አስፈላጊ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክንውኖች ከፖለቲካ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ቢሆንም ከሰሞኑ በተለይም የኦዴፓ አደረጃጀት የሰላም፣ የይቅርታ እና የምስጋና ታላቅ በዓል የሆነውን ኢሬቻን መጥለፉ ሳያንስ የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የሚጎትት እና የሚበርዝ በመሆኑ እንዲህ ዓይነትቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም አንጠይቃለን። የሀገር አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሂደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ አዲስ አበባ ለተከበረው ኢሬቻ በዓል ከየቦታው የመጡ የበዓሉ ታዳሚ ኢትዮጵያዊያንን በመንከባከብ ላሳየው አብሮነት እና ወገናዊ ፍቅር እንዲሁም በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላሳየው ትዕግስት ያለንን አክብሮት እና ምስጋና እየገለጽን ወደፊትም ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲታገል የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡
- የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን አፈና እስካሁን በሆደሰፊነት ማለፉ ሊያስመሰግነው ቢገባም ይህን ያልተረዱ ወገኖች ትዕግስቱን እንደፍርሀት፤ ጨዋነቱን እንደ የዋህነት እየወሰዱ ማኅበረሰቡን መተንኮስ እየተለመደ መጥቷል። ይህ የሀገራችንን ሁሉንም ሕዝብ አቅፎ የያዘ፤ ከዚያም በላይ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከል የሆነና ለፌደራል መንግሥቱም ከፍተኛ የሆነ የግብር ገቢ የሚያስገኝ ከተማን በጥንቃቄና በአክብሮት፤ የሚገባውን መብት አክብሮ መያዝ ይገባል። የከተማው ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም እውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን አይቀበልም። ይህንን መብቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅም ራሱን ከቀበሌ ጀምሮ በሁሉም ያስተዳደር እርከን በጠንካራ ሁኔታ አደራጅቶ የራሱን መብት ለማስከበርና የራሱን መሪዎች ለመምረጥ መዘጋጀት ይጠበቅበታል። ኢዜማ ይህንን ራስን የማስተዳደር እንቅስቃሴውን እውን ለማድረግ ከከተማው ሕዝብ ጋር አብሮ ይሠራል፤ የከተማውን ሕዝብም ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ በዜግነቱና በከተማ ነዋሪነቱ ያደራጃል። ከዚህም በተጨማሪ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንደግፋለን፤ በሥነ ሥርዓት እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በጠበቀና ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጎለብት ሁኔታ እንዲካሄድም ጥሪ እናስተላልፋለን።
- በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ያስተዋወቀው አዲስ የደንብ ልብስ ለከተማ የፖሊስ አገልግሎት የሚመች ባለመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውል አጥብቀን እናሳስባለን። የከተማዋ ፖሊስ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እንዲሁም በኮሚኒቲ ፖሊስ ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት እያለው እና የፌደራል ፖሊስ ኃይል በቋሚነት በሚገኝበት ከተማ ውስጥ ተጨማሪ ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ማቋቋም ተቀባይነት የለውም። ይልቁንም የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የከተማዋን ኅብረተሰብ ደኅንነት ማስጠበቅ እና አባላቱ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። በክልሎች የተደራጀው ልዩ ኃይል እና አዲስ አበባ አስተዳደር አቋቋምኩት ያለው ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ለሚደረገው ትግል ትልቅ ተግዳሮቶች ናቸው። ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው እነዚህ አደረጃጀቶች ፈርሰው ወደመደበኛ ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት እንዲካተቱ በድጋሚ ጥሪ እናስተላልፋለን።
