Search Results for 'የትምህርት ሚኒስቴር'

Home Forums Search Search Results for 'የትምህርት ሚኒስቴር'

Viewing 15 results - 31 through 45 (of 83 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የተፈጥሮ ሳይንስ እና ግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ተገለጸ።

    በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገራችን አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።

    የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕለት የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ቀን በሚል ችግኝ የመትከል ማዕድ የማጋራትና ደም የመለገስ መርሃ-ግብሮች ተከናውነዋል።

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአሰላ ከተማ የሚገኘው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት መርሃ-ግብሩን ያስጀመሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፥ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የግብርና ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

    በቅድመ ተከላ፣ በተከላ ወቅትና ድኅረ ተከላ መደረግ ያለባቸውን እንክብካቤዎችን እና ጥንቃቄዎችን በማስተማርና እንዲሁም እንደየአከባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ተስማሚ የሆኑትን ችግኞች እንዲባዙ ጥናትና ምርምር ከማድረግና ማማከር በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ችግኞችን አባዝተው ለአከባቢው ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

    አያይዘውም በየአከባቢው ያለው የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማኅበረሰቡ እንዲሁም ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን እየተጠነቀቁ በዚሁ ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ማዕድ እንዲያጋሩ እና ደም በመለገስም ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት እንዲታደጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን ሦስቱን ግቢዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን የጎበኙ ሲሆን፥ በጉብኝቱ ከሰባ ዓመታት በፊት በስዊድን ድጋፍ የተቋቋመውና በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የግብርና ምርምር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ እና የጤና ሳይንስ ኮሌጁም የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ለመከላከል የሚያመስገን ሥራ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።

    ፕሮፌሰር አፈወርቅ በማዕድ ማጋራት ዩኒቨርሲቲው የሚደግፈውን አፎምያ የአረጋውያን መርጃ ማኅበር የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው የዱቄትና ዘይት ድጋፍ አድርጓል።

    ከአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ከድምጻውያን ጋር በመሆን በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ ውስጥ (የካ ተራራ) ችግኞችን ተክለዋል።

    ከንቲባው በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዓለም-አቀፍ ስጋት የሆንውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሸኝን ከመከላከል በተጓዳኝ ነዋሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ችግኞች እንዲተክሉ አሳስበዋል። ችግኝ ከመትከል ባለፈም ችግኞች በየጊዜው መንከባከብም ያስፈልጋል ብለዋል።

    የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ሕብረት ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ሕብረተሰቡ ችግኞች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመረዳት በራሱ ተነሳሽነት መትከልና መንከባከብ ይገባል ብለዋል። ሕብረቱም የተከላቸውን ችግኞች ለመንከባከብም ቃል ገብተዋል።

    በሥፍራው ተገኝቶ አረንጓዴ አሻራ በማኖሩ ደስተኝነቱን የገለጸውና ተግባሩ መቀጠል አለበት ያለው ድምፃዊ ነዋይ ደበበ ነው።

    ”ንጹህ አየር ለሰው ልጅ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ችግኝ መትከል ግዴታ ነው። በዚህም ቦታ ተገኝቼ አረንጓዴ አሻራ በማኖሬ ደስተኛ ነኝ” ሲል የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ተናግሯል።

    በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰባት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከሚተከሉት መካከል ለጥምር ግብርና የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች ይገኙበታል።

    ምንጮች፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አረንጓዴ አሻራ

    Anonymous
    Inactive

    የጤና ሳይንስ ምሩቃን በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ከሀገር ውጭ ሲወጡ ደግሞ በተማሩበት የሙያ መስክ ጥራት ያለውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ የሚያበቃ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና የስልጠና ፕሮግራም ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

    በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የጤና ሳይንስ ትምህርቶችን ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር Jhpiego ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር የጤና የሰው ኃይል ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም (Health Workforce Improvement Program /HWIP/) ላይ የቪዲዮ ውይይት (webinar) አድርጓል።

    በውይይቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጤና ሳይንስ የሚመረቁ ምሁራን በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ከሀገር ውጭ ሲወጡ ደግሞ በተማሩበት የሙያ መስክ ጥራት ያለውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ የሚያበቃ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና የስልጠና ፕሮግራም ደረጃ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

    ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው እንዲህ ዓይነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እገዛም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በጤና ዘርፍ በየዓመቱ መሰልጠን ያለባቸውን ቁጥር አጥንቶ መመጠን፣ ኢ-ለርኒንግን (e-learning) ማጠናከር፣ የትምህርት መርሃግብሮች ዕውቅና አሰጣጥ (programs accreditation) ላይ መሥራት፣ የመርሃግብር ደረጃ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎች ይጠበቃል ብለዋል።

    የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው ሆስፒታል እና የጤና ማዕከላት ሲኖራቸው የሌላቸው ደግሞ ተማሪዎቻቸውን በአከባቢያቸው ከሚገኙ የጤና ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ያሰለጥናሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ስለሆነም በጤና ዘርፍ ያሉ አመራሮችን፣ መምህራንን እና የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባትና ግብዓት ማሟላት ለጥራት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

    ፕሮጀክቱ የ5 ዓመት መሆኑን እና በጤና ዘርፍ የሚወጡ ተማሪዎች ጥራት እንዲኖራቸው መሥራትና፣ ለጤና ዘርፍ ትምህርት ጥራት የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ግብዓቶችንና ቴክኒካዊ ምክረሃሳቦችን በማቅረብ ተግባራዊ እንዲረግ መሥራት ዋና ዓላማቸው መሆኑን የገለፁት የJhpiego ዳይሬክተር ዶ/ር ተግባር ይግዛው የጤና ሳይንስ ትምህርትን ጥራትን ለመደገፍ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

    የ39.5 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክቱን ተግባዊ ለማድረግም በጤና ትምህርት ዘርፍ በሚደረጉ ድጋፎች ላይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በተለይ ለጾታ እኩልነት ቦታ እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።

    ዶ/ር ተግባር ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ውስጥ የሚከሰቱትን ወሳኝ የሰው ኃይል ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ መንገዶችን ለማመቻቸት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ስምምነት የሚሠራ መሆኑን ገልጸው፥ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራትም የኢትዮጵያን የጤና ባለሙያዎች ጥራት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ብቃት ለማሻሻል እና የጤና የሰው ኃይል አስተዳዳሪዎች ችሎታን ለመገንባት በተቋም እና ግለሰቦች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ብለዋል።

    በውይይቱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ቢሠራበት የሚሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል። በዚህም በሚኒስቴሩ በኩል ከድርጅቱ ጋር በጋራ የሚሠራባቸው መስኮች ተለይተው እና የትግበራ ዕቅድ አውጥተው ወደሥራ እንደሚገቡ ተጠቁሟል።

    በውይይቱ ዩኒቨርሲቲዎችን ዓለምአቀፋዊ ማድረግ ላይ የሚሠራውን ሥራ ለማገዝ ዕውቅና መስጠት (accreditation) መጀመር እንዳለበትና በተለይ የሕክምና ትምህርት ላይ ቀድሞ መጀመር ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑም ተመላክቷል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የጤና ሳይንስ ትምህርት

