Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 196 through 210 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፣
    ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና ያመለጡን ዕድሎች በብሔራዊ መግባባት መነፅር ሲታይ

    መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)
    ለብሔራዊ መግባባት ውይይት የቀረበ ጥናት
    ነሐሴ 2012

    አብዛኛዎቹ የሀገራችን የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በአስረኛው ምዕተ ዓመት የንግስት ሳባ እና የንጉሥ ሰለሞን ግንኙነት በሚባለው ጊዜ ይጀምራል ይላሉ። ይህ ለአንዳንዶቹ የሚታመን ታሪክ ተደርጎ የሚወሰደው፤ ለሌሎች ደግሞ ተረት እንደነበረ የሚነገረው ክስተት የማስመሰያ ትርክቱ የእስራኤል አምላክ የቀባቸው ገዥዎች ተብሎ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ንጉሦቹ ቅቡልነትን አግኝተውበታል። በትርክቱም ሀገሪቷን እስከ 1966 ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ያለ ብዙ ጭንቀት ገዝተውበታል።

    የዛሬይቱ ሰፊዋ ኢትዮጵያ እንደ ሕብረ ብሔራዊ የነገሥታት መንግሥት (multi-ethnic empire state) የተፈጠረችው በ2ኛው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ግማሽ፤ የዘመነ መሳፍንት ከሚባለው ዘመን በኋላ ስለሆነና ዛሬም በጣም ሰፊ ቀውስ ውስጥ የከተተን ታሪካዊ ዳራም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ፥ ጽሑፌም ከዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ጋር በተፈጠሩ ችግሮች ላይ ያተኩራል።

    የዘመነ መሳፍንትን ክስተት በመለወጥ የተጀመረው የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሕልም በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ከሦስት እጥፍ በላይ የሰፋች ኢትዮጵያን መፍጠር ችሎዋል። ይህ የታሪክ ክስተት የሦስት ምኞቶች ዉጤት ነበር። እነዚህም፡-

    1ኛ/ ተበታትና የነበረችውን የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማሰባሰብ የታለመ ምኞት፣
    2ኛ/ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን ጨምሮ ሰፊውን የደቡብ ክፍል የማስገበር ምኞት፣
    3ኛ/ አፍሪካን ለመቀራመት የመጡትን የአውሮፓ ሀገሮች ጋር የመፎካከር ምኞት ነበሩ።

    እነዚህን ሦስት ምኞቶች ለማሳካት የመጀመሪያ የሆነውን ሙከራ የጀመሩት እንደምታውቁት አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ። ቴዎድሮስ ሕልሞቹን ለማሳካት ጠንካራና ሰፊ ሠራዊት ማደራጀት ነበረባቸው፤ ለዚህም ሰፊ መሬት የያዙትን ቄሶች መሬት መቀማትና ዘመናዊ መሣሪያን ከክርስቲያን አውሮፓ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነበር። የአዉሮፓ መሪዎችን ማሳመን ሲያቅታቸው ደግሞ ሙያው የሌላቸውን አውሮፓዊያንን ሳይቀር በቤተ መንግሥታቸው ሰብስበው ከባድ የጦር መሣሪያ ውለዱ እስከማለት ደርሰዋል። ይህም ምኞታቸዉ ይሳካ ዘንድ በነበራቸዉ የጦር መሣሪያ የአካባቢ ገዥዎችንም ለማንበርከክ ተንቀሳቅሰዋል።

    ቄሶችን ለመግፋት ያደረጉት ሙከራ እግዚአብሔርን የካዱ ንጉሥ ተብሎ ተሰባከባቸዉ። የአውሮፓውያንን ዘመናዊ መሣሪያ ለማግኘት ገደብ ያለፈ ጉጉታቸው ከእንግሊዘኞች ጋር ያለጊዜ አላተማቸው። የየአከባቢውን ገዥዎች በጉልበት ለማንበርከክ እጅና አንገት በመቁረጥ የገፉበት ሙከራ ከእንግሊዞች ጋር ለመዋጋት የቁርጥ ቀን ሲመጣ፥ የትግራይ፣ የወሎ፤ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጎንደር ገዥዎች ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ካዷቸው። በአጭሩ የየአከባቢዉ ገዥዎች በእንግሊዞች እጅ መሞታቸውን ሲሰሙ ከማዘን ይልቅ ተገላገልን ያሉ ይመስላል። ለዚህም ይመስለኛል ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሴር ባህሩ ዘውዴ የቴዎድሮስን ሚና በተሻለ የታሪክ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ ሲሞክር፥ “የተወናበዱ የለዉጥ ነቢይ” (“confused prophet of change”) ያላቸዉ።

    በዚህ የቴዎድሮስ የታሪክ ሚና ላይ ብዙ ሰው ልብ የማያደርገውን የታሪክ ማስታወሻ አስቀምጬ ልለፍ። ይኼውም ቴዎድሮስ በጊዜው ለነበሩ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ፥ “አባቶቼ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር “ጋሎችን” በሀገሬ ላይ ለቆ፣ እነሱ ጌቶች ሆነው፣ እኛ የእስራኤል ልጆች የነሱ አሽከሮች ሆነን እንኖር ነበር። አሁን እግዚአብሔር ከትቢያ አንስቶኝ የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎኛል። እናንተ ከረዳችሁኝ በጋራ እየሩሳሌምንም ነፃ ልናወጣ እንችላለን” ማለታቸዉ ነዉ (ትርጉም የኔ ነው)። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ልበል፦

    1) “ጋሎቹ” የሚባሉት በዘመነ መሳፍንት የጎንደርን ቤተ መንግሥት በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበሩ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውና እየሩሳሌም በጊዜው በእስላሞች እጅ የነበረች መሆንዋን ነው።
    2) ከዚህ አንጻር ማስታወስ የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ አፄ ቴዎድሮስ የብሔረሰብ (የዘር) ፖለቲካን በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው።

    ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ለሦስት ዓመታት በተክለጊዮርጊስ እና ካሣ (አማቾች የነበሩ ይመስለኛል) ከተካሄደው የሥልጣን ትግል በኋላ በአሸናፊነት የወጡት አፄ ዮሐንስ (ካሣ ምርጫ) ነበሩ። አፄ ዮሐንስ ከሀገር ውስጥ ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ ገዢዎች ጋር እየተጋጩ፥ ከውጭ ደግሞ ከጣሊያኖች፣ ከግብፆችና ከሱዳን መሐዲስቶች (ደርቡሾች ) ጋር ሲዋጉ በመጨረሻ በመሐዲስቶች እጅ ወድቋዋል።

    በአጭሩ ዮሐንስ ለትግራይ ሊሂቃን የኢትዮጵያ ማዕከል ነበርን፤ የአክሱም ሀቀኛ ወራሾች እኛ ነን የሚለውን የፖለቲካ ስሜት መፍጠር ቢችሉም፥ በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተለየ ሚና መጫወት አልቻሉም።

    በማያሻማ ቋንቋ፥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዋናነት የተፈጠረችውና የዛሬው የታሪክ ጣጣችንም በዋናነት የተፈጠረው በአፄ ምኒልክ ነው። ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስን የሱዳን መሐዲስቶች እስኪገድሉላቸው ድረስ ከአውሮፓ መንግሥታት፥ በተለይም ከጣሊያን በገፍ ባገኙት የጦር መሣሪያ እነራስ ጎበና የመሳሰሉ የኦሮሞ የጦር መሪዎችን በመጠቀም በጊዜው ጠንካራ የሚባል ግዙፍ ሠራዊት መገንበት ችለዋል። ይህንን ግዙፍ ሠራዊትን ከዮሐንስ ጋር በመዋጋት ከማድከም ይልቅ፥ በአንድ በኩል ዮሐንስን እየገበሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የነበረችውን ኢትዮጵያ ሦስት እጅ እጥፍ የሆነ ሰፊ ግዛት መፍጠር ችሎዋል። በዚህም መጀመሪያ ሳይጠቀለሉ የቀሩትን የሸዋ ኦሮሞዎችን ጠቅልለው ያዙ። ከዚያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) በ1876 ጉራጌን ብዙ ሕይወት ከጠየቀ ጦርነት በኋላ አስገበሩ። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የምኒልክን የመስፋፋት ጦርነቶች እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል። ይኸውም በምኒልክና ጀኔራሎቹ ብዙ የግዛት መስፋፋት ጦርነቶችን ቢወጉም ሦስቱ ወሳኝ ጦርነቶች ነበሩ።

    አንደኛው በምዕራብ በኩል በእማባቦ (ዛሬ ሆሮ ጉዱሩ በሚባለው ላይ በጎበና መሪነት እ.አ.አ በ1882 የተዋጉት ጦርነት ነበር። ይህ ጦርነት ኦሮሞን ጨምሮ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ዕድልና የጎጃም መሪዎች ከሸዋ ጋር የነበራቸውን ፉክክር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወሰነና የሸዋንም የበላይነት ያረጋገጠ ነበር።

    ሌላው የምኒልክ ጦርነት በአርሲ ላይ እ.አ.አ በ1886 የተደመደመዉ ነው። አርሲዎች ከሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች በተለየ መንገድ ለአምስት ዓመታት በጀግንነት ተዋግተዋል። በመጨረሻም በራሳቸው በምኒልክ በተመራ ጦር የአውሮፓ መሣሪያ በፈጠረው ልዩነት ሊሸንፉ ችለዋል። ተመሳሳይ የመከላከል ጦርነት እንዳይገጥማቸው ይመስላል ምኒልክ ዛሬ አለ፣ የለም የሚባለውን የአኖሌ ዓይነት የጭካኔ በትር በአርሲዎች ላይ አሳርፈዋል። እዚህ ላይ ዛሬ እየተነጋገርንበት ላለው የብሔራዊ መግባባት መሳካት፥ የለም ከሚለው አጉል ክርክር ወጥተን የትናንትናውን የታሪክ ቁስላችንን በሚያክም መልኩ እንድናስተካክል መምከርን እወዳለሁ።

    ሦስተኛው የምኒልክ ትልቁ ጦርነት አሁንም በእሳቸው የተመራውና እ.አ.አ በ1887 የተካሄደው የጨለንቆ ጦርነት ነበር። የዚህ ጦርነት ውጤት በጊዜው የሀብታሟ የሐረር ከተማ መንግሥት (the Harari city-state) ጨምሮ ምስራቅ ኢትዮጵያ ያለ ደረሰኝ ምኒልክ እጅ የገባበት ሁኔታን ፈጥሯል። ከዚህም በኋላ ከፋን፣ ወላይታን፣ ወዘተ ለመያዝ ብዙ ደም የፈሰሰባቸው ጦርነቶች ነበሩ። እንደሚባለው በእንግሊዝ ተስፋፊዎችና በምኒልክ ኢትዮጵያ መካከል የመምረጥ ዕድል የገጠማቸው የቦረና ኦሮሞዎች፥ ‘ማንን ትመርጣላችሁ?’ ሲባሉ፥ የፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ፊትን አይተው፥ የእኛኑ ፊት የሚመስለው ይሻላል ብለው በሪፈረንደም (referendum) እየሰፋ በመጣው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ግዛት ውስጥ የተቀላቀሉበት ሁኔታም እንዳለ ይነገራል።

    እ.አ.አ በ1889 አፄ ዮሐንስ በመሐዲስቶች ሲገደሉ፥ ኦሮሞን ጨምሮ አብዛኛው ደቡብን የተቆጣጠሩት ምኒልክ ለሰሜኑ ወንድም መሪዎች ፈረንጆች እንደሚሉት “ካሮትና ዱላን ማስመረጥ” (carrot-and-stick approach) ብቻ በቂ ነበር። የሰሜኑ መሪዎች ምርጫም በማያሻማ መንገድ ካሮት ነበር። ስለካሮቱም በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኦሮሞ አከባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ የተገኘውን እጅግ በጣም ሰፊ ግዛት ዉስጥ በታናሽ ወንድምነት ሹማቶችን መቀራመት ነበር።

    በብሔራዊ መግባባታችን ውይይት አንፃር በምኒልክ በተፈጠረው ሰፊ አፄያዊ ግዛት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ወደ ማንሳቱ ልለፍ። አንደኛው ችግር ከላይ እንዳነሳሁት፥ በጉልበት የግዛት ፈጠራ ላይ አኖሌን የመሳሰሉ የታሪክ ጠባሳዎች መፈጠራቸው። ሁለተኛውና ዋናው ነገር ግን ከማቅናቱ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካል ኤኮኖሚው ነው። ይህም በነፍጥ ላይ የተመሠረተዉ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ዛሬም እያወዛገበን ያለው የነፍጠኛ ሥርዓት በሚባለው ላይ የተመሠረተዉ ነዉ። ለማቅናት የተሰማራው የፊውዳሉ ሥርዓት ሠራዊት የገባር ሕዝቦችን ነፃነት ቀምተዋል፤ መሬታቸዉን ዘርፈዋል፤ ሕዝቦችን በገዛ መሬታቸው ላይ ጭሰኛና አሽከር አድርገዋል፤ ቋንቋቸውን አፍነው በ’ስማ በለው’ ገዝቷቸዋል። በአጭሩ፥ እጅግ በጣም ዘግናኝና ጨካኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ጭነውባቸዋል። አንዳንዱ ነፍጠኛ በሃያ ሺዎች የሚቆጠር ጋሻ መሬትም ነበረው። ወረ-ገኑ የመሳሰሉ የቤተ መንግሥት መሬቶች እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት ይዞታም በፍጹም የተለያዩ መሆናቸው ነው። አነሰም በዛ የሰሜኑ ገበሬ የዘር ግንዱን ቆጥሮ መሬት ያገኛል። መሬት አያያዙም የወል ነበር። ሌላው ቢቀር የሚገዛውም በራሱ ቋንቋ ነበር። በደቡቡ ያለው ግን የመሬት ሥርዓቱ የግል ሆኖ፥ ጭሰኝነት እጅግ የተንሠራፋበት ነበር። ሲሶ ለነጋሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ፣ ሲሶ ለአራሽ የሚባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የመሬት ፖሊሲ እጅግ በጣም ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሥራ ላይ የዋለው በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ነው።

    በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን “መሬት ላራሹ” እና “የብሔረሰቦች እኩልነት” የተባሉ ሕዝባዊ መፈክሮች የተወለዱት ከዚሁ ጨቋኝ ሥርዓት ነበር። ዛሬ የታሪክ ክለሳ ውስጥ ብንገባም፥ በእውነቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራክ የወጡ ወጣቶች፥ እንዲያውም በወቅቱ ‘አማራ’ ከሚባለው ክፍል የሚበዙ ይመስለኛል፤ መፈክሮቹን በጋራ አስተጋብተዋል።

    ለማንኛውም ከብሔራዊ መግባባታችን አንፃር አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ። ‘ነፍጠኛ’ የሚባለው ሥርዓት ገዝፎ የነበረ ሥርዓት መሆኑና፥ ይህም ሥርዓት ከደቡቡ አርሶ አደር የተሻለ ኑሮ የማይኖሩትን፥ ቢፈልጉ እንኳን የደቡቡን ገበሬ ለመዝረፍ አቅሙም ሆነ ዕድሉን ያልነበራቸውን የአማራ አርሶ አደርን አይጨምርም፤ መጨመሩም ጩቡ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ አንዳንድ የአማራ ሊሂቃን “እኔም ነፍጠኛ ነኝ” የሚለውን መፈክር ሲያሰሙ፥ ጥቅሙ ኦሮሞን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ከአማራ ሕዝብ ጋር ከማጋጨት የዘለለ የፖለቲካ ትርፍ የሚኖረው አይመስለኝም። ስለሆነም የምንችለውን ያክል ሁላችንም ከሁለቱም ጩቡዎች እንጠንቀቅ ዘንድ አደራ እላለሁ።

    ወደ ሌሎች ነጥቦች ከማለፌ በፊት በዋናናት በምኒልክ የተፈጠረችዉ ኢትዮጵያን ለማስተካከል ያቃታቸዉና መሪዎች ማለፍ ያልቻሉት የታሪክ ፈተና ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በንጽጽር እንደ ታሪክ ቁጭት ማንሳትን እወዳለሁ። አፄ ቴዎድሮስ የሞቱት እ.አ.አ በ1868 ነበር። ጃፓንን ከታላላቅ የዓለም መንግሥታት ተርታ ያሰለፏት መጅ (Meiji) የሚባሉ የንጉሣውያን ቤተሰብ ወደ ሥልጣን የተመለሱት (The Meiji Restoration) በዚሁ ዓመተ ምኅረት ነበር። የጃፓን ንጉሣዊ ቤተሰቦች በሰላሳ ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ የበለፀገች ታላቋ ጃፓንን ፈጠሩ። የጃፓኖች የሀገር ፍቅር ግንባታቻውም ባዶ አልነበረም። ትዝ እስከሚለኝ ድረስ አንድ የጃፓን ወታደር ንጉሤ የጃፓንን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሸነፍ አልነገሩኝም ብሎ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ በፊሊፕንስ ይሁን፤ በኢንዲኔዢያ ጫካ ውስጥ ተገኝቷል። ለሀገር ፍቅር ሲባል እራስን በራስ ማጥፋት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በትናንሽ አይሮፕላኖችን የአሜሪካን መርከቦች ውሰጥ እየጠለቁ አጥፍቶ መጥፋትን የጀመሩት የጃፓን ካሚከዞች (Kamikaze) የሚበሉ ነበሩ። የኢትዮጵያ መሪዎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ (እ.አ.አ 1868-1900) ድረስ ሀገሪቷን ከዓለም ጭራነት አላላቀቋትም። በነገራችን ላይ ጃፓንና ኢትዮጵያ በ1868 ላይ ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ።

    ሌላው ንጽጽሬና የታሪክ ቁጭታችን መሆን ያለበት፥ ታላቋ ጀርመንን የፈጠሩት ቢስማርክ (Otto von Bismarck) እና ምኒልክ የአንድ ዘመን ሰዎች ነበሩ። ምንም ይሁን ምን እነ ቢስማርክ ዓለምን ሁለት ጊዜ ጦርነት ውስጥ መክተት የቻለች ኃያሏን ጀርመን ሲፈጥሩ፥ የኢትዮጵያ ገዥዎች ግን ኋላቀር ኢትዮጵያን ትተውልን ሄደዋል። በነገራችን ላይ ሀገር ትፈርሳለች ተብሎ ስለተሰጋ፥ የምኒልክ ሞት ለሕዝብ ይፋ የሆነው ከዓመታት በኋላ ነበር ይበላል።

