Search Results for 'አዲስ አበባ'

Home Forums Search Search Results for 'አዲስ አበባ'

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 495 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የ70/30 የማኅበር ቤት ግንባታ ፕሮግራም ይፋ አደረጉ

    • ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የ70/30 የማኅበር ቤት (ኮንዶሚኒየም ቤቶች) ግንባታ ፕሮግራም ይፋ አደረጉ። ታህሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም የተደረገው ስምምነት የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ ካቀረባቸው አማራጮች አንዱ በሆነው የጋራ መኖሪያ (ኮንዶሚኒየም) ቤቶች ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን በ2005 ዓ.ም በ20/80 እና በ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮግራሞች የተመዘገቡና በሕብረት ሥራ ማኅበራት በመደራጀት ቤት ለማልማት ፍላጎት ላላቸው ነዋሪዎች ብድር ለማመቻቸት ያለመ ነው።

    በስምምነቱ መሠረት በማኅበራት የተደራጁ ቤት ገንቢዎች የግንባታ ወጪውን 70 በመቶ ያህል ሲቆጥቡ 30 በመቶውን ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር እንዲያገኙ ይደረጋል።

    በስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት በሚያከናውናቸው ተግባራት ባንኩ ድርሻውን በከፍተኛ ደረጃ ሲወጣ መቆየቱን ገልፀዋል።

    አሁን ከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደው የ70/30 የማኅበር ቤት ((ኮንዶሚኒየም ቤቶች) ግንባታ ፕሮግራምም እንዲሳካ ባንኩ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ በጋራ ይሠራል ብለዋል።

    በምክትል ከንቲባ ማዕረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ያስሚን ውሃብረቢ እንዳሉት፥ ቢሮው ባደረገው ጥሪ መሠረት ፍላጎት አሳይተው ከተመዘገቡት ከ12,000 በላይ ቆጣቢዎች ውስጥ 4,580 የሚሆኑት በዳግም ምዝገባው ተገቢውን መረጃ ይዘው የቀረቡ በመሆኑ በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ትግበራ ይገባሉ።

    በአሁኑ ወቅት የተዘገቡት 4,580 በላይ ቆጣቢዎችን በ57 ሕብረት ሥራ ማኅበራት እንዲደራጁ የመደልደል ሥራ ተጠናቋል ያሉት ወ/ሮ ያስሚን ውሃብረቢ፥ ለአዲሱ ፕሮግራም 30,000 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ነው የገለፁት።

    በቤት ልማት ዘርፉ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ለዓመታት የዘለቀ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የገለፁት ወ/ሮ ያስሚን፥ ባንኩ ሃገራዊ ግዴታውን በመወጣቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

    በቀጣይ ተገቢውን ቅድመ-ሁኔታ አሟልተው ህጋዊ ሰውነት አግኝተው በሕብረት ሥራ ማኅበር ሲደራጁ የፕሮጀክት ሳይት እና የብሎክ እጣ በማውጣት የመሬት ርክክብ ለማኅበራቱ በማድረግ ግንባታ እንደሚጀመር በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

    ከዚሁ ፕሮግራም ጋር በተያያዘ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን፥ ከእነዚህም መካከል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት፣ በከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊው የመሬት አቅርቦት ዝግጅት፣የህንፃ ዲዛይን ሥራ፤ ከአዲስ አበባ የሕብረት ሥራ ማኅበር ኤጀንሲ በቀጣይ ሥራ ስምምነት ማመቻቸትን እንደሚያካትት የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

    የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር

    Semonegna
    Keymaster

    ፀሐይ ባንክ አ.ማ. ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊየን ብር ለማሳደግ ወሰነ፤ የቦርድ አስመራጭ ኮሚቴንም አስመረጠ።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የፀሐይ ባንክ አ.ማ. በባለአክሲዮኖች አንደኛ መደበኛና አንደኛ አስቸኳይ ጉባኤ ታኅሳስ 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ የባንኩን የተፈረመ ካፒታል ከብር 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን እንዲያድግ ተወሰነ።

    ፀሐይ ባንክ ካፒታሉን ለማሳደግ በምክንያትነት ያቀረበው በዓለም አቀፍ፣ ሀገራዊ እና በፋይናንስ ዘርፉ የታዩ ዓበይት ለውጦች ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሀገር በቀል ባንኮች ሊኖራቸው የሚገባው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ላይ ማሻሻያ በማድረጉ፤ የውጪ ባንኮች በባንክ ዘርፉ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ፖሊሲ በመውጣቱ እና ወደ የባንኩን ዘርፍ በሚቀላቀሉበት ወቅት በሚፈጠረው ውድድር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የተሻለ የካፒታል ቁመና ላይ መገኘት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ተብሏል።

    በተጨማሪም እጅጉን ተለዋዋጭ በሆነው የፋይናንስ ዘርፍ ምኅዳር ውስጥ አሸናፊ ሆኖ የመሥራች ባለአክሲዮኖች ራዕይ ማሳካት የሚቻለው በቅድሚያ የተፈረመ ካፒታል ቀሪ ክፍያ በአጠረ ጊዜ ውስጥ መሰብሰብ ሲቻል እንደሆነ እና ባንኩ የነደፈውን ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲሁም ከግብ ለማድረስ የተፈረመ ካፒታሉን መሰብሰብ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ በጉባኤው ላይ ተመልክቷል።

    በዚሁ መሠረትም ቀደም ተብሎ የተፈረመ ካፒታሉ ላይ ያልተሰበሰበ ገንዘብ የመጀመሪያውን ግማስ 37 ነጥብ 5 በመቶ በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ ጥር 2023 (January 2023) መጨረሻ ድረስ፤ እንዲሁም ቀሪውን 37 ነጥብ 5 በመቶ እስከ መጋቢት2023 (March 2023) መጨረሻ፤ በመጨረሻም የማጠናቀቂያውን ክፍያ እስከ ሰኔ 2023 (June 2023) መጨረሻ እንዲከፈል ተወስናል።

    የካፒታል ማሳደጉን በተመለከተ አምስት ቢሊዮን ለመሙላት የሚቀረውን 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በፈረንጆች አቆጣጠር በሐምሌ 1 ቀን፥ 2023 (July 1, 2023) ተፈርሞ በዓመቱ ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ የተወሰነ ሲሆን፤ የካፒታል እድገት ውስኔው ተግባራዊ የሚደረገው ቀደም ሲል ተፈርመው ያልተከፈሉ የባንኩ አክሰዮኖች ሙሉ በሙሉ ተከፍለው ሲጠናቀቁ መሆኑ ተገልጿል።

    በተጨማሪም የፀሐይ ባንክ አ.ማ. ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚመሩ የዳይሬክተሮች ቦርድን ለማስመረጥ የሚሠሩ የአስመራጮች ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፤ አስር አባላት ተጠቁመው ከፍተኛ ድምጽ ያገኙ አምስት አስመራጮችን ጉባኤው መርጧል።