- በአማራ ክልል የተከሰቱ የወንድማማች ሕዝብ ግጭቶች ተከትሎ ሁኔታው እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሰፍን ከመስበክ ይልቅ ሥራዬ ብለው ወሬ እየፈበረኩ ግጭቶችን በሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣን በአስቸኳይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እናሳስባለን።
- ላለፉት 27 አመታት ሲሰራበት የቆየው ሀገርን እና ሕዝብን ሆን ብሎ የሚከፋፍልና የሚበትን የዘረኝነት አሠራር ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም የሚቻለው ፖለቲካችንን በማዘመንና በመግራት፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ተደራጅቶ በመታገል በመሆኑ፤ ሌሎች ያደርጉልናል ብሎ ከመጠበቅ ዜጎች በተለይም ለዘብተኛ አመለካከት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ እንድናልፍ ባላችሁ አቅም ሁሉ በሀገራችሁ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ እንድትሆኑ የዘወትር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በአጠቃላይ ሰላምን፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያይ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲገነባ ሕዝባችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ የኢዜማ አደረጃጀቶች በመግባት የጀመረውን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ ከዳር እንዲያደርስ ጥሪያችንን እያቀረብን ሌሎች የማኅበረሰብ መሪዎች ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ መረጋጋት ዘብ መቆም የሚገባቸው ጊዜ ዛሬ መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሀገር አንድነትን ማስቀጠል እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። አሁን ያለንበት የሽግግር ወቅት የሀገር አንድነትን እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን እንዲያረጋግጥ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንደምናደርግ እና አስፈላጊውን መስዕዋትነት ለመክፈልም ወደኋላ እንደማንል በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናችን እንደሚቆም አንጠራጠርም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በዓለም ምርጡ ተብሎ በይፋ የተሰየመውን እና በህዳር ወር የሚካሄደውን 45,000 ህዝብ የሚሳተፍበት የ2012 ዓ.ም. ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪ.ሜ. ውድድር የሚያዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዚህ ጎን ለጎን የሚያካሂደውን “ሌሎችን ለመርዳት ሮጣለሁ” የእርዳታ ማሰባሰቢያ ሥራ እንዲሁም የዘንድሮውን ሩጫ መሪ ቃል “ሴቶች ልጆች በእኩል ሚዛን መታየት፤ መደመጥ እና ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል” በመለየት መሰናዶውን በተቀላጠፈ መልኩ በማካሄድ ላይ ሲሆን ውድድሩ ከዛሬ 45 ቀን በኋላ እሁድ ህዳር 07 እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በጎ አድራጎ ሥራ ከተጀመረበት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ከ13.5 ሚሊዮን ብር በላይ ሰላሳ (30) ለሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተሰባሰበበት “ሌሎችን ለመርዳት ሮጣለሁ” መርሀ ግብር 9 ሚሊዮን ብሩ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተሰባሰበ ሲሆን ዘንድሮ 1.9 ሚሊዮን ብርለማግኘት ታቅዶበታል። ይሄም ገንዘብ በዋግህምራ ዞን ትምህርት ቤት ለማስገንባት የሚውል ሲሆን የፕሮጀክቱ መነሻ ጀግናው አትሌት ሀይሌ ገብረሥላሴ በቅርቡ በአካባቢው አንድ ትምህርት ቤት ማሠራቱን ተከትሎ የመጣ ነው።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ በውድድር ዝግጅት ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ አንጋፋ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ጋር ተፎካክሮ ያገኘው ትልቅ ዕውቅና እና ሽልማት ለሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ የሚኖረው ጉልህ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። ስኬቱ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ይበልጥ ለማስተዋወቅ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን እንደ አንድ መስህብ መጠቀም የሚያስችል ሲሆን በተለይም ከቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ሌሎች የውድድሩ አጋሮች ጋር አብሮ በመሥራት የአገሪቷን ቱሪዝም ለማሳደግ ካለው አላማ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።