    በአጠቃላይ ከብሔራዊ መግባባት ፈጠራችን አንፃር መረሳት የሌለበት ቁመነገር፥ በምኒልክና ጣይቱ የተመራው የአድዋው የጋራ ድል እንኳ ያልፈቱት የሚጋጩ ሦስት አመለካከቶች ዛሬም ከእኛ ጋር መኖራቸዉ ነዉ።

    አንደኛው፥ የሀገራችን ሀገረ-መንግሥት ግንባታ አንድ የነበሩና የተበታተኑ ሕዝቦችን አንድ ላይ መልሶ ያመጣ ነዉ የሚላዉ አመላካከት (reunification)፤
    ሁለተኛው፥ በአንድ ላይ ያልነበሩ ሕዝቦችን ወደ አንድ ማምጣት ነዉ የሚለዉ አመላካከት (unification and/or expansion)፤
    ሦስተኛው፥ ነፃ ሕዝቦችን ጨፍልቆ በኃይል ማቅናት ነዉ የሚላዉ አመላካከት (colonial thesis) ናቸው። የበለጠ ግልፅ ለማድረግ፥ የኢትዮጵያ አንድነት አጥባቂዎች ነን የሚሉ በዋናነት የምኒልክን ኃጢአቶች አይቀበሉም። እንደሚሉት እምዬ ምኒልክ በዓለም ከተደረጉት የሀገር ግንባታዎች ምን የተለየ ነገር ሠራ የሚለውን ሐሳብ ያራምዳሉ። ከዚያም አልፈዉ ምኒልክ የሠራዉ ሥራ ተለያይተዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ ግዛቶችን መመለሰ ነበር ይላሉ። በአንፃሩ የኢትዮጵያ አንድነትን የማያጠብቁ ብሔረተኞች ደግሞ የአቶ ሌንጮ ለታን አባባል ለመጠቀም (አሁን አቋማቸዉ ያ መሆኑን አላዉቅም)፥ ሲያንስ “ኢትዮጵያዊ ለመሆን እንደራደራለን ሲበዛ ደግሞ ነፃ መንግሥታትን እስከ መፍጠር ድረስ እንሄደለን” የሚሉ ናቸው። በጥቅሉ እነዚህ አመለካከቶች በፖለቲካችን ለሚጋጩ ሕልሞቻችን መሠረት የሆኑና ካልተገደቡ የሥልጣን ሕልሞች ጋር ተደምሮ የብሔራዊ መግባባት ጥረታችንን የሚያወሳስቡ አመለካከቶች መሆናቸውን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል።

    በእነምኒልክ የተፈጠረችዉን ኢትዮጵያን ለማስተካከል የተደረጉ ሙከራዎችና ያመለጡን ዕድሎች፡-

    1) የልጅ ኢያሱ ሙከራ

    ልጅ ኢያሱ የምኒልክ ልጅ ልጅ ሲሆን፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩ ዕድል የነበረውና ያንንም ልዩ ዕድል አውቆ ለመጠቀም ሲሞክር በወጣትነት ዕድሜው ላይ የተቀጨ መሪ ነበር። በብሔር ግንዱ ኦሮሞና አማራ የነበረ፣ በሃይማኖት ጀርባዉ ክርስቲያንና ሙስሊም የነበረ ሰዉ ነዉ። ከወሎም በመወለዱ፣ ትግራይንና ሸዋን ለማገናኘት የተሻለ ድልድይ ለመሆን ይችል ነበር። የሚገርመው ግን፥ የልጅ ኢያሱ ወንጀሎች የሚመነጩት እነዚህኑ አዎንታዊ እሴቶችን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለመጠቀም መሞከሩ ነበር። ለምሳሌ አንዳንድ የታሪክ ማስታወሻዎች እንደሚያስረዱት፥ አርሲዎች እንደልጃቸው ይመለከቱት ነበር ይባላል። ከሱማሌዎችና ከአፋሮች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው በቂ የሆነ የታሪክ ማስረጃ አለ። ከጎጃሙ ራስ ኃይሉና ከወለጋው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ጋር የጋብቻ ዝምድና እንደነበረው ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያንን ለማሠራት የሚጥረውን ያክል (ለምሳሌ የቀጨኔውን መድሃኔዓለምን እሱ ነው ያሠራው ይባላል) መስግዶችን ያሠራ ነበር። ከሥልጣን ላወረዱት የሸዋ ሊሂቃን ግን፤ አንዱና ትልቁ የልጅ ኢያሱ ወንጀል መስጊዶችን ማሠራቱ ነበር። የመጨረሻው ትልቁ ወንጀል ደግሞ ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያንዣበቡ የቅኝ ገዥ ኃይሎች ከሰሜንና ምስራቅ ጣሊያን፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በምስራቅ እንግሊዝ፣ በምስራቅ ፈረንሳይ የሦስትዮሽ ስምምነት (tripartite treaty) የሚባለውን እ.አ.አ በ1903 ፈርሞ የምኒልክን ሞት ይጠብቁ ከነበሩት መራቅና በአንደኛው የዓለም ጦርነት በአከባቢያችን ግዛት ካልነበራቸው ከነጀርመንና ቱርክ ጋር ለመደጋገፍ መሞከሩ ነበር።

    በጥቅሉ ከሁሉም በላይ ወንጀሎቹ ሰፊዋን ኢትዮጵያን የፈጠርን እኛ ነን የሚሉትን የሸዋ ልሂቃንን መጋፋቱ ነበር። በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኢያሱ ወንጀሎች የሸዋ ልጅ አለመሆኑ (የኢያሱ አባት ወሎ ነው)፣ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አለመሆኑ (አባቱ የግድ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት መሐመድ ዓሊ ነበሩና) እንዲሁም የአውሮፓ የቅኝ ገዥ ኃይሎችን ማስቀየሙ ናቸው።

    እ.አ.አ በ1916 በመስቀል ቀን ኢያሱን ለማውረድ ሁሉም መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ተሰለፉ። ቄሶቹ ኢያሱ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አይደለም በማለት በማውገዝ፣ የሸዋ ሊሂቃን ሠራዊታቸውን በመሳለፍ፣ የአውሮፓዊያኑ መንግሥታት ምክርና ጥበባቸውን ይዘው ተሰለፉ። የአውሮፓዊያኑ ጥበብ የሚገርም ነበር፤ ኢያሱ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የእስልምና ምልክት የሆነውን ግማሽ ጨረቃ ለጥፎ ለቱርኮች ዲፕሎማት ሲሰጥ የሚያሳይ ፎቶ ሾፕ የሆነ ሥዕል (ፎቶ ሾፕም፣ የባንድራ ፖለቲካም በልጅ ኢያሱ ዘመንም ነበር) መፈንቅለ መንግሥት እንድያከሄዱ የሸዋ ሊሂቃንን መርዳት ነበር። እዚህ ላይ ለታሪክ ትዝብት አንድ ነገር ልብ በሉልኝ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሳስተምር፥ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ችግሮቻችንን በሚመለከት ፈተናም ፈትኜበታለሁ፤ የሸዋው ጦር መሪ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የመፈንቅለ መንግሥቱም መሪ ነበሩ፤ ልጅ ኢያሱን ሲያወርዱ ባስተላለፉት መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል።

    “He claims that he eats flesh of cattle slain by Muslims in order to extend frontiers and to win hearts. But these Somali and Muslims have already been brought to heel [and do not need such diplomacy]”

    በጥሬው ሲተረጎም፥ ግዛትን ለማስፋፋትና ልቦችን ለመሳብ ብዬ በሙስሊም የታረደውን የከብት ሥጋ እባላለሁ ይላል። ነገር ግን እነዚህን ሱማሌዎችና ሙስሊሞችን ቀድሞውኑ ስላንበረከክን እንዲህ ዓይነቱ ዲፕሎማሲ አያስፈልጋቸውም።

    ይህንን የሀብተጊዮርጊስን ንግግር በሚመለከት ሰፊውን ትንተና ለናንተ ትቼ፥ በዚህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን አስተካክሎ በሰፊ መሠረት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ፥ ልጅ ኢያሱን ለሥልጣን ተብሎ በተጠነሰሰው ሤራ መውረዱን እንዳትረሱት አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ያመለጠንን ዕድል ትርጉም ግን ለታሪክ መተውን አመርጣለሁ።

    2) ኢያሱን በወሳኝነት የተኩት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ

    የሀገራችንን ሀገረ-መንግሥት ግንባታን በተሻለ መሠረት ላይ ለመገንባት ረጅም ጊዜ (ለ60 ዓመታት ገደማ አገሪቷን መርተዋል) በልጅነታቸው የተሻለ የፈረንጅ ዕውቀት የቀመሱና ከማንም የበለጠ ተደጋጋሚ ዕድል ያገኙ ነበሩ። ነገር ግን በእኔ ግምት ታሪክ የሰጣቸዉን ዕድል አልተጠቃሙበትም። ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ የታሪክ ሚዛን ላይ ቢያስቀጣቸውምና እኔም ቢሆን በዘመናዊ ትምህርትና በመሳሰሉት ላይ የነበራቸውን አሻራ ቀላል ነው ብዬ ባላስብም፥ ንጉሡ ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ የግል ዝናንና ሥልጣንን ማዕከል ማድረጋቸው ኢትዮጵያዉያንን የ20ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች ማድረግ አልተቻላቸውም። ስለዘር ግንዳቸው ሀሜቱ እንዳለ ሆኖ፥ ከኢያሱ በተሻለ ደረጃ ኦሮሞም፣ ጉራጌም አማራም ነበሩ። ይህንን ስረ ግንድ አልተጠቀሙም። በተለይ ኦሮሞ ከሚባል ሕዝብ ሲሸሹ እንደኖሩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለማንኛዉም፤ አንድንድ ወሳኝ ነገሮችን እንመልከት።

    አምቦ 2ኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የሰማሁት ይመስለኛል፤ አንድ ጋዜጠኛ ካነበቡት መጽሐፍት ዉስጥ የትኛውን እንደሚያደንቁ ሲጠይቃቸው፥ ቀልባቸውን በጣም የሳበውና ብዙ ጊዜ ደጋግመው ያነበቡት በኒኮሎ ማኪያቬሊ (Niccolò Machiavelli) የተፃፈውን “The Prince” የተባለውን እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ንጉሡ አብዘኛዉን የሕይወት ዘመናቸዉን የተመሩት በማኪያቬሊ ምክር ነበር ብዬ እጠረጥራለሁ። በማክያቬሊ ትምህርት በመመራትም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን አንድ በአንድ አስወግደው ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1930 ጥቁር ማክያቬሊ ፈላጭ ቆራጭ ንጉሥ ሆነው ወጡ።

    እንደ ሀብተጊዮርጊስ ዓይነቱን እግዚአብሔር በጊዜ ሲገላገልላቸው፣ እንደ ጎንደሩ ራስ ጉግሳና ባለቤታቸው ንግስት ዘዉድቱን ያስወገዱበት የፖለቲካ ጥበብ፣ በጊዜው በርግጥም አስደናቂ ነበር። ይህ የንጉሡ ጥበብ፤ አርባ ዓመታትን ቆጥራ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የመጣቸውን ጣሊያንን ለመከላከል አልረዳም። መንግሥታቸዉንም፤ ሀገሪቷንም ለክፉ ቀን አላዘጋጁም።

    አድዋ ላይ ታሪካዊ ድል ያስገኙ ጀግኖችም የሉም። አንድ ለታሪክ የተረፉት ደጀዝማች ባልቻ ሣፎም በንጉሡ ዉሰኔ እስር ቤት ነበሩ። እዚህም ላይ አንድ የታሪክ ትዝብት አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለሁ። ኃይለ ሥላሴ ለሥልጣናቸዉ ብሎ የገፏቸው ብዙ የአከባቢ መሪዎች፥ ከትግራዩ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ጀምሮ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጅማ፣ የወለጋ ገዥዎች የጣሊያን ባንዳ ሆኑ። ከሚታወቁት ውስጥ ለታሪክ ‘ተፈሪ ሌላ፣ ሀገር ሌላ’ ብለው ሲዋጉ የሞቱት ደጃዝማች ባልቻ ብቻ ነበሩ። በንጉሡ ስህተት ሀገሪቷ ውድ ዋጋ ከፍላለች። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ጠዋትና ማታ ባንዳ፣ ባንዳ ሲሉ፥ ግብፅ ሱዳንን ይዛ የምር ከመጣች ሰው ያላሰበውን አሳስበው ለኪሳራ እንዳይዳርጉን የሚፈራው።

    ያም ሆነ ይህ፥ ኃይለ ሥላሴ ለጦርነት ያላዘጋጇትን ሀገር በክፉ ቀን ጥለው ሸሹ። ሐረርጌ ላይም የጂቡቲን ባቡር ሲሳፈሩ ከጦር ሜዳ መሸሻቸውን ለመሸፈን፥ ‘የት ይሄደሉ?’ ብሎ ለጠያቀቸዉ የፈንሳይ ጋዜጠኛ፡ “Je ne suis pas né soldat” (“ወታደር አይደለሁም”) ብለው ያለፉት። ለሳቸዉም ፍትሃዊ ለመሆን፥ የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ቢክዷቸውም በዓለም መንግሥታት ማኅበር ላይ የሚያስመካ ሥራ ሠርተዋል። ሆኖም ከጦር ሜዳ የመሸሻቸው ጉዳይ እስከ መንግሥታቸው ፍፃሜ ድረስ እንደ ጥቁር ነጥብ ስትከታላቸዉ ኖራለች። የአርበኞችም ሆነ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዋናው የተቃውሞ መፈክርም ይህች የሽሸት ጉዳይ ነበረች። ከጣሊያን ወረራ በኋላም ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ምክንያት፥ ጋዜጣቸውን “አዲስ ዘመን” ብለው እንደሰየሙ፥ በእርግጥም አዲስ ዘመን፤ ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ይፈጠራሉ ብሎ የጠበቁ ብዙ መሆናቸውን ብሎ መገመት አስቸጋሪ አይመስለኝም።

    ለአምስት ዓመታት በእንግሊዝ ሀገር በስደት ሲኖሩ ስለራሳቸው ስህተትም ሆነ የሰለጠነው ዓለም ንጉሦች እንዴት ሕዝቦቻቸውን እንደሚመሩና በዚያም ምክንያት በሕዝቦቻቸው ዘንድ ተከብረው እንዴት እንደሚኖሩ ተምረዋል ብሎ መጠበቅ ይቻል ነበር። ከሁሉም በላይ በጣሊያን ወረራ ምክንያት እሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ከገጠመው ውርደትና ኪሳራ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅም ነበር። ከሁሉም አልተማሩም። በባሰ ሁኔታና ፍጥነት ወደ ድሮአቸው ተመለሱ። ለዓቢይነት፥ አስተዳደራቸውን የተቃወሙ የራያ ገበሬዎችን (ቀዳማይ ወያኔ የሚባለዉ ነዉ) ከየመን በመጡ የእንግሊዝ አይሮፕላኖች አስደበደቡ። የሪፐብሊካን አስተሳሰብ ነበራቸው የሚባሉትን አርበኛ ደጃዝማች ታከለን (ደጃዝማች ታከለ ወልደሀዋርያት) አሰሩ። እኚህ ሰው ከተደጋጋሚ እስር በኋላ በመጨረሻም ሊይዟቸው ከተላኩ የንጉሡ ወታደሮች ጋር ሲዋጉ ሞቱ። ሌላው ስመጥር አርበኛ የነበሩ በላይ ዘለቀንም ያለርህራሄ ሰቀሉ።

    የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ግልፅ ደብዳቤ እንኳን (አምባሳደር ብርሃኑ፤ በአሜሪካ አምባሳደር የነበሩና ንጉሡ የገፉበት መንገድ ዉሎ አድሮ ንጉሡንም ሆነ ሀገሪቷን ለዉርደት እንደሚያበቃ የመጀመሪያ የማስጠንቃቂያ ደወል በአደባባይ የሰጡ ባለስልጣን ነበሩ) አሠራራቸውን አላስለወጧቸውም።

    በፖለቲካ ሥርዓታቸው ላይ በተከታታይ ቦንቦች ፈነዱ። የመጀመሪያዉ ትልቁ ቦንብ በራሳቸው ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈነዳው የነመንግሥቱ ንዋይ ያውም የእሳቸውን ክብርና ሞገስ ለመጠበቅ ከፈጠሩት የክብር ዘበኛ ጦር ነበር። ንጉሡ ከክስተቱ ከመማር ይልቅ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን በሞት ቀጡ፤ የታናሽ ወንድማቸውን ሬሳ እኔን ያየህ ተቀጣ በሚመስል መንገድ በስቅላት ቀጡ። የበሉበትን [ወጭት] ሰባሪዎች ናቸው ብለውም በአዝማሪ አዘለፏቸው።

    ማን እንደመከራቸው ባይታወቅም ትልቁን የመንግሥታቸውን የዲፕሎማሲ ውጤትን ያበላሸውና ለትልቅ ኪሳራ ያበቃንን የኤርትራን ፌዴሬሽንን አፈረሱ። ውጤቱም ሁላችንም እንደምናውቀው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር መፈጠር ሆነ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ኦሮሞዎች የሜጫና ቱለማ ልማት ማኅበር በመፍጠራቸው ጠገቡ ተብሎ መሪዎቹ እነ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር ተሰቀሉ፤ ኃይለማርያም ገመዳ እስር ቤት ውስጥ በተፈፀመበት ድብዳባ ሞተ። ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሞት ተፈርዶባቸው በአማላጅ ወደ ሐረርጌ በግዞት ተላኩ። እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ አልነበራቸውም። ውጤቱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን መፍጠር ሆነ። በነገራችን ላይ በእነ ኤሌሞ ቅልጡ በኦነግ ስም የመጀመሪያዋ ጥይት የተተኮሰችው ጀኔራል ታደሰ ብሩ የታሰሩበት ሥፍራ ሐራርጌ ዉስጥ ነበር። በዚሁ ጊዜ ሰፋፊ ማኅበራዊ ፍትህን የሚጠይቁ ተከታታይ ጥያቄዎችም መቅረብ ጀመሩ። እ.አ.አ በ1965 የንጉሡ ፊውዳላዊ ሥርዓት የተመሠረተበት ላይ በመሬት ላራሹ ሰልፍ ድንገተኛ የፖለቲካ ቦንብ ፈነዳ። ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ እስከዛሬ ኢትዮጵያን እያመሰ ያለው በእነ ዋለልኝ መኮንን የብሔረሰቦች ጥያቄ ታወጀ። ይህችኛውን ንጉሡና ሥርዓቱ በቀላሉ የተመለከቷት አይመስልም። ንጉሡ የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ፥ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዝደንት የነበረውን ጥላሁን ግዛዉን በማሰገደል “ልጆቼ” ከሚሏቸው ተማሪዎች ጋር ደም መቃባት ዉስጥ ገቡ። በዚህም የታሪክ ጎማው ወደፊት እንዳይሽከረከር ጣሩ።