    ፀሐይ ባንክ አ.ማ ሀምሌ 16 ቀን፥ 2014 ዓ.ም “ፀሐይ ለሁሉ” በሚል መሪ ቃል በይፋ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ በመላ ሀገሪቱ በርካታ ቅርንጫፎች ከፍቶ መደበኛ እና “ፈጅር” የተሰኘ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በመስጠት ላይ የሚገኝ ባንክ ነው።

    ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የቅርንጫፍ ቁጥሩን ወደ 100 የሚያደርስ ሲሆን፤ በተጨማሪም 15 የኤቴኤም ማሽን በመትከል አገልግሎት እንደሚሰጥና ከ356 ሺህ በላይ ደንበኞችን የማፍራት እቅድ ይዞ በመሥራት ላይ መሆኑ በጉባኤው ላይ ተገልጿል።

    ምንጭ፦ የባንኩ ፈስቡክ ገጽ

    ፀሐይ ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም የሚቀጥል ነው – አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር

    አዲስ አበባ (ኢፕድ) – “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም ተጠናክሮ የሚቀጥልና ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ቢሮ ተቋቁሞለት በጥብቅ ዲስፕሊን እየተመራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

    የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) እንደገለፁት፥ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ እሳቤው በጣም ሰፊ እና በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

    እንደሀገር ለኢትዮጵያ የማምረት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው፤ ኢትዮጵያ ማምረት አለባት ያሉት ሚኒስትሩ፥ የለመድነውና ደጋግመን የምንለው መሪ ሀሣብ አለን። ይህም “ኢትዮጵያ ለዘላላም ትኑር” እንላለን፡፡ ኢትዮጵያ ዘላለም መኖር የምትችለው ማምረት ስትችል ነው ብለዋል።

    ‘የምንፈልጋት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ለማድረግ ማምረት አለብን፤ ሁሉም ዘርፎችም ማምረት አለባቸው’ ያሉት ሚኒስትሩ፥ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚጀምርበት ወቅት የማምረቻ (manufacturing) ኢንዱስትሪ ላይ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር ምርትና ምርታማነት በማተኮር የመነጨ የአንድ ተቋም ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነት አጀንዳም ጭምር መሆኑን አመልክተዋል።

    ለመልፋት፣ ለመድከምና በኢኮኖሚ ጠንካራ ለመሆን መሥራት ያለብንን ባለመሥራታችን ምክንያት ወደ ኋላ ቀርተናል፤ በመሆኑም “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የሉዓላዊነት፣ የመኖርና የህልውና እሳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዘ ፖለቲካውንም፣ ኢኮኖሚውንም ማኅበራዊ ጉዳይንም የሚነካ ነው። በመሆኑም ለጠላት ያልተንበረከከ ጉልበት ለስንዴ መንበርከክና እጁን መዘርጋት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

    “ያለፉትን 6 ወራት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አፈፃፀም ከፌደራልና ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ዛሬ [ኅዳር 9 ቀን፥ 2015 ዓ.ም] ገምግመናል። በተገኙ አበረታች ውጤቶችና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይም ተግባብተናል።” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው

    “ኢትዮጵያ ታምርት” የንቅናቄ አጀንዳ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጀምረውት እስከ ታች ወረዳ ድረስ አምራቾች ማግኘት የሚገባቸውን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው በሚል መነሻ የመጣ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከዚህ አኳያ አንዱ የተሳካው ግብ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እንደነበር ተናግረዋል።

    በተጨማሪም አምራቾች ከእያንዳንዱ የመንግሥት አካልም ማግኘት ያለባቸውን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው የሚለው እሳቤ ስኬታማ እየሆነ ነው፤ አጀንዳም ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

    “በየትኛውም ሀገር ላይ ኢንዱስትሪዎች ጠንካራ የፖሊሲ ድጋፍ የሚያደርጉ መንግሥታት ውጤት ናቸው” ያሉት አቶ መላኩ አለበል፥ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ኢንዱስትሪዎች የገጠሟቸው ማነቆዎች እንዲፈቱ በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በዚህም የቆሙ ኢንዱስትሪዎች ችግራቸው ተፈትቶ ወደ ሥራ ተመልሰዋል፤ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ገብተዋል፤ ያለአግባቡ የባከኑ መንግሥትና የሕዝብ ሀብቶች እንዲመለሱ ማስቻሉን አብራርተዋል።

    በኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት መሬት ነው። ያለአግባብ መሬት ከያዙት በመቀበል ለአልሚዎች ተላልፏል። ችግሮችን በመለየት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ችግሮቻቸውን ለመፍታት አቅም ሰጥቷል፤ የአደረጃጀት ችግሮችም ተፈትተዋል። በመሆኑም “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው ንቅናቄ ትልቅ ውጤት አስገኝቷል። ይህም የአንድ ዓመት ዘመቻ ሳይሆን በዘላቂነት የሚሠራ ነው። የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ፥ ያለውን ፖሊሲ በመተግበርና አማራጮችን በመመልከት የሚስተካከሉ ጉዳዮች መኖራቸውንም አስገንዝበዋል።

    ባለፈው ዓመት (የ2014 በጀት ዓመት) የአስር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ጊዜ፥ በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤት ማምጣቱን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር

    ምንጭ፦ ኢፕድ

    ኢትዮጵያ ታምርት

    Semonegna
    Keymaster

    በኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ተጀመረ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ኅዳር 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

    በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ ከጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱንም ኩባንያው አስታውሷል።

    ኅዳር 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ ኃይል ማስተላለፍ የጀመረው የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት (500 kilovolt) የማስተላለፊያ መስመር በዓመት እስከ አንድ መቶ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማስገባት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከኬንያ አልፎ ከታንዛኒያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ላሉት ሀገራት እስከ ሁለት ሺህ ሜጋ ዋት (2000 MW) ኤሌክትክ የማስተላለፍ አቅም አለው፡፡

    የኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ጣቢያ ፕሮጀክት ለአማካሪ ድርጅቱ፣ ለካሳ ክፍያና የተሰረቁ መሰረተ ልማቶችን ለመተካት የወጣውን ወጪ ጨምሮ ወደ አምስት መቶ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡

    ከዚህ ውስጥ 214 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩ ለኮንቨርተር ስቴሽኑና ለግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመር የግንባታ ሥራ እንዲሁም 120 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ለማስተላለፊያ መስመሩ የዋለ ነው፡፡

    የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራ “China Electric Power Equipment and Technology Co. Ltd (CET)” በተሰኘ የቻይና ኩባንያ የተከናወነ ሲሆን፤ የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያውና የግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመሩ ደግሞ ሲመንስ (Siemens AG) በተሰኘው የጀርመን ኩባንያ ተከናውኗል፡፡

    በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው የማስተላለፊያ መስመር እና የፕሮቴክሽንና የዳታ ኮሙዩኒኬሽን መስመር (ኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበር) 440 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 994 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ታወሮች አሉት።