    Anonymous
    Inactive

    የከፍተኛ ትምህርትን በቴክኖሎጂ በመታገዘ ማስቀጠልን አስመልክቶ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ በቴክኖሎጂ በመታገዘ የከፍተኛ ትምህርትን ለማስቀጠል መወሰኑን መግለፁ ይታወቃል። ይሄንንም ተከትሎ በትግበራው ዙርያ ከስጋትና ከመረጃ ጉድለት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። አፈፃፀሙ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህን ሚኒስቴሩ ይህን ፅሑፍ (ማብራሪያ) አዘጋጅቷል።

    የተነሱት ጥያቄዎች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን የተመለከቱ፣ የኢንተርኔት ዋጋ ውድ መሆን ፣ የኔትወርክ ችግር መኖርን፣ የመብራት አለመኖርና መቆራረጥን፣ ሁሉም ተማሪዎች ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ አቅም ሳይኖራቸው ትግበራው የሚያስከትለውን ኢ-ፍትሃዊነት እና ቢተገበር ውጤታማ ላይሆን ይችላል ከሚል ስጋት የሚነሱ ናቸው።

    ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት የሰው ልጆችን ህልውና በሚፈታተኑ አስቸጋሪ ወረርሽኞች ውስጥ አልፋለች። ከነዚህም አንዱ በዘመናችን ያጋጠመን ኮቪድ-19 ነው። ቫይረሱ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም መዛመት ከመቻሉ ጋር ተያይዞ የበርካታ አገራትን ዜጎች ከቤት ውጭ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ገድቧል። በሁሉም ዘርፎች ዓለምን ለቀውስ ዳርጓል።

    ታዲያ ይህ ቫይረስ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ሲል መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል። ከነዚህም አንዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ወደየቤተሰቦቻቸው መመለስ ነው።

    አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቫይረሱ መቼ በቁጥጥር ስር ውሎ እነዚህ ተማሪዎች ወደቀድሞ እንቅስቃሴያቸው እንደሚመለሱ ስለማይታወቅ ትምህርትን ከማስቀጠል አንፃር የተለያዩ አማራጮችን መመልከት አስፈልጓል።

    ከዚህ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ስንመለከት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ/ UNESCO) በቀውስና አደጋ ጊዜ ስለትምህርት ማስቀጠል “Education Response in Crises and Emergencies” ሲያስረዳ፥ በችግር ጊዜ ትምህርት ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ አገራት የተለያዩ የትምህርት ማስቀጠያ መንገዶችን ተከትለው እንዲሰሩ ያስቀምጣል። በተለይም “Education 2030 Incheon Declaration and Framework for Action“ ላይ በተለያዩ የአደጋ ጊዜዎች በመደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ መንገዶችን በመጠቀም ተለዋጭ የመማር-ማስተማር ዘዴዎችን በመተግበር አካታችና ፍትሃዊ ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ስለሆነም ይህ በትምህርት ላይ የነበሩና በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎቻችንን በተቻለ መጠን በሚቻለው ሁሉም አማራጭ ንባቦችን እንዲያገኙ በማድረግ እያነበቡ እንዲቆዩና ከትምህርታቸውም እንዳይቆራረጡ ማድረግን ግብ አድርጎ እየተሠራ ያለ ተግባር ነው። ስለዚህ እንደሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ባለን አቅም፣ ሀብትና ግብዓት የከፍተኛ ትምህርቱን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማስቀጠሉ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር በመሆኑ ውሳኔው ተላልፏል።

    በዚህም የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን በተመለከተ፡

    የሁለተኛ ሴሚስተር የሁሉም ትምህርት ዓይነቶች ሞጁሎች (modules)፣ አጋዥ ንባቦች እና ሌሎችም በየትምህርት ዓይነቱ ተሰንደው የሚገኙባቸው ድረ-ገፆችን (ዌብሳይቶችን) የማሟላት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በዚህም፦

      • የተዘጋጁ የኮርስ ማቴሪያሎችና አጋዥ የትምህርት መጽሃፍቶች ተደራሽ የሚሆኑበት የዲጂታል ላይብረሪ ዝግጁ ተደርጓል። (http://ndl.ethernet.edu.et/) አስፈላጊ በሆኑ የትምህርት ይዘቶች እየበለፀገ ይገኛል።
      • እንዲሁም በርካታ ይዘቶችን የያዘዉ የ TechIn ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ዝግጁ ሆኗል (http://library.techin.et/)
      • የኦንላይን ትምህርት መስጠት የሚያስችል የLearning Management System/MOOCS ዝግጁ ተደርጓል። (https://courses.ethernet.edu.et/)

    እንዲሁም ተማሪዎች ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በስልክም ይሁን በላፕቶፕ እንዲሁም በታብሌት ወደእነዚህ ዌብሳይቶች ገብተው በሚያነቡበት ጊዜ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ከኢትዮ ቴሎኮም ጋር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

    እንደተገለፀው ወረርሽኙ መቼ እንደሚገታ አይታወቅም። ነገር ግን ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑ ተረጋግጦ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እስከሚመለሱ ድረስ በተለያዩ ድረ-ገፆች (ዌብሳይቶች) ለንባብ የቀረቡላቸውን ግብዓቶች (ማቴሪያሎች) እያነበቡ ይቆዩና ሲመለሱ እንደየተቋማቱ ተጨባጭ ሁኔታ ቀሪ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት ፕሮግራም ይቀይሳሉ።

    የምረቃ እና ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎችን በሚመለከት

    አብዛኞቹ የማስተር (MSc, MA, MPH…) እና የፒኤችዲ (PhD) ተማሪዎች በምርምር ላይ እንደመሆናቸው ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ትምህርቱን በኦንላይን ለማስቀጠል እንዲያመቻቹ ሆኗል። በዚህም ለመማር-ማስተማሩ የሚያግዙ ግብዓቶች (ማቴሪያሎች) በኦንላይን፣ በኢ-ሜይል እና ሌሎች ዘዴዎች ለተማሪዎች እንዲቀርቡ እየተሠራ ይገኛል። ምርምሮቻቸውን ያላጠናቀቁና ዳታ ለማሰባሰብ የግድ መውጣት ከሚያስፈልጋቸው ውጭ ያሉት በሙሉ የመመራቂያ ጽሁፋቸዉን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እንዲያቀርቡ ይመቻቻል።

    የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸዉ ጋር የሚገናኙበት የኦንላይን የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማድረግ፣ ማንኛዉንም ሰነዶችን ማጋራት ሌሎችንም የቨርቹዋል (virtual) ግንኙነቶች ማድረግ የሚያስችል የ Office 365 Teams ቴክኖሊጂ ዝግጁ ተደርጓል። በተጨማሪም በሃገር ዉስጥ የተሠሩ የ Thesis and Dissertations ሰነዶች ለማጣቀሻ እንዲሆኑ በ<https://nadre.ethernet.edu.et/> ዝግጁ ሆነዋል።

    በተጨማሪም አብዛኞቹ የ Educational Private አገልግሎቶች ከኢተርኔት ዳታ ማዕከል የሚሰጡ ስለሆነ፣ ለዳታ ማዕከሉ ለጊዜዉ ያልተቆጠበ የኢንተርኔት ባንድዊድዝ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲያቀርብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመነጋገር ላይ ይገኛል።
    ይህ አቅጣጫ እንዳለ ሆኖ ዩኒቨርስቲዎች እንደየትምህርት ክፍላቸውና የትምህርት ዓይነቶቹ እንደሚያስፈልጓቸው ተጨማሪ ሁኔታዎች እያዩ ሌሎች የመገናኛ ፕላትፎርሞችንም የሚያቻቹ ይሆናል።