    አሳዛኙ ጉዳይ መካሪዎቻቸውም ሆኑ እሳቸው አስተዳደራቸው ለሃያኛዉ ክፍለ ዘመን የማይመጥን መሆኑን፣ በጣም እወዳታለሁ የሚሏትም ኢትዮጵያ በታሪክ ፍራሽ ላይ ተኝታ የምትሸሞነሞን ሀገር መሆኗን አልተረዱም። የኤርትራ ግንባሮች ጥይትም ከረጅም ዘመን እንቅልፋቸው አላነቋቸውም። የባሌና የጎጃም ሕዝብ አመፅም አልቀሰቀሳቸውም። ለዓመታት የቆየው የተማሪዎች ንቅናቄ ጩኸትም አላነቃቸውም። ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በቀጥታ የወጡ የመኢሶንና የኢህአፓ የሶሻሊስት አብዮት ደወልም አላነቃቸውም። በመጨረሻም በመቶ ሺዎች የሚቆጠረው የወሎ ሕዝብ እልቂት እንኳን ከእንቅልፋቸዉ አላበነናቸውም።

    በነገራችን ላይ፥ ብልጡ ደርግ በጠዋቱ ሊያወርዳቸው፣ ማታ ያሳየው የወሎ ሕዝብ እልቂት፥ በአንድ በኩል የንጉሡ ውሻ በጮማ ሥጋ ሲጫወት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃብ በተረፈረፈ ሕዝብ ውስጥ ሕፃን ልጅ የሞተች እናቷን ጡት ስታጠባ የሚያሳየዉን የጆናታን ዲምበልቢ (Jonathan Dimbleby, “The Unknown Famine”) ፊልም ነበር። ያንን ፊልም ደርግ በቅድሚያ ንጉሡና የኢትዮጵያ ሕዝብን እንዲያዩ ስለጋበዘ ቴሌቪዥን ያልነበረን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አካባቢዎች ያሉትን ቡና ቤቶችን አጣብበን ስንመለከት ነበር። የንጉሡ ደጋፊዎች እንኳ ጃኖሆይ እንዲህ ጨካኝ ነበሩ እንዴ? የሚሉትን ይዘን ወደ ዶርማችን እንደገባን ትዝ ይለኛል። ምናልባት ከእንቅልፋቸው የነቁት በማግስቱ የደርግ አባላቱ በኩምቢ ቮልስዋገን ከቤተ መንግሥታቸው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሲወስዷቸው በሠሩባቸው ድራማ ይመስለኛል። ብልጣብልጦቹ ደርጎች የተጠቀሙት ቮልስ መጀመሪያ መስኮቷ ዝግ ነበር ይባላል።

    ንጉሡ ከውጭ ብዙ ሰው ሲጮህ ተመልክተው፥ “እናንተ ልጆች የሚወደን ሕዝባችን ንጉሤን የት እየወሰዳችሁ ነው እያለ ነዉ” ሲሉ፥ ብልጦቹ ደርጎችም መስኮቱን ከፍተው የሕዝቡን ድምፅ ሲያሰሟቸው ጩኼቱ “ተፈሪ ሌባ፤ ተፈሪ ሌባ” የሚለውን ሰምተው፥ “አይ ኢትዮጵያ ይኼን ያክል በድዬሻለሁ እንዴ?” አሉ ይባላል። በዚህ ሽኝታቸው ድሮ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ዳቦ የሚጥሉላት ለማኝ ዳቦዋን ስትጠብቅ፥ ‘ንጉሡ ወረዱ፤ ንጉሡ ወረዱ’ ሲባል ሰምታ፥ ‘ለዚህ ያበቃኸኝ አንተ ነህ!’ ብላ በቮልሷ አቅጣጫ የወረወረችው ዳቦ ብቻ ነበር ይባላል። የንጉሡ ሬሳም ከ17 ዓመታት በኋላ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ሽንት ቤት ሥር ተቆፍሮ እንደተገኘ ይታወቃል። እዚህ ላይ ልብ አድርገን ማለፍ ያለብን የፖለቲካ ቁም ነገር ለ60 ዓመታት ገደማ (የአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ እንዳለ ሆኖ) በፈላጭ ቆራጭነት ኢትዮጵያን ሲገዙ የሀገረ መንግሥታቸው ግንባታ ፕሮጀክት በአጉል ምክርም ይሁን በራሳቸው ገታራ አቋም ከሽፎ ሽኝታቸው በለማኟ ዳቦ፣ ቀብራቸው ደግሞ በአሳደጓቸው ወታደሮች ሽንት ቤት ሥር መሆኑ ነው።

    3) አብዮቱ እና የደርግ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሕዝባዊ አብዮቱ ልዩ ዕድል ፈጥሮ ነበር። አብዮቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የመጡ የአዲሱ ትዉልድ ምሁራን ድጋፍና ተሳትፎ ነበረው። እንደ አብዮቱ መሪ ወደፊት የመጣውን መንግሥቱ ኃይለማርያምም ‘ቪቫ መንግሥቱ፣ ቪቫ መንግሥቱ!’ ብለን ተቀብለን ነበር።

    የኢትዮጵያ አብዮትን አብዮት ያደረገው የጭሰኝነት ሥርዓትን ያስወገደውና የደርግ እርምጃ (ውለታው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቢሆንም) እስከዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አለው ብዬ ባምንም፥ ነገሮችን በቶሎ የሚያዩ ወጣቶች “ተፈሪ ማረኝ፤ የደርጉ ነገር አላማረኝ ” ማለት የጀመሩት ብዙዉም ሳይቆዩ ነበር። በአጭሩ ለማስቀመጥ፥ የደርግ የሥልጣን ፍቅር፣ የመኢሶንና የኢህአፓ አሳዛኝ ክፍፍል፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት የተናጠል የፖለቲካ ፕሮጀክቶች በአብዮቱ መፈንዳት የተፈጠረውን ልዩ ታሪካዊ ዕድል አምክኖታል።

    ደርግ መሃይምነትና የሥልጣን ፍቅር ስለተደባለቀበት፥ የሶሻሊስት አብዮቱን እንደሰው ማሰርና መግደል ወሰደው። በዚህ ሶቭዬት ህብረት ድረስ ሄዶ የሌኒን ሐውልት አይተው የመጡት ባለሥልጣኖቹ ስለሶሻሊዝም የተማርነው ከበሰበሰ ከቡርዧ ቤተ መፃሕፍት ሳይሆን ከምንጩ ከሌኒን ሀገር ነው እያሉ ተዘባበቱ። ካደሬዎቻቸው ድንቅ የሶሻሊስት ዕውቀታቸውን ከፍተኛነት ለማሰየት በሚመስል መንገድ የስታሊን ቀይ በትር ሥራ ላይ ይዋል አሉ። ደርግ የሱማሌ ወረራን፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ አንድነት እንዲነግድ ልዩ ሁኔታ ስለፈጠሩለት “አብዮታዊት እናት ሀገር፥ ወይም ሞት!” አለ።

    ከኤርትራ ግንባሮች እስከ ኢህአፓ እና መኢሶን (ኢጭአት/ ኦነግን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች እዚህ መሃል ናቸው) የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነትና የአብዮት ጠላቶች ሆነው ልዩ ልዩ ስሞች ተለጣፈበቸው። በአጭሩ የኢህአፓና መኢሶን መከፋፈልም ደርግን ብቻኛ የሀገር አንድነትና የአብዮት ተወካይ አደረገው። ሌሎች ዝርዝሮችን ትቼ ለኢትዮጵያ አንድነትና አብዮት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ላንሳ።

    የደርግ የመጀመሪያው ሊቀ መንበር አማን አንዶም የሚባሉ ኤርትራዊ ጀኔራል ነበሩ። የደርግ ሊቀ መንበር ተብሎ ከደርግ ውጭ የተመረጠትም ለኢትዮጵያ አንድነት ብሎ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ ሄዶ ካልተዋጋሁ ብሎ ንጉሡን ያስቸገሩ መኮንን ስለነበሩ ነዉ። በወታደሮቹ ዘንድም ተወዳጅ ስለነበረ በራሳቸው በደርግ አባሎቹ ጥያቄ መጀመሪያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከዚያም ከደርግ ውጭ የደርግ ሊቀ መንበር የሆነው የተመረጡትና በአደባባይ እስከሚታወቀውም በኢትዮጵያ አንደነት ላይም (መቼም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ልዩ ፍቅር አለን የሚሉ ብዙ ቢኖሩም፥ ፍቅራቸውን የሚለካልን መሣሪያ በሜዲካል ሳይንስ እስካሁን አልተፈጠረልንም) ምንም ዓይነት ጥያቄ ያልነበራቸውና የኤርትራን ችግር በሰላም ለመፍታት አሥመራ ድረስ ሄዶ ሕዝቡን ያወያዩ ነበሩ። ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አለኝ የሚሉ እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን ጠረጠሯቸዉ፤ በታንክ እቤታቸው ውስጥ ገደሉት። በእኔ ግምት ውጤቱ የኤርትራና የኢትዮጵያን አንድነት መግደል ነበር። በዚህም ኤርትራ የደም ምድር ሆነች። ዛሬ እንዲህ ልንሆን የፈሰሰው የሰው ደም ዋጋም ሆነ ለጠፋው ሀብትና ንብረት ሂሳብ ለፈረደበት ታሪክ መተው ይመረጣል።

    የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን ልታመጡብኝ ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁለተኛውን የደርግ ሊቀ መንበር የነበሩትን ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ከደጋፊዎቻቸው የደርግ አባላት ጋር ረሸናቸው።

    ኮሎኔል አጥናፉ አባተንም ቅይጥ ኢኮኖሚ ልታመጣብን ነው ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም በፀረ-አብዮታዊነት ረሸነዉ። በነገራችን ላይ የመጨረሻ ጭንቅ ሲመጣ መንግሥቱ ኃይለማርያም የአጥናፉን ቅይጥ ኢኮኖሚ ላይ ለመንጠላጠል ሞክሮ ነበር።

    በዛሬው የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላቸው ጀኔራል ታደሰ ብሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሞት ተፈርዶባቸው ተረሸኑ። እኔ መከታተል እስከቻልኩ ድረስ ታደሰ ብሩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ፍጹም ጥያቄ ያልነበራቸው፤ ለኢትዮጵያ ብሎ ከሰላሌ ጫካ እሰካ ሞቃዲሾ ድረስ ተወስደው የታሰሩ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን ብለው ሲመጡ ከነሱ ጋር እየተዋጉ የመጡ አርበኛ ነበሩ። ከተራ ወታደርነት እስከ ጀኔራል ማዕረግ ድረስ ሀገራቸውን ያገለገሉም ነበሩ። እግር ጥሏቸው አብዮቱ ውስጥ የገቡት መንግሥቱ ኃይለማርያም ያላርህራሄ ገደሏቸዉ። በነገራችን ላይ ከጀኔራል ታደሰ ብሩ ጋር በፀረ አንድነት ክስ የተገደለ፣ ብዙ ሰው የማያስታውሰው መለስ ተክሌ የሚባል በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪ መሪዎች አንዱ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ነበር (በጊዜዉ ከነበረዉ አቋም ተነስቼ፥ ይህ ሰው ቢቆይ ኖሮ የትኛው ድርጅት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ዶክተር አረጋዊን ደግሜ መጠየቄን አስታውሳለሁ)። ይህ ሰዉ ሌላ ተከታይ ቢያጣ ለሩብ ምዕተ ዓመት አከባቢ የምኒልክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥሮ በፈላጭ ቆራጭነት ሀገሪቷን የገዛው ለገሠ ዜናዊ ስሙን አንስቶ ትግራይ በረሃ ገብቷል። ይህም ደርግ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ያመጣብን የታሪክ ዕዳ ነው።

    በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳልነበራቸው በተሻለ የማውቃቸውን የመኢሶን መሪዎችን ላንሳ። ለሥልጣን ተብሎ በደርግና ብዙ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ዘንድ እንደ ኦሮሞ ድርጅት፥ በኦሮሞ ደግሞ እንደነፍጠኛ ድርጅት የሚታየው መኢሶን በዘመኑ በየትኛውም ሚዛን የተሻለ ትምህርት የነበራቸው መሪዎች ነበሩት፤ በስብጥራቸውም ኤርትራዊ የዘር ግንድ አላቸው ከሚባሉት ኅሩይ ተድላ እና አበራ የማነአብ እስከ ሲዳማው እሼቱ አራርሶ የነበሩበት ነው። ሽኩሪ የሚባል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብረን የነበርነው ልጅ በስተቀር ሰፊ ተሳትፎ እንደልነበራቸዉ የማዉቀዉ የሱማሌ ምሁራንን ብቻ ነበር።

    የመጀመሪያዉ የመኢሶን ሊቀ መንበር የሰሜን ሸዋ አማራ ከሚባለው የተወለዱ፥ ዶ/ር ወርቁ ፈረደ፣ ሁለተኛው ኃይሌ ፊዳ፣ ሦስተኛው የወሎ አማራ ከሚባለው የመጡ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ነበሩ። ሕብረ ብሔር ነን፤ ለሀገረ- መንግሥት ግንባታው የተሻለ ግንዛቤም እዉቀትም አለን ለሚሉ የመኢሶን ምሁራንም ደርጎች ርህራሄ አላደረጉም። በተለይ የመጀመሪያው የኦሮሞ የምሁር ትዉልድ የሚባሉት ኃይሌ ፊዳን ጨምሮ አብዱላህ ዩሱፍ፣ ዶ/ር ከድር መሀመድ፣ ዶ/ር ተረፈ ወልደፃዲቅ፣ ዶ/ር መኮንን ጆቴ የመሳሰሉት ሕበረ ብሔር በሚባለው መኢሶን ውስጥ አልቀዋል። በእኔ እምነት ብዙዎች ሊቀየሙኝ ቢችሉም፥ እንደስማቸው በኢትዮጵያ ምድር ሕብረ ብሔር የነበሩ ድርጅቶች መኢሶንና ኢህአፓ ብቻ ነበሩ። አላስፈላጊ ክርክር ዉስጥ ሳልገባ፥ እኔ እስከ ማምነው ድረስ ኢሠፓ የወታደሮች ፓርቲ ነበር። የኢህአዴግን ምንነት ለብልጽግና አበላት እተዋለሁ። የብልጽግናን ምንነት ደግሞ የታሪክ ፈተናዉን ሲያልፍ ብንነጋገርበት የተሻለ ይመስለኛል።

    ደርግ ሕበረ ብሔር ድርጅቶችን በቀላሉ አንድ በአንድ ቀርጥፎ በላቸው። ኢህአፓን ቁርስ አደረገ፤ መኢሶንን ምሳ አደረገ:: ብሔር ሆኖ ለመውጣት ገና ዳዴ የሚሉትን ወዝሊግንና ማሌሪድን እራት አደረጋቸው። ከደርግ ዱላ የተረፉት በደርግ አስተዋጽኦ ጭምር በተሸለ ሁኔታ ኃይል ሆነዉ የወጡት የብሔር ንቅናቄዎች ናቸው። ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) ወደ ኦነግ ተጠቃልሎ ገብቶ ዛሬ የምናውቀው ኦነግን ፈጠረ። የሱማሌ ድርጅቶች ኦብነግ ዓይነትን ፈጠሩ። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ቢያንስ ዋናው ክንፍ ዛሬ ሲአን (የሲዳማ አርነት ንቅናቄ) የሚለው ሆነ። አፋሮችም የአፋር ግራ ክንፍ አርዱፍ እያሉ በሕይወት ያሉ ድርጅቶች አሏቸው። በጣም የተሳካላቸው የብሔር ንቅናቄዎች በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ደርግን ለሁለት ቀብረው መንግሥታት ሆኑ።

    የደረግ ዘመንን ስናጠቃልል መረሳት የሌለባቸው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች፥ ለሥልጣን ብሎ ደረግ ባካሄዳቸው ጦርነቶች፡-

    የሀገረ-መንግሥት ግንባታውን የበለጠ አወሳስቦ መሄዱን፣
    ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በፃፉት መጽሐፍ በትክክል እንዳስቀመጡት፥ ደርግ ትቶት የሄደው በደም እምባ የታጠበች ሀገር መሆንዋን፣
    በሀገር አንድነት ስም ባካሄደው ትርጉም-የለሽ ጦርነት የባከነው የሀገር ሀብት ብቻ ሳይሆን በዓለም ትልቋ ወደብ-አልባ ሀገር ኢትዮጵያን ትቶ መሄዱን ነዉ።

    ደርግ ለ17 ዓመታት የተጫወተዉ የአጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካን እንደ ኑዛዜም፣ እንደ ቁጭትም የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ (ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርምም ሆነ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ እድፋቸውን ከታጠቡበት በጣም ይሻላል) በፃፉት መጽሐፍ ልዝጋ።

    የኢህአፓ ወጣቶችን የትግል ስሜት፣ የመኢሶን መሪዎች ዕውቀትና የእኛን የወታደሮቹን የሀገር ወዳድነት ብንጠቀምበት ኖሮ ሀገራችን እንዲህ አትሆንም ማለታቸውን እስር ቤት ሆኜ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ምክራቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይም የሚሆን ይመስለኛል። በነገራችን ላይ በታሪክ አጋጣሚ ወደ አስር ወሮች ገደማ በኢህአዴግ እስር ቤት የተኛሁበት አልጋ ኮ/ል ፍስሃ ደስታ ይተኙበት እንደነበረ ሰምቻለሁ።