    ኢትዮጵያ የምታስተላልፈው ኃይል ያልተቆራረጠና አስተማማኝ እንዲሆን የሚያግዙ ተግባራትን ያጠናቀቀች ሲሆን በኬንያ በኩል ተመሳሳይ ሥራዎች ተሰርተው በቅርቡ ወደተግባር እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

    የማስተላለፊያ መስመሩ ከደቡብ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የወላይታ፣ ጋሞ እና ኮንሶ ዞን እንዲሁም ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቦረና ዞን አቋርጦ ነው ወደ ኬንያ ኃይል የሚያስተላልፈው።

    ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ከጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ እያካሔደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች።

    ባለፈው ዓመት ለሱዳን እና ለጅቡቲ ኤክስፖርት ከተደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል 95 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

    በኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ተጀመረ

    Semonegna
    Keymaster

    ተሰርዞ የነበረው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ ((የዕድለኞች ስም ዝርዝር))

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ተሰርዞ የነበረውን የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ አወጣ። የ14ኛዉ ዙር የ20/80 እና 3ኛዉ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (condominium houses) ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት ህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሂዷል።

    በዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተዋል።

    በዕጣው የ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 18,930 ቤቶች፣ በ40/60 ደግሞ 6,843 ቤቶች እንዲሁም ተጨማሪ 18 ስቱዲዮ ቤቶች በድምሩ 25,791 ቤቶች በዕለቱ ዕጣ ወጥቶባቸዋል።

    የጋራ ቤቶች (condominium houses) ዕጣ ሐምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ወጥቶ የነበረ ቢሆንም በዕጣው ማውጣት ሂደት በገጠመ ችግር ምክንያት ዕጣው በመሰረዙ ነው አሁን በድጋሚ የዕጣ ማውጣት ሂደት የተከናወነው።

    የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከግንባታ እስከ ዕጣ ማውጣት ሂደት ባለፉት ጊዜያት ከውስጥም ሆነ ከውጭ በርካታ ችግሮች አስተናግዷል። ከዚህ አንፃር ዛሬ የወጣው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በርካታ ችግሮችን በማለፍ በስኬት መከናወኑን አንስተዋል።

    በተለይ በለውጡ ዋዜማ የሥራ ተቋራጮች ሥራውን አቋርጠው የመጥፋት፣ የመሠረተ ልማት ዝርፊያ የግንባታ ጥራት ችግር፣ የፋይናንስ እጥረትን ጨምሮ ዘርፉ የተወሳሰበ ሂደት ውስጥ ለማለፍ ተገድዷል ነው ያሉት።

    የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ በመበደር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም እንዲሁ አስታውቀዋል።

    ሆኖም ከዚህ በፊት ዕጣ የወጣባቸውን የጋራ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የተደረገው ሙከራ በተለያዩ የሌብነት ተግባራት ምክንያት ሳንካ ገጥሞት እንደነበርም ጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ ለረጅም ዓመታት በትዕግስት ሲጠባበቅ ለነበረው ሕዝብ አሳዛኝ ዜና እንደነበር አውስተዋል።

    በዕጣ ማውጣት ሂደቱ ከተፈጠረው ችግር ጀርባ የቤት ልማት መርሃ-ግብርን ለግል ጥቅም ማካበቻ ከማድረግ ባለፈ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመተማመን ለመፍጠር ያለመ ሴራም እንደነበር ነው የተናገሩት። የከተማ አስተዳደሩ የገጠመውን ችግር ለሕዝብ በግልፅ ይፋ በማድረግ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን ማስፈኑን ጠቅሰዋል።

    ተዓማኒነቱ የተረጋገጠ አዲስ የዕጣ ማውጫ ሥርዓት በማልማትም ከዚህ ቀደም ተሰርዞ የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አሁን (ህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም) በድጋሚ እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በድጋሚ እንዲወጣ ያለመታከት ጥረት ያደረጉ ሰራተኞችና አመራሮችን አመስግነው ባለእድለኞችንም እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

    ዛሬ የጋራ መኖርያ ቤት ዕጣ ለደረሳችሁ 25,791 ባለ እድለኞች እንኳን ደስ አላችሁ!!
    ለዘመናት በትዕግስት ስትቆጥቡና ስትጠባበቁ የነበራችሁ የ14ኛ ዙር የ20/80 እንዲሁም የ3ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤት ባለ እድለኞች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ!!
    ከዚህ ቀደም በቤት የዕጣ አወጣጥ ሂደት በገጠመን የማጭበርበር ችግሮች ምክንያት የእጣ አወጣጥ ሂደቱ ቢዘገይና እክል ቢገጥመውም የህዝብን ሃብት ለማዳን ያደረግነውን ጥረት በመረዳት ከጎናችን ስለሆናችሁና በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት የህግ የበላይነት እንዲከበር በትዕግስትና በማስተዋል እገዛችሁ ላልተለየን የከተማችን ነዋሪዎች በሙሉ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡
    እንዲሁም ለዚህ ስራ ስኬት በትጋት የተሳተፋችሁ ፤በየደረጃው የምትገኙ የስራ ሃላፊዎች፣ አመራሮች ፣ሰራተኞች፣ ባለሙያዎችና የፌደራል ተቋማት ስላበረከታችሁት ታላቅ አስተዋፅኦ በከተማ አሳተዳደሩ ስም ልባዊ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ!!
    አሁንም የጀመርነውን ከተማችንን እንደ ስሟ ውብና ደማቅ ለነዋሪዎቿ የምትስማማ የማድረግ ስራ ቃላችንን ጠብቀን በመቀጠል ከተማችንን ተወዳዳሪ ብቁና የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ስራ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡
    ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!!
    ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

    የ14ኛ ዙር የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤት ባለ ዕድለኞችን ለማየት ተከታዩን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ቴሌግራም ማስፈንጠሪያ ይጫኑ – EBC Telegram Link

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

    የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ

    Semonegna
    Keymaster

    ኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አደረገ
    የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ በሴቶችና ሕፃናት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል

    አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመስከረም 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ባለ 36 ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

    ይህ ዓመታዊ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪነት በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በዝርዝር በማተኮር ኮሚሽኑ የለያቸውን አበረታች እመርታዎችን፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮችን እና ምክረ-ሃሳቦችን አካቷል፡፡ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያዘጋጀው ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምርመራዎችና የመስክ ምልከታዎች፣ ባስተናገዳቸው የግለሰቦች አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶች እና ምክክሮች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲሁም የውትወታ እና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ በመመስረት ነው።

    የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅ እና ከማስፋፋት አንፃር በሕግ ረገድ የታዩ ክፍተቶች፣ የሴቶችና የሕፃናት ከጥቃት እና ከብዝበዛ የመጠበቅ፣ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ የማድረግ፣ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያለው አያያዝ፣ የቤተሰብ መብቶች እንዲሁም የሴት ሠራተኞች ሁኔታ ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