    በመጨረሻም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሁን በዓለማችን ያጋጠመውን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሁሉም ዘርፍ ያለውን የሀገራችንን እና የዜጎቿን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እና በተቻለ መጠን ሁሉ ትምህርትን ተደረሽ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትክክለኛ የTelegram Channel <https://t.me/MinistryoSHE>ነው። ይቀላቀሉ! በሌላ አማራጭ ትክክለኛ መረጃ ያግኙ።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    የከፍተኛ ትምህርትን በቴክኖሎጂ በመታገዘ ማስቀጠልን አስመልክቶ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ

    Semonegna
    Keymaster

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 34 የሕክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ለሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1233 ተማሪዎቸ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመርቋል።

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በዋና ግቢው እና በዱራሜ ካምፓስ 6 ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በተከታታይ ትምህርት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።

    በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፥ ኢትዮጵያ ለእርሷ እና ለዜጎቿ ክብር እና ፍቅር ያለው ባለሙያ ያስፈልጋታል ብለዋል። አክለውም ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት በተገቢው ሁኔታ ለማኅበረሰብ ለውጥ እንዲያውሉት አሳስበዋል።

    ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን በማጠናከር የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስረግጡም ዶ/ር ሳሙኤል ጠይቀዋል።

    የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያየ መልኩ ከሚንፀባረቀው የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ኋላ ቀርነት በመራቅ ለኅብረተሰብ ዕድገት እና ብልፅግና እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።

    በሌላ በኩል ደግሞ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም ያሰለጠናቸውን 33 የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ።

    ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም (hybrid innovative curriculum) በሕክምና ዶክትሬት ያሰለጠናቸውን 33 ተማሪዎች በተመሳሳይ ቀን አስመርቋል።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ለተማሪዎቹ የሥራ መመሪያ የሰጡት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ ተመራቂዎቹ ቃለመሀላ በገቡለት የሕክምና ሥነ-ምግባር በመታገዝ ቅን አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል። ከዚህም ባለፈ በተግባር በተደገፈው ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም የቀሰሙትን የሕክምና ትምህርት የሀገሪቱን ብሎም የዓለምን ሕዝብ ስጋት ላይ ከጣሉ ዘመን-ወለድ የጤና ችግሮች ኅብረተሰቡን ለመታደግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በውጤት በታገዘው የቅይጥ ፈጠራ-አከል ሥርዓት (ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም) ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸው በመሆናቸው ማኅበረሰቡን ከጤና እክሎች ከመታደግ ባለፈ በምርምር ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር ብልፅግና የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ 26 የማስተርስ ዲግሪ (ሁለተኛ ዲግሪ) ተማሪዎችንም አስመርቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    የጋሞ ሽማግሌዎች (የጋሞ አባቶች) መንግሥት ኖረም አልኖረ በአካባቢያቸው ላይ፤ በተለይም በገዛ ልጆቻቸው የማንም ሌላ ኢትዮጵያውን ሕይወትም ሆነ ንብረት እንደማይወድም ተንበርክከው፤ ግን ደግሞ በመንፈስ ልዕልና ከፍ ብለው አሳይተውናል።

    ታላቅ ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!
    (ያሬድ ኃይለማርያም)

    ለእውነት የቆሙ ሽማግሌዎች እጦት፣ በካድሬ እና በመንጋ ፖለቲከኛ ክፉኛ ለተመታችው አገሬ የጋሞ ሽማግሌዎች (የጋሞ አባቶች) ፍቱን መድኃኒት ናቸው። እንደ ጋሞ ሽማግሌዎች ዓይነት ቅን አሳቢ፣ የፍቅር መምህር፣ የተግባር ሰው፣ ደፋር እና ዝቅ ብለው የከፍታን ውሃ ልክ የሚያሳዩ ሽማግሌዎች ከየማህበረሰቡ ቢገኙ ከገባንበት ቅርቃር በቀላሉ ለመውጣት ዕድል ይኖረን ነበረ። በሽማግሌ እና በካድሬ መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ያልቻሉ ቀሳውስት፣ ሼኾች፣ አባገዳዎች፣ ፓስተሮች፣ መንፈሳዊ አባቶች ኮሽ ባለ ቁጥር አበል እየተከፈላቸው በየሆቴሉ ሲማማሉ እና በሕዝብ ስም እነሱ ሲታረቁ ቢውሉም መሬት ላይ ጠብ ያለ ነገር የለም።

    የአገራችን ችግር ቅን አሳቢ እና ለእውነት የወገነ፣ ያመነበትን በትክክል የሚናገር፣ ክፉን የሚያወግዝን እና ጥሩውን የሚያበረታታ እውነተኛ ሽማግሌ፣ ደፋር ምሁር፣ ሃቀኛ ፖለቲከኛ፣ ሚዛናዊ ጋዜጠኛ እና መሰሪ ያልሆነ የአገር መሪ ይፈልጋል። ለጋሞ ሽማግሌዎች እና ሽማግሌዎቹንም ለሚያከብሩት የጋሞ ወጣቶች ትልቅ ክብር አለኝ። ጥሩ ምሳሌም ሊሆኑ ይችላሉ።

    የአማራ ሽማግሌዎች ከወዴት አላችሁ? የትግራይ ሽማግሌዎች ከወዴት አላችሁ? የኦሮሞ ሽማግሌዎች እና አባገዳዎች ከወዴት አላችሁ? እነዚህን ክልሎች በተለየ ሁኔታ የምጠራው ሦስቱም ክልል ውስጥ ያለው እሳት አገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ እየገፋት ያለ ስለመሰለኝ ነው። በማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት ሲፈጠር፣ ዜጎች በጠራራ ፀሀይ ሲታረዱ፣ እናት ከነልጆቿ ከቅዮዋ ተፈናቅላ ዱር ስታድር፣ ሕጻናት በነፍሰ በላዎች ታፍነው ገሚሱ ሲገደሉ፣ የዩንቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች በወሮበላ ታጣቂዎች ታፍነው ሲወሰዱ የመንግስት ክርን ቢዝል እናንተ የአገር ሽማግሌዎች የት ገባችሁ?

    የጋሞ ሽማግሌዎች (የጋሞ አባቶች) መንግሥት ኖረም አልኖረ በአካባቢያቸው ላይ፤ በተለይም በገዛ ልጆቻቸው የማንም ሌላ ኢትዮጵያውን ሕይወትም ሆነ ንብረት እንደማይወድም ተንበርክከው፤ ግን ደግሞ በመንፈስ ልዕልና ከፍ ብለው አሳይተውናል። ከዛም አልፈው ይህን ትልቅ የሽምግልና እና የፍቅር መንፈስ ይዘው ከአንድ አገሪቱ ጫፍ ወድ ሌላው ጫፍ ተጉዘዋል። መንፈሳችሁ በሌሎች ሽማግሌዎች ይደር!!

    ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!
    (ያሬድ ኃይለማርያም)

    ከጋሞ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ የጋሞ አባቶች እና ወጣቶች ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. “የሰላም ጉዞ” በሚል መርህ ከአርባ ምንጭ በመነሳት የተለያዩ ከተሞችን በማቋረጥ መዳረሻቸውን ጎንደር ከታማ እና የጥምቀት በዓልን አድርገው መጓዛቸውንበዚህ ሳምንት ተዘግቧል።

    በጉዞው የጋሞ አባቶች የአካባቢያቸውን ሰላም እንዴት እንዳስጠበቁ ተሞክሮዎቻቸውን ለሌሎች እንዳካፈሉ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ተምሳሌትነትም ለሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተሞክሮነት አሳይተዋል። አባቶች በጉዞው የተለያዩ ከተሞችን ያቋረጡ ሲሆን፥ በጉዟቸው መሃል ባረፉባቸው ከተሞችም ስለ ሰላም እና አንድነት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር አድርገዋል። እንዲሁም ተማሪዎችን ስለአቃፊነት፣ ስለ ሰላምና አንድነት እንደመከሩም የጋሞ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ ሰጥቶ ነበር።

    የሰላም ዦቹ የጋሞ አባቶች እና ወጣቶች በአዲስ አበባ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተገኝተው የአንድነት ፓርክን የጎበኙ ሲሆን፥ የጉዞው መዳረሻ በሆነችው ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማም ከከተራ በዓል ጀምረው እስከ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ለአራት ቀናት እንደሚቆዩ ተዘግቧል።

    የአብሮነትና የሰላም ጉዞውን ኅብረ መንጎል ሚዲያና ኦሞቲክ ጀኔራል ጠቅላላ ንግድ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፥ የጉዞውን አላማ በመደገፍ የሰላም ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የደቡብ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮዎች ለአዘጋጆች የድጋፍ ደብዳቤ ሰጥተዋቸዋል።

    ምንጮች፦ ያሬድ ኃይለማርያም እና ፋና ብሮድካስቲንግ

    የጋሞ አባቶች

    Anonymous
    Inactive
    • በሥራ ላይ ያለው ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ይቀየራል።
    • በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት አስፈላጊ ነው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጋጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ላይ እንደገለፁት ከ2012-2014 የትምህርት ዘመን በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የአስር ዓመታት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቷል።

    በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት መቀየር ያስፈለገው በፍኖተ ካርታው ምክረ-ሃሳቦች መሠረት ችግሮች ስላሉበት ነው። በመሆኑም በመጭዎቹ ዓመታት በአዲስ የሚተካው ሥርዓተ-ትምህርት የተማሪዎችን ሥነ-ምግባር ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቃዋል።

    በአውደ-ጥናቱም ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች፣ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ሃላፊዎች፣ ከሁለተኛና ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን፣ የመምህራን ኮሌጆችና ከአምስቱ የመምህራን ማሰልጠኛ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

    በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው ሥርዓተ-ትምህርቱ እየተዘጋጀ ያለው ከፍኖተ ካርታው በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ጥቆማዎች (recommendations an suggestions) እንዲሁም የካንብሪጅ ኢንተርናሽናል አሰስመንትን (Cambridge Assessment International Education) ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻዎች በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ተጨማሪ አስተያየት መሠረት ነው።

    በምክክር መድረኩም የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ፣ የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት መርህ አቅጣጫ (position papers) እና ሌሎችም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ሰለሞን መግለፃቸውን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።

    ከሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ደግሞ፥ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት፣ ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሒዷል።

    በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም “በዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በተሟላ ሁኔታ ተተገብረው ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባር የተላበሱ ምሩቃን አፍርተን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እያለፍን የሀገራችንን የማስፈጸም አቅም በመገንባት በብልጽግና ከፍታ ላይ ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን” ብለዋል።

    ሚኒስቴሩ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ላይ የተቀመጡ ምክረ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ በነባሩ የትምህርት ሥርዓት ላይ ያለውን ጉድለት ለመሙላት እና ለማሻሻል አዳዲስ የለውጥ ኃሳቦችን በማካተት ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ትግበራ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፥ ከነዚህም መካከል የከፍተኛ ትምህርትን ሥርዓተ ትምህርት የማሻሻል፣ የትምህርት አሠጣጥ ሥነ-ዘዴዎቹንና የትምህርቶቹንም ይዘት የመከለስና የኮርስ ካታሎግ (course catalog) የማዘጋጀት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንን በተልዕኮና በልህቀት ለይቶ የማደራጀት እንዲሁም አዳዲስ የሕግና የአሠራር ማዕቀፎችን የማውጣትና ነባሮቹንም የመከለስ ሥራዎች ይገኙበታል ብለዋል።

    እንደ ፕሮፌሰር ሂሩት ገለፃ፥ የምክክር መድረኩ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ሚኒስቴሩ በሚያከናውናቸው የለውጥ ሥራዎች ላይ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ስለሚያምንና በተለይም በቂ ግንዛቤ ያለውና የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ለለውጥ ሥራዎቻችን ስኬት ቁልፍ ስለሆነ ነው ሲሉ አስቀምጠዋል።

    ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መድረክ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጉዳዮች፣ በፍኖተ ካርታ ምክረ-ሃሳብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሴክተር የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እንዲሁም በሰላማዊ መማር ማስተማር ዙሪያ የተሠሩ አንኳር ሥራዎች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።

    በመጨረሻም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የልህቀት ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴን የሚጎበኙ ይሆናል።

    ምንጮች፦ የትምህርት ሚኒስቴር/ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ሥርዓተ-ትምህርት

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሳይንስ ሳምንትን ከጥቅምት 25 ቀን እስከ ህዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት ያከብራል።

    የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ዓላማዎችና መሪቃል ይከበራል። የኢትዮጵያው የሳይንስ ሳምንት ሲከበር የተባበሩት መግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) በየዓመቱ ኖቬምበር 10 ቀን የሚያከብረውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ባማከለ ሁኔታ ይፈፀማል።

    ይህ ሀገራዊ የሳይንስ ሳምንት ሲከበር ዋና ዓላማው ሳይንሳዊ አስተሳሰብንና አሠራርን፣ የሳይንስ ባህል ግንባታ ሥራዎቻችንን ለማሳወቅና እንዲሁም በተለያዩ ሳይንሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በቀጣይም የወጣቱን ትውልድ የሳይንስ ፍላጎት ለማሳደግ እንዲያግዝ ሳይንስ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሳይንስን፣ ሳይንሳዊ እንቅስቃሴዎችን እና የሳይንሳዊ ጥናቶችን ለሕዝብ ለማስተዋወቅም ያለመ ነው።