በሌላ በኩል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውድድር ስያሜ ስፖንሰሩ ቶታል ጋር ያለውን ኮንትራት ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት አድሷል። ከዚህ በተጨማሪ የ2012 ዓ.ም. ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የምዝገባ ሰኔ ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን የተቀሩት ጥቂት ለበጎ አድራጎት የሚውሉ ቦታዎች ለማቀላጠፍ ከአሞሌ የዲጂታል መገበያያ ቴክኖሎጂ ጋር በአጋርነት መሥራት ጀምሯል። ማንኛውም ለበጎ አድራጎት የሚውለውን የሩጫ ቲሸርት የሚፈልግ ግለሰብ አሞሌን በመጠቀም መግዛት የሚችል ሲሆን አሞሌን ለማይጠቀሙ ግለሰቦች ደግሞ በማንኛውም የዳሽን ባንክ በመሄድ 600ብር በመክፈል መመዝገብ የሚችሉበትን መንገድ አመቻችቷል። የመወዳደሪያው ቲሸርት ለሁሉም ተሳታፊዎች ከጥቅምት 28-30 ቀን ከውድድሩ 1 ሳምንት ቀድሞ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በታላቁ ሩጫ የስፖርት ኤክስፖ ላይ ይሰጣል።
ዘንድሮ ታላቁ ሩጫ አዳዲስ አጋሮችን ይዞ መቷል። “ከሥራዎች ሁሉ ውድ ÷ ክፍያ የማይፈፀምላቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች እና ክብካቤዎች ናቸው!”) የሚል መልዕክት ይዞ የመጣው አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ (ActionAid Ethiopia)፤ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራው ኤች ፒ (HP) እና ዘመናዊው ሃየት ሬጀንሲ ሆቴል (Hyatt Regency Addis Ababa) ናቸው።
ከ2012 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ በሩጫው ዋዜማ በድምቀት የሚካሄደውና በአጠቃላይ 3,500 ልጆች የሚሳታፉበት የሕፃናት ውድድር ከአዋቂዎቹ ሩጫ ጋር በተመሳሳይ “ሴቶች ልጆች በእኩል ሊታዩ፤ ሊደመጡ እና ቦታ ሊሠጣቸው ይገባል” በሚል መሪ ቃል ይደረጋል። የልጆች ሩጫ ከሚያስተላለፈው መልዕክት በተጨማሪ ሕፃናት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ገና በለጋ እድሜያቸው እንዲለምዱ እድል ሲሰጥ በተጨማሪም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ተሳትፎ የሚያሰፋበት መንገድ ነው።
የ14ኛው የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ (Plan International Ethiopia) የሕፃናት ሩጫ ምዝገባ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ቦሌ መንገድ ዓለም ህንጻ በሚገኘው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ ይጀመራል ።
የ19ኛው ዙር የ2012 ዓ.ም. ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከፊታችን እሁድ 6 ሳምንታት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን በቀጣይ ያሉት 6 ሳምንታት የተለያዩ 6 አንኳር ህሳቦች ላይ እንዲያጠነጥኑ የታቀደ ሲሆን እነሱም፡
- ዱበ ዱብ፡ ተሳታፊዎች ለሩጫው ዝግጅታቸውን የሚጀምሩበት ሳምንት ሲሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ6 ሳምንት የልምምድ ምክር ከሻለቃ ሀይሌ ገብረሥላሴ እንዲያገኙ ያመቻቻል።
- ጥንቃቄ፡ ይህ ተሳታፊዎች ጤናቸውን የሚያረጋግጡበት (ቼክ የሚያደርጉበት) ሳምንት ሲሆን አዘጋጆች ደግሞ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እንዲሁም ከጠብታ አምቡላንስ እና ከውድድሩ ሜዲካል ዳይሬክተር የተጠናከረ ዝግጅት የሚደረግበት ነው።