    4) የኢህአዴግ ዘመን የሀገረ-መንግሥት ግንባታ

    ለአራተኛ ጊዜ የሀገራችን ፖለቲካን ማሰልጠንና የተሻለ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል ያመለጠን የኢህአዴጉ ዘመን ነው (ይህ የመለስ እና የኃይለማርያም ዘመንን ይጨምራል)። የኢህአዴግ ዘመን ሌላው ቢቀር የብሔረሰቦች ጥያቄን ለሁሉም ሕዝቦች ተቀባይነት ባለው መንገድ ይመልሳል ብሎ (እኔን ጨምሮ) የጠበቁ ብዙ ናቸው። ይህም ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የተሻለ ዕድል ይፈጠራል ተብሎም ተገምቶ ነበር።

    ገና የሽግግር መንግሥቱ ሲመሠረት፥ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንደግል ሠርጋቸው የፈለጉትን ጠርተው፣ ያልፈለጉትን በመተው የሠሩት የፖለቲካ ቲያትር ጫካ ሆነው ስደግፋቸው ከነበሩት የኢህአዴግ መሪዎች ተለየሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ብዙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጓደኞቼ በዚህ ጊዜ የተለዩዋቸዉ ይመስለኛል። ኢህአዴግ መጀመሪያ በጦርኛነት፤ ቀጥሎ ደግሞ በዘመኑ ቋንቋ የሽብርተኝነት ታርጋ እየለጠፈ ለ27 ዓመታት ሕዝብና ሀገርን አመሰ። ዝርዝር ነገሮች ውስጥ ሳልገባ፥ በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች፤ በሲዳማ፣ በሀዲያ፤ በወላይታ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ ቁጥራቸውን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንኳ የማያውቁት ሕይወት ጠፋ። የአፍሪካ መዲና የምትባለው አዲስ አበባ/ፊንፊኔም ሆነች የኢህአፓን ጠበል በቀመሱ ብአዴኖች የሚመራው የአማራ ክልልም ውሎ አድሮ ከኢህአዴግ ዱላ አልተረፉም።

    በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም (ነገርየው መሬት ላይ ሲፈተሽ፥ የአብዮታዊነትም የዴሞክራሲያዊነትም ባህርይ አልነበረውም) የተተበተበው የሞግዚት አስተዳደር እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት ሊሆን አልቻለም። የሕዝቦችን እራስን በራስ ማስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት ያልነበረው፥ ጆርጅ ኦርዌል የእንስሳት እርሻ (George Orwell, “Animal Farm”) በሚለዉ መጽሐፉ ላይ፥ ሁሉም እንስሶች እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንስሶች የበለጠ እኩል ናቸው “All animals are equal, but some are more equal than others” ከሚለው ያለፈ የፖለቲካ ፋይዳ አልነበረውም። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተብዬዎቹም ከ97ቱ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ይቅርና ቅርጫ እንኳ ሊ ሆኑ አልቻሉም። ዉጤቱም ዴሞክራሲያዊ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል መጨናገፉ ብቻም ሳይሆን ለ27 ዓመታት ውድ የሕይወት ዋጋ ጭምር ሲያስከፍለን ኖሯል። በዚህም ምክንያት የታሪክ ጣጣችንን አስተካክለን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የመፍጠር ተስፋችን ሕልም ሆኖ ቀርቷል።

    5) በማምለጥ ላይ ያለ አዲስ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አሁን እየገጠመን ያለውን የታሪክ ፈተናን ለማለፍ፥ ጨክነን በቁርጠኝኘት ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መግባት ወይም ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ-መንግሥት የምታበቃበት የሚጨምር ቀውስ ውስጥ መግባት ይመስለኛል። እዚህ ላይ የሌሎች ሀገሮችን ፖለቲካ በድኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን ብቻ እንኳን በመቀኛት ብጀምር፥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በቁርጠኝነት የሠሩት ተሳክቶላቸዋል። ያንን ያልቻሉት ወይ ፈርሰዋል ወይም አሁንም በቀውስ ውስጥ እየዳከሩ ነዉ። ቅኝታችንን በላቲን አሜሪካ ብንጀምር፥ ቀዉስ ገጥሟቸዉ አነ አርጀንቲና፣ ቺሌ፣ ፔሩ፣ ኒካራጓ፣ ኮሎምቢያ የመሰሰሉ ሀገሮች በተለያየ ደረጃ ፖለቲካቸውን ያስተካከሉ ሀገሮች ናቸው። ከ60 ዓመታት በላይ ለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ሳትበገር በአሜሪካ አፍንጫ ሥር የኖረችው አስደናቂዋ ሶሻሊስት ኩባና በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አሁን በሁለት ፕሬዝዳንቶች የምትገዛዋ ሶሻሊስት ቬኔዙዌላም በዚሁ ክፍለ ዓለም ይገኛሉ። በአውሮፓ ፖርቹጋል፣ ስፓኝ፣ ግሪክ፣ ፖለቲካቸዉን ማስተካከል ችለዋል። ዩጎዚላቪያ ውድ ዋጋ ብትከፍልም ከመፍረስ አልደነችም። ሶቭዬት ህበረትና (ግማሽ አውሮፓ ነች) ቼኮዝላቫኪያ በሰላማዊ መንገድ ፈርሰዋል። በኤዥያ፥ ኔፓል የፓለቲካ ችግርዋን በብሔራዊ መግባባት ስትፈታ፥ፓኪስታን፣ ቬየትናም፣ ካምቦዲያና ላኦስ ደግሞ ችግሮቻቸውን በጦርነት ፈተዋል። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን አሁንም እየቀወሱ ነው። ወደ አፍሪካችን ስንመጣ፥ ደቡብ አፍሪካና ጋና ከመሳሰሉት በስተቀር አብዘኛዎቹ በይስሙላ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ አምባገነን መንግሥታት ሲሆኑ፥ የአፍሪካ ሕብረትም የዲክታተሮች ማኅበር (trade union of dictators) ከመሆን አላለፈም (በኢህአዴግ ጊዜ የተከሰስኩበት አንዱ ወንጀሌ የአፍሪካ መሪዎችን ተሰደብክ የሚል ነበር)። ሱማሊያና ሊቢያ ፈረንጆች የወደቁ መንግሥታት (failed states) የሚሏቸው ሲሆኑ፤ ሩዋንዳ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ሌላ ቦንብ የምትጠብቅ ይመስለኛል።

    በዚህ የአፍሪካ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ውስጥ አንዱ የሚገርመኝ ላለፉት 60 ዓመታት ፖለቲካቸውን ማስተካከል አቅቷቸው በቀውስ ሲናጡ የኖሩ ሁለት ሀገሮች፥ በተፈጥሮ ፀጋ እጅግ ሀብታሟ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑቢሊክና የሦስት ሺህ ዓመታት ዕድሜ አለኝ የምትለዋ ድሃዋ ኢትዮጵያ መሆናቸው ነው።  ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ይህንኑ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቆቅልሾችን የተከታተለ፣ ያጠና፣ ያስተማረና ብዙ ጽሑፎችን የፃፈበት ጆን ማርካከስ (John Markakis) የሚባል ፈረንጅ፥ የታሪክና ፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሴር “Ethiopia: The Last Two Frontiers” (የኢትዮጵያ፥ የመጨረሻዎቹ ሁለት ድንበሮች) ብሎ ፅፏል። ምሳ ጋብዞኝ መፅሐፉን ለዶ/ር ዓቢይ ስጥልኝ ብሎኝ፥ ዶ/ር ዓቢይ ያንብበው አያንብበው ባላውቅም፥ እሳቸውን ማግኘት ለሚችል ለኦፒድኦ ባለሥልጣን ልኬላቸው እንደነበርም አሰታዉሰለሁ። መፅሐፉ በአጭሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የንጉሦቹ ሞዴል (the Imperial model) ፣ የደርግ የሶሻሊስት ሞዴልና የኢህአዴጉ ፌዴራሊስት ሞዴል በሙሉ ከሽፈዋል ይላል። የከሸፉበትም ዋናዉ ምክንያት የባለጊዜ ገዥዎችን ሥልጣን ለማሳካት የተገፋበት መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እኩልነት ያላጎናፀፈና የልማት ጥማታቸውንም ያላረካ በመሆኑ ነው ይላል።

    ይህ የፈረንጅ ምሁር እንዳለው፥ ፖለቲካችንን ማሰልጠን ባለመቻላችን ሚሊየኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሚሊዮኖች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሚሊዮኖችም ተሰደዋል። እኔም ከላይ ባነሳሁት ከዚሁ ምሑር ዕይታ ተነስቼ ሀገራችን ስለገባችበት የፖለቲካ ቅርቃርና በብሔራዊ መግባባት አንፃር ከቅርቃሩ ለማውጣት በሌኒን ቋንቋ ምን መደረግ አለበት (What is to be done?) የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ የሀገራችን ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ ልመልስ።

    1. መሠረታዊ ችግራችን በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎቻችን ሀገርን የመምራት ሕልማቸው፤ ሥልጣንን ጨምድዶ ከመቆየት ሕልማቸው ጋር ሁሌ ስለሚጋጭባቸው ነው። ለሕዝብ አለን ከሚሉት ፍቅር የሥልጣን ፍቅራቸው ስለሚበልጥባቸው ነው። ለዚህ ነው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የሚወደንና (ሕዝቡ ምን ያከል እንደሚወደቸዉ እንዴት እነዳወቁ ባናዉቅም) የምንወደው ሕዝባችን ሲሉ ኖረው ለ60 ዓመታት ገደማ የገዟትን ኢትዮጵያ ለ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ሳያበቁ ከዓለም ሀገሮች ጭራ ደረጃ ትተዋት የሄዱት። የሕዝብ ፍቅራቸውንም ደረጃ በረሃብ በመቶ ሺህዎች ያለቀው የወሎ ሕዝብ ይመሰክራል። ይህን የመሳሰሉ የመሪዎቻችን ባዶ የሕዝብና የሀገር ፍቅር፥ የንጉሡ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት የመለስ ዜናዊ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገቡ ዜጎችን እፈጠራለሁ ወ.ዘ.ተ መሸፈን አይችልም። ለዚህ አሁን ያሉ መሪዎቻችንም ሆኑ ተስፈኛ መሪዎች ይህንን የታሪክ እውነታ በውል እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ።
    2. የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የተቀሩት ልሂቃን በተለያየ ደረጃ የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን ይዘው መጓዛቸው ነው። ከመኢሶንና ኢህአፓ ዘመን እስከዛሬ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና መሪዎቻቸው ይህንን እውነታ በውል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የሕልሟን ጉዳይ በፈንጆቹ አባባል ከዜሮ ድምር ፖለቲካ (zero-sum game politics) የመውጣቱን ጉዳይና የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸዉን በገደብ የማድረጉን ነገር በጥብቅ እንዲያስቡበት እመክራለሁ። ዋና ጉዳያችን ሥልጣን ሆኖ ከፊንፊኔ እስከ መቀሌ ባንዳ፣ ባንዳ እየተባባሉ መካሰሱ ሕዝባችንን ከማደናገር በላይ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የለውም። ዛሬ በአሜሪካና በአውሮፓ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ በአንድ እጅ እስክንድር ነጋ ይፈታ፣ በሌላ እጅ ጃዋር ሽብርተኛ ነው የሚሉት መፈክር ዓይነቶቹ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታችንም ሆነ ለብሔራዊ መግባባት ሥራችን ብዙ የሚጠቅሙ አይመስሉኝም። በእኔ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ስላስቸገረኝ ነበር በ2008 በፃፍኩት መፅሐፍ ላይ ለቡዳ ፖለቲካችን መላ እንፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚጋጩ ሕልሞች ሊታረቁ ወይስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ በሚል ግልፅ ጥያቄ የደመደምኩኝ። ለእኔ መፍትኼው ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ፈጠራ የሚሆን አዲስ ማኅበራዊ ውል (new social contract) ከመፈራረም ውጭ የተሻለ የማጂክ ፎርሙላ ያለን አይመስለኝም። ይህንን እውነታ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ያሉ የብልጽግና ወንድሞቻችንም ሆኑ ከአዲስ አበባ/ፍንፍኔም እስከ አውሮፓና አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ግፋ በለው የሚሉ ሁሉ እንዲረዱልኝ አደራ እላለሁ። በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ቀውስ በሁሉም በኩል ላለቁትም የተሻለ የሐዘን መግለጫ የሚሆነውና ዕንባቸውን የሚያብሰው የችግሮቻችን ምንጭ አዉቀን ዘለቂ መፍትኼ ስንፈልግ ይመስለኛል።
    1. ከላይ ካነሳኋቸው ሁለት ነጥቦች ጋር ተያይዞ ሺህ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እየተባለ በሕዝብ ላይ የሚሠራዉ የፖለቲካ ትያትር መቆም አለበት።
      የንጉሡ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የደርግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የኢህአዴግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ ሲያንሱ በዴሞክራሲ ስም የተቀለዱ  ቀልዶች፣ ሲበዙ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተሠሩና ታሪክ ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ነበሩ። በሰለጠነው ዓለም የሕዝብን ድምፅ ከመስረቅ በላይ ወንጀል የለም። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን አስታውሼ ልለፈው። በ“ኢህአዴግ-1” ዘመን አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉትና በዝረራ ያሸንፋል” ብሎ ሲያስቸግረኝ፤ አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዞች አሉት፤ አንደኛው ምርጫ ቦርድ ነው። ሁለተኛው ጠመንጃችሁ ነው። ሁለቱን ምርኩዞቻችሁን አስቀምጣችሁ ተቃዋሚዎችን ካሸነፋችሁ፥ እኔ በግሌ እናንተ የምትሉትን 20 ና 30 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለሃምሳ ዓመታት እንድትገዙን እፈርምልሀለሁ” እንዳልኩት አሰታዉሰለሁ። በ“ኢህአዴግ-2” ጊዜ ደግሞ ዶ/ር ዓቢይ በጠሩት ድንገተኛ ስብሰባ ላይ ገለልተኛ የሆነው ጠቋሚ ኮሚቴ ስምንት ሰዎች አጣርቶ ስላቀረበ አራት ሰዎች መመረጥ ስላለባቸው በተጠቆሙት ሰዎች ላይ አስተያየት ስጡ አሉን። ሌሎች ስብሰባው ላይ የተገኙ የየድርጅት መሪዎች ያሉትን ብለዋል፤ እኔ ጨዋታው ስላላማረኝ፥ “አብዛኛዎቹን ዕጩዎች ብዙዎቻችን አናዉቃቸውምና ከየት እንደመጡ እንኳ ለማወቅ የ24 ሰዓት ጊዜ ስጡኝ” ብዬ አጥብቄ ጠየኩኝ። ዶ/ር አቢይ ‘አይቻልም’ አሉ። ነገ የምናገረው እንዳይጠፋኝና ለታሪክም ቢሆን ተአቅቦ (reservation) መዝግቡልኝ ማለቴ ትዝ ይለኛል። ምስክሮችም አሉኝ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች የምርጫ ጊዜውን ሰሌዳ ለማስተላለፍ በጠሩት የምክክር ስብሰባ ላይ እንደተናገርኩኝ፥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት (divine intervention) ነው እንዳልኩኝ ምርጫው ባይተላለፍ ኖሮ የአዲሱ ምርጫ ቦርድ አካሄድ ሌላ ከበድ ቀውስ ሊያስከትል ይችል እንደነበረ ዛሬ ላይ ሆኜ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይህንኑ ደግም ብዙ ጊዜ በታጋይነቷ ለምናውቃት ክብርት ብርቱካንም ጭምር መናገሬን አስታውሳለሁ።

    ስለሆነም የሚመጣውን ምርጫ አዲስቷን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ እንድትወለድበት ካላደረግን፥ የንጉሥ የማክያቬሊ ምክር፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የጆሴፍ ስታሊን ቀይ በትር፣ የመለስ ዜናዊ፣ የሊቀ መንበር ማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውሰት፣ ኢትዮጵያን ለመለወጥ የታሪክ ፈተናውን ለማለፍ እንዳላስቻላቸዉ፥ የዶ/ር ዓቢይም የመደመር የፖለቲካ ቀመር አዛውንቱ የፈረንጅ ምሁር የሚለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጨረሻ ሁለት ድንበሮችን የሚያሻግረን አይመስለኝም። እሱን ካልተሻገርን ደግሞ ሁሌም እንደምለው ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ የምትፈጠር አይመሰልኝም።

    ከማጠቃለሌ በፊት የብሔረታዊ መግባባቱ የፖለቲካ ጥረታችን ይሳካ ዘንድ መፍትሄ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮች ላስቀምጥ፦

    1. ያለ ሀገራዊ ስምምነት በዋናነት በአንድ ቡድን ሕልምና ፍላጎት (በተለይ የአንድ ቡድን ፍኖተ-ካርታ /road map/) የመመረቱ ጉዳይ ለዉጡን አጣብቂኝ ዉስጥ ማስገበቱን የማወቅ ጉዳይ፤
    2. ለውጡን ለማምጣት በዋናነት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ኃይሎች (ለምሳሌ እንደ ኦሮሞ ቄሮ ዓይነቶቹ) ወደ ዳር የመገፋታቸው ጉደይ፤
    3. ለውጡን እየመራ ያለው ከራሱ ከኢህአዴግ የወጣ ቡድን ቢሆንም፥ በለውጡ ምንነት፣ ፍጥነት፣ ስፋትና ጥልቀት ላይ የተለያዩ የኢህአዴግ ክንፎች ስምምነት ማጣታቸውና በዚህም ምክንያት እያመጣ ያለው አደገኛ ሁኔታ፤
    4. በሚጋጩ ሕልሞቻችን ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት መፍትሄ ያላገኘንለት የመከፋፈል ፖለቲካችን (political polarization) ጉዳይ፤
    5. ዴሞክራሲያዊ ለውጡ ለአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የፓለቲካ ኃይሎች ተቀባይነት ያለዉ፣ ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የጋራ ፍኖተ-ካርታ (roadmap) የመቀየስ አስፈላጊነት ጉዳይና፤ የተቀየሰዉን በጋራ ሥራ ላይ የማዋል ጉደይ፤
    6. ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማለት በእርግጥም በሕዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ጨዋታ መሆኑን የመረዳት ጉዳይ፤
    7. ሀገራችን እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፈድራል ሥርዓት ያስልጋታል ስንል፥ ከሕልሞቻችን በሻገር በሕዝቦቻችን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፖሊቲካ ሥርዓት መሆኑን የማረጋገጥ ጉዳይ፤
    8. ብሔራዊ መግባባቱ በተሻለ መንገድ የሚሳካው፥ በደቡብ አፍሪካ እና ኮሎምቢያ በመሰሰሉት ሀገሮች እንዳየነው የፖለቲካ እስረኞችንና የጫካ አማፅያንን መጨመርን የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    9. የተሳካ ብሔራዊ እርቅን ለመምጣት ከሥልጣን በሻገር የምር የፖለቲካ ቁረጠኝነት (political will) የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    10. ስለኢትዮጵያ አንድነት ያለን ግንዘቤ ከፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ እይታ የሰፋና ለሀገሪቷ ያለን ፍቅርም ገደብ የማድረጉ ጉደይ ናቸዉ።