    በሳይንስ ሳምንት ከሚከናወኑ ዝግጅቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

    1. ከጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል በSTEM (Science, Technology, Engineering, and Mathematics) ዘርፎች ውድድር ይካሄዳል። ተማሪዎቹ በአራቱ የትምህርት ዘርፎች ለውድድር በሚያቀርቡት ፈጠራ ላይ ተመሥርቶ በሚሰጠው ዳኝነት አሸናፊዎች እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ተሸላሚ ይሆናሉ።
    2. ሐሙስ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶችና ሙያ ማኅበራት ጋር በሒልተን ሆቴል ምክክር ያደርጋል:: በምክክር መድረኩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሳይንስ ሥራዎችና የትኩረት አቅጣጫ፣ የሙያ ማኅበራት ሚና ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና፤ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት ዕይታ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶች የሳይንስ ሥራዎች ትኩረትና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር “ለኢትዮጵያ ግብርና አገር በቀል እይታ” በሚል የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ ይካሄዳል።
    3. አርብ ጥቅምት 28 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ሳይንስ ለልማትና ብልፅግና በሚል ርዕስ የተለያዩ ባድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሀገራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር ወርክሾፕ ይካሄዳል።
    4. እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የአረንጓዴ ቀን (Green Day) ይከበራል። በዕለቱ ባለፈው ክረምት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተተከሉ ችግኞችን ቦታቸው ድረስ በመገኘት የመንከባከብ ሥራዎች ይሠራሉ። እፅዋቱ ባሉበት ደረጃ በሚሠሩ የእንክብካቤ ሥራዎች ላይም በተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ሳይንሳዊ ገለፃ ይቀርባል።
    5. ሰኞ ሕዳር 01 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የባዮዳይቨርሲቲ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute) ጋር በመተባበር “ሰውና ሥነ ምህዳር (Man and Biosphere)” በሚል ርዕስ ትምህርታዊ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል። በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጥሮ ሳይንስና ግብርና ኮሌጆች በርዕሱ ላይ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።
    6. ማክሰኞ ሕዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biotechnology Institute) ጋር በመተበባር “ባዮቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ በዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርታዊ ገለፃ ይቀርባል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ ሳይንሳዊ ገለፃዎችና ውይይቶች ይካሄዳሉ።

    ስለሆነም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. በሚጀምረው የሳይንስ ሳምንትን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተውት ለህብረተሰቡ የሚመጥኑና ሳይንሳዊ ግንዛቤዎችን የሚፈጥሩ ሥራዎችን በመሥራት የሳይንስ ሳምንት አከባበር አካል እንዲሆኑ እንጋብዛለን።

    በተጨማሪም ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የሳይንስ ሳምንት፣ በየዘርፋቸው ሳይንስ ለአገር ልማትና ብልፅግና ያለውን ፋይዳ የሚያሳዩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ በበዓሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንጋብዛለን።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሳይንስ ሳምንት በኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም. የመማር ማሰተማር ሥራውን በይፋ ጀመረ
    —–

    ቦንጋ ከተማ፣ ከፋ ዞን (ሰሞነኛ) – ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከመስከረም 24 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ የምዝገባ ሂደቱን ካጠናቀቀ በኋላ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ለ2ኛ እና 3ኛ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ትምህርትን (first day, first class) በይፋ መስጠት ጀምሯል። በዕለቱም የዩኒቨርሲቲው የመ/ማ/ም/ፕሬዝዳንት በመማሪያ ክፍል አካባቢ በመገኘት የመማር ማስተማር ሥራው በአግባቡ መጀመሩን ዞረው የጎበኙ ሲሆን ለተማሪዎችም መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው በመግለፅ የመማር ማስተማሩም ተግባር በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሠረት እንዲጀምር አስተዋፅኦ ላበረከቱ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባላት በ2012 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ውይይት አማድረጋቸውን ዩኒቨርሲቲውስ አስታውቋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የሴኔት አባላትን በማሰባሰብ የ2012 ዓ.ም. የአንደኛ ሩብ አመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ፣ ከተማሪዎችና ከትምህርት ክፍል ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ በአካዳሚክ ዘርፍ ያለውን መዋቅር ማስፋትን እና የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን በተመለከተ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።

    በመድረኩም በያዝነው የትምህርት ዘመን ከተማሪዎች ቁጥር እና የትምህርት ክፍል መጨመር ጋር በተያያዘ የአካዳሚክ ዘርፍ መዋቅርን ማስፋት በሚለው አጀንዳ ላይ በመወያየት የየዘርፉን ሥራ ለማሳለጥ የመዋቅሩ መስፋት አስፈላጊ መሆኑን በጋራ በመስማማት ለአምሰቱም ኮሌጆች በምክትል ዲን ማዕረግ የሚሠራ፣ በጥናትና ምርምር ዘርፍና በትምህርት ጥራት ዘርፍም በምክትል ዲን ማዕረግ የየኮሌጆች አስተባባሪ በመሆን እና በሬጅስትራር ዘርፍም በተባባሪ ሬጅስትራር ማዕረግ ተጨማሪ ሰው በመሰየም ሥራው በአግባቡ እንዲሠራ ተወስኗል።

    በመጨረሻም አዲስ የሚመጡ የመደበኛ መርሀ ግብር ተማሪዎችን (freshman students of the regular program) ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ በቀረበው አጀንዳ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደተለመደው የተዋጣለትን አቀባበል ለማድረግ የተዋቀሩ ኮሚቴዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜ ከጥቅምት 8 እስከ ጥቅምት 10 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ እምደሆነ አስታውቋል።

    * Bonga University is one of the Public Higher Education Institution in Ethiopia. It is established with its own legal personality by the Proclamation No. 349/2015 of the Council of Ministers of the Federal Democratic Republic of Ethiopia. It is found in the South Western part of Ethiopia, in the Southern Nations, Nationalities and Peoples (SNNP) region.

    Anonymous
    Inactive

    የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል አንደማይልክ አስታወቀ
    —–

    መቐለ (ቢቢሲ አማርኛ) – የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንደማይልክ አስታውቋል።

    የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ገብረመስቀል ካሕሳይ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ “ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ወደ ሚሰነዘሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እና ኃላፊነት ወደማይወስድ ክልል አዲስ ተማሪዎችን ላለመላክ የክልሉ አቋም ነው” ብለዋል።

    “አማራ ክልል የተመደቡት 600 ተማሪዎች እንደማይሄዱ ለሚመለከተው የፌደራል መንግሥት አሳውቀናል። ይህ የክልሉ አቋም ነው” ሲሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

    ዘንድሮ፤ በትግራይ ክልል የዩኒቨሲቲ መግብያ ፈተና ወስደው ማለፍ የቻሉ የተማሪዎች ቁጥር ከ9000 በላይ መሆኑን የጠቀሱ ኃላፊው፤ ወደ አማራ ክልል ተመድበው የነበሩ ተማሪዎች ከ2000 በላይ እንደነበረ እና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ወደ 600 ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።

    “ከአንድ ወር ተኩል በላይ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲወያይ ቆይቷል። የተቀሩ 600 ተማሪዎችን ሌላ ቦታ እንዲመደቡ ይሠራል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የትግራይ ክልል ሌላ አማራጭ ይፈልጋል እንጂ ተማሪዎቹን ወደዚያ አይልክም” ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲ አመዳደብ ሥርዓት መሠረት ከአንድ ክልል አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በክልላቸው የተቀሩት 60 በመቶ ደግሞ ሌላ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይመደቡ እንደነበረ የሚያስታውሱት ኃላፊው፤ “ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በበዙበት ወቅት ይህ ተቀይሮ 10 በመቶ በክልላቸው 90 በመቶ ደግሞ ወደ ሌላ ክልል እንዲላኩ መደረጉ አግባብ አይደለም” ብለዋል በሰጡት መግለጫ።

    ይህ እንዲስተካከል ከፌደራል እና ከሌሎች አካላት ጋር ውይይት መደረጉን እና 20 በመቶ በክልላቸው 80 በመቶ ደግሞ ከክልል ውጪ እንዲመደቡ መወሰኑን ጨምረው ተናግረዋል።

    የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ገብረመስቀል ካሕሳይ ትግራይ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚመጡ ተማሪዎች “ምንም አይነት የደህንነት ችግር አይገጥማቸውም” ብለዋል።

    የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ሁለተኛ ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ተማሪዎች ዙሪያ ያሉት ነገር የለም።

    ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲ ስለሚገቡ አዲስ ተማሪዎች እና የሚደረግላቸውን አቀባበል በተመለከተ የሰጠው መግለጫ
    —–

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በ2011 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ 142,840 ተማሪዎች በመደበኛ መርሀ ግብር (regular program) በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል። ምደባቸውም የተማሪዎቹን የትምህርት መስክና የተቋም ምርጫ፣ የተማሪዎቹን ውጤት እና የዩኒቨርሲቲዎችን የቅበላ አቅም ባገናዘበ መልኩ የተካሄደ ነው።

    በዚሁም መሠረት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ተቀብለዋል። ቀሪዎቹም እየተቀበሉ ይገኛሉ። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አብዛኞቹ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በተመደቡበት በመገኘት ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል። ነባር ተማሪዎችም ትምህርታቸውን መከታተል ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

    ከዚህ ጋር ተያይዞም የ2012 ዓ.ም. የመማር-ማስተማር ሰላማዊ እንዲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ከነዚህም መካከል አንዱ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚረዳ ወላጆችን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የኃላፊነት መውሰጃ የስምምነት ውል እንዲገቡ መደረጉ አንዱ ነው። በዚህም ላይ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል አዲስ ተማሪዎች ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ከመግባታው ቀድም ብሎ እንዲሁም ከገቡ በኃላ፣ ነባር ተማሪዎችም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠናዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደርጓል። በተጨማሪም በያዝነው ዓመትም አዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ተደርጓል።

    የመማር-ማስተማር ሥራው የግብዓትም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙትም ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን አቋም እና ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረጉትን ቅድመ-ዝግጅት ለመገምገም ያገዙ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተሳተፉባቸው የመስክ ጉብኝቶች ተካሂደዋል። በቪዲዮ ኮንፈረነስም ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችና የደረሱበትን የዝግጅት ደረጃ የመገምገም እና የማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በውጤቱም ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሰላማዊ ለማድረግ ሊሠሩ የሚገባቸው አስፈላጊ ቅድመ-ዝግጅቶችን ማካሄዳቸው ተረጋግጧል።

    ከተማሪዎች ቅበላ ጋር ተያይዞም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች) ሲታይ እንደነበረው ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበት አከባቢ ማኅበረሰብ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የአከባቢው የጸጥታ ኃላፊዎች ጋር በመተባበር ፍፁም ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ቤተሰባዊ አቀባበሎችን ሲያደርጉ ታይቷል፤ እያደረጉም ይገኛሉ። ይህ በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ከተካሄዱ ተከታታይ ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች በኋላ የተገኘ ውጤት ነው።
    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምደባውን ተግባራዊ ሲያደርግ የተማሪዎችን ምርጫ፣ ውጤት እና የየተቋማቱን የቅበላ አቅም ከማገናዘብ ጎን ለጎን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚያስችሉ አካሄዶችንም ተከትሏል። ይሄው ታውቆ የክልል መንግስታት፣ የዩኒቨርሲቲ ቦርዶችና አመራሮች እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት በጠቅላላ የተቀመጠውን የቅበላና ድልደላ መርህ ተገንዝበው ለአፈፃፀሙ ሁሉም የድርሻቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ እንተማመናለን።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜ ይፋ ተደረገ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አደረገ። ሚኒስቴሩ በ2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እንዳደረገ መግለጫ ሰጥቷል።

    በተከለሰው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረትም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ ሴሚስተር በአራት ቅበላ ዓይነቶች እንደሚሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

    በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ በመምህርነት፣ በማኅበራዊ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ በመምህርነት የቅበላ ክፍል በመምህርነት የተከፈለ ነው ብለዋል።

    በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ደግሞ የመጀመሪያውን ሴሚስተር ውጤት መሠረት በማድረግ በአምስት የሙያ መስኮች ማለትም በሕግ፣ ሕክምናና የጥርስ ሕክምና፣ ፋርማሲ፣ የእንስሳት ሕክምና እና ምሕንድስና ናቸው።

    ሌሎቹ የትምህርት መስኮች ምደባ የሚደረገው ከአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ ነው። በ‹ቪዲዮ ኮንፈረንስ› ዝግጅት ግምገማ በማድረግ የመምህራን ቅጥር እንደሚካሄድም ተጠቅሷል።

    አዳዲስ ፟ዩኒቨርሲቲዎችም ለተማሪ ቅበላ ዝግጁ እንደሆኑ ተጠቁሟል። የቅበላው ጊዜም ለነባር ተማሪዎች ከመስከረም 5 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እየተካሄደ ይገኛል ነው የተባለው። አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ከመስከረም 25 እስከ 29 ቅበላው ይካሄዳል ተብሏል። ጥቅምት 03 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ ሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የሚያስጀምሩ ይሆናል ነው የተባለው።

    አዲስ ተማሪዎች በክልሉ ወይም በየወረዳው ስለመብቶቻቸውና ግዴታዎቻቸው ስልጠና ይሰጣቸዋል። ወላጆችና ተማሪዎች በሚፈርሙት ውል መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ።

    142 ሺህ 943 ተማሪዎችን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቀብለው እንደሚያስተምሩና የሴት ተማሪዎች ብዛት 43 ከመቶ እንደሆነ ተገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ዝውውር የሚጠይቁት በጤና እክል ምክንያት ብቻ እንደሆነም ተጠቁሟል።

    ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስና ከማኅበራዊ ሳይንስ ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ ዝውውር ማድረግ ይቻላል፤ ዝውውር ማድረግ የሚቻለው ግን የየመስኮቹን የማለፊያ ውጤት ሲያሟሉ እንደሆነ ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ ዋልታ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በ2012 የትምህርት ዘመን የሚካሄደው የተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ምደባ ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን መቀየር እንሚችሉ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የዘንድሮ ምደባ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ እና በመምህርነት የሚካሔድ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ተማሪዎች ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት መስክ መቀየር እንሚችሉ ገለፀው ተቋሙ ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ መቀየር የሚቻለው ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የተዘጋጀውን ማለፊያ ነጥብ ለሚያሟሉ ተማሪዎች ብቻ መሆኑን አስታውቋል።

    የትምህርት መስክ ምርጫ በተመለከተም ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች፣ ተፈጥሮ ሳይንስና መምህርነት፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ማኅበራዊ ሳይንስና እና መምህርነት ብቻ እንደሚሆንም ነው የገለፀው።

    ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን መቀየር እንሚችሉም ተገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲ ምርጫን ማስተካከልም ሆነ የትምህርት መስክ መቀየር (ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ) የሚቻለው ተማሪዎች ትምህርታቸዉን በተከታታሉበት ትምህርት ቤት ወይም ፈተና በወሰዱበት የፈተና ጣቢያ ነው ተብሏል።

    የዩኒቨርሲቲ ምርጫ ማስተካከያና የፊልድ መቀየሪያ ቀናት እስከ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ብቻ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር በድረ ገፁ አስነብቧል።