- ምንጭ፡ አርንጓዴ ምንጭ በመባል የሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የአትሌቲክስ ቡድን ሲሆን የዚህ ምንጭ የሆኑት ታዳጊ እና አዳዲሰ አትሌቶች በቃታቸውን የሚያሳዩበት የምርጫ ውድድር የምናደርግበት ሲሆን፣ ጥቅምት 9 ቀን 300 የሚሆኑ ታዳጊ አትሌቶች በውድድሩ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ወድድሩ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሜ የሚካሄድ ይሆናል።
- በጎ ፈቃደኛ፡ ለውድድራችን በየአመቱ መሳካት ትልቅ ድጋፍ ለሚያደርጉልን በጎ ፈቃደኞቻችን እውቅና የምንሰጥበት ሳምንት ነው።
- ጽዱ፡ የሩጫችን መንገድ ንጹህ ሆኖ እንዲዘጋጅ የሙከራ የጽዳት ፕሮግራም የምናደርግበትና በዋናነት ከቂቆስ ክ/ከተማ ጽዳት ቢሮ ጋር የሚሰራ ሲሆን ውድድሩ የሚንካቸውን ሌሎች ክ/ከተማዎችን ጨምሮ የሚካሄድ ሲሆን ከውድድሩም በኋላ ከተማችን ጽድ እንድትሆን ከአጋሮቻችን አርኪ ውሃ እንዲሁም ዳይናሚክ የጽዳት ድርጅት ጋር አብረን እንሰራለን።
- ስፖርት ኤክስፖ፡ ለተሳታፊዎቻችን የሩጫ ቲ-ሸርት የሚሰጥበት ሳምንት ሲሆን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከጥቅምት 27-30 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ የስፖርት ትጥቅ የሚያገኙበት እንዲሁም የተለያዩ ስፖርቶችን የሚሞክሩበት እና የሚዝናኑበት ነው።
ለበለጠ መረጃ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የማርኬቲንግ እና ኮሚኒኬሽን ሃላፊ መርከብ መንግስቱን በስ.ቁ. 0911-671002/0116-635757 ኢሜይል፡ merkeb@ethiopianrun.org ማግኘት ይችላሉ።
ምንጭ፦ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት የነበራቸው 12 የአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ለኢቢሲ የላከው መግለጫ ያስረዳል።
አልሸባብ እና አይ ኤስ የሽብር ቡድኖቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እና የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በመላክ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ ለማድረስ እንዲሁም የሀገራችንን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ እንዳሉ ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።
ይህንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ሀገር ውስጥ የገባው አንድኛው የአልሸባብ የሽብር ቡድን በሙሐመድ አብዱላሂ ዱለት በሀሰተኛ ስሙ ያህያ አሊ ሃሰን የሚመራ ሲሆን የሽብር ጥቃት ተልዕኮ ይዞ በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት ህዝብ የሚባዛባቸውን ቦታዎች እንዲሁም የሀይማኖት ክብረ በዓል የሚካሄድባቸውንና የተለያዩ ሆቴሎችን የመለየትና የፎቶግራፍ መረጃዎችን የመሰብሰብ ጥናት ካደረገ በኃላ ወደ ሽበር ተግባራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳለ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከጅቡቲ ወደ ሀገራችን ሲገባ ጀምሮ ክትትል ሲደረግበት ስለነበር በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ከእርሱ ጋር በመሆን የተለያዩ ጥናቶችን ሲያካሄዱ የነበሩና ጁቡቲ የሚገኙ አብደክ መሃመድ ሁሴንና ሬድዋን መሃመድ ሁሴን የተባሉት ግብረአበሮቹም ጅቡቲ ከሚገኘውና ሁኔታውን ሲያመቻችላቸው ከነበረው ሌላ የአልሸባብ አባል በቅፅል ስሙ ስመተር መሀመድ ኢማን ዩሱፍ የተባለውን ጨምሮ ከሀገሪቱ የመረጃ ተቋም ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።
አልሸባብ የሽብር ጥቃት እንዲፈፅሙ ካሰማራቸው ሌሎች ቡድኖች ውስጥም ከደቡባዊ ሶማሊያ ተነስተው ሱማሊላንድ ሐርጌሳ ከተማ ከገቡ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ዝግጅት ሲያደርጉ ከነበሩ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት መካከልም ይሳቅ አሊ አደንና አደን ሙሃሙድ መሃመድ በቅፅል ስሙ አደን ቦራይ የተባሉት የፈንጅና የአጥፍቶ መጥፋት ስልጠና የወሰዱና የቡድኑ ቁልፍ አባላት ከመነሻቸው ጀምሮ በተደረገባቸው ክትትል ከሱማሊላንድ የመረጃ ተቋም ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ሶማሊላንድ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሌሎች የአልሸባብ ሽብር ቡድን አባላት መካከል ኢሳቅ አሊ አደን የተባለው የሽብር እቅዱን ለመፈፀም እንዲያመቸው ከሶማሊያ ክልል ቦህ ወረዳ ጨርቃን ቀበሌ ኢብራሂም ዓሊ አደን በሚል ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በእጁ ይዞ የተገኘ ሲሆን አደን ማሕሙድ መሐመድ ወይም አደን ቦራይ የተባለው በበኩሉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት የሂሳብ አካውንት በመክፈት ለሽበር ተልዕኮ መፈፀሚያ ሊጠቀሙበት የነበረ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በተደረገው ጥብቅ ክትትል መገኘቱን ለማረጋገጥ ተችሏል።