    በመደምደሚያዬም፥ እዚህ ያደረሰንን የሀገራችንን ፖለቲካ ጉዞ ታሪክ ወደኋላ እያየሁ፥ የወደፊቱን የሀገራችንን ዕጣ ፈንታንም እያማተርኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለሁላችንም የታሪክ የግርጌ ማስታወሻ ልተዉ።

    በቅርብ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን የሚያፈርሷት እኛን ቀድሞ ሲያፈርሱ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይፈቀድላቸውም’ ሲሉ አዳምጫለሁ። ሀገርን ለመፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች መጀመሪያኑ ፈቃድ ይጠይቃሉ፤ አይጠይቁም የሚለዉን ክርክር ውስጥ ሳልገባ፥ በጨዋ ቋንቋ ንግግራቸውን አልወደድኩላቸውም። ንግግራቸውንም ተከትሎ የኢሳት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ተንታኞች የሚታወቁ የአዛውንት ምሁርን በመጥቀስ (ይህኑን ምሁር መንግሥቱ ሀይለማርያምም ያዉቃል ብለን ስለተሠሩ የንጉሡ ባለስልጣኖች ምክር ጠይቀነዉ፥ ጠመንጃዉ በእናንተ እጅ ነዉ፤ የምን ምክር ትጠይቁናላችሁ ብሎኛል ማለቱን አንብቤአለሁ) ዶ/ር ዓቢይ ጥሩ ይዘዋል፤ ሕጉንም ሰይፉንም እየተጠቀሙ ነው ያሉት የበለጠ ሥጋት ፈጥሮብኛል። እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁላችንም ደጋግመን ማሰብ ያለብን ጨዋታው ከተበላሸ አብዛኛው ዓለምን በሰዓታት ውስጥ ወደ አመድነት የሚለወጥ ወይም ሕይወት-አልባ ሊያደርግ የሚችል የኒዩክሊየርር መሣርያ የታጠቀ፣ ነፍሷን ይማርና የሶቭዬት ህብረት ሠራዊት ዓይኑ እያየ ሀገራቸው መበቷን ነው። የሀገራችንን ፖለቲካ በጋራ አስተካክለን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ።

    ዋቢ መፃሕፍት:

    1. Bahiru Zewde (1991) A History of Modern Ethiopia, 1885 -1991.
    2. Gebru Tareke (1996) Ethiopia: Power and Protest, Peasant Revolts in the Twentieth Century.
    3. John Markakis, (2011) Ethiopia: The Last Two Frontiers.
    4. Merera Gudina, (2002) Ethiopia: Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy, 1960-2000.
    5. Teshale Tibebu, (1995), The Making of Modern Ethiopia, 1896-1974.

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forumsላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ… መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)

    Anonymous
    Inactive

    በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ ― ኢሕአፓ

    በጀግኖች ሰማዕታት ብርቱ ተጋድሎና ክቡር መስዋዕትነት የተገነባዉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢ.ሕ.አ.ፓ)፥ በታሕሳስ 4 እና 5 ቀን 2012 ዓ.ም. 9ኛ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ አድርጎ አመራሮቹን መምረጡ ይታወቃል። የኢሕአፓ ቋሚ ኮሚቴ በሀገራዊና ድርጅታዊ አጅንዳዎቸ ላይ ከነሐሴ 2 እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ፣ በኢትዮጵያ ስላለው የሰላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ክንዉን ሂደቶች በስፋት መክሯል። ፓርቲው የ2012 ዓ.ም. የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን ግምግሞ የ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የፓርቲዉ ዕቅድ ላይ ከፍተኛ ዉይይት አድርጓል። በተጨማሪም፥ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የሰላማዊ ትግል መርሆዎችና ስልቶችን ተግባራዊ በሚያደርግ፣ የትግል ቁርጠኝነታቸውን ጠብቀው ለማይቀረው ድል እንዲሰለፉና ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ካንዣበበባቸው አደጋ እንዲከላከሉ ጥሪውን አቅርቧል።

    የኢሕአፓ ቋሚ ኮሚቴም የሚከተሉትን ዉሳኔዎችና የአቋም መግለጫዎችን በሰፊው ከተወያየ በኋላ አዉጥቷል።

    1ኛ. መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና በቅርቡ የጀመረውን ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ እውን መሆን የሚያደርገዉን ጥረት እያደነቅን፥ ይህን መሰሉ ሕግን የማስከበር ጉዳይ አስቀድሞ ተከናውኖ ቢሆን ኖሮ ዜጎች በጠራራ ጸሐይ ከመገደልና ሃብት ንብረታቸውም ከመውደም መታደግ ይቻል እንደነበር ኢሕአፓ እምነቱን እየገለጸ፥ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግጭት፣ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ለንጹሀን ዜጎች ሞት፣ ስደት፣ እንግልትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ፣ ንብረት ያወደሙና የዘረፉ ወንጀለኞችን ለሕግ በማቅረብ ተጠያቂ የማድረገረ ሂደቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ እና ተጠርጣሪዎችና ከሁከቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁሉ አፋጣኝ የፍርድ ሂደት እንዲያገኙ ኢሕአፓ መንግሥትን ይጠይቃል።

    2ኛ. የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በታቀደለት ጊዜ በመጠናቀቁ ኢሕአፓ የተሰማውን ልባዊ ደስታ እየገለጸ፥ መንግሥት በጣና ሐይቅ ዙሪያ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ችግርና በወንዞቻችን፣ ሐይቆቻችንና በተፈጥሮ ሀብቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ብሔራዊ አደጋ ለማስቀረት ሕዝባዊ ንቅናቄ አስፈላጊ በመሆኑ፥ የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤንና ጥበቃን ለማጎልበት በንቃት እንዲሳትፉ ጥሪውን ያስተላልፋል።

    3ኛ. በደቡብ ክልል እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶችና ሰሞኑን በወላይታ ዞን የተፈጸመው ሁከትና ብጥብጥ ወደከፋ ሁኔታ ከመቀየሩ በፊት መንግሥት የ’ክልል እንሁን’ ጥያቄዎችና የአከላልለ ጉዳይን በተመለከተም በተጠናና በማያዳግም ሁኔታ እንዲፈታው እየጠየቅን፥ ችግሮችን በክልሉ በሚኖሩት ሕዝቦች ፍላጎትና ውይይት መሠረት አድርጎ መፍታት አለበት። የአስተዳደር በደል ጥያቄዎቹንና አለመረጋጋቱን ተገን አድርገዉ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ተከትሎ የሚጠፋዉ የሰዉ ሕይወትና የሀገር ሀብት ውድመት በአስቸኳይ እንዲያቆምና ችግሮችም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢሕአፓ በአንክሮ ይጠይቃል። በግጭቱ ሰበብ ለሞቱት ወገኖች የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን፥ በየትኛውም የፌዴራሉ ክልሎች ውስጥ ለዘመናት ተዋዶና ተከባብሮ የሚኖረውን ሕዝብ እርስ በርስ ለማጋጨትና ሀገራችንን ወደ አልተፈለገ የእርስ በርስ ግጭት ለመክተት የሚሯሯጡ ቡድኖችና ኃይሎችን ለፍርድ ለማቅረብ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ርምጃ ኢሕአፓ ይደግፋል።

    4ኛ. የኮቪድ-19 ወረርሽኝኝ በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ፣ በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ጫና በመላው ሕዝባችን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሆኑና የዕለት-ተዕለት የምግብና ሸቀጣ ሸቀጦችም ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት እየተከሰተ ስለሆነ፥ የዋጋ ንረቱም የሀገራዊ ምርት እጥረት ሳይሆን የአቅርቦት ውሱንነት ያስከተለው በመሆኑ፣ መንግሥት በአፋጣኝ ገበያውን በመቆጣጠርና ሕዝቡን ካልተገባ የኢኮኖሚ ምዝበራ እንዲታደገው እንጠይቃለን። ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ያለዉ ከፍተኛ የሕዝብ ትራንስፖርት እጥረት ረጃጅም ሰልፎችን እየፈጠረ ሕብረተሰቡን ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዲሆን እያደረገዉ ስለሆነ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግለት አሕአፓ በአጽንኦት ያሳስባል።

    5ኛ. በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በሰላምና መረጋጋት እጦት ምክንያት አካላቸው ለጎደለባቸው፣ ንብረታቸው ለወደመባቸው፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች መንግሥት ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው መመለስ የሚችሉበትን ካሳ እንዲከፍልና ዜጎች በብሔራቸዉና በማንነታቸዉ እየተለዩ የሚደርስባቸዉን ጥቃት እንዲከላከል ኢሕአፓ ጥሪዉን ያቀርባል።

    6ኛ. የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ስብሰባዎችና ብዙሃን መገናኛ ድርጅቶች ላይ የሚያደርጉት ከፋፋይና በተወሰኑ ብሄሮች ላይ የሚያነጣጥር ንግግር በኢትዮጵያዉያን ዜጎች መካከል ለብዙ ዘመናት አብሮ የኖረዉን የመቻቻልና የመከባበር እሴት የሚሸረሽርና ለጥላቻ፣ ለግጭትና እርስ በርስ በጥርጣሬ ዓይን ለመተያየት በር የሚከፍት አደገኛ ተግባር ስለሆነ፥ ኢሕአፓ እንደዚህ ዓይነት ንግግሮች እንዲታረሙ በጥብቅ ያሳስባል፤ ለአብነትም፥ ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ብልጽግናን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር በኢትዮጵያዉያን መካከል የነበረዉን የእርስ በርስ ግንኙነትና ዉሁድ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽር፣ አደገኛና ዘረኛ ሀሳብ መሆኑ ግልጽ ነዉ፤ ይህ ሀሳብ እዉን የብልጽግና ፓርቲ ሀሳብ ከሆነ የተረኝነት ጉዳይ እንጂ የለዉጥ ጉዳይ ሊሆን ስለማይችል ሀሳቡ የግለሰብ ወይም የፓርቲዉ ሀሳብ መሆን አለመሆኑን መንግሥት ግልጽ እንዲያደረግ እንጠይቃለን።

    7ኛ. በፌደራል መንግሥትና አምባገነኑ ህወሓት በሚመራዉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካካል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ የመጣዉ ዉዝግብና አለመግባባት በንጹሃን የአማርኛና የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ኑባሬ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑ እሙን ነዉ። ስለዚህ መንግሥት ለንጹሃን ዜጎች ሲል የሕግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ጥብቅ እርምጃ በመዉሰድ ስርዓት አልበኞችንና አምባገነኖችን ለሕግ እንዲያቀርብ እየጠየቅን፥ ያለምርጫ ቦርድ ፈቃድና ዕዉቅና ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳያካትት ህወሓቶች በተናጠል የፊታችን ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊያደርጉት ያቀዱትን ምርጫም ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆም ኢሕአፓ በአጽንኦት ይጠይቀል።

    8ኛ. ፓርቲያችን ኢሕአፓ ባለፉት 6 (ስድስት) ወራት ውስጥ ያከናወናቸዉን ዋና ዋና ተግባራት በጥልቀት የገመገመ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ የዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ደማቅና ጉልህ ስፍራ ያለውና ዘመን ተሻጋሪ የሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የኢትዮጵያን ሕዝብ ታግሎ-በማታገል መርሆውና አይበገሬነቱ ጸንቶ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን ለመላው አባላቱና ደጋፊዎቹ እየገለጸ፥ ከርዕዮት-ዓለማችን ከማኅበራዊ ዲሞክራሲ (social democracy) ጋር ተመሳሳይነትና ተቀራራቢነት ያላቸውንና በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና እኩልነት ላይ ጽኑ እምነት ያላቸውን ፓርቲዎችና የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ የትብብርና የአጋርነት ጥሪ ያቀርብላችኋል።

    ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!

    ኢ.ሕ.አ.ፓ ለተሻለ ነገ!!

    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

    Anonymous
    Inactive

    ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በ3 ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ገርጂ የመኖሪያ መንደር ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ

    አዲስ አበባ (ኢብኮ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሶስት ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ዘመናዊ መንደር (ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት/ Gerji Village Project) ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተቋራጮች ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ፈፅሟል። ኮርፖሬሽኑ ስምምነቱም ያደረገው ከኮሪያ፣ ከህንድ እና ከኢትዮጵያዊያን የህንጻ ተቋራጮች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ዘግቧል።

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክትን ይፋ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስተሩ የካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቦርድ ኃላፊ ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ናቸው።

    በስምምነቱ መሠረት ገርጂ የመኖሪያ መንደር ውስጥ በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ 510 መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ። የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ባለ 10 ወለል የሚኖራቸው 16 ህንጻዎች መሆናቸው ተገልጿል።

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ በከተማዋ የሚታዩ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን በተወሰነ መልኩ የሚያቃልል መሆኑን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ገልጸዋል።

    ግንባታው በዘመናዊ መንገድ የሚገነባ በመሆኑ የግንባታ ወጪውንም ሆነ ጊዜውን የሚያቀላጥፍ መሆኑ ተመክቷል፤ አንድ የህንጻ ወለልን በአምስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ የሚያጠናቅቅ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።

    አዲአ አበባ ውስጥ ሲ.ኤም.ሲ ከሚገኘው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመኖሪያ መንደር ልምድ ተወስዶ፥ በሦስት ሔክታር ላይ የሚገነባው የገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ ዘመናዊነትን የተላበሰ የመኖሪያ መንደር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የመኖሪያ መንደሩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ይውሏል ተብሏል።

    የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመት በኋላ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ወደ ቤቶች ግንባታ ራሱን በመመለስ፣ በተለያዩ ስምንት የግንባታ ቦታዎች ቤቶችን እየገነባ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ገቢውን እያሳደገ ሰፊ የቤት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ይሠራልም ብለዋል አቶ ረሻድ።

    ምንጭ፦ ኢብኮ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሌሎች ዜናዎች

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በቀጥታ ለሚያሠራጩ የሚዲያ ተቋማት ሊሸጥ መሆኑ ተገለጸ
    የሀገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት በ2013 በጀት ዓመት በሚያከናውኗቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሁለት ውይይት አካሂደዋል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የኢትዮጵያን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በቴሌቭዥን ማስተላለፍ ለሚችሉ የሚዲያ ተቋማት ሊሸጥ መሆኑ ታውቋል።

    የፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒው በቀጣይ የሚካሄደውን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በቀጥታ የቴሌቭዥን ሥርጭት የማስተላለፍ ፈቃድ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የሚዲያ ተቋማት ለመሸጥ ጨረታ ሊያወጣ መሆኑ ተሰምቷል።

    ከዚህ በተጨማሪ ሊግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን ስም ለመሸጥ በሚቀጥለው ሳምንት ጨረታ እንደሚያወጣ ለማወቅ ተችሏል።

    የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ከቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት እና ከውድድር ስያሜ ሽያጭ የሚያገኘው ገቢ የካምፓኒውን እና የተወዳደዳሪ ክለቦችን የገንዘብ (financial) አቅም ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።

    ከስፖርቱ ዜና ሳንወጣ፥ የሀገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት በ2013 በጀት ዓመት በሚያከናውኗቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ውይይት ተጠናቋል። በውይይቱ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች ዋነኛው በጥናት ተለይቶ የወጣውን የስፖርት ማሻሻያ መርሀ ግብር (Sport Reform Program) ተግባራዊ በማድረግ ሕዝባዊ አደረጃጀቱን የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል።

    የሀገራችን ስፖርት ፖሊሲ ስፖርቱን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት በዋናነት ለሕዝባዊ የስፖርት አደረጃጀቶች ይሰጣል። ፖሊሲው ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለው እና ጠንካራ አደረጃጀት ሊፈጠር እንደሚገባ ጨምሮ ያስቀምጣል።

    በሀገር አቀፍ ደረጃ 20 ፌዴሬሽኖች ፣ ዘጠኝ ማኀበራት (associations) እንዲሁም ሁለት ኮሚቴዎች በአጠቃላይ 31 የስፖርት ማኀበራት ከኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን እውቅና ወስደው የተመዘገቡበትን የስፖርት ዓይነት ለማሳደግ እና ለማስፋፋት እንዲሁም ውጤት ለማስመዝገብ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ የስፖርት ማኀበራት በ2013 በጀት ዓመት በሚያከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ነሐሴ 12 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕቅዳቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።

    በቀረበው ዕቅድም የስፖርት ማኀበራቱ እራሳቸውን በሰው ኃይል እና በገንዘብ (personnel and finance) ከማጠናከር፣ አደረጃጀታቸውን ከማስፋፋትና የተደራጁትንም በመደገፍ ረገድ ሊሠሯቸው ያሰቧቸውን ተግባራት አቅርበዋል። እንዲሁም የታዳጊ ወጣቶች ስልጠናን ከማስፋፋት እና ተተኪዎችን ከማፍራት፣ የባለሙያዎችን (ዳኞች እና አሰልጣኞች) አቅም ከመገንባት አንፃር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ አብራርተዋል።

    በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን እና ወደ በ2021 ይካሄዳል ተብሎ በሚታሰበው ቶክዮ ኦሎምፒክ እና ፓራሊምፒክ ለመሳተፍ እና ውጤት ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት መጀመራቸውን ገልፀዋል። በሌላ በኩል የስፖርት ማኀበራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል።

    በቀረበው ዕቅደም ወረረሽኙ በስፖርቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተገለፀ ሲሆን፥ በተለይ ስፖርቱን የሕይወታቸው መሠረት እና መተዳደሪያቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ የስፖርት ቤተሰቦች ክፉኛ መጎዳታቸውን አንስተዋል። በተጨማሪም ውድድርና ስልጠናዎች በመቆማቸው ከውድድር ገቢ፣ ከስፖንሰርሺፕ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙ ገቢዎች በመቆማቸው መቸገራቸውን እና መንግሥትም ችግሩን ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈልግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