    በኢትዮጵያ በተከሰቱት ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ሕፃናት ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብ እና ከቤተሰብ ማግኘት ያለባቸው ጥበቃ በመጓደሉ ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት መጋለጣቸው እና ሴቶች በተፈጸሙባቸው ጾታዊ መድሎዎችና ጥቃቶች ምክንያት መሰረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሱ፣ ነጻነቶቻቸውን የሚገድቡ እንዲሁም ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ በደሎች እንደደረሱባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በተጨማሪም በብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥም ለሕፃናትና ለሴቶች ሰብአዊ መብቶች በቂ የሕግ ከለላ በመስጠት ረገድ የተለያዩ ክፍተቶች መስተዋላቸው ተጠቅሷል።

    በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ጦርነትና ቀጥሎም በየመሀሉ ማገርሸቱ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶች፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለጦርነት ዓላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ ጭምርም መፈጸማቸውን ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ውጤታማ ፍትሕ እና መፍትሔ የሚያስገኝ የወንጀልና የፍትሐ-ብሔር የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ የወንጀል ምርመራና የክስ አመሰራረት መጓደል በሪፖርቱ ከተዘረዘሩት ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው። በሌላም በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች በተለያየ ወቅት በተነሱ ግጭቶችም ሴቶችና ሕፃናት ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸው ተጠቅሷል።

    ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ሕፃናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥም ለጾታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸውና ልዩ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች አለማግኘታቸው ተደራራቢ የመብቶች ጥሰትን አስከትሏል። በሀገሪቱ በተከሰቱ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ወይም የተለያዩ ገደቦች መኖራቸው በሴቶችና ሕፃናት ትምህርትና ጤና የማግኘት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለብዝበዛ መጋለጥ፣ በኢንደስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች መሰረታዊ መብቶች ጥሰቶች መቀጠል እና በእነዚህ የመብቶች ጥሰት ረገድ የቁጥጥርና የተጠያቂነት መላላት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ በሪፖርቱ ።

    በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ መብት ጋር በተያያዘም፣ ሕፃናት በማናቸውም ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽና በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብታቸውን ለመተግበር የሚያስችል ሕግ አለመኖር፤ ሴቶችም በምርጫና በፖለቲካ ውስጥ ውጤታማ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የአመለካከት ችግሮች እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እክል መፍጠራቸው፤ እንዲሁም በሰላም ግንባታ እና በሀገራዊ ምክክር እና ሌሎች የሕዝባዊ ውይይት መዋቅሮች ውስጥም ጾታዊ አካታችነት በእጅጉ ውስን በመሆኑ፣ የሴቶች ተሳትፎ ተገድቧል፡፡

    ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ልጆች አያያዝ ከሕፃናት ፍትሕ መርሆዎችና መመዘኛዎች ውጪ መሆን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሴቶች ሁኔታ ከመሰረታዊ የሴት እስረኞች አያያዝ መስፈርቶች ጋር አለመጣጣም፣ ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩ ሕፃናት ትምህርትና አማራጭ እንክብካቤ የማግኘት መብቶች መጓደል፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክፍተቶች በሪፖርቱ ከተለዩ ጉድለቶች መካከል ናቸው። ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ለሕፃናት ነፃና ለሁሉ ተደራሽ የሆነ የልደት ምዝገባ አሠራር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕግ አለመደንገጉ እንዲሁም በተወሰኑ ክልሎች ደግሞ የቤተሰብ ሕግ አለመውጣቱ ከተስተዋሉት የሕግ ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

    በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የደኅንነት ሥጋቶች መቀጠላቸው የሴቶችን እና ሕፃናትን ሁኔታ በሚፈለገው ቅርበት እና ፍጥነት ለመከታተል እንዳይቻል እንቅፋት የፈጠረ መሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሠሩ የሲቪል ማኅበራት እና አጋሮች አቅምም መዳከሙና በኮሚሽኑ የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ጠንካራ የጋራ መድረክ አለመኖር ፈታኝ ሁኔታ መፍጠሩም ተጠቁሟል፡፡

    የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ የሴቶችንና የሕፃናት መብቶችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምክክሮች እና የተለያዩ ክንውኖች ትብብር በማድረግ እና ግብዓት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሕፃናትና ሴቶች ከግጭት፣ ከጥቃትና ከመድልዎ ነፃ የሆነ፤ ዘላቂ ሰላምና እኩልነት የሰፈነበት ሕይወትን እውን ለማድረግ በሪፖርቱ የተካተቱትን ምክረ-ሃሳቦች በመፈጸምና በማስፈጸም የተቀናጀ ጥረት እና ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

    ኮሚሽነር መስከረም አክለውም “ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስጠበቅ እና ማሟላት የመንግሥት ዋነኛ ግዴታ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ተቋማትን እና አሠራሮችን በማሻሻል፣ ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ፣ በግጭቶች የወደሙ የትምህርትና የጤና ተቋማትን እና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን መልሶ በመገንባት እና ለተጎጂዎች ሁለንተናዊ ተሐድሶን በማመቻቸት የሕፃናትንና የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች የማሻሻል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በተጨማሪም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ጠቅላላ ማህበረሰቡ በሰብአዊ መብቶች ማዕቀፍ በተቀመጠው አግባብ በሀገሪቱ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች አፈጻጸምን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።

    ሙሉ ሪፖርቱ እዚህ ተያይዟል

    [caption id="attachment_53773" align="aligncenter" width="600"]የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት[/caption]

    Semonegna
    Keymaster

    ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያ መዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቡራዩ ከተማ የተገነባውን የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት (ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያ መዕከል ) መርቀው መክፈታቸው ተገለጸ፡፡

    በመደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በማሰልጠኛ ተቋማትና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች የወጣቶችን ተሰጥኦ የማጎልበት ሥራ ማከናወን አስፈላጊ ነው።

    አሁን ባለው እውነታ ወጣቶቹ ተሰጧቸውን አበልጽገው ወደምርትና አገልግሎት ለመቀየር ከፈለጉ የትምህርት ሥርዓቱ የሚፈልገውን ቆይታ ማጠናቀቅ ግድ ይሆንባቸዋል።

    ወጣቶቹ የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድ ማለፍ ሲሳናቸው ደግሞ ተሰጥኦዋቸውን ለመረዳት፣ ለማውጣትና ለመተግበር ስለሚቸገሩ ባክነው የሚቀሩበት ዕድል ሰፊ ነው።

    በመሆኑም ከመደበኛው መማር ማስተማር ሳይለዩ ተሰጧቸውን ያለጊዜ ገደብ ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲለወጡና አገር እንዲጠቅሙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ይነገራል።

    የተገነባው ማዕከልም በሀገራዊ ለውጥ ምክንያት በነበሩ ጫናዎች ውስጥ ሆኖ መጠናቀቁና የአካባቢው ሕዝብ በግንባታ ሂደቱ ንብረት እንዳይጠፋና እንዳይባክን ጠብቆ ለምረቃ ያበቃው መሆኑ ተገልጿል።