ከእነዚህ በተጨማሪም ተመሳሳይ ተልእኮ ይዞው ወደ ሃገር ውስጥ ከገቡት መካከል ዒድ መሃመድ ዓሊ የተባለው በሶማሊ ክልል ጨርጨር ዞን አራርሶ ወረዳ፣ በሽር ዑስማን አብዲ በዚሁ ክልል ፊቅ አከባቢ እንዲሁም ዑስማን አሊ ሁሴን የተባለው በኦሮሚያ ክልል በሞያሌ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እንደሚፈጽም ሲዝት የነበረው ሁለተኛው የአይ ኤስ የሽብር ቡድን ደግሞ ከቦሳሶ በሶማሌላንድ ሃርጌሳ በኩል ወደ አዲስ አበባ በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በተደረገበት ጥብቅ ክትትል ፋዕድ አብሽር የሱፍ የተባለው የቡድኑ አባል አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገ ሲሆን ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የዚሁ ቡድን አባላት መካከልም ሙህመድ ጉሀድ ቡዲል የተባለው በሱማሌ ክልል በአፍዴር ዞን ምዕራብ ኢሚ ወረዳ በቁጥጥር ስር ዉሏል። ሌላ በሀገር ውስጥ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባል የሆነ ሰይድ ዑመር ሸበሺ የተባለው በፀጥታ አካላት በአዋሽ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
እነዚህ አሸባሪዎች የጥፋት ተለዕኮቸውን ለማስፈፀም የሚጠቀሙባቸው የግንኙነት መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። የሸብር ቡድኖችን በመከታተል በቁጥጥር ሰር እንዲውሉ ለማድረግ በተካሄደው ሰፊ የኦፕሬሽን ስራም የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላት እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት አጋር የመረጃ ተቋማት ድጋፍ አድርገዋል። በተለይም ደግሞ የጁቡቲ፣ የሶማሊላንድ፣ የፑንትላንድ የአሜሪካ፤ የጣሊያን፣ የፈረንሳይና የስፔን የመረጃ ተቋማት እገዛ ማድረጋቸውን ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው አሳውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አግልግሎት በከፍተኛ ክትትል ያገኛቸውን መረጃዎች ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ፤ ለመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም ለአፍሪካና ለኤዢያ በአጠቃላይ 16 ለሚሆኑ ሀገራት ከተያዙት የሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተደረሰባቸውን የሽብር ቡድኑ ህዋስ አባላት በሀገራቱ እንደሚገኙ የሚያረጋግጥ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።
አሸባሪዎቹ በሀገራችን ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች፤ ሆቴሎች፤ በመንግሥትና በግል ተቋማት እንዲሁም የሃይማኖት ክብረ ባዓላት በሚከበርባቸው ስፍራዎች በፈንጂ ፍንዳታና በተኩስ የታጀበ የሸብር ጥቃታ በመፈፀም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ለማድረስ ተዘጋጅተውበት የነበረው የሽብር ጥቃትም የከሸፈው በህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ መሆኑን ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት መግለፅ ይወዳል።
በቀጣይም የሽበር ቡድኑ በሀገራችን ጥቃት ለመፈፀም ካለው ዝግጅት አንጻር ህዝባችን ይሄን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግና የተለየ ነገር ሲመለከትም በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ፤ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አግልግሎት በሀገራችንና በህዝባችን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም የሽብር ጥቃቶች አስቀድሞ በማወቅ ሙያዊ ብቃቱን በማሳደግ ላይ ያለ ተቋም መሆኑን በመገንዘብ የመላው ህዝባችን ድጋፍ እንዳይለየው አብክሮ ጥሪ ያቀርባል።
ምንጭ፦ ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