    የቀረበውን ዕቅድ ያዳመጡት የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር የስፖርት ማኀበራት በጥናት ተለይቶ የተዘጋጀውን የስፖርት ማሻሻያ መርሀ ግብር (Sport Reform Program) ጋር ራሳቸውን በማስተዋወቅ እና የእቅዳቸው አካል በማድረግ ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

    ሕዝባዊ አደራጀቱን የማጠናከር ሥራ በ2013 በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ሥራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፥ በተለይ አመራሩ ወደ ማኀበሩ ሲመጣ ስፖርቱን ሊቀይርና ሊያሻግር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሕዝባዊ አደረጃጀቱ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር በመዘርጋት፣ ደንብ እና መመሪያን መሠረት በማድረግ በነፃነት የሚሠራበት ተቋም መገንባት እንደሚያስፈልግ ለዚህም በቅንጅትና በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።

    የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩቸው በመድረኩ የስፖርት ማኀበራት በ2012 ዓ.ም ያከናወኗቸውን ተግባራት፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች እና ጥንካሬና ድክመታቸውን የተገንዘብንበት ነበር ብለዋል። ያቀረቡት ዕቅድም ኮሚሽኑ ካስቀመጠላቸው አቅጣጫ እና ከራሳቸውን ነባራዊ ቁመና ጋር በማጣጣም የስፖርት ልማትን፣ ውድድርን፣ ስልጠናን እና አደረጃጀትን መሠረት ያደረገ ዕቅዱም በበጀት የተደገፈ እንደሆነ ጠቁመዋል። በመሆኑም የታቀደው ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን እና ወደ ውጤት ለመቀየር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ትልቅ ስጋት ቢሆንም፥ ለዕቅዱ ተግባራዊነት ኮሚሽኑ በሰው ኃይል እና በገንዘብ አቅሙ በፈቀደ መጠን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ዱቤ ጅሎ አስታውቀዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ሰነድ በማዘጋጀት ለመንግሥት ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

    ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን

    የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

    Anonymous
    Inactive

    ኢሰመኮ (ጋዜጣዊ መግለጫ) ― ኦሮሚያ፡ የሞት እና አካል ጉዳት አደጋ በተቃውሞ ሰልፎች 

    አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ምክንያት የሚከሰተው የሰዎች ሕይወት መጥፋት በእጅጉ እንደሚያሳስበው እየገለጸ፥ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪውን ያቀርባል።

    በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በተለይም በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሀሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ የሞት ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ ደርሶታል፡፡ የሞት ጉዳቶቹ የደረሱት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

    “የመንግሥት አካላት የዜጎችን በሰላማዊ መልኩ ተቃውሞ የማሰማት መብት ማረጋገጥ እንዳለባቸው እና ሕግ የማስከበር ሥራ ተመጣጣኝነት እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው”የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ ገልፀዋል።

    የኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት የተከሰቱ አሳዛኝ ግድያዎች ከፈጠሩት ሰቆቃ አሁንም ፈጽሞ አላገገመም። እነዚህ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አዝማሚያዎች እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም” በማለት አክለው ገልጸዋል።

    እስካሁን በአንዳንድ ሚዲያዎች የወጡ ሪፖርቶች እና በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ መረጃዎች የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በሚመለከት የተለያየ አሃዝ አስቀምጠዋል። ኢሰመኮ የደረሰውን ሞትና ጉዳት መጠን ለማረጋገጥ ከየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ምስክሮች፣ ሆስፒታሎች እና የአስተዳደር አካላት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።

    ኢሰመኮ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ጉዳዩን ለማጣራት በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪውን ያቀርባል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
    ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ መንግሥት (ሰኔ 1986 ዓ.ም.) አዋጅ ቁጥር 210/1992 ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዲሠራ ሰኔ 27 ቀን 1992 .. የተመሠረተ ተቋም ነው።

    ተመሳሳይ ዜናዎች

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

    Anonymous
    Inactive

    የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ አስር የማዕድን ምርመራ እና ሁለት የማዕድን ምርት ፈቃዶችን ሰጥቷል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የማዕድናት ፍለጋ እና ልማት ለማካሄድ ፈቃድ ለጠየቁና የፈቃድ መውሰጃ መስፈርቶችን አሟልተው ለቀረቡ ለ12 የማዕድን ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰጥቷል። ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ሲሆኑ አስሩ የምርመራ ፈቃዶች ናቸው።

    የምርት ፈቃድ የተሰጣቸው የባዛልት እና የዕምነበረድ ማዕድን ምርት ሲሆኑ ሌሎች አስር ኩባንያዎች ደግሞ በደለል ወርቅ፣ ወርቅ እና መሰል ማዕድናት፣ ብረት፣ ማንጋኔዝ፣ ክሮማይት፣ ብር እና ጀምስቶን ማዕድናት ምርመራዎች ናቸው።

    ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ለኢንቨስትመንት 270,186,310.00 (ሁለት መቶ ሰባ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ ሶስት መቶ አስር) ብር የተመዘገበ ካፒታልና ለ187 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲሆን፥ የምርመራ ፈቃዶች ደግሞ 131,935,555.00 ብር (አንድ መቶ ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ መቶ ሰላሳ አምስት ሽህ ዘጠኝ አምስት መቶ አምሳ አምስት) ብር የተመዘገበ ካፒታል እና በምርመራ ወቅት በድምሩ ለ293 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ምርመራ ሂደታቸውን በስኬት አጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡም ከሥራ ዕድል ፈጠራ እስከ ውጭ ምንዛሬ ግኝትና ማዳን ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።

    የምርመራ ፈቃዱ የውሉ ስምምነት ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ እንደ የፍቃድ ዓይነት ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት የሚፀና ሆኖ፥ የፈቃድ ዘመኑም ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረትና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲያምንበት ሊታደስ የሚችል ነው።

    ስምምነቱን በፈቃድ ሰጪው መሥሪያ ቤት በኩል የፈረሙት ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ (የማዕድን ዘርፍ) ሲሆኑ፥ በባለፈቃዶቹ በኩል የፈቃድ ወሳጅ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ለወጠነችው የኢንዱስትሪያዊነት መዋቅራዊ ሽግግር የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈልገውን የማዕድናት ግብዓት ለሟሟላት በሁሉም ዓይነት የዘርፉ ሃብቶቻችን ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል።

    ዛሬ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች የምርትም ሆነ የምርመራ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በፌደራልና በክልል የማዕድን አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን መሠረት አድርጎ በጥንቃቄ በትጋትና ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ በማዕድን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተቀባይነት ባለው የአሠራር ዘዴ ለማከናወን በስምምነቱ ውስጥ የተካተተ ሲሆን፥ ተመጣጣኝ ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ቅድሚያ የሥራ ዕድል ለመስጠትና ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን ሥልጠና የመስጠት ግዴታ አለባቸው።

    የአካካቢ ጥበቃን (environmental protection) በተመለከተ የሠራተኞቹን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጤንነትና ደህንነት በማይጎዳና ብክለት በማያስከትል መልኩ የምርት ሥራውን ለማከናወን ውል የተፈፀመ ሲሆን፥ ሥራውን ሲያቋርጥ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ፣ በሰው ሕይወትና ንብረት እንዲሁም ዕፅዋት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ማናቸውም ቅሪቶችና ግንባታዎችን ያስወግዳል።

    የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የፕሮጀክቶችን ውልና አፈጻጸም በየጊዜው እየገመገመ በገቡት ውል መሰረት ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑትን የመደገፍና የማበረታታት፣ በውላቸው መሠረት የማይሠሩትን ደግሞ ፍቃድ የመሰረዝና ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

    ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዜና ሳንወጣ፥ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዕለቱ አስር ሹመቶችን በሰጡበት ጊዜ፥ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሁነው ተሹመዋል። በዕለቱ የተሰጡት አስር ሹመቶች የሚከተሉት ናቸው።

    1. ዶ/ር ቀንዓ ያደታ – የመከላከያ ሚኒስትር
    2. ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
    3. ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
    4. ኢንጂነር ታከለ ኡማ – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር
    5. አቶ ተስፋዬ ዳባ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
    6. አቶ ዮሐንስ ቧያለው – የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
    7. አቶ ንጉሡ ጥላሁን – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር
    8. አቶ እንደአወቅ አብቴ – የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር
    9. አቶ ፍቃዱ ጸጋ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
    10. ፕ/ር ሂሩት ወልደማርያም – በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ በመሆን መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅሕፈት ቤት አስታውቋል።

    የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር

    Semonegna
    Keymaster

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ እንዲሁም ሊያስከትል ይችል የነበረዉን ጉዳት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫዉቷል።

    የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወረርሽኙ/ቫይረሱ ሊያስከትል ከሚችለዉ የከፋ ጉዳትን በመቀነስ በኩል ያበረከተዉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ ገልጸዋል።

    የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በተለመደው የጤና አጠባበቅ ዘዴ እና አካሄድ ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ፥ ሀገራችንም የወረርሽኙን አደገኛነት በመገንዘብ ይህን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲቻል መጋቢት 30 ቀን 2012 .ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በሥራ ላይ እንዲውል አድርጋለች።

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ሦስት ደንቦችና ስድስት መመሪያዎችን በማውጣት የተለያዩ ክልከላዎችንና ግዴታዎችን በመደንገግ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ ሲሆን ሥራውን የሚመሩ ከብሔራዊ ኮሚቴ ጀምሮ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ባሉ አደረጃጀቶች የተለያዩ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ በማድረግ ሥራውን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ እየሠሩ ይገኛሉ።

    ከተቋቋሙት ንዑስ ኮሚቴዎች መካከል ከፌዴራል እስከ ክልል እና ወረዳ ባሉ አደረጃጀቶች የተቋቋመው የሕግ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ አንዱ ሲሆን፥ ይህ ንዑስ ኮሚቴ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሚመራ ሆኖ የወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጎች ለሚመለከተው አካል በወቅቱ እንዲደርሱ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ሕጎቹ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሲያከናውን የቆየ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

    ግንዛቤ ከተፈጠረ በኋላ ንቃተ ሕጉ በሕብረተሰቡ ላይ ያመጣዉን ለዉጥና አፈፃፀሙስ ምን ይመስላል የሚሉትን በመለየትና ወጣ ገባ የታየባቸዉን ጉዳዮች በመለየት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር መድረኮችን በመፍጠርና በቪዲዮ ኮንፈረንስና በፊት ለፊት ስልጠና በመታገዝ የተስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ዉይይቶች እየተደረጉ አቅጣጫ እንዲሰጥባቸዉ የማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸዉን አክለዉ ገልጸዋል።

    በአንዳንድ ክልሎች ወጣ ገባ አፈፃፀም መኖር እና ሕጉን አዉቆ መተግበር ላይ በማኅበረሱ ዘንድ የታዩት ቸልተኝነቶች የፈጠሩት አንዳንድ ክፍተቶች የተስተዋሉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በላይሁን፥ ሆኖም ግን አዋጁ መታወጁ የኮሮና ወረርሽኝ ሊያደርሰዉና ሊያስከትለዉ ይችል ከነበረዉ የከፋ አደጋ ታድጎናል ሲሉ ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው አሰልጥኖ ነሐሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምረቃ ካበቃቸው 2 ሺህ ተማሪዎች  በዶክትሬት ዲግሪ እና በሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

    በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጥቂት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በቨርቹዋል (virtual) አማካይነት ምርቃታቸውን ማካሄዳቸው ታውቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ለማ ጉዲሳ፥ ተማሪዎች በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውን በተማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። “የሲቪል ሰርቪሱን ሀገልግሎት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድርግ በተማሩት የትምህርት መስክ የበለጠ መሥራት ይኖርባቸዋል” ሲሉም አመልክተዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው እንደ ኦንላይን (online) ያሉ የተለያዩ አማራጭ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ምሩቃን ተማሪዎች ማሟላት ያለባቸውን እንዲያሟሉ ማድረጉንም ገልጸዋል።

    ምሩቃኑ በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማሩ ሀገራዊ ለውጡንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ሀገልግሎት በመስጠት ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም ነው ያስገነዘቡት። ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣትና ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

    ከዛሬው ተመራቂዎች መካከል ብቸኛ የዶክትሬት ተመራቂ የሆኑት ዶ/ር ሰይፉ ተሾመ በበኩላቸው፥ በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በተሻለ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። “ሁላችንም በመተባበር ለሀገራችን ብልጽግና በአንድነትና በመተባበር መሥራት አለብን” ብለዋል።

    ሌላዋ ተመራቂ መሠረት መልኬ በበኩሏ፥ በምትሰማራበት የሥራ መስክ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ እድገት የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግራለች። በሀገሪቱ በሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩሏን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጻለች።

    የዛሬ ምሩቃንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በቅድመ ምረቃ እና ድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል።

    ዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴም ለ300 አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች በኮሮና ቫይረስ የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቀነስ የምግብ እና የዘይት ድጋፍ አድርጓል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት በልዩ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተገለጸ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ጋር ለሕዝብ አርዓያነት ያለው ተግባር ላይ ያተኮረ ሆኖ በልዩ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

    ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ የሚካሄደውን የበጎ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር አስመልክቶ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የበጎ ሰው የሽልማት በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፥ ወቅታዊ ሁኔታውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በዘርፎች ላይ ሳይሆን በሁለት ወቅታዊ እና ሀገራዊ አንኳር ጉዳዮች ላይ ልዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።

    እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ምክንያት በዓለም ላይም ሆነ በሀገሪቱ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የተነሳ ሽልማቱን በተለመደው መንገድ ለመስጠት አይቻልም፤ በመሆኑም የዘንድሮውን መርሃ ግብር በተለየ መንገድ ለማከናወን ተወስኗል፤ በበሽታው ምክንያት ከሰዎች ንክኪና ግንኙነት ነጻ በሆነ መንገድ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሽልማቱ ከዚህ ቀደም ከተለመደው በተለየ ሁኔታ ይካሄዳል።

    የበጎ ሰው ሽልማት በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ጸሐፊ አቶ ቀለመወርቅ ሚዴቅሳ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ በየዓመቱ በአስር ዘርፎች በየሙያቸው ለሀገራቸው የላቀ ተግባር ላከናወኑ ኢትዮጵያውያን በሕዝብ ፊት ዕውቅና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፥ “በጎ ሰዎችን በማክበርና ዕውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሰዎችን እናፍራ” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሽልማቱ ሲከናወን መቆየቱን ጠቁመዋል።

    የዘንድሮውን ሽልማት ለማከናወንም ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሁለት መቶ በላይ ዕጩዎችን በመቀበል ታሪካቸውንና አበርክቷቸውን የማጥናት ሥራ መሰራቱንም አመልክተው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመቀስቀሱና በሀገሪቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ በዕቅዱ መሠረት እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት ባለመቻሉ የዘንድሮው ሽልማት በልዩ ተሸላሚ ሥነ ሥርዓት እንዲካሄድ በቦርዱ አባላት በተወሰነው መሠረት የሚከናወን መሆኑን አቶ ቀለመወርቅ አስታውቀዋል።

    አቶ ቀለመወርቅ ሁለት ወቅታዊና አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች መመረጣቸውንና ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ለሕዝብ አርዓያነት ያለውና የላቀ ተግባር ላከናወኑ ግለሰቦችና ተቋማት በልዩ ሁኔታ የዘንድሮው በጎ ሰው ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተናግረዋል።

    የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሳካ፣ ለመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት እንዲበቃና በሕዝቡ ዘንድ ብሔራዊ ኩራት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ በጎ ሰዎችና ድርጅቶች የዘንድሮው የበጎ ሰው ተሸላሚ ይሆናሉ ብለዋል።

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ለመከላከል፣ በበሽታው መስፋፋት የተነሳም በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እና በተለያዩ መንገዶች ለተጎጂ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ የተጉና አርዓያነት ያለው ተግባር የፈጸሙ ኢትዮጵያውያን የሚመሰገኑበት እንደሚሆንም አክለዋል።

    በሁለቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለሀገራቸው የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ስምንት ኢትዮጵውያን ግለሰቦችና ድርጅቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና የጤና ተቋማት ደንብን ባከበረ መንገድ በተመጠኑ ታዳሚያንና በቀጥታ የሚዲያ ስርጭት በመታገዝ ጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሄድ መርሃ ግብር የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት የሚከናወን ይሆናል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት

    Anonymous
    Inactive

    በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የቀዳሚ ምርመራ ሂደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
    የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

    በዛሬው ዕለት (ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም.) አቶ ጃዋር መሃመድ ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ አቶ ጃዋር መሐመድ አሞኛል በማለታቸው ተስተጓጉላል። ከዚህም የተነሳ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን የመስማት ሂደቱን ለማካሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

    በዚህ አጋጣሚ ለሕዝብ እና ጉዳዩን ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ለማድረግ የምንፈልገው፥ እነ አቶ ጃዋር መሃመድ በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ስር እንደመሆናቸው፥ ጤናቸውን ለመጠበቅ ባለው አሠራር አስፈላጊውን የጤና ክትትል እና አገልግሎት የሚያገኙ እና እያገኙ ያሉ ሲሆን ጤናቸውም በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል።

    ለዚህም ማሳያ ከተደረገላቸው የሕክምና በተጨማሪ ዛሬ (ነሐሴ 11) በዋለው ችሎት ምስክር መሰማት እንዳይጀምር የተለያዩ ምክንያቶችን እያነሱ ለረጀም ሰዓት ሲከራከሩ ከቆዩ በኃላ በክርክሩ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ ምስክር መሰሚያ ሰዓት ሲደርስ ወጣ ገባ ማለታቸው የሚፈለገው የምስክሮችን የማሰማት ሂደቱን ለማስተጓጎል እና በግብረ አበሮቻቸው ሁከት እና አመጽ ለመቀስቀስ ነው።