    የአካባቢው ነዋሪ ከመሬት ስጦታ እስከ ጉልበት ያለምንም ካሳ አስተዋጽኦ ያደረገበት በመሆኑ ሕዝብ ከተባበረ ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑም ተመልክቷል።

    የማዕከሉ መገንባት አዲስ ከተማ ከመፍጠር ባለፈ ከትምህርት፣ ከሰው ኃይል ልማትና ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማትና ምርምር አኳያ መሠረት ይጥላል ተብሏል።

    በአንድ ጊዜ 1 ሺህ ባለተሰጥኦ ወጣቶችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችለው ትምህርት ቤቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ 500 ሰልጣኞችን የሚያስተናግድ ይሆናል።

    የፕሮጀክቱ ተጨማሪ ማስፋፊያ ሲገነባ በ10 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን አሁን የተመረቀው በ4.3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑ ታውቋል።

    በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያ ነው የተባለው ማዕከል የመመገቢያ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ሕንጻ፣ የሕክምና ማዕከል፣ የመማሪያ ክፍሎችና የጋራ መማሪያ አዳራሽ እንዲሁም ቤተ ሙከራን የያዘ ዘጠኝ ብሎክ ህንፃ ያለው መሆኑ ታውቋል።

    በተጨማሪም ኤሌክትሮ መካኒካል፣ የኬሚካልና ዲጅታል፣ ወርክሾፖች፣ ቤተ መጻሕፍት እና ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን ያሟላ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ለትምህርት ቤቱ የተሟሉት ቁሳቁሶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ እንደሆኑም ተመልክቷል።

    ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጠንሳሽነት የተጀመረና በእርሳቸው ጥብቅ አመራር የተፈጸመ መሆኑ ታውቋል።

    በዚሁ አጋጣሚ ለአካባቢው ሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ የጎዳና እና የውስጥ ለውስጥ መብራትና የውሃ አገልግሎት ማቅረብ ማስቻሉም ተመላክቷል፡፡

    የፕሮጀክቱ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሠረቱ ተጥሎ ሥራው የተጀመረው በ708 ሚሊዮን 693 ሺህ ብር መሆኑ ታውቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያ መዕከል

    Semonegna
    Keymaster

    የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ይከናወናል – የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልነት ጥያቄ ላይ የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ቦርዱ በተገቢው መንገድ ኃላፊነቱን ይወጣል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ።

    በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ኮንሶ፣ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች የሚካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚከናወን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

    የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት መግለጫ፥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከጊዜ ወደጊዜ አሠራሩንና ደረጃውን እያሳደገ በመሆኑ ሕዝብ ውሳኔውም በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወን ያደርጋል ብለዋል። ሕዝብ ውሳኔው ሰላማዊ፣ ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ቦርዱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣል ሲሉ ዋና ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

    ሕዝበ ውሳኔው ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ከሚደረጉ ዝግጅቶች መካከል የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሥራ እንደሚገኝበት ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል። ለምልመላ በሚቀርቡ እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ ላይ ቅሬታ አለኝ ያለ አካል ሪፖርት ማድረግ የሚችልበት አሠራር መዘርጋቱን አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ፓርቲ፣ በሲቪክ ማኅበራትና በተቋማት ካልሆነ በቀር በግለሰብ ደረጃ በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ቅሬታ የሚቀርብበት አካሄድ እንዳልነበር አስታውሰዋል። በሕዝብ ውሳኔው ላይ ግን በምርጫ አስፈጻሚዎች ሥነ-ምግባርና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አለኝ የሚል ማንኛውም ግለሰብ በማስረጃ በተደረፈ መንገድ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

    በእስካሁኑ የአስፈጻሚዎች ምልመላ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሳተፉ ዘጠኝ ሺህ አስፈጻሚዎች በደቡብ ኢትዮጵያ የሕዝበ ውሳኔ ላይ በድጋሚ ለማገልገል ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ፥ በአጠቃላይ 18,750 የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች እንደሚያስፈልጉ አስረድተዋል።

    ቀሪዎቹን የምርጫ አስፈጻሚዎች ለመመልመል ቦርዱ የቅጥር ማስታወቂያ እንደሚወጣ ገልጸዋል። እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ ከሆነ፥ ከምልመላ ሥራው ባለፈ ለሕዝበ ውሳኔው መሳካት የሚረዱ የውይይት መድረኮች ከሲቪክና ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማኅበረሰቡና ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር ተካሂደዋል።

    በእስካሁኑ የዝግጅት ሥራ የሕዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በአርባ ምንጭ ከተማ ተቋቁሟል። በዞንና በልዩ ወረዳዎች መከፈት ያለባቸው 11 ጽሕፈት ቤቶች እስከትናንትናው ዕለት ድረስ አልተከፈቱም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የየአካባቢው አስተዳደሮች በወቅቱ አስፈላጊውን ትብብር ባለማድረጋቸው የተፈጠረ በመሆኑ አስተዳደሮቹ አስፈላጊውን ትብብር በወቅት እንዲያደርጉ ዋና ሰብሳቢዋ ጥሪ አቅርበዋል።

    በደቡብ ብሔሮች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እንዲሁም አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ዜጎች ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል አዲስ ክልል እንመስርት፤ አሊያም በነበረው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልነት እንቀጥል በሚል ሕዝብ ውሳኔውን ያደርጋሉ።

    ለሕዝበ ውሳኔው በመራጭነት ሊመዘገቡ የሚችሉ ግምታዊ መራጮች ሦስት ሚሊዮን 106,585 ሰዎች መሆናቸውን ቦርዱ አሳውቋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ 410.1 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት ተፈቅዷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

    Semonegna
    Keymaster

    በ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል — የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፥ በተለያዩ አካባቢዎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መሥመር ውጪ ያሉ (ኦፍግሪድ/off-grid) የተሠሩ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን ቤቶችን ተጠቃሚ አድርገዋል።

    ከኦፍ ግሪድ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎቹ በተጨማሪ የቤት ለቤት የፀሐይ ኃይል ቁሶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህ ሥራ በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

    የ2014 ዓ.ም በተለይ በኢነርጂው ዘርፍ ትልቅ የማምረት አቅም የተፈጠረበት ዓመት መሆኑን የጠቁመው ሚኒስቴሩ፥ ሆኖም እምርታ እየታየበት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያዳርሳቸው የማይችላቸው የተንጠባጠቡ መንደሮችን የፀሐይ ኃይል እንደ አማራጭ እንደሚወሰድም ገልፀዋል።