    ምንጭ፡- ኢቢሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተጠሪነቱ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን ተወሰነ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ሲመራ የነበረው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተጠሪነቱ ለፌዴራል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

    በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሚያስተምሩ መምህራንና የስፖርትና የሰውነት ማጎልመሻ ባለሙያዎችን በብቸኝነት በማፍራት ይታወቅ የነበረው የዛሬው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሥራውን የጀመረው በ1951 ዓ.ም. በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ነው፡፡
    በኋላም የአዲስ አበባ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በሚል ስያሜ ሜክሲኮ አካባቢ ባሁኑ ተግባረ ዕድ ግቢ በርካታ መምህራንን በማሰልጠን ለመላው ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶቸ አበርክቷል። በ1967 ዓ.ም. አሁን ወደሚገኝበት ኮተቤ ተዛውሮ ‘ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ’ በሚል ስያሜ ሲሠራ ከቆየ በኋላ በ1990 ዓ.ም. ተጠሪነቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆኖ ለከተማው ትምህርት ቤቶች መምህራንን ሲያሰጥን ቆይቷል፡፡ ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ባሁኑ ወቅት በመምህራን ስልጠናና ሌሎችም መስኮች ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ስር ሦስት ኮሌጆች እና አራት ፋኩልቲዎች እንዲሁም 26 የትምህርት ክፍሎች አሉት።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች፣ በውጭ ወራሪ ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሰዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው።

    እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱትን ዘመናት የማይሽሩት ታሪካዊ ውለታዎችን ለሀገር ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የጥፋት ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚፈጽሙት ከፍተኛ የሆነ አስተዳደራዊ በደልና የተቀናጀ ጥቃት እያደረሰብን ያለውን መከራና ችግር ቤተ ክርስቲያናችን ባላት ሀገራዊ ኃላፊነት ችግሩን በትዕግስት አሳለፈችው እንጂ እየተፈጸመባት ካለው ግፍና በደል አንጻር ይከሰት የነበረው ችግርና ሀገራዊ ቀውስ በቀለሉ የሚታለፍ ባልሆነም ነበር።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ እየደረሰብን ያለውን በደልና መከራ ከዛሬ ነገ ይሻላል በማለት ታግሰን ብንችለውም እያደር እየባሰና የችግሩም አድማስ እየሰፋ ሊሄድ ችሏል። ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም ቅሉበተለይ በአሁኑ ወቅት መልኩን እየቀያየረ እና ለዘመናት የቆየ አንድነቷን በማፈራረስ ከቤተ ክርስቲያኒቱም አልፎ ሀገራዊ ቀውስና አለመረጋጋት የሚያስከትል የጥፋት አጀንዳን ባነገቡ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የጀመሩት እንቅስቃሴ ወደከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ እና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በስፋት ከተወያየ የሚከተለውንየአቋም መግለጫ አውጥቷል፡-