    የተጠርጣሪው ግብረ አበሮች በተለያየ መንገድ ምስክሮችን በማስፈራራት የፍትህ ሂደቱ እንዲስተጓጎል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ፍጹም አግባብነት በሌላቸው መነሻዎች እና በተለያየ ሰበቦች ምስክሮች በቀዳሚ ምርመራ የሚሰሙበተ ሂደት እንዲራዘም እና እንዲሰናከል ለማድረግ ጥረት እያደረጉ በመሆኑ እንደ ወትሮም ሁሉ ተቋማችን ለምስክሮች ተገቢውን የሕግ ጥበቃና ከለላ የሚያደረግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንፈልጋለን።

    ከምንም በላይ በተለያዩ ጥቃቅን ጉዳዮች አላግባብ ከሚቀርቡ አቤቱታ እና ይግባኞች ጀምሮ፣ አልተዘጋጀንም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን፣ ዳኛው ፌገግ ብሏል እና ይቀየርልን በማለት በሰበብ አስባቡ የፍርድ ሂደቱን ለማደናቀፍ በተጠርጣሪዎቹ በኩል የሚደረግ ጥረት እንዳለ ግልጽ ሆኗል። ይህን እውነታ ሕዝቡም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡ እና በአፋጣኝ ፍትህ እንዲረጋገጥ ከምናደርገው ጥረት ጎን እንዲሰለፉ ጥሪያችንን እያቀረብን፥ ማንም ይሁን ማን ከሕግ በላይ መሆን የማይቻል መሆኑን በአጽንኦትት ለመግለጽ እንወዳለን።

    የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
    ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    ተያያዥ ዜናዎች

    ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ

    Semonegna
    Keymaster

    “የወላይታ ዞን ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕጋዊ ነው።”
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በወላይታ ዞን የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲጣራና ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠየቀ።

    ፓርቲው በሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ በኩል ነሐሴ 05 ቀን 2012 ዓ.ም «በወላይታ ዞን የተፈጠረው አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ ይፈታ» በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በዞኑ በተፈጠረው አለመረጋጋት ሕይወታቸውን ባጡ ዜጎች ምክንያት የተሰማውን ሐዘን ገልፆ፥ መንግሥት በአስቸኳይ ጉዳዩን አጣርቶ ይፋ ያድርግ ሲል ጠይቋል። «የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ተገቢ ያልሆነ ኃይል በፍጹም እንዳይጠቀም እና የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ ሳይዳርግ ሕግን በማስከበር ዞኑን ለማረጋጋት ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት እንዲሠራ» በማለት ኢዜማ ማሳሰቢያውን ሰጥቷል።

    በክልሉ የሚገኙ ማኅበረሰቦች የሚያነሷቸውን የራስን በራስ የማስተዳደር ተገቢ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ መመለስ ይገባል ማለቱን ያስታወሰው ኢዜማ፥ ይህን ለማድረግ ግን ማኅበረሰቡ በነፃ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ የመረጣቸው፣ የሚፈልገውን የሚፈጽሙለት ተወካዮች መኖራቸው እና በጉዳዩ ላይ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች መደረጋቸው አስፈላጊ ስለሆነ ሕዝቡ ተወካዮቹን መርጦ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች ተደርገው ሕዝበ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጠይቆ እንደነበር አስታውሷል። ፓርቲው ይህንን ጥያቄውን አቅርቦ የነበረውም ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደነበር ጠቁሟል።

    የዞኑ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕጋዊ መሆኑን እንደሚያምን በመግለጫው ላይ የጠቆመው ኢዜማ፥ ሀገሪቷ እና ዓለም ያለበት ሁኔታ ግን ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅደውን የክልልነት ሒደት ለማሟላት የሚያስችል እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል። ለዚህም በምክንያትነት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን አንስቷል። ኮቪድ ወረርሽኝ ተከትሎ በታወጀው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ የተነሳ ውይይት ማድረግም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ ያስታወሰው ኢዜማ፥ በክልሉ በአጠቃላይ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የሕዝብ ውክልና ያላቸው ተወካዮች መኖራቸው እንዲሁም በቂ ውይይት እና መግባባት ስለሚያስፈልግ በትዕግስት መጠበቁ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ ብሏል።

    ጥያቄውን የሚያነሱት ወገኖችም ሰላማዊ ከሆነ መንገድ ውጪ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይገኝ መረዳት እንዳለባቸው እና እንቅስቃሴያቸውን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ማድረግ እንደሚገባቸው ፓርቲው አሳስቧል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ገዢው ፓርቲ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልልን መልሶ ለማዋቀር ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረበው ምክረ ሀሳብ ክልል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡትን የዞን አስተዳደሮች ጥያቄን የማይመልስ፣ ክልሉ መጀመሪያ ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት መልሶ የሚደግም፣ ሕገ ወጥ እና ግጭት የሚጋብዝ እንዲሁም እንደሀገር ካሉ ውስብስብ ችግሮች ላይ ሌላ ችግር የሚጨምር መሆኑን በማስረዳት ወደትግበራ እንዳይገባ በማለት ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜማ

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ

    Anonymous
    Inactive

    የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክት ግንባታ ደረጃ 84 በመቶ መድረሱ ተገለጸ

    አዲስ አበባ – በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተገነባ ያለውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት /Innovation and Technology Talent Development Institute/ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፌደራልና የክልል ቢሮ አመራሮች ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጎብኝተውታል። ከጉብኝቱ በተጨማሪም አመራሮቹ የአረንጓዴ አሻራቸውን በማዕከሉ ቅጥር ግቢም አኑረዋል።

    እንደ የኢኖቬሽን ልማትና ምርምር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ክቡር አቶ ሲሳይ ቶላ ፕሮጀክቱ ባለፉ ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ምክንያቶች መዘግየት አጋጥሞት ነበር። በአሁኑ ወቅት በተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ በተጠናከረ አመራርና ድጋፍ በማጠናቀቅ በ2013 ዓ.ም. ሁለተኛ ሩብ ዓመት መጀመሪያ ወራት ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ ነው ብለዋል።

    ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ለአካባቢው ማኀበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር በሀገራችን የሚገኙ ባለተሰጥኦዎችን አሰባስቦ ተሰጥኦዋቸውን በማጎልበት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩበት ስለሆነ፥ መላ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉትና እንዲሳተፉበት ጥሪ አቅርበዋል። ያለፉ ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ለውጥ ሂደቶች የተነሳ ያጋጠሙ መዘግየቶችን በቀሪ ወራት አካክሶ ሥራ ለማስጀመር የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅም ተመድቦለታል።

    ክቡር አቶ ሲሳይ አክለውም ለዓመታት ያጋጠመ የመዘግየት ችግር ተካክሶ በሦስት ወራት ውስጥ አመርቂ የግንባታ ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል። በቀጣይም በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉና መሟላት የሚገባቸው ግብዓቶችን ከግንባታው ጎን ለጎን እየተሟሉ ይገኛል። ለስልጠናና ትምህርት እንዲሁም ተሰጥኦ ማፍለቅና ትግበራ የሚውሉ የቁሳቁስ እገዛና ድጋፍ ከልዩ ልዩ አካላት መገኘት ጀምሯል ያሉት ክቡር አቶ ሲሳይ፥ በቀጣይ የግሉ ዘርፍ፣ ሀገር-አቀፍና ዓለም-አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ልዩ ልዩ ተቋማት እና የመንግሥት አካላትን ትብብር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን ብለዋል።

    የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ሥራ ሲጀምር በየደረጃው ካሉ አመራሮች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እንደሚጠበቅ አውስተው፥ ተቋሙ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካና ዘላቂነት እንዲኖረው የአሠራር መመሪያዎችን፣ የትብብር ማዕቀፎችን፣ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትን፣ የተውህቦና የክህሎት መለያ መስፈርቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ቀድሞ የማዘጋጀት ሥራ ከወዲሁ እየተሠራ ነው ብለዋል።

    በመጨረሻም ለዚህ ሀገራዊ ማዕከል መገንቢያ ቦታ በመስጠት፣ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ክስተቶች ወቅት የተጀመሩ ግንባታዎችና ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላደረጉ የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል። ባለተሰጥኦዎችም ወደፊት ወደተቋሙ መጥተው በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን እገዛና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ሁሉ ትብብራቸው እንዳይቋረጥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    ተቋሙን ሥራ ማስጀመር የሚያስችሉትን የግንባታ ሥራዎችን ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንዲቻል በተሰጠ አመራር እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የግንባታ ሥራ ተቋራጩ ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር መስፍን ባልቻ ናቸው። እንደ ኢ/ር መስፍን የቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ ወርክሾፖች፣ የመማሪያ ክፍል እና የማደሪያ ሕንጻዎችን በልዩ ትኩረት ተገንብተው ከ78% እስከ 90% የአፈጻጸም ደረጃዎች ማድረስ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ያለበት አማካይ የአፈጻጸም ደረጃ ከ84% በላይ ነው። ቀሪ የሲቪል ሥራዎችን በማጠናቀቅ የቁሳቁስ ገጠማና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ ለማጠናቀቅ እየተሠራ በመሆኑ በቀጣይ ሦስትና አራት ወራት ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል ብለዋል።

    የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ግንባታ ከሦስት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በተሰጠ አምስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በተያዘ የመንግሥት በጀት የተጀመረ ነው። ከመላው ኢትዮጵያ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል እስከ 1000 ባለተሰጥኦዎችን መልምሎና ተቀብሎ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለግን ተሰጥኦዋቸውን በማልማት፣ በማጎልበትና ወደ ተጨባጭ አምራችነት በመቀየር ለሀገራዊ ብልጽግና መሠረት መጣል የሚችል ተቋም መሆኑን መግለጻችን ይታወቃል።

    ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

    የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት

    Semonegna
    Keymaster

    በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ በማንሳት የሚንቀሳቀሰው የዞኑ አመራርና ሕዝብ
    በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ተገቢ መልስ በሰላማዊ አግባብ ሊሰጠው ይገባል!
    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)

    ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልላዊ መንግሥት የማቋቋም መብት እንዳላቸው በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 47(2) ላይ ተደንግጓል። ይህን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ለማስከበር ከአስር በላይ የሆኑ የደቡብ ብሔራዊ ክልል ዞኖች፣ በየዞናቸው ምክር ቤት በማስወሰን ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄዎቻቸውን ማቅረባቸውንና ውሳኔ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከተለያዩ ምንጮች ስንሰማ ቆይተናል።

    እስከ አሁን ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ዞኖች መካካል በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ በክልልነት የመደራጀት መብት የተከበረለት የሲዳማ ዞን ብቻ ሲሆን፥ የሌሎች ዞኖችን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በቡድን /በክላስተር/cluster/ በማሰባሰብ ከአንድ በላይ በሚሆኑ ክልሎች ለማደራጀት በመንግሥት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ በመንግሥት እየተደረገ ያለውን በክላስተር የማደራጀትን አማራጭ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ ዞኖች እየታዩ ናቸው። በመሆኑም ከሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ አልተሰጠንም ከሚል ተስፋ መቁረጥ ተነስቶ፥ ሕዝቡ ወደ ግጭት እንዳይገባ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ሥጋቱን ገልጿል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የተፈራው ስጋት እውን ሁኖ የወላይታ ዞን አመራር የመንግሥትን የመፍትሄ አቅጣጫ በመቃወም የምክክር ስብሰባ እያደረገ ባለበት ወቅት መንግሥት በወሰደው እርምጃ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ተሰምቷል። በዚህ መነሻነትም ሕዝቡ ተቃውሞ እያሰማ እንደሆነና ከፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በሚፈጠሩ ግጭቾች የሰው ሕይወት እስከ መጥፋት እየደረሰ መሆኑም በእጅጉ አሳስቦናል።

    ስለሆነም፥ መንግሥት የጉዳዩን ሰፊ እንደምታ በጥልቀት በመመልከት፣ በዞኑ ለተነሳው ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት፣ ጥያቄውን በማንገብ ምላሽ ለመሻት የተንቀሳቀሱትን የወላይታ ዞን አመራር አካላትን እና በጉዳዩ ሳቢያ የታሰሩትን ሁሉ በመፍታት፣ ለተከሰተው ችግር ሰላማዊ መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲፈልግ ኢሶዴፓ ያሳስባል። አስተዋዩ ሰፊ የወላይታ ሕዝባችንም ጉዳዩን በወትሮ ጥበቡ በትዕግስት በመያዝ፣ የሰላማዊ መፍትሄ አካል እንዲሆን ኢሶዴፓ በአክብሮት ጥሪ ያደርጋል!!

    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)
    ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    *የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በሀገራችን ኢትዮጵያ ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በመመሥረት ለመሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ርዕዮተ-ዓለሙ ማኅበረ-ዴሞክራሲ (social democracy) ሆኖ ኢኮኖሚያዊና ማኅብራዊ ፍትህን በሀገሪቱ እውን ለማረግ የሚንቅሳቅስ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)

    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መግለጫ
    ሀገራችን ካጋጠማት ፈተና እንድትወጣ በሰላማዊ ትግላችን እንድንቀጥል የቀረበ ጥሪ

    ያለፈው የሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ምን ክስተት ተከትሎ በሀገራችን በተቀሰቀሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል የንብረት ጉዳት ደርሷል፤ ዜጎች በሃይማኖታቸው እና በብሔራቸው ምክንያት ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፤ ሃብት ንብረታቸውም ወድሟል። ለዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ዋነኛ ተጠያቂው የሥርዓቱ አውራዎች በተለይም የኦህዴድ/ብልጽግና፤ ብሔረሰብን በብሔረሰብ ላይ የሚያነሳሳ እኩይ ተግባር መሆኑን በወሰድነው የአቋም መግለጫ በተደጋጋሚ መግለፃችን ይታወሳል። ከሰሞኑም በድብቅ ወጥቶ የተደመጠው የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ምስጢራዊ ንግግር የአቋማችንን ትክክለኛነት አረጋግጦልናል።

    ሆኖም የሥርዓቱ ዓይን ያወጣ ክህደት ከዚህ እኩይ ክስተት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውን የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር አባላት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ሌሎች አባላትና ደጋፊዎቻችን ለሰው ሕይወትና ንብረት ውድመት ተጠያቂ ናችሁ በሚል አስረው እጅግ የሚያሳዝን ተግባር በመፈፀም ላይ ይገኛል። ከአንድ ወር በላይ በቆየው የፍርድ ቤት ሂደት የታየው እጅግ አሳፋሪ ትዕይንት በኢትዮጵያ አሁንም ፍትህ ቀን እንዳልወጣላት በገሃድ ያሳየ ነው። የሥርዓቱ ቁንጮ ነኝ የሚለው ኦህዴድ/ብልጽግና በገሃድ በሚታይ መልኩ የፍትህ ሥርዓቱን መቀለጃ እና የፖለቲካ ፍላጎቱን ማስፈፀሚያ መሣሪያ አድርጎታል። የፍትህ ሥርዓቱ እንኳን ሊሻሻል በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ከነበረው ሁኔታ በብዙ መልኩ የባሰ ሁኖ ይገኛል። በተለይ ሰሞኑን በድምጽ የተለቀቀው የኦህዴድ/ብልጽግና ከፍተኛ አመራር ሕገ-ወጥ እና ለሀገር ህልውና አደገኛ የሆነ ንግግር /በከፊልም ወደ መሬት የወረደ መሆኑን ልብ ይሏል/ እንደሚያስረዳው፥ በተደጋጋሚ ስንወተውት የነበረውን በአዲስ አበባም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተዘረጋ ያለውን በተረኝነት ፖለቲካ የተቃኘ፣ አምባገነናዊ አገዛዝን ለማዳበር ተግቶ የሚሠራ አመራር መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ማስረጃ ሁኖ ቀርቧል። ከመጋረጃ በስተጀርባ ተደብቀው በዘር ማጥፋት ሂደት ውስጥ በዋነኛነት ሲመሩ የነበሩት የሥርዓቱ ዋነኛ ባለስልጣናት ሳይጠየቁ በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው የሚታወቁት የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች መጠየቃቸው ሳያንስ፥ የፍርድ ሂደቱ በድብቅና በዝግ ችሎት እንዲከናወን የተፈለገበት መንገድ በእጅጉ አሳፋሪ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካገኘው በግልጽ ችሎት የመዳኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ያፈነገጠ፣ ሥርዓት አልበኝነትና ምን ታመጣላችሁ የሚል መልዕክት ያለው ሆኖ አግኝተነዋል።

    የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች የችሎት ውሎ አሳፋሪነቱ ምንም እንኳን ከአቃቤ ሕጉ ቅድመ ምርመራ መዝገብ የጀመረ ቢሆንም፥ የተቋሙን ገለልተኛነትና የፍትህ ሂደቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲታዘብ በማሰብ መታገሳችን ይታወሳል። ሆኖም ረቡዕ ዕለት /ነሐሴ 06 ቀን 2012 ዓ.ም./ በዋለው ችሎት አቃቤ ሕግ ሦስት ምስክሮች ከመጋረጃ በስተጀርባ እና ማንነታቸው ሳይገለጽ፥ እንዲሁም አራት ምስክሮች ደግሞ በዝግ ችሎች እንዲደመጡ የሚል ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ የአመራሮቻችን ጠበቆች ለመመካከር እንዲሁም ውሳኔያችንን በጽሁፍ እንድናቀርብ ባሉት መሠረት የተከሰሱበት ወንጀል ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውና ወደ ዘር ማጥፋት የሚወስድ በመሆኑ ይህንን የሚመሰክሩ ምስክሮች በግልጽ ችሎት ፊት ለፊት ቀርበው እንዲያስረዱ፥ ክርክሩ አስተማሪና ሂደቱ ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን ቢጠይቁም በአንፃሩ የፍርድ ቤቱ ዳኛ በአቃቤ ሕግ ብቻ የተጠየቀውን ተቀብሎ ሂደቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዝግ ሆኖ እንዲቀጥል ወስኗል።