    እስካሁን በተጠኑ ጥናቶችና ባለው ነባራዊ እውነታ በሀገሪቱ ያሉ የኢነርጂ ምንጮች የመጀመሪያው ውሃ፣ ቀጥሎ ደግሞ የፀሐይ ኃይል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ከውሃ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማሳደግ ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን ሶላር ኢነርጂን (solar energy) በመጠቀም የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከፍ ለማድረግ እየሠራች የምትገኘው ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

    በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሕብረተሰቡ በመንግሥት በኩልና በግሉ ከሚያገኛቸው የፀሐይ ኃይል አገልግሎቶች በተጨማሪ በተበታተነ መልኩ ያሉ መንደሮችን ለማገልገል የተገነቡ የውሃ ተቋማት ከሚጠቀሙት ጄነሬተር ኃይል በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ ኢነርጂዎች እንዲጠቀሙ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

    ሕብረተሰቡ በግሉ የፀሐይ ኃይልን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀይሩ መሣሪያዎችን መጠቀም መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ፥ መንግሥት ይህንን ለመደገፍ በአግባቡ የማይሠሩና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የሶላር ኢነርጂ መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በትኩረት መሥራቱንም ተናግረዋል።

    ከዚህ ጎን ለጎን የተበታተኑ መንደሮችን ከዋናው የኤሌክትሪክ መሥመር ውጭ በሆነ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በ2015 ዓ.ም አነስተኛ የሆኑ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ዲዛይን ማድረግ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

    በተለይ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ብዙ ወንዞች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ ወንዞቹን ለኃይል ማመንጫነት በመጠቀም ዜጎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

    ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ፥ ሀገሪቱ ካላት ወንዞች አብዛኞቹ ያሉበት ተፋሰስ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ምቹ መሆናቸው መረጋገጡንና በትናንሽ ወንዞች እንኳ ብዙ የኃይል እጥረቶች መፍታት እንደሚቻልም አብራርተዋል።

    በተመሳሳይ መልኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በባዮጋዝ (biogas) አጠቃቀም ረገድም ሕብረተሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ እንዲጠቀም ለማስቻል ጥረት መደረጉን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በዚህም ብዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በዘርፉ በመቀላቀል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፤ ጥረቱ በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

    Semonegna
    Keymaster

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በባህር ዳር ከተማ፣ በጣና ሐይቅ እና ሐዋሳ ሐይቅ ሦስት ሆቴሎችን ሊከፍት ነው
    /MIDROC Investment Group to open three international brand hotels in Bahir Dar, Lake Tana, and Lake Hawassa/

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ “ፕሮቴያ ማርዮት”ን በባህር ዳር ከተማ፣ በጣና ሀይቅ እና በሀዋሳ ሀይቅ ደግሞ “ፎር ፖይንትስ ባይ ሸራተን”ን ለመክፈት የሚያስችሉ ሦስት የፍራንቻይዝ ስምምነቶችን ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር ተፈራረመ።

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር በባህር ዳር የሚገኘውን ጣና ሆቴል እና ሀዋሳ የሚገኘውን ፕሮግረስ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ሁለቱንም በ“ፎር ፖይንት ባይ ሸራተን” ብራንድ እንዲሁም የብሉ ናይል (አቫንቲ) ሪዞርትን በ“ፕሮቴያ ማርዮት” ብራንድ ለመክፈት ነው ስምምነቱን ያደረገው።

    በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኩል ስምምነቱን የተፈራረሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አህመድ እና የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሰለሞን ዘውዱ ናቸው፡፡ ሚስተር ከሪም ቼሎት፣ ሚስተር ጁጋል ኩሻላኒ እና ሚስተር ኤድዋርድ ኤድዋርት ሳንቼዝ ደግሞ በማርዮት ኢንተርናሽናል በኩል ስምምነቱን ፈርመዋል።

    የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድም ከማርዮት ኢንተርናሽናል ጋር ስምምነት በማድረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ፥ “ከዚህ ዝነኛ ብራንድ ጋር የረጅም ጊዜ አጋርነታችንን እያሰፋን በመምጣችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።

    ማርዮትን ወክለው የተናገሩት ሚስተር ከሪም ቼሎት በበኩላቸው ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ያላቸውን አጋርነት በማሳደጋቸው እና በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ በማስፋታቸው ደስታ እንደተሰማቸው አስረድተዋል።

    ሁለቱ ወገኖች ባለፈው በፈረንጆቹ ህዳር 2021 በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ የሚገኘውን የዌስቲን ሆቴል ለማስተዳደር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ

    MIDROC Investment Group to open three international brand hotels in Bahir Dar, Lake Tana, and Lake Hawassa

    MIDROC Investment Group signs three franchise agreements with Marriott International to open Protea by Marriott in Bahir Dar, Four Points by Sheraton at Lake Tana as well as another Four Points by Sheraton at Lake Hawassa, Ethiopia.

    MIDROC Investment Group has signed an agreement with Marriott International to open the Tana Hotel located in Bahir Dar and Progress International Hotel located in Hawassa, both with Four Points by Sheraton, and Blue Nile (Avanti) Resort, located in Bahir Dar to Protea by the Marriott brand.

    Mr. Jamal Ahmed, CEO, and Mr. Solomon Zewdu, D/CEO of the Hospitality Cluster, signed the agreement on the Midroc Investment Group side. On the other hand, Mr. Karim Cheltout, Mr. Jugal Khushalani, and Mr. Edward Edwart Sánchez signed the agreement on Marriott International’s side.

    Mr. Jamal Ahmed, CEO of the Investment Group, said that we are excited to work with Marriott International as we continue to expand our long-standing partnership with this famous brand.

    Mr. Karim Chelout of The Marriot said with this significant project, we are thrilled to grow our partnership with MIDROC Investment Group and expand our presence in Ethiopia.

    It is recalled that the two parties signed to manage the Westin Addis Hotel located next to the African Union Headquarters in Addis Ababa in last November 2021.

    Source: MIDROC Investment Group

    Semonegna
    Keymaster

    የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ (tax incentive) ተግባራዊ ተደረገ

    አዲስ አበባ (የገንዘብ ሚኒስቴር) – የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን እና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር መስከረም 6 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. አስታውቋል።

    በዚህም የታክስ ማሻሻያ (tax incentive) ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከተጨማሪ እሴት ታክስ / ቫት/ (value added tax /VAT/)፣ ከኤክሳይዝ ታክስ (excise tax) እና ከሰር ታክስ (surtax) ነፃ እንደሚደረጉም ታውቋል።

    የታክስ ማሻሻያው ዓላማ በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደኅንነት ጋር የሚስማማ (environmentally friendly) ለማድረግ፣ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝኃ ህይወት (climate and biodiversity) ላይ ተጽዕኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን፥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻልም ነው።

    በታክስ ማሻሻያው መሠረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

    በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም 5 በመቶ (5%) የጉምሩክ ቀረጥ (custom duty) ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

    ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ (15%) የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፥ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ የመለክታል።

    ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሽከርካሪና የተሽከርካሪ ባለቤቶችን ቁጥር ለመጨመር መንግሥት ተሽከርካሪ በማምርት ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን ከመሳብና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ታክስ ላይ ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

    መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ ተሽከርካሪዎች ካሏቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፥ የእ.ኤ.አ 2019 ዓ.ም መረጃ እንደሚያሳየው፥ በአማካይ ሁለት መኪኖች ለአንድ ሺህ ሰዎች (2 cars to 1000 people) ነው።  በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተሽከርካሪዎቾ ቁጥር 600,000 አካባቢ ሲሆን፥፥ ከእነዚህ ውስጥ 84 በመቶ (84%) የሚሆኑት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ናቸው። አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎችም ከውጭ ሀገር ሲገቡ ያገለገሉ (secondhand) ሲሆኑ፥ አብዛኛዎቹም የሚመጡት ከገልፍ (Gulf) ሃገራት ከፍተኛ ቀረጥ (ታክስ) ተከፍሎባቸው ነው ሲል ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።

    የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ

    Semonegna
    Keymaster

    ጥቁር ገበያ ላይ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ ደርሷል

    አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቁር ገበያ ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

    ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ እንቅስቃሴ ነው ያለው ብሄራዊ ባንክ ዝውውሩ የሚከናወንባቸውን የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ባላገሩ ቴሌቭዥን ዘግቧል።

    ከብር አንፃር የዶላር ዋጋ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ መደበኛ ባልሆነው የሃዋላ ምንዛሬ (ጥቁር ገበያ) ባለፉት ጥቂት ቀናት ዶላር ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱን የባላገሩ ዘጋቢ ባደረገው ቅኝት ተረድቷል።

    ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አንድ ዶላር ጥቁር ገበያ ላይ ከ85 እስከ 87 ብር ድረስ በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ ዋጋ እስከ 92 ብር ድረስ ከፍ እንደሚል ባላገሩ ቴሌቪዥን ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ ከሚገኙት የጥቁር ገበያ መንዛሪዎች መረዳት ችሏል፡፡

    በመደበኛው የምንዛሬ ገበያ አንድ ዶላር በ53 ብር አከባቢ እየተመነዘረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ ያሳያል። በአሁኑ ጊዜ በጥቁር ገበያ እና መደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከ26 ብር በላይ ሆኗል።

    የዶላር ዋጋ መጨመሩ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ዋጋ ንረት ላይ የራሱን የሆነ ጫና የሚያሳድር መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ ያነሳሉ፡፡ የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያ ላይ በዚህ ያህል መናር የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ንግድ አለመመጣጠን መሠረታዊ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር አጥላው ገልጸዋል፡፡

    ሀገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሏ ነጋዴው ማኅበረሰብ በቂ ዶላር በባንክ ቤቶች በኩል ማግኘት አለመቻሉን ዶ/ር አጥላው አንስተዋል፡፡ በዚህም ምርት ከውጭ የሚያስገቡ ነጋዴዎች የጥቁር ገበያውን እንደ ዋና የውጭ ምንዛሬ ምንጭነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን እንዳሳደገው አብራርተዋል፡፡

    የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር በዋናነት የባንኮችን የዶላር ክምችት ማሳደግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ያነሱ ሲሆን፤ ለዚህም ምርትን በማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

    በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ከሰሞኑ ሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በተለይም ጥቁር ገበያ ላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

    ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን ጦርነት ተከትሎ የዓለም ምርት ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት መጨመሩንና ይህን ተከትሎ በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ እድገት ማሳየቱን ምክትል ገዥው አብራርተዋል፡፡

    በዓለም ገበያ ላይ የዩሮ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ በተቃራኒው የአሜሪካ ዶላር ፍላጎቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

    ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ ባንኩ የዚህ እንቅስቃሴ ማካሄጃ የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤ በቅርቡም በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ሲሳተፉ በተገኙ የሒሳብ ቁጥሮች ላይ እርምጀ እንደሚወሰድ ጨምረው አንስተዋል፡፡

    በመደበኛ የዶላር ምንዛሬ ገበያውም ላይም ቢሆን ባለፉት ስድስት ወራት በአንድ ዶላር የምንዛሬ ዋጋ ላይ የ2 ብር ከ60 ሳንቲም ጭማሪ እንደተደረገበት ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

    ምንጭ፦ ባላገሩ ቴሌቭዥን

    Semonegna
    Keymaster

    ሳንቴ የሕክምና ኮሌጅ ለ5ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የጤና ባለሙያዎች አስመረቀ

    አዲስ አበባ (የጤና ሚኒስቴር) – ሳንቴ የሕክምና ኮሌጅ በአጠቃላይ ሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ፣ በጥርስ ሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ፣ በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በBSc እና MPH ዲግሪ፣ በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ፣ ኒውትሪሽን በMPH ዲግሪ እና በሥነ-ተዋልዶ ጤና በMPH ዲግሪ ያሰለጠናቸውን የጤና ባለሙያዎች አስመረቀ።

    በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተግንኝተዉ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ እንዳሉት፥ ተመራቂዎች በኮሌጁ ቆይታችሁ ፈታኙን የሕክምናና የጤና ሳይንስ ትምህርት እንዲሁም ሌሎች ተግዳሮቶችን አልፉችሁ ነውና የእናንተን የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ ያረጋገጣችሁበት ስለሆነ ላደረጋችሁት ጥረት፣ ውጤታማነት ምስጋናና አድናቆት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

    ዶ/ር አየለ አያይዘውም የተመራቂ ቤተሰቦችንና የኮሌጁ መምህራን እንዲሁም አመራር/አስተዳደር አባላት ተማሪዎች በስኬት መንገድ እንዲጓዙና ውጤታማ እንዲሆኑ ለከፈላችሁት ዋጋ የሚያስመሰግናቸውና የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ገልፀው፤ በዛሬው ጊዜ ልጆችን በኃላፊነት አንፆ ለፍሬ ማብቃትና ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ የወላጅ፣ መምህራን እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጥረት እንደሚያስፈልግ አንስተው፣ ለትውልድ ቅብብሎሹ ላደረጉት መስዋዕትነት ሀገርም እንደምታመሰግናቸው ተናግረው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዘርፉ የሚስተዋለውን የጤና ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከከፍተንኛ ትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የጤናና የሕክምና ትምህርት የሚሰጡ በርካታ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።