    1. አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ እና ለጥፋት ለተደራጁ ቡድኖች ፖለቲካዊ ሽፋን በመስጠት በልዩ ልዩ ክልሎች የተፈጸሙት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የአገልጋይ ካህናት እና ምእመናን መገደል፣ ዘመን የማይተካቸው የሀገር መገለጫ የሆኑትን ጥንታውያን እና ታሪካውያን ቅርሶችን በማቃጠል ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿን ታሪክ እና ቅርስ አልባ በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን በደሎች እና ግፎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል።
    2. ቤተ ክርስቲያኒቱ ባህል፣ ቀለም፣ ቋንቋ እና ብሔር ሳትለይ በአንድነት እና በአቃፊነት ለሀገር ውለታ ያበረከተች መሆኗ ተዘንግቶ በእምነት ሽፋን የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች የሆኑ ምእመናን ካደጉበትና ሀብት እና ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ፣ በእምነታቸው ብቻ ተገደው በመደፈር እና ልዩ ልዩ የሥነ ልቦና ጥቃት እንዲደርስባቸው በማድረግ እንዲሁም በድብደባ እና በዛቻ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረገ ያለውን ሕገ ወጥ አድራጎትን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል።
    3. ለባለውለታዋ እናት ቤተ ክርስቲያን በማይመጥን እና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕጋዊ ይዞታዋን እና የአምልኮት ቦታዎቿን በመንጠቅ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን እንደ ሽፋን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በደል እና ግፍ የሚፈጽሙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎችን ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ አድራጎታቸው እንዲታቀቡ በጥብቅ ያሳስባል።
    4. እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ በሀገራዊ የሀላፊነት ስሜት ታግሶ እና ችሎ ሞቱ፣ እሥራቱ፣ ዛቻው፣ ስደቱ እና እንግልቱ ሳይበግረው ሀገር በአንድነት እና በፍቅር እንዲሁም በመተሳሰብ እንድትቀጥል ታሪክ የማይረሳው መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን አገልጋይ ካህናት እና መላውን ምእመናንን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአጠቃላይ መላው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ላሳያችሁት ትዕግስት የተመላበት ሀገራዊ ሀላፊነት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያመሰገነ እንደአሁን ቀደሙ ሁሉ ትዕግስት የተመለበትን ሀገራዊ ኃላፊነታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን እና ወደፊትም ሊደርስ የታቀደውን ግፍ እና ጥፋት በአንድነት እና በኅብረት ከእኛ ከመንፈስ ቅዱስ አባቶቻችሁ ጋር በመሰለፍ በጽናት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንድትጠብቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን ያስተላልፋል።
    5. በቤተ ክርስቲያናች እምነት እና ቀኖና መሠረት በእምነታቸው ምክንያት በሰይፍ የታረዱ፣ በጥይት የተገደሉት፣ በእሳት የተቃጠሉ፣ ሕይወታቸውን ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው የሰጡ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በሰማእትነት ክብር እና ማዕረግ ዘወትር እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በሰማእትነት ሕይወታቸውንየሰጡ አገልጋዮች እና ምእመናን ቤተሰቦች ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይናጋ በተቻለ አቅም ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ ሁላችንም ከጎናቸው በመሆን የድርሻችንን እንወጣ ዘንድ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽኑ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።
    6. እናት ቤተ ክርስቲያችን በእንግዳ ተቀባይነቷ እና በአቃፊነቷ ዛሬ ለቁጥር አዳጋች የሆኑት ቤተ እምነቶች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ሰላማዊ፣ የማምለክ መብታቸው እንዲረጋገጥ የበኩሏን ድርሻ የተወጣች መሆኗን ሁሉም ቤተ እምነቶች በየአደባባዩ የሚመሰክሩት እውነታ እንደመሆኑ መጠን በእናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ ሁሉም ቤተ እምነቶች በአንድነት እና በተባበረ ድምጽ በጽናት እንዲያወግዙ እና ለእምነት ተከታዮቻቸውም የቤተ ክርስያናችን ጥፋት እና በደል እንዲወገድ የበኩለቸውን ሚና እንዲወጡ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን እንዲያስተላልፉልን በቅድስተ ቤተ ክርስቲያናችን ስም የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለልን።
    7. የፍትሕ አካላት ለምሥረታችሁ እና ለእድገታችሁ ውለታ የከፈለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የቀደመ ውለታዋን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ ተጥሶ እና ፍትሕ ተጓድሎ በቤተ ክርስቲያነቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል በጽናት ከማውገዝ በተጨማሪ አጥፊዎችን ለፍትሕ በማቅረብ እና ተመጣጣኝ እና ለሌሎችም አስተማሪ የሆነ ውሳኔ በመስጠት እና በማሰጠት የራስዋየሆነ ተቋማዊ ሕልውና እና መዋቅር ያላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት እና ልእልና መከበር የበኩላችሁን ድርሻ ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ጥሪ ያስተላልፋል።
    8. በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የተከበረውን እና የተረጋገጠውን የእምነት ተቋማት ነፃነት እና ሉዓላዊ ክብር በሚጋፋ ሁኔታ እየተፈጸሙ ያሉት የመብት ጥሰቶች እና የጥፋት በደሎችን የማረም እና ከመፈጸማቸውም በፊት የመከላከል ኃላፊነት ያለባችሁ በየደረጃው የምትገኙ የመንግሥት አካላት በሕገ መንግሥቱ የተጣለባችሁን ሕግን የማስከበር አደራና ኃላፊነት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መብት የማስጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስያኒቱን ልዕልና እና ክብር እንድታስጠብቁ በቅድስት ቤተ ክርስያናችን ስም ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎባችኋል በማለት በጽኑ ያሳስባል፤
    9. አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ ሰላም እና ፍቅርን በመስበክ እና በተግባር በመፈጸም ለሀገር እና ለመላው ዓለም አርኣያ የሆነችውን እናት ቤተ ክርስቲያን ያለ ስሟ ስም፣ ያለግብረዋ ግብር በመስጠት በተለይም የተከበረውን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ባለውለታ የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳገለልችው እና አቅዳ እንደበደለቸው ለማስመሰል እና ለማስቆጠር አቅደው ቤተ ክርስያኒቱን እና ሀገርን ለመከፋፈል ድብቅ አጀንዳ ይዘው በተነሡ ግለሰቦች እና ቡድኖች አለአግባብ እየተሠራጨ ያለው አፍራሽ እና ከፋፋይ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም እና ድምጽ ካለመሆኑ በተጨማሪ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ እንደሚያስረዳን ሕገ ወጦቹ ግለሰቦቹ እና ቡድኖች የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የሚያገለግለው እና የሚባርከው መንፈሳዊ አባት እንደሌለው ቢገልጹም እንኳንስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ነፃነት ከተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ የተገኙት እና ነፍሳቸውን ሳይሳሱ በሰማዕትነት ዋጋ የከፈሉትን የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ታሪክ የማይረሳውን ውለታ የዘነጋ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት በመዓርገ ጵጵስና ሹማ በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት ለሐዋርያ አገልግሎት አሠማርታ መላውን የክልሉን ሕዝበ ክርስቲያን በማገልገል ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ ለክልሉ ሰላም እና አንድነት ዋጋ በመክፈል ላይ የሚገኙትን ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙትን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና በእነሱ የሚመሩ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ያሉ በርካታ ጽ/ቤቶች ከዐሥራ አምስት የሚበልጡ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶች እና መዋቅሮችን ፈጽሞ የካደ አድርጎት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ እያወገዘ በዚህ አድርጎት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከዚህ አድርጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል።
    10. የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የኦሮሞ ሕዝብ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ እንደ ትናንቱ ሁሉ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ በተቻላት አቅም መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ለማድረግ የጸሎት፣ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እና ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጎም እና በማዘጋጀት፣ ከአምስት በላይ የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ አንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅን በጀት መድባ በማቋቋም መላውን የኦሮሞ ብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ስታገለገል የቆየችውን እና ያላቸውን ወደ ፊትም ዘመኑን በዋጀ መልኩ አጠናክራ የምታገለግለውን እናት ቤተ ክርስያናችሁ መሆኗን አውቃችሁ አንድነታችሁን እና ፍቅረ ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመከፋፈል የተነሡትን የጥፋት ኃይሎች በጽናት በመቃወምና አንድነት እና ፍቅራችሁን አጠናክራችሁ ቤተ ክርስያናችሁን እና ሃይማኖታችሁን ከጥፋት ኃይሎች ትጠብቁ እና ትንከባከቡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል።
    11. አዲስ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚል መዋቅር በራሳቸው ሥልጣን መሥርተው በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ በሰጣቸው እድል ቀርበው የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም ወቅት ጥያቄውን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን ቀደም በኮሚቴ ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቶበት እያለ ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠው በማስመሰል ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ አዲስ መዋቅር ፈጥረው መግለጫ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን አምነው ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 የተቀጠሩ ቢሆንም በዕለቱ የኮሚቴው ዋና ተጠሪ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ያልተገኙ ሲሆን 2 የኮሚቴው አባላት ብቻ ከተሰጣቸው ሰዓት አሳልፈው ከመምጣታቸውን በላይ 2ቱ ግለሰቦች በጽሑፍ ባቀረቡት ምላሽ በሕገወጥ አቋማቸው የፀኑ መሆናቸውን የገለጹ በመሆኑ የግለሰቦቹ እንቅስቃሴም ሆነ የኦሮሞ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተብሎ የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን አውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተ ክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ትጠብቁ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል።
    12. ከዚህ በላይ በተገለጸው መሠረት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልናም ሆነ ከሕገ የመነጨ ሥልጣን ሳይኖራቸውና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሕግ የመነጨ መብት በመጋፋት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሎጎ /አርማ/፣ ማህተምና መጠሪያ ስያሜ መጠቀማቸው ሕገወጥ አድራጎት በመሆኑ የሚመለከታችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሎጎ /አርማ/ እና ማህተም እንዲሁም መጠሪያ ስያሜ መጠቀም የማይችሉ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምት በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ታስከብሩ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት እያሳሰበ፤ የጽ/ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያም በሕገወጦች ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ አዟል።

    ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በዝርዝር በተገለጹት የአቋም መግለጫዎችና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል።

    እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
    ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ
    ኢትዮጵያ

    (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ)

    ቅዱስ ሲኖዶስ


    Semonegna
    Keymaster

    የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላይ ውሳኔ ላይ ከመደረሳቸው በፊት በፈተናው ያጋጠመውን ችግር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲመረምር መቆየቱን ገልጸዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ውሳኔ አሳለፈ።

    ሚኒስቴሩ በተፈተኞች ወጤት መሰረት እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ባደረገው ጥናት ማረጋገጡንም አስታውቋል።

    የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) እና የክልል ትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ በፈተናው ያጋጠመውን ችግር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲመረምር መቆየቱን ገልጸዋል።

    በዚሁ መሰረት በተፈጥሮ ሳይንስ (natural science) እና ማኅበራዊ ሳይንስ (social science.) መስኮች ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ፈተናቸው የተሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ታሳቢ የተደረጉ ሲሆን ሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ ፈተናዎች ውጤቶች ግን ተሰርዘዋል።

    ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ እንዲያገለግሉ የተወሰነው ሂሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ፊዚክስ፣ አፕቲትዩድ እና ጂኦግራፊ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።

    ሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡ ፈተናዎች ከግምት ውስጥ ያልገቡት እጅግ የጋሸበ ውጤት የተመዘገበባቸው በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት


Viewing 15 results - 31 through 45 (of 83 total)