    አቶ እስክንድር ነጋ ፈጽማችኋል የተባልነው ጉዳይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይዘት ስላለው በአደባባይ እንጠየቅ፤ ክሱም ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ ችሎቱ በድብቅ ምስክርነት እንዲሰማ ከወሰነ እራሳችንን ከፍርድ ሂደቱ አግልለናል፤ ጠበቆቻችንንም አሰናብተናል፤ ፍርድ ቤትም አንገኝም፤ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ብይን ራሱ ተከታትሎ ይስጥ የሚል አቋም ወስዷል። ይሁንና አቃቤ ሕግ እነ አቶ እስክንድር በፖሊስ ተገደው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ማለቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ይህንኑ የአቃቤ ሕግ ጥያቄ ተቀብሎ ትዕዛዝ ማሳለፉ የዳኝነት ሂደቱ በሕገ መንግሥቱና በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ድንጋጌዎች ሳይሆን በፖለቲካ አመራር እየታዘዘ የሚሠራ መሆኑን በገሃድ ለመገንዘብ ተችሏል። በኦህዴድ/ብልጽግና “የለውጥ ዘመን” የፍርድ ሂደቱ አያያዝ ከህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን በከፋ ደረጃ ኢ-ፍትሃዊነትን እየተላበሰ ስለመሆኑ አስረጂ ሆኗል። አቶ እስክንድር ነጋ መንግሥት የሚያቀርብለትን ጠበቃም ሆነ በፖሊስ ተገዶ መቅረብ እንደማይቀበል “ለፍርድ ቤቱ” አበክሮና አስረግጦ አስረድቷል።

    በከፍተኛ አመራሮቻችን የክስ ሂደት ፖሊስ በተደጋጋሚ ማስረጃ አቅርብ በሚባልበት ወቅት ከተከሰሱበት ጉዳይ ጋር የተያያዘ አንዳችም ማስረጃ ለማቅረብ መቸገሩን በተደጋጋሚ በፍርድ ቤቱ ሂደት ሲታይ እንደነበር ይታወሳል። ፖሊስ ለመክሰስ የሚያስችለው ምንም ማስረጃ ማቅረብ ሲያቅተው በድብቅ ምስክሮችን ለማቅረብ በማሰብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን እያለ የፍርድ አሰጣጡን ሂደት ያለበቂ ምክንያት ሲያራዝመው መታየቱ፥ ከጅምሩም ክሱ የሃሰት እንደሆነ ለከፍተኛ አመራሮቻችን፣ ለጠበቆቻቸው እንዲሁም የችሎቱን ሂደት በአንክሮ ይከታተል ለነበረው ፓርቲያችን ግልጽ ነበር። እስከዛሬ ለማሳየት የደከምንበት ሃቅ ይህንኑ የሚያስረዳ ነው። መሪያችን ከዚህ ትክክለኛ ካልሆነ ከሕገ መንግሥቱና ከወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ድንጋጌዎች ካፈነገጠና በተግባር ካልተሻረው የፀረ-ሽብር ሕግ በተወሰነ አንቀጽ ከሚመራ የፍርድ ቤት ሂደት ራሱን ማግለሉ በእጅጉ ትክክለኛ እና የምንደግፈውነው። በዚህ ዓይነት ቅጥ አንባሩ ከጠፋው የአምባገነኖች “ካንጋሮ ፍርድ ቤት” ፍትህ ማግኘት ስለማይቻል የአመራሮቻችን ውሳኔ ትክክል መሆኑን ድርጅታችን ያምንበታል። በመሆኑም ድርጅታችን ከአመራሮቻችን ጎን ዛሬም እንደትላንቱ ከጎናቸው በጽናት እንደሚቆም ማረጋገጥ ይወዳል።

    ኦህዴድ/ብልጽግና በኦሮሚያ ክልል በተደጋገሚ የዜጎችን ዘር እና ሃይማኖት ተገን ተደርጎ ለተፈጠረው የዘር ማጥፋት /genocide/ እና የሥርዓቱ ጋሻጃግሬዎች ላደረሱት ወንጀል ሽፋን በመስጠት በሌሎች ንፁሃን ላይ በማላከክ ሕግ እንዳይከበር እና አለመረጋጋቱ ተባብሶ እንዲቀጥል እንየተደረገ እንደሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጉዟችን በአግባቡ ተገንዝበናል። በመሆኑም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሀገራችን በተደጋጋሚ የደረሱት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሆን ተብለው በሥርዓቱ አመራሮች ድጋፍና ተሳትፎ ጭምር የተካሄዱ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚቀርቡት እውነታዎች በገሃድ የሚያሳዩ መሆናቸውን ተመልክተናል። እንደማሳያነትም በቅርቡ በኦህዴድ/ብልጽግና ከፍተኛ አመራር በድብቅ ወጥቶ በተደመጠ ንግግር “ቄሮን የምናዘው፣ የምናወጣውም እንዲሁም የምንበትነው እኛ ነን” ማለታቸውን ልብ ይሏል። እውነተኛ ፍትህ ቢኖር በዚህ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አባባል መሠረት ቄሮ በተሰኘው ኢ-መደበኛ አደረጃጀት እስካሁን ለተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ መሆን የሚገባው ማን እንደሆነ በግልጽ መገንዘብ ይቻላል።

    ስለዚህ የዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀሙት ብቻ ሳይሆን፥ ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው ያስፈጸሙትን ጭምር ለሕግ እንዲቀርቡ እንዲደረግ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች የፓርቲያችንን ጥረት እንዲያግዙ በድጋሚ እንጠይቃለን። በተጨማሪም በሀገራችን የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን አስቀድመን ስንጮህ ከጎናችን የነበራችሁ በሀገር ውስጥና በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን፣ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ማኅብረሰብ፣ ለፓርቲያችን ቀጣይና ቁርጠኛ ለሆነው ሰላማዊ እና ሕጋዊ ለሆነው የትግል እንቅስቃሴያችን ከጎናችን በመቆም ድጋፍና እገዛ እንድታደርጉልን በአክብሮት እንጠይቃለን።

    ድል ለዲሞክራሲ!

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
    አዲስ አበባ
    ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም.

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    የአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚስጥር ንግግር
    (ሙሉሸዋ አንዳርጋቸው)

    ኢትዮ 360 አቶ ሽመልስ አብዲሳ የዛሬ 7 ወር ገደማ በከፍተኛ ሚስጥር ይጠበቅ ብሎ በኦሮምኛ በስብሰባ ላይ የተናገረውን የኦሮሙማ ፕሮጄክት ለሕዝቡ ሰሞኑን ለቆታል

    መረጃውን ለኢትዮ 360 ማን ለምን እንዴት ሰጠ የሚለውን ለጊዜው ወደጎን ትተን፥ ኢትዮ 360 ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ተማክረው የኢትዮጵያን ህልውና ግምት ውስጥ በመክተት ነገሮች እስኪረጋጉ መረጃውን ከመልቀቅ በመቆጠባቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ይሄ ነው በተግባር ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ ማስቀደም። እንደ ጋዜጠኞች መረጃውን ማግኘት መቻላቸውም በራሱ በተጨማሪ ሊያስመሰግናቸው ይገባል።

    ወደ ሽመልስ ንግግር ፍሬ ነገር ስንገባ፥ አነ ሽመልስ አብዲሳ እና በጥቅሉ የኦሮሙማ አራማጆች ምን እንደሚያስቡ ማወቅ ተገቢውን የትግል ስልት ለመቀየስ በእጅጉ ይረዳል። ከዚህ በፊት ኦቦ ለማ መገርሳ ስለ ዲሞግራፊ ሃሳባቸው፣ አያቶላ ጃዋር ስለ 2ኛው የቄሮ ስውር መንግሥት፣ አሁን ደግሞ ሽመልስን በዚህ ረገድ እናመሰግናቸዋለን።

    ከዚህ ቀጥዬ የሽመልስን ንግግር ልፈትሸው እሞክራለሁ። እነ ሽመልስ አብዲሳ እና ኦሮሙማ አራማጆች ምን እንዳሰቡና ምን እንደሚፈልጉ ለሁላችንም ግልጽ ነው፤ ነገር ግን እግረ መንገዴን ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ መሆናቸውን ለማሳየት እሞክራለሁ። መደስኮርና በተግባር ማሳካት ትልቅ ልዩነት አላቸው።

    1. በመጀመርያ ይሄ ዲስኩር የተደረገው የዛሬ 7 ወር ገደማ መሆኑን ልብ እንበል። Fast forward ዛሬ ላይ ባጭሩ ኦሮሙማ አራማጆች ላይ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል። የ2ኛው መንግሥት መሪያቸው ጃዋር ታስሯል፤ ኦ ኤም ኤን (OMN) የሀገር ቤት መርዛማ ስርጭቱ ተዘግቷል፤ ቀላል የማይባሉ የኦሮሙማ አራማጆች ታስረዋል፤ የዲሞግራፊ ቅየሳ መሃንዲሱ ኦቦ ለማና የለገጣፎ/ሱሉልታ/ሰበታ አፈናቃይዋ ጠቢባ ሀሰን ሳይቀሩ ከፓርቲው ታግደዋል። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ አባ ገዳዎች ከብት እያረዱ ሊያስማሟቸው ቢሞክሩም፥ ዛሬ ላይ የኦሮሙማ አራማጆች እርስ በእርስ ከመጨራረስ ምንም ምድራዊ ኃይል የሚያስቆማቸው ያለ አይመስልም። ዛሬ ላይ ለዐቢይ ከጃዋር በላይ፣ ለጃዋር ከዐቢይ በላይ ጠላት ከየትም አይመጣም። መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይሄ ነው።
    2. ሽመልስ አብዲሳ እኛ ነን ትህነግን (የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር) በቁማር ጨዋታ ያባረርነው የሚለውን እስቲ እንፈትሸው።

    በረከት ስምዖን በቶሎ ካልተቀየርን አደጋው የከፋ ነው ብዬ ስለፈልፍ አልሰማ ብለውኝ፤ የጎንደር አመጽ ሲጀመር የኢህአደግ አመራሮች የምር መሆኑ ዘግይቶም ቢሆን ገባቸው አለ። በሕወሃት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የተጻፈው የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ መጽሐፍ ላይ የገዱ አንዳርጋቸው ቡድን ከትህነግ ጋር ለረጅም ጊዜ ፊት ለፊት ሲጋፈጥ እንደነበር ቀን፣ ቦታና አጀንዳ ጠቅሶ ያስረዳል። ዐቢይ ከመመረጡ በፊት የአማራ ሚዲያ ከትህነግ ቁጥጥር ውጪ ወጥቶ ተደማጭ ሚዲያ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ቴዲ አፍሮ በአዲስ አበባ በትህነግ የተከለከለውን ኮንሰርት ባህር ዳር በነጻነት ያውም በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቆ ማድረጉን እናውቃለን። ባህር ዳር እነ ለማ መገርሳን የጋበዛቸው፣ በሰላምም ቆይተው በሰላም እንዲመለሱ ያደረገው የገዱ አንዳርጋቸው ቡድን ነው። በትህነግ እነ ለማን ለማሰር ታስቦ ደመቀ እምቢ ብሎ ማስቀረቱን ሰምተናል።

    ጥሬ ሃቁ ይሄ ከሆነ እነ ሽመልስ ቁማር ከተጫወቱ፥ ባለቀ ሰዓት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ከውስጥ ደግሞ የገዱ ቡድን በዋናነት ገዝግዞ የጣሉትን ትህነግ፣ በቁማር ጨዋታ የገዱን ቡድን በልጠው ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት መግባታቸው ነው። የገዱ ቡድን ትልቁ ድክመቱ ባህር ዳር ከአዲስ አበባ ርቆ ተወሽቆ፣ ከመሃል ሀገር ስነ ልቦና መራቁና ስልጣን ይገባኛል የሚል ስነ ልቦና ስላልነበረው ነው።

    1. አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስለ ኦሮሙማ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ተናጋሪ አይደሉም። በእርግጠኝነት የመጨረሻም ተናጋሪ አይሆኑም። ኦዴፓን (ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ጨምሮ የኦሮሞ ፓርቲዎች በኦሮሙማ አራማጆች የተሞሉ ናቸው።

    አቶ ሽመልስ ከዚህ ቀደም የማናውቀውን ነገር ብዙም አልነገሩንም። ክብርና ምስጋና በዋናነት ለእስክንድር ነጋ ይግባውና፥ የኦሮሙማ ፕሮጀክትን ከስር ከስር እየተከታተለ አዲስ አበባ ውስጥ ስር እንዳይሰድ አጋልጧቸዋል። እስክንድር ተወልዶ ባያነሳ ብዕር፣ አዲስ አበባ ይሄኔ የኦሮሙማ መቀለጃ ትሆን ነበር። እስክንድርን ለምን እንዳሰሩት ይገባናል።

    1. የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግርና የኦሮሙማ አራማጆች ፍላጎት ላይ ምንም ብዥታ የለንም። ቢችሉ አማርኛን ሙሉ ለሙሉ ቢያጠፉና ኦሮምኛ ብቻ ቢነገር ደስተኞች ናቸው፤ ቅዠታቸው እዚህ ድረስ ነው። ሽመልስ አማርኛ ቋንቋ እንዲሞት፣ ኦሮምኛ ደግሞ እያደገ እንዲመጣ እንዳደረጉ፥ ኦሮምኛ ቋንቋ በ22% እንዳሳደጉ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሀረሪ፣ በሶማሌ የኦሮሞኛ ቋንቋ እንዳሳደጉ ይናገራል። ለሽመልስ ጥያቄዬ ይሄን ሁሉ ያደረጉት በዚህ 2 ዓመት ውስጥ ነው? የመረጃው ምንጩ ምንድን ነው? ማስረጃ እስኪጠቀስ ድረስ እንደ ኦሮሙማ ምኞት ቢወሰድ የሚመረጥ ይመስለኛል።

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ ብልጽግና ውስጥ የኦዴፓ ውክልና በምንወክለው ሕዝብ ብዛት መጠን እንዲሆን አድርገናል ይላል። በዚህ የተነሳ ኦሮሞ ያልሆነ ወይም ኦሮሞ ያልፈለገው ሊቀ-መንበርም ሆነ ምክትል ሊቀ-መንበር እንዳይወጣ አድርገን ብልጽግናን ሠርተናል ይላል። ሲጀምር ፓርቲዎቹ በሚወክሉት ሕዝብ ብዛት መጠን ድምጽ መኖሩን ከትህነግ በቀር ሁሉም ፓርቲዎች ይፈልጉትታል። ሲቀጥል ሽመልስ 40% ድምጽ አለን የሚለውን እውነት አድርገን እንውሰደውና፥ በየትኛው ቀመር ይሆን የተቀሩት 60% ድምፅ ካላቸው ፍላጎት ውጪ ኦዴፓዎች የፈለጉትን እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው? ወይስ የብልጽግና ደንብ ኦዴፓ ያልፈቀደው ሊቀ-መንበር ወይም ምክትል ሊቀ-መንበር መሆን እንደማይችል “veto power” ለኦዴፓ ይሰጣል? እንዴት አርገው ነው 30% የሕዝብ ብዛት ኢትዮጵያን በኦሮሙማ ቅድ መስፋት የሚቻልው? ሌላው ጉራጌው፣ አማራው፣ ሱማሌው፣ ደቡቡ፣ ትግሬው እሺ ብሎ ይገዛል ወይ?

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአዲስ አበባ በሕጋዊ መንገድ ይሁን ከሕግ ውጪም የኦሮሞን ቁጥር እንጨምራለን ይላል። መጀመርያ የለማ በአዲስ አበባ ዙርያ ሰፋሪዎች፣ ቀጥሎ ታከለ ኡማ በዚህ ጉዳይ ላይ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መሬት ላይ ምን እያደረገ እንደሆነ እናውቃለን። አቶ ሽመልስ ምንም አዲስ ነገር እዚህ ላይ አልነገረንም።

    አዲስ አበባን ሌሎች ሁለት ወይም ሦስት ተጨማሪ የፌዴራል መቀመጫ ከተሞች በመጨመር እናዳክማታለን አለ። አቶ ሽመልስ አብዲሳ አዲስ አበባን ለማዳከም መወሰን ማለት “ፊንፊኔ ኬኛ” ቀረ እያለን እንደሆነ ገብቶታል? አዲስ አበባን ማዳከም እንደ ማውራት ቀላል ይሆን? ከተጨማሪ የፌዴራል ከተሞች ውስጥ ለምሳሌ አንዱ ናዝሬት የሁሉም ኢትዮጵያኖች ከተማ ቢሆን፣ “ናዝሬት ኬኛ” በኋላ ማለት ሊጀምሩ ይሆን?

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአሁኑ ወቅት በልበ-ሙሉነት እንደ ኦሮሚያ እየለማ ያለ ቦታ የለም ይላል። Really? የቄሮ እብደት ከጀመረ በኋላ ፋብሪካዎች በኦሮሞ አካባቢ ሲቃጠሉና ሲዘጉ አይደል እንዴ እያየን የለነው? አሁን እንኳን ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣… እንዳልነበሩ ሆነው አልወደሙም? ስንት ዓመት ይፈጅ ይሆን የተቃጠሉትን ከተሞች ያሉበት ቦታ ለመመለስ? በተጨማሪ “ፊንፊኔ ኬኛ” ብለው የኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ የኦሮሞ መሥሪያ ቤቶች፣ቢሮዋች፣…. ሸገር ላይ ነው የሚሠሩት። ታዲያ እንዴት አድርገው ነው አዱ ገነትን መግደል የፈለጉት? በኦሮሞ አካባቢ አለመረጋጋትና በኦሮሙማ አራማጆች ድንቁርና እየተመነደጉ ያሉት ከተሞች ሌሎች ናቸው። በስታትስቲክስ የተደገፈ መረጃ እዚህ ላይ ለሽመልስ ማቅረብ ይቻላል።

    1. ማጠቃለያ
      የሽመልስና የቢጤዎቹ ኦሮሙማ አራማጆች ሴራ በንቃት ሁላችንም መከታተልና ማጋለጥ አለብን። ለሴራቸውም ማክሸፊያ በሕብረት መፈለግ አለበት። በተለይ ሌሎቹ የብልጽግና አባሎች ይሄንን የእነ ሽመልስን የኦሮሙማ ቅዠት በዋዛ ፈዛዛ ሊያልፉት አይገባም። ከስር ከስር እነ ሽመልስን እየተከታተሉ ማጋለጥና ማርከሻ መፈለግ አለባቸው። የእነ ሽመልስን እጅና እግር ለማሰር የብልጽግናን ደንብ መለወጥ ካለባቸው አይናቸውን ማሽት የለባቸውም። እንዲህ በማድረግ ነው የኦሮሙማ ቅዠታሞችን እሩቅ አሳቢ፣ ቅርብ አዳሪ አድርገን የምናስቀረው።

    ሙሉሸዋ አንዳርጋቸው

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ

Viewing 15 results - 196 through 210 (of 730 total)