    የኮሌጁ ተጠባባቂ ዲን ዶ/ር አህመዲን ኑርሁሴን በበኩላቸው፥ የኮሌጁ ዓላማ ከኮሌጁ ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎች ሰውን ወዳድ እና አክባሪ፣ አዋቂ፣ በተለያዩ ክህሎቶች የታነፁ፣ ብቁ ለህሙማንና ለማኅበረሰቡ ተቆርቋሪና በጎ አመለካከት ያላቸው ጠቅላላ ሀኪሞች፣ የጥርስ ሀኪሞች፣ ጤና መኮንኖች፣ የሜዲካል ላብራቶሪ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ (ፐብሊክ ሔልዝ)፣ ሥነ ምግብ (ኒውትሪሽን) እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሆነ ገልፀው፥ ተመራቂዎች ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ ትውልድ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመው ለ5ኛው ዙር ተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሌጁ የቦርድ አባል በተጨማሪ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተመራቂዎች የተማራችሁት የትምህርት ዓይነት ስለ ሰው ነው፤ ሰው ደግሞ ክቡር የሆነ ህይወትን የተላበሰ ልዩ የሆነ የእርሱ ፍጡር እንደሆነ አንስተው፤ ተመራቂዎች በተማራችሁበት ትምህርት ማኅበረሰቡን ለመርዳትና ሀገራችንን በሕክምናው ዘርፍ የላቀ ደረጃ ለማድረስ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድትወጡ በማለት ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው መልካም የምርቃ ጊዜ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

    ምንጭ፦ የጤና ሚኒስቴር

    Semonegna
    Keymaster

    ከ350 በሚበልጡ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን
    የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በ2014 በጀት ዓመት የሥነ-ሥርዓት ጥሰት በፈጸሙ ከ350 በላይ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ ከአረጋገጣቸው 10 ሺህ የትምህርት ማስረጃዎች 505 ቱ ሀሰተኛ ናቸው ብሏል።

    የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር ዶ/ር አንዷለም አድማሴ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በ2014 በጀት ዓመት ከየትኛውም በጀት ዓመት የበለጠ የትምህርት ጥራትን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን የማጽዳት ሥራ ተከናውኗል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ገምግሞ አቅጣጫ ካስቀመጠ ጊዜ ጀምሮ ከ350 በላይ በሚሆኑ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ወስዷል።

    መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየወሰዳቸው ካሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ውስጥ ሕገ-ወጥ የትምህርት ተቋማትን መቆጣጠር አንዱ ተግባር ነው ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ አሁን ላይ የትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ትርፍን ብቻ አላማ ያደረጉ ሕገ ወጥ የግል የትምህርት ተቋማት መስፋፋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

    ተቋምና ፕሮግራም መዝጋት አማራጭ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጣቸው በትውልድ ህይወት የሚነግዱ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

    እንደ ዶ/ር አንዷለም ገለጻ፥ በርካታ ዜጎች እውቅና በሌለው የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገንዘባቸውን ከፍለው ከተማሩ በኋላ ባለስልጣኑ ማረጋገጫ ሲሠራላቸው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሆንባቸው ለተመሰቃቀለ ህይወት እየተዳረጉ ነው። በተቋማት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ በ355 የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ከፕሮግራም መዝጋት እስከ ተቋሙን ሙሉ በሙሉ እስከ መዝጋት የደረሰ የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል። ለዚህም መገናኛ ብዙኃን የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

    የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ሥራ በበጀት ዓመቱ በትኩረት ከተሠራባቸው መካከል መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር አንዷለም፤ በዘርፉ የጤና ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን ለሚቀጥሯቸው ሠራተኞች ቅጥር ከመፈጸማቸው በፊት የትምህርት ማስረጃቸው በባለስልጣኑ እንዲረጋገጥ የሚያደርጉበት አግባብ ለሕገ-ወጥ የትምህርት ማስረጃ ቁጥጥር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። ዕድገትና ቅጥር ሲያከናውኑም በሙሉ ሳያስፈትሹ እንደማያከናውኑ ተናግረዋል።

    ዋና ዳይሬክተሩ የትምህርት ማስረጃ ሲረጋገጥ በቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች ተገደው የሚመጡ አካላትን የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥና ከውጭ ሀገር የተገኘ የትምህርት ማስረጃን አቻ ግምት በመስጠት በሁለት መልኩ የሚረጋገጥ ነው ብለዋል። የማረጋገጥ ሥራ የሚጀምረው ከሀገር አቀፍ ፈተናዎች እንደሆነና በወቅቱ ከነበረው የመቁረጫ ነጥብ በመጀመር እያንዳንዱ የትምህርት ማስረጃ ተፈትሾ እስከ ዲፕሎማና ዲግሪ እንደሚረጋገጥም ጠቁመዋል።

    በ2014 በጀት ዓመት የጤና ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽንን ሳያካትት ተገደው ከመጡ ከ10 ሺ በላይ የትምህርት ማስረጃዎችን ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ ከተረጋገጡት የትምህርት ማስረጃዎች 505 የሚሆኑት ትክክለኛ ያልሆኑ የትምህርት ማስረጃዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።

    ፈቃድ ሳያገኙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዱ ያሉ ትውልድን እያቀጨጩ የሚገኙ ሕገ-ወጥ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደት ሕብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርግም ዶ/ር አንዷለም ጥሪ አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    በሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያገኛሉ

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት አስታወቀ።

    የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዲጅታል መታወቂያ የሕግ አግባብነት፣ ዓላማና አዋጅ ጋር በተያያዘ ውይይት አድርጓል።

    የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ግንኙነት መሪ ሚና አወል፤ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ አንድን ሰው ማንነት በእርግጠኝነት መለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። መታወቂያው ዕድሜ፣ ፆታ፣ የአስር ጣቶች አሻራ፣ የመኖሪያ አድራሻና ሌሎች ገላጭ መረጃዎችን የሚይዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

    በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮችና በገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዴት መመዝገብ ይችላሉ የሚለውን ለማወቅ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች 125 ሺህ ዜጎች በሙከራ ደረጃ ተመዝግበው ውጤታማነቱ ተረጋግጧል ብለዋል። በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚኖሩ 12 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ለዚህም በንግድ ባንክ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና መሰል አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ በቀላሉ መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል።

    የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል፥ ዲጅታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ ነው። ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ በኪስ የሚያዝ ወረቀት ሳይሆን የራሱ መለያ /ፋይዳ/ የሚባል ቁጥር ብቻ ይዞ በማንኛውም ቦታ በቁጥሩ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዘመናዊ አሠራር መሆኑንም አስረድተዋል። ከቤቱ ሆኖ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማግኘትና በአገልግሎት ሰጭውና ተቀባዩ ዘንድ መተማመን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

    በዚህም እስከ 2018 ዓ.ም ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዕቅድ መያዙን አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል። የፎቶ ኮፒና ሌሎች የህትመት ሥራዎች ሁሉ የንግዱ ማኅበረሰብ በየሱቆቹ ማስመዝገብ የሚችልበትን አሠራር እንዘረጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

    የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ለጤናው ዘርፍ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ባለመኖሩ ምክንያት ዲጅታል የጤና መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያው ሥራ መጀመር በመላ ሀገሪቱ ያሉ ከ40 ሚሊየን በላይ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መታወቂያቸውን በቀላሉ አድሰው የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል። የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ትብብር እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል። ዘገባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ነው።

    የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 495 